Monday, 15 April 2024 08:43

የጣልነውን ፍለጋ…!

Written by  -ባዩልኝ አያሌው-
Rate this item
(1 Vote)

በአንድ አጋጣሚ፣ አንድ ወዳጃችን በአፋን ኦሮሞ (በኦሮምኛ) ቋንቋ ተርቶልን፣ ወደ አማርኛ መልሶ ጭብጡን ባስጨበጠን ጥዑም ተረት ነገሬን ልጀምር፡፡ ተረቱን የምጠቅሰው ተረቱ በተከየነበት እናት ቋንቋው አይደለምና፣ መልዕክቱን እንጂ ውበቱን ለማስተላለፌ ቃሌን አልሰጥም፡፡
ተረቱ እንዲህ ይላል፡፡ “ታመን ሳለን፣ ‘የበሽታው መድሐኒት የጅብ ሥጋ ነው’ አሉን፡፡ እኛም ‘ወጥተን ወርደን፣ እጅግ ብዙ ደክመን የጅቡን ሥጋ አገኘን፡፡ ነገር ግን መልሰው፣ ‘የለም የጅብ ሥጋ የረከሰ ቆሻሻ ነው፤ በፍጹም መድሐኒት አይደለም’ አሉን፡፡ እኛም ሥጋውን ጠርገን አውጥተን ጣልን፡፡ ሌሎች መፍትሔ ናቸው ያሏቸውን ሁሉ ሲሞክሩ ቆይተው፣ በመጨረሻ በብዙ መቆጨት ‘የለም ተሳስተናል፤ ለበሽታው ፍቱን መድሐኒቱ የጅብ ሥጋ ነው’ አሉን፡፡ ሆኖም ጠርገን የጣልነውን በብዙ ድካም ብንፈልገውም አላገኘነውም፡፡” የጣሉትን መፈለግ፤ ፈልጎም ማጣት!
ይህ ተረት እንደ ሀገር በእኛና በሞራል እሴቶቻችን ላይ የሆነውን በቅጡ የሚያሳይ ይመስለኛል፡፡ እንዴት? ብለን በመጠየቅ ነገራችንን እናርዝም፡፡ በርካታ ተቀጥላ ሰበቦችን መጥቀስ ቢቻልም፣ በሀገራችን የ“ዘመናዊ” ትምህርትን ያህል የሞራልና የሥነምግባር እሴቶቻችንን በመንጠቅ ድርሻ ያለው ሌላ ያለ አይመስልም፡፡ (“ዘመናዊ” የሚለውን ቃል በትእምርተ ጥቅስ ማስቀመጤ በአንድ በኩል “ዘመናዊ” ቃሉ ምንን? የትኛውን? መቼን? በምን ምክንያት? የሚሉትን ጥያቄዎች በቅጡ የማይመልስ በመሆኑ ሲሆን፣ በሌላም በኩል ከውጪ፣ በተለይም ከምዕራቡ ዓለም ለተገኘው ወይም ለመጣው ብቻ ሲያገለግል የሚገኝ በመሆኑ ነው፡፡ እነዚህ ምክንያቶች የ“ዘመናዊነት” ዕሳቤን በብዙዎች አጠያያቂ ያደረጉት ይመስለኛል፡፡) ወደ ነገሬ ልመለስ፡፡


ሀገራችን የምዕራቡን ዓለም ሥርዓተ ትምህርት ከነቋንቋው የተቀበለችው ተማሪ ቤት አቁማ (አንጻ)፣ መምህር ተውሳ፣ ነጋሪት ጎስማ… ነበር ብሎ ማለት እውነቱን መመስከር እንጂ ማጋነን አይደለም፡፡ በዛው ቅጽበት ለዘመናት ማህበረሰብን በሕግና በሥርዓት፣ በዕውቀትና በጥበብ፣ በሞራልና በሥነምግባር ያቆየውን ሀገራዊ ትምህርት ባህላዊ ብላ (ኋላቀርም) ከዕውቀት ማዕዷ ገሸሽ አደረገችው፡፡ (ጠርጎ እንደመጣል ዓይነት!)
የአፍሪካን ሀገሮች ምድራቸውን ይዘው የህዝባቸውን አስተሳሰብ ቢሉ ኑሮ ለመቀየድ ያህላል የማይሉትን በርካታ ሀብትና የወታደሮቻቸውን ሕይወት ገብረው ድካማቸው በአንዳንድ ሀገሮች ላልያዘላቸው እንደ እንግሊዝና ፈረንሣይ ላሉ ምዕራባውያን መንግስታት፣ በአንዲት ሉዐላዊት ሀገር ላይ አንዳች ሳይደክሙ ሥርዓተ ትምህርታቸውን አጥልቀው መትከል ማለት በብዙ መስዋዕትነት እንደርስበታለን የሚሉትን ግብ፣ እጅግ በጥቂት ድካም ያስጨበጠ ነበር፡፡
ከልጅነታቸው ጀምሮ ለፈረንሣይ የተለየ መደነቅና መሳብ የነበራቸው ቀዳማዊ ኃይለሥላሴ፣ በመጀመሪያ የልባቸውንም የሀገራቸውንም ልብ የከፈቱት ለፈረንሣይ መንግስትና ተወላጆች ነበር፡፡ በዚህም የምዕራቡ ዓለም ትምህርት ይቀሰምባቸው ዘንድ የታነጹትን ተማሪ ቤቶች፣ በፈረንሣይ የትምህርት ሥርዓት በፈረንሳይኛ ቋንቋ እንዲያስተምሩ አደረጉ፡፡ “ያለባለቤቱ…” እንዲሉ፣ የፈረንሣይ ተወላጆች በመምህርነትና ዳይሬክተርነት ትምህርት ቤቶቹን እንዲያስተዳድሩም ይሁንታቸውን ሰጡ፡፡


ከአምስት ዓመቱ የጣሊያን የወረራ ዘመን በኋላም (የአርበኞቹ የነጻነት ተጋድሎ ወሰን ባይኖረውም) በእንግሊዝ “ድጋፍ” ከስደት ወደ መናገሻ ከተማቸው የገቡት ንጉሠ ነገሥቱ፣ በውለታ አስሮ ላስጨነቃቸው የእንግሊዝ መንግስት ስጦታ በሚመስል መልኩ ያቀረቡለት፣ በፈረንሣይ ሥርዓተ ትምህርትና ቋንቋ ይሰጥ የነበረውን ትምህርት ወደ እንግሊዝ ሥርዓተ ትምህርት ማዛወርን ነበር፡፡
በወቅቱ ጥቂት የማይባሉ አርቆ አሳቢዎች ቢያንስ የምዕራቡ ዓለም ትምህርት፣ ከነዋሪው ሀገር በቀል ትምህርት (በተለይም በአብነት ትምህርት ቤቶች እና በደረሳዎች ይሰጥ ከነበረው) እንዲዋሐድ ምክር ለገሱ፡፡ በቃልም ቀርበው፣ በጽሑፍም ተግተው ማስተዋል ያቀበላቸውን አሳሰቡ፡፡
ሥርዓቱ ግን ገብቶትም ይሁን ሳይገባው የበርካታ ጥበባት፣ የሞራል እና ሥነምግባራዊ እሴቶች ቋት የነበረውን የትምህርት ሥርዓት “ባህላዊ” (ዘመናዊ ብሎ ለጠራው አቻ ተቃራኒ እንዲሆን)፣ “የቄስ ትምህርት” (የሃይማትና የቤተክርስቲያን ዕውቀቶችን ብቻ ነው የያዘው ለማሰኘት) ሲለውም “ኋላቀር” (ከስልጣኔ፣ ከእድገት የተፋታ ወይም እንቅፋት፣ ጎታች ብሎ ሊያስጠላው) የሚል ስም ለጥፎበት ወደ ጎን ገፋው፡፡ በዚህም የሀገሪቱን ትውልድ የዕውቀትና የጥበብ እጣ ፈንታ እጅና እግሩን ጠፍሮ ለምዕራቡ አስተሳሰብና ርዕዮት አሳልፎ ሰጠው፡፡


ወላጆች ልጆቻቸውን አዲስ ወደተከፈቱት ተማሪ ቤቶች ለመላክ በማስቸገራቸውና፣ ከወደቤተክህነቱም የገጠመውን ጠንካራ ጉርምርምታ ለማርገብ በሚመስል መንገድ፣ የአጼው ሥርዓት ጥቂት የቤተ ክህነት ትምህርት ያላቸውን ካህናት በአማርኛ ቋንቋ እና በግብረገብ መምህርነት በተማሪ ቤቶቹ እንዲያስተምሩ ቢያደርግም፣ በሥርዓት የደረጀውና በዋናነት በፈረንሣይ፣ በኋላም በእንግሊዝ ተወላጆች ይሰጡ የነበሩት ትምህርቶች ይዘቶች የትውልዱን መንገድና አስተሳሰብ በመቅረጽ ረገድ የነበራቸውን ድርሻ የሚገዳደር አልነበረም፡፡
እናም ከእናት ከአባቱ፣ ከማህበረሰብ ከእምነቱ፣ ብሎም ከአብነት ትምህርት ቤቶቹና ከደረሳዎቹ የቀሰማቸውን ሞራላዊ እሴቶች አስጥለው፣ በሚፈልጉት አጥምቀው ወደወደዱት ሊወስዱት ብዙ አልተቸገሩም፡፡ በሥጋውም በነፍሱም እነሱን ለመምሰል ሳይሆን ለማከልና ለመሆን እንቅልፍ ያጣ ትውልድ መፍጠር ቻሉ፡፡
በጊዜው ቀደም ሲል ወደ አውሮፓ ሀገሮች እና ወደአሜሪካን ተጉዘው የምዕራቡን ዓለም ትምህርትና አስተሳሰብ ተዋሕደው የመጡትና፣ በእነዚህ ተማሪ ቤቶች ትምህርታቸውን የቀሰሙቱ እንደ ፍጹም አዋቂና ስልጡን መወሰዳቸው፣ በአንጻሩ የሀገር በቀል እውቀቶች ባለቤቶቹን እንደ ኋላቀርና ጎታች አስቆጠራቸው፡፡ ይህንን ብሽሽቅ በሚመስል መልኩ ጎልቶ የታየን አሳዛኝ ግድድሮሽና መገፋፋት፣ ቀደምት ጸሐፍቶቻችን በልቦለዶቻቸው፣ ሌሎችም በሕይወት ታሪክ ድርሳኖቻቸው፣ ቀርጸው ሰንደውልናል፡፡


ያምሆኖ ያቆየንን፣ እንደህዝብም እንደሀገርም ለዘመናት ያኖረንን መድሐኒታችንን አውጥተን ጥለናልና ዋጋውን ለመክፈል ያስፈለገን ጥቂት ዓመታት ነበር፡፡ በምዕራቡ ዓለም ፍልስፍና እና የፖለቲካ ርዕዮቶች ብዙ እየጠለቀ የሄደው “ዘመናዊው” ትውልድ፣ በዛው ልክ እትብቱን ከጣለበት፣ ተገርቶ ካደገበት ማህበረሰብ ክቡር እምነቶችና እሴቶች እየተነጠለ መጣ፡፡ ደግሞም ቀድሞም አነውሯቸዋልና፣ ጆሮውን የሚሰጣቸው አልሆኑም፡፡ እንዳይመለስ ሆኖ ርቆ ተጓዘ፡፡
ጉዞው ያተረፈለት ዕውቀት የለም ባያሰኝም፣ የፈጠረው ቀውስና ውጤቱ ግን እስካሁን ድረስ የተሻገረ ነው፡፡ ይኸው “ዘመናዊ” ትውልድ የፈጣሪን ህልውና እስከመጨረሻው ድረስ በመካድ፣ በእምነቱ ላይ የተመሠረቱትን የሞራልና የሥነምግባር እሴቶች ከመሠረታቸው ናደ፡፡
እነዚህን ከሕግ በላይ ሕግ ሆነው፣ የሰው ልጅን ለብዙ ሺ ዘመናት ያኖሩትን ክቡር እሴቶች ንዷልና ከዚህ በኋላ የቀጠለው ሕይወቱ የመቃበዝም የመቅበዝበዝም ዓይነት ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ለሚያደርጋቸው፣ ለሚሆናቸው ሁሉ አመክንዮን የሚጠይቀው ዓላማዬ ካለው አንጻር ብቻ እንጂ፣ ሞራል፣ ሥነምግባር፣ እምነት፣ ባህል… ለቅጽበት በአእምሮውና በአስተሳሰቡ ውልብ የሚሉ አልሆኑም፡፡ ነገሬን መሬት ቢያስይዝልኝ አንድ ማሳያ ላንሳ፡፡
እንደሚታወቀው በ1966ቱ ቅድመ እና ድህረ አብዮት በሁሉም ጎን ተዋናይ የነበሩት ይህ የትምህርት ሥርዓትና አስተሳሰብ ያፈራቸው ናቸው፡፡ ጥቂት የማይባሉትም በምዕራብ ሀገሮች፣ በአሜሪካና በሌሎችም ሀገሮች የከፍተኛ ትምህርታቸውን የተከታተሉ፣ ብዙ ያነበቡ፣ የተወያዩ፣ የተከራከሩ፣ የሞገቱ፣ የተሞገቱ “ምሁራን” ናቸው፡፡
እነዚህ “ምሁራን” በየፖለቲካ ቡድናቸው በሚያደርጓቸው ስብሰባዎች ላይ መገደል ስላለባቸው (በእነሱ ቋንቋ እርምጃ ስለሚወሰድባቸው) የተቀናቃኝ ኃይሎች አባላት ወይም ግለሰቦች ሲመክሩና ውሳኔዎችን ሲወስኑ፣ ለመወሰን የሚያነሷቸው ሃሳቦች የሚያተኩሩት “እሱን ብንገለው እንዲህ ይሆናል”፤ “እንዲያ ይሆናል”፤ “ይህ ሊደርስብን ይችላል” በሚለው ላይ እንጂ የትም ቦታ ላይ ሰው መግደል እጅግ የመጨረሻው ኢሞራላዊ ተግባር በመሆኑ ላይ ማንም ሲጠይቅ፣ ሲሞግት አልተሰማም፡፡ (የዘመኑ የየድርጅቶቹ አባላት የጻፏቸውን መጻሕፍት ምስክር እጠራለሁ፡፡)
ቀድመው የሞራልና የሥነምግባር እሴቶች መሠረት ከሆነው ከፈጣሪ ጋር ፍቺ ፈጽመዋልና ገሳጭ ቢሉ ዳኛ የለባቸውም፡፡ ነገሩን አጋነንከው ካልተባልኩ በቀር፣ የዛን ዘመን የፖለቲካ ተዋናዮችን ያህል ለመጀመሪያ ጊዜ (ለመጀመሪያ ጊዜ ነው ያልኩት) በዚህች ሀገር ላይ መግደልን ያወጀና በአደባባይ የፈጸመ ያለ አይመስለኝም፡፡
እስከዛሬም ለአፍታ ቆም ብለን ምንድን ነው የሆነው? የቱ ጋር ነው መንገድ የሳትነው?  የቱ ጋር ነው የተበጠሰው? ብለን ከልብ አልጠየቅንምና ሰብአዊ ድቀታችን ከጊዜ ጊዜ ከፍቶ እንደቀጠልን አለን፡፡ ሠርክ ስንነጋገርና ስናማርር የምንገኘው መንስኤው ላይ ሳይሆን ውጤቱ ላይ ነውና፣ መድሐኒቱ እንደራቀን እኛም ባልዋለበት ስንፈልግ እነሆ አለን፡፡


ሰዎች እንዴት በዚህ ደረጃ ሰውነታቸውን አጡ? ለምን ይህንን ያህል ግብራቸው አውሬ እንኳን የማይፈጽመው ሆነ? እንደምን ይህንን ያህል ሙሰኞች፣ ቀማኞች፣ ለእኔ ብቻ ባዮች ሆኑ? ቀደም እንደዚህ ካልነበርን የቱ ጋር ነው ሁሉም የጀመረው? በምን ምክንያት?... ብሎ መጠየቅ “ባህላዊ”፣ “ኋላቀር” ብለን አውጥተን የጣልነውን መድሐኒት ደግመን የምናገኝበትን መንገድ ይመራን፣ እንድናገኘውም ያግዘን ይመስለኛል፡፡
ያልሰጠነውን የምንፈልግበትን ትውልድም መፈረጅና መውቀስ፣ እኔ ግን እንደእሱ አይደለሁም ብሎ ከማለት ያለፈ ተራ ትርፍ የለውም፡፡ አዝመራውም የሚሰጠን የዘራንበትን ነውና፡፡
ቸር እንሰንብት!     
ከአዘጋጁ፡- ባዩልኝ አያሌው በኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ የቋንቋና ሥነጽሑፍ መምህር ሲሆኑ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በተለያዩ የኪነጥበብ መድረኮች ላይ በሚያቀርቧቸው ግጥሞችና አዲስ አድማስን ጨምሮ በሌሎች የሕትመት ውጤቶች ባስነበቧቸው ሥነጽሑፋዊ ሂሶቻቸው ይታወቃሉ፡፡

Read 752 times