በትግራይ ክልል፣ ምስራቃዊ ዞን፣ ሃውዜን ከተማ የሚገኝ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቅርስ መዘረፉ ተሰምቷል። ቅርሱ በከተማዋ በሚገኘው እንዳ ተክለሃይማኖት ቤተ ክርስቲያን ይገኝ እንደነበረ ተገልጿል።
ይኸው ቅርስ ከወርቅና በከፊል ከብር የተሰራ መስቀል መሆኑን አንድ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የቤተ ክርስቲያኑ አገልጋይ ለአዲስ አድማስ ጠቁመዋል።
ከ125 ዓመታት በላይ ዕድሜ ያስቆጠረው ይህ መስቀል፣ በ1891 ዓ.ም. ራስ መኮንን ሃውዜንና አካባቢውን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ለቤተ ክርስቲያኗ ያበረከቱት እንደነበር እኚሁ አገልጋይ ጨምረው አብራርተዋል። የቅርሱ መዘረፍ የታወቀው በቅርቡ ቢሆንም፣ ቅርሱ ከንብረት ክፍል እንዲወጣ የተደረገው ግን ሐምሌ 19 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሆነ አገልጋዩ ይናገራሉ።
ንብረቱ ከተቀመጠበት ክፍል የወጣው በቤተ ክርስቲያኗ ሰበካ ጉባዔ ዋና ጸሐፊው መልዓከ ብርሃናት አሸናፊ ወረስ ፈቃድ ሲሆን፣ የወጣበት ምክንያት ቅርሱን ለጎብኚዎች “ለማሳየት” በሚል እንደነበር እኚሁ አገልጋይ ተናግረዋል።
ይሁንና ለተወሰኑ ወራት በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ሳቢያ ለሞቱ ሰዎች የፍትሐት ጸሎት በብዛት ሲደረግ በመቆየቱ፣ የቅርሱን ሁኔታ ለማረጋገጥና የት እንዳለ ለማወቅ አጋጣሚው እንዳልነበር ጠቅሰዋል።
በመጨረሻም፣ መጋቢት 6 ቀን 2016 ዓ.ም ቀን የመስቀሉ አለመኖር ሊታወቅ መቻሉን አገልጋዩ ያወሳሉ። ይህንንም ተከትሎ፣ የቤተ ክርስቲያኑን ቄሰ ገበዝ ጨምሮ ሌሎች የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ቅርሱን ለማፈላለግ ቢሞክሩም ሙከራቸው አለመሳካቱን ነው የሚያመለክቱት።
የቤተ ክርስቲያኗ አገልጋዮች ለፖሊስና ለትግራይ ክልል ባሕልና ቱሪዝም ቢሮ ጥቆማ ማቅረባቸውን እኚሁ አገልጋይ ገልጸው፣ ነገር ግን ተገቢው ትኩረት እንዳልተሰጠው አስረድተዋል።
የዚህ መስቀል ሙሉ መረጃ በትግራይ ባሕል እና ቱሪዝም ቢሮ ተሰንዶ የተቀመጠ መሆኑን አዲስ አድማስ ከተመለከተው የቅርሱ መረጃ ለመረዳት ተችሏል።