Wednesday, 08 May 2024 08:23

በአሜሪካ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊ ለመቄዶንያ ከ2.5 ሚ. ብር በላይ ድጋፍ አደረጉ

Written by 
Rate this item
(2 votes)

ነዋሪነታቸውን በአሜሪካ ያደረጉት  አቶ ጥበበ እሸቱ ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ከ2.5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጣ የቁሳቁስ ድጋፍና ለ7ሺ500 አረጋውያን ሙሉ ወጪውን በመሸፈን የምሣ  ማብላት መርሃ ግብር አከናውነዋል፡፡  

አቶ ጥበበ ትላንት ሚያዝያ 29 ቀን 2016 ዓ.ም በመቄዶንያ ማዕከል በመገኘት አረጋውያኑን ምሣ ያበሉ ሲሆን፤ በርካታ ብርድልብሶችንና ጫማዎችንም ለማዕከሉ አበርክተዋል፡፡

ድጋፉን በማድረጋቸው  ደስተኛ መሆናቸውን የገለጹት አቶ ጥበበ እሸቱ፤ ቀጣይነት ያለው ድጋፍ ለመቄዶንያ የአረጋዊያንና የአዕምሮ ህሙማን መርጃ ማዕከል ለማድረግም ቃል ገብተዋል።

ከዚህ ቀደም ደቡብ ወሎ ጋሸና አካባቢ በጦርነቱ ምክንያት ለተፈናቀሉ ሰዎች 150 ቤቶችን ሰርተው ያስረከቡት በጎ አድራጊው አቶ ጥበበ፤በቅርቡም በትግራይና በአማራ ክልል ጉዳት ለደረሰባቸው ወገኖች ድጋፍ ለማድረግ ቅድመ ዝግጅት ማጠናቀቃቸውን ተናግረዋል፡፡

መቄዶንያ የበጎ አድራጎት ማህበር ምንም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን በተለይም ደግሞ እራሳቸውን ችለው መንቀሳቀስ፣ መመገብና መፀዳዳት የማይችሉ የአልጋ ቁራኛ የሆኑና የሰው ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው አረጋውያንንና አዕምሮ ሕሙማንን ከወደቁበት ጎዳና ላይ በማንሳት ከ7,500 በላይ የሚሆኑ ተረጂዎችን በአዲስ አበባ፣ ደሴ፣ ድሬዳዋ፤ ሻሸመኔ፣ አድዋ፤ ባህርዳር፣ ሐረር፤ ጋምቤላ እና ጎሬ፣ መቱ፣ ጂማ፤ ሰንዳፋ በኬ፣ ሐዋሳ፣ አሶሳ፣ ጎንደር፣ ደብረማርቆስ፣ አምቦ፣ ኮረም፣ ሰመራ፣ ሰቆጣ፣ አምደወርቅ፣ ላሊበላ፣ አዲስ ዘመን፤ አምቦ እና አርባምንጭን ጨምሮ በአጠቃላይ በ25 ከተሞች ውስጥ በመደገፍ ላይ  ይገኛል።

በቀጣይም በወሊሶ፣ ሱልልታ፣ ሰበታ፣ ደብረ ብርሃን፤ ሆሳዕና፣ ዲላ፣ ጂግጂጋ  እና በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞች ላይ የበጎ አድራጎት ተግባሩን ለማከናወን  ከወዲሁ እንቅስቃሴ መጀመሩን ለማወቅ ተችሏል፡፡

Read 1160 times