Monday, 13 May 2024 00:00

የመፅናኛ ማጣረሻዎቻችን

Written by  -ዓለማየሁ ገላጋይ-
Rate this item
(2 votes)

አንዳንዴ እንዲህ እናስባለን…
…. ካሰብን በኋላ “ምን ነካኝ?” ብሎ መደመም የወግ መሆኑ ሳይረሳ…
“ጓደኝነት በተመሳስሎ እንጂ በተቃርኖ ላይ ይመሰረታል? አንዳዴ እንዲህ ይሆናል። ጓደኛሞች አውቃለሁ፤ አንዷ በጣም ቆንጆ ናት፤ ሌላኛዋ የደበዘዘች ….በባህሪም አንዷ የተረጋጋች፣ የተቀረችው ደርሶ ግንፍል የሚያደርጋት። አንዷ ልታይ ፣ ሌላኛዋ ልደበቅ ባይ ናቸው። አንዷ እግሯ ሲለግም፣ የሌላኛዋ ልጓም አልፈጠረበትም። አሁንም አንዲቷ ማመንታት ተፈጥሮዋ ሲሆን፣ ሌላይቷ አስባ ከመወሰኗ በፊት በማድረግና በማለት ፀፀት የተሞላች…
… አንድ ቀን ሁለቱ ባሉበት “ሥነ-ውበት” (aesthetics) ላይ ውይይት ተነሳ። “ውኃ ወቀጣ” አይነት ክርክር፤ውበትን ለውበቱ መለኪያ ያደርጉና ውበትን ከተመልካቹ አንፃር የሚያዩ፤ ውሃ ቢወቅጡት እንቦጭ በሆነ ክርክር ላይ ወዛቸውን ያንጠፈጥፋሉ። ሊቀርብ የቀረበውን ተከራካሪ መቀበል እንጂ የመሸናነፍ ቅጥ የሌለበት ሥነ-ውበታዊ ጎራ።
ከሁለቱ ጓደኛሞች አንዷ እየተናጠቀችና እየተቧጨቀች ታወራለች። ሌላኛዋ “ያንቺስ አስተያየት ምንድነው?” ስትባል ብቻ እየተሽኮረመመች ከዝምታ አለሟ በቀስታ ትወጣለች።
“ለእኔ ውበት ውስጣዊ ነው። ፀባይ ካማረ ውበት አላፊ ጠፊ ከመሆን ወደ ዘላለማዊነት ተሸጋገረ ማለት ነው” ሽኩርምምምም…
“ወዴት? ወዴት? ወዴት?” ምስግ አለች ጓደኛዋ። ሥነ-ውበትና ሥነ-ምግባር ምን አገናኛቸው? ውበት ካለ አለ፤ ከሌለ የለም!! በሥነ-ምግባር መለኪያ የሥነ-ውበትን ጥያቄ መመለስ ኢ-ሳይንሳዊ ነው። ምን አገናኛቸው? ይሄ ውበት ባለመኖሩ ለመጽናኛ የሚደረግ ጥረት ብቻ ነው።”


ውይይቱ ወደ ሌላ አቅጣጫ ሸኝቶኝ ተመለሰ። የሚጎመዝዝ ቢሆንም ቅሉ የልጅቷ ምላሽ እውነትነት አለው። ሥነ- ውበትንና ሥነ-ምግባርን ማተካካት ከመጽናኛነት ያለፈ ዕውነትነት ያለው አይመስልም። ሩስያዊው ደራሲ Fyodor Mikhailovich Dostoevsky ውበትንና ምግባርን ያተካካ አንድ ገፀ-ባህርይ አለው። ራስኮሊንኮቭ ይባላል።   “Crime and Punishment” የተሰኘ ልጨኛ ልቦለዱ ውስጥ የሰው ልጅ ውበት የባህሪው ጠንካራ ጎን ነው ብሎ ያስባል። አስቀያሚነቱ ደግሞ ግድያን ለማከናወን የሚገፋፋው የሥነ-ምግባር ጉድለቱ። ስለዚህ በራስኮሊንኮቭ ድምዳሜ፣ ሰዎች በሁለት አበይት ጎራ ይከፈላሉ፡- ቆንጆዎቹና አስቀያሚዎቹ። ራስኮሊንኮቭ የሚያንፀባርቀው ባህርይና በድርጊቱ ራሱን ካስቀያሚዎቹም ሆነ ከቆንጆዎቹ ወገን መመደብ ስለተሳነው “I am an Aesthetic Louse” (ሥነ-ውበታዊ ቅማል ነኝ) በሚል አደናጋሪ ብያኔ ያልፈዋል። ቅማልን ተባይ ሆነው ካላይዋት ሥነ-ውበት ውስጥ ምን ከተታት? ያሰኛል።
የሰው ልጅ ነኝና የማይገናኙ ጎራዎችን በማጣረስ መፅናኛዎቻችንን እናፈላልጋለን!! ያጣነውን እንዳላጣን፣ ያላገኘነውን እንዳገኘን የሚያስመስል ቅዠት ውስጥ መዘፈቃችን ከዚህ ሳይመነጭ አይቀርም። ውጫዊውን፣ ውስጣዊ፣ ውሥጣዊውን ውጫዊ የሚያስመስል ማደናገሪያ ውስጥ እንዘፈቃለን። እንደሚታወቀው ሥነ-ውበትና ስነ-ምግባር ሁለት መወዳደሪያ ዘርፎች እንጂ የሚዛነቁ እንዳልሆነ ልቦናችን አውቆ ንቋቸዋል። እውነታ ሳይሆን መፅናኛችን በልጦብናል…


… የማዛነቅ አባዜአችን በሥነ-ውበትና በስነ-ምግባር ብቻ አያቆምም። በሀብትና በጤና ላይ እንዲሁ ሌላ የመፅናኛ ማጣረሻ ፈጥረናል። ችግር ለጸናበት የጤናን ረብጣ እንደገንዘብ ማስቆጠር ከመፅናኛነት ያለፈ ፋይዳው ምን ይሆን? ጤነኛ ሆኖ ሀብታምነት አይገኝም? ሀብታ ሆኖ  ጤነኝነት አይታሰብም? ሁለቱ ተቃራኒዎች ናቸው? ከሀብትና ከጤና ምረጥ ማለትስ የጤና ነው? “ቸገረኝ” ያለ ሰው ሰብስቦ ስለዓይን መጥፋት፣ ስለእግር መሰናከል እየዘረዘሩ በገንዘብ መተመን መልስ ይሆናል?
መፅናኛዎቻችን ፈር ለቀዋል። Dale Carnegie የተባውን የስነ-ልቡና ባለሙያ ጠቅሶ “እግር የሌለው እስካይ ድረስ ጫማ ስለሌለኝ እከፋ ነበር” ብሎ መስበክ የጤና ይመስላችኋል? ጫማ እና እግር ምን አገናኛቸው? የጫማ አለመኖርን እግር የሌለው ማየት ያፅናናል? ጫማም እግርም ሊኖረን አይገባም? እግር የሰጠው ሰው ጫማ መግዛት አለመቻሉ እራሱን የቻለ አሳፋሪ ነገር አይደለም? ጫማ መግዛት የተሳነን ደካሞች እንዴት እግር በሌለው እንድንፅናና እንገፋፋለን?
… ያኔ በዚያ ሰሞን ነው፤ አንድ አዳራሽ ውስጥ መጽናኛ በመሻት ለተሰበሰቡ የቀረበ ማሳሰቢያ በቴሌቪዥን ሲተላለፍ አይቻለሁ። የሳንባችን  ረቂቅነት እንዲያስገርመን ሆኖ ይተነተናል፤ የልባችን አሰራር፣ የመተንፈስ መቻላችን ፀጋ፣ እግር እና እጅ እንዴት እንደሚታዘዙልን… ሌላው ቀርቶ የተጎዳ አካላችን ላይ ህመም የመሰማቱ ትሩፋት ይተነተናል… ዋናው ጉዳይ በተፈጥሯችን ከመደመም አልፈን ለችግሮቻችን መጽናኛ አድርገን መቁጥር ተገቢነት አለው? ተሟልቶ በረቂቅ መፈጠርና የኑሮ መጓደል የተለያዩ ነገሮች አይደሉም? ኑሯቸው የተሟላ ረቂቅ አፈጣጠራቸው ተጓድሏል? የዚህ ዘመን የኑሮ ጥያቄ፤ የሰው አፈጣጠሩን ረቂቅነት በመተንተንና በማሳወቅ  እንመልሰዋለን?...


… በረቂቅ መፈጠር፣ ኑሮን ከማቅለልና በህይወት ከመደሰት ያለፈ ፋይደ ይኖረዋል? ለመሆኑ የጤና መሟላት ለዚህ ዓለም የኑሮ ስርዓት ምኑ ነው? “ጤና ገበያ ነው” ማለት ሰርቶ ከመክበር ያለፈ እንቁልልጮ የሚሉበት ትርጉም አለው? በአፈጣጠር መርቀቅ ለየትኛው የገንዘብ ተቋም በመያዣነት  ይቀርባል? ተፈጥሮንና ፈጣሪን ከማመስገኛ ሰበብነት ያለፈ ፋይዳ ይኖረዋል?
… ስብሃት ገብረእግዚአብሔር “አመስግን” የሚለው የጤናንና ያልተሳከረ የተፈጥሮ ህግን ምክኛት አድርጎ ነው። “ጠዋት ስትነሳ አመስግን፣ ምክንያቱም ላትነሳ ትችል ነበርና… በመንጠራራትህም አመስግን፤ ከመንጠራራት የሚገኘው ደስታ ሊያመልጥህ ይችል ነበርና… ቁርስህን ስላገኘህ አመስግን፣ ላታገኝ ትችል ነበርና… የመብላት ፍላጎትህ ስላልተዘጋ አመስግን፣ ምግቡ ኖሮት ፍላጎቱ የተዘጋ ብዙ አለና… ፀሐይን ስትሞቃት አመስግን፣ በጤና እክል ጸሐይን ሳያገኝ ያልጋ ቁራኛ ሆኖ የቆየ ሞልቷልና”
ከዚህ ባለፈ መጽናኛዎቻችን ፈር ለቀዋል። መልስ ባልሆኑ መልሶች ተወረናል። የሀብት ጉዳይ ስናነሳ እጅ እግር ማስቆጠር ቋሚ ሆነ። አላቂ ካፒታል አይሆንም። “ጎመን በጤና”ን አስተምህሮ አድርጎ የሚቀርብ ከጎመን የተሻለ ድርሻህን ለመንጠቅ ያቆበቆበ ብቻ መሆኑ መታወቅ አለበት። ከጎመን የተሻለ ምግብና ጤና አንድ ላይ ሊገኙ የሚችሉ የተለያዩ ነገሮች እንደሆኑ አይገባን ይሆን?...
…አንዳንዴ እንዲህ ይታሰባል።
***
ከአዘጋጁ፡- ጋዜጠኛ ደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ ከአሥር በላይ መጻህፍትን ለህትመት ያበቃ የብዕር ሰው ሲሆን፤ የሚበዙት የህትመት ውጤቶቹ የፈጠራ ሥራዎች ናቸው - ልብወለዶች፡፡ የጋዜጠኝነት ልምድና ተሞክሮ ያካበተው አለማየሁ ገላጋይ፤በሥነጽሁፍ ሃያሲነቱም በእጅጉ ይታወቃል፡፡ ማህበራዊ ሃያሲም ነው፡፡

Read 774 times