Saturday, 11 May 2024 00:00

እያሽቆለቆለ የመጣው የነጻው ፕሬስ

Written by  ደረጀ በላይነህ
Rate this item
(0 votes)

      የሰው ልጅ ሐሳቡን መግለጥ እንዲችል አንደበት ተሰጥቶታል። ሐዘኑንም ሆነ ደስታውን ለሌሎች ያካፍል ዘንድ ማኅበራዊ አድርጎ ፈጥሮታል። ስሜትም አእምሮም አለው። ስሜቱ የነገረውን አእምሮው አጥልሎና መዝኖ በሕሊናው ዳኝነት ለሌላው ወገን ያቀብላል።
ሰው በተፈጥሮው ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን፣ሐሳቡን በነፃነት የመግለጥ መብት ይዞ የተወለደ ነው። ማኅበራዊነቱን” ሰው ብቻውን ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም” የሚለው መለኮታዊ ትዕዛዝ ሲያሳይ፤ሐሳቡን በነፃነት የመግለጥ መብቱን በሚመለከት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን የተናገረውን ቃል እማኝ ማድረግ ይቻላል።”In every country where man is free to think and speak ...”
የሰው ልጅ ማኅበራዊ ኑሮው መልክ አበጅቶ፣ሀብት አፍርቶ መኖር ሲጀምር፣ደኅንነቱ አደጋ ላይ እንዳይወድቅ፣ያለው እንዳይዘረፍ፣እርሻውና አዝመራው ከንቱ እንዳይቀር ሕግ ካበጀና በስምምነት እንደየዐውዱ ድንጋጌ ካስቀመጠ በኋላ፣ ሰዎች ከሰዎች ጋር ባላቸው መስተጋብር መረጃዎችን መቀባበል አስፈላጊ በመሆኑ፣ የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን በየዘመኑ ሥልጣኔ ልክና ደረጃ ብቅ ማለት ጀምረው እስከዛሬ ደርሰዋል። በእኛ ሀገር እንኳ”እረኛ ምን አለ? “ከሚለው የሕዝብ ድምጽ ጀምሮ እስካሁኑ የቴክኖሎጂና የሶሻል ሚዲያ ዘመን ደርሷል።
ይሁንና ሁሉም ነገር በዘመን ዳና ላይ እያደገና እየተሻሻለ የመምጣቱን ያህል፣የማኅበራዊ ሚዲያው በያንዳንዱ ግለሰብ እጅ መውደቅ፣እጅግ ወደተበላሸና ሥነምግባራዊ ቀውስ ውስጥ እንዲገባ አድርጎታል።
ቀደም ባለው የሚዲያ ሥራ የሚጠበቁ መስፈርቶች ሁሉ ቀርተው፣ያለምንም ሥልጠናና ዝግጅት የትኛውም በእጁ ስልክ የያዘ ሰው የፈቀደውን መረጃ ያለ ተጠያቂነት ለሕዝብ የሚያደርስበት ዕድል/አጋጣሚ በማግኘቱ፣ በኅብረተሰቡ ውስጥ ሊስተካከሉና ሊቃኑ የማይችሉ ችግሮች እስከመፍጠር ተደርሷል።


አሁን ሁሉም ሰው ጋዜጠኛ ነው። የቱም ሰው በራሱ ዕውቀትና ኀላፊነት ስሜት ልክ የወደደውን ማድረግ የሚችልበት ደረጃ ደርሷል። ተጠያቂነቱና ኀላፊነቱ የሚያስፈራና በሕግ የሚያስጠይቅበት ደረጃ አልደረሰም። ምናልባት ወደፊት ችግሩ እየከረረ ሲመጣ የሚፈጠረውን ስልትና ስትራቴጂ ባናውቅም፣ለአሁን ግን ሚዲያውን በቅጣት ከመዝጋት የዘለለ የሕግ መታገጊያ መኖሩን በግሌ አላውቅም።
ቀደም ሲል ግን ጋዜጠኝነት ከፍ ያለ ግምት የሚሰጠው ኀላፊነት በመሆኑ፣በተለይ በሠለጠኑት ሀገራት ከፍተኛ ጥንቃቄና የትምህርት ዝግጅት የሚጠይቅ ዘርፍ ነበር።
ለማሳያ አንድ ሰለጋዜጠኛና ጋዜጠኝነት የተጻፈ መጽሐፍ እንዲህ ይላል፡-
“Learn history,government,working with numbers and the sciences,The things which happen every day in the world are not simple,and a journalist must know everything he can about their past history to understand the reason why they happen.”
እንግዲህ ለዛሬው ችግር፣የትናንት መነሻ ምንጩን ወደ ኋላ ሄዶ እስከመመርመር የሚጠይቀው ጋዜጠኝነት፤ ምን ያህል በጥንቃቄ የተሞላ ኃላፊነት እንደሚጠይቅ የሚያሳይ ነው። ስለዚህም በዐለም ላይ የሠለጠኑት ሀገራት ለፕሬስ ነጻነት ከፍተኛ ግምት ይሰጡት እንደነበር ታሪክና የየሀገራቱ ሕጎች ያስታውሱናል።
ፕሬስ መረጃ ከማቅረብ ባሻገር፣ኢ-ፍትሐዊነትን፣ሙሰኝነትንና የማኅበረሰብ ሕጸጾችን ነቅሶ በማውጣት የመተቸትና የማቃናት ሥራ ይሠራል።
በዚህ ሥራም ሞያዊ ብቃት እንዲኖርና ማኅበራዊና ሀገራዊ መብትና ግዴታን በሚመለከት የተሻለ ኪህሎት እንዲያገኝ መንግሥት ማሠልጠኛ ተቋማትን ይገነባል፤የመረጃ ምንጮችን የሚያሳልጡ ሀዲዶችን ይዘረጋል። ይህ ግን በየሃገራቱ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ አቅምና መጠን ይወሰናል። የሠለጠኑት ሀገራት ፕሬስን እንደሀገር ልማትና ዕድገት አጋዥ አድርገው ሲመለከቱ ደኻና ኋላቀር ሀገራት የመንግሥታቸው ደመኛ አድርገው የጎሪጥ ይመለከቱታል።


በዴሞክራሲ መስመር ውስጥ እጅግ ትልቅ ስምና ታሪክ ያለው ቶማስ ጀፈርሰን፣ ገና በማቆጥቆጥ ላይ የነበረው የሀገሩ ፕሬስ በውሸትና በቅጠፈት ባበሳጨው ጊዜ፣ምሬቱን ውጦ፣”እንዲህም ሆኖ መኖሪያ ቤቴን እስኪያቃጥል ድረስ እታገሳለሁ”ያለው ዝም ብሎ አልነበረም። ያለ ፕሬስ ልማትም፣ዕድገትም የማኅበረሰብ ንቃተሕሊና ከፍታም የማይገኝ በመሆኑ ነው። ይህ በሠለጠኑ ሰዎችና ሀገራት የሚሰጠው ትርጉምና ዋጋ ሲሆን፤ በብዙ ታዳጊ ሀገራት ግን መንግሥታት ፕሬሶችን በማፈን የሕዝብን ድምፅና ፍላጎት ሽባ ለማድረግ ይሠራሉ፤ጋዜጠኞችንም ዐሥረው ያንገላታሉ።
ወደ ራሳችን ሀገር ስንመጣ፣በደርጉ ዘመን ፈጽሞ ነፃ የሚባሉ ፕሬሶች የተከለከሉበት ሲሆን፣አንድም ሰው በየትኛውም መገናኛ ብዙኀን መንግሥትን መተቸትና መቃወም አይችልም ነበር። ስለዚህ የሕዝቡ ጩኸት የታፈነ፣ሀሳቡም አደባባይ እንዳይደርስ የተከለከለ ነበር። ቀጥሎ የመጣው ኢሕአዴግ አጀማመሩ መልካም ተብሎ የተጨበጨበለት፣ውሎ ሲያድር ግን ጋዜጠኞችን በማፈን በዐለም ላይ ከሚታወቁት አፋኝ ሀገራት ጎራ የተመደበ ነበር። ይሁን እንጂ እንደዚያም ሆኖ በርካታ የፕሬስ ውጤቶች ከአደባባይ አልጠፉም። በሰበብ አስባቡ በክስና በእሥር ማዋከብ ቢኖርም፣ እንደሕጉ ፍርድ ቤት አቅርቦ መክሰስና ማሰር እንጂ ከዚያ የከፋ መዘዝ አልነበረውም። በለውጡ ማግስት ግን  የሁላችንንም ልብ በተስፋ የሞላ ጅማሮ ብናስተውልም ቅሉ፣አይተነው ወደማናውቀው የሠለጠነ መንገድ ያደርሰናል የሚል ጉጉታችን እውን አልሆነም። ፖለቲካውና ተቃውሞው ብቻ ሳይሆን የወረቀት ዋጋው ንረት የኅትመቱን ሠፈር ቅርቃር ከቶታል።


የግል ሬዲዮና ቴሌቪዥኖች ቢኖሩንም ያን ያህል ነፃነት ያላቸው አይመስሉም። ቢኖሩ እንኳ ከመንግሥት የሚመጣውን መዘዝ በመፍራት ስፖንሰር አድራጊ ተቋማት ስለሚሸሿቸው ውጤታማ ሆነው መቀጠል አይችሉም።  በአጠቃላይ ፕሬሱንና መገናኛ ብዙኃንን ስንመለከት፣በተለይ የማኅበራዊው ሚዲያ አካሄድ እጅግ የሚያሠጋ ሆኖ እናገኘዋለን። ከላይ የተጠቀሱት ማኀበራዊ ኀላፊነቶች እንዳሉ ሆነው፣ቀላሉንና ሀገራዊ ባሕልና ወግን የሚጥሱ መልዕክቶች፣ሲተላለፉ እናያለን። በተለይ አሁን አሁን የተፈጥሮ መልክ መመዘኛ የሆነ ይመስል፣መልካቸውን አሳምረው፣ፊታቸውን ተቀባብተው እጅግ በሚዘገንንና የማኅበረሰቡን ሃይማኖታዊም ሆነ ማኅበራዊ ድንጋጌ በሚጣረስ መንገድ ሀገር አፍራሽ፣ትውልድ ሰባሪ መልዕክቶች ይተላለፋሉ።
አሳዛኙ ነገር የነዚህ መረን የወጡ ሰዎች ሥርዐት ማጣት ብቻ ሳይሆን፣የእነርሱ ተከታይ፣ወይም ተደራስያን ዙሪያውን እያዳነቁ ማጀብ ነው። ይህ ዕብደትና የዕብደት አጀብ መጨረሻው ምን ይሆናል?..የሚለውን መገመት ቢያዳግትም፤ገደብ ካልተበጀለት ግን ከፊታችን የሚጠብቀንን ጥልቅ ገደል ለማየት ዐይናችንን መኳል አይጠበቅብንም። ስለዚህ የተሻሉ ሚዲያዎች፣ከመንግሥት መለጎሚያ የፀዱ ታማኝ ሚዲያዎች ቢኖሩን ከመጪው ጥፋት ሊታደጉን የሚችሉ ይመስለኛል።


ፕሬስ ለልማትና ለሥልጣኔ፣ለተሻለ ትውልድ ዕድገት ወሳኝ መሆኑን ያልተገነዘበ ሕዝብና መንግሥት ወደፊት ፈቅ ማለት እንደማይችል ካላወቅን፣የእነጀፈርሰን ሀገር ያየችውን ዐለም ማየት አንችልምና ቆም ብለን እናስተውል ባይ ነኝ።
የሰው ልጅ አሐዱ ብሎ ሕይወትን ሲጀምር፣ ሐሳቡን መግለጥ ይችል ዘንድ አንደበት ተሰጥቶታል። ሐዘኑንም ሆነ ደስታውን ፣ተስፋና ምጡን ለሌሎች ያካፍል ዘንድ ማኅበራዊ ተፈጥሮው ግድ ይለዋል። ሰው ስሜትም አእምሮም ፈቃድም  አለው። ስሜቱ የነገረውን አእምሮው አጥልሎና መዝኖ በሕሊናው ዳኝነት ለሌላው ወገን ያቀብላል፤ፈቃዱ ደግሞ ወዳሻው ያጋድላል።
ሰው በተፈጥሮው ማኅበራዊ ብቻ ሳይሆን፣ሐሳቡን በነፃነት የመግለጥ መብት ይዞ የተወለደ ነው። ማኅበራዊነቱን ሰው ብቻውን  ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም”የሚለው መለኮታዊ ትዕዛዝ ሲያሳይ፤ሐሳቡን በነፃነት የመግለጥ መብቱን በሚመለከት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ቶማስ ጀፈርሰን የተናገረውን ቃል እማኝ ማድረግ ይቻላል።”In every country where man is free to think and speak ...”Read 408 times