Administrator
“ቁና - እህል ጠላ ጨረስን እባካችሁ፤ ማጥለያ ስጡን”
አንድ አባ ዳካ የሚባሉ በሠፈር ባገሩ በጨዋታና በነገር አዋቂነታቸው የታወቁ አዛውንት በየጊዜው በየዕድሩ፣ በየሰንበቴውና በየድግሱ ሁሉ እየተገኙ በሚያጋጥማቸው ነገር ላይ ይተርባሉ፣ ወግ ያወጋሉ፣ ቀልድ ይቀልዳሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ሰው አባባላቸውን እየጠቀሰ፤ “አባ ዳካ እንዲህ አሉ” እያለ ይተርታል፡፡ አለቃ ገብረ- ሃና እንዲህ አሉ፡፡ ካሳ ደበሉ እንዲህ አሉ፤ እንደሚባለው መሆኑ ነው፡፡
አባ ዳካ፣ አንድ ቀን ከአንድ ሹም ጋር ተጣልተው በብዙ ጅራፍ ተገርፈው ሲመጡ ወዳጃቸው የሆነ ሰው ያገኛቸውና “ምን አርገው ነው እንዲህ የተገረፉት አባ ዳካ?” ሲል ጠየቃቸው፡፡
አባ ዳካ፣ “ያየሁትን ተናግሬ” ይላሉ፡፡
“ምን አይተው፣ ምን ተናገሩ?” ብሎ ይጠይቃቸዋል፡፡
“ትላንትና ወንዝ ወርጄ ውሃ ቀጂዎቹ እወንዙ ዳር ሆነው በብዛት ውሃ ይቀዳሉ፡፡ ይሄኔ አንድ ሹም ከሚስቱ ጋር ይመጣል፡፡ ከዚያም ሚስቱ ከሌሎቹ ውሃ-ቀጂዎች እኩል መቅዳቷ የውርደት ይመስለውና፣ በሰላም ውሃ እየቀዱ ያሉትን ሴቶች፣ “አንቺ መጀመሪያ፣ ቀጥሎ አንቺ፣ ቀጥሎ አንተ” ማለት ጀመረ፡፡
ይሄኔ እኔ በሆዴ “ወንዙ ላገር የሚበቃ ነው፡፡ ሁሉም እንደየአቅሙ መቅዳት ይችላል፡፡ አሁን ተራ ግቡ፣ በዚህ ውጡ፣ በዚህ ውረዱ፣ ማለትን ምን አመጣው? አልኩና ባካባቢዬ ላሉት ሰዎች የሀገሬ ሰው “ሹመት የለመደ፣ ወንዝ ወርዶ፣ እርስዎ ይቆዩ፣ እርስዎ ይቅዱ” ይላል አልኩኝ፡፡
ሰው ሲስቅ ሹሙ ተናደው አርባ ጅራፍ ፈረዱብኝ፡፡
ሌላ ቀን ደግሞ አባ ዳካ ብዙ ያገር ሰው የተጠራበት ሰንበቴ፣ ድግስ ሄደው ኖሯል፡፡ እዚያ የሚመገቡትን ተመግበው ሲያበቁ የሚጠጣው ጠላ ቀረበ፡፡ በመጀመሪያ ዙር የተሰጣቸው ጠላ ጉሽ ነበር፡፡
እንደምንም ብለው “እንትፍ፣ እንትፍ” እያሉ ጠጡ፡፡
ሁለተኛው ዙር መጣ፡፡ አጋፋሪው ቀዳላቸው፡፡ አሁንም ጉሽ ነው፡፡
ሦስተኛውን ደገሙ፡፡ አሁንም ጎሸባቸው፡፡ ያም ሆኖ አባ ዳካ ሞቅ እያላቸው ሄዱ፡፡
በአራተኛው፣ አጋፋሪው ሲመጣ አባ ዳካ ቀና አሉና፣
“ሰማህ ወይ አጋፋሪ?”
“አቤት አባ ዳካ፣ ምን ፈለጉ?”
አባ ዳካ ጮክ ብለው ቀጠሉ፣
“ቁና- እህል ጠላ ጨረስን፣
እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” አሉ፡፡
ተጋባዡ ሁሉ በሆዱ ይህንኑ ያስብ ኖሮ ሳቅ በሳቅ ሆነ፡፡
***
ፈረንጆች “ማንኛውም ነገር ሊቀለድበት የማይችልበት ደረጃ ሲደርስ፣ ተስፋ እየራቀ ሄደ ማለት ነው” ይላሉ፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ግን ምናልባት በተቃራኒው፣ ተስፋ የማይደረስበት ርቀት ላይ ቢሆን እንኳ ህዝቡ እንደልብ መቀለዱን፣ እንደልብ መጫወቱን፣ እንዳሻው መተረቡን አይተውም ማለት ይቀላል፡፡ እንደነሩሲያ፣ እንደነሩማኒያ፣ መራር ቀልድ ለመቀለድ የሚችል ሕዝብ ነው፡፡ ቻይናውያን እንደሚሉት “እሳተ-ገሞራ ላይ ሆኖም በራሱ ላይ አነጣጥሮ የሚቀልድ እውነተኛ ኮሜዲያን” ነው፡፡ አባ- ዳካ አንዱ ምሳሌ ናቸው፡፡ አንዳንዴ እንደ አባ ዳካ ያሉ ሰዎች ባይኖሩን ምን ይውጠን ነበር? ያሠኛል፡፡ መራር ቀልድ የሚቀልዱ ሰዎች ማግኘት መታደል ነው፡፡
የሀገራችን የፖለቲካ መንገድ ሁሌም ረዥም ነወ፡፡ ደረጃው ይለያይ እንጂ ወጣ ገባም፣ መራራም ነው፡፡ የፖለቲካ መንገደኞቹ ደግሞ በብዛት ረዥም መንገድ ተጓዥ ሆነው አይገኙም፡፡ ወይ የንድፈ-ሀሳብ ስንቅ ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ የልምድ መዳበርና መሰናዶ ያንሳል፡፡ ወይ በቀና አመለካከት የታነፁ አባላት ይጎድላቸዋል፡፡ ወይ በትግሉ ጥልቀትና ጠመዝማዛ ርቀት ላይ ያለው አስተውሎት ደብዛዛ ይሆናል፡፡ ወይ በሰርጎ-ገብ፣ ወይ በአድርባይ፣ ወይ ባለሁሉ-አለሁ ባይ፣ ወይ በዕውቀት የበታችነት ስሜት፣ አሊያም በአመለካከት የበላይነት ጫና፣ በየጊዜው ውጥረት ውስጥ ሲገቡ ይታያል፡፡ አጠቃላዩ የፖለቲካ አየር ሁሌ በተለመደና ተደጋጋሚ ውጥረት ውስጥ መግባቱ አስገራሚ ነው፡፡ እርግጥ የፖለቲካው ሀይል የስበት ማእከል በጋለ ሙቀት በተከበበ ቁጥር የተቃራኒ ሀይሎች ፍትጊያ ሰበቃ አይቀሬ ነው፡፡ በዚህ ሰበቃ ውስጥ እየተሸረፈ የሚወድቅ፣ እየተፈረካከሰ የሚበተን፣ እንደ ባቡር ፉርጎ የሚጎረድ፣ እንደ ባህር ጨው ሟሙቶ የሚቀር መኖሩ፣ ያለ፣ የነበረና የሚኖር ነው፡፡ ይህ ሀቅ ገዢ ተገዢ ሳይል በየፓርቲው ላይ ሁሉ ሲከሰት የሚታይ ነው፡፡ ዋናው ነገር ግን የዚህ ሁሉ መጨረሻ አገር ወዴት እያመራች ነው? ህዝቡስ ምን ፋይዳ እያገኘ ነው? የሚለው ጥያቄ ነው፡፡ ይህን ጥያቄ ለአፍታም አለመዝለል ያሻል፡፡
በሀገራችን ከ1960ዎቹ ጀምሮ በመንግሥት ውስጥም ሆነ ውጪ ብዙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል፡፡ ዛሬም ብዙ የፖለቲካ ፓርዎች አሉ፡፡ የዱሮዎቹ በተለይ ተቃዋሚዎቹ፣ ጥቂትና በህቡዕ (በሚሥጥር) የተደራጁ ሲሆኑ፣ የአሁኖቹ በአደባባይ ሰው አውቋቸው፣ ፀሐይ ሞቋቸው የተቋቋሙና ብዙ መሆናቸው ነው፡፡ በሁለቱም ዘመን፣ በጋራ የምናየው ብርቱ ጉዳይ፣ አንዱ በሌላው ፓርቲ ወይም ቡድን ውስጥ በታኝ ሃይል ማስረጉ ነው፡፡ ያህያ ቆዳ ለብሰህ ጅብን ውጋ፣ አሊያም የበግ ለምድ ለብሰህ ተኩላ ነኝ በል፣ ነው ነገሩ፡፡ ሌላው ክስተት፣ ለብዙኃን ዲሞክራሲ ተገዢ አለመሆን፣ የመሰነጣጠቅ አደጋ፣ የግትር እምቢተኝነት ጠባይ፣ በፊት ለፊት እምቢ ሲል በጓሮ መሄድ፣ በማላተም እምቢ ሲል፤ በማጠቋቆም መጠቀም፣ በምክክር ሲያቅት በሸር፣ በረድፈኝነት ሲያቅት በአንጀኝነት፣ በድቁና ሲያቅት በሙስና፣ በማስፈራራት ሲያቅት በመቅጣት፣ በመሞዳሞድ ሲያቅት በማዋረድ፣… መጓዝ ነው፡፡
እነዚህ ሁሉ የፖለቲካ ፈሊጦችና አካሄዶች አገሪቱ ባለችበት እንድትረግጥ አሊያም የኋሊት እንድትንሻተት ማድረጋቸውን ልብ አለማት፣ ክፉ የጥፋት አባዜ ነው፡፡ ነገ ከነግወዲያ ለሀገርና ለህዝብ ምን ፈየድኩ? ሲባል በእኩይነታችን ማፈር፣ በውድቀታችን መፀፀት ይሆናል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶች፣ በተለይም ጠንካራ ተቃዋሚ ድርጅቶች መኖር፣ ለዲሞክራሲያዊ ሁኔታዎች ማበብ ወደድንም ጠላንም እርሾ ነው፡፡ ያለእነዚህ ድርጅቶች የህዝቦችን ፍላጎት ማንፀባረቅና ማርካት ምኞት ብቻ ነውና፡፡ በእርግጥም አንዴ የትግል አምባ ከተወጣ ድካሙን፣ ሥቃዩን፣ ውጣ ውረዱን፣ አታካችነቱን፣ በተደጋጋሚ ሊያጋጥም የሚችለውን እልህ- አስጨራሽ ፈተና መቀበል አሌ የማይባል የጉዞው አካል ነው፡፡ ይህ ግን ገና ትግልን ሲጀምሩ መጤን ያለበት የትግሉ ሥጋና ደም ነው፡፡ ትግልን ረዥምና እሾሃማ የሚያደርገውም ይኸው ነው፡፡ ዲሞክራሲያዊና ሰብዓዊ መብትን ማስከበር፣ ፍትሐዊ ሁኔታን መፍጠርና ሰላምን መጎናፀፍ የአንድ ጀምበር ተግባር አይደለም የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ ዐይንን ከፍቶ ክፉና ደጉን መለየት፣ ነገሮች ሲጎሹ ሳይደናገጡ ማጥራት፣ ለዲሞክራሲያዊ ሂደት ሠናይነት እጅግ ወሳኝ ነው፡፡ “ቁና-እህል ጠላ ጨረስን፤ እባካችሁ ማጥለያ ስጡን” የሚባለው ተረትም ይህንኑ የሚያፀኸይ ነው፡፡
የአማራ ክልል እየተፈጸሙ ያሉ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያስቆም ተጠየቀ
የአማራ ክልል መንግስት፣ በክልሉ በታጠቁ ኃይሎች እየተፈጸሙ ያሉ ከፍተኛ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን እንዲያስቆም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ጉባዔ (ኢሰመጉ) ጠየቀ። ኢሰመጉ ባወጣው መግለጫ፤ በአማራ ክልል ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚፈጸመው እስር መቀጠሉንና የሚያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት እንደማይቀርቡ አስታውቋል።
ተቋሙ ባለፈው ረቡዕ ጥቅምት 27 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው በዚህ መግለጫ፤ አማራ ክልልን ጨምሮ በሌሎች ክልሎች ተፈጽመዋል ያላቸውን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በዝርዝር ያቀረበ ሲሆን፣ በአማራ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በርካታ ሰዎች መገደላቸውን አመልክቷል። በክልሉ እየተካሄደ ባለው ግጭት ሳቢያ፣ ጥቅምት 17 ቀን 2017 ዓ.ም. በአዊ ዞን፣ አዲስ ቅዳም ከተማ በመንግስትና በተለምዶ ፋኖ በመባል በሚታወቁ የታጠቁ አካላት መካከል ውጊያ ከተደረገ በኋላ፣ የመንግስት የጸጥታ ሃይሎች “የፋኖ ደጋፊ ናችሁ” በሚል በየቦታው ያገኟቸዉን አረጋውያንን ጨምሮ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን ሰዎችን ከሕግ አግባብ ዉጭ ግድያ እንደፈጸሙባቸው ኢሰመጉ ጠቅሷል።
ጥቅምት 18 ቀን 2017 ዓ.ም. ምሽት አካባቢ ባሕር ዳር ከተማ፣ ቀበሌ 07 በሚገኘው ሃን ጤና ጣቢያ ተቀጥራ ከ30 ዓመት በላይ ስትሰራ የነበረች ሴት የጤና ባለሙያ፣ ከመንግሥት የጸጥታ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት እንደተገደለች ያመለከተው ኢሰመጉ፤ “ጥቅምት 21 ቀን 2017 ዓ.ም. በደቡብ ጎንደር ዞን ከጋሳይ ወደ ጉና በጌምድር [ክምር ድንጋይ] ተሳፋሪዎችን ጭኖ ሲጓዝ የነበረ የሕዝብ ማመላለሻ መኪና፣ ከመኪናው ራስ/ፖርቶ መጋላ ላይ ተሳፍረው ሲሄዱ የነበሩ ሰዎች በታጠቁ ሃይሎች በተተኮሰ ጥይት ሁለቱ ተሳፋሪዎች ሲገደሉ፣ አንድ ተሳፋሪ ላይ ደግሞ ከፍተኛ የአካል ጉዳት መድረሱን ለማወቅ መቻሉን ገልጿል፡፡
ከዚህም በተጓዳኝ በክልሉ ያለፍርድ ቤት ትዕዛዝ የሚደረገው እስር እንደቀጠለና የሚያዙ ሰዎች ፍርድ ቤት እየቀረቡ አለመሆኑን ኢሰመጉ አስታውቋል፡፡
ኢሰመጉ በመግለጫው ላይ ለአማራ ክልል መንግስት፣ በመንግስት የጸጥታ ሃይልና በታጠቁ አካላት እየተፈጸመ ያለውን ከፍተኛ የሆነ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰቶችን በቂ ትኩረት በመስጠት እንዲያስቆምና ዜጎቹን የመጠበቅ ሃላፊነቱን በአግባቡ እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።
አምነስቲ ኢንተርናሽናል በበኩሉ፣ በመከላከያ ሰራዊትና በአማራ ክልል የጸጥታ ሃይሎች አማካኝነት ከአንድ ወር በላይ ለእስር የተዳረጉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በአፋጣኝ እንዲለቀቁ ጠይቋል። የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ ከመስከረም ወር ጀምሮ አደረግሁት ባለው ማጣራት፣ በክልሉ በአራት ጊዜያዊ የማቆያ ስፍራዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ገልጿል።
የሰብዓዊ መብት ተሟጋቹ፣ ከጊዜያዊ የማቆያ ጣቢያዎቹ የወጡ ሁለት ሰዎችን፣ አምስት የታሳሪ ቤተሰቦችንና ዘጠኝ ከጅምላ እስሩ ጋር በተያያዘ በስልጣን ላይ ያሉ ሰዎችን ማነጋገሩን አመልክቷል። በዚህም በዳንግላ፣ ሰራባ (ጭልጋ)፣ ኮሪሳ (ኮምቦልቻ) እና ሸዋሮቢት በተዘጋጁ ጊዜያዊ ጣቢያዎች በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአንድ ወር በላይ በእስር ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጡን ነው የጠቆመው።
አምነስቲ በሪፖርቱ በአራት ከተሞች በሚገኙ ጊዜያዊ ካምፖች የታሰሩት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የተሃድሶ ስልጠና ወስደው ካጠናቀቁ በኋላ፣ “ይለቀቃሉ” መባሉን ከታሳሪ ቤተሰቦች መስማቱን ገልጿል።
”በትግራይ 1 ሚ.የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም“
በትግራይ ክልል ወደ አንድ ሚሊዮን የሚጠጉ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው አልተመለሱም ሲል የኢትዮጵያ ሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መቐለ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ። እነዚህ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው ያልተመለሱት የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ነው ብሏል፡፡
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ ሃላፊ የሆኑት አቶ ጸሐዬ እምባዬ ለክልሉ መገናኛ ብዙሃን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ፤ ከ970 ሺ በላይ በክልሉ ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች የፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ ባለመደረጉ ወደ ቀያቸው አለመመለሳቸውን አመልክተው፣ በረሃብና በሽታ ምክንያት ሕይወታቸው የሚቀጠፍ ተፈናቃዮች ቁጥር እየጨመረ መጥቷል ብለዋል። አያይዘውም፣ ተቋማቸው ባደረገው ጥናት መሰረት፤ ለተፈናቃዮቹ የሚቀርበው እርዳታ በአግባቡ እየተዳረሰ አለመሆኑን ጠቅሰዋል።
ሃላፊው በሰላም ስምምነቱ “ይመለከታቸዋል” ተብለው ለተጠቀሱት አካላት ባቀረቡት ጥሪ፣ በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት ተፈናቃዮች ወደ ቀድሞ ቀያቸው እንዲመለሱ ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ ተማጽነዋል።
የቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቱ የሴቶችና ሕጻናት ክፍል ሃላፊ አቶ ሃፍታይ አሰፋ በበኩላቸው፤ ከሰብዓዊ ዕርዳታ አቅርቦት እጥረት ባሻገር ተፈናቃዮቹ መሰረታዊ መብቶቻቸውን በመነፈጋቸው ሳቢያ፣ ለሞትና እንግልት እየተዳረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። በሽረ እንዳስላሰ ከተማ ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል 42 ሺ ያህሉ መሰረታዊ ዕርዳታ ያላገኙ ሲሆኑ፣ ከ78 ሺ በላይ የሚሆኑት ደግሞ፣ ንጹህ ውሃ እንደማያገኙ ሃላፊው ጠቅሰዋል።
በሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም የተሰራው ጥናት እንደሚያመለክተው፣ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነትም በኋላ የእርዳታ አቅርቦት በቂ አይደለም።
አገልግሎት አሰጣጥ ድክመት አንጻር ለመንግስት ሰራተኞች የ17 ወር ደመወዝ አለመከፈልና ሌሎች ምክንያቶች እንደ መንስዔ እንደሚጠቀሱ ተቋሙ አመልክቷል። የሕዝብ ዕንባ ጠባቂ ተቋም፣ መቐለ ቅርንጫፍ፣ ከፕሪቶሪያው ስምምነት በኋላ የሚቀርቡለት ቅሬታዎች በርካታ መሆናቸውንም ጠቁሟል፡፡
የኢትዮጵያ አማካይ የዋጋ ንረት 25 በመቶ እንደሚሆን ተገለጸ
በዚህ ዓመት የኢትዮጵያ አማካይ የዋጋ ንረት 25 በመቶ እንደሚሆን ዓለም አቀፉ የገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ገልጿል። ድርጅቱ የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ባንኮች ላይ የጣለውን አስገዳጅ የ20 በመቶ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ “ያነሳል” ሲል አመልክቷል።
አይኤምኤፍ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር የተራዘመ የብድር አቅርቦትን በተመለከተ ያደረገውን ስምምነት የሚዳስስ የመጀመሪያ ዙር አጠቃላይ ሪፖርት ባለፈው ሰኞ ጥቅምት 25 ቀን 2017 ዓ.ም. ይፋ አድርጓል። ኢትዮጵያ አገር በቀል የምጣኔ ሃብት ፖሊሲ ማሻሻያን ጨምሮ በገበያ ስርዓት ላይ የተመሰረተ የውጭ ምንዛሪ ግብይት ተመንን ተግባራዊ ማድረጓ የሚበረታታ እንደሆነ የድርጅቱ የስራ አመራር ቦርድ በሪፖርቱ አስታውቋል።
የኢትዮጵያ መንግስት የፋይናንስ ስርዓቱን ዋስትና ለማረጋገጥ እየተገበራቸው የሚገኙት የማስተካከያ ጥረቶች ከአይኤምኤፍ የፖሊሲ መስፈርቶችና የፕሮግራም መመዘኛዎች ጋር መጣጣም እንደሚገባቸው ድርጅቱ አሳስቧል፡፡ የአይኤምኤፍ ምክትል ማኔጂንግ ዳይሬክተርና የቦርዱ ሰብሳቢ ቦ ሊ የኢትዮጵያ መንግስት በብሔራዊ ባንክ አማካይነት ሲያደርጋቸው የቆዩትን በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ የሚደረጉ ጣልቃ ገብነቶች የመቀነስ ተግባራት አጠናክሮ መቀጠል “አለበት” ብለዋል።
“ቀጣይነት ያለው እና ጥብቅ የሆነ የገንዘብ ፖሊሲ፣ እንዲሁም የመንግስት የበጀት ጉድለቶችን ለመሸፈን የሚደረጉ የገንዘብ ድጎማዎች ማስወገድን ጭምሮ ጥንቃቄ የተሞላባቸው የማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲዎች መተግበራቸው በኢኮኖሚው ላይ የሚከሰቱ የሚዛን መዛባቶችን ለመቀነስ እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማምጣት አስፈላጊ ናቸው።” ብለዋል፣ የቦርዱ ሰብሳቢ።
በተጨማሪም የኢትዮጵያ መንግስት በንግድ ባንኮች ላይ የጣለውን አስገዳጅ የ20 በመቶ የግምጃ ቤት ቦንድ ግዥ በሰኔ ወር 2017 ዓ.ም. ሙሉ በሙሉ እንደሚያነሳ አይኤምኤፍ ማረጋገጡን በሪፖርቱ ላይ ጠቅሷል፡፡ በተቃራኒው ደግሞ በ2017 ዓ.ም. ሁሉም ባንኮች ከሚፈጽሙት አስገዳጅ የቦንድ ግዥ በአጠቃላይ 55 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ማቀዱን መንግስት ለአይኤምኤፍ መግለጹ ተጠቁሟል፡፡
አይኤምኤፍ ይፋ ባደረገው በዚህ ሪፖርት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ በዋና ዋና የኢኮኖሚ አመላካቾች ሲታይ የሚኖረው የዕድገት ሁኔታ ምን እንደሚመስል ያመላከተ ሲሆን፣ “ዕውነተኛ የአገራዊ ጥቅል ምርት ዕድገት” በተሰኘው መስፈርት መሰረት ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በ2024/25 የሚኖራት ዕድገት 6 ነጥብ 5 በመቶ እንደሚሆን ተገምቷል። በተጨማሪም፣ የአገሪቱ አማካይ የዋጋ ንረት 25 በመቶ “ይሆናል” ሲል ድርጅቱ ግምቱን አስቀምጧል፡፡
አይኤምኤፍ በመስከረም ወር 2017 ዓ.ም. መጀመሪያ ላይ ኢትዮጵያ ከኢኮኖሚ ማሻሻያው በኋላ ያለችበትን አጠቃላይ ሁኔታ ከገመገመ በኋላ፣ “ጥብቅ የሆኑ የገንዘብ ፖሊሲዎች እንዲቀጥሉ” የሚል የመጀመሪያ ዙር መግለጫ መስጠቱ ይታወሳል። ይህን ተከትሎ የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ ጥብቅ የሆነውን የገንዘብ ፖሊሲ ኢትዮጵያ “ታስቀጥላለች” የሚል መግለጫ ሰጥተው እንደነበር አይዘነጋም።
“ፕሬዚዳንት እንድሆን በተደጋጋሚ ብጠየቅም ጥያቄውን አልተቀበልኩም”
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ምክትል ፕሬዚዳንት ጄኔራል ጻድቃን ገብረትንሳዔ “ፕሬዚዳንት እንድሆን በተደጋጋሚ ብጠየቅም ጥያቄውን ግን አልተቀበልኩም” ሲሉ ተናገሩ። ጄኔራል ጻድቃን፤ የትግራይ ሕዝብ በተመረጠለት ሳይሆን በመረጠው መሪ መተዳደር ይገባዋል ብለው እንደሚያምኑ ጠቁመዋል፡፡
ባለፈው እሁድ ጥቅምት 23 ቀን 2017 ዓ.ም. በመላው ዓለም ከሚገኙ የዲያስፖራ ማሕበረሰብ አባላት ጋር በበይነ መረብ ውይይት ያደረጉት ጄኔራል ጻድቃን፣ ለተለያዩ ሃሳቦች ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፣ ለቀረቡላቸው ጥያቄዎችም ምላሽ ሰጥተዋል።
በዚህ ውይይት ላይ ጄኔራል ጻድቃን፣ የብሔራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዳይሬክተር ጄኔራል አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ፣ የጦር ሃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በኬንያ ናይሮቢ እንዲሁም በሃላላ ኬላ ተገኝተው በነበሩበት ወቅት የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት እንዲሆኑ ጥያቄ እንዳቀረቡላቸው አስታውሰው፤ “‘እኔ ግን የትግራይ ሕዝብ ሲመርጠኝ እንጂ እናንተ በትግራይ ሕዝብ ላይ እንድትሾሙኝ አልፈቅድም። ይህ ለትግራይም፣ ለታሪኬም የሚመጥን አይሆንም’ የሚል መልስ ሰጠኋቸው።” ብለዋል።
በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ባለስልጣናቱ ለአቶ ጌታቸው ረዳ በተደጋጋሚ ተመሳሳይ ሃሳብ ያቀርቡላቸው እንደነበር ያወሱት ጄኔራሉ፣ በአሜሪካ በኩልም ይኸው ፍላጎት ሲንጸባረቅ መቆየቱንና እርሳቸው ግን ፍላጎቱ እንዳልነበራቸው አስረድተዋል። “ዶክተር ደብረጽዮን ‘በረሃ ሳለን፣ እኔን ከስልጣን ለማንሳት ፈልጎ ነበር’ ሲሉ የተናገሩት ነገር የሚያሳዝን ነው። ሰራዊታችን ከተበታተነ በኋላ ‘እንደገና ተደራጅተን እንዴት ትግሉን እናስተባብር?’ ብለን መከርን። ዶ/ር ደብረጽዮን የውጭ፣ እኔ ደግሞ የአገር ውስጥ ትግሉን ለማስተባበር ተመረጥን። ይህንን ነው ዶ/ር ደብረጽዮን ‘ከስልጣን ለማንሳት ፈልጎ ነበር’ በማለት ሊገልጹ የፈለጉት።” ሲሉ ያስረዱ ሲሆን፣ አክለውም፤ “እኔ ሕዝቤን ለማገዝ እንጂ የሆነ ስልጣን በአቋራጭ ለመውሰድ ዓላማ የለኝም። ስልጣን ለማግኘት የፕሪቶሪያ፣ የናይሮቢና የሃላላ ኬላ እንዲሁም ሌሎች አጋጣሚዎች ነበሩ። ይህ ግን ከዓላማዬና ከሰብዕናዬ ጋር የሚሄድ ስላልሆነ አላደረግሁትም።” ብለዋል፡፡
“ውስጣዊ ችግራችንን ከፈታን፣ የውጭ ችግሮቻችንን ለመፍታት ብዙም አንቸገርም” ያሉት ጄኔራል ጻድቃን፤ የትግራይ ሕዝብ ከላይ በተመረጠለት ሳይሆን ራሱ በመረጠው መሪ መተዳደር እንደሚገባው በአጽንዖት ተናግረዋል፡፡ ትእምት (EFFORT) የትግራይ ሕዝብ በመሆኑ ድርጅቱ ወደ ዋና ባለቤቱ፣ ወደ ትግራይ ሕዝብ ሊዘዋወር እንደሚገባ በውይይቱ ላይ አንስተዋል።
ከተፈረመ ሁለት ዓመታትን ያስቆጠረው የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት በውስጡ ያሉትን ዕድሎች በአግባቡ ከተጠቀምንባቸው፣ ከገባንበት ችግር በፍጥነት እንወጣለን ብለዋል፣ ጄኔራል ጻድቃን።
ነገረ መጻሕፍት!
ነገ ቅዳሜ ጥቅምት 30 2017 ዓ.ም ከቀኑ 8:00 ጀምሮ ምኒልክ ሆስፒታል አካባቢ በሚገኘው "FSS" አዳራሽ ውስጥ ይካሄዳል።
የፕሮግራሙ አዘጋጅና አቅራቢ ደራሲ እንዳለጌታ ከበደ ነው።
ሰባራ ጥላ
ቅዳሜ ጥቅምት 30 አመሻሽ ላይ ከ( 10:00 ) ጀምሮ አብዬ በርሶማ አንጋፋ እና ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች በክብር እንግድነት በተጋበዙበት መድረክ በብሔራዊ ቤተ መዛግብት እና ቤተ መጽሐፍት አገልግሎት(ወመዘክር) ሥራውን ያቀርባል።
መንታ ፍቅር
መንታ ፍቅር:: አዲስ አስገራሚ: ግራ እያገባን እየሳቅን ዋሽንግተን እና እዲስ አበባ የምንመላለስበት ፊልም:: አርብ ፡ ጥቅምት 29:በ 8: በ10: በ1 ሰዓት:: ቅዳሜና እሁድ በ8: 10: 12 ሰአት ተጋብዘዋልና ይምጡ !