Administrator

Administrator

መኪና ሲያሽከረክሩ የተያዙ ሁለት የሳኡዲ ሴቶች ለአንድ ወር ገደማ ከታሰሩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ጉዳያቸው ሽብርተኝነትን ለሚመለከት ልዩ ፍ/ቤት እንደተላለፈ ተገለፀ፡፡
የ25 ዓመቷ ሎዩጄይን አል ሃትሎል እና የ33 ዓመቷ ማይላ ይሳ አል - አሙዲ ጉዳይ ወደ ልዩ ፍ/ቤት የተላለፈው በማህበራዊ ሚዲያ ላይ በሰጡት አስተያየት ነው ብለዋል - የመብት ተሟጋቾች፡፡ ሳኡዲ በዓለም ላይ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የምትከለክል ብቸኛ አገር ናት፡፡
ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ በፅሁፍ የተቀመጠ ህግ ባይኖርም የመንጃ ፈቃድ የሚሰጠው ግን ለወንዶች ብቻ ነው፡፡ ሴቶች በአደባባይ ሲያሽከረክሩ ከተገኙም በፖሊስ ተይዘው ከመታሰርም ባሻገር ይቀጣሉ፡፡
የሳኡዲ ሴቶች መኪና እንዳያሽከረክሩ የተጣለባቸው እገዳ እንዲነሳላቸው ማህበራዊ ሚዲያን ጨምሮ የተለያዩ ተከታታይ እንቅስቃሴዎች ሲያካሂዱ ቆይተዋል፡፡
አዣንስ ፍራንስ ፕሬስ የዜና ወኪል እንደዘገበው፤ ሚስ ሃትሎል የተያዘችው ከጐረቤት አገር፣ ዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ እያሽከረከረች ወደ ሳኡዲ ለመግባት ስትሞክር ነው፡፡
ነዋሪነቷን በዩናይትድ አረብ ኢምሬትስ ያደረገችው የሳኡዲ ጋዜጠኛ ሚስ አላሙዲም የተያዘችው ሚስ ሃትሎልን ለመርዳት ድንበር ላይ ስትደርስ ነው ብሏል - የዜና ወኪሉ፡፡
ሁለቱም ሴቶች በትዊተር እጅግ በርካታ ተከታይ ያሏቸው ሲሆን ሚስት ሃትሎል ወደ አገሪቱ ለመግባት አንድ ቀን ሙሉ ያችውን ውጣ ውረድ በትዊተር ገጿ ላይ እንዳሰፈረች ተዘግቧል፡፡ ባለፈው ሐሙስ በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል የሚገኘው አል - አህሳ ፍ/ቤት፤ የሁለቱ ሴቶች ጉዳይ በሪያድ የሽብርተኝነት ክሶችን ለመከታተል በተቋቋመው ልዩ ፍ/ቤት እንዲዳኙ በይኗል፡፡ የሴቶቹ ጠበቆች ግን ይግባኝ ለመጠየቅ ማሰባቸውን የመብት ተሟጋቾች ለአዣንስ ፍራንስ ፕሬስ ጠቁመዋል፡፡

     በደራሲ ሐማቱማ “The case of the Socialist witchdoctor” በሚል ርዕስ ተፅፎ በህይወት ታደሰ “የሶሻሊስቱ ጠንቋይ ጉዳይ” በሚል ወደ አማርኛ የተመለሰው መፅሃፍ ለንባብ በቅቷል፡፡ የተለያዩ በርካታ ታሪኮች ስብስብ የሆነው ይሄው መፅሃፍ፤ በአንድ ሶሻሊስት ጠንቋይ ላይ ያተኮረ ታሪክ የያዘ ሲሆን ሌሎችም አስገራሚ ፖለቲካዊ ታሪኮችን አካትቷል፡፡ መፅሃፉ በ307 ገፆች የተቀነበበ ሲሆን በ50 ብር ከ65 ሳንቲም ለገበያ ቀርቧል፡፡

 “የዘንድሮ ትዳሮች” በሚል ርዕስ በመቅደስ በቀለ (ማክዳ) ተፅፎ በእርከን ቢዝነስ ዲቨሎፕመንት አሳታሚ የታተመው መፅሐፍ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ በቅርቡም ይመረቃል ተብሏል፡፡
በመፅሀፉ የዘንድሮ ትዳሮችን ጨምሮ ሌሎች እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሰረቱ ከ15 በላይ አጫጭር ልቦለዶች እንደተካተቱበትና በ200 ገፆች ተሰናድቶ በ60 ብር ለገበያ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የመፅሃፉ ደራሲ መቅደስ በቀለ (ማክዳ) የበርካታ ፊልሞች ደራሲና ዳይሬክተር ስትሆን “የዘንድሮ ትዳሮችና ሌሎች” ሁለተኛ መፅሃፏ መሆኑ ታውቋል፡፡ ደራሲዋ ከዚህ ቀደም “የፍቅር መስዋዕት” የተሰኘ መፅሃፍ አሳትማለች፡፡

የገጣሚ የሺመቤት ካሳ “አመሻሽ” የግጥም መድበል ሰሞኑን በ25 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
የግጥም መድበሉ 62 አጫጭርና ረጃጅም ግጥሞች የተካተቱበት ሲሆን ገጣሚዋ ማስታወሻነቱን ለቀደምት ደራሲያንና ለነገው ደራሲያን ማድረጓን አስታውቃለች፡፡

የደራሲ ስንዱ አካልነህ “ኤል-ማጐት” የተሰኘ የረዥም ልቦለድ መፅሃፍ እየተነበበ ነው፡፡
በጐንደር ማተሚያ ድርጅት ታታሞ ለገበያ የቀረበው መፅሃፉ መቼቱን በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ያደረገ መሆኑን ለማወቅ ተችሏል፡፡ መፅሃፉ በ75 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡

በጋዜጠኛና ደራሲ አሰግድ ሀምዛ ተፅፎ የታተመው “በህይወት መስኮት” የተሰኘ መፅሃፍ ዛሬ በሀዋሳ ከተማ ይመረቃል፡፡ መፅሃፉ፤ ወጎችና የፍቅር ደብዳቤዎችን ያካተተ ሲሆን ደራሲው በመምህርነት ባገለገለበት ሙርሲ ብሔረሰብ ውስጥ የታዘበውንና የኖረውን እውነታ በሚጥም ቋንቋና ውበት ፅፎታል፡፡
141 ገፆች ያሉት መፅሀፉ ዛሬ ሲመረቅ፣ የዘርፉ ምሁራን አስተያየት የሚሰጡ ሲሆን በስነ ስርዓቱ ላይ የጥበብ አፍቃሪዎችና ቤተሰቦች እንደሚታደሙ ታውቋል፡፡ መፅሃፉ አገር ውስጥ በ40 ብር፣ በውጭ አገር በ8 ዶላር እንደሚሸጥ ተገልጿል፡፡

እንዴት ሰነበታችሁሳ!
ሰውየው አእምሮ ሀኪም ዘንድ ይሄድና…“ዶክተር፣ መጥፎ ተግባራት እየፈጸምኩ ህሊናዬ እየረበሸኝ ነው…” ይለዋል፡፡
ዶክተሩም… “እና መጥፎ ድርጊት ከመፈጸም የሚከላከል ህክምና እንዳደርግልህ ነው የምትፈልገው?” ይለዋል፡፡ ሰውየውም… “አይደለም…”  ይላል፡፡
ዶክተሩም… “ታዲያ ምን ፈልገህ መጣህ?” ይለዋል፡፡
ሰውየው ምን ቢል ጥሩ ነው…“ህሊናዬን ከሥሩ ነቅለህ አውጣልኝ!”
‘አልሰሜን ግባ በለው’ አሉ…እኛ ዘንድ ቢመጣ ህሊና እያለም እንዴት ‘ህሊናቢስ’ መሆን እንደሚቻል ‘በስምንተኛ ዲግሪ’ ደረጃ እናሰለጥነው ነበር፡፡ የምር ግን የህሊና ነገር እኮ እኛ አገር የሆነች ተረስታ ከአሮጌ አንሶላ ጋር የተጠቀለለች ነው የምትመስለው፡፡  
እናላችሁ…“ትንሽ ህሊና እንኳን የለህም!” ብሎ አማረኛ ቀረ፡፡ ህሊና የሰው ስም ብቻ የሚመስለን እየበዛን ነዋ! (“ህሊና ቢኖረኝ እዚህ አገር ታገኙኝ ነበር ወይ…” ያልከን ወዳጃችን በእግርህ አስነካኸው እንዴ!)
እኔ የምለው…እንግዲህ ጨዋታን ጨዋታ ያነሳው የለ…ነገርየው እንዴት ነው…‘ጉልቤ’ ነገሮች በዙብና! ልክ ነዋ…ጉልቤነት ማለት እኮ የግድ ‘አገጭ ማጣመም’፣ ጥርስን ‘በመሀረብ ማስቋጠር’ ምናምን ማለት ብቻ አይደለም፡፡ የዘንድሮ ‘ጉልቤነት’… አለ አይደል…መአት መልክ አለው፡፡
እንግዲህ ጨዋታም አይደል…ይቺን ስሙኝማ…የሆነ ሚኒባስ ታክሲ ላይ ያየነው ‘ጥቅስ’ ነው…‘ጥቅሱ’ ምን ይል መሰላችሁ… (ምንም ደስ ባይልም መነገር አለበት፣) “አፍህን ከምትከፍት ሱቅ ክፈት” ይላል፡፡
እናላችሁ…እንዲህ አይነት በህዝብ መገልገያ ላይ ከእግር ጥፍር እስከ ራስ ጸጉር ‘ሙልጭ የምንደረግበት ዘመን ላይ ደርሰንላችኋል፡፡ የምር ግን… እንደዚህ አይነት ነገር መጀመሪያ ስናይ ፈገግ እንደ ማለት ይቃጣናል፡፡ ግን… እኛም ተሰዳቢዎች መሆናችን ሲገባን…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
ምን መሰላችሁ…‘የቤትሽን ዓመል እዛው’  ‘አትንጣጪ’ ምናምን ሲባል ዝም ተብሎ ተከረመና አሁን ደግሞ “አፍህን አትክፈት…” ወደ መባል ደርሰናል፡፡
የምር እኮ…ነገርየው በዚሁ ከቀጠለ …ቀስ ብሎ…በአንድ ወቅት እዚች ዋና ከተማችን ጎራ ያለ የገጠሩ ሰውዬ… “አዲስ አበባ ገዳይ ጠፋ እንጂ ሟች ብዙ ነበር!”  ያለበት አይነት ስድብ ነገ ተነገ ወዲያ የማይለጠፍበት ምክንያት የለም፡፡ እነማ…እንደዚህ አይነት ነገር ሲበዛብን፣
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
የምር አስቸጋሪ ጊዜ ነው፡ የደንብ ልብስ የለበሱ በከተማው ጎዳናዎች በበዙበት ጊዜ፣ ማስቲካና መፋቂያ ሻጮች ሲሯሯጡ በምናይበት ጊዜ… አንዳንድ አካባቢ ተረጋግቶ መገበያየት እንኳን እያስቸገረ ነው፡፡ እኔ የምለው… እግረ መንገዴን…የገበያተኛ መዋከብ ‘የደንብ ጥሰት’ ለመሆን ያንሳል እንዴ!
በቀደም መርካቶ ዕቃ ቢጤ ለማየት ወጣ ብለን… “አይ መርካቶ!”  ብለን ተመለስን እላችኋለሁ፡፡ የምር እኮ… የምንጣፍ ሱቆች በበዙበት አካባቢ መራመድ እስኪያቅታችሁ ድረስ ትከበባላችሁ፡፡  ‘የደላላው’ ብዛት! የሆነ ሱቅ ውስጥ ለመግባት ስታስቡ ወጣት ደላሎች እየተከተሉ… “መጋዘኑ እዛ’ጋ ነው፣ ቅናሽ አለው…” “እዛ ሱቅ ያለው አሪፍ ነው…” ምናምን እየተባለ እስኪሰለቻችሁ ድረስ የሚቀባበሏችሁ ወጣቶች ብዛታቸው… አለ አይደል… ያበሳጫል ብቻ ሳይሆን ‘ያስፈራል’ ቢባል ማጋነን አይሆንም፡፡
እንግዲህ ይህ ሁሉ ሲሆን በአካባቢው የደንብ ልብስ የለበሱ ሰዎች ውር፣ ውር ይታያሉ— የሚያስጥል የለም እንጂ፡፡ እናላችሁ… ገበያተኛ ሲጉላላ፣ ደንብ አስከባሪውም ዝም፣ ነጋዴውም ዝም፣ ሁሉም ዝም ሲሆን… አለ አይደል…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንላለን፡፡  
ስሙኝማ…እንግዲህ ጨዋታም አይደል…እዚህ አገር መድረክ ላይም ‘ሙልጭ’ ተደርጎ መሰደብ እየተለመደ ነው፡፡ መጀመሪያ ሰብሳቢው…“መሀላችን የተሰገሰጉ የራሳቸው ዓላማ ያላቸው…” ምናምን እያለ ‘ሆረር’ ምናምን ነገር ይለቅባችኋል፡፡
‘አስተያየት ሰጪው’ ተነስቶ… “በተባለው ላይ የምጨምረው የለኝም…” ይልና  “ዕድገታችንን ለመግታት የሚፍጨረጨሩ አንዳንድ የስብሰባው ተካፋዮች ላይ እርምጃ ለምን እንደማይወሰድ…” በቁጭት ይጠይቃል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን እከሌ፣ እከሌ ተብሎ እስካልተጠቀሰ ድረስ አንዳንድ “…የስብሰባው ተካፋዮች…” የሚለው ሁላችንንም ስለሚመለከት…አለ አይደል…
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” እንድንል ያደርገናል፡፡
አሀ… ማን በበላው ማን ‘ራዳር’ ውስጥ ይገባል! ልጄ ዘንድሮ ‘…ሁሉም እንደ የሥራው…” ምናምን የሚል አባባል፣ ‘ጥቅስ’…ነገር አይሠራም፡፡ ልጄ…ዘንድሮ ሰው ‘ባልሠራው’ የሚበላበት፣ ‘ባልሠራውም’ የሚበላውን የሚያጣበት ዘመን ነው፡፡
ይቺን ስሙኝማ…የመንገድ ግንባታ ሥራ ላይ ነው አሉ፡፡ እናላችሁ…አንዱ ሠራተኛ አካፋ አልነበረውም፡፡ ታዲያ…አለቃውን፣ “አካፋ የለኝም…” ይለዋል፡፡ አለቅየውም…“ታዲያ ምን ያነጫንጭሀል! አካፋ ከሌለህ ሥራ አትሠራ!” ይለዋል፡፡ ሰውየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው… “ታዲያ እንደ ሌሎቹ ሠራተኞች ምን ተደግፌ ልቁም?” ብሎ አረፈላችሁ፡፡
እናማ…በየቢሮው፣ በየሥራ ቦታው ‘አካፋ ተደግፈን’ የምንቆም መአት ነን፡፡
ይቺን አሪፍ ነገር ስሙኝማ…ሰውየው ለጓደኛው ሲደውል ከጀርባ ድምጽ ይሰማል፡፡ “የምን ጫጫታ ነው የምሰማው?” ይለዋል፡፡ ጓደኝየውም… “የእህቴን ልደት ዓመታዊ በዓል እያከበርን ነው…” ይለዋል፡፡ ሰውየውም ግራ ይገባዋል፡፡ “የእህቴን ልደት ዓመታዊ በዓል ብሎ ነገር ምንድነው? ወይ ልደት ታከብራለህ፣ ወይ ዓመታዊ በዓል ታከብራለህ፡፡ ሁለቱ የሚገናኙ አይደሉም…” ይለዋል፡፡
ጓደኛየው ምን ብሎ ቢመልስ ጥሩ ነው…“አይ ሞኞ…የእህቴን አሥራ ስምንተኛ ዓመት ልደት አሥራ አምስተኛ ዓመታዊ በዓል እያከበርን ነው…” ብሎት አረፈ፡፡ አሪፍ አይደል!
የዕድሜ ነገር ከተነሳ… ይቺን ስሙኝማ…“በቀደም ሀያ ዘጠነኛ ዓመቴን ሳከብር ለምንድነው ስጦታ ያልሰጠኸኝ?”  ብትለው እሱዬው… “ረሳሽው እንዴ! የዛሬ አምስት ዓመት ሀያ ዘጠነኛ ልደትሽን ስታከብሪ ሽቶ አልሰጠሁሽም?” ብሏት አረፈ፡፡
እናላችሁ…ጉልቤነት መልኩን እየለዋወጠ መከራችንን እያበላን ነው፡፡ ቤት አከራይ በቀን ሁለት ባሊ ውሀ ብቻ እየፈቀደ፣ መብራት በሦስት ሰዓት ላይ እያጠፋ፣ “ከአንድ ሰዓት በኋላ ማምሸት ክልክል ነው…” አይነት ክፉ ሚስት እንኳን የማታስበው ‘ህግ እያረቀቀ’ ይቆይና አንድ ቀን ማታ በር ይንኳኳል፡፡ እናንተም ስትከፍቱ አከራያችሁ ተኮሳትረው ቆመዋል፡፡ እናንተም…“ደህና አመሹ፣ ምነው ደህና!” ስትሉ ምን ትባሉ መሰላችሁ…“ኪራዩ ላይ ከሰኞ ጀምሮ አንድ ሺህ ብር ጨምረናል፡፡
 ካልተስማማችሁ በሁለት ቀን ውስጥ ቤቱን ልቀቁልን፡፡” የምር ያበሳጫል፡፡ ስሙኝማ…የብስጭት ነገር ከተነሳ … “እንትናዬው ምን ያህል ብታበሳጨው ነው ሴቶችን እንደዚህ ጠምዶ የያዛት!” የሚያሰኝ ንግግር ገጥሟችሁ አያውቅም!
ሰውየው ጓደኛውን… “ሬድዮ ለመጀመሪያ ጊዜ የተፈጠረው በገነት ውስጥ ነው ሲሉ ሰማኋቸው፡፡
ምን ማለታቸው ነው?”  ሲል ይጠይቀዋል፡፡ ጓደኝዬውም ምን ብሎ መለሰ መሰላችሁ…“እሱን የነገሩህ ሰዎች ፈጣሪ አዳምን ፈጠረ፡፡ ከዚያም ከጎኑ የጎድን አጥንት አወጣና የመጀመሪያውን ድምጽ ማጉያ ፈጠረ ማለታቸው ነው፣”  ብሎት አረፈ፡፡‘ጉልቤነትን’… አለ አይደል… ሲሆን ያስወግድልን፣ ካልሆነም የምንሸከምበትን ትከሻ ያደንድንልን፡፡
“የበጎቹ ጠባቂ ሆይ፣ ‘ወየት’ ነህ!” የምንልበትን ጊዜ ያሳጥርልን፡፡  
ደህና ሰንብቱልኝማ!

   ከዕለታት አንድ ቀን አንዲት የውሃ ኤሊ የመውለጃዋ ጊዜ ደርሶ ኖሮ ከውሃው ወጥታ ወደ ባህሩ ዳርቻ ትሄዳለች፡፡ይቺ ኤሊ ቀስ እያለች በረጅሙ የአሸዋ መንገዷ ስታዘግም ሁለት ጓደኛሞች ያዩዋታል፡፡
አንደኛው ፤ “ይቺ ዔሊ ወዴት ነው የምትሄደው?” ይላል፡፡
ሁለተኛው፤ “የመውለጃ ጊዜዋ ደርሶ ይሆናል”
አንደኛው፤ “የመውለጃዋ ጊዜ ቢደርስ ወደ አሸዋው ምን ያስኬዳታል? መኖሪያዋ ውሃ ውስጥ ነው፡፡ እዚያው ወልዳ ተገላግላ እርፍ አትልም እንዴ?”
ሁለተኛው፤ “ለምን ውሃ ውስጥ እንደማትገላገል አላውቅም፤ የማውቀውና ሰዎች ሲሉ የሰማሁት ግን፤ ኤሊ የመውለጃዋ ጊዜ ሲደርስ ወደ ባሕሩ ቅርብ ዳርቻ አይደለም የምትጓዘው፡፡ ከውሃው እጅግ እርቃ ወደማይታይ አቅጣጫ ነው የምትሄደው”
“ልጆችዋን እሩቅ ቦታ ሄዳ የምትገላገል ከሆነ፤ በኋላ እንዴት አድርገው ልጆችዋ ከሷ ጋር ይገናኛሉ? እናታቸው በባሕሩ ውስጥ መሆኗንስ እንዴት ያውቃሉ?”
ይህ ጥያቄ በጣም ውስብስብና በቀላሉ የሚፈታ ስላልሆነላቸው በአቅራቢያው ወደሚገኝ አንድ ጠቢብ ዘንድ ሄደው ሊጠይቁ ይስማማሉ፡፡
ጠቢቡ ቤት ሄደውም፤ “ጠቢብ ሆይ! አንዲት የውሃ ኤሊ አየን፤ ከውሃው ወጥታ ወደ አሸዋው ዘልቃ እርቃ ሄደች፡፡ በኛ ግምት የመውለጃዋ ቀን ደርሶ ይሆናል ተባባልን፡፡ ግን አንድ ጥያቄ አነሳን፡፡ ወልዳ ወደ ባሕር ስትመለስ ልጆችዋን ማን ያመጣላታል? መቼም ህፃናት ናቸውና አውቀው ወደ ባሕሩ አይመጡም፡፡ ደግሞስ ያን ያህል ሰፊ ባሕር ውስጥ እናታቸው የት ትኑር የት እንደምን ያውቃሉ” ሲሉ ጠየቁት፡፡ ጠቢቡም “የአምላክን ተአምር የምታደንቁት እነዚህን አይነት ጉዳዮችን ለመመርመር ስትችሉ ነው፡፡ ኤሊዋ ልጆችዋን የምትወልደው እንዳላችሁት ከባሕሩ ራቅ ያለ ቦታ ሄዳ ነው፡፡ እንዳላችሁትም ከተገላገለች በኋላ የባሕሩ ዳርቻ አሸዋ እንዲሞቃቸው እዚያው ትታቸው ነው ወደ ባሕሩ የምትመለሰው፡፡ ልጆችዋ እስኪጠነክሩ ድረስ እዚያው አሸዋው ላይ ይቆዩና ሰፊውን አሸዋ አቋርጠው ወደ እናታቸው ይመለሳሉ፡፡ የተፈጥሮ ህግ ስለሆነ ያለ ጥርጥር በባሕሩ ውስጥ እናታቸው የቱ ጋ እንዳለች ያውቃሉ፡፡ ዋና አስገራሚ ነገር ግን ወደ ባሕሩ በሚመጡ ጊዜ መንገድ ላይ አደጋ መኖሩ ነው፡፡ በባሕሩ ዳርቻ ላይ የኤሊ ጫጩት እየተመገቡ የሚኖሩ ወፎች አሉ፡፡ ከጫጩቶቹ መካከል በወፎቹ ከመበላት ተርፈው እናታቸው እቅፍ ውስጥ ለመግባት የሚችሉት ጥቂቶቹ የታደሉቱ ናቸው፡፡ ይህ የአምላክ ስርዓተ ተፈጥሮ ነው፡፡ ትላንት እንደዚያ ነበረ፤ ዛሬም አለ፤ ነገም በአግባቡ ይቀጥላል፡፡” አላቸው፡፡
የፍጥረታትን ተዓምር እያደነቁ ወደመጡበት ተመለሱ፡፡
***
በዓለም ላይ በዚህም ቢሉት በዚያም ከመሆን የማይቀር ነገር አለ፡፡ መንግስታት ይለወጣሉ፤ አገሮች ባሉበት ይቆያሉ፡፡ የሚሠሩ ያገኛሉ፡፡ ዳተኞች ባዶ እጃቸውን ይቀራሉ፡፡ የሚጥሩ ዳር ይደርሳሉ፡፡ የተኙ ወደ ኋላ ይሄዳሉ፡፡ ይሄ ተፈጥሮአዊ የሆነው ነገር አይቀሬ ነው፡፡ ከኤሊ ጫጩቶች መካከል ተርፈው ለእናታቸው የሚኖሩ ጥቂቶቹ ይሁኑ እንጂ ይኖሩ ዘንድ የተፈቀደላቸው የታደሉ ናቸው፡፡ ያልታደሉት ባጭር ይቀጫሉ፡፡ ይህ ህግ ሁሌም የሚኖር ነው፡፡ ሰው የሚሰራው ነገር ተጨማሪ ነው፡፡ ያም ሆኖ
“አለ አንዳንድ ነገር
በዚህ ቢሉት በዚያ ከመሆን የማይቀር”  ይላሉ ደራሲ ከበደ ሚካኤል፡፡ በዚህ ውስጥ የተቃራኒዎች አንድነትና ትግል ሁሌም አይቀሬ ነው፡፡ ገዢው ፓርቲ መግዛቱን ለመቀጠል ተገዢዎች የኛም ፓርቲ የገዢነት ቦታ ሊኖረው ይገባል በማለት እስኪሸናነፉና እስኪለይላቸው ጉዞአቸውን ይቀጥላሉ፡፡
“ልምድን ከሩቅ ሆነህ አታየውም፤ ሲከሰት ግን መኖሩን ታውቃለህ” ይላሉ ፈረንጆች፡፡ ለመማር ዝግጁ የሆነ ባወቀው ይጠቀማል፡፡ አትማር ያለው ባወቀውም ይደነቁራል፡፡ በሀገራችን ብዙ ፓርቲዎች ተወልደዋል፡፡ ብዙዎች ሞተዋል፡፡ አንዳንዶች ቀንቷቸዋል፡፡ አንዳንዶች በአጭር ተቀጭተዋል፡፡ የሁሉም የጋራ ሀብት ግን ከኖሩት አለመማር ሆኖ ታዝበነዋል፡፡ አሸናፊው ድሉን ከማሸብረቅ በቀር የሄደበትን መንገድ ዳግመኛ ለመመርመር አይቃጣውም፡፡ ተሸናፊው ቂም በቀሉን ከማመንዠክ እና ጊዜ ከመጠበቅ በቀር ያለፈውን ሁኔታ አጥንቶ በወጉ ለነገ ለመዘጋጀት ከቶም ልቦና የለውም፡፡ ይህ ሀቅ ሁሌም ምርጫ በመጣ ቁጥር የሚያጋጥመው እውነታ ነው፡፡ ትላንት በምርጫው አሸናፊ ነኝ የሚለው ወገን ለአሸናፊነት ሁሌም የታጨሁና ሁሌም የሚሳካልኝ ነኝ የሚለውን አስተሳሰብ የማይለወጥ እውነታ አድርጐ መውሰዱን አይን ካለን እናያለን፡፡ በአንፃሩ ትላንት በምርጫው ተሸናፊ የሆነው ወገን ደግሞ በመጭበርበር ተሸነፍኩ እንጂ ልክ ነበርኩ የሚለውን ሃሳቡን ሳይለውጥ አምስት አመት ይኖራል፡፡ በኢትዮጵያ ሠርጉ ካልደረሰ በርበሬ አይቀነጠስም ይባላል፡፡ አድፍጦ፣ አሳቻ ጊዜ መርጦ ለማነቅ ጀግና መባል አንዱና ዋነኛው የትግል ዘዴ በሆነበት ሀገር፣ የዲሞክራሲ እውንነት ሁሌም ጥያቄ ውስጥ ነው፡፡
ያለ ዲሞክራሲያዊ መስተጋብር ህይወት የአዘቦት መንገዷን እንጂ የተለወጠ ጐዳና ወይም እግረ መንገድ እንኳ ልትቀዳጅ አይቀናትም፡፡ የትግሉን ሂደት ከማየት ይልቅ ስወለድም እንዲህ ነበርኩ ማለትም አጉል መመካት ነው ይሉናል አበው ጠበብት፡፡ እኛ ብቻ ነን ለዚህ ስልጣን የተቀባን የሚለው ሃሳብ ግዘፍ ነስቶ የምናየው ለዚህ ነው፡፡ ከዚህ ይሰውረን ብለን እናማትብ፡፡ አንድ የፖለቲካ ድርጅት በእውነትም ሆነ በውሸት ምርጫ ሲያሸንፍ “ፍፁም ስለሆንኩ አሸነፍኩ” የሚል አስተሳሰብ ውስጥ መዋኘቱ አይገርሜ ነው! ግቡን መምታቱ ያላጋጠሙትን አሊያም አጋጥመውት ያልዘገባቸውን መንሸራተቶችና መሰናክሎች ወይም ሰንካላ እድሎች እንዲረሳ የደረሰበት ወንበር ክፉ ንቀት ይሰጠዋል! ዛሬ እዚህ የደረስከው በሠራኸው ጥሩም፣ መጥፎም ነገር  ነው፡፡ የሚለውን ልብ አይልም፡፡ “መሠላል ያላንሸራተተው ሁሌ ጫፍ የሚወጣ ይመስለዋል” የሚለው ተረት ከላይ የተጠቀሰውን ሁሉ ያጠቃልላል፡፡
“ጥሩው ብቻ አይደለም እዚህ ያደረሰህ
መጥፎም ነው እኮ ያንተ ማንነትህ” እንደማለት ነው በግጥም ሲለገጥ፡፡  




     በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ የፓትርያርኮች መንበር (መንበረ ፕትርክና) በኾነችው ቅድስተ ቅዱሳን ማርያም ገዳም፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብና ንብረት በአስተዳደር ሓላፊዎችና ሠራተኞች መመዝበሩን ምንጮች ጠቆሙ፡፡ጥቆማው የቀረበው፣ የገዳሟ ማኅበረ ካህናትና የልማት ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያኒቱን የገንዘብና የንብረት አሰባሰብ በተመለከተ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሠራር እንዲዘረጋ የገዳሟ ልማት ኮሚቴ የበላይ ጠባቂ ለኾኑት ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ ባቀረቡት ማመልከቻና ሪፖርት ነው፡፡የቤተ ክርስቲያኒቱ መተዳደርያ ቃለ ዐዋዲና ደንቡን መሠረት አድርጎ በሀገረ ስብከቱ የተዘጋጀው የገንዘብ ቆጠራ፣ የንብረት አመዘጋገብና አጠባበቅ መመሪያ የካህናቱን፣ የምእመናኑንና የእያንዳንዱን ሠራተኛ የሥራ ድርሻና ተጠያቂነት በግልጽ ማስቀመጡን የጠቀሱት ማኅበረ ካህናቱ÷ የገዳሟን ገንዘብና ንብረት የመቆጣጠርና የመከታተል መብታቸው በአስተዳደሩ ሓላፊዎች ተነፍጓቸው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራና የንብረት ቁጥጥር ለማድረግ ሳይችሉ መቆየታቸውን ገልጸዋል፡፡ገዳሚቷ በየዕለቱና በየበዓላቱ ከምእመናን በስጦታና በስእለት የምታገኘው ሀብትና ንብረት ከራስዋ አልፎ ለተቸገሩ ገዳማትና አድባራት የሚተርፍ ቢኾንም ግልጽነትና ተጠያቂነት በጎደለው የአስተዳደሩ አሠራርና በሰበካ ጉባኤው የቁጥጥር ማነስ ሳቢያ የገቢ አቅሟን ለማጎልበት ከዓመታት በፊት የወጠነችው ኹለ ገብ ሕንፃ ግንባታ ከመጓተቱም በላይ ለሀገረ ስብከቱ መከፈል ለሚገባው ውዝፍ ዕዳ መዳረጓን ካህናቱ አስታውቀዋል፡፡ በገንዘብ አያያዝና በንብረት አሰባሰብ ረገድ በአስተዳደሩ እየተባባሰ የመጣው ሙስና እንዲወገድና ካለፈው ዓመት ነሐሴ ወር ጀምሮ የተስተጓጎለው የልማት ሥራ እንዲቀላጠፍ በኅዳር ወር አጋማሽ ፓትርያርኩን መጠየቃቸውንም አመልክተዋል፡፡ከገዳሚቷ የልማት ኮሚቴ ጋራ በመቀናጀት የቀረበውን የማኅበረ ካህናቱን ማመልከቻ መነሻ በማድረግ ፓትርያርኩ አቡነ ማትያስ በሰጡትና በረዳት ሊቀ ጳጳሱ በኩል ተፈጻሚ በኾነው መመሪያ፤ የገዳሟን የገንዘብና ንብረት አሰባሰብ የሚከታተል አምስት ካህናት ያሉት የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ ኮሚቴ ኅዳር 18 ቀን መቋቋሙ ታውቋል፡፡ ኮሚቴው ከተቋቋመበት ማግሥት አንሥቶ ኅዳር 19 እና 22 ቀናት ባካሔደው የሙዳየ ምጽዋት ቆጠራ የተገኘውን ከብር 826‚000 በላይ ገቢ ጨምሮ ከንብረት ሽያጭና በሞዴል 30 የተሰበሰበውን በማካተት ከ1.2 ሚሊዮን ብር በላይ አጠቃላይ ገቢ በአንድ ወር ብቻ መመዝገቡ ተገልጧል፡፡ በካህናቱ አስፈጻሚነት በአንድ ወር የተወሰነ ቆጠራ ብቻ ይህን ያኽል ገቢ መመዝገቡ፣ የገዳሟ ገቢ ‹‹የግለሰቦች መደራጃ ኾኖ መኖሩን የሚያሳይ ነው፤›› ብለዋል - ማኅበረ ካህናቱ፡፡ አያይዘውም ለሀገረ ስብከቱ መከፈል የሚገባው የኻያ በመቶ ውዝፍ ዕዳ ሳይፈጸም አኹን በካዝና ያለው ብር 129‚000 ብቻ እንደኾነ በመጥቀስ ገዳሟ በየዓመቱ በሚሊዮኖች የሚቆጠር ብር ስትመዘበር እንደኖረችና ጠቅላይ ቤተ ክህነቱም ኾነ ሀገረ ስብከቱ በየደረጃው ማግኘት የነበረባቸውን የፐርሰንት ፈሰስ ማጣታቸውን ስለሚያረጋግጥ ‹‹የአስተዳደር ሠራተኞቹን ተጠያቂ የሚያደርግ ነው፤›› ብለዋል፡፡   እንደ ማኅበረ ካህናቱ እምነት፣ የገዳሟ ገቢ ለአስተዳደር ሠራተኞቹ ምዝበራ የተጋለጠው የተጠናከረ ሰበካ ጉባኤ ባለመኖሩ ነው፡፡ አኹን ያለው የገዳሙ ሰበካ ጉባኤ በቃለ ዐዋዲው መሠረት፣ የገዳሙን የሥራ ክፍሎች አገልግሎት አፈጻጸም በወቅታዊ የክንውን መግለጫዎች የመከታተል፣ የሒሳብ አያያዙንና የንብረት እንቅስቃሴውን ጊዜውን ጠብቀውና እንዳስፈላጊነቱ በሚቀርቡ ሪፖርቶች የመቆጣጠር ሓላፊነቱን ካለመወጣቱም በላይ ‹‹ገዳሚቷ ችግር ላይ ስትወድቅ ዝም ብሎ የኖረ ተባባሪ›› በመኾኑና የሥራ ጊዜውም በማለፉ ጠንካራና ሓላፊነት በሚሰማው ሰበካ ጉባኤ እንዲተካ መመሪያ እንዲሰጥላቸው፣ ተጀምሮ የቆመው ልማት እንዲቀጥል፣ የገዳሟ ገቢና ወጪም በውጭ ኦዲተሮች እንዲጣራ ማኅበረ ካህናቱ ፓትርያርኩን ጠይቀዋል፡፡ ያለማኅበረ ካህናቱና ማኅበረ ምእመናኑ ፈቃድ ጊዜው በሀ/ስብከቱ ውሳኔ ተራዝሟል የተባለው ሰበካ ጉባኤ፣ በቆጠራ ኮሚቴው የተሰበሰበውን ከብር 440‚000 በላይ የገዳሚቷን ከፍተኛ ገንዘብ ያለተቆጣጣሪ ወጪ ማድረጉን ካህናቱ ገልጸው፣ ሕጋዊ ሰበካ ጉባኤ ሳይቋቋም ቀጣይ ቆጠራ እንደማይካሔድ አስጠንቅቀዋል፡፡ በገዳሚቷ አስተዳደር ውስጥ ሙስናዊ ጥቅማቸው የተነካባቸው ናቸው ያሏቸው ግለሰቦች፣ የቆጠራ ኮሚቴውን ለማፍረስ÷ ‹‹ማኅበረ ቅዱሳንና ግንቦት ሰባት ናችኹ፤ ምርጫውን ለማወክ ትንቀሳቀሳላችኁ፤ ወደ ሌላ ደብር እናዘዋውራችኋለን›› በሚል ከሚያደርሱባቸው ዛቻና ማስፈራራት እንዲቆጠቡ አስተዳደራዊ ርምጃ እንዲሰጥላቸው አመልክተዋል፡፡የማኅበረ ካህናቱንና የልማት ኮሚቴውን ጥያቄ ተከትሎ ፓትርያርኩ በሰጡት መመሪያ÷ ሰበካ ጉባኤው የሥራ ክንውን ሪፖርት ካቀረበ በኋላ የአዲስ ሰበካ ጉባኤ ምርጫ እንዲካሔድ፣ የገዳሚቷ ገቢና ወጪ ሒሳብ በአስቸኳይ በውጭ ኦዲተር ተከናውኖ እንዲቀርብ፣ የቆጠራ ኮሚቴው የአስተዳደሩን ዕውቅና አግኝቶ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ በ48 ሚልዮን ብር ወጪ በኹለት ምዕራፎች የተጀመረውና የተጓተተው የባለስድስት ፎቅ የአገልግሎትና ኹለገብ ሕንፃ ግንባታ የብቃት ማረጋገጫ ባለው አካል ክትትል እንዲፋጠን ማዘዛቸው ታውቋል፡፡

Saturday, 27 December 2014 16:25

ዛሬም ይዞረኛል

ሄደ … አለፈ ብዬ ትንሽ ፋታ ሳገኝ፣
የተጫነኝ ችግር የጠፋ ሲመስለኝ፣
ተመልሶ መጥቶ ጎንተል ያደርገኛል፣
የራቀ ሲመስለኝ ዳግም ይቀርበኛል፣
ከጋለው ሊጥደኝ መልሶ ይዞረኛል፡፡
እኔ ቀርቤው ነው? ወይ እሱ እየመጣ፣
የማንለያየው - የማንተጣጣ፡፡
አንዴ እየራቀ፣ ዳግም እየመጣ …
        ይሽከረከረኛል፣
ቁራኛዬ ሆኖ አልለቅህም ብሎ …
        ያንዣብብብኛል፡፡
ከዚህ ችግር ዕዳ - ከእንቶ ፈንቶ ጣጣ፣
ሊያድነኝ ከሁሉም ከማጡ ሊያወጣ፣
ዳግም ወደ መሬት ክርስቶስ አይመጣ፣
ታዲያ እንዴት ልሁነው?
እንዲሁ እንዳለሁ ፍግም ልበለው!?
        … ኧረ አሳዝናለሁ፣
        … አፈር እከብዳለሁ፡፡
ይህ መንገራገጩ ጠቅልሎ አልሄድ ያለው፣
እንዴት ቢያፈቅረኝ ነው ከኔ የማይለየው!?
ፊትም፣ አምና፣ ዛሬ አልተውህ ብሎኛል፣
ነገሩ ምንድነው? - ዛሬም ይዞረኛል፡፡

ከአምሳሉ ጌታሁን ደርሰህ
ታህሣሥ 2007 ዓ.ም