Administrator

Administrator

ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል


በተለያዩ  የበጎ አድራጎትሥራዎች ላይ ገንዘቡንና ጊዜውን በመሥጠት በንቃት የሚሳተፈው  ወጣቱ ባለጸጋ ምህረትአብ ሙሉጌታ፤ በዛሬው ዕለት አበበ በቂላ  ስቴዲየም አካባቢ ባለው  ባቡልኬይር በመገኘት  ከ1 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ በማድረግ የ4ሺ ሰው የምሳ ወጪ ሸፍኗል፡፡

ከዚህም ባሻገር፣ ድርጅቱ እየሰራ ያለውን የበጎ  አድራጎት ለማገዝ የ1 ሚሊየን ብር ድጋፍ አድርጓል።

ስጦታውን የተረከቡት የድርጅቱ ዋና ሥራ አስኪያጅ ወይዘሮ ሀናን ማህሙድ ምህረት አብ፣"ዛሬ ሰርፕራይዝ ነው ያደረግኸን፤ ይሄን ያህል መጠን ያለው  ድጋፍ ሲደረግልን የመጀመሪያው ነው።" ሲሉ ለባለሃብቱ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡



በሀገራችን በራስ ተነሳሽነት በደጋግ ኢትዮጵያውያኖች ከተመሠረቱ የበጎ አድራጎት ድርጅቶች መካከል ባቡል ኬይር የበጎ አድራጎት ድርጅት አንዱ ሲሆን፤ድርጅቱ ከተመሠረተበት ጊዜ አንስቶ በርካታ አስታዋሽ ያጡ ኢትዮጵያውያንን በመርዳት ላይ ይገኛሉ፡፡ ባቡል ኬይር በቀን ከ4 ሺ በላይ ወገኖችን ይመግባል፡፡

"የአዲስ አበባ ከተማ ማዘጋጃ ቤት ለሕዝብ ማስታወቂያ"

ከዚህ ቀድሞ በመስከረም 11 ቀን 1928 ዓ.ም በተነገረው አዋጅ እንደሰማችሁት የኢጣልያ መንግሥት በኢትዮጵያ ላይ የአጥቂነት ሥራ በመሥራቱ ኢትዮጵያዊ የሆነ ሁሉ ከተነሣበት ጠላት እንዲከላከል ምንም ቢታዘዝ ጠላት የተባሉት ወሰን አልፈው መሣሪያ ይዘው የወገኖቻችንን የኢትዮጵያን ሰዎች ደም ለማፍሰስ የሚመጡ ኢጣልያኖች ናቸው እንጂ በአዲስ አበባ ከተማም ቢሆን ከከተማ ውጭም ቢሆን በኢትዮጵያ የሰላማዊነት ሥራ እየሠሩ ለመኖር የመጡት አይደሉምና የኢትዮጵያ ሕዝብ በእንግዳ ተቀባይነቱና በአክባሪነቱ ከውጭ አገር ሰዎች ጋራ ተስማምቶ በሳላም በመኖሩ በዓለም የተመሰገነ ስለሆነ ይህ መልካም ስማችን ሳይጠፋ ተከብሮ እንዲኖር ገፍቶ የመጣውን ጠላታችንን ወደድንበራችን ሒደን ለመመለስ ከማሰብ በቀር በመካከላችን እኛን ዘመድ አድርገው በሚኖሩ የውጭ አገር ሰዎች ላይ ማናቸውንም የጠላትነት አሳብ የሚገልጥ ነገር እንዳታደርጉ እናስታውቃለን። አሁን ከኢጣልያን ጋራ በተነሣው ጠብ ምክንያት በማስፈራራት በመጋፋት ወይም የማይገባ ቃል በመናገር ይህን በመሰለ አደራረግ ሁሉ በኢትዮጵያ የሚኖሩትን የውጭ አገር ሰዎች ያዋረደ፥ የማይገባም ቃል የተናገረ እንደ ሕጉ በብርቱ ቅጣት ይቀጣል።

መስከረም 14 ቀን 1928 ዓ.ም
የአዲስ አበባ ከንቲባ

ምንጭ:- ብርሃንና ሰላም ጋዜጣ

•  የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ተጠይቆ ነበር

ለወራት በዘለቀ ውዝግብ ውስጥ የሚማስኑት የህወሓት አመራሮች ትላንት በአዲስ አበባ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድና ከሌሎች የፌደራል መንግሥቱ ከፍተኛ ባለሥልጣናት ጋር በትግራይ ውስጥ ስላለው አጠቃላይ ሁኔታ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡
 
በህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልና በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መካከል የተፈጠረው ውዝግብና አለመግባባት መፍትሄ ሳይበጅለት የቀጠለ ሲሆን፤  ሁለቱም ወገኖች ቡድን ለይተው  መካሰሳቸውን ቀጥለውበታል፡፡

ትላንት ሐሙስ ኅዳር 26 ቀን 2017 ዓ.ም. በጠ/ሚኒስትሩ ጽህፈት ቤት ውስጥ በክልሉ የፀጥታና የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ ውይይት የተደረገ  ሲሆን፤ በዚህ ስብሰባ ላይም ሁለቱ ቡድኖች መካሰሳቸው ተነግሯል፡፡  

ቢቢሲ ስማቸውን መጥቀስ ያለፈለጉ ውይይቱን በቅርበት የተከታተሉ ታማኝ ምንጩን ጠቅሶ እንደዘገበው፣ የውይይቱ ዋነኛ ትኩረት በትግራይ ክልል  የፀጥታና የፖለቲካ ችግሮችን በጋራ መፍታት በሚቻልባቸው ሁኔታዎች ላይ ቢሆንም፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት ከሥልጣን እንዲነሱ ጥያቄ ቀርቧል ብሏል፡፡

በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን በትግራይ እየተከሰተ ላለው ችግር የጊዜያዊ አስተዳደሩን ደካማነት በምክንያትነት  በመግለጽ፣ ፕሬዚዳንቱ አቶ  ጌታቸው ረዳ ከሥልጣን እንዲነሱ ለጠ/ሚኒስትሩ ጥያቄ ማቅረባቸው ተነግሯል፡፡

 "ጌታቸው ተነስቶ ምክትሉ ጄኔራል ታደሰ ወረደ" ቦታውን እንዲይዙ ሃሳብ ማቅረባቸውን ጉዳዩን በቅርብት የተከታተሉት አንድ  ተሳታፊ ለቢቢሲ ትግርኛ መናገራቸው ታውቋል፡፡

በጊዜያዊ አስተዳደሩ አቶ ጌታቸው ረዳ የሚመራው የህወሓት ቡድን በበኩሉ፤ "ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን በተገቢው መንገድ እንዳያከናውን" በማድረግ ዶ/ር ደብረጽዮንንና ቡድናቸውን ከሷል።

"ለጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራዎች እንቅፋት የሆናችሁት እናንተ ናችሁ" በማለት ምላሽ የሰጡት ጌታቸው ረዳ፤ በጦርነቱ የተፈናቀሉ ሰዎች ወደ ቀያቸው እንዳይመለሱ አድርገዋል ሲሉም ከሰዋል።

በድርጅቱ አባላትና አመራሮች እንዲሁም በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እውቅናን ያላገኘው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ ተካሂዶ አቶ ጌታቸውና ሌሎችም ከፍተኛ አመራሮች ከፓርቲው ከተባረሩ በኋላ ደብረጽዮን የሚመሩት ቡድን፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ መሪዎች ሥልጣን ላይ ጥያቄ ሲያነሳ ቆይቷል።

አቶ ጌታቸው የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንትነትን ቦታ የያዙት በህወሓት ውክልናቸው ነው በሚልም ከሃላፊነታቸው እንዲነሱ የፌደራል መንግሥቱን ሲጠይቁ ነበር ተብሏል። አሁን ውዝግቡ እየተባባሰ ባለበት ጊዜም፣ ችግሮችን ለመፍታት ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በተደረገው ስብሰባ ደብረጽዮን ይህንኑ ጥያቄ ማንሳታቸው ተነግሯል፡፡
 
ዶ/ር ደብረጽዮን፣ አቶ ጌታቸው ከጊዜያዊ አስተዳደር መሪነታቸው ተነስተው በቦታው ጄኔራል ታደሰ እንዲተኩ ያቀረቡትን  ሃሳብን ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሳይቀበሉት መቅረታቸውን ታማኝ ምንጩ ለቢቢሲ ትግርኛ ተናግረዋል።

"ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሥራውን እንዳያከናውን 'የትግራይ ሠራዊት' ከጎናችን ነው' በማለት ሕዝቡን ግራ እያጋባችሁት ነው" በማለት የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድንን የወቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ "በስመ ምክር ቤት በሚል ሕዝቡን እየረበሻችሁት ነው" ሲሉ ወቅሰዋቸዋል።

ጠ/ሚኒስትሩ ጨምረውም፣ መንግሥታቸው የክልሉን ጊዜያዊ አስተዳደር ሙሉ ለሙሉ ድጋፍ አድርጌለታለሁ እንደማይል በማንሳት፣ ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪደረግ ድረስ የሚጠበቅበትን እያከናወነ እንደሚቆይ ማሳወቃቸውን የቢቢሲ ምንጭ ገልጸዋል።

ኢትዮጵያውያን ግጭቶችና ልዩነቶችን ከሚፈጥሩ አጀንዳዎች ይልቅ ብሔራዊ ጥቅምን በሚያስከብሩ አጀንዳዎች ላይ የጋራ አቋም መያዝ እንዳለብን ኡስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ጉዳይን በተመለከተ ያላትን አቋም ለአረብ ሀገራት በአረብኛ ቋንቋ በስፋት በማድረስ የሚታወቁት ኡስታዝ ጀማል በሽር፤ እንደ ሕዝብ ብሔራዊ የሆኑ አጀንዳዎቻችን ላይ አንድ ሆነን መቆም አለብን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ከኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋር ባደረጉት ቆይታ፣ ግብጻውያን በመሀከላቸው መከፋፈል ቢኖርም በሀገር ጉዳይ ላይ ያላቸው አንድነት ጠንካራ መሆኑን በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

“ግብጻውያን በየትኛውም የሥራ ዘርፍ ላይ የሚገኙ ፤ ረጅም ዓመት ተፈርዶባቸው በእስር የሚገኙ ዜጎቻቸው ጭምር በሀገራቸው ጉዳይ ያላቸው አቋም አንድ ከመሆኑም በላይ ጠንካራ ነው፡፡” ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ የዓባይ ውሃ ባለቤት ብትሆንም በዜጎች ዘንድ የሚሰጠው ትኩረት ሊሠራበት የሚገባው መሆኑንም አንስተዋል፡፡ በትምህርት ሥርዓታችን ውስጥ ተተኪ ለሆኑ ትውልዶች ኢትዮጵያ ያላትን የውሃ ሀብትና የዓባይን ውሃ የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ተሠጥቶ በመሥራት ረገድ ያለን ተሞክሮ ደካማ መሆኑን በመግለጽም፤ ይህ ጉዳይ ሊሻሻል እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡

ኡስታዝ ጀማል ሀገርን ወክለው በዓባይ ጉዳይ ላይ ኢትዮጵያ ያላትን አቋም በማሳወቅ፣ በበርካታ የመገናኛ ብዙሃን ላይ በመቅረብና የራሳቸውንም ሚዲያ በማቋቋም በአረብኛ ቋንቋ በመሞገት ይታወቃሉ፡፡

• በመቀሌ የህወሓት ጽ/ቤት ሰላማዊ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ ጠየቀ

 

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳና የህወሓት ሊቀመንበር ዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤልን ጨምሮ የክልሉ የፖለቲካና የጸጥታ አመራሮች በአዲስ አበባ፣ ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተገኙበት፣ ከፌደራል መንግሥት አመራሮች ጋር በትግራይ ክልል ባለው አጠቃላይ የፖለቲካ፣ የአስተዳደርና የጸጥታ ሁኔታ ላይ ዛሬ ውይይት ማድረጋቸው ታውቋል፡፡

በውይይቱም ላይ በክልሉ የሚታዩ ችግሮችን እንዴት በጋራ መፍታት እንደሚገባ ምክክር የተደረገ ሲሆን፤ በተለያዩ አንኳር ጉዳዮች ላይ በተቀመጡ የጋራ አቅጣጫዎች መሠረት በጋራ ለመስራትና የክልሉ ህዝብ የፀጥታ፣ የመልካም አስተዳደርና የልማት ፍላጎት ለማሟላት አስቻይ ሁኔታ ለመፍጠር መግባባት ላይ ተደርሷል ተብሏል።

በተለይም ከመኖርያቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደ ቀዬአቸው የሚመለሱበትን ሁኔታ፣ ታጣቂዎች ወደ መደበኛ ሕይወት የመመለስ ሂደትን በትኩረት በሚሰራበትና በሚሳለጥበት ሁኔታ ላይ መግባባት ተደርሷል።

በተጨማሪም በክልሉ ያሉ የተፈጥሮ ሃብቶች አጠቃቀም ህጋዊ በሆነ አግባብ የህዝብንና የሀገርን ጥቅም የሚያስጠብቅ እንዲሆን፣ ለህዝብ የሚቀርቡ የመንግስት አገልግሎቶች የሚሻሻሉበትና የህዝብን ፍላጎት የሚመጥኑ እንዲሆኑ፣ ቀጣይነት ያለው ጠንካራ ስራ እንዲሰራ ተገቢው አቅጣጫ በውይይቱ መለየቱ ተነግሯል፡፡

በመጨረሻም ጊዜያዊ አስተዳደሩ ክልላዊ ምርጫ እስኪካሄድ ድረስ ያለበትን ሃላፊነት ለመወጣት በሚያስችለው አግባብ ላይም አቅጣጫ በማስቀመጥ ውይይቱ መቋጨቱ ታውቋል፡፡

በሌላ በኩል፤ በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን፣ የፊታችን እሁድ ህዳር 29 ቀን 2017 ዓ.ም በመቀሌ ከተማ የተቃውሞ ሰልፍ ለማድረግ ፈቃድ መጠየቁ ተሰምቷል፡፡

ቡድኑ ለመቀሌ ከተማ አስተዳደር በጻፈው ደብዳቤ እንደገለጸው፤ “ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም በትጥቅ የተደገፈ የአስተዳደር ፈረሳ በመከናወኑ፣ ይህን ለመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ እናደርጋለን” ብሏል። ለዚህም የከተማ አስተዳደሩ ፈቃድ እንዲሰጠው ቡድኑ ጠይቋል፤ በደብዳቤው፡፡

“ለዘመናት መስዋዕት ከፍለን የመሰረትናቸው ምክር ቤቶች በግለሰቦች ሲፈርሱ አንታገስም በሚል ምክንያት፤ ከህዝባችንና አባላቶቻችን በተደጋጋሚ ጥሪ እየቀረበልን በመሆኑ ህዳር 29 በመቀሌ ከተማ ሰልፍ ለማድረግ አቅደናል” ብሏል፤ ቡድኑ።

እሁድ ህዳር 29 ከጠዋቱ 2 ሰዓት እስከ 6:30 ሰልፉን ለማድረግ ተዘጋጅተናል ያለው የህወሓት ቡድን፤ የጸጥታ ኃይል ጥምር ኮሚቴ ሰልፉን እንዲፈቅድለትና ከለላ እንዲያደርግለት ጠይቋል፤ በመቀሌ የህወሓት ጽ/ቤት፡፡

• ሁለት ታዋቂ ሴት አርቲስቶች በአመራሩ ተካትተዋል


የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ዓመታዊ መደበኛ ጠቅላላ ጉባኤውን ዛሬ በጊዮን ሆቴል ያካሄደ ሲሆን፤ ለቀጣይ አራት አመታት የሚመሩትን ፕሬዚዳንትና ሥራ አስፈፃሚዎችን መርጧል። አርቲስት ማስተዋል ወንደሰንና አርቲስት ሐረገወይን አሰፋ በአመራሩ ውስጥ ተካትተዋል፡፡


ፌዴሬሽኑ የቀድሞውን አልቢትር ኢንጂነር ኃይለየሱስ ፍሰሃን በፕሬዚዳንትነት የመረጠ ሲሆን፤ አርቲስት ማስተዋል ወንደሰን በምክትል ፕሬዚዳንትነት መርጧል፡፡

አንጋፋዋ ተዋናይት ሀረገወይን አሰፋን ጨምሮ አቶ ሲሳይ ዳኜ፣ ዶ/ር ወገኔ ዋልተንጉስ፣ አቶ ኢሳያስ ታፈሰ፣ አቶ ሸሀመለ በቀለ፣ አቶ በለጠ ወልዴና ወ/ሮ አሰፋሽን በሥራ አስፈፃሚ ውስጥ ተካተዋል።


ፌዴሬሽኑ አለብኝ የሚለውን የገንዘብ እጥረት ለመቅረፍ አርቲስቶችን ወደ ሥራ አስፈፃሚ በማምጣት የማርኬቲንግ ስራዎችን ለመስራት እንዳሰበ ተነግሯል፡፡

ጉባኤው የአዲስ አበባ ከተማ እግር ኳስ ፌዴሬሽንን ለአራት ዓመታት በፕሬዚዳንትነት እንዲመሩ ኢንጂነር ሀይለእየሱስ ፍስሀን መምረጡን ከአዲስ አበባ ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።

አምስቱ የታዋቂው የሬጌ ንጉስ የቦብ ማርሌይ ልጆች የሚሳተፉበት የሙዚቃ ድግስ በኢትዮጵያ ሊካሄድ ነው፡፡
የሙዚቃ ድግሱን ከሚያዘጋጁት መካከል አንዱ የሆነው ድምጻዊ ዘለቀ ገሰሰ ከፋና ሚዲያ ኮርፖሬሽን ጋር ባደረገው ቆይታ፤ “ዋን ላቭ” የተሰኘ የሰላም የሙዚቃ ድግስ ለማካሄድ ዝግጅት መጀመሩን ተናግሯል።
በመጭው ግንቦት ወር ሊካሄድ የታቀደው ታላቅ የሙዚቃ ድግስ 5ቱን የቦብ ማርሌይን ልጆች የሚያሳትፍ ሲሆን፤ እነሱም ዚጊ ማርሌይ፣ ስቴፈን ማርሌይ፣ ጁሊያን ማርሌይ፣ ዳሚያን ማርሌይ እና ኪማኒ ማርሌይ ናቸው፡፡
ከዚህም ባሻገር ከኬንያ፣ ሩዋንዳ፣ ታንዛንያና ደቡብ አፍሪካ የተውጣጡ ድምጻውያንም በሙዚቃ ድግሱ እንደሚሳተፉ ተጠቁሟል፡፡
የሙዚቃ ድግሱ ሰላም ፍቅርና አንድነት ላይ ያተኮረ መሆኑን የገለጸው ድምጻዊ ዘለቀ ገሰሰ፤ ዝግጅቱ ከኢትዮጵያ ባሻገር በአፍሪካ የተለያዩ አካባቢዎች ያለውን ውጥረት ለማርገብና ሰላም ለማስፈን ያለመ ነው ብሏል፡፡
የቴሌግራም ቻናልችንን በመቀላቀል የአዲስ አድማስን መረጃ ይከታተሉ…
https://t.me/AdissAdmas

እናት ፓርቲ ትናንት ህዳር 24 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ በኦሮሚያ ክልል፣ ምሥራቅ ወለጋ ዞን፣ የአንዶዴ ዲቾ እና ደጋ ጂጊ ቀበሌዎች ነዋሪዎች “መከላከያ ሰራዊት ነን” ያሉ ሃይሎች ሰኞ ህዳር 23 ቀን 2017 ዓ.ም. ከንጋት 12 ሰዓት እስከ ጠዋት 3 ሰዓት በድንገት ከበባ በማድረግ ከ80 የማያንሱ የጦር መሳሪያዎቻቸውን እንደገፈፏቸው መናገራቸውን ገልጿል። ፓርቲው “በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍና ሊበረታታ እንጂ እንደወንጀል ሊቆጠር አይገባም” ሲልም አመልክቷል።

ፓርቲው በርካታ አርሶ አደሮች “መሳሪያችንን አንሰጥም” በማለት ጫካ እንደገቡና መሳሪያዎቹን ነጥቀው “የራሳችን” ለሚሉት ሰው “ሰጥተውታል” በማለት እንዳማረሩ “ሰምቼአለሁ” ያለው ፓርቲው፣ “የዞንና ወረዳ ካድሬዎችም ጫካ የገባውን ቤተሰቡን ‘እናስራለን፣ እንቀጣለን’ እያሉ እንደሚዝቱ ነዋሪዎቹ ተናግረዋል” በማለት አስረድቷል። “በአካባቢው ከፍተኛ ዘር ተኮር ጭፍጨፋ የተከሰተበት በመሆኑ ራስን መከላከል በሕግና በሥርዓት እንዲመራ ማድረግ የተሻለ አማራጭ እንደኾነ መታወቅ አለበት” ብሏል፣ እናት ፓርቲ በመግለጫው።

እናት ፓርቲ “የጸጥታ ሃይሉ ትርጉም ያለው ጥበቃ ለዜጎች በማያደርግበት ሁኔታ ነዋሪው ራሱን የሚከላከልበትን መሳሪያ መቀማት በቅርቡ በአርሲ የተከሰተው ዓይነት ጥፋት ለማድረስ ካልሆነ፣ ሌላ ትርጉም ሊሰጠው እንደማይችል ታውቆ የእርምት እርምጃ በአስቸኳይ እንዲወሰድ” ሲል ጥሪ ያቀረበ ሲሆን፣ “በአሁኑ ወቅት ሕዝቡ በራስ ተነሳሽነት ራሱን ለመጠበቅ እያደረገ ያለው ጥረት ሊደገፍና ሊበረታታ እንጂ እንደወንጀል ሊቆጠር አይገባም” በማለት አጽንዖት ሰጥቶ ነው ያመለከተው።

የክሪስታል ፓላስ አምባል ማርክ ጉዬ ባለፈው ቅዳሜ ከኒውካስል ጋር በነረበው ግጥሚያ የአምበልነት መለያው ላይ ‘አይ ላቭ ጂሰስ’ (እየሱስን እወደዋለሁ) ብሎ መፃፉ አነጋጋሪ ሆኗል።

የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ አስተዳዳሪ የሆነው ኤፍኤ አምበሉ ላይ እርምጃ ከመውሰድ ቢቆጠብም ለክለቡ እና ተጫዋቹ መለያ ላይ ኃይማኖታዊ ፅሑፎችን መፃፍ ክልክል ነው የሚል ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

ማክሰኞ ምሽት ፓላስ ከኢፕስዊች ታውን ጋር በነበረው ጨዋታ ማርክ ጉዬ የኤፍኤውን ማስጠንቀቂያ ችላ ብሎ ‘ጂሰስ ላቭስ ዩ’ አሊያም ‘እየሱስ ይወዳችኋል’ የሚል መልዕክት ፅፎበት ገብቷል።

የፕሪሚዬር ሊጉ ክለቦች ለኤልጂቢቲኪው+ ማኅበረሰብ ያላቸውን ድጋፍ ለማሳየት አምበሎቻቸው የቀስተ ደመና ኅብረ ቀለማት ያሉትን መለያ ክንዳቸው ላይ አጥልቀው እንዲገቡ ያደርጋሉ።

ፉትቦል አሶሲዬሽን የተባለው የሊጉ አስተዳዳሪ ኃይማኖታዊ ምልክቶች የእግር ኳስ ማሊያ እና ሌሎች ቁሳቁሶች ላይ መፃፍ ክልክል ነው ሲል ለክለቡ እና ለአምበሉ ማስጠንቀቂያ የላከው ባለፈው ቅዳሜ ነበር።

በተመሳሳይ የኢፕስዊች አምበል የሆነው ግብፃዊው አማካይ ሳም ሞርሲ ባለፈው ቅዳሜም ሆነ ማክሰኞ ምሽት በነበረው ጨዋታ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን የአምበሎች መለያ ሳያጠልቅ ነው የገባው።

 

ኢፕስዊች ታውን በለቀቀው መግለጫ ሞርሲ “በኃይማኖቱ ምክንያት” መለያውን ማድረግ እንደማይፈቅድ ማሳወቁ ይታወሳል።

ማክሰኞ ምሽት ከነበረው ጨዋታ በኋላ የፓላስ አሰልጣኝ ኦሊቨር ግላስነር ስለጉዳዩ ተጠይቀው “ማርክ የራሱ አተያይ አለው። የሁሉን ሰው አመለካከት እንቀበላለን፤ እናከብራለንም” ብለዋል።

ጉዬ ማስጠንቀቂያ ቢሰጠውም ጉዳዩን በመድገሙ ኤፍኤው ሊቀጣው እንደሚችል ይጠበቃል።

ይህ ዘመቻ ከአውሮፓውያኑ ኅዳር 29 እስከ ረቡዕ ታኅሣሥ 5 የሚዘልቅ ነው። የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ስቶንዎል ከተሰኘው የእርዳታ ድርጅት ጋር በመጣመር ነው አምበሎች ይህን ባንዲራ እንዲያጠልቁ የሚያደርገው።

የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የኢፕስዊቹ አምበል ግብፃዊው ሳም ሞርሲ ይህን ባንዲራ አላጠልቅም ያለ የመጀመሪያው ተጫዋች አይደለም።

ከዚህ ቀደም በተመሳሳይ የእስልምና እምነት ተከታይ የሆነው የሼፊልድ ዩናይትዱ ተከላካይ አኔል አህመድሆድዚች ባንዲራውን አላጠልቅም ማለቱ ይታወሳል።

አሁን ለኤቨርተን የሚጫወተው ሴኔጋላዊው አማካይ ኢድሪሳ ጋና ጉየ ለፓሪ ሳን ዠርማ በሚጫወትበት ወቅት በተመሳሳይ የቀስተ ደመና ቀለማት ያሉትን ማሊያ አልለብስም ማለቱ አይዘነጋም።

Page 1 of 740