Administrator
እንደ ንጉስ የኖሩት ተራማጁ ፊደል ካስትሮ
ታጋዮች የህዝብ ጫማ ናቸው፤ ታጋዮች የግል ጥቅምና ምቾታቸውን በሰፊው ህዝብ ጥቅምና ምቾት የቀየሩ የህዝብ መድህኖች ናቸው፤ ታጋዮች ለህዝባቸው ምቾትና ድሎት ሲሉ ከፍተኛ መስዋዕትነት የሚከፍሉ የህዝብ ቤዛዎች ናቸው፡፡…
እነዚህን የመሳሰሉ የአብዮታውያን የፕሮፓጋንዳ ርግረጋዎች የኢትዮጵያ አብዮት በግብታዊነት ፈነዳ ከተባለበት ከየካቲት 1966 ዓ.ም ጀምሮ አብዮታዊና ተራማጅ ነን ከሚሉ ሃይሎች ዘንድ ስንሰማው የኖርነውና ዛሬም እየሰማነው ያለነው ጉዳይ ስለሆነ ምንም አስደናቂ ነገር የለውም፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ይህ የአብዮታውያኑ መሀላ፣ የታጋዮቹን ሰውነትና የሰውን ልጅ ባህርይ በወጉ ከግምት ውስጥ ያስገባ አይደለም፡፡ እናም ነገሩ አብዛኛውን ጊዜ የሚባለውን ያህል ትክክል ወይም እውነት ሆኖ አይገኝም፡፡ ይህን ለማረጋገጥ ደግሞ ማስረጃ ፍለጋ የአለም አብዮተኞችን የታሪክ መዝገብ ማገላበጥ ጨርሶ አያስፈልገንም፡፡ የሀገራችን አብዮተኞች ታሪክ ከበቂ በላይ ነው፡፡
የጊዜያዊ ወታደራዊ መንግስት መሪዎች በስልጣን ላይ በቆዩበት አስራ ሰባት አመታት ሰፊውን የኢትዮጵያ ህዝብ ከአስከፊ ድህነት ለማላቀቅ ሲሉ አንድም ቀን እንኳ ሳይደላቸውና ሳይስቁ ከፍተኛ መስዋዕትነት ይከፍሉ እንደነበር በተደጋጋሚ ይናገሩ ነበር፡፡ እነዚህ አብዮታውያን ወታደራዊ መሪዎች በተግባር ያደረጉት ግን ካለፈው እጅግ የከፋ ድህነትን ለሰፊው ህዝብ እኩል በማካፈል፣ ራሳቸውንና የራሳቸውን ወገን ከድህነት ማላቀቅ ነው፡፡
“አብዮታዊውን” ወታደራዊ መንግስት ለአስራ ሰባት አመታት በዘለቀ የትጥቅ ትግል የዛሬ 23 አመት አሸንፎ ስልጣን የተቆጣጠረው ኢህአዴግ፣ ተራራ ያንቀጠቀጡት ታጋዮቹ በግል ጥቅምና ምቾት የማይንበረከኩ፣ የህዝብ ጥቅም፣ ምቾትና ብልጽግና የመጀመሪያም የመጨረሻም የትግል ግባቸው እንደሆነና ለዚህም ግብ መሳካት የህይወት መስዋዕትነት እንደከፈሉ በተደጋጋሚ ሊያስረዳን ሞክሯል፡፡
ጥረቱ ያላቋረጠና ከባድ መሆኑ ሲታይ ደግሞ ኢህአዴግም እንደሌሎቹ አብዮታዊ ድርጅቶች ሁሉ የታጋዮቹን ሰውነት ጨርሶ የረሳ አስመስሎት ነበር፡፡ የማታ ማታ በተግባር የታየው ግን በቃል ከተወራው በእጅጉ የተለየ ነበር፡፡ የራሳቸውን ጥቅምና ብልጽግና ከምንም ሳይቆጥሩ ለህዝባቸው ጥቅም፣ ምቾትና ብልጽግና እውን መሆን የህይወት መስዋዕትነት ለመክፈል ለአፍታም እንኳ አያመነቱም ተብለው ብዙ እጅግ ብዙ የተነገረላቸው “አብዮታውያን” ታጋዮች “የከተማ ስኳር ፈታቸው፤ የድል ማግስት ህይወት ጽኑ የትግል መንፈስና ስሜታቸውን ሰልቦ ከማይወጣው የትግል አላማቸው አሳታቸው” ተብሎ በራሳቸው ድርጅት አንደበት ተነገረባቸው፡፡
ይህንን በይፋ የተናገረው ድርጅታቸው ኢህአዴግ፤ በዚህ ብቻ አላበቃም፡፡ በማግስቱ እንደ ከፍተኛ የድርጀቱና የሀገር መሪነታቸው ለሌሎች አርአያ መሆን ሲገባቸው፣ በከተማው ስኳር ተታለው ከህዝብ ጥቅምና ብልጽግና ይልቅ ለራሳቸው ጥቅም፣ ምቾትና ብልጽግና ሌት ተቀን ሲጥሩና ህገወጥ ድርጊቶችን ሲፈጽሙ አግኝቻቸዋለሁ ያላቸውን ከፍተኛ የኢህአዴግና የመንግስት ባለስልጣናት እንደ እጅ ስራቸው መጠን ህግ ያውጣቸው ብሎ ዘብጥያ አወረዳቸው፡፡
የአብዮታዊቷ ኩባ ታሪክም ከኢትዮጵያም ሆነ ከሌሎቹ አብዮተኛ ሀገራት የተለየ አይደለም፡፡ እንደ አውሮፓውያን ዘመን አቆጣጠር በ1959 ዓ.ም የባቲስታን መንግስት በትጥቅ ትግል አስወግደው ስልጣን ስለተቆጣጠሩት የኩባ አብዮታዊ ታጋዮች ያልተባለና፣ ያልተነገረ ገድል አለ ለማለት ያስቸግራል፡፡ በተለይ ደግሞ የኩባ አብዮት ግንባር ቀደም መሪና የኩባ ጭቁን ህዝብ አባት ስለሚባሉት ስለ ጓድ ፊደል ካስትሮ በቃል ያልተነገረ፣ በጽሑፍ ያልተፃፈ፣ በፊልምም ያልቀረበ… እራስን ለህዝብ ጥቅም አሳልፎ ስለመስጠት ገድል.. ለሞት መድሃኒት እንኳ ፈልጐ ማግኘት አይቻልም፡፡
ራሳቸውን ለሰፊው ጭቁን የኩባ ህዝብ ፍፁም አሳልፈው የሰጡና ከወታደር ካኪ ሌላ የረባ ልብስ እንኳ የላቸውም እየተባለ ነጋ ጠባ የሚወደሱት ጓድ ፊደል ካስትሮ ግን እንደሚወራላቸው አይነት ሰው ሳይሆኑ ይልቁንም ልክ እንደ አንድ ታላቅ ንጉስ እጅግ በተንደላቀቀ ሁኔታ በምቾት የኖሩ ሰው እንደሆኑ ከተለያዩ ወገኖች በሹክሹክታ ሲወራ ቢከርምም ማረጋገጥ ሳይቻል ቆይቶአል፡፡
ሁዋን ሮናልዶ ሳንቸዝ የተባለ የ65 አመት ጐልማሳ ኩባዊ ግን ይህንን የሚያረጋግጥ ማስረጃ በቅርቡ ይፋ አድርጓል፡፡ ከ1977 እስከ 1994 ዓ.ም የፕሬዚዳንት ካስትሮ የቅርብ አማካሪና ከታናሽ ወንድማቸው ከራውል ካስትሮ ቀጥሎ እጅግ ጥብቅ ሚስጥረኛቸው የነበረው ሁዋን ሮናልዶ ሳንቸዝ፣ በቅርቡ ባሳተመው መጽሐፍ፤ ፕሬዚዳንት ጓድ ፊደል ካስትሮ 20ትላልቅ የቅንጦት መኖሪያ ቤቶች፣ የግል ደሴትና የመዝናኛ ጀልባ አሏቸው፡፡
የኩባው አብዮተኛ ጀግና ጓድ ፊደል ካስትሮ፤ በተጠቀሰው አመት ውስጥ በከፍተኛ ሚስጥር ይካሄድ በነበረ የእፅ ዝውውር ንግድ ውስጥ ተሳታፊ ነበሩ፡፡ ሀቫና ከተማ አቅራቢያ ባቋቋሙት የወታደራዊ ማሰልጠኛ ካምፕ ውስጥም እንደ አይ አር ኤ የመሳሰሉ ታጣቂ የሽብር ቡድኖችን ያሰለጥኑ ነበር፡፡
2 ሚሊዮን ዶላር የተሸጠው የዘፈን ግጥም
የታዋቂው ድምጻዊ ቦብ ዳይላን አንድ የዘፈን ግጥም፣ ሰሞኑን ሱዝቤይ በተባለው አለማቀፍ አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለጨረታ ቀርቦ 2 ሚሊዮን ዶላር በመሸጥ ክብረወሰን ማስመዝገቡን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
ከቦብ ዳይላን ታዋቂ ስራዎች አንዱ የሆነው ‘ላይክ ኤ ሮሊንግ ስቶን’ የተባለው ዘፈን ግጥም፣ በራሱ በድምጻዊው የተጻፈ ሲሆን፣ በአራት ነጠላ ወረቀቶች ላይ በእርሳስ የተጻፈው የግጥሙ ኦሪጅናል ኮፒ ነው በጨረታው የተሸጠው፡፡
ቦብ ዳይላን የከፍተኛ መደብ አባላት በሚኖሩበት ማህበረሰብ ውስጥ የብቸኝነት ኑሮን በምትገፋ አንዲት ባይተዋር ሴት ዙሪያ የሚያጠነጥነውን ይህን የዘፈን ግጥም፣ የ24 ዓመት ወጣት ሳለ ነበር እ.ኤ.አ በ1965ዓ.ም የጻፈው፡፡
የአጫራቹ ኩባንያ ባልደረባ የሆኑት ሪቻርድ ኦስቲን እንዳሉት፣ የቦብ ዳይላን ሥራዎች በዘመናዊው ሙዚቃ ጉዞ ላይ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ያበረከቱና አቅጣጫ የቀየሩ ናቸው፡፡
ግጥሙን ለአጫራቹ ኩባንያ ያቀረበው ግለሰብ ማንነት ባይገለጽም፣ የድምጻዊው የረጅም ጊዜ አድናቂ መሆኑ ተነግሯል፡፡
ከዚህ በፊት ለጨረታ ቀርቦ በከፍተኛ ዋጋ በመሸጥ ክብረወሰኑን ይዞ የነበረው፣ እ.ኤ.አ በ1967 በታተመው ‘ሎንሊ ሃርትስ’ የተሰኘ አልበም ውስጥ የተካተተው የታዋቂው ድምጻዊ ጆን ሌነን ሙዚቃ፣ ‘ፎር ኤ ዴይ ኢን ዘ ላይፍ’ የተሰኘ ግጥም ነበር፡፡ ግጥሙ ከሶስት አመታት በፊት ለጨረታ ቀርቦ በ1 ነጥብ 2 ሚሊዮን ዶላር መሸጡን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
የጸሐፍት ጥግ
(ስለ ሂስና ሃያስያን)
ሃያሲ ማለት መንገዱን የሚያውቅ ነገር ግን መኪና ማሽከርከር የማይችል ሰው ነው፡፡
ኬኔዝ ቲናን
(እንግሊዛዊ የትያትር ሃያሲ)
ፊልሞቼን የምሰራው ለህዝቡ እንጂ ለሃያስያን አይደለም፡፡
ሴሲል ቢ.ዲ.ሚሌ
(አሜሪካዊ የፊልም ፕሮዲዩሰርና ዳይሬክተር)
ነፍሳት የሚነክሱን ለመኖር ብለው እንጂ ሊጎዱን አስበው አይደለም፡፡ ሃያስያንም እንደዚያው ናቸው፤ ደማችንን እንጂ ስቃያችንን አይሹም፡፡
ፍሬድሪክ ዊልሄልም ኒቼ
(ጀርመናዊ ፈላስፋና ገጣሚ)
ሃያስያን ለሚሉት ነገር ትኩረት አትስጡ፡፡ ለሃያሲ ሃውልት ቆሞለት አያውቅም፡፡
ዣን ሲቤሊዩስ
(ፊንላንዳዊ የሙዚቃ ቀማሪ)
ሰዎች ሂስ እንድትሰጣቸው ይጠይቁሃል፤ የሚፈልጉት ግን ሙገሳ ብቻ ነው፡፡
ሶመርሴት ሟም
(እንግሊዛዊ ደራሲ)
ሃያሲ ህግ ሳይሆን አስተላላፊ፣ ድልድይ መሆን አለበት፡፡
ቶኒ ሞሪሶን
(አሜሪካዊ ደራሲ)
ጌታዬ፤ ዝንብ ትልቁን ፈረስ ልትነክሰውና ዓይኑን ልታርገበግበው ትችላለች፡፡ ይሄ ግን አንደኛቸው ነፍሳት፣ ሌላኛቸው ፈረስ መሆናቸውን አይለውጠውም፡፡
ሳሙኤል ጆንሰን
(ስለሃያስያን የተናገረው)
ሃያስያን እነማን እንደሆኑ ታውቃላችሁ? በሥነጽሑፍና በሥነጥበብ ዘርፍ ያልተሳካላቸው ሰዎች ናቸው፡፡
ቤንጃሚን ዲስራሊ
(የእንግሊዝ ጠ/ሚኒስትርና ፀሐፊ የነበሩ)
ሃያስያን የሚሉትን ብሰማቸው ኖሮ፣ በስካር ናውዤ የውሃ አሸንዳ ስር እሞት ነበር፡፡
አንቶን ቼኾቭ
(ሩሲያዊ ደራሲ)
ሽልማት የሚያሸንፉ ትያትሮች የሚፃፉት ለሃያስያን ብቻ ነው፡፡
ሊው ግሬድ
(ዩክሬን ተወላጅ እንግሊዛዊ
የፊልምና ቴሌቪዥን ፕሮዲዩሰር)
ማራኪ አንቀፅ
…የኢትዮጵያ መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር በትግራይ ክልል ርእሰ መስተዳድር ጽሕፈት ቤት፣ መቀሌ፣ ከረፋዱ 3፡30 ላይ፡፡
አሥራ አንዱም የትግራይ ሕዝብ ሐርነት ግንባር የፖሊት ቢሮ አባላት በርእሰ መስተዳድሩ ቢሮ ለአስቸኳይ ስብሰባ ተቀምጠዋል፡፡ የድርጅቱ ሊቀመንበርና የኢትዮጵያ መንግስት ጠቅላይ ሚኒስትር በሰብሳቢ ቦታቸው ተሰይመዋል፡፡ የፓርቲ ስብሰባዎች ላይ ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት ቀለል ያሉ አልባሳትን ተጠቅመዋል፡፡ ነጣ ያለ ጉርድ ሸሚዝ፣ ቀለል ካለ ባለ ዚፕ ውሃ ሰማያዊ ጃኬት ጋር፡፡ አጠገባቸው ማንም አልነበረም፡፡
በትጥቅ ትግሉ ወቅት የተጐሳቆለ የፊታቸው ገጽታ ፍጹም መልኩን ቀይሮ ሞላ ብሎ ይታያል፣ ወትሮ ወደ ቢጫነት የሚያዘነብለው የፊት ቆዳቸው ጽድት ከማለቱ የተነሳ ራሰ - በረሃቸውን መስሏል። ከግንባራቸው አንስቶ በአገጫቸው ዙሪያ ክብ ሰርቶ የሚያልፈው ጠየም ያለ የፊት መስመር ፊታቸውን ፍሬም ውስጥ የተቀመጠ ውድ ፎቶ አስመስሎታል፡፡ ጠርዝ አልባ መነጽራቸውን ሰክተውም ቢሆን ቅልብልብ የሚሉት ዓይኖቻቸው አያርፉም፡፡ በአንድ ጊዜ ሺ ነፍስን የመቆጣጠር ተፈጥሮን የተቸሩ ናቸው፡፡ በሲጋራ ጢስ ጠይመው የነበሩ ትንንሽና ግጥምጥም ያሉ ጥርሶቻቸው እንደነገሩ ጸድተው እጭ መስለዋል፡፡ የዛሬው ስብሰባ የሲጋራ ፍጆታቸውን በሁለት አሀዝ የሚያስጨምር እንደሚሆን አላጡትም፡፡
የተወሰኑት የፖሊት ቢሮ አባላት የቢሮውን ግርግዳ ተከትለው መደዳውን በተደረደሩ ጥቁር የፕላስቲክ ሶፋ ወንበሮች ላይ ዘርዘር ብለው ተቀምጠዋል፡፡ ከፊሎቹ በተዘረጉ ማስታወሻ ደብተሮቻቸው ላይ አንዳች ነገር ይቸከችካሉ፡፡ የተቀሩት ፊታቸውን ወደ መድረኩ መልሰው ሊቀመንበሩ በትግርኛ ቋንቋ የሚናገሩትን በአንክሮ ይከታተላሉ፡፡ ሰብሳቢያቸው ተናግሮ ማሳመን ጥርሳቸውን የነቀሉበት ጥበብ ስለመሆኑ አይጠራጠሩም፡፡ በርሃ ሳሉ ጀምሮ ድንጋዩን ዳቦ ነው እያሉ ያሳምኗቸዋል፡፡ ዛሬ ያ እንዳይደገም የሰጉ ይመስል ጠቃሚ የሚሉት ነጥብ የተነገረ በመሰላቸው ቁጥር በማስታወሻቸው ያሰፍራሉ፡፡ የዕለቱ የመነጋገሪያ አጀንዳ “ኤርትራና የወረራ አደጋ” የሚል ነበር፡፡ ሊቀመንበሩ ባለሁለት ቀለም ገጽታ ካለው የፊታቸው ገጽ ላይ የሚታየውን ብርቱ መሰላቸት መደበቅ እንዳልቻሉ ሁኔታቸው በግልጽ ይናገራል…
“እኔ እስኪገባኝ ድረስ ማንኛውም ዓለም አቀፍ ጦርነት በአንድም ይሁን በሌላ መልኩ ፖለቲካዊ ምክንያት አለው…” ብለው ረገጥ አድርገው መናገር ቀጠሉ፤ እንደዚህ ረገጥ አድርገው መናገር ከጀመሩ ሰውየውን መርታት ዳገት እንደመግፋት ከባድ እንደሚሆን የሚያውቁት የትግል አጋሮቻቸው ማስታወሻ ደብተሮቻቸው ላይ ተደፍተው ይጫጭራሉ። “…ኤርትራ ኢትዮጵያን የምትወር ከሆነ የሕዝባዊ ግንባር መሪዎች ይህ ምክንያት ለእነሱም ያስፈልጋል፡፡ በኔ እምነት እነዚህ መሪዎች በሦስት አሳማኝ ምክንያቶች ኢትዮጵያን ለመውረር የሚያደፋፍር ግፊት ሊኖራቸው አይችልም፡፡ የመጀመሪያው ነጥብ ለሠላሳ ዓመታት ደም ያፋሰሳቸው የነፃነት ጥያቄ ለሁለተኛ ጦርነት መንስኤ የሚሆን አንድም ሽርፍራፊ ሰበብ ሳይተው መልስ አግኝቷል… እደግመዋለሁ፡፡ ቅንጣት ሽርፍራፊ ሰበብ ሳይተው መልስ አግኝቷል ይህ ለአሁኑ መሪዎች በመንግሥት ደረጃ ነፃና እኩል ሆነው የመደራደር ሉዓላዊ መብት አስገኝቶላቸዋል፡፡
አሁን ምናልባት የቀሩ ጥቃቅን ችግሮች ቢኖሩ ወይም ወደፊት ቢከሰቱ ይህንን ሉአላዊ ስልጣን ሊጠቀሙ ይችላሉ ብቻ ሳይሆን የተለየ ሌላ አማራጭም የላቸውም፡፡ ይህ አሁን መሬት ላይ ያለው እውነታ ነው። ይህን ግንዛቤ ከወሰድን ዘንዳ በዚህ መሐል ጦርነት ሊፈጠር የሚችለው አንድም በእብደት አልያም ደግሞ አዲስ ጦር መሣሪያ በጀብደኝነት ለመሞከር ከተፈለገ ብቻ ነው…”
ሊቀመንበሩ ዓይኖቻቸውን ተራ በተራ ከሚያይዋቸው ጓደኞቻቸው አንስተው ወደ ማስታወሻ ደብተራቸው የተከፈተ ገጽ መለሱ… ጠርዝ… አልባ መነጽራቸውን ሽቅብ ወደ አፍንጨቸው ገፋ አደረጉት፡፡
(“አውሮራ” ከተሰኘው የሀብታሙ አለባቸው ልቦለድ መፅሃፍ የተቀነጨበ)
ጤናማ አመጋገብ ይኑርዎት
ጤናማ አመጋገብ ከተከተሉ ጤናማ የሰውነት ገጽታ ይኖርዎታል፡፡ ለጋ ፍራፍሬና አትክልት የሰውነት ቆዳ ህዋሳትን ይበልጥ የማይናወጡ በማድረግ ጤንነታቸውን የሚጠብቁ ሲሆኑ ከዶሮና ከዓሳ የሚገኘው ሊን ፕሮቲን ደግሞ የሰውነት ቆዳ እንዲታደስ በማድረግ ከፍተኛ ጠቀሜታ ያለው ነው።
ውሃ ይጠጡ
የጤና ባለሙያዎች በቀን ከ6 እስከ 8 ብርጭቆ ውሃ እንዲጠጡና መርዛማነት ያላቸው ንጥረ ነገሮችን ከሰውነትዎ እንዲያስወጡ ይመክራሉ። ከባድ አይደለም፤ ሁሌም ምግብ ከመመገብዎ በፊትና በኋላ አንድ አንድ ብርጭቆ ውሃ ቢጠጡ እንኳን ስድስት ብርጭቆ ይደርሳሉ፡፡
ከሰውነት ቆዳዎ ላይ
የሞተ ቆዳን ያስወግዱ
በሳምንት ሁለት ሶስቴ ቀስ በለው ከሰውነትዎ ላይ የሞቱ ህዋሶችን ያስወግዱ፡፡
ከዚያን በኋላ የሚጠቀሙት የሰውነት ቆዳ መንከባከቢያ ምርት በአግባቡ በቆዳዎ ላይ መስራት እንዲችል ያደርገዋል።
እነዚህን ቀላል መንገዶች በአግባቡ ከተጠቀሙ የሰውነት ቆዳዎ ገጽታ ተመሳሳይነት ያለውና ወጥ ይሆናል፡፡ በቀላሉ ቆዳዎ ወደነበረበት ጤናማ ሁኔታ መመለስ ይችላሉ፡፡
ጤናማ የሰውነት ቆዳ
- ቤተሰባዊ ጉዳይ ነው
የሰውነታችን ቆዳ ከሰውነታችን አካሎች ሁሉ ትልቁና መላ ሰውነታችንን የሚሸፍን ነው። እንደ ሙቀት፣ ጨረርና በሽታ አምጪ ተዋህሲያን ካሉ ነገሮች ይጠብቀናል፡፡ ከባድ ነገሮችን ከሰውነታችን አካሎች ሁሉ ቀድሞ የሚከላከለን አካላችን ነው፡፡ ጤናማ የሰውነት ቆዳ በከፍተኛ ሁኔታ ያስፈልገናል፡፡
የሰውነታችን ቆዳ ሌላው ከፍተኛ ጥቅሙ የሰውነታችንን የሙቀት መጠን ማመጣጠን፣ የውሃ ብክነትንና ባክቴሪያው ሰውነታችን እንዳይገባ መከላከል ነው፡፡ በጣም ወሳኝ የሰውነታችን አካል በመሆኑ ተገቢውን እንክብካቤ ልናደርግለት ይገባል፡፡ ስለዚህ ምርጥ የሆነ የሰውነት ቆዳ መንከባከቢያ መጠቀም አለብን፡፡
በአስራዎቹ ያሉ
ወጣቶች የሰውነት ቆዳ
በዚህ እድሜ ላይ የሰውነት ቆዳ ልዩ ትኩረት ይፈልጋል፡፡ የሰውነት ሆርሞን መቀያየር ጤናማ የሰውነት ቆዳን ሊያውክ ይችላል፡፡ በአስራዎቹ እድሜ ብጉር በከፍተኛ ሁኔታ የሚከሰት ሲሆን የጀርባ፣ የአንገትና የደረት አካባቢዎችን በተለይ ያጠቃል፡፡ በሰዎች ዘንድ ካለ የተሳሳተ አመለካከት አንዱ በብጉር የሚጠቃ የሰውነት ቆዳ ቅባታማ ስለሆነ በተጨማሪነት ሎሽን አያስፈልገውም የሚል ነው፡፡ ይህ የተሳሳተ አመለካከት ነው፤ ቅባታማ የሆነ የሰውነት ቆዳ ተገቢውን የእርጥበት መጠን ካላገኘ ሴባሽየስ የሚባሉ የሰውነት እጢዎች የበለጠ ቅባት እንዲያመነጩ ያደርጋቸዋል፡፡ በየቀኑ ፊትንና መላ ሰውነትን በመታጠብ ቅባትንና ቆሻሻን ማስወገድ ያስፈልጋል፡፡
ዕድሜ ሲገፋ
የሚኖር የሰውነት ቆዳ
ዕድሜያቸው ለገፋ ምርጥ የሚባሉት የሰውነት ቆዳ መንከባከቢያ ምርቶች፣ ድርቀትንና ተመሳሳይነት የሌለው የሰውነት ቆዳ ገጽታን የሚያስቀሩ ናቸው። በየቀኑ ሻወር ከወሰዱ በኋላ በደንብ ሎሽን በመቀባት የሰውነት ቆዳን ማስዋብና ወጣት ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ቫዝሊን ቶታል ሞይስቸር ኮኮዋ ግሎው ሎሽን ተገቢ የሆነ እርጥበት በሰውነት ቆዳ ውስጥ እንዲኖር ያደርጋል፡፡ ለቆዳዎ ውበትንና ጤናማነትን ያላብሳል፡፡
በክረምት የሚከሰት
የሰውነት ቆዳ ችግርን ያስወግዱ
ብርዳማ አየር የሰውነት ቆዳን ሊያውክ ይችላል። የአየር የሙቀት መጠን ሲቀንስ በሰውነት ቆዳ ላይ የመድረቅ፣ የማሳከክና የመላላጥ ስሜት ይፈጥራል፡፡
ሌሎች ምክንያቶችም ለቆዳ መድረቅ መንስኤ ሲሆኑ፤ ለምሳሌ ለረጅም ጊዜ በሙቅ ውሃ ገላን መታጠብ በቆዳ ውስጥ ያለውን የእርጥበት መጠን እንዲጠፋ ያደርጋል፡፡ የመኖሪያ ቤትና የመኪና ውስጥ አየር ማሞቂያ በአየር ውስጥ ያለውን የእርጥበት መጠን ስለሚቀንሰው የሰውነትዎ ቆዳም በውስጡ ያለውን እርጥበት እንዲያጣ ያደርገዋል፡፡ እንዲህ አይነት ችግሮችን ለሰውነት ቆዳ ተገቢውን እርጥበት የሚሰጥ ትክክለኛ የሎሽን ምርት በመጠቀም ማስቀረት ይቻላል፡፡
(“ቫስሊን” ከሚለው ቡክሌት የተወሰደ)
የነጭ ሽንኩርትን መጥፎ ጠረን መከላከል ይቻላል
የነጭ ሽንኩርት ጠረን የሚፈጠረው ሰልፈር የተባለውን ማዕድን ከያዙ አራት ዋና ዋና ውህዶች ነው፡፡ እነዚህ ውህዶች ሲበሉ ደም ዝውውር ውስጥ ይገቡና በሳምባና በላብ ዕጢዎች ይወጣሉ፡፡ ይህ ሂደት ግን መጥፎ ጠረናቸው እንዲቀንስ አያደርግም። በኦሃዮ ስቴት ዩኒቨርሲቲ ያሉ የምግብ ሳይንቲስቶች፣ የነጭ ሽንኩርትን ጠረን ማጥፋት ባይችሉም፣ ሽንኩርት ከተበላ በኋላ የትኞቹ ምግቦችና መጠጦች ቢወሰዱ ጠረኑን ሊያለዝቡ (ሊቀንሱ) ይችላሉ በማለት ጥናት ያደረጉባቸውን ምግቦችና መጠጦች ባለፈው ኤፕሪል አንድ የጥናት ወረቀት አሳትመዋል፡፡ መረጃውን ያቀረበው ፖፑላር ሳይንስ፣ የተባሉትን ምግቦችና መጠጦች ሞክሮ መደምደሚያ ላይ መድረሱንም አውስቷል፡፡
ፖም (አፕል) ይብሉ፡- ለአየር ሲጋለጡ ወደ ቡናማ ቀለም የሚቀየሩ አትክልቶች የፕሮቲን መጠን የሚቆጣጠር ኢንዛይም (Oxidating enzyme) ይኖራቸዋል፡፡ የኦክሲጅንና ኢንዛይሙ ኮምፓዎንድ (ውህድ) የነጭ ሽንኩርቱን መጥፎ ሽታ የሚያጠፋ (የሚቀንስ) የኬሚካል ሰንሰለት ይፈጥራል፡፡ ስለዚህ ነጭ ሽንኩርት ከተመገቡ በኋላ ፖምን መብላት መጥፎ ሽታውን ይቀንሳል ብለዋል ሳይንቲስቶቹች፡፡
አረንጓዴ ሻይ ይጠጡ፡- ይህ ሻይ ፖሊፌኖልስ (Polyphenols) በተባለ የአትክልት ኬሚካል የተሞላ ነው፡፡ ኬሚካሉ ደግሞ በተመሳሳይ መንገድ አራቱንም የሰልፈር ውህዶች የሚፈጥረውን መጥፎ ሽታ ያጠፋል ወይም ይቀንሳል፡፡ ስለዚህ ነጭ ሽንኩርት ከበሉ በኋላ አረንጓዴ ሻይ ፉት ይበሉበት።
ትንሽ የሎሚ ጭማቂ ይጠጡ፡- የአሲድ መጠናቸው፣ ከ3.6 የዘ (የዘ የአሲድ መለኪያ ሲሆን የውሃ የአሲድ መጠን 7 ነው) በታች የሆኑ መጠጦች ነጭ ሽንኩርት ሲበላ ተነቃቅቶ የሰልፈር ሽታ እንዲፈጠር የሚያደርገውን alliinase የተባለ ኢንዛይም ያጠፋል፡፡ ስለዚህ ነጭ ሽንኩርት ከበሉ በኋላ ሎሚ መምጠጥ፣ ሌላ የሽታው መከላከያ አማራጭ ነው፡፡
የውርስ ነገር!...
“ልጆቼ ሆይ!... ከ182 ሚ. ፓውንድ ሃብቴ ሽራፊ ሳንቲም አላወርሳችሁም!” - ታዋቂው ሙዚቀኛ ስቲንግ
“በፍጹም!” አለ ስቲንግ፡፡
“በፍጹም አላደርገውም!... ይሄን ሁሉ ሃብትና ንብረቴን አውርሼ፣ በልጆቼ ላይ እንደመርግ የከበደ ጫና አላስቀምጥም!” በማለት እቅጩን ለጋዜጠኞች ተናገረ፡፡ ይህን የሰሙ የዓለማችን ታዋቂ ጋዜጦችና ድረ-ገጾችም፣ ያሳለፍነውን ሳምንት ነገሩን እየተቀባበሉ አሰራጩት። ስቲንግ እንዲህ አለ የሚሉ ዘገባዎች በስፋት ተነበቡ፡፡
ስቲንግ ማን ነው?
በቅጽል ስሙ ስቲንግ እየተባለ የሚጠራው ጎርደን ሰምነር፣ በሰሜናዊ ቲንሳይድ ዋልሴንድ የተባለች ከተማ ውስጥ የተወለደ እንግሊዛዊ ነው፡፡ አራት ልጆች ለነበሯቸው ወላጆቹ የበኩር ልጅ የሆነው ስቲንግ፣ እናቱ ጸጉር ሰሪ አባቱ መሃንዲስ ነበሩ፡፡ አባትዬው ከስራቸው ጎን ለጎንም ከብት ያልቡ ነበርና፣ ስቲንግም ልጅነቱን የገፋው አባቱ የሚያልቡትን ወተት በየሰፈሩ እየዞረ በማደል ነበር፡፡
ገና በልጅነቱ የሙዚቃ ስሜት በውስጡ ያደረበት ስቲንግ፤ የ10 አመት ልጅ ሳለ ጀምሮ ነበር የአባቱን ጓደኛ ጊታር አንስቶ ክሮቹን መነካካት የጀመረው። ሙዚቃ እንጀራው እስክትሆን ድረስ፣ ሌላ የእንጀራ መብያ ስራ መስራት ነበረበትና፣ ሳያማርጥ ስራዎችን ሰርቷል፡፡ በህንጻ ግንባታዎች የቀን ሰራተኛ ሆኖ አሸዋና ጠጠር አመላልሷል፡፡ የቀረጥ ሰብሳቢ ድርጅት ሰራተኛ ሆኖ ሌት ተቀን በትጋት ሰርቷል፡፡ ጎን ለጎን ትምህርቱን በመከታተልም፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን አጠናቆ ኖርዘርን ካውንቲስ ኮሌጅ በመግባት በመምህርነት ተመርቋል፤ ለሁለት አመታትም አስተምሯል፡፡
ስቲንግ ከአባቱ የከብቶች በረት ራሱን አውጥቶ፣ ህይወቱን ወደተሻለ አቅጣጫ ለማምራት ከልጅነት እስከ እውቀት ታትሯል፡፡ ኑሮውን ለማሸነፍ ደፋ ቀና ሲል ኖሯል፡፡ ከልጅነቱ አንስቶ በውስጡ የነበረው የሙዚቃ ፍቅር ግን፣ ወደኋላ ላይ ራሱን ከፍ ወዳለ ደረጃ የምታወጣው መክሊቱ ሆነች፡፡
በተውሶ ጊታር ጣቶቹን ማፍታታት የጀመረው ብላቴና፤ ቀስ በቀስ ራሱን አሰልጥኖ፣ በተለያዩ የምሽት ክለቦች ሙዚቃዎቹን ማቅረብ ቀጠለ፡፡ እንዲህ እንዲህ እያለም በአገረ እንግሊዝ ስማቸው ጎልቶ ከሚጠቀስ አርቲስቶች ጎራ ተቀላቀለ፡፡ በሂደትም በጃዝ፣ ሮክ፣ ሂፕ ሆፕና በተለያዩ ስልቶች የተቀነቀኑ ከ17 በላይ የቡድንና የነጠላ የሙዚቃ አልበሞችን ለአድማጭ አበረከተ፡፡ አለማቀፍ ኮንሰርቶችን በግሉና በቡድን በማቅረብ ዝናው ናኘ፡፡ በበርካታ ፊልሞችና የቴሌቪዥን ድራማዎች ላይ በተዋናይነት ተሳትፎ የጥበብ ክህሎቱን አስመሰከረ፡፡
በህይወቱና በስራዎቹ ዙሪያ የሚያጠነጥኑ 6 መጽሃፍት የተጻፉለት የ62 ዓመቱ ዝነኛ እንግሊዛዊ ድምጻዊ፣ የፊልም ተዋናይና ፕሮዲዩሰር ጎርደን ሰምነር (ስቲንግ) 16 የግራሚ ሽልማቶችን ተቀብሏል፤ የብሪት፣ ጎልደን ግሎብ፣ ኤሚ ተሸላሚ ሆኗል፤ የኦስካር ዕጩም ለመሆን በቅቷል፡፡
ሰውዬው በረጅሙ የሙያ ጉዞው ከፍተኛ ዝናን ብቻም አይደለም የተጎናጸፈው፣ ከባለጠጎች ተርታ የሚያስመድበውን ሃብት ጭምር እንጂ፡፡ የሙዚቃ ስራዎቹ በመቶ ሚሊዮን ኮፒ በአለም ዙሪያ ተቸብችበዋል፡፡ ወተት ሲያመላልስ ያደገው ድሃ አደግ ብላቴና፣ አሁን 182 ሚሊዮን ፓውንድ የሚገመት ሃብት ያፈራ ባለጸጋ ነው፡፡ “ሰንደይ ታይምስ” የአመቱ የእንግሊዝ 100 ቀዳሚ ባለጸጎች ብሎ ከመረጣቸው ሰዎች ተርታ ያሰለፈው፣ ከሶስት አመታት በፊት ነበር፡፡ በወቅቱ በእንግሊዝ የሙዚቃ ኢንዱስትሪ ውስጥ ከፍተኛ ሃብት ካፈሩ አስር ዝነኛ አርቲስቶች አንዱ ስቲንግ ስለመሆኑ ተመስክሮለታል፡፡ ስለዝናውም ስለ ሃብቱም ብዙ ተዘግቦለታል፡፡
ከሰሞኑ ደግሞ መገናኛ ብዙሃን ስለዚሁ ባለጸጋ አርቲስት ሌላ ዘገባ አሰራጭተዋል - “ስቲንግ ሃብቴን ለልጆቼ አላወርስም አለ” የሚል፡፡ የ182 ሚሊዮን ፓውንድ ባለጸጋው ስቲንግ፣ ባሳለፍነው እሁድ ከታዋቂው “ዘ ደይሊ ሜይል” ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስ ነበር፣ ልጆቹ የሃብት ንብረቱ ወራሾች እንደማይሆኑ በግልጽ የተናገረው፡፡
“ይሄን ሁሉ ገንዘብ ለልጆቼ ማውረስ፣ መጥቀም ሳይሆን መጉዳት ነው!... ሰርተው ያላገኙትን የውርስ ገንዘብ ለልጆቼ መስጠት፣ ሊሸከሙት የማይችሉትንና የሚያጠፋቸውን ከባድ ጫና በአንገታቸው ላይ እንደማሰር ነው የምቆጥረው፡፡” ብሏል ስቲንግ ለጋዜጠኞች፡፡
ይሄን የሰሙ ሌሎች መገናኛ ብዙሃንም ነገሩን እየተቀባበሉ አስተጋቡት፡፡ የሚያወርሱት የተትረፈረፈ ሃብት ይዞ፣ ለልጆች ላለማውረስ መወሰን ለእኛ እንጂ ለውጪው አለም አዲስ ባይሆንም፣ የስቲንግ ውሳኔ ግን የመገናኛ ብዙሃን ቀዳሚ ወሬ መሆኑ አልቀረም፡፡
ስቲንግ ውሳኔውን ያሳለፈው ለልጆቹ የማያስብ ጨካኝ አባት ሆኖ አይደለም፡፡ ሃብቱን ሳይሆን ትጋቱን ቢወርሱ እንደሚበጃቸው ስለተሰማው እንጂ። የራሳቸውን ህልም አልመው ቢነሱ የተሻለ ውጤታማ እንደሚሆኑ በማመኑ እንጂ፡፡ ይህን እምነት ደግሞ ከራሱ የህይወት ተመክሮ ነው የቀዳው፡፡
ልጆቹ አባታቸው ባፈራው የውርስ ሃብት ሳይሆን፣ የራሳቸውን መንገድ ተከትለው ተግተው በመስራት ውጤታማ መሆን አለባቸው ብሎ የሚያምነው ስቲንግ፤ እሱም በዚህ መንገድ ራሱን ወደ ስኬት ማድረሱን ያስታውሳል፡፡ እሱ የሚወረስ ሃብት ያፈራ አባት ያሳደገው ልጅ አይደለም፡፡ አባቱ የሚያልበውን ወተት በየቤቱ ሲያመላልስ፣ በቀን ሰራተኛነት የራሱን ጥሩ ቀን ለመፍጠር ሲባዝን ነው ያደገው፡፡ በአባቱ ውርስ ሳይሆን በራሱ ህልም ራሱን ሰው ለማድረግ ቃል ገብቶ ነው ረጅሙን ጉዞ የጀመረው፡፡
ትዝ ይለዋል፡፡ ልጅ እያለ አንድ ዕለት አንዲት የተከበሩ እንግዳ ወደሚኖርበት አካባቢ ለጉብኝት መምጣታቸውን ሰማ፡፡ ማናት ሴትዮዋ ሲል ጠየቀ፡፡ የእንግሊዟ ንግስት መሆናቸው ተነገረው፡፡ ብላቴናው ስቲንግ ወደጉብኝቱ ስፍራ አመራ፡፡ በግርግሩ ውስጥ ተሽሎክሉኮም አይኖቹን አሻግሮ ላከ፡፡
ንግስቲቱ በርቀት ታዩት፡፡ አሻግሮ እያያቸው ድምጹን ዝቅ አድርጎ የህይወቱን ግብ የተለመባትን ነገር ለራሱ ተናገረ - “ሃብታም፣ ታዋቂና ስኬታማ ሰው እሆናለሁ!... እኔም እንደ ንግስቲቷ ዘመናዊ ሮልስ ሮይስ መኪና እነዳለሁ!” በማለት፡፡
ስቲንግ እሆናለሁ ያለውን ሆነ፡፡ አሻግሮ ያማተራትን ስኬት ተግቶ ደረሰባት፡፡ ብዙ ዝና፣ ብዙ ክብር፣ ብዙ ሃብት አካበተ፡፡ ስቲንግ እዚህ የደረሰው በራሱ ጥረት እንደሆነ ያምናል፡፡ ይሄን ሁሉ ሃብት ያፈራው፣ በላቡ መሆኑን ያውቃል፡፡ ይሄን ስለሚያውቅና እንዲህ ስለሚያምን ነው፣ በእጆቹ የያዘውን ሃብት ለልጆቹ ላለማውረስ የወሰነው፡፡
ሶስት ወንድ እና ሶስት ሴት ልጆቹ እንደ እሱ ስኬታማ እንዲሆኑ፣ የእሱን መንገድ መከተል እንጂ የእሱን ሃብት መጠበቅ እንደሌለባቸው ነግሯቸዋል፡፡ ከአባታቸው ጥረትን እንጂ ጥሪትን እንዳይወርሱ አበክሮ መክሯቸዋል፡፡ በጥንታዊ አሰራር የተሰራው የእንግሊዙ ማራኪ ቤቱም ዊልትሻየር ውስጥ የሚገኘውን ዘመናዊ ቪላውን፣ በገጠራማዋ የእንግሊዝ የሃይቆች አውራጃ የሚገኘው የተንጣለለ ቤቱን፣ የኒውዮርኩን ዘመናዊ ቤቱንም ሆነ የጣሊያኑን የሪል ስቴት መኖሪያውን… ሁሉንም እንወርሳለን ብለው እንዳያስቡ ከአሁኑ እቅጩን ነግሯቸዋል፡፡“ልጆቼ ተግተው መስራት እንዳለባቸው ነው የማምነው፡፡ ይህንንም ስለሚያውቁ፣ ሁሉም ልጆቼ አልፎ አልፎ ካልሆነ በቀር ምንም አይነት ድጋፍ አጠይቁኝም። ይህ ደግሞ ይበል የሚያሰኝ ነገር ነው፡፡ ችግር ውስጥ ካልሆኑ በቀር፣ የገንዘብ ድጋፍ አድርጌላቸው አላውቅም። በራሳቸው ተሰጥኦና ችሎታ ተጠቅመው ስኬታማ የመሆን ፍላጎት የሚያሳድርባቸውን ይሄን አካሄድ ነው የሚከተሉት፡፡” ብሏል ስቲንግ፤ ስለልጆቹ ሲናገር፡፡
“ይሄን ሁሉ ገንዘብ ለልጆቼ ማውረስ፣ ከጥቅሙ ይልቅ ጉዳቱ ያመዝናል፡፡ በራሳቸው አቅም ሃብት መፍጠር እንዲችሉ ማገዝ እንጂ፣ የኔን ሃብት በማውረስ ልጆቼን ማኮላሸት አልፈልግም፡፡ ሰርተው ያላገኙትን በመቶ ሚሊዮኖች ፓውንድ የውርስ ገንዘብ ለልጆቼ መስጠት፣ ሊሸከሙት የማይችሉትንና የሚያጠፋቸውን ከባድ ጫና በላያቸው ላይ መጫን ነው፡፡” ብሏል፤ ሃብቱን ከልጆቹ ይልቅ ለበጎ አድራጎት ስራ ለመስጠት የወሰነው ስቲንግ ለጋዜጠኞች፡፡
እንዲህ እንደ ስቲንግ ሃብታቸውን ለልጆቻቸው ላለማውረስ የወሰኑ በርካታ የዓለማችን ባለጸጎች አሉ። ከእነዚህ አንዱ የአለማችን ባለጸጎች ፊታውራሪ የማክሮሶፍት ኩባንያ መስራች ቢል ጌትስ ነው። ቢል ጌትስ ከ76 ቢሊዮን ዶላር በላይ ሃብቱን ለልጆቹ እንደማያወርስና እነሱም እንወርሳለን ብለው እንደማይጠብቁ ተናግረዋል፡፡225 ሚሊዮን ዶላር ሃብት ያፈራው ዝነኛው የሙዚቃ ተሰጥኦ ውድድር ዳኛ ሲሞን ኮዌልም፣ በዚህ አመት መጀመሪያ ለወለደው ልጁ ለኤሪክ ሳይሆን፣ ለበጎ አድራጎት እንደሚያውለው ተናግሯል - “ሀብትን ዘር ቆጥሮ ከትውልድ ወደ ትውልድ በውርስ መልክ በማስተላለፍ አላምንም” በማለት፡፡
ቦዲ ሾፕ የተባለው ታዋቂ ኩባንያ መስራች የሆነችው አኒታ ሮዲክም ብትሆን፣ ጥሪት ሳልተውላቸው ብሞት ምን ይውጣቸው ይሆን ብላ ሳትሰጋ 51 ሚሊዮን ዶላር የሚገመት ሃብቷን ሙሉ ለሙሉ ለበጎ አድራጎት ስራ ሰጥታለች፡፡
ለዚህች ሴት፣ ሃብት ንብረትን ለልጅ ወይም ለሌላ የቤተሰብ አባላት ማውረስ፣ አሳፋሪና ነውር ድርጊት ነው፡፡ኤኦ ዶት ኮም የተባለውን ትርፋማ ኩባንያ በዋና ስራ አስፈጻሚነት የሚመራው ጆን ሮበርትስም፣ 500 ሚሊዮን ዶላር ሃብቱን የአብራኩ ክፋይ ለሆኑት ልጆቹ እንደማያወርስ አፍ አውጥቶ ከተናገረ ቆይቷል፡፡ ሰውዬው ይሄን ውሳኔ ያስተላለፈው፣ በልጆቹ የሚጨክን ክፉ አባት ስለሆነ አይደለም፡፡ ስለልጆቹ የሚጨነቅ አርቆ አሳቢ በመሆኑ እንጂ፡፡ ሃብቱን ለልጆቹ የማያወርሰው የወደፊት ህይወታቸው ሰላማዊ እንዲሆንና የስኬታማነት ስሜት እንዲፈጠር በማሰብ መሆኑን ነው ሮበርትስ የተናገረው፡፡
ህፃናት ለእግዚአብሔር የፃፏቸው ደብዳቤዎች
ውድ እግዚአብሔር፡-
ትልቋ እማማ ወደ ቤቷ ስትሄድ ከእኛ ጋር የምትሆን ሌላ እማማ ልትልክልኝ ትችላለህ?
ሶፊ - የ4 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አባቢ ዶክተር እንድሆን ይፈልጋል፡፡ እኔ ደሞ አልፈልግም፡፡ አንተ ግን ሳይንቲስት እንድሆን ትፈቅድልኝ የለ?
ብሩክ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ዳዲን ካየሁት ብዙ ጊዜ ሆኖኛል፡፡ ማሚን ስጠይቃት የሄደበትን አታውቀውም፡፡ አንተ ጋ መጥቷል እንዴ?
ጆሲ - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
በዚህ ዓመት ከክፍላችን አንደኛ የሚወጣው ማነው? ለእኔ ብቻ በጆሮዬ ንገረኝ፡፡
ሄለን - የ5 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ታላቅ እህቴ፤ ማሚ ያስቀመጠችውን ቸኮላት ሰርቃ ስትበላ አየኋት፡፡ ለማሚ ልንገርባት ወይስ አንተ ትቆጣታለህ?
ዴቭ - የ6 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
አንተ ጋ ትምህርት ቤት የለም አይደል! አለ እንዴ?
ሳሚ - የ7 ዓመት ህፃን
ውድ እግዚአብሔር፡-
ከክፍላችን ልጆች ሁሉ ቀድሜ መሮጥ እንድችል ታደርገኛለህ? እርግጠኛ ነኝ ትችላለህ፡፡
ፊሊፕ - የ5 ዓመት ህፃን
የፍቅር ጥግ
የሴትን ልብ ለማግኘት እርግጠኛው መንገድ ተንበርክኮ ማለም ነው፡፡
ዳግላስ ጄሮልድ
(እንግሊዛዊ ፀሃፌ ተውኔት)
ማናቸውንም የፍቅር ጉዳዮች አላስታውስም። ሰው የፍቅር ጉዳዮችን በምስጢር ነው መያዝ ያለበት፡፡
ዋሊስ ሲምፕሰን
(ትውልደ-አሜሪካ እንግሊዛዊ መኳንንት)
መጀመሪያ ማፍቀር እንጂ መኖር አልፈልግም፡፡ መኖር የምሻው እግረመንገዴን ነው፡፡
ዜልዳ ፊትዝጌራልድ
(አሜሪካዊ ፀሃፊ)
ከሁሉም ዓይነት ሴቶች ጋር ፍቅር ይዞኛል። ወደፊትም ሙሉ በሙሉ በዚሁ ለመቀጠል አቅጃለሁ፡፡
ቻርልስ
(የዌልስ ልኡል)
በፀደይ ወራት የጎረምሳ ህልም በስሱ ወደ ፍቅር ሃሳብ ይገባል፡፡
አልፍሬድ ቴኒሰን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ፍቅር እንደ ሲጋራ ነው፤ ከጠፋብህ እንደገና ትለኩሰዋለህ፡፡ ነገር ግን ፈፅሞ እንደ መጀመሪያው አይጥምም፡፡
አርኪባልድ ፐርሲቫል ዋቬል
(እንግሊዛዊ ወታደር)
ጓደኝነት ክንፍ አልባ ፍቅር ነው፡፡
ሎርድ ባይረን
(እንግሊዛዊ ገጣሚ)
ከማፈቅረው ሰው ጋ መሄድ ፍላጎቴ ነው፡፡ ወጪውን ማስላት አልፈልግም፡፡ ጥሩ ይሁን መጥፎ ማሰብ አልሻም፡፡ ያፍቅረኝ አያፍቅረኝ ማወቅ አልፈልግም፡፡ ከማፈቅረው ጋ መሄድ ፍላጎቴ ነው፡፡
ቤርትሎት ብረሽት
(ጀርመናዊ ፀሐፌ ተውኔትና ገጣሚ)
ፍቅር ከድህነትና ከጥርስ ህመም በቀር ሁሉንም ነገሮች ያሸንፋል፡፡
ማ ዌስት
(አሜሪካዊ ተዋናይና ኮሜዲያን)
ፍቅር ደስታ መሆኑ የቀረው ምስጢር መሆኑ የቀረ ጊዜ ነው፡፡
አፍራ ቤኸን
(እንግሊዛዊ ደራሲና ድራማ ፀሃፊ)
የአልማዝ ስጦታውን እስከ መመለስ የሚያደርስ ጥላቻ ለወንድ ኖሮኝ አያውቅም፡፡
Zsa Zsa Gabor
(ትውልደ - ሃንጋሪያዊ አሜሪካዊ ፊልም ሰሪ)
የፖለቲካ ጥግ
(ስለ ጠላት)
ጠላቶችህን ሁልጊዜ ይቅር በላቸው፣ ስማቸው ግን ፈፅሞ አትርሳ፡፡
ሮበርት ኬኔዲ
(አሜሪካዊ ፖለቲከኛ)
ጠላቶቼን ይቅር ማለት አይጠበቅብኝም፤ ሁሉንም ገድያቸዋለሁ፡፡
ራሞን ማርያ ናርቫዝ
(ስፔናዊ ጄነራልና ፖለቲከኛ)
ጠላቶቼ እውነት እንዳላቸው መቀበል አልወድም።
ሳልማን ሩሽዲ
(ትውልደ - ህንድ እንግሊዛዊ ደራሲ)
ጠላትህን በስትራቲጂ መናቅ፣ በታክቲክ ግን ማክበር አለብህ፡፡
ማኦ ዜዶንግ
(ቻይናዊ ፖለቲከኛ)
በወዳጆችህ ትከበራለህ… በጠላቶችህ ትታወቃለህ። እኔ በእጅጉ የታወቅሁ ነበርኩ፡፡
ጄ. ኤድጋር ሁቨር
(አሜሪካዊ የወንጀል ጥናት ባለሙያና የመንግስት ባለስልጣን)
ዝናና እውቅና ለጠላቶች ያጋልጣል፡፡
ሲ.ኤል.አር.ጀምስ
(የትሪኒዳድ ፀሃፊ፣ የፖለቲካ ንድፈ ሃሳብ ቀማሪ)
ከአስተዋይነት የበለጠ ጠቃሚ መሳሪያ፣ ከድንቁርና የከፋ ጎጂ ጠላት የለም፡፡
አቡ አብደላህ መሃመድ
አል-ሃሪቲ-አል-ባግዳድ-አል-ሙፊድ
(ኢራቃዊ ምሁርና የህግ ባለሙያ፤ በ10ኛው ክ/ዘመን የኖረ)
ገንዘብ ወዳጆችን መግዛት አይችልም፡፡ ነገር ግን የተሻለ የጠላት መደብ ሊያስገኝልህ ይችላል፡፡
ስፓይክ ሚሊጋን
(ትውልደ-ህንድ እንግሊዛዊ ፀሃፊ፣ ተዋናይና ተረበኛ)
ሰላም የሚፈጠረው ከትላንት ጠላቶች ጋር ነው፡፡ ሌላ ምን አማራጭ አለ?
ሺሞን ፔሬስ
(የእስራኤል ጠቅላይ ሚኒስትር)