Administrator

Administrator

ቻይና፣ ህንድ፣ ኢንዶኔዢያ ለእግር ኳስ ባይተዋር ናቸው
በአሜሪካ ክቧ ኳስ ከሞላላ ኳስ ጋር መፎካከር አልቻለችም

የህንድ ቡድን በአለም ዋንጫ የመካፈል ጥሩ እድል ያገኘው ከ64 አመታት በፊት ነው። በብራዚል በተዘጋጀው የያኔው የአለም ዋንጫ ላይ ያለ ማጣሪያ እንዲካፈል የተጋበዘው የህንድ ቡድን፣ እድሉን አልተጠቀመበትም - በሁለት ምክንያቶች። አንደኛው ምክንያት፣ ድህነት ነው። የመጓጓዣና የመሰንበቻው ወጪ ከበዳቸው። ሁለተኛው ምክንያት ደግሞ ኋላቀርነት ነው። የህንድ ቡድን የፊፋን ህግ ለማክበር አልፈለጉም - ያለ ጫማ ነው የምንጫወተው በማለት። ጫማ ካደረግን፣ ጥቃቅን ነፍሳትን ረጋግጠን ልንገድል እንችላለን ብለው የሰጉት የህንድ ተጫዋቾች፤ ሃጥያት ውስጥ መግባት አንፈልግም ብለው ከአለም ዋንጫ ቀርተዋል። እንዲህ፣ ተረት የሚመስል ኋላቀር ባህል ምን ይባላል?
ቻይናን ጉድ ያደረጋት ግን፣ ጥንታዊ ባህል አይደለም። ለነገሩማ፣ እግር ኳስ የሚመስል ጨዋታ የተጀመረው በጥንታዊ ቻይና እንደሆነ ይነገር የለ! ቻይናዊያን ከእግር ኳስ ጋር የተራራቁት በኮሙኒዝም ምክንያት ነው። የድሮዎች የአገራችን የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች፣ እነ ደርግና እነ ኢህአፓ ጭምር በአድናቆት የዘመሩላቸው የቻይና መሪ ማኦ ዜዱንግ፣ አገሬውን ሁሉ ሌት ተቀን ፋታ በማይሰጥ ስብሰባ፣ ግምገማና የስራ ዘመቻ ወጥረው ነበር የያዙት። ኳስ ለመጫወት ጊዜ አልነበረም።
ስብሰባውና የስራ ዘመቻውም ጠብ የሚል ነገር አልተገኘበትም - 20 ሚሊዮን ቻይናዊያን በረሃብ ያለቁት በማኦ ዘመን ነው። ከማኦ በኋላ፣ በዴንግ ዚያዎፒንግ ዘመን በመንግስት ተተብትቦ የቆየው ኢኮኖሚ ለግል ኢንቨስትመንት ሲከፈት፣ ከዚያም ሲስፋፋ አገሪቱ በፍጥነት ወደ እድገት መጓዝ ጀምራለች። በመንግስት የተተበተበው ፖለቲካ ግን ብዙም አልተቀየረም። ያለ መንግስት ፈቃድ ከ10 በላይ ሰዎች በአንድ ቦታ ቢሰባሰቡ ይታሰራሉ። ክልክል ነው።
የሰፈር ወጣቶች እግር ኳስ ለመጫወት በየቀኑ ቀበሌና ወረዳ ሊቀመንበር ጋ እየሄዱ የፈቃድ ማመልከቻ ሲያስገቡ ይታያችሁ። “ስፖርት ለአገር ልማትና ለጤናማ ህብረተሰብ ወሳኝ አስተዋፅኦ እንደሚያበረክት ይታወቃል። እኛ ስማችን ከዚህ በታች የተዘረዘረ የሰፈር ወጣቶች፣ ለአገርና ለህብረተሰብ ልማት በማሰብ ዛሬ ከቀኑ ዘጠኝ ሰዓት እግር ኳስ ለመጫወት አስበናል። ፅ/ቤቱ ፈቃድ እንዲሰጠን እየጠየቅን፣ ለሚደረግልን ትብብር አብዮታዊ ምስጋና እናቀርባለን...”  
“አብዮት ወይም ሞት!” በሚል መፈክር የታጀበ ማመልከቻ እየፃፉ እግር ኳስ ለመጫወት የሚጓጓ ብዙ ወጣት አይኖርም። በኮሙኒዝም የተሽመደመደው  የቻይና እግር ኳስ፤ እስከዛሬ ገና ቆሞ የመራመድ ብርታት አላገኘም። ደግነቱ፣ እንደ ታሊባን ወይም እንደ አልሸባብ የእግር ኳስ ጨዋታ በቲቪ መመልከት አልተከለከለም። ብዙ ቻይናዊያን እግር ኳስ ባይጫወቱም፣ መመልከት ግን ይወዳሉ። 300 ሚሊዮን ቻይናዊያን በ2010 የአለም ዋንጫ ውድድሮችን በቲቪ ተከታትለዋል።
ህንድና ቻይና ከእግር ኳስ አለም የራቁት በጥንታዊ ኋላቀር ባህልና አኮራምቶ በሚተበትብ የኮሙኒዝም አፈና ሳቢያ ከሆነ፤ አሜሪካ ከእግር ኳስ ጋር ያልተወዳጀችው በምን ምክንያት ይሆን? በሌሎች ተወዳጅ ስፖርቶች ምክንያት ነው። በአሜሪካ ስቴዲየም የሚገባ ብዙ ተመልካች የሚሰበሰበው በሞላላ ኳስ የሚካሄደውን ጨዋታ ለማየት ነው። በአማካይ በእያንዳንዱ ጨዋታ ከ68ሺ በላይ ተመልካች ስቴዲየም ይገባል - ያንን ነው ፉትቦል የሚሉት። እግር ኳስን፣ ሶከር እያሉ ነው የሚጠሩት። ከዚያ በኋላ ደግሞ ቤዝ ቦል አለ። የቤዝ ቦል ጨዋታ ለመመልከት በአማካይ ከ30ሺ በላይ ሰው ስቴዲየም ይገባል። እግር ኳስ ለማየት የሚሰበሰበው ተመልካች፣ ከቅርጫት ኳስ ተመልካቾች ቁጥር ብዙም አይራራቅም - በአማካይ 18ሺ ገደማ ሰው።
በአጭሩ፤ አውሮፓን፣ ደቡብ አሜሪካንና አፍሪካን ያጥለቀለቀው የእግር ኳስ ዝና፣ በአሜሪካ ገና አልተስፋፋም። እንዲያም ሆኖ፣ ከሌሎቹ ትልልቅ አገራት (ከህንድ እና ከቻይና )ጋር ሲነፃፀር፣ የአሜሪካ ሳይሻል አይቀርም። የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን በተደጋጋሚ በአለም ዋንጫ ላይ ሲሳተፍ እያየን አይደል?
ሶስቱ ትልልቅ አገራት፤ (ህንድ፣ ቻይና እና ኢንዶኔዢያ) ግን፤ ለአለም ዋንጫ ባይተዋር ናቸው። በእርግጥ፤ ቻይና አንዴ በአለም ዋንጫ ተሳትፋለች። ግን፤ እንደተሳተፈች አይቆጠርም። የቻይና ቡድን አንድም ጊዜ አላሸነፈም። ጨርሶ፣ አንድም ጎል ሳያስገባ ነው በመጀመሪያው ዙር ከውድድሩ የተሰናበተው። እግር ኳስ ለማየት ወደ ስቴዲየም ጎራ ማለት፤ በህንድ፣ በኢንዶኔዢያና በቻይና ገና አልተለመደም።
በዚህ በዚህ ጀርመንን የሚስተካከል የለም። በእያንዳንዱ የቡንደስ ሊጋ ጨዋታ በአማካይ 42ሺ ተመልካች ስቴዲየም ይገባል። በእንግሊዙ ፕሪሚየር ሊግ ደግሞ፣ 36ሺ ሰዎች ስቴዲየም ይታደማሉ። በቅርቡ የተጠናቀቀውን የፕሪሚየር ሊግ ለማየት በድምሩ 14 ሚ. ገደማ ቲኬቶች ተሽጠዋል።

   በእያንዳንዱ ጨዋታ ላይ ለቁማርና ለውርርድ የሚከፈለው ገንዘብ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መጥቷል። በአለም ዋንጫ ውድድሮች ላይ በየጨዋታው በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ለቁማር እየዋለ መሆኑን የዘገበው ዘ ኢኮኖሚስት፣ በአጠቃላይ ከ30 ቢ. ዶላር በላይ ገንዘብ የቁማር መጫወቻ እንደሚሆን አመልክቷል።
የለንደን ህገወጥ ሬዲዮ ጣቢያዎች እያበቃላቸው ይሆን?
በሃያኛው ክፍለዘመን’ኮ ያልተበላሸ አገር የለም ማለት ይቻላል። “የግለሰብ መብት” እና “የነፃ ገበያ ስርዓት” የተወለዱባት እንግሊዝ ሳትቀር፣ ቀስ በቀስ ከስልጣኔ ማማ ቁልቁል መንሸራተት አልቀረላትም ነበር። መንግስት፣ የግል ኩባንያዎችን እንዲወርስ ባይደረግም፤ ካሳ እየከፈለ የተወሰኑ ድርጅቶችን ወደ መንግስት ይዞታነት ሲያዛውር አልነበር? በዚያ ላይ የግል ሬድዮና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በብዛት እንዳይቋቋሙ በህግ ታግደው ነበር። በዚህ ምክንያት ነው፤ በርካታ የሬዲዮ ጣቢያዎች በድብቅ መስራት የጀመሩት።
የመንግስት ሪፖርት እንደሚገልፀው፣ በለንደን ውስጥ 75 ያህል ድብቅ የሬዲዮ ጣቢያዎች አሉ። ከእነዚህ “ህገወጦች” መካከል አስሩ ጣቢያዎች፣ የ24 ሰዓት ስርጭት ያስተላልፋሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ፣ ለበርካታ አመታት ያለማቋረጥ የሰሩ ናቸው። ዛሬ ዛሬ ግን፣ ቀስ በቀስ እየተዳከሙ ህልውናቸው እያበቃለት ይመስላል። ጣቢያዎቹ የተዳከሙት በመንግስት ቁጥጥርና ክትትል ሳቢያ አይደለም።
በእርግጥ “ህገወጥ” ስለሆኑ፤ አድራሻቸውን አጥፍተው በድብቅ ካልሰሩ በቀር መዘጋታቸውና መቀጣታቸው አይቀርም። የማሰራጫ አንቴናቸውን የሚተክሉት በድብቅ ነው። ከስቱዲዮ ወደ አንቴና የሬዲዮ ስርጭት የሚያስተላልፉትም በጥንቃቄ ነው - ለቁጥጥር በማያመች ጨረር አማካኝነት። ነገር ግን፣ የመንግስት ባለስልጣናትም፣ “ህገወጥ” የሬዲዮ ጣቢያዎችን አሳድደው ለመያዝ የአሰሳ ዘመቻ አያካሂዱም። ክትትልና ምርመራ ለማካሄድ ጊዜና ገንዘብ አያባክኑም። ለድብቅ ጣቢያዎች፣ “ህጋዊ እውቅና መንፈግ በቂ ነው” ብለው ያስባሉ - ባለስልጣናት። በአጭሩ፣ ጣቢያዎቹን ያዳከማቸው ወይም ስጋት ላይ የጣላቸው መንግስት አይደለም። ቴክኖሎጂ እንጂ።
ዘመኑ የኢንተርኔት ዘመን ነው። የፅሁፍ፣ የምስል፣ የድምፅና የቪዲዮ መልእክቶችን በቀላሉ በኢንተርኔት ማሰራጨትና መለዋወጥ ይቻላል። እገዳና ክልከላ ስለሌለ፣ ድብቅነትና ህገወጥነትም አያስፈልገውም። እናም አብዛኞቹ ድብቅ የሬዲዮ ጣቢያዎች፣ ስርጭታቸውን ወደ ኢንተርኔት ማዞር ጀምረዋል።  

ዋና ስራ - የኢንተርኔት አገልግሎት፣ ሶፍትዌር እና የቴሌኮም ምርት
በአመት የ60 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያላቸው አገልግሎቶችንና ምርቶችን ይሸጣል
ባለፈው አመት 13 ቢ. ዶላር አትርፏል
የኩባንያው ሃብት 120 ቢ. ዶላር ገደማ ነው
50ሺ ሰራተኞች አሉት
በኢንተርኔቱ አለም ቀዳሚ ስፍራ ይዟል
አስር የሚሆኑ ቶዮታ፣ አውዲ እና ሌክሰስ መኪኖች ያለ አሽከርካሪ እንዲቀሳቀሱ  ለማድረግ በተራቀቁ ቴክኖሎጂዎች ሙከራ ሲያካሂድ የከረመው ጉጉል፣ ከመቶ እስከ ሁለት መቶ የሚደርሱ የራሱ አዳዲስ መኪኖችን በመፈብረክ ለገበያ እንደሚያቀርብ ገልጿል። ጉጉል ሙከራውን ያካሄደው፣ ሁለት የአሜሪካ ግዛቶች (ኔቫዳ እና ፍሎሪዳ) በየጎዳናው አሽከርካሪ አልባ መኪኖች እንዲንቀሳቀሱ የሚፈቅድ ህግ ካወጡ በኋላ ነው።
ለሙከራ ያገለገሉት አስር መኪኖች ያለ አሽከርካሪ እንዲንቀሳቀሱ፣ ለእያንዳንዳቸው የ70ሺ ዶላር የራዳር ሲስተምን ጨምር 150ሺ ዶላር የሚያወጡ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ተገጥሞላቸዋል። በአመት ውስጥ ለገበያ ይቀርባሉ የተባሉት የጉጉል መኪኖች፣ ቢያንስ ቢያንስ ሰፊ ገበያ እስኪያገኙ ድረስ ዋጋቸው ውድ ሊሆን ይችላል ተብሏል። መሪ አልያም ፍሬን የሚባል ነገር የላቸውም። ማብሪያና ማጥፊያ በመንካት ነው መኪናውን የሚያስነሱት።
በፅሁፍ ወይም በካርታ የት መሄድ እንደሚፈልጉ ሲያሳውቁ፤ መኪናው በራሱ ጊዜ ይንቀሳቀሳል። ለሙከራ የተገጣጠሙት መኪኖች በመቶ ሺ ኪሎሜትር የሚቆጠር መንገድ በከተማና በገጠር ተጉዘዋል፤ አንድም ጊዜ ግጭት አላገጠማቸውም።

ዋነኛ ስራው - የኢንተርኔት አገልግሎት
በአመት ወደ 8 ቢ. ዶላር ገደማ የአገልግሎት ሽያጭ ያገኛል
ባለፈው አመት 1.5 ቢ. ዶላር አትርፏል
የኩባንያው ሃብት 18 ቢ. ዶላር ገደማ ይገመታል
በኢንተርኔት አለም በ2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል - 1.3 ቢ. ገደማ ደንበኞችን በማስተናገድ
በደንበኞች ብዛት አቻ ያልተገኘለት ፌስቡክ፣ ገና የረካ አይመስልም። ተጨማሪ ደንበኞችን ለማፍራት ዘዴ ማፈላለግ ከጀመረ ውሎ አድሯል። ከከተማ ርቀው የሚገኙና በቀርፋፋ የኢንተርኔት ግንኙነት የተቸገሩ ብዙ ሚሊዮን ሰዎች አሉ።
እነዚህን ሁሉ ደንበኛ ለማድረግ አዲስ ብልሃት ያስፈልጋል። በየአገሩ እየሄደ የግንኙት መስመር መዘርጋት አይችልም። እንደኢትዮጵያ በመሳሰሉ አገራትማ፣ ከመንግስት ውጭ የቴሌኮም አገልግሎት መስጠት ክልክል ነው።
ፌስቡክ የወጠነው ዘዴ፣ ከሰማይ ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ማቅረብ ነው። ከምድር በ30 ኪሎሜትር ርቀት የሚያንዣብቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ለማሰማራት ሙከራ እያከናወነ የሚገኘው ፌስቡክ፤ በፀሐይ ሃይል ለረዥም ጊዜ አየር ላይ የሚቆዩ አውሮፕላኖችን ሰርቷል።
ከሰማይ ላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ለማቅረብ እየሞከረ ያለው ፌስቡክ ብቻ አይደለም። ጉጉልም በፊናው እየተጣጣረ ነው።
በአንድ በኩል በከፍተኛ ርቀት የሚንሳፈፉ “ባሉኖች”ን ለመጠቀም ራሱን የቻለ ፕሮጀክት ሲያከናውን የቆየው ጉጉል፤ በፀሃይ ሐይል ለ5 ዓመታት አየር ላይ የሚያንዣብቡ ሰው አልባ አውሮፕላኖችን ሰርቷል።

  • ዋና ቢዝነስ፡ መጽሐፍ፣ ሲዲ፣ ዲቪዲ፣ የኤሌክትሮኒስ እቃ፣ ልብስ፣ ምግብ በኢንተርኔት መሸጥና በአካል ማድረስ
  • በአመት የ74 ቢሊዮን ዶላር ሸቀጦችንና አገልግሎቶችን ይሸጣል
  • አምና ሩብ ቢሊዮን ዶላር አትርፏል
  • የኩባንያው ሃብት 40 ቢሊዮን ዶላር ይገመታል
  • 120ሺ ገደማ ሰራተኞች አሉት

በኢንተርኔት ጎብኚዎች ብዛት በአለም 12ኛ ደረጃ ላይ ይገኛል
ከሳምንት በኋላ፣ አዲስ ታሪክ ይሰራል የተባለለትና “3ዲ” ስክሪን ያለው ሞባይል ስልክ ለገበያ እንደሚያቀርብ ያበሰረው አማዞን ዶት ኮም፤ እቃ የሚያደርሱ ሰው አልባ በራሪዎችን ሰርቶ እንዳጠናቀቀ ገለጿል።
አመት ሙሉ ሲወራለት የነበረው የአማዞን አዲስ ሞባይል ስልክ በወሬ አልቀረም።  አይፎን እና ጋላክሲ ከመሳሰሉ ስማርትፎኖች በምን እንደሚለይ በዝርዝር ባይገለፅም፤ በስክሪን ቴክኖሎጂው የላቀ እንደሚሆን ተገምቷል። ምስሎችን በአካል የማየት ያህል አንዳች የ3ዲ ቴክኖሎጂ ጥቅም ላይ እንዳዋለ ኩባንያው ጠቁሟል። ዋጋው ገና አልታወቀም።
የተለያዩ ሸቀጦችን በኢንተርኔት በመሸጥና ሸቀጦቹን ለደንበኞች በአካል በማድረስ የሚታወቀው አማዞን፤ አዲሱን የሞባይል ስልክ ለሚገዙ ደንበኞች ተመሳሳይ አገልግሎት መስጠቱ አይቀርም።
የቀረ ነገር ቢኖር፣ እቃዎችን ለደንበኞች የሚያደርስ ሰው አልባ በራሪ (ድሮን) ብቻ ነው። አማዞን እንደሚለው፣ ያለ አብራሪ እቃ ለማጓጓዝ የተሰሩት ሚኒ ሄሊኮፕተሮች በተግባር ተሞክረዋል። አደጋ የማድረስ ወይም የመጋጨት ስጋት የለባቸውም። በራሪዎቹ ሚኒ ሄሊኮፕተሮች ለአገልግሎት ዝግጁ ናቸው። እና ምንድነው የሚጠብቁት? የአውሮፕላን በረራዎችን ለመቆጣጠር በመንግስት የወጡ ህጎች እስኪሻሻሉ ድረስ፣ ሰው አልባ አውሮፕላኖችንም ሆነ ሄሊኮፕተሮችን በብዛት መጠቀም አይቻልም። ህጎች እስኪሻሻሉ እየጠበቅሁ ነው የሚለው አማዞን፤ “ፕራይም ኤር” የተሰኙት ሚኒ ሄሊኮፕተሮች በአመት ውስጥ ለደንበኞች እቃ የማመላለስ አገልግሎት ይጀምራሉ የሚል ተስፋ እንዳለው ገልጿል።
ታዲያ የእቃው ክብደት ከ2 ኪሎ ግራም መብለጥ የለበትም። ቦታውም  ከ17 ኪ. ሜትር በላይ መራቅ አይኖርበትም። እናም በኢንተርኔት አማካኝነት ያዘዙት እቃ በግማሽ ሰዓት ውስጥ ከቤትዎ ደጃፍ ከች ይላል - በሰው አልባ ሚኒ ሄሊኮፕተር።

Saturday, 07 June 2014 14:23

የግጥም ጥግ

ዛሬስ ስሌቱ ስንት ሆነ?

“መሬት፣ሴትና ሀገር…፣ አንድ ናቸው”
አትበሉኝ፤ አንድነታቸው ከሩቅ ይቀፋል፣
ሶስቱም ባንድ ላይ የከሸፉ እንደሁ፣ ነገረ
ትምህርት ባፉ ይደፋል…!
የ‘ውነት፣ የ‘ውቀት ሀቲታችን፣ እንደ
ፈርስ እጣቢ ይከረፋል፤
ሰብአዊነት እስከ መለኪያው፣ በየጎሰኛው
ከርስ ሰጥሞ ይነጥፋል፤
በዘመን እርከን ሳይገደብ፣ ትውልድም
በትውልዱ ይጣፋል!
ታዲያ እኛ እንኳ፣ እናስላው ጎበዝ
የአዙሪት ርዕዮትዓለሙን  ጣጣ፣
‹‹የዜሮ ድምር ፖለቲካችን››፣ ዛሬም
‹‹ነጋቲቭ›› እንዳይመጣ…!
        መስከረም፣ 1998ዓ.ም.

 ሩሲያዊው ቢሊየነር ድሚትሪ ራይቦሎቭሌቭ፤ በቅርቡ ከቀድሞ ሚስቱ ጋር የፈፀመውን ፍቺ እንደ ድንገተኛ የቢዝነስ ኪሳራ መቁጠሩ አይቀርም። የኢትዮጵያ ታላቁ ህዳሴ ግድብን እኮ ነው ክፈላት የተባለው፡፡ ቢሊዬነሩ 27 ዓመት በትዳር አብራው ከዘለቀችው ኢሌና ጋር ፍቺ መፈፀሙን ተከትሎ የስዊስ ፍ/ቤት የቀድሞ ባለቤቱ 4.8ቢ. ዶላር ብት ልትካፈል ይገባል ሲል ወስኗል፡፡ የኢሌና ጠበቃ በሰጠው መግለጫ “እጅግ ውድ ፍቺ ነው” ብሎታል። ይሄ እጅግ ውድ የፍቺ ክፍያ ለድሚትሪ ከፍተኛ ኪሳራ ሲሆን ለቀድሞ ሚስቱ ግን የማይታመን የሃብት ጎርፍ ነው፡፡
የዛሬ 15 ዓመት ደግሞ ሌላ ውድ ፍቺ ተፈጽሟል። አውስትራሊያዊው የሚዲያ ከበርቴና ለ32 ዓመታት በትዳር አብራው የኖረችው የ3 ልጆቹ እናት አና ሙድሮክ፤ እ.ኤ.አ በ1999 ዓ.ም ፍቺ ሲፈጽሙ ፍ/ቤት ለሚስትየው የ1.7 ቢሊዮን ዶላር ሃብት (110 ሚ.ዶላር ካሽ ይጨምራል) እንድትካፈል ነበር የወሰነላት። ከሃብት ክፍፍሉም በኋላ ሁለቱም የየራሳቸውን ህይወት ቀጥለዋል፡፡ በእርግጥ ሩፐርት ሙድሮክ በ38 ዓመት ከምታንሰው ዌንዲ ዴንግ ጋር ትዳር የመሰረተው ፍቺ በፈፀመ በ17ኛ ቀኑ ነበር ሳይፈታ በፊት ያዘጋጀ እኮ ነው የሚመስለው፡፡ አናም በበኩሏ፤ ከወራት ቆይታ በኋላ አንድ ኢንቨስተር አግብታለች፡፡ በሃብት ላይ ሃብት አትሉም፡፡ እነ አሜሪካን በመሳሰሉ የበለፀጉ አገራት፤ ቢሊዬነሮችን አግብቶ መፍታት አትራፊ ኢንቨስትመንት እየሆነ ነው፡፡

ውድ እግዚአብሔር፡-
ስቴፕለር ከታላላቅ ፈጠራዎችህ አንዱ ይመስለኛል፡፡
        ሩት
- የ5ዓመት ህፃን

ውድ እግዚአብሔር፡-
ቀናተኛ ዓምላክ ነህ ሲባል ምን ማለት ነው? እኔ እኮ ሁሉ ነገር ያለህ ነበር የሚመስለኝ፡፡
                        ጆን
- የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
የሰንበት ት/ቤት ለምን እሁድ ሆነ? የእረፍት ቀናችን እኮ ነው፡፡
        ራሄል
 - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
በእናትህ ትንሽዬ ፈረስ ላክልኝ፡፡ ብትፈልግ መዝገብህን ማየት ትችላለህ፡፡ ምንም ጠይቄህ አላውቅም፡፡
                        ብሩስ
- የ 5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ምናልባት ቃየንና አቤል የየራሳቸው ክፍል ቢኖራቸው ኖሮ አይገዳደሉም ነበር፡፡
ላሪ
 - የ8 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አንዳንዴ የፀሎት ጊዜም ባይሆን ስለአንተ አስባለሁ፡፡
ማርሻ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ለአንተ ከሚሰሩልህ ሰዎች ሁሉ የበለጠ የምወዳቸው ኖህና ዳዊትን ነው፡፡
ሳሚ
- የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
በመፅሃፍ ቅዱስ ላይ እንዳለው ሰውዬ 900 ዓመት መኖር እፈልጋለሁ፡፡ እወድሃለሁ እሺ፡፡
ዶን
- የ6 ዓመት ህፃን

በአብዱል ፈታህ አብደላህ አዘጋጅነት በኮንሶ የባህል ህግ ላይ ጥናት ተደርጐበት የተዘጋጀው “ሤራ አታ ኾንሶ” የተሰኘ መጽሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ መጽሐፉ ትኩረት ያደረገው በኮንሶ የባህል ህግ ስርዓት ላይ ሲሆን በጥናቱ ውስጥ የኮንሶ የአገር ሽማግሌዎችና የአካባቢው ተወላጅ ምሁራን ተሳትፈውበታል፡፡ በ197 ገፆች የተዘጋጀው መጽሐፉ፤ በኮንሶ የባህል ህግ ስርዓት ላይ ትኩረት ቢያደርግም አጠቃላይ የማህበረሰቡን ባህል፣ ወግ፣ ቋንቋና ሃይማኖታዊ ሁነቶች ይቃኛል፡፡ መጽሐፉ በኢትዮጵያ የፍትህ ሥርዓቶች ማዕከልና በኮንሶ ወረዳ አስተዳደር ትብብር ታትሞ በነፃ ለአንባቢያን ደርሷል፡፡ በተያያዘ ዜና የቱሪዝምና እና የሙዚየም ማውጫዎችን በማሳተም የሚታወቀው ሀገሬ ሚዲያና ኮሚዩኒኬሽን፤ የኮንሶ ህፃናት ስለ አካባቢያቸው የቱሪዝም መስህቦች እንዲያውቁ የሚረዳቸውን “ኮንሶን ለህፃናት” የተሰኘ የቱሪዝም መጽሐፍ ለንባብ ያበቃ ሲሆን “ሴራ አታ ኾንሶ” ከተባለው መጽሐፍ ጋር በኮንሶ ካራት ከተማ ባለፈው ሳምንት ተመርቋል፡፡

መቀመጫውን አሜሪካ ሂዩስተንና ኢትዮጵያ በማድረግ በቴአትር ዘርፍ የሚንቀሳቀሰው ዮሐንስ ቴአትር ፕሮዳክሽን፤ “ደላሎቹ” የተሰኘውን ቴአትር በሚቀጥለው ሳምንት እሁድ  ለእይታ ያበቃል፡፡ የምርቃት ስነስርዓቱ በዕለቱ ከምሽቱ 12፡00 ሰዓት በሀዋላ ሴንትራል ሆቴል እንደሚካሄድም ድርጅቱ በላከው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በኤርሚያስ ጌታቸው ተደርሶ፣ በህይወት አራጌ በተዘጋጀው በዚህ ቴአትር ላይ ችሮታው ከልካይ፣ ህይወት አራጌ፣ ኤርሚያስ ጌታሁንና ሌሎች አንጋፋና ወጣት ተዋንያን እንደሚሳተፉበት ለማወቅ ተችሏል፡