Administrator

Administrator

(ሃተን ሙነቅዮ ዴሬ ኢተ ጋደ ጩቸን መነቅዮ ዴሬ ገከውሱ) - የወላይትኛ ተረት

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዛፍ ቆራጭ ከወንዝ ዳር ዛፍ እየቆረጠ ሳለ መጥረቢያው ከእጁ ወጥቶ፣ ግንዱ ላይ ነጥሮ ወንዙ ውስጥ ወደቀበት፡፡ በወንዙ ዳር ቆሞ፣
“አዬ ጉድ! የእንጀራ ገመዴ ተበጠሰ!” እያለ ሲያለቅስ፤ የውሃው አማልክት መልክተኛ ሜርኩሪ ብቅ አለና፤
“ምን ሆነህ ታለቅሳለህ? ለምን አዘንክ?” አለው፡፡
“የሥራ መጥረቢያዬ ወንዝ ውስጥ ገባብኝ” አለው፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃው በዋና ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ወጣ፡፡ ከዚያም፤ “ይሄ መጥረቢያ ያንተ ነውን?” ሲል ጠየቀው፡፡
ዛፍ ቆራጩም፤
“የለም ይሄ የእኔ መጥረቢያ አይደለም” አለና መለሰ፡፡
ሜርኩሪ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ወደ ወንዙ ጠለቀና አንድ ሌላ ከብር የተሰራ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፡፡
“ይሄስ ያንተ ነውን?” አለና ጠየቀው፡፡
“እረ የለም ይሄ የእኔ አይደለም” አለ ዛፍ ቆራጩ፡፡
ሜርኩሪ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ውሃው ጠልቆ ሌላ ተራ መጥረቢያ አወጣ
“ይሄስ?” አለው
ዛፍ ቆራጩ “በትክክል ይሄኛው የእኔ መጥረቢያ ነው!” አለ በከፍተኛ ሐሴት ተውጦ፡፡ “እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!” አለ፡፡
ሜርኩሪም በጣም ረክቶ፤
“ስለታማኝነትህ እነዚህን ሁለት መጥረቢያዎች - ከወርቅ የተሰራውንና ከብር የተሰራውን፤ ሸልሜሃለሁ!” ብሎ ሰጠው፡፡
ዛፍ ቆራጩ ወደ ሰፈሩ ሲደርስ፤
“ዛሬ ትልቅ ፌሽታ ነው ያጋጠመኝ!” ብሎ የሆነውን ሁሉ ለባልንጀሮቹ ነገራቸው፡፡
ከዛፍ ቆራጮቹ አንዱ ቅናት ይይዘዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ሄዶ እሱም እድሉን ለመሞር ይወስናል፡፡
ቀናተኛው ዛፍ ቆራጭ አንድ ከወንዙ ዳር ያለ ዛፍ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ ከዚያም አውቆ ወደ ውሃው መጥረቢያውን ይወረውረውና፤
“ወይኔ መጥረቢያዬ! ወይኔ የሥራ መሣሪያዬ!” እያለ ይጮሃል፡፡
ይሄኔ ሜርኩሪ ብቅ አለ፡፡
“ምን ሆነህ ነው የምትጮኸው?”
“መጥረቢያዬ በሥራ ላይ ሳለሁ ውሃ ውስጥ ወደቀብኝ” አለ፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃ ውስጥ ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፤ ከዚያም
“የጠፋብህ መጥረቢያ…” ብሎ ሊጠይቀው ሲጀምር፤
ዛፍ ቆራጩ በስግብግብነት፤
“አዎን፡፡ የኔ የራሴ መጥረቢያ ነው! የገዛ ራሴ መጥረቢያ ነው!!” አለና ሁለት እጆቹን ዘረጋ፡፡
ሜርኩሪ የማይታመን ሰው በመሆኑ በጣም በመከፋት፤
“አንተ ታማኝ አይደለህም! ስለዚህም እንኳንስ፤ የወርቅ መጥረቢያ ውሃ ውስጥ የጣልከውን የራስህን ተራ መጥረቢያም፣ አታገኝም!” አለው፡፡
***
ታማኝነት የህይወታችን መሰረት መሆን አለት፡፡ ለሥራ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለእውቀት ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለፖለቲካ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሀገራችንና ለህዝባችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ በሌሎች ላይ ልናደርገው ያሰብነውን ወይም ያደግነውን በራሳችን ላይ ሲሆን የምንሸሽ፣ አሊያም መመሪያ የምናወጣበት ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “ሲያቃጥል በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡
ጐር ቫይዳል፤ ምቀኝነትን ሲገልፅ፤ “ጓደኛዬ ሲሳካለት፣ አንድ ነገር ከውስጤ ይሞታል/ይቀንሳል” እንዳለው፤ ጓደኛችን የተሻለ አገኘ ብለን ዐይናችን የሚቀላ ከሆነ ታማኝነት የጐደለው መንፈስ ነው፡፡ “ጐረቤታችን ጫጩት ሲያረባ ስናይ፣ እኛ ሸለምጥማጥ ማርባት የምንጀምር” ከሆነ ፍፁም ታማኝነት የጐደለው የምቀኝነት ድርጊት ነው፡፡ ለእድገት የበቃ ባልደረባችን በደስታ ሲጥለቀለቅ ስናይ እንባ የሚተናነቀን ከሆነ ፈርዶብናል ማለት ነው፡፡ የተያይዘን እንለቅ ፍልስፍና የትም አያደርሰንም - እርግማን ነው፡፡ በሌሎች ደስታ ውስጥ የእኛን ደስታ ለማየት መቻል አለብን፡፡ ደስታችንን ለሌሎች እናጋራ፡፡ ራስ ወዳድነትን እንታገል!
“ደስታን ከራሱ ጋር፣ አጥብቆ ያሰረ
ክንፍ - ያላትን ህይወት፣ ትንፋሽ አሳጠረ፡፡
ደስታ እየከነፈች፣ የሳማት ሰው ግና
የዘለዓለም ፀሀይ ይሞቀዋል ገና”፤ እንዳለው ነው ዊልያም ብሌክ፡፡
ደስታችን የአገር ይሁን እንደማለት ነው፡፡ ደስታ የእኔና የእኔ ብቻ ይሁን ብሎ የሙጥኝ አለማለት ነው፡፡ ከአገር ካዝና የወጣ ደስታ የአገር ነውና ለህዝብ እናዳርሰው፡፡ ለራሳችን ሸሽገን አንቀራመተው ማለት ነው፡፡ የጋራ ቤታችንን እናስብ፡፡ በፓርቲ አጥር አንታጠር፡፡ ደፋር - መሀይም ብቻ ሳይሆን፣ ጭምት - ምሁር የሚኖርባትም አገር እናልም! ዕቡይ - ምሁር ብቻ ሳይሆን ያልተማረ - ጨዋ ህዝብ ያላት አገር እናስብ፡፡ ከፓርቲም ውጪ በቤተሰብ፣ በቢሮ፣ በተቋም፣ በንግድ ድርጅት ውስጥ የሚኖር ነፃ ዜጋ አለ ብለን፣ ከሳጥን ውጪ እንመልከት! ቢያንስ ባስበው ያስበኛል ብሎ ግንዛቤ መውሰድ ያባት ነው፡፡ “የእኔ ወንበር እስካልተነካች ድረስ” የሚል እሳቤ ኃላፊነትን ዘንግቶ አጥር ማጠር፣ ረጅም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ማምታታት ነው (Mistaking Longevity for immortality እንደማለት ነው)፡፡ በዚህም እሳቤ ምክንያት ነው መተካካትን ከብወዛ ጋራ አንድ አድርገን (Mistaking Replacement for Reshuffling እንደማለት) የምናየው፡፡ ወደድንም ጠላንም ቢያንስ ማንም ሰው ሊተካ የሚችል ነው፤ የማይተካ የለም (No one is indespansable) የሚለውን ሁለንተናዊ መርህ ያለራስ ወዳድነት፤ ያለ ምቀኝነት እንቀበል፡፡ ከአጠቃላይ ነባራዊ እውነታው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ አናመልጥም፡፡ እውነታውን ተቀብሎ መፍትሄውን መሻት ከአላስፈላጊና ከማናመልጥበት ሽሽት ይገላግለናል፡፡ አገርም ለቅቀን እንሽሽ ብንል አይሆንም፡፡ ከራስ የህሊና ቁስል ማምለጥ አይቻልምና፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የናዚም ወታደር ይያዛል፤ ተብሏል፡፡ በመሸሽ፣ በመሸሸግና ሌላ አገር በድሎት ከመኖር ጋር ራስን ማስተሳሰር ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ እንኳን በባሌ በቦሌም ምቾት ቅርብ አደለም፡፡ ምቾትና ነፃነትን በሌላ ምድር ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በሰሜንኛ “ጠላ አገኛለሁ ብለህ ውሃ ረግጠህ አትሂድ” ይባላል፡፡ በወላይትኛ ደግሞ “በውሃ የሚያቦኩበት አገር መጥፎ ነው ብላ፤ በምራቅ የሚያቦኩበት አገር ደረሰች” ማለት ነው፡፡ በማህል አገርኛ “ከድጡ ወደ ማጡ” ብለው ያጠቃልሉት ይሆናል፡፡ ብቻ ከዚህ ይሰውረን!!

 

 

 

የቦይንግ ኩባንያ ዘመናዊ ምርት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪም ላይነር አውሮፕላን (“B787”) ባለፈው አርብ ለንደን ደርሶ ካረፈ በኋላ ጭራው አካባቢ እሳት ተነስቶበት መለብለቡ የሚታወስ ሲሆን፤ የቃጠሎው መነሻ ከሬዲዮ መገናኛ አንቴና ጋር የተያያዘ እንደሆነ በምርመራ ተረጋገጠ፡፡ የእንግሊዝ የአየር አደጋ ምርመራ ክፍል ትናንት ባወጣው ሪፖርት፤ ከአውሮፕላኑ ጭራ አካባቢ የተተከለው አንቴና በመደበኛ በረራ ላይ አገልግሎት የማይሰጥ መጠባበቂያ አንቴና መሆኑን ገልጿል፡፡ የራሱ አነስተኛ ባትሪ ጋር የተገጠሙ አንቴና ላይ በሽቦዎች መጠላለፍ አልያም ባትሪው ላይ በተፈጠረ አንዳች እክል እሳት እንደተፈጠረ የምርመራ ክፍሉ ገልፆ፤ በተጨማሪ ምርመራ ትክክለኛው መንስኤ ከነመፍትሔው እስኪታወቅ ድረስ፣ መጠባበቂያውን አንቴና ለጊዜው በማላቀቅ አውሮፕላኖች ያለ ስጋት መብረር ይችላሉ ብሏል፡፡

አዲሱና ዘመናዊው ድሪም ላይነር (“B787”) ከወራት በፊት በዋናው የባትሪ ማስቀመጫ ቦታ እሳት በመነሳቱ፣ በመላው አለም ሁሉም “B787” አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ባትሪው ላይ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጐ አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ ከተመለሱ በኋላ እንደገና ተጨማሪ ችግር መፈጠሩ የቦይንግ ኩባንያን እና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የ (“B787”) ቀዳሚ ተጠቃሚ ደንበኞች በእጅጉ አሳስቧቸው ነበር፡፡ ባለፈው አርብ የተፈጠረው ችግር ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ በምርመራ ተረጋግጦ ትናንት በይፋ ከተነገረ ወዲህ፣ የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ ወዲያውኑ እንዳንሰራራ ተገልጿል፡፡

                        ከወር በኋላ በራሽያዋ መዲና ሞስኮ ለሚካሄደው 14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን ምርጫ እና ዝግጅት በተመለከተ በግልፅ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ኬንያ ተሳታፊ ቡድኗ ለመምረጥ ባዘጋጀችው ብሄራዊ ሻምፒዮና ላይ ሰሞኑን ከፍተኛ ትኩረት አድርጋ ቆይታለች፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በዓለም ሻምፒዮናው በስንት የውድድር መደቦች እንደሚሳተፍ እና ስንት አትሌቶችን እንደሚልክ አለማሳወቁየሚኖረውን ዝግጅት እንዳያስተጓጉል ተሰግቷል፡፡ ከወር በፊት በአሜሪካ ዩጂን በተደረገው የፕሮፈንታይኔ ክላሲክስ ውድድር በ10ሺ ሜትር በሁለቱም ፆታዎች ለዓለም ሻምፒዮናው የሚመረጡ አትሌቶችን ለመለየት ፌደሬሽኑ ተጠቅሞበታል፡፡ ዓለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ከሚጠይቀው ሚኒማ ባሻገር በየውድድር መደቡ ለሁሉቱም ፆታዎች ለእያንዳንዳቸው ሶስት ምርጥ አትሌቶችን ለመመልመል ስለሚከተለው አሰራር ግልፅ መረጃ አለመኖሩ ግን የሚያሳስብ ይሆናል፡፡

በዳይመንድ ሊግ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ አትሌቶች በዓለም ሻምፒዮናው የዝግጅት ወቅት ካለባቸው የውድድር መደራረብ አንፃር ብቃታቸው የወደ እንዳይሆን ያሰጋል፡፡ በትልልቅ የዓለም ማራቶን ውድድሮች ያሸነፉ በርካታ ማራቶኒስቶች መኖራቸውም ለምርጫ ማስቸገሩ አይቀርም፡፡ በአጠቃላይ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮናው በምታሳትፈው ቡድን ምርጫ ላይ ውስብስብ ችግሮች እንደሚኖሩም ይገመታል፡፡ ከሁለት ሳምንት በፊት የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኬንያ የዓለም ሻምፒዮና ተሳታፊ ቡድኗን የምትመርጥበት አይነት ተመሳሳይ ብሄራዊ ሻምፒዮናን በአሰላ ከተማ በሚገኘው አረንጓዴ ስታድዬም ማካሄዱ አይዘነጋም፡፡ ከ35 በላይ የክልል፤የከተማ መስተዳድሮችን፤ የክለብ እና የብሄራዊ ቡድን ውክልና ያላቸው 1070 አትሌቶችን ያሳተፈው ብሄራዊ ውድድር በጋራድ ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ኩባንያ አብይ ስፖንሰርነት 42ኛው የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በሚል ስያሜ የተዘጋጀ ነበር፡፡ የመከላከያ አትሌቲክስ ቡድን አጠቃላይ አሸናፊ በሆነበት ብሄራዊ ሻምፒዮናው በ5 የስፖርት አይነቶች ብሄራዊ ሪከርዶች ከመሻሻላቸውም በላይከ1 በላይ የወርቅ ሜዳልያ የተጎናፀፉ 5 አትሌቶችም ተገኝተውበታል፡፡

ይሁንና ይህ ብሄራዊ ሻምፒዮና በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያን ስለሚወክለው ቡድን ምንም የሰጠው ፍንጭ አልነበረም፡፡ በተያያዘ ግን የኬንያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፉ አትሌቶችን ለመመልመል ዓመታዊ ብሄራዊ ሻምፒዮናውን ዛሬ በናይሮቢ ከተማ በሚገኘው ናያዮ ስታድዬም ያካሂዳል፡፡ ብሄራዊ ሻምፒዮናው ምርጥ እና ልምድ ያላቸው ፤ወጣት እና አዳዲስ አትሌቶችን በዓለም ሻምፒዮናው ቡድን ለማካተት የተዘጋጀ እንደሆነ ሲታወቅ በኬንያ ከፍተኛ ተመልካች የሚያገኝ የአትሌቲክስ ውድድር እንደሆነና ሳፍሪኮም በተባለ የቴሌኮም ኩባንያ በ23ሺ ዶላር የስፖንሰርሺፕ ድጋፍ እንደተዘጋጀ ተገልጿል፡፡ በዚሁ ሻምፒዮና በ10 የአትሌቲክስ ስፖርቶች መሳተፍ እንዲችሉ አስፈላጊውን ሚኒማ ያሟሉ፤ ከሁለት ዓመት በፊት የዓለምና የኦሎምፒክ ሻምፒዮን የሆኑ 192 አትሌቶች (132 ወንድ እና 60 ሴት) ጥሪ የቀረበላቸው ሲሆን በየውድድር አይነቱ አንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ማግኘት የሚችሉት በቀጥታ ለዓለም ሻምፒዮናው ቡድን የመመረጥ እድል እንዳላቸው ታውቋል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው 3ኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች አስቀድሞ በነበራቸው ውጤት ግምገማ ተደርጎ የመመረጥ እድል ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡ በብሄራዊ ሻምፒዮናው የተመረጡ አትሌቶች ከአንድ ሳምንት በኋላ በካሳራኒ በሚገኘው የመኖርያ እና የልምምድ ካምፕ በመግባት የመጨረሻ ዝግጅታቸውን ያደርጋሉ፡፡

ኬንያ ለዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመካከለኛ ርቀት፤ በ5ሺ ሜትርና በ10ሺ ሜትር ውድድሮች እና በማራቶን ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ የሚበቃ የቡድን ስብስብ እንደሚኖራት ትጠብቃለች፡፡ አይኤኤኤፍ ሰሞኑን እንዳስታወቀው ከ200 አገራት የተወከሉ 2000 አትሌቶች የሚሳተፉበት የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በመላው ዓለም በሚኖረው የቀጥታ ቴሌቭዥን ስርጭት በሪከርድነት የሚመዘገብ ተመልካች ያገኛል፡፡ በርካታ የዓለም ክፍሎችን በቴሌቭዥን ስርጭት ለማዳረስ ስምምነቶች መደረጋቸውን የገለፀው ዓለም አቀፉ የአትሌቲክሰ ፌደሬሽኖች ማህበር ለ9 ቀናት የሚካሄደው የዓለም ሻምፒዮናው በ200 አገራት ሽፋን እንደሚኖረውና የሚያገኘው ድምር ተመልካች እስከ 5 ቢሊዮን እንደሚገመት አስታውቋል፡፡ ከ2 አመት በፊት በደቡብ ኮርያ ዳጉ ተደርጎ በነበረው 13ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኬንያ 47 አትሌቶችን በማሳተፍ በ17 ሜዳልያዎች (7 የወርቅ፤ 6 የብርና 4 የነሐስ) ከዓለም ሶስተኛ ከአፍሪካ 1ኛ ደረጃ አግኝታ እንደነበር ሲታወስ፤ ኢትዮጵያ በ34 አትሌቶች ተካፍላ 5 ሜዳልያዎችን (1 የወርቅና 4 የነሐስ) በማግኘት ከዓለም ዘጠነኛ ከአፍሪካ ሁለተኛ ነበረች፡፡ ባላፉት 13 የዓለም ሻምፒዮናዎች ደግሞ ኬንያ በተሳትፎ ታሪኳ በሰበሰበቻቸው 100 ሜዳልያዎች (38 የወርቅ፤ 33 የብርና 29 የነሐስ) ከዓለም በሶስተኛ ደረጃ ላይ ስትመዘገብ፤ ኢትዮጵያ በ54 ሜዳልያዎች(19 የወርቅ፤ 16 የብርና 19 የነሐስ) 7ኛ ላይ ናት፡፡

በደራሲና ሃያሲ አለማየሁ ገላጋይ አርታኢነት ሰላሳ ፀሐፍት ገጣሚያንና ሰዓሊያን በስብሐት ገብረእግዚብሔር ህይወትና ሥራ ላይ ያቀረቧቸው ፅሁፎች የተካተቱበት “መልክዐ ስብሀት” የተሰኘ መጽሐፍ የፊታችን ሰኞ በ11 ሰዓት በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡ መፅሐፉ በደራሲ ስብሐት ገብረእግዚአብሔር ሥራና ህይወት ላይ የሚያተኩር እንደሆነ ታውቋል፡፡
ፅሁፎቻቸው በመፅሐፉ ከተካተቱ ፀሐፍት መካከል ሃያሲ አስፋው ዳምጤ፣ ቴዎድሮስ ገብሬ፣ ሌሊሳ ግርማ፣ አዳም ረታ፣ ኢዮብ ካሣ፣ ሚካኤል ሽፈራው፣ ነቢይ መኮንን፣ አልአዛር ኬ፣ አውግቸው ተረፈ የሚገኙበት ሲሆን ከሰዓሊያን ደግሞ በቀለ መኮንን፣ ፍፁም ውብሸት፣ ቴዲማን ተካትተዋል፡፡
መፅሐፉ ሲመረቅ ነቢይ መኮንን፣ ታገል ሰይፉ፣ በቀለ መኮንን፣ ተፈሪ አለሙ እና ሌሎችም ሥራዎቻቸውን ያቀርባሉ፡፡
“መልክዐ” በሚል ቅድመ ግንድ ተከታታይ መፅሐፍት ለመታተም መታቀዱንና “መልክዐ ፀጋዬ ገብረመድህን” በዝግጅት ላይ መሆኑን የገለፀው አርታኢው፤ ስለ ስብሃት የታተመው “መልክዐ ስብሐት” መድበል ሚዛናዊነቱን የጠበቀ እንዲሆን ጥረት መደረጉን ተናግሯል፡፡

ትናንት በተከፈተው የሞንታና ፎልክ ፌስቲቫል ፈንዲቃ የባህል ቡድን ኢትዮጵያን በመወከል እንደሚሳተፍ ተገለፀ፡፡ ከ200 አገራት የተውጣጡ የሙዚቃ ቡድኖችና የፋሽን ባለሙያዎች የሚሳተፉበት ዓለም አቀፉ የሙዚቃ ፌስቲቫል እስከ 31 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የንግድ ስራዎች የሚንቀሳቀስበትና ከ16ሺ በላይ ጎብኝዎች የሚገኙበት ነው፡፡ ፈንዲቃ የኢትዮጵያ አዝማሪ ባንድ እና የባህል ውዝዋዜ ቡድን ሲሆን ስድስት ሙዚቀኞች፤ ሁለት ተወዛወዦች እና አንድ ድምፃዊን በማቀፍ በሞንታና ፎልክ የሙዚቃ ፌስቲቫል በመሳተፍ የአገር ባህልን በማስተዋወቅ ከፍተኛ ትኩረት ያገኛል ተብሏል፡፡ ፈንዲቃ የባህል ቡድን ከአምስት ዓመት በፊት በተወዛዋዥነቱና በባህል አምባሳደርነቱ በሚታወቀው አርቲስት መላኩ በላይ እንደተመሰረተ ይታወቃል፡፡

አዳዲስና ነባር የልጆች ተረቶች የተካተቱበት “የልጆች ዓለም” መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ ዝግጅትና ቅንብሩ በመብራቱ ካሳ የተሰራው መጽሐፍ በሥዕሎች የታጀበ ሆኖ 85 ገፆች አሉት፡፡ በነጭ ሳር ማተሚያ ድርጅት የታተመው “ከልጆች ዓለም” በ25 ብር ከ30 ለገበያ ቀርቧል፡፡

በአለን ሌከን ተፅፎ አባተ መንግሥቱ የተረጐመው “ስኬታማ የጊዜ አጠቃቀም” እየተሸጠ ነው፡፡ በውጤታማ የጊዜ አጠቃቀም ዙርያ የተፃፈው መፅሐፍ ኤችኬ ፐብሊሺንግ የታተመ ሲሆን ዋጋው 25 ብር ከ35 ነው፡፡የመጽሐፉን የአርትኦት ስራ ደራሲና ሃያሲ መስፍን ሃብተማርያም ነው የሰራው፡፡ ይህ በዚህ እንዳለ የሮቢን ሻርማ “The Monk Who Sold His Ferrari” በብርሃኑ በላቸው “ራስን ማወቅ” በሚል ርዕስ ተተርጉሞ ለገበያ የበቃ ሲሆን በ35 ብርም እየተሸጠ ነው፡፡ በፋርኢስት ትሬዲንግ የታተመው መፅሐፉ፤ 176 ገፆች አሉት፡፡ መፅሐፉን መገናኛ አካባቢ የሚገኘው ዩኒቲ መፃህፍት መደብር እንሚያከፋፍል ታውቋል፡፡

በወይንሸት መርከቡ የተደረሱ አምስት አጫጭር ልቦለዶች የተካተቱበት “እኔና ቄስ ገንዘቤ” የአጫጭር ልቦለዶች መድበል ለንባብ በቃ፡፡ በመፅሐፉ “እኔና ቄስ ገንዘቤ” ባለ አራት ክፍል አጭር ልቦለድ እንዲሁም “ማትሪክ”፣ “አቢይ እና አባይ”፣ “ኮሌጅ” እና “ይድረስ ለፈጣሪ” የተሰኙ ሌሎች አጫጭር ልቦለዶች ተካተውበታል፡፡ 118 ገፅ ያለው መፅሐፉ ባናዊ ማተሚያ ቤት የታተመ ሲሆን ዋጋው ለሀገር ውስጥ 25 ብር፣ ለውጭ ሀገራት 10 ዶላር ነው፡፡ በሰሎሞን ታደሰ የተደረሱ ወጐችና እውነተኛ ታሪኮች የተካተቱበት “የሸገር ወጐች እና እውነተኛ ታሪኮች” መፅሐፍ እንዲሁ ለንባብ በቅቷል፡፡ በመፅሐፉ “የሸገር ወጐች”፣ “መጣንላችሁ ማሳጆች”፣ “የጨለሙ ታሪኮች በዱባይ” እና ሌሎች ታሪኮች ተካተዋል፡፡ ደራሲው ካሁን በፊት “ቦሌ ፒኮክ ጋ ጠብቂኝ” የተሰኘ መፅሐፍ ለንባብ አብቅቷል፡፡ “የሸገር ወጐች” በ39.50 ብር እየተሸጠ ነው፡፡

በሙዚቃው ንጉስ ማይክል ጃክሰን አሟሟት ላይ በተመሰረተ ክስ የተጀመረው የፍርድ ሂደት 10ኛ ሳምንቱን ሲይዝ ሁኔታዎች እየተወሳሰቡ መምጣታቸውን ዘገባዎች አመለከቱ፡፡ ታዋቂው የኮንሰርት አዘጋጅ ኤኢጂ ላይቭ ለአሟሟቱ ተጠያቂ መሆን አለበት በሚል የማይክል ካትሪን ጃክሰን እና ቤተሰባቸው ክስ እንደመሰረቱ ሲታወቅ፤ በክሱ የ40 ቢሊዮን ዶላር ካሳ የከፈለን በሚል እየተሟገቱ ናቸው፡፡ ማይክል ጃክሰን ከአምስት ዓመት በፊት ከመጠኑ ያለፈ መድሃኒት በመውሰድ ለድንገተኛ ሞት መብቃቱ የሚታወስ ሲሆን የተጠየቀው ካሳ አርቲስቱ በ50 ዓመቱ እድሜው ህይወቱ ባያልፍ ኖሮ በኮንሰርት ስራዎች እና በአልበም ሽያጭ ሊያገኝ የሚችለው ገቢን በማስላት የተተመነ ነው፡፡ የግሉ ሃኪም የነበሩት ዶክተር ኮናርድ ሙራይ ለሞቱ መንስኤ የሆነ መድሃኒት ያለጥንቃቄ ሰጥተዋል በሚል ክስ ተጠያቂ መደረጋቸው ይታወቃል፡፡ አሁን በተጀመረው የፍርድ ክርክር ደግሞ የኮንሰርት አዘጋጁ ኤኢጂ ላይቭ ታላቁን ሙዚቀኛ አላግባብ ትኩረት በመንፈግ ከሞት አደጋው ሳይታደጉ ቀርተዋል በሚል ተከስሰዋል፡፡ የኤኢጂ ጠበቃዎች ማይክል ጃክሰን ለሞት የተዳረገው ራሱ በቀጠረው እና በወር እስከ 150ሺ ዶላር በሚከፍለው የግሉ ሃኪም ስህተት እንጂ ከሚያቀርበው ዓለም አቀፍ ኮንሰርት በተያያዘ አለመሆኑን በመግለፅ የክስ መከላከያቸውን አቅርበዋል፡፡

ኤኢጂ ላይቭ የማይክል የግል ሀኪም የነበሩትን ዶክተር ኮናርድ ሙራይ አልቀጠርኩም ብሎ ከመካዱም በላይ ለሞቱ ምን ሃላፊነት የለብኝም ይላል፡፡የማይክል ቤተሰብ በጉዳዩ ላይ 97 ምስክሮችን እንዲሁም ኤኢጂ ላይቭ ደግሞ 113 ምስክሮችን ለክስ መከላከያው በማቅረብ ለወራት በጉዳዩ ላይ በመሟገት ይቀጥላሉ፡፡ በሌላ ዜና ማይክል ጃክሰን በሞቱ ማግስት በ500 ሚሊዮን ዶላር እዳ ተይዞ እንደነበር ያስታወሰው ሴሌብሪቲኔይዎርዝ ከዚህ እዳው ሙሉለሙሉ ነፃ መውጣቱን አስታውቋል፡፡ የማይክል ጃክሰን ሃብት ንብረትን ለመሰብሰብ ቤተሰቡ ለጠበቆች እስከ 13.6 ሚሊዮን ዶላር መክፈላቸውን ያወሳው ሴለብሪቲ ኔትዎርዝ የሃብት መጠኑ 600 ሚሊዮን ዶላር እንደሚደርስ አመልክቷል፡፡ ማይክል ጃክሰን በኑዛዜው ከሃብት ንብረቱ 40 በመቶውን ለልጆቹ፤ 40 በመቶውን ለእናቱ እና ቀሪውን 20 በመቶ ለበጎ አድራጎት መለገሱ ሲታወቅ እናቱ ካተሪን ጃክሰን ከመየርሳቸውን ድርሻ ልጆቹ እንዲወርሱ መናዘዙን ለማወቅ ተችሏል፡፡

ታዋቂው ራፐር 50 ሴንት በቀድሞ ፍቅረኛው ላይ አድርሷል በተባለ ጥቃት ሊከሰስ ነው፡፡ ጥፋተኛ ሆኖ ከተገኘ የአምስት አመት እስርና የ46ሺ ዶላር ካሳ እንዲከፍል እንደሚወሰንበት የቢልቦርድ ዘገባ አመልክቷል፡፡ 50 ሴንት ከሁለት ሳምንት በፊት ወደ ቀድሞ ፍቅረኛው የኮንዶሚኒዬም መኖርያ በመሄድ ጥቃት ማድረሱ ተገልጿል፡፡ በሌላ በኩል ከፈፀመው ፆታዊ ጥቃት ጋር በትችት መወጠሩ ሳያንሰው ራፐሩ በስልክና በፅሁፍ መልዕክት የ16 ዓመት ልጁን በማስፈራራቱም እየተብጠለጠለ ነው፡፡ ራፐሩ ከታዳጊ ልጁ ጋር በስልክ ባደረገው ንግግር “የእናትህ ልጅ እንጂ የእኔ አይደለህም፡፡ ገና የደም ምርመራ ሁሉ አደርጋለሁ፡፡ እንደ እናትህ እና እንደ ቤተሰብህ ከእኔ የምትፈልገው ስጦታ ብቻ ነው፡፡ ከእንግዲህ ግን ምንም እንዳትጠብቅ፡፡ ስልኬን ሰርዘው፡፡ ሁለተኛም እንዳትደውልልኝ” ብሎታል፡፡

ቢልቦርድ መፅሄት እንደዘገበው፤ ራፐሩ በቀድሞ ፍቅረኛው እና በልጁ ላይ የፈፀማቸው ተግባራት ገፅታውን እያበላሸበት ነው፡፡ በሌላ በኩል ፊፍቲ ሴንት ከሙዚቃው ባሻገር በተሰማራበት ንግድ እጅግ ትርፋማ እየሆነ መምጣቱን ያመለከተው ሂፖፕ ኒውስ፤ በ260 ሚሊዮን ዶላር ከአምስቱ የዓለም ሃብታም ራፐሮች አንዱ ሊሆን እንደበቃ ጠቁሟል፡፡ ለ50 ሴንት ሃብት ማደግ በዋናነት “ቪታሚን ዎተር” በተባለው የውሃ ምርት አምራች ኩባንያ ያዋለው ኢንቨስትመንት ትርፋማነት መሆኑን የጠቀሰው ዘገባው፤ ‹ጂ ዩኒት› በተባለው የፋሽንና የሙዚቃ ኩባንያው እንዲሁም በፊልም ስቱድዮው እና በተለያዩ የማስታወቂያ ስራዎችም የተወጣለት ነጋዴ መሆኑን አብራርቷል፡፡