
Administrator
ሳያልፍብን ውዴ...
ዘመን ሳይለወጥ እቴ ውዴ ሆይ
መግደርደር ተይና አንዴ እንተያይ!
ዝናቡን ዘንግተሽ፤ ጳጉሜን ግን አስታውሰሽ
ዣንጥላ ሳትይዢ በታክሲም ሳትመጪ
እንጠመቅ ፍቅር ከዝናብ ጋር ውጪ፡፡
ወደ አውላላ ሜዳ ተሸክሜሽ ልክነፍ
ያንቺ ጉልበት እስኪያልቅ
የኔ እስኪንጠፈጠፍ፤
ወድቀን እንጫወት
ፍቅር ለጭቃ አይሰንፍ!
ከዚያም እንተኛ ትራስ ሆኖሽ ክንዴ
የጭቃ ላይ ፍቅር ውብም አደል እንዴ?
እንደተጋደምን እንደተዋሃድን
ለፍቅራችን ማህተም ትሆንልን ዘንዳ፤
ፍቀጅላት ውዴ - መስከረም አንድ ሲል
ከናፍራችን ላይ
አደይዋ ትፈንዳ!
ለዑል ብርሃኑ
ነሐሴ 26/97
ጭፈራችን ተመልሷል!
“ጭፈራችንን መልሱ”፤ ብለን ነበር ትላንት በስቲያ
“አገራችንን መልሱ”፤ ብለን ነበር ትላንት በስቲያ
የሰሙን ምሥጋን ይግባቸው፤ እሰየው አለች ኢቶ’ጵያ!!
ወትሮም መደማመጥ እንጂ፣ መደነቋቆር ክሶ አያቅ
ቆርጠው ካልበጠሱት በቀር፣ ከዘመዘሙት ቂም አያልቅ
ዛሬን ድል አገኘሁ ብሎ፣ የነግ ፈተናም አይናቅ!
በአገር ጉዳይ ቂም አያቅም፣ ይሄው ህዝቡ ይጨፍራል፡፡
ይሄው መሬቱ ይጨሳል፡፡
ባንዲራው እንደነበልባል፣ ዳር ከዳር ይንቀለቀላል!!
መብራት ቢጠፋ ምን ግዱ፣ ህዝቡ እሳት ሆኖ ይበራል
ብርሃን ነው ይነድዳል አበሽ፤ ኤሌትሪክ ነው ይያያዛል!!
ዕድሜ ለልጆቻችን ጭፈራችን ተመልሷል፡፡
“…እስኪበጣጠስ ላንቃችን”
መጅ እስኪያወጣ ጉሮሮአችን
“አገር ላዕላይ ነው” እንዳልን
እንደህፀፁ ብዛት ሳይሆን፣ እንደልባችን ጽናት
አቆጥቁጦ ልሣናችን፣ እስከነገና እስከትላንት
እንደፊኒክስ ከረመጥ፣ ከትቢያ እንነሳለን፡፡
እንደ ድመት ዕድሜ ጥናት አሥራ ሶስት ነብስ ነው ያለን፤
ከሣግ ጩኸት ሞታችን ውስጥ፣ ለእንቁጣጣሽ ፀሐይ በቃን!
ህይወትም ትግል ነውና፣ መከራችንም ባያልቅ
ይውለበለባል እንጂ፣ ባንዲራ አያዘቀዝቅ
ልብ ነብሱን ይገብራል፣ ጀግና አገሩ እስከምትስቅ
ዕድሜ ለልጆቻችን እግራቸው ላልዶለዶመ
ያም ያን ቢል፣ ያም ያን ቢላቸው፣ ቅን ቅስማቸው ላልታመመ፡፡
ወትሮም አቀርቅረው እንጂ፣ አንዴ ከተለኮሱማ
የወይራ ለበቅ ናቸው፣ የቁርጡ ቀን ከመጣማ
በአሸዋ እርሻም ሜዳ ቢሆን፣ አንዴ አውድማ ከገቡማ
መንሽ ነው ልባም እግራቸው፣ አሂዶ እኮ ነው ኳሱማ!!
ምሥጋና ይግባቸው አቦ!!
ዕድሜ ለልጆቻችን
ተመልሷል ጭፈራችን!!
አካፋን አካፋ እንዳልነው
ወርቅ እግሩን እናመስግነው፡፡
ይህንን ባህል እናርገው፡፡
ዛሬስ ህዝባችን ታድሏል
የእንቁጣጣሽ ድል አዝምሯል!
የሀገር ፍቅር ነው እንጂ፣ ወኔ ወጌሻ አይፈልግም
ወድቆ መነሳትን ማወቅ፣ ልብ እንጂ ወግ አይክሰውም
ሐሞትን አጠንፍፎ እንጂ፣ በዕንባ ጐርፍ ጉድፍ አይጠራም፤
በቆራጥነት በተቀር፣ የልባም ቀን ጥም - አይቆርጥም፡፡
ጨክነው ከተዘጋጁ፤ እንዲህ እዚህ ይደረሳል
ህዝብም አካሉን ሁሉ፣ በባንዲራ ይነቀሳል…
የአገሩን ቀለም ይኳላል
አገሩን ፊቱን ይቀባል፡፡
በቄጤማ በዐደይ ማህል፣ ኳስም ጮቤ ረገጠች
ኳስም አበባ - አየሁ አለች
የነግ መንገዷን ለማብራት፣ የተስፋ ችቦ ለኮሰች
“የሽንፈት ምንቸት ውጣ”፣ “የድሉ ምንቸት ግባ” አለች!!
ዕድሜ ለልጆቻችን፣ ተክሷል ህዝብ ተክሷል
የአዲሱን ዓመት፣ ድል ለብሷል
በደልም በድል ይረሳል፤
ድል በትግል ይወረሳል!!
ጭፈራችን ተመልሷል!
ጳጉሜ 2 2005 ዓ.ም
(ዛሬም ለኳስ ተጨዋቾቻችንና
ለቅኑ የኢትዮጵያ ህዝብ)
“ቆመን ጠበቅናቸው፤ ጥለውን አለፉ” - ይድነቃቸው ተሰማ
“ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው!
አምሣ ጥገቶች አሥረው…!”
ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አሳማ፤ በጐች በብዛት ወደተሰማሩበት የግጦሽ መስክ ጐራ ይላል፡፡ እረኛው “ምን ሊያደርግ መጣ” በሚል ጥርጣሬ ያስተውለዋል፡፡ አሳማው ወደ በጐቹ ለመቀላቀል ይሞክራል፡፡ እኛው ያደፍጥ ያደፍጥና ፈጥኖ ተጠግቶ አሳማውን ይይዘዋል፡፡ ከዚያም፤
“ለምን መጣህ?” ብሎ ይጠይቀዋል፡፡
አሳማውም፤
“ከበጐች ልመሳሰል ጀ.ቨ” ሲል ይመልሳል፡፡
“ተመሳስለህስ?”
“እንደበጐች ልኖር”
“ኖረህስ?”
“እንደበጐች እንድታኖረኝ!?”
“አንተን እንኳን ለዚህ አልፈልግህም አያ አሳማ”
“እንግዲያ እንዴት እንድኖር ትፈልጋለህ?”
“አይ፤ ኑሮው ይቅርብህና ወደገቢው ቦታ ብወስድህ ነው የሚሻለው፡፡” ብሎ፤ እየጐተተ ወደ እንስሳ ማረጃው ቦታ ይዞት ሊሄድ ይጐትተዋል፡፡
አሳማው፤ መወራጨት፣ መንፈራገጥ፣ ማጓራት መጮህ ይጀምራል፡፡
ይሄኔ ከበጐቹ መካከል አንዱ ብቅ ይልና፤
“አያ አሳማ?” አለ በለጋስ ጥያቄ ቅላፄ፡፡
“አቤት” አለ አያ አሳማ፡፡
“ምንድነው እንደዚህ የሚያስጮህህ? እኛ ሁላችንምኮ በጌታችን እየተጐተትን ወደሌላ ቦታ እንወሰዳለን፡፡”
“ነው፡፡ ግን የእኔ ይለያል” አለ አሳማ፡፡
“እንዴት?” አለ በጉ፡፡
“አይ አያ በግ የሁለታችን ለየቅል ነው!”
“እኮ እንዴት?”
“ጌታህ አንተን የሚፈልግህ ከቆዳህ ሱፍ ለመሥራት ነው፡፡ እኔን የሚፈልገኝ ግን ለሥጋዬ ነው - ጠብሶ ሊበላኝ”
አያ አሳማ፤ እንደፈራው እየተጐተተ ሄደ፡፡
* * *
በአዲሱ ዓመት ከእንዲህ ያለ ምርጫ ይሰውረን፡፡ ለጥብስ ይሁን ለሱፍ፣ ዞሮ ዞሮ መታረድ ላይቀር ምርጫውን በቅናት መልክ ከማሰብ ይሰውረን፡፡ አራጁንም መሆን ታራጁንም መሆን በፖለቲካ ሥርዓት ውስጥ አሰቃቂ ነው፡፡
“አውራ ዶሮ ጮኾ መንጋቱን ነገረኝ
ዛሬ ማታ ላርደው ቀጠሮ ነበረኝ”
እንዳለው አንዱ የእኛ ገጣሚ፤ የታራጅና አራጅ ምፀት የምንነጋገርበት እንዳይሆን አዲሱ ዓመት ልቡን ይስጠን፡፡
አዲሱን ዓመት የእኩልነት ያድርግልን!
ይገብር ካላችሁ ዝንጀሮም ይገብር
የንጉሥ አይደለም ወይ የሚጭረው ምድር”
የምንልበት ዘመን ይሁንልን!
እንደ ዱሮው ሳይሆን እንደዛሬው ተስፋችን፣ ምኞታችንና ርዕያችን አይሞትምና
“ከብረው ይቆዩኝ ከብረው
ባመት ወንድ ልጅ ወልደው
አምሣ ጥገቶች ወልደው…
በኳስ በድል ታጅበው…”
ስንባል ሞቅ የሚለን፣ ከጭንቅ የሚገላግለን የአዎንታዊነት ምርቃት እንዲሆንልን እንጽና፣ እንጽናና፡
በመጪው ዓመት በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን፤ “የኢትዮጵያ ሬዲዮ መብራት በመጥፋቱ ከሚሴ አካባቢ የሥርጭት ችግር ገጠመኝ፤ አለ” የሚል ዜና የሚያሰማበት ዓመት እንዳይሆን እንመኝ!!
የአቦ - ሰጡኝ ሳይሆን የትግል ዓመት እንዲሆንልን ልብና ልቡናውን ይስጠን!
የችግር ማውሪያ ሳይሆን የመፍትሔ መፈለጊያ ዘመን እንዲሆንልን አንጐሉን ይስጠን!
የመለያያ ሳይሆን የመዋሃጃ፣ የመተሳሰቢያ ዘመን እንዲሆን በጐ አመለካከቱን አያጨልምብን!
ዕድሜ የጊዜ ሳይሆን፤ የመጠንከር፣ አቅም - የመገንባት፣ እርምጃችንን የማትባት ይሆንልን ዘንድ እርዳታው አይለየን፡፡
ሽቅብ እየተመነደግን እንጂ ቁልቁል እያደግን እንዳንሄድ፣ ድላችንን አስተማማኝ ያድርግልን፡፡
ፀሐፊዎቹ እንዳሉን፤
“አንድ ግዙፍ የብርቱካን ዛፍ እናስብ፡፡ በስሎ የተንዠረገገ ብዙ ብርቱካን አለው፡፡ ወደታች፣ በሰው ቁመት ያሉትን ብርቱካኖች በብዛት ለቀምኳቸው፡፡ ከዚያ በላይ ያሉትን ለመቅጠፍ ቁመት አጠረኝ፡፡ ከዚህ አንፃር ሲታይ የብርቱካን እጥረት አለ ልል ነው፡፡ ከጥቂት ጊዜ በኋላ ግን አንድ አዋቂ ሰው አንድ ቴክኖሎጂ ፈጠረ፤ መሰላል የሚባል፡፡
ወደ ማይደረሱት ብርቱካኖች መድረሻዬን አበጀልኝ፡፡ ችግሬ ተቃለለ፡፡ ቴክኖሎጂ ወደኃይል ምንጭ መዳረሻ/ ማግኛ ስርዓት ነው፡፡ ያኔ እጥረት ያልነውን ነገር፣ አሁን በሽ - በሽ፤ ነው ያሰኘናል፡፡ (“አበንዳንስ”፤ በፒተር ዲያማንዲስ እና ስቲቨን ኮትለር)
ስለ ዕጥረትና ስለ ዕጦት የምናስብበት ዓመት እንዳይሆን መሰላሉን የሚሰጠን አዋቂ ይዘዝልን፡፡
የኳስ ድል ይለምልም፡፡ ሩጫውም ይቅናን፡፡
የዕውነት ለውጡም ይቅናን፡፡ ኑሮም ይታደገን!
በጐ እንድንመኝ፣ በጐ እንድናገኝ፤ በጐ እጅ ይስጠን!
“አይቀጭ ትልማችን፣ አይራብ ህልማችን!
አይመት ሐሞታችን፣ አይቃዥ ርዕያችን!
አይንጠፍ ጓዳችን፣ አትምከን ላማችን!
አይክሳ ቀናችን፣ አይላም ጉልበታችን!!
ከሁሉም ከሁሉም አይጥፋ ሻማችን!”
ብለን የምንመኝበትን የህይወት ፀጋ አይንሳን!!
ታዋቂው የእስፖርት ሰው ይድነቃቸው ተሰማ ሱዳን ከእግር ኳሱ አምባ ጠፍታ ከርማ ወደሜዳ ስትመለስ ያሳየችውን ድንቅ እርምጃ በተመለከተ የሰጡት አስተያየት፤ ማስገንዘቢያ፣ ማስጠንቀቂያና የእግር ኳሱን ሂደት ማሳያ ነው፡፡ ለኢትዮጵያ ደግሞ ዋና ማሳሰቢያ ነው!
“ቆመን ጠበቅናቸው ጥለውን አለፉ!” ነበር ያሉት፡፡ ነብሳቸውን ይማርና ዛሬ፤ ቆመን አልጠበቅናቸውም!
እየሄድን ነው!” እንላቸው ነበር፡፡ እንዴት ደስ ባላቸው!
እንደ አዲስ ዓመት ምላሽ “ከብረው ይቆዩን ከብረው” የምንባባልበት እንዲሆን እንመኛለን”
መልካም አዲስ ዓመት!!
የላቀ ስኬት የተቀዳጁ የዓመቱ ፈርጦች
ሳላዲን ሰኢድ
ዝነኛው የእግር ኳስ ተጫዋች ሳላዲን ሰኢድ ለኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ባደረጋቸው 12 ጨዋታዎች 9 ጐሎችን አግብቷል፡፡ በዓለም ዋንጫ ማጣርያ እስካሁን አራት ጎሎችን ያገባው የ24 ዓመቱ ሳላዲን፤ደቡብ አፍሪካ ላይ አንድ፤ ሴንትራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ላይ 3 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡ ሳላዲን በ300ሺ ዩሮ (ከ6ሚ ብር በላይ) የዝውውር ሂሳብ በኢትዮጵያ በከፍተኛ ዋጋ የተሸጠ የእግር ኳስ ተጫዋች ነው፡፡
መሠረት ደፋር
በዘንድሮ የሞስኮ የአለም አትሌቲክስ በ5ሺ ሜትር ለአገሯ ወርቅ ያስገኘችው ጀግናዋ አትሌት መሠረት ደፋር፤ ባለፈው ነሐሴ ወር በተካሄደው የ2013 የዳይመንድ ሊግ ውድድር በ5ሺ ሜትር ከአገሯ ልጅ አትሌት ጥሩነሽ ዲባባ ጋር ተፎካክራ በማሸነፍ፣ የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች፡፡
ጥሩነሽ ዲባባ
በዘንድሮው የሞስኮ የአለም አትሌቲክስ በ10ሺ ሜትር ውድድር አሸናፊ በመሆን ወርቅ ያጠለቀችው ጥሩነሽ ዲባባ፤ በዳይመንድ ሊግ ውድድር በአትሌት መሰረት ደፋር ተቀድማ ሁለተኛ በመውጣት የ5ሺ ዶላር (95ሺብር ገደማ) ተሸላሚ ሆናለች፡፡ ብዙም ሳትቆይ በቲልበርግ፣ ሆላንድ በተካሄደው 10ኪ.ሜ የጐዳና ላይ ሩጫ ተወዳድራም በአንደኝነት በማሸነፍ የወርቅ ባለድል በመሆን ዓመቱን በስኬት ቋጭታለች፡፡
መሃመድ አማን
በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ በ800 ሜትር የወንዶች ውድድር አሸናፊ በመሆን የወርቅ ሜዳሊያ የተሸለመው መሃመድ አማን፤ በነሐሴ ወር በተካሄደው የዳይመንድ ሊግ ውድድር ድል በመቀዳጀት የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) በማግኘት ተደራራቢ ስኬት አግኝቷል፡፡
የኔው አላምረው
በሞስኮው የአለም አትሌቲክስ የ5ሺ ሜትር ውድድር የፍፃሜ ተፋላሚ የነበረው የ23 ዓመቱ የኔው አላምረው፤ በርቀቱ የዳይመንድ ሊግ አሸናፊ በመሆን የዳይመንድ ሊግ ዋንጫና 50ሺ ዶላር (1ሚ ብር ገደማ) በመሸለም የዓመቱ የስኬት ፈርጥ ለመሆን በቅቷል፡፡
ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል 200ሺህ ብር ቃል ተገባ
50ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብና 100ሺህ ብር ግምት ያለው ቁሳቁስ ተበረከተ
የተለያዩ ድርጅቶች ለመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል 50ሺህ ብር በጥሬ ገንዘብ ሲያበረክቱ 200ሺህ ብር ለመስጠት ቃል ገቡ፡፡ እንዲሁም 100ሺህ ብር ግምት ያላቸው የተለያዩ ቁሳቁሶች ተበረከቱ፡፡
ዜማ ብዕር የኢትዮጵያ ሴቶች ማኅበር የአዲሱን ዓመት መቀበያ ከመቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ጋር ለማክበር ጳጉሜ 3 ቀን 2005 ዓ.ም ባዘጋጀው ፕሮግራም የተሳተፉ ድርጅቶችና ግለሰቦች የተለያዩ ስጦታዎች በዓይነት የሰጡ ሲሆን 200ሺህ ብር ለመስጠት ቃል ገብተዋል፤ 50ሺህ ብር አሰባስበው ሰጥተዋል፡፡
ቼሬአሊያ ብስኩትና ዱቄት ፋብሪካ፣ ዲ ኤች ገዳ፣ አዲካ፣ ቢጂአይ የተለያዩ ቁሳቁሶች በዓይነት የሰጡ ሲሆን ሆም ቤዝ የእንጨት ሥራ 50ሺህ ብር ሰጥቷል፡፡ የአፍሪካ ጤና ኮሌጅ ደግሞ የተለያዩ አልባሳትና የፅዳት ቁሳቁሶች የሰጠ ሲሆን ያለማቋረጥ ሙያዊ ድጋፍ ለማበርከት ቃል ገብቷል፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሳይንስና ቴክኖሎጂ ማኅበራት አንድ ሺህ ብር የሰጡ ሲሆን ጂኤም የወጣቶች ማዕከልና ሴንትራል ጤና ኮሌጅ የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብተዋል፡፡
መቄዶንያ የአረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን ማዕከል በአሁኑ ወቅት 200 አረጋውያንና የአዕምሮ ሕሙማን እየረዳ ሲሆን፣ በአዲሱ ዓመት ደግሞ 200 ተጨማሪ ሰዎች ለመቀበል ተዘጋጅቷል፡፡
ዋልያዎቹ በሞት ሽረት ምዕራፍ ላይ
ዛሬ የምድብ 1 የሞት ሽረት ፍልሚያዎች በኮንጎ ብራዛቪል ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ከኢትዮጵያ እንዲሁም ደርባን ላይ ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና በሚገናኙባቸው ጨዋታዎች ይደረጋሉ፡፡ በምድብ 1 የደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በ5 ጨዋታዎች ምንም ሳትሸነፍ በ1 ጨዋታ በቅጣት 3 ነጥብ ተቀንሶባት በ10 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ ምድቡን ትመራለች፡፡ ደቡብ አፍሪካ በ8 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ 2ኛ ደረጃ ላይ ናት፡፡ ቦትስዋና በ7 ነጥብና በ1 የግብ ክፍያ ሶስተኛ ነች፡፡ የኢትዮጵያ ተጋጣሚ የሆነችው መካከለኛው አፍሪካ በ3 ነጥብና በ6 የግብ ዕዳ መጨረሻ ነች፡፡
ዛሬ ከመካከለኛው በአፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር በኮንጎ ብራዛቪል የሚፋለመው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው ሐሙስ ምሽት በኢንተር ኮንቲኔታል ሆቴል አሸኛኘት ሲደረግለት የአግር ኳስ ፌደሬሽን ፕሬዚዳንት አቶ ሳህሉ ገብረወልድ ‹‹የፈፀምነውን ታሪካዊ ስህተት በታሪካዊ ድል በመመለስ ድሉን ለህዝባችን የአዲስ አመት ስጦታ እናደርገዋለን ›› ብለው የተናገሩ ሲሆን ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በበኩላቸው ቡድናቸው ወሳኙን ጨዋታ አሸንፎ ለመውጣት የሚያስፈልገውን ዝግጅት እንዳደረገ፤ ተጨዋቾቻቸው በሙሉ ጤንነት ላይ እንደሚገኙ ገልፀዋል፡፡ የብሄራዊ ቡድኑ አምበል የሆነው ደጉ ደበበ ‹‹የህዝብ አደራ ተቀብለን እንደምንጓዝ እናውቃለን በድል አድራጊነት የተጓዝንበትን የ2005 ዓ.ም በድል እንደምናጠናቅቀው እምነቴ ነው›› ብሏል፡፡ ዋልያዎቹ ሞቃታማ የሆነውን የኮንጎ ብራዛቪል የአየር ጠባይ ለመላመድ በአዳማ ዝግጅታቸውን ሲያደርጉ ሰንብተዋል፡፡ ዋልያዎቹ በዛሬው ጨዋታ የሚኖራቸው ውጤታማነት አዲሱን ዓመት በታላቅ ተስፋ ለመጀመር ከማስቻሉም በላይ በሚቀጥሉት ሁለት ወራት ስፖርት አፍቃሪው ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመጀመርያ ጊዜ ወደ የዓለም ዋንጫ የምታልፍበትን እድል በስፋት እንዲነጋገርበት ምክንያት ይሆናል፡፡
ጎል የተባለው የስፖርት ድረገፅ ከምድብ 1 የዓለም ዋንጫ የምድብ ማጣርያ የመጨረሻ ትንቅንቆች በፊት ከአንባቢዎቹ ድምፅ በማሰባሰብ ባወጣው ትንበያ በኢትዮጵያ እና መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ጨዋታ ሙሉለሙሉ የአሸናፊነቱ ግምት ለዋልያዎቹ አድልቷል፡፡ ኢትዮጵያ ሴንተራል አፍሪካ ሪፖብሊክን 3ለ1 ታሸንፋለች ያሉት 30.1 በመቶ፤ 2ለ1 ያሉት 15.53 በመቶ እንዲሁም 2ለ0 ያሉት 14.56 በመቶ ናቸው፡፡ ለሌላው የምድቡ ጨዋታ በተሰጠ ግምት ደቡብ አፍሪካ ከቦትስዋና 1ለ1 አቻ ይወጣሉ ያሉትቨ 13.04 በመቶ ያህሉ ሲሆኑ 17.39 በመቶው 2ለ0 እንዲሁም 21.74 በመቶ 3ለ1 ደቡብ አፍሪካ እንደምትረታ ተንብየዋል፡፡
ዋልያዎቹ እና
የምድባቸው ቡድኖች ዝግጅት
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ባለፈው 1 ዓመት በዓለም ዋንጫው የ3 ዙር ማጣሪያዎች ባደረጋቸው 7 ጨዋታዎች አልተሸነፈም፡፡ በተጋጣሚዎቹ ላይ 11 ጐል አግብቶ የቆጠረበት 5 ነው፡፡ በእያንዳንዱ ተጋጣሚው ላይ በአማካይ 1.57 ጐል ያገባል፤ 0.71 ጐል ይገባበታል፡፡ በማጣሪያዎቹ በአጠቃላይ 12 ቢጫ ካርዶች የዋልያዎቹ ተጨዋቾች ተቀጥተዋል፡፡ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ከጋና ብሄራዊ ቡድን ጋር የወዳጅነት ጨዋታ የሚያደርግበት ግብዣ ከወር በፊት ቀርቦለት የነበረ ቢሆንም ብዙዎቹ ተጨዋቾች እረፍት ላይ በመሆናቸው እና ቅዱስ ጊዮርጊስ በኮንፌደሬሽን ካፕ ከነበረው ተሳትፎ በተያያዘ እድሉን ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል፡፡ ከዚያ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ለአቋም መፈተሻ የሚሆኑትን ሁለት የወዳጅነት ጨዋታዎች ከሱዳን እና ብሩንዲ ጋር ለማድረግ ጥያቄ ቢያቀርብም ምላሽ አላገኘም፡፡ የመካከለኛው አፍሪክ ሪፖብሊክ ቡድን ከኢትዮጵያ ጋር ከሚያደርገው ጨዋታ በፊት ለአቋም መፈተሻ የሚሆነውን ግጥሚያ ከሊቢያ ጋር በማድረግ 0ለ0 ተለያይቷል፡፡ ዛሬ ከሴንትራል አፍሪካ ሪፖብሊክ ጋር ለሚደረገው ወሳኝ ፍልሚያ ለዋልያዎቹ 23 ተጨዋቾች ተመርጠዋል፡፡ ከተለያዩ አገራት ለብሄራዊ ቡድኑ የተመረጡ ፕሮፌሽናል ተጨዋቾች ሳላዲን ሰኢድ ከስኬርቴ ክለብ ቤልጅዬም፤ ጌታነህ ከበደ ከዊትስ ክለብ ደቡብ አፍሪካ፤ሽመልስ በቀለ ከአሊትሃድ ክለብ ሊቢያ እንዲሁም አስራት መገርሳ ከራህማት ክለብ እስራኤል ናቸው፡፡8 ተጨዋቾችን ለብሄራዊ ቡድኑ ያስመረጠው የቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ ነው ሲሆን ሳምሶን አሰፋ ፣ ሳላዲን በርጌቾ ፣አበባው ቡጣቆ ፣ቢያድግልኝ ኤልያስ፣ ምንያህል ተሾመ፣ በኃይሉ አሰፋ፣ አዳነ ግርማና ኡመድ ኡክሪ ናቸው፡፡ ከዘንድሮው የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ደደቢት አምስት ተጨዋቾች ሲመረጡ እነሱም ሲሳይ ባጫ ፣ ብርሃኑ ቦጋለ ፣ስዩም ተስፋዬ፣ ዳዊት ፍቃዱ እና ማይክል ጆርጂ ናቸው፡፡ ቶክ ጀምስና ፋሲካ አስፋው ከኢትዮጵያ ቡና፤መድሃኔ ታደሰና ሽመልስ ተገኝ ከመከላከያ ፤ዮናታን ከበደና ደረጀ ዓለሙ ከዳሸን ቢራ፤ ሙሉዓለም መስፍንና አንተነህ ተስፋዬ ከአርባምንጭ ተመልምለዋል። የተቀሩት ሞገስ ታደሰ ከመድን፤ በረከት ይስሃቅ ከመብራት ሃይል፤ ተክሉ ተስፋዬ ከንግድ ባንክ ናቸው፡፡ባፉና ባፋዎቹ ለመጨረሻው የሞት ሽረት ትንቅንቅ በፕሮፌሽናል ቡድናቸው ተጠናክረዋል። 4 ተጨዋቾች ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ፣ ሁለት ወጣት አማካዮች ከሆላንዱ ኤር ዲቪዜ፣ ከፍተኛ ልምድ ያለው የቀኝ ተመላላሽ ከቤልጅዬም ክለብ እና ምርጥ የመሀል ተከላካይ ከሩስያ ፕሪሚዬር ሊጋ በመጥራት ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡ ቦትስዋና በአመዛኙ በደቡብ አፍሪካ አብርሣ ፕሪሚዬር ሊግ በሚወዳደሩ ክለቦች ውስጥ ያሉ ከ10 በላይ ተጨዋቾች አሰባስባለች፡፡
የደቡብ አፍሪካው አሰልጣኝ ጐርደን ሌጀንሰንድ ከቦትስዋና ጋር በሚደረገው ጨዋታ በዓለም ዋንጫ ማጣሪያው ማናቸውንም ነፍስ የምንዘራበት ውጤት እና ሂሳባዊ ስሌትን ከቡድኔ እፈልጋለሁ ብለዋል፡፡ ከአጀማመር ይልቅ አጨራረስን ማሰብ ይሻላል ብለው የሚሰሩ አሰልጣኝ መሆናቸውን ሱፐር ስፖርት በዘገባው ገልጿል፡፡ ጎርደን ሌጀሰንድ አስተያየታቸውን ሲቀጥሉ ‹‹ቦትስዋናን ካሸነፈን በተከታታይ ካደረግናቸው 4 ጨዋታዎች 3 አሸንፈን ማለት ነው፡፡ ይህ በውድድር አንድ ብሔራዊ ቡድን ሊያገኝ የሚቻለው ከፍተኛ ውጤት ነው። ዋናው ነገር ቦትስዋን እንደምናሸንፍ እርግጠኞች መሆናችን ነው፡፡ በተቀረ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ ኢትዮጵያን በማሸነፍ ትረዳናለች ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ” ሲሉ ተናግረዋል፡፡ የቦትስዋና ብሄራዊ ቡድን በሞግዚት አሰልጣኙ ስታንሌ ቶሶሄኔ የሚመራው ሲሆን በዛሬው ጨዋታ ቡድናቸው ያልተጠበቀ ድል ማስመዝገቡ እንደማይቀር እምነቴ ነው ብለው ተናግረዋል፡፡አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በጨዋታው ላይ አስተያየት ሲሰጡ‹ የሞት ሽረት ፍልሚያ ነው፡፡ ብሄራዊ ቡድናችን በፊፋ ቅጣት 3 ነጥብ በተቀነሰበት ሰሞን ከሩዋንዳ ጋር ለቻን ውድድር ለማለፍ የደረሰውን የደርሶ መልስ ትንቅንቅ በማሸነፍ ጥንካሬው ታይቷል፡፡ በተቀነሰብን ነጥብ ምክንያት ለደቡብ አፍሪካ እና ቦትስዋና በማጣርያው የማለፍ ተስፋን ፈጥሯል፡፡ ይሁንና በኛ ተጨዋቾች ያለው ጠንካራ መንፈስ ሙሉ ለሙሉ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን በማሸነፍ ላይ የሚያተኩር ነው። ሙሉ 3 ነጥብ በመውሰድ እናሸንፋለን። በማለት ተናግረዋል፡፡ የመካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክ አሰልጣኝ የሆኑት ሄርቬ ሉጁዋንጂ‹‹ ብራዛቪል የገባነው ኢትዮጵያን ለማሸነፍ ነው፡፡ በምድቡ ሁሉም የሚገርፈው ቡድን የእኛ መሆኑን የሚያስቡ አሉ፡፡ ይህን አስተሳሰብ ፉርሽ ማድረግ እንፈልጋለን። በሁሉም የምድብ ጨዋታዎች ጥሩ ነበርን፤ ውጤት ያጣነው በእድለቢስነት ነው። ኢዮጵያን እናከብራታለን እንጅ እንፈራትም፡፡›› በማለት ለሱፕር ስፖርት አስተያየት ሰጥተዋል፡፡
አስሩ ምድቦች ያሉበት ሁኔታ
በዓለም ዋንጫ የተሳትፎ ታሪካቸው እስከ ሩብ ፍፃሜ በመድረስ የአፍሪካን ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገቡት ጋና እና ሴኔጋልን ጨምሮ 5 አገራት ዛሬ እና ነገ በሚደረጉ የመጨረሻ ዙር የማጣርያ ግጥሚያዎች ምድቦቻቸውን በመሪነት ጨርሰው ለማለፍ አንድ ነጥብ ብቻ የሚፈልጉ ናቸው። ጋና፤ ናይጄርያ፤ ሴኔጋል፤ ካሜሮንና ቱኒዚያ ምድቦቻቸውን በመሪነት ለመጨረስ በሜዳቸው በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች አቻ ውጤት ይበቃቸዋል፡፡ በምድብ 1 ኢትዮጵያ ለማለፍ መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን ማሸነፍ ግድ ይሆንባታል፡፡ የኢትዮጵያ አቻ መውጣት ለደቡብ አፍሪካ ቦትስዋናን አሸንፎ የማለፍ እድል የሚፈጥር ሲሆን መሸነፍ ደግሞ ደቡብ አፍሪካን ማሸነፍ ከቻለች ለቦትስዋናም ማለፍ ምክንያት ሊሆን ይችላል፡፡ በምድብ 2 ከፍተኛ የማለፍ እድል ያላት በ11 ነጥብና በ6 የግብ ክፍያ የምትመራው ቱኒዚያ ነች፡፡ ከምድብ 3 አይቬሪኮስት ማለፉ አረጋግጣለች፡፡ በምድብ 4 ጋና በ12 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ መሪነቱን ብትይዝም ዛምቢያ በ1 ነጥብ ብቻ ተበልጣ በተመሳሳይ የግብ ክፍያ እየተከተለች ነው፡፡ በምድብ 5 ኮንጐ በ10 ነጥብ 5 በ1 የግብ ክፍያ እየመራች ነው፡፡ ቡርኪናፋሶ በ9 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ እንዲሁም ጋቦን በ7 ብር በ5 የግብ ክፍያ የማለፍ ዕድል እንደያዙ ናቸው፡፡ በምድብ 6 ናይጄሪያ በ9 ነጥብና 3 የግብ ክፍያ ብትመራም ማላዊ በ7 ነበር በ3 የግብ ክፍያ እንዳደፈጠች ነው፡፡ ግብጽ ከምድብ 7 ከመጨረሻዎቹ ግጥሚያዎች በፊት ማለፏን ያረጋገጠችው በ15 ነጥብና በ5 የግብ ክፍያ በማስመዝገብ ነው፡፡ አልጀሪያ ደግሞ ምድብ 8ን በ12 ነጥብና በ4 የግብ ክፍያ ከ6ኛው ጨዋታ በፊት በመቆጣጠር ማለፏን አረጋግጣለች፡፡ በምድብ 9 መሪነቱን ካሜሮን በ10 ነጥብና በ3 በግብ ክፍያ ብትይዘውም ሊቢያ በ9 ነጥብና በ2 የግብ ክፍያ ትከተላታለች፡፡ በመጨረሻም በምድብ 10 ሴኔጋል በ9 ነጥብና 4 የግብ ክፍያ መሪነቱን ስትይዝ ኡጋንዳ በ8 ነጥብና 5 የግብ ክፍያ ተናንቃለች፡፡ በማጣሪያው የኮከብ ግብ አግቢነት ፉክክር በ5 ጐሎቻቸው ሦስት ተጨዋቾች ሲጠቀሱ፤ እነሱም ኢስማን ሱሊማን በ5 ጨዋታዎች 293 ደቂቃዎች በመጫወት፣ ጌታነህ ከበደ በ5 ጨዋታዎች 312 ደቂቃዎች በመጫወት እንዲሁም የግብፁ መሃመድ ሳላህ በ5 ጨዋታዎች 450 ደቂቃዎች በመጫወት ነው፡፡ ሌላው ኢትዮጵያዊ ሳላዲን ሰይድ በ4 ጨዋታዎች 347 ደቂቃዎችን ተጫውቶ ባስመዘገበው 4 ጐል ከሌሎች 7 ተጨዋቾች ጋር በማጣሪያው የኮከብ ግብ አግቢው ፉክክር የደረጃ ዝርዝር ተጠቅሷል፡፡
የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ
የዓለም ዋንጫው የመጨረሻው ጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ የማጣሪያው 3ኛ ዙር ምዕራፍ ነው፡፡ በ2ኛው ዙር በምድብ ድልድል ላለፈው 1 ዓመት ሲደረግ በቆየው ፉክክር በአስሩ ምድቦች አንደኛ ደረጃ የያዙት 10 ብሔራዊ ቡድኖች ወደ ዓለም ዋንጫ የማለፍ ዕድላቸውን በደርሶ መልስ ጨዋታዎች ይወስኑበታል፡፡ ከምድብ ማጣሪያው የመጨረሻ 6ኛ ግጥሚያዎች በፊት ከምድብ 3 አይቬሪኮስት ከምድብ 8 ግብጽ እንዲሁም ከምድብ 9 አልጀሪያ ወደ 3ኛው ዙር ጥሎ ማለፍ መሸጋገራቸውን አረጋግጠዋል፡፡ ለቀሩት የ7 ብሔራዊ ቡድኖች ኮታ ዛሬና ነገ በሚደረጉ የምድብ ማጣርያው የመጨረሻ ፍልሚያዎች ይታወቃሉ፡፡ ኢትዮጵያ በዛሬው ጨዋታ ለዓለም ዋንጫ የመጨረሻ የጥሎ ማለፍ ማጣሪያ ከበቃች በውድድሩ የተሳትፎ ታሪክ ትልቅ ውጤት ይሆናል፡፡ በታሪካዊው የጥሎ ማለፍ ምዕራፍ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን ከአፍሪካ 10 ብሔራዊ ቡድኖች አንዱ ሲሆን ከምዕራብና ከሰሜን አፍሪካ ብሔራዊ ቡድኖች የሚገናኝበት እድል ያመዝናል፡፡ ከአይቬሪኮስት፣ ከጋና ወደ ከናይጀሪያ ወይም ከአልጀሪያ፣ ከግብፅ ወይም ከቱኒዚያ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ሊገናኝ ይችላል፡፡ የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ ድልድል ለ10ሩ ብሔራዊ ቡድኖች የሚወጣው ከሳምንት በኋላ በካይሮ ነው፡፡ አስሩ ብሔራዊ ቡድኖች ለጥሎ ማለፍ ድልድል የሚወጣላቸው በሁለት ማሰሮዎች ሆነው አምስት አምስት ሆነው በመቧደን ሲሆን በሁለቱ ማሰሮዎች የሚገቡት ቡድኖች ማንነትን የሚወስነው በሚቀጥለው ሰሞን በፊፋ ይፋ በሚሆነው ወርሃዊ የእግር ኳስ ደረጃ ነው፡፡የ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ የደርሶ መልስ ጨዋታዎቹ ከወር በኋላ በኦክቶበር 11-15 የመጀመርያዎቹ ጨዋታዎች እንዲሁም ኖቬምበር 15-19 ላይ የመልስ ጨዋታዎቹ ይደረጋሉ። አፍሪካን ወክለው በ2014 እ.ኤ.አ ብራዚል ወደምታስተናግደው 20ኛው የዓለም ዋንጫ የማያልፉ 5 ብሔራዊ ቡድኖች በ3ኛው ዙር የጥሎ ማለፍ ትንቅንቅ ተለይተው ይታወቃሉ፡፡
ጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምሕርት ክፍል ሊከፍት ነው
የጎንደር ዩኒቨርሲቲ የትያትር ትምሕርት ክፍል ለመክፈት በቅድመ ዝግጅት ላይ መሆኑ ታወቀ፡፡ ለዚሁ ቅድመ ዝግጅት ይረዳ ዘንድ የዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎች ትምሕርት ክፍል ምሁራን እና ሌሎች ጉዳዩ የሚመለከታቸው ኃላፊዎች፤ የሀገሪቱን ከፍተኛ የትምሕርት ተቋማት እየጎበኙ ነው፡፡ የአዲስ አድማስ ምንጮች የትምሕርት ክፍሉ በ2006 ዓ.ም የትምሕርት ዘመን እንደሚከፈት የገለፁ ሲሆን በዩኒቨርሲቲው የኢትዮጵያ ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ አማርኛ ትምሕርት ክፍል ኃላፊ አቶ አማረ ተሾመ ግን “አንድ ባልደረባችን ባቀረቡት ፕሮፖዛል መሠረት የቅድመ መነሻ ሀሳብ ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነን፡፡ በትክክል መቼ እንደምንከፍት አልወሠንንም” ብለዋል፡፡
“መልክዐ ስብሐት”
ነገ ለውይይት ይቀርባል
በአርታዒ አለማየሁ ገላጋይ የተዘጋጀው “መልክዐ ስብሐት” ነገ ለውይይት እንደሚቀርብ ሚዩዚክ ሜይዴይ ኢትዮጵያ አስታወቀ። “ስብሐትን ከሌላ ማእዘን” በሚል የትኩረት ሀሳብ መነሻ በማቅረብ ውይይቱን የሚመሩት አርኪቴክት ሚካኤል ሽፈራው ናቸው፡፡ ውይይቱ በብሄራዊ ቤተመፃህፍት ከቀኑ 8 ሰዓት ጀምሮ ለሦስት ሰዓት ይካሄዳል፡፡
በራያ ሕዝብ ላይ የተፃፈው መጽሐፍ ዛሬ ይመረቃል
በሲሳይ መንግስቴ አዲሱና አለሙ ካሳ ረታ የተዘጋጀው በራያ ሕዝብ ላይ ያተኮረ መጽሐፍ ዛሬ እንደሚመረቅ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ “የራያ ሕዝብ የማንነት ጥያቄና የማእከላዊ መንግስታት ምላሽ፤ ከአጼ ዮሐንስ ፬ኛ እስከ ኢህአዴግ” በሚል ርእስ የተፃፈው መጽሐፍ የሚመረቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ዋናው ግቢ በሚገኘው ራስ መኮንን አዳራሽ ነው፡፡
የግጥም በጃዝ 26ኛ ዝግጅት ለእንቁጣጣች ይቀርባል
በራስ ሆቴል ትልቁ አዳራሽ እየቀረበ ያለው “ግጥም በጃዝ” 26ኛ ዝግጅቱን በመጪው ረቡዕ መስከረም ፩ እንደሚያቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ። በረቡዕ ልዩ ዝግጅት አበባው መላኩ፣ ግሩም ዘነበ፣ ደምሰው መርሻ፣ ነቢይ መኮንን የግጥም ሥራዎቻቸውን ፋቡላ የኪነጥበባት ማሕበር “ከነፃ አውጪ” ባንድ ጋር በመሆን የሥነ ቃል ትርዒት ያቀርባሉ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በሚቀርበው ዝግጅት የፍልስፍና ምሁሩ ዶር. ዳኛቸው አሰፋ ዲስኩር ያቀርባሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡