Monday, 01 July 2024 09:34

ካርማ

Written by  በኪሩቤል ሳሙኤል
Rate this item
(2 votes)

 ፓስተር ትዝታህ  አይኖቹ ተገለጡ፡፡ የጥፍንግ ታስሯል፡፡ ሙሉ ሱፉን እንደለበሰ ነው የታሰረው፡፡ የት እንዳለ ለማወቅ አልቻለም፡፡ አንድ ጨለማ ክፍል ውስጥ ሁለት ወንበሮች ናቸው ያሉት…አንዱ ላይ ነው ታስሮ የተቀመጠው፡፡ ፍርሀት የመጀመሪያውን መስተንግዶ አደረገለት፡፡ በጣም ፈራ፡፡ በምንና እንዴት አድርጎ እዚህ እንደደረሰ  ሊረዳ አልቻለም፡፡ ከጥቂት ሰዓታት በፊት በትልቅ መድረክ ላይ ቆሞ በሰይጣናት የታሰሩትን ነፍሶች ነፃ የማውጣት ስራ ላይ ነበር… አሁን እሱ ራሱ ታስሮ ምን እንደሚያደርግ ግራ ገብቶት ተቀምጧል፡፡ ከሰዓታት በፊት በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመናን  የሱፉን ገላ ለመዳሰስ እርስ በርሳቸው  እየተደራረቡ እሱ ጋ ለመድረስ ሲጋጋጡ፣ ፈገግ ብሎ እያያቸው ነበር…አሁን ግን ብቻውን በርባሮስ ጨለማ ውስጥ ግር ያሉት አይኖቹን ማረፊያ እየፈለገላቸው ተጠፍንጎ ተቀምጧል፡፡
ተጣራ…
“ማነው ያሰረኝ፡፡ እባካችሁን ያለኝን እሰጣለሁ፡፡ በጌታ ስም እለምናችኋለሁ…ቃሌን አላጥፍም፡፡ ያላችሁኝን አደርጋለሁ…”
ጨለማው አንደበት የለውም፡፡ ህይወትን እየተነፈሰ ቢመስለውም የሞት ጥፍሮች የአፍንጫውን ቀዳዶች እየሞነጫጨሩ ባፍንጫው በኩል ሲወጡ ይታወቀዋል፡፡ የመታሰሩን ነገር ትርጉም አጣበት፡፡ ምድር ላይ ስልሳ አመት እስኪሞላው ድረስ ተሸክሞት የመጣው ህይወት፣ በሚያመልከው ፈጣሪው ምክንያት ስርዓቱን ጠብቆ፣ አሁን ለሚሰማው ቅድስና እንዳደረሰው አምኗል፡፡   
የጭንቅ ሰዓት ጎትቶ የሚያመጣውን የትዝታ ጋሪ ተሳፍሮ ወደ ኋላው ነጎደ…፡፡ ከዚህ ቀደም ሰርቶት የነበረ አስከፊ ሀጥያትን ፍለጋ፣ አይኖቹን ጨፍኖ ወደ ኋላው ተወነጨፈ፡፡ ሆኖም ፓስተር ትዝታህ እንዲሁ ከራሱ ጋር በፍቅር ተደፍቆ የተጠመቀ ነውና፣ ጭንቅላቱ ከሰራው ሀጥያት ይልቅ አግዝፎ የሚያሳየው የፅድቅ ስራዎቹን ብቻ ነው፡፡ በትዝታው ውስጥ ዘልቆ ገብቶ አንዳች ስህተት ህይወቱ ውስጥ አለማግኘቱ በጣም ደነቀው፡፡ ምናልባትም ለመጀመሪያ ጊዜ ሊሆን ይችላል፤ የኋላ ታሪኮቹን ማሰላሰል የጀመረው፡፡ ረስቶት ነበር…፤ የምዕመኑ ጩኸት፣ ለቅሶና፣ ደስታ ከራሱ ጋር ለይቶት ብዙ አድርጎት ነበር፡፡ ስለ ሁሉም ሰዎች ምንነት እያሰላሰለ መዋሉ፣ የራሱን ምንነትና ነበርነት እንዲረሳው አድርጎታል፡፡ ይህም የሆነው በፈጣሪው ጥበብና የመመረጥ ቅባት የተነሳ እንደሆነ አድርጎ  ነው የሚያስበው፡፡
አሁንም ተጣራ….
“አረ እባካችሁ…ቢያንስ ከፊቴ ቀርባችሁ አናግሩኝ፡፡ በጌታ የሆንኩ ሰው ነኝ፡፡ ሀጥያት አትግቡ ልጆቼ፡፡ ብትፈቅዱ ቀርባችሁ ሀሳባችሁን ንገሩኝ….”
ጨለማው ድምፁን ስልቅጥ አድርጎ ወደ ፀጥታ ፉጨትነት ይቀይርበታል፡፡ ማንም እየሰማው እንዳልሆነ ጠረጠረ፡፡ ብቻውን እንደሆነ ገብቶት በሀይል ራሱን ከወንበሩ ላይ ለማላቀቅ ታገለ፡፡ ወንበሩ ከመሬቱ ጋር የተበየደ መሆኑን አወቀ፡፡ የታሰረበትም አስተሳሰር እጅግ ውስብስብ ስለነበር ጣቶቹን እንኳን እንደልቡ ማንቀሳቀስ አልቻለም፡፡
ድንገት ከፊቱ ያለው ግድግዳ ላይ መብራት በርቶ፣ ብርሀኑ በግድግዳው ላይ ተለጥፎ ያለውን የክርስቶስ ምስል ያሳየው ጀመር፡፡ ፓስተሩ ልቡ ጥላው ልትበር መሰለው፡፡ ራሱ ክርስቶስ ከፊቱ የመጣለት ነበር የመሰለው፡፡ ማንም የሌለበት ክፍል ውስጥ ክርስቶስ ራሱ ካልሆነ ማንም ይህን ምስል ከፊቱ እንደማያቀርብለት አምኗል፡፡ ለረዥም ደቂቃ ምስሉ ላይ አፈጠጠ፡፡ ትንሽ  እየቆየ በሄደ ቁጥር ግን ማን አብስሎ እንደሰደደው የማይታወቅ ትኩስ እንባ በጉንጩ ላይ መውረድ ጀመረ፡፡ እያለቀሰ እንደሆነ  ያወቀው ቆይቶ ነው፡፡ ምስሉን መሸከም ያቃተው ህሊናው፣ ሊሸሽ የፈለገው ከምስሉ ይሁን ከራሱ በግልፅ አላወቀም፡፡
እንደዛው እንደተቀመጠ፡፡ እንደዛው የኢየሱስ ምስል አይኖች እንዳፈጠጡበት፤ እዛው ያለበት ቦታ ላይ እንዳለ ሁለት ቀናት አለፉ፡፡ ያለ ምግብ ያለ መጠጥ፡፡ ሰውነቱ ግን አልደከመም፡፡ አይኖቹም ካልደከማቸው በስተቀር ከክርስቶስ ላይ አልተነሱም ነበር፡፡ በነዚህ ሁለት ቀናት ውስጥ ደርሶ ያልተመለሰበት የሀሳብ መንደር የለም፡፡ ሆኖም አሁን ላይ ለሚያየው መከራ የሚያበቃ ሀጥያት ማድረጉን እስካሁን ጭንቅላቱ አስሶ አልደረሰበትም፡፡
በሩ ድንገት ተከፈተ፡፡  አይኖቹ በሩ ላይ እንደተተከሉ ለመጮህ ሞከረ….ድምፁ ግን በረዥም ዝምታ ምክንያት ተዘግቶበት ነበር፡፡ መጮህ ይፈልጋል እንጂ አይችልም፡፡ ለጊዜው ማየትና ማሰብ ብቻ ነው የሚችለው፡፡ ድንገት አንዲት ሴት መጥታ ከፊት ለፊቱ ተቀመጠች፡፡ ከዚህ በፊት አይቷት አያውቅም፡፡ ሰውነቱ ደክሟል፡፡ በመራብ ሳይሆን በሀሳብ ዝሏል፡፡
መናገር ግን ይችላል፡፡ “የኔ እህት…እባክሽን….” ከዚህ በላይ መሄድ አልቻለም፡፡ ዝም ብሎ ዝም ብላ የምታየውን ውብ ሴት ማየት ውስጥ ገባ…ረዥም ሰዓት አፍጥጣ አየችው፡፡ አይኖቹ ወደ የትም እንዳይሸሹ አድርጋ በአይኖቿ አጣብቃ ያዘቻቸው፡፡ ሁለቱም ፀጥታውን ተጠቀሙበት፡፡
ሩሀማ ከተቀመጠችበት በጥቂቱ ወደ ፓስተር ትዝታው ጠጋ ብላ ተቀመጠች፡፡ አተኩራው እያየችው የመጀመሪያዋን ንግግር አደረገች…
“ፓስተር ትዝታው…እንዴት ከረምክ?”
ፓስተር ትዝታው ከንግግር ይልቅ አንገቱን ከፍና ዝቅ አደረገላት፡፡
“ስሜቱ እንዴት ነው…? መናገር እየፈለጉ አለመናገር፣ መጮህ እየፈለጉ በፀጥታ ገመድ ጉሮሮ ሲታነቅ፣ መሮጥ እየፈለጉ ከርቀት መዳረሻን በአይን ብቻ እየናፈቁ መመልከት ውስጥ ብቻ ያለው ስሜት እንዴት ነው? ብዙ ማውራት እንደምትፈልግ አውቃለሁ…ሆኖም እስከዛሬ ያወራኸውንና ያደረከውን በፍርድ ሚዛን ላይ የምናይበት ሰዓት ላይ ደርሰናል፡፡ ስጠይቅህ ብቻ ነው የምትመልስልኝ….”
ፓስተሩ በእሺታ ራሱን ነቀነቀ፡፡
“ከዚህ በኋላ ለምትሰጣቸው መልሶች ተጠንቀቅ፡፡ እኔ ብቻ አይደለሁም የማዳምጥህ…እስከዛሬ ሲያዳምጥህና  የስራህን ውጤት ሲያጤንልህ የነበረው ፈጣሪህም አብሮኝ ስላለ፣ እሱም እንደሚሰማህ አውቀህ ነው መልስ የምትሰጠኝ፡፡ “
“የፈለግሺው ጠይቂኝ የኔ ልጅ….” ታግሎ ተናገረ፡፡
“የኔ ልጅ ነው ያልከኝ ….” የለበጣ ሳቅ ስቃ ወዲያው ደግሞ ሰይጣናትን በሚያርበደብድ ኩስትርና ተመለከተችው፡፡ መልኳን የሚተካ አስፈሪ ድምፅ ድንገት ማውጣት ጀመረች፡፡
“ለምን ፓስተር ሆንክ?”
ፓስተር ትዝታህ ያልጠበቀውን ጥያቄ ነው የመጣበት፤ ሆኖም በሞትና ህይወት ያለ ሰው እንኳን ጥያቄ ሌላንም መከራ ይወጣልና፣ በልቡ ፀልዮ መልስ መስጠቱን ጀመረ…፡፡
“በጌታ ተመርጬ ነው የኔ ልጅ፡፡ የአለም ፈራጅ የሆነው በጉ በራዕይ ታየኝ…ልጆቼን ሰብስብልኝ አለኝ፡፡ እኔም የፍቃዱን አደረኩኝ፡፡”
“የተበተኑት ልጆቹ እነማን ናቸው?”
“በሰይጣን ስራ የታሰሩትና በእርግማን የሚመላለሱት ናቸው፡፡ የጌታን ቃል ከልባቸው ፍቀው ያጠፉና መንገዳቸው የሞት የሆኑ ናቸው፡፡”
“አንተን ለምን የመረጠህ ይመስልሀል?”
“መንገዴን አገኘሁት የኔ ልጅ፡፡ የመለኮትን ሚስጥር ፍለጋ በጉብዝናዬ ዘመን ሁሉ ተመላለስኩ፡፡ እሱም አየኝ፡፡ መረጠኝ፡፡”
“እንግዲያውስ አሁን የመለስክልኝ መልስ ጀርባውን እንዳስረዳህ ነው፣ ፈጣሪ እኔን መርጦ ወዳንተ የላከኝ፡፡ መች እንደመረጠኝ ማወቅ ትችላለህ?”
“አሁን ላውቅ አልችልም ልጄ…እባክሽ አታስጨንቂኝ? ከዚህ ቀደም አይቼሽም አላውቅ፡፡ ምንም አይነት አደጋም በሰው ላይ የማደርስ ሰው አይደለሁም…”
“ዝም በል…!” በጩኸት አቋረጠችው፡፡ ደንግጦ ዝም አለ፡፡
“አንድ ታሪክ ልንገርህ…በጥሞና አድምጠኝ፡፡ አምላክህ ላንተ ይህን መልዕክት እንዳደርስልህ የመረጠኝ አንተ የካድከው ቀን ላይ ነው፡፡ ገና ሳልወለድ፡፡ ገና የሀጥያት ገፅህ መገለጥ የጀመረበት ደቂቃ ላይ እኔ ተመረጥኩ፡፡ ይሄን ታሪክ ስማ…
“በአንድ ገጠራማ አካባቢ ትኖር የነበረች አንዲት ምስኪን ሴት ነበረች፡፡ ለአባቷም ለእናቷም አንድ ብቻ የሆነች፡፡ ይህች ሴት ፈጣሪዋን አክባሪ፣ ሰጋጅ፣ ከምንም በላይ ፅድቅናዋን የምትሻ ምስኪን ሴት ነበረች፡፡ በሄደችበት ሁሉ የፈጣሪዋን ቃላት ማድመጥ እጅግ ነበር የሚያስደስታት፡፡ አንድ ቀን ላይ ግን እያደረገች ያለችውን  መለኮታዊ ጉዞ   የሚያስት ገዳፋ ሰዓት፣ ከአንድ መልከመልካም ወጣት ጋር ሆኖ ያለችበት መጣ፡፡
“የዛን ቀን ብቻዋን ነበረች፡፡ ቤተሰቦቿ ድግስ ተጠርተው ወጥተው ሳለ፣ ይህች ሴት ብቻዋን ከቀሳውስቱ ያደመጠችውን መዝሙር በስሱ እየዘመረች፣ በትካዜ ግልገል በጓን አቅፋ ተቀምጣለች፡፡ ይህ አሁን ያልኩህ ሰው በግራ እጁ አነስ ያለ ሰማያዊ መልክ ያለው መፅሐፍ ቅዱስ ይዞ ነበር፡፡ ተጠግቶ አናገራት፡፡ ልጅነትና ውበት አጥሮ ያስቀመጠው ማንነቷ፣ የሰማይ መላዕክትን ጨምሮ ያስደምም ነበር፡፡ ነበር…አስከፊ ቃል ነው አይደል?...እናም ይህ ሰው የዛን ቀን እጅግ በተመረጡ ቃላት ስለ መለኮት ሚስጥር፣ ስለ ክርስቶስ ጌትነትና ስለ ንስሀ ጥቅም አስረዳት፡፡
“በዛን ወቅት ላይ ይህች ምስኪን ፍጥረት የፈጠራት ራሱኑ በሰው አምሳል መጥቶ የተናገራት ያህል ሆኖ ተሰማት፡፡ በየደቂቃው የምትናፍቀውን የፈጣሪ ቃል፣ በተዋቡና ጉልበት ባላቸው ቃላት ልቧ ድረስ ዘልቆ ተረዳችው፡፡ በነዛ ደቂቃዎች ውስጥ ፈዛ ቀረች፡፡ ይህ ሰው የሚናገራትን በሙላ ለማድረግ ተስማማች…ከራሷ ጋር፡፡ ንስሀ መግባት እፈልጋለሁ አለች፡፡ ይህን ግን ያለችው ሚዛን የደፋ ሀጥያት ተሸክማ፣ የሰው አይን የማያሳይ ስህተት ሰርታና ፈጣሪዋን ስቶ ከሌላ የባዕድ እምነት ውስጥ የሚለጠፍ መንፍቃዊ ልብ ኖሯት አልነበረም፡፡ ንስሀ መግባት የፈለገችው የሰባኪዋን የቃላት ፍሰት ያመጣውን ጎርፍ፣ መቋቋም ስላልቻለች ብቻ ነው፡፡
“ንስሀ ሊያስገባት ከተራራ ላይ ይዟት ወጣ፡፡ ከተራራው አናት ላይ ሆና በጣፍጭ የልጅነት ከንፈሮቿ ሀጥያቷን ስትተርክለት፣ ሰባኪው ድምጿን በወንድ ስሜቱ ገርድፎ ጥሎት ከንፈሮቿን ብቻ አዳመጠባት፤ ለፈጣሪዋ ስስትና ናፍቆት ያዘሉት አይኖቿ፣ እንባ እያመረቱ፣ ፊቷን ሲያጠምቁት፣ ይህ ሰባኪ ግን ሀዘኗን ንቆ አይኖቿ ላይ ብቻ ድንኳኑን ጣለ፡፡ እየዳነች እንደሆነ ሲሰማት የምታደርገውን የሰውነት መወራጨት ተመልክቶ፣ ለአፍታ ያህል አላማውንና ፈጣሪውን እርግፍ አድርጎ ረሳ፡፡ ይህም በጭንቅላቱ ውስጥ ጥያቄ ሆኖ መቅረብ ሲኖርበት፣ ስሜቱን እንደተፈጥሮ መልስ አድርጎ ተረጎመው፡፡ በራሱ መንገድ መብት ብሎ የተረጎመውን የወንድነት ስሜቱን ሊወጣባት በላይዋ ላይ ሰፈረ፡፡ ደፈራት…፡፡ ደግማ እንደማታገኘው እያወቀ ደፈራት፤ የልጅነት እግሮቿ የትም ድረስ ሮጠው እንደማይደርሱበት እየተረዳ ደፈራት፤ ምስኪንነቷ የተጫነው ነፍሷ የትም ድረስ ቢሰቃይ እንደማይጮህ እያመነ ደፈራት…ደፈራት፡፡”
በእንባ የተቸመቸመው አይኑን መሬት ላይ ቀብሮ፣ ልብ ድረስ በሚደርስ ንግግር ሊያስቆማት ሞከረ…
“እባክሽ የምትይኝ ታሪክ አውቀዋለሁ…እባክሽ አቁሚው?”
“በእርግጥም እስካሁን ያወራሁትን በሙላ ታውቀው ይሆናል፡፡ ከዚህ በኋላ ግን የሆነውን ግዴታ ማወቅ አለብህና እወቅ….” አይኖቿ እየፈጠጡ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡ “እናም ይህች ምስኪን በደም የራሰው ቀሚሷን እንደያዘች ከቤተሰቦቿ ልትቀላቀል ብትሞክር፣ ዘማዊና አሰዳቢ ተብላ ተሰደደች…ይህች ምስኪን ሴት በቤተሰቦቿ የደማውን ልቧን ይዛ ዘመድ አዝማድ ጋር ብትመላለስ፣ ቀድመው አውቀው ነበርና ከደጃቸው ሳትደርስ ከውጭ በር ተዘጋባት… ብዙ ቦታ በብዙ መከራ ተመከረች፡፡ ያ ንፁህ ነፍስ ግን አሁንም ማመኑን አያቆምም፡፡ ማርገዟን አውቃ አዲስ አበባ መጣች፡፡ ከልጇ ጋር ብዙ ተሰቃየች፡፡ በተፈጠረችበት ምድር ላይ…በተፈጠሩት እንግዶች መሀል እንግዳ ሆነች፡፡
“እንግድነቷን የሚያቀልላትንና እስከዛች ሰዓት ድረስ ስታምነው የከረመችውን ፈጣሪዋን ፍለጋ የልጁ የክርስቶስ ስም የሚጠራበት ክርስቲያን ቤት ሁሉ ተመላለሰች፡፡ አንድ ቀን ላይ ግን የልጇን አባት አየችው፡፡ በመድረኩ ላይ ቆሞ እየሰበከ፡፡ ንስሀ ግቡ እያለ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ምዕመን ሰብስቦ አብራችሁኝ የምድርን መከራ እናሸንፍ ብሎ በሀያል ድምፅ ሲሰብክ ተመለከተችው፡፡ እርግጥ ነው ብዙ ጥራ ነበር፤ እሱን ለማግኘት፡፡ ያ የጌታ ሰው ግን ለእንደሷ አይነት ሴት ጊዜ የለውም፡፡ ማጌጥ ስላለበት ከአዳፋ ጋር የሚነካካበት ምክንያት ጥሎት  ኮብልሏል፡፡
ሮሀማ ከተቀመጠችበት ተነስታ ፓስተሩ አይኖች ስር ገብታ ማውራት ጀመረች፡፡
“አሁን የምታያቸው አይኖች ያንን ሁሉ መከራ በዘመናት ለውጥ እንዳይረሱ ሰልጥነው ለብቀላ የተበጁ አይኖችን ነው፡፡ የሚተርክልህ አንደበት አንድ ቀን አባት አለኝ…አባቴ ብሎ መጥራትን ናፍቆ ዘመኑን በሙሉ የተነፈገ አንደበት ነው፡፡ ያኔ ነው በቀል በልቤ ውስጥ ዘሩን የዘራው፡፡ ዛሬ የማጭድበት ቀን ነው…የዛች ምስኪን ሴት ልጅ አይኖችን ነው እያየህ ያለኸው….ክደህ የሸሸኸው መልክ ነው፣ እድሜና ዘመኑን ጠብቆ ከፊትህ የተደነቀረው፡፡ አሁን እንደ እናቴ ተረጋግተህ ንስሀ እንድትገባ አይደለም የመጣሁት….
ፓስተር ትዝታው፣ አይኖች ደርቀው ውሀ በጠማው አንደበቱ እንዲህ  አለ….”ልጄ ነሽ…?”
ሮሀማ ድንገት ከኋላ ኪስ ውስጥ አንድ ሴንጢ አውጥታ ኩላሊቱ አካባቢ በሀይል ወጋችው፡፡
“ይሄ እናቴን ያንከራተታት…አንተም በበደል ጉልበትህ ጠርተህ እሷን ላስረከስካት ነው….”
በሌላኛው ኩላሊቱ በኩል ደግማ ሰካችበት…
“ይሄ ደግሞ አባቴ እንዳልልህ…እንድክድህ አድርገህ የህይወቴን ምዕራፍ ሀ ብለህ ላስጀመርከኝ ነው፡፡ ደምህ ፈሶ እስክትሞት ትንሽ ትቆያለህ…ለፈጣሪዬ ቅርብ ነኝ ብለህ የምታስብ ከሆነ ለሁለታችንም ንስሀ ግባ፡፡ በዛውም ይቅር በለን…እኔንም እናቴንም ይቅር በለን፡፡ እኔም አባቷን አስሳ የተበቀለች ተብዬ በሰው ዘር ልረገም፡፡ ሆኖም ከዛሬዋ ቀን አንስቶ መኖር እንደምጀምር በመከራዋ ጀልባ እዚህ ያደረሰኝ የእናቴ ነፍስ ብቻ ናት የምታውቀው፡፡ ደህና ሁን አባቴ… ምናልባት እናቴን ካገኘሀት ንገራት…ሮሀማ ናት ወደዚህ የላከቺኝ በላት፡፡ አምናለሁ…ያኔ ፈገግ ብላ ታይሀለች…ያኔ ነው ፈጣሪህ ይቅር የሚልህ፡፡”   
ሮሀማ ጥላው በሩን ከፍታ ልትወጣ ስትል፣ በሲቃ ውስጥ ሆኖ ይህን ተናገራት…
“ይቅር በይኝ…ይቅር በይኝ...?”
ሮሀማ ግን አቅሙ አልነበራትም፡፡
“እኔም እንዳንተው የገዛ ስራዬ አንድ ቀን ያለሁበት መጥቶ ይገድለኛል፡፡ ያለህበት እመጣለሁ፡፡ ያኔ ይቅር እልሀለሁ፡፡”
ይህን ተናግራ በሩን ዘግታው ወጣች፡፡ ፓስተር ትዝታህ እንዳትከተለኝ ብሎ፣ አቅም የለህም ብሎ፣ ከረሳውህ ሞተሀል ማለት ነው ብሎ፣ የሰማይ ነፍስ ውስጥ የወረወረው ትዝታው፣ ከፅዕረ አርያም ነጥሮ ተመልሶ መጥቶ ወግቶ ገደለው፡፡          



Read 393 times