Saturday, 11 May 2024 00:00

የተሻለ ይገባታል

Written by 
Rate this item
(1 Vote)

    ለአንዲት ሀገር ሁለንተናዊና የተሟላ እድገት አስተማማኝነት፣ የስርአተ ጾታ እኩልነትን ማስፈንና በተለይም የህብረተሰብና የሀገር ተፈጥሮአዊ የህልውና መሰረት የሆኑትን ሴቶች ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት በማያወላዳ መልኩ ማረጋገጥ ለጥያቄ የማይቀርብ ቁልፍ ጉዳይ ነው፡፡
በከተማችን ባለፉት ተከታታይ የለውጥ አመታት ለትውልድ የሚተላለፉ ትላልቅና ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በአጭር ጊዜ በመጨረስና ለህዝብ የገባውን ቃል በተግባር በማሳየት አንጸባራቂ ውጤቶችን ያስመዘገበው መንግስትም፤ የሴቶችን ጾታዊ ጥቃት ለመከላከልና ሁለንተናዊ ተሳትፎዋቸውንና ተጠቃሚነታቸውን ለማረጋገጥ የህግ ማዕቀፎችን ከማዘጋጀት ባለፈ አስተማማኝነቱ ሊረጋገጥ የሚችለው የተጋላጭነታቸውን ምንጭ በማድረቅና አስፈላጊውን ስራዎች በመስራት ላይ መሆኑን በተግባር ለማሳየት ቆርጦ በመነሳት፣ በከተማችን አዲስ አበባ ደቡባዊ አቅጣጫ፣ አቃቂ ቃሊቲ ክፍለከተማ በሀገራችን በአይነቱ የመጀመሪያው ፈርቀዳጅ የሆነ የሴቶች የተሀድሶና የክህሎት ማበልጸጊያ ማዕከል በከፍተኛ ጥራት ገንብቶ በማጠናቀቅ ሌላኛውን ታሪካዊ አሻራ አኑሯል፡፡


ይህ ማእከል በአንድ ዙር በሺዎች የሚቆጠሩ የጾታዊ ጥቃት ሰለባ የሆኑ እና ለማህበራዊ ቀውስ የተጋለጡ ሴቶችን ያለአንዳች ቅድመ ሁኔታ ተቀብሎ ምግብ፤ መኝታና አልባሳትን ጨምሮ ሌሎች ሁሉን አቀፍ መሰረታዊ ፍላጎቶችን አቅርቦ ከሶስት እስከ ስድስት ወራት የሚቆይ ሞያዊና ስነ-ልቦናዊ ድጋፍና ስልጠናዎችን በመስጠት ስርነቀል ለውጥ ለማምጣት ጉልህ አስተዋጽኦ አለው፡፡ ማእከሉ በውስጡ ከሚሰጣቸው አገልግሎቶች መካከል የስነ-ውበት ፤የሞግዚትነት ወይም የህጻናት ክብካቤ ፤የመስተንግዶ፤የአሌክትሪክና የሸክላ የእንጨት ስራዎች፤እንዲሁም የጋርመንት ስልጠና እና ሌሎች ዘርፈብዙ አገልግሎቶችን አካቷል፡፡ የግንባታ ጥራቱም እልፍ ሴቶችን ከአስከፊው የወሲብ ንግድ ወይም ከጨለማ ህይወት አርነት በማውጣት የአዲስ ብሩህ ተስፋ ህይወት ብርሃን እንደሚያጎናጽፍ ብሎም ለከተማችን ብቻ ሳይሆን ለክልል መስተዳድር እህት ከተሞችም አንድ ምእራፍ ወደፊት የሚያሻግር ተግባራዊ ትምህርት እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡


ይህ ማዕከል በክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ሀሳብ አመንጪነት የብዙሀን ሴቶች መኖሪያ በሆነችው መዲናችን በተገቢው መንገድ ራሳቸውንና ቤተሰባቸውን መጥቀም ያልቻሉ
ከዚህም ባለፈ ለዘርፈ ብዙ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች የተጋለጡ መሆናቸውን በማስተዋል፣ ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታት የረጅም ጊዜ ጥናት እንዲደረግበት አቅጣጫ በማስቀመጥና ለዘርፉ ምሁራኖች የተለያዩ ገንቢ ሀሳቦችን በማቅረብ ግንባታው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ድረስ በመከታተል አላማውን ለማሳካት በሚያስችል መልከአ ምድራዊ አቀማመጥና ምቹ የአየር ንብረት ላይ እንዲገነባ ከፍተኛ ሚና ተጫውተዋል፡፡ ይህ ፕሮጀክት በተለይም ክብርት ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ፣ የህብረተሰቡን ችግር በዘላቂነት ለመፍታት ሀሳቡን ከማመንጨት አንስቶ እስከ ማገባደጃው ባለው ሂደት በልዩ አይን ክትትል በማድረግ በ11 ወራት እንዲጠናቀቅ ያላሰለሰ ድጋፍና ክትትል በማድረግ፣ ችግር ፈቺ ሀሳብ የማፍለቅና ፕሮጀክቶችን የማስፈጸም አቅማቸውን በተግባር ያሳዩበት ነው፡፡ማእከሉ በውስጡ የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ የየራሳቸው ኪነ-ህንጻዊ ውበት እንዲሁም የስፋትና የከፍታ ደረጃ ያላቸው ህንጻዎችን የያዘ፤ ዘመናዊ የስፖርት ማዘውተሪያ ሜዳዎችን፤ግዙፍ ኤልኢዲ ስክሪን የተገጠመለት የመዝናኛ አምፊ ቴአትር፤ የአትክልት እርሻ ማሳን ብሎም ከፍተኛ መጠን ያለው ንጹህ ውሃ የሚያቀርብ የራሱ የከርሰ ምድር ውሃ ጉድጓድ ከነ ግዙፍ ታንከሩ የያዘ ነው፡፡


ይህ ማዕከል የስርአተ ጾታ እኩልነትን ከማረጋገጥ እንዲሁም ለወደፊት አጠናክረን የምንከተለውን የፖለቲካ አቅጣጫ ከማመላከት አኳያ በመዲናችንም ሆነ በሀገራችን የመጀመሪያው ቢሆንም ተጨባጭ ውጤትና ስር ነቀል ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ ለውጦችን እንደሚያመጣ ጅማሬው ያመላክታል፡፡ በመሆኑም ከዚህ ተቋም የሚገኘው ተሞክሮ ተቀምሮና ሰፍቶ በአጭር ጊዜ ውስጥ በእህት ክልል መስተዳድር ከተሞችና በአጎራባች ሀገራት
ትምህርት የሚወሰድበት ተምሳሌት ፕሮጀክት እንደሚሆን አያጠራጥርም፡

Read 801 times