Wednesday, 17 April 2024 19:11

የእስራኤል እና የኢራን ፍጥጫ

Written by 
Rate this item
(8 votes)

(ከእስራኤል  ምክትል አምባሳደር ጋር የተደረገ ልዩ ቃለ መጠይቅ)

ኢራን ባለፈው ቅዳሜ ሚያዝያ 5 ቀን 2016 ዓ.ም ሌሊት ከ300 በላይ የድሮኖችና የሚሳኤሎች ጥቃት  በእስራኤል ላይ ያደረሰች  ሲሆን፤ እስራኤል አሜሪካና እንግሊዝን ጨምሮ ከአጋሮቿ ጋር በመተባበር ከተወነጨፉት ድሮኖችና ሚሳኤሎች ውስጥ 99 በመቶውን ከአየር ክልሏ ውጭ ማምከን መቻሏን አስታውቃለች፡፡ ኢራን የፈጸመችው ጥቃት የዛሬ 20 ቀን ገደማ በሶሪያ በሚገኝ ቆንስላዋ ውስጥ እስራኤል በፈጸመችው ጥቃት ለገደለቻቸው ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዦቿ አጸፋዊ ምላሽ መሆኑን ገልጻለች፡፡ የእስራኤል ጦር አዛዥ ጥቃቱን ተከትሎ ከሰሞኑ በሰጡት መግለጫ፤ በእስራኤል ግዛት ለተወነጨፉ ድሮኖችና ሚሳኤሎች ምላሽ መስጠታችን አይቀርም ብለዋል፡፡

የጆ ባይደን አስተዳደር፤ በኢራን ላይ በሚወሰድ የአጸፋ እርምጃ አሜሪካ ተሳታፊ እንደማትሆን ግልጽ አድርጓል፡፡ ኢራን በበኩሏ፤ እስራኤል የአጸፋ እርምጃ ከወሰደች ፈጣንና ከአሁኑ የከፋ ምላሽ እንደምትሰጥ ዝታለች፡፡ አሜሪካ የእስራኤልን የአጸፋ እርምጃ የምትደግፍ ከሆነም፣ በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ ጥቃት እንደምትሰነዝር ኢራን አስጠንቅቃለች፡፡ የእስራኤል አጋሮች የኢራንን ጥቃት አጥብቀው ቢያወግዙም፣ የጠ/ሚኒስትር ኔታንያሁ አስተዳደር አጸፋዊ ምላሽ ላይ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡

በሌላ በኩል፤ እዚህ አዲስ አበባ የሚገኘው በኢትዮጵያ የእስራኤል ኤምባሲ በጥቃቱ ማግስት እሁድ ሚያዝያ 6 ቀን 2016 ዓ.ም ኢራን ለመጀመሪያ ጊዜ በእስራኤል ላይ ያስወነጨፈቻቸውን ድሮኖችና ሚሳይሎች አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ያወጣ ሲሆን፤የአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ፣ ከእስራኤል ምክትል አምባሳደር ሚስተር ቶመር ባር-ላቪ ጋር በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ  ተከታዩን ቃለ መጠይቅ አድርጓል፡፡
***

እስቲ ባለፈው ሳምንት ቅዳሜ፣ ኢራን በእስራኤል ላይ ስለፈጸመችው የድሮንና የሚሳኤል ጥቃት ይንገሩን ?

ቅዳሜ ሌሊት፣ ኤፕሪል 13፣ የኢራን አገዛዝ፣ በእስራኤል ላይ ታይቶ የማይታወቅና ግዙፍ ጥቃት አድርሷል፤ከ300 በላይ የባላስቲክ ሚሳኤሎች፣ ክሩዝ ሚሳኤሎችና ድሮኖዎችን  በእስራኤል ኢላማዎች ላይ በማስወንጨፍ፣ ከፍተኛ እልቂትና ውድመት ለማድረስ ሞክሯል። ደግነቱ፣ በእስራኤል  የላቀ ወታደራዊ አቅምና በአጋሮቻችን ትብብርና  ድጋፍ ከተወነጨፉት ውስጥ  99 በመቶ የሚሆኑት ወደ እስራኤል የአየር ክልል ከመግባታቸው በፊት መትተን መጣል ችለናል።

በኢራን አብዮታዊ ጋርድ (IRGC) የተፈፀመው ይህ ጥቃት፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ቻርተርን የሚጥስ ሲሆን፤ሌላ ቀይ መስመር ያለፈና  እስራኤል ለዓመታት ስትናገረው የኖረችውን የሚያረጋግጥ ነው፤ የኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ በመካከለኛው ምስራቅ ለሚታየው አለመረጋጋትና ሽብርተኝነት ዋነኛ ምንጭ መሆኑን፣ እንዲሁም ለአካባቢያዊና ለዓለም ሰላም ስጋት መደቀኑን፡፡ ኢራን የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ባለቤት እንድትሆን ፈጽሞ ሊፈቀድላት የማይገባው ለምን እንደሆነም የሚያጎላ ድርጊት ነው፤ ጥቃቱ፡፡


የእስራኤል የጦር አዛዥ፣ ለዚህ ጥቃት የአጸፋ ምላሽ እንደሚሰጥ ተናግረዋል፡፡ እስራኤል   እንዴት ነው ምላሽ ልትሰጥ ያቀደችው?

ለዚህ ግዙፍ ጥቃት የሚሰጠው ምላሽ መከናወን ያለበት በብዙ ግንባሮች ነው፡- በመጀመሪያ ደረጃ ይህን ጥቃት ያደረሰው የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC) በአስቸኳይ በመንግስታትና በአለም አቀፍ አካላት በአሸባሪነት መፈረጅ አለበት።  የኢራን አብዮታዊ ዘብ (IRGC)፤ በጋዛ ሃማስና ኢስላሚክ ጂሃድን፣ በሊባኖስ ሂዝቦላን፣ በየመን ሁቲዎችንና በኢራቅ  የሺአ ሚሊሻዎችን ጨምሮ፣ በአካባቢው የኢራን አገዛዝ ተጨማሪ የሽብር ተላላኪዎችን በገንዘብ፣ በማሰልጠንና  በማስታጠቅ ይደግፋል፡፡  የኢራንን እኩይ ተጽእኖ ለማስፋፋትና የመካከለኛው ምስራቅን ለዘብተኛ  ኃይሎች ለማተራመስ በአካባቢው ምስቅልቅል ይፈጥራል፡፡

 በሁለተኛ ደረጃ ይህ ጥቃት፣ የኢራን የተራቀቁ ሚሳኤሎችንና ተዛማጅ ቴክኖሎጂዎችን ጨምሮ ስልታዊ አቅሞችን ማሳደድ፣ የአገዛዙን ወረራ ለማራመድና እስራኤልንና የአለምን ስርዓት ለአደጋ የሚያጋልጥ  መሆኑን አሳይቷል፡፡ የኢራን አገዛዝ ላይ በሚሳኤል መስክ ብቻ ሳይወሰኑ እንደዚህ አይነት ስትራቴጂካዊ አቅሞችን የማሳደድ እንቅስቃሴው  ላይ ጥብቅና አስጨናቂ  ማዕቀብ ሊጣልበት ይገባል።


በመጨረሻም፣ እንደማንኛውም እንዲህ አይነት መጠነ ሰፊ ጥቃት የተፈፀመባት ሀገርና የእስላማዊ  ሪፐብሊክ ባለስልጣናት ሀገራችንን ለማጥፋት በየእለቱ የሚሰነዝሩትን የዘር ማጥፋት ዛቻ ተከትሎ፣ እስራኤል ከዚህ ጥቃት ራሷን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ነው። ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው ወደፊትም ራሳችንን ከኢራን ጥቃቶች መከላከል እንቀጥላለን።


ኢራን ላይ የአጸፋ እርምጃ መውሰድን በተመለከተ የእስራኤል ጦር  ካቢኔ ለሁለት መከፈሉ ተነግሯል፡፡ በዚህ ጉዳይ ላይ ማብራሪያ ሊሰጡን  ይችላሉ ?

ቀደም ሲል እንደገለጽኩት፣ እስራኤል ከዚህ የኢራን መንግስት ህገወጥ ጥቃት ራሷን የመከላከል መብቷ የተጠበቀ ሲሆን፤ እኛም ከዚህ ቀደም እንዳደረግነው እናደርጋለን።

አሜሪካ፤ እስራኤል በኢራን ላይ በምትወስደው የአጸፋ እርምጃ፣ እጄን አላስገባም  ማለቷን በተመለከተ እርስዎ  ምን ይላሉ?

አሜሪካና ሌሎች አጋሮች ከእኛ ጋር መቆማቸውን እስራኤል ታደንቃለች፤ ይህ ደግሞ የቅዳሜውን ጥቃት ለመከላከል በተደረገው ትብብር በግልፅ ታይቷል። በአሜሪካ የሚመራው ድጋፍና ትብብር በዋጋ የማይተመንና ወደር የለሽ ነው።

የትኛውም ሀገር በህልውናዋ ላይ የመጣ አደጋን ሊቀበል አይችልም ፤ እስራኤልም ከዚህ የተለየች  አይደለችም። እስራኤል ከኢራን የሚደቀንባትን ስጋት  አትታገስም፤ ጉዳት ለማድረስ ለሚደረገው ማንኛውም ሙከራ ሁሉ ጠንከር ያለ ምላሽ ትሰጣለች። እስራኤል፤ ኢራንም ሆነች ተላላኪ ድርጅቶቿ በዜጎቿ ላይ ስጋት አለመፍጠራቸውን ታረጋግጣለች።


የኢራን የድሮንና የሚሳኤል ጥቃት፣ በተለይም፣ ከቀጠናዊው ውጥረት አንጻር ያለውን አሁናዊና የረዥም ጊዜ የደህንነት አንደምታ እስራኤል እንዴት ትገመግመዋለች?

ኢራን ሽብርተኝነትንና አለመረጋጋትን በማስፋፋት፣ ቀጣናዊ ወኪሎቿን በገንዘብ በመደገፍና  በማስታጠቅ ለዓመታት ዘልቃለች፡፡ ሃማስ በገንዘብ የሚደገፈው፣ የሚሰለጥነውና የሚታጠቀው በአብዛኛው በኢራን አገዛዝ ሲሆን፤ ለዚህ የዘር ማጥፋት አሸባሪ ቡድን የኢራን ድጋፍ ባይኖር ኖሮ፣ እ.ኤ.አ. ጥቅምት 7 ቀን 2023 በእስራኤል ላይ የተፈፀመው ጥቃት አይከሰትም ነበር፡፡  ላለፉት ስድስት ወራት ኢራን በተላላኪዎቿ - ሃማስና ኢስላሚክ ጂሃድ በጋዛ፣ ሂዝቦላ በሊባኖስ፣ ሁቲዎች በየመንና  የሺዓ ሚሊሻዎች በኢራቅ፣ አማካኝነት በእስራኤል ላይ ጦርነት ስትከፍት ቆይታለች። በእስራኤል ሰሜናዊ ድንበር የሚሰነዘረው የሂዝቦላ ጥቃት ቀስ በቀስ እያደገና  ሙሉ ለሙሉ የባለብዙ ግንባር ጦርነት ስጋት እየሆነ መምጣቱን እንዲሁም  በቀይ ባህር ላይ በአለም አቀፍ መርከቦች ላይ በሁቲዎች የሚፈጸመው ጥቃት ዓለማቀፍ ንግድን እየጎዳውና የመላው ዓለም ኢኮኖሚ ላይ ተጽዕኖ ማድረሱን  እናያለን።

 

የሰሞኑ ጥቃት የእስላማዊ  ሪፐብሊክ፣ እስራኤልን ከኢራን ግዛት በቀጥታ ሲያጠቃ ለመጀመሪያ ጊዜ ከመሆኑ አንጻር፣ ግጭትን የማባባስ ተግባር  ተደርጎ የሚታይ ነው፡፡ ይህ መባባስ ክልሉን ከዚህ በፊት ታይቶ በማይታወቅ ሁኔታ ወደ አለመረጋጋት እንዲመጣ በማድረግ፣ የከፋ ግጭት እንዳይፈጠር  ያሰጋል።  ክልላዊና ዓለም አቀፋዊ ትብብር በእንደዚህ ዓይነት ምክንያታዊ ያልሆኑ ተዋናዮች ላይ ያለውንም ጠቀሜታ ያሳያል።

ከዚህ ጥቃት አንጻር፣ እስራኤል፣ የኢራን ወታደራዊ አቅም የጋረጠውን መጠነ ሰፊ ስጋት እንዴት ትመለከተዋለች?

እስራኤል ይህ ጥቃት እስላማዊ ሪፐብሊክ በኢራን አብዮታዊ ዘብ በኩል፣ አካባቢውን ለማተራመስና ሽብርተኝነትን ለማስፋፋት እንዲሁም ተጽእኖውን ለማስፋትና በመካከለኛው ምስራቅ ላይ ትርምስ ለመፍጠር የሚያደርገውን ጥረት በተመለከተ ለብዙ አመታት ያስጠነቅቅነውን እንደ ማረጋገጫ አድርጋ ነው የምትመለከተው፡፡ በክልሉ ውስጥ ያሉ ብዙ ለዘብተኛና ኃላፊነት የሚሰማቸው ተዋናዮች፣ ይህን እውነታ ከረጅም ጊዜ በፊት ተገንዝበዋል።

የኢራን ተጽዕኖ ፈላጊነት ከመካከለኛው ምስራቅ ባሻገር  የተስፋፋ ሲሆን፣ በዓለም ላይ ያሉ ኃላፊነት የሚሰማቸው ተዋናዮች፣ የኢራን መንግስት ተፅእኖ ለመፍጠርና የአለምን ስርዓት ለማተራመስ የሚያደርገውን ጥረት ትኩረት ሰጥተው መቃወም አለባቸው። በቅርቡ የተፈፀመው ጥቃት፣ የኢራን አገዛዝ ስለ እስራኤል መጥፋትና ስለ ሽብርተኝነትን ማስፋፋት ጥሪ ሲያደርግ፣ ከምሩ ለመሆኑ ለሚጠራጠሩ ሁሉ እንደ ማንቂያ ደወል ማገልገል አለበት። የዚህ አገዛዝ ድርጊት እጅግ ጽንፈኛ የሆኑ መሪዎቹን ቃል የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እስራኤል የኢራንን ጥቃት ለመግታት ምን ዓይነት ዲፕሎማሲያዊ መንገዶችን ትከተላለች?

የቅዳሜ ሌሊቱን ጥቃትን ተከትሎ፣ በተባበሩት መንግሥታት የእስራኤል አምባሳደር፣  የተመድ የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ እንዲያደርግና በጉዳዩ ላይ እንዲወያይ ጠይቀዋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና ተጨማሪ አካላት እንዲሁም ሀገራት የኢራንን ጥቃት በማያሻማ መልኩ እንዲያወግዙና እስላማዊ ሪፐብሊክና ደጋፊዎቿ ጥቃታቸውን በአስቸኳይ እንዲያቆሙ ጥሪያችንን ማቀረባችንን እንቀጥላለን፡፡
እስራኤል፣ በዓለም ዙሪያ በርካታ ሀገራት፣ ኢራን በፈጸመችው ጥቃት ላይ ጠንከር ያለ ውግዘት ማሰማታቸውን በበጎነቱ  ተቀብላለች፣ ሌሎች ሀገራትም ይህን አስከፊ የአለም አቀፍ ህግ ጥሰት የሚያወግዙትን እንዲቀላቀሉ እናበረታታለን።
እደግመዋለሁ፣ በዲፕሎማሲው መስክ፣ ሁለት ፈጣን ተግባራዊ እርምጃዎች መወሰድ አለባቸው፣ እነዚህም፡-
1- የኢራን አብዮታዊ ዘብን (IRGC) በአሸባሪነት መፈረጅ።
2- ኢራን ለማሳካት እየሰራች ያለችውን  ባላስቲክ ሚሳኤሎች፣ ድሮኖች፣ በመካሄድ ላይ ያለውን የኒውክሌር መርሃ ግብርና የህዋ አቅሞችን ጨምሮ የኢራን ስትራቴጂካዊ  አቅሞች ላይ ያነጣጠረ ጉዳት የሚያስከትል ማዕቀብ መጣል። አለም ኢራንን  እንደዚህ አይነት ስትራቴጂካዊ አቅሞች እንዳታገኝና እንዳታዳብር ማገድና መከልከል አለበት፡፡
ጥቃቱ፤ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2023 በተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት ውሳኔ 2231 ጊዜው ያለፈበትን  የማዕቀብ ስርዓት፣ በአማራጭና ሁሉን አቀፍ በሆነ  የማዕቀብ ሥርዓቶች በመተካት ማዕቀቡን የማስፋፋትና የመጣል አስፈላጊነትን አጽንኦት ሰጥቶታል፡፡ ጥቃቱ በተጨማሪም የኢራን  የኒውክሌር መርሃ ግብር፣ ከመርፈዱ በፊት  በአስቸኳይ የማቆምና የመቀልበስ አስፈላጊነቱን አጉልቶታል፡፡

እስራኤል ተጨማሪ የግጭት መባባስን ለማስቀረትና በቀጣናው መረጋጋትን ለማስፈን ምን እርምጃዎችን ልትወስድ አስባለች?

እስከ ኦክቶበር 7, 2023 ድረስ መካከለኛው ምስራቅ ወደ ሁለንተናዊ ለውጥ እየገሰገሰ ነበር። ከ2020 ጀምሮ በአብርሃም ስምምነት፣ እስራኤል ከተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች፣ ባህሬንና ሞሮኮ ጋር የመደበኛ ግንኙነትና የሰላም ስምምነቶችን ተፈራርመናል፣ከሱዳን ጋር ያለውን ግንኙነት መደበኛ ለማድረግ እየሰራንም ነበር። ሂደቱ ቀጠለና፣ ይህ ጦርነት ከመጀመሩ በፊት ባሉት ወራት ውስጥ ከሳውዲ አረቢያ ጋርም እንኳን ወደ መደበኛ ግንኙነት ለመግባት  እየተጓዝን ነበር። ይህ የመካከለኛው ምስራቅ የበለጠ ትስስርና ትብብር ያለው ራዕይ፣ቀጣዩ መንገድ ነበር፡፡

እንደ አለመታደል ሆኖ፣ የኢራን አገዛዝና በአካባቢው ያሉ ፅንፈኛ ተላላኪዎቹ፣ እንደዚህ አይነት አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ እድገቶች ስጋት ውስጥ ጣላቸው፡፡ ይህ ለቀጣናው ህዝብ የተሻለ የወደፊት ተስፋ ቢፈነጥቅም፣ በመካከለኛው ምስራቅ የኢራን  ቀጣይ ተጽእኖና ሽብርተኝነት መስፋፋት ላይ እንቅፋት ፈጥሯል። በትንሹም ቢሆን፣ በጥቅምት 7 የተፈጸመው አሰቃቂ የሃማስ የሽብር ጥቃት ጽንፈኞች - በኢራን የሚመራው የኔትዎርክ አካል -- ባለፉት ጥቂት ዓመታት በእስራኤልና በአረቡ ዓለም መካከል የተደረጉትን አዎንታዊ ዲፕሎማሲያዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ስኬቶች ለማስቆምና ወደ ኋላ ለመመለስ ያደረጉትን ሙከራ ይወክላል።

በዚህ የለዘብተኞች እና ጽንፈኞች ጦርነት፣ የቀጣናው ለዘብተኞች ያሸንፋሉ ብለን እናምናለን፤ እናም የእኛ ይበልጥ የተሳሰረና የተባበረ የመካከለኛው ምስራቅ የመፍጠር  የጋራ ራዕያችን፣ ይህ ጦርነት አብቅቶ፣ እስራኤል የድንበሯና ዜጎቿ ደህንነት ጉዳይ ወደ ቀድሞ ሁኔታው ከተመለሰ በኋላ ዳግም መስመር ይይዛል፡፡  

እስራኤል የዓለማቀፍ አጋሮች፣ በተለይም የቀጣናው አጋሮች፣ የኢራንን የጥቃት እርምጃ በማውገዝና በመቃወም የሚያደርጉትን አስተዋጽኦ  እንዴት ታየዋለች?

አሁንም ይህ የለዘብተኞችና የአክራሪዎች ጦርነት ነው -- ወደፊት የተሻለና ሰላማዊ ይሆናል ብለው  በሚያምኑ እና ግጭት፣ ሽብርተኝነትና ትርምስ ቀለባቸው በሆኑት መካከል  የሚደረግ ጦርነት ማለት ነው፡፡ በዚህ ጦርነት ደግሞ በአለም አቀፍም ሆነ በክልል ደረጃ አጋሮች አሉን፤ ባለፈው ቅዳሜ ለደረሰው ጥቃት ምላሽ በሰጡበት ወቅት ይህንን ለማየት የቻልን ይመስለኛል። እነዚህ አጋርነቶችና ትብብሮች  ጠቃሚ ናቸው፡፡ በአሜሪካ የሚመራው የእስራኤል አጋሮችና ተባባሪዎች  እኩይ ባላጋራ ሲገጥማቸው በጋራ መስራት ይችላሉ።

ከዚህ ክስተት ጋር በተገናኘ ለዓለማቀፉ ማህበረሰብ ምን መልዕክት ማስተላለፍ ይፈልጋሉ?

እስራኤል፤ አሜሪካና ሁሉም አጋሮቿ ከጎኗ መቆማቸውን ታደንቃለች፤ የኢራንን ጥቃት ለመከላከል ያደረጉትን እገዛም እናደንቃለን። የአለም አቀፉ ማህበረሰብ በዚህ ጥቃት ላይ የሚያደርሰውን ውግዘት በበጎነቱ  ስንቀበል፣ ሌሎችም  ኃላፊነት የሚሰማቸው ተዋናዮች፣ የኢራንን ጥቃት በማውገዝ ከእስራኤል ጎን እንዲቆሙና የእስራኤልን እራሷን የመከላከል መብት እንዲደግፉ እናበረታታለን።

በተጨማሪም እስራኤል፣ የኢራንን ህዝብ እንደ ጠላት እንደማታየው ማጤን አስፈላጊ ነው፤ ይልቁንም ትኩረቷ የገዛ ህዝቡን በሚጨቁነውና ግቡ  እስራኤልን ማጥፋት በሆነው አክራሪ የኢራን አገዛዝ ላይ ነው፡፡ በእርግጥ ከቅዳሜው ጥቃት ወዲህ ባሉት ቀናት #IraniansStandWithIsrael የሚለው ሃሽታግ በማህበራዊ ትስስር X (የቀድሞው ትዊተር) ላይ እየታየ ነበር። የኢራን ህዝብ በዚህ አገዛዝ እየተሰቃየ መሆኑን እንረዳለን፤ እናም በአስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ላሉቱ  ድጋፋችንን እንገልፃለን።

Read 1090 times