Administrator

Administrator

ዲያቆን ዳንኤል ክብረት በተለያዩ ማህበራዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ጉዳዮች ዙርያ መጣጥፎች የሚያቀርብበት “የዳንኤል ዕይታዎች” የጡመራ መድረክ (Blog) የተመሠረተበት ሶስተኛ አመት ሚያዚያ 5 ቀን 2005 ዓ.ም በአዲስ አበባ አክሱም ሆቴል አዳራሽ ከቀኑ 7፡00 ሰዓት ጀምሮ በሚካሄድ ፕሮግራም እንደሚከበር ተገለፀ፡፡ በዕለቱ በሚካሄደው ፕሮግራም ላይ “የዳንኤል እይታዎች” ጡመራ ላይ የቀረቡ ጽሑፎች ቅኝት፣ የኢትዮጵያውያን ማህበራዊ ድረ ገፆች ዳሰሳ፣ የማህበራዊ ሚዲያ ህጋዊና ሥነ ምግባራዊ ሃላፊነት በሚሉና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ዙርያ ጥናታዊ ጽሑፎች እንደሚቀርቡና ሰፊ ውይይት እንደሚካሄድም የፕሮግራሙ አዘጋጆቹ ገልፀዋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ ትውልድን በመቅረጽ ለሀገርና ለህዝብ የሚበጁ በጐ ሥራዎች የሚያከናውኑና ሃሳብ የሚያመነጩ ግለሰቦችና ተቋማት እውቅናና ሽልማት እንደሚሰጣቸው ታውቋል፡፡ ዲያቆን ዳንኤል ክብረት፤ ደራሲና የቤተክርስቲያን ተመራማሪ ሲሆን፤ 16 መፃሕፍትን በግሉ፣ ሶስት መፃሕፍትን ከሌሎች ጋር ለህትመት አብቅቷል፡፡ በብዙ መቶዎች የሚቆጠሩ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ የሚያጠነጥኑ መጣጥፎችንም በጋዜጦችና መፅሄቶች ላይ አስነብቧል፡፡

ፊልሞች በህገወጥ መንገድ እንዳይገለበጡና እንዳይሰረቁ የሚከላከል “የጥበብ ዋርድያ” የተሰኘ ሶፍትዌር መስራቱን የገለፀው ሴባስቶፖል ሲኒማ፤ ከሚቀጥለው ወር ጀምሮ ሥራ ላይ እንደሚውል ሰሞኑን አስታወቀ፡፡ ሶፍትዌሩ ፊልም ሰሪዎች ፊልም በሚያሳዩ ወቅት “ይሰረቅብኛል” ከሚል ስጋት ያድናቸዋል ተብሏል፡፡

ባለፈው ረቡዕ በሴባስቶፖል ሲኒማ መግለጫ የሰጡት ሶፍትዌሩን ያዳበሩ ባለሙያዎች እንዳሉት፤ ሶፍትዌሩ አንድ ፊልም በሕገወጥ መንገድ ሳይገለበጥ በአንድ ጊዜ ብዙ ቦታ እንዲታይ ያስችላል ብለዋል፡፡ ፊልሙ ስንት ጊዜ እንደታየ ጭምር ለማወቅ ያስችላል የተባለው ሶፍትዌር፤ ፊልሞቹን በጥቂት ደቂቃዎች ውስጥ በማስቆለፍ ከስርቆት ስጋት ነፃ እንደሚያወጣ ተገልጿል፡፡

ታዋቂ ራፕሮች ከተለያዩ ኩባንያዎች ጋር በሚሰሯቸው የስፖንሰርሺፕ ውሎች እና ማስታወቂያዎች ሃብታቸውን እያሳደጉ መሆናቸውን ሴለብሪቴኔትዎርዝ አስታወቀ፡፡ የራፕ ሙዚቃን መጫወት፤ ማሳተም እና የተለያዩ የሙዚቃ ዝግጅቶችን በማቅረብ የሚገኘው ገቢ እጅግ እያነሰ መምጣቱን ዘገባው አመልክቷል፡፡ ሴሌብሪቲ ኔትዎርዝ ከሙዚቃ ውጭ የእውቅ ራፕሮች ገቢ በጣም እያደገ መምጣቱን ያመለከተው የ2013 የዓለም ራፕሮች የሃብት ደረጃን ሰሞኑን ይፋ ሲያደርግ ነው፡፡ ሲን ኮምበስ ወይም ፒዲዲ ባለፈው አንድ አመት በሃብቱ ላይ ተጨማሪ 80 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል ያለው ሴሌብሪቲ ኔትዎርዝ 580 ሚሊዮን ዶላር አስመዝግቦ በአንደኝነት እንደሚመራ ገልጿል፡፡

ለፒዲዲ ሃብት ማደግ ከአልኮል መጠጦች አንዱ ከሆነው የቮድካ አልኮል ብራንድ ሲሮክ የተባለ ምርት ላይ በሚሰራው ንግድ ሽያጭ በመድራቱ ነው ያለው ሴሌብሪቲ ኔትዎርዝ ራፕሩ ይህን ኩባንያ ቢሸጥ እስከ 150 ሚሊዮን ዶላር የተጣራ ገቢ ሊያገኝ እንደሚችል ጠቁማል፡፡ ባለፈው አንድ ዓመት በሃብቱ ላይ ተጨማሪ 25 ሚሊዮን ዶላር የጨመረው ጄይዚ በ500 ሚሊዮን ዶላር የሃብት ግምቱ ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ፤ ቢትስ ባይ ድሬ በተባለ የጆሮ ማዳመጫ ምርቱ ያለፈውን አንድ አመት 100 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ሰብስቦ የሃብት መጠኑን 360 ሚሊዮን ዶላር ያደረሰው ዶር ድሬ ሶስተኛ ሆኗል፡፡ ሌሎች ራፕሮች ማስተር ፒ በ350 ሚሊዮን ዶላር፤ ሴንት በ260 ሚሊዮን ዶላር፤ በርድ ማን በ150 ሚሊዮን ዶላር፤ ኤሚነም በ140 ሚሊዮን ዶላር፤ ስኑፕ ዶግ በ130 ሚሊዮን ዶላር፤ አይስ ኪውብ በ120 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ሊል ዋይኔ በ110 ሚሊዮን ዶላር የሃብት መጠን እስከ 10 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡

አንጋፋና ወጣት ከያንያን የግጥም፣ የቅንጭብ ትያትር፣ የወግና ሌሎች የኪነጥበብ ሥራዎቻቸውን በጃዝ ሙዚቃ ታጅበው የሚያቀርቡበት “ግጥም በጃዝ” ሃያ አንደኛ ዝግጅት የፊታችን ረቡዕ ከቀኑ 11፡30 ሰዓት እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ ገለፁ፡፡ ባሁኑ ዝግጅት ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ፣ ሞገስ ሀብቱ፣ ምስራቅ ተረፈ፣ በረከት በላይነህ፣ ግሩም ዘነበ ግጥሞቻቸውን ሲያቀርቡ፣ ወ/ሮ ሰሎሜ ታደሰ ዲስኩር እንዲሁም ዲያቆን ዳንኤል ክብረት ወግ ያቀርባሉ፡፡

ሚዩኒክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ በሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ታሪካዊ ተውኔቶች ላይ ነገ ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ አምስት ኪሎ በሚገኘው ብሄራዊ ቤተመዘክር ውይይት እንደሚያካሄድ አስታወቀ፡፡ ውይይቱን የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የትያትር ጥበባት መምህር ነብዬ ባዬ ይመሩታል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ጀስቲን ቲምበርሌክ ከ4 ዓመታት በፊት ከላይቭ ኔሽን ጋር በተፈራረመው የኮንሰርት ውል አስገዳጅነት ወደ ሙዚቃ ስራው ሊመለስ መወሰኑን ቢዝነስ ኢንሳይደር ዘገበ፡፡ አርቲስቱ የሙዚቃ ስራውን ለተወሰነ ጊዜያት በማቆም በፊልም ትወና ለማተኮር የነበረውን ፍላጎት ሲገልፅ ቆይቷል፡፡ ከአራት አመት በፊት ላይቭ ኔሽን ከተባለው የኮንሰርት አዘጋጅ ድርጅት ጋር የገባውን ውል በማደስ ጀስቲን ቲምበርሌክ ወደ ሙዚቃ ፊቱን ያዞረው የ20 ሚሊዮን ዶላር ስምምነቱ ስላማለለው እንደሆነ ቢዝነስ ኢንሳይደር በዘገባው አትቷል፡፡ ከእነ ማዶና እና ጄይዚ ጋር በመስራት ዓለም አቀፍ ሽፋን ያላቸውን ኮንሰርቶች የሚያዘጋጀው ላይቭ ኔሽን በውሉ መሰረት ለጀስቲን ቲምበርሌክ በመላው ዓለም ለሚያቀርበው ኮንሰርት 15 ሚሊዮን ዶላር እንደሚከፍል ገልጿል፡፡

ከ4 ዓመት በፊት ጀስቲን ቲምበርሌክ ከላይቭ ኔሽን 5 ሚሊዮን ዶላር ቀብድ ተከፍሎት እንደነበር ያስታወሰው ቢዝነስ ኢንሳይደር ይህን ቀብድ መልሶ ውሉን የማፍረስ መብት ነበረው ብሏል፡፡ ጀስቲን ቲምበርሌክ ከ3 ወራት በፊት ‹‹ዘ 20 /20 ኤክስፒሪያንስ›› በሚል የሰራውን አልበም ለገበያ ካበቃ በኋላ ለተወሰኑ ዓመታት ከሙዚቃ ስራው ለማረፍ ፈልጎ እንደነበር የገለጸው ቢዝነስ ኢንሳይደር ሊመለስ መወሰኑ ያልተጠበቀ መሆኑን አብራርቷል፡፡ ከ2 ዓመት በፊት በትወና ስራው ትኩረት አድርጎ የነበረው የፖፕ ሙዚቀኛው 3ቱን ፊልሞች ‹‹ባድ ቲቸር››፤ ‹‹ፍሬንድስ ዊዝ›› እና ‹‹ኢንታይም›› ተውኖ ነበር፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት ከክሊንት ኢስትውድ ጋር ትራብል ዊዝ ከርቭ የተባለውን ፊልም የሰራው ጀስቲን ቲምበርሌክ በሆሊውድ ፊልም ሰሪዎች ተፈላጊነት እያገኘ ነበር፡፡

አይረን ማን 3 ከወር በኋላ ይታያል በ2013 በመላው ዓለም ከሚታዩ የሆሊውድ ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ማግኘት በተለይ ለአዲሶቹ ሊከብድ እንደሚችል ተመለከተ፡፡ በ3ዲ በድጋሚ በመሰራት ለእይታ የሚበቁ እና በተከታታይ ክፍል የሚሰሩ ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ለመሰብሰብ ተስፋ አላቸው ተብሏል፡፡ በ3ዲ የተሰሩት ጁራሲክ ፓርክና ስታር ትሬክ ኢንቱ ዘ ዳርክነስ እንዲሁም አይረን ማን 3፣ ፋስት ኤንድ ፊውሪዬስ 6 የቢሊዮን ዶላር ገቢ ግምት ካገኙት ይጠቀሳሉ፡፡ ባለፈው የፈረንጆች አመት 4 ፊልሞች ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ እንዳስገቡ ይታወሳል፡፡ የሆሊውድ ፊልሞች በ3ዲ በተፈጠረላቸው ውድ የትኬት ዋጋ እና እንደ ቻይና፤ ራሽያ እና ጃፓን የገበያ ከፍተኛ መስፋፋት ማሳየታቸው ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ዓለም አቀፍ ገቢ መሰብሰብን ፊልም ሰሪዎች ተስፋ እንዲያደርጉ ምክንያት ሆኗል፡፡

ከፊልም ሰሪ ኩባንያዎች፤ በሰራው ፊልም ዓለም አቀፍ ገቢውን 1 ቢሊዮን ዶላር በፍጥነት በማሳካት ፓርማውንት ፒክቸርስ ግንባር ቀደም ነው፡፡ፐርማውንት ከ4 ዓመታት በፊት ይህን የገቢ ጣራ በ174 ቀናት በማሳካት የመጀመርያውን ደረጃ ይዟል፡፡በመላው ዓለም ከ1 ቢሊዮን ዶላር በላይ ያስገቡ ፊልሞች ብዙዎቹ ተከታታይ እና እንደ ፍራንቻይዝ የሚሰሩ ሲሆኑ ይህን የገቢ ጣራ በመድረስ የተሳካላቸው ፊልሞች ብዛታቸው 15 ነው፡፡ ከእነዚህ 15 ፊልሞች መካከል 11 ያህሉ ባለፉት አምስት አመታት በመላው ዓለም ለመታየት የበቁ ናቸው፡፡

ከ2 ቢሊዮን ዶላር በላይ በማስገባት የምንጊዜም ከፍተኛውን የገቢ ሪከርድ ያስመዘገበው ደግሞ አቫታር በ2.78 ቢሊዮን ዶላር ገቢው እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በተያያዘ ከወር በኋላ በመላው ዓለም ለመታየት የሚበቃው አይረን ማን 3 በሚኖረው ትእይንቶች ለቻይና ገበያ ተጨማሪ ቦነሶች ይዟል ተባለ፡፡ በማርቭል ስቱድዮስ በ200 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው ፊልም ለቻይና ፊልም አፍቃሪያን የሚመቹ ትእይንቶች ተጨምረውለታል፡፡ በ2008 እኤአ ላይ ለመጀመርያ ጊዜ የታየው አየርን ማን 1 በመላው ዓለም 585.2 ሚሊዮን ዶላር ያስገባ ሲሆን በ2010 እኤአ ላይ የታየው አይረን ማን 2 ደግሞ 1.3 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በዓለም ገበያ ሰብስቧል፡፡

ዩኒቨርሳል ክሊኒክ የታይፎይድ በሽታን መርምሮ ውጤቱን በ37 ደቂቃዎች ውስጥ ለማረጋገጥ የሚያስችል መሣሪያ ማስመጣቱን የገለፀ ሲሆን፤ በታይፎይድ ህክምና ላይ በመላ አገሪቱ ይታዩ የነበሩ ችግሮችን ለመፍታት የሚያስችል መሆኑን የክሊኒኩ ሃኪም ተናግረዋል፡፡ በአገራችን ውስጥ በስፋት ሲያገለግሉ የቆዩ መሳሪያዎች ሁለት ጉድለት እንደነበረባቸው ዶ/ር ምክሩ ጠቅሰው፤ ምርመራው ፈጣንና አስተማማኝ አልነበረም ይላሉ፡፡ የታይፎይድ ባክቴሪያ በሰውነት ውስጥ እንዳለና እንደሌለ በፍጥነት ለማረጋገጥ የሚደረገው ምርመራ አስተማማኝ ስላልነበረ የተሳሳተ ውጤት ያመላክት ነበር ብለዋል፡፡

“ቀድሞ የነበረው መሣሪያ በሽታው ሣይኖር አለ ብሎ የሚያመላክትበት አጋጣሚ ስለነበር፤ ህመምተኛው ተገቢውን የህክምናና የመድሃኒት አገልግሎት በተገቢው መንገድ ጥርት ያለ ምርመራ ለማድረግም “Blood Culture” በሚባል የምርመራ ዓይነት ናሙናዎች ተወስደው ውጤቱን ከሣምንት በላይ መጠበቅ ግድ ነበር የሚሉት ዶ/ር ምክሩ፣ በሽተኛው እስከዚያ ድረስ ጉዳት ይደርስበታል ብለዋል፡፡ ክሊኒኩ አዲስ ያስመጣው መሣሪያ ትክክለኛውን የህክምና ውጤት በደቂቃዎች ውስጥ ከማሣወቁም በላይ በምርመራው ሂደት ይፈጠሩ የነበሩ ስህተቶችን ሙሉ ለሙሉ የማስወገድ አስተማማኝ መሳሪያ ነው ብለዋል - ዶ/ር ምክሩ፡፡

የሶርያ ምግቦች አዘጋጅቶ ለተጠቃሚዎች የሚያቀርብ ሬስቶራንት በ2 ሚሊዮን ብር ተቋቁሞ በአዲስ አበባ አገልግሎት መስጠት የጀመረ ሲሆን ሦስት ተጨማሪ ሬስቶራንቶችን ለመክፈት እንደተዘጋጀ ሶሪያዊው ባለሀብት ተናግረዋል፡፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ በግብጽ፣ ፊሊፒንስ፣ ዱባይ፣ ቤሩት እንዲሁም በሶሪያ ተመሣሣይ ሬስቶራንቶችን መክፈታቸውን የሚናገሩት የድርጅቱ ባለቤት አህመድ አሊ በክሪ፣ ሬስቶራንቱ የሶሪያ ባህላዊ ጣፋጭ መብሎችንም ሰርቶ በማቅረብ የሚያስተዋውቅ ነው ብለዋል፡፡

በሶሪያ ለምግብ የሚጠቀሙባቸው ግብአቶች ከኢትዮጵያ ጋር ተመሣሣይ እንደሆኑ ጠቁመው፤ ኢትዮጵያውያን የሶርያ ምግቦችን እንደሚወዷቸው እርግጠኛ ነኝ ብለዋል፡፡ “ሲሪያን ስዊት ኤንድ ሬስቶራንት” በተጨማሪ በአዲስ አበባ ለሚከፈቱ ሦስት ተመሣሣይ ሬስቶራንቶች ሠራተኞችን እያዘጋጀ ሲሆን፤ እስካሁን ለ12 ኢትዮጵያውያን ሼፎች የጣፋጭ ምግቦች አሠራር ስልጠና መሠጠቱን አህመድ በክረ ገልፀዋል፡፡ ከሬስቶራንት አገልግሎቱ በተጨማሪም በትላልቅ አለማቀፍ ስብሠባዎች የምግብ መስተንግዶ እንደሚያቀርቡ የተናገሩት ባለሀብት፣ አንድ የምግብ ኢንዱስትሪ ኩባንያን ለመግዛት በድርድር ላይ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

ዱሮ የሠራሃቸውን ዘፈኖች እንደገና ተቀርጸሐል፤ ከአሁኑና ቀደም ሲል ከነበረው አሠራር እና ቴክኖሎጂ የትኛው ተሻለህ?

ከሃያ አራት ዓመታት በፊት የነበረው ጊዜ ስህተት ላለመሥራት የምንጠነቀቅበት በጣም ከፍተኛ የኾነ ትግልና ልፋት የሚጠይቅ፣ ጊዜ ነበር፡፡ እኔ በተለይ የመጀመሪያውን አልበሜን ላወጣ ሥራዬን ከሮሃ ባንድ ጋር ሠርቼ ካጠናቀቅኹ በኋላ ባንዱ ሁለት ዘፈኖችን እንዲያስተካክል አሣታሚው ሲጠይቃቸው ሥራ ስለሚበዛባቸው ይሁን መሥራት ባለመፈለጋቸው ፍቃደኛ ሳይኾኑ ቀሩ፡፡

ዘፈኖቹን ናሙናው ላይ እንደነበሩት አድርጌ አለመምራቴን አሣታሚው ስላመነበት ሌላ ስቱዲዮ ገብተን ሁለቱን ዘፈኖችና ሁሉንም አፍርሰን በአንድ ዓይነት አሠራር ለመቅረጽ ተስማምተን እንደገና ሠራናቸው፡፡ ሙዚቃውን የሠሩት ፈለቀ ኃይሉ፣ኃይለእግዚአብሔር ገዳሙና ነፍሱን ይማረውና ደረጀ ተፈራ ነበሩ፡፡ የቀረጸው ደግሞ እሱንም ነፍሱን ይማረውና አሣታሚው የ‹‹ሶል ኩኩ›› ባለቤት ሣህለ ነበር፡፡ ሙዚቀኞቹ ከሮሃ ባንድ የወጡ ስለነበሩ ‹‹አሞራ ባንድ›› የሚል አዲስ ስም አውጥተው አብረን ጥሩ ነገር ሠራን፡፡ ለእኔ ግን በጣም ፈታኝ እና አድካሚ ነበር ፡፡

ጨረስኩ ብዬ ሳስብ ከአንድ ባንድ ወደ ሌላ ባንድ ተሸጋግሬ መሥራቴ በጣም ልፋት ነበረው፡፡ ቴክኖሎጂውን በሚመለከት የመጀመሪያውን አልበሜን ዘፈን ለመቅረጽ ስንሰባሰብ ሰባራ ባቡር ይባል በነበረው ሰፈር ውስጥ አነስተኛ ሙዚቃ ቤት እና ከጀርባው ደግሞ ትንሽዬ ስቱዲዮ የመሰለ ቤት የነበረው ተክሌ ተስፋዝጊ ጋር ነበር የምንሠራው፡፡ ቤቷ በጣም ጠባብ ስለነበረች ሁላችንም በቅርበት ተጠጋግተን ዙሪያ ሠርተን ነበር የምንቀርጸው፡፡ ሁለተኛውንም አልበም ስሠራም ከ‹‹ሶል ኩኩ›› ሙዚቃ ቤት ጋራ በጋራ ይሠራ የነበረው የ‹‹ናዲ›› ሙዚቃ ቤት ባለቤት የእነኑረዲን መኖሪያ ቤት እንቁላል ፋብሪካ አካባቢ ይገኝ ነበር፡፡ ሳሎን ቤታቸው ሰፋ ያለ ስለነበር እዛ ነበር የቀረጽነው፡፡ ዘፈኑ የሚቀዳው ደግሞ በዴክ ስለነበር ሁሉም ነገር የሚቀረጸው አንድ ላይ ነበር፡፡

ቀረጻው ከተበላሸ ከመጀመሪያው ጀምሮ እንደገና ይቀዳል፡፡ ዛሬ ግን እኔ ባበላሽ የሚደገመው የእኔ ብቻ ነው ያውም ያበላሸኋት ቦታ ተለይታ፡፡ አንዱ ሙዚቀኛ ቢበላሽበትም እንደዚያው ለብቻው ገብቶ ይሠራዋል፡፡ የአሁኑ አደረጃጀቱም ኾነ የድምጽ መቅረጫ መሳሪያዎቹ ዘመናዊነት የሚያጠያይቅ አይደለም ከዚህ አንጻር ሳየው የቀድሞው የእኛ ልፋት ተወዳዳሪ አይገኝለትም፡፡ ለድምጻዊው ግን በጣም ጠቃሚ የኾነ አሠራር ነበር፡፡ ለዘፈኖቹ ከፍተኛ ግምት በመስጠት በተደጋጋሚ ጥናት የዳበረ ሥራ ስለሚኾን ወደ ሰው ጆሮ ሲደርስ የሚደመጥ ያደርገዋል፡፡ መድረክ ላይ ሲወጣም የተዋጣለት ሥራ ለመሥራት ያስችላል፡፡

ዛሬ ለሥራው ግምት አይሰጥም ማለቴ ሳይኾን ያለምንም ጥናት በአንድ ቀን ሁሉንም ነገር የሚጠናቀቅበት አሠራር አለ፡፡ ከዚህ አንጻር የዛን ጊዜውን ያህል የጠነከረ ሥራ ይሠራል ማለት ይከብዳል፡፡

ዘፈኖቹን የተቀረጽከው እንደ አዲስ በመኾኑ ልፋቱ እንዴት ነበር?

ዘፈኑን የሚያውቁትን ባለሞያዎች አሰባስቤ በክብረት መሪነት የተሠራ ነው፡፡ ዘፈኖቹን በጥሩ ሁኔታ ያደራጃቸው እና በሙዚቃው ሕግ መሠረት መስመር ያስያዘው ደግሞ ፈለቀ ነው፡፡ እኔ ድምጼን የሰጠሁት ፈለቀ አስተካክሎ ባመጣው ሙዚቃ ነው፡፡ ከዛ በኋላ ሙዚቀኞቹ ገብተው ሠሩት፡፡ በዚህም ምክንያት ምንም የሥራ ጫና ሳይኖርብኝ በተረጋጋ ሁኔታ ነው የሠራነው፡፡ በዚህ በኩል ባለሞያዎቹ ትልቅ አስተዋፆ አላቸውና ላመሰግናቸው እፈልጋለሁ፡፡

ለምን እንደገና መሥራት ፈለክ?

ዘፈኖቼ በብዛት የነበሩትና አሁንም ያሉት በኦዲዮ ካሴት ላይ ነው፡፡ የዛን ዘመን ቴክኖሎጂ እየቀረና በአዳዲስ እየተተካ ሲመጣ ይህ ትውልድ ከእኔ ዘፈን ጋር እየተራራቀ ሊሄድ ይችላል የሚል ስጋት አደረብኝ፡፡ ዕድሜዬም ለዱላ ማስያዝ ከመድረሱ በፊት መዘጋጀት እና ለትውልዱ አንድ ነገር ትቼ ማለፍ አለብኝ በሚል አስቤ ነው እንደ አዲስ ስቱዲዮ ገብቼ ነው የሠራሁት፡፡ ዘፈኖቹን ከየአልበሞቹ ላይ እንዴት መረጥካቸው? ለሰው ጆሮ ቅርብ ናቸው ያልኳቸውን ዘፈኖች ነው የመረጥኩት፡፡ በዛን ዘመን ዘፈን ስናወጣ የአልበም ስያሜ አልነበረውም፡፡ አንዱን ዘፈን መርጠን ነው መጠሪያ የምናደርገው፡፡ ‹‹እሄዳለሁ ሐረር›› የሚለው ዘፈን ካለበት የመጀመሪያው አልበም ላይ ስድስት ዘፈን መረጥኩ፡፡ ‹‹ለሠርጓ ተጠራሁ›› ካለበት ሁለተኛው አልበም ደግሞ አራት ዘፈን መረጥኩ፡፡ ከሦስተኛው አንድ ዘፈን መረጥኩና ሌሎቹን ከተለያዩ ድምፃውያን ጋራ ከሠራኋቸው ኮሌክሽኖች በአጠቃላይ 14 ዘፈን ነው መርጬ በድጋሚ የሠራሁት፡፡ በምርጫዬም የተከፋ ሰው የለም፡፡

ከቀድሞው ጋራ የድምፅ ልዩነት የለውም?

ብዙ የተለየ ነገር የለውም፡፡ ምናልባት በጉርምስና ወቅት የተሠራና ዕድሜ 40ን ካለፋ በኋላ የሚሠራ ሥራ ትንሽ ልዩነት ያመጣል የሚል ሐሳብ ከተነሳ አሁን ያኔ ከነበረኝ ነገር ትንሽ በሰል ያልኩበት ሥራ ይመስለኛል፡፡ እንዲህ ያለውን ዘፈን ለምን አላካተትክም ያለህ የለም? እንደሱ የሚልማ በጣም በርካታ ሰው አለ፡፡ በአብዛኛው የሚወደውን ዘፈን እያስታወሰ ለምን እንዳስቀረሁት ይጠይቀኛል፡፡ በአንድ ጊዜ ሁሉኑም ዘፈን ማካተት ስለማይቻል የቀሩትን ዘፈኖች አሰባስቤ የማውጣት ሐሳብ እንዳለኝ እነግራቸዋለሁ፡፡ ነገር ግን አሁን ይፋ በማላደርገው መንገድ የምሠራው አንድ አልበም፣ አንድ አልበም ደግሞ በተለመደው ስልት የምሠራው እንዲሁም ከአብርሃም ወልዴ ጋራ አንድ ነጠላ ዜማ እስከነ ቪዲዮ ክሊፑ የመሥራት ዕቅድ ስላለኝ እነዚህን ስጨርስ በኦዲዮ ካሴት ያሉትን ሁሉንም ሥራዎቼን አሰባስቤ ወደ ሲዲ መቀየር እፈልጋለሁ፡፡

ከመጀመሪያው አልበምህና ከአሁኑ በወጪ ደረጃ የቱ ፈታኝ ነው?

የመጀመሪያውን አልበሜን ስሠራ ሁሉንም ወጪ የሸፈነው ሙዚቃ ቤቱ ነበር፡፡ እኔን ከፍሎ አዘፈነኝ እንጂ ለማን ምን ያህል ገንዘብ እንደከፈለ የማውቀው ነገር እንኳን አልነበረም፡፡በወቅቱ የማውቀው ነገር ቢኖር ለሮሃ ባንድ ተከፍሎት የነበረውን ዐስራ አንድ ሺሕ ብር ብቻ ነው፡፡ሆኖም የቱንም ያህል ቢከፍል አሁን እኔ ለዜማ፣ለግጥም እና ለቅንብሩን ካወጣሁት ወጪ ጋር የሚደራረስ አይሆንም፡፡ እኔም አሁን ማስተሩን ለናሆም ሪከርድስ የሸጥኩበት ዋጋ ያኔ ከተከፈለኝ ጋር በፍጹም የሚቀራረብ አይደለም፡፡

ለመጀመሪያው አልበም ሥራህ ሙዚቃ ቤት ያገናኘህ ኮመዲያን ልመንህ ነበር፡፡ ኮሚሽን ከፍለኸው ነበር?

ልመንህ ታደሰ እኔን ብቻ ሳይኾን ነፍሱን ይማረውና ኬኔዲ መንገሻንም ከሶል ኩኩ ሙዚቃ ቤት ጋራ ያገናኘው እርሱ ነበር፡፡ እኔ በዛን ጊዜ የተዋዋልኩት በሦስት ሺሕ ብር ነበር፡፡ ግማሹን መጀመሪያ ተቀብዬ ቀሪው መጨረሻ ላይ ነው የተከፈለኝ፡፡ በወቅቱ ደግሞ አብረን አንድ ኪነት እንሠራ ስለነበር እርሱም ስጠኝ አላለኝም እኔም ኮሚሽን አልከፈልኩትም፡፡ በዛን ጊዜ ደግሞ ኮሚሽን የሚባል ነገር አይታወቅም ነበር፡፡

ሐሳቡም ቢተነፈስ ክፍያ የሚጠየቅበት ዘመን ላይ የደረስነው አሁን ነው፡፡

ልመንህን አግኝተኸው ታውቃለህ?

አሜሪካ እያለ በብዛት አገኘው ነበር እዚህ ከመጣ በኋላ ግን አግኝቼው አላውቅም፡፡ ለማግኘት በጣም ሞክሬ ነበር ስልም አልዋሽም፡፡ አልበምህን ባወጣህ ሰሞን ወደ ድሬደዋ እና ሐረር ለ27 ቀናት ኮንሰርት ሠርተህ ነበር ክፍያው ጥሩ ነበር? ለሥራው የወሰዱኝ ጅጅጋ ውስጥ የነበሩ የወታደር ባንድ ነበር፡፡ በቀን 700 ብር ይከፈለኝ ነበር፡፡ መድረክ ላይ በወጣሁ ቁጥር ደግሞ ሽልማት ነበረኝ፡፡ የሄድኩት አልበሜ በወጣ በአንድ ወሩ ስለነበር በዚያች በአጭር ጊዜ ድሬደዋ፣ሐረር፣ጅጅጋ፣አለማያ፣ ሂርና እያዞሩኝ ስዘፍን ሕዝቡ ዘፈኖቼን ለምዶና ወዶት ስለተቀበለኝ ገንዘቡ ላይ ትኩረት አላደረኩበትም እንጂ የቆየሁበት ቀናት ተቆጥሮ ለወቅቱ በጣም ጥሩ ክፍያ ነበር የተከፈለኝ፡፡ በዛ ላይ ሁሉንም ወጪዬን ችለው እንዲሁም የምንጓጓዝበትን ትራንስፖርት ሸፍነው ስለሚያንቀሳቅሱኝ የሰጡኝን ገንዘብ ሳልነካው ነበር አዲስ አበባ የተመለስኩት፡፡

በምን ነበር የምትጓጓዙት?

ዘፋኝ ስለነበርኩ ጋቢና ይታዘዝልኛ እንጂ በ‹‹አይፋ›› (ትልቁ የወታደር መኪና) እየተጓጓዝን ነበር የምንሠራው፡፡

ምን ዓይነት መድረክ ላይ ነበር የምትሠራው? ምን ያህል ሰው ይታደም ነበር?

በተለያዩ አዳራሾች ውስጥ ነበር፡፡ እኛ ከመድረሳችን በፊት ከተማ ውስጥ እየገቡ የሚቀሰቅሱ ልጆች ስለነበሩ የከተማውን ሰው አነቃቅተው ይጠብቁናል፡፡ በአንድ መድረክ እስከ 400 ሰው ይታደም ነበር፡፡ በጣም ደስ የሚል ጊዜ ነበር፡፡

‹‹እሄዳለሁ ሐረር ባቡር ተሳፍሬ›› የሚለው ዘፈንህን የሚያዳምጡ ሰዎች ‹‹አንደኛ ሐረር ባቡር የለም፡፡ ሁለተኛ እርሱ የሚለውን ፍራፍሬ የለም›› ሲሉ ይወቅሱሃል፡፡ የቪዲዮ ክሊፑንስ እዛው ሄደህ ነበር የተቀረጽከው?

አይደለም፡፡ አዲስ አበባ ስቱዲዮ ውስጥ ነው የተቀነባበረው፡፡ ግን ቦታው ሂርና አካባቢ ነበር፡፡ ሐረር ከባቡር ጋራ ለምን ተያያዘ ለሚባለው መውረጃው ድሬደዋ ይሁን እንጂ ሐረር ለመሄድ እኮ ባቡር መሳፈራችን ግድ ነበር፡፡ከድሬደዋ በኋላ በመኪና ሐረር እንገባለን፡፡ ፍራፍሬውም በወቅቱ የነበረው ነው፡፡ ያን ግዜ ስንሄድ የነበረው ጫካ ውበት ራሱ ትዝ ይለኛል፡፡ እንደዛኛው ግዜ በብዛት አይኑር እንጂ በፍራፍሬ እንኳን ሐረር እና ድሬደዋ አሁንም አይታሙም፡፡ ሁለቱም በጣም የምወዳቸውና የሚመቹኝ ከተሞች ናቸው፡፡

የሠርግ ሥራዎችህን ቀጠሮ በመያዝና በመደራደር በአገር ፍቅር ትያትር ቤት የዘመናዊ ዳንስ አሰልጣኟ ባለቤትህ ወ/ሮ ዘነበች ጌታሁን እንደምታግዝህ ሰምቻለሁ፡፡ ከአንተ እና ከእርሷ ዋጋ ማን ይቀንሳል?

ባለቤቴ ሥራ ስላላት የምታግዘኝ በትርፍ ጌዜዋና ከኢትዮጵያ ውጭ ስሆን ነው እንጂ እኔ ሁልጊዜ እርሷ ብትሆንልኝ ደስ ይለኛል፡፡ ምክንያቱም እኔ ብዙ የማወዳድራቸው ነገሮች አሉ አንዳንድ ግዜ እኔ ተጎድቼ ብሠራስ የምልባቸው ሥራዎች አሉኝ፡፡

ሴቶች ሰዎችን አግባብቶ የማሠራት አቅም ስላላቸው ለንግድ ሥራ ጎበዝ ናቸው፡፡ ስለዚህ እርሷ ስትሆን ጠንከር ስለምትል ጥሩ የመደራደር አቅም አላት፡፡

አልበም ከማውጣትህ ካለፉት 25 ዓመታት ጀምሮ በዓመት ከ30 እስከ 40 ሠርግ ትሠራለህ?

በተለየ ሁኔታ የምታስታውሰው ሠርግ እና ሙሽራ አለ? ማስተካከያ ይደረግልኝ፡፡ የተጠቀሰው ቁጥር ቀደም ሲል የነበረ ነው፡፡ ካለፉት ሁለት እና ሦስት ዓመታት ወዲህ የሠርግ ሥራ ቀንሷል በዓመት 15 ሠርግ እንኳን አይገኝም፡፡ ለዚህ ደግሞ ጊዜ ያመጣቸው የተለያዩ ምክንያቶቹ አሉ፡፡ በእኔ በኩል ግን ይችን ታህል ካገኘን ተመስገን ይበቃል ነው የምለው፡፡ የሚገርመው ከዚህ ሁሉ ሙሽራ ላወራበት የምችለው በተለየ የማስታውሰው የተጋነነ ነገር የለኝም፡፡

የሠርግ ሥራ መለያህ ኾኗል፤ ኮንሰርት ትሠራለህ?

አዎ ከኢትዮጵያ ውጪ እየተጋበዝኩ ለተለያዩ ፕሮግራሞች እሠራለሁ፡፡ እዚህ አገር ግን ፕሮግራም ይኖረዋል ወይም ደግሞ ጸጋዬ የሠርግ ድምፃዊ ብቻ ነው ተብሎ እንደሆነ አላውቅም ኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ አልታይም፡፡ ምናልባት ነገ ከነገወዲያ ምን እንደሚፈጠር አላውቅም፡፡      የማኅበራዊ ድረ-ገጽ ፌስቡክ ተጠቃሚ ነህ?

አዎን ተጠቃሚ ነኝ፡፡ ፌስቡክ በጣም ጠቃሚ ነገር መሆኑን ያወኩት አሁን ነው፡፡ ዱሮ አልበም ስናወጣ የሕዝቡን አስተያየት ማግኘት የምንችልበት መንገድ በጣም የተጣበበ ነበር፡፡ ግፋ ቢል አንዳንድ ታታሪ ሰዎች በፖስታ ከሚልኩት አስተያየት በቀር እንዲህ በቀጥታ አስተያየት የምናገኝበት እኛም የምንፈልገውን መልእክት በፈለግነው ሰዓት በቀጥታ የምናስተላልፍበት መንገድ አልነበረም፡፡ አሁን ይህንን አዲሱን ሥራዬን ስሠራ ሥራዬን አስተዋውቄበታለሁ፡፡ ወዳጆቼም ከሚገባው በላይ አስተያየት በመስጠት አበረታተውኛል፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አስደስቶኛል፡፡ በቅርቡ የተቋቋመው የድምፃውያን ማኅበር ፕሬዝዳንት ነህ ከምስረታችሁ በኋላ ምን ሠራችሁ? ማኅበሩን የመሰረትነው በቅርብ ነው፡፡ ለረጅም ጊዜያት ለድምፃውያን የሚናገሩላቸው ሌሎች ሰዎች ነበሩ፡፡

ነገር ግን የራሳቸው የኾነ በርካታ ችግሮች አሏቸው፡ ይህን ችግራችንን ሰብሰብ ብለን በጋራ ለምን አንፈታውም በሚል የሞያ ማኅበር መቋቋሙን አምነንበት ነው የመሠረትነው፡፡ የማኅበሩን ፈቃድ ካገኘን በኋላም በርካታ ድምፃውያንን በአባልነት ተቀብለን ደስ በሚል መንፈስ የመጀመሪያ ጠቅላላ ጉባኤያችንን አካሂደን ጉባኤው አመራሩን መርጧል፡፡ ለቦርድ አመራርነት የተመረጥነው እኔን ጨምሮ አመልማል አባተ፣ ሚካኤል በላይነህ፣ ቴዎድሮስ ሞሲሳ፣ ጸደኒያ ገ/ማርቆስ፣ ታደለ ገመቹ እና ብርሃኑ ተዘራ ነን፡፡ አሁን ብሬ ላልተወሰነ ጊዜ ከኢትዮጵያ ውጪ ስለምሄድ በሌላ ሰው ተኩኝ እያለ ነው፡፡ እናም አሁን ማኅበሩን በገንዘብ ለማጠናከር የሚያስችለንን ሥራ እየሠራን ነው፡፡ በቀጣይ ባለን ዕቅድ ለባለሞያው ጠቃሚ የኾነ ጥሩ ሥራዎችን ለማከናወን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ ይህን ደግሞ ወደፊት የምታዩት ይኾናል፡፡