Saturday, 04 May 2024 09:58

“ሰላም ፈላጊና ጦርነት ፈላጊ” የሚለው ትርክት ስህተት መሆኑን ጄ/ል ታደሰ ተናገሩ

Written by 
Rate this item
(3 votes)

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች መካከል፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ፣ “ሰላም ፈላጊ እና ጦርነት ፈላጊ አለ” በሚል እየተፈጠረ ያለው የልዩነት ትርክት ስህተት ነው፤ ሲሉ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር  ምክትል ፕሬዚዳንት  ጄነራል ታደሰ ወረደ ተናገሩ፡፡
ጄነራሉ ባለፈው ረቡዕ ሚያዝያ 23 ቀን 2016 ዓ.ም  ለትግራይ ክልል መገናኛ ብዙኃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፣ የፕሪቶሪያ ግጭትን በዘላቂነት የማቆም ስምምነት አተገባበርን በተመለከተ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፌደራል መንግስትና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር የሁለት ቀን ውይይት ማድረጉን አመልክተዋል።
የፕሪቶሪያ ውል አተገባበርን በተመለከተ  በተደረገው  ውይይት፣ የአፈፃፀም ስምምነት ላይ ተደርሷል ያሉት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፤ “ከውይይቱ የማጠቃለያ ስምምነት በመነሳት የትግራይ ደቡባዊ ዞንና ፀለምት እስከ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም.፤ የምዕራብ ትግራይ ጉዳይ ደግሞ እስከ ሰኔ 30 ቀን 2016 ዓ.ም.  ዕልባት እንዲያገኙ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰናል” ብለዋል።
ተፈናቃዮች በሁለት ወራት ውስጥ ወደቀያቸው  እንደሚመለሱ የገለጹት ጄነራል ወረደ፤ ተፈናቃዮቹ  ወደቀያቸው ከመመለሳቸው በፊት “መሬታቸው፣ ቤታቸውና እርሻቸው ተይዞ ስለሚገኝ በመጀመሪያ ምቹ ሁኔታ እንዲፈጠር” መግባባት  ላይ መደረሱን ጠቁመዋል፡፡
አያይዘውም፤ “ትጥቅ ማን ይፈታል ? እንዴትስ ይፈታል? የትኞቹ አስተዳደሮች ይፈርሳሉ? ተፈናቃዮች በምን መልኩ ይመለሳሉ?” በሚሉ ነጥቦች ላይ ውይይት ተካሂዶ ዝርዝር እቅድ እንደወጣለት ጠቅሰዋል።
 በትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር አመራሮች መካከል፣ በፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አፈፃፀም ዙሪያ፣ “ሰላም ፈላጊ እና ጦርነት ፈላጊ አለ” በሚል እየተፈጠረ ያለው የልዩነት ትርክት ስህተት ነው  ያሉት ጄነራሉ፤ “ትርክቱ ስህተት መሆኑን ለፌደራል መንግሥት ገለፃ ሰጥተናል” ብለዋል፡፡ ይሁንና ጄነራሉ  እየተፈጠረ ነው  ያሉት የትርክት ስሕተት ከየትኛው ወገን እንደመነጨ በግልጽ አልተናገሩም፡፡
“የፕሪቶሪያው ውል ስምምነቱ ከተፈፀመበት ቀን ጀምሮ ከማንኛውም አይነት ግጭት በፀዳ መልኩ ተፈፃሚ ይሆናል ተብሎ ባይጠበቅም፣ አሁን መሬት ላይ ካለው ሁኔታ አንጻር  አንዳችም ለግጭት የሚጋብዝ ሁኔታ የለም” ያሉት  ጄነራሉ፤ “የፌደራል መንግስት በበኩሉ፣ የስምምነቱን ትግበራ እስከ ታች ድረስ እንደሚያወርደው እንጠብቃለን” ብለዋል፡፡  
ከሰሞኑ በራያ ወረዳዎች እና አላማጣ ከተማ እንደ አዲስ ከተቀሰቀሰው ግጭት ጋር ተያይዞ የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ50 ሺህ ማለፉን  የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (ኦቻ) አስታውቋል።

Read 979 times