Monday, 29 April 2024 07:46

ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ አዲስ የማስተር ክላስ ሥልጠና ጀመረ

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

 መንግሥት ለእንዲህ ያሉ ተቋማት ድጋፍ እንዲያደርግ ተጠየቀ



          ከተከፈተ 17ኛ ዓመቱን ያስቆጠረውና እስካሁን ከ3ሺ800 በላይ የፋሽን ዲዛይነሮችን አሰልጥኖ ያስመረቀው ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ ፤ አዲሱን ከፍተኛ የማስተር ክላስ ሥልጠናውን ባለፈው ቅዳሜ ምሽት ሚያዝያ 12 ቀን 2016 ዓ.ም ቦሌ ዩጎ ሰርች አጠገብ በሚገኘው ሪያሊቲ ፕላዛ ህንጻ ላይ በይፋ መጀመሩን አስታወቀ፡፡
የፋሽን ማስተር ክላስ ለተማሪዎቹ ከሚሰጣቸው ሥልጠናዎች መካከል፡- ስፔሻል ፓተርን ዲዛይን፣ አርት ድሮዊንግ፣ ፋብሪክ ፔይንቲንግ፣ ፋሽን ስታይሊንግ፣ 3ዲ ዲዛይን፣ ፋሽን ማኔጅመንትና ሌሎችም ይገኙበታል ተብሏል፡፡
የኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ መሥራችና ባለቤት ወ/ሮ ሣራ መሃመድ በምሽቱ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ “ማስተሪንግ ክላስ ሰዎች እንደ መክሊታቸው (ተሰጥኦዋቸው) ከፍተኛና ልዩ ሥልጠና የሚያገኙበት ፕሮግራም ነው” ብለዋል፡፡
በምሽቱ በኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ ተመራቂዎች የተዘጋጀ አስደማሚ የፋሽን ትርኢት ለታዳሚዎች የቀረበ ሲሆን፤ ሞዴሎች የተለያዩ የፋሽን ዲዛይን ውጤቶችን ያሳዩት በመድረክ ላይ በቄንጥ እየተራመዱ ሳይሆን በየቦታው እንደ ሃውልት ወይም የቅርስ ጥበብ በየቦታው ተገትረው ነበር - በመጀመሪያ እይታ በልብስ መሸጫ መደብሮች የሚታዩትን አሻንጉሊቶች የመሰሏቸውም አልጠፉም፡፡
ኮሌጁ ባለፉት ዓመታት ከዓለማቀፍ ተመሳሳይ የማሰልጠኛ ተቋማት ጋር በፈጠረው መልካም የሥራ ግንኙነት 42 ዲዛይነሮች በህንድ አገር ሙሉ የነጻ ትምህርት እንዲያገኙ ያደረገ ሲሆን፤ሥልጠናቸውን ተከታትለው በመመለስም ለኢንዱስትሪውና ለአገራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ እያበረከቱ እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ኮሌጁ ከሥልጠናው ጎን ለጎን፣ የተለያዩ የፋሽን ትርኢቶችን ከአገር ውስጥ ባሻገር በኒውዮርክ፣ ፈረንሳይ፣ ጣልያን፣ ጀርመን፣ ስዊዘርላንድ፣ ኡጋንዳና ሌሎችም አገራት በማቅረብ ስኬትና ዕውቅና ተቀዳጅቷል ተብሏል፡፡
ኔክስት ፋሽን ዲዛይን ኮሌጅ፤ በቅርቡ ከሳውዲ አረቢያ ተባረው ወደ አገራቸው የተመለሱ እንስት ኢትዮጵያውያንን በነጻ በማሰልጠን የሥራ ዕድል እንዲያገኙና ለሌሎች የሥራ ዕድል እንዲፈጥሩ ማስቻሉ ይነገርለታል፡፡ ሴቶችን ፋሽን ዲዛይንና ሞዴሊንግን ጨምሮ በሌሎች ዘርፎች በማሰልጠን ጉልህ አስተዋጽኦና ተጽዕኖ በመፍጠር ላይ የሚገኘው ኮሌጁ፤ እስካሁን የራሱን መሬት ባለማግኘቱ ለህንጻ ኪራይ ከፍተኛ ወጪ እንደሚያወጣ የተናገሩ አንድ የዕለቱ የክብር እንግዳ፤መንግሥት ለእንዲህ ዓይነቶቹ  ተቋማት ትኩረት ሰጥቶ መደገፍ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡ “እኔ መንግሥት ብሆን መሬት የምሰጠው እንደ ኔክስት ፋሽን ኮሌጅ ላሉ የግል ተቋማት ነው፡፡” ሲሉም አክለዋል፡፡

Read 169 times