Saturday, 11 May 2024 00:00

የ66ቱ አብዮት - በ50ኛ ዓመቱ ማግስት “አብዮቱ እንደ እንጉዳይ የፈላ አይደለም”

Written by  ሚኪያስ ጥላሁን
Rate this item
(3 votes)

      በ1966 ዓ.ም ዘመኑ በተማሪዎችና ምሁራን የተቀጣጠለው የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመት አስመልክቶ በግልም በቡድንም በተለያዩ ኹነቶች እየተዘከረ ይገኛል፡፡ ሰሞኑን የኢትዮጵያ አብዮት 50ኛ ዓመትን የሚዘክር ሴሚናር በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ፣ ራስ መኮንን አዳራሽ ተካሂዷል። ከትናንት በስቲያ በተካሄደው ሴሚናር ላይ አምስት የአብዮቱ ዘመን ምሁራን የተሳተፉ ሲሆን፣ ከአብዮቱ ጋር የተገናኙ በርካታ የተለያዩ ጉዳዮች ተነስተው ውይይት ተደርጎባቸዋል።የሴሚናር መድረኩን በንግግር የከፈቱት የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ፕሬዚዳንት ሳሙዔል ክፍሌ (ዶ/ር)፣ በርዕሰ ጉዳይ ላይ ከዚህ ቀደም አራት ሴሚናሮች መካሄዳቸውን አውስተው፣ ይህም ዩኒቨርስቲው ራስ ገዝ እንዲሆን ከተደረገ በኋላ ከተጀመሩ አዳዲስ እንቅስቃሴዎች አንዱ መሆኑን አመልክተዋል።በሴሚናር መድረኩ ላይ ለውይይት የሚረዳ የመነሻ ሃሳብ በምሁራን ቀርቧል።


የታሪክ ኤሜረተስ ፕሮፌሰር ባሕሩ ዘውዴ የመጀመሪያው የመነሻ ሃሳብ አቅራቢ ሲሆኑ፣ ትኩረታቸውን ያደረጉት በተማሪዎች ንቅናቄ ላይ ነበር። የ1966 ዓ.ም. አብዮትን “የመደብ አብዮት” የሚል ስያሜ የሰጡት ፕ/ር ባሕሩ፣ አብዮቱን ያዋለዱ መንስዔዎች ላይ ዝርዝር ማብራሪያ አቅርበዋል።የስልጣን ጠቅላይነት፣ የተማከለ አስተዳደር እና የመሬት ይዞታ ዋነኛ የአብዮቱ ቀስቃሽ መንስዔዎች “ናቸው” ብለዋል።“አብዮቱ እንደ እንጉዳይ የፈላ አይደለም።” ያሉት ፕሮፌሰሩ፣ በ1960ዎቹ በዓለም አቀፍ ደረጃ የነበረው የተማሪዎች ንቅናቄ የራሱን ጥላ በአብዮቱ ላይ ማጥላቱን አውስተዋል።
ሁለተኛውን የመነሻ ሃሳብ ያቀረቡት አምባሳደር ታደለች ሃ/ሚካኤል ትኩረታቸውን በሴቶች የመብት እንቅስቃሴና ማሕበራት ላይ በማድረግ፣ የአብዮቱን ሂደት አብራርተዋል።
“አብዮቱ ‘ፈንድቷል’ በሚለው አገላለጽ አላምንም፤ ሲንከባለሉ የከረሙ ጥያቄዎች የፈጠሩት አብዮት ነው።” የሚሉት አምባሳደሯ፤ አብዮቱን  “የተሟላ አብዮት ነው” ሲሉ ያሞካሹታል።
የአብዮቱን ዋነኛ እክል ሲያነሱም፣ “የኢትዮጵያን ልዩ ሁኔታ የመረዳት ችግር ነበረበት” ብለዋል።


የቀድሞ የመሬት አስተዳደር እና ይዞታ ሚኒስትር አቶ ዘገዬ አስፋው በበኩላቸው፤ የአብዮቱ እና የመሬት ይዞታ ጉዳይ ላይ ያተኮረ የመነሻ ሃሳብ አቅርበዋል፡፡
የቀዳማዊ ሃይለ ስላሴ ዘመነ መንግስት የመሬት ስሪት ምን እንደሚመስል በስፋት የዳሰሱት አቶ ዘገዬ፤ የመሬት ስሪቱ እንዲለወጥ የተደረጉ ጥረቶችን ወደኋላ ተጉዘው ቃኝተዋል።
በኋላም እርሳቸው በደርግ ዘመን ሚኒስትር የነበሩበት መስሪያ ቤት የ”መሬት ለአራሹ” ዓዋጅን ከማርቀቅ እስከ ማስፈጸም ያከናወናቸውን ተግባራት ለታዳሚው አቅርበዋል።
ዲማ ነገዎ ዶ/ር ደግሞ  ስለ አብዮቱ ጠቅላላ ገለጻ የሰጡ ሲሆን፣ “አብዮት እና የመንግስት ለውጥ ይለያያሉ” በማለት፣ የሌሎች አገራትን ልምዶች በማንሳት ተናግረዋል።
ከ1966 አብዮት በኋላ መንበረ ስልጣኑን የተቆጣጠረው የደርግ መንግስት የሚታወቀው “በሽብር ነው” ብለዋል፣ ዶክተሩ።


የመጨረሻው ሃሳብ አቅራቢ አረጋዊ በርሔ (ዶ/ር) ሲሆኑ በ1960ዎቹ መጀመሪያ በዩኒቨርስቲ ውስጥ የነበራቸውን የተማሪዎች ንቅናቄ ትዝታ ለታዳሚዎች አጋርተዋል።
የተማሪው ንቅናቄ ሲቀጣጠል የተስተዋለውን አገራዊ አውድ ያተቱ ሲሆን፣ አጠቃላይ የፍትሐዊነት ችግር መታየቱን ጠቅሰዋል።የንቅናቄውን ድክመት ሲያነሱ፣ “በንቅናቄው ውስጥ የተተነተነ አቅጣጫ አለመኖሩ ለበርካታ ድርጅቶች መፈጠር ምክንያት ነበር፤ ከዚያም በኋላ ለተፈጠሩ ነውጦች መነሻ ሆነ” ብለዋል። ሁሉም የራሱን ወገን አብዮተኛ አድርጎ በመቁጠር፣ ሌላውን በጸረ አብዮተኛነት መፈረጁም ሌላኛው ድክመት መሆኑንም ጠቁመዋል።የውይይት መነሻ ሃሳቦች ከቀረቡ በኋላ ከታዳሚዎች የተለያዩ ጥያቄዎች ቀርበው ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
“ለእኔ የ2010 ዓ.ም. እንቅስቃሴ አብዮት ነው።” የሚሉት ዶ/ር አረጋዊ ፣ ምክንያታቸውን ሲያስቀምጡም “ህወሓትን አስወግዶ መቀሌ እንዲከትም አድርጎታል” ብለዋል።
ዲማ ዶ/ር ፣ በበኩላቸው፤ በዚህ ሃሳብ አይስማሙም “የስርዓት ለውጥ አልመጣም። የቀድሞው ስርዓት ነው የቀጠለው። በእኔ አስተያየት አብዮት አይደለም” ሲሉ የዶክተር አረጋዊን ሃሳብ ሞግተዋል።
ፕ/ር ባሕሩ ዘውዴ በበኩላቸው፣ “አብዮት እና ለውጥ ይለያያሉ። አብዮት የመደብ ሹምሽር ነው። ለውጥ ሁሉ አብዮት አይደለም” ብለዋል።

Read 734 times