Administrator

Administrator

መንግስት መሰረተቢስ ውንጀላ ነው በሚል ያጣጥለዋል
የኢትዮጵያ መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው የተራቀቀ ጫና፣ ሚዲያዎቹ በመጪው ግንቦት ወር የሚካሄደውን ምርጫ በተመለከተ በሚሰሩት ዘገባ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ምህዳሩን እያጠበበባቸው ነው ሲል ሂዩማን ራይትስ ዎች ገለጸ፡፡
መንግስት የግሉን ሚዲያ እንደ አንድ የታመነ የመረጃና የትንተና ምንጭ ሳይሆን እንደ ስጋት በመቁጠር የተጠና ጫና ያደርስበታል ያሉት የሂውማን ራይት ዎች የአፍሪካ ምክትል ዳይሬክተር ሌስሊ ሌፍኮው ሚዲያው በመጪው ምርጫ ቁልፍ ሚና መጫወት ቢኖርበትም፣ በአንጻሩ ግን በርካታ የአገሪቱ ጋዜጠኞች ምርጫን በተመለከተ በሚያቀርቡት ዘገባ ለእስር እንዳረጋለን የሚል ስጋት እንዳደረባቸው ገልጸዋል፡፡
መንግስት በአገሪቱ የግል ሚዲያ ላይ የሚያደርገው ጫና እየተባባሰ በመምጣቱ ባለፈው አመት ብቻ ስድስት የግል የህትመት ውጤቶች ተዘግተዋል፤ በ22 ጋዜጠኞች፣ ብሎገሮችና አሳታሚዎች ላይ የወንጀል ክስ ተመስርቶባቸዋል፤ ከ30 በላይ ጋዜጠኞችም እስራትን በመፍራት አገራቸውን ጥለው ተሰደዋል ብሏል ሂዩማን ራይትስ ዎች ከትናንት በስቲያ ባወጣው ሪፖርት፡፡
“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም፣ የመገናኛ ብዙሃን ነጻነት ጥሰት በኢትዮጵያ” የሚል ርዕስ ያለው  ሪፖርቱ፣ የኢትዮጵያ መንግስት ላለፉት አራት አመታት ነጻ ዘገባን የሚያቀጭጩ ተግባራትን ሲፈጽም እንደቆየ ጠቅሶ፣ በእነዚህ አመታትም ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብታቸውን በመጠቀማቸው 19 ጋዜጠኞች መታሰራቸውንና 60 ያህሉም መሰደዳቸውን ገልጿል፡፡
ሂውማን ራይትስ ዎች በስደትና በአገራቸው የሚገኙ ከ70 በላይ ጋዜጠኞችን አነጋግሬ ያዘጋጀሁት ነው ባለው በዚህ ሪፖርቱ፣ በአገሪቱ አብዛኞቹ የህትመትና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች በመንግስት ቁጥጥር ስር እንደሚገኙ ጠቁሞ፣ ጥቂት የግል የህትመት ውጤቶችም እንዳይዘጉ በመስጋት ፖለቲካዊ ጉዳዮችን ሲዘግቡ በአብዛኛው በራሳቸው ላይ ሳንሱር እንደሚያደርጉ ጠቁሟል፡፡መንግስት በበኩሉ፤ ሂዩማን ራይትስ ዎች የሚያወጣቸው የነፃነትና መብት ጥሰትን የተመለከተ ሪፖርቶች መሰረተ ቢስ እንደሆነ በመግለፅ በተደጋጋሚ ማጣጣሉ ይታወቃል፡፡

           በኢትዮጵያ ተግባራዊ በመደረግ ላይ የሚገኙት የታክስ ፖሊሲዎችና ህጎች ከወቅታዊ አለማቀፍና አገራዊ ሁኔታዎች ጋር ተገናዝበው መሻሻል እንደሚገባቸው የፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ (የማህበራዊ ጥናት መድረክ) ጥናት  አመለከተ፡፡በመድረኩ አዘጋጅነት “የኢትዮጵያ የታክስ ፖሊሲና ህጐች ቅኝት” በሚል ርዕስ መድረኩ ያቀረበው ጥናታዊ ፅሁፍ እንደጠቆመው፤ የአገሪቱ የገቢ ግብርና የቫት ህጎች ከአስር አመት በላይ ያስቆጠሩ ቢሆኑም ጉልህ የማሻሻያ ለውጥ አልተደረገባቸውም፡፡ ከወር ደሞዝ ታክስ የማይከፈልበት 150 ብር ወይም ከአመት ገቢ 1800 ብር እንዲሆን ከአመታት በፊት የወጣው ህግ ከብር የመግዛት አቅም መሸርሸርና ከዋጋ ንረት ጋር ተያይዞ ከመጡ ለውጦች ጋር ተገናዝቦ አልተሻሻለም፡፡ አላግባብ ከፍተኛ የታክስ ክፍያ የተጣለባቸው ድርጅቶች ጉዳያቸው እንዲመረመር አቤቱታ ማቅረብ ከፈለጉ፣ በቅድሚያ ግማሽ ያህሉን ክፍያ እንዲፈፅሙ እንደሚገደዱና ለአቤቱታቸው ምላሽ ለማግኘት ረጅም ጊዜ እንደሚንገላቱ የጠቆመው ጥናቱ፤ ብዙውን ጊዜም የሚያገኙት ውሳኔ ፍትሀዊ  እንዳልሆነ ይነገራል ብሏል፡፡ የታክስ ኦዲትን አስመልክቶም የታክስ ኦዲት የሚደረገው ከ4 እና ከ5 አመት በኋላ ስለሆነ የተጠራቀመ የታክስ እዳ እንዲከፍሉ የሚወሰንባቸው ድርጅቶች ከፍተኛ ወለድም ጭምር እንደሚጫንባቸው ጥናቱ ገልጿል፡፡የንግድ ድርጅቶች የ‹‹ሀ›› ምድብ፣ የ‹‹ለ›› ምድብ በሚል የሚፈረጁበት አመታዊ የሽያጭ ገቢ  በዋጋ ንረት ሳቢያ የብር የመግዛት አቅም ተሸርሽሮ ሽያጫቸው ላይ ጭማሪ ቢያሳይም ህጉ ግን እንዳልተሻሻለም በጥናቱ ተጠቅሷል፡፡የ‹‹ሐ›› ምድብ ተብለው በሚፈረጁትና አመታዊ ሽያጫቸው እስከ 100 ሺህ ብር  በሆኑ ድርጅቶች ላይ የሚደረገው የታክስ ክፍያ አወሳሰንም ውስብስብና በግምት ላይ የተመሰረተ ነው ብሏል፡፡
ብዛት ያላቸው መመሪያዎች በስራ ላይ መዋላቸው በታክስ ከፋዩና አንዳንድ ጊዜም በግብር ሰብሳቢ መስሪያ ቤቱ ባለሙያዎች ግራ አጋቢ እንደሚሆኑ ያመለከተው ጥናቱ፤ በተለያዩ የግብር መሰብሰቢያ ቢሮዎች ወጥ የሆነ መረጃ ያለመኖር እንዲሁም  ባለሙያዎችም መረጃዎቹን የሚረዱበት አግባብ ወጥ አለመሆኑ እንዲሁም በህጉ ላይ የተቀመጠውና በተግባር የሚታየው የተለያዩ መሆናቸው እንደችግር ተጠቅሰዋል፡፡ጥናቱ በታክስ ፖሊሲና ህጎች ዙሪያ መሻሻል ያለባቸውን ነገሮች ያስቀመጠ ሲሆን በአጠቃላይ ግን በአገር ውስጥና በአለም አቀፍ ደረጃ ያሉ ለውጦችን ግምት ውስጥ ማስገባት እንደሚኖርበት ተጠቁሟል፡፡
 “ፎረም ፎር ሶሻል ስተዲስ” (የማህበራዊ ጥናት መድረክ) በማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ጥናትና ምርምር እንዲሁም ሕዝባዊ ውይይቶችን የሚያካሂድ መንግስታዊ ያልሆነ አገር በቀል ድርጅት ነው፡፡

ተደጋጋሚ የቅጥር ማስታወቂያ ባወጣም ሠራተኛ ማግኘት አልቻልኩም ብሏል
በአመራር ደረጃ ላይ ያሉ ሠራተኞች የአመለካከትና የአቅም ችግር እንዳለባቸውም ገልጿል

   የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር በያዝነው አመት ካጋጠሙት ችግሮች ሁሉ እጅግ የከፋው በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው ከሥራ መልቀቃቸው መሆኑንን በመጠቆም ይህም በሚፈልገው መጠን ለመሥራት እንዳይችል እንቅፋት እንደሆነበት ተገለፀ፡፡ የመገናኛና ኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዶ/ር ደብረፅዮን ገ/ሚካኤል፤ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከትናንት በስቲያ ባቀረቡት የስድስት ወራት እቅድ አፈፃፀም ሪፖርት ላይ እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ የተለያዩ ችግሮች የገጠሙአቸው ቢሆንም በጐላ መልኩ የሚጠቀሰው ግን በርካታ ሠራተኞች በየጊዜው መልቀቃቸው እንደሆነ ገልፀዋል፡፡ ከሥራቸው በለቀቁ ሠራተኞች ምትክ ለመቅጠርና ክፍት የሥራ ቦታዎች ለማሟላት የቅጥር ማስታወቂያ በተደጋጋሚ ቢወጣም በሚፈለገው መጠንና ጊዜ የሰው ኃይል ከገበያው ለማግኘት አለመቻሉን ገልፀዋል፡፡ ችግሩን ለመቅረፍ ከፍተኛ ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ተደጋጋሚ የሥራ ማስታወቂያዎችን ማውጣትና ያሉት ሰራተኞች በተቻለ መጠን ስራዎችን በማካካስ እንዲሰሩ ማድረግ እየተወሰዱ ካሉት እርምጃዎች ተጠቃሽ እንደሆኑም ገልፀዋል፡፡ የሥራ ተቋራጮች
በውላችን መሰረት የግንባታውን ሥራ በተቀመጠው ጊዜ ያለማስኬድ ችግር አለባቸው ያሉት ሚኒስትሩ፤ የስራ ተቋራጮቹ በገቡት ውል መሰረት ስራዎቹን እንዲያከናውኑ ኃላፊነት እንዳለባቸው የማስገንዘብ ስራ እየሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡ ሚኒስቴር መ/ቤቱ በዋናነት ከኮንስትራክሽን ፕሮጀክቶች አፈፃፀም መጓተት ጋር በተያያዘ የተመደበለትን በጀት በተሟላ መልኩ መጠቀም አለመቻሉን ሚኒስትሩ በሪፖርታቸው ላይ ገልፀዋል፡፡

“የስዕል ስራዎቿን ለእይታ በማብቃታችን ኩራት ይሰማናል”
                           - የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆን ኬሪ
 
ትውልደ ኢትዮጵያዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት በአለማቀፍ ደረጃ የላቀ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የስነ-ጥበባት ባለሙያዎች በየአመቱ የሚሰጠውን የ2015 የስነ-ጥበባት ሜዳሊያን ተቀበለች፡፡ኢትዮ- አሜሪካዊቷ ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ በአለማቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የስነ-ጥበብ ስራዋ እና ባህላዊ ዲፕሎማሲን በማጠናከር ረገድ በፈጠረችው ተጽዕኖ ለዚህ ሽልማት መብቃቷን የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡የመስሪያ ቤቱ ቃል አቀባይ ለአርት ኒውስ ድረገጽ እንደተናገሩት፣ ሰዓሊዋ በሙያዋ ላሳየችው ጉልህ ቁርጠኝነት እንዲሁም አርት ኢን ኢምባሲስ በተሰኘው ፕሮግራምና በአለማቀፍ የባህል ልውውጥ መስክ ላበረከተችው አስተዋጽኦ እውቅና ለመስጠት፣ የዘንድሮውን ሽልማት ከተቀበሉት 7 ሰዓሊያን አንዷ ተደርጋ ተመርጣለች፡፡እ.ኤ.አ በ1970 በአዲስ አበባ የተወለደችው ሰዓሊ ጁሊ ምህረቱ፤ በተለያዩ የውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች የስነጥበባት ትምህርቶችን የተከታተለች ሲሆን፣ በአለማቀፍ ደረጃ በተዘጋጁ በርካታ የግልና የጋራ የስዕል አውደ ርዕዮች ላይ ስራዎቿን ለእይታ በማብቃትና የታላላቅ ሽልማቶች አሸናፊ በመሆን ትታወቃለች፡፡ በአሁኑ ሰዓትም ነዋሪነቷ በአሜሪካ ኒውዮርክ ነው፡፡የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጆን ኬሪ በሽልማት ስነስርዓቱ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ የጁሊ ምህረቱን ስዕሎች በተመለከተ በሰጡት አስተያየት፣ በተለያዩ አገራት በሚገኙ ኤምባሲዎቻችን ለእይታ ያበቃናቸው የጁሊ ስዕሎች እጅግ ማራኪ ናቸው፣ በስራዎቿ ኩራት ይሰማናል ብለዋል፡፡ ላበረከተችው አስተዋጽኦም ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

•    በኢትዮጵያ ቅርንጫፍ ስትተዳደር ቆይታለች
ከሀያኛው ክፍለ ዘመን መጀመሪያ አንስቶ የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን አካል የነበረችው የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ሰሞኑን  በራሷ እንድትተዳደር የተወሰነ ሲሆን  አባ መንግስተአብ ተስፋማሪያም የመጀመሪያው የኤርትራ ሊቀጳጳስ ሆነው ተሾሙ፡፡ ኤርትራ ከኢትዮጵያ ከተነጠለች በኋላም የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን  በአዲስ አበባ ቅርንጫፍና በአንድ የጳጳስ ጉባኤ ስር ስትተዳደር የቆየች ቢሆንም ሰሞኑን ከቫቲካን የወጣ መረጃ፤ የሮማ ካቶሊካዊት ቤ/ክርስትያን አቡን ጳጳስ ፍራንሲስ የኤርትራ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን በአስመራ ቅርንጫፍ ራሷን ችላ እንድትተዳደር መወሰናቸውንና አባ መንግስተአብ ተስፋማሪያምን ሊቀጳጳስ አድርገው መሾማቸውን ጠቁሟል፡፡
የኤርትራ የመጀመሪያው የካቶሊክ ሊቀጳጳስ ሆነው የተሾሙት የአስመራ  ሀገረስብከት ጳጳስ  የነበሩት አባ መንግስተአብ ተስፋማርያም፤ ኤርትራ የ23ኛ አመት የነፃነት በአሏን ስታከብር “ወንድምህ የት ነው” በሚል ርዕስ በወቅታዊ የኤርትራ ሁኔታ ላይ በተለይ የወጣቶችን ስደት የተመለከተ  ሀተታና ጥያቄዎችን የያዘ ሰነድ ለፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ካስረከቡ አራት ጳጳሳት  አንዱ ነበሩ፡፡የጳጳሱን መሾም ተከትሎም የኤርትራ መንግስት ደጋፊ በሆኑ ድረገፆች አቡነ መንግስተአብ ተስፋማርያምን የሚያጥላሉ አስተያየቶች እየተሰነዘሩ ይገኛሉ፡፡ ኢትዮጵያና በኤርትራ የተደረገውን ጦርነት ተከትሎ  የሁለቱ አገራት ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያናት ስብሰባዎቻቸውን በኢትዮጵያም ሆነ በኤርትራ ሊያደርጉ ባለመቻላቸው በሮም ሲያካሂዱ መቆየታቸው ታውቋል፡፡

የደቡብ አፍሪካው ስታንዳርድ ባንክ በመጪው መጋቢት ወር መጨረሻ በኢትዮጵያ ተወካይ ቢሮ
ሊከፍት መሆኑን ቬንቸርስ አፍሪካ ድረገጽ ዘገበ፡፡የአገሪቱ የፋይናንስ ህግ የውጭ አገራት ባንኮች በመስኩ እንዳይሰሩ የሚከለክል እንደመሆኑ፣ ባንኩ ኢትዮጵያ የሚከፍተው ተወካይ መስሪያ ቤት የገንዘብ ብድርና ቁጠባን የመሳሰሉ ስራዎችን እንደማያከናውን የስታንዳርድ ባንክ ምክትል ፕሬዚዳንት ጣይቱ ወንድወሰንን ጠቅሶ ዘገባው ገልጿል፡፡በአዲስ አበባ የሚከፈተው ቢሮ ስታንዳርድ ባንክ በአገሪቱ ከሚገኙ ኩባንያዎች ጋር መልካም የስራ ግንኙነት ለመፍጠር የሚያስችሉ ስራዎችና የገበያ ጥናቶች የሚከናወንበት እንደሚሆን የገለጸው ዘገባው፤ የቢሮው መከፈት ባንኩ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ስራዎችን ለማከናወን ፍላጎት ላላቸው ደንበኞቹ የማማከር አገልግሎት ለመስጠት እንደሚያግዘውም አስረድቷል፡፡

    በአምስት አመቱ የጣሊያን ወረራ ወቅት በውስጥ አርበኛነታቸው የሚታወቁትን ወ/ሮ የሸዋረገድ ገድሌን የህይወት ታሪክ የሚዘክረው መፅሐፍ ዛሬ ከቀኑ 7፡30 ጀምሮ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቤተመዛግብትና ቤተ መጽሐፍት ኤጀንሲ (ወመዘክር) አዳራሽ ይመረቃል፡፡ “ሸዋረገድ ገድሌ፤ የአኩሪ ገድላት ባለቤት” በሚል ርዕስ የታተመው መጽሃፍ፤ ከ1878-1942 ስለኖሩትና በጣሊያን ወረራ ወቅት በዱር በገደሉ ላሉ አርበኞች  መረጃዎችን በማቀበል ታላቅ ገድል ስለፈፀሙት እናት አርበኛ ይተርካል፡፡ የመፅሐፉ ፀሐፊ ደራሲ ሺበሺ ለማ ሲሆኑ መጽሐፉን ያሳተሙት የአርበኛዋ የወንድም ልጅ ዶ/ር ክፍሌ ማርቆስ ገድሌ መሆናቸው ታውቋል፡፡ መፅሐፉ ለአገር ውስጥ በ70ብር፣ ለውጭ በ25 ዶላር ለገበያ የቀረበ ሲሆን በዛሬው የምረቃ ስነስርአት ላይ የቀድሞ ፕሬዚዳንት አቶ ግርማ ወ/ጊዮርጊስ እና ሌተናል ጃገማ ኬሎ እንደሚገኙ ታውቋል፡፡

አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛው የህይወት ዘመን ተሸላሚ እጩ ሆኗል
በመጪው የካቲት የሚያካሂደውና በኢትዮ ፊልምስ ባለቤትነት የሚመራው የጉማ ፊልም ሽልማት ምርጥ አምስቶች ከትናንት በስቲያ በሃርመኒ ሆቴል ይፋ ሆኑ፡፡ በህይወት ዘመን ተሸላሚነት አርቲስት ደበበ እሸቱ ብቸኛ እጩ መሆኑም ተገልጿል፡፡ በዕለቱ በ17 ዘርፎች በዳኞችና በተመልካች የተመረጡ አምስት አምስት እጩዎች የታወቁ ሲሆን ዘርፎቹም በምርጥ የተማሪ አጭር ፊልም፣ በምርጥ ድምፅ፣ በምርጥ ሙዚቃ፣ በምርጥ ስኮር፣ በምርጥ ሜክአፕ፣ በምርጥ የፊልም ጽሑፍ፣ በምርጥ ቅንብር፣ በምርጥ ሲኒማቶግራፊ፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለባት ህፃን ተዋናይት፣ በምርጥ ተስፋ የተጣለበት ህፃን ተዋናይ፣ በምርጥ ረዳት ሴት ተዋናዮች፣ በምርጥ ረዳት ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ ሴት ተዋናይት፣ በምርጥ ወንድ ተዋናይ፣ በምርጥ የተመልካች ምርጫ፣ በምርጥ ዳይሬክተርና በምርጥ ፊልም ጐራ በሚል ተከፋፍለዋል፡፡ መቶ ዳኞች በተሳተፉበት በዚህ ምርጫ ምርጥ አምስቶቹ የታወቁ ሲሆን በቀጣይ ከአንድ እስከ ሦስት የሚወጡት ተለይተው፣ የካቲት 16 ቀን 2007 ዓ.ም ደማቅ የሽልማት ስነ ስርዓት እንደሚካሄድ የኢትዮ ፊልም መስራችና ስራ አስኪያጅ ዮናስ ብርሃነ መዋ ለጋዜጠኞች ተናግሯል፡፡ ፕሮግራሙን ሙሉ በሙሉ ስፖንሰር ያደረገው በደሌ ቢራ ነው፡፡

በታሪካዊቷ ደሴ ከተማ መሀል በሚገኘው ደሴ ህንጻ ላይ ደረጃውን የጠበቀ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት መከፈቱ ተገለፀ፡፡ “
ዙም ሲኒማ” ቤት 265 ምቹ መቀመጫዎች ያሉት ሲሆን ኤች.ዲ ዘመናዊ ፕሮጀክተርና ዘመኑ የደረሰባቸው የድምፅ ቴክኖሎጂዎች ተገጥሞለታል፡፡
ሲኒማ ቤቱን በባለቤትነት የሚያስተዳድረው የጂታብ ኢንተርቴይመንት ሥራ አስኪያጅ አቶ ታዲዮስ ጌታቸው፤ “ደሴ ካላት ረጅም ዕድሜና የከተማው ነዋሪ ለኪነጥበብ ካለው ጥልቅ ፍቅር አንፃር ደሴ እስካሁን እንዲህ ያለ ዘመናዊ ሲኒማ ቤት ሳታገኝ መቆየቷ የሚያስቆጭ” ነው ብለዋል፡፡
ዳራሹ ከሲኒማ በተጨማሪ እንደ ቴአትር፣ ስታንድአፕ ኮሜዲና  ሰርከስ ለመሳሰሉ ጥበባዊ ትርዒቶች ምቹ በመሆኑ በዘርፍ የተሰማሩ ባለሙያዎች ቢመጡ አብሮ ለመስራት ዝግጁ ነን ብለዋል - አቶ ታዲዮስ፡፡ አስራ አንድ በአምስት (11x5) ሜትር ስፋት ያለው ዘመናዊ ስክሪን የተዘረጋለት አዲሱ ሲኒማ ቤት፤ ከጥር 16 ቀን 2007 ዓ.ም ጀምሮ በይፋ ስራ የሚጀምር ሲሆን የፊልም ፕሮዱዩሰሮች በሲኒማ ቤቱ ፊልማቸውን እንዲያሳዩ ጥሪ ቀርቧል፡፡   

   ከእለታት አንድ ቀን ከባድ የበረዶ ዘመን መጣና እፅዋትና እንስሳትን በቅዝቃዜ ጨረሰ፡፡ በየእለቱ ሞቶ የሚያድረው ነብስ እጅግ እየረከተ መጣ፡፡ ይሄኔ የባህር አሳዎች መመካከር ጀመሩ፡፡ ከነዚህ አሳዎች መካከልም በጣም እሾካማ የሆኑ አሳዎች አሉ፡፡
አንደኛው አሳ፤ ለሌኛው አሳ፡-
“እስከመቼ ድረስ ዝም ብለን ተቀምጠን በበረዶ ቅዝቃዜ እናልቃለን? ለምን ቢያንስ ተጠጋግተን፣ ተቃቅፈን አንተኛም?” ይለዋል፡፡
ሁለተኛው አሳም፤
“ተቃቅፈንና ተጠጋግተን መተኛቱ ለምን ይጠቅመናል?” ሲል ይጠይቀዋል?
አንደኛው አሳ፤
“በበረዶ ባህር ውስጥ ተራርቀንና ተለያይተን ከሚቀዘቅዘን ተጠጋግተን ብናድር አንዳችን ለአንዳችን ሙቀት እንሰጣለን፡፡ ስለዚህም እርስ በርስ እንክብካቤ የመደራረግ እድል እንፈጥራለን” አለው፡፡ በዚህ ሃሳብ ተስማሙ፡፡ አጠገብ ላጠገብ ሆነው ተኙ፡፡ ሆኖም አንድ ችግር ገጠማቸው፡፡
ሲጠጋጉ ሁሉም እሾሃማ ቆዳ ስለሆነ ያላቸው ያንዱ ቆዳ የሌላኛውን እየወጋው፣ እንደቆንጥር እየጠቀጠቀው ፈፅሞ ለመተኛት አዳገታቸው፡፡ ቢለያዩ ቅዝቃዜው ሊገላቸው ሆነ፡፡ ቢቀራረቡ እሾክ ለሾክ ሆኑና ሊወጋጉ ሆነ፡፡ ምርጫቸው ከሁለቱ አንዱን ማድረግ ሆነ፡- ወይ ተለያይቶ በበረዶው ቅዝቃዜ ማለቅ፤ ወይም ደግሞ እንደምንም እሾክ ለእሾክ ተቻችሎ የጐድን ውጋቱን ችሎ ማደር፡፡
በሁለተኛው ምርጫ ተስማሙ፡፡ ብዙ ሳይገላበጡ፣ ሙቀት እየተለዋወጡ ክፉውን የበረዶ ጊዜ ማለፍ! ጐረቤት ለጐረቤቱ የጐን ውጋት እንዳይሆን መጠንቀቅ፡፡ ውጋቱ ቢኖርም ቁስል ቢፈጠርም ታግሶ፣ ችሎ ማደርን መልመድ! በዚህ ዘዴ ህያው ሙቀት እየተሰጣጡ ያንን ዘመን ተሻገሩ፤ ይባላል!
ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል!
ቀጥቃጭ ሲያረጅ ዱልዱም ይቀጠቅጣል
በሀገራችን የተለያዩ የፖለቲካ ድርጅቶች አንዱ ያንዱን ችግር ችሎ፣ አንዱ ያንዱን ቁስል አክሞ መከራን በትእግስት አልፎ፣ ቢቻልም እሾኩን ነቅሎ፤ ህያው ሙቀት ፈጥሮ አገር ማዳን ባለመቻሉ፤ ብዙ እድልና አጋጣሚ አምልጧል፡፡ ጥቃቅን ችግሮችን በወቅቱ ለማለፍ ባለመቻሉ የመፈረካከስ፣ የመሰነጣጠቅ ከናካቴውም የመበታተን አደጋ ደርቷል፡፡ የእኔ ትልቅ ነኝ …እኔ ትልቅ ነኝ ፍትጊያ ለብዙ መከራ ዳርጓል፡፡ የእኔ ልዋጥ እኔ ልዋጥ ሽኩቻ (Big Fish - Small Fish Theory እንዲሉ ፈረንጆች) ለብዙ አበሳ አጋልጧል፡፡ አገርና ህዝብን ማስቀደምና የጋራ ቤት የሚሰራበትን ወቅት ለየግል ፍልሚያ በመጠቀም አያሌ የአዝመራ ጊዜዎች ባክነዋል፡፡ ልብ ማለት ያለብን ከትላንት የእርስ በርስ አለመግባባት፣ ከትላንት እኔ እበልጥ እኔ እበልጥ ትርምስ ማን ተጠቀመ? የሚለውን ነው፡፡ ዛሬም ከትላንት ለመማር አልረፈደም፡፡ አንድን ወቅት የዓለም ፍፃሜ አድርጐ መፈረጅ ወደ ተስፋ-መቁረጥ ነው የሚያመራው፡፡ ይልቁንም ሁሉን ነገር በትላንት በዛሬና በነገ ሰንሰለት ላይ እንዳለ ክስተት እያዩ፣ በትእግስትና በፅናት መጓዝን ለማወቅ ታላቅ ጥበብ ነው፡፡ አገር “በእድገት ላይ ነን ተብሎ ሊፃፍባት አይችልም፡፡ ወይም እንደ ንግድ በአዲስ መልስ ሥራ ጀምረናል” አይባልባትም፡፡ ዲሞክራሲ የተከለከለች የበለስ ፍሬ የማትሆነው ሁሉን ነገር እንደ ሂደት እያያያዝን ካየን ነው፡፡ ፍፁም የሆነ ዲሞክራሲ እንዳለመኖሩ፤ በተናፅሮ የምናገኘውን ዲሞክራሲ ለመጨበጥም ብዙ ድካም ይጠይቃል - በድሮው ቋንቋ ያለመስዋዕትነት ድል የለም - እንደ ማለት ነው፡፡ ከማማረር መማር ነው ነገሩ!” ጥርስ ነጭ ይሁን አይሁን፤ ግን ይጠንክር” ይላሉ አበው፡፡ አንድም፤ “በካፊያው ምን አስሮጣችሁና ገና ዝናቡ አለ አይደለም ወይ” የሚለውን ልብ ብሎ ማሰብ ነው፡፡
ዲሞክራሲን፤ ፍትሐዊነትን፣ መልካም አስተዳደርን፣ እውነተኛ ምርጫን፣ እኩልነትትን፣ ዲፕሎማሲን፣ ለማግኘት አያሌ አመታትን አሳልፈናል፡፡ እንደ አፍ እንደማይቀልም፣ አውቀናል፡፡ ተገንዝበናል፡፡ አንድም የራሳችንን የሽኩቻ ባህላዊ አሽክላ በቀላሉ ለመላቀቅ ባለመቻል፤ አንድም ደሞ ከውጪ የሚመጣብንን ጫና ለመመከት ባለመታደል፣ ጠንክረን ዳር የመድረስ ነገር የህልም ሩጫ ሲሆንብን ከርሟል፡፡ ዊንስተን ቸርችል፤ “እውነት በጣም እፁብ በመሆኗ በውሸት የክብር ዘቦች መጠበቅ ይኖርባታል” ያለውን እንኳ ለመፈፀም መቻቻል አልሆነልንም፡፡ ድህነትን ለመዋጋት ያላግባብ የመበልፀግን አባዜ አስቀድሞ ማሸነፍ ያስፈልጋል፡፡ ወዲህ እየለፈፉ ወዲህ እየዘረፉ አይሆንም፡፡ ከልብ የማናደርገውን ነገር በአዋጅ ብንናገረው ግማሽ-ጐፈሬ ግማሽ-ልጭት ሆኖ ነው የሚቀረው፡፡ ሕግ ለሁሉም እኩል የሚሰራባት አገር ታስፈልገናለች! “ድካማችን ሁሉ የእንቧይ ካብ፣ የእንቧይ ካብ” የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ሟርት የማይበዛባት አገር ታስፈልገናለች! በአንድ ሰሞን ዘመቻ ብቻ አገር ይለወጣል ከሚል አስተሳሰብ የፀዳች አገር ታስፈልገናለች! ጅራፍ ራሱ ገርፎ እራሱ ሲጮህ የማናይባት አገር ታስፈልገናለች! ራሱ ሰርቆ አፋልጉኝ ይላል እንደተባለው አይን-አውጣ፣ ሌባ እያየን ዝም የማንልባት አገር ታስፈልገናለች! ባንድ በኩል የራሳችንን ድምፅ ብቻ መልሰን ለማዳመጥ ዝግጁ ከሆን፣ በሌላ በኩል እኔ ያልኩትን ብቻ አዳምጡ ካልን፤ የትላንትናን ዜማ ብቻ የምንደግም ከሆነ፤ “ገልቱ የራሷ ወጥ ይጣፍጣታል”፤ “ቀጥቃጭ ሲያረጅም ዱልዱም ይቀጠቅጣል” የሚሉትን ተረቶች ስናሰላስል መክረማችን ነው!