Tuesday, 30 April 2024 00:00

ከእኛና ከይሁዳ ከሀዲው ማን ነው?..

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

 በሕይወት መም ላይ፣በአዳም ልጅ ሩጫ ብዙ እንቅፋቶች፣በርካታ ውጣ ውረዶች ይኖራሉ። የሰው ልጅ ማኅበራዊ ፍጡር ነው፤ ሩጫው ግላዊ ብቻ ሳይሆን ቡድናዊም በመሆኑ እንደ ማኅበረሰብና አደግ ሲልም እንደ ኅብረተሰብ ብዙ በጎና በጎ ያልሆኑ ገጠመኞችን ያስተናግዳል። ማኅበር ወይም ደግሞ ኅብረት ደግሞ የሚፈጠረው፣ በሁለት ቡድኖች መካከል በሚደረግ  የጋራ ቃልኪዳን ነው።
በሚገርም ሁኔታ ቃልኪዳን የተጀመረው በሰው ልጆች መካከል ብቻ ሳይሆን፣በፈጣሪና በሰው ልጆች መካከል እንደሆነ የመንፈሳዊው ዐለም ድርሳናት ያሳዩናል። ምናልባትም በአዳምና በእግዚአብሔር መካከል የነበረው ቃል ኪዳን የመጀመሪያውና በአንደኛው ወገን መንሸራተት የተነሳ የፈረሰ ነው ማለት ይቻላል። ከዚያ በኋላ ቃሉን ጠብቋል የሚባለው የእግዚአብሔር ወዳጅ አብረሃም ነው። በመቀጠል የሰው ልጅ በቤተሰብ፣በጉርብትና፣በጓደኝነትና በትዳር ሲኖር፤ የጋራ የሆኑ ውሎችና ኪዳናት፣እንዲሁም ያቋቋማቸው የጋራ ተቋማት ጥብቅ ትስስሮች ይኖሩታል።


አንዳንዶቹ ተቋማት ውሎችን በመፈጸምና ባለመፈጸም ምክንያት የሚፈጠሩ ሳንካዎችን ውል ለማያስያዝና እልባት ለመሥጠት የሚቋቋሙ ሲሆኑ፣ሌሎቹ  ደግሞ ውሎችን በአግባቡ ለማስፈጸም የሚዘጋጁ ግዳጆችም የሚያካትቱ ናቸው። ስለዚህ የሰው ልጅ ገና ከጅማሬው አንስቶ አሁን እስካለንበት የተራቀቀ ቴክኖሎጂ ዘመን፣ ራሱን በኪዳንና በውል የሚቋጭባቸው ቀበሌያዊና ዐለምአቀፋዊ ተቋማት አሉት። ከእነዚህ ተቋማት አንዳንዶቹ ጸጥታን ለማስጠበቅና ፍትሕን ለማስከበር ሲሉ የተቋቋሙ ናቸው። ለምሳሌ ዐለም አቀፍ ጉዳዮችን ለማስከበር የተቋቋሙት የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቋማት፣ የሁለተኛው ዐለም ጦርነት በሰው ልጆች ሕይወትና ኑሮ ላይ ያደረሰው አደጋና ሠቆቃ ዳግም እንዳይፈጸም የተደረጉ የጋራ ስምምነቶች ናቸው።


ይሁን እንጂ ብዙ ጊዜ በግልም ሆኑ በቡድን የተደረጉ ስምምነቶችና ውሎች ሁሉ አይጸኑም። ቃልን በማጠፍ ምክንያት በክህደት የሚቋጩ ብዙ ቃልኪዳኖች አሉ።በጓደኛሞች መካከል፣በቤትና በጎረቤት፣በሠራተኛና አሠሪ የሚፈጸም ቢሆንም፤ አልፎ አልፎ በክህደት ይቋጭና አንደኛውን ወገን ያሳዝናል። ይህም ክህደት በአብዛኛው የሚፈጸመው፣በራስ ወዳድነት፤ምናልባትም አቅም በማጣት ሊሆን ይችላል። በነዚህ ሰበቦችም ምክንያት ዋነኛ ዐላማቸውን የጣሉ፣ኪዳናቸውን ያሽቀነጠሩ ብዙ ናቸው። አብረው ጀምረው፣መንገድ የቀሩ፣ወይም በጥቅም የያዙትን ጥለው፣ ነገር ያበላሹ የትየለሌ እንደሆኑ በሠፈርም በሀገርም ሠምተናል፤እንሠማለንም።
ይሁን እንጂ ስለክህደት በተነሳ ቁጥር ቀንደኛ ብለን የምንወቅሰው፣ ከኢየሱስ ክርስቶስ ሐዋርያት አንዱ የሆነው የአስቆርቱ ይሁዳ ነው። ስለዚህም በተለምዶ በፍቅር ሕይወት ተከዳሁ ያለ ሰው፣በንግድ አክሲዮን ወይም በሌላ ሥራ ቃሌን ተበላሁ ብሎ ያሰበ ሰው፣ለአንደኛው ወገን “ይሁዳ”የሚል ታርጋ ይለጥፍበታል። ነገር ግን ይሁዳ ሕይወቱና ፍጻሜው የተበላሸው ከጴጥሮስ የበለጠ ከሀዲ ሆኖ አይደለም። ይልቅስ ስሜቱ በጣም ስስ ሆኖ በራሱ ላይ ቸኩሎ እርምጃ በመውሰዱ ነው። ጴጥሮስ መሳሳቱን ሲያውቅ ያየው ወደ ራሱ ጥፋት ሳይሆን፣ወደ ጌታው ምሕረት ስለነበረ ነገሩን በይቅርታ ቋጭቶታል።
ሌላኛውና ከዋና ዋና ከሀዲዎች ተርታ የተቆጠረው፣በሮማ ኢምፓየር በጦር ስትራቴጂው፣ሮማን በኀይል በመግዛትና ለሮም ሕዝብ ባመጣው ተሀድሶ የሚታወቀው ጁሊየስ ቄሳርን የከዳው ብሩተስ ነው። ይህ ሰው ከቱጃሯ፣ ዝነኛና መልከ ቀናዋ  ንግሥት ኪሊዎፓትራ፣ ልጅ መውለዱ የሚነገርለትን ቄሳርን የከዳውና ለተፈጸመበት ግድያ  ተጠያቂ ነው የሚባለው ነው። የከዳውም  ለጥቅሙ ነበር።


ስለከዳተኞች ካነሳን፣ ግለሰብ ብቻ ሳይሆን ቡድንም ይከዳል። ሀገራችን ኢትዮጵያ በተቋም ከተከዱት አንዷ ነች። የከዳትም ለሕዝቦች ፍትሕና እኩልነት የተቋቋመው ሊግ ኦፍ ኔሽን ነው። ይህ ተቋም የሌሎችን ሉዐላዊ ሀገራት ድንበር ጥሶ ወረራ መፈጸም በደል መሆኑን እያወቀ፣የኢጣሊያ ፋሽስት ጦር ኢትዮጵያን ሲወርር  ባለመከላከል የገባውን ቃል ከድቷል።
ክህደት በግልና በቡድን የሚፈጸም በመሆኑ ወደ ታችኛው መዋቅር ሲወርድ ይበልጥ ሕመሙ ይበረታል። ምክንያቱም አንድ ሰው ከሌላ ሰው ጋር የሚኖረው ውል በግል በመቀራረብና በመተማመን የሚፈጸም ስለሆነ፣ከቡድኑ ወይም ከተቋሙ ይልቅ ጉዳቱ ቅርብና መረር ያለ ነው። ለምሳሌ፣የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ስንል፣ በሩቅ የምናውቀውና የተለያዩ ሰዎችን በተለያዩ ጊዜያት ወክሎ የሚያሠራ እንጂ በአካል የሚታወቅ፣ለአንድ ሰው የቅርብ ወዳጅ፣ወይም በቡናና ሻይ፣በእድር፣በእቁብና በማኅበር የሚገናኝ ስላልሆነ አካላዊ ግንኙነቱ ሩቅ ነው። በሌላ በኩል ስናየው ደግሞ አንድ ባል ለሚስቱ፣ወይም የጦር አዛዥ ለሠራዊቱ የገባውን ቃል ባይጠብቅ ከባድና መራራ ነው።


በደጉ ቀን ሞትኩልህ፣ሞትኩልሽ የተባባሉ ፍቅረኞች ቢከዳዱ ለተመልካች ግርምት፣ ለታሪኩ ባለቤት አሠቃቂ ነው። ባልና ሚስት በጥቅምና በመሠል ችግሮች ቢከዳዱ፣ሠራዊቱን የሚከዳው አዛዥ ደግሞ ራሱን ከሞት ለማዳን ሲል ቢሸሽ ክህደቱ የበለጠ የስሜት ንዝረት አለው። በተቃራኒው ጽኑ የሆኑት ደግሞ ሞት አፉን ከፍቶ  ሲመጣ እንኳ፣ ስለ ቃልኪዳናቸው ይሰዋሉ። ለዚህ ዐይነቱ ኪዳን፣ የሞሶሎኒን ፍቅረኛ የፔታቺን ያህል የሚደንቅ የለም። ምክንያቱም ሰውዬው ሥልጣኑ እየከሰመ፣ቀኑ እየጨለመ፣በጦርነቱ ሽንፈቱን ተጎንጭቶ ፣የመቅረዙ ዘይት ባለቀ ሰዐት ሞት ደጅ ላይ ቆሞ ሳለ፣ ደረትን ለጥይት መሥጠት የሚደንቅ ጥንካሬ ነው። ይህንን ብዙዎች አያደርጉትም።


ከግለሰባዊ ክህደትና ታማኝነት ከፍ ስንል፣ በኢትዮጵያ ታሪክ በርካቶች ከሀገራቸው ይልቅ ጥቅማቸውን አስበልጠው፣በክፉ ቀን ሕዝባቸውን ክደዋል። ከእንደዚህ ዐይነት ከሀዲዎች አንዱ ናቸው የሚባሉት፣በቀዳማዊ ኀይለሥላሴ ዘመን በሀገሪቱ የሚኒስትርነት ሥልጣን የነበራቸውና በጠላት ወረራ ወቅት ከጠላት ጋር የቀሩ ሰው ነበሩ። ስለእኚህ ሰው የጻፉት የወቅቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር አቶ አክሊሉ ሀብተወልድ እንዳሉት፤ ሚኒስትሩ ሀገራቸውን የከዱት “ልጆቼን ላሳድግበት”በሚል ሥጋት ነበር፡፡  በወቅቱ አቶ አክሊሉ በዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ የሀገራችንን የነፃነት ትግል በተመለከተ ሲሠሩ፣ከጎናቸው እንዲቆሙ የጠየቋቸው ሚኒስትር መልስ የራስ ወዳድ ነበር። ሀገር በጠላት እጅ ወድቃ፣ሰንደቅ ዐላማ እንደ ጨርቅ ተጥሎ፣ወገን በጠላት ጅራፍ እየተገረፈና እየሞተ ልጆችን ማሳደግ ምን እንደሆነ የነፃነትን ጣዕም ለሚያውቅ ትርጉም አይሰጥም።
ክህደት ዘርፈ-ብዙ በመሆኑ፣ከሀገራዊ ክህደት ሌላ ሉዐላዊ ሀገራት ለሌሎች  ሀገራት የገቡትን ቃል አጥፈው ባልታሰበ ሁኔታ ሊፈጽሙ ይችላሉ። ለዚህ ምሳሌ በሁለተኛው የዐለም ጦርነት ጅማሬ፣ የናዚ ጀርመን መንግሥት በሶቪየት ኅብረትና በሌሎችም መሰል መንግሥታት ላይ የፈጸመውን ክህደት ለአብነት ማንሳት ይቻላል። ለዚህ ማሳያው በክህደት ሰበብ የዐለምን ዝብርቅርቅ ከፈጠሩት እ.ኤ.አ 1939 ፣ ኦገስት 23 እና 24 ቀን፣”The molotov-ribbentrop pact” በሚል እርስ የተፈረመው እርስ በርስ ላለመዋጋትና ወደ ጥቃት ላለመምጣት የተገባው ቃልኪዳን በጀርመን ከተጣሰና፣ወዳጇ ላይ ጦር ከሠበቀች በኋላ የተፈጠረው ቀውስ ነው።


በዚሁ ዐለም አቀፍ ሁነት ጀርመን ታላቋ ብሪታንያ ላይም ተመሳሳይ ክህደት ፈጽማለች። ይህ እንዳይሆን የሠጉት የወቅቱ የታላቋ ብሪታኒያ አምባሳደር የነበሩት የጆን ኤፍ ኬኔዲ አባት፣ ”አንቺ ሀገር ሆይ ንቂ፤አትዘናጊ!”ሲሏት፣ከእርሳቸው  ይልቅ፣የጀርመንን ማባበል በመሥማታቸው፣ቀኑ ደርሶ ምድረ ሰማዩን የብረት አሞራዎች ወርረው እሳት እስኪረጩ፣አልገባቸውም ነበር።
ክህደትን በተመለከተ ናዚ ጀርመን በሁለተኛው የዐለም ጦርነት አቻ በሌለው ሁኔታ በርካታ ሀገራትን ከድታ፣ዐሥራ አንድ ሀገራትን ወግታለች። ቀደም ሲል በየፈርጁ እንዳየነው፣ ዓለም ከግለሰብ ጀምሮ፣እስከ ኅብረተሰብ ለጥቅም ሲል እየተከዳዳ መቀጠሉን አይተናል። ግለሰብ ግለሰብን፣ግለሰብ ሀገርን፣ሀገር ሀገርን ሲከዳ ኖሮ፣ አሁንም በዚያው ሀዲድ ላይ አለ፤ ወደፊትም ይቀጥላል።
ይሁን እንጂ አብዛኛዎቻችን ሌሎችን ከዳተኛ ከማለት ያለፈ ራሳችንን እንደ ከዳተኛ ለማየት አንሞክርም። በራሳችን ዐይኖች ውስጥ ያለውን ምሰሦ አስቀምጠን፣ የሌሎች ስንጥር ላይ እናተኩራለን። ስለዚህ የትኛውንም ክህደት ማንጸሪያ አድርገን ዕድፍና ጉድፉን ሁሉ ይሁዳ ላይ እንመርጋለን፤አንዳንዴም ዴማስ ላይ እናላክካለን። ወደ እውነቱ ስንመጣ ግን ብዙዎቻችን የይሁዳን ያህል እንኳ ታማኝ አይደለንም። ይሁዳ ሕሊናው ሕያው ባይሆን ኖሮ አይጸጸትም፤ባይጸጸት ኖሮ ራሱን አያጠፋም። ለሞት አሳልፎ የሰጠው ጌታ፣ ንጽህና ውስጡን ወቅሶት፣ነፍሱን አምሶት መኖር ከልክሎታል።


እኛስ?...እኛ በቢሯችን፣እኛ በንግድ ሥፍራችን፣እኛ በተመደብንበት የሥራ መደብ፣የገባነውን ቃለመሐላ ለመፈጸም ምን ያህል ታማኞች ነን? ሐኪሙ ምን ያህል በታማኝነት አገልግሎት ይሰጣል?...መሐንዲሱ ተቋማት ግንባታና የመንገድ ሥራ ላይ ለጥራት ምን ያህል ጥንቃቄ ያደርጋል? ለሕዝብ  አስተዳደር ተመርጠን የገባነውን ቃልኪዳን ፣ በተቃራኒው ለሕዝብ መከራ የሆንን ሰዎች ክህደታችን ከይሁዳ አይከፋም?
ቀደም ሲል ተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ ሆነን፣ እኩልነትና ፍትሕ ያሠፍኑልናል ተብለን በሕዝብ ተስፋ ሲጣልብን፣ ከአቋማችን ተንሸራትተን በጥቅማጥቅም የሕዝብን ኀላፊነት አሽቀንጥረን የጣልን ጥቂት አይደለንም። ያንን አድርገን እንደ ይሁዳ ጸጸት፣ እንቅልፍ አልከለከለንም። የገዛነው መሬት (የደም መሬት) እርም ብለን አልተውነውም። ያመነን ሕዝብ እንባ ረግጠን፣በሥቃዩ ላይ አበባ ነስንሰን፣ እስክስታ ከወረድን፣ ከእኛና ከይሁዳ ከሀዲው ማን ነው?..ዴማስ ይህን ዐለም ወድዶ ጥሎኝ ሄዷል ያለው ሐዋርያ፣እኛን ቢያየን ምን ይለን እንደሆነ ስሌቱ ሩቅ ነው። ስለዚህ ብዙዎቻችን፣ወገናችንንና ሀገራችንን በተግባር በመክዳታችን፤ከድተን ባለመጸጸታችን ከይሁዳ ይልቅ ከዳተኞች ነን ባይ ነኝ።
ከአዘጋጁ፡-
ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ፣ ላለፉት በርካታ ዓመታት በዚሁ ጋዜጣ ላይ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ዙሪያ አያሌ መጣጥፎችን አስነብቧል፡፡ በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎች ላይ ሂሳዊ ትንተና አቅርቧል፡፡ ደረጀ በላይነህ ገጣሚና አርታኢም ነው፡፡ 12 ያህል መጻሕፍትን አሳትሞ  ለአንባቢያን አድርሷል፡፡

Read 613 times