Sunday, 26 May 2024 00:00

ሦስት

Written by  ሌሊሳ ግርማ
Rate this item
(5 votes)

“ወደፊት ሳገባ” የሚለውን ሀረግ የሚጠቀምን ሰው፣ ሦስቱም እህትማማቾች አያምኑትም ነበር፡፡ በተለይ ያኔ ልጆች እያሉ፡፡ ከሃያ ወይንም ከሃያ ሁለት አመታት በፊት ገደማ፡፡ ያኔ አይገባቸውም ነበር፡፡
 እናትና አባታቸው ተቸግረው እንጂ ወደው የተጋቡ አይመስሏቸውም ነበር፡፡ እነሱን ስለወለዱ እንጂ ባይወልዱ ኖሮ ቻው እንኳን ሳይባባሉ ጀርባቸውን አዙረው፣ ሁለተኛ ደግመው በማይገኛኙበት አቅጣጫ የሚለያዩ ነበር የሚመስላቸው፡፡ ደግሞም ሊሆን ይችላል፡፡ አላማ ከሌለ አላሚው ምን ያደርጋል?
በእድሜ ከፍ እያሉ ሲሄዱ ነገሩ እየገባቸው መጣ፡፡ እየገባቸው መጣ ማለት ግን ተቀበሉት ማለት አይደለም፡፡ ሰው ዞረም ቀረ መሞት እንደማይቀርለት እንደ መቀበል፡፡ ግን አብዛኛው ዘመድ ነኝ ባይ… የእውነትም ይሁን በማስመሰል፣ መቀበል ተስኖት ቀብሮ ሲመለስ ያዙኝ ልቀቁኝ እያለ እየተነፋረቀ ነው፡፡ ግን እየተነፋረቀም ቢሆን ይገባዋል፡፡
እነሱም ከፍ ሲሉ እንደ ወላጆቻቸው ነው የሆኑት፡፡ በተለያየ አቅጣጫ ሄደው የተለያየ ስምና የመልክ ገፅታ ያላቸው ባሎች አገቡ፡፡ ልጆች አረቡ፡፡ የእነሱ ወላጆች ለምን እንደገቡበት የማይገባቸው ውል ውስጥ እነሱም በጊዜያቸው ገቡ፡፡ ከዛ ውጭ ሊሆን እንደማይችል በደመ ነብስ ታውቋቸዋል፡፡ ሳይገባቸው ማግባት፡፡ የሚመራቸው የሆነ ነገር ግን አለ፡፡ አንዳንዴ የሚመራቸው ማህበረሰቡ ይመስላቸዋል፡፡ ማህበረሰቡን ለማስደሰት፡፡ ሌላ ጊዜ ደግሞ ስሜት ይመስላቸዋል፡፡ ስሜትን ለማርካት፡፡ በደንብ አይገባቸውም፡፡ ሳይገባቸው አገቡ፡፡ በደመነብስ የሚያደርጉት ሁሉ ገብቷቸው ተቀብለውታል ማለት አይቻልም፡፡
ሦስት ሆነው በተዘጋ ቤት ውስጥ በልጀነታቸው ሲያድጉ፣ አንድ ይበቃቸው ነበር ብለው ያምኑ ነበር፡፡ አንደኛይቱ ትበቃ ነበር ብለው የሚስማሙት ደግሞ ሁለተኛይቱም ሦስተኛይቱም ናቸው፡፡
የመጀመሪያይቱ የበኩር ልጅ በመሆኔ ደርሶብኛል ብላ ለብቻዋ የምታመሰኳው፣ እንደ ብጉንጅ እንዳይፈርጥ ተጠንቅቃ የምታሻሸው የራሷ ህመም አላት፡፡ ከበታች እህቶቿ፣ ከወላጆቿም ጋር የማትጋራው የራሷ ህመም ነው፡፡ እንደ ልጅ ሳይሆን፣ እንደ ቤት ሰራተኛ፣ እንደ ሞግዚትም፣ እንደ እናትም ሆና ታናናሽ እህቶቿን እያሳደገች ማደጓ ይቆጫታል፡፡ መልሳ ወዲያው ደግሞ ደስ ይላታል፡፡ “ልጅነቴን ሳልቦርቅበት… ያለ ፍላጎቴ በቁም ነገር ውስጥ እንዳልፍ ተገድጃለሁ” ብላ ከቆዘመች በኋላ ድንገት ደግሞ ደስ ይላታል፡፡ ታናናሾቿ የሆኑትን ሁሉ ለመሆናቸው የእሷ እጅ እንዳለበት ስታስብ ያኮራታል፡፡ ባታሳድጋቸው ተወልደው ብቻ ሳያድጉ የሚቀሩ እስኪመስላት ድረስ፡፡
“አንደኛይቱ ትበቃ ነበር” ይላሉ ሁለቱ በእሷ እጅ ያደጉት፡፡ ሊሞግቷት ሲሞክሩ ሙሉ ለሙሉ የማትስማማው በዚህ ምክኒያት ነው፡፡ ሁለቱን ለማሳደግ የራሷ እድገት አምልጧታል፡፡ እንዴት ይኼ ሁሉ መስዋዕት ተከፍሎ “እኛ ባንወለድ ይሻል ነበር” ይሏታል?
 እሷ እያለች እንደሌለች ሆና ራሷን ማሳደጓን ባለማስተዋላቸው ስለሆነ ይቅር ትላቸዋለች፡፡ ወደፊት ይረዱታል ብላ ታስባለች፡፡
ደግሞም ከእውነቱ ያን ያህልም የራቀ ግምት አልነበረም የወሰዱት፡፡
 “እናንተን ስወልድ ነው ----- የተውኩት” የሚል አማርኛ ከወላጅ እናታቸውም አፍ ጠፍቶ አያውቅም፡፡ የኮሌጅ ትምህርቷ ሳይበጠስ ትንሽ ገዝግዛ የተወችው እነሱን በመውለዷ ምክኒያት ነው፡፡ ለእነሱ ቅድሚያ በመስጠቷ ነው መቅደም የነበረበት ያመለጣት፡፡ ፀጉሯ የሳሳው፣ መልኳ የጠፋው እነሱን በመውለዷ ነው፡፡ ከማግባቷ በፊት ትመስል የነበረችዋን ኮረዳ አጥፍተው ይህችኛዋን በፋንታዋ የተኩት ሦስቱ ናቸው፡፡ ብላ ታምናለች፡፡
ባሏን ግን አንድም ቀን ልጆቿን በምትወነጅልበት ክስ ከሳው አታውቅም፡፡ እሱ ለእሷ እንደ መማጠኛዋ ነው፡፡ድሮ የነበረችውንና በኋላ የሆነችውን የሚያውቅ እሱ ብቻ ነበር፡፡ አንድ ላይ ነው የሆኑትን አብረው የሆኑት፡፡ አንድ ላይ ነው የተለወጡት፡፡  ባሏ የተለወጠው በመልክ ገፅታ ሳይሆን በስነ ልቦና ነው፡፡ የሆነ የወለቀ እቃ ወይንም የተነቃነቀ እንዳለው እሱም ያስታውቃል፡፡ የወለቀውን ለማግኘት እንደማይችል ደግሞ ብዙ ሞክሮ እንዳወቀ፡፡ አንድ ላይ ነው አባትና እናት የተለወጡት፤ በአንድ አይነት መዘዝ፡፡ የገቡበት መዘዝ በቁጥር ሶስት ናቸው፡፡
ወላጆቻቸው የተዋወቁበትን ቀን አይረሱም፡፡ ልጆች ከወለዱ በኋላ የተዋወቁበትን ቀን ሲያስታውሱ መልካቸው ትንሽ ይለወጣል፡፡ ፈካ ይላል፡፡ አይናቸው የዋህ ለዘብታ ያመጣል፡፡ ያስታውሱታል፡፡ ማስታወስ እንዳይቀጥሉ የሚያደርጓቸው ሶስቱ ናቸው፡፡ የተዋወቁበት ቀን ወደምን እንዳመራቸው ግን ማሰብ አይፈልጉም፡፡
ልጆቹ አድገው ቢወጡላቸው ተመልሰው ፍቅራቸውን በብሄረ ፅጌና በአምባሳደር ሲኒማ ቤት የሚቀጥሉ ይመስላቸዋል፡፡ ወይንም እንደሚመስላቸው ነው መስለው የሚቀርቡት፡፡ በሦስቱ ሴት ልጆቻቸው ፊት በተለይ፡፡
በልጆቻቸው ፊት ምኞታቸውን ይፋ አድርገው አይገልጡም፡፡ በአፍ ባይገለፅም ድርጊታቸው ግን ያሳብቃል፡፡ “አድርጌልሻለሁ” ብሎ የሚያምን ሰው ሁሌ ለአፀፌታ የሚሆን ማካካሻ ይፈልጋል፡፡ አንዳች ነገር ይጠብቃል፤ ምን እንደሚጠብቅ ግን እቅጩን አይገልፅም፡፡
ሦስቱም የሚጠበቅባቸው ነገር እንዳለ ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡ የሚጠበቅባቸው ነገር ከሁለቱ ወላጆቻቸው በኩል እንደ አንፃሩ የተለያየ ነበር፡፡ ሦስቱ ሴቶች በትምህርታቸው ጥሩ ውጤት የሚያመጡት ለአባታቸው ይመስላቸው ነበር ድሮ ልጆች ሳሉ፡፡ ነገሩ ሳይገባቸው በፊት፡፡ የሚላላኩት፣ የቤትን ስራና ባልትና ላይ የሚጠመዱት ደግሞ ለእናታቸው ይመስላቸው ነበር፤ ለባላቸው እንደሆነ አያውቁም፡፡ ሁለተኛይቱ እና ሦስተኛይቱ ለመጀመሪያይቱ ታላቅ እህታቸው የሚከፍሉት ካሳ ነበራቸው፡፡”አድርጌላቸዋለሁ” ብላ ስለምታምን፣ እነሱንም ስላሳመነቻቸው ካሳ መክፈላቸውን ያለ ምንም ቅሬታ ተቀብለዋል፡፡ ለታላቅ እህታቸው የሚከፍሉት ማካካሻ  ልክ እንደ እናታቸው መላላክን በመደበኛነት ይዞ፣ ምክርና ተግሳፅን መስማትን ይጨምራል፡፡ የመጀመሪያይቱ የቁጣና የተግሳፅ ክፍልን በጥሩ ሁኔታ ጠበቅ አድርጋ ስለያዘችው፣ እናታቸው የመበሳጨትና የመቆጣትን ሃላፊነት ሙሉ በሙሉ ከራሷ አውርዳለች፡፡ ያወረደችው ሁሉ የሚጫነው የመጀመሪያይቱ ላይ ነው፡፡
የመጀመሪያይቱ በራሷ የእድገት ጊዜ ከልጅነት ወደ አክስትነት ተዛውራ ተገኘች፡፡ የእናታቸው ታናሽ እህት ነገር ሆነች፡፡ አንዳንዴ ታላቅ እህትም ትሆናለች፡፡ በተለይ ወደ መጨረሻ አሳድጋ ልትጨርስ አካባቢ፡፡ ራሷን ወደ መቻል እና ስራ ይዛ ወደ መውጣት ስትደርስ፡፡ ያን ሰሞን የሁሉም ታላቅ መሆን ጀምራ ነበር፡፡ የአባቷም ጭምር፡፡ ልክ እንደታናሽ እህቶቿ ወላጆቿንም የማይገባ ነገር አድርገው ስትደርስባቸው አስቀምጣ ትገስፃቸዋለች፡፡ እነሱም ወደ ብሄረ ፅጌና ወደ አምባሳደር ሲኒማ መመለሻ ጊዜያቸው እንደደረሰ ስላወቁ ላላ ማለት ጀምረው ነበር፡፡ ወደ ድሮው ልጅነታቸው መመለስ ፈልገዋል፡፡ ሳናስበው አጥተነዋል ብለው ወደሚያስቡት፡፡
አንዳንድ ጊዜ አንድ ላይ ወጥተው ጥንብዝ ብለው ሰክረው ይመለሳሉ፡፡ ስካራቸው እስኪበርድ ልጆች እንደ ልጆች ከመሆን ውጭ አማራጭ የላቸውም፡፡ ያስፈሩዋቸዋልና፡፡ ጓዳ ገብተው ይደበቃሉ፡፡ በዛ ከፍታ ላይ ሲሆኑ ባልና ሚስትየው ራሳቸው ብቻ እርስ በእርስ ይጣላሉ፡፡
የመጀመሪያይቱ ልጅ ስሟ ቤሎ ነው፡፡ ሁለተኛይቱ ብሩሂት፡፡ ሶስተኛይቱ ሚራዌል፡፡ የአባታቸው እና የእናታቸው ስም ለጊዜው አያስፈልግም፡፡ በአቶ እና በወይዘሮ የታፈረ ማዕረግ አላቸው፡፡ “በእርሶ” ማካበሪያ የህይወት ቆይታቸው እውቅና ይሰጠዋል፡፡
ቤሎ ልታገባ መሆኗን ስትነግራቸው ሁለቱ እህቶቿ አላመኑም ነበር፡፡ ማመናቸው እንኳን ዞሮ ዞሮ አልቀረም፡፡ መቀበል ግን አልቻሉም፡፡ በልጅነታቸው የተማማሉበትን ፅላት የካደች መሰላቸው፡፡ “ፍቅር ይዞኛል” አለቻቸው፡፡ ይሄ ግን የሁሉንም ቅሬታን የሚሽር መልስ ነበር፡፡ ሁሉም ሴቶች በልባቸው የሚመኙት ነገር ነውና፡፡
ከዛ በኋላ ሁሉም ነገር ፈጠነ፡፡ ወላጆቻቸውም የልጆች ቀንበር ሲነሳላቸው የእድሜ ቀንበር በፋንታው ተተካ፡፡ ወገቤን፣ ፕሮስቴቴን፣ ዲያሌሲሴን ማለት ጀመሩ፡፡ የሚሸከሙት ልጅ ባይኖራቸውም ራሳቸውን ተሸክመው መቆም መከራ ሆነባቸው፡፡ የልጆቻቸው ድጋፍ ወዲያው ከጫንቃቸው ላይ እንደተነሳላቸው መልሶ አስፈለጋቸው፡፡ እንደ ቀንበር ሳይሆን እንደ ምርኩዝ፡፡
እየተፈራረቁ መታመም ጀመሩ፡፡ እየተተራረፉ አልጋ መያዝ፡፡ የማያውቁት አለም ውስጥ ራሳቸውን ድንገት ያገኙ ይመስል አፋቸውን ገርበብ አድርገው በረንዳ ላይ እግራቸውን ፀሐይ እያሞቁ ይጠብቃሉ፡፡ የሚጠብቁት ወጣትነታቸውን አለመሆኑ ግልፅ ነው፡፡
ቀደም ሲል “ወጣትነታችንን የነጠቁን” ብለው በድብቅ ይቆጩባቸው የነበሩትን ሦስቱን ሴቶች “መቼ መጥተው ይጠይቁን ይሆን” እያሉ ደጅ ደጁን መማተር ሞያ አደረጉት፡፡ የአመት በዐል ቀንን ጓጉተው የሚጠብቁት ለምግብ እና ለመጠጡ ሳይሆን ሦስት ሴት ልጆቻቸው ከእነ ባሎቻቸው እና ከነ ልጅ ልጆቻቸው ይመጣሉ ብለው ስለሚጓጉ ነው፡፡ ደግሞም አሳፍረዋቸው አያውቁም፡፡ ሁሌ ይመጣሉ፡፡ የተኩዋቸውንም ይዘው ይመጣሉ፡፡ ሦስተኛውን ትውልድ፡፡ አሁን ሦስቱ ሴት ልጆች ሦስት እናቶችን መስለዋል፡፡ ሆነዋል፡፡ እንደ ቅደም ተከተላቸው ወልደዋል፡፡ የወለዷቸውም በቅደም ተከተል እያደጉ ነው፡፡
ልጆቻቸውን የሚያሳድጉበት መንገድ እነሱ ካደጉበት ትንሽ ይለያል፡፡ ትንሽ ነፃነት ይሰጧቸዋል፡፡ ፀፀት እና “የአድርጌልሻለሁ” የባለ እዳነት መንፈስ በልጆቻቸው ላይ አልጫኑባቸውም፡፡ ፍቅራቸውም ወደ ባላቸው ከመሆን ይልቅ ወደ ልጆቻቸው ያዘነብላል፡፡ ሁሉን ነገር አራግፈው ሰጥተዋቸውም ያጎደሉባቸው ነው የሚመስላቸው፡፡ ይሳሱላቸዋል፡፡
የሦስቱ እህትማማቾች ልጆች ግን ልጅ ሆነው ነው ያደጉት፡፡ ሃላፊነት አልተሸከሙም፡፡ ግን ነፃነትም ቀንበር ነው፡፡  ነፃነት ቀንበር ሳይሆን ቀንበር መስበሪያ ነው ብለው ነበር እንዲሸከሙት የፈቀዱላቸው፡፡ እነሱ እንደሆኑት እንዳይሆኑ፡፡ እንደ ስስ ፒጃማ፣ እንደ ናይለን ጨርቅ ቀላል ነገር ብቻ እንዲጫናቸው ነበር ፍላጎታቸው፡፡ ማንኛውም አይነት ክብደት እንዳጫንባቸው… እያሟለጨ እንዲያስመልጣቸው የነፃነትን ቅባት ቀቡዋቸው፡፡ ግን ቅባቱ እንደ ጭቃ ማጥ ሆኖ አፈናቸው፡፡
ሦስተኛ ትውልድ የሆኑት የሦስቱ ሴቶች ልጆች በራሳቸው ኩራት ተከለሉ፡፡ የራሳቸውን ፍላጎት፣ የራሳቸውን እምነት፣ የራሳቸውን አቅጣጫ እንጂ የማንንም የሌላ እንዳያዩ ሆነው አይናቸው ታወረ፡፡ በራሳቸው አምሳል የተሰራ ጣዖት ቀርፀው ለቀረፁት ምስል ሰገዱ፡፡ ለሰገዱለት ደግሞ ተገዙ፡፡
ነፍሳቸው እስክትወጣ የደደዱዋቸው እናቶቻቸውን ወነጀሉ፡፡ የተወነጀሉት እናቶች ደግሞ የብልሹ ልጆቻቸውን አያቶች፣ የራሳቸውን አሳዳጊ ወላጆች ጊዜው ከዘገየ በኋላ አከበሩ፡፡ ያለፈ ነገርን ለማክበር ይቀላል፡፡ የሚከበረው ነገር ከትዝታ ማህደር ራቅ ብሎ የሚጨለፍ እና የቁጭት ሃሳብን ያዘለ ሲሆን ከመከበርም አልፎ መመለክ ይጀምራል፡፡
ሦስቱ እናቶች ሞተው ለተቀበሩት ወላጆቻቸው ሐውልት አቆሙ፡፡ ጠዋት እና ማታ ሳይሳለሙት የማይውሉ የምንነታቸው መወከያ ሆነ፡፡ መነሻችን እነሱ ናቸው አሉ፡፡ ልጆቻቸውን መውደድ አላቆሙም፡፡ ሊያቆሙም አይችሉም፡
ወላጆቻቸው እነሱን ያሳደጉበትን ድባብ ጠልተው ስለነበር ተቃራኒውን አስተዳደግ ለልጆቻቸው መረጡ፡፡ ልጆቻቸው በተሰጣቸው ነፃነት የራሳቸውን እጣ ፈንታ መረጡ፡፡ እርስ በራስም ተቀራርበው ስለማይግባቡ በራሳቸው ወደፊት ላይ አቋም ወሰዱ፡፡ በፍፁም እንደማያገቡ፤ በፍፁም ልጅ የሚባልም እንደማይወልዱ፡፡
ለነገሩ ሁሉም እንደዛ ይሉ ነበር፡፡ መጨረሻ የሚሆነው ግን ያው ነው፡፡ ቢያንስ መፍታት ስለሚፈልጉ መጀመሪያ ማግባት የግድ ይኖርባቸዋል፡፡


Read 528 times