Administrator
የአባባ ተስፋዬ 91ኛ ዓመት ልደት ዛሬ ይከበራል
በኢትዮጵያ ቴሌቪዥን “የልጆች ፕሮግራም” ተረት በማቅረብ ህፃናትን ለረጅም አመታት ያዝናኑትና ያስተማሩት እንዲሁም በተዋናይነታቸው የሚታወቁት አርቲስት ተስፋዬ ሳህሉ (አባባ ተስፋዬ) 91ኛ ዓመት የልደት በዓል ዛሬ ከቀኑ 8፡30 ጀምሮ በእቴጌ ጣይቱ ሆቴል እንደሚከበር ተገለፀ፡፡
የአባባ ተስፋዬን የልደት በዓል ያዘጋጁት ቤተሰቦቻቸውና “ልጆች ኢንተርቴይንመንት” ሲሆኑ አርቲስቶች፣ ታዋቂ ሰዎችና ጋዜጠኞች በሚታደሙበት በዚህ የልደት በዓል ላይ የተለያዩ ዝግጅቶች እንደሚካሄዱ ተጠቁሟል፡፡
የፍቅር ፈተና” በገበያ ላይ ዋለ
“windmills of the Gods” የተሰኘው የእንግሊዛዊው ደራሲ የሲድኒ ሼልደን ልቦለድ መጽሐፍ “የፍቅር ፈተና” በሚል በፋንታሁን ኃይሌ /አስኳል/ ወደ አማርኛ ተተርጉሞ ሰሞኑን ለገበያ ቀረበ። በ302 ገፆች የተቀነበበው ልቦለዱ፤ በ50 ብር ከ70 እየተሸጠ ሲሆን መጽሐፉን የሚያከፋፍለው ብርሃኔ መፃህፍት መደብር ነው፡፡
መፃህፍት አውደ ርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ ትላንት ተከፈተ
አሳታሚዎች፣ መፃሕፍት ሻጮችና መገናኛ ብዙኃን የሚሳተፉበት “ኢትዮ አለም አቀፍ የመፃህፍት አውደ ርዕይ እና የሚዲያ ኤክስፖ” በትላንትናው እለት በአዲስ አበባ ኤግዚቢሽን ማዕከል የተከፈተ ሲሆን ዝግጅቱ እስከ ፊታችን ሰኞ ክፍት ሆኖ እንደሚቆይ ታውቋል፡፡
ዝግጅቱ የንባብ ባህል እንዲዳብር፣ የመፃህፍት ገበያ እንዲጎለብት፣ የአሳታሚና የህትመት ኢንዱስትሪው እንዲጠናከር ታልሞ የተሰናዳ እንደሆነ አዘጋጆቹ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡ “በእውቀትና በመረጃ ለበለፀገ ህብረተሰብ መፃህፍትና ሚዲያ በአንድ ስፍራ” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው አውደ ርዕይና የሚዲያ ኤክስፖ ላይ የተለያዩ አዝናኝ ዝግጅቶች እንደሚቀርቡም ታውቋል፡፡
ትላንትን ጨምሮ ለአምስት ቀናት በሚዘልቀው ዝግጅት ላይ ከ60 በላይ አሳታሚዎች፣ መፃሕፍት ሻጮች፣ የግልና የመንግስት መገናኛ ብዙኃን፣ የጠፉና የማይገኙ መፃሕፍት አቅራቢዎች ይሳተፋሉ ተብሏል፡፡
“ሀገርና ፖለቲካ” መፅሀፍ ለንባብ በቃ
የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ (አንድነት) የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ በሆነው ሀብታሙ አያሌው የተፃፈው “ሀገርና ፖለቲካ” የተሰኘ መፅሀፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ በ18 ምዕራፍና በ272 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ፤ ስለ ኢትዮጵያ አመሰራረት፣ ስለ ኢትዮጵያ ስያሜ፣ ስለ ፖለቲካና ሃይማኖት፣ ስለ ቀደምት ኢትዮጵያ አፄዎችና ሌሎች በርካታ ርዕሰ ጉዳዮች ተነስተውበታል፡፡ የመፅሀፉ አዘጋጅ አቶ ሃብታሙ አያሌው፤ የኢህአዴግ መንግስት ለታሪክና ለሀገር ያለው እጅግ የመረረ ጥላቻና አፍራሽ ተልዕኮ መፅሀፉን ለመፃፍ እንዳነሳሳው በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ መፅሀፉ በ54 ብር ከ99 ሳንቲም እየተሸጠ ነው፡፡
“ህልፈተ አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢህአፓ” መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ
“ህልፈተ አንጃ ወ ክሊክ ዘ ኢህአፓ” በሚል ርዕስ በኃይለማርያም ወልዱ የተዘጋጀው መፅሀፍ ከሰሞኑ በገበያ ላይ ውሏል፡፡ “ማን ነው ኢህአፓን ያፈረሰው?” ሲል የሚጠይቀው መፅሀፉ፤ መልሱን በውስጥ ገፁ ያብራራል፡፡ በ18 ክፍሎች እና በ387 ገፆች ተመጥኖ የተሰናዳው የተቀነባበረው መፅሃፉ ትኩረቱን ከኢህአፓ አመሰራረት እስከ መፍረሱ እንዲሁም በመኢሶን እንቅስቃሴ ላይ ያደረገ ሲሆን ለአገር ውስጥ በ150 ብር፣ ለውጭ በ20 ዶላር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡
“የሞግዚቷ ልጆች” ፊልም ነገ ይመረቃል
በደራሲ ዮሀንስ ፀጋዬና አብዲሳ ምትኩ ተፅፎ በስንታየሁ አባይ የተዘጋጀው “የሞግዚት ልጆች” ፊልም ነገ ከቀኑ 8፡30 ሰዓት ጀምሮ በሁሉም ሲኒማ ቤቶች ለእይታ ይቀርባል፡፡ በያሬድ ፊልም ፕሮዳክሽን ፕሮዲዩሰርነት የቀረበው ይሄው ፊልም፤ የ1፡45 ሰዓት ርዝመት ያለው ሲሆን የሮማንስ ኮሜዲ ዘውግ እንዳለውም ለማወቅ ተችሏል፡፡
በፊልሙ ላይ አርቲስት አዳነች ወ/ገብርኤል፣ ታሪኩ ብርሀኑ (ባባ)፣ ሚካኤል ጆርጅ፣ ምህረት አበበና ሌሎችም ተዋንያን ተሳትፈውበታል፡፡ የፊልሙ አቅራቢ ያሬድ ፊልም ፕሮዳክሽን ከዚህ ቀደም “ክስተት” እና “አሜን” የተሰኙ ፊልሞችን ማቅረቡ ይታወቃል፡፡
“ሰኔ 30 የንባብ ቀን” ነገ ይከበራል
የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር ነገ “ሰኔ 30 የንባብ ቀን” በሚል መሪ ቃል ልዩ ፕሮግራም ያካሄዳል፡፡ የፕሮግራሙ አላማ በንባብ ላይ አገር አቀፍ መነሳሳትን መፍጠር መሆኑን የገለፀው ማህበሩ፤ ፕሮግራሙ ነገ ከጠዋቱ 4 ሰዓት ጀምሮ መነሻውን አራት ኪሎ አደባባይ፣ መድረሻውን አምስት ኪሎ ቴክኖሎጂ ፋኪልቲ የሚያደርግ የእግር ጉዞ እንደሚያካትት አስታውቋል፡፡
በእግር ጉዞው ላይ የኢትዮጵያ ደራሲያን ማህበር አባላት፣ የመንግስት ተወካዮች፣ የተለያዩ ድርጅቶች ሰራተኞች፣ የኢትዮጵያ ስካውት ማህበር አባላትና ሌሎችም የሚሳተፉ ሲሆን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባኤ አቶ ካሳ ተክለብርሃንና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ በክብር እንግድነት ተገኝተው ንግግር ያደርጋሉ ተብሏል፡፡ የዝግጅቱ ዋነኛ አላማ ሰኔ 30ን የንባብ ቀን አድርጎ ለመሰየም እና አገር አቀፍ የንባብ መነቃቃትን ለመፍጠር እንደሆነ ከማህበሩ መግለጫ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ፕሬዚዳንቱና አፈጉባኤው ኮከባቸው አልገጠመም
“ፕሬዚዳንት ኦባማን
ሳልከሳቸው አልቀርም”
“ፕሬዚዳንቱ የሀገሪቱን ህጎች በታማኝነት እያስፈፀሙ አይደለም፤ ስለዚህ ክስ መስርቼ ፍርድ ቤት ሳልገትራቸው አልቀርም፡፡” ሲሉ የተናገሩት የአሜሪካ ኮንግረስ አፈጉባኤ ቦህነር ናቸው፡፡
በኦባማ የመጀመሪያው አራት አመት የፕሬዚዳንትነት የስልጣን ዘመን አጋማሽ ላይ በተደረገው የኮንግረስ ምርጫ ሩፐብሊካኖች አሸንፈው አብላጫውን መቀመቻ እንደተቆጣጠሩ የኮንግረንሱ አፈጉባኤ በመሆን የተመረጡት ሪፐብሊካኑ ፖለቲከኛ ቦህነር ከፕሬዚዳንት ኦባማ ጋር አንድም ቀን እንኳ ኮከባቸው ገጥሞ አያውቅም፡፡ አንዳቸው ላንዳቸው ያላቸውን ጥላቻም ደብቀውት አያውቁም፡፡
ፕሬዚዳንት ኦባማም የማወጣቸው እቅዶችና ፕሮግራሞች በኮንግረሱ ተቀባይነት አግኝተው ስራ ላይ እንዳይውሉ አላስፈላጊ ችግር እየፈጠረ ስራዬን ይበጠብጣል በማለት አፈጉባኤ ቦህነርን በተደጋጋሚ ይነቅፋሉ፡፡
አፈጉባኤ ቦህነር በበኩላቸው ደግሞ “ፕሬዚዳንት ኦባማ እንደ አሜሪካ ፕሬዚዳንትነታቸው የሀገሪቱን ህጎች በታማኝነት ሥራ ላይ እያዋሉ አይደለም፤ እንዲያውም ይባስ ብለው በአሜሪካ ህዝብና በኮንግረሱ ላይ ልክ እንደ ንጉስ በግል ስልጣናቸው መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡” ሲሉ በጥላቻ የታሸ ስሞታቸውን በተደጋጋሚ ያቀርባሉ፡፡
ሰሞኑን ግን አፈጉባኤ ቦህነር፤ በፕሬዚዳንት ኦባማ ላይ ስሞታ በማቅረብ ብቻ አልተወሰኑም፡፡ ባለፈው ረቡዕ በሰጡት መግለጫ በፕሬዚዳንት ኦባማ ድርጊት ቆሽታቸው እንዳረረና ክስ ሊመሰርቱባቸው እየተዘጋጁ እንደሆነ በይፋ አስታውቀዋል፡፡
እንደ እውነቱ ከሆነ አፈጉባኤ ቦህነር ፕሬዚዳንት ኦባማን ልን እንደ ንጉስ የግል ስልጣናቸውን በመጠቀም መንቀሳቀስ ጀምረዋል እንዲሉና በንዴት እንዲንጨረጨሩ ያደረጋቸው ዋነኛው ምክንያት፣ ፕሬዚዳንት ኦባማ የሚያወጧቸውን አንዳንድ እቅዶችና የሚወስዷቸውን ውሳኔዎች ያለ ኮንግረንሱ ፈቃድና ስምምነት የግል ፕሬዚዳንታዊ ስልጣናቸውን (Executive order) በመጠቀም ስራ ላይ እንዲውሉ በማድረጋቸው ነው፡፡
በእርግጥም ይህ ሁኔታ አፈጉባኤ ቦህነር የፕሬዚዳንት ኦባማን ውሳኔዎች ኮንግረንሱ እንዳያፀድቀው በማድረግ፣ የአፈጉባኤነት ስልጣናቸውን ማሳየት እንዳይችሉ አድርጓቸዋል፡፡ ፕሬዚዳንት ኦባማ ደግሞ “ከእሱና በሪፐብሊካኖች ከተሞላው ኮንግረንስ ጋር አጽድቁ አታጽድቁ እያልኩ ምን አዳረቀኝ” ባይ ናቸው፡፡
የሆኖ ሆኖ በርካታ የአሜሪካ የዜና አውታሮች የአፈጉባኤ ቦህነርን ውሳኔ በሰፊው አራግበውላቸዋል፡፡ በርካታ የህግ ባለሙያዎች ግን ለቢራ ቤት ወሬ ማዳመቂያ ከመሆን ያለፈ አንዳችም ህጋዊ መሰረትና ፋይዳ የሌለው ነው በማለት አጣጥለውታል፡፡ የካሊፎርኒያ ዩኒቨርሲቲ የኤርቪን ህግ ትምህርት ቤት ዲን ኤርዊን ቸመሪንስኪ፤ “አፈጉባኤ ቦህነር እንዳለው ፕሬዚዳንታዊ ስልጣኑን ለምን ተጠቀመ በሚል በፕሬዚዳንቱ ላይ ክስ ከመሠረተ የአሜሪካንን ህገ መንግስት ጨርሶ አያውቀውም ወይም አልገባውም ማለት ነው፡፡ ይህ ደግሞ ለእርሱ ብቻ ሳይሆን በአፈጉባኤነት ለሚመራው ለአሜሪካ ኮንግረስ እጅግ ከባድ ሀፍረትና ውርደት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ዕጩ ፕሬዚዳንትና የከሸፈው የዴቪድ ካሜሮን ቅስቀሳ
ከሀያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት ውስጠ ህብረቱን አምርራ የምትጠላ፣ አባልነቱንም የማትፈልግ አንዲት ሀገር ብትኖር እንግሊዝ ብቻ ናት፡፡
እንግሊዝ ከዛሬ ሶስት ዓመት በፊት ከአውሮፓ ህብረት አባልነታቸው ለመውጣት ህዝበ ውሳኔ ካካሄዱት ሀገራት አንደኛዋ ናት፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮንና በስልጣን ላይ ለው የወግ አጥባቂ ፓርቲ በርካታ ባለስልጣናትና አንጋፋ አባላት እንግሊዝ የአውሮፓ ህብረት አባልነቷን ለቃ እንድትወጣ ከፍተኛ ፍላጎት አላቸው፡፡ በተለይ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዴቪድ ካሜሮን፤ በቀጣዩ ምርጫ በድጋሚ መመረጥ ከቻሉ፣ በ2017 ዓ.ም እንግሊዝ ከአውሮፓ ህብረት አባልነቷ እንድትወጣ ለማድረግ፣ ህዝበ ውሳኔ እንደሚያካሂዱ ቀደም ብለው ቃል ገብተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ባለፈው ግንቦት ወር በተካሄደው የአውሮፓ ፓርላማ ምርጫ የእንግሊዙን ዩኬአይፒ ፓርቲን ጨምሮ ፀረ አውሮፓ ህብረት የሆኑ ብሔርተኛና አክራሪ ፓርቲዎች ከፍተኛ ውጤት በማስመዝገባቸው አልተከፉም፡፡
በአንፃሩ ደግሞ የአውሮፓ ህብረት ጠላት የሆኑት የሀገራቸው መራጮች ከሳቸው የወግ አጥባቂ ፓርቲ ይልቅ ዩኬአይፒ ፓርቲን በአንደኛ ደረጃ በከፍተኛ ድምጽ መምረጣቸው፣ በቀጣዩ ዓመት ግንቦት ወር ላይ በሚደረገው ምርጫ በድጋሚ የመመረጣቸውን እድል አጠራጣሪ በማድረግ ከፍተኛ ጭንቀት ውስጥ ከቷቸዋል፡ላለፉት ዓመታት የአውሮፓ ህብረት ያጋጠሙትን በርካት ችግሮችና ፈተናዎች እንዲወጣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱት በአፍቃሬ አውሮፓ ህብረት አቋማቸው የታወቁት አንጋፋ ፖለቲከኛና የቀድሞው የሉክሰምበርግ ጠቅላይ ሚኒስትር የዦን ክሎድ ዩንከር የአውሮፓ ህብረት ጠንካራ ክንድና የስራ አስፈፃሚ አካል የሆነውን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንን የወቅቱን ፕሬዚዳንት ፖርቹጋላዊውን ማኑኤል ባሮሶን በመተካት ግንባር ቀደም እጩ ሆነው መቅረባቸው ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን በቀላሉ የማይቋቋሙት በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነበር፡፡
መጠጥ በመድፈር የታወቁ ጣጤ ከመሆናቸው በስተቀር ለብቃታቸው አንዳችም አቃቂር የማይወጣላቸው ሉክዘንበርጌው አንጋፋ ፖለቲከኛ ዦን ክሎድ ዮንከር፣ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን አዲሱ ፕሬዚዳንት ሆነው ከተመረጡ የአውሮፓ ህብረት የስራ አስፈፃሚ አካል የሆነውን የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን የሚታማበትን ችግሮች በተለያዩ የተሀድሶ እርምጃዎች በማስተካከል ከመቸውም ጊዜ በበለጠ ጠንካራ ኮሚሽን እንደሚያደርጉት በርካቶች እምነታቸውን የጣሉባቸው ሰው ናቸው፡፡ ይህንን ሁኔታና የሚያስከትለውን ፖለቲካዊ ጣጣ በሚገባ የተረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሩንም የዥን ክሎድ ዬንከርን ከቻሉ እጩነታቸውን ለማስቀረት፣ ይህን ማድረግ ካልቻሉ ደግሞ በቂ ድምጽ አግኝተው እንዳይመረጡ ለማድረግ ዙሪያ መለስ ቅስቀሳቸውን የጀመሩት ገና በማለዳ ነበር፡፡
ከፊንላንድ እስከ ስፔይን፣ ከፖርቹጋል እስከ ዴንማርክ ድረስ ባደረጉት ፀረ ዦን ክሎድ ዮንከር ቅስቀሳ የአብዛኞችን የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች ድጋፍ ማግኘት በመቻላቸው የልባቸውን እንዳደረሱ በመተማመን፣ የተወዳዳሪው ቀንደኛ ደጋፊ በሆኑት የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል ላይ የለበጣ ሳቅ ስቀውባቸው ነበር፡፡ ባለፈው አርብ ሰኔ 21 ቀን 2006 ዓ.ም ሃያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት መሪዎች አዲሱን የህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ለመምረጥ ስብሰባ እንደተቀመጡም፤ የእንግሊዝ ጠቅላይ ምኒስትር በከፍተኛ የድል አድራጊነትና የእርካታ ስሜት ተሞልተው ከዚህ በፊት አድርገውት በማያውቁት ሁኔታ አጠገባቸው ተቀምጠው ከነበሩት ከሮማንያና ከስፔይን መሪዎች ጋር ድምፃቸውን ከፍ አድርገው ያወሩ ነበር፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን የብራ መብረቅ የወረደባቸው የምርጫውን ውጤት ሲሰሙ ነው፡፡ በድንጋጤ በተቀመጡበት ክው ያሉት ዴቪድ ካሜሮን ያዩትንም ሆነ የሰሙትን ማመን አልቻሉም። አንጋፋው ፖለቲከኛ ዦን ክሎድ ዩንከር ከሃያ ስምንቱ የአውሮፓ ህብረት አባል ሀገራት የሀያ ስድስቱን ድምጽ በማግኘት፣ አዲሱ የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽን ፕሬዚዳንት ሆነው ተመረጡ። ከሀንጋሪው ጠቅላይ ሚኒስትር ቪክቶር ኦባን በስተቀር ለጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን ዦን ክሎድ ዩንከርን እንደማይመርጡ ቃላቸውን ሰጥተዋቸው የነበሩት መሪዎች ሁሉ ቃላቸውን በማጠፍ ለሰውየው ድምፃቸውን ሰጡ።
ኢትዮጵያዊያን “የፈሩት ይደርሳል፣ የጠሉት ይወርሳል፡፡” የሚሉት ተረት እነሆ በዴቪድ ካሜሮን ላይ ደረሰና ዦን ክሎድ ዩንከር ተመረጡ። የጠሏቸው እኒሁ ሰውም የአውሮፓ ህብረት ኮሚሽንን በአዲስ ፕሬዚዳንትነት ወረሱባቸው፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዴቪድ ካሜሮን አጠገባቸውና ፊት ለፊታቸው የተቀመጡትን መሪዎች በትዝብት አይን እያዩ “የፈፀማችሁብኝ ታላቅ ክህደት ነው!” አሉና በለሆሳስ ተናገሩ፡፡ሁሉም ነገር አልቆ በመውጣት ላይ እንዳሉ ከቻንስለር አንጌላ መርከል ጋር ተገናኙ፡፡
በሰውየው መመረጥ አንጀታቸው ቅቤ የጠጣው አንጌላ መርከል፤ የለበጣ ሳቅ በመሳቅ ብድራቸውን ለመመለስ አልሞከሩም፡፡ ይልቁንም የዴቪድ ካሜሮንን ጀርባ መታ መታ በማድረግ “አይዞህ! እንግዲህ መቻል ነው እንጂ ምን ይደረጋል!” በሚል አይነት አጽናንተዋቸው አለፉ፡፡
“በመሬት ቅርምት” ሚሊዮኖችን መመገብ ይቻላል ተባለ
የተለያዩ ሀገራት እንደሚከተሉት የኢኮኖሚ ፖሊሲ አይነት የተለያየ የኢንቨስትመንት አሠራሮችን ይከተላሉ፡፡ በተለይ የውጭ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ በየሀገሮቻቸው ባሉ የኢንቨስትመንት እድሎች ለውጪ ባለሀብቶች የተፈቀዱና የተከለከሉትን በግልጽ ለይተው ያስቀምጣሉ፡፡
በእኛ ሀገር ለምሳሌ የፋይናንስ፣ የቴሌኮሙኒኬሽንና የኢነርጂ ሴክተሮች ለውጪ ኢንቨስትመንት ዝግ ሲሆኑ የእርሻው ሴክተር ግን ክፍት ነው፡፡ በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ሶስት ሚሊዮን ሄክታር የእርሻ መሬት ለውጪም ሆነ ለሀገር ውስጥ ኢንቨስትመንት አዘጋጅታለች፡፡
እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ ሌሎች ታዳጊ ሀገራትም በሚሊዮን ሄክታር የሚቆጠር ሰፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጪ ባለሀብቶች ይሰጣሉ፡፡ የአካባቢና የቀደምት ነዋሪ ማህበረሰቦች መብት ጥበቃ ተሟጋች ተቋማትና ግለሰቦች፣ ሀገራት ሰፋፊ የእርሻ መሬቶችን ለውጪ ባለሀብቶች ኢንቨስትመንት የሚሰጡበትን አሠራር “የመሬት ቅርምት” (Land - grabbing) ይሉታል፡፡
የመብት ተሟጋቾቹ የወቅቱ “የትግል አጀንዳ” ይህን “የመሬት ቅርምት” አጥብቀው መቃወም ነው፡፡ እነዚህ ወገኖች ለተቃውሟቸው የሚያቀርቡት ዋነኛ መከራከሪያ፣ የቀደምት ነዋሪ ማህበረሰቦችን ጥንታዊ የአኗኗር ዘይቤ ያዛባል፣ ከአካባቢያቸው እንዲፈናቀሉና ለባሰ ችጋር እንዲጋለጡ ያደርጋል፣ የአካባቢ ጥበቃንም ያባብሳል፣ ባጠቃላይ የሀገሪቱን ነዋሪዎች ወደ ባሰ ድህነት ይከታል የሚል ነው፡፡
ሰሞኑን በአሜሪካ የቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ አማካኝነት የተደረገ ጥናት ግን የመብትና የአካባቢ ጥበቃ ተሟጋቾችን ተቃውሞ ፉርሽ የሚያደርግ መረጃ ይዞ ወጥቷል፡፡ በቨርጂኒያ ዩኒቨርስቲ የአካባቢ ጥናት ሳይንቲስት ፓውሎ ዲኦዶሪኮና በኢጣሊያ የሚላኖ ፖሊ ቴክኒክ ተቋም ከፍተኛ ተመራማሪ ማሪያ ክርስቲና ሩሊ የተደረገው ጥናት፣ በ “መሬት ቅርምት” ከለማ እርሻ በሚገኝ ምርት ቢያንስ ሶስት መቶ ሚሊዮን ሰዎችን አጥግቦ መመገብ እንደሚቻል ይፋ አድርጓል፡፡
ተመራማሪዎቹ ከዚህ ውጤት ላይ ለመድረስ እንደ አውሮፓ አቆጣጠር ከ2000 ዓ.ም ወዲህ በታዳጊ ሀገራት የተደረጉ ከ200 ሄክታር በላይ የእርሻ የውጭ ኢንሽትመንት ስምምነቶችን እንዳጠኑ ተናግረዋል። ለውጪ ኢንቨስትመንት ከተሰጡ የእርሻ መሬቶች በተገኘ ምርት በኢንዶኔዢያ፣ በማሌዢያ፣ በፓፑዋ ኒው ጊኒና በሱዳን የሚገኙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጐችን በሚገባ መመገብ እንደተቻለ መረጋገጡን አክለው ገልፀዋል - ተመራማሪዎቹ፡፡