
Administrator
“ሳላዛት” ረዥም ልብወለድ ለገበያ ቀረበ
በአብርሃም ገነት የተጻፈው “ሳላዛት” የተሰኘ ረዥም ልብወለድ መጽሐፍ፤ ሰሞኑን ገበያ ላይ እንደዋለ ደራሲው ለአዲስ አድማስ ገለጸ፡፡
በ500 ብር ለሽያጭ የቀረበው ልብወለድ መጽሐፉ፤ በጃፋርና በሀሁ መጽሐፍ መደብሮች ማግኘት እንደሚቻል ታውቋል፡፡
አብርሃም ገነት በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተወዳጅ አጫጭር ልብወለዶቹና ወጎቹም ይታወቃል፡፡
“ሳላዛት” በረዥም ልብወለድ ዘርፍ፣ ለጸሃፊው የበኩር ሥራው እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል፡፡
****
"አለማችን ፕላኔታዊ ውሕደት ያስፈልጋታል"
”--ዓለምን በአንድ ፌደሬሽን ማሰባሰብ ግቡ ሰዋዊና ፕላኔታዊ አንድነት ለማምጣት ቢሆንም ውጤቱ ግን ከዚህ ያለፈ ነው። ዓለምን በአንድ ፕላኔታዊ ፌደሬሽን ማሰባሰብ ያስፈለገው ጦርነትን ለማስቀረት፣ ሰላምና ፍትሕን ለማስፈን፣ የምድር አየር ንብረት ለሰው ልጅና ለሌሎችም ፍጡራን ተስማሚ ሆኖ እንዲቀጥል ለማድረግና ስልጣኔን በተለይም የህዋ ስልጣኔን ለማቀላጠፍ ነው። ስለ ህዋ ስልጣኔ በቀጣዩ ሁለንታዊ መድረክ ስለምናወሳ አሁን በዝርዝር አንሄድበትም። አስተዳደርን በተመለከተ ይህ ፌደሬሽን፣ ዓለምን ጠቅልሎ ይዞ የሚገዛ ተደርጎ መታሰብ የለበትም። አሁን በፌደሬሽኑ ስር ያሉ ሀገራትን እውነታ በተግባር ማየት ትችላላችሁ። የፌደሬሽኑ ስልጣን እንደ መከላከያ፣ የህዋ ምርምር፣ አየር ንብረትና የውጭ ግንኙነት ባሉ የተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ነው። እነዚህ ጉዳዮች በቁጥር ውስን ቢሆኑም የምድርንና የሰው ልጅን ዕጣ የሚወስኑ ታላላቅ ጉዳዮች ናቸው። እነዚህ ታላላቅ ጉዳዮች ላይ ስኬት ማምጣት የሚቻለው በሀገራት ደረጃ በተበጣጠሰ ሁኔታ ሳይሆን እንደ ፕላኔት በአንድ ማዕከል መሥራት ሲቻል ነው። ከዚህ ውጭ ሀገራቱ ራሳቸውን ነው የሚያስተዳድሩት። ዓለም በሙሉ በፌደሬሽኑ ስትካተት ደግሞ የፌደሬሽኑ የውጭ ግንኙነት ስልጣን ፕላኔቷን ወደ መወከል ይሸጋገራል።”
( ከ”ሳላዛት“ የተቀነጨበ)
***
መጽሐፉ፤ በአዲስ አበባ በጃፋር እና ሀሁ መጽሐፍ መደብሮች፣ እንዲሁም በባሕርዳር አዳነ መፅሐፍ መደብርና በሌሎች የክፍለ ሀገር ከተሞች መፅሐፍ መደብሮችም ይገኛል፡፡
በቀጥታ መግዛት ለምትፈልጉ ባሕር ዳር፡- 0910625217 አዲስ አበባ፡- 091 396 0314 ወይም 091 128 0984 ደዉሎ ማግኘት ይቻላል፡፡
ኢትዮ ቴሌኮም በ6 ወራት ውስጥ 61. 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ
” በቴሌ ብር አንድ ትሪሊዮን ብር ዝውውር ተፈጽሟል“
ኢትዮ ቴሌኮም በ2017 በጀት አመት ስድስት ወራት ውስጥ 61 .9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን አስታወቀ። የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ፣ የተቋሙን የግማሽ ዓመት የስራ አፈፃፀምን አስመልክቶ፣ ዛሬ የካቲት 5 ቀን 2017 ዓ.ም ረፋዱ ላይ ለጋዜጠኞች መግለጫ ሰጥተዋል።
ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ በስካይ ላይት ሆቴል በሰጡት መግለጫም፣ በበጀት አመቱ የመጀመሪያዎቹ ስድስት ወራት፣ በቴሌ ብር አማካኝነት አንድ ትሪሊዮን ብር ዝውውር መፈፀሙን ተናግረዋል፡፡ ወጪ ቆጣቢ የዲጂታል አገልግሎትን ተግባራዊ በማድረግ 3.5 ቢሊዮን ብር ማዳን መቻሉንም ተናግረዋል፡፡
ተቋሙ ባለፉት ስድስት ወራት 202 በሚሆኑ አካባቢዎች አዳዲስ የገመድ አልባ አገልግሎቶችን ማስፋት መቻሉን የገለጹት ዋና ሥራ አስፈጻሚዋ፤በስምንት ከተሞች ላይ የ5ኛ ትውልድ (5ጂ ኔትወርክ) አንዲሁም 67 ከተሞችን የ4ኛ ትውልድ (4ጂ ኔትወርክ) ተጠቃሚ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ አገልግሎት የተቋረጠባቸው አካባቢዎችን ዳግም ወደ አገልግሎት ለማስገባት በተሰራው ስራ 216 አካባቢዎች ሙሉ የቴሌኮም አገልግሎት እንዲያገኙ መደረጉን ዋና ስራ አስፈፃሚዋ አብራርተዋል።
ተቋሙ እኒህን ጨምሮ ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ ተግባራትም ባለፉት 6 ወራት 61.9 ቢሊዮን ብር ገቢ ማግኘቱን ያስታወቁት ወ/ት ፍሬህይወት ታምሩ፤ ይህም ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር የ43 በመቶ ብልጫ ማሳየቱን ጠቁመዋል፡፡
ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና ተመረጠች
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የስራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ በህብረቱ ዋና መቀመጫ አዲስ አበባ በዛሬው ዕለት መካሄድ የጀመረ ሲሆን፤ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና ተመርጣለች፡፡
ስብሰባው፤"የማካካሻ ፍትሕ ለአፍሪካውያንና ዘርዓ-አፍሪካውያን” በሚል መሪ ሀሳብ የሚካሄድ ሲሆን፤ከስብሰባው አጀንዳዎች መካከል የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት የአምስት አባላት ምርጫ ይገኝበታል።
በዚህም ኢትዮጵያ የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት አባል ሆና የተመረጠች ሲሆን፤ ለሦስት ዓመታትም የምክር ቤቱ አባል ሆና ታገለግላለች።
በአፍሪካ ሰላምና መረጋጋት ለረጅም ዘመናት በቁርጠኝነት የሰራችው ኢትዮጵያ፤ የምክር ቤቱ አባል ሆና መመረጧ ብሔራዊና ቀጣናዊ ፍላጎቶቿንና ጥቅሞቿን ከማስጠበቅ አንጻር ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያስገኝላታል ተብሏል።
የአፍሪካ ህብረት የሰላምና ጸጥታ ምክር ቤት፤ 15 አባል አገራት አሉት።
46ኛው የአፍሪካ ሕብረት የሥራ አስፈጻሚ ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባ ዛሬ ሲጀመር
የቀዳማዊ እመቤቶች አማካሪዎች የአድዋ ድል መታሰቢያንና የብሔራዊ ቤተመንግስትን ጎበኙ
ለ29ኛው የአፍሪካ ቀዳማዊ እመቤቶች የልማት ተቋም ጠቅላላ ጉባኤ ለቅድመ ስብሰባ አዲስ አበባ የመጡ የቀዳማዊ እመቤቶች አማካሪዎች የአድዋ ድል መታሰቢያንና የብሔራዊ ቤተመንግስትን ጎብኝተዋል።
የነብይ ገፅ
ንክሻ
የነብይ ገፅ
ነቢይ መኮንን!
-1
ትናንት ማታ ግር የሚያሰኝ ነገር አጋጠመኝ ። ሌሊቱን ሁሉ ግር ብሎኝ አደረ።
እግዚአብሔር ይይላትና … ፣ ያቺ ልጅ አካላቴን አተኩሳው አደረች። እንዲችው ስገላበጥ። እሷና እኔ በጥቂት ወይም ምንም አልባሳት እየተረዳን የምንተውንባቸው የተለያዩ ተውኔቶች ስደርስ። በሀሳብ ልምምድ ስናደርግ .......
-2
ትናንት ማታ ቢሮ ሥራ አምሽተናል። ደክሞኝ ነበር። ወደ ቤት ለመግባት መገናኛ የሚወስደኝን ሚኒባስ ታክሲ ከስቴድዮም ያዝኩ። ታክሲው ቢሞላም እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጋ ጥቂት ተሳፋሪዎች እንድንታቀፍ በወያላው መታዘዛችን አልቀረም። ለእኔ እና ከጐኔ ለነበረችው ልጅ የደረሱን ሴትዮ እጅግ ወፍራምና ረዥም በመሆናቸው በልከኛ ሰው እንዲቀየሩልን፤ ይኸ ካልተቻለም እሳቸው ተቀምጠው እኛን ይታቀፉን ዘንድ አመለከትኩ። ለፈገግታ ያሰብኩት ነገር ባይሆንም ተሳፋሪው መሳቁ አልቀረም።
መገናኛ ጫፍ ስደርስ ጣመኔን ለማስታገስ እና አንድ ነጭ ማኪያቶ እየጠጣሁ ከእግሬ ላይ ለአፍታ ልወርድለት በማሰብ እዚያው አካባቢ ካለ ሻይ ቤት ጐራ አልኩ። ቤቱ ሙሉ ነበር። ይንጫጫል። ዙሪያውን የተገጠሙት መስታወቶች ምስሉን እየተቀባበሉ የቤቱን ስፋትና የሕዝቡን ቁጥር አባዝተውታል።
-3
ልታስተናግደኝ የመጣችውን ልጅ አተኩሬ ዐየኋት።
በሻይ ቤቱ የሥፍራ መታጣት ምክንያት አሁን ግልፅ ሆኖልኛል። ማንም ጐረምሳ (እስከ ጐልማሳ ሊዘልቅ ይችላል) ይኸች ውብ ቀንበጥ ልጅ ከማራኪ ፈገግታዋ ጋር የምታቀርብለትን ቡና አየደጋገመ ከመጨለጥ ሌላ እምብዛም አማራጭ አልተተወለትም።
“ነጭ ማኪያቶ” አልኳት እሷን በማየት እንደ ባለጌ የላሉ ዐይንና ከንፈሮቼን ቀይ ፊቷ ላይ አንጠልጥዬ።
እመኑኝ፤ ለእኔ ብቻ የተሰናዳ ፈገግታ መግባኝ ስታበቃ ወደ ትዕዛዝ ሄደች። ዛሬም ቢሆን ሳይንስ ያልደረሰባቸው ብዙ ምሥጢሮች እና ያልተመለሱ በርካታ ጥያቄዎች አሉ። ለምሳሌም ያከል፣ የረዥም ቆንጆ ልጅ የሚያምር ፈገግታ በዚያች ቅዕበት፤ በየት በኩል ገብቶ፣ ምን ልዩ ቅመም ጨምሮ የኔን ደም እንዲያ አጣፈጠው? ምን እቶን አንድዶ እንዲያ አፈላው?
- 4 -
አደንቃት ጀመር። ደሞም ይገባታል።
ከዛሬ ሃያ ዓመት በፊት ኧረ የምን ሃያ … ፣ ከዛሬ ዐሥር ዓመት በፊትም ይቺን የመሰለች ለጋ ቆንጆ በጠኔ ጥንፍር ትላታለች እንጂ በሰደፍ ቢያስፈራሯት እንኳ ኬክ ቤት ሙባሽር አትሆንም ነበር። አውሮፓና አሜሪካ በስደት ላይ ካልሆነች በቀር።
ይኸው አሁን ይቺ ለልዕልትነት የታጨች የምትመስል ልጅ፣ ሽርጧን በአጭር ታጥቃ ስታበቃ ለእኔ ነጭ ማኪያቶ ለማቅረብ ሽር ጉድ ስትል ትታያለች።
“ጐሽ እሙዬ አበጀሽ” አልኳት በሆዴ ዐይኔን ከረዥም አንገቷ ላይ ሳልነቅል። ግዴለም ጐበዝ በዚህች ቅድስት ሀገራችን ልጆች ዘንድ የሥራ ክቡርነት ...
-5-
ማኪያቶዬ መጣ።
አወይ! የሲኒውን ማስቀመጫ የያዙት ጣቶች! የምሽቱ ሳይንስ ያልደረስበት ሁለተኛው ምሥጢር የዚህች ልጅ ረዣዥም ጣቶች ያለአጥንት አበቃቀል ነው። ቀና ብዬ ሳያት (አሁንም እመኑኝ) ያን ለእኔ ብቻ የተሰናዳ ፈገግታ ደግማ መገበችኝ።
በምሽቱ እጅግ ያስደነገጠኝ ነገር ግን ወዲያው ተከተለ። ልጅቷ ዐይኗን በዐይኔ ጠብቃ ከቆለፈች በኋላ የውብ ከንፈሮቿን ዙሪያ ዳር ድንበር በምላሷ አረጠበች። ይኽ እንደተጠናቀቀም የማርጠብ ሥራ የተከናወነላቸው የታች ከንፈሮቿ በነጫጭ ትክክል ጥርሶቿ እየነካከሰች ታየኝ ጀመር።
-6-
የመረበሼን ጕዳይ አታንሱት! በርግጥ ጐረምሳ ነኝ ። ጥሩም ለብሻለሁ። ሰውነቴም በኘሮግራም በማደርገው የአካል እንቅስቃሴ የዳበረ ነው። ሆኖም ግን ምንም ያህል የደረት ስፖርት/push up/ ብሠራና ብረት ባነሳ ደረቴ ከመደደሩ በፊት ተፈጥሮ ከለገሰችኝ ሜትር ከኀምሳ ሳንቲም ቁመት አንዲት ጋት ስንኳ መጨመር አልቻልኩም። አፍንጫዬም ትንሽ ስፋቱን የማስቀንስበት መንገድ ቢገኝ የሚጠላ ዓይነት አይደለም።
“ቀዮ!” ብሎ ሊያቆላምጠኝ የሚችል ጤነኛ ሰው የለም … ዘመናዊ ወጣት ሴት የኔ ቢጤዎች ካልሆኑ በቀር። በትምህርታቸው ጐበዝ የሆኑ መጠነኛ መልክ የታደሉና አዘውትረው የቤተክርስቲያን የሰንበት ትምህርት የሚከታተሉ ወይም በመንፈሳዊ ማኅበር የታቀፉ ዓይነት ኮረዳዎች ካልሆኑ በቀር ... ቆነጃጅት ሁለቴ ዞረው የሚያዩት ዓይነት ቁመናና ውበት አልታደልኩም፤ እንግዲህ መቼም … ፣ ሀቅ እንነጋገር ከተባለ።
በእርግጠኝነት ደግሞ ያቺን የመሰለች ቆንጆ ላይ በቅፅበት የፍቅር ረሀብ ፈጥሮ ሲያበቃ ከንፈር የሚያሳኝከ ዓይነት ሸበላ በጭራሽ እንዳልሆንኩ ምዬ መመስከር እችላለሁ።
-7
እንገደና ከሩቅ ዐይን ለ0ይን ተገጣጠምን። አልተሳሳትኩም። አሁንም ከንፈሯን እጅግ ክፋት በሚያሳስብ አኳኋን እየበላች ዐይኗን አፈዘዘችብኝ። ሰው ነኝና ከአዳም ተፈጥሬያለሁና … ልሳሳት ጀምሬያለሁ። የመታጠቂያዬ ክልል ሙቀት አስጊ በሆነ አኳኋን ሲጨምር ይታወቀኛል።
ከልኳ በሁለት ደረጃ ጠብቦ በተሰፋው መለዮ ልብስ ውስጥ የተከተተውን ጥብቅ ቀጥ ያለ ቁመና እንደ ኬሚስትሪ አጠናሁት። ከቶ ፍላጐቷን ልረዳው አልቻልኩም።
“የከተማው ስመ ጥር ኢንቬስተር የወቅቱ አስተናባሪ ነው” የሐሰት ወሬ ነግረዋት ይሆን?
እንጃ!
-8
ገና ልጠራት እጄን ማንቀሳቀስ ስጀምር ካለችበት እየተሳበች መጣች። አሁንም በብልግና አኳኋን ያን የቀድሞ ረብሻዋን ጀመረች።
“ሒሣብ ስንት ነው?” አልኳት።
-9
ከሰጠችኝ መልስ ላይ አንድ ብር ጉርሻ ኒኬሉ ላይ ሳስቀር በመልካም የቋንቋው ዐዋቂ ቅላፄ እና ሆን ተብሎ ጉሮሮ ላይ እንዲሻክር በተደረገ አማላይ ድምፅ ‘Thank you lt is more than enough’ አለችኝ።
-10
ስወጣም ንግሥት ሳባ ከምሽት ጉብኝቱ በኋላ ንጉሥ ሰለሞንን ከመኝታ ክፍሏ በሸኘችበት ቅሬታና ዐተያይ በዐይኗ ሸኘችኝ።
-11
ጠዋት ከእንቅልፌ ስነሳ እሷው ነበረች የምናቤ መከፈቻ። ቁርስ እንደ ወትሮው አልተበላልኝም።
ዘወትር ከፍ እንጂ ዝቅ ሲል ታይቶ የማይታወቀውን የምግብ ፍላጐቴን የምትወደው እናቴ፤ “ምን ነክቶሀል? ማታ እንቆቆ ወይም የዱባ ፍሬ አቆይሀለሁ” አለችኝ ያልተነካውን ፍርፍር እያነሳች።
- 12
ቀኑን ሙሉ ሳስባት ዋልኩ። ለሰው የማይነገር ሆነብኝ። መቼም ለምቀርባት የአለቃዬ ፀሐፊ “አንዲት ቆንጆ ልጅ በፍቅሬ ተቸግራለች ብላት” እስከ ምሳ ሰዓት በድፍን መሥሪያ ቤቱ ተዳርሶ በሽርደዳ ልጟዕ ይጨርሱኝ ነበር። ለብቻዬ በሆዴ ይዣት ዋልኩ።
ያቺ ውብ ልጅ እንዴት ከሰው ሁሉ መርጣ አኔን እንደወደደች አያሰብኩ ሆዴ አሁንም አሁንም በሚፍነከነኩ ጥቃቅን ደስተኛ ቢራቢሮዎች እንደተመላ ሆነ።
ለሥራ ክብርና ፍቅር ያላት የሰውን ውስጣዊ ማንነት እና ትልቅነት በቅፅበት አበጥራ የማወቅ ተሰጥኦ የታደለች ውብ የሐበሻ ወጣት በመሆኗም ጥቂት ጥናት አካሂጄ ለቁም ነገር ላስባት ወሰንኩ።
“እንዴ ‘ከዚህች ልጅ ጋር አንተ ትብስ አንቺ ትብሽ አየተባባሉ ከፍ ያለ ደረጃ ለመድረስ ይቻላል !!” ስል አመንኩ።
ማታ እሄዳለሁ። በቃ ወስኛለሁ! ማታ ሄጀ ሳበቃ ለውዷ ልጅ የፍቅር ጥያቄ ተገቢውን የፍቅር ምላሽ እሰጣለሁ።
- 13
ዛሬም ሥራ አምሽቻለሁ። ተከታታይነት ያለው እና በጥድፊያ መጠናቀቅ ያለበት ዓይነት ሥራ ነው።
እንደወጣሁ ወደ መገናኛ የሚወስደኝን ሚኒባስ ታከሲ ከስቴዲዮም ያዝኩ። ታክሲው ቢሞላም … . እስጢፋኖስ ቤተክርስቲያን ጋ ጥቂት ተጨማሪ ተሳፋሪዎችን እንድንታቀፍ በወያላው መታዘዛችን አልቀረም። ዛሬ ደግሞ ለእኔ እና ከጎኔ ለተቀመጠው ልጅ የደረሰን ጐረቤት የሆነው ቴዎድሮስ ነበር። “ሃይ ዳዊት ትንሽ ጠጋ በል” አለኝ ቀኝ የጭን አጥንቴን እያደቀቀ።
- 14
መናገኛ ስንደርስ “ .. ቴዲ አንተ ሠፈር ግባ ። እኔ እዚህ ሻይ ቤት ሰዎች ቀጥሬያለሁ።” አልኩት አብሮኝ እንዳይመጣ ከሩቅ እየተከላከልኩ።
“ሀሀሀ …” ዳዊት ሸር የተመላው ሳቅ እየሳቀ “እዚያ ሻይ ቤትማ … እኔም ደረስ እላለሁ። አንዲት ከንፈሯን የምትነክስብኝ ቀይ ቆንጆ ልጅ … ..”
***
(የትሮይ ፈረስ፤ በአሳምነው ባረጋ)
በ800 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና አትሌት ፅጌ ድጉማ ድል ቀናት
በፈረንሳይ ሜዝ በተካሄደ የ800 ሜትር የዓለም የቤት ውስጥ ሻምፒዮና ውድድር እትሌት ፅጌ ድጉማ አሸንፋለች፡፡ ፅጌ የ800 ሜትሩን 1 ደቂቃ ከ58 ሴኮንድ ከ97 ማይክሮ ሴኮንድ በመጨረስ በቀዳሚነት ማጠናቀቋን የዓለም አትሌቲክስ መረጃ ያመላክታል፡፡
ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ ረግጠህ አትሻገር
በፐርሺያ ስለፐርሺያ የጥንት ንጉሥ የሚነገር አንድ አፈ - ታሪክ አለ፡፡
እንዲህ ይላል፡፡
አንድ ጊዜ የንጉሡ ሁለት ባለሟሎች ባጠፉት ጥፋት ዙፋን ችሎት እንዲቀርቡ ይታዘዛሉ፡፡ ከዚያም ያጠፉት ጥፋት ፍርዱ እንደሚከተለው ተነገራቸው፡፡
ንጉሱ፤ ተደላድለው ዙፋናቸው ላይ ከተቀመጡ በኋላ፡-
“ያጠፋችሁት ጥፋት ፍፁም ምህረት የማይደረግለት ነው፡፡ በዚህም ምክንያት ሁለታችሁም በሞት እንድትቀጡ ተወስኗል፡፡ ይግባኝ ማለት ወይም የመሰላችሁን አስተያየት መስጠት ትችላላችሁ” አለ፡፡
ከሁለቱ ፍርደኞች አንደኛው ንጉሱ ከልብ የሚወድዱት ፈረስ እንዳላቸው ስለሚያውቅ፤
“ንጉስ ሆይ! አንድ ዓመት ይሰጠኝና የሚወድዱት ፈረስዎን በአየር ላይ እንደ ወፍ መብረር ላስተምረው፡፡ ይህንን ካደረግሁኝ ነብሴን ይምሩልኝ ከሆነ ማስተማሬን ልቀጥል” አለና ተማጠነ፡፡
ንጉሱ፤ በአንድ ወገን የሚወድዱት ፈረሳቸው መብረር መቻል፣ በሌላ በኩል የጥፋተኛውን ፍርድ መሻር፣ በጣም ካማለላቸው በኋላ፣ በአለም ላይ የሚበር ፈረስ ያለው ንጉስ እሳቸው ብቻ መሆናቸውን አሰቡና ልባቸውን ሞቅ አላቸው፡፡ በመጨረሻም፤
“ይሁን፤ ፈረሴን በአየር ላይ መብረር አስተምርልኝ! አንድ ዓመት ሰጥቼሀለሁ” አሉት፡፡
ይህን ወስነው እንደሄዱ ሁለቱ ሰዎች መወያየት ጀመሩ፡፡
ሁለተኛው ፍርደኛ - “ስማ፤ አብደሃል እንዴ? ፈረስ በአየር ላይ በምንም አይነት እንደማይበር ታውቃለህ፡፡ በምን ተአምር ፈረሱን በአየር መብረር ልታስተምረው ነው? አንድ አመት እሩቅ መሰለህ? የማይቀረውን ነገር ቀኑን ማስተላለፍስ ለምን ይጠቅምሀል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
አንደኛው ፍርደኛም፤
“ይህንን ያደረግሁት በአራት መንገድ ነፃ እወጣለሁ የሚል ተስፋ ታይቶኝ ነው” አለና መለሰ፡፡
“አራት መንገድ? ለመሆኑ ንጉሱን የሚያሳምን አንድስ መንገድ ይገኛል? ስማ፤ ንጉሱ የሚለቅቁህ ፈረሳቸውን ለማብረር ከቻልክ ብቻ ነው፡፡ ለመሆኑ ምን ምን መንገድ ታይቶህ ነው?”
አንደኛው ፍርደኛም እንዲህ ሲል መለሰ፡-
“አንደኛ፤
በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ንጉሱ እራሳቸው ሊሞቱ ይችላሉ፡፡
ሁለተኛ፤
እኔ እራሴ ልሞት እችላለሁ፡፡
ሦስተኛ፤
ፈረሱ ሊሞት ይችላል፡፡
አራተኛ፤
ማን ያውቃል፤ ምናልባት ፈረሱን በአየር ላይ መብረር ላስተምረው እችል ይሆናል” አለ፡፡
* * *
ከእንዲህ ያለ አጣብቂኝና ውጥረት ሀገራችንን ይሰውራት፣ ማለት ደግ ነው፡፡ በማንኛውም ጉዳይ አማራጭ ማግኘት ወሳኝ ነገር ነው፡፡ አማራጮች ሌላ አማራጭ ቢፈልጉም እንኳ የሚቻለውን ጥረት አድርጎ መፈለጉን መቀጠሉን ሁኔታዎች ግድ ይላሉ፡፡ ከአማራጮች መካከል መደራደር አንዱ መንገድ ነው፡፡ ብዙ ነገሮች እጅግ በተወጣጠሩ ሰአት ረጋ እና ሰከን ብሎ የሚያስብና መውጫ መንገዶችን የሚያሰላ ግለሰብ ወይም ቡድን ማግኘት መታደል ነው፡፡ በጣም አስፈላጊም ነው፡፡
የመጨረሻ ውጥረት ቢኖርም እንኳ ማረጋጋትና ማርገብ ሁሌም ከአማራጮች መካከል የማይቀር ነው፡፡
ዛሬ ሀገራችን ባለችበት ሁኔታ ሀገርና ህዝብን የማረጋጋት ሂደት ተቀዳሚ ነው፡፡ ሰላም የሁሉ ማሰሪያ ነው፡፡ ምንም እንኳን ግጭትና ፍጭት የሰፈነበት የአሁኑ ሁኔታ፣ የህዝቡን ብሶትና ምሬት የፈጠሩት ሁኔታዎች የነባራዊና ህሊናዊ መንስኤዎች ጥምርና ድምር ቢሆንም፣ ህዝብ የሚለውን ሳይታክቱ መስማትና የልብ - ትርታውን ማዳመጥ፣ ተገቢ ጉዳይ ነው፡፡ በሰላማዊ መንገድ ሀሳብን መግለፅ የህዝብ መብት ነው፤ የሚለውን ቋሚ መርህ ከልብ ማመን ያስፈልጋል፡፡ ህዝብ መቼም ቢሆን መች “ላይ ላዩን ይነጋገራሉ፣ ልብ ለልብ ይተዛዘባሉ” እያለ ጀምሮ፣ ከሮና መርሮ የብስጭትና ምሬቱ ጫፍ ላይ እስኪደርስ መጠበቅ ኋላ ማጣፊያው እንዲያጥር ያደርጋል፡፡
የህብረተሰብ ድርና ማግ በረዥም ሂደት ውስጥ የተሸመነ እንደመሆኑ፤ የተጠራቀሙ ብሶቶች ያልተፈቱ ችግሮች፣ መናቅና መግፋት፣ እንዲሁም ሁኔታዎችን እንደማያድጉ አድርጎ ማሰብ፤ ውሎ ሲያድር ውሉ ከማይታወቅ ውስብስብ ችግር ውስጥ ሊከት እንደሚችል ከዛሬው ሁኔታ ሌላ አስተማሪ አይኖርም፡፡ ዴቪድ ፖል ቴሩ የህዝብ አልታዘዝ ባይነት በሚለው ታዋቂ ፅሁፉ፤ “የህዝብ አልታዘዝ - ባይነት ማለት የሲቪል ህግጋት ወይም ድንጋጌዎች አልቀበል ወይም አልታዘዝም ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ተቃውሞ የሰላማዊ ተቃውሞን ወይም የሀይል - አልባ ተቃውሞን ቅርፅ የያዘ ነው፡፡ ይህ አይነት ተቃውሞ የሚያካሂዱ ዜጎች ህግን የማያከብሩት ኢ-ፍትሀዊነት አለ ብለው ከልብ ሲያምኑና እንለውጠዋለንም ብለው ተስፋ ሲያደርጉ ነው” ይላል፡፡
እስከዛሬ በነበረችው ኢትዮጵያ “ባለቤቶች ሲሸሹ፣ ባለቆዳዎቹ ይዋጋሉ” የሚባለው አይነት ሁኔታ ውስጥ የቆየው ህዝብ ወደፊት አምርቶ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብቶችን ራሱ ወደ ማወቅ ሲጓዝ መታየቱ ታሪካዊ ነው፡፡ ልዩ እመርታም ነው፡፡ ይህ ልብ መባል ያለበት ጉዳይ ነው፡፡ ቀና ብሎ መብቴን ነፃነቴን ስጠኝ የሚልበት ብቻ ሳይሆን መብቱም ነፃነቱም የእኔ ነው፡፡ የሚልበት ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል እያንዳንዱ ፓርቲ ሊገነዘበው ይገባል፡፡
በተደጋጋሚ በዓለም ያየነው የፖለቲካ ታሪክ “ሰው እስኪጠላህ እድሜ አይስጥህ” በሚለው ተረት የሚጠቃለል እንደሆነ እናስተውላለን፡፡ በዚህ እረገድ ሁሉም እራሱን ቢፈትሽ መልካም ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ እርጋታ ያስፈልጋል፡፡ በጥሞና የሄዱበትንና የሚሄዱበትን ሁሉ መመርመር ያስፈልጋል፡፡ ካጠፉ ለመታረም፣ ከተቃረኑ ለመደራደር የፀና ልቦና የሰለጠነ አእምሮ ያስፈልጋል፡፡
ህዝብ የታሪክ ወንዝ ነው፡፡ መንግሥታት ይለወጣሉ፡፡ መሪዎች ይቀየራሉ፡፡ የሀገሪቱ ነገ በህዝቡ ዛሬ የሚወሰን ነው፡፡
የህዝቡ ዛሬ ደግሞ በሁላችንም እጅ ላይ ነው፡፡ ህዝቡን ማዳመጥ ፣ ጎንበስ ብሎ የልብ-ትርታውን ማወቅ እና መረዳት ግዴታችን ነው፡፡ “ጠላ እጠጣለሁ ብለህ ወንዝ እረግጠህ አትሻገር” መባሉ ለዚህ ነው፡፡ ሰላም የዚህ ሁሉ ቁልፍ ይሁን፡፡
የሌሊሳ ግርማ “በታችም በምድር” ነገ በገበያ ላይ ይውላል
በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የደራሲ ሌሊሳ ግርማ “በታችም በምድር” የተሰኘው ወጥ የልቦለድ መፅሐፍ በነገው ዕለት በገበያ ላይ ይውላል፡፡
በተለያዩ መጣጥፎችና አጭር ልብ ወለድ ጽሁፎች በአንባቢያን ዘንድ ተወዳጅነትን ያተረፈው ሌሊሳ ግርማ፤ አሁን ደግሞ በመጀመሪያ የወጥ ልቦለድ ድርሰት መጥቻለሁ እያለ ነው፡፡
ደራሲ ሌሊሳ ግርማ፤ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ በሚያቀርባቸው ጥበባዊ መጣጥፎቹም ይታወቃል፡፡
ደራሲው ከዚህ ቀደም “የንፋስ ህልም እና ሌሎች አጫጭር ታሪኮች”፣ “አፍሮ ጋዳ”፣ “መሬት - አየር - ሰማይ”፣ “የሰከረ እውነታ”፣ “እስቲ ሙዚቃ”፣ “ነፀብራቅ”፣ “ይመስላል ዘላለም”፣ የሚሰኙ የመጣጥፍና የአጭር ልብ ወለድ ስብስብ መድበሎችን ለአንባቢያን ማበርከቱ ይታወሳል፡፡
የመጽሐፉ አሳታሚ ዋሊያ መፅሐፍት ድርጅት ሲሆን፤ መጽሐፉ ከነገው ዕለት ጀምሮ በከተማዋ በሚገኙ መጻሕፍት ቤቶች ሁሉ ለገበያ እንደሚውል ታውቋል፡፡
ከአድማስ ትውስታ ፤ 1992
“ሴቶች ይሄን ያህል ወሬኛ የሆኑት ለምንድነ ነው?”
ለመሆኑ ለምን ከወንዶች ይልቅ ሴቶች የበለጠ እንደሚያወሩ በመገረም ራሳችሁን ሳትጠይቁ ትቀራላችሁ? ሴቶች ደክሟቸው ተዝለፍልፈው እስከሚወድቁ ድረስ ገበያ ሲገበዩ ቆይተው፣ ቤት የተቀመጠውን አባወራ “የአልጋ ላይ አንበሳ ነህ አንተ” እያሉ እየዘለፉት ለምን ለማሳመን እንደሚችሉስ ታውቃላችሁ? በአንፃሩ ወንዶች ሚስቶቻቸውን ለማታለል ለምን እንደሚፈልጉ፤ በምንም ዓይነት ጥፋተኛ ተደርገው ለመታየት ለምን እንደማይሹና ምክር አልቀበልም ማለታቸውስ ከምን እደሚመጣ ታውቃላችሁ?
ይህ ፅሁፍ በወንዶችና በሴቶች መሀከል ያለውን ልዩነት የፈጠሩት የሰው ልጅ ስነ - ተፈጥሮአዊና ዝግመተ - ለውጣዊ (Evolutionary) ሳይንሳዊ ሂደቶች መሆናቸውን የሚያሳይ ነው፡፡ አለንና ባርባራ ፒስ የተባሉ ፀሃፊዎች “ወንዶች ለምን ምክር ለመስማት ፈቃደኞች አልሆኑም፤ ሴቶችስ ለምን ካርታ ማንበብ አይችሉም?” ከሚለው መፅሀፋቸው የሚጠቅሱልን ነው፡፡
ሴቶች ይሄን ያህል ወሬኛ የሆኑት ለምንድን ነው?
ለመናገር የሚያስችለንን ችሎታ የሚሰጠን የአንጎል ክፍል የሴቶች ሁለት ሲሆን፤ የወንዶች ግን አንድ ብቻ ነው፡፡
ወንዶች ዕቃ ፈልጎ ማግኘት የማይሆንላቸው ለምንድን ነው?
ወንዶች “ተነል ቪዥን” የሚባል ተፈጥሮአዊ የሆነ “የርዝመት - እይታ ማነጣጠሪያ አሸንዳ” አላቸው፡፡ ይሄ የዕይታ አሸንዳ የዕይታ ዳርቻን የሚወስን ሲሆን፤ ከሴቶች ይልቅ የወንዶቹ ሰፊ የርቀት አድማስ ይዳስሳል፡፡ ይሄ ጉዳይ በቅድመ - ታሪክ ወንዶች ለአደን በሚወጡበት ሰዓት ረዥም እርቀት ላይ ያለ ታዳኝ አውሬ ለማየት ከመፈለጋቸው ጋር ተያያዥነት ያለው ነው፡፡ ባንፃሩ የዚያን ዘመን ሴቶች በቅርብ ዕይታ ስር ያሉትን ጎጆዎቻቸውን በመጠበቅ ላይ ብቻ ይሰማሩ እደነበር ይታወቃል፡፡ በዚህ ምክንያት ወንዶች የሩቅ የሩቁን ለማነጣጠር ብቻ ዐይናቸውን ገርተውታል፡፡
ወንዶች ብዙ ሴት ወዳጆች እዲኖሯቸው የሚፈልጉትስ ለምንድን ነው?
የዝግመተ - ለውጥ ጥያቄ ነው፡፡ የኢቮሊዩሽን፡፡ ብዙ ሴቶች የማግኘት ፍላጎት ከወንዱ አንጎል ጋር ድርና ማግ ሆኖ የተሰራ ነገር ነው፡፡ በታሪክ እንደሚታወቀው በጦርነት ሳቢያ በብዛት የሚያልቀው ወንዱ በመሆኑ የሴቶች መትረፍረፍና የወንዱ ቁጥር ማነስ በግልፅ የሚታይ ችግር ሆኗል፡፡ ማንኛውም ጎሳ ደግሞ የዘሮቹን ቁጥር መጠበቅና ማብዛት ይሻል፡፡ ስለዚህ ወንዱ ዘሩን በብዛት መዝራት ይኖርበታል ማለት ነው፡፡
በሰው አንጎል ውስጥ የወሲብ ግፊትና ፍላጎት የሚመለከተው ክፍል ከሴቶች ይልቅ የወንዶቹ ትልቅ ነው፡፡
ወንዶች ጥፋተኛ ሆኖ ለመቆጠር ለምን አይሹም? ምክር ለመቀበልስ ስለምን ፈቃደኛ አይሆኑም?
አንድ ወንድ ወደ አንድ ቦታ መኪና ሲነዳ ድንገት የሚሄድበት ቦታ ቢጠፋው አቁሞ መንገድ ይጠይቃል፡፡ ሆኖም ከጎኑ ሴት ካለች ግን በጭራሽ አይጠይቅም፡፡
ምክንያቱ አሁንም ያው እዋሻ - ውስጥ ጥንት የነበረው ወንድ ደመ - ነብስ እውስጠ በመኖሩ ነው፡፡ አንዳች የደካማነት ስሜት ካሳየ ቤተሰቡን ያስጨንቃልና፣ በጭራሽ ያ እንዲሆን አይፈቅድም፡፡ ጀግናውና ከቤቱ ወጥቶ አድኖ ቤተሰቡን መጋቢው የዋሻ ሰው፤ በቤተሰቡ ፊት ደካማ መስሎ መታየት አይፈልግም፡፡ በዚህ ምክንያት ነው ወንዶች ተሸናፊ ሆነው መታየት የማይሹት፡፡
ሴቶች ለምን ሱቅ ሄዶ መገብየት ይወዳሉ?
ለሴቶች ገበያ መውጣት እንደማውራት ነው፡፡ ያዝናናቸዋል፡፡ ወንዶች ከ20 ደቂቃ በኋላ ገበያ ውስጥ አይቆዩም፡፡ ይሰለቻቸዋል፡፡ ወንድ አስቀድሞ ምን ምን ለመግዛት ወደ ገበያ እንደሚሄድ ማወቅ ይፈልጋል፡፡ የትና ምን ያህል ጊዜም እንደሚፈጅ ሊያውቅ ይፈልጋል፡፡ ምክንያቱ ምንድን ነው ቢባል፣ እንደማንኛውም አዳኝ - ወንድ ቶሎ ግዳይ - ጥሎ ወደ ቤቱ ይዞ መምጣት ስለሚፈልግ ነው፡፡
ትናንሽ ወጠጤ ወንዶ ልጆች ወደ ጉርምስና እየተጠጉ ሲመጡ ለምንድን ነው ሰው የሚላቸው የማይሰሙት?
ወደ መጎርመስ ሲጠጉ የጆሮዋቸው የማዳመጫ አሸንዳ በድንገት የመወፈር ፀባይ ይፈጥራል፡፡ ይህም ጊዜያዊ ነው፡፡ ግን ጊዜያዊ የመደንቆር ችግር ያስከትላል፡፡
ወንዶች አንድ ነገር አንድ ጊዜ መስራት ነው የሚሆንላቸው፡፡ ሴቶች ደግሞ ግራና ቀኙን አይለዩም፡፡ ይህስ ለምን ይሆናል?
በወንዱ አንጎል ውስጥ ግራና ቀኙን ክፍል የሚያዝዙት የነርቭ ድሮች ቁጥራቸውን ትንሽ ነው ከሞላ ጎደል የአንጎላቸው ግራና ቀኙ እራሱን የቻለ ክፍል ነው፡፡ የሴቶች ግን ግራና ቀኙ በብዙ ድሮች የተገናኘ ነው፡፡ በዚህ ምክንያ ግራና ቀኙን ወገን አይለዩም፡፡ በዙ ነገር በአንዴ ማሰብ ይችላሉ፡፡
ወንዶች “አፈቅርሻለሁ” ብለው በአፋቸው ለመናገር የማይችሉትስ ለምንድን ነው?
ወንድ በተፈቀርኩኝ ስሜት በመገበዝ እና ከፍተኛ የፍቅር ፍላጎት /ጉጉት/ በማሳየት መካከል ያለው ልዩነት ይምታታበታል፡፡ በተጨማሪም በወሲብ ፍላጎቱ ሳቢያ አሊያም ዘር ለማፍራት በመሻቱ ምክንያት ብቻ ራሱን በቃል-ኪዳን ማሰር ያስፈራዋል፡፡ ስለዚህም አፍ አውጥቶ ማፍቀሩን አይናገርም፡፡
ለምንድ ነው? ከወዶች ይልቅ ሴቶች ብዙ ልብስ እንዲኖራቸው የሚፈልጉት?
ሴቶች ብዙ ስሜቶችና የፀባይ መለዋወጥ አመል አላቸው፡፡ ከእዚህ ጋር የሚጣጣም ቀለም ያላቸውና ፋሽን የተከተሉ ልብሶች ይፈልጋሉ፡፡ በሴት ልጅ አንጎል ውስጥ ዙሪያ - ገባውን ስሜቶቿን የሚቆጣጠሩና የሚቃኙ ክፍሎች አሉ፡፡ የወንድ ልጅ አንጎል ግን በስተቀኙ ወገን ብቻ ሁለት የቁጥጥር ማዕከሎች ናቸው ያሉት፡፡ ለዚህ ነው የወንዱን ማንነቱን በቀላሉ ለመገመት የሚቻለው፡፡ ግትርም የሚሆነው በዚህ ምክንያ ነው፡፡ በተጨማሪም ከስምንት ወንዶች መሀከል አንዱ የቀለም ዳፍንት /Color Blindness/ እንዳለበት ታውቋል፡፡