
Administrator
መንግስት ከኦነግ ሸኔ ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ግልጽ እንዲያደርግ ፓርቲዎች ጠየቁ
መንግሥት በጃል ሰኚ ነጋሳ ከሚመራው የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ጋር የተፈራረመውን ስምምነት ለሕዝብ ግልጽ እንዲያደርግ ፓርቲዎች ጠየቁ፡፡ ፓርቲዎቹ በጋራ ባወጡት መግለጫ፤ “በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የዘለቀው ተኩስ በሰላም ስምምነት የመጣ ሳይሆን፤ ሆን ተብሎ የሕዝብን ሥነ ልቡና ለመስለብና ለማስፈራራት የተደረገ ነው” ብለዋል።
መኢአድ፣ ኢሕአፓ፣ አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ እና እናት ፓርቲ በጋራ መግለጫቸው ላይ በሰጡት ማብራሪያ ከዚህ ቀደም የመንግስት ከፍተኛ አመራሮችና ኦነግ በፈጸሙት ግልጽነት የጎደለው ስምምነት ሳቢያ፣ ከመንግስት በኩል ቃል የተገባለት እንዳልተፈጸመ የገለጸው የኦነግ አንደኛው ክንፍ፣ ተመልሶ ጫካ መግባቱን አውስተዋል። ይህን ተከትሎም፣ በአገር ላይ በተለይም በኦሮሚያ ክልል አለመረጋጋት ሰፍኖ ለዓመታት መዝለቁን አመልክተዋል።
ከሰሞኑ መንግስት “ኦነግ ሸኔ” በማለት ከሚጠራው እና በጃል ሰኚ ነጋሳ የኦሮሞ ነጻነት ጦር አንደኛው ወገን ጋር የሰላም ስምምነት መፈረሙን ያስታወቁት ፓርቲዎቹ፣ ስምምነቱን “መጥፎ ሰላም የለም” በማለት መቀበላቸውን በመግለጫቸው ላይ አትተዋል። ስምምነቱን ተከትሎ በአዲስ አበባ በተለያዩ አካባቢዎች ለሦስት ቀናት የዘለቀ ተኩስ ሲሰማ መቆየቱን በመግለጽ፤ “በተኩሱም እስከ አሁን አንዲት እናት በጥይት ተመትተው ሕይወታቸው ማለፉን አረጋግጠናል።” ብለዋል።
የሰላም ስምምነቱ ጥርጣሬ እንዳጫረባቸው የጠቆሙት ፓርቲዎቹ፤“ጥርጣሬያችን የሚነሳው ከስምምነቱ ግልጸኝነት ማጣት ብቻ ሳይሆን፤ ከእንዲህ ዓይነት ክስተቶች ጭምር ነው።” ብለዋል። “ስምምነቱ መሳሪያ ማውረድን አይጨምርም ወይ?” ሲሉ የሚጠይቁት ፓርቲዎቹ፤ በሂደቱ ዙሪያ የግልጽነት አለመኖርና የሰላሙ ዘላቂነት በእጅጉ እንደሚያሳስባቸው ተናግረዋል፡፡
የሰላም ስምምነቱ ሂደትና ዝርዝር ነጥቦች ለሕዝብ ይፋ እንዲደረጉ የጠየቁት አራቱ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ “በአዲስ አበባ የተለያዩ አካባቢዎች የዘለቀው ተኩስ በሰላም ስምምነት የመጣ ሳይሆን ሆን ተብሎ የሕዝብን ስነ ልቡና ለመስለብና ለማስፈራራት የተደረገ ነው” በማለት አስረድተዋል። በተኩሱ ምክንያት መገናኛ አካባቢ ለተገደሉት እናት መንግስት “ሃላፊነት ወስዶ” ቢያንስ ቤተሰባቸውን ይፋዊ ይቅርታ እንዲጠይቅና ተገቢውን ካሳ እንዲከፍል ጠይቀዋል።
በተያያዘ ዜና፣ ኢዜማ የኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት ከታጠቁ ሃይሎች ጋር የደረሰበትን የሰላም ስምምነት ቅርጽና ይዘት ለሕዝብ ግልጽ እንዲያደርግ ኢዜማ ባለፈው ሰኞ ህዳር 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ጠይቋል። “ታጣቂዎቹ ወደ ከተማ ሲገቡ በተለያዩ ቦታዎች ተኩስ ማሰማታቸው በንጹሃን ዜጎች ላይ ከፍተኛ ስጋትና የስነ ልቦና ጫና የሚያሳድር፣ አግባብነት የሌለው ተግባር ነው“ ሲል ፓርቲው ኮንኖታል።
በሁሉም ቦታዎች ተኩስ እንዲቆምና መንግስት ክስተቱን አጣርቶ ለሕዝብ እንዲያሳውቅ የጠየቀው ኢዜማ፤ወደ ከተማም ሆነ ወደ ተሃድሶ ስልጠና የሚገቡ ታጣቂዎች ትጥቃቸውን ለጸጥታ አካላት አስረክበው ሊሆን ይገባል” ብሏል፤ በመግለጫው፡፡
በርካታ ኤርትራውያን ኮንትሮባንድን ጨምሮ በሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት መሰማራታቸው
በርካታ ኤርትራውያን ስደተኞች የኮንትሮባንድ ንግድን ጨምሮ በሌሎች ሕገ ወጥ ተግባራት መሰማራታቸው ተነግሯል። የኢሚግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት እንደገለጸው፣ ስደተኞችን ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማስገባትና ለመመዝገብ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም፣ ተመዝግበው ወደ ህጋዊ ስርዓቱ የገቡ ግን በጣም ጥቂት ናቸው ብሏል።
አገልግሎቱ ትናንት ታህሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም. በሰጠው ማብራሪያ፣ ከኤርትራ ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ ኤርትራዊያን ለ9ዐ ቀናት ያለቪዛ ክፍያ በቀን ማህተም ገብተው እንዲቆዩ ማድረጉን አውስቶ፣ “በሁለቱም ህዝቦች ያለው ግንኙነትና ወንድማማችነት ለማጠናከር ምን ያህል ቁርጠኛ አቋም እንዳለው ለመገንዘብ ይቻላል” ብሏል። አያይዞም፣ በርካታ ኤርትራውያን በሕገ ወጥ መንገድ ወደ አገር ውስጥ በመግባትና በሕጋዊ መንገድ ገብተው ከተፈቀደላቸው የጊዜ ገደብ በላይ በመቆየት በሕገ ወጥ መንገድ እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙ አመልክቷል።
ተቋሙ ኤርትራውያኑን ወደ ሕጋዊ መንገድ ለማስገባትና ለመመዝገብ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢያደርግም፣ ተመዝግበው ወደ ህጋዊ ስርዓቱ የገቡ ግን “በጣም ጥቂት ናቸው” ብሏል። “በርካታ የኤርትራዊ ዜግነት ያላቸው ዘመድ ለመጠየቅ በማስመስል ከዱባይ፣ ከኤርትራና ከኡጋንዳ በመመላለስ የተለያዩ ሸቀጣ ሸቀጦች በሻንጣ በማስገባትና በማስወጣት የኮንትሮባንድና ሌሎች ህገወጥ ተግባራት ሲያከናውኑ ተገኝቷል” ሲልም አብራርቷል።
ኤርትራውያኑ በተለያዩ አገራት ከሚገኙ ሌሎች ሕገ ወጥ ደላሎች ጋር በመተሳሰር በርካታ ስደተኞችን በሕገ ወጥ መንገድ ሲያዘዋውሩ መገኘታቸውን ተቋሙ አስታውቋል። ለተለያዩ ሕገ ወጥ ተግባራት የሚያገለገሉ ሐሰተኛና የተጭበረበሩ የጉዞና የይለፍ ሰነዶች፣ ማህተሞች፣ የባንክ ሂሳብ ደብተሮች በማዘጋጀትና በመጠቀም ህገ-ወጥ ተግባራት ሲፈጽሙ፣ የተለያዩ ሐሰተኛ ሰነድና ማንነት በመጠቀም ህገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውር ሲያከናውኑ እና ከህግ ውጭ ሰነዶችን ሲጠቀሙ መገኘታቸውንም ተቋሙ በማብራሪያው ላይ ገልጿል።
በመሆኑም ማንኛውም የውጭ አገር ዜጋ የአገሪቱን ሕግ ተላልፎ ከተገኘ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆን የጠቀሰው የኢሚግሬሽን እና ዜግነት አገልግሎት፣ በተለያዩ መገናኛ ብዙሃን አማካይነት በኤርትራውያን ስደተኞች ላይ ያለአግባብ ክፍያ እንደሚጠየቁና ዲፖርቴሸን እንደሚፈጸምባቸው ተደርጎ መዘገቡ ከእውነት የራቀ መሆኑን ነው ያመለከተው።
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ አደራዳሪነት ስምምነት ላይ ደረሱ
• ለአዲስ የትብብር ምዕራፍ ትልቅ እርምጃ ነው ተብሏል
ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን አደራዳሪነት፣ ከስምምነት ላይ መድረሳቸው ተገለጸ፡፡ ሁለቱ አገራት በትላንትናው ዕለት በአንካራ ለሦስተኛ ጊዜ ባደረጉት ድርድር ለአንድ ዓመት የዘለቀ ዲፕሎማሲያዊ ፍጥጫቸውን በስምምነት ፈትተዋል ነው የተባለው፡፡
ትላንት ረቡዕ ታህሳስ 2 ቀን 2017 ዓ.ም፣ ከ8 ሰዓታት ውይይት በኋላ የተደረሰው ስምምነት፤ በሁለቱ የአፍሪካ ቀንድ ሀገራት መካከል ዳግም ሰላምና ትብብር እንዲሰፍን መንገድ እንደሚከፈት ይጠበቃል።
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድና የሶማሊያው ፕሬዚዳንት ሀሰን ሼክ ማሃሙድ በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው የሦስተኛው ዙር ድርድር አንካራ የገቡ ሲሆን፤ ባለፈው ሀምሌና ጥቅምት ወር የተደረጉ የድርድር ጥረቶች ውጤት አለማምጣታቸው ይታወቃል፡፡
የቱርኩ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋን ከድርድሩ በኋላ በጋራ በሰጡት መግለጫ፤ ስምምነቱን ለአዲስ የትብብር ምዕራፍ ትልቅ እርምጃ ነው ብለውታል፡፡
"ይህ ስምምነት በጋራ መግባባትና በጋራ ግቦች ላይ የተመሰረተ አዲስ ዘመን መጀመሩን ያመለክታል" ያሉት ኤርዶጋን፤ ስምምነቱ የሶማሊያን ሉዓላዊነት በማክበር፣ የኢትዮጵያን አሳሳቢ የባህር በር ፍላጎት እንደሚፈታ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።
በጋዜጣዊ መግለጫው ወቅት ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፣ ኢትዮጵያ እርግጠኛና አስተማማኝ የባህር በር እንደምትፈልግ አፅንኦት የሰጡ ሲሆን፤ ስምምነቱን፣ የውጥረት ዓመት ወደ አዲስ አጋርነት የተቀየረበት ነው ሲሉ ገልጸውታል።
"ይህ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለጎረቤቶቻችንና በአጠቃላይ ለአካባቢው ሁሉ የሚጠቅም ነው" ሲሉም ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ፕሬዚዳንት መሀሙድ በበኩላቸው፤ ስምምነቱ ለልዩነቶቻቸው መፍትሔ የሰጠ ሲሉ በማወደስ፣ የሶማሊያን የትብብር ቁርጠኝነት አረጋግጠዋል፡፡ “ወደፊት የጋራ ብልጽግናን ለመገንባት ከኢትዮጵያ አመራርና ህዝብ ጋር ለመስራት ዝግጁ ነን” ብለዋል፤ፕሬዚዳንቱ፡፡
ለዚህ ታሪካዊ ስምምነት የቱርክ የሽምግልና ሚና ወሳኝ ነበር ተብሏል፡፡ ኤርዶጋን በግል የሦስቱንም ዙር ድርድሮች ተከታትለዋል፡፡ የእርሳቸው ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች በአፍሪካ ቀንድ ውስጥ እያደገ የመጣውን የቱርክን ተፅእኖ የሚያንፀባርቅ ሲሆን፤ አገሪቱ በአካባቢው መረጋጋትን በማስፈን ረገድ ቁልፍ ሚና እየተጫወተች ነው፡፡
የከፍተኛ ትምህርት ኤግዚቢሽን በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ ለ2 ቀናት ተካሄደ
• 7ሺ የሚደርሱ የዩኒቨርሲቲና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ጎብኝተውታል
የአውሮፓ ህብረት ከኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ያዘጋጀው የ2017 ዓ.ም የአውሮፓ የከፍተኛ ትምህርት ኤግዚቢሽን፣ ባለፈው ሰኞ ህዳር 30 እና ታህሳስ 1 ቀን 2017 ዓ.ም በኮተቤ ዩኒቨርሲቲ የተካሄሰ ሲሆን፤ 7ሺ የሚደርሱ የሁለተኛ ደረጃና የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች እንደጎበኙት አዘጋጆቹ ገለጹ፡፡
በኤግዚቢሽኑ መክፈቻ ላይ የአውሮፓ ህብረት የኢትዮጵያ አምባሳደር ሶፊ ፉሮም ኤምስበርገር፣ የኮተቤ የትምህርት ዩኒቨርሲቲ ፕሬዚዳንት ዶ/ር ብርሃነ መስቀል ጠና፣ የአውሮፓ ህብረት አምባሳደሮችና ከፍተኛ የመንግሥት ሃላፊዎች ተገኝተው እንደነበር ለማወቅ ተችሏል፡፡
ለሁለት ቀናት በተካሄደው የከፍተኛ ትምህርት ኤግዚቢሽን፤ ቤልጂየም፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ሀንጋሪ፣ስፔይንና ፖርቹጋልን ጨምሮ አስር የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራትና ሦስት የአውሮፓ የትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የሚሰጧቸን የከፍተኛ ትምህርት ዕድሎች ለጎብኚዎች አስተዋውቋል፡፡
የትምህርት ኤግዚቢሽኑ ዓላማ የአውሮፓ አባል አገራትና የከፍተኛ ትምህርት ተቋማቶቻቸው ለኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ያዘጋጇቸውንና የሚሰጧቸውን የነጻ ትምህርት ዕድሎች (ስኮላርሺፕ) ማስተዋወቅና ግንዛቤ መስጠት ነው ተብሏል፡፡ በዚህም ረገድ የዘንድሮ ኤግዚቢሽን የታለመለትን ግብ መምቱን አዘጋጆቹ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
የአውሮፓ የከፍተኛ ትምህርት በአውሮፓ ህብረት በአዲስ አበባ ሲዘጋጅ የዘንድሮ ለሁለተኛ ጊዜ ሲሆን፤የመጀመሪያው ኤግዚቢሽን የዛሬ 5 ዓመት፣ በ2012 ዓ.ም በስካይላይት ሆቴል ነበር የተካሄደው፡፡
የአውሮፓ ህብረት፤ የኢትዮጵያን ትምህርት ከሚደግፉ የልማት አጋሮች ግንባር ቀደሙ ሲሆን፤በያዝነው የ2017 ዓ.ም ለ57 ኢትዮጵያውያን ተማሪዎች ሙሉ የማስተርስ ዲግሪ የኤራስመብ ሙንደስ ነጻ የትምህርት ዕድል መስጠቱ ይታወቃል፡
የጃዋር መሃመድ “አልጸጸትም” በመጪው ሐሙስ ይመረቃል
የቀድሞው ታዋቂ አክቲቪስትና ፖለቲከኛ ጃዋር መሃመድ የጻፈው፣ “አልጸጸትም” የተሰኘ ግለ ታሪክ (Memoir) መጽሐፍ በመጪው ሳምንት ሐሙስ ታህሳስ 10 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በኬንያ ናይሮቢ ይመረቃል፡፡ መጽሐፉ በአማርኛና ኦሮሚፋ ቋንቋዎች ነው የተዘጋጀው፡፡
ጃዋር ሞሃመድ የታዋቂው የኦሮምኛ አቀንቃኝ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያን ተከትሎ፣ ለእስር መዳረጉ የሚታወስ ሲሆን፤ ከእስር በተፈታ ማግስት ኢትዮጵያን ለቅቆ በመውጣት፣ መኖርያውን በኬንያ ናይሮቢ ማድረጉ ይታወቃል፡፡
“ተድባብ” ታሪካዊ ልብ-ወለድ መፅሐፍ ለገበያ ቀረበ
በአጭር ጊዜ ውስጥ በሥራዎቿ ተወዳጅነትን ባተረፈችው ደራሲ ህይወት ተፈራ የተፃፈው “ተድባብ” የተሰኘ ታሪካዊ ልብ ወለድ መፅሐፍ ከሰሞኑ ለገበያ ቀረበ። በዋልያ መፃሕፍት የታተመው ይህ ታሪካዊ ልብ-ወለድ፤ ጭብጡን በአድዋ ጦርነትና ድል ዙሪያ ያደረገ ነው፡፡
ደራሲዋ ከአንባቢያን ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ የተዋወቀችው “ማማ በሰማይ” በሚል ወደ አማርኛ በተተረጎመው “Tower in the sky” በተሰኘ የበኩር መጽሐፏ ነው፡፡ ለጥቃም “ሃሰሳ” በሚል የተተረጎመ “Mine twin” እና “ምንትዋብ” የተሰኙ ታሪካዊ ልብወለዶችን ለአንባቢያን አድርሳለች፡፡ ከሰሞኑ ለንባብ የበቃው “ተድባብ” ታሪካዊ ልብ ወለድ ለደራሲዋ አራተኛ ሥራዋ መሆኑ ነው።
“ተድባብ” ለደራሲ ህይወት ተፈራ አራተኛ ሥራዋ ነው
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ልትሸጥ ነው
ኢትዮጵያ ለደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መሆኗን የውሃና ኢነርጂ ሚኒስትር አቶ ሀብታሙ ኢተፋ ትናንት ማምሻውን አስታውቀዋል።
ኢትዮጵያ ላለፉት ዓመታት ለሱዳን፣ኬንያና ጅቡቲ የኤሌክትሪክ ኃይል ስትሸጥ የቆየች ሲሆን፤ አሁን ደግሞ ለደቡብ ሱዳንና ታንዛኒያ ለመሸጥ በዝግጅት ላይ መሆኗ ተነግሯል፡፡
ኢትዮጵያ፣ ኬንያንና ታንዛኒያን የሚያገናኘውን 400 ኪሎ ዋት የኤሌክትሪክ ማስተላለፊያ መስመር በቅርቡ ባጠናቀቀችው ኬንያ በኩል፣ ኢትዮጵያ ለታንዛኒያ የኤሌክትሪክ ኃይል እንደምታቀርብ ይጠበቃል፡፡
የምስራቅ አፍሪካ ፓወር ፑል (ኢኤፒፒ) ስብሰባ ከትናንት ጀምሮ በኬንያ ሞምባሳ እየተካሄደ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ተወካይ የኃይል አቅርቦቱን ስምምነት ለማጠናቀቅ ከታንዛኒያና ኬንያ አቻዎቻቸው ጋር እየተወያዩ መሆኑ ታውቋል፡፡
ኢኤፒፒ በምስራቅ አፍሪካ በሚገኙ 11 ሀገራት የኤሌክትሪክ ሃይሎቻቸውን ለማገናኘት የተቋቋመ ሲሆን፤ ብሩንዲ፣ የኮንጎ ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ሱዳን፣ ታንዛኒያ፣ ሊቢያ፣ ጅቡቲና ኡጋንዳ የኢኤፒፒ አባል ናቸው።
አማራ ባንክ አጠቃላይ ሃብቱ ከ35 ቢ. ብር መላቁን አስታወቀ
አማራ ባንክ የባለ አክስዮኖች 3ኛ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በሚሊኒየም አዳራሽ ያካሄደ ሲሆን፤ የባንኩ አጠቃላይ ሀብት 35.2 ቢሊዮን ብር መድረሱን አስታውቋል፡፡
አማራ ባንክ ባለፉት ዓመታት ተግዳሮቶች ቢገጥሙትም፣ ዘንድሮ 669 ሚሊዮን ብር ትርፍ ማግኘቱን ይፋ አድርጓል፡፡
ባንኩ ለደንበኞቹ የሚሰጠውን የብድር መጠን 33 በመቶ በማሳደግ 20 ቢሊዮን ብር ገደማ ማድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፤ አጠቃላይ የተቀማጭ ገንዘብ መጠኑ 26 በመቶ አድጓል፡፡ የመደበኛና ከወለድ ነፃ የባንክ አገልግሎት በድምሩ 25 ቢሊዮን ብር መድረሱንም አመልክቷል፡፡
በተጨማሪም የባንኩ ዓመታዊ ገቢ 146 በመቶ ዕድገት በማሳየት፣ 4.4 ቢሊዮን ብር ገቢ አስመዝግቧል።
ከ1.8 ሚሊዮን በላይ ደንበኞችና ወደ 600 ሺ የሚጠጉ የሞባይል ባንኪንግ ተጠቃሚዎች ያሉት አማራ ባንክ፤ የደንበኞቹ ብዛት እያደገ መምጣቱን አስታውቋል።
በተደራሽነት ረገድም በበጀት አመቱ 143 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመላ አገሪቱ በመክፈት አመርቂ እድገት ያስመዘገበ ሲሆን፤ አጠቃላይ የቅርንጫፎቹን ቁጥርም 310 አድርሷል፡፡
”አዲስ ገና 2017 ኤክስፖ“ የፊታችን አርብ ይከፈታል
• ኤክስፖው በኤግዚቢሽን ማዕከልና በመስቀል አደባባይ ይካሄዳል
• አዘጋጁ ጨረታውን ያሸነፈው በ80ሚ.600ሺ ብር ነው
• መኖሪያ ቤት የሚያሸልም የሎተሪ ዕጣ ተዘጋጅቷል
ሮበስት ቢዝነስ ግሩፕና ሠላሳ መልቲ ሚዲያ ከንግድና ቀጠናዊ ትስስር ሚኒስቴር ጋር በመተባበር ያዘጋጁት ”አዲስ ገና 2017 ኤክስፖ“፤ የፊታችን አርብ ታሕሳስ 4 ቀን 2017 ዓ.ም በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና በመስቀል አደባባይ ይከፈታል፡፡
የገና ኤክስፖን በተመለከተ አዘጋጆቹ በዛሬው ዕለት ረፋዱ ላይ በስካይላይት ሆቴል ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫው ላይ እንደተነገረው፤ የዘንድሮው የገና ኤክስፖ ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከልና በመስቀል አደባባይ በጥምረት ይካሄዳል፡፡
በገና ኤክስፖው ላይ ከ500 በላይ የሚሆኑ የአገር ውስጥ አምራች ፋብሪካዎች፣ የኢንዱስትሪ መንደሮች፣ ትላልቅ አስመጪዎች፣ ማህበራትና ዩኒዬኖች፣ የሪል እስቴት አልሚዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የኤሌክትሪክ መኪና አቅራቢዎችና ከስምንት የተለያዩ አገራት የተውጣጡ የውጭ ኩባንያዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
የበዓል ኤግዚቢሽኖች የሚዘጋጁበት አንዱ ዓላማ ገበያውን ለማረጋገት እንደሆነ ያስረዱት አዘጋጆቹ፤ በአንድ የ20 ሊትር ዘይት ላይ እስከ 400 ብር ቅናሽ ተደርጎ ለሸማቹ እንደሚቀርብ ጠቁመዋል፡፡ ሌሎች የዕለት ተዕለት ፍጆታዎችም በፋብሪካ ዋጋ ለሽያጭ እንደሚቀርቡ ተነግሯል፡፡
እስከ ታሕሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም ለ25 ቀናት ክፍት ሆኖ በሚዘልቀው የገና ኤክስፖ የተለያዩ መዝናኛዎች እንደሚኖሩ የተገለጸ ሲሆን፤ 100 ተወዳጅ ድምጻውያን ከአምስት የሙዚቃ ባንዶች ጋር ታዳሚዎችን እንደሚያዝናኑ ታውቋል፡፡
የተለያዩ የህጻናት መጫዎቻዎችን ያካተተ “የህጻናት ዓለም” መዘጋጀቱም በመግለጫው ላይ ተጠቁሟል፡፡ ለልጆች በተዘጋጀው የጌም ዞን፤ የዳይኖሰሮች ትርኢት፣ የግመልና ፈረስ ሽርሽር፣ የገና ጨዋታና የህጻናት የገና ስጦታዎች እንደሚኖሩም ታውቋል፡፡
በዚህ ኤክስፖ ላይ የፌስቲቫል ድባብ ለመፍጠር የተለያዩ ጥረቶች መደረጋቸውንም አዘጋጆቹ አብራርተዋል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ አንዱ ትልቁ የገና ዛፍ ሲሆን፤ ሌላው 2017 ስኒዎችን የሚይዝ ትልቅ ረከቦት ነው ተብሏል፡፡
”አዲስ ገና 2017 ኤክስፖ“ን ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ህዝብ ይጎበኘዋል ተብሎ የሚጠበቅ ሲሆን፤ የመግቢያው ዋጋ 100 ብር እና 200 ብር መሆኑን አዘጋጆቹ ተናግረዋል፡፡
በዘንድሮው የገና ኤክስፖ ከብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር ጋር በመተባበር የመኖሪያ ቤት የሚያሸልም የሎተሪ ዕጣ መዘጋጀቱም ታውቋል፡፡
ሮበስት ቢዝነስ ግሩፕ የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ለገና በዓል ያወጣውን ጨረታ ያሸነፈው በ80 ሚሊዮን 600 ሺ ብር ሲሆን፤ ይህም በማዕከሉ ታሪክ ከፍተኛው የጨረታ ዋጋ መሆኑ ታውቋል፡፡
የአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል ሃላፊዎች በመግለጫው ላይ በሰጡት ማብራሪያ፤ ማዕከሉ ለገና በዓል ባወጣው ግልጽ ጨረታ ከ5 በላይ ተወዳዳሪዎች የተሳተፉ ሲሆን፤ በመጨረሻም ሮበስት ቢዝነስ ግሩፕ ጨረታውን በከፍተኛ ዋጋ አሸንፏል፡፡
“አንድም ከቀበሮ፤ አንድም ከአንበሳ ተማር” አንበሳ ከወጥመድ ለማምለጥ አይችልም። ቀበሮ ደግሞ ከተኩላ ለማምለጥ አትችልም። ወጥመዱን ለማየት ቀበሮ ሁን። ተኩላ እንዳይጠጋህ አንበሳ ሁን።
ማኪያቬሊ (ጣሊያናዊ የታሪክ ባለሙያ፣ የሀገር መሪ፣ እና የፖለቲካ ፍልስፍና አዋቂ)
አንድ ጊዜ እንዲህ ሆነ።
የዱር አራዊት ንጉሥ አንበሳ ታሞ አልጋ ላይ ዋለ። ጠያቂና አስታማሚ አጣ። ከህመሙም በላይ ጠያቂ ማጣቱ በጠናበት ጊዜ፣ ለአሣማና ለዶሮ በደብዳቤ መልዕክት ላከ። እንዲህ ብሎ፡-
“ውድ አሳማ!
ውዲት ዶሮ!
እነሆ ካመመኝና አልጋ ከዋልኩ አያሌ ወራት ሆኑኝ። እህል ከቀመስኩ ደግሞ ሣምንት አለፈኝ። ዞር ዞር ብዬ የሚበላ ፈልጌ እንኳ አፌ እንዳላረግ ህመምተኛ ሆንኩ። አቅሜም ደከመ። የሰው ልጆች አንበሳ ሲያረጅ የዝምብ መጫወቻ ይሆናል፤ የሚሉት የዋዛ አነጋገር አይደለም። ዱሮ የሚሰግዱልኝ፣ የሚሽቆጠቆጡልኝና ከሥሬም የማይጠፉ ብዙ አውሬዎች ዛሬ አንዳቸውም አጠገቤ ያሉ አይመስሉም። አንዳንዱ ያለወትሮው ዝምተኛ ሆኗል። በአንፃሩ አንዳንዱ፣ ምንም ፍሬ ጠብ አይለውም እንጂ፤ አፍ ለቆበታል። አንዳንዱ እኔ ካልኖርኩ የማይኖር ይመስል በፍርሃት ተውጦ ተደብቆ ይተኛል። ሌላ ቀርቶ፣ አይምሬውን ክርኔን የቀመሱት፣ ሳገሣ ድራሻቸው ይጠፋ የነበሩት እነ አያ ጅቦ፣ እነ አያ ከርከሮ፣ እነ ብልጢት ጦጣ፣ ዛሬ አልጋዬ ድረስ መጥተው እንኳ ለመጠየቅ ንቀት አደረባቸው። እንዲያውም “አንበሳ ከታመመ፣ የልብ ወዳጅ ከጠመመ፣ መመለሻ የለውም” እያሉ እየረገጡ አላገጡብኝ አሉ። በዙሪያዬ የነበሩት ሁሉ “አምላክ አንተንም እኛንም እኩል ነው የፈጠረን” ማለት ጀምረዋል። ይሄ ቀን የማያልፍና፣ ከታመምኩት በሽታ ድኜ፣ ካልጋ ቀና የማልል መስሏቸው ነው። እንግዲህ የቀራችሁኝ ውድ ወዳጆች እናንተና ይህን ደብዳቤ ይዞላችሁ የመጣው ዝንጀሮ ብቻ ናችሁ። ስለዚህ አደራ ሳልሞትባችሁ ድረሱልኝ።”
ፊርማ የማይነበብ
የናንተው አንበሳ፣
የጥንቱ የጠዋቱ የዱር አራዊት ንጉሥ
አሳማና ዶሮ ደብዳቤው እንደደረሳቸው በጣም አዘኑ።
“ምን ብናደርግለት ይሻላል?” አለ አሳማ።
ዶሮም፤ “መቼም ነግ በእኔ ማለት ደግ ነው። አንድ ነገር ማድረግ አለብን”
አሳማ፤ “ግን አያ አንበሶን እንዲህ እስኪማረር ድረስ ያደረሱት እነማን ይሆኑ?”
ዶሮ፤ “ዛሬ ማን ይታመናል ብለህ ነው አሳምዬ? የልብ ወዳጅ የታለና? ያው እሱ ራሱ የጠቃቀሳቸው በጣም ቅርብ ቅርብ ያሉ ባለሟሎች እነ አያ ጅቦ፣ እነ እመት አህያ፣ እነ አቶ በቀቀን፣ እነ ጆሮ-ትላልቄ ይሆናሏ።”
አሳማ፤ “አትይኝም? ጆሮ.. ትላልቄም ጨከነበት?”
ዶሮ፤ “እየነገርኩህ! ባለንበት ዘመን፣ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ማንም አይተኛም”
አሣማ፤ “ዕውነትሽን ነው። በይ እኛም ሳይረፍድ የምንይዘውን ይዘን ሄደን እንጠይቀውና ይውጣልን”
ዶሮ፤ “እንዲህ እናድርግ። እኔ እንቁላል ላዋጣ። አንተ ደግሞ ስጋ አዋጣና ሃምበርገር ይዘንለት እንሂድ”
አሣማ፤ “በጣም ድንቅ ሃሳብ አመጣሽ። በቃ ሀምበርገር እንውሰድለት”
በዚሁ ተግባቡና ጠዋት ወደ አንበሳው ሊሄዱ ተስማምተው ተለያዩ።
ጥቂት እልፍ እንዳሉ ግን፤ አሣማ አንድ ነገር ትዝ አለውና ዶሮዋን ጠራት። ከዚያም “ስሚ አንቺ ዶሮ፤ አሁን እናዋጣ የተባባልነው፤ ሚዛናዊ መዋጮ አይደለም። እኔ ተበድያለሁ!”
ዶሮም ነገሩ ስላልገባት፤ “ለምን? እንዴት ነው ሚዛናዊ ያልሆነው?”
አሳማም፤ “አየሽ፤ አንቺ ዕንቁላሉን የምታዋጪው ወልደሽው ነው። እኔ ግን ሥጋ እምሰጠው ከገዛ አካሌ ቆርጬ ነው። ያንቺ ተሳትፎ ብቻ ነው (Participation እንዲሉ)። የእኔ ግን ጉዳዩ ውስጥ በአካል መግባት ነው (Involvment እንዲሉ)” አላት።
***
ህመም፣ ችግርና ሣንካ ሲያጋጥመን ወዳጅ አይክዳ። እንደ አረጀ አንበሳም የዝምብ መጫወቻ ከመሆን ይሰውረን። ከፍሬ-ቢስ ልፈፋ ያውጣን። በእኩልነት የማያምን “ዲሞክራት መሪ” አያጋጥመን።
በአገራችን ውስጥ ያሉ የፖለቲካ ሰዎች ሚና፣ ጉዳዩ ውስጥ የመግባት እንጂ ዕንቁላል የመጣል ተሳትፎ ብቻ እንዳይሆን የሁሉም ወገን ጥረትና ትግል ሊኖርበት ይገባል። በሀገራችን የፖለቲካ ውጣ - ውረድ ውስጥ አያሌ አንበሶች ታይተዋል። ሆኖም የአንበሳነታቸው መጠንም ሆነ አንበሳዊ ባህሪያቸው፤ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። አንዳንዱ በጭራሽ ሌላ ፍጡር አያስጠጋም። ንፁህ ነው እንኳ ቢባል። ዲ.ኤች.ሎረንስ እንዳለው ነው፡- “አንበሳን ማንም ኃይል፤ ከበግ ግልገል ጋር ሊያስተኛው አይችልም። ግልገሏ ሆዱ ውስጥ ካልገባች በስተቀር።” አንዳንዱ ደግሞ ቀን ሲጨልምበት ወይም እክል ገጥሞት ከአልጋ ሲውል በቀላሉ የሚደፈር ይሆናል። ሆራስ የተባለው የዜማና ምፀታዊ ግጥም ፀሀፊና ታዋቂ ሮማዊ (ከክርስቶስ ልደት በፊት በ65-ዓመት)፤
ታሞ ልትጠይቀው፣ ሄዳ ወደ አንበሳ
ቀን- አይታ ቀበሮ፣ ነገር ልታነሳ
እንደዚህ አለችው፣ በሰላ ወቀሳ
“ጌታው አቶ አንበሶ፤
የእግር-ጥፍር አሻራህ፣ ያስፈራኛል በጣም፤
ግን ምስሉ ይገርማል፤ መሬት ላይ ሲታተም
ወደ ራስህ ዞሮ፣ አንተኑ ሲጠቁም።
ከያዘው አቅጣጫ እንደማይመለስ፣ አሳምሬ ባቅም
የእግር- ጥፍር አሻራህ፣ ያስፈራኛል በጣም።
ከሄደበት መንገድ፣ ወደኔ ባይመጣም።”
ብሎ እንደፃፈው ነው።
አንዳንዶቹ፤ በ19ኛው ክ/ዘመን አጋማሽ የነበሩት የአርጀንቲናው ፕሬዚዳንት በአንድ ወቅት “በአሁኑ ሰዓት ሰላማዊ አብዮተኛ (Pacifist Revolutionary ማለት) አትክልት-በል አንበሳ Vegetarian Lion ማለት ነው” ብለው እንደገለጹት ዓይነት ናቸው።
በአገሬው ዐይን ሌላ፣ በአለም አቀፍ ማህበረሰብ ዐይን ሌላ፣ የሆኑም አሉ። ሩሲያዊው ደራሲ ሶልዘንስቲን እንደሚለው፤ “ለእኛ ሩሲያ ውስጥ ላለነው፤ ኮሙኒዝም የሞተ ውሻ እንደማለት ነው። ለብዙ ምዕራባውያን ግን በህይወት ያለ አንበሳ ይመስላቸዋል” ማለት መሆኑ ነው።
ሌሎች አንበሶች ደግሞ፤ ዊንስተን ቸርችል 80ኛውን የልደት በዓላቸውን ሲያከብሩ ለሁለቱም ምክር ቤቶች እንደተናገሩት፤ “አገሬ የአንበሳ ልብ አላት። እኔ ደግሞ እንደዳልጋ አንበሳ መጮህን ታድያለሁ”፤ የሚሉ ናቸው።
በኢትዮጵያ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሁሉ ያየናቸው የፖለቲካ ፓርቲም ሆነ የብዙኃን ንቅናቄ መሪዎች አንድ የጋራ ጠባይ አላቸው። ይህንን ፀባይ አፍሪካዊው የስዋሂሊኛ ተረት በደንብ ይገልጠዋል፡- “የተቆለመመ ጥፍር ያላቸው ሁሉ አንበሳ አይደሉም”።
ትላንት በተካሄደውም ሆነ ዛሬ በአገራችን እየተካሄደ ባለው ፖለቲካዊ ሂደት ውስጥ የሚጓዙ ኃይሎች ሁሉ መማርና ማወቅ ያለባቸው አንድ ቁም ነገር አለ፡-
“አንድም ከቀበሮ፤ አንድ ከአንበሳ ተማር”
አንበሳ ከወጥመድ ለማምለጥ አይችልም።
ቀበሮ ደግሞ ከተኩላ ለማምለጥ አትችልም።
ወጥመዱን ለማየት ቀበሮ ሁን።
ተኩላ እንዳይጠጋህ አንበሳ ሁን።