Administrator

Administrator

   አሜሪካ ለግብጽ ስትሰጥ የቆየችውንና ለሁለት አመታት ያህል አቋርጣው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደገና ሙሉ ለሙሉ መስጠት ልትጀምር እንደሆነ ማስታወቋን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ፡፡ የኦባማ አስተዳደር ለግብጽ ሲሰጠው የቆየውንና ከ2013 ጥቅምት ወር ወዲህ አቋርጦት የነበረውን 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አመታዊ የወታደራዊ መሳሪያዎች ድጋፍ እንደገና ለመጀመር ውሳኔ ላይ መድረሱን ባለፈው ክሰኞ አስታውቋል፡፡የግብጹ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ እስከምትረጋጋና ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ እስኪታይ ድረስ፣ አሜሪካ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ አቋርጣ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመስጠት መወሰኑ፣ ግብጽን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ አሜሪካ ሰራሽ የወታደራዊ መሳሪያዎች ባለቤት ያደርጋታል ያለው ዘገባው፣ ላለፉት ሁለት አመታት በአሜሪካ እጅ የቆዩ 12 ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶችን፣ 20 ቦይንግ ሃርፖን ሚሳየሎችን፣125 አሜሪካ ሰራሽ አብራምስ ኤምዋንኤዋን ታንኮችንና ሌሎች መሳሪያዎችን ማግኘት እንደሚያስችላት የአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ካውንስል ቃል አቀባይ በርናዴት ሜሃን መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡  አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመቀጠል የወሰነችው፣ የራሷን የብሄራዊ ደህንነት ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ፣ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፤ የድንበርና የባህር ደህንነቶችን ለማስጠበቅና አይሲሲ የተባለው ታጣቂ ቡድን በሲናይ አካባቢ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲውሉ በሚያስችል መልኩ ማሻሻሏንም አስታውቀዋል፡፡ ኦባማ ክግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን ወታደራዊ ድጋፍ በዘላቂነት ለማስቀጠል ለአሜሪካ ምክር ቤት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ግብጽ ከ2018 ጀምሮ የጦር መሳሪያዎችን በብድር መግዛቷን ማቆም እንደሚገባት አሳስበዋቸዋል፡፡አልጀዚራ በበኩሉ፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አሜሪካ ለግብጽ ሙሉ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኗ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸውን ጠቅሶ፣ ሂውማን ራይትስ ፈርስት የተባለው ተቋም ዳይሬክተር ኔል ሂክስ “አሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለሚታዩባት ግብጽ ድጋፏን ለመቀጠል መወሰኗ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ አትሰጥም የሚል አደገኛ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡አሜሪካ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ለግብጽ የምትሰጠውን ድጋፍ በከፊል እንደምትጀምር ማስታወቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ ግብጽ ከአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ በማግኘት ከእስራኤል ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ጠቁሟል፡፡

Monday, 06 April 2015 08:58

የፍቅር ጥግ

ፍቅር ልዩ ቃል ነው፡፡ የምጠቀምበት ከልቤ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ቃሉን ደጋግማችሁ ስትሉት ይረክሳል፡፡
ሬይ ቻርልስ
ድንገት በጭጋጋማው የለንደን ከተማ ውስጥ አየሁሽ፡፡ ፀሐይዋ ሁሉን ስፍራ አድምቃው ነበር፡፡
ጆርጅ ገርሽዊን
ፍቅር እንደ ቧንቧ መክፈቻ ነው፤ ይዘጋል ይከፈታል፡፡
ቢሊ ሆሊዴይ
ከፍቅረኛህ ጋር ስትለያይ ጠቅላላ ማንነትህ ይፈራርሳል፡፡ ልክ እንደሞት ማለት ነው፡፡
ዴኒስ ቋይድ
ለሥራ ጊዜ አለው፡፡ ለፍቅር ጊዜ አለው፡፡ ከሁለቱ የሚተርፍ ሌላ ጊዜ የለም፡፡
ኮኮ ቻኔል
በዓለም ላይ ምርጡ ጠረን የምትወጂው ወንድ ነው፡፡
ጄኔፈር አኒስተን
ጀግንነት ሰውን ያለቅድመ ሁኔታ፣ ምላሽ ሳይጠብቁ ማፍቀር ነው፡፡
ማዶና
ፍቅር እንደ ጦርነት ሁሉ ለመጀመር ቀላል፤ ለመጨረስ ግን ከባድ ነው፡፡
ያልታወቀ ሰው
ሦስት ነገሮችን መደበቅ አይቻልም፡- ጉንፋን፣ ድህነትና ፍቅር፡፡
የአይሁዳውያን አባባል
ፍቅር ማለቂያ የሌለው ይቅር ባይነት ነው፡፡
ፒተር ኡስቲኖቭ
ፍቅር ነበልባል የመሆኑን ያህል ብርሃንም መሆን አለበት፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዮ
ፍቅር የሌላው ሰው ደስታ ለራስህ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ ነው፡፡
ሮበርት ሔይንሌይን
ፍቅር ሰውን ከራሱ ባርኔጣ ውስጥ ስቦ የሚያወጣ ምትሃተኛ ነው፡፡
ቤን ሄሽት

Monday, 06 April 2015 08:55

የሲኒማ ጥግ

ሥራውን ሰርተህ ሰዎች እንዲያዩልህ ትፈልጋለህ፡፡ ነገር ግን ሥራውን እየሰራሁ ሳለ ስለውጤቱ አላስብም፡፡ ፊልሙ ተወዳጅ ሆኖ ቦክስ ኦፊስ ቢገባ ወይም ከንቱ ቢሆን ግዴለኝም፡፡ ለእኔ ፊልሙ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በራሱ  ስኬት ነው፡፡ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ስኬት ናቸው፡፡
ጆኒ ዲፕ
የአማካዩ የሆሊውድ ኮከብ ተዋናይ ፍላጎት በአሜሪካዊ መደነቅ፣ በጣሊያናዊ መጠበስ፣ ከእንግሊዛዊ ጋር ትዳር መያዝና ፈረንሳዊ ፍቅረኛ መያዝ ነው፡፡
ካትሪን ሄፕበርን
ለወጣት ፊልም ሰሪዎች የምለግሰው ምክር፡- “ያለውን አካሄድ አትከተሉ፤ አዲስ ጀምሩ!” የሚል ነው፡፡
ፍራንክ ካፕራ
ፊልም ከሦስቱ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አንዱ ነው፡፡ የቀሩት ሁለቱ ሂሳብና ሙዚቃ ናቸው፡፡
ፍራንክ ካፕራ
ለፊልም ፈተና መሄዴ ነው ብዬ ስናገር መላው ቤተሰቤ ከልቡ ነበር የሳቀው፡፡
ቪክቶሪያ አብሪል
ታላቅ የፊልም ተዋናይ እሆናለሁ፡፡ ይሄ የሚሆነው ግን መጠጥና ወሲብ ካልቀደሙኝ ብቻ ነው፡፡
ጄይ ፕሪሰን አለን
ተዋናይ ከሚሰራበት ፊልም የበለጠ ገዝፎ መታየት የለበትም፡፡
ክርስቲያን ቤል
ፊልምን በተመለከተ ሰዎች ብዙ ጊዜ የመጥፎ ማዕከላዊ ገፀ ባህርይ መልዕክትንና የፊልሙን መልዕክት ብዙ ጊዜ አይለዩትም፡፡ ግን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡
ክርስቲያን ቤል
ሜክሲኮ ያገኘኋት አንዲት ሴት እንድፈውሳት ፈልጋ ነበር፡፡ እኔ ግን ማንንም መፈወስ አልችልም፡፡ እጄን ጭንቅላቷ ላይ አድርጌ፤ “ፊልሙን በማየትሽ አመሰግንሻለሁ” አልኳት፡፡
ጂም ካቪዜል

በኢጋ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አዘጋጅነት የሚቀርበው “ሰሙነ ህማማት የስነ ጽሑፍና የበገና ምሽት” የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡
በዝግጅቱ ላይ አንጋፋና ወጣት ፀሐፍት፤ ግጥሞችንና ወጐችን በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እየታጀቡ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በምሽቱ ከ20 በላይ የበገና ደርዳሪዎች በአንድ ላይ ተጣምረው በገና በመደርደር ዝግጅቱን እንደሚያደምቁም ተገልጿል፡፡ የዝግጅቱ አላማ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያና ስነ - ጽሑፍ ያላቸውን ተዛምዶ ለማህበረሰቡ ማስገንዘብና ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው ብለዋል - አዘጋጆቹ፡፡  

   ወጋገን ኮሌጅ በፊልም ሙያ ያሰለጠናቸውን ከ130 በላይ አንጋፋና ጀማሪ አርቲስቶች በዛሬው እለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአለም ሲኒማ አዳራሽ ያስመርቃል፡፡ በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ታዋቂ አርቲስቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የምረቃ ፕሮግራሙን ይታደማሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አርቲስቶች መካከል መሰረት መብራቴ፣ ይገረም ደጀኔ፣ ሸዊት ከበደ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡

Monday, 06 April 2015 08:34

የፖለቲካ ጥግ

ወፍራም ደሞዝ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች!!

የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ጃኮብ ዙማ መደበኛ ትምህርት እንዳልተከታተሉ “አፍሪካ ክራድል” የተባለው ድረገፅ ሰሞኑን ይፋ ያደረገ ሲሆን “7 ቀለም ያልዘለቃቸው የአፍሪካ ፕሬዚዳንቶች” በሚል ባወጣው ዝርዝር ውስጥ ዙማን በአንደኝነት ነው ያስቀመጣቸው፡፡  ሰውየው ያልተማሩ መሆናቸው እምብዛም አልጐዳቸው፡፡ እንደውም ሳይጠቅማቸው አልቀረም፡፡  የዙማ ዓመታዊ ገቢ 270ሺ ዶላር (5ሚ.400ሺ ብር ገደማ) ሲሆን በአሁኑ ሰዓት በአፍሪካ ከፍተኛ ተከፋይ  ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ ዙማ ከዓለማችን 10 ከፍተኛ (Top 10) ተከፋይ ፕሬዚዳንቶች ውስጥ አንዱ ናቸው፡፡
አልጄሪያን እ.ኤ.አ ከ1999 ጀምሮ በመምራት የአገሪቱ አምስተኛ ፕሬዚዳንት የሆኑት አብደላዚዝ ቡቴፍሊካ ዓመታዊ ደሞዛቸው 168ሺ ዶላር ነው፡፡ ቡቴፍሊካ ሁለተኛው፤ ከፍተኛ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡
ኡሁሩ ሙይጋይ ኬንያታ አራተኛው የኬንያ ፕሬዚዳንት ሲሆኑ ሥልጣን የተቆናጠጡት እ.ኤ.አ በ2013 ዓ.ም ነበር፡፡ ኬንያታ በዓመት 132ሺ ዶላር ያገኛሉ፡፡ በ2014 ዓ.ም በወር ይከፈላቸው የነበረውን 14ሺ ዶላር ወደ 11ሺ ዶላር እንዲቀነስ በማድረግ አርአያ ለመሆን ሞክረዋል፡፡ እንዲያም ሆኖ ግን ሶስተኛው የአፍሪካ ከፍተኛ ተከፋይ ፕሬዚዳንት ከመሆን ያገዳቸው ነገር የለም፡፡
ኮሞሮስን ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ በመምራት ላይ የሚገኙት አይኪሊሎ ዲሆይኒኔ፤ በ115ሺ ዶላር ዓመታዊ ገቢ 4ኛው ከፍተኛ ተከፋይ ፕሬዚዳንት ሆነዋል፡፡ ሰውየው ስልጣን ሲይዙ ሙስናን ከአገሪቱ ለማጥፋት ቃል እንደገቡ ተዘግቧል፡፡ ዲሆይኒኔ ያጠኑት ፋርማሲስትነት ነው፡፡
ዴኒስ ሳሶ ንግዩሶ፤ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ የኮንጎ ሪፐብሊክ ፕሬዚዳንት በመሆን አገሪቱን  እየመሩ ይገኛሉ፡፡ በቅርቡ  “ግሎባል ዊትነስ”  እንደዘገበው፤ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ዴኒስ ክሪስትል የአንድ ወር የግል ፍጆታ፣ የ80ሺ የኮንጎ ህፃናትን የኩፍኝ መከላከያ ክትባት ወጪ ይሸፍናል፡፡ የኮንጐው መሪ ዓመታዊ ክፍያ 110ሺ ዶላር ሲሆን 5ኛው ከፍተኛ ተከፋይ የአፍሪካ ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡

Monday, 06 April 2015 08:19

የፀሐፍት ጥግ

ከሞትክ በኋላ መረሳት የማትፈለግ ከሆነ አንድም ለመነበብ የሚበቁ ነገሮችን ፃፍ አሊያም ለመፃፍ የሚበቁ ነገሮችን ሥራ፡፡ ቤንጃሚን ፍራንክሊን ተሰጥኦ ብቻውን ፀሐፊ አያደርግም፤ ከመፅሐፉ ጀርባ ሰው መኖር አለበት፡፡ ራልፍ ዋልዶ ኢመርሰን ራሱን የማይመግብ አዕምሮ ራሱን ይበላል፡፡ ጎሬ ቪዳል የመፃፍ ክህሎት፤ ሌሎች ማሰብ የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ነው፡፡ ኢድዊን ስክሎስበርግ ድድብና ላለማሰብ ምክንያት አይሆንም፡፡ ስታኒስላው ጄርዚሌክ ብዕር የአዕምሮ ምላስ ነው፡፡ ሰርቫንቴስ ስለችሎታዬ ቅንጣት ታህል ጥርጣሬ ኖሮኝ አያውቅም፡፡ መፃፍ እንደምችል አውቅ ነበር፡፡ እየፃፍኩ እንዴት ሆዴን እንደምሞላ ብቻ ነው ማሰብ የነበረብኝ፡፡ ኮርማክ ማክካርቲ ሰው ብዙ በመፃፍ በወጉ መፃፍ ይለምዳል፡፡ ሮበርት ሳውዜይ ከእያንዳንዱ የሰባ መፅሃፍ ውስጥ ለመውጣት የሚፍጨረጨር ቀጭን መፅሃፍ አለ፡፡ ያልታወቀ ፀሐፊ ፀሐፊ ይመሰገን እንደሆነ ለማየት ሌላ የህይወት ዘመን ያስፈልገዋል፡፡ ጆርጅ ሉዊስ ቦርግስ ለራስህ በጣም ቀሽም ፅሑፍ የመፃፍ ዕድል ካልሰጠኸው በጣም ግሩም ፅሁፍ ለመፃፍ ትቸገራለህ፡፡ ስቲቨን ጋሎዌይ አንባቢውን ማሰልቸት ይቅር የማይባል ሃጢያት ነው፡፡ ላሪ ኒቬን

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ባላገር አንድ የማያውቀው ጫካ አቋርጦ ወደ መንገዱ ሊወጣ ሲጓዝ፤ አንድ የንጉሥ ልጅ በፈረስ ሆኖ ሲንሸራሸር ባላገሩን ያገኘዋል፡፡ ባላገሩ እጅ አልነሳም ልዑሉን፡፡ አልተሸቆጠቆጠም፡፡
ልዑሉ በጣም ገረመው፡፡ በአገሩ ደንብ ንጉሥን አክብሮ ለጥ ብሎ እጅ መንሳት ነበረበት፡፡ ባያውቅ ነው ብሎ በመገመት፤
“እንደምን ዋልክ?” ይለዋል፡፡
“ደህና እግዚሐር ይመስገን” ይላል ባላገሩ፡፡
“ለመሆኑ ንጉሥ ማለት ምን ማለት እንደሆነ ታውቃለህ?”
“አላውቅም” አለ ባላገር፡፡
“እንግዲያው ና ፈረሴ ላይ ውጣ፡፡ አፈናጥጬ ይዤህ እሄዳለሁ፡፡ ንጉሥ ማለት በሄደበት ሁሉ ሰው እጅ የሚነሳው፣ መንገደኛ ቆሞ የሚያሳልፈው የተከበረ ሰው ነው። ስለዚህ ቀስ በቀስ ንጉሥ ምንና ማን እንደሆነ ይገባሃል” አለና ያን ባላገር አፈናጠጠው፡፡
ወደ ከተማ እየተቃረቡ መጡ፡፡
“እንግዲህ አሁን ልብ ብለህ አስተውል” አለ ልዑሉ፡፡
የከተማው ሰው ልዑሉን ሲያይ ወዲያው የሚሄደው ቆመ፡፡ የቆመው ለጥ እያለ እጅ ነሳ፡፡ ልዑል  ዝም ብሎ መንገዱን ይቀጥላል፡፡ ህዝም እየቆመ እጅ እየነሳ ማሳለፉን ቀጥሏል፡፡ ይሄኔ ልዑሉ፡-
“አንተ ባላገር፤ ንጉሥ ማን እንደሆነ አሁን ገባህ?” ሲል የጠቀው፡፡
ባላገሩም፤
“አዎን አሁን ገብቶኛል” አለ፡፡
ልዑሉ ቀጥሎ፤
“ማን ነው ንጉሡ?” አለና ጠየቀ፡፡
ባላገሩም፤  
“እንግዲህ ወይ እኔ ወይ አንተ ነና!” አለና መለሰ፡፡
*       *      *
ስለተፈናጠጡ ብቻ የነገሡ የሚመስላቸው አያሌ አይተናል፡፡ በተሰጣቸው ትርጓሜ - ነገር (Definition) መሠረት ብቻ ጉዳዮችን እየተረጎሙ የሚጓዙ የዋሃንንም አስተውለናል፡፡ ግራ ቀኙን ሳያዩ በተሰመረው መስመር ላይ ብቻ የሚነጉዱ፣ ወቅት የሚለወጥ የማይመስላቸውና ወቅትም የማይለውጣቸው በርካታ መንገዶችን ታዝበናል፡ “ሳይማር ያስተማረንን ገበሬ አንረሳውም” ብለው ሲያበቁ ከተማ ገብተው ከተሜ ሲሆኑ፤ የሚገነቡትን ህንፃ ብቻ ዐይን ዐይኑን እያዩ መሰረታቸውን የረሱ ዕልቆ መሣፍርት የሌላቸው መሆናቸውንም ገርሞን አይተናል፡፡ ጥንት “ሠፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ! የረሱህን አልረሳናቸውም” ብለው ጀምረው ከነመፈጠሩም ያላስታወሱት ባለጊዜዎችንም ተመልክተናል፡፡ በህዝብ የሚምል የሚገዘት ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ማህበር አገራችን አጥታ አታውቅም!
የፖለቲካ አየር የኢኮኖሚውን ንፋስ መከተሉ በዓለም ታሪክ እንግዳ ነገር አይደለም። የኢኮኖሚ ብሶት ወደ ፖለቲካ ምሬት መለወጡና የፖለቲካ ጥያቄን መውለዱም ሁለንተናዊ ዕውነታ ነው፡፡ ይሄ የቆረቆረው ፓርቲ፣ ድርጅት፣ ቡድን ወዘተ… ጥያቄውን አንግቦ መነሳቱና መልስ መሻቱ አይቀሬ ነው፡፡
ከጭፍን ጥላቻ ውጪ ይሄን ጥያቄ ማንሳት ዲሞክራሲያዊ መብት ነው፡፡ መብቱን የሚያውቅ፣ የገባውና የሚገባውን የሚያውቅ ዜጋ ያላት አገር የታደለች ናት! ይህንን ዕድል ለመጠቀም የሚችል ንቃተ ህሊናው የበለፀገ ዜጋ ሀገሩን በቅጡ ይታደጋታል ተብሎ ይገመታል፡፡ እንዲህ ያለ ዜጋ የገዛ ዐይኑን ጉድፍ ሳያነፃ ከወንድሙ ዓይን ጉድፍ አወጣለሁ ብሎ አይፍረመረምም፡፡ ራሱን ከሙስና አያድንምያላፀዳ ዜጋ፤ አገሩን ከሙስና አያድንም፡
ራሱን ዲሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ያላደረገ ታጋይ፤ ዴሞክራሲያዊና ፍትሐዊ ሥርዓትን እገነባለሁ ቢል ሐሳዊ ታጋይ ከመሆን አያልፍም፡፡ ራሱ ህገ - ወጥ የሆነ ኃላፊ፤ የህግ የበላይነትን ያስከብራል ብሎ ተስፋ ማድረግ ከእባብ ዕንቁላል እርግብ መጠበቅ ነው፡፡
የምርጫ ወቅት ላይ ብቻ ስለ ኢ-ወገናዊነት የሚሰብክ ሰሞነኛ ወይም የወረት መንገደኛ ፍሬው በቀላሉ አይጐመራም፡፡ ጧት የተነሳ ብቻ ነው የማታ አዝመራው የሚሰምርለት፡፡
ፀሐፍት እንደሚሉት፤
“የምርጫ ወቅት ሙስና፡- Fake የይስሙላ ፓርቲዎችን ተወዳዳሪ አስመስሎ ከማቅረብ፣ እስከ ድምጽ ስርቆት ሊሄድ ይችላል፡፡
“በዚህ ምክንያት ነው በብዙ የአፍሪካ አገሮች ምርጫ ከመነሻው እስከ መድረሻው በውዝግብ የታጀበ የሚሆነው!”
ይሄን ልብ ብሎ ያልተገነዘበ ዜጋ ቡድን፣ ድርጅት ለራሱም አይሆን፤ ለአገሩም አይበጅ፡ ይልቁንም ነቅቶ መጠበቅ፤ ድምፁን እንዳያጣ፣ እንዳይጭበረበር፣ ያግዘዋል፡፡ ያ ካልሆነ ህዝባዊ ገዥነቱን የሚያረጋግጥበትን ዋና አቅሙን፣ ሠረገላ ቁልፉን አጣ ማለት ነው፡፡ የሚከበርና የሚፈራ ህዝብ የሚኖረው መብቱን የሚያውቅና የሚያስከብር ሆኖ ሲገኝ ነው፡፡ መብቱን ሲሸራርፉበት እምቢ! ማለት ሲችል ነው፡፡ በደልን፣ ግፍን እያየ ዝም ሳይል ሲቀር ነው፡፡ የፖለቲካ ሙስናን አልቀበልም ማለት ሲችል ነው፡፡ አስተዳደራዊ ብልሹነትን አሻፈረኝ ማለት ሲችል ነው! ቢሮክራሲያዊ እንቅፋቶችን አልቀበልም ማለት ሲችል ነወ፡፡ ባላስደሰተኝ ነገር አላጨበጭብም ማለት ሲችል ነው፡፡ እስከዛሬ ባየናቸው የተቃውሞ ጉዞዎች ውስጥ አማራጭ የትግል ስልቶችን ሳይቀይሱ በአንድና አንድ ግትር ስልት ብቻ እንጓዝ ብለው ብቸኛ መንገድ የመረጡ ሰዎች ቢያንስ መጨረሻቸው አያምርም፡፡ ሁለተኛም ሶስተኛም መጓዣ መንገዶችን ገና በጠዋት ማዘጋጀት ይገባቸዋል፡፡ ፈረንጆቹ “ፕላን ቢ”፣ “ፕላን ሲ” እንደሚሉት ነው፡፡ በአማርኛ “ሁለት ባላ ትከል፤ አንዱ ቢሰበር ባንዱ ተንጠልጠል” እንደማለት ነው!



“ሉዓላዊነት” በሚል ሰበብ፣ አገር ውስጥ “በዜጎች ላይ ያሻኝን ብፈፅም ማንም አያገባው” ብሎ መዝመት አስቸጋሪ ሆኗል
“አሜሪካ፣ አውሮፓ ገብቻለሁ” ብሎ፣ በዘፈቀደ “የኤምባሲ አጥሮችን በመጣስ” ላይ ያተኮረ የተቃውሞ ስትራቴጂ አያዋጣም
እንግዳ ቁጥር 1
   “በመንግስት የሰፈራ ዘመቻ ከእርሻ ማሳዬ ተፈናቅያለሁ” የሚሉ አንድ የጋምቤላ ገበሬ፤ ከአዲስ አበባው የአራት ኪሎ ቤተመንግስት እስከ ለንደኑ የዌስትሚንስተር ፓርላማ ድረስ፣ “ቁንጮ ፖለቲከኞችን የሚያጨቃጭቅ አሳሳቢ ጉዳይ ይሆናል” ብሎ ማን ጠበቀ? እንዴትስ የ10 ቢሊዮን ብር ጥያቄ ሊሆን ይችላል? ለመንግስት፣ ፈፅሞ ያልተጠበቀ ትልቅ ፈተና እንደሚሆንበት አያጠራጥርም፤ “ዱብዳ” ነው። ለአንዳንድ ተቃዋሚዎች ደግሞ፣ ያልታሰበ ሲሳይ ነው፤ “በተዓምር የተገኘ መና”። በእውን እንዲከሰት ይቅርና በህልማችን እንዲመጣ ያልጠበቅነው ድንገተኛ ነገር ነው በማለት፤ እንደ “ዱብዳ” ወይም እንደ “ተዓምር” ቢቆጥሩት አይገርምም። ግን ለምን ድንገተኛ ሆነባቸው? ዘመኑን እለት በእለት እየተከታተሉ፤ ዓለምን ከዳር እስከ ዳር እየቃኙ፣ የፖለቲካና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማናገናዝብ በቂ ጥረት አላደረጉም ማለት ነው።
እንግዳ ቁጥር 2
አሜሪካ ዋሺንግተን የሚገኘው የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ባነጣጠሩ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎችና በኤምባሲው የፀጥታ ሰራተኞች መካከል አምባጓሮ የተፈጠረ ጊዜ ታስታውሳላችሁ? የፀጥታ ሰራተኛው የማስጠንቀቂያ ጥይት እንደተኮሰ፤ ተቃዋሚዎች ግቢውን ጥሰው በመግባት ባንዲራ እንዳወረዱ... ወዘተ የወቅቱ ትልቅ መነጋገሪያ ነበር። በዚሁ አላቆመም። በዋሺንግተንም ሆነ በአውሮፓ መዲናዎች፣ ተመሳሳይ ጀብዱ ለመፈፀም እንዳቀዱ የገለፁ አንዳንድ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች፣ “ሁነኛና አስተማማኝ የተቃውሞ ስትራቴጂ” የተገለጠላቸው ያህል ፈንጥዘዋል። ለብዙዎችም አሳማኝ ሆኖ ታይቷቸው ነበር። መንግስት በበኩሉ ከፍተኛ ስጋት እንዳደረበት፣ በወቅቱ ካወጣቸው መግለጫዎች መታዘብ ይቻላል።
እንደተጠበቀውም፣ በአሜሪካ እንደታየውን ክስተት ወዲያውኑ ለመድገም የወሰኑ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች፣ በስዊድን የኢትዮጵያ ኤምባሲን ጥሰው ለመግባት እንደሞከሩ ሲዘገብ ሰማን። ከዚያስ? ከዚያማ ኤምባሲ ጥሶ የመግባት ወሬ፣ እንደ ሰደድ እሳት ሲግለበለብ እንዳልሰነበተ ድንገት እልም ብሎ ጠፋ። ይሄውና ድምፁን ሳንሰማ ወራት ተቆጠሩ። ምን ተፈጠረ? ያ አንዳንድ የዳያስፖራ ተቃዋሚዎች የተዘመሩለትና መንግስት የሰጋበት፣ “የተቃውሞ ስትራቴጂ” ድንገት ኩምሽሽ ብሎ መጥፋቱ፤ ለተቃዋሚዎቹ “ዱብዳ”፣ ለመንግስት ደግሞ “ተዓምር” ሆኖ ሊታያቸው ይችላል። የዘመኑንና የአለምን ሁኔታ ባያገናዝቡ እንጂ፤ ነገሩ ድንገተኛ ባልሆነባቸው ነበር። እንዴት በሉ።
የኤምባሲው አምባጓሮ በተፈጠረበት ሰሞን፣ እዚያው ዋሺንግተን ውስጥ የአገሪቱን ፖለቲከኞች ዘንድ አሳሳቢ የነበሩ ሁለት ጉዳዮችን ብቻ ማስታወስ በቂ ይመስለኛል። አንደኛው፣ የፕሬዚዳንቱ ቤተመንግስትን ለአደጋ ያጋለጠ ድርጊት ነው - የኋይት ሃውስን አጥር ጥሶ የገባ ተጠርጣሪ፣ የፀጥታ ሰራተኞች፣ አነፍናፊ ውሾች፣ የጥበቃ መቆጣጠሪያ መሳሪያዎች ሳያግዱት፣ የፕሬዚዳንቱ ቢሮና መኖሪያ ቤት ወደሚገኝበት ህንፃ ገብቶ ከኮሪደር ኮሪደር ሲዟዟር እንደተያዘ በአገሪቱ የሚዲያ ተቋማት ሲዘገብ ምን የተፈጠረ ይመስላችኋል? የፖለቲካ ማዕበል።
ዋሺንግተን ቀውጢ ሆነች። ቀደም ሲል ሳይታወቁ የቆዩ ሌሎች የፀጥታ ጥበቃ ድክመቶች ከተደበቁበት እየፈለፈሉ የሚያወጡ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች፣ ነገሩን የዋዛ አላዩትም። የአገሪቱ ኮንግረስ (ፓርላማ) በበኩሉ፣ ባለስልጣናትንና ባለሙያዎችን እያስጠራ በጥያቄ ለማፋጠጥ ጊዜ አልፈጀበትም። የቤተመንግስት የፀጥታ ኤጀንሲ ዳሬክተር፣ በጥቂት ቀናት ውስጥ ከስልጣናቸው ተሰናበቱ። አሸባሪነት በገነነበት ዘመን፣ አጥር ተጥሶ የፀጥታ ሲፈጠር፣ እንደዋዛ አይታይም። በዚያ ላይ፣ በዋሺንግተን የኤምባሲዎችን ፀጥታ የመጠበቅ ሃላፊነት የማን ቢሆን ጥሩ ነው? የቤተመንግስት ፀጥታ ኤጀንሲ ነው፣ የኢንባሲዎችን ፀጥታ የሚቆጣጠረው። የኋይትሃውስ አጥር ተጥሶ፣ ከፍተኛ የፖለቲካ ቅሌት የወረደበት ይሄው ኤጀንሲ፤ እንደገና በየኤምባሲው ሌላ የፀጥታ አደጋ እንዲከሰት ፈቃደኛ የሚሆን ይመስላችኋል? የማይመስል ነገር!
ምን ይሄ ብቻ! ከኤምባሲ ጋር በተያያዘ፣ የአሜሪካ መንግስት ሌላ ተጨማሪ ራስ ምታት አለበት። ከ30 ዓመታት በፊት በኢራን እና በሊባኖስ ምድር የአሜሪካ ኤምባሲዎች ላይ የደረሰውን ጥቃት ስለማይረሱት ብቻ አይደለም። ከዚያ በኋላም ኬንያና ታንዛኒያ ውስጥ ትልልቅ ጥፋቶችን አስተናግደዋል። ይሄ አልበቃ ብሎ፤ በሊቢያ የአሜሪካ አምባሳደርን ጨምሮ የበርካታ አሜሪካዊያንን ሕይወት የቀጠፈው ጥቃት፣ እንደ እሳት እያንገበግባቸው እንደሆነ ለመረዳት ከባድ አይደለም። በኮንግረስና በፕሬዚዳንታዊ የምርጫ ዘመቻ ሳይቀር ላይ እንደ ትኩስ ጉዳይ ፖለቲከኞችን ዛሬ ድረስ ሲያጨቃጭቅ መስማት ትችላላችሁ!
“Benghazi Attack” ብለው የሰየሙትን ጥቃት፣ ኮንግረስ ውስጥ አራት ቋሚ ኮሚቴዎች ባለስልጣናትን፣ ምስክሮችንና ባለሙያዎችን እየጠሩ ለበርካታ ወራት በየፊናቸው ምርመራ ማካሄዳቸውንም አትርሱ። ይህም አልበቃም፤ ጉዳዩን የሚያጣራ ራሱን የቻለ ኮሜቴ እንዲቋቋም በኮንግረስ ስለተወሰነ፤ ይሄውና እስከዛሬ ምርመራው አለመቋረጡን ስትመለከቱ፤ ምን ያህል አክብደው እንደሚያዩት መገንዘብ ትችላላችሁ። ደግሞስ፣ በሊቢያ፣ በግብፅ፣ በቱኒዚያ እና በበርካታ አገራት ውስጥ፣ ለአሜሪካ መንግስት የኤምባሲዎች የፀጥታ ጥበቃ፣ እረፍት የማይሰጥ ስጋት እንደሆነ አናውቅም እንዴ? ለአውሮፓ መንግስታትም እንዲሁ ያሳስባቸዋል። ምናለፋችሁ? የአሜሪካና የአውሮፓ መንግስታት፣ ኤምባሲዎቻቸውን የፀጥታ ጥበቃ የሚነካ ነገር በቸልታ ወይም በዋዛ እንዲታለፍ አይፈልጉም። በዋና ከተሞቻቸው ውስጥ የሚገኙ የሌሎች አገራት ኤምባሲዎችም ላይ፣ ምንም አይነት ስጋት እንዲፈጠር አይፈቅዱም።
ምን ለማለት ፈልጌ ነው? ይህንን የዘመናችንና የአለምን ሁኔታ የሚያገናዝብ ሰው፤ “ኤምባሲዎች ላይ ያነጣጠረ የተቃውሞ ስትራቴጂ” ከአንድ ሰሞን ሆይሆይታ በኋላ፣ ድምፁ እልም ብሎ ቢጠፋ፤ “ዱብዳ” ወይም “ተዓምር” ሆኖ አይታየውም ለማለት ነው።                                  
ወደ ደቡብ አፍሪካ ቪዛ አስመታለሁ በማለት ሰዎችን አጭበርብረዋል ተብለው የተከሰሱ፣ የባሌስትራ ቁርጥራጭ ወርቅ ነው ብለው ብሔራዊ ባንክን አታልለዋል ተብለው የተከሰሱ፣ ሚስታቸውን ደብድበው ገድለዋል ተብለው የሚፈለጉ ሦስት ተጠርጣሪዎች፣ ከደቡብ ሱዳን፣ ከአረብ አገር እና ከጀርመን ተይዘው እንደመጡ ታውቃላችሁ።
ቀደም ብዬ ያነሳሁት የእርዳታ ጉዳይም፣ ከበድ ያለ ጉዳይ ነው። ብዙዎች ከባድነቱን ለማመን ይቸገሩ ይሆናል። ነገር ግን፣ የጋምቤላው ገበሬ፣ “ከእርሻ ማሳዬ በመንግስት የሰፈራ ዘመቻ ተፈናቅያለሁ፤ የእንግሊዝ መንግስት ለሰፈራ ዘመቻው እርዳታ በመስጠት ስለተሳተፈ ይጠየቅልን” በማለት በለንደን ያቀረቡት ክስ የዋዛ አይደለም። በስደት ኬንያ የሚገኙት እኚሁ ገበሬ በጠበቃቸው ባቀረቡት ክስ፣ የካሳ ክፍያ ቢጠይቁም፣ ጉዳዩ በዚህ ብቻ አላበቃም። እንግሊዝ ለኢትዮጵያ መንግስት የሚሰጠው እርዳታ፣ ከላይ እስከ ታች ተመርምሮ መጣራት እንደሚኖርበት ፍ/ቤቱ ተናግሯል። እርዳታው ቀላል እንዳይመስላችሁ። ከአሜሪካ በመቀጠል፣ ለኢትዮጵያ ዋነኛዋ እርዳታ ሰጪ የሆነችው እንግሊዝ፣ በየአመቱ ወደ 10 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ እርዳታ ትለግሳለች። በአንድ ገበሬ ክስ የተነሳ፣ የሃያሏ አገር መንግስት የውጭ ጉዳይ ፖሊሲውን እንዲመረምር የፍርድ ቤት ጫና ሲመጣበት አስቡ። ከዚሁ ክስ ጋር ተያይዞ፣ የኢትዮጵያ መንግስት በየአመቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬና እርዳታ የሚኛገኝበት ትልቅ ምንጭ ስጋት ላይ ሲወድቅ ይታያችሁ።
አስቸጋሪ ነው። መንግስት እንደዘወትሩ፤ “ይሄ የኒዮሊበራሎች ዘመቻ ነው” በማለት ለመከራከር ቢያስብ እንኳ፣ አመቺ አይደለም። ሶሻሊስቶች፣ አሜሪካንና እንግሊዝን ለማንቋሸሽ በሚዘወትሩት የፕሮፓጋንዳ ስልት፣ “የኒዮሊበራሎች ሴራ ነው” የሚል አባባል እያስተጋባ፣ አንድ ተራ ገበሬ ያቀረቡትን ክስ ለመከላከል ቢሞክር ትዝብት ላይ ከመውደቅ ያለፈ ውጤት አያገኝም። ይሄኛው የፕሮፓጋንዳ ስልት አላዋጣ ሲል፤ በአገራችን ባህል እንደተለመደው፣ “ይሄ የአንድ ግለሰብ ጉዳይ ነው” በማለት መንግስት ነገሩን ለማጣጣልና ለማስተባበል ቢሞክርስ? ይሄም አያዋጣውም። እንዲያውም በተቃራኒው፤ “እንዲህ አይነት ማስተባበያ፣ የመንግስትን ጥፋተኝነት ከማረጋገጥ አልፎ፣ ሰዎች ላይ ለሚደርስ ጉዳት ደንታ ቢስ መሆኑንም ያሳያል” የሚል ምላሽ ነው የሚያጋጥመው። የእያንዳንዱ ሰው መብት መከበር አለበት የሚለው መሰረታዊ የነፃነት አስተሳሰብ፣ በአሜሪካና በአውሮፓ አሁንም ድረስ ጠንካራ ነዋ።
በተቃራኒው፣ የእንግሊዝ መንግስትን ምላሽ ተመልከቱ - “ለሰፈራ ዘመቻ እርዳታ አንሰጥም። ለኢትዮጵያ መንግስት የምንሰጠውን የእርዳታ ትብብር፣ በየጊዜው እንመረምረዋለን። ወደፊትም እንመረምረዋለን። ውጤታማ ያልሆኑትን እየሰረዝን፣ ውጤታማ የትብብር መስኮችን በማጠናከር ነው የምንሰራው” ብሏል የእንግሊዝ መንግስት። እንግዲህ፤ በርካታ ነገሮች እንደድሮ ስላልሆኑ፤ የአገራችን መንግስት የዘመናችንንና የዓለምን ሁኔታ በማገናዘብ፣ የእንግሊዝን አይነት ምክንያታዊ አካሄድ ከወዲሁ ቢለማመድ አይሻለውም ትላላችሁ?
በሚዲያ ነፃነት ዙሪያም፣ ከዘመኑ ጋር ለመራመድ፣ ገና ሊለማመዳቸው የሚገቡ ቁምነገሮች አሉ። የቴሌቪዥን ጣቢያ ስርጭትን ለብቻው በሞኖፖል የያዘው የአገራችን መንግስት፤ በርካታ ሬድዮ ጣቢያዎችን እየተቆጣጠረና አዳዲስ ጣብያዎችን እየገነባ ቢሆንም፣ ለሁለት ለሦስት የግል የኤፍኤም ሬድዮ ጣቢያዎች ፈቃድ መስጠቱ በጎ ጅምር ነበር። በእርግጥ፣ ከ15 አመት በፊት የወጣው የብሮድካስት አዋጅ ላይ፣ ለሬዲዮ ብቻ ሳይሆን ለቴሌቪዢንም ጭምር፣ የግል የስርጭት ጣቢያ ለማቋቋም የሚያስችል ፈቃድ እንደሚሰጥ ይዸነግጋል። ግን ተግባራዊ አልሆነም። ወደፊትም ተግባራዊ አይሆንም ተብሏል። የማሰራጫ ጣቢያ ማቋቋም የሚችለው መንግስት ብቻ እንደሚሆንና፣ ለግል ድርጅቶች ቻናል እንደሚያከራይ የሚገልፅ አዲስ ረቂቅ ህግ ተዘጋጅቷል። እስቲ አስቡት። በዛሬው የቴክኖሎጂ ዘመን፣ እንደ ድሮው መንግስት ሁሉንም ነገር በሞኖፖል ተቆጣጥሮ ሊቀጥል ይፈልጋል? ለነገሩ፣ ከሬድዮና ከቴሌቪዢን በተጨማሪ፣ የጋዜጣ ስርጭትንም ካልተቆጣጠርኩ ብሎ አዲስ ህግ ወይም መመሪያ እንደሚያዘጋጅ ሲገልፅ ከርሞ የለ!
እንዴት ነው ነገሩ? ብዙ ነገሮች እንደድሯቸው እንዳልሆኑና ብዙ ነገሮች እንደተቀየሩ አልገባውም ማለት ነው? በመላ አገሪቱ በየቀኑ የሚሰራጨው የግል ጋዜጣና መፅሔት ስንት ቢሆን ነው? ምናልባት 10ሺ? እና የእነዚህን ጋዜጦች ስርጭት ለመቆጣጠር ይፈልጋል።
እስቲ ሁላችሁም፣ የመንግስት ሃላፊዎችም ጭምር፣ የየራሳችሁን ግቢ እና ጎረቤቶቻችሁን ይመልከቱ። ምን ይታያችኋል? የሳተላይት ቴሌቪዥን ዲሽ! ዲሽ የተከሉ ሳይሆን ያልተከሉ መቁጠር ይሻላል። ከግቢ ወጣ ብለው የየሰፈራቸውን ግራና ቀኝ ሲቃኙስ፣ በየጣሪያው ወደ ሰማይ ያንጋጠጡ ዲሾች አካባቢውን እንዳጥለቀለቁት አያዩም? ለዚያውም በትላልቅ ብቻ ሳይሆን በትናንሽ ከተሞችም ጭምር ነው። ይህ ብቻ አይደለም።
የቅርብ ጊዜ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት ወደ ሁለት ሚሊዮን የሚጠጉ ኢትዮጵያውያን ኢንተርኔትን ይጠቀማሉ። አንዳንዱ ሰሞነኛ የሆሊውድ ፊልሞችንና እለት በእለት በአሜሪካ የሚሰራጩ ተከታታይ የቴሌቪዥን ድራማዎችን በትኩሱ ከኢንተርኔት እየሸመጠጡ ይኮመኩማሉ። አዳዲስ ሙዚቃዎችን ያፍሳሉ። አንዳንዱ ደግሞ፣ ዘመን የማይሽራቸው ትልልቅ መፃህፍትን በገፍ ያካብታል። ወይም በየእለቱና በየሳምንቱ እየታተሙ በአለም ገበያ ቁንጮውን ቦታ የሚይዙ መፃህፍትን ከኢንተርኔት እየበረበረ ያከማቻል። አንዳንዶቹ ብልጦች፣ ለሙያቸው የሚጠቅሙ መጻሕፍትን፣ ጥናቶችንና የስልጠና ቪዲዮዎችን ይሰበስባሉ። በእርግጥ፣ እንዲህ አይነት የኢንተርኔት ተጠቃሚ ኢትዮጵያዊያን ሲደማመሩ፣ በቁጥር ጥቂት ሊሆኑ ይችላሉ። አብዛኛው ተጠቃሚስ?መጀመሪያ ላይ በዲቪ ሎተሪ አነሳሽነት ነው ብዙ ሰው የኢሜይ ደንበኛ የሆነው። ቀጥሎም በስካይፒ እና በዩቱብ። ከዚማ ፌስቡክ እና ረቀቅ ያሉ ሞባይሎች መጡና አዳሜ ወደ ኢንተርኔት ሰተት ብሎ እንዲገባ ሰበብ ሆኑለት። ዛሬ፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን፣ ኢንተርኔት ከዘወትር ሕይወታቸው ጋር እያዋሃዱት ነው። በየፊናቸው፣ ከመቶ ሺ እስከ ዘጠኝ መቶ ሺ የሚደርሱ ተከታታይ ደንበኞችን ለማፍራት የቻሉ በርካታ ዌብሳይቶችና የፌስቡክ ገፆች እንደተፈጠሩ ብቻ ማየት በቂ ይመስለኛል።
እንዲያም ሆኖ፣  መንግስት ዛሬም በጣት የሚቆጠሩት ጋዜጦችና መፅሔቶችን በአይነቁራኛ ከማየትና ሙሉ ለሙሉ ለመቆጣጣር ከመጣጣር አልተቆጠበም። ዘመኑ የኢንተርኔት እንደሆነ ጠፍቶት ነው? ወይስ፣ ኢንተርኔትን መቆጣጠር፣ ጋዜጣና መፅሔትን እንደመቆጣጠር ቀላል ስላልሆነ? በእርግጥ አንዳንድ ዌብሳይቶች ኢትዮጵያ ውስጥ በቀላሉ እንዳይታዩ መሰናክልና አጥር መዘርጋት አይከብድም። ነገር ግን፣ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የፌስቡክ ደንበኞች ዘንድ የሚደርሱ መረጃዎችን፣ ፅሁፎችን፣ ምስሎችንና ቪዲዮዎችን ለመቆጣጠር መሞከር ግን አስቸጋሪ ነው። ብዙ ገንዘብና ብዙ ጊዜ ማባከን ነው ትርፉ። እንደ ቻይና እንኳ መሆን አይቻልም። እንደ ሰሜን ኮሪያ አገሬውን ከአለም ነጥሎ በመቆለፍ አፍኖ መያዝም አያዛልቅም። ለጊዜው የአገራችን መንግስት በኢንተርኔት አለም ውስጥ ብዙም የአፈና አማራጮች የሉትም። ያው፤ የልማድ ነገር ሆኖ፣ የፈረደባቸው የግል ጋዜጦችና መፅሔቶችን ማስጨነቁን ግን አያቋርጥም - ትርጉም የለሽ ቢሆንም። ውጤት ለሌለው ነገር ጊዜውንና ገንዘቡን ያባክናል። ከዚህ ይልቅ፤ ለስልጡን የሚዲያ ነፃነት ቢጣጣርና ቢለማመድ አይሻለውም?
ነገሮች እንደድሮ አይደሉም።   

30 ኢትዮጵያውያን ከየመን ጅቡቲ ገብተዋል
    በየመን የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ የተፈፀመው ጥቃት  በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነና  ከየመን ወደ አገራቸው ለመመለስ በኤምባሲው በኩል ከተመዘገቡ ኢትዮጵያውያን ውስጥ 30 ዜጎች  ጅቡቲ መድረሳቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አቶ ተወልደ ሙሉጌታ ለአዲስ አድማስ ገለፁ፡፡ በየመን መዲና ሰንአ የሚገኘው  የኢትዮጵያ ኤምባሲ ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተከትሎ ጥቃቱ በማን እንደተፈፀመ እየተጣራ እንደሆነ የገለፁት አቶ ተወልደ፤ በተፈፀመው ጥቃት በኤምባሲው ሰራተኞች ላይ ምንም የደረሰ  ጉዳት የለም ብለዋል፡፡ የኢትዮጵያ ኤምባሲ በየመን የሚገኙ ዜጎች ተመዝግበው ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ባደረገው ጥሪ መሰረት፤ ከተመዘገቡት ውስጥ 12 ሴቶች፣ 11 ህፃናት እና 7 ወንዶች የተካተቱበት አንድ ቡድን ጅቡቲ መድረሱን ቃል አቀባዩ ጠቁመዋል፡፡
የመን ውስጥ በስደተኞች መጠለያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን በሳኡዲ የአየር ጥቃት ተደብድበው ህይወታቸው አልፏል በሚል የተሰራጩ ዘገባዎችን በተመለከተ አቶ ሙሉጌታ በሰጡት ምላሽ፤ “በኛ በኩል ባደረግነው ማጣራት በዚህ ሁኔታ የሞተ ሰው የለም” ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል፤ የየመኑ የሁቲ አማፂ ቡድን ከኢራን የሚያገኘውን የወታደራዊ ቁሳቁስ ድጋፍ በቀይ ባህር በኩል በማሻገርና ለአማፂያኑ የወታደራዊ ስልጠና ቦታዎችን በአገሯ ላይ በማመቻቸት በተደጋጋሚ ስሟ የሚነሳው ኤርትራ፤ ሰሞኑን ተመሳሳይ ውንጀላ በሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን ተደርጎብኛል በሚል በሰጠችው ምላሽ፤ ውንጀላው መሰረተቢስ እንደሆነ ገልፆ የወሬው ምንጭም የአፍሪካ ቀንድ አገራት ናቸው ስትል አጣጥላለች፡፡
አብዛኛውን የየመን ክፍሎች በመቆጣጠር የአገሪቱን መሪ ከስልጣን ያስወገደው የሁቲ አማፂያን ቡድን፤ ከኢራን ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚደረግለት የሚነገር ሲሆን የሚያገኘውንም ድጋፍ በማስተላለፍና ለወታደራዊ ስልጠና ቦታ በመስጠት ኤርትራ በተደጋጋሚ ስሟ እንደሚነሳ አገር እንደሆነች ይታወቃል፡፡ የመካከለኛው ምስራቅ የሚዲያ የምርምር ተቋም ከጥቂት አመታት በፊት “ኢራን በቀይ ባህር የእንቅስቃሴ አድማሷን እያሰፋች ነው” በሚል ርዕስ  ባወጣው መረጃ፤  ኢራን ለሁቲዎች የምታደርገው የወታደራዊ ቁሳቁሶች ድጋፍ በኤርትራ በኩል እንደሚያልፍ ጠቁሞ ኢራን ሁቲዎችን የምታሰለጥንበት ካምፕ ኤርትራ ውስጥ ከየጊንዳዕ ከተማ በስተምስራቅ ደንጎሎ የሚባል ቦታ እንደሚገኝ አስታውቆ ነበር፡፡ ሰሞኑን የሳኡዲ የመገናኛ ብዙሀን፤ ሁቲዎች ከኢራን ለሚያገኙት ድጋፍ ኤርትራ ትብብር ታደርጋለች ሲሉ ዘግበዋል፡፡
“ዘገባው ከሙያዊ ስነምግባር ያፈነገጠ ነው” በማለት ባለአስር ነጥብ መግለጫ ያወጣው የኤርትራ መንግስት፤ ዜናውን መሰረተ ቢስ ሲል ያጣጣለ ሲሆን የመረጃው ምንጮችም የአፍሪካ ቀንድ አገራት እንደሆኑ ገልጿል፡፡ “ሻባይት” የተባለው የኤርትራ መንግስት ድረገፅ በበኩሉ፤ የዚህ መረጃ ምንጮች አንዳንድ የስለላ ተቋማትና የኢትዮጵያው ህወሓት ነው ብሏል፡፡
የኤርትራ መንግስት ባወጣው ባለአስር ነጥብ አቋም ውስጥ፤ የየመን ጉዳይ የራሷ የውስጥ ጉዳይ ስለሆነ የትኛውንም የውጭ ሀይል በመደገፍ ኤርትራ እንደማትሰለፍ አስታውቋል፡፡
የሳኡዲ መንግሥት በበኩሉ፤ የሁቲ አማፅያን እንቅስቃሴ ለአገሬ ስጋት ናቸው በሚል  በየመን ወታደራዊ ድብደባ እየፈፀመ እንደምገኝ የሚታወቅ ሲሆን የኢትዮጵያ መንግስትም የሳኡዲን አቋም እንደሚደግፍ አስታውቋል፡፡