Tuesday, 07 May 2024 00:00

ምክክር - የተምታታበት ከፋፋይ ዘመን ላይ!

Written by  ዮሃንስ ሰ.
Rate this item
(3 votes)

ሰዎች ተነጋግረው ሲግባቡና ሲስማሙ ካየ ደሙ ይፈላል። ሰዎች፣ በዘርና በሃይማኖት፣ በፆታና በኑሮ ደረጃ ተቧድነው እንዲነታረኩና እንዲወነጃጀሉ ይፈልጋል።
•     የሚተጋገዙና የሚገበያዩ ሰዎችን ካየ ዐይኑ ይቀላል። ሁሉም እየሟገቱ ለንጥቂያ ሲሻሙ ለማየት ይናፍቃል። ንፁሕ መስተዋት ካልተሰበረ ፋብሪካም ካልተቃጠለ ይከፋዋል።
•     ተከባብረውና ቀና ብለው የሚራመዱ ሰዎችን ማየት ያንገበግበዋል። በጥበብና በግል ብቃታቸው የላቁ ሰዎችን ማክበር፣ እንደ “ጭቆና” ይቆጥረዋል።
•     “የተረጋገጠና ተቀባይት ያገኘ እውነተኛ አስተሳሰብ”… እንዲህ ዓይነት አባባል ይጎመዝዘዋል።
•     “በሥራ የተገኘ ፍሬ፣ በትጋት የተፈጠረ ሀብት” ብለን ከተናገርን ለነጣቂና ለዘራፊ ያመቻቸነው ይመስለዋል። ሀብትና ንብረት የዝርፍያና የንጥቂያ ውጤቶች ናቸው ይላል።
•     እጅግ የተደነቀ፣ የተከበረና የተወደደ ነገር ካየ፣ “ሌሎችን በማዋረድ የተገኘ ክብር ነው” ብሎ በንዴት ይኮንናል። የተደነቁ ነገሮችን ማናናቅ መደበኛ ስራችን እንዲሆን ያነሳሳናል።
•     ማን ነው እሱ? የዘመናችን መንፈስ ነዋ። የዘመናችን የዓለማችን አስተሳሰብ ነዋ። አንዳንዶች፣ Postmodernism በማለት ይጠሩታል።


የዘመናችንን የአስተሳሰብ ቅኝት እጅግ የተጣመመና በጭፍንነት የተዋጠ እንደሆነ በመተቸት ምንነቱን በዐጭሩ ብሩስ ባወር  ሲገልጹ እንዲህ ይላሉ። “the conviction that … we live in a world without reliable truths… without absolute values,… and without durable meanings”…
እንዲህ ዐይት የቅዠት የአስተሳሰብ  የፖስትሞደርኒዝም አቀንቃኞች የሚሰብኩት አስተሳሰብ እንደሆነ ባወር ይናገራሉ። እንዴት?
የፓስት ሞደርኒዝም ሰባኪዎች በየፊናቸው የሥልጣኔ ገጽታዎችን ያንቋሽሻሉ።
 እውነትና ዕውቀት፣ ሥነ ምግባርና የግል ነጻነት፣ ሕግና ሥርዓት  የሚሉ ቃላትና ሐረጎች በሙሉ ከተረት ያለፈ ትርጉም የላቸውም በማለት  ያጥላላሉ። እንዲያውም ለብልጣ ብልጦችና ለጉልበተኞች የሚያገለግሉ የማታለያ ጭንብሎችና የጭቆና መሣሪያዎች ናቸው ብለው እውነትን ያወግዛሉ። ሥነ-ምግባርን ይኮንናሉ።
አንድ ሐሳብ ከሌላ ሐሳብ አያንስም፤ አይበልጥም ብለው “ያስባሉ”። ለመሆኑ እንዲህ ዐይነት ሐሳብስ ብልጫ አለው?
ልማድና ባህል፣ የአኗኗርና የእምነት ዘይቤ ሁሉ እኩል እንደሆነ ይናገራሉ። ባሕልን ከባሕል፣ የአኗኗር ዘይቤን ከሌላ ዘይቤ የሚያበላልጥ ተጨባጭ ምክንያት የለም ብለው ይሰብካሉ። እናም፣ ሁሉንም ልማድ በእኩል ዐይን የሚያስተናግድ አካታች ባህል መልመድ አለባችሁ ይላሉ። ለመሆኑ የሚነግሩንን ሰምተን የምንለምደው ዘይቤ ከሌሎች ዘይቤዎች ይልቃል? በእነሱ ስብከት የተቃኘ ባህልና ልማድስ ከሌሎች ሁሉ ብልጫ አለው?
ተፈጥሯችን  በጎራ እያቧደነ የሚያናክስ ተፈጥሮ እንደሆነ ያውጁልናል።  ማለቂያ በሌለው ቅራኔ እንድንጠመድ፣ አንዳችን ከሌላችን ጋር የማይታረቅ ጸብ እንደተጠናወተን ይነግሩናል። ሁላችን ከሁላችንም ጋር መፍትሔ በሌለው ግጭት ከመጠፋፋት ውጭ ሌላ አማራጭ ሊኖረን እንደማይችል ያረዱናል። አስፈሪ ቅዠት ውስጥ ያስገቡናል።
“እውነተኛ ሐሳብ፣ መልካም ተግባር፣ የሕይወት ትርጉም” ብለን ብንናገር የፖስትሞደርን አቀንቃኝ ይናደዱብናል።
ከላይ እንደጠቀስነው የፖስትሞደርኒዝም ጠቅላላ አስተሳሰብን በዐጭሩ ብሩስ ባወር  ሲገልጹ፣ “the conviction that … we live in a world without reliable truths… without absolute values,… and without durable meanings” ማለት እንደሆነ ያስረዳሉ። (The Victims’ Revolution, The Rise of Identity Studies and the Closing of the Liberal Mind, Bruce Bawer, 2012)
እንዲሁ ስታዩት እንዲህ ዐይት ፍልስፍና፣ የተሳከሩ ሐሳቦችን እየወለደ፣ እርስ በርሱ እየተጣፋ፣ በቅዠት አዙሪት ውስጥ የሚቅበዘበዝ የስህተት ፍልስፍና እንደሆነ ግልጽ ነው። ነገር ግን፣ “እውነት ብሎ ነገር የለም” ብለው የሚሰብኩ ሰዎች ሐሳቦቻቸው እርስ በርስ ቢታጠረሱ ባይጣረሱ ደንታ አይኖራቸውም። ደግሞም፣ “ማን ዳኛ አደረጋችሁ?” የሚል ምላሽ መስጠት ይችላሉ። “ሐሳቦቼ አይጣረሱም ብል ማን ይከለክለኛል?” ይሏችኋል።
እውኑን ዓለም በተጨባጭ አገናዝቦ በትክክል መገንዘብና ዳኝነት መስጠት የሚችል አንድም ሰው ወይም ሌላ አንድም  አካል፣ ወይም ሌላ አንዳችም  ኀይል የለም በማለት ይናገራሉ፤ ይጽፋሉ።
የሁሉም ሰው ሐሳብና ተግባር በዘርና በብሔረሰብ የተቃኘ ነው ብለው በድፍረት ይፈርጃሉ። ሐሳብህና ተግባርህ የግልህ አይደለም፤ በመኖሪያ አካባቢህ ባህልና ቋንቋ አማካኝነት የተቀረጸ ነው ይላችኋል። ሐሳብሽና ተግባርሽ በራስሽ አእምሮና ውሳኔ የተመራ አይደለም ይልሻል።
የሰው ሐሳብና ተግባር በአጠቃላይ፣ በጀነቲክ ውቅር እና በጾታው፣ በኑሮ ደረጃውና በሀብት እርከኑ፣ በኑሮ መደቡ የተገነባ ነው ብሎ ይሰብካችኋል።
ዘር፣ ጾታና ሀብት የሁሉም ነገር መዘውሮች እንደሆኑ ያምናሉ።
የፖስትሞደርኒዝም አቀንቃኞች…
እውነት፣ መልካም፣ ድንቅ የሚሉ ቃላትን ይጠላሉ።
ዘር፣ ጾታ፣ መደብ የሚሉ ቃላትን ያዘወትራሉ።  (Explaining Post Modernis, stephen Hicks, 2010)
እናም፣  የእገሌ የታታሪነት ባህርይ ከእገሌ ሾላካ ባህርይ አይበልጥም ባይ ናቸው- ፖስት ሞደርኒስቶች።
የእገሌ የሳይንስ ግኝት ከእከሌ የጥንቆላ መነባንብ አይበልጥም። እከሊት የምታወራልን አሉቧልታ፣ እገሊት ካመጣችው ዜና አያንስም። ይልቅስ፣ እበልጣለሁ ብላ ከተናገረችና ሰዎችን ካመኑላት፣ አንዳች ግፍ ሰርታለች ማለት ነው። ሥልጣኗን ወይም ሀብቷን ተጠቅማየበላይነት በማግኘቷ  ነው ራሷን ማግነን ሌሎችን ማብጠልጠል የቻለችው ይላሉ።
“የኔ ወሬ ትልቅ ዜና ነው፤ ያንቺ ግን ተራ አሉቧልታ ነው” ብላ መናገሯ  ጨቋኝነቷን ያጋልጣል እንጂ፣ ትክክለኛነቷን አይመሰክርም  ባይ ናቸው የፖስትሞደርኒዝም አቀንቃኞች።
የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ በሳይንስ አይደለም ብልጫ ያገኙት። የጉልበት ብልጫ ስላገኙ፤ “የኛ ሐሳብ ሳይንሳዊ ዕውቀት ነው፤ የናንተ ሐሳብ ግን ኋላቀር እምነት ነው” ብለው ይናገራሉ ብለው ያወግዛሉ። ጉልበትና ሀብት ያለው ምንም ቢናገር እውነት ነው፣ ምንም ቢፈጽም መብት ነው።
አካል ጉዳተኛና ድሀ ሰው ምንም ቢናገር ሞኝነት ነው፤ ምንም ቢፈጽም ከንቱ ነው። ተበዳይ ሆኖም ወንጀለኛ ነው።  
ሳይንስና ታሪክ፣ ሕግና ሥርዓት የሚሉ ቃላትም የጭቆና መሣሪያዎች ናቸው በማለት የፖስትሞደርኒዝም አቀንቃኞች ሁሉንም በአንድነት ጠቅልለው ይኮንናሉ።
ማን ማንን ለመጨቆን?
ሀብታሞች ድሆችን ለመጨፍለቅ፣ አሜሪካና አውሮፓ አፍሪካን ለመደፍጠጥ፣  ነጮች ጥቁሮችን ለመርገጥ፣ ወንዶች ሴቶች ለመድፈቅ፣  
ክርስትናና እስልምና ነባር አገራዊ ባህሎችንና እምነቶችን ለማጥፋት፣ አገራዊ ባህሎችና እምነቶች ደግሞ የብሔር ብሔረሰብ ነባር ባህሎችና ቋንቋዎችን ለመደምሰስ፣
ሸንቃጣ ረዣዥም ሰዎች አጫጭርና አለቅጥ የወፈሩ ሰዎች ላይ ለማላገጥ፣ በአእምሮና በአካል ብቃት  ብልጫ ያገኙ ዕድለኞች የአካል ጉዳትና ኦቲዝም ባለባቸው ሰዎች ላይ ለመንጠባረር…
በፖስት ሞደርኒዝም ዐይን ሲታይ፣ ሁሉም የሰው ተግባር የክፋት ስሌት ነው። ወይም ደግሞ ከዱር አውሬዎች የተለየ አይደለም። እንዲያውም ይብሳል። ብልጠትና ተንኮል ይጨመርበታል።
የበላዮቹን ተሸክሞ እያመፀ፣ የበታቾቹን  ለመደፍጠጥ ማሤር ነው የሰው ነገር ይላሉ የዘመናችን መንፈስ ናፋሽ ሰባኪዎች። ሁሉም ተሰባበስቦ የተጫናቸው… ከታች ከሥር እነማን ይኖራሉ? “ጥቁር- ድሀ- ሴት- ስደተኛ- አካል ጉዳተኞች?”
አዎ የሚል መልስ ይሰጥዋችኋል።
አካል ጉዳተኞች በጾታና በኑሮ ደረጃ ተከፋፍለው፣ ወንድ አካል ጉዳተኞች በሴት አካል ጉዳተኞች ላይ፣ ሴት አካል ጉዳተኞች በጥቁር ሴት አካል ጉዳተኞች ላይ፣ እነዚህ ሁሉ አብረው ተባብረው ደግሞ፣ ሌሎችን ይረግጣሉ -  “ጥቁር አካል ጉዳኛ ድሀ ስደተኞች”ን።   
ብቻ ምናለፋችሁ?  የፖስትሞደርኒዝም አዝማሪዎች፣…
በዘርና በሃይማት በፆታና በኑሮ ደረጃ እየተቧደኑና እየተወነጃጀሉ መጠፋፋት የሰዎች እጣ-ፈንታ እንደሆነ በመስበክ ለክፉ ዘመቻ የሚያነሳሱ ናቸው- በቀጥታና በተዘዋዋሪ።
ታዲያ በዚህ የዘመናችን ከፋፋይና በታኝ መንፈስ ሥር፣ “ምክክር” ብሎ መሰባሰብ ያወጣል? በቂ ጥንካሬና ጥበብ ይዘናል?



Read 457 times Last modified on Tuesday, 07 May 2024 20:23