Administrator

Administrator


            ባለፈው ቅዳሜ ምሽት በዩክሬን ላይ በፈጸመችው ጥቃት ሃይፐርሶኒክ ሚሳኤልን ለጦርነት የተጠቀመች የመጀመሪያዋ የአለም አገር የሆነችው  ሩስያ፣ የህዝቧን ደህንነትና አገራዊ ህልውናዋን አደጋ ላይ የሚጥል የከፋ ነገር ካጋጠማት የኒውክሌር ጦር መሳሪያ ልትጠቀም እንደምትችል የአገሪቱ መንግስት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ በይፋ ያስታወቁ ሲሆን፣ የአሜሪካ የመከላከያ ሚኒስቴር መግለጫውን አደገኛ ብሎታል፡፡
የሩስያ ጦር ሃይል ባለፈው እሁድም ኪንዛል የተሰኘውንና ከደምጽ በአምስት እጥፍ ይፈጥናል የተባለውን ሃይፐር ሶኒክ ሚሳኤል በድጋሚ በማስወንጨፍ በዩክሬን የሚገኝ የነዳጅና የጦር መሳሪያ መጋዝኖችን ማውደሙ የተነገረ ሲሆን፣ ሚሳኤሉ እስከ 2 ሺህ ኪሎ ሜትር ርቀት ሊያጠቃ እንደሚችልም ተዘግቧል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ፤ #የሰላም አስከባሪ ሃይል ወደ ዩክሬን ለማስገባት መሞከር እጅግ የከፋ ጥፋት ያስከትላል; ስትል ሩሲያ የሰሜን ጦር ቃል ኪዳን ኔቶን አስጠንቅቃለች፡፡
ሩስያ ባለፈው ሰኞ በዩክሬኗ ስትራቴጂካዊ የወደብ ከተማ ማፓሪፖል የመሸጉ የዩክሬን ወታደሮች በሰላም እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቅርባ የነበረ ቢሆንም፣ ዩክሬን ግን ጥያቄውን ውድቅ በማድረግ በትግሏ መጽናቷን ሩስያም ከተማዋን በአሰቃቂ ሁኔታ መደብደብና ዶግ አመድ ማድረጓን መቀጠሏ ነው የተነገረው፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ሚኒስቴር እንደሚለው፤ የዩክሬን ወታደሮች የሩስያ ጦር በቁጥጥሩ ስር አድርጓቸው የነበሩ የአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎችን ለማስለቀቅ ስኬታማ ትግል እያደረጉ እንደሚገኙና ከመዲናዋ ኬዬቭ በ40 ማይሎች ርቃ የምትገኘውን ማካሪቭ ከተማ መልሰው መያዛቸውን ሀሙስ እለት ያስታወቀ ሲሆን የጀርመኑ ቻንስለር ኦላፍ ሹልዝ በበኩላቸው፤ የሩስያ ጦር ከዩክሬን ብርቱ መከላከልና ጥቃት እንደገጠመውና ወደፊት መግፋት እንዳልቻለ መናገራቸውን ቢቢሲ ዘግቧል፡፡
የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ከሰሞኑ ለጃፓን ፓርላማ አባላት በቪዲዮ ባደረጉት ንግግር፤ የሩስያ ጦር ቼርኖቤልን ጨምሮ በተለያዩ የኒውክሌር ማብላያ ማዕከላት ላይ ጥቃት ሊፈጽም እንደሚችልና ይህም እጅግ አደገኛ እንደሆነ በማስጠንቀቅ ጃፓን ከዩክሬን ጎን እንድትቆም ጠይቀዋል፡፡ በማሪፖል ከተማ ከ100 ሺህ በላይ ንጹሃን ዜጎች በጭንቅ ውስጥ እንደሚገኙ የዘገበው ዘ ጋርዲያን፤ ባለፈው ረቡዕ እነዚህን ዜጎች ከአደጋ ለማውጣት የሚያስችል ነጻ መስመር ለመክፈት ስምምነት ላይ መደረሱንም አመልክቷል፡፡
የሩስያ ጦር ጦርነቱን ካወጀበት ጊዜ አንስቶ 10 ሆስፒታሎችን ሙሉ ለሙሉ በድብደባ ማውደሙን የዩክሬን መንግስት ማስታወቁ የተዘገበ ሲሆን፣ ዩክሬን ከ15 ሺህ በላይ የሩስያ ወታደሮችን መግደሏንም አስታውቋል፡፡
አንድ የሩስያ ጋዜጣ በበኩሉ፤ ሩሲያ በጦርነቱ 9ሺህ 861 ወታደሮች እንደሞቱባትና 16ሺህ 153 እንደቆሰሉባት ቢዘግብም፣ የአሜሪካ የስለላ ተቋም ግን የሟቾችን ቁጥር ወደ 7ሺህ ዝቅ እንዳደረገው ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡
ከአውዳሚው ጦርነት ጋር በተያያዘ ተሰብስቦ እጅ ከማውጣት ያለፈ የረባ ነገር ሲሰራ ያልታየው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባኤ፣ ከሰሞኑም ሩስያን የሚያወግዝ መግለጫ ለማውጣት ድምጽ እንደሚሰጥ ይጠበቃል፡፡
የሁለቱን አገራት ጦርነት ለማብረድና ሰላማዊ መፍትሄ ለመሻት የተጀመረው ጥረት ይህ ነው የሚባል ውጤት ባያስገኝም፣ ችግሩን በድርድር መፍታት እጅግ አስቸጋሪ ተልዕኮ ቢሆንም በአገራቱ መካከል በየደረጃው የሚደረጉ ጥረቶች አሁንም ተጠናክረው መቀጠላቸውንና የተወሰኑ ተስፋ ሰጪ ውጤቶች መመዝገባቸውን የዩክሬኑ ፕሬዚዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪ ባለፈው ረቡዕ በቴሌግራም ቻናላቸው በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ባለፈው ማክሰኞ ሁለቱ አገራት ወደ ጦርነት ከገቡበት ጊዜ ጀምሮ የመጀመሪያውን የጦር ምርኮኞች ልውውጥ ማድረጋቸውን ቲአርቲ የዘገበ ሲሆን፣ የሩስያ ጦር አግቷቸው የነበሩትን የዩክሬኗ ሜሊቶፖል ከተማ ከንቲባ በመልቀቅ በምላሹ በዩክሬን የተማረኩ 9 ሩሲያውያን ወታደሮችን ማስመለሱን አመልክቷል፡፡
አለም በሁለቱ አገራት ጦርነት ሳቢያ ያለ ዕዳዋ ገፈት መቅመሷን ቀጥላለች፡፡ የጦርነቱ ጦስ የነዳጅ፣ የምግቦች፣ የሸቀጦችና የአገልግሎቶች ዋጋ በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡ የአለማችን ኢኮኖሚ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ካደረሰበት ጉዳት እንዳያገግምና እድገት እንዳያስመዘግብ ጦርነቱ ሰበብ ይሆንበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ አለማቀፉ የገንዘብ ተቋም አይኤምኤፍ አስታውቋል፡፡ በሁለቱ አገራት መካከል የተጀመረው ጦርነት በዚሁ ተባብሶ የሚቀጥል ከሆነ፣ በመላው አለም የሚገኙ 40 ሚሊዮን ያህል የተለያዩ አገራት ህዝቦች ለከፋ ድህነት ሊጋለጡ እንደሚችሉም ከሰሞኑ የወጣ አንድ መረጃ አመልክቷል፡፡
ሴንተር ፎር ግሎባል ዲቨሎፕመንት የተባለው ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገ ተቋም ባወጣው መግለጫ እንዳለው፣ የሁለቱ አገራት ጦርነት የምግብና የሸቀጦች ዋጋን በአለማቀፍ ደረጃ በከፍተኛ ሁኔታ እንዳናረውና ይህም 40 ሚሊዮን ያህል የአለማችን ዜጎችን ወደ ከፋ ድህነት ሊያስገባ ይችላል የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡
ዩክሬን ወደቦቿ በሩስያ ጦር ቁጥጥር ስር በመዋላቸው ምክንያት የጥራጥሬ እህሎች ምርቶቿን ለውጭ ገበያ መላክ ባለመቻሏ ብቻ 6 ቢሊዮን ዶላር ያህል ገቢ እንደምታጣም ተነግሯል፡፡ አሜሪካን ጨምሮ ምዕራባውያን አገራት ሩስያን የአለማችን ባለጸጋ 20 አገራት ከተካተቱበት ቡድን 20 አባልነት ለማስወጣት እያሴሩ እንደሚገኙ የሚያመለክቱ መረጃዎች እየወጡ ቢሆንም፣ "ማንም ማንንም ማባረር አይችልም" ስትል የሩስያን ከቡድኑ መባረር በይፋ ከተቃወመችው ቻይና በስተቀር ድምጽን በድምጽ የመሻር መብት ያላቸው የቡድኑ አባል አገራት፣ በጉዳዩ ላይ ያላቸው አቋም አለመታወቁን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡
የቡድን 8 አገራት ከ8 ወራት በኋላ በኢንዶኔዢያ ጃካርታ ጠቅላላ ጉባኤ እንደሚያካሂዱ የተነገረ ሲሆን የሩስያው ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በጉባኤው ላይ እንደሚሳተፉ መነገሩንም ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሩስያ ከ8 አመታት በፊት ክሪሚያን መጠቅለሏን ተከትሎ፣ ከቡድን 8 አገራት አባልነቷ በአሜሪካ፣ ካናዳ፣ ጃፓን፣ እንግሊዝ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመንና ጣሊያን ሙሉ ስምምነት መባረሯንም ዘገባው አስታውሷል፡፡
ፖላንድ በበኩሏ በስለላ ተግባር ላይ ተሰማርተው ተገኝተዋል ያለቻቸውን 45 የሩስያ ዲፕሎማቶች ለማባረር መወሰኗን ያስታወቀች ሲሆን፣ የአውሮፓ ህብረትም ከሰሞኑ ተጨማሪ አዳዲስ ማዕቀቦችን በሩስያ ላይ ለመጣል ማሰቡ ተነግሯል፡፡

ንብረትነቱ የቻይና ኢስተርን አየር መንገድ የሆነው ቦይንግ 737-800 አውሮፕላን ባለፈው ሰኞ 133 መንገደኞችን አሳፍሮ ሲጓዝ ጉዋንግዚ ጉዋንግ በተባለው የቻይና ግዛት ተከስክሶ ሁሉም ተሳፋሪዎች መሞታቸውን ተከትሎ፣ የአምራቹ ኩባንያ ቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ በ5.6 በመቶ ቅናሽ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
አውሮፕላኑ 9 የበረራ ሰራተኞችንና 123 መንገደኞችን አሳፍሮ ኩሚንግ ከተባለችዋ የቻይና ከተማ በመነሳት ለአንድ ሰዓት ያህል ወደ ጉዋንግዡ ከበረረ በኋላ ድንገት ከፍታውን በፍጥነት በመቀነስ ቁልቁል ወርዶ በደን በተሸፈነ ተራራማ ቦታ ላይ መከስከሱን ተከትሎ፣ የእሳት ቃጠሎ እንደገጠመውና ስብርባሪው ብቻ እንደተገኘ የዘገበው ቢቢሲ፤ አደጋው ከአውሮፕላኑ ዲዛይን ችግር ጋር ተያይዞ የተከሰተ ነው ተብሎ እንደማይጠበቅና ምርመራው እየተከናወነ እንደሚገኝም ገልጧል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ ይሄኛው አደጋ ያጋጠመው በኢትዮጵያና በማሌዢያ በደረሰበት አደጋ ምክንያት ለ3 አመታት ከበረራ ታግዶ የነበረውን ቦይንግ 737 ማክስ አውሮፕላኑን ለቻይና ለማቅረብ በዝግጅት ላይ እያለ መሆኑን የጠቆመው ብሉምበርግ፣ ይህም በኩባንያው ላይ ተጨማሪ ኪሳራንና ወጪን ሊያስከትልበት እንደሚችል አመልክቷል፡፡
ቻይና ኢስተርን አየር መንገድ ለ7 አመታት ያህል አገልግሎት በሰጠው አውሮፕላኑ ላይ አደጋው መከሰቱን ተከትሎ፣ ሁሉንም ቦይንግ 737-800 አውሮፕላኖቹን ከማክሰኞ ዕለት ጀምሮ ከበረራ ያገደ ሲሆን፣ አደጋው በቻይና ከ12 አመታት ወዲህ የተከሰተ የከፋ አደጋ መሆኑም ተነግሯል፡፡
ቦይንግ ኩባንያ 737-800 ኤንጂ በመባል የሚታወቀውን አውሮፕላኑን ለመጀመሪያ ጊዜ በገበያ ላይ ያዋለው እ.ኤ.አ በ1997 እንደነበር ያስታወሰው ብሉምበርግ፤ የደህንነት ታሪኩ ጥሩ የሚባል መሆኑንና ከ7 ሺህ በላይ ከሚሆኑ አውሮፕላኖች የከፋ አደጋ ያጋጠማቸው 11 ብቻ መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡
አደጋውን ተከትሎ የህንድ የሲቪል አቪየሽን ባለስልጣን በቦይንግ አውሮፕላኖች በሚያደርጋቸው በረራዎች ለየት ያለ ከፍተኛ የደህንነት ቁጥጥርና ክትትል እንደሚያድርግ ያስታወቀ ሲሆን፣ ሌሎች አየር መንገዶችም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዳሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ ተዘግቧል፡፡


    የበርካታ አገራት መንግስታትን፣ ግለሰቦችንና ባለጸጎችን የግል ሚስጥራዊ መረጃዎች እየጎለጎለ በአደባባይ በማስጣት የሚታወቀው የዊኪሊክስ ድረገጽ መስራችና ባለቤት ዊሊያም አሳንጄ፣ በእስር ላይ በሚገኝበት የለንደን እስር ቤት ጋብቻውን ሊፈጽም መዘጋጀቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
አሜሪካ ከ10 አመታት በፊት ወታደራዊና የደህንነት መረጃዬን ዘርፎ አሰራጭቶብኛል በሚል ስታሳድደው የኖረችውና 18 ክሶችን የመሰረተችበት የ50 አመቱ አውስትራሊያዊ አሳንጄ፣ ከረጅም ጊዜ የፍቅር ወዳጁ ስቴላ ሞሪስ ጋር በእስር ላይ በሚገኝበት የእንግሊዙ ቤልማርሽ እስር ቤት በመጠነኛ ሰርግ እንደሚሞሸር ነው የተነገረው፡፡
በጥንዶቹ የሰርግ ስነስርዓት ላይ የሚታደሙት 2 አፈራራሚዎችና 2 ጠባቂዎች ብቻ እንደሚሆኑ የጠቆመው ዘገባው፤ ዊሊያም አሳንጄ ከአሜሪካ መንግስት ለማምለጥ 7 አመታት ለንደን በሚገኘው የኢኳዶር ኤምባሲ ጥገኝነት ጠይቆ መቆየቱንና ካለፉት 3 አመታት ወዲህ በቤልማርሽ እስር ቤት እንደሚገኝም አስታውሷል፡፡ የሙሽሮችን አልባሳት ያዘጋጀችው ታዋቂዋ ብሪታኒያዊት የፋሽን ዲዛይነር ቪቬኒ ዌስትውድ መሆኗን የጠቆመው ሮይተርስ፤ የአገሪቱ መንግስት አሳንጄን ለአሜሪካ አሳልፎ እንዳይሰጥ ሲወተውቱ ከነበሩ ታዋቂ ዝነኞች አንዷ መሆኗንም አክሎ ገልጧል፡፡           ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዋቂና አንድ አላዋቂ ሰው መንገድ ሲሄዱ ይገናኛሉ።
አዋቂ፡-
“እንደምን ውለሃል ወዳጄ?” ሲል በሰላምታ ጀመረ፡፡
አላዋቂ፡-
“ደህና እግዚአብሔር ይመስገን፡፡ ወዴት እየሄድክ ነው?”
አዋቂ ፡-
“ወደ ገበያ”
አላዋቂ፡-
“ጎሽ ብቻዬን ከምጓዝ የሚያካሂደኝ አገኘሁ፡፡ እኔም ወደዚያው ስለሆንኩ አብረን እንጓዛለን”
በዚሁ ተስማምተው እየተጨዋወቱ ሲጓዙ ድንገት አንድ አጥር ላይ የተቀመጠ አውራ ዶሮ ያያሉ፡፡
አላዋቂ፡-
“አሁን ይህ አውራ ዶሮ እዚህ ሲጮህ ሰማይ ቤትም ይህንኑ የሚመስል አውራ ዶሮ ይጮኻል” አለ፡፡
አዋቂው፡-
“አይ አይመስለኝም”
አላዋቂው፡-
“ለምን?”
አዋቂው፡-
“መንግስተ ሰማይ’ኮ የንፁሃን ቦታ ነው፡፡ እንደ ዶሮ ያለ ኩሳም ነገር እዚያ አይገባም፡፡”
አላዋቂውም፤
“አይ፤ አውራ ዶሮው ቂጡን ወደ ገሃነም አፉን ወደ ገነት አድርጎ ነው የሚጮኸው”
አዋቂው፤
“አይምሰልህ ሲዖል’ኮ እንኳን የዶሮ ላባ አይነት ደረቅ ነገር አግኝቶ የሰውንም እርጥብ ገላ የሚያነድ ነው፡፡”
አላዋቂ፤
“ዎዎ! እኔ ምን ቸገረኝ፤ ያባቴ ዶሮ አይደለ ቢያንቦገቡገው!” አለው ይባላል።
*  *  *
አገራችን በእንደዚህ ዓይነት የአዋቂና የአላዋቂ አተካሮ ውስጥ መግባት ከጀመረች ዘመናት ተቆጥረዋል፡፡ በከንቱ ሙግት የሚጠፋው ጊዜ በርካታ ነው፡፡ ያም ሆኖ ግን ክርክሩ ለአገርና  ለህዝብ ሁነኛ ጥቅም ሲባል በሆነ እሰየው ነበር። ሆኖም እንዲያው ለአፍ ወግና ውግ ብቻ እንዳፈተተ የሚነገርና የሚሰነዘረው ይበዛል። ከሁሉ የሚከፋው ደግሞ በከፍተኛ ስልጣን ቦታ የተቀመጡ ሹማምንት፣ ምንም ሳይሉ ለሰዓታት የቴሌቪዥንና የሬዲዮ አየር ሰዓት ሲያባክኑ ማየት ነው፡፡ በተሰብሳቢው ፊት ቆሞ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊም ሆነ ኢኮኖሚያዊ ፍሬ-ነገር የሌለው ውትወታና ሀተታ ለማንም አይበጅም! በአፍ ይጠፉ በለፈለፉም ነው፡፡
የአገራችን እጅግ ሥር የሰደደ ችግር ዛሬም ትክክለኛው ሰው በትክክለኛው ቦታ አለመቀመጡ ነው፡፡ (THE RIGHT MAN AT THE RIGHT PLACE እንዲሉ) የተማረና ባለሙያ ሰው አለመኖሩ ሳይሆን፣ እያለ ሁነኛ ቦታ አለመመደቡ ነው፡፡ እንደገና መበወዝ የሚያሻቸውን ወንበሮች ቦታ የማለዋወጥ ነገር ከታሰበበት ይቻላል። ሆኖም ከታሰበበት ነው! አለበለዛ ወርውረውት ራስን መልሶ እንደሚወጋው ቀስት (boomerang) ይሆናል፡፡ አገር ለመምራትና ለማሳደግ ለዋናው ወንበር ቀረቤታ ያላቸውን ባለስልጣናት መመልመልና መሾም ሳይሆን፤ ከዝምድናና ከቦናፓርቲዝም በፀዳ መልኩ ካቢኔን ማዋቀር ብልህነት ነው፡፡ ምንጊዜም ቢሆን የቅራኔ አፈራረጅና አፈታት በጥበብ የተሞላ ሊሆን ይገባዋል። ከሙስና የነጻ ይሆንም ዘንድ ጥበብ ያስፈልጋል፡፡ “አህያን ስጋ ጭነህ፣ ጅብን ንዳ ብለህ፤ አይሆንም” ይላሉ አበው፡፡
የለውጥና እንቅስቃሴ መስተጋብራችን ምንጊዜም ወርቅና ሰም፤ ፈትልና ቀሰም ሊሆን ይገባዋል፡፡ ይሄውም በአያሌው ከተጠያቂነት ጋር  በአግባቡ የተሰናሰለ ተደርጎ ከተበጀ ነው፡፡ አለበለዚያ ጅራፍ እራሱ ገርፎ እራሱ ይጮህ የሚባለውን ተረት መድገም ይሆናል። ራሳችን መመሪያ አውጥተን፣ ራሳችን መመሪያ ጥሰን አይሆንም - A LAW MAKER IS A LAW BREAKER - ይሆንብናልና! “ራሷ ጋግራው አልበሰለም፤ ራሷ ወልዳው አልመሰለም” ማለት ይሄው ነው! የጀመርነውን መጨረስ፣ የጨረስነውን መገምገም፣ ስህተት ካለ መቀበል የስራ መርሃችን ሊሆን ይገባዋል፡፡Saturday, 26 March 2022 11:15

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

  የዕድሜ ግ-ሽበት
                             በእውቀቱ ስዩም

          አዲሳባ እየሰፋች ነው፤ ከጥቂት አመታት በሁዋላ “በአዲስ አበባ አስተዳደር በአንኮበር ክፍለ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ በእውቀቱ“ የሚል ነገር መስማታችን  አይቀርም፥ አያት ወደሚባለው ሰፈር ብቅ ካሉ የፈረስ ጋሪ፥ ባጃጅና ዘመናዊ መኪና ትከሻ ለትከሻ እየተጋፉ ሲያልፉ ያያሉ፥ ባንድ ከተማ ውስጥ ሶስት ክፍለዘመኖች፥ ጎን ለጎን ይራመዳሉ፥
ሀብታሞች በሀብት ላይ ሀብት ጭነዋል፥ ድሆች የባሰ ድሀ ሆነዋል፥ የዛሬ ሶስት አመት ያንድ ሆቴል ባለቤት የነበረው ሰውዬ፤ ዛሬ ሶስት ቅርንጫፎች ከፍቷል! የዛሬ ሶስት አመት መጽሐፍ እሚያዞረው ልጅ ዛሬም መጽሐፍ አዟሪ ነው፥
ከትናንት ወዲያ። በከተማው ዘናጭ ከተባሉት ሬስቶራንቶች ወደ አንዱ ጎራ አልኩ፥ አዲስ ዩኒፎርም የተሰፋለት ዘበኛ፥ ከሸራ ጫማዬ እስከ ጋሜዬ ድረስ ገምግሞኝ ሲያበቃ፥
“ወዴት ነው?” አለኝ፥
“ወደ ምሳ;
ዘቡሌው ያለምንም እፍረት እንዲህ ሲል ጠየቀኝ፥
“መኪናህስ?”
“ትናንት ከዱባይ ተጭኗል፥አየሩ ጥሩ ከሆነ ነገ ጅቡቲ ይደርሳል”
ገባሁ፤
ምግብ ቤቱ ጠረጴዛ ላይ እንደ ሪፖርተር ጋዜጣ ዳጎስ ያለ ገጽ ያለ ሜኑ ተከምሯል፥ ይህንን ሲገልጥ ማን ይውላል?
“አስተናጋጅ”
“አቤት”
“ግማሽ ሽሮ ግማሽ ቲማቲም፥ ከስንግ ቃርያ ጋር፥ ስንት ሺ ብር ነው?”
በማግስቱ፥ ካስፓልት ዳር ያለች፥ በቆርቆሮ የተከበበች መናኛ ምግብ ቤት ሄድኩ፥ ድንች ጥብስ በሚጥሚጣ ተበላ! የጀበና ቡናም ደርሶናል፥ ጥቂት ሰዎች በሰማያዊ ፕላስቲክ በርጩማ ላይ ተደርድረዋል፤ ካጠገቤ የተቀመጠ ሰውዬ በወሬ ጠመደኝ። ንግግሩ ሳይሆን በካቲካላ የተመረዘ ትንፋሹ እጄን ባፌ አስጫነኝ!
“ስራህ ምንድነው?” አለኝ፥
“ጸሀፊ ነኝ”
“የመዝገብ ቤት ነው?”
ገላመጥሁት፥
“ስንት ልጆች አሉህ?” ሲል ቀጠለ፥
“አልወለድሁም”
“ያልወለድክበት ምክንያት ምንድነው?”
“ከግብረስጋ ታቅቤ ስለምኖር ነው”
“ቡና ጠጣ”
“አሁን ጠጣሁ”
"ግዴለህም ጠጣ”
“አልጠጣም”
“የይርጋ ጨፌ ቡና ነው”
“ለምን የይርጋ ዱባለ አይሆንም፥ አልጠጣም ካልሁ አልጠጣም”
በምልልሳችን መካከል ተንቃሳቃሽ ነጋዴዎች ጣልቃ ገቡ፥
- "ነጭ ሽንኩርት! ነጭ ሽንኩርት!
- ሸንኮራ ያስፈልጋል ፍሬንድ?
ጭራሽ የሆነ ሰውየማ ደርዘን ከዘራ ይዞ ቀረበኝ፥
“በዚህ ዘመን ከዘራ ገዝቼ ምን አደርገዋለሁ ዠለስ! ጨዋታው በስናይፐርና በዲሽቃ ነው" አልኩት፥
“እንድትፋለምበት ሳይሆን እንድትመረኮዝበት ብዬ ነው፤" ሲለኝ፥
ስለ ኢኮኖሚ ግሽበት ማሰብ አቁሜ፣ ስለ እድሜዬ ግሽበት ማሰብ ጀመርኩኝ፡፡


Saturday, 26 March 2022 11:11

ከፌስቡክ ገጾች በጨረፍታ

      ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ፣ በእንባ ተሞልታ ያቀረበችው ተማፅኖ


            “...የሀገራችን ጉዳይ ያመናል ሁላችንንም። ... ሁላችንም የትግራይ እናቶች አባቶች፤ እናቶቻችን አባቶቻችን ናቸው። በእርግጠኝነት ደግሞ ነገ ሌላ ቀን ነው፤ ኢትዮጵያ ታርቃ አንድ ሆና ትቆምና የኢትዮጵያን ባንዲራ ታውለበልባለች። ስለዚህ አይክፋችሁ ክብር ይገባችኋል። በብዙ ፈተናዎች አልፋችሁ፣ በብዙ ተፅእኖ አልፋችሁ፣ የኢትዮጵያን ባንዲራ ከፍ ስላደረጋችሁ በጣም እናመሰግናለን።
ትግራይ ትላንትም ብትሆን ኢትዮጵያ ናት፤ ዛሬም ኢትዮጵያ ናት፤ ነገም ኢትዮጵያ ነች፤ ስለዚህ እባካችሁ መሪዎቻችን እባካችሁ ... እባካችሁ ... እባካችሁ ተጠቅማችሁ አይደለም፤ ተጎድታችሁ ኢትዮጵያን አንድ አድርጓት እባካችሁ!!! ከእግዚአብሔር ጋር ትችላላችሁ። ስለዚህ መሪዎቻችን ተጎድታችሁ ለኢትዮጵያ ብላችሁ፣ ለህዝብ ብላችሁ፣ እናንተ አንድ ካደረጋችሁ፣ ኢትዮጵያ አንድ ትሆናለች።
...ስፖርት ወንድማማችነት፣ ፍቅር፣ ሰላም ነው!! ለሰላም፣ ለፍቅር ቆመው፣ እነዚህ ልጆች ምንም ሳይበግራቸው ለዚህ ውጤት በቅተዋልና፣ አሁንም ቢሆን ክብር ይገባቸዋል። እናከብራችኋለን። በእርግጠኝነት ቤተሰቦቻችሁ የት እንዳሉ ታውቃላችሁ፤ ግድ የላችሁም እንወዳችኋለን እናከብራችኋለን፤ እንደ ልጆቻችን ነው አሁንም የምናያችሁ፤ ስለሆነም ትግራይ ዛሬ ብቻዋን አይደለችም፤ ከኢትዮጵያ ጋር ነች፤ ነገም ከኢትዮጵያ ጋር ትሆናለች።
አሜሪካ ትግራይን ለመጥቀም አይደለም፤ ኢትዮጵያንም ለመጥቀም አይደለም ለመበተን ነው፤ H.R. 6600 የሚባለው አሁን ሊፀድቅ በመንገድ ላይ ያለው፤ መሪዎቻችን ስለ ህዝባችን ብለው፣ ስለ ወደፊት ኢትዮጵያ ብለው ከተስማሙ፣ H.R. 6600 የሚፀድቅበት ምክንያት የለውም።
ህዝባችን  ከመንግስቶቻችን ጎን ቆሞ ሁላችንም የትግራይ፣ የኢትዮጵያ ህዝብ፣ እኔ- የትግራይ ህዝብና የኢትዮጵያ ህዝብ ስል ምቾት አይሰማኝም፤ እንደ ኢትዮጵያ ነው ሁላችሁንም የምናየው፤ ሁሉም ብሔር ብሔረሰቦቻችን ኢትዮጵያ ናቸው፤ ትላንትም ተባብረው ነውና ኢትዮጵያን ለዚህ ያበቋት፤ ነገም ዛሬም እንተባበር፤ ኢትዮጵያን አንድ እናድርጋት።
እኛ ልጆቻችሁ ከኦሮሞ የመጣ፣ ከአማራ የመጣ፣ ከትግሬ የመጣ፣ ከጉራጌ፣ ከየትም የመጣው ለዚህ ነው አንዷን ባንዲራ ከፍ ያደረግነው፤ ስለሆነም ብሔር ሳንለይ፣ ሃይማኖት ሳንለይ፣ ፆታ ሳንለይ፤ ባንዲራችንን ያነሳነው ስለተባበርን ነው፤ በፅናት ስለቆምን ነው። ለእናንተም አያቅትም፤ የትግራይ ክልላዊ መንግስትም የኢትዮጵያ መንግስትም እባካችሁ፤ ...ስለ ነገዋ ኢትዮጵያ አንድነት፣ ስለ ብልፅግናዋ፣ ስለ እድገቷ፣ ስለ ሰላሟ፣ እባካችሁ አያቅታችሁም፤ እኛም ከጎናችሁ አለን፤ ስፖርት ሰላም ነው፤ ስፖርት ፍቅር ነው ብለናል፤ ተያይዘን ኢትዮጵያን አንድ እናድርጋት። እግዚአብሔር ደግሞ አንድ ያድርግልን። “


  በ2021 የአለማችን ሙዚቃ 26 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል


            ትውልደ ኢትዮጵያዊው የአለማችን የሙዚቃ ኮከብ አቤል ተስፋዬ (ዘ ዊክንድ) በአመቱ የአለማችን የድረገጽ የነጠላ ዜማ ሽያጭ 1ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ እንግሊዛዊቷ ድምጻዊት አዴል በበኩሏ፤ ከፍተኛ የሙዚቃ አልበም ሽያጭ በማስመዝገብ ቀዳሚነቱን ይዛለች፡፡
አቤል ተስፋዬ በቅርቡ ያወጣው ሴቭ ዩር ቲርስ የተሰኘ ነጠላ ዜማ በድረገጾች አማካይነት በአለማቀፍ ደረጃ 2.15 ቢሊዮን ጊዜ በመታየት የ1ኛ ደረጃን ሲይዝ፣ ዘ ኪድ ላሮል እና ጀስቲን ቢበር በጋራ የለቀቁት ስቴይ በ2.07 ቢሊዮን እይታ ሁለተኛ፣ የዱዋ ሊፓ ሊቪቴቲንግ ደግሞ በ1.88 ቢሊዮን ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
አዴል በበኩሏ 30 የተሰኘው አራተኛ አልበሟ በወጣ በ2 ወራት ጊዜ ውስጥ ብቻ 5 ሚሊዮን ኮፒ እንደተሸጠላትና በአልበም ሽያጭ 1ኛ ደረጃን መያዟን የዘገበው ብሉምበርግ፣ የኦሊቪያ ሮድሪጎ ነጠላ ዜማ ሶር 2ኛ፣ የጀስቲን ቢበር ጀስቲስ ደግሞ 3ኛ ደረጃን መያዛቸውን አመልክቷል፡፡
አለማቀፉ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 ያስመዘገበው ገቢ በ18.5 በመቶ በማደግ፣ 26 ቢሊዮን ዶላር መድረሱንና የገቢ እድገቱ ሙዚቃ እየተቀረጸ በአልበም መልክ መሸጥ ከጀመረበት እ.ኤ.አ 1990ዎቹ ወዲህ ከፍተኛው መሆኑ ተነግሯል፡፡
ለገቢው በከፍተኛ መጠን መጨመር በምክንያትነት የተጠቀሰው በድረገጾች አማካይነት ሙዚቃዎችን እየገዙ የሚያዳምጡ ሰዎች መበራከታቸው ነው ያለው የብሉምበርግ ዘገባ፣ የድረገጽ ደንበኞች ቁጥር 523 ሚሊዮን መድረሱንም አመልክቷል፡፡
የሙዚቃ ኢንዱስትሪውን ገቢ 65 በመቶ ድርሻ የያዘው በድረገጾች አማካይነት የሚከናወን የቀጥታ ሽያጭ ሲሆን፣ በሲዲና በካሴት እየታተሙ የሚሸጡ የሙዚቃ ስራዎችም 19 በመቶ እና 4 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው ተነግሯል፡፡

Saturday, 26 March 2022 10:36

ማራኪ አንቀፅ

  ሁለተኛው ጎጆ በማይታወቀው ቤተሰብ መካከል


              ፀሐይ የተወለደችበትንና ያደገችበትን ቤትና ቤተሰብ የሚያስረሱ በጣም ብዙ ጉዳዮች ቀልቧን ወስደውታል። የእናት የአባቷን ጎጆ፣ የወተት የእንቁላሉን፣ የላምና በጉን ፍቅር ረስታ አዳዲስ የህይወት ልምምዶች ማርኳታል።
የልጅነት ህልሟ እውን ሊሆን መንገዱም የተጠረገ፣ እንቅፋቱ የተነጠለ መሰላት። በዚህ በሁለተኛው የወላጆች ቤት የጎደለባት ነገር ቢኖር የላሞቹ ጠረን፣ የበጎቹ ጩኸት ብቻ ነው። በዚህ ቤት ከቁጥር በላይ የጎኑ መጫወቻዎች አሉ። ብዙ ስዕሎች፣ ብዙ አይነት ምግቦች፣ ብዙ የፈረንጅ መጠጦችና ቸኮሌቶች ይገኛሉ።
ከአንድ ቅያሬ ልብስና ጫማ በላይም አሏት። ኑሮ በነጮቹ ቤት ደስተኛ አድርጓታል። እነ ሊሊን በፈለገችው ሰዓት ቀስቅሳ ለጨዋታ ትጋብዛቸዋለች። ያለ ማንም ከልካይ በግቢው ውስጥ እየተሯሯጡ በመስኩ ላይ እየቦረቁ ይጫወታሉ። ቤተሰቦቿ በሚናፍቋት ጊዜ ነጮቹን ይዛ በመሄድ ሲጫወቱ ውለው ሲመሽ ይመለሳሉ።
ፀሐይ አሁን ላይ በቆዳዋ ቀለም ካልሆነ በአለባበስና በአኗኗር ዘይቤዋ ከነጮቹ የሚለያት ነገር የለም። አንዳንድ ወፍ በረር ቋንቋዎችን እሷ ከእነሱ፣ ነጮቹም ከሷ እየለቃቀሙና እየገጣጠሙ ለመግባቢያነት እያዋሏቸው ነው።
በተለይ በምልክት የፈጠሯቸው የመግባቢያ ቋንቋዎች ከምንም በላይ እርስበርስ እንዲደማመጡ አድርጓቸዋል።
ከዓመት በኋላ ፀሐይን አዲሶቹ ቤተሰቦች ፒያሳ አፍንጮበር አካባቢ የሚገኘው “ብርሃን ኢትዮጵያ” ከሚባለው ት/ቤት አስገቧት። የፈረንጆቹ ልጆች ቀደም ሲል ጀርመን ት/ቤት (6 ኪሎ) አካባቢ ገብተው እየተማሩ ነበር። ፀሐይም ወላጆቿን ቤት በመተው ሙሉ በሙሉ ከአቶ ዴቪድ መኖሪያ ቤት ጓዟን ጠቅልላ ገባች። አቶ ዴቪድ ልጆቻቸውን በሚወስዱበት ሰዓት ፀሐይንም ከብርሃን ኢትዮጵያ ት/ቤት በመኪና ያመላልሷት ነበር።
ስድስት ኪሎ፣ አራት ኪሎ፣ ፒያሳ እና አምስት ኪሎ የቤተመንግስቱን አጥር የሚጋሩ፣ የንጉሡን የዙፋን በሮች በቅርብ ርቀት የሚቃኙ፣ የሀገሪቱ ፖለቲካ የሚጠነሰስበት፣ የሚጠመቅበት አካባቢ ነው።
ይህ የመንግስት ዋና ዋና መስሪያቤቶች መነሃሪያ የሆነው ቦታ የተማሪዎች እንቅስቃሴ ረብሻና ብጥብጥ የማያጣ ነውጠኛ ሰፍራ ሲሆን በየጊዜውና በየዘመኑ የፖለቲካው ድፍድፍ የሚጣልበት በመሆኑ ጤንነት የማይሰማው መንደር ነው።
አንድ ቀን ይኸው ነውጠኛ ሰፈር አገረሸበትና “ንጉሡ ይውረዱልን፣ ሕዝባዊ መንግሥት ይመስረትልን” በሚሉ ሃይሎች ጩኸትና መዝሙር ተናወጠ። ከሁሉም ት/ቤቶችና መ/ቤቶች የሚገኙ ለውጥ ፈላጊ ወጣቶች ሰልፉንና ነውጡን ተቀላቀሉ። ስድስት ኪሎን፣ አራት ኪሎን፣ ፒያሳንና አምስት ኪሎን አመለኛ በሬ የዋለበት ሜዳ አስመሰሉት። የመኪና መስታዎት የቤትና የቢሮ በሮች ከየአቅጣጫው የሚወረወሩ ድንጋዮች ስብርብራቸው ወጣ። በመንገድ የሚያልፉ ሰዎች እየተመቱ በየቦታው ወደቁ።
ት/ቤቶች ተማሪዎች ተረጋግተው መማር አልቻሉም በሚል እንዲዘጉ ታዘዙ። በራቸውን ባልዘጉ ት/ቤቶች ላይም የድናጋይ ናዳ ይወርድባቸው ጀመር።
ፀሐይ የምትማርበት ብርሃን ኢትዮጵያ፣ የዚሁ የረብሻው ቀጠና አካል በመሆኑ፣ የድንጋይ በትር ከቀመሱ ት/ቤቶች መካከል አንዱ ነበር። ት/ቤቱ ተማሪዎችን ወደቤታቸው እንዲሄዱ በለቀቀበት ወቅት ታዲያ የተወረወረ ነውጠኛ ድንጋይ በፀሐይ ግራ እጅ ላይ አረፈ።
ምንም እንኳን ጉዳቱ መካከለኛ ጉዳት ቢሆንም፣ የረብሻ ቀጠና ከሆነው ከዚያ አካባቢ አውጥተው ወደ ሌላ ቦታ ቢያስገቧት አዲሶቹ ወላጆቿ መከሩበት።
“ይሄ የግል ት/ቤት ቢቀርባት ይሻላል” አሉ አቶ ዴቪድ።
“አዎ! ለዛሬ ቢሰውራትም ድጋሚ ይመቱብኛል ት/ቤቱ ይቀየር” አሉ ወ/ሮማርያ።
“ከነ ሊሊ ጋር ትማር ከልጆቹ ጋር ብትሆን ይሻላል፤ ለማምጣትም አልቸገርም” አሉ አቶ ዴቪድ።
“ለቋንቋውም ቢሆን ከእነሱ ጋር ብትማር ነው የሚሻለው፤ ሀበሻ ብቻ ከሚማርበት ት/ቤት አንድ አይነት ቋንቋ ብቻ ተናጋሪዎች ስለሆኑ ሌላ ቋንቋ ለመልመድ አስቸጋሪ ነው የሚሆነው” አሉ ወ/ሮ ማርያ።
ፀሐይ በአዲሶቹ ወላጆቿ አማካኝነት ፒያሳ ከሚገኘው ብርሃን ኢትዮጵያ ት/ቤት ወጥታ፣ የፈረንጆች ልጆች ከሚማሩበት ከስድስት ኪሎ ወደ ፈረንሳይ ኤምባሲ በሚወስደው መንገድ፣ ከጃንሜዳ ጀርባ ከሚገኘው ጀርመን ት/ቤት ገብታ መማር ጀመረች።
መስከረም ወር በ1963 ዓ.ም (በፈረንጆች) ፀሐይ የ10 ዓመት ልጅ እያለች፣ ሙሉ ለሙሉ ተጠቃላ ከፈረንጆቹ ቤት ገባች። አይኖቿን ለማየት የሚጓጉት እናቷና ወላጅ አባቷ፤ መልኳ እስኪጠፋባቸው ድረስ ለረዥም ጊዜ ወደ ቤቷ ሳትመለስ ትምህርቷን እየተማረች ከነጮች ፊት ገብታ ቀረች።
ፈረንጆቹ ቤተሰቦቿ ይናፍቋታል ብለው እንድትሄድ ሲጠይቋት፣ ብዙም የናፍቆትና የመጓጓት ባህሪ ስለማይታይባት ውትወታውን ትተው፣ እሷን እንደልጃቸው አድርገው መንከባከብና ማሳደጉን ገፉበት።
ፈረንጆቹ እየሰባበሩ በሚያወሯት አንዳንዴ ወደ ጀርመንኛው በተጠጋ አማርኛ ሲያናግሯት፣ ፀሐይም አስቂኝ በሆነው ጀርመንኛ ቋንቋ እየመለሰችና እያወራቻቸው በመካከላቸው የሚፈጠረው በቋንቋ ግራ የመጋባት ችግር እየተቀረፈ መጥቷል። በተለይ በተለይ ጀርመን ት/ቤት ከገባች ጊዜ ጀምሮ የሚከብዳትን በማስጠናትና የቤት ስራ በማሰራት ወ/ሮ ማርያ ከፍተኛ እገዛ ስለሚያደርጉላት፣ የመግባባት ችሎታዋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል።
አቶ ዴቪድ በመካኒካል ኢንጅነሪንግና በኮንትራት ከሚያስተምሩበት አምስት ኪሎ ዩኒቨርስቲ፣ በመግቢያና በመውጪያ ሰዓት አምስቱንም ታዳጊዎች በማመላለስ አስፈላጊ የሆነውን የትምህርት አጋዥ መጸሐፍት በመግዛትና ወደተለያዩ ቦታዎች በዕረፍት ሰዓት ወስዶ በማዝናናት እንዲሁም በትምህርታቸው ውጤታማ እንዲሆኑ ድጋፍ ያደርጉላቸዋል።
ወ/ሮ ማርያ በበኩላቸው፤ ከልጆቻቸው ጋር የቤተሰቡ አምስተኛ አካል የሆነችውን አዲሲቷ ልጃቸውን ፀሐይን ከወለዷቸው ልጆቻቸው አስበልጠው ይንከባከቧታል። የቋንቋ ችግር ስላለባትና በፍጥነት እንዲገባት ረዥሙን ሰዓታቸውን እሷን የቋንቋው ባለቤት ለማድረግ ሲጥሩ ይውላሉ።
የፀሐይ ቤተሰቦች ልጃቸውን የሚያዩት በዓመት በዓል ጊዜ በ3 ወር አለዚያም በ6 ወር አንድ ጊዜ ብቻ ቢሆን ነው። ዓመት በዓል ሲመጣ በፋሲካ እንቁጣጣሽና ገና ወቅት ግን መላውን ቤተሰቡን ስለሚጠሯቸው ፀሐይና አዲሶቹ ቤተሰቦቿ ወደ ወላጆቿ ቤት በመሄድ በዓሉን ያከብራሉ። በዚህም የፀሐይ ወላጆች ልጃቸውን ለረዥም ሰዓት የሚያዩበትና ናፍቆታቸውን የሚወጡበት ጊዜ ነው።
በበዓሉ ቀን ዶሮ ተሰርቶ፣ ቅርጫ ገብቶና በግ ተገዝቶ ይታረዳል። ጠላ ይጠመቃል። የሐበሻ አረቄም ተገዝቶ ይመጣና ለፈረንጆቹ ይቀርባል።
ፈረንጆቹ በበኩላቸው፤ ወደ ፀሐይ ቤተሰብ ከመሄዳቸው በፊት ለበዓሉ ያስልጋቸዋል የሚሉትን ጤፍ፣ የቅርጫ ስጋ መግዣና መጠነኛ ብር ለወ/ሮ አበባ ይልኩላቸዋል። ለልጆቻቸው ደግሞ ልብስና ጫማ ገዝተው ለበዓሉ ዋዜማ ይልኩላቸዋል።
(በወሰን ደበበ ማንደፍሮ ከተፃፈው “የደመና ሥር ፀሐይ” የተሰኘ መፅሐፍ የተቀነጨበ)

Tuesday, 29 March 2022 00:00

አድማስ ትውስታ

በደግነት የተንቆጠቆጠ ልብ! (የቅጣት ትኬት ወይስ የፍቅር ትኬት?!)             የ28 ዓመቱ ዴል የ3 ዓመት ህፃን ልጁን ጨምሮ ቤተሰቡን በመኪናው ጭኖ በአሜሪካ ዌስትላንድ ግዛት አውራ ጎዳና ላይ እያሽከረከረ ነበር እ.ኤ.አ በ2016 ሰኞ ቀን።
ዴል መኪናውን እያሽከረከረ ከሰጠመበት ሰመመን የነቃው የፖሊስ መኮንን ድንገት ሲያስቆመው ነው። የመኪናው የጎን መስታወት ዕይታን በሚጋርድ ፕላስቲክ ተሸፍኖ ነበር ጆሱዋ ስካልጂዮን የተባለው የፖሊስ መኮንን ወደ መኪናው ቀርቦ ወደኋላ መቀመጫ ሲመለከት የ3 ዓመት ህጻን ልጁ  ደህንነት መጠበቂያ ወንበር ነው የተቀመጠችው፡፡ የህጻን ልጁን ህይወት ለአደጋ አጋልጦ መኪና ለማሽከርከር መድፈሩ ሳያስገርመው አልቀረም። “ጌታው፤ ህፃን ልጅህን እንዴት ያለ ደህንነት መጠበቂያ ወንበር ጭነሃት ትዞራለህ?” ሲል ጠየቀው አሽከርካሪውም፤ “ምን መሰለህ የዕዳ መዓት ተከምሮብኝ የደህንነት ወንበሩን የምገዛበት ገንዘብ አጥቼ ነው አለው፡፡
የፖሊስ መኮንኑ፣ ዴል ከመኪናው እንዲወጣ ጠየቀው ንግግራቸውን ቤተሰቡ እንዲሰማ አልፈለገም፡፡ ዴል ግን በሌለኝ ገንዘብ የቅጣት መዓት ሊጭንብኝ ነው በሚል ደንግጦ ነበር፡፡ ዴል ከመኪናው ከወረደ በኋላ የደረሰበትን የኑሮ ፈተና አሁን ያለበትን ሁኔታ፤ የሚጠበቀውን የተከመረበትን የዕዳ መጠንና፤ የገጠመውን የገንዘብ እጥረት ለፖሊሱ በዝርዝር ነገረው። “ወንድሜ፤ ወደ ዎልማርት ተከትለኸኝ ልትመጣ ትችላለህ?” አለው የፖሊስ መኮንኑ- ዴልን። “ለምን?” በድንጋጤና ግራ በተጋባ ስሜት ጠየቀ፤ ዴል።
“የህፃናት የደህንነት መጠበቂያ ወንበሩን ደስ እያለኝ ልገዛልህ እወዳለሁ” መለሰለት ፖሊሱ ዴል ጆሮውን ማመን አልቻለም። ፖሊሱን ተከትሎ ወደ ተባለው መደብር ለመከተል ከመንቀሳቀሱ በፊት ጥቂት አፍታ መውሰድ ነበረበት- ለመረጋጋት።
ዴል እና ስካልጂዮኒ ወደ ሸቀጥ መደብሩ ሲጓዙ፣ ስለ ህይወት ተሞክሯቸው በጥልቀት እያወጉ ነበር።
“ሁለታችንን ዎልማርት ውስጥ ድንገት የተመለከተን ሰው የረዥም ጊዜ ምርጥ ጓደኛሞች መሆናችንን ፈጽሞ አይጠራጠርም።”  ሲል ዴል ጽፏል-በፌስ ቡክ ገፁ።
ስካልጂዮኒ ህፃኗ የምትወደውን ፒንክ ቀለም ያለው ፒንክ-የደህንነት መጠበቂያ ወንበር ነበር የገዛው- ያውም በቢራቢሮዎች ያሸበረቀ ያጌጠ።
ዴል “ከዚህ ቀደም ከገጠሙት ፖሊሶች ሁሉ የተለየ መሆኑን ለስካልጂዮኒ እንደነገረው ይገልጻል። የስካልጂዮኒ መልስ ግን ቀለል ያለ ነበር- “እኔ ሥራዬን ብቻ ነው የሰራሁት” ሲል መለሰለት።
“የቅጣት ትኬት ብቆርጥልህ አንተን የባሰ መከራ ውስጥ ከመዝፈቅ ውጭ ፋይዳ የለውም ብዬ ነው” እንዳለውም ዴል ያስታውሳል።
አዲሱን የህጻናት የደህንነት መጠበቂያ ወንበር መኪናው ውስጥ በደስታ ተሞልቶ ከገጠመ በኋላ  ነበር ዴል ለካስ የዚህን ደግ ፖሊስ ስም እንደማያውቅ የተገነዘበው።
ይሄን ጊዜ ነው የሆነውን ሁሉ በፌስቡክ ለማጋራትና የፖሊስ መኮንኑን የደግነት ተግባር ዕውቅና በመስጠት ለዓለም ለማስተዋወቅ የወሰነው። ታሪኩም በማህበራዊ ሚዲያ በአስደናቂ ፍጥነት ተሰራጨ። የዌስትላንድ ፖሊስ መምሪያ ዘንድም ደረሰ። ፖሊስ መምሪያው ግን ይሄንን የደግነት ተግባር የፈጸመው የትኛው የፖሊስ መኮንን እንደሆነ ለማወቅ በቀላሉ አልቻለም። ለምን ቢሉ? ስካሊጅዮ ይህን በጎ ስራውን ለማንም ትንፍሽ አላለም ነበር።
“የሱ ብቸኛ ዓላማ አሽከርካሪውን መርዳት እንጂ ዕውቅና ማግኘት አልነበረም” ሲል የፖሊስ መምሪያው በፌስቡክ ገፁ ባሰፈረው መግለጫው ጠቁሟል፡፡
የፖሊስ መምሪያው ለስካልጂዮን ውዳሴና ሙገሳ ያቀረበ ሲሆን፤ ዴልንም አመስግኗል- ተሞክሮውን በማጋራቱ።
“በአሉታዊ ታሪኮች በተሞላ ዓለም ውስጥ ያንተን በጎ ታሪክ ማጋራትህ በሁላችንም ላይ የማይታመን በጎ ተፅዕኖ ያሳድርብናል።” ብሏል- የፖሊስ መምሪያው- በመግለጫው።
የዌስትላንድ ፖሊስ መምሪያ ይሄን በጎ ተግባር የፈጸመው ስካልጂዮኒ መሆኑን ካረጋገጠ በኋላ ከዴል ጋር ዳግም የሚገናኙበትን ቀን ፈጥሯል- በመመሪያው ቅጥር ግቢ። በነገራችን ላይ ታዋቂው አሜሪካዊ የቲቪ ሾው አዘጋጅ፣ ኮሚዲያንና ደራሲ ስቲቭ ሃርቬይ፤ ዴልንና ስካጂዮን በታዋቂው የቴሌቪዥን ፕሮግራሙ እንግዶች አድርጎ አቅርቧቸው ነበር-ሌሎች ከታሪኩ ትምህርት እንዲወስዱ። በርግጥም ልብን የሚያሞቅ የደግነት ተግባር ነው የፖሊስ መኮንኑ የፈጸመው። የቅጣት ትኬት ይቆርጣል ተብሎ ሲጠበቅ፣ የፍቅር ትኬት ቆርጦ መላ ታሪኩን ለወጠው፡፡


 *የዜግነት መብት ቅድሚያ ሲሰጠው ኢትዮጵያዊ ማንነትም ይጎለብታል
           *ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን ማስታረቅ ያስፈልጋል

          ቀድሞ በእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎና ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ ሃሳብ ተጠንስሶ ብዙም ያልተራመደው፣ ኋላም የዛሬ 10 ዓመት ነዋሪነታቸውን አሜሪካ ባደረጉ ኢትዮጵያውያን በድጋሚ የተቋቋመው "ኢትዮጵያዊነት የዜጎች መብት ማስከበሪያ ድርጅት (ኢትዮጵያዊነት)"፤ ከሦስት ዓመት በፊት በስፋት ወደ እንቅስቃሴ የገባ ሲሆን ድርጅቱ በተለይ ኢትዮጵያዊነትና የኢትዮጵያዊነት እሴቶችን የማጽናት አላማን አንግቦ እየተንቀሳቀሰ ይገኛል። ለመሆኑ "ኢትዮጵያዊነት" የተባለው ድርጅት ምንድን ነው? ለምን ዓላማ ተቋቋመ? እሳቤውና ፍልስፍናው ምንድን ነው? ለአገርና ለህዝብ ምን ፋይዳ አለው?  የድርጅቱ አመራር አቶ ተስፋ ሚካኤል መኮንን፣ ከአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ አለማየሁ አንበሴ ጋር አጭር ቆይታ አድርገዋል፡፡  እነሆ፡-


                እስቲ  ድርጅቱ መቼና እንዴት እንተቋቋመ ይንገሩን?
“ኢትዮጵያዊነት” የተመሰረተው ወይም ደግሞ ተጠናክሮ የተቋቋመው እ.ኤ.አ በ2013 በሰሜን አሜሪካ ነው። የተቋቋመበት ምክንያትም በዋናነት በብሄር ማንነት ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚደረጉ ሁኔታዎች ስላላማረንና አገሪቱንም ወደ አጉል አቅጣጫ እየወሰደ በመሆኑ፣ ያን ሚዛን የሚያስጠብቅ ደግሞም ነባሩን የኢትዮጵያን እሴቶች የሚያጎላ ንቅናቄ አስፈላጊ ነው ብለን በማመናችን ነው። በነገራችን ላይ “ኢትዮጵያዊነት” የተመሰረተው በኛ አይደለም። በ1984 ዓ.ም በታዋቁ አባቶቻችን በእነ ጄነራል ጃጋማ ኬሎ፣ በእነ ደጃዝማች ዘውዴ ገ/ስላሴ፣ በእነ ልጅ ሚካኤል እምሩ፣ ዮዲት እምሩ፣ ፀሃይ ብርሃነስላሴና በመሳሰሉት ነው።
በሰሜን አሜሪካ የዛሬ 10 ዓመት ድጋሚ ስንመሰረት ግን ወደ 16 የሲቪክ ድርጅቶችን አነጋግረን፣ በመጨረሻም አራት ድርጅቶች ተዋህደው ነው፣ኢትዮጵያዊነት ብለው ድርጅቱን ያቋቋሙት። ከመስራቾቹ መካከል እነ ዶ/ር ጌታቸው ሃይሌ፣ እነ ዶ/ር አክሊሉ፣ እነ ዶ/ር ፀሃይ ይጠቀሳሉ።
የ"ኢትዮጵያዊነት" ዋነኛ አላማና ግቡ  ምንድን ነው?
ዋነኛ ዓላማው፤ ኢትዮጵያዊነትን በኢትዮጵያ እንደገና ለማጽናት ነው። በአንድ በኩል የዜግነት መብት እንዲከበር፣ በሌላ በኩል ኢትዮጵያዊነት በጣም ጥልቅ የሆነ ህዝብ እየኖረው ያለ ግን በጋራ ወጥቶ ያልታየ ስለሆነ፣ ያንን አጉልቶ ለማሳየት ነው፡፡ የኢትዮጵያ መሰረቱ ኢትዮጵያዊነት ነው። ነገር ግን ባለፉት 30 ዓመታት የመጣው ብሄር ላይ ብቻ ያነጣጠረ ትርክት፣ ወጣቱን መሰረቱን እያሳጣው ስለሆነ፣ ያንን ሚዛን የማስጠበቅ ግብና ዓላማ ይዘን ነው የምንቀሳቀሰው።
በምን መልኩ ነው ይሄን አላማችሁን የምታሳኩት?
እንግዲህ በርካታ እንቅስቃሴዎችን እናደርጋለን። አንዱ ትውልድን ማስተማር ነው። በሌላ በኩል፤ የቃልኪዳን ሰነድ ወይም አሜሪካኖች ቢል ኦፍ ራይትስ የሚሉት አይነት ለማዘጋጀት ነው እቅዳችን። እነዚህ  በቃል ኪዳን ሰነዱ ላይ የሚቀመጡ አንቀጾች የማይሻሩ የማይለወጡ ናቸው። በዚህ መልኩ ሰነዱ በምሁራን ተዘጋጅቷል። ይሄን የፖለቲካ ፓርቲዎችም ተቀብለው አጽድቀውታል። ይሄ የቃልኪዳን ሰነድ ሁሉም ተወያይቶ ከተቀበለው ሃገራችንን በጽናት ለማስቀጠል በጣም ወሳኝ ነው።
አሁን በሥራ ላይ ያለውን ህገ-መንግስት ተቋማችሁ እንዴት ይመለከተዋል?
እኛ በህገ-መንግስቱ ያሉ ሁሉ ትክክል አይደሉም የሚል ድምዳሜ የለንም። ነገር ግን ከእሳቤው ጀምሮ በርካታ አንቀጾች መሻሻል ይገባቸዋል ብለን በዝርዝር አስቀምጠናል።
ለምሳሌ የትኞቹ?
አንቀጽ 39  አንዱ ነው፣ የዜግነት መብትን በተመለከተ፣ የዜጎችን ከቦታ ቦታ ተንቀሳቅሶ የመኖር፣ የሃገር ባለቤትነትን የሚገድቡ የክልል ህገ-መንግስቶች ላይ የሰፈሩ አንቀጾች ተጠቃሽ ናቸው። በርካታ መሻሻል ያለባቸው አንቀጾች አሉ።
ኢትዮጵያዊነት ባለፉት 30 ዓመታት የገጠመው ፈተና ምንድን ነው? መፍትሄውስ ምንድን ነው ትላላችሁ?
እኛ በጉዳዩ ላይ በርካታ ውይይቶች አድርገናል፤ እናደርጋለን። በፖለቲካ፣ በማህበራዊ፣ በኢኮኖሚ የገጠሙን ችግሮች በርካታ ናቸው። ኢትዮጵያዊነት ባለፉት 30 ዓመታት እንዲደበዝዝ፣ ብሄር እንዲጎላ ተደርጓል። የኢትዮጵያዊነት እሴቶች እንዲደበዝዙ ተደርገዋል። ኢትዮጵያዊነት ዜግነት ነው፤ ኢትዮጵያዊነት ማንነትም ነው። የያዘን የጋራ ማንነት አለን። ህዝባችን በደም የተዋሃደ፣ ሲበላለቅ የኖረ ነው። በእነዚህ ዘመናት ሁሉ ያዳበራቸው የጋራ እሴቶች አሉት። በዘረመል ደረጃም እንለካው ከተባለ እጅጉን ተመሳሳይ ነው። በልዩነት ላይ ብቻ ስለተሰበከ ልዩነታችን ብዙ ይመስላል እንጂ የጋራ ማንነታችን እጅግ ትልቅ ነው።
የዘውግ ብሄርተኝነትንና ኢትዮጵያዊ ብሄርተኝነትን ማስታረቂያው መንገድ ምንድን ነው? እናንተስ እንደ ተቋም በዚህ በኩል ምን ልትሰሩ አስባችኋል?
ሰዎች የዘውግ ብሔርተኛ መሆናቸው ችግር የለውም። ችግር የሚሆነው የዘውግ ብሔርተኝነቱ ዋነኛ የፖለቲካ ማቀንቀኛ መሳሪያ ሲሆን ነው። ተቋማችን “ኢትዮጵያዊነት”፤ በግለሰብ መብት፣ በአገር አንድነት፣ በአብሮነት፣ በኢትዮጵያዊ እሴቶች እንዲሁም በዲሞክራሲ ያምናል። በአካባቢ ደረጃ ቋንቋዎች መከበር አለባቸው። ሰዎች በራሳቸው ቋንቋ መማራቸው ምንም ችግር የለውም፤ ግን ከኢትዮጵያዊነት ጋር ሊቃረን አይገባውም። ኢትዮጵያዊነት በአንድ በኩል የዜግነት መገለጫ ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ማንነት ነው።
የዜግነት መብት ቅድሚያ ሲሰጠው ኢትዮጵያዊ ማንነትም ይጎለብታል። በአለም ላይ ሁሉም ሃገሮች ሊባል በሚችል ደረጃ ቅድሚያ የሚሰጡት ለዜግነት መብት ነው። በእኛ ሀገር ግን ቅድሚያ የሚሰጠው ለብሔሮች መብት ነው። የብሔሮች መብት መከበሩ ትክክለኛና ተገቢ ነው። ነገር ግን ዜግነትንና ኢትዮጵያዊ ማንነት በሚጠላት መልኩ ችግር ይፈጥራል። ኢትዮጵያዊነትንና የብሔር ማንነትን ማስታረቅ ያስፈልጋል። ለዚህ ምሁራን ቁጭ ብለው ሊወያዩና ሊመክሩ ይገባል።