Administrator

Administrator

Thursday, 25 November 2021 06:59

የስኬት ጥግ

 * ከተለመደው አካሄድ ሳትወጣ ዕድገትን እውን አታደርግም፡፡
    -ፍራንክ ዛፓ-
  * በዝግታ መጓዝን አትፍራ፤ መፍራት ያለብህ ባለህበት መቆምን ነው፡፡
   -የቻይናውያን አባባል-
 * ያንተን ዕድገት ከሌሎች ጋር አታወዳድር፡፡ የራሳችንን ርቀት ለመጓዝ የራሳችን ጊዜ ያስፈልገናል፡፡
   -ያልታወቀ ሰው -
 * ዝግ ያልኩ ተጓዥ ነኝ፤ ነገር ግን ፈፅሞ ወደ ኋላ አልጓዝም፡፡
  - አብርሃም ሊንከን-
 * ያለ መስዋዕትነት ዕድገትም ሆነ ስኬት አይገኝም፡፡
   -ጄምስ አለን-
 * እድገት ማለት ደስተኝነት ነው፡፡
   -ቶኒ ሮቢንስ-
 * ትግል በሌለበት ዕድገት የለም፡፡
   -ፍሬድሪክ ዳግላስ-
 * ለዕድገት ምርጡ መንገድ የነፃነት መንገድ ነው፡፡
   -ጆን ኤፍ. ኬኔዲ-
 * ዕድገት በዕድል ወይም ባጋጣሚ አይሳካም፤በየዕለቱ በራስ ላይ በመስራት እንጂ፡፡
   -ኤፒክቲተስ-
 * ዕድገት ከለውጥ ውጭ እውን አይሆንም፡፡
   -ዋልት ዲዝኒ-
 * ሁሉም ዕድገት የሚከናወነው ከምቾት ቀጠና ውጭ ነው፡፡
   - ማይክል ጆን ቦባክ-
 * ግቦችህ ላይ ሳይሆን ዕድገትህ ላይ አተኩር፡፡
   - አና ባርኔስ-
 * ዕድገት የህይወት ብቸኛው ማስረጃ ነው፡፡
   - ጆን ሄነሪ ኒውማን-
 * ፍቅር የሚሞተው ዕድገት ሲቆም ብቻ ነው፡፡
   - ፐርል ኤስ. በክ-
 * ምቾት የዕድገት ጠላት ነው፡፡
   - ፒ.ቲ.ባርነም-

 “ጋሽ ሙሉጌታ የተዋጣለት ጸሐፊ፣ ተቺ፣ ገምጋሚ ነበር፡፡ በሥራው ባሕርይ የተነሳ ኢትዮጵያን በአብዛኛው ዞሮ ያየ ሰው ነበር፡፡ የሚጽፈው የሚያውቀውን የሚያምነውን ነበር፡፡ እምነቱ ደግሞ መሠረት፣ ጥልቀት ካለው ባሕር የሚቀዳ እንጂ ከድስት የሚጨለፍ አ ልነበረም… በ ስደት ባ ይሆን ጥ ሩ ነ በር!!--ያ ደግሞ የአገራችን አካልና አ ምሳል ገ ላጭ ባ ሕር ሆ ኗል!--;
           
          አንጋፋውን ጋዜጠኛ፣ ኃያሲና ተንታኝ ሙሉጌታ ሉሌ ደስታን የምናስታውስበት በርካታ ምክንያቶች ይኖሩናል፡፡ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት መምርያ ኃላፊ ነበር፡፡ በኢትዮ ሶማሊያ ጦርነት ጊዜም ወደ ምስራቅ በመዝመት ሀገሩ ከሱ የምትፈልግበትን አስተዋጽዖ አበርክቷል፡፡ በቀይ ኮከብ ዘመቻ የዕውቁ ደራሲና ጋዜጠኛ በዐሉ ግርማ ምክትል ሆኖ በምድረ ኤርትራ ከርሟል፡፡ በ1983 ዓ.ም ኢህአዴግ ሥልጣን ሲይዝ ሙሉጌታና በርካታ ታዋቂ ጋዜጠኞች ከሥራ ገበታቸው ተሰናብተዋል፡፡ ከሥራ እንጂ ከዕውቀትና ሙያ ባለመሰናበቱ ከሙያ አጋሮቹ ጋር በመሆን ጦቢያ መጽሔትን መሥርቶ ሲሰራ ቆይቷል፡፡ ኅትመቱ እስከተቋረጠበት ጊዜ ድረስም በተነባቢነት ዘልቋል፤መጽሔቱ፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ ሙሉጌታ ሉሌ፤ ኢትዮጵያዊነቱን እጅግ የሚወድ ለዚያም መስዋዕትነት የከፈለ በሳል ባለሙያ እንደነበር የሥራ ባልደረቦቹ ይናገራሉ፡፡ ትውልዱና እድገቱም ሀገር ወዳድነቱን ያጎለመሰለት ይመሥላል፡፡ምንጫቸው ከጎጃም ከሆነ ነጋዴ ቤተሰቦቹ የተወለደው የጣሊያን ወራሪ ከኢትዮጵያ በተባረረበት ዓመት ሐምሌ 5 ቀን 1933 ዓ.ም ግንደበረት ነው፡፡ የአንደኛ ደረጃ ትምህርቱን አምቦ በማዕረገ ሕይወት ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ትምህርት ቤት፣ ሁለተኛ ደረጃን ደግሞ ደብረብርሃን ኃይለማርያም ማሞ ከተማረ በኋላ አዳማ በሚገኘው ባይብል አካዳሚ ገብቶ ተምሯል፡፡ በመቀጠልም ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመርያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡
ወደ ናዝሬት/አዳማ ተመልሶ በተማረበት ባይብል አካዳሚ በቋንቋ መምህርነት ካገለገለ በኋላ ነው ወደ ጋዜጠኝነት የገባው፡፡ በቀለም ትምህርት ካስተማራቸው ታዋቂ ሰዎች መካከል የቀድሞው የኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት ዶክተር ነጋሶ ጊዳዳና አንጋፋው የታሪክ ምሁር ዶክተር ላጲሶ ጌ.ዲሌቦ ይገኙበታል፡፡ ባለፈው ቅዳሜ ኅዳር 4 ቀን 2014 ዓ.ም ረፋድ ላይ ሙሉጌታ ሉሌ የተዘከረበትና የተወዳጅ ሚዲያ እና ኮሚዩኒኬሽኑ ዕዝራ እጅጉ ያዘጋጀው የጋዜጠኛውን ታሪክ የያዘ ሲዲ የተመረቀበት ሥነሥርዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር ተከናውኗል፡፡ በመርሃግብሩ “ሙሉጌታ ሉሌ፤ የኢትዮጵያ ባለውለታ” በሚል ርእስ ከቀረበው የ22 ሰዎች ቃለ ምልልስ የተካተተበት የ120 ደቂቃ ሲዲ ሌላ ቅንጭብ ተውኔት፣ የባልደረቦቹና አድናቂዎቹ ትውስታና ሌሎችም ዝግጅቶች ቀርበው ነበር፡፡ ቃለምልልስ ከተደረገላቸው ግለሰቦች መካከል አንጋፎቹ ጋዜጠኞች አዲሱ አበበ፣ ክፍሌ ሙላት፣(የአዲስ ዘመን አድማስ ገጽን ያዘጋጅ የነበረው)፣ ይንበርበሩ ምትኬ (ኢትዮጵያ ሬዲዮ ስፖርት)፣ አጥናፍሰገድ ይልማ ይገኙበታል፡፡
አንጋፋው ጋዜጠኛ አጥናፍሰገድ ይልማ ከሙሉጌታ ጋር በቅርበት ከሠሩ ባለሙያዎች አንዱ ነው፡፡ ለስልሳ ዓመት ነው ትውውቃቸው፡፡ አንጋፋው ጋዜጠኛ የሙሉጌታ ሉሌን ባሕርይ ሲገልጽ #የሚስማማው ሊስማማ ሲችል ብቻ; መሆኑን ጠቅሷል፡፡ አጥናፍሰገድ አንድ ወቅት በተደረገ የመዋቅር ለውጥ ሙሉጌታ የሱ አለቃ መሆኑን ሲገልጽ “በተደረገ የመዋቅር ለውጥ እሱ የመነን መጽሔት ዋና አዘጋጅ፣ እኔ ምክትል ዋና አዘጋጅ ሆኜ ስመደብ ተቃወምኩ፡፡ በአገልግሎት ስለማይበልጠኝ አለቃዬ ሊሆን አይገባም ብዬ ተቃወምኩ፡፡ ካልሆነ ሥራውን እለቃለሁ አልኩ፡፡ ልብ በሉ፤ አመጼ ከሥርዓቱ አንጻር የተቃወምኩት ሥርአቱን እንጂ ሙሉጌታን አይደለም፡፡ ስለዚህ ከሙሉጌታ ጋር ማታ ማታ እንገናኝ ነበር፡፡ ‘አርፈህ ቤትህ ተቀመጥ’ ብሎ መጽሐፍ አምጥቶ ይሰጠኝ ነበር” ካለ በኋላ አጥናፍሰገድ እስር ቤት ሆኖ ከእስር ቤት ውጪ ላለው ሙሉጌታ በሚታጠብ ልብስ ኮሌታ ውስጥ የተጻፈበት ወረቀት በስልት በመጠቅጠቅ መረጃ ያቀብለው እንደነበርም ገልጧል፡፡
ሙሉጌታ ከመነን መጽሔት ወዲህ ባለው ጊዜ በተለይ የፕሬስ መምርያ ኃላፊ በነበረበት ጊዜ በእሱ ኃላፊነት ለሚታተሙት አዲስ ዘመን፣ ዘ ኢትዮጵያን ሔራልድ፣ በሪሳ እና አልአለም ጋዜጦች ኤዲቶርያል ውይይት ይቀርብ የነበረው በሚያውቃቸው ቋንቋዎች የተጻፉትን ራሱ በማንበብ፣ በሌሎቹ የተጻፉትን ደግሞ በማስተርጎም ነበር፡፡ ከዚህም ሌላ ፋታ በማይሰጥ የመምርያ ኃላፊነት ሥራ ላይ ሆኖ ለጋዜጦቹ ርእሰ አንቀጽ ከመጻፉም ሌላ ለተለያዩ ጋዜጦችና መጽሔቶች ጽሑፍ ያቀርብም ነበር፡፡ በኃላፊነት ሥራው ላይ የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ ብስለት አውቆ እንደየ ዐቅሙ በማሰማራት የጋዜጠኞቹን ብቃት ከማሳደጉም በላይ ማንም ይጻፈው ማንም አንድ ጽሑፍ ካልጣመው #እንጨት እንጨት ይላል; ብሎ ይተች እንደነበርም በሲዲ ምርቃቱ ወቅት ተገልጧል፡፡ ይህንኑ አስመልክቶ አብሮት የሠራው አንጋፋው ደራሲና ጋዜጠኛ ዶክተር ታደለ ገድሌ፤ “ጋሽ ሙሉጌታ በኢትዮጵያ ጋዜጠኝነት ታሪክ ተወርዋሪ ኮከብ ናቸው፡፡ የእያንዳንዱን ጋዜጠኛ ችሎታም ጠንቅቀው ያውቃሉ፡፡” ብሏል፡፡
በዚያውም መጠን የሐሳብ ልዩነትን እንደሚቀበል የመሰከሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ አያሌው አስረስ፤ አብረው ይሠሩ በነበረበት ጊዜ የጋሽ አያሌው ጽሑፍ አፈንጋጭ ቢሆንም ተዉት ይል እንደነበር አስታውሰዋል፡፡
ልዩነትን ማቻቻልና ማክበርን በተመለከተ ልጁ ዔዶም ሙሉጌታ ሉሌ ስለ አባቷ ስትገልጽ፤ “ብዙ ጊዜ ፓስተር አካባቢ ወደሚገኘው ቤታችን ስንሔድ መኪና ውስጥ አልፎ አልፎ የፕሮቴስታንት መዝሙር ይከፍትና፣ ዮሐንስ ቤተ ክርስትያን (የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ) ስንደርስ መዝሙሩን ዝቅ አድርጎ ኮፍያውን በማውለቅ ይሳለም ነበር፡፡ ለዚያም ይመስለኛል ድፍረት አግኝቼ የዘመኑ ጀግና የሆነውን ዶክተር እስማኤል ሸምሰዲን ሃሰንን ለማግባት ድፍረት ያገኘሁት፡፡” ብላለች፡፡
እሱን ለመጨበጥ ዕድሉን አግኝቼ ነበር የሚለው የአሀዱ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ የዩኒቨርሲቲ ተማሪ ሆኖ በሙሉጌታ ጽሑፎች ላይ ይወያዩ እንደነበርና ከሙሉጌታ የብእር ስሞች አንዱ የሆነው ጸጋዬ ገብረመድሕን አርአያ ብዙ ሰዎች ናቸው አንድ ሰው? ብለው መሟገታቸው የሙሉጌታን ታላቅ ብዕረኛነት ያሳያል ብሏል፡፡ ስለ እለቱ ዝግጅትም ሲናገር፤ “በብዙ የሚመነዘረውንና አርአያ የሆነውን አንጋፋውን ጋዜጠኛና ተንታኝ ሙሉጌታን በመዘከራችሁ ምስጋና ይገባችኋል” ሲል ተወዳጅ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽንን አመስግኖ፣  “ሙሉጌታ ብዙ ጋዜጠኞች አፍርቷል፡፡ የጋዜጠኝነትን ጣራ አሳይቶናል፡፡ የበዓሉ ግርማ ከአድማስ ባሻገር መጽሐፍ ላይ መጀመርያ ሂስ የሰጠው ሙሉጌታ ነው፡፡ የሙሉጌታ ሂስ እስካሁንም የሚጠቀስ ነው” ብሏል፡፡
ሙሉጌታ የሥነጽሑፍ ሂስ ብቻ ሳይሆን መንግሥትንም በወቅቱ በመሸንቆጡ ይታወቃል፡፡ በተለይ በህወሓት ይመራ የነበረው የኢህአዴግ መንግሥት አሥራ ስድስት ጊዜ አስሮታል፡፡ ቀድሞውኑ ያለጥፋት በመታሰሩም ሲታሰር ሲለቀቅ ኖሯል፡፡ በመኪና የግድያ ሙከራ ተደርጎበትም በጽኑ ቆስሎ ተርፏል፡፡ እሱን ማሰር መፍታቱ አልሆን ያለው መንግሥትም፤ ያለ ሙሉጌታ ፍቃድ ወደ ውጪ ሀገር እንዲሰደድ አድርጎታል፡፡
ከዚያ በፊት በደርጉ የማስታወቂያ ኮሚቴ አብረው በቅርበት ይሰሩ እንደነበር ያስታወሱት ደራሲ ገስጥ ተጫኔ እና ኮለኔል ናደው ዘካርያስ ከዘመነ ኢህአዴግ በፊት የነበረውን ሙሉጌታ ሉሌን አብረው በመሥራታቸው በሥራዎቹና በሰብዕናው እንደሚያደንቁት ነው የተናገሩት፡፡ ኮሎኔል ናደው በተጨማሪም፣ ለዓመታት ታስረው ሲፈቱ፣ ከአሜሪካ መጀመርያ ደውሎ የጠየቃቸው ሙሉጌታ ሉሌ እንደሆነ አስታውሰዋል፡፡
በዚያው ጊዜ የነበሩት ብርጋዲየር ጄነራል ካሳዬ ጨመዳም ሙሉጌታን አስመልክቶ ሲናገሩ፤ “በኤርትራ ‘ኢትዮጵያ’ የሚባል ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ነበር፡፡ በብስራተ ወንጌል ሬዲዮም ሠርቷል፡፡ ከፍተኛ አንባቢ ስለነበር የንባብ እውቀቱን ለጽሑፍ ዝግጅቱ ይጠቀም ነበር፡፡ ዛሬ ሳያነቡ የሚጠይቁ ጋዜጠኞች ከሱ ሊማሩ ይገባል፡፡ በሥሙም ማስታወሻ የሚሆን ሀውልትና ማዕከል ሊኖር ይገባል” ብለዋል፡፡
በእርግጥም ከተሰደደ በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ሲያገለግልበት የነበረው የኢሳት የዋሺንግተን ዲሲ ስቱዲዮ፣ በስሙ የተሰየመ ትልቅ ቤተ መጻሕፍት እንዳለው፣ በቅዳሜው የ#ሙሉጌታ ሉሌ የኢትዮጵያ ባለውለታ; ሲዲ ምርቃት ላይ ተጠቅሷል፡፡
በ1933 ዓ.ም ተወልዶ በ2008 ዓ.ም በስደት በአገረ አሜሪካ ያረፈውን የሙሉጌታን ሥራዎች በዝርዝር በጋዜጣ ላይ መተንተን አይቻልም፡፡ ሆኖም ለማስታወስ ያህል ይህን ጻፍኩ፡፡
የማጠቃልለው በዚሁ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ነፍስ ሔር አሰፋ ጫቦ በጻፉት እና “ሰው ስንፈልግ ባጀን” በተሰኘው የሙሉጌታ ሉሌ መጽሐፍ የጀርባ ሽፋን ላይ በሠፈረው ጽሑፍ ቅንጭብ ነው፡፡
“ጋሽ ሙሉጌታ የተዋጣለት ጸሐፊ፣ ተቺ፣ ገምጋሚ ነበር፡፡ በሥራው ባሕርይ የተነሳ ኢትዮጵያን በአብዛኛው ዞሮ ያየ ሰው ነበር፡፡ የሚጽፈው የሚያውቀውን የሚያምነውን ነበር፡፡ እምነቱ ደግሞ መሠረት፣ ጥልቀት ካለው ባሕር የሚቀዳ እንጂ ከድስት የሚጨለፍ አልነበረም… በስደት ባይሆን ጥሩ ነበር!! ያ ደግሞ የአገራችን አካልና አምሳል ገላጭ ባሕር ሆኗል! ዋናው ነገር እንዴት ሞተ መሆን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ’እንዴት ኖሮ ነበር!’ ነው፡፡ ሙሉጌታ አንገቱን ቀና አድርጎ ያመነበትን በግልም በአደባባይም ተናግሮም ጽፎም ያለፈ ጀግና ነው፡፡” ብለዋል፤ አሰፋ ጫቦ፡፡
**
ከአዘጋጁ፡- ጸሃፊውን በኢ-ሜይል አድራሻው፡- This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ማግኘት ይቻላል፡፡

    የእለቱ የክብር እንግዳ ክቡር ፕሮፌሰር ነቢዩ ባዬ ከጠቅላይ ሚኒስትር  ጽ/ቤት  ተገኝተው  የመክፈቻ ንግግር  አድርገዋል። ለታዳሚዎች  ስራ ፈጣሪነትን የሚያነሳሳ አጅግ ጠቃሚ መልእክት አስተላልፈዋል ።ኢትዮጵያ ለእድገትና ለብልጽግና ጉዞዋ በርካታ ስራ ፈጣሪዎች እንደሚያስፈልጓት ገልጸዋል።
የአእምሮ ኢንተርፕረነርሽፕ ማስፋፊያ አገልግሎቶች  አክሲዮን ማህበር ቦርድ ፕሬዘዳንት  አቶ ጌታቸዉ ቢራቱ ባደረጉት ንግግር፤ ለሀገር እድገት የሰላም መኖር መተኪያ የሌለዉ ሁላችንም የበኩላችን ልናበረክት  እንደሚገባን  ታላቅ አጽንኦት  ሰጥተዋል።
የኩባንያው  ዋና ስራ አስካያጅ፡-
ዶ/ር ወሮታው በዛብህ በበኩላቸው ለአስተማማኝ የሀገር ሰላም እድገትና ብሌጽግና ኢንተርፕረነርሽፕ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልጸዋል።
 በእለቱ  12 ባለሙያዎች ጠቃሚ ትምህርቶችና ልምዶችን ለታዳሚው አጋርተዋል። የሰልጣኞች ምረቃም ተካሂዷል ።


   የተለያዩ የአለማችን አገራትን የህግና ስርዓት ሁኔታ በመገምገም በየአመቱ ይፋ የሚያደርገው ጋሉፕ የተባለው ተቋም ከሰሞኑም የ2021 ሪፖርቱን ያወጣ ሲሆን፣ ኖርዌይ እንዳምናው ሁሉ ዘንድሮም በአንደኛ ደረጃ ላይ ስትቀመጥ ናሚቢያ፣ ማሊ፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎና ዛምቢያ እጅግ የከፋ ሁኔታ ያለባቸው የአለማችን አገራት ናቸው ተብሏል፡፡
ተቋሙ ለበርካታ ሰዎች ቃለመጠይቅ በማድረግ በአገራት ውስጥ ያለውን የህግና ስርዓት ሁኔታ ለመገምገም ከሚጠቀምባቸው መስፈርቶች ውስጥ ዜጎች ምን ያህል በፖሊስ ላይ እምነት አላቸው፣ ደህንነት ይሰማቸዋል፣ ዝርፊያና ሌሎች ጥቃቶች ደርሶባቸዋል የሚሉት እንደሚገኙበት የተነገረ ሲሆን፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ቻይናና ስዊዘርላንድ በተመሳሳይ ነጥብ ሁለተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በአመቱ በተመሳሳይ ነጥብ ሶስተኛ ደረጃን የያዙት የአለማችን አገራት ደግሞ ፊንላንድ፣ አይስላንድና ታጃኪስታን መሆናቸውን የተቋሙ ሪፖርት ያሳያል፡፡ ደቡብ አፍሪካ በከፋ የህግና ስርዓት ሁኔታ የሁለተኛነት ደረጃን የያዘች ሲሆን፣ ናይጀሪያና ፔሩ በተመሳሳይ ነጥብ የሶስተኛ ደረጃን መያዛቸውንም መረጃው ያመለክታል፡፡

   የአለም የጤና ድርጅት በአለም ዙሪያ የሚገኙ ሲጋራ አጫሾች ቁጥር ከአምስት አመት በፊት ከነበረበት ጋር ሲነጻጸር በመጠኑ ቅናሽ ማሳየቱንና የአጫሾች ቁጥር በ2015 ከነበረበት 1.32 ቢሊዮን ዘንድሮ ወደ 1.30 ቢሊዮን ዝቅ ማለቱን አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ሰሞኑን ባወጣው አለማቀፍ ሪፖርቱ እንዳለው፣ በ2020 የፈረንጆች አመት ከአጠቃላዩ የአለም ህዝብ 22.3 በመቶ ያህሉ ሲጋራ የሚያጨስ ሲሆን 38 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ህጻናትና 231 ሚሊዮን ሴቶች አጫሽ ናቸው ተብሎ ይገመታል፡፡
የአጫሾች ቁጥር በመጪዎቹ አራት አመታት ውስጥ ወደ 1.27 ቢሊዮን ዝቅ ይላል ተብሎ እንደሚጠበቅ የገለጸው ድርጅቱ፤ እ.ኤ.አ ከ2010 እስከ 2025 የሲጋራ አጫሽ ዜጎችን ቁጥር በ30 በመቶ ለመቀነስ ቃል ከገቡ የአለማችን አገራት መካከል ስድሳ ያህሉ ወደ ግባቸው እየተቃረቡ እንደሚገኙም ገልጧል፡፡ከአለማችን ዝቅተኛ የአጫሾች ቁጥር የተመዘገበው በአፍሪካ መሆኑንና ከአህጉሪቱ ህዝብ 10 በመቶው ሲጋራ ያጨሳል ተብሎ እንደሚገመት የጠቆመው ድርጅቱ፣ በአንጻሩ የደቡብና ምስራቅ እስያ አገራት ደግሞ ከፍተኛ የአጫሽ ቁጥር እንደተመዘገበባቸውና ከአገራቱ ህዝብ 29 በመቶው ወይም 432 ሚሊዮን ያህሉ አጫሽ መሆኑንም አክሎ ገልጧል፡፡

  #ከትዳር ውጭ የሚወለዱ ኬንያውያን ውርስ አያገኙም;

               በኬንያ የተፈጠረው የኮንዶም እጥረት በከፍተኛ ሁኔታ መባባሱንና በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በወር 455 ሚሊዮን ኮንዶሞች የሚያስፈልጉ ቢሆንም መንግስት ግን እያቀረበ ያለው 1.6 ሚሊዮን ብቻ መሆኑ ዜጎችን ለከፋ የጤናና ማህበራዊ ችግር ሊዳርግ እንደሚችል መነገሩን ዘ ኔሽን ጋዜጣ ዘግቧል፡፡ ዘ ኔሽን ጋዜጣ ከትናንት በስቲያ ባወጣው ዘገባ እንዳለው፣ በአገሪቱ የሚገኙ የጤና ተቋማት፣ ሆስፒታሎችና ሌሎች ተቋማት ለደንበኞቻቸው በነጻ የሚሰጡትን ኮንዶም ማሰራጨት ካቆሙ አንድ አመት ያለፋቸው ሲሆን፣ ባለሙያዎች ለኮንዶም እጥረቱ መከሰት ምክንያት ነው ብለው የሚተቹት የአገሪቱ መንግስት ከፍተኛ ቀረጥ መጣሉን ነው፡፡
ከኮንዶም እጥረቱ ጋር በተያያዘ ጥንቃቄ በጎደለው የግብረ ስጋ ግንኙነት ለእርግዝና የሚጋለጡ ወጣት ሴቶችና ለተለያዩ በሽታዎች የሚጋለጡ ዜጎች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ማደጉን የጠቆመው ዘገባው፣ ለጋሽ ድርጅቶች በበቂ መጠን ኮንዶም እንዳያቀርቡ ከፍተኛ ቀረጥ እንቅፋት እንደፈጠረባቸውም አክሎ ገልጧል፡፡
የአገሪቱ የኤችአይቪ ኤድስና በወሲብ የሚተላለፉ በሽታዎች ቁጥጥር ቢሮ፣ አገሪቱ 2.1 ሚሊዮን ያህል ኮንዶሞችን ለመግዛት 4.6 ሚሊዮን ዶላር እንደሚያስፈልጋት መናገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ በኬንያ ከህጋዊ ትዳር ውጭ የሚወለዱ ልጆች፣ ወላጆቻቸው በሚሞቱበት ጊዜ ሃብታቸውን እንዳይወርሱ የሚከለክል አዲስ ህግ ከቀናት በፊት ጸድቋል፡፡ ህጉ ከትዳር ውጭ የወለዱ ቅምጦችም የሃብት ውርስ እንዳያገኙ እንደሚከለክል የጠቆመው ዘገባው፣ በርካታ ኬንያውያን ህጉ በስራ ላይ መዋሉን በመደገፍ በማህበራዊ ድረገጾች ድጋፋቸውን እየሰጡት እንደሚገኝ የዘገበው ኦልአፍሪካን ኒውስ፣ አንዳንዶች ግን እንደኮነኑት አልሸሸገም፡፡

    ታዋቂው ጎግል 2 ቢሊዮን በሚደርሱ የክሮም መፈለጊያ አውታር ተጠቃሚ ደንበኞቹ ላይ የድረገጽ መረጃ ምንተፋ ጥቃት ሊሰነዘር እንደሚችል ከሰሞኑ ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል፡፡
ባለፉት ሁለት ሳምንታት በደንበኞች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በከፍተኛ ሁኔታ መጨመራቸውን የገለጸው ጎግል፤ ከደረሰባቸው 25 ያህል ጥቃቶች መካከል ሰባቱ እጅግ አደገኛ መሆናቸውም አመልክቷል፡፡
ተጠቃሚዎች ከጥቃቱ ራሳቸውን ለመጠበቅ በአፋጣኝ ተገቢ ጥንቃቄዎችን እንዲያደርጉ የመከረው ጎግል፤ ከእነዚህም መካከል አፕሊኬሽኖቻቸውን ማዘመን እና ከማያውቋቸው ላኪዎች የሚደርሷቸውን መልዕክቶች አለመክፈት እንደሚገኙበት ተነግሯል፡፡

      የፊሊፒንሱ መሪ ከልጃቸው ጋር ላለመፎካከር በምርጫ እንደማይወዳደሩ አስታወቁ

                          በቀጣዩ ወር በሚካሄደው የሊቢያ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት የቀድሞው የአገሪቱ መሪ ሙአመር ጋዳፊ ልጅ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ በአገሪቱ ወታደራዊ አቃቤ ህግ በወንጀል ስለሚፈለጉ በምርጫው መወዳደር የለባቸውም የሚል ተቃውሞ እንደገጠማቸው ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
በደቡባዊ ሊቢያ በምትገኘው ሴብሃ ከተማ ለፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር በዕጩነት የቀረቡት የ49 አመቱ ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ወንጀሎችን በመፈጸማቸው ጉዳዩ ተጣርቶ ብያኔ እስኪሰጥ ድረስ ከምርጫው ይታገዱ ሲል የአገሪቱ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ለምርጫ ኮሚሽን አቤቱታ እንዳቀረበባቸው ነው ዘገባው የገለጸው፡፡
አቃቤ ህግ በሰብዓዊ መብቶች ጥሰት በአለማቀፉ የወንጀለኞች ፍርድ ቤት ከሚፈለጉት የጋዳፊ ልጅ በተጨማሪም በፕሬዚዳንትነት ሊወዳደሩ የተዘጋጁትና በአሰቃቂ ወንጀሎች የሚጠረጠሩት የምስራቃዊ ሊቢያ አማጺ ጦር አዛዥ የነበሩት ጄኔራል ካሊፋ ሃፍታርም ከምርጫው እንዲታገዱ መጠየቁን ዘገባው አመልክቷል፡፡
አባቱ ሙአመር ጋዳፊ በ2011 በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን ተከትሎ በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ውሎ ከስድስት አመታት እስር በኋላ የሞት ፍርድ የተላለፈበትና ፍርዱ ተፈጻሚ ሳይሆን የቀረው ሳይፍ አል ኢስላም ጋዳፊ፣ ከሰሞኑ በፕሬዚዳንትነት እንደሚወዳደር በይፋ ማስታወቁ በጎም መጥፎም ምላሽ እንዳገኘ ዘገባው ገልጧል፡፡
ከጋዳፊ ሞት ማግስት ጀምሮ በጊዜያዊ መንግስት ስር ሆና ወደከፋ የእርስ በርስ ግጭትና ጦርነት ውስጥ የገባችው ሊቢያ፣ በቀጣዩ ታህሳስ ወር ከቀውስ ያወጣታል ተብሎ ተስፋ የተጣለበትን ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ለማድረግ በዝግጅት ላይ ትገኛለች፡፡
በሌላ የምርጫ ዜና ደግሞ፣ የፊሊፒንሱ ፕሬዚዳንት ሮድሪጎ ዱሬቴ በመጪው አመት በሚካሄደው የአገሪቱ ምርጫ በምክትል ፕሬዚዳንትነት ከምትወዳደረው ልጃቸው ሳራ ዱሬቴ ጋር ላለመፎካከር ሲሉ በምርጫው እንደማይወዳደሩ በይፋ ማስታወቃቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
ዱሬቴ ምንም እንኳን በአገሪቱ ህገመንግስት መሰረት ለፕሬዚዳንትነት መወዳደር ባይችሉም በምክትል ፕሬዚዳንትነት ለመወዳደር አስበው የነበረ ቢሆንም ልጃቸውን ላለመጋፋት ሲሉ ሃሳባቸውን መሰረዛቸውን የጠቆመው ዘገባው፤ ሰውዬው ከወራት በፊት ባደረጉት ንግግር  ከፖለቲካው ራሳቸውን እንደሚያገልሉ አስታውቀው  እንደነበርም አስታውሷል፡፡

    አጠቃላዩ የአለማችን ሃብት 514 ትሪሊዮን ዶላር ደርሷል

           የአለማችን አጠቃላይ ሃብት ከ20 አመታት በፊት ከነበረበት 156 ትሪሊዮን ዶላር በሶስት እጥፍ ያህል በማደግ በ2020 የፈረንጆች አመት 514 ትሪሊዮን ዶላር መድረሱንና ቻይና አሜሪካን በመብለጥ ቁጥር አንድ የአለማችን ሃብታም አገር ለመሆን መብቃቷን ብሉምበርግ ዘግቧል፡፡
ታዋቂው የጥናት ተቋም ማካንሲ ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ዘገባው እንዳለው፣ ከ20 አመታት በፊት አጠቃላይ ሃብቷ 7 ትሪሊዮን ዶላር ብቻ የነበረው ቻይና ኢኮኖሚዋን በከፍተኛ ፍጥነት በማሳደግ በ2020 አጠቃላይ ሃብቷን 120 ትሪሊዮን ዶላር በማድረሷ አሜሪካን በመብለጥ ቁጥር አንድ የአለማችን ባለጸጋ አገር ለመሆን በቅታለች፡፡
አሜሪካ በ20 አመታት ውስጥ አጠቃላይ ሃብቷን በሁለት እጥፍ ያህል በማሳደግ 90 ትሪሊዮን ዶላር ብታደርስም፣ የአንደኝነት ደረጃዋን ለቻይና ለቅቃ ወደ ሁለተኛነት ዝቅ ማለቷን ነው ዘገባው ያመለከተው፡፡   
ከአጠቃላዩ የአለማችን ሃብት 68 በመቶውን የሚይዘው የሪልእስቴት ዘርፍ መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፤ በአለማቀፍ ደረጃ የሃብት ክፍፍል ሚዛናዊ አለመሆኑንና በቻይናም ሆነ በአሜሪካ ከአጠቃላዩ አገራዊ ሃብት 67 በመቶ ያህሉን የያዙት 10 በመቶ የሚሆኑት የአገራቱ ባለጸጋ ቤተሰቦች እንደሆኑም አመልክቷል፡፡

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ልጅ ሁልጊዜ መኝታ ቤቱን ይዘጋና ይፀልያል፡፡
 “አምላኬ ሆይ ያባቴን የንጉሱን መንግስት ወራሽ እሆን ዘንድ እባክህ ያረጀውን አባቴን በግዜ ከዚህ አለም አሰናብትልኝ” ይላል። ይህንን የልጁን ፀሎት የሰማው አባት፤ አንድ ቀን በጨለማ መልዕክተኛ መላዕክት ተመስሎ፤ “ወጣት ሆይ፤ ፀሎትህ ተሰምቶልሀል፤ አባትህ ከእንግዲህ በህይወት የሚቆየው ጥቂት ጊዜ ነው” አለው። ከዚያን ቀን ጀምሮ አባት የታመመ መስሎ ተኛ። በግራም በቀኝም ልጁ ላይ ጠላቶች ተነሱበት። መንግስቱንም ለመገልበጥ ያሴሩ ጀመር። ልጅ ጭንቅ በጭንቅ ሆነ። አምላኩንም ይማጠን ገባ፡- “አምላኬ ሆይ፤ ከውስጥም ከውጭም ተከበብኩ፤ ምን ባደርግ ይበጀኛል?”
አምላክም እንዲህ አለው ወደ አባትህ ዘንድ ሂድምክርንም ጠይቀው፤ መዳኛህ የርሱ ምክር ነው፡፡
ልጅ እየሮጠ ወደ  አባቱ ሄደ።
 “አባቴም ክርህን እሻለሁ” አለው። አባትም “በመጨረሻ ወደ እኔ መጣህ፤ አሁንም አልረፈደም የምልህን አድርግ” ብሎ ጀመረ።
በመከራ ሰአት የቅርብ ሰው እንደሚያስፈልግህ አትርሳ፤ ከቶውንም ለውርስ ብለህ ያባትህን ሞት አትመኝ፤ ተጣጥረህ በግንባርህ ወዝ ብላ እንጂ ባቋራጭ መንገድ ለመበልፀግ አትሞክር፤ አባትህ መመኪያህ ነው፤ ማዕረግህ ነው፤ ማስፈራሪያህ ነው አባትህ የኋላ ታሪክ ያለው ስለሆነ ባላንጣዎች ሁሉ አንተን ባለታሪክ አድርገው ያዩሀል፣ ይፈሩሀል፤ ድንበርህን አይነኩም ጠላትህን አትናቅ፤ በራስህ ተማምነህ በራስህ ቆመህ አገርህን በትክክል እንድትመራ፤ የሚያደርግህ ያ ብቻ ነው፡፡
እንደውነቱ ከሆነ ዋነኛው የታላቅነታችን ምልክት አበው የሚሉንን ማዳመጣችን ነው። አገር የምትድነው ትላንትናዋን መሰረቷን አጥብቃ ይዛ ስተትጓዝ ነው። ህዝብ ነገውን የሚያውቀውና አምኖ የሚራመደው ታሪኩን ሲገነዘብ ነው፤ ወዴት እንደሚሄድ የማያውቅ ህዝብ፣ ዳፍተኝነት ያጠቀቃዋል፡፡
ተስፋ ለመቀርቀብ እንቅፋት ይበዛበታል። ስለዚህም በምንም መልኩ ቢሆን ወዴት እንደሚሄድ   ማወቅ ግዴታ ነው። መንግስት ይለዋወጣል እንጂ ሕዝብ አይለዋወጥም፡፡ ከውድቀቱ የሚማር ብቻ ነው የብልህ መንግስት። ልጆቹም የተማሩ የበቁና የላቁ የሚሆኑት፣ ለጥበብ ቅድሚያ ሲሰጡ ነው፡፡
ጥበብን ያልያዙ ልጆች እድገታቸው የቀጨጨ ይሆናል፡፡ በምንም አይነት ያባታቸውን ማንነት ያልያዙና ያላበለፀጉ ልጆች ለመበርገግ ቅርብ ናቸው። ስለዚህ ፅናትም ቅናትም እንዲኖራቸው ማድረግ ተገቢ ነው፡፡
ያለበለዚያ “አጓጉል ትውልድ ያባቱን መቃብር ይንድ” የሚለው ብሂል ይከሰታል፡፡ ስለዚህ ዛሬ ላይ ቆመን ነገን እናስብ ነገ ላይ እናተኩር፤ ለማደግ ቅርብ የምንሆነው ስለ ነገ ስናውቅ ነውና!


Page 11 of 573