
Administrator
470, 000,000 ብር ደረሰ
" ሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ለመቄዶንያ 10 ሚሊዮን ብር "
ተወዳጅዋ ዳጊ ከቤተሰቧቿ ጋር በመሆን አንድ ሚሊዮን ብር ለገሰች
የአዋጭ መስራች እና ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ዘሪሁን ሸለመ በአዋጭ የገንዘብ ቁጠባና ብድር ኅብረት ስራ ማህበር አንድ ሚሊዮን ብር እንዲሁም በአዋጭ ፋውንዴሽን ስም አንድ ሚሊዮን በድምሩ ሁለት ሚሊዮን ብር ለመቄዶንያ ድጋፍ ያደረጉ ሲሆን በአዋጭ ፋውንዴሽን በኩል በየአመቱ አንድ ሚሊዮን ብር ለመለገስ ቃል ገብተዋል፡፡
ያስጀመረን ያስፈፅመናል!!!
“ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት” የኪነጥበብ መርሃ ግብር በአድዋ ሙዚየም ይካሄዳል
“ዝክረ አድዋ ኢትዮጵያዊነት” የተሰኘ ልዩ የኪነ-ጥበብ መርሃ ግብር፣ በመጪው ሳምንት አርብ የካቲት 21 ቀን 2017 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት ጀምሮ በአድዋ ሙዚየም ይካሄዳል፡፡
የመርሃ ግብሩ አዘጋጅ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴይንመንት እንደገለጸው፣ በአድዋ ድል ዋዜማ በሚካሄደው በዚህ የኪነጥበብ መርሃ ግብር፤ ‹‹ኢትዮጵያዊነት ዝክረ አድዋ” የተሰኘ ጥናታዊ ፅሁፍና ዲስኩር በምሁራን የሚቀርብ ሲሆን፤ የግጥም ምሽትና የስታንዳፕ ኮሜዲም እንደተሰናዳ ተጠቁሟል፡፡
በተጨማሪም ፖለቲከኞች በሰላምና አንድነት ዙሪያ አነቃቂ ንግግር፣ እንዲሁም ጀግኖች አርበኞች ሽለላና ፉከራ በባህላዊ ባንድ ታጅበው ያቀርባሉ ተብሏል።
በመርሃ ግብሩ ደራሲ፣ ገጣሚና ፀሀፌ ተውኔት አያልነህ ሙላቱ፣ አምባሣደር ዲና ሙፍቲ፣ ዶ/ር ወዳጄነህ ማህረነ፣ ኡስታዝ አቡበከር አህመድ፣ መምህር ዲያቆን ዳንኤል ሰይፈ ሚካኤል፣ ጋዜጠኛና ደራሲ ጥበቡ በለጠ፣ መጋቢ ቸርነት በላይነህ (ፓስተር ቸሬ)፣ አርቲስት ተስፋዬ ሲማ፣ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤልና ሌሎችም እንደሚሳተፉ ተነግሯል፡፡
የኢትዮጵያውያንና የአፍሪካውያን ብሎም የጥቁር ህዝቦች የነጻነት ምልክት በሆነው የአድዋ ድል ዋዜማ ላይ በሚካሄደው መርሃ ግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ አርቲስቶችና ጋዜጠኞች እንዲሁም ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚታደሙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመግቢያ ዋጋ መደበኛ 300 ብር፣ VIP ደግሞ 500 ብር ሲሆን፤ ትኬቱ በቴሌ ብር፣ በጃፋር ቤተ-መፅሐፍት፣ በ2 ሺህ ሐበሻ የባህል ምግብ አዳራሽ እንደሚገኝ አብርሃም ግዛው ኢንተርቴንመንት ጠቁሟል፡፡
የአዲሱ_ኢ-ፓስፖርት መረጃዎች
• አዲሱን ኢ-ፓስፖርት በሁለት ወር ከ10 ቀን ማግኘት ይቻላል፣
• 14 አዳዲስ ቅርንጫፎችን በመክፈት አገልግሎቱን ለመስጠት ዝግጅት ተጠናቋል፣
• ከአንድ ነጥብ 5 ሚሊዮን በላይ ኢ-ፓስፖርት ታትሞ ተዘጋጅቷል፣
• ከፓስፖርት በተጨማሪ ከ10 በላይ የጉዞ ሰነዶችን ማዘመን ተችሏል፣
• አዲሱ ኢ-ፓስፖርት በነበረው ዋጋ ለተጠቃሚዎች ተደራሽ ይሆናል፤
• ለፓስፖርት ህትመት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ በማስቀረት የሚኖረው ፋይዳ ጉልህ ነው፣
• ከዚህ በፊት አገልግሎት እየተሰጠ የቆየው 20 ዓመት ባለፈው ቴክኖሎጂ ነው፣
• ይህንን ቴክኖሎጂ በሀገር ውስጥ መገንባት መቻሉ ትልቅ ድል ነው፣
• አዲሱ ቴክኖሎጂ ደንበኞች ባሉበት ፓስፖርታቸውን በፍጥነት ማግኘት እንዲችሉ ያደርጋል፣
• ከዚህ በፊት የሚያጋጥሙ የደህንነት ችግሮችን ሙሉ በሙሉ ይቀርፋል፤
• ነባሩ ፓስፖርት የአገልግሎት ጊዜው እስኪያበቃ ጥቅም ላይ መዋሉን ይቀጥላል፤
• የዕድሳት ጊዜው ሲደርስ በኢ-ፓስፖርት ይተካል፤
**
(ምንጭ፡- የኢምግሬሽንና ዜግነት አገልግሎት)
ኢትዮጵያ በየG-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባዔ ላይ ትሳተፋለች
የG-25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት ጉባዔ ለ3ኛ ጊዜ በታንዛኒያ ዳሬ ሰላም የሚካሄድ ሲሆን፤ የአህጉሩ ቀዳሚ የቡና አምራች የሆነችው ኢትዮጵያን ጨምሮ 25 የአፍሪካ ቡና አምራች ሀገራት በጉባዔው ላይ ይሳተፋሉ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ በጉባኤው ላይ ለመሳተፍ ታንዛኒያ ዳሬ ሰላም ከተማ ገብተዋል።
''የአፍሪካ የቡና ኢንዱስትሪን በማነቃቃት ለወጣቶች የሥራ ዕድሎችን መክፈት'' በሚል መሪ ቃል በሚካሄደው በዚህ ጉባዔ ላይ ዘርፉን ለማነቃቃትና ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ ውይይቶች እንደሚደረጉ ኢዜአ በዘገባው አመልክቷል፡፡
በአንድ ጊዜ 16 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል ሥራ ጀመረ
• ለመዲናዋ የመጀመሪያው ማዕከል ነው ተብሏል
በአንድ ጊዜ 16 የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ቻርጅ ማድረግ የሚያስችል የመጀመሪያው የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል በአዲስ አበባ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ በቀጣይም በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች እንደሚስፋፋ ተነግሯል፡፡
ዘመናዊነትና ጤናማ የከተማ ኑሮን ለማንበር ትልቅ ወጪ በማውጣት የተለያዩ ስራዎችን እያከናወነ የሚገኘው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ብክለትን ለመቀነስ የሚረዱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎችን ከማበረታታት ባሻገር የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች መሰረተ ልማት እየገነባ ይገኛል፡፡ በዚሁ መሰረትም በከተማዋ የመጀመሪያውን የንግድ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከል ሥራ አስጀምሯል፡፡
በሁለተኛው ምዕራፍ የኮሪደር ልማት ስራ፣ በከተማዋ 58 የሚደርሱ የኤሌክትሪክ ተሽከርካሪ ቻርጅ ማድረጊያ ማዕከላት እየተገነቡ እንደሚገኙ ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ የኢትዮጵያ ኢ-ፓስፖርት ይፋ ሆነ
የኢሚግሬሽን እና የዜግነት አገልግሎት አዲስ የኤሌክትሮኒክስ ፓስፖርትን ይፋ አደረገ ፡፡
አዲሱ ፓስፖርት ደህንነቱ የተጠበቀ እና በሀገር ዉስጥ የሚመረት ነዉ ተብሏል፡፡
ፓስፖርቱ በአዲስ አበባ ከተማ በሚገኘዉ የለሚ ኢንደስትሪያል ፓርክ የሚመረት ሲሆን ጥራቱ አለም አቀፍ ደረጃውን የጠበቀ ስለመሆኑም ተነግሯል፡፡
በፓስፖርቱ ገፆች ላይ የሀገር ገፅታ የሚያስተዋዉቁ የኢትዮጵያ መለያዎች እንደተካተቱበትም ለማወቅ ተችሏል፡
ፀሐይ -2 አውሮፕላን የመጀመሪያ የሙከራ በረራዋን በስኬት አጠናቀቀች

የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም
#በዛሬዋ_ዕለት
ከ 88 ዓመት በፊት ልክ በዛሬዋ ቀን በአብርሃም ደቦጭ እና ሞገስ አስገዶም መሪነት በኢጣልያኑ የጦር አዛዥ ጄነራል ግራዚያኒ ላይ በቦንብ ያደረጉት የግድያ ሙከራ ምክንያት የኢጣሊያን ወታደሮች በቂም በቀል በመነሳት በሺዎች የሚቆጠሩ የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎችን ለ 3 ተከታታይ ቀናት ዘግናኝ እና ጭካኔ በተሞላበት ሁኔታ በህዝቡ ላይ ጭፍጨፋ ያደረሱበት ዕለት ነበር።
የካቲት 12 ቀን 1929 ዓ.ም በፋሺስት ኢጣሊያ በግፍ የተጨፈጨፉ ኢትዮጵያውያን ሰማዕታት ሲታወሱ......
የካቲት 12 ቀን በኢትዮጵያ ታሪክ የተለየ ቀን ነው፡፡ የኢጣሊያዋ ኔፕልስ ግዛት ልዑል ልጅ መውለዱን ለመዘከር ግራዚያኒ በዚህ ቀን የአዲስ አበባን ደሃዎች ሰብስቦ ለመመጽወት ባደረገው ጥሪ መሰረት ከ 3ሺ የሚበልጡ አቅመ ደካሞች በጥዋቱ በ 6 ኪሎው ቤተመንግስት ተገኝተዋል፡፡
በዚህ ቀን ኢትዮጵያውያን ጥቃት ሊያደርሱ ይችላሉ የሚለው መረጃ እስከ ሮም በመሰማቱ የቤተመንግስቱ ውስጥና ዙሪያ መትረየስ በታጠቁ ልዩ ወታደሮች እንዲጠበቅ ተደርጓል፡፡ አብርሃ ደቦጭና ሞገስ አስገዶም ይህንን ጠንካራ ጥበቃ አልፈው ውስጥ ገብተዋል፡፡
ከቀኑ ለስድስት ሩብ ጉዳይ አካባቢ ሲሆን ከፍተኛ ፍንዳታ በቤተ መንግስቱ ተሰማ፡፡ ከፍ ወዳለው የቤተመንግስቱ ደረጃ የተወረወረው ቦምብ ደግሞ ግቢውን በጩሀት አናጋው፡፡ የመጀመሪያው ቦምብ ባለመትረየስ ጠባቂውን አስወገደው፡፡ 2ኛው ቦምብ ከግራዚያኒ አጠገብ የነበረውን ምሰሶ አፈራረሰው፡፡ ግራዚያኒ ወደ ውስጥ ሲሸሽ ጀርባው፣ ትከሻውና የቀኝ እግሩን ከ 350 በሚበልጥ የቦምብ ፍንጣሪ ቆሰለ፡፡ የካሜራ ባለሙያውና ወታደሮች ግራዚያኒን ከወደቀበት አንስተው በመኪና በመጫን ወደ ሆስፒታል ይዘውት በረሩ፡፡
ሶስተኛው ቦምብ ፖጊያሊ ፊት በመውደቅ ፍንጣሪው አቡነ ቄርሎስን ሲያቆስላቸው ጃንጥላ ያዣቸውን ደግሞ ገደለው፡፡ የኢጣሊያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ጄኔራል ሊዮታ በቦምብ እግሩን አጣ፡፡ የፋሺስት ፓርቲ ዋና ጸሀፊና የቤተመንግስቱ ጠባቂዎች በድንጋጤ ለምጽዋት በ6 ኪሎ በተሰበሰበው ህዝብ ላይ እሩምታ በመተኮስ ከ1ሺ የሚበልጡትን ገደሉ፡፡ የጥቃቱ ዋና ፈጻሚዎች ሞገስ አስገዶምና አብርሃ ደቦጭ ከጊቢው በመውጣት ተሰወሩ፡፡
በቀጣይ ሰአታት ጥቁር ከነቴራ ለባሽ የኢጣሊያ ልዩ ወታደሮች የቴሌፎንና የፖስታ አገልግሎትን ዘጉ፡፡ ወዲያው መሃል ፒያሳ አራዳ ባለው የፋሽስት ዋና ጽ/ቤት የነበረው ጎዶ ኮርቴሌ የፋሽስት ወታደሮች ለሚቀጥሉት 3 ቀናት ኢትዮጵያውያንን እንዲጨፈጭፉ ትእዛዝ ሰጠ፡፡ በዚሁ ምሽት አዲስ አበባ የእርድ ቄራ ሆነች፡፡
ነዋሪዎቿ ቤት ከውጭ እየተቆለፈባቸው ከውጭ በሚለኮስ እሳት እንዲነዱ ተደረገ፡፡ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች የተገኙት ደግሞ እየታፈሱ በመኪና ተጭነው ተወስደው በግራዚያኒ ዋና መምሪያ ተረሸኑ፡፡ ከሚነዱት ቤቶች አምልጦ ለመውጣት እድል ያገኘውን ደግሞ የኢጣሊያ ወታደሮች ከደጅ ሆነው በጥይት ለቀሙት፡፡
የጥቃቱ አቀናባሪዎችንና አድራሾችን ለመያዝ ጥብቅ ምርመራና አሰሳ ተጀመረ፡፡ የኢጣሊያ ደህንነቶች ከምሽቱ በ 2 ሰአት የአብረሃ ደቦጭን ቤት ሰብረው ሲገቡም እጀታው አረንጓዴ፣ቢጫ እና ቀይ በሆነው የኢትዮጵያ ባንዲራ ቀለማት በተቀባ ሳንጃ የኢጣሊያ ባንዲራ ተቦጫጭቆ አገኙ፡፡ በመቀጠል የሞገስና የአብርሃ ጓደኞችን ማደን ተጀመረ፡፡
አብርሃና ሞገስ ከምሽቱ 1:00 ሰአት አካባቢ ወደ ጀርመን ሚሽን በመሄድ ጓደኛቸው ስብሀትን በአጥር ቢያስጠሩትም ስብሀት አብሯቸው ለመሄድ ዝግጁ ስላልነበር ብቻቸውን ከተማውን ለቀው ሸሹ፡፡ ከጥቂት ሰአታት በኋላ የኢጣሊያ ወታደሮች የጀርመንን ሚሽን በመክበብ ስብሀትን እያዳፉ ወሰዱት፡፡ አርበኛ ሸዋ ረገድ ገድሌንም በማታ ወስደው በኤሌክትሪክ ንዝረት ቢያሰቃይዋትም ሚስጥር ሳታወጣ ቀረች፡፡
ቅዳሜ ጥዋት በድንጋጤ በአዲስ አበባ ጎዳናዎች ሲሯሯጡ የተገኙ ነዋሪችም ታፍሰው ፒያሳ ራስ መኮንን ድልድይ አጠገብ ተረሸኑ፡፡ በአሜሪካ ኤምባሲ ተሸሽገው የነበሩ በ 100ዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያንን ኤምባሲው አሳልፎ እንደሰጣቸው ኤምባሲው በር ላይ እንደ ውሻ እየተቀጠቀጡ ተገደሉ፡፡
ይህ ለአሜሪካ ህዝብ ይፋ ከሆነ በኋላ የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚ/ር እና ኢትዮጵያ የሚገኘው አምባሳደር ዜናውን በማግስቱ አስተባበሉ፡፡ ምኒልክ አደባባይ አቅራቢያ ሆኖ ይህንን ግፍ ይመለከት የነበረው ወጣቱ ልጅ እምሩ ዘለቀም ከሰአታት በኋላ ቤቱን ሰብረው በገቡ የኢጣሊያ ወታደሮች ከእናቱና 2 እህቶቹ ጋር ተይዞ ታሰረ፡፡
እሁድ እለት የ 3 ቀኑን ጭፍጨፋ ለማስቆም በአዲስ አበባ የተለያዩ ቦታዎች የሚከተለው አዋጅ ተለጠፈ፣
“ ሞሶሎኒ እንደ ፈጣሪ ሃያል ነው፡፡ ፈጣሪም ሆነ ሞሶሎኒ ተመሳሳይ ባህሪ አላቸው፡፡ ሞሶሎኒ ተበሳጭቶባችሁ ነበር፡፡ አሁን ግን ቁጣው በርዷል፡፡ ወደ የቤታችሁ በመሄድ እለታዊ ተግባራችሁን ቀጥሉ፡፡”
ይሁን እንጂ ከዚህ አዋጅ በኋላም ግድያው ቀጥሎ ነበር፡፡ የበቀል ቅጣቱን ለማምለጥ ከቤታቸው ከወጡት ወደ 5ሺ የሚጠጉ የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ውስጥ ብዙዎቹ የአርበኞችን ትግል ተቀላቀሉ፡፡ በሁለት ቀን ተኩል በኢጣሊያ የግፍ ጭፍጨፋ የተገደሉትን የአዲስ አበባ ነዋሪዎች ቁጥር አንዳንድ ወገኖች እስከ 30ሺ እንደሚደርስ ሲገልጹ ሌሎች ደግሞ ቁጥሩን ከላይ 17ሺ - 18ሺ ያደርሱታል፡፡
©️ የአርበኞች ጀብዱ፣ Jeff Pearce እንደጻፈው፣ ኤፍሬም አበበ እንደተረጎመው፣ ገጽ 205-212
ክብና ዘላለማዊ ዕረፍት ለሰማዕታት ????
#ታሪክን_ወደኋላ
የረዳን ፈጣሪ ይመስገን!
በበጎነት የመኖሪያ መንደር" ለአቅመ ደካሞች እና ለልማት ተነሺዎች ያስገነባናቸውን 192 የመኖሪያ ቤቶችን የያዙ ሁለት ባለ 9 ወለል ህንጻዎች ለነዋሪዎቻችን አስተላልፈናል።
አዲስ አበባ ባለፉት 6 ወራት ምን አከናወነች
• ከተሰበሰበው ግብር 70 በመቶው ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት ውሏል
• በግማሽ ዓመቱ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ ተነግሯል
• አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካቱን አስታውቋል
የ2017 በጀት ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸሙን ባለፈው ሳምንት ማገባደጃ ላይ የገመገመው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ ባለፉት ስድስት ወራት ጠንካራ የሥራ ባህል፣ የአመራር ቁርጠኝነትንና ቅንጅትን በማጠናከር፣ እንዲሁም የገቢ አሰባሰብን በማሳደግ፤ በርካታ ፕሮጀክቶችን በተያዘላቸው ጊዜና በጀት፣ በጥራት አጠናቆ፣ ለህዝብ አገልግሎት ክፍት ማድረግ መቻሉ ተነግሯል።
በግምገማው ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ክብርት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ ባለፉት ስድስት ወራት በሁሉም ዘርፎች አመርቂ አፈጻጸሞች መመዝገባቸውን ጠቁመው፤ የከተማ አስተዳደሩ ከዕቅዱ 90 በመቶውን ማሳካት መቻሉን አረጋግጠዋል፡፡
በእነዚህ ስድስት ወራት የከተማዋን ገጽታ የቀየሩና የህዝቡን የልማት ጥያቄ የመለሱ ሰፋፊ ስራዎች መከናወናቸውን የገለጹት ከንቲባዋ፤ “አገልግሎት አሰጣጣችንን ቀልጣፋና ከብልሹ አሰራር የጸዳ ለማድረግና መሰረታዊ ለውጥ ለማምጣት አሰራራችንን ዲጂታላይዝ ለማድረግ አቅደን የሰራናቸው ሥራዎችም ለውጦችን አሳይተዋል” ብለዋል፡፡
በግማሽ ዓመቱ በመዲናዋ 111.6 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡ የተገለጸ ሲሆን፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ50 በመቶ ብልጫ ማሳየቱ ተነግሯል፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደራዊ ወጪንና ብክነትን በመቀነስ፣ አብዛኛው ገቢ፣ ነዋሪዎችን ለሚጠቅም ተግባር በመዋሉ፣ ፈጣን ለውጦችን ማስቀጠል መቻሉንም ነው ከንቲባ አዳነች አቤቤ የጠቆሙት፡፡
“ከህዝብ ከሰበሰብነው ግብር 70 በመቶ የሚሆነውን የነዋሪዎቻችንን እንግልት ለሚቀንሱና ህዝብን ለሚጠቅሙ ተግባራት እንዲሁም ለዘላቂ ልማት በማዋላችን፣ የፈጣን ለውጦቻችንን ቀጣይነት አስጠብቀናል” ብለዋል፤ከንቲባዋ ፡፡
“ባለፉት ስድስት ወራት የዕቅድ አፈጻጸማችን፣ ከተማችንን ከነዋሪዎቿ ኑሮና አኗኗር ጋር አስተሳስረን ውብና አበባ የማድረግ እንዲሁም የቱሪስት መተላለፊያ ሳትሆን፣ መዳረሻ እንድትሆን ለማድረግ አቅደን እየሰራን ያለነውን ስራ ቀጣይነት እንዲኖረው ማድረግና ውጤታማነቱን ማስጠበቅ ችለናል” ሲሉም አክለዋል።
በተለያየ እርከን የሚገኙ የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች በተሳተፉበት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ ላይ ሰፊ ማብራሪያ የሰጡት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ በመዲናዋ የተከናወኑ ጎላ ጎላ ያሉ ተግባራትንና የተገኙ ውጤቶችንና ለውጦችን ዘርዘር አድርገው አቅርበዋል፡፡ የተስተዋሉ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም ጠቃቅሰዋል፡፡
በመዲናዊ ሰፊ የሥራ ዕድል እየተፈጠረ መምጣቱን ያነሱት ከንቲባዋ፤ አዲስ አበባ 24 ሰዓት የምትሰራ ከተማ ናት ብለዋል - ቀንም ሌሊትም፡፡ መሥራት ለሚችሉና ሥራን ለማይመርጡ ሁሉ በሯን ከፍታ እያስተናገደች እንደምትገኝም ጠቁመዋል፡፡
የኑሮ ጫናን ለማቃለል የተከናወኑ ተግባራት
የከተማው ህዝብ ያለበትን የኑሮ ውድነት ጫና ለማቃለል ታልመው የተከናወኑ በርካታ ተግባራት እንዳሉ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገልጸዋል፡፡ ከእነዚህም መካከል በመዲናዋ የተለያዩ አካባቢዎች ተገንብተው አገልግሎት መስጠት የጀመሩ ትላልቅ የገበያ ማዕከላት ይጠቀሳሉ፡፡ እነዚህ የገበያ ማዕከላት በአብዛኛው የግብርና ምርቶችን እንዲሁም አትክልትና ፍራፍሬዎችን በቀጥታ ከአምራቹ ለሸማቹ (ደላላን ከመሃል በማስወጣት) የሚቀርብባቸው ናቸው፤ በተመጣጣኝ ዋጋ፡፡ ከዚህም ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ገበሬዎች፣ ያለአንዳች ችግር አዲስ አበባ ውስጥ ገብተው፣ ምርታቸውን ሸጠው የመውጣት ዕድል እንደከፈተላቸውም ከንቲባዋ አንስተዋል፡፡
ከንቲባ አዳነች በተጨማሪም፣ በትራንስፖርት እንዲሁም በጤና መድህን በሚሊዮኖችና ቢሊዮኖች በጀት በመመደብ፣ ነዋሪው በተመጣጣኝ ዋጋ አገልግሎት ማግኘት እንዲችል እያደረግን ነው ሲሉም ተናግረዋል፡፡ “ይህም ለህዝባችን የገባነውን ቃል በተግባር መፈጸማችንን ማሳያ ነው” ብለዋል፡፡ በሌላ በኩል፣ በመዲናዋ በቀን 35ሺ የሚደርሱ ዜጎች በነጻ የሚመገቡባቸው የምግብ ማዕከላት ቁጥር 26 መድረሳቸውን ገልጸዋል፤ ሁለቱ ገና አገልግሎት አለመጀመራቸውን በመጠቆም፡፡ ዘንድሮ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት በርካታ የልማት ጥያቄዎችንና የኑሮ ውድነት ጫናዎችን ማቃለል በሚቻልበት ደረጃ መሰራቱንም ተናግረዋል፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት በበጎ ፈቃድ ወደ 9.2 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሆን ወጪ መሸፈኑን የጠቆሙት ከንቲባ አዳነች አቤቤ፤ ይሄ የሚያስደንቅ ክንውን ነው ብለዋል፡፡
በአገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል ታይቷል
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በሰጡት ማብራሪያ፤ አገልግሎት አሰጣጥ ላይ መሻሻል መምጣቱን ተናግረዋል፡፡ “ሰራተኞቻችንን መፈተን እና መመዘን አለባችሁ ምክንያቱም ህዝቡ በአገልግሎት እየተማረረ ነው፡፡ይሄን ዕድል የሰጠን ህዝብ ስለሆነ ህዝባችንን ለማገልገል የሚያስችል ብቃትም፣ሥነምግባርም፣ተነሳሽነትም ሊኖረን ይገባል የሚል እምነት ሰራተኞቻችን ላይ መፍጠር መቻሉ አንድ እርምጃ ነዉ፡፡” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ሁለተኛው ደግሞ ይላሉ ከንቲባዋ፤ “ሁለተኛው እርምጃ ደግሞ ፈተና ሰጥተን ሥራና ሰራተኛን (ባለሙያን) ለማገናኘት የሄድንበት ሂደት ነው፤ በእርግጥ በደንብ እየተመዘነ መታየት አለበት፡፡ ነገር ግን ሂደቱም ለውጥ ነው” ብለዋል፡፡ ምክንያቱንም ሲያስረዱ፤ “አንዴ ሰራተኛ ሆኜ ከተቀጠርኩ አልነካም የሚለው አስተሳሰብ መሰበሩ በራሱ ለውጥ ነው” ይላሉ፡፡
በርካታ አሳሪ አሰራሮች ተፈተዋል
ከዚህ ቀደም የነበሩ በርካታ አሳሪ አሰራሮችን ፈተናል ያሉት ከንቲባ አዳነች፤ ”ቀልጣፋ አሰራርና ግልጽነት እንዲኖር ህዝቡን የሚያሳትፍና አቅሙን የሚገነባው እንዲሁም እኛን ግልጽ ለመሆን የሚያስገድዱን አሰራሮችን አውጥተን ተግብረናል” ሲሉም አብራርተዋል፡፡
ሦስተኛው እርምጃ ቴክኖሎጂ ነው ይላሉ፡፡ 87 ያህል የአገልግሎት ዓይነቶችን በቴክኖሎጂ አገልግሎት መስጠት ጀምረናል ያሉት ከንቲባዋ፤የስራ ቦታ ምቹ እንዲሆኑ፣አገልግሎት የሚፈልጉ ተገልጋዮች ፊት ለፊት ከሰራተኞች ጋር እየተያዩ አገልግሎት የሚያገኙበት እንዲሁም ኃላፊዎች ያለውን የስራ እንቅስቃሴ መከታተልና መቆጣጠር የሚችሉበት ሁኔታ እንዲቀል እየተደረገ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
አምና በዚህ ወቅት ስንገመግም እዚህ ከነበረው አመራር ውስጥ ረቡዕና አርብ ቁጭ ብሎ አገልግሎት የሚሰጠው 64 በመቶ ያህሉ ብቻ እንደነበር ያስታወሱት ከንቲባ አዳነች፤ ዘንድሮ አገልግሎት የሚሰጠው አመራር 89 በመቶ መድረሱን ተናግረዋል፤ይሄም ለውጥ መሆኑን በመጠቆም፡፡
በብልሹ አሰራር ላይ ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት በተደረገው ጥረትም፣ ባለፉት ስድስት ወራት ለመጀመሪያ ጊዜ በብልሹ አሰራር የተጠረጠሩ 78 ዳይሬክተሮችና 2ሺ46 የሚሆኑ ሰራተኞች ተጠያቂ እንዲሆኑ መደረጋቸውን ከንቲባዋ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ ባለፈም በከተማችን ውስጥ የተጠረጠሩ 928 የሚሆኑ ግለሰቦች ለህግ እንዲቀርቡ መደረጋቸውንም አክለዋል፡፡
የጥንካሬያችን ምንጭ ምንድን ነው?
የእነዚህ ጥንካሬዎች መነሻ ምንድን ነው ሲሉ የሚጠይቁት ከንቲባዋ፤ የመጀመሪያው አመራር ነው ይላሉ፡፡ “አመራሩ በየደረጃው ሃላፊነቱን ለመወጣት የሚያደርገው ጥረት ተነሳሽነት እንዲሁም መሰጠት እነዚህን ለውጦች ማስመዝገብ ችለዋል” ብለዋል፡፡ ሁሉም የራሱን ሃላፊነት ለመወጣት፣ የተሻሻለ የሥራ ባህል ለመፍጠር እንዲሁም የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት የሚደረጉ ጥረቶች የዚህ ማሳያዎች ናቸው፤ ሲሉም ያብራራሉ፡፡
ሁለተኛው የገቢ አሰባሰባችን መሻሻል ነው ይላሉ፤ በዚህ ስድስት ወር ከአምናው ተመሳሳይ ጊዜ 50 ፐርሰንት ጭማሪ ያለው ገቢ መሰብሰብ መቻሉን በመግለጽ፡፡ የተሰበሰበው ገቢም ወደ 37 በመቶ ዕድገት አሳይቷል ተብሏል፡፡
በርካታ የመልካም አስተዳደር፣ የልማትና ማህበራዊ ውዝፍ ጥያቄዎች ያሉበት ትልቅ ከተማን ችግር ለመፍታት፣ በመንግሥት በጀት ብቻ እንደማይወጡት መገንዘብ መቻላቸውን የሚናገሩት ከንቲባዋ፤ ለዚህም “ዝቅ ብለን የተለያዩ ባለድርሻ አካላትን ግንዛቤ ፈጥረንና አሳምነን፣ በበጎ ፈቃድ የተለያዩ የልማት ጥያቄዎች እንዲሟሉ አድርገናል” ይላሉ፡፡ ባለፉት ስድስት ወራት 9 ቢሊዮን ብር ገደማ የሚሸፍኑ ሥራዎች መከናወን መቻላቸውን - በመግለጽ፡፡
ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ የመንግሥትና የግል አጋርነትም አዲስ አበባ ላይ በደንብ እየተተገበረ መሆኑን በመጠቆም፤ በመዲናዋ የ120ሺ ቤቶች ግንባታ መጀመሩን ለአብነት ይጠቅሳሉ፡፡
በሌላ በኩል፤ ትልቁ የጥንካሬያችን ምንጭ የበጀት አጠቃቀማችን ነው፤ ይላሉ ከንቲባዋ፡፡ “ሩቅ ሳትሄዱ የዛሬ አራትና አምስት ዓመት የነበረው ዳታ በእጃችን አለ፡፡ ካፒታል በጀት ከ50 እጅ በታች ነው የነበረው፡፡ በዚህ ሩብ ዓመት 70 እጁ ነው ለካፒታል በጀት የዋለው፡፡” ብለዋል፤ በንጽጽር በማሳየት፡፡
ሌላው የጥንካሬ ምንጭ ደግሞ ውጤታማ የክትትልና የቁጥጥር (ሱፐርቪዥን) ሥራ መሆኑን የገለጹት ከንቲባ አዳነች፤ “ቆመን ባንከታተል በዚህ ደረጃ ውጤት ሊመጣ አይችልም ነበር” ሲሉ አስረግጠው ይናገራሉ፡፡ የክትትልና የድጋፍ ሥርዓቱ ውጤትን የሚያመጣ ይሆን ዘንድ የሚሰራን የሚያበረታታ፣ ጉድለት ያለበትን ጉድለቱን ማሟላት የሚችልበትን አቅም እንዲፈጥር የሚደግፍ ሆኖ መቀረጽ እንዳለበትም ያስረዳሉ፡፡ ክትትልና ድጋፍ እንዲሁም ሱፐርቪዥንና ኦዲት የሚያደርጉት ደግሞ የተለያዩ አካላት ናቸው - ከምክር ቤት እስከ ፌደራል መንግሥት እንዲሁም እስከ ፓርቲ የሚደርሱ፡፡
ወደ ኋላ መመለስ አይታሰብም
ከንቲባዋ የተመዘገቡ ውጤቶችንና የመጡ ለውጦችን ብቻ አይደለም የዘረዘሩት፤ ጉድለቶችንና ውስንነቶችንም አንስተዋል፡፡ ውጤቶችና ለውጦች የተገኙበትን መንገድ ስናይ በብዙ ክትትል፣ በብዙ ጉትጎታና በብዙ ግምገማ ነው የሚሉት ከንቲባዋ፤ በትጋት ሰርቶ ውጤት ማስመዝገብ ገና ባህልና ልምምድ አለመሆኑን ይገልጻሉ፡፡ “ክትትልና ጉትጎታው ቀዝቀዝ ቢል የጀመርናቸው ሥራዎች ይቀዛቀዛሉ፤ ስለዚህ ወደ ባህል መቀየር አለብን” ብለዋል፡፡
ከንቲባዋ አክለውም፤ “አቅዶ 24 ሰዓት መሥራትን እንዲሁም በሽፍት መሥራትን ባህል ልናደርገው ይገባል፡፡ ጽዳትና ውበት ባህል መሆን አለበት፤መቆሸሽን መጠየፍ አለብን፡፡ እኒህ የምንላቸውን አሰራሮች እንዲሁም ውጤታማነትን ባህል እያደረግን ለመሄድ ነው ማቀድ ያለብን፡፡ አዲስ አበባ ይሄን ጉዞ ጀምራለች፤ ወደ ኋላ መመለስ አይቻልም፤ መመለሻ መንገድም የለም፤ መሄድ ያልቻለ ይወጣል እንጂ፡፡” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በግምገማው ማጠናቀቂያም የአፈፃፀም ውስንነትን በማስተካከል፣ አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ በማስደገፍ፤ፈጣን፤ቀልጣፋና ተደራሽ እንዲሆን አሰራሮችን ይበልጥ በማዘመን፣ ብልሹ አሰራርና ጉቦኝነትን በመታገል እንዲሁም የገቢ አሰባሰብና ቅንጅታዊ አሰራርን በማጠናከር የተጀመሩ ስራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ በትኩረት እንደሚሰራ አቅጣጫ ተቀምጧል፡፡