Administrator

Administrator

Monday, 13 January 2025 00:00

ሀ’ሊዩ

ዓለምን እየገዛ ያለው
 የደቡብ ኮርያ ሞገድ



ሀገራችንን ጨምሮ “በማደግ ላይ ያሉ” ተብለው የተፈረጁ ሀገራት (developing countries) ስለእድገታቸውና ስለወደፊት ውጥኖቻቸው ሲወያዩ፣ ደቡብ ኮርያን እንደ አብነት ሲጠቅሱ መስማት የተለመደ ጉዳይ ነው። እውነት አላቸው! ደቡብ ኮርያ ከጥቂት አስርት ዓመታት በፊት በቅኝ ግዛት ስር የምትማቅቅና በእርስበርስ ጦርነት ምክንያት ኢኮኖሚዋ የደቀቀ ሀገር ነበረች። ለማስታወስ ያህል እ.ኤ.አ. ከ1910 እስከ 1945 ድረስ በጠቅላላው በኮርያ ልሳነ ምድር (Korea peninsula) ይኖሩ የነበሩት ኮርያውያን በጃፓን ቅኝ ግዛት ሥር ይተዳደሩ ነበር። ከዛ አስከፊ የጭቆና ጊዜ ነጻ ከወጡ በቅጡ እንኳን አምስት ዓመት ሳይሞላቸው ደግሞ በእርስበርስ ጦርነት መታመስ ጀመሩ። ዓለማችን ካስተናገደቻቸው አስከፊ ጦርነቶች መካከል አንዱ የሆነውና እ.ኤ.አ. ከ1950 እስከ 1953 ድረስ የዘለቀው የኮርያ ጦርነት (Korean war) የኮርያን ምድር ሰሜንና ደቡብ በሚባሉ ሁለት ሀገራት ከፋፈለ።
 እዚህ ላይ ሀገራችን ኢትዮጵያም 6,037 እግረኛ ጦር ሰራዊት (የቃኘው ሻለቃ ጦር) በመላክ በኮርያ ጦርነት ተሳትፋ እንደነበር ልብ ይሏል። እነዚህ ሁለት አበይት ክስተቶች የኮርያን ምድር ወደ ድህነት አረንቋ ከመክተት አልፈው የኮርያውያንን የመኖር ህልውና ጭምር የተፈታተኑም ነበሩ። ደቡብ ኮርያ ግን ትንግርታዊ በሆነ መልኩ ባጭር ጊዜ ውስጥ ኢኮኖሚዋን በማሳደግ ከዓለም ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገራት ተርታ መመደብ ቻለች። ከምንም በላይ ደግሞ ሀገሪቱ እዚህ ግባ የሚባል የተፈጥሮ ሀብት ሳይኖራት፣ ለዚህ መብቃቷ የጽናትና የእድገት ምልክት እንድትሆን አስቻላት።
ዛሬ ዛሬ ደቡብ ኮርያ በኢኮኖሚዋ ብቻ ሳይሆን ተጽዕኖ ፈጣሪ በሆኑ ባህሎቿም በዓለም መድረክ እየታወቀች መጥታለች፡፡ እነዚህ ተጽዕኖ ፈጣሪ ባህላዊ እሴቶች በሀገሬው ዘንድ “ሀ’ሊዩ (한류)” በመባል የሚጠሩ ሲሆን፤ የምዕራቡ ዓለም ደግሞ የኮርያ ሞገድ (K-wave) ሲል ይጠራቸዋል። ይህን አይነት ስያሜ ማግኘታቸው መቼም በጣም ባጭር ጊዜ (በፍጥነት) የዓለምን ቀልብ መሳብ መቻላቸውን ለማሳየት እንደሆነ መገመት ይቻላል። በዚህች አጭር ጽሑፍም ትኩረታችንን ዓለምን እየገዙ ባሉት የደቡብ ኮርያ ዋና ዋና ባህላዊ እሴቶች ላይ በማድረግ በወፍ በረር እንዳስሳቸዋለን። ቅኝታችንንም ሀገሪቱ በዓለም መድረክ በበጎ ጎኑ እንድትሳልና እንድትታወቅ ካደረጓት ባህላዊ እሴቶቿ መካከል ግንባር ቀደሙ በሆነው የደቡብ ኮርያ የፖፕ ሙዚቃ ስልት (K-pop) እንጀምራለን።
 የK-ፖፕ ማዕበል ከሀገሬው አልፎ ዓለም አቀፋዊ ወደሆነ የሙዚቃ ዘውግ የተሸጋገረው በጣም አጭር በሚባል ጊዜ ውስጥ ነው። በተለይ ደግሞ እ.ኤ.አ. በ2012 ፓርክ ጄይ ሳንግ በሚባለው ሙዚቀኛ (በመድረክ ስሙ PSY) የተቀነቀነውና “ጋንግናም ስታይል” በመባል የሚታወቀው ነጠላ ዜማ ለኮርያ ፖፕ ሙዚቃ የዓለም አቀፍ ስኬት መንገዱን የጠረገ ተደርጎ ይወሰዳል። ከዚያን ጊዜ ጀምሮ በየጊዜው ገናና የሆኑና ዓለም አቀፍ አድናቆትን ያተረፉ በርካታ የK-ፖፕ አርቲስቶች (ዘፋኞች) መምጣት ችለዋል። አንዳቸውም ግን በአሁኑ ወቅት እጅግ ተወዳጅ የሆኑትንና “BTS” በመባል የሚታወቁትን የሙዚቃ ቡድኖች የሚስተካከሉ አይመስሉም። BTS የሙዚቃ ቡድን ሰባት ወጣት ድምጻውያንን ያካተተ ሲሆን፤ ድምጻውያኑ በግልም በቡድንም በመሆን በርካታ ዓለም አቀፍ ሽልማቶች ማሸነፍ የቻሉ ናቸው። ይህም ብቻ ሳይሆን ባላቸዉ ዓለም አቀፍ ተቀባይነት ምክንያት በተባበሩት መንግሥታት ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ተገኝተዉ ንግግር እስከማድረግ ድረስም ደርሰዋል። ባጠቃላይ BTSን ጨምሮ ሌሎች የK-ፖፕ አቀንቃኞች ቋንቋ ሳይገድባቸው የደቡብ ኮርያን ባህል የሚያንጸባርቁ ዜማዎችን በማቀንቀን ሚሊዮኖች በደቡብ ኮርያ ፍቅር ሀ’ሊዩ — ዓለምን እየገዛ ያለው የደቡብ ኮርያ ሞገድ እንዲወድቁ አድርገዋል። በዚህ ዓለም አቀፍ ተጽዕኗቸውም በየደረሱበት ሁሉ የሀገሪቱ የባህል አምባሳደር መሆን ችለዋል።
ልክ እንደ K-ፖፕ ሁሉ በመዝናኛው ኢንዱስትሪ ዘርፍ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ መፍጠር የቻሉትና የኮርያ ሞገድ አካል የሆኑት ደግሞ የኮርያ የቴሌቪዥን ድራማዎች (K-drama) እና ፊልሞች (K-movie) ናቸው። በቅርቡ እንኳን እጅግ ገናና ከሆኑትና የተለያዩ ሽልማቶችን ማሸነፍ ከቻሉት መካከል “Parasite” የተሰኘውን ፊልምና “Squid Game” የተሰኘውን ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማን መጥቀስ ይቻላል። እነዚህ ጥልቅ በሆኑ ስሜቶችና ትእይንቶች የሚታወቁት የደቡብ ኮርያ የቴሌቪዥን ድራማዎችና ፊልሞች የሀገሪቱን ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ልማድ በዓለም ዙሪያ ላሉ ማህበረሰቦች (ተመልካቾች) ማስተዋወቅ ችለዋል። በዚህም ከመዝናኛነት አልፈው የደቡብ ኮርያን የቱሪዝም ፍሰት እጅግ እንዲያድግ በማድረግ ጉልህ ሚና እየተጫወቱ ነው። ይህንንም ለመረዳት በደቡብ ኮርያ ድራማዎችና ፊልሞች ፍቅር ተነድፈው ወደ ሀገሪቱ የሚጎርፉትንና ስፍር ቁጥር የሌላቸውን አሜሪካውያን፣ አውሮፓውያንና እስያውያን መመልከት በቂ ነው።
በእኛም ሀገር ቢሆን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የደቡብ ኮርያ ድራማዎችና ፊልሞች ተወዳጅነትን እያተረፉ መጥተዋል፡፡ በመቐለ ዩኒቨርሲቲ በማስተማር ላይ በነበርኩበት ወቅትም የK-ፖፕ ሙዚቃዎችን ማድመጥ ብቻ ሳይሆን የኮርያ ድራማዎችንና ፊልሞችን በፍቅር የሚመለከቱና ቋንቋውን ጭምር መማር የቻሉ በርካታ ወጣቶችን ማግኘት ችዬ ነበር። አንዳንዶቹም ወደ ደቡብ ኮርያ መዝለቅና ስለሀገሪቱ ይበልጥ ማወቅ ትልቁ ጉጉታቸው እንደነበር አጫውተውኛል። በቅርቡም KBS በሚባል የሀገሪቱ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተላለፈ አንድ ዶክመንተሪ ላይ አንዲት ኢትዮጵያዊት ቤተሰቦቿ ለደቡብ ኮርያ ድራማዎች ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር ስትገልጽ ሰምቻለሁ። እነዚህ አጋጣሚዎች “እውነትም ሞገዱ ዓለም አቀፍ ነው!” እንድንል ያስገድዱናል። ከዚህ ባለፈም “ዓለም እንደ አንድ መንደር እየጠበበች መጥታለች” ለሚለው ዲስኩር እንደ አንድ ማሳያ መንገድ ይሆኑናል።
የደቡብ ኮርያ ሞገድና ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በመዝናኛ ኢንዱስትሪው ዘርፍ ብቻ የተገደበ አይደለም። ለዚህ ደግሞ ሁነኛ ማሳያ የሚሆነው በዓለም አቀፍ ደረጃ ተወዳጅነትን እያተረፈ ያለው የኮርያ ምግብ (K-food) ነው። ከባህላዊ ምግቦች ጀምሮ በፋብሪካ እስከሚቀነባበሩት ድረስ ያሉትን የኮርያ ምግቦች ለማጣጣም የማይፈልግ የማህበረሰብ ክፍል ያለ አይመስልም። በተለይ ደግሞ በምዕራቡ ዓለምና በሌሎች የእስያ ሀገራት ተፈላጊነታቸዉ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መሆኑ እየተስተዋለ ነው፡፡  ስፍር ቁጥር ከሌላቸዉ የደቡብ ኮርያ የባህል ምግቦች መካከልም “ኪምቺ” ተብሎ የሚጠራውና በዋናነት ከጎመን (የቻይና ጎመን) የሚሰራው የምግብ ዓይነት ከእስያ አህጉር አልፎ የምዕራቡን ዓለም ማዳረስ ከጀመረ ውሎ አድሯል። በመብላላት ሂደት (fermentation) የሚሰራውን ኪምቺ ጨምሮ ሌሎች የሀገሪቱ ባህላዊ ምግቦች በርካታ የጤና በረከቶች እንዳሏቸው መታወቁ የብዙዎች ምርጫ እንዲሆኑ አስችሏቸዋል። በነገራችን ላይ የኪምቺ ባህላዊ አሰራር ሂደት (ኪምጃንግ) እ.ኤ.አ. በ2013 በዩኔስኮ (UNESCO) የማይዳሰሱ ቅርሶች ዝርዝር ውስጥ መካተትም ችሏል። ባጠቃላይ ልክ እንደ K-ፖፕና K-ሲኒማ ሁሉ የደቡብ ኮርያ ባህላዊ ምግቦችም የዓለምን ትኩረት እየሳቡና ለሀገሪቱ እድገት የራሳቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ያሉ የሞገዱ አካል ናቸው።
ከላይ ከተጠቀሱት ዘርፎች በተጨማሪ ደቡብ ኮርያ በመዋቢያ እቃዎች (K-beauty) እና በፋሽን (K-fashion) ማዕበሎችም ዓለምን ማጥለቅለቅ ከጀመረች ሰነባብታለች። የደቡብ ኮርያ የባህል ሞገድ እያሳደረ ያለው ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ በጥናት እየተደገፈ መሆኑ ደግሞ ቀጣይ ተመሳሳይ ዘርፎች ሊኖሩ እንደሚችሉ ማሳያ ነው። እነዚህ የደቡብ ኮርያ ሞገዶች ዓለም አቀፍ ትኩረት እንዲያገኙ ያስቻሏቸው ምክንያቶች ቢኖሩም፣ ባህልን ከዘመናዊነት ጋር በተዋጣለት መልኩ አዋህደው ማንጸባረቃቸው ዋናው እንደሆነ ይነገራል። እናም ደቡብ ኮርያ ባህሏን፣ ታሪኳንና ወጎቿን በK-ፖፕ ዘፈን ምት፣ በK-ድራማና ፊልም፣ K-ምግብና ሌሎች ሞገዶች እያዋዛች ለዓለሙ ማህበረሰብ እንካችሁ እያለችና ተምሳሌትነቷን እያገዘፈች ትገኛለች። ህዝቦቿም ከባዶነት፣ ከድህነትና ከአስከፊ ጦርነት ተነስቶ ዓለም አቀፍ ተጽዕኖ ፈጣሪ መሆን የሚቻልበት መንገድ ገብቷቸዋል። “የነብርን ጭራ ከያዙ አይለቁ” ነዉና ነገሩ፣ ለዚህም ዕለት ተዕለት በጽናት የሚታትሩ ሆነዋል።
የአዲስ አድማስ ጋዜጣ የረጅም ጊዜ አምደኛ የሆነዉ ደራሲና ሃያሲ ደረጀ በላይነህ ባሳለፍነዉ ሳምንት ባስነበበን “የአዲስ አድማስ ትዝታዬ አጽቆች!” ጽሑፍ ዉስጥ የአዲስ አድማስ ጋዜጣን ጉዞ ሲገልጽ እንዲህ አለ፤ “…በተለያዩ የዕድገት አንጓዎች፣ በተዥጎረጎሩ የሀገር ጉዞ ምዕራፎች፣ በምጣኔ ሀብታዊ መንገዳገዶች ስታልፍ ያንን ሁሉ አስልታ፣ መክራና ዘክራ ኀላፊነቷን ተወጥታለች። በዚያ ሂደት እነሆ አሁን የብር ኢዩቤልዩ ደጅ ላይ መድረሷ የሚያሳየን፣ ብስለትና ዕድሜ በንባብ ከታጀቡ፣ ከኪሳራ ነፃ መሆናቸውን ነው።” እኔም የደቡብ ኮርያን አጠቃላይ የእድገት ጉዞ ለመግለጽ ጸሐፊዉ የተጠቀማቸዉን ቃላት መዋስ ፈለግሁ። ማጠቃለያ ይሆነኝ ዘንድ! ደቡብ ኮርያ በኢኮኖሚ ኃያል ሀገር ለመሆን ባደረገችው ጉዞ በተለያዩ የዕድገት አንጓዎች ውስጥ አልፋለች። በእነዚህ የእድገት ምዕራፎች ዉስጥ ያጋጠሟትን የትየለሌ ፈተናዎች ተቋቁማ ዛሬ ላለችበት ደረጃ መብቃቷ ደግሞ ሀገሪቱ የእድገት ብቻ ሳይሆን የጽናት ተምሳሌት መሆኗንም ያሳያል። የደቡብ ኮርያ የእድገት ጉዞ የሚያሳየን ሌላዉ ነገር ብስለት፣ ጥበብና ማስተዋል የተሞላበት አካሂያድ መከተል ከጦርነት ኪሳራ ነፃ መዉጫ ሁነኛ መንገድ መሆኑን ነው። በተጨማሪም እንዲህ አይነት አካሂያድ መከተል ባህልና እሴት ብለው የያዟቸው ነገሮች ተጽዕኖ ማምጣት የሚያስችሉ ሞገዶችን መፍጠሪያ ግብዓቶች ሊሆኑ እንደሚችሉ ያመላክታል። አልታየን ብሎ እንጂ እንደኛ የባህል ጎተራ የሆነ ሀገር ማግኘት መቼም ቀላል አይደለም። ለዚያውም ከዉጭ ሲታይ የሚያስቀና! እናም የአዲስ አድማስ ጋዜጣን የ25ኛ ዓመት የብር ኢዩቤልዩ በዓል ስናከብር ትልቁ ምኞቴ፣ ዓለምን የምናንበረክክበት የሀ’ሊዩ ውሽንፍር ይመታን ዘንድ ነው። ኢ-ፖፕና ኢ-ድራማ ብለን ብለን ቢያቅተን ኢ-እስክስታ፣ ኢ-ጩምቦ፣ ኢ-ጥዕሎ፣ ኢ-ቡና፣ ኢ-ጠላ፣ ኢ-ቡሄ፣ ኢ-ቡርሳሜ… ማለት መቼም አያቅተን!? ቸር ያቆየን!

በሀገራችን የሥነጽሑፍ ጉዞ ውስጥ አሻራቸው የማይደበዝዝ፣ አበርክቷቸው የጎላ፣ በዚህም ስማቸው በደማቁ የሚጠቀሱ ጸሐፍት ጥቂቶች ናቸው፡፡ ከእነዚህም አንዳንዶቹ ብዙ የጻፉ፣ ደጋግመው ያሳተሙ ናቸው፡፡ ከፊሎቹ ደግሞ ሁለት እና ሦስት ሥራዎችን ብቻ ያሳተሙ (የጻፉ ከማለት መቆጠቤ፣ አለማሳተም ላለመጻፍ ምስክር አይቆምም በሚል ነው) ናቸው፡፡ ከእነዚህ ከሁለት ዓይነቶቹ ወጣ ብለን ስንማትር ደግሞ፣ በሌላ ጎራ ልናስቀምጣቸው የሚቻለን ጸሐፍት አሉ - መልከ ብዙ ልንላቸው የሚቻለን ጸሐፊያን፡፡
እነዚህኞቹ በበርካታ ዘውጎች ራሳቸውን የገለጡ ብቻ ሳይሆኑ፣ መቻላቸውንም ያስመሰከሩ፣ ገበታቸው የደረጀ፣ ማዕዳቸው የሰፋ፣ በዚህም ያቀብሉት የሞላቸው ዓይነት ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ ሥነጽሑፋችን ብዙም ደረታችንን ነፍተን፣ ድምጻችንን አሰምተን የምንጠቅሳቸው ጸሐፍት ያሉት አይመስልም፡፡ ወይም ሥራቸውን አደባባይ አውለው፣ እኛም ዳብሰን፣ አንብበን እንመሰክርላቸው ዘንድ አላገኘናቸውም፡፡
በእኔ ዕይታ መልከ ብዙ ብለን እንጠራቸው ዘንድ የእጃቸው ፍሬዎች ከሚፈቅድላቸው፣ ደግሞም ካሳመኑን ጸሐፍት አንዱ ነቢይ መኮንን ይመስለኛል፡፡ በእርግጥ በተለያዩ አጋጣሚዎች ነቢይ “ከሁሉም በላይ ገጣሚ” ነኝ ሲል ቢደመጥም ቅሉ፣ እኛም መረጃ ጠቅሰን፣ ምስክር አቁመን ሌሎች አቻ መልኮችም አሉህ የማለት መብታችንን ተጠቅመን፣ የከያኒውን መልከ ብዙነት መመስከር ማንም የማይነጥቀን የራሳችን ፈቃድ ነው፡፡ የዚህ ጽሑፍ ዓላማ ነቢይ የተገለጠባቸውን በልዩ ልዩ ዘውጎች ሥር የሚመደቡ ሥራዎቹን የጋዜጣ አምድ በሚፈቅድልን መጠን በማነሳሳት፣ የከያኒውን መልከ ብዙነት መግለጽ ነው፡፡
፩. ተርጓሚው ነቢይ
ትርጉም፣ እጅግ ጥልቅ ቢሉ ውስብስብ፣ በርካታ ብቃቶችን በአንድ ጊዜ በዛው ቅጽበት መጠቀምን ወይም አገልግሎት ላይ ማዋልን የሚጠይቅ መጠበብ ነው፡፡ ተርጓሚውም በዚህ መጠበብ ውስጥ በምልዐት ማለፍ ይችል ዘንድ በርካታ ብቃቶችን ሊካን ይገባዋል፡፡ ተተርጓሚውንና የሚተረጎምበትን ቋንቋ ማወቅ ብቻ (ቋንቋውን መናገር፣ በቋንቋው መጻፍ) ተርጓሚ አያደርግም፤ በፍጹም፡፡ ይልቁንም የሚተረጉሙትን ድርሰት ባህል፣ እሴቶች፣ እምነቶች፣ ተተርጓሚው ድርሰት የተጻፈበትን ዘመንና የዘመኑን መንፈስ የመሳሰሉትን ጠንቅቆ መረዳት ይጠይቃል፡፡ ከዚህ ሁሉ በፊትም ተተርጓሚውን ቋንቋ ከእነጓዙ በጥልቀት ማወቅን ግድ ይላል፡፡ ይሄ እንግዲህ ከተተርጓሚው ቋንቋ አንጻር ነው፡፡ ከዚህ በበለጠ ደግሞ ድርሰቱ የሚቀዳበትን/ የሚተረጎምበትን ቋንቋ መጠንቀቅ (በምልዐት ማወቅ) ያስፈልጋል፡፡ እነዚህ ብቃቶች በትርጉም ሥራዎቹ ላይ ፍንትው ብለው የሚታዩ ጸሐፊ ለብቁ ተርጓሚነቱ አሌ የለውም፡፡   
ነቢይ እንደጸሐፊ በኖረበት የሥነጽሑፍ ዓለም በርካታ ዘውግ ያላቸውን ሥነጽሑፋዊ ሥራዎችን (አጭርና ረጅም ልቦለዶችን፣ ተውኔቶችን እና ግጥሞችን) ተርጉሟል፤ አሳትሟልም፡፡ እነዚህም የትርጉም ሥራዎቹ ሙሉ ለሙሉ መነበብንም መደነቅንም የተቸሩ ናቸው፡፡
ስሙ በጉልህ ከሚነሳበት በከባዱና በአሰቃቂው የማዕከላዊ እስር ቤት ሆኖ “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚል ርዕስ የተረጎመውን የእውቋ አሜሪካዊት ደራሲ Margaret Mitchell “Gone with the Wind” ረጅም ልቦለድን ጨምሮ፣ የDan Brown ረጅም ልቦለድ “The Da Vinci Code” “ዘ ዳ ቬንቺ ኮድ” በሚል ርዕስ፣ የNawal El-Saadawiን “Woman at Point Zero”፣ የMitchell David Albomን “Tuesdays with Morrie” “ፕሮፌሰሩ” ብሎ፣ የMarina Lewycka “A Short History of Tractors in Ukrainian” የRandy Pauschን “The Last Lecture” “የመጨረሻው ንግግር” ብሎ ድንቅ በሚባል የቋንቋ ብቃት፣ በውብ ስልት ተርጉሟል፡፡
አስቀድሜ እንዳልኩት ድንቅ ተርጓሚነቱን ያሳየው በልቦለድ ዘውግ ብቻ አይደለም፡፡ የዓለማችንን ስመ ጥር ጸሐፌ ተውኔቶችን ተውኔቶች፣ ገጣሚያንንም ግጥሞች ዕጹብ ድንቅ በሚባል ብቃት ተርጉሟል፡፡ የእውቁን ጀርመናዊ ፈላስፋና ጸሐፊ የEphraim Lessing ተውኔት የሆነውን “Natahn the Wise” “ናትናኤል ጠቢቡ” ብሎ የBernard Shawን ተውኔት፣ እንዲሁም የShakespeare ተወዳጅ ሥራ የሆነውን “Julius Caesar” ተርጉሞ ለመድረክ አብቅቷል፡፡ ሌሎች የነቢይን የተርጓሚነት ብቃት የሚመሰክሩት ደግሞ፣ የበርካታ ባለቅኔዎች ለቁጥር የሚታክቱ በርካታ ግጥሞች ሲሆኑ፣ እነዚህ ትርጉም ግጥሞቹ ለዓመታት በአዘጋጅነት በመራው በአዲስ አድማስ ጋዜጣ፣ አለፍ አለፍ እያሉም ባሳተማቸው የግጥም መድበሎቹ ውስጥ እናገኛቸዋለን፡፡
፪. ጋዜጠኛው ነቢይ
የነቢይን ብርቱ ጋዜጠኝነት ለመመስከር ብዙ መድከም፣ አስረጂ ፍለጋ መባዘን ያስፈልግ አይመስለኝም፡፡ የዚህችው (የአዲስ አድማስ) ጋዜጣ አንባቢያን አጋዥ ተባባሪ ሆነው እንደሚሞግቱልኝ ጥርጥር የለውም፡፡ ነቢይ የዛሬ 25 ዓመት በምስጉኑ የኪነጥበብ ተቆርቋሪ እና የቢዝነስ ሰው በአሰፋ ጎሳዬ የተመሠረተችው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ፣ ተናፋቂና ተነባቢ፣ በብዙ ሺዎች የምትወደድ ሆና ከዓመት ዓመት እንድትዘልቅ ማድረግ ችሏል፡፡ በአንድ ጋዜጣ ወይም መጽሔት ላይ የዋና አዘጋጁ ተግባር ምን ያህል አድካሚና በጥንቃቄ የተሞላ የሠርክ ተግባር መሆኑን እዚህ ለመዘርዘር መሞከር ድካም ነው የሚሆነው፡፡ ምናልባት “architect of the building” ወይም “captain of the ship” የሚሉትን አነጋር ጠቅሶ ማለፉ ይሻል ይሆናል፡፡
ነቢይን እና በዋና አዘጋጅነት ከሁለት አሠርት ዓመታት በላይ የመራትን አዲስ አድማስን አንስቶ የነቢይን ርዕሰ አንቀጾች እና የጉዞ ማስታወሻዎች አለማንሳት ማጉደል ነው የሚሆነው፡፡ ወዲህም ብርቱ ጋዜጠኛ ነው ብዬ ለምሞግትለት መልከ ብዙ ከያኒ ነቢይ አስረጂዎቼ ናቸውና ትንሽ ልሂድባቸው፡፡
ነቢይ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ አዘጋጅነት ዘመኑ ቢያንስ ከ900 በላይ ርዕሰ አንቀጾችን ጽፏል፡፡ በእኔ ግምገማ እነዚህ ርዕሰ አንቀጾች ከዚህ በፊት በሀገራችን የሕትመት ሚዲያ ውስጥ ከስልት አንጻር ፍጹም ያልታዩ (በዓለምም ያላጋጠሙኝ) የተለየ ቅርጽና ስልት ያላቸው ናቸው፡፡ የነቢይ ርዕሰ አንቀጾች መንገር ወይም ማስተላለፍ የሚፈልጉትን መልዕክት የሚገልጹት በተረት ውስጥ ነው፡፡ እጅግ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር፣ ሙሉ ለሙሉ በሚባል ደረጃ ነቢይ ተረቱን ሲቋጭ የሚላት ነገር ጥቂት ናት፡፡ እነዚህ ተረቶች በተረት ያደገውን ቢሉ የኖረውን፣ ለሁሉ ስለሁሉ ተረትን እማኝ የሚያደርገውን ኢትዮጵያዊ አንባቢ ፍላጎት በመግዛት ተነባቢነትን በማትረፍ፣ አዘጋጁ ነቢይ የጋዜጣዋ አቋም የሆነውን ሃሳብ በዚሁ ውስጥ እያዋዛ ማድረስ እንዲችል አድርጎታል፡፡ ይህንን መንገድ ከነቢይ በፊት ማንም አልሞከረውም፡፡    
ነቢይ በዚህ ስልት ተነባቢ ርዕሰ አንቀጽን ከመፍጠር ባለፈ (በአጋጣሚም ይሁን ይሁነኝ ብሎ) ሌላም ያሳካው አቢይ ጉዳይ አለ፡፡ ይህም ጋዜጣዋን ከጥቃትና ከመዘጋት ከልሎ በዘመናት ውስጥ ህልውናዋን ጠብቃ እንድትዘል ማስቻሉ ነው፡፡ ምንም እንኳን አዲስ አድማስ በአብዛኛው ማህበራዊና ኪነጥበባዊ ጉዳዮች ላይ የምታተኩር ብትሆንም፣ ሁሌም እንደማንኛውም የሕትመት ሚዲያ ሁሉ በሀገሪቱ ፖለቲካዊ፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሌሎች ጉዳዮች ላይ የራሷ አቋም አላት፡፡ ይህንንም በዋና አዘጋጁ በሚጻፈው ርዕሰ አንቀጽ ላይ ታሰፍራለች፡፡ ሆኖም ጥንቁቁና በሳሉ ነቢይ የተከተለው ስልት በማዋዛት መግለጽ መሆኑ፣ በጋዜጣዋ ሚዛናዊነት ላይ ተደምሮ ጋዜጣዋ በየወቅቱ በገጠሙ ከባድ ፖለቲካዊ ምስቅልቅል ውስጥም ከሕትመት ሳትጎድል ለአንባቢዎቿ እንድትደርስ ምክንያት የሆነ ይመስለኛል፡፡
ነቢይ በርካታ ተወዳጅ የጉዞ ማስታወሻዎችን ከትቦ አስነብቦናል፡፡ የነቢይ የጉዞ ማስታወሻዎች ተራ ዘገባዎች አይደሉም፡፡ በጉጉት የሚጠበቁ፣ ተስገብግበው የሚነበቡ ዓይነት እንጂ፡፡ በሀገረ አሜሪካን በእንግድነት በነበረው ቆይታ ያስነበበን “የእኛ ሰው በአሜሪካ” እና እንደ ኢራን በመሳሰሉት የውጪ ሀገሮች ባደረጋቸው ጉዞዎች የከተባቸው የጉዞ ማስታወሻዎች በጠንካራ ሥነጽሑፍነት ሊጠቀሱ የሚችሉ ዓይነት ናቸው፡፡ እነዚህ ማስታወሻዎች በወቅቱ ለአንባቢ ይደርሱባት የነበረችውን ጋዜጣ (አዲስ አድማስ) ተናፋቂነትና ተነባቢነት በመጨመር ረገድ የነበራቸው አስተዋጽኦ ቀላል አልነበረም፡፡  
፫. የድራማ እና የዘፈን ግጥም ጸሐፊ
ነቢይ በቴሌቪዥን ድራማ እና በዘፈን ግጥም ጸሐፊነትም ራሱን መግለጥ የቻለ መልከ ብዙ ከያኒ ነው፡፡ ትኩረቱን የወቅቱ የሀገሪቱ (በእርግጥ ዛሬ ብሷል) አንገብጋቢ ሰንኮፍ በነበረው ሙስና ላይ ያደረገ “ባለጉዳይ” የተሰኘ ሳትሪካል ድራማ ጽፎ ለዕይታ አብቅቷል፡፡ በ1980ዎቹ መጨረሻ በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ለበርካታ ሳምንታት ይታይ የነበረው ይህ ድራማ፣ ከፍተኛ ትኩረትን የሳበና በርካታ ተመልካቾችን ከቴሌቪዥን ፊት ያስቀመጠ ድንቅ ኪነጥበባዊ ሥራ ነበር፡፡
መልከ ብዙው ከያኒ ነቢይ ቁጥራቸው ጥቂት ቢሆንም በዘፈን ግጥሞችም ተራቋል፡፡ በ1990ዎቹ ኤችአይቪ ኤድስ የብዙዎችን ቤት የሐዘን ማቅ ባለበሰበት፣ በርካታ ህጻናትን ወላጅ አልባ ባደረገበት፣ የቫይረሱ ተጠቂዎች እንደ አውሬ ይፈሩበት፣ እንደ ጸያፍ ይገለሉበት በነበረበት በዛ ጨለማ ውስጥ፣ እጅግ አስተማሪ የሆነ መልዕክት በውብ አቀራረብና የሙዚቃ ስልት ለአድማጭ ተመልካች ያቀረበው “ማፍቀር ነው መሰልጠን” የተሰኘው የወቅቱ ተወዳጅ የሙዚቃ ሥራ ግጥም ጸሐፊ ነቢይ ነው፡፡ እንዲሁም የኢትዮጵያ ዘመናዊ ሙዚቃ ተጠቃሽ ድምጻዊ አስቴር አወቀ ያቀነቀነችው “መጠንቀቅ ነው ደጉ፤ ላንተም ለኔም ጤና” የሙዚቃ ሥራ ግጥም ደራሲ መልከ ብዙው ከያኒ ነቢይ መኮንን ነው፡፡
፬. ከሁሉም በላይ ገጣሚ
ምንም እንኳን ነቢይ ራሱን ከሁሉም በላይ እንደገጣሚ ቢቀበልም፣ የጠቆምኳቸውን ራሳቸውን የገለጸባቸውን ዘውጎች አስረጂ አድርገን ገፍተን ብንመረምር “ገጣሚ ብቻ አይደለህም፤ መልከ ብዙ ከያኒ እንጂ” ብለን አፋችንን ሞልተን እንሞግተው ዘንድ ይቻለናል፡፡ እንዴት ቢሉ፣ ከያኒው ራሱን የገለጠባቸው ዘውጎችም ሊያስጠሩት የሚያንሱ ስላይደሉ፡፡ የነቢይን ግጥሞች ተተኳሪ ጭብጦች እና ግጥሞቹ የተበጀባቸውን ቋንቋ ብቻ በጥቂቱ ላንሳ፡፡ ነቢይ ሦስት የግጥም መድበሎችን አሳትሞ ለአንባቢያን እነሆኝ ብሏል፡፡ እነዚህ መድበሎች “ጥቁር ነጭ ግራጫ”፣ “ሥውር ስፌት ቅጽ 1” እና “ሥውር ስፌት ቅጽ 2” ናቸው፡፡ የነቢይን ግጥሞች በመቃኘት የግጥሞቹ ተመላላሽ ጭብጦች ሀገር፣ ጥበብ፣ ፍልስፍና፣ ሞትና (ተቃራኒው) ህይወት፣ ፍቅር፣ ጊዜ እና ባይተዋርነት ናቸው ማለት እንችላለን፡፡ ሀገር፣ ነቢይ በርካታ ግጥሞቹን የጻፈበት ዋነኛው ማተኮሪያው ነው፡፡ ከእነዚህ ሀገር ከሚገዳቸው ግጥሞቹ መካከል “ሀገርህ ናት በቃ” ቁጥር 1 እና 2 ውስጥ ድረስ ዘልቀው የሚሰሙ ሀገር ሙሉ ስሜትን ያቋቱ ደማቅ ግጥሞቹ ናቸው፡፡  ሞትና ተቃራኒው የሚመስለው ሕይወት፣ ሌሎቹ የነቢይ ተመላላሽ ጭብጦች ናቸው፡፡ ነቢይ ሞትን ጭብጡ አድርጎ በርካታ ግጥሞችን ጽፏል፡፡ ከእነዚህ ሞትን ጭብጣቸው ካደረጉ ግጥሞቹ አብዛኞቹ ሞትን የጠመዱ (የጠሉ)፣ በግብሩ የሚብሰለሰሉ ዓይነት ናቸው፡፡ እዚህ ላይ “ከሞት ጋር ተቃጥረን”፣ “ለካስ ሞት ግጥም አይችልም”፣ “የእድሜ እቁብ ቢኖር”… የመሳሰሉትን ተወዳጅ ግጥሞቹን ልብ ይሏል፡፡ ነቢይ ተብሰልሳይ ገጣሚ ነው፡፡ በተለይም የደጋግ (የታላላቅ) ሰዎች እጦት በእጅጉ ያብሰለስለዋል፡፡ ሞታቸው የሚፈጥረውን ሽንቁር የሕይወቱ ሽንቁር አድርጎ ነው የሚወስደው፤ የእግር እሳት ሆኖ ያትከነክነዋል፡፡ ለዚህም ይመስላል የሀገር ዋርካዎቹ ህልፈት የነቢይ ግጥሞች ጭብጥ የሆኑት፡፡ ነቢይ በመድበሉ ውስጥ የዚህ ዓይነት ጭብጥን ያዘሉትን ግጥሞቹን ክቡር ስም ብሎ ነው በወል የሚጠራቸው፡፡
በዚህ ረገድ ለሠዓሊና ገጣሚ ገብረ ክርስቶስ ደስታ ህልፈት የተቀኘው “ገብሬ”፣ ለታላቁ ባለቅኔ ለጸጋዬ ገብረ መድኅን ህልፈት የከተበውን “አይሉት ነገር አባባል/ የጥበብ ሰው ቅስም ያማል”ን ማንሳት እንችላለን፡፡ ለታላቁ ደራሲያችን ለበዓሉ ግርማ የጻፈው ግጥምም እንዲሁ ቀጣዮቹን ተብሰልሳይም ጠያቂም ስንኞች አዝሏል፡፡
ይሄ ምን አማርኛ ነዉ፣ ፌዙ ለጆሮ የከፋ
ምን ያለስ ልብስ ሰፊ ነዉ፣ ሞትን በልኬ እሚሰፋ?
ሞት ከአረጋዊ ቢያረጅም፣ ከሰዉ የባሰ ክፉ ነዉ
በተለይ ደራሲ ሲያገኝ፣ ሲስገበገብ ለብቻዉ ነው
የነቢይ ቋንቋ ጸናን ያይደለ ገር ነው፡፡ ደግሞም ቀላል፤ እንደጨዋታ ያለ፡፡ ደግሞም ለወግ የሚቀርብ፡፡ ነቢይ የደረጀ ቃላዊ ሀብቶች ባለቤት ነው፡፡ ግን ደግሞ እነሱን እንደወረዱ ሲጠቀማቸው አይስተዋልም፡፡ ይልቁንም ደቂቁ ቢሉ ለጋ አንባቢው ሳይቀር እንዲረዳቸው አድርጎ አቅልሎ ነው የሚሸምናቸው፡፡ የነቢይ ቋንቋ ቀላል ነው፤ ተራና ተርታ ያልሆነ፡፡ ደግሞም አዘቦታዊ፤ ያልጨረተ ኦርጅናሌ ነው፡፡ ነቢይ የትኛውን ቃል የት፣ ከምን ጋር እንዴት ባለ መልኩ ማቀናጀት እንዳለበት የሚያውቅ ጥንቁቅና በሳል ገጣሚ ነው፡፡ በእኔ መረዳት ነቢይ በቀላል የቋንቋ አጠቃቀም ግጥምን ለወግ ያቀረበ ገጣሚ ይመስለኛል፡፡
፭. ሌሎች የነቢይ መልኮች
ነቢይ መኮንን ጽፎና አሳትሞ ከማለፍ ባለፈ በአማርኛ ሥነግጥም ውስጥ የሚወሳባቸውን መልኮች ነድፎ ያለፈ ከያኒ ይመስለኛል፡፡ እነዚህም መልኮች ከቀላል አሰነኛኘት እና በአዘቦታዊ ቃላት ረቂቅና ውስብስብ ሃሳቦችን መግለጽ ከመቻል አንጻር ሊወሱ ይችላሉ፡፡
ነቢይ ከግጥማዊ የአሰነኛኘት ድንጋጌዎች ይልቅ ሃሳቡ የሚገደው ዓይነት ገጣሚ ነው፡፡ ይህንን ስል ግን ነቢይ ለተለመዱት የአማርኛ ግጥም አሰነኛኘቶች አይገዛም እያልኩ አይደለም፤ ፍጹም ተገዢያቸው ሆኖ ሲያገለግላቸው አይታይም እያልኩ እንጂ፡፡ የነቢይ ግጥሞች ከአሰነኛኘታቸው ግላዊነት በመነጨ፣ አንዳንዶቹም በተለመደው የግጥም አነባበብ ስልት ከመነበብ ይልቅ ሌላ መንገድን የሚጎተጉቱ ዓይነት ናቸው፡፡ ነቢይ ማቅለል ላይ አብዝቶ ይተጋል፡፡ “If you can’t explain it simply, you don’t understand it well enough” እንዲል Albert Einstein፡፡
ሌላው የነቢይ መልክ እጅግ አዘቦታዊና ተርታ በሚመስሉ ቃላት ታላላቅና ውስብስብ ሃሳቦችን በቀላሉ ማቅረብ/መጻፍ መቻሉ ነው፡፡ ረቂቁ ቢሉ፣ ቀድሞ ያልተሰማ/ያልታወቀ፣ ጸናን ሃሳብ በነቢይ ብዕር የሚቀርበው በቀላል ቃላት ነው፡፡ በሚያጫውቱ፣ በሚያግባቡ፣ አሁን እየገባህ ነው አይደል እያሉ ሃሳባቸውን በሚያሰርጹ ቃላት፡፡
ነቢይ በንባብ፣ በልምድ እና በበርካታ ተጋልጦዎች የበለጸገ ታላቅ ገጣሚ ነው፡፡ እውቁ የሥነጽሑፍ መምህርና በተለይም የግጥም ተመራማሪ ብርሃኑ ገበየሁ የነቢይን ምልዑ ገጣሚነት ሲመሰክር እንዲህ ይላል፡፡
“የራሱን የነቢይ ግጥሞች ኪናዊ ውበትና አማላይነት ከሦስት የገጣሚው ታላላቅ ችሎታዎች የሚነቃ ይመስለኛል፡፡ አንደኛው፣ የተራችነት ችሎታውና የገጣሚው ሰፊ የባህል እውቀት፣ ሁለተኛው ታላቅና የማይመጠን የቋንቋ ችሎታው፣ ሦስተኛው ደግሞ የአገላለጹ ወርጅናሌነት፣ ትኩስነትና ትባት ነው::”
ሌሎችም መልከ ብዙ ሊያሰኙት የሚችሉ በርካታ ጸጋዎች የከያኒው ነቢይ ሀብቶች ናቸው፡፡ ነቢይ ማንም ሊያደምጠው የሚናፍቀው፣ እድሉን አግኝቶ ማዳመጥ ከጀመረም ሁለመናውን ጆሮ አድርጎ የሚያደምጠው ድንቅ ታሪክ ነጋሪ (storyteller) ነው፡፡ ይህንን አሌ የሚለኝ ቢኖር፣ በየመድረኮቹ ያወጋቸውን፣ እንዲሁም ቃለመጠይቆቹን እንዲያደምጥ እጋብዘዋለሁ፡፡ ከዛ በኋላ ከእኔ ጋር እንደሚስማማ ጥርጥር የለኝም፡፡
በዚህ ሁሉ ላይ መልከ ብዙ ከያኒው ነቢይ ቀደምቶቹን ጸሐፍት የሚያከብር፣ ሥራቸውን ደጋግሞ የሚያወሳና የሚያከብር ትሁት ሰው ነው፡፡ ትሁትነት የነቢይ ብርቱ መገለጫ ይመስለኛል፡፡ የትኞቹንም ሃሳቦቹን በፍጹም እርጋታ ሲገልጽ ነው የምታገኙት፡፡ እሱ ቀድሞ የደረሰበትን ጉዳይ እንኳን ነቢይ የሚነግራችሁ በአዋቂነት መመካትና ኩራት ሳይሆን፣ በዛችው አፋራም ፈገግታ በከበባት የሠርክ ትህትናው ውስጥ ሆኖ ነው፡፡
እነሆ ነቢይም እንደቀደምቶቹ ሁሉ፣ የዚህችን ምድር ቆይታውን አጠናቆ ሥፍራውን ወደሌላኛው ዓለም ቢቀይርም ቅሉ፣ ራሱን በደማቁ የገለጠባቸው ታላላቅ ሥራዎቹ ሞትን አሸንፎ በትውልድ ውስጥ እንዲወሳ፣ ሃሳቦቹ እንዲጠቀሱ በዚህም ሕያው ሆኖ እንዲኖር ያስቻሉት ከያኒ ነው፡፡ ማንስ በቀጣዩ ትውልድ ውስጥ ሕያው ሆኖ ከመኖር በላይ ምንን ይመኛል?
ቸር እንሰንብት!  

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዕምሮውን ነካ ያደርገዋል የሚባል ሰው ቀን በጠራራ ፀሐይ ወደ አንድ የስልክ እንጨት (ምሰሶ) ይሄዳል፡፡ ከዚያም እንደ ስልከኛ ምሰሶው ላይ እግሩን አጠላልፎ መውጣት ይጀምራል፡፡
ሰው ምን ሊያደርግ ነው እያለ ዙሪያውን መክበብ ጀመረ፡፡ ዙሪያውን የከበበውን ሰው ያየ መንገደኛ ሁሉ ወደ ስብስቡ ተቀላቀለ፡፡ የሁሉም ሰው ጥያቄ፤
“ምን ሊያደርግ ይሆን?” የሚል ሆነ፡፡
ሰውየው መውጣቱን ቀጠለ፡፡ ህዝቡም መሰብሰቡን ቀጠለ፡፡
ከፊሉ - “ይሄ ሰውዬ ጫፍ ከደረሰ በኋላ ሊወረወር ነው፡፡ በጊዜ እናስወርደው” አለ፡፡
ከፊሉ - “ለማንኛውም ፖሊስ ብንጠራ ይሻላል”
ሌላው - “ፖሊስ ቢመጣ ምን ሊያደርግ ይችላል፡፡ በገመድ አይጠልፈው”
ሌላው - “ግዴላችሁም አንድ ሰው ተከትሎት ይውጣ”
“ተከትሎት ወጥቶ በእርግጫ ቢለውስ ዕብድ አይደለ እንዴ?”
“እባካችሁ ምንም አይሆን፤ ዝም ብለን የሚያደርገውን እንይ”
“ለምን አንጠይቀውም?”
“ምን ብለን ልንጠይቀው ነው፤ እኛ ቴሌ ኮሙኒኬሽን አደለን”
“ለምን ለሚመለከተው መስሪያ ቤት አንነግርም”
“መሥሪያ ቤቱ ንብረቴ ነው ካለ እራሱ ይምጣ እንጂ እኛ ምን ቤት ነን?”
ዕብዱ ሰው መውጣቱን ቀጠለና ጫፍ ደረሰ፡፡
ቀጠለና ከኪሱ እስክሪቢቶና ወረቀት አወጣ፡፡
ታች ያለው ሰው ግምቱን አወጋ-
“ይሄዋ ኑዛዜውን እየፃፈ ነው”
“ዕብድ ደሞ ምን ኑዛዜ ይኖረዋል?”
“ምን ይታወቃል? ሰውኮ ሊሞት ሲል የሚናገረው ነገር ይበዛል”
“እባክህ፤ መንግሥትን ሊሳደብ ይሆናል”
“መንግሥት ለመሳደብ ምሰሶ ጫፍ ላይ መውጣት አለብህ እንዴ?”
ዕብዱ ሰው ጽሑፉን ጨረሰ፡፡ በፕላስተር ምሰሶው ጫፍ ላይ ለጠፈው፡፡
እየተንሸራተተ ወደ መሬት ወረደ፡፡
ታች ከተሰበሰበው ህዝብ አንዱ፤
“ምን ብለህ ጽፈህ ነው የለጠፍከው?” አለና ጠየቀው፡፡
ዕብዱ ሰውም፡-
“ወጥቶ ማየት ነዋ!” ብሎ ሄደ፡፡
ከህዝቡ ማህል አንደኛው፤
“ወጥተን እንየው እንጂ” አለ፡፡
ሁሉም “አንድ ሰው ይውጣ” አለ፡፡
አንድ ጐበዝ ከማህል ወደ ስልክ እንጨቱ ሄደ፡፡
ሁሉ ሰው አበረታታው፡፡ “ጐበዝ ውጣ!” “ቀጥል ጀግናው!” “ይሄ ነው ወንድ!” “ግፋ!”
ሰውየው እግሩን እየሳበ ወጣ ወጣና ጫፍ ደረሰ፡፡ ወረቀቱ ላይ የተፃፈውን አየ፡፡
ታች ያለው ህዝብ “አንብብልን!” ብሎ ጮኸ፡፡
ጐበዙ ሰው ጮክ ብሎ አነበበው፤ “የምሰሶው ጫፍ እዚህ ጋ ነው!”

***
ማንኛውም ሰው ህዝብን እንዳሻው ለመንዳት ከቻለ ሀገር ላይ ችግር አለ፡፡ ያ ሰው ዕብድ ከሆነ ደግሞ የባሰ ችግር አለ፡፡ አሳሳቢ ሆነ ማለት ነው፡፡ ጥርጣሬ ላይ የወደቀ ህዝብ ይዋልላል፡፡ በመንግሥት፣ በተቋማትና በማህበራት ላይ ዕምነት አይኖረውም፡፡ ዕምነት ያጣ ህዝብ ከመምራት ዕምነት ያለው የልቡን የሚናገር ተቃዋሚ ህዝብ መምራት ይሻላል ይላሉ ፀሐፍት፡፡
ኢትዮጵያን በተለየ መንገድ ለማሳደግ ህዝብ በአጭበርባሪዎች እንዳይታለል ተቆጣጥሮ ህጋዊነትን ማስከበር ያሻል፡፡ ህዝብ ሙሉ ዕምነት ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ተቋማቱን አስተማማኝና እርግጠኛ ፍቃደ ልቡና ይለግሳቸው ዘንድ እንዳይመዘበር፣ እንዳይበዘበዝ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል፡፡ ለዚህም የአስተሳሰብ ብልጽግና፣ የግንዛቤ ጥራት፣ የልብ ለልብ መግባባትና የመቻቻል ምንነት በግልጽ የገባው ሊሆን ያሻል፡፡ ከጦርነት ይልቅ ሰላምን የሚመርጥበት ምክንያት ከልምድ ከተማረው በተጨማሪ ወቅታዊ ንቃት እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡
ሙስናን ለመቋቋም እየሰጋን መሆን የለበትም፡፡ መታሠር ያለበት ህገ ወጥ ሰው ከሆነ የፍርድ ቤት ጉዳይ እንጂ የእከሌ ከእከሌ አማራጭ መፍጠር ወይም “አጥፊው ስለበዛ እንተወው” መፍትሔ አይሆንም፡፡ ሁሉም የየድርሻውን ማግኘቱ የፍትሕን መጉላትና መጠንከርን እንደሚያሳይ አለመዘንጋት ነው፡፡ በተለይ በህዝብ ላብ የሚቀልድ ማንም ይሁን ማን ሊተው አይገባም፡፡ በተለይም በልዩ መዋቅር ተሳስሮ ጀርባው ደንደን ያለውን መተው፣ ኮሳሳውን ማጥቃት ለፍትሕ ጐጂ ባህል ነው፡፡ ይህን የሚያስከብሩ ተቋማት መጠንከር አለባቸው። ይህም ሲባል ተቋማቱ ግዑዝ አይደሉምና የሚመሯቸው ሰዎች በሚሠሩት አምነውና ጠንክረው ይጓዙ ማለታችን ነው፡፡
አበሻ አደባባይ ያምናል፡፡ ለአበሻ ሚዲያ መንግሥት ነው፡፡ ስለሆነም ለማናቸውም ሚዲያ ተጠቃሚ ተአማኒ ነው፡፡ ሚዲያ ላይ የቀረበ፤ አንድም መንግሥታዊ ነው፣ አንድም የታመነ ነው!  ቴሌቪዥን አይቶ፣ ሬዲዮ ሰምቶ የማያውቅ ሰው እንኳ ቢሆን በቴሌቪዥን ታየ፣ በሬዲዮ ተነገረ ካሉት የዕምነቱን ዣንጥላ ይዘረጋል፡፡ በአደባባይ የታየው፣ የተሰማው ነገር ህጋዊ ነው እንደማለት ነው! የዛሬ ዘመን የ “ቢዝነስ” ሁኔታ የደራሲ አቤ ጉበኛን “ጐብላንድ አጭበርባሪው ጦጣን” የሚያስታውሰን ነው፡፡ ለነገሩ የተመዘበረው ብር ብዛት ሲታይ እሰው እጅ ያለው ገንዘብ ኤሎሄ ያሰኛል፣ እንደ ልብ ደረቅ ቼክ መፃፍ፣ ባንክ ውስጥ በቂ ገንዘብ የለውም መባል፤ የወትሮ ነገር ሆኗል፡፡ ዲቪ የደረሰው ቀርቶ ያልደረሰው ይሄዳል በሚባልበት፣ ኮንዶምኒየም የደረሰው ቀርቶ ያልደረሰው ይኖርበታል በሚባልበት፣ ፖለቲካው ግራ ሲያጋባንና የምሁርነት ጥልቀት እያደር እንደ ውሃችን ቱቦ ሲደፈን
“እንተኛም ካላችሁ፣ እንገንደሰው
መኝታ እንደሆነ ቀርቷል ካንድ ሰው”
የሚል ዘፈን በምናቀነቅንበት ሀገር፤ ፖለቲካ ሁሉ የመሬት ጉዳይ ቢሆን ብዙ የሚያስደምም ሁኔታ አይሆንም፡፡
በተደጋጋሚ የምናሰማው እሮሮ መጠነ ሰፊ ሆኗል፡፡ ሙስና አጠጠ፣ ት/ቤቶች ጥራት የላቸውም፡፡ መሠረተ - ጤና እንደምንፈልገው አልተስፋፋም፡፡ ተቋማት ይቋቋማሉ እንጂ አፈፃፀም የላቸውም፡፡ ባንኮች ንፅህናቸው አልተፈተሸም፤ የከፍተኛ አመራሩ ችግር አለበት፡፡ ከፖለቲካ ልዩነት፤ ከሃይማኖት ልዩነት፣ ከዘር ልዩነት ነፃ ነን እንበል እንጂ ጣጣው አልለቀቀንም፡፡ “ሃጢያት ከተደጋገመ ፅድቅ ይመስላል” ይሏልና፣ ቆም ብለን ተግባር ላይ እናተኩር!!

የመጀመሪያው አዲስ አድማስ ጋዜጣ ታትሞ ለንባብ የበቃው ታህሳስ 29 ቀን 1992 ዓ.ም ነበር - የዛሬ 25 ዓመት በዕለተ ቅዳሜ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ያለ አንድ ቅዳሜ በስተቀር ጋዜጣው ያልታተመበት ጊዜ  የለም፡፡ ያም ቢሆን የተከሰተው በ97 ምርጫ ማግስት በተፈጠረው  ፖለቲካዊ ቀውስ ሳቢያ ነበር፡፡
የዛሬ 20 ዓመት፣ የአዲስ አድማስ ጠንሳሽ፣ መሥራችና ባለቤት አሰፋ ጎሳዬ (አሴ) በድንገተኛ ህመም ህይወቱ ባለፈበት ወቅት እንኳን ጋዜጣው ሳይታተም አልቀረም፡፡ ረቡዕ ከቀብር በኋላ ቢሮ ገብተን የቅዳሜውን ጋዜጣ ስናዘጋጅ ነበር፡፡ ከሃዘናችን ጋር እየታገልንም ቢሆን የቅዳሜውን ሳምንታዊ ጋዜጣ በጉጉት ለሚጠብቁን ውድ አንባቢያን  አድርሰናል፡፡ በዚህም ኩራትና ክብር ይሰማናል፡፡ የጋዜጣው መሥራች አሰፋ ጎሳዬም ቢሆን፣ ከምንም በፊት ቅድሚያና ትኩረት የሚሰጠው ለአንባቢያን ነበርና፡፡   
እነሆ አዲስ አድማስ  ከዚያም በኋላ ሁለት አሰርት ዓመታትን አስቆጥራ፣ በብዙ ውጣ ውረዶችና ተግዳሮቶች አልፍ፣ እነሆ ለ25ኛ ዓመቷ በቅታለች፡፡ ኮረኮንች በበዛበት የአገራችን የግል ፕሬስ፣ ሩብ ክፍለዘመን ቀላል ዕድሜ አይደለም፡፡ ረዥም ዕድሜ ነው፡፡ ትልቅ ስኬትም ነው ማለት ያስደፍራል፡፡   
ለዚህ የደረስነው ግን  በውድ አንባቢያን ገንቢ አስተያየትና ድጋፍ ነው፡፡ ስለዚህም በዚህ አጋጣሚ ልባዊ ምስጋናችንን ለማቅረብ እንወዳለን፡፡ ለአዲስ አድማስ ህልውናና በስኬት መቀጠል ከእኛ ከአዘጋጆቹ እኩል የሚጨነቁና የሚጠበቡት የረዥም ጊዜ ጽሁፍ አቅራቢዎችም ሌሎቹ ትልቅ ምስጋና የምንቸራቸው ባለውለታዎች ናቸው፡፡
ማስታወቂያቸውን በጋዜጣችን ላይ የሚያወጡ የንግድ ድርጅቶችና የመንግሥት ተቋማትም ሁነኛ  አጋሮቻችን  ናቸውና ከልብ ልናመሰግናቸው እንወዳለን፡፡
መጪው ጊዜም ነጻ ሃሳብ በነጻነት የሚንሸራሸርበት፣ ዕውቀትና ሥልጡንነት የሚያብብበት፣ የንባብ ባህል የሚዳብርበት  እንዲሆን እንመኛለን፤ ለዚያም በትጋት መሥራታችንን እንቀጥላለን፡፡
እንኳን አደረሳችሁ፤ አደረሰን!!

የአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምህርት ጽሕፈት ቤት የከተማዋ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃብ እንዳይለብሱ የጣለውን ዕግድ ለማስነሳት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት መውሰዱን የትግራይ ክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ም/ቤት አስታውቋል። ቀደም ሲል ምክር ቤቱ ዕግዱን ለማስነሳት በተለያዩ መንገዶች ያደረጋቸው ጥረቶች እንዳልተሳኩ ገልጿል።
ባለፈው ረቡዕ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. ም/ቤቱ ባወጣው መግለጫ፣ “የክልሉ ትምህርት ቢሮ ችግሩን በመፍታት ረገድ ደብዳቤ ከመጻፍ ያለፈ ውጤታማ ሚና አልተጫወተም” ብሏል። አክሎም፣ በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው አስታውቋል።ምክር ቤቱ በማብራርያው፣ የአክሱም ከተማ ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ሂጃባቸውን ለብሰው እንዳይማሩ የተደረገው ክልከላ ሃይማኖታዊና ዓለማዊ የሰው ልጆችን መብት የሚጋፋ መሆኑን አንስቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ ችግሩን ለመፍታት ብዙ አማራጮች መሞከራቸውም ተጠቅሷል።
“ክልከላው እንዲነሳ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ ያልተሳካ ሽምግልና እና መተግበር የማይችል ደብዳቤ ከመፃፍ የዘለለ ያመጣው ተጨባጭ ለውጥ የለም” ሲል ምክር ቤቱ ስሞታውን አትቷል። በአክሱም ከተማ የሚገኘው ትምሕርት ቤት አንዳንድ አመራሮች ከራሳቸው የሃይማኖት ፍላጎትና የትምህርት መብት አተያይ በመነሳት ተማሪዎች ወደ ትምሕርት ገበታቸው እንዳይመለሱ ማድረጋቸውን ምክር ቤቱ ጠቁሟል።በሂጃብ ምክንያት የ12ኛ ክፍል ሴት ሙስሊም ተማሪዎች ለዩኒቨርሲቲ መግቢያ ፈተና የመቀመጥ ዕድል እንደተነፈጋቸው የከሰሰው ከፍተኛው ምክር ቤት፤ ዕገዳው የሙስሊም ተማሪዎችን መብት ብቻ ሳይሆን በአጠቃላይ የሴቶችን ሰብዓዊ መብት የጣስ ድርጊት ነው በማለትም ምክር ቤቱ ዕገዳውን አውግዞታል። ምክር ቤቱ ጉዳዩን ሁሉም ትግራዋይ እንዲያወግዘው ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “ከቀናት በፊት በአቋም መግለጫችን እንደጠቀስነው ‘ክልከላው በአፋጣኝ ዕልባት ካልተሰጠው፣ በሕግ እንጠይቃለን’ ባልነው መሰረት ጉዳዩን ወደ ሕግ ወስደነዋል” ብሏል።
የትምህርት ቢሮው ችግሩን በጥቂት ቀናት ውስጥ ካልፈታ፣ ቀጣይ ሕጋዊ ዕርምጃዎችን እንደሚወስድ ምክር ቤቱ ባለፈው ሳምንት አስጠንቅቆ እንደነበር ይታወሳል።በተያያዘ ዜና፣ ቅድሚያ ለሰብዓዊ መብቶች የተሰኘው የሰብዓዊ መብቶች ተሟጋች ድርጅት፣ የትግራይ ክልል ትምህርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቋል።
ድርጅቱ ባለፈው ዓርብ ታሕሳስ 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ለአዲስ አድማስ በላከው አጭር ሪፖርት፣ በተማሪዎቹ ላይ የተጣለውን ዕግድ ተከትሎ፣ የክልሉ ትምሕርት ቢሮ ለአክሱም ከተማ አስተዳደር ትምሕርት ጽሕፈት ቤት  የጻፈው ደብዳቤ ለችግሩ ግልጽ መፍትሔ የሚሰጥ አለመሆኑን ጠቅሶ፣ “ችግሩ እስከ አሁን እንዲቀጥል አስተዋጽዖ አድርጓል” በማለት ነቅፏል።
በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ሕገ መንግስት አንቀጽ 25 ላይ የተደነገገውን የዕኩልነት መብት፣ የሃይማኖት፣ የዕምነትና የአመለካከት ነጻነት መብት አንቀጽ 27ን ጨምሮ፣ ልዩ ልዩ መመሪያዎች መጣሳቸውን አትቷል። ድርጅቱ፣ የትግራይ ክልል ትምሕርት ቢሮ በአክሱም ከተማ ትምሕርት እንዲቋረጥ ባደረጉ አካላት፣ ትዕዛዝ የሰጡና ወደ ግቢው እንዳይገቡ የከለከሉ አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ የጠየቀ ሲሆን፣ ተማሪዎቹ ወደ ትምሕርት ገበታ በአፋጣኝ እንዲመለሱ በማድረግ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፎርም እንዲሞሉ እንዲደረግም ጥሪ አቅርቧል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን በገና ዋዜማና በበዓሉ ዕለት በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ንጹሃን ዜጎች እንደተገደሉ የዞኑ ነዋሪዎችና አንድ የመንግሥት ሃላፊ ለአዲስ አድማስ ተናገሩ። ጥቃቱን የፈጸሙት አዋሳኝ ከሆነው የምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች መሆናቸውን ነዋሪዎቹ ገልፀዋል።
ለደህንነታቸው ሲሉ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የጎርካ ወረዳ፣ ከሬዳ እና ጀሎ ቀበሌዎች ነዋሪዎች ለአዲስ አድማስ እንዳስረዱት፣ ታሕሳስ 28 እና 29 ቀን 2017 ዓ.ም. በታጣቂዎቹ በተፈጸመው ጥቃት ሁለት በግብርና ስራ ሲተዳደሩ የነበሩ ዜጎች ተገድለዋል። ነዋሪዎቹ አያይዘውም፣ አርሶአደሮቹ የተገደሉት በጥይት ተደብድበውና አካላቸው ተቆራርጦ መሆኑንም አብራርተዋል።ሟቾቹ አርሶአደሮች አንታዮ ዦላና አድማሱ አሰፋ የተባሉ ሲሆን፣ ታሕሳስ 30 ቀን 2017 ዓ.ም. የቀብር ስነ ስርዓታቸው መፈፀሙን ነዋሪዎቹ ጠቁመዋል። አክለውም፣ “አቶ አንታዮ ዦላ የተገደሉት ታሕሳስ 28 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 11:30 ኬረዳ ቀበሌ ውስጥ ነው። ገዳዮቹ ጥቃቱን የፈጸሙት ከምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ጋላና ወረዳ፣ የተለያዩ የጦርና ስለታማ መሳሪያዎች ታጥቀው ወደ ኮሬ ዞን ዘልቀው ገብተው ነው። የቡልቶ ጃልደሳ ታጣቂዎች ናቸው።” ብለዋል።“በዚሁ ቀበሌ ጥቃት ከመፈጸም ባሻገር፣ የቤት እንስሳትን ዘርፈዋል” ያሉት ነዋሪዎቹ፣ “አድማሱ አሰፋ ደግሞ ታሕሳስ  29 ቀን 2017 ዓ.ም. ከቀኑ 6:30 ገደማ ጄሎ ቀበሌ ውስጥ ተገድሏል ” ሲሉ ገልጸዋል። ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ከምዕራብ ጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች ጥቃት እየተባባሰ እንጂ እየቀነሰ አለመምጣቱን ነዋሪዎቹ አመልክተዋል።
የዞኑ የሕዝብ ተወካይ የሆኑት አቶ ዘናነም አዱላ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፣ ከ2009 ዓ.ም. አንስቶ ጥቃት መፈጸሙን አጽንዖት ሰጥተው፣ ከ300 በላይ ዜጎች ሕይወታች እንደተቀጠፈ ተናግረዋል። ከባድ የንብረት ውድመትና ዝርፊያ በታጣቂዎቹ ሲፈጸም መቆየቱን ገልፀዋል።“መንግስት የሕዝቡን ደህንነት ለማስጠበቅ ቸልተኝነት አሳይቷል። ሃላፊነቱን እየተወጣ አይደለም” የሚሉት የሕዝብ ተወካዩ፣ “ተጠያቂነትን በማስፈን ረገድ ከፍተኛ ክፍተት አለ” በማለት ያስረዳሉ። በምዕራብ ጉጂ በኩል አልፎ ወደ ዲላ እና ሃዋሳ ለመጓዝ የሚያስችለው መንገድ መዘጋቱን ጠቁመው፣ ይህም በዞኑ ነዋሪዎች ላይ እንግልት ከመፍጠሩ ሌላ፣ ከመስከረም 2 ቀን 2017 ዓ.ም. ጀምሮ ጥቃቱ እንዳገረሸ ጠቅሰዋል።አቶ ዘናነም ግጭቱን ለዝርፊያና የኮንትሮባንድ ንግድ የሚጠቀምበት ሃይል እንዳለ የተናገሩ ሲሆን፣ ስለዚሁ ሃይል በግልጽ ከማብራራት ተቆጥበዋል። ታጣቂዎቹ ከብቶችና ሌሎች የቤት እንስሳት እንደሚዘርፉም ተናግረዋል።
የኮሬ ዞን ኮሙኒኬሽን ሃላፊ አቶ ትግሉ ዘብዶስ የጥቃቱን መደጋገም አንስተው፣ “ከምዕራብ ጉጂ ዞን ጋር የጸጥታ ችግሩን ለመቅረፍ እየሰራን እንገኛለን” ሲሉ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል።
 ይሁንና ሌሎች ዝርዝር ጉዳዮችን ለመግለጽ ፈቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።

Friday, 10 January 2025 21:24

25ኛው የብር ኢዮቤልዩ

ወይዘሮ ፈለቀች ለማ እባላለሁ፡፡ የቤተሰብ አስተዳዳሪና የአስራ አንድ ልጆች እናት ነኝ፡፡ በጥሩ ቤተሰብ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡ ትምህርት የጀመርኩት በቄስ ትምህርት ቤት ነው፤ ከዚያም በመንግሥት ትምህርት ቤት ገብቼ እስከ ስድስተኛ ክፍል ከተማርኩ በኋላ በሀገሩ ባህልና ወግ መሠረት በጣም በልጅነቴ ተዳርኩ፡፡ ሆኖም ያኔ ሲንጀር ካምፓኒ የሚሰጠውን የዲዛይን ትምህርት ጨርሼ ከተመረቅሁ በኋላ፣ በጅማ የሴቶች በጎ አድራጎት ድርጅት፣ ከጓደኞቼ ጋር በመሆን፣ ሴቶች ራሳቸውን እንዲችሉ፣ የልብስ ስፌትና ጥልፍ ስልጠና በመስጠት እናስመርቅ ነበር።

አዲስ አድማስ ከመጀመሩ በፊት ባለቤቴ ሁሌም ጋዜጣና መፅሔት እንዲሁም መጻሕፍት እየገዛ ያመጣ ስለነበር፣ ንባብ የቤታችን ባህል ሆኗል፡፡ በኋላም አዲስ አድማስ ቅዳሜ መውጣት ሲጀምር ልጆቹም በዚያው ቀጠሉበት፡፡ እኔም ጋዜጣውን ማምጣት እንዳይረሱ ሁሌም አስታውሳቸዋለሁ፤ በጣም የሚወደድ ጋዜጣ ስለሆነ ምንጊዜም እንዲያልፈኝ አልፈልግም፡፡

አዲስ አድማስን ለብዙ ዓመታት አንብቤአለሁ፤ ወደፊትም አነባለሁ፡፡ ጋዜጣውን እንዳገኘሁ መጀመሪያ የማነበው የነቢይ መኮንንን (ነፍሱን ይማረውና) ርዕስ አንቀጽ ነው፤ ሁለተኛ የማነበው ደግሞ የዮሐንስ ሰ.ን ጽሁፍ ነው፡፡ እኔ ከልጆቹ ቀድሜ ካነበብኩ ጥሩ የምላቸውን ጽሁፎች እንዲያነቡ እጠቁማቸዋለሁ፡፡ ሁሉም አምዶች ሳምንቱን ሙሉ የሚነበቡ ናቸው፡፡ በእኔ በኩል፣ አዲስ አድማስን በድረ ገፅ አላነብም፤ለዕድሜዬ አይሆንም፤ በዚያ ላይ ጋዜጣው ሁሌም በእጄ ነው።

በአዲስ አድማስ ላይ በርካታ አስገራሚና አስደማሚ ታሪኮችን አንብቤአለሁ፡፡ ከእነዚህ ውስጥ አንዱና ሁሌም የማይረሳኝ፣ ኮፊ አናን ኢትዮጵያ በነበሩ ጊዜ የቤት ውስጥ ረዳታቸው የነበሩትን ሴት ተመልሰው ሲመጡ ሊያገኟቸው ፈልገው፣ ሴትየዋ በቀጠሮው ሰዓት ባለመድረሳቸው ሳይገናኙ መቅረታቸውን የሚያትተው ታሪክ ነው፡፡ የቀጠሮ ሰዓት የማያከብር ሰው ስለሚገርመኝ ይሆናል፣ ይሄ ታሪክ ሁሌም ትዝ የሚለኝ፡፡

በእርግጥ የማነበው ጋዜጣ ብቻ አይደለም፤ መፅሔቶች የታሪክና የሀይማኖት መጻሕፍትንም አነባለሁ፡፡ ዜናም አያመልጠኝም፡፡ ማንበብ ብዙ ጠቀሜታዎች አሉት፡፡ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ዕውቀትን ያስታጥቃል፡፡ መረጃን ከሰው አፍ ከመስማት አንብቦ መረዳት የተሻለ ነው፡፡

የአዲስ አድማስ ፀሐፊዎችና አዘጋጆች፣ ከአንባቢዎቻቸው ቀድመው መገኘት አለባቸው፤ በሁሉም ረገድ ሊበረቱ ይገባል፡፡ ጋዜጣው አምዶቹን መጨመር እንጂ መቀነስ የለበትም፤ የተቀነሱ አምዶች ስላሉ የጎደሉትን ማሟላት ያስፈልጋል፡፡ በመጨረሻ እንኳንም ለአዲስ አድማስ 25ኛ ዓመት አደረሳችሁ እላለሁ፡፡ መልካም የሥራ ዘመን ይሁንላችሁ።

• በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ
አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ ነው ተብሏል

ከ60 ዓመታት በላይ በተወዳጅነት ያቀነቀነው “የትዝታው ንጉስ” ማህሙድ አህመድ፣ በነገው ዕለት ጥር 3 ቀን 2017 ዓ.ም፣ በሚሊኒየም አዳራሽ፣ በአድናቂዎቹ በክብር ከመድረክ ይሸኛል።

ዛሬ በሚሊኒየም አዳራሽ የመርሃ ግብሩ አዘጋጆች ጆርካ ኢቨንትስ ኦርጋናይዘር እና ዳኒ ዴቪስ በጋራ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንደተናገሩት፤ የስንብት ኮንሰርቱ ለጋሽ ማህሙድ በሚመጥን መልኩ የተዘጋጀ ነው። በኮንሰርቱም ላይ ተወዳጆቹ ድምጻዊያን ጎሳዬ ተስፋዬ፣ ኤፍሬም ታምሩ፣ ብዙአየሁ ደምሴ፣ አደም መሐመድ፣ ወንዶሰን መኮንን (ወንዲ ማክ) እና ዜና ሃይለማሪያም ታላቁን አርቲስት አጅበው ያቀነቅናሉ ተብሏል።

አርቲስቶቹ ከጋሽ ማህሙድ በተረፈው ሰዓት ታዳሚን ለማስደሰትና፣ አንጋፋውን ሙዚቀኛ በክብር ለመሸኘት በከፍተኛ ደረጃ እየተዘጋጁ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ጋሽ ማህሙድም “አሳድጎ ለዚህ ክብር ያበቃኝን አድናቂ፣ በተቻለኝና አቅሜ በፈቀደው መጠን በመጫወት አስደስቼ ለመሰናበት ተዘጋጅቻለሁ” ያለ ሲሆን፤ “ሁላችሁም መጥታችሁ ብትሸኙኝ ደስታውን አልችለውም” ሲል ሁሉም እንዲታደም ጥሪ አቅርቧል።


ጋሽ ማህሙድን አጅበው የሚያቀነቅኑት ለምን ወንዶች ብቻ ሆኑ፣ ሴት አቀንቃኞች ለምን አልተካተቱም? በሚል ከአዲስ አድማስ ጋዜጣ ለቀረበው ጥያቄ፣ ከስንብት ኮንሰርቱ አዘጋጆች አንዱ የሆነው ዳኒ ዴቪስ በሰጠው ምላሽ፤ " አስቴር አወቀ እንድትሳተፍ ፈልገን ጋብዘናት ነበር፤ ወደ ውጪ በመውጣቷ ልትገኝ አልቻለችም፤ እኛም የፈለግነው እሷን ነበር፤ አልሆነም" ብሏል።

የአንጋፋውን ሙዚቀኛ የጋሽ ማህሙድ አህመድን የህይወት ታሪክ የሚተርክ መፅሐፍ በትላንትናው ዕለት የተመረቀ ሲሆን፤ በስሙ አደባባይ ለመሰየምና ሐውልት ለማቆም ከከተማ አስተዳደሩ ምላሽ እየተጠበቀ መሆኑም በጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ተብራርቷል።

“መጻሕፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ”


ጄምስ ፓተርሰን በዓለም ዝናው የናኘ እጅግ ታዋቂና ትጉህ አሜሪካዊ ደራሲ ነው። የ77 ዓመቱ ፓተርሰን እ.ኤ.አ ከ1976 ዓ.ም ጀምሮ 200 ገደማ ረዥም ልብ ወለዶችን ጽፎ ለህትመት ያበቃ ሲሆን፤ መፃህፍቱ በዓለም ዙሪያ ከ425 ሚሊዮን ቅጂዎች በላይ ተሸጠውለታል። 1 ሚሊዮን ያህል ኤሌክትሮኒክስ መፃሕፍት (e-books) በመሸጥም የመጀመሪያው ደራሲ ነበር፡፡
ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2016 ዓ.ም በፎርብስ የከፍተኛ ተከፋይ ደራሲያን ሰንጠረዥን በመቆጣጠር ለሦስት ተከታታይ ዓመታት ዘልቋል- በ95 ሚሊዮን ዶላር ገቢ። አጠቃላይ ገቢው ደግሞ ከአሰርት ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ 700 ሚሊዮን ዶላር ይገመት ነበር፡፡
ሚሊየነሩ አሜሪካዊ ደራሲ ከተወዳጅ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ ባሻገር የመጻሕፍት ሻጮች አለኝታም ነው፡፡ የመፅሐፍ ኢንዱስትሪውን የጀርባ አጥንት በመደገፍ ይታወቃል - የግል የመፃሕፍት መደብሮችን።
በዚህ የፈረንጆች በዓል ሰሞን በመላው አሜሪካ በሚገኙ 600 የግል መፃህፍት መደብሮች ውስጥ ለሚሰሩ ሰራተኞች በአጠቃላይ የ300ሺ ዶላር የበዓል ቦነስ አበርክቷል - በነፍስ ወከፍ 500 ዶላር!
“መፃህፍት ሻጮች ህይወትን ይታደጋሉ- አራት ነጥብ!” በማለት ለABC ኒውስ የተናገረው ደራሲው፤ “በዚህ የበዓል ወቅት ለእነሱም ሆነ ለትጋታቸው ዕውቅና መስጠት በመቻሌ ደስተኛ ነኝ።” ብሏል።
ለዓመት በዓል የገንዘብ ስጦታው የታጩት የ600 መፃሕፍት መደብር ሠራተኞች አንድም ራሳቸው ያመለከቱ አሊያም በመደብር ባለቤቶች፣ በደራሲያን ወይም በደንበኞች የተጠቆሙ ናቸው ተብሏል- በትጋትና ታታሪነታቸው።
“የሚስተር ፓተርሰንን የገንዘብ ልግስናና የልብ ቸርነት እናደንቃለን። ሁላችንም ሚስተር ፓተርሰን ለግል መፃሕፍት ሻጮች ለሚያደርጉት የማያቋርጥ ድጋፍ ምስጋናችን ወደርየለሽ ነው፡፡” ብለዋል፤ የአሜሪካ መፃህፍት ሻጮች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አሊሰን ሂል በመግለጫቸው፡፡
“መፃሕፍት ሻጮች በኢንዱስትሪው ውስጥ የሚጫወቱትን ወደር-የለሽ ሚና መገንዘባቸውና መሸለማቸው ከምንም ነገር የላቀ ነው” ሲሉም አክለዋል፤ ዋና ሥራ አስፈፃሚው።
ደራሲው ለመፃሕፍት ሻጮች የ500 ዶላር የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ያሁኑ የመጀመሪያው አይደለም። ላለፉት አስርት ዓመታት ሲያደርገው የቆየው የልግስና ተግባር ነው፡፡ ሥነ-ፅሁፍን በማሳደግና ንቁ ማህበረሰቦችን በመገንባት ረገድ ወሳኝ ሚና እንደሚጫወቱ በማመን፣ የግል የመፃሕፍት መደብሮችንም ያለማቋረጥ በመደገፍ ይታወቃል፤ በአገረ አሜሪካ፡፡
በመጋቢት ወር ላይ ፓተርሰን ለመፃሕፍት ሻጮች የሚከፋፈል 600ሺ ዶላር እንደሚያበረክት የአሜሪካ መፃሕፍት ሻጮች ማህበር አስታውቆ ነበር፡፡ ቀደም ብሎ እ.ኤ.አ በ2020 ደግሞ በመላው አሜሪካ ለሚገኙ የግል መፃሕፍት መደብሮች 500ሺ ዶላር ለግሷል- ሥራቸውን እንዲያሳድጉና እንዲነቃቁ።
“ዋይት ሐውስ የአየር መንገድ ኢንዱስትሪንና ትላልቅ ቢዝነሶችን ከውድቀት መታደግ ያሳስበዋል - ያንን እረዳለሁ። እኔ ግን በመላ አገሪቱ ዋና ጎዳናዎች እምብርት ላይ የሚገኙ የግል የመፃሕፍት መደብሮች ህልውና ያሳስበኛል።” ብሏል ፓተርሰን በሰጠው መግለጫ።
“የምናሰባስበው ገንዘብ የመፃሕፍት መደብሮችን በጣም በምንፈልግበት በዚህ ወቅት ህያው እንደሚያደርጋቸው ተስፋ አደርጋለሁ።” ሲልም አክሏል፤ ደራሲው።
ጄምስ ፓተርሰን እ.ኤ.አ በ2014 ዓ.ም ለአሜሪካ የግል የመፃሕፍት መደብሮች 1 ሚሊዮን ዶላር ለግሶ ነበር- ለእያንዳንዳቸው 15ሺ ዶላር የሚከፋፈል። ባለፉት ዓመታት ደራሲው ለመፃሕፍት መደብሮችና መጻሕፍት ሻጮች ብቻ ሳይሆን ለቤተመጻህፍት ባለሙያዎችና ለመምህራንም የበዓል ቦነስ ሲያበረክት ቆይቷል።
የመፃሕፍት መደብሮችንና መፃሕፍት ሻጮችን በገንዘብ ከመደገፍና ከማገዝም በተጨማሪ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ መፃሕፍትን ለት/ቤቶች ቤተ-መፃሕፍት ለግሷል። የህፃናት መፃሕፍትንም በመፃፍ የሚታወቀው ደራሲው፤ ህፃናት የንባብ ባህል እንዲያዳብሩም በትጋት ይሰራል። “ህፃናት በለጋ ዕድሜያቸው የማንበብ ልማድ ካላዳበሩ ለውጭው ዓለም ባዕድ ከመሆናቸውም ባሻገር በራስ መተማመን ይጎድላቸዋል፤ ስለዚህ የግድ ማንበብ አለባቸው፤ ይህን ማድረግ ደግሞ የኛ የወላጆች ሃላፊነትና ግዴታ ነው፡፡” ይላል- ፓተርሰን።
ጄምስ ፓተርሰን የበኩር ስራውን ለንባብ ያበቃው እ.ኤ.አ በ1976 ዓ.ም ሲሆን፤ ርዕሱም “The Thomas Berryman Number” ይሰኛል። ከሌሎች በርካታ የሥነጽሁፍ ሥራዎቹ መካከልም፡- Alex Cross, Michael Bennet, Women’s Murder Club እና Maximum Ride የተሰኙት ልብወለዶች ይጠቀሳሉ። ቁጥራቸው ቀላል የማይባሉ ልብወለዶቹም ወደ ፊልም ተቀይረውለታል፡፡

 

Page 1 of 748