Administrator

Administrator

“እስካሁን በሁለቱ ከተሞች እንቅፋት አላጋጠመንም”

ከሃያ በሚበልጡ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን ሲያካሂድ የቆየው አንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ፤ ነገ በአዳማ ናዝሬት ከተማና በአዲስ አበባ የማጠቃለያ ሰልፍ ለማካሄድ ዝግጅት ማጠናቀቁን ገለፁ፡፡
በሶስት ወራት ውስጥ ሰላሳ ያህ ሰልፎችንና ስብሰባዎችን ለማካሄድ አቅዶ ብዙዎቹን ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት የፓርቲው ዋና ፀሃፊ አቶ ዳንኤል ተፈራ፤ ብዙ እንቅፋቶች ቢያጋጥሙንም ከመቀሌና ከወላይታ ሶዶ በስተቀር ብዙዎቹን እቅዶች አከናውነናል ብለዋል፡፡ የፀረሽብሩ ህግ እንዲሰረዝና የዜጎች ማፈናቀል እንዲቆም የህዝቡን ድምፅ እያሰማን ነው ያሉት አቶ ዳንኤል፤ በንግዱ ማህበረሰብ ላይ የተጫነው ሸክም እንዲነሳና ለአሳሳቢው የወጣቶች ስራ አጥነት በአስቸኳይ መፍትሄ እንዲሰጠው ጥያቄያችንን እያቀረብን ነው ብለዋል፡፡

የህዝቡን ድምፅና ጥያቄ ለማስተጋባት ጎንደር ላይ የጀመረው የአንድነት ሰላማዊ ሰልፍ እንቅፋቶች ቢገጥሙትም እንደተሳካና በአዲስ አበባ እንደሚጠናቀቅ ተናግረዋል - አቶ ዳንኤል፡፡ የአዳማው ሰላማዊ ሰልፍ ለነሀሴ 19 ቀን ቀጠሮ ተይዞለት እንደነበረና በእለቱ በሚካሄድ ሌላ ሰልፍ ለፀጥታ አካላት ስምረት አስቸጋሪ እንደሆነ በመስተዳድሩ ስለተነገረ ለአንድ ሳምንት እንደተራዘመ ገልፀዋል፡፡ ሰልፉ እንደገና በሳምንት ተራዝሞ ወደ ነገ የተሸጋገረው ደግሞ ነሃሴ 26 ቀን በሰማያዊ ፓርቲ የተጠራ ሰልፍ ይካሄድ ስለነበረ ነው ብለዋል፡፡ ይሁን እንጂ በአዳማ ናዝሬት ከመንግስት ወይም ከገዢው ፓርቲ እንቅፋት እንዳልገጠማቸው አቶ ዳንኤል ገልፀዋል፡፡ በተለያዩ ክልሎች ባደረግናቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ከፍተኛ ጫናዎች፣ ድብደባዎችና እንቅፋቶች ገጥመውናል ያሉት አቶ ዳንኤል፤ ግን ፖስተር ስንለጥፍና ከሀምሳ ሺህ በላይ በራሪ ወረቀቶች ስንበትን ምንም ችግር አልገጠመንም ብለዋል፡፡

Saturday, 07 September 2013 09:58

በትግራይ ታሪካዊ ቅርስ ተገኘ

                   በትግራይ ክልል ሃውዜን አካባቢ በ6ኛው ወይም በ7ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ለነገስታቶች ከአውሮፓ በስጦታነት የመጣ ሳይሆን እንደማይቀር የተገመተ የጥቁር ሰው ምስል ያለበት የሽቶ ማስቀመጫ ጠርሙስ በቅርቡ መገኘቱን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
በኤጀንሲው ጽ/ቤት የሚገኘው የሽቶ ማስቀመጫ አነስተኛ ጠርሙስ፣ ጠፍጣፋ የብርሌ ቅርጽ ያለው ሲሆን፤ በላዩ ላይ የጥቁር አፍሪካዊ ወንድ ምስል ተቀርፆበታል፡፡ የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ ስራ አስኪያጅ አቶ ከበደ አማረ እንደገለፁት፤ ይህ ታሪካዊ ቅርስ ሃውዜን አካባቢ በእርሻ ስራ ላይ የነበረ ገበሬ ያገኘው ሲሆን አንዲት እንግሊዛዊት አርኪዎሎጂስት ከገበሬው ላይ ገዝታ ለኤጀንሲው ማስረከቧን ገልፀዋል፡፡ አርኪዎሎጂስቷ የሽቶ ጠርሙሱን ትክክለኛ እድሜ ለማወቅና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮችን ለመመርመር ጥናት እያደረገች መሆኑን አቶ ከበደ ተናግረዋል፡፡
የሽቶ ጠርሙሱን የጥንት ሮማውያን ይሠሩት እንደነበረ የታወቀ ሲሆን ሮማውያኑ በሽቶ ጠርሙሶች ላይ የአፍሪካውያንን ምስል ይጠቀሙ እንደነበርም አመላካች እንደሆነ በጥናት ተደርሶበታል ተብሏል፡፡ በሃውዜን ገበሬ የተገኘው እድሜ ጠገብ የሽቶ ጠርሙስ፤ በአሁን ሰአት ብቸኛ ተመሳሳዩ በእንግሊዝ ሃገር ሙዚየም እንደሚገኝ አቶ ከበደ ገልፀዋል፡፡ የተገኘው ቅርስ ጥናት ከተደረገበትና በሚገባ ከተፀዳ በኋላ በሙዚየም ተቀምጦ ቱሪስቶች እንዲመለከቱት ይደረጋል ብለዋል - ሃላፊው፡፡
በትግራይ ክልል ከውቅሮ ከተማ በ8 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በአዲ አካውህ በተመሳሳይ በ1999 ዓ.ም በተደረገ የአርኪዮሎጂ ቁፋሮ የአምልኮ መስዋዕት ማቅረቢያ እና የሴት ምስል ሃውልት መገኘቱ እንዲሁም ስርአቱ ይፈፀምበት የነበረ ቤተ መቅደስ ፍርስራሽ መገኘቱ የሚታወስ ነው፡፡
በክልሉ በርካታ የአርኪዮሎጂ ቦታዎች እንዳሉ የጠቀሱት አቶ ከበደ በርካታ ቦታዎች ተለይተው ጥናት እየተደረገባቸው ሲሆን ሌሎችም ቀደም ሲል የት እንዳሉ የማይታወቁትን ለማፈላለግ ጥረት እየተደረገ መሆኑን ገልፀዋል፡፡ ለዚህም ሲባል የሰለጠነ የሰው ሃይል ማፍራቱ አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ የአክሱም ዩኒቨርስቲ የአርኪዮሎጂ ዲፓርትመንት ተከፍቶ ባለሙያዎች በመጀመሪያና በሁለተኛ ዲግሪ እንዲሰለጥኑ እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ኤጀንሲ የአካባቢውን የቤት አሠራር ጥበብ ጠብቆ ለማቆየትና ለማስቀጠል ይቻል ዘንድ ህድሞ የሚባሉት ከድንጋይ ብቻ የሚሰሩ ቤቶች የሚገነቡበት የመቀሌ ከተማ ክፍል እንዲኖር ለማድረግ መመሪያ እየተዘጋጀ መሆኑን አስታውቋል፡፡

የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ረቡዕ የተነገራቸው የአውራምባ ታይምስ ዋና አዘጋጅ የነበረው ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ እና የኢብአፓ ፓርቲ አመራር አቶ ዘሪሁን ገ/እግዚያብሄር፤ በየአመቱ የይቅርታ ጥያቄ ማቅረብ ስለሚቻል በድጋሚ እንደሚሞክሩ ቤተሰቦች ተናገሩ፡፡
በሽብርተኝነት ከተፈረጁ ድርጅቶች ጋር በመተባበር አመፅ የሚያስነሳ ፅሁፍ አቅርባችኋል በሚል የ14 እና 17 አመት እስር እንዲሁም ከ30ሺ ብር ያላነሰ ቅጣት እንደተፈረደባቸው የሚታወስ ሲሆን፤ ለይቅርታ ቦርድ በደብዳቤ ጥያቄ ያቀረቡት ከአንድ አመት ከአራት ወር በፊት እንደሆነ የጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ ባለቤት ወ/ሮ ብርሃኔ ተስፋዬ ለአዲስ አድማስ ገልፃለች፡፡ ይቅርታ እንደሚያገኙ ጠብቀን ነበር የምትለው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በተመሳሳይ ጉዳይ ሁለት የስዊድን ዜጐችም ይቅርታ ተደርጐላቸው ከእስር እንደተፈቱ በማስታወስ፣ በኢትዮጵያዊነታቸው አዎንታዊ ምላሽ እንደሚያገኙ ተስፋ ነበረን ብላለች፡፡
የይቅርታ ጥያቄያቸው ተቀባይነት እንዳላገኘ ሲነገራቸው በጣም ደንግጠናል ያለችው ወ/ሮ ብርሃኔ፤ በህጉ መሠረት ዘንድሮም የይቅርታ ጥያቄያቸውን እንደገና ለማቅረብ አስበዋል ብላለች፡፡
ከጋዜጠኛ ውብሸት እና ከአቶ ዘሪሁን ጋር የተከሰሱት ሂሩት ክፍሌ ያቀረቡት ተመሳሳይ የይቅርታ ጥያቄ ውድቅ እንደተደረገ በደብዳቤ የተገለፀላቸው ከሦስት ሳምንት በፊት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የ14 አመት እስርና የ30ሺህ ብር ቅጣት ተፈርዶባት ይግባኝ ያቀረበችው ጋዜጠኛ ርዕዮት አለሙ ቅጣቱ ወደ 5 ዓመት ዝቅ እንደተደረገላት ይታወሳል፡፡

             በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ከሞላ ጎደል ስኬታማ የሆነው የኢትዮጵያ አትሌቶች ቡድን በመንግስት እና በተለያዩ ባለድርሻ አካላት በኩል መቼ እንደሚሸለም አልታወቀም፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን የልዑካን ቡድኑን ወጤታማነት እና ድክመት በመገምገም በቅርቡ ይፋዊ መግለጫ እንደሚሰጥ የሚጠበቅ ሲሆን ለተገኘው ስኬት አስፈላጊውን የማበረታቻ ሽልማት ለማከናወን በዝግጅት ላይ እንደሆነ ምንጮች ገልፀዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮናው የሜዳልያ ደረጃ ሰንጠረዥ ኢትዮጵያ በሰበሰበቻቸው 10 ሜዳልያዎች ከዓለም 6ኛ እንዲሁም ከአፍሪካ ሁለተኛ ደረጃን ማግኘቷ ይታወሳል፡፡ ሞስኮ ላይ የኢትዮጵያ ቡድን በድምሩ 10 (3 የወርቅ፤ 3 የብርና 4 የነሐስ ) ሜዳልያዎች መሰብሰቡ በዓለም ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ከፍተኛው የሜዳልያ ብዛት ሲሆን አስሩ ሜዳልያዎች በ10 የተለያዩ አትሌቶች መገኘታቸው፤ በአዳዲስ የውድድር መደቦች ለመጀመርያ ጊዜ የተገኙ ሜዳልያዎች መኖርና ወጣት እና ተተኪ አትሌቶች በውጤታማነት መውጣታቸው የስኬቱን ታሪካዊነት አጉልቶታል፡፡ የኢትዮጵያን 3 የወርቅ ሜዳልያዎች በ10ሺ ሜትር ሴቶች ጥሩነሽ ዲባባ፤ በ800 ሜትር ወንዶች መሃመድ አማን እንዲሁም በ5ሺ ሜትር ሴቶች መሰረት ደፋር አስመዝግበዋል፡፡ ሶስቱን የብር ሜዳልያዎች ኢብራሂም ጄይላን በወንዶች 10ሺ ሜትር፤ ሃጎስ ገብረህይወት በወንዶች 5ሺ ሜትር እንዲሁም ሌሊሳ ዴሲሳ በወንዶች ማራቶን ሲጎናፀፉ አራቱን የነሐስ ሜዳልያዎች ደግሞ በ10ሺ ሜትር ሴቶች በላይነሽ ኦልጅራ፤ በ3ሺ መሰናክል ሶፍያ አሰፋ፤ በ5ሺ ሜትር ሴቶች አልማዝ አያና እንዲሁም በወንዶች ማራቶን ታደሰ ቶላ አግኝተዋቸዋል፡፡ ብዙውን ጊዜ በዓለም ሻምፒዮና እና በኦሎምፒክ ውድድሮች ማግስት ውጤታማ ለሚሆኑ የአትሌቶች ቡድን አባላት እና ለአጠቃላይ ልዑካኑ በመንግስት እና በሌሎች ባለድርሻ አካላት በኩል የገንዘብ፤ የማዕረግ እና ልዩ ልዩ የክብ ሽልማት ይሰጥ የነበረ ሲሆን ለአሁኑ ቡድን የሚደረገው ርብርብ ያነሰ መስሏል፡፡ ኒያላ ኢንሹራንስ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ሜዳልያ ላገኙ አትሌቶች የህይወት ዋስትና በመግባት ማበረታቱን ጀምሯል፡፡
በተያያዘ ዜና በዓለም ሻምፒዮናው ለሜዳልያ አሸናፊዎች እና እስከ ስምንተኛ ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች ከቀረበው እስከ 7 ሚሊዮን ዶላር የሚደርስ የሽልማት ገንዘብ በ10 ሜዳልያዎች እና በወንዶች ማራቶን በቡድን ውጤት በተገኘው ተጨማሪ የወርቅ ሜዳልያ ኢትዮጵያ 330ሺ ዶላር ስታገኝ በአጠቃላይ 12 ሜዳልያ የሰበሰበችው ኬንያ ድርሻዋ 640ሺ ዶላር ነው፡፡ ኢትዮጵያ ከሜዳልያ ተሸላሚዎች ከሰበሰበችው 330ሺ ዶላር ባሻገር እስከ ስምንት ባለው ደረጃ አራተኛ የወጡ 2 ፤ 5ኛ የወጡ 3፤ ሰባተኛ የወጡ 2 እና 8ኛ የወጡ 2 አትሌቶች በማስመዝገቧ በአጠቃላይ ከቀረበው የሽልማት ገንዘብ 408ሺ ዶላር ስታገኝ የኬንያ ድርሻ 891ሺ ዶላር ሆኗል፡፡
በሌላ በኩል የኬንያ ቡድን በሞስኮው የዓለም ሻምፒዮና አመርቂ ውጤት አላመጣም በሚል ከፍተተኛ ትችት ከሚዲያው እና ከአንዳንድ ባለሙያዎች እየደረሰበት ሰንብቷል፡፡ በወንዶች ማራቶን የኬንያ አትሌቶች በኡጋንዳ፤ በኢትዮጵያ፤ በጃፓንና በብራዚል ማራቶኒስቶች መበለጣቸው፤ በ3ሺ መሰናክል ከ1 እስከ 3 ደረጃ አለመገኘቱን የጠቀሱት ተቺዎቹ ሞስኮ ላይ የኬንያ ቡድን በቡድን ስራ እና በሚማርክ ቅንጅት አልሰራም በማለት ተቃውመዋል፡፡ የኬንያ ምክትል ፕሬዝዳንት በዓለም ሻምፒዮናው ሜዳልያ ላመጡ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት ሰሞኑን ያበረከቱ ሲሆን፤ ለወርቅ ሜዳልያ አሸናፊዎች 11495 ዶላር ፤ ለብር ሜዳልያ 8621 ዶላር እንዲሁም ለነሐስ ሜዳልያ 5748 ዶላር ተሰጥቷቸዋል፡፡
በአጠቃላይ በ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው የሜዳልያ ስብስብ ደረጃ ሰንጠረዥ ላይ 1ኛ ሆና የጨረሰችው ራሽያ በ7 የወርቅ፤ 4 የብርና 6 የነሐስ ሜዳልያዎች ሲሆን የደረጃ ሰንጠረዡን መሪነት ከአሜሪካ ስትነጥቅ ከ12 ዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ አሜሪካ በ6 የወርቅ፤ 14 የብርና 5 የነሐስ ሜዳሊያዎች ሁለተኛ ደረጃን አግኝታለች፡፡ ጃማይካ በ5 የወርቅ፤ በ2 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ ሶስተኛ ፤ ኬንያ በ5 የወርቅ፤ በ4 የብርና በ3 የነሐስ ሜዳልያዎች 4ኛ እንዲሁም ጀርመን በ4 የወርቅ፤ በ2 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያ አምስተኛ ሆነዋል፡፡ በሻምፒዮናው የአፍሪካ አገራት በነበራቸው ተሳትፎ 8 አገራት ብቻ የሜዳልያ ስኬት አግኝተዋል፡፡ ከአፍሪካ አህጉር ከፍተኛውን ውጤት በማስመዝገብ አንደኛ ደረጃ የያዘችው ኬንያ ስትሆን ኢትዮጵያ ሁለተኛ ሆናለች፡፡ ሌሎች አፍሪካን የወከሉ አገራት ኡጋንዳ በወንዶች ማራቶን ባገኘችው ብቸኛ የወርቅ ሜዳልያ ሶስተኛ፤ አይቬሪኮስት በ2 የብር ሜዳልያዎች አራተኛ፤ ናይጄርያ በ1 የብርና በ1 የነሐስ ሜዳልያዎች አምስተኛ፤ ቦትስዋና በ1 የብር ሜዳልያ ስድስተኛ እንዲሁም ደቡብ አፍሪካ እና ጅቡቲ በእያንዳንዳቸው በወሰዷቸው አንድ ነሐስ ሜዳልያዎች ሰባተኛ ደረጃን ለማግኘት ችለዋል፡፡ በዓለም ሻምፒዮና በተሳተፉባቸው የውድድር መደቦች ከ1 እስከ ስምንት ባለው ደረጃ ባስመዘገቡት ውጤት በመመስረት በተሰራው ደረጃ ኬንያ 3ኛ ስትሆን ኢትዮጵያ ደግሞ ስድስተኛ ነች፡፡ በሜዳልያ ስብስብ እና በአጠቃላይ ውጤት በወጣው ደረጃ አሜሪካ በ282 ነጥብ አንደኛ ደረጃ ስታገኝ፤ ራሽያ በ83 ነጥብ ሁለተኛ፤ ኬንያ በ139 ነጥብ ሶስተኛ፤ ጀርመን በ102 ነጥብ አራተኛ፤ ጃማይካ በ100 ነጥብ አምስተኛ፤ ኢትዮጵያ በ97 ነጥብ ስድስተኛ፤ እንግሊዝ በ79 ነጥብ ሰባተኛ እንዲሁም ዩክሬን በ51 ነጥብ ሰባተኛ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
ከ14ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በኋላ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የምንጊዜም የሜዳልያ ስብስብ የደረጃ ሰንጠረዥም ለውጦች ታይተዋል፡፡ በ14 የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የሰበሰበቻቸውን ሜዳልያዎች 300 (138 የወርቅ፤ 88 የብርና 74 የነሐስ) ያደረሰችው አሜሪካ አንደኛነቷን እንዳስጠበቀች ናት፡፡ ራሽያ 168 ሜዳልያዎች (53 የወርቅ ፤ 60 የብርና 55 የነሐስ)፤ ኬንያ 112 ሜዳልያዎች (43 የወርቅ፤ 37 የብርና 32 የነሐስ) ፤ ጀርመን 101 ሜዳልያዎች (35 የወርቅ፤ 28 የብርና 38 የነሐስ)፤ ጃማይካ 98 ሜዳልያዎች (24 የወርቅ፤ 42 የብርና 32 የነሐስ)፤ ሶቭዬት ህበረት 75 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 25 የብርና 28 የነሐስ) እንዲሁም ኢትዮጵያ 64 ሜዳልያዎች (22 የወርቅ፤ 19 የብርና 23 የነሐስ) በ14 የዓለም ሻምፒዮናዎች የተሳትፎ ታሪካቸው በማስመዝገብ እስከ 7 ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡

              የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የዛሬ ሳምንት በኮንጎ ብራዛቪል ከሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር የሚያደርገው ወሳኝ ጨዋታ እንደዘበት ደረሰ፡፡ ዋልያዎቹ በዚሁ ወሳኝ ፍልሚያ አድራጊነት ብቸኛው አማራጫቸው ነው፡፡ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን በበቂ የዝግጅት ግዜ እና የተጨዋቾች ስብስብ ሳይሰራ መቆየቱና የወዳጅነት ጨዋታ አለማድረጉ ያለውን እድል አስጨናቂ አድርጎታል፡፡ ዋልያዎቹ በኮንጎ ብራዛቪል መካከለኛው አፍሪካ ሪፖብሊክን ካሸነፉ ብራዚል በ2014 እኤአ ላይ ለምታዘጋጀው 20ኛው የዓለም ዋንጫ ለማለፍ በአፍሪካ ዞን ለሚደረገው የ10 ብሄራዊ ቡድኖች የመጨረሻ ጥሎ ማለፍ ማጣርያ ይበቃሉ፡፡ በምድብ 1 ሌላ ጨዋታ በደርባን በሚገኘው የሞሰስ ማዲባ ስታድዬም ደቡበ አፍሪካ ቦትስዋናን ታስተናግዳለች፡፡ ሁለቱ ቡድኖች ከምድባቸው የማለፍ እድል የሚኖራቸው ኢትዮጵያ ከተሸነፈች ብቻ ነው፡፡ በምድቡ ሁለተኛ ደረጃ ይዛ የምትገኘው ደቡብ አፍሪካ የማለፍ እድል የሚኖራት ቦትስዋናን ካሸነፈች በኋላ ኢትዮጵያ ከሴንተራል አፍሪካ ሪፐብሊክ ጋር አቻ ከወጣች ወይንም ከተሸነፈች ብቻ ይሆናል፡፡ በምድቡ በሶስተኛ ደረጃ ላይ የምትገኘው ቦትስዋና በበኩሏ ማለፍ የምትችለው ደቡብ አፍሪካን ማሸነፍ ከቻለች እና ኢትዮጵያ በሴንተራል አፍሪካ ከተረታች ይሆናል፡፡
የቦትስዋናው ጋዜጣ ሜሜጌ በድረገፁ እንደፃፈው ዜብራዎቹ በደቡብ አፍሪካ በሚኖራቸው ጨዋታ በቀላሉ 3 ነጥብ እንደማይጥሉ እና እጅ እንደማይሰጡ አትቷል፡፡ ደቡብ አፍሪካ ለወሳኙ ጨዋታ በጣም ጠንካራ የቡድን ስብስብ ለማዋቀር ደፋ ቀና ስትል መሰንበቷን ሲያወሳም፤ ከ23 የባፋና ባፋና አባላት ከ8 በላይ በአውሮፓ ፕሮፌሽናል ደረጃ የሚጫወቱ መሆናቸውን ጠቁሟል፡፡ ቦትስዋና ለሳምንቱ ጨዋታ በአብሳ ፕሪሚዬር ሊግ የሚጫወቱ ተጨዋቾችን እንዳሰባሰበች የሚገልፀው ጋዜጣው እነዚህ ልጆች በደቡብ አፍሪካ ሊግ ባላቸው ከፍተኛ ልምድ ጨዋታው የካይዘር ቺፍ እና የኦርላንዶ ፓይሬትስ ደርቢ ይመስላል ብሏል፡፡የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እያደረገ ባለው ዝግጅት አንድም የወዳጅነት ጨዋታ አለማሳቡ የሳምንቱን ግጥሚያ አቋሙን ሳይፈትሽ የሚደርስበት ሆኗል፡፡ ዋና አሰልጣኝ ሰውነት ቢሻው በተለያዩ አገራት ለፕሮፌሽናል ቅጥራቸው የተሰማሩ ምርጥ ተጨዋቾችን በቶሎ ማሰባሰብ ባይችሉም፤ 32 ተጨዋቾችን በመጥራት እየተዘጋጁ ነው፡፡ በብሄራዊ ቡድኑ ስብስብ በደቡብ አፍሪካ ሊግ የሚጫወተው ጌታነህ ከበደ፤ በሱዳን ሊግ ያለው አዲስ ህንፃ፤ በእስራኤል ያለው አስራት መገርሳ እንዲሁም በስዊድን ያለው ሳላዲን ሰኢድ በቶሎ አለመካተታቸው በቡድኑ መቀናጀት የተወሰነ ተፅእኖ ሊፈጥር ይችላል፡፡ በዝግጅት ቡድኑ ጊዮርጊስ 11፤ ኢትዮጵያ ቡና 4፤ ደደቢት 3፤ መከላከያ 2 ፤ መብራት ሃይል 2 ተጨዋቾች ሲያስመለምሉ በ2006 የውድድር ዘመን ፕሪሚዬር ሊጉን የሚቀላቀለው የዳሸን ቢራ ክለብ 3 ተጨዋቾች በማስመረጥ ብሄራዊ ቡድኑን ማጠናከሩ አስደንቋል፡፡ከደቡብ አፍሪካ ጋር ተደርጎ በነበረ ጨዋታ እያንዳንዳቸው ሁለተኛ የቢጫ ካርዳቸውን ያዩት የኋላው ደጀን አይናለም ሃይሉና ግብጠባቂው ጀማል ጣሰው በሳምንቱ ጨዋታ በቅጣት አይሰለፉም፡፡

ጆን ማን “The On’s Share” በሚል ርዕስ የፃፈው መፅሃፍ “የጃንሆይ ወርቅ መዘዝ” በሚል ርዕስ በሙሉቀን ታሪኩ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ፡፡
መፅሃፉ የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት መንግስቱ ኃይለማርያም፣ ከምዕራባውያን በተለይ ከአሜሪካ ድጋፍ በማግኘት የተራቡ ወገኖችን ለማበራከት የነደፉት እቅድ ባለመሳካቱ ወደ ሩሲያ መዞራቸውን፣ ከአንድ ባንክ የተበደሩትን 200 ሚሊዮን ዶላር ከሩሲያ የጦር መሳሪያ ለመግዛት ማዋላቸውንና ሌሎች ጉዳዮችን ይገልፃል፡፡ በኤችዋይ ኢንተርናሽናል አታሚዎች የታተመው ባለ 173 ገፅ መፅሃፍ፣ በ40.50 ብር እየተሸጠ ነው።

ኩኑዝ ኮሌጅ ከደረጃ ሁለት እስከ አራት በአካውንቲንግ ያስተማራቸውን 81 ተማሪዎችና ሁለት መፅሃፍት ዛሬ ከጠዋቱ 3 ሰዓት በአዲስ አበባ ማዘጋጃ ቤት ትያትርና ባህል አዳራሽ እንዲያስመርቅ አስታወቀ፡፡
የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ረዳት ፕሮፌሰር በድሉ ዋቅጅራ በክብር እንግድነት ይገኙበታል ተብሎ በሚጠበቀው የምረቃ ሥነስርዓት ላይ “የኢትዮጵያ የትምህርት ችግሮች ያስከተለው ኪሳራና መፍትሄዎች” የሚለውና “ወርቃማ ቁልፍ” የተሰኘ የእንግሊዘኛ ማስተማሪያ መፅሃፍ ይመረቃሉ ተብሏል፡፡ መፅሃፎቹን ያዘጋጁት የኩኑዝ ኮሌጅ እና የሜሪት የቋንቋ ትምህት ቤት ባለቤትና ፕሬዝዳንት አቶ ተስፋዬ ለጋ ናቸው፡፡
በተያያዘ ዜና ቅድስት ልደታ የጤና ሳይንስ ኮሌጅ በነርሲንግ፣በፋርማሲና በህክምና ላብራቶሪ የሰለጠኑ 169 ተማሪዎችን ነገ ከጠዋቱ 2 ሰአት፣ አምስት ኪሎ በሚገኘው የጠቅላይ ቤተክህነት አዳራሽ ያስመርቃል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን ፓትሪያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማቲያስ በምርቃት ሥነስርዓቱ ላይ ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በሌላም በኩል ኒው ጄኔሬሽን ዩኒቨርስቲ ኮሌጅ በተለያዩ የትምህርት ዘርፎች ያሰለጠናቸውን 250 ተማሪዎች ዛሬ ያስመርቃል። ተማሪዎቹ የሚመረቁት ሜክሲኮ አደባባይ በሚገኘው የአፍሪካ ህብረት አዳራሽ ነው፡፡

የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የትያትር ጥበባት መምህር የሆኑት አቶ ኤፍሬም ለማ ያዘጋጁት “መሰረታዊ የፊልም ድርሰት አፃፃፍ ዘዴ” መፅሃፍ ነገ ይመረቃል፡፡ መፅሃፉ በቀኑ 8ሰዓት የሚመረቀው በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ ስድስት ኪሎ ግቢ፣ ኔልሰን ማንዴላ አዳራሽ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትር በኢትዮጵያ ኪነጥበብ ጉልህ ድርሻ ያላቸውን ከያንያን ዛሬ እንደሚዘክር አስታወቀ፡፡ የትያትር ቤቱ ባልደረቦች “የኢትዮጵያ ብሄራዊ ትያትርን በአዲስ ራዕይ” በሚል መርህ በሚያቀርቡት ዝግጅት ላይ በትያትር ቤቱ የሰሩ እና ሌሎች አንጋፋ ባለሙያዎች ልምዳቸውን የሚያካፍሉ ሲሆን የቀይ ምንጣፍ አቀባበልና የምሳ ግብዣ እንደሚደረግላቸው ትያትር ቤቱ ጨምሮ ገልጿል፡፡

Saturday, 31 August 2013 12:40

ላ-ቦረና ሰኞ ይመረቃል

በኢንጂል አይስ ፊልም ፕሮዳክሽን የተዘጋጀውና በደራሲ ዮናታን ወርቁ የተደረሰው ላ-ቦረና ፊልም፣ የፊታችን  ሰኞ በ11 ሰዓት በብሄራዊ ትያትር ቤት ይመረቃል፡፡ በላይ ጌታነህ ዳሬክት ያደረገው ፊልሙ፣ በአንዲት ፈረንሳዊት አንትሮፖሎጂስት ጥናት ላይ ያተኮረ ሲሆን የቦረናን ባህልና ወግ ያንፀባርቃል  ተብሏል፡፡ በፊልሙ ላይ አለም ሰገድ ተስፋዬ፣ ማርያኔ ቤለርሰን፣ አንተነህ ተስፋዬና ሌሎችም ተውነውበታል፡፡ ፊልሙ የ1፡40 ርዝማኔ እንዳለውም ተገልጿል፡፡