Monday, 08 July 2024 00:00

የጽድቅ መምህሩ

Written by  ነቢል አዱኛ
Rate this item
(0 votes)

ምናባዊ ወግ

“እንዴት ዋሉ ጋሼ?”
“አለኹኝ በሰላም። አለኹኝ በጤና”
“ጥሩ ነው። እንዴት ነው ውሎ?”
“ማለፊያ ነው። የዕለት ጉርሳችንን ፍለጋ በጠዋት ነው የምንወጣው። መሬቷ’ም ታበቅላለች፣ ላሞቹም ወተት ይታለቡልናል፣ ንቦቹም ማር ይሰጡናል። ከቅቤው ከማሩ የወዛን ነን።”
“ጥሩ ነው ጋሼ። ዛሄር ይመስገን ማለት ነው።”
“ምን አልክ ልጄ?”
“ምንም ጋሼ፤ ፈጣሪን ማመስገን ነው አልኩ”
“አዎ ፈጣሪ። የንብ ፈጣሪ፣ የላም፣ የእሸት፣ የአዝመራ፣ የጸሀይ፣ የዝናብ፣ የመሬት፣ የሰው ፈጣሪ አዎ ይመስገን። ግን ልጄ ከየት መጣሁ አልከኝ? አላወኩህም”
“እኔ እንኳ አመጣጤ ከከተማ ነው። እዚህች መንደር ላይ ምንም ዓይነት ቤተ-ክርስቲያን ስላላየን በጋራ ልናሰራ ስለሆነ፣ እርዳታ ከመንደሯ ነዋሪዎች እየጠየቅን ነው።”
“ቤተ ምን አልከኝ?”
“ቤተ ክርስቲያን”
“ቤተስኪያን?”
“አዎ። እዚህች መንደር ብቻ ሳይሆን ሙሉ ከላይም ከታችም 300 ኪሎ ሜትር ርቀት በላይ ቤተ-ክርስቲያን አላየንም። እና ከጓደኞቼ ጋር ሆነን ልናሰራ ነው። ከመንደሮቹም ከሌሎቹ ብዙ ሰው እዚህ ስለሚገኝ እርዳታ መጠየቁን ከዚህ እንጀምር ብለን ነው።”
“ምንድነው እሱ የምታሰሩት? ቤተስኪያን ምንድነው?”
“አዎ ጋሼ። ከጓደኞቼ ጋር ሆነን እንዳየነው እዚህ አካባቢ ሁላችሁም ሃይማኖት የላችሁም። በዚህም ላይ ከጓደኞቼ ጋር መክረን ነበር። የቱ ይቅደም? ቤተ-ክርስቲያን እንስራ? ወይስ ሰውን ስለ ሃይማኖት እናሳውቅ? ብለን በመጨረሻ ከተሰራ በኋላ እዚያ እንዲመጡ እያደረግን፣ እዚያ ብናስተምር ይሻላል ብለን ወሰንን።”
“አልገባኝም የምትለው። ሃይማኖት ምንድነው?”
“ሃይማኖት እንግዲህ ከፈጣሪ ጋር የምትገናኙበት መንገድ ነው። ፈጣሪን ማምለኪያ። ወደ እሱ መቅረቢያ ነው ሃይማኖት።”
“ፈጣሪን እኮ አውቀነዋል። ይፈጥረናል። ያበላናል፣ ያጠጣናል። አዝርዕቶች እንዲበቅሉ ዝናብና ጸሀይ ይሰጣል። በቃ ሌላ ከዚህ በላይ ምኑን እናውቃለን?”
“እኮ ልክ ነዎት! ግን በሃይማኖት በኩል ቤተ ክርስቲያኒቱ ስትሰራ እዚያ እየሄዳችሁ ትማራላችሁ። የፈጣሪን ጥበብና ሃያልነት ትረዳላችሁ። ሌላም ብዙ ታሪኮችን ተዓምራቶችን ታውቃላችሁ።”
“ይኸው ፍሬ መሬት ውስጥ ወርውረን ዛፍ ሆኖ ሲበቅል ከማየት በላይ ተዓምር አለ?”
“ቆይ ጋሼ ቆይ... አንድ ሰው ሲሞት የት ይሄዳል?”
“ጉድጓድ ውስጥ። አፈር ይደፋበታል።”
“ማለቴ ሰው ከሞተ በኋላ ነፍሱ የት ትሄዳለች?”
“ነፍስ?”
“አዎ ነፍስ። ሰው እንዴት ተፈጠረ ጋሼ?”
“ከአባቱ ዘር ፍሬ... ከእናቱ ሆድ”
“ከዚያ በፊት የነበረው ሰውስ?”
“ከእናቱ”
“ከዚያ በፊትስ?”
“ከእናቱ ቀጥሎም ከእናቱ”
“በቃ? መጨረሻ የለውም?”
“ምን ያረግልኛል መጨረሻው?”
“ማወቅማ ግድ ይላል”
“ግድ ይላል? እንዴት? ጠዋት ላሞቹን ለግጦሽ ሳወጣ ያግዘኛል? ማታስ በረታቸው ያስገባልኛል? ከቀፎ ውስጥ ማር ቆርጦ ያመጣል? ይሄን ማድረግ ካልቻለ ምን ጥቅም አለው? ለኛ ግዳችን ይሄን ማድረግ ሲችል ነው።”
“አይ ጋሼ። ይበልጥ ቤተስኪያኒቱ ስትሰራ እዚያ ይማራሉ። አሁን ስለምቸኩል ቢተባበሩኝ ብዬ ነው። ከቻሉ ያለዎትን ይስጡን። ከማሩም ከወተቱም። ተሽጦ በገንዘቡ ይሰራበታል። ለርስዎም ጽድቅ ነው መንግስተ ሰማይ ይገባሉ”
“የት ይገባሉ?”
“መንግስተ ሰማይ። ገነት።”
“ገነት? ሰማይ? መንግስት? በየት በየት ብዬ ልጄ? ስታየኝ ከስቼ ሳጥርብህና ወፍራም ልብስ ስለብስ ክንፏን የደበቀች ወፍ መሰልኩህ እንዴ? እንዴት ብዬ ነው ሰማይ የምወጣው? ደሞ በየት ሃገር ነው ተራ ገበሬ መንግስት የሚሆነው?”
“አልገባዎትም ጋሼ። ቅድም እንዳልኩዎ ሰው ሲሞት ነፍሱ ወደ ሰማይ ታርጋለች። ይህ ሰው ምድር ላይ እያለ መልካም ሰው፣ ፈጣሪን አምላኪ፣ ጿሚ ሰጋጅ ከነበረ ገነት ይገባል። ከዚህ በተቃራኒው አማጺ ከነበረ ደሞ ሲዖል እሳት ውስጥ ይገባል።”
“ስለምን ነፍስ ነው የምታወራው? ሰው ይወለዳል፣ ያድጋል፣ ይሞታል። ሲሞት ደሞ ይቀበራል። አፈር ይመለስበታል። ሰውየው የሚቀጥለው በስሙ የሚጠራ የወለደው ልጅ ሲኖረው ነው። አበቃ! ሌላ ሰማይ፣ እሳት ብሎ ነገር የለም ሆሆ...”
“አይደለም እኮ ይሄን እንዲያውቁ፣ እንዲረዱ ነው ቤተስኪያን አስፈላጊነቱ። ደሞ...”
“አታውቅም፣ አይገባህም እያልከኝ ነው?”
“አይደለም ኧረ! ቆይ አስጨርሱኝ ቤተስኪያኒቱ ስትሰራ ስለ አምላክ፣ ስለ ሰው ልጅ አፈጣጠር፣ ስለ ገነት፣ ሲዖል ያውቃሉ። በዚያውም ጿሚ ሰጋጅ ይሆኑና...”
“ጿሚ ምንድነው?”
“በሁሉም የሃይማኖቱ ተከታዮች ዘንድ የታወቁ ቀናቶች አሉ፤ በነዚያ ቀናት ከምግብና ከመጠጥ፣ ሚስትዎትን ከመገናኘትና ከመጥፎ ስራዎች ይቆጠባሉ።”
“ለምን ሲባል?!”
“ገነት እንዲገቡ”
“እንዴ! ሃይማኖት ነው ብዬ ራሱ ፈጣሪ ያበቀለውን ምግብ የማልበላው ለምን ነው? እንደውም ካልክ አይቀር ‘ዝም ብዬ ነው ያበቀልኹላችሁ?’ እንዳይለን ስለበላሁ ነው፣ እዚያ ትገባለህ ያልከው ቦታ መግባት ያለብኝ። ከምስኪኒቷ ላም ወተት አልበን እንዳንጠጣ እየከለከላችሁ ነው ፈጣሪን አወቅን የምትሉት? ድንቄም ታወቀ! ከፈለጋችሁ ያለምንም እርዳታ ማሰባሰብ እኔ ዘንድ ቁጭ ብላችሁ እየበላችሁ፣ እየጠጣችሁ ስለፈጣሪ ላስተምራችሁ።”
“አልተግባባንም ጋሼ። ይበልጥ ቤተስኪያኒቱ ስትሰራ እዚያ ተምረው ይረዱታል። ለማሰሪያ የሚሆን የቻላችሁትን ብትሰጡኝና ስለምቸኩል ብሄድ ጥሩ ነው። ለርስዎም ጽድቅ ነው። ገነት ያስገባዎት ይሆናል።”
“ቆይ ቆይ ልጄ። ጿሚ ሰጋጅ፣ ይሄ ምንድነው ያልከው ቤተ ምናምኑን አሰርታችሁ ከዛስ ምን? ለምን ነው የምትለፉት ይሄን ሁሉ? ጾምን ብላችሁ ራሳችሁን ቀጥታችሁ ከዛስ?”
“ከዚያማ ገነት እንገባለን!”
“ገነት?”
“አዎ”
“በቃ ህልማችሁ ገነት ነው? ያማረች፣ የተኳለች፣ የተዘየነች ሚስታችሁን አይን አይኗን ማለት ትታችሁ፣ አይን አይኗን እያያችሁ አድራችሁ...ገነት?”
“አዎን! የሁሉም አማኝ ህልም ከእሳት ርቆ ገነት መግባት ነው”
“ምን አለ እዚያ?”
“ገነትማ ጋሼ... የወተት ወንዙ፣ ማሩ፣ ወይኑ፣ አትክልቱ፣ ውብ ውብ ሴቶቹ፣ በቃ ምን ልበሎት ጋሼ? እዚያ ረፍት ነው፤ ስራ፣ ልፋት የለም፣ አንድ ነገር ከፈለጉ.. መፈለግ ብቻ ነው የሚጠበቅብዎ፤ ወዲያው እጅዎ  ይገባል። በቃ ተድላ ብቻ ነው። ቁጭ ብሎ መብላት፣ መዝናናት ነው።”
“ምን - ምን? ወተት? ይሄ ከዚችኛዋ ላሜ የማልበው ወተት? ልጆቼ ጠግበው የሚረጫጩበት ወተት? ወንዙስ ስትል ይሄ ከጎረቤቶቼ ጋር ልብስ የምናጥብበትና ገላችንን የምናጥብበት? አትክልት እርሻዬን የሞላው? ሴቶች ላልከው ደሞ እትዬ... ማናት እቺ ጎረቤቴ አራት ሴት ልጅ አላት - ያላገቡ። የኔም ሁለቱ አላገቡም። ጓደኞችህን ጥራና እኔ እድርሃለሁ። ምን የመሳሰሉ ቆንጆዎች መሰሉህ! ሌሎችም እላይ ቀዬ አሉ። ሆሆ.. ወተት ይበለኝ!”
“ጋሼ እርዳታውን ይሰጡኛል? ወይስ ልሂድ?”
“ስማኝ ልጄ እርቦህ ከሆነ አበላሃለሁ። ለጓደኞችህም ይዘህ የምትሄደውን እስጥሃለሁ። ምን የመሰለ የማር እንጀራ አለ፤ ከወተት ጋር እስጥሃለሁ። እንጂ ለዚያ ለማሰሪያ ነው ምናምን ላልከው አልሰጥም። አሁን የምበላውን ማር ለምን ገነቴ እያልኩ ለሌላ እሰጣለሁ? ልጆቼን ባበላ አይሻልም? ኖርናታ!”
“በቃ ጋሼ?”
“ቁጭ ብሎ መብላት? ምነው ይሄን ያክል ባለጌ አደረከኝ? እንዴት ሰው ሳይሰራ ቁጭ ብሎ ይበላል? ያልሰራሁትን? ያልዘራሁትን? ያላጨድኩትን? ይኼ ነውር ነው።”
“አይደለም ጋሼ እዚህ የሰሩትን መልካም ስራ ነው እዚያ የሚያገኙት። እዚህ የሚዘሩት መልካም ስራ እዚያ ይታጨዳል። እዚያ የሚፈልጉት ሁሉ አለ።”
“አይ እንግዲህ! የምታጃጅለውን ሄደህ እዛ አጃጅል። የፈለኩት ሁሉ ኖሮ የፈለኩትን እያገኘሁ ነው የምኖረው?”
“አዎ ጋሼ አዎ!”
“ምኑን ኖርኩታ?”
“ማለት?”
“ተስፋ ሳይኖረኝ? ለፍቼ ላግኝ፣ ሰርቼ ላምጣ ሳልል፣ የሆነ ህልም ሳይኖረኝ እንዴት እኖራለሁ? ደሞ በምን እርግጠኛ ሆኜ ነው፣ በእጄ ያለውን ዳቦ ሰጥቼ ስጋ የምጠብቀው?”
“ደህና ይደሩ ጋሼ”
“ልትሄድ ነው? ተው ና እዚህ አትክልት አለ... ተው ና እዚህ ወተት አለ... ተው ቆንጆ ሴቶች አሉ... ማር አለ... ተው ና... ተው...”


Read 212 times