Tuesday, 30 April 2024 19:43

ከስህተት እንማር፡- የአልጀርስ ስምምነት መሰረታዊ ግድፈቶች

Written by  (በ ደረጀ ጥጉ፤ የአለም አቀፍ ህግ መምህር
Rate this item
(3 votes)

 መንደርደሪያ
እ.ኤ.አ. ከ1890-1941 ከነበረው የጊዜ ቅንፍ ውጭ ራሱን ችሎ የሚታወቅ ኤርትራ የሚባል ሉአላዊ ሀገር በአለም ታሪክ አይታወቅም ነበር፡፡ እ.ኤ.አ ከ1890-1941 በፊት እና በኋላም አለም የሚያውቀው እውነት፤ ኤርትራ የኢትዮጵያ አንድ የግዛት አካል እንደነበረች ነው፡፡ ለዛም ነው የ1952 (እ.ኤ.አ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በውሳኔው ቁጥር 390(V) ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሀድ የወሰነው፡፡ ጣልያን በሁለተኛው የአለም ጦርነት ድል በመደረጓ በምስራቅና በሰሜን አፍሪካ የነበሯት የቅኝ ግዛት ሀገሮችን ለድል አድራጊዎቹ ሀገራት እንድታስረክብ በ1947 የፓሪስ ስምምነት ተገዳለች፡፡ ጣልያን በአፍሪካ ውስጥ የነበሯትን ሀገሮች እንድታስረክብ በመደረጓና ይህንንም ተከትሎ ከመጣው የ10 አመት  የእንግሊዝ ወታደራዊ ሞግዚት አስተዳደር በኋላ፣ በ1952 (እ.ኤ.አ) የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሚከተሉትን መሰረታዊ ነጥቦች ግምት ውስጥ በማስገባት፣ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሀድ ወሰነ፡፡ ነጥቦቹም፡-
በኤርትራ የሚኖሩ ህዝቦችን ፍላጎትና ደህንነትን በማጤን የተለያዩ የዘር፤ የሃይማኖትና የፖለቲካ ቡድኖችን ሀሳብ ግምት ውስጥ በማስገባትና ህዝቡ እራሱን በራሱ የማስተዳደር አቅሙን በመረዳት፡-
በምስራቅ አፍሪካ ያለውን የሰላምና የደህንነት ሁኔታ በማጤን፡-
የኢትዮጵያን መብት ማለትም ጂኦግራፊያዊ፤ ታሪካዊ፣ ባህላዊ፣ ኢኮኖሚያዊ የይገባኛል መብትን በተለይም ኢትዮጵያ የሚያስፈልጋትን የባህር በር ግምት ውስጥ በማስገባት ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በፌደሬሽን እንድትዋሀድ ወሰነ፡፡
ከላይ እንደተመላከተው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በ1952 ኤርትራ በፌደሬሽን ከኢትዮጵያ ጋር እንድትወሀድ ሲወስን፣ የኢትዮጵያን የባህር በር ባለቤትነትን ግምት ውስጥ በማስገባት ጭምር ነበር፡፡ ይህ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ውሳኔ የድንበር ጉዳይን እስከ ወዲያኛው ድረስ እልባት የሰጠ ብቸኛው አለም አቀፍ ውሳኔ ነው፡፡ ኤርትራ የኢትያጵያ የግዛት አካል እንደመሆኗ መጠን በንጉሱም ሆነ በደርግ መንግስት ዘመን ኤርትራን ጨምሮ ለአስተዳደር እንዲመች የህዝቡን ባህል፤ ቋንቋ፤ አሰፋፈር መነሻ በማድረግ በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ የወሰን ማካለል ሽግሽግ ተደርጓል፡፡ በፌደሬሽን የተዋቀረ ሀገር ማለት እንደ አንድ አህዳዊ መንግስት በአንድ ሉኣላዊ ሀገር ውስጥ ያለ አስተዳደር ነው እንጂ በራሱ ሉኣላዊ አይደለም፡፡ ለዚህ ማሳያ የሚሆነው የአፋር ግዛት የአሰብን ክፍል ይዞ ለዘመናት የኖረ የኢትዮጵያ ክፍል ነው:: ለ46 አመታት ለፀናው የጣልያን ቅኝ ግዛት ዘመን ካልሆነ በስተቀር አሰብና የቀይ ባህር ክፍል የአፋር ግዛት አካል ሆኖ ኖሯል:: ኤርትራም ያለ ቀይ ባህር አፋር ክልል ራስ ገዝ ሆኖ በኢትዮጵያ ታሪክ እንደምትታወሰው ሁሉ፤ የቀይ ባህር ክፍልም የአፋር ራስ ገዝ ክፍል ሆኖ የተመዘገበ እውነታችን ነው፡፡ በአሀዳዊም ሆነ በፈደራላዊ አወቃቀር ሉአላዊነት የሚከፋፈል ሳይሆን አንድ እና ወጥ ነው፡፡ ህወሓትም ሆነ ሻእቢያ ስልጣን ሲይዙ የሰሜኑ የኢትዮጵያ ግዛት ክፍል የድንበር ለውጥ የተደረገበትና ህጋዊም ጭምር ነበር፡፡ እንዲህ አይነት የውስጥ ግዛት አወቃቀር ለውጥ ህጋዊና በየትኛውም የአለም ክፍል የሚደረግ  የሉአላዊነት መገለጫም ጭምር ነው፡፡ ሊቀበሉት ባይፈልጉም ህወሓትም ሻእቢያም በ1983 ዓ.ም ስልጣን ሲይዙ የተረከቡት ይህንን እውነት ነበር፡፡
የአልጀርስ ስምምነት መሰረታዊ ግድፈቶች
በድንበር ውዝግብ መነሻነት ለተቀሰቀስውና አስከፊ ለነበረው ደም መፋሰስ ምክንያት የሆነውና ለሁለት አመታት የቆየው ጦርነት በኢትዮጵያ አሸናፊነት ቢደመደምም፣ የኢትዮጵያ መንግስት በጥድፊያ ለፊርማ በአልጀርስ ተቀመጠ፡፡ ጦርነቱ በኢትዮጵያ አሸናፊነት እንደ አውሮፓ አቆጣጠር በ2000 ቢደመደምም፣ የኢትዮጵያ መንግስት ለፊርማ የተቀመጠው በጥድፊያና በችኮላ (ወይም ደግሞ ህወሓት በውስጡ ይዞት የነበረውን እኩይ አላማ ለማስፈፀም) ነበር፡፡ ይሄ መጣደፍና ሁለቱ መንግስታት ወሰን ለማካለል የተጠቀሙባቸው ማስረጃዎች የአልጀርስ ስምምነትን፣ ስምምነት ተብሎ እንዳይወሰድ ያደረገ ነበር፡፡ የአልጀርስ ስምምነት ያዋቀረው የቦርድ ኮሚሽን የተሰጠው ስልጣን፤ ድንበር ለማስመርና ለማካለል ነው፡፡ ይህንንም ለማድረግ ማስረጃ አድርጎ የተጠቀማቸው የሚከተሉትን ሰነዶች ነው፡፡
የ1900፣ 1902፣ 1908 በጣልያን እና በኢትዮጵያ ማሀከል የተደረጉ ስምምነቶች፤-
የ1964 የአፍሪካ አንድነት መሪዎች ውሳኔ (The Cairo resolution) እና፡-
አግባብነት ያለው አለማቀፍ ህግ ናቸው፡፡
ከመነሻው አስረጅ ተብለው የቀረቡት የ1900 ሰነዶች ውድቅ የሆኑ ናቸው፤ ምክንያቱም ጣልያን ኢትዮጵያን በ1935 (እ.ኤ.አ) ለሁለተኛ ጊዜ ስትወር የ1900 ስምምነቶችን ውድቅ አድርጋቸዋለች፡፡  ይህ የሆነበት ዋነኛ ምክንያት ጣልያን ኢትዮጵያን ስትወር በአለም አቀፍ ህግ መሰረት ኢትዮጵያ የምትባል ሉአላዊ ሀገር አልነበረችም እንደ ማለት ነው፡፡ በ1969ኙ የቪየና የውል ስምምነት ድንጋጌ (The Vienna Convention on law of Treaties) አንቀፅ 60  መሰረት፤ “ከተዋዋዮች አንዱ የተዋዋሉበትን የውል አላማ ከጣሰ ፣ ሌላው ተዋዋይ ውሉን ውድቅ የማድረግ መብት አለው” ይላል፡፡ ስለዚህም በቪየና የውል ስምምነት ድንጋጌ አንቀፅ 60 መሰረት፤ ከላይ የተጠቀሱት ውሎች  በተዋዋዮቹ (ማለትም በጣልያን እና በኢትዮጵያ) ላይ አይፀናም፡፡ ከዚህም በተጨማሪ የ1947 የፓሪስ ስምምነት የቅኝ ግዛት ስምምነቶቹን ውድቅ አድርጓቸዋል፤ ምክንያቱም ጣልያን ግዛቷን በሙሉ ለሁለተኛው የአለም ጦርነት ድል አድራጊዎች እንድታስረክብ ተደርጋለችና፡፡ ስለዚህም በኢትዮጵያ እና በኤርትራ መካከል ድንበር ለማካለል ሊጠቀስ የሚችል ምንም አይነት የቅኝ ግዛት ውል ድሮም አልነበረም፤ አሁንም የለም፡፡ በኮሎኒያል ጣልያን እና ኢትዮጵያ መሀከል የነበረው የድንበር ግንኙነት እስከ 1941 እና እስከ ፌደሬሽኑም ውሳኔ ድረስ አልተሰመረም አልተከለለም፤ እስከ አሁንም አልተከለለም፡፡ ሌላው ነጥብ ኤርትራ ነፃነቷን ስትቀዳጅ ምንም አይነት በአለም አቀፍ ደረጃ እውቅና ያገኘ ወሰን አልነበራትም፡፡ የአልጀርስ የድንበር ኮሚሽን  የሰጠው ውሳኔ በህግ ፊት ህያው በሆኑ ውሎች ሳይሆን በውድቅና ሙት በሆኑ ህጎች ላይ በመመስረት ነበር፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ዶ/ር ያእቆብ ሐይለማርያም (አሰብ የማን ናት በሚለው መፅሐፋቸው) እንዳሰፈሩት፤ የ1900 ስምምነቶች፣ ጣልያን በማንኛውም መንገድ ግዛቷን  የምታጣ ከሆነ ለማንም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ታስረክባለች የሚል አንቀጽ አላቸው፡፡
እንደ 1969ኙ የቪየና የውል ስምምነት ድንጋጌ ውል የሚፈረመው ሁለት እና ከዛ በላይ በሆኑ የመዋዋል ህጋዊ ብቃት ባላቸው አካላት ነው፡፡ ውሉ የሚያስረውም በሌላ መልኩ ካልተገለጸ በቀር ተዋናዮቹን ወይም በህግ የወከሉትን ብቻ ሲሆን፤ ሌላ ሰው ወይም አካል ባልተደራደረበትና ባልተስማማበት ውል ሊጠቀምም ሆነ ሊጠየቅ አይችልም፡፡ ይህንን መነሻ በማድረግ ኢትዮጵያ እና ጣልያን በ1900፣1902፣1908 የፈረሟቸው ውሎችን እንኳን ህጋዊ ውል ናቸው ብለን ብንቀበል፣ ውሉ አሳሪነቱ ኢትዮጵያ እና ጣልያንን እንጂ በውሉ ውስጥ ህጋዊ ህልውን ያልነበራትን ኤርትራ አይመለከትም፡፡ በዚህ ምክንያት ኤርትራ የጣልያን ውል ወራሽ ልትሆን አትችልም፡፡
ኤርትራ የጣልያን ቅኝ ግዛት ስለነበረች ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር የገባችው ግዴታም ሆነ መብት ኤርትራ ነፃ ስትወጣ ትወርሳለች የሚል መከራከሪያ ሊነሳ ይችላል፡፡ ዶ/ር ያእቆብ ሐይለማርያም እንደሚሉት፤ አንድ ሀገር ከቅኝ ግዛት ነፃ ሲወጣ ቅኝ ገዢው የገባቸው ግዴታዎችን እንደገና ተደራድሮ ግዴታውን ካላደሰ፣ ቅኝ ገዢው ከገባው ግዴታ አዲስ አገር ነፃ መሆኑን ወይም እንደማይመለከተው ማሳወቅ አለበት፡፡ ኤርትራ ግን ይህንን አላደረገችም፡፡ በቅኝ ገዢዎች ቀድሞ ይተዳደር የነበረ ግዛት ለአዲሱ መንግስት ሲተላለፍ አዲስ ኢንተርናሽናል ህይወት እና ህልውና መጀመሩ ስለሆነ ከማናቸውም ግዴታ ነፃ መሆኑ እሙን ነው፡፡
የ1964 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት
የመሪዎች ውሳኔ
ባለህበት እርጋ (uti posssiditis) የሚለው መርህ፤ አገሮች ነጻ ሲወጡ የያዙትን ድንበር እንዲያከብሩ ይደነግጋል፡፡ ከዚህ አግባብ ውጪ ባለህበት እርጋ የሚለው መርህ፣ በኢትዮጵያ እና ኤርትራ ድንበር ጉዳይ መጠቀስ አልነበረበትም፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ የግዛት አካል እንጂ ቅኝ ግዛት አልነበረችም፡፡ ባለህበት እርጋ የሚለው መርህ በላቲን አሜሪካና በአፍሪካ ውስጥ በቅኝ ግዛት ስር የነበሩ ሀገሮች፣ ከቅኝ ግዛት አገዛዝ ነፃ ወጥተው ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ የያዙትን ድንበር እንዲያከብሩ ቢያሳስብም፣  መርሁ በኢትዮጵያ ላይ አይሰራም፤ ምክንያቱም ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ አልነበረችም፡፡ ኤርትሪያ ከኢትዮጵያ ጋር ድንበር አካልላለሁ ካለችም በ1983 ዓ.ም የተረከበችውን ግዛት ማክበር አለባት እንጂ ሌላ የምትጠቅሰው ውልም ሆነ መርህ የላትም፡፡ ባለህበት እርጋ የሚለው መርህ  እና የ1964 የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመሪዎች ውሳኔ የሚያሳስበው ይህንን ነው፡፡ ከቅኝ ግዛት ነፃ የወጡ ሀገሮች በነፃነታቸው ወቅት የያዙትን ድንበር ማክበር አለባቸው፡፡ ኤርትራ የኢትዮጵያ ቅኝ ተገዢ ነበረች የሚለው እውነት ቢሆን እንኳን፣ ኤርትራ ነፃ ስትወጣ የያዘችውን ግዛት ማክበር አለባት ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በኤርትራ መገንጠል ምክንያት ኢትዮጵያም ከ1983 ዓ.ም ወዲህ አዲስ ሀገር ስለሆነች  ነፃነታቸውን ሲቀዳጁ የያዙትን ድንበር ማክበር አለባቸው የሚለው ለኢትዮጵያም ይሰራል ማለት ነው፡፡
የ1900 ስምምነቶች በሚከተሉት
ምክንያቶች ውድቅ ሆነዋል፡-
ጣልያን ከኢትዮጵያ ጋር የፈረመቻቸው ውሎችን በመጣስ ኢትዮጵያን ወርራ ከኢትዮጵያ ጋር የተስማማችባቸው ስምምነቶችን አፍርሳ ኢትዮጵያ ኤርትራ እና የጣልያን ሱማልያን አንድ ላይ አጣምራ፣ የጣልያን ምስራቅ አፍሪካ ግዛት ለመመስረት በመነሳቷ ውሎቹ ውድቅ ሆነዋል፡፡ የመጀመሪያው የአልጀርስ ስምምነት ስህተት ሙት እና ውድቅ የነበሩትን የ1900 ውሎችን ከመቃብር ቆፍሮ አስረጅ መከራከሪያዎች አድርጎ ማቅረቡ ነው፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው ጣልያን ኢትዮጵያን ለሁለተኛ ጊዜ ስትወር የ1900 ውሎቹን ፉርሽ አድርጋለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የ1952 የተባበሩት መንግስታት ውሳኔም ውድቅ አድርጓቸዋል፡፡ ስለዚህ ውሎቹ ህይወት የላቸውም ማለት ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የሚከተሉት ነጥቦች ስምምነቶቹ ፉርሽ መሆናቸውን የሚያረጋግጡ ናቸው፤-
ሁለተኛው የአለም ጦርነት ተደምድሞ ድል አድራጊ አገራት ጣልያን እና ሌሎች አገራትን ኢትዮጵያንም ጨምሮ በ1947 ዓ.ም በተፈራረሙት የፓሪስ የሰላም ውል አንቀፅ 23 መሰረት፣ ጣልያን በአፍሪካ የነበራት ማንኛውም መብቶች ሲሰረዙ፣ ከኢትዮጵያ ጋር የተፈራረመቻቸው ውሎችም አብረው ተሰርዘዋል፡፡
በ1952 በተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በውሳኔ ቁጥር 390 V፤ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ጋር በኢትዮጵያ ንጉሰ ነገስት ዙፋን በፌደሬሽን እንድትተዳደር ሲወስን፣ ቀደም ሲል ጣልያን እና ኢትዮጵያ የተፈራረሟቸው ውሎች ውድቅ ሆነዋል ማለት ነው፡፡
ዶ/ር ያእቆብ ሐይለማርያም በመፅሐፋቸው እንዳሰፈሩት፤ ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የ1900 ውሎችን ተደራድረው አላደሱዋቸውም፡፡ ውሎቹ ሙት ሆነዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በንጉሱ ዘመን ሦስቱ ውሎች በነጋሪት ጋዜጣ በወጣ ትእዛዝ ቁጥር 6/1952 ዓ.ም  በኢትዮጵያ የተሰረዙ መሆኑ ተደንግጓል፡፡ 60ኛው የቪየና ኮንቬንሽን እንደሚለው፤ “ማንኛውም ውል ከተዋዋዮቹ በአንዱ ተዋዋይ ቢጣስ ሌላው ተዋዋይ ጥሰቱን እንደምክንያት በመውሰድ ውሉን ውድቅ ማድረግ ይችላል”፡፡ ኢትዮጵያም ያደረገችው ይህንን ነው፡፡
ማጠቃለያ
ኤርትራ ከኢትዮጵያ ስትገነጠል በአለም አቀፍ ደረጃ  እውቅና የተሰጠው ድንበር አልነበረም፡፡ ነበር ከተባለም በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ የነበረው የውስጥ ወሰን ብቻ ይሆናል፡፡ ከላይ እንደተጠቀሰው፤ ኢትዮጵያን በተለያየ አጋጣሚ የመሩ መንግስታት፣ የተለያዩ የውስጥ ድንበር ማካለል አድርገዋል፡፡ ኤርትራም ራስ ገዝ አስተዳደር ሆናለች፡፡ የትኛውም አህጉርና  አለም አቀፍ ድርጅት ይህን የኢትዮጵያ ድርጊት ተቃውሞ ጥያቄ አላነሳም ነበር፡፡ በነዚህ የታሪክ  ወቅቶች የ1964 ካይሮ የመሪዎች ውሳኔ አልተነሳም ነበር፤ ምክንያቱም አስፈላጊ አልነበረም፡፡ ምንም እንኳን በኢትዮጵያ ውስጥ የትግል እንቅስቃሴ ቢኖርም የአ.አ.ድ በ1963  ሲመሰረት ኢትዮጵያ ኤርትራን አቅፋ እንደ አንድ ሉአላዊ አገር አባል ሆናለች፡፡ እንዲህ አይነት ትጥቅ ትግል ቢኖርም የትኛውም የአ.አ.ድ አገር እንደ ልዩ ክስተት አልተመለከተውም ነበር፡፡. መንግስትም ሲዋጋ የነበረው የአ.አ.ድ የግዛት አንድነት መርህ መከበር አለበት የሚለውን ለማስከበር ነበር፡፡
የድንበር ጉዳይን በተመለከተ የሚነሳ ግጭትን እስከ ወዲያኛው ያስቀራል በሚል እምነት ነበር ሁለቱ መንግስታት  የአልጀርስ ስምምነትን የፈረሙት፡፡ መንግስታት ስምምነት ውስጥ ሲገቡ ስምምነቱ በምንም መንገድ አንዱን ወይም ሁለቱን ተዋዋዮች በከፋ ሁኔታ እንደማይጎዳ ልብ ይሉታል፡፡ ይህ የተለመደ ነው ፤ በኢትዮጵያ በኩል የሆነው ግን “ባሏን ጎዳሁ ብላ እንትንዋን በእንጨት ወጋች” የሚለውን ብሂል የሚያስንቅ ነው፡፡ በአለም ታሪክ እራሱን በሞተ እና ውድቅ በሆን ውል ያሰረ መንግስት ቢኖር፣ የኢህአዴግ መንግስት ብቻ ሳይሆን አይቀርም፡፡ ይሆናል የተባለው ሁሉ እንዳይሆን ሆኖ ሁለቱን ሀገሮች ለሌላ ዙር ጠብና ጥላቻ አፋጠጣቸው፡፡
ስምምነቱም ሆነ የድንበር ኮሚሽኑ ውሳኔ እስከ አሁን ድረስ ችግሩን መቅረፍ ሳይችል ባዶ  ሆኖ ቀርቷል፡፡ ይህም ስምምነቱ በግድፈቶች የተሞላ መሆኑን መስካሪ ነው፡፡ ከሁሉም ነገር በላይ የአልጀርስ ስምምነት ምክንያታዊነት፤ ፍትህ እና ርትእ ይጎድለዋል፤ ይላሉ ዶ/ር ያእቆብ፡፡  ከሌላ ዙር ግጭት ጠብቆ ፈጣሪ ያቆየን፡፡ ቸር እንሰንብት፡፡
ከአዘጋጁ፡-
ፀሀፊውን በኢሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡


Read 884 times