Administrator

Administrator

 አሸናፊው ሮቦት 3.5 ሚሊዮን ዶላር ይሸለማል

    በሮቦቲክስ መስክ የተሰማሩ 24 የአለማችን ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ያመረቷቸው ሮቦቶች የተሳተፉበትና 3.5 ሚሊዮን ዶላር ሽልማት የሚያስገኘው የዳርፓ የሮቦቶች ውድድር ትናንትና ዛሬ በአሜሪካ እየተካሄደ እንደሚገኝ ቢቢሲ ዘገበ፡፡
በአሜሪካው መከላከያ ቢሮ ፔንታጎን ድጋፍ በሎሳንጀለስ አቅራቢያ በመከናወን ላይ በሚገኘው በዚህ ውድድር የሚሳተፉ ሮቦቶች አደጋን የመቋቋም ብቃታቸውን የሚያሳዩ አስቸጋሪ ተግባራትን እንዲፈጽሙ በማድረግ አሸናፊው ይለያል ተብሏል፡፡
ሮቦቶቹ እንዲያከናውኗቸው ከተመደቡላቸው ስምንት ተግባራት መካከል፡- መኪና መንዳት፣ በር መክፈትና ማለፍ፣ ግድግዳ መብሳት፣ በደረጃዎች ላይ መወጣጣት የሚገኙበት ሲሆን፣ በውድድሩ ላይ የሚገለጽ ሌላ ለየት ያለ ተልዕኮም እንዲፈጽሙ ይደረጋል፡፡
እያንዳንዱ ሮቦት እነዚህን ስምንት ተግባራት ለማከናወን ሁለት ሙከራዎች የሚሰጡት ሲሆን ፈጥኖ ተግባራቱን በተሳካ ሁኔታ ማከናወንም ለአሸናፊነት በመስፈርትነት ከተቀመጡት ነጥቦች አንዱ እንደሆነ ዘገባው ጠቁሟል፡፡
የውድድሩ አዘጋጅ የሆኑት ዶክተር ጊል ፕራት እንዳሉት፣ የዘንድሮው ውድድር ከአምናው ጋር ሲነጻጸር በአስር እጥፍ አስቸጋሪ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የተለያዩ የአለም አገራት የሮቦቲክስ ዘርፍ ኩባንያዎችና የምርምር ቡድኖች ለውድድሩ የቀረቡ ቢሆንም፣ የመጀመሪያውን ማጣሪያ አልፈው ለፍጻሜ የደረሱት፣ 24 መሆናቸውንና ከእነዚህም መካከል የአሜሪካ፣ የደቡብ ኮርያ፣ የጃፓን፣ የጀርመንና የጣሊያን ኩባንያዎች እንደሚገኙበት ዘገባው አመልክቷል፡፡  

  ከአለማችን ታላላቅ የኤሌክትሮኒክስ እቃዎች አምራች ኩባንያዎች ተርታ የሚሰለፈው የጃፓኑ ሻርፕ ኩባንያ፣ በያዝነው የፈረንጆች አመት  ብቻ 1.45 ቢሊዮን ዶላር ይከስራል ተብሎ እንደሚጠበቅ ሮይተርስ ዘገበ፡፡
ከቅርብ አመታት ወዲህ እየደረሰበት ካለው ኪሳራ ለማገገም ደፋ ቀና ማለቱን የቀጠለው ሻርፕ፣ በዘንድሮው አመት  1.45 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ ይደርስበታል ተብሎ እንደሚጠበቅ የጃፓኑ ኮዮዶ ኒውስ ይፋ ያደረገውን መረጃ ጠቅሶ ዘገባው ገልጧል፡፡
ኩባንያው ባለፈው አመት 222 ቢሊዮን የጃፓን የን መክሰሩን ያስታወሰው ዘገባው፣ የአምናው ኪሳራው ባለፉት አራት አመታት ከደረሱበት ኪሳራዎች በሶስተኛ ደረጃ ላይ እንደሚገኝም ገልጧል፡፡ ኩባንያው ባለፉት አመታት ለከፍተኛ ኪሳራ የተዳረገው በተለያዩ አለማቀፋዊና ውስጣዊ ምክንያቶች መሆኑን የጠቆመው ዘገባው፣ ከእነዚህም መካከል የምርቶች ሽያጩ መቀነሱ፣ የገበያ ውድድሩ ከፍተኛ መሆኑና የወጪዎች መብዛት ይጠቀሳሉ ብሏል፡፡ ሻርፕ ባለፈው አመት በአለም ዙሪያ ከሚገኙ 49 ሺህ ሰራተኞቹ መካከል 10 በመቶውን ከስራ እንደቀነሰና ከእነዚህም መካከል 3ሺህ 500 የሚሆኑት በጃፓን ይሰሩ የነበሩ መሆናቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡

የማይመለሱ 4 ነገሮች፡- ከአፍ የወጣ ቃል፣ የተወረወረ ቀስት፣ ያለፈ ህይወት እና የባከነ ዕድል፡፡
የቻይናውያን አባባል
ለማቀድ መስነፍ ለመውደቅ ማቀድ ነው፡፡
የቻይናውያን አባባል
ማለም ብቻ በቂ አይደለም፤ መምታት አለብህ፡፡
የጣሊያኖች አባባል
መሬት ላይ እሾህ ከበተንክ ባዶ እግርህን አትሂድ፡፡
የጣሊያኖች አባባል
ሁልጊዜ የምትሰጥ ከሆነ ሁልጊዜ ይኖርሃል፡፡
የቻይናውያን አባባል
በአንድ እጅህ ሁለት እንቁራሪቶችን ለመያዝ አትሞክር፡፡
የቻይናውያን አባባል
የተጠበሰች ዳክዬ መብረር አትችልም፡፡
የቻይናውያን አባባል
አበቦች በያዛቸው እጅ ላይ መዓዛቸውን ይተዋሉ፡፡
የቻይናውያን አባባል
ጠብ ከፈለግህ ለጓደኛህ ገንዘብ አበድረው፡፡
የቻይናውያን አባባል
የምላስ ብዕር፣ የልብ ቀለም ውስጥ መነከር አለበት፡፡
የቻይናውያን አባባል
የአንድ ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ እህል ዝራ፤ የ10 ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ ዛፎች ትከል፤ የ100 ዓመት ብልጽግና ከፈለግህ ሰዎችን አልማ፡፡
የቻይናው ያን አባባል
የአንድ ሰዓት ደስታ ከፈለግህ አሸልብ፤ የአንድ ቀን ደስታ ከፈለግህ ሃብት ውረስ፤ የዕድሜ ልክ ደስታ ከፈለግህ ሰዎችን እርዳ፡፡
የቻይናውያን አባባል

ወይዘሮ ተናኘ ስዩም “የፍቅር ድንግልና” በሚል ርዕስ ፅፈው ያሳተሙት ረጅም ልብወለድ መፅሃፍ በዛሬው ዕለት ከጠዋቱ 2፡30 ጀምሮ በአምስት ኪሎ ድህረ ምረቃ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ በምረቃ ስነ - ስርዓቱ ላይ ደራሲ አበረ አዳሙ በመፅሃፉ ላይ ሥነ - ፅሁፋዊ ዳሰሳ ያቀርባል ተብሏል፡፡
ደራሲዋ የዕውቋ ድምፃዊት ጂጂ (እጅጋየሁ ሽባባው) እናት እንደሆኑ ታውቋል፡፡ የልቦለዱ ታሪክ ከኢጣሊያ ወረራ በፊትና በኋላ የነበረች አንዲት ወጣት ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን የወቅቱን ባህላዊና ማህበራዊ ገፅታ ያሳያል። በ349 ገፆች የተቀነበበው “የፍቅር ድንግልና”፤ በ100 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡ 

የወጣት ፍሬዘር ዘውዴን (ቬኛ) የግጥሞችና ደብዳቤዎች ስብስብ የያዘው “የፍቅር ገፆች” የተሰኘ መድበል ካለፈው ሳምንት ጀምሮ ለንባብ በቅቷል፡፡
መፅሃፉ በ110 ገፆች 52 ግጥሞችንና 12 ደብዳቤዎችን ያካተተ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ30 ብር፣ ለውጭ አገራት በ9.99 ዶላር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡

በአለማየሁ ገበየሁ የተፃፈው  “የረከሰ ፍርድ በኢትዮጵያ” የተሰኘ የአጫጭር ወጐች መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡
ጭብጡን ፖለቲካዊና ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ ያደረገው መጽሐፉ፤ ታሪኮቹ በወግ መልክ  የቀረቡ ናቸው፡፡ ደራሲ አለማየሁ ገበየሁ የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅትን ጨምሮ በተለያዩ ሚዲያዎች በጋዜጠኝነት መስራቱ ታውቋል፡፡
ደራሲው በእለት ማስታወሻ ደብተሩ የመዘገባቸውን አስገራሚ ሁነቶች በወግ መልክ ማቅረቡን  የጠቆመ ሲሆን መፅሃፉ በ49 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

 ባለፈው ዓመት በአገራችን ለመጀመሪያ ጊዜ በብሔራዊ ቴአትር የተከበረው “የዓለም የቴአትር ቀን”፤ በደሴ ከተማና በኮምበልቻ እንደሚከበር በባህልና ቱሪዝም ሚ/ር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አስታወቀ፡፡
“ቴአትር ለማህበራዊ ለውጥ፤ ማህበራዊ ለውጥ ለቴአትር” በሚል መሪ ቃል ከዛሬ ጀምሮ ለ3 ቀናት የሚከበረውን በዓል ወሎ ዩኒቨርሲቲና የባህልና ትብብር ዳይሬክቶሬት በጋራ እንዳዘጋጁት ታውቋል፡፡
“የዓለም የቴአትር ቀን” በደሴና ኮምበልቻ በተለያዩ አዳራሾች እንደሚከበር የጠቆሙት አዘጋጆቹ፤ በየመድረኩ ቴአትሮች፣ ትውፊታዊ ድራማዎች፣ ልዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችና ቱባ ባህልን የሚያንፀባርቁ ውዝዋዜዎች፣ የቅኔ ጉባኤ፣ መንዙማና ሌሎች ኪነ - ጥበባት ይቀርባሉ ብለዋል፡፡
“የዓለም የቴአትር ቀን” ከ1962 ዓ.ም አንስቶ በዓለም አቀፍ ደረጃ መከበር የጀመረ ሲሆን ዘንድሮ ለ53ኛ ጊዜ እንደተከበረ ተጠቁሟል፡፡

  ከ1.5 ሚ. ብር በላይ ፈጅቷል

   የጠፈር ሳይንስ ተመራማሪ የነበሩትን የሳይንቲስት ዶ/ር ቅጣው እጅጉ ህይወት የሚዳስስ የ50 ደቂቃ ዘጋቢ ፊልም በዛሬው ዕለት ከምሽቱ 12፡30 ጀምሮ በሂልተን ሆቴል ይመረቃል፡፡
“ልጃችን” የተሰኘውንና ከ1.5 ሚ. ብር በላይ ወጪ የተደረገበትን ይሄን ዘጋቢ ፊልም ሰርቶ ለማጠናቀቅ ከ2 ዓመት በላይ እንደፈጀ የዶ/ር ቅጣው እጅጉ ቤተሰቦች ጠቁመዋል፡፡ ከቦንጋ እስከ አሜሪካ ድረስ ያለውን የሳይንቲስቱን ህይወት በስፋት ይዳስሳል በተባለለት በዚህ ዘጋቢ ፊልም፤ ከዶ/ር ቅጣው ጋር ተያይዘው የሚነሱ በርካታ የተዛቡ ጉዳዮች ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል ተብሏል፡፡

የደራሲ ተስፋዬ ዘርፉ “የስደታችን ማስታወሻ” የተሰኘው መፅሃፍ በነገው ዕለት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ውይይት እንደሚካሄድበት ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ ገለፀ፡፡ ለውይይቱ መነሻ ሀሳብ የሚያቀርቡት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፕሬስ ኤዲተር የሆኑት አቶ ብርሃኑ ደቦጭ ሲሆኑ ውይይቱ በብሔራዊ ቤተ - መፃህፍትና ቤተ - መዛግብት ኤጀንሲ አዳራሽ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡ የሥነ - ፅሑፍ አፍቃሪያን በውይይቱ ላይ እንዲገኙ ሚዩዚክ ሜይዴይ ጥሪ ጋብዟል፡፡

Saturday, 06 June 2015 14:21

የፍቅር ጥግ

ፍቅር የሚያንዘፈዝፍ ደስታ ነው፡፡
ካህሊል ጂብራን
እግዚአብሄር የተሰበረ ልብ መጠገን ይችላል፡፡ ነገር ግን ስብርባሪዎቹን ሁሉ ማግኘት አለበት፡፡
ያልታወቀ ደራሲ
የትዳር ግብ ተመሳሳይ ነገር ማሰብ ሳይሆን አብሮ ማሰብ ነው፡፡
ሮበርት ሲ.ዶድስ
ሚስት ጥሩ ባል ሲኖራት ፊቷ ላይ ያስታውቃል፡፡
ገተ
አባት ለልጆቹ ማድረግ የሚችለው ትልቁ ነገር እናታቸውን መውደድ ነው፡፡
ቲዎዶር ሄስበርግ
አንዳንዴ አንድ ሰው ስናጣ መላው ዓለም ህዝብ አልባ የሆነ ይመስለናል፡፡
ላማርቲን
እግዚአብሔር የተሰበረ ልብ ላላቸው ቅርብ ነው፡፡
የአይሁዶች አባባል
ሁልጊዜ ከሚስቴ ጋር እጅ ለእጅ እንያያዛለን። ከለቀቅኋት አንድ ነገር ትገበያለች፡፡
ሄኒ ያንግማን
አብሮ መሆን ጅማሮ ነው፡፡ አብሮ መቀጠል ዕድገት ነው፡፡ አብሮ መስራት ስኬት ነው፡፡
ሔነሪ ፎርድ
በእኔ ቤት ውስጥ አለቃው እኔ ነኝ፤ የሚስቴ ሚና የውሳኔ ሰጪነት ብቻ ነው፡፡
ውዲ አለን
ትዳር ለማደግ የመጨረሻችን ምርጥ አጋጣሚ ነው፡፡
ጆሴፍ ባርዝ
ሃዘን በጊዜ ክንፍ በርሮ ይሄዳል፡፡
ዣን ዲ ላፎንቴን
አንተ በልቤ ክንፍ በርረህ ሄድክ፣ እኔን ግን ክንፍ አልባ አደረግኸኝ፡፡
ቴሪ ጉይሌሜትስ
ትዳርን ጠብቆ የሚያቆየው ሰንሰለት አይደለም፡፡ ክሮች ናቸው፡፡ ሰዎችን በአንድ ላይ ሰፍተው የሚያቆዩት በመቶዎች የሚቆጠሩ ቀጫጭን ክሮች ናቸው፡፡
ሳይሞን ሲኞሬት