Administrator
“ቼ ጉቬራያ የአብዮተኛው ህይወት” መፅሀፍ ገበያ ላይ ዋለ
በነፃ አውጭ ታጋይነት ዓለም አቀፍ ዝናና አድናቆት ያተረፈውን የቼ ጉቬራን ህይወት የሚያስቃኝ “ቼ ጉቬራ! የአብዮተኛው ህይወት” የተሰኘ መፅሀፍ ባለፈው ሳምንት መጀመሪያ ገበያ ላይ ውሏል፡፡
መፅሀፉ ከጆን ሊ አንደርሰን “Che Guevara፡ A Revolutionary Life” እና ከሪቻርድ ኤል ሃሪስ “Che Guevara፡ A Biography” መፅሀፎች ተጠናቅሮ የተሰናዳ መሆኑን አዘጋጁ ብርሃነ መስቀል አዳሙ በመፅሃፉ መግቢያ ላይ ገልጿል፡፡
ድህረ ታሪኩን ጨምሮ በስድስት ምዕራፍ የተከፋፈለውና በ254 ገፆች የተቀነበበው መፅሀፉ በ50 ብር ከ70 ለገበያ ቀርቧል፡፡
ማራኪ አንቀጽ
“..ምን ልርዳችሁ? ምን ፈልጋችሁ ነው?” አሉ ግራ ተጋብተው፡፡
ተዘጋጅተንበት ስለነበር ሁላችንም በአንድ ድምፅ
“ዜግነት!!! ዜግነት!!!...ነፃነት!!...አባት ሀገር!!...አባት ሀገር!!! Our father land!!...Father land!!!” እያልን መጮህ ጀመርን፡፡
ወንበር ላይ ወጥቼ እያጨበጨብኩ፤
“ነፃነት!! ዜግነት!! ነፃነት!! ዜግነት!!...” በማለት መዝፈን ስጀምር ሁሉም እኔን እየተከተሉ መዝፈንና ግድግዳ እየደበደቡ ሲረብሹ፣ አቶ ተስፋዬ የሚሰማቸው ስላጡ ቢሮውን ለቀው ወጡ፡፡ የኤምባሲው ሰራተኞች በሙሉ ደንግጠው ሲመለከቱን ጭራሽ ባሰብን፡፡ ከአስር ደቂቃ በኋላ አቶ ተስፋዬ አምባሳደሩን፣ ቆንስሉንና ሌሎች ነጭ ሆላንዳዊያንን አስከትለው መጡ፡፡
“እባካችሁ ተረጋጉና የምትፈልጉትን ንገሩን፡፡” ቢሉንም እኛ ግን መጮሃችንን ቀጠልን፡፡
“እንዲህ መሆናችሁ ጥቅም የለውም፡፡ ይልቁንስ አምባሳደሩ አጠገባችሁ ስለሚገኝ ይህን ዕድል ተጠቅማችሁ ጥያቄያችሁን ብታቀርቡ ይሻላል” አሉ አቶ ተስፋዬ፡፡
ይህን ስንሰማ ቀስ በቀስ ተረጋጋን፡፡ ወዲያውኑ አምባሳደሩ ንግግር ጀመረ፡፡ አቶ ተስፋዬ የአምባሳደሩን ንግግር ማስተርጐም ሲጀምሩ ከቆምኩበት ወንበር ላይ ዘልዬ ወረድኩ፡፡
“አቶ ተስፋዬ እንዲያስተረጉምልን አንፈልግም። እንግሊዘኛ ቋንቋ የሚችል ሰው አለን፡፡ አንተ እኛን ለማስፈራራት ብቻ ነው የምትፈልገው፡፡” ብዬ ጮህኩኝ።
ኢዩኤል በእንግሊዝኛ መናገር ሲጀምር ፀጥታ ሠፈነ፡፡
“እኛ የተረሳን የሆላንድ ተወላጆች ነን። አባቶቻችን ጥለውን ጠፍተዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ሀገራችን መሄድ እንፈልጋለን! ጥያቄያችን ይህ ነው፡፡” አለና በእንግሊዝኛ የተናገረውን ወዲያው በአማርኛ ለእኛ ተረጐመልን፡፡ አምባሳደሩ የተናደደ መሰለ፡፡
“የሆላንድን ዜግነት በጉልበት ማግኘት ትችላላችሁ?! ሁላችሁም ከዚህ ቢሮ አሁኑኑ ለቃችሁ ውጡ! በፖሊስ ሃይል ተገዳችሁ ከመውጣታችሁ በፊት አሁኑኑ በሰላም ውጡ!” ብሎ ድምፁን ከፍ አድርጐ ተናገረ፡፡
በመቀጠል ቆንስሉ ወደ እኛ ተጠግቶ “በሉ ውጡ!” እያለ ሲንጐራደድ፣ ሁሉም ልጆች “ምን እናድርግ?” በሚል ስሜት ተመለከቱኝ፡፡
“በለው! በለው!” አልኩና ከባድ ግርግር አስነሳሁ። ሰለሞን ታይሰን አይኑን አፍጥጦ ቆንስሉን ሲጠጋው ቆንስሉ ወደ ውጪ ሮጠ፡፡
“ነፃነት! ዜግነት! ነፃነት! ዜግነት! ዜግነት!” የሚል ጩኸት ተጀመረ፡፡
ሁሉም ሸሽተውን በርቀት ይመለከቱናል። ከሰላሳ ደቂቃ በኋላ አምስት የታጠቁ የኢትዮጵያ ፖሊሶች የእንጨት ዱላና ካቴና ይዘው መጡ፡፡ አምስቱም ፖሊሶች ተከታትለው ገብተው፤
“ፀጥ በል! ፀጥ በል! ለምንድነው የምትረብሹት?! ተነስ ውጣ! ውጣ!” እያሉ ያመናጭቁን ጀመር፡፡
ሳያስቡት ዘልዬ መጀመሪያ ወደኛ የተጠጋውን ፖሊስ ሁለቴ በቦክስ ስመታው፣ ተንገዳግዶ ጥግ ያዘ። ሰለሞን ሮጠና ጥግ የያዘውን ፖሊስ እግሩን ዘርጥጦ ጣለውና፣ በጉልበቱ ግንባሩን መቶት ራሱን አሳተው። የቀሩት ፖሊሶች ራሳቸውን ለመከላከል በያዙት ዱላ ሰለሞንን ፈነከቱት፡፡ በግብግቡ ውስጥ እንደምንም ብለው የተመታውን ፖሊስ ከቢሮ ጐትተው አወጡት። በመስታወት ውስጥ ቆመው ጠቡን የሚያዩት አምባሳደሩ፤ ቆንስሉና ሌሎችም ነጭ ሆላንዳዊያን በኛ ቁርጠኛነት ደንግጠዋል፡፡
በቢሮው ውስጥ የነበረውን አግዳሚ ወንበር አንስተን ለስድስት ተሸከምነውና ፊት ለፊት የሚያዩበትን መስታወት ለመስበር በወንበሩ መምታትና መደብደብ ጀመርን፡፡ በአምስተኛው ምት መስታወቱ ፈረሰ፡፡ ቢሮው ውስጥ የነበሩት አምባሳደሩ እና ሌሎች የኤምባሲው ሰራተኞች ቢሮውን ጥለው ከፖሊሶች ጋር ተቀላቀሉ። እንደማይቋቋሙን ሲረዱ ከሃያ በላይ የሚሆኑ ፖሊሶች አስጨምረው ከብዙ ትግልና መስዋዕትነት በኋላ ስለተዳከምን፣ ሁላችንንም በካቴና አስረው እየጐተቱ እና በዱላ እየቀጠቀጡ፣ በፖሊስ መኪና ወደ ፖሊስ ጣቢያ ወሰዱን፡፡ ፖሊስ ጣቢያ ስንደርስ ካቴናችንን እየፈቱ፣ አንድ ቤት ውስጥ አስገብተው ቆለፉብን፡፡ ሁላችንም በጣም ደክሞን ስለነበር ወለሉ ላይ በጀርባችን ተዘርረን ተኛን፡፡ ማታ ራት አቀረቡልን፡፡ በነጋታው ሁላችንም ሻወር ወስደን እስር ቤት ውስጥ መጫወትና ያደረግነውን ትግል ጀብዱ፣ ድፍረት፣ ቆራጥነት ስናወራ፣ የፖሊስ ጣቢያው መርማሪዎችና መቶ አለቃው በሩን ከፍተው መሃላችን ቆሙ፡፡ ለሁለት ደቂቃ አዩንና
“አመፀኛው ክልስ የታል? የዚህ አመጽ መሪ አንተ ነህ?” ብሎ አፈጠጠብኝ፡፡ የቀሩት መርማሪ ፖሊሶች “አመፀኛው ክልስ ተነስ!! አመፀኛ!!” እያሉ በጥፊ እየመቱኝ፣ ለምርመራና ጥየቃ የመቶ አለቃው ቢሮ አስገቡኝ፡፡
“አመፀኛው ክልስ ስምህ ማነው” አለ መቶ አለቃ፡፡
“ዳንኤል ሁክ” አልኩት…
(ከዳንኤል ሁክ “አመፀኛው ክልስ”
እውነተኛ ታሪክ መፅሃፍ የተቀነጨበ -2005 ዓ.ም)
የፍቅር ጥግ
ስለጓደኝነት
ጨርሶ አታብራራ - ወዳጆችህ አያስፈልጋቸውም፤ ጠላቶችህ ደግሞ አያምኑህም፡፡
ቪክቶር ግራይሰን
(እንግሊዛዊ ፖለቲከኛ)
ዕጣፈንታ ዘመዶችህን ይመርጥልሃል፤ አንተ ደግሞ ጓደኞችህን ትመርጣለህ፡፡
ጃኪውስ ዴሊሌ
(ፈረንሳዊ ገጣሚና የገዳም ሃላፊ መነኩሴ)
ወዳጆችና መልካም ባህሪያት ገንዘብ ወደማይወስድህ ቦታ ይወስዱሃል ይዘውህ ይሄዳሉ፡፡
ማርጋሬት ዎከር
(አሜሪካዊ ገጣሚ፣ ደራሲና ጋዜጠኛ)
እኩያህ ያልሆኑ ጓደኞችን አትያዝ፡፡
ኮንፉሺየሽ
(ቻይናዊ ፈላስፋ)
ሺ ጓደኞች ያሉት አንዳቸውም ለክፉ ቀን አይደርሱለትም፡፡ አንድ ጠላት ያለው በየሄደበት ያገኘዋል፡፡
አሊ ቤን አቢ ታሌብ
(“Hundred sayings”)
አየህ፤ የአዕምሮህ ጓደኛ የሆነች ሴት ስታገኝ ጥሩ ነው፡፡
ቶኒ ሞሪሶን
(አሜሪካዊ ደራሲ)
የድሮ ጓደኞች ሸጋ ናቸው፡፡ ንጉስ ጄምስ፤ የድሮ ጫማዎቹ እንዲያመጡለት ሁልጊዜ ይጠይቅ ነበር፡፡ እነሱ ነበሩ ለእግሩ የሚደሉት፡፡
ጆን ሴልደን
(እንግሊዛዊ የታሪክ ምሁር፣ የህግ ባለሙያ እና ፖለቲከኛ)
በወይን ጠጅ የተመሰረተ ወዳጅነት ደካማ ነው፤ እንደወይን ጠጁ የአንድ ምሽት ብቻ ነው፡፡
ፍሬድሪክ ቮን ሎጋው
ጠላቶችህን ከመውደድ ይልቅ ለወዳጆችህ ትንሽ እንክብካቤ ጨምርላቸው፡፡
ኤድጋር ዋትሰን ሆዌ
(አሜሪካዊ ደራሲ)
ሰው ወደፊት በህይወቱ ወደፊት በተራመደ ቁጥር ከአዳዲስ ሰዎች ጋር ካልተዋወቀ ብቻውን ይቀራል፡፡ ጌታዬ ሰው ወዳጅነቱን ሳያቋርጥ ማደስ አለበት፡፡
ሳሙኤል ጆንሰን
(እንግሊዛዊ የመዝገበ ቃላት አዘጋጅና ፀሐፊ)
“አደገኛ አጥር” እና አደጋው
በገጠር ገበሬው መኖርያ ቤቱን በእሾህ ያጥራል፡፡ በከተማ ደግሞ አጥር ከማጠር በተጨማሪ ቤት ጠባቂ ውሻ በማሳደግ፣ “ሃይለኛ ውሻ አለ” የሚሉ ማስጠንቀቂያዎች ተለጥፎ ማየት የተለመደ ነው፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን እንዲህ ያለው ማስጠንቀቂያ “አደገኛ አጥር” በሚል እየተተካ የመጣ ይመስላል፡፡ ቀድሞ በጥቂት ግለሰቦችና ድርጅቶች እንዲሁም ኤምባሲዎች ጥቅም ላይ ይውል የነበረው የኤሌክትሪክ አጥር አሁን በብዛት ጥቅም ላይ መዋል ጀምሯል፡፡
“ኔምቴክ” መቀመጫውን በደቡብ አፍሪካ ያደረገ፣ በ54 የተለያዩ የዓለም አገራት የኤሌክትሪክ አጥር በመስራት የሚታወቅ ዓለምአቀፍ ድርጅት ነው። ሚስተር ዲክ ኢራስመስ፤ በዚህ ድርጅት ውስጥ በኤክስፐርቶች ማናጀርነት ይሰራሉ። በቅርቡ በአዲስ አበባ በኤሌክትሪክ አጥር አተካከልና አጠቃቀም ዙሪያ በተዘጋጀ ስልጠና ላይ የኤሌክትሪክ አጥሮችን ወጪ በሚቆጥብና የላቀ ውጤት በሚያስገኝ ሁኔታ እንዴት መጠቀም እንደሚቻል አሰልጥነዋል፡፡ ላለፉት 25 ዓመታት በዘርፉ ሲሰራ የቆየው “ኔምቴክ”፤ በተለያዩ የአፍሪካ አገሮች ተመሳሳይ ስልጠናዎችን በመስጠት ይታወቃል። በነገራችን ላይ ድርጅቱ ከሚሰራባቸው የዓለም አካባቢዎች አብዛኞቹ የሚገኙት በአፍሪካ ውስጥ ነው፡፡ ለዚህ ምክንያቱ ደግሞ ከወንጀሎች መበራከት ጋር የተያያዘ እንደሆነ ዲክ ኢራስመስ ይናገራሉ፡፡
ኢራስመስ በኤሌክትሪክ አጥር አጠቃቀም ዙሪያ፣ ስለአደገኛነቱና በኢትዮጵያ ስላለው ሁኔታ እንደሚከተለው አስረድተዋል፡፡
የኤሌክትሪክ አጥሮች አጠቃቀም
የኤሌክትሪክ አጥሮች ውጤታማ እንዲሆኑ ከተፈለገ በመጀመሪያ በደንብ መተከል አለባቸው። የኤሌክትሪክ አጥሮች የሚተከሉት ሰውን ለመግደል አይደለም፡፡ ሌሎች ጉዳቶችንም ማድረስ የለባቸውም፡፡
ደቡብ አፍሪካ በአለም ላይ በርካታ ወንጀሎች ከሚፈፀምባቸው የአለማችን ክፍሎች አንዷ ናት። በአገሪቱ በሚፈፀሙ የተለያዩ ወንጀሎች ብዙ ሰዎች ንብረታቸውንና ህይወታቸውን ያጣሉ። የተለያዩ ወገኖች በኤሌክትሪክ አጥር አስፈላጊነት ላይ ጥያቄዎችን ቢያነሱም በወንጀሎች መበራከት የተነሳ፣ የኤሌክትሪክ አጥር ተጠቃሚዎች ቁጥር በእጅጉ እየጨመረ መጥቷል፡፡ የኤሌክትሪክ አጥር፤ ዝርፊያን ለመከላከልና ደህንነትን ለማረጋገጥ አስተማማኝ ብቃት አለው፡፡ በወጪም አንፃር ቢሆን የተጋነነ አይደለም፡፡
የኤሌክትሪክ አጥርን እኔ “ስሪ ዲ” ነው የምለው። “ዲተር”፣ “ዲቴክት እና “ዲሌይ” ማድረግ ነው ስራው፡፡ በመጀመሪያ አንድ ሰው አጥሩ ላይ ያለውን ማስጠንቀቂያ ሲያይ ወደዚያ እንዳይጠጋ ምልክት ይሰጠዋል፡፡ ያን አልፎ የሰው አጥር መንካት ሲጀምር “ዲቴክት” በማድረግ ገፍትሮ ይጥለዋል፡፡ በዚህም ግለሰቦች ወይም ቡድኖች ሊፈፅሙ ያሰቡትን ወንጀል እንዳይፈፅሙ በማዘግየትና ድምፅ በማሰማት ሰዎች በንብረታቸው ወይም በህይወታቸው ላይ ሊፈፀም ከታቀደ አደጋ ይጠብቃቸዋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ግን የኤሌክትሪክ አጥሮች በሰው ህይወት ላይ የሞት አደጋ ማድረስ የለባቸውም፡፡
የማይሰሩ የኤሌክትሪክ አጥሮች
በመስክ ስልጠናው የታዘብኳቸው ስህተቶች አሉ፡፡ በተለይ የኤሌክትሪክ አጥሮቹ በትክክል አለመተከል ዋነኛው ነው፡፡ አጥሩን ያስተከሉ ሰዎች መስራት አለመስራቱን ስለማያረጋግጡ አጥሩ ቢኖርም ላይሰራ ይችላል፡፡ ዋናው ስህተት በሽቦውና በኤሌክትሪኩ መካከል ያለው ልዩነት ሰፊ መሆኑ ነው፡፡ ይሄ ደግሞ ወንጀል ለሚፈፅሙ ሰዎች ምቹ ሁኔታን ይፈጥራል፡፡ እንዲህ ሲሆን ከኪሳራውም ባሻገር ሰዎች ለዘረፋና በህይወት ላይ ለሚቃጣ አደጋ ይጋለጣሉ፡፡
ሌላው አጥሩ ላይ ሌሎች ነገሮች ተሰቅለው የሚታዩበት ሁኔታ መኖሩ ነው፡፡ የሆኑ ብረቶች ተቀላቅለው ያየሁባቸው ቦታዎች አሉ፡፡ ዛፍና አትክልቶች ከአጥሩ ጋር ይቀላቀላሉ፡፡ እነዚህ ነገሮች የኤሌክትሪክ አጥሩ በተገቢው መንገድ አገልግሎት እንዳይሰጥ እንቅፋት ይሆናሉ፡፡ በስልጠናው ወቅት የኤሌክትሪክ አጥር የሚተክሉ ሰዎች በተገቢው መንገድ እንዲተክሉ በንድፈ ሃሳብና በተግባር የታገዘ ስልጠና ሰጥተናቸዋል፡፡ ከቤት ውበት ጋር በተያያዘም አተካከሉ ላይ የሚደረጉ ጥንቃቄዎች ተዳስሰዋል፡፡
አጥሩን ሊነካ የሚሞክር ሁሉ ወንጀለኛ ነው ብሎ ለመደምደም አስቸጋሪ ስለሚሆን፣ ይህ አጥር በተተከለበት ቦታ ሁሉ በግልፅ ሥፍራ የማስጠንቀቂያ ማስታወቂያ መለጠፍ ግዴታ ነው። ይሄ በደቡብ አፍሪካ በህግ ተደንግጐ የተቀመጠ ጉዳይ ነው፡፡ ይህንን አጥር የሚተክሉ ሰዎች ተገቢ ስልጠና ያገኙ መሆን እንዳለባቸው ህጉ ይደነግጋል፡፡ ባለቤቱ ሰው የማይገድልና የጥራት ደረጃውን ያሟላ ምርት መሆኑን ማረጋገጥ እንዳለበት ተቀምጧል፡፡ ማስጠንቀቂያውን ያላዩ ሰዎች አጥሩን ቢነኩ እንኳን ገፍትሮ ይጥላቸዋል እንጂ አይገድላቸውም፡፡
በዚህ አጥር እንስሳትም ቢሆኑ መጐዳት የለባቸውም፡፡ በኤሌክትሪክ አጥሩ ጉዳት የሚደርስባቸው በማንኛውም ኤሌክትሪክ ሊጎዱ የሚችሉ እንደ ሸረሪትና እባብ አይነት እንስሶች ብቻ ናቸው፡፡ ወፎች የሚቆሙት ብረቶቹ ላይ ስለሆነ ጉዳት አይደርስባቸውም፡፡
አፍሪካ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በብዙ ቦታዎች እንደ ስዊድን፣ አውስትራሊያና ኔዘርላንድስ ባሉ አገራትም የኤሌክትሪክ አጥሮች ብዙ ህይወቶችንና የንብረት ጉዳቶችን ታድገዋል፡፡
አጥሮቹ መብራት በሌለበት ጊዜ የባትሪ መጠባበቂያ ስላላቸው ስራቸውን አያቋርጡም፡፡ እኔ እንዳየሁትና ከሌሎች ቦታዎች ጋር እንዳነፃፀርኩት፣ አዲስ አበባ ያለው የመብራት ሀይል አቅርቦት እምብዛም የከፋ አይደለም፡፡
ኬኒያ፣ ናይጄሪያና፣ ጋና በመሳሰሉት አገራት የሀይል አቅርቦቱ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ተከታታይ የሀይል አቅርቦት በማይኖርባቸው ጊዜያት ወይም ቦታዎች ሶላር እንጠቀማለን፡፡
አዲሱ የ“ደህንነት” ኩባንያ
አቶ ሳምሶን ገብረስላሴ፤ የ“ሳሜክ ኢንጂነሪንግ” ባለቤትና ስራ አስኪያጅ ናቸው፡፡ በቅርቡ በ ደህንነት እና አደጋ መከላከል ስራ ላይ የተሰማራ አዲስ ድርጅት በአዲስ አበባ ከፍተዋል፡፡ “ሳሜክ ኢንጂነሪንግ ለንደን የሚገኘው የ “ሳሜክ” ኩባንያ እህት ድርጅት ነው፡፡ የደህንነት እና የአደጋ መከላከያ እቃዎችን ከውጪ በማስመጣት፣ በኢትዮጵያ በዚህ ስራ ላይ ለተሰማሩ ድርጅቶች ያቀርባል፡፡ እነዚህ ድርጅቶቹ መሳሪያዎቹን ከመግጠማቸው በፊት ስልጠናዎች በመስጠት ጥራቱን የጠበቀ ሥራ እንዲሰሩ ያግዛል፡፡ የ“ኔምቴክ” ስልጠናም የዚሁ አካል ነው፡፡ የ“ሳሜክ ኢንጂነሪንግ” ባለቤት አቶ ሳምሶን ገ/ሥላሴ፤ በኢትዮጵያ ስላለው የኤሌክትሪክ አጥሮች ተሞክሮአቸውን እንዲህ ይገልፁታል፡፡
“እኛ አገር ያለው ችግር አጥሩ በብዛት የሚተከለው በልምድ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የሚጠቀሙት ኤምባሲዎችና ትልልቅ መስሪያ ቤቶች ነበሩ፤ አሁን ግን ወንጀል እየተበራከተ ሲመጣ በመኖሪያ ቤቶች በስፋት እየተገጠመ ነው፡፡ አጥሩ መስራት አለመስራቱ የሚታወቀው ሌባ ያን አጥር ነክቶ ገፍትሮ ሲጥለው ነው፤ ተከላው በትክክል ስለማይከናወን ውጤታማነቱ አጠያያቂ ነበር። የሚገጥሙት ሠራተኞች መስራት አለመስራቱን ለማወቅ በቂ ስልጠናም ሆነ ማረጋገጫ መሳሪያዎች አልነበራቸውም፡፡
ከዚህ በፊት የተገጠሙትን ስናይ፤ መስመሩ የተላቀቀ፣ የተቆራረጠ፣ በቂ የኤሌክትሪክ ሀይል የሌለው ሁሉ አጋጥሞናል፡፡ ወደፊት ተከታታይ ስልጠናዎች ይኖራሉ፤ የሚተክሉት ሰዎች ብቃት ያላቸው እንዲሆኑና በአገራችን መንግስት የኤሌክትሪክ አጥር ህግ እንዲያወጣ ግፊት እናደርጋለን፡፡”
እስከዚያው ግን የኤሌክትሪክ አጥር ባለበት ሥፍራ ሁሉ ይሄንኑ የሚገልጽ ማስታወቂያ በግልፅ በሚታይ ቦታ ላይ መሰቀል እንዳለበት ባለሙያዎቹ በአጽንኦት ይናገራሉ፡፡
የጸሐፍት ጥግ
የማየውን ስዬ አላውቅም፡፡ ሰውነቴ የሚነግረኝን ነው የምስለው፡፡
ባርባራ ሄፕዎርዝ
(እንግሊዛዊ ቀራፂ)
ለእውነተኛ የፈጠራ ሰዓሊ ፅጌረዳን እንደመሳል የሚያስቸግረው ምንም ነገር የለም፤ ምክንያቱም ያንን ከማድረጉ በፊት በመጀመርያ እስከ ዛሬ የተሳሉትን ፅጌረዳዎች ከአዕምሮው ማውጣት አለበት፡፡
ሔንሪ ማቲሴ
(ፈረንሳዊ ሰዓሊና ቀራፂ)
ከራስህ ውስጥ መተዳደርያህን መፍጠር በጣም እንግዳ ነገር ነው፡፡
ጄምስ ቴይለር
(አሜሪካዊ ዘፋኝና የዘፈን ግጥም ደራሲ)
በፈጠራ የታከለ የሂሳብ አሰራር ባለበት ማን ማጭበርበር ይፈልጋል?
ካታሪን ዋይትሆርን
(እንግሊዛዊ ጋዜጠኛና ፀሐፊ)
ዕድል ለዝግጁ አዕምሮ ታደላለች፡፡
ሉዊስ ፓስተር
(ፈረንሳዊ ሳይንቲስት)
ሁሉም ሰው የፈጠራ ችሎታ ቢኖረውም የጥበብ ሰዎች ግን ጥቂት ናቸው፡፡
ፖል ጉድማን
(አሜሪካዊ ፀሐፊ፣ አስተማሪና የሥነ-አዕምሮ ሃኪም)
ከሥርጭት በፊት ፈጠራ ይቀድማል - አለበለዚያ የሚሰራጭ ነገር አይኖርም፡፡
አየን ራንድ
(ትውልደ ራሽያ አሜሪካዊ ፀሐፊና ፈላስፋ)
ደስታ ለሰውነት ጠቃሚ ነው፤ የአዕምሮን አቅም የሚያሳድገው ግን ሀዘን ነው፡፡
ማርሴል ፕሮስት
(ፈረንሳዊ ደራሲ)
ምስቅልቅሎሽ ግሩም ሃሳብ ይፈጥራል የሚል ታላቅ እምነት አለኝ፡፡ ምስቅልቅሎሽን እንደ ስጦታ ነው የምቆጥረው፡፡
(ሴፕቲማ ፓይንሴቴ ክላርክ
አሜሪካዊ የትምህርት ባለሙያ)
ዐይነ ስውር ድንጋይ ወርውሮ፣ ጠላቱን ስቶ ወዳጁን መታ!
“ምነው ወዳጅህ እኮ ነኝ፤ ቢለው”
“ዝም በል! ዋናው አለመሳታችን ነው!” አለው
ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት ጓደኛሞች ጫካ ሄደው እንጨት ቆርጠው ለመምጣት ይፈልጋሉ፡፡ አንደኛው በመጥረቢያ ቅርንጫፍ እየቆረጠ ሳለ እጁና ሳያስበው ቆርጦ ጣለው፡፡
ጓደኝየው የተቆረጠውን ክንድ በፌስታል ውስጥ ከትቶ፤ እጁ የተቆረጠ ጓደኛውን ይዞ ወደ ቀዶ - ጥገና ሐኪም ወሰደው፡፡
ዶክተሩም - “በጣም ዕድለኛ ነህ እኔ የተቆረጡ አካላትን መልሶ የማጣበቅ ክሂል ባለሙያ ነኝ፡፡ በአራት ሰዓት ውስጥ ተመልሰህ ና” አለው፡፡
ጓደኝየው - “እሺ ዶክተር ባሉኝ ሰዓት እመጣለሁ” ይልና ይሄዳል፡፡
ከተባለው ሰዓት በኋላ ሲመለስ፤ ዶክተሩ፤
“እጨርሳለሁ ካልኩበት ሰዓት ቀድሜ ጨረስኩ፡፡ ገዋደኛህ ጤንነቱ ተመልሶ እዚህ ታች ወዳለው ግሮሠሪ ሄዷል፡፡”
ጓደኝየው በደስታ ጮቤ እየረገጠ ወደተባለው መጠጥ ቤት ሄደ፡፡ ጓደኝየው ጭራሽ የዳርት ውርወራ ግጥሚያ ይዟል፡፡
ከጥቂት ሣምንታት በኋላ ጓደኛሞቹ አሁንም ወደጫካ ሄደው እንጨት ቆረጣ ላይ ተሰማሩ፡፡ ባለፈው እጁን የቆረጠው ሰው አሁን ደግሞ እግሩን ቆርጦ ጣለው፡፡ ጓደኝየው እንዳለፈው ጊዜ የተቆረጠውን እግር ፌስታል ውስጥ ከትቶ ጓደኛውን ይዞ ወደዚያው የአካል ቀዶ ጥገና ሐኪም ዘንድ ይዞት ሄደ፡፡
ሐኪሙም፤
“አየህ፤ የእግር ቀዶ - ጥገና ትንሽ ከበድ ያለ ነው፡፡ ከስድስት ሰዓት በኋላ ተመለስ” አለው፡፡
ጓደኝየውም፤
“እንዳልከው አደርጋለሁ ዶክተር” ብሎ ሄደ፡፡
ከስድስት ሰዓታት በኋላ ተመልሶ ውጤቱን ለማወቅ ወደ ሐኪም ሲመጣ፤
ሐኪሙ “ይገርምሃል ከነገርኩህ ሰዓት አስቀድሜ ሥራ አገባደድኩ፡፡ ጓደኛህ እዚያ ታች ወዳለው እግር ኳስ ሜዳ ሄዶልሃል” አለው፡፡
ጓደኝየው ሐኪሙ አመስግኖ ወደ ኳስ ሜዳው ወርዶ ሲያየው፡፡ ያ እግረ የተገጠመለት ጓደኛው ምን የመሳሰሉ ጎሎች እያገባ ነው፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ግን፣ ያ ጓደኝየው እጅግ ከባድ የመኪና አደጋ ይገጥመውና አንገቱ ሙሉ ለሙሉ ተቆረጠ፡፡ ጭንቅላቱ ብቻውን ወደቀ፡፡
እንደተለመደው የፈረደበት ጓደኛ ጭንቅላቱን በፌስታል ከትቶ ቀሪውን የጓደኝየውን አካል ጭኖ ወደ ሐኪሙ በረረ፡፡
ሐኪሙም፤
“ጭንቅላት መግጠም እጅግ ከባድ ነው፡፡ ለማንኛውን ከአሥራ ሁለት ሰዓት በኋላ ተመለስ” አለው፡፡
ተመልሶ ሲመጣ፤ ሐኪሙ፡-
“ይቅርታ አድርግልኝ፡፡ ጓደኛህ ሞቷል” አለው፡፡
ጓደኛውም፤
“ዕውነትክን ነው፡፡ የጭንቅላት ነገር ከባድ መሆኑን እገምታለሁ” አለ፡፡
ሐኪሙም፤
“ቀዶ ጥገናውን እንኳ ደህና አድርጌ ነበር የሰራሁት፡፡ ግን አየህ፤ አንተ ስታመጣው እዛ ፌስታል ውስጥ ታፍኖ ትንፋሽ አጥሮት ነው የሞተው!”
* * *
እጅ እግሩን ከቆረጠበት አደጋ ያልተማረ፣ አንገቱን የሚቆረጥበት ሰዓት ይመጣል! ከስህተት አለመማር መዘዙ ራስን እስከማጣት ያደርሳል፡፡
የአካላችን ሁሉ አናት የሆነው ጭንቅላት የሁሉ ነገራችን መሪ ነው፡፡ አንዴ ካመለጠ የማይገጣጠም መሆኑም ይሄንኑ የሚያመላክተን ነው፡፡ ሁሉን ተግባራችንን በአቅል በአቅል የሚያስቀምጥልን፣ የሚያደራጁልን፣ መንገድ የሚያገባልን የህይወት መሪያችን እሱ ነው፡፡ በሀገር ደረጃ ሲታይም፤ ተቋሞቻችንን፣ ድርጅቶቻችንን፣ ት/ቤቶቻችንን፣ ኮሚሽኖቻችንን፣ ሚኒስቴሮቻችንን፣ ኢንዱስትሪዎቻችንን ወዘተ የሚመሩ ርዕሰ - አመራሮች እንደጭንቅላት ናቸው፡፡ የእነዚህ ጭንቅላቶች ልክ መሆን፣ ቅጥ መያዝና የድርና ማግ መቀናጀት ነው የሀገርን ጤና ልክነት የሚረጋግጠው፡፡ ይህ የጭንቅላት ክህሎት ከሌለ፣ ካልተባ፣ ከቀልብ ካልተዋሃደ ወጥነት ያለው አመራር ማግኘት አይቻልም፡፡ ጨርሶ ባዶ የሆነ ዕለት ደሞ መሄድ ቀርቶ መቆም ያቅታል፡፡
ገጣሚና ፀሐፌ ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን፣ በ “በልግ” መጽሐፉ፤
“በዚህ በያዝኩት ጎራዴ፣ አንተግክን ቀንጥሼ ብጥለውም”
ከባርኔጣህ በስተቀር፣ ዋጋ ያለው ነገር አይወድቅም”
የሚለን ለዚህ ነው
“የዕውቀት ማነስ ፓለቲከኛ አደረገኝ” ከሚል ሰው ይሰውረን፡፡ አንዳንድ ፖለቲካ እጅግ አስመሳይ ከመሆኑ የተነሳ “የፆም መኪያቶ” “መኪያቶ” የሚባለውን ዓይነት ይሆናል፡፡ ወይ ሙሉውን መፆም ነው፣ አሊያ የሚለውን ሃሳብ ጨርሶ መርሳት ነው፡፡ “ፀብ ክርክር ካለበት ጮማ - ፍሪዳ፤ ፍቅር ያለበት ጎመን ይሻላል” ይላሉ አበው፡፡ በላሸቀ ኢኮኖሚ ውስጥ የፖለቲካ ጀግና መሆን እያደር ሽባ እንደሚያደርገን መገንዘብ ጭንቅላት ይዞ ማሰብን አይጠይቅም፡፡ ስለዚህ አስቀድሞ ኢኮኖሚውን ማዳን ነው፡፡ የዝሆን ጥርስ አናት ያለው ጉልላት ላይ ያለ የታችኛው ህዝብ መከራ አይታየውም፡፡ ያም ሆኖ የማይለወጥ ነገር የለም ሁሉም የጊዜ ጉዳይ ነው፡፡ ወይም እንደ ቪክተር ፍራንክል፤
“ሁኔታዎችን መለወጥ ካልቻልክ ራስህን ለመለወጥ ትገደዳለህ” እንላለን፡፡ ቪክተር ከ2ኛው ዓለም ጦርነት ሆሎኮስት ቃጠሎ እልቂት የተረፈ ሳይካትሪስትና ፀሐፊ ነው፡፡ ከእልቂት ከተረፈ በኋላ በሰው ልጅ ላይ ምን ለውጥ እንደሚመጣ አስተውሏል፡፡ ለእያንዳንዱ ለውጥ ያ ሁሉ መስዋዕትነት መደገም አለበት ማለት አይደለም፡፡ ከማዕበሉ በኋላ የረጋ አየር፣ አየርም ቢሉ ለውጥ የሰፈነበት፤ ይመጣል ማለት እንጂ!
የበላይም ይናገር የበታች ለሀገራችን የሚጠቅመው መደማመጥ ነው፡፡ በአንድ አቅጣጫ ብቻ እንደሚኬድበት መንገድ (One way road) አንሁን፡፡ የሚነገረንን እንስማ፡፡ ሌላው ሰው ድንገት ከእኔ የተሻለ ሀሳብ ቢያቀርብስ? እንበል፡፡
ደራሲ ከበደ ሚካኤል
“አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ”
ያሉትን አለመዘንጋት ከብዙ አባዜ ያድናል፡፡ እርግጥ ይህንንም የሚሰማ ካለ ነው፡፡
አበሻ በኢኮኖሚው መዘበትና ምፀት ማውራት ይችልበታል፡፡ ኢኮኖሚው አላፈናፍን ሲለው መውጫው በግጥም መተንፈስ ነው፡-
“በቆሎ፤ በዝናብ፣ ሲጠብስ እያያችሁ
ሰዉ ሥራ አይሰራም፣ ለምን ትላላችሁ!”
የፖለቲካ ምፀት ሲያምረው ደግሞ፤
ዐይነ ስውር ድንጋይ ወርውሮ፣ ጠላቱን ስቶ ወዳጁን መታ፡፡
“ምነው? ወዳጅህን? ወዳጅህ ነኝ እኮ!” ቢለው፤
“ዝምበል፡፡ ዋናው አለመሳታችን ነው!” አለ ይባላል፤ ይላል፡፡
የሰሞኑ ክስና ሥጋት ውስጥ የወደቀው የግሉ ፕሬስ
በማተሚያ ቤት ክልከላ ከ“ፋክት” በስተቀር ሁሉም አልታተመም
ሁሉም ተከሳሾቹ ክስ አልደረሰንም ብለዋል
“የግል ፕሬሱን ለማሸማቀቅና የስነ-ልቦና ጫና ለመፍጠር የተደረገ ይመስላል”
- ጋዜጠኛ ጌታቸው ወርቁ
“መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደመጥፎ ነገር አናየውም”
- አንተነህ አብርሃም (የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት)
“መንግስት ክስ የመሰረተው ከምርጫው ጋር በተያያዘ ሊሆን ይችላል”
- ዘ ኢኮኖሚስት
የፍትህ ሚኒስቴር ባለፈው ሰኞ ምሽት በኢቴቪ ባወጣው መግለጫ፤ ስርዓቱን በሃይል ለመናድ የአመፅ ቅስቀሳና የሐሰት ወሬዎች በመንዛት፣ ህገመንግስታዊ ስርዓቱ በሃይል እንዲፈርስና ህዝቡ በመንግስት ላይ ያለአግባብ አመኔታ እንዲያጣ የሚያደርጉ የወንጀል ተግባሮችን ፈጽመዋል ባላቸው አምስት መፅሄቶችና አንድ ጋዜጣ ላይ ክስ መመስረቱን ጠቁሟል፡፡
ክስ ተመስርቶባቸው የተባሉት “ፋክት”፣ “ጃኖ”፣ “ሎሚ”፣ “አዲስ ጉዳይ” እና “እንቁ” መፅሄቶች እንዲሁም “አፍሮ ታይምስ” ጋዜጣ አሳታሚዎች በበኩላቸው፤ መከሰሳቸውን በሚዲያ ከመስማታቸው ውጭ ምንም ዓይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ገልፀው መከሰሳቸው በሚዲያ መታወጁን ተቃውመውታል፡፡
የግል ፕሬሶቹ መከሰስ በሚዲያ መገለፁን ተከትሎ ማተሚያ ቤቶች “አናትምም” እንዳሏቸው አሳታሚዎች የተናገሩ ሲሆን በዛሬው ዕለት መውጣት ከነበረባቸው የህትመት ውጤቶች ከ “ፋክት” በስተቀር ሁሉም እንደማይታተሙ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡
ክስ ከቀረበባቸው የግል ፕሬሶች አንዱ የሆነው የ“ሎሚ” መፅሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ግዛው ታዬ፤ የክስ ዝርዝር እንዳልደረሳቸውና ጉዳዩን የነገራቸው አካል እንደሌለ ጠቁመው፤ ክሱ በቴሌቪዥን መገለፁ በሚዲያ ተቋሙ ጋዜጠኞች ላይ የስነልቦና ጫና ማሳረፉን ተናግረዋል፡፡ “ቀደም ብሎ እንደታሰሩት ጦማሪያንና ጋዜጠኞች አፈሳ ሊካሄድብን ይችላል በሚል ስጋት ጋዜጠኞች በተረጋጋ ሁኔታ በቢሮአቸው ተቀምጠው ስራቸውን መስራት አልቻሉም” ብለዋል፡፡
መንግስት የግል ፕሬሶቹ መከሰሳቸውን በሚዲያ ማወጁ ህገ መንግስቱን የጣሰ አካሄድ ነው ያሉት አቶ ግዛው፤ “ከዚህ በፊት በነበረው አሰራር ከፖሊስ ተደውሎ ቀጠሮ ከተሰጠን በኋላ በምንጠየቅበት ጉዳይ ላይ ቃላችንን እንድንሰጥ ይደረግ ነበር፤ ይሄኛው ለየት ያለ አካሄድ ነው” ብለዋል፡፡
የ“አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ሥራ አስኪያጅ አቶ እንዳልካቸው ተስፋዬ በበኩላቸው፤ መንግስት ጉዳዩን በተመለከተ በሚዲያ ከገለፀው ውጪ ምንም አይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው፣ በዛሬው እለት ይወጣ የነበረው “አዲስ ጉዳይ” መፅሄት ክሱ በቴሌቪዥን ከተነገረ በኋላ ማተሚያ ቤቱ “አላትምም” በማለቱ መጽሔቱለንባብ ባይበቃም ሰራተኞቻቸው ግን ያለምንም መረበሽ በመደበኛ ስራቸው ላይ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በሚቀጥለው ሳምንት “አዲስ ጉዳይ” ሌላ ማተሚያ ቤት ታትሞ እንደሚወጣ የጠቆሙት አቶ እንዳልካቸው፤ ተመስርቷል በተባለው ክስ ጉዳይ ድርጅታቸው ከህግ አማካሪዎች ጋር እየተማከረ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደሌሎቹ ተጠርጣሪ ፕሬሶች ሁሉ የክስ ዝርዝር እንዳልደረሳቸውና የህግ ሰው እንዳላነጋገራቸው የገለፀው የ “ፋክት” መጽሔት አምደኛ ተመስገን ደሳለኝ፤ መፅሄቱ እንደወትሮው መደበኛ ህትመቷ እንደሚቀጥልና በዛሬው እለትም እንደምትወጣ አስታውቋል፡፡ ከማተሚያ ቤት በኩል እስካሁን የገጠማቸው ችግር እንደሌለም ጋዜጠኛ ተመስገን ጨምሮ ገልጿል፡፡
መንግስት በአደባባይ ይፋ ባደረገው ክስ ፕሬሶቹን ወንጀለኛ ሳይሆን ተጠርጣሪ ማለቱን ያስታወሰው ተመስገን፤ ከዚህ መግለጫ ተነስተው “አናትምላችሁም” የሚሉ ማተሚያ ቤቶች ካሉ ትልቅ ስህተት እየሰሩ ነው ብሏል፡፡
በክሱ ተደናግጠን ስራችንን አናቆምም ያለው ጋዜጠኛው፤ “ወደፊት ይመጣል ብለን የምናስበው “የህዳሴ አብዮት” እስኪካሄድ ድረስ ማንኛውንም መስዋዕትነት እንከፍላለን፤ እንደዚህ ያሉ አፈናዎች ለጊዜው ካልሆነ በቀር ዘላቂ አይሆኑም” ብሏል፡፡ “ሠሞነኛው የመንግስት እርምጃ “የህዳሴ አብዮት”ን ለመቀልበስ የሚደረግ መፍጨርጨር ነው፤ ነገር ግን አይሳካላቸውም፤ መከሰሳችንም አዲስ አይደለም፤ በአብዮታዊ ጋዜጠኝነታችን እንቀጥላለን፤ ትግላችን ቀራኒዮ ድረስ ነው” ብሏል፡፡
የ“እንቁ” መፅሄት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ማህተመወርቅ በበኩላቸው፤ መንግስት ክሱን በአደባባይ ይፋ ካደረገ በኋላ ማተሚያ ቤቶች አናትምም እንዳሏቸውና ዘወትር ቅዳሜ ገበያ ላይ ትውል የነበረችው መጽሔት በዚህ ሣምንት ለገበያ እንደማትበቃ ገልፀዋል፡፡
መንግስት ከዚህ ቀደም በህትመት ውጤቶች ላይ የሚወጡ ፅሁፎች ህግ ጥሰዋል ካለ ዋና አዘጋጁን ይከስ እንደነበር የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፤ በዚህኛው ክስ አሣታሚዎች ላይ ማነጣጠሩ ሚዲያዎቹ እንዲዘጉ ያለውን ፍላጐት ያሣያል ብለዋል፡፡ ቀደም ሲል በመንግስት የሚዲያ ተቋማት በኩል በእነዚህ የህትመት ውጤቶች ላይ ሰፊ የማጥላላት ስራ ሲሰራ መቆየቱን ያስታወሱት ማኔጂንግ ዳይሬክተሩ፤ በተደጋጋሚ “መንግስት ሆደ ሰፊ ነው፤ ተቀራርበን እንሠራለን” የሚሉ መልዕክቶች በመንግስት ወገን እየተላለፉ ቢቆዩም የመንግስትን ሆደ ሰፊነትና ታጋሽነት በተግባር አላየነውም ብለዋል፡፡ “እንቁ” መጽሔት በፕሬስ አዋጁ መሠረት ክስ ቀርቦበት ወንጀለኛነቱ የተረጋገጠበት ጊዜ አለመኖሩን የጠቆሙት አቶ ፍቃዱ፤ አሁን ግን መጽሔቱ በህትመት ኢንዱስትሪው ይቀጥላል አይቀጥልም የሚለውን ለመወሰን እንደተቸገሩ ገልፀዋል፡፡
ሌላው ክስ የቀረበበት የ“ጃኖ” መጽሔት ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ አስናቀ ልባዊ፤ ምንም ዓይነት ክስ እንዳልደረሳቸው ጠቁመው የክሱ መግለጫ በቴሌቪዥን ከተሰራጨ በኋላ ማተሚያ ቤቶች መጽሔታቸውን አናትምም እንዳሏቸው ገልፀዋል፡፡ “ማተሚያ ቤቶች ፍቃደኛ ካልሆኑ የት ሄደን እናሣትማለን?” ሲሉ የጠየቁት አቶ አስናቀ፤ “የመንግስት መልካም ፍቃድ ከሆነ እንቀጥላለን፤ ካልሆነ ለማቆም እንገደዳለን፤ ነገር ግን ሚዲያው በመንግስት መልካም ፍቃድ ብቻ መንቀሳቀሱ ያሣዝናል” ብለዋል፡፡
በክሱ ውስጥ ያልተካተቱ የግል ፕሬስ አሳታሚዎችና አዘጋጆች በበኩላቸው፤ ሰሞኑን በመንግስት ተመሰረተ የተባለው ክስ የግል ሚዲያውን ስጋት ውስጥ እንደከተተው ተናግረዋል፡፡
የኢትዮ ምህዳር ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ አቶ ጌታቸው ወርቁ፤ “የሰሞኑ የመንግስት ክስ ለተቀሩትም የማስጠንቀቂያ መልዕክት ያስተላለፈ እንደመሆኑ “ማነሽ ባለተራ” እየተባለ በስጋት እንድንሠራ የሚያደርግ ነው፤ ይህ ደግሞ በአሣታሚዎችም ሆነ በጋዜጠኞች ላይ የሚፈጥረው የስነልቦና ጫና በቀላሉ የሚታይ አይደለም” ብለዋል፡፡
ሚዲያና ህዝብ ከሚፈላለጉበት ጊዜ አንዱ የምርጫ ወቅት መሆኑን የጠቆሙት አቶ ጌታቸው፤ ክሱ በመንግስት መገናኛ ብዙሀን ይፋ መደረጉ የግል ፕሬሱን ለማሸማቀቅና የስነልቦና ጫና ለመፍጠር ይመስላል ብለዋል፡፡ “ክሱ በቀጥታ አሣታሚው ላይ እንዲያነጣጥር መደረጉ ከአሣታሚዎች ነፃ ሊሆን ይገባዋል በሚባለው የጋዜጣው ኤዲቶሪያል ፖሊስ ላይ ጣልቃ መግባት እንዲጀምሩ ያደርጋቸዋል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀው፤ ይሄ ደግሞ በዚህም ጋዜጠኞች በሙያቸው ነፃ ሆነው እንዳይሠሩ የሚሸብብ የሚዲያ ድባብ ሊፈጠር ይችላል ብለዋል፡፡
“በመግለጫው ላይ ክሱ ህግን በማያከብሩ ሌሎች ሚዲያዎች ላይም ይቀጥላል መባሉ በአጠቃላይ ሃሳብን በነፃነት የመግለጽን መብት ጥያቄ ውስጥ ከትቶ በነፃ ሚዲያው አካባቢ ፍርሃትና መሸማቀቅ እንዲፈጠር ያደርጋል” ሲሉም አክለው ገልፀዋል፡፡
“መንግስት በሚዲያ ክሱን ይፋ ማድረጉ አጠቃላይ የሚዲያ ምህዳሩን ይረብሸዋል” ያሉት የሪፖርተር ጋዜጣ ማኔጂንግ ዳይሬክተር አቶ መላኩ ደምሴ፤ ከሁለት አስርት አመታት እድሜ ያልዘለለውን ፕሬስ ገና ዳዴ እያለ ባለበት ወቅት እንደመንከባከብ እንዲህ ያሉ እርምጃዎች መወሰዳቸው አግባብ አይደለም ብለዋል፡፡
ክስተቱ በሃገራችን ፕሬሶች ላይ መሠረታዊ ችግሮች እንደሚንፀባረቁ ይጠቁማል የሉት አቶ መላኩ፤ ከመንግስት ባለስልጣናት ጫና ባሻገር የሙያ እውቀት ችግር እንደሚንፀባረቅም ተናግረዋል፡፡ ሚዲያው እየተንቀሳቀሰበት ያለው ድባብ በራሱ ጥሩ አይደለም፤ በዚህ የተነሳ የትኛውም ባለሀብት ወደዚህ ዘርፍ መግባት አይፈልግም ሲሉ በአጠቃላይ ሚዲያው በአሣሣቢ ደረጃ ላይ መድረሱን ጋዜጠኛ መላኩ ገልፀዋል፡፡
አዲስ የተቋቋመውና እውቅና ለማግኘት በሂደት ላይ ያለው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች መድረክ ምክትል ሊቀመንበር ጋዜጠኛ ስለሺ ሃጐስ በበከሉ፤ በመንግስት በኩል እንዲህ መሰሉ እርምጃ እንደሚወሰድ አስቀድሞ ይታወቅ እንደነበር ይናገራል፡፡ ማህበራቸው የመንግስትን እርምጃ እንደሚቃወምና አሁን ባለው የሚዲያ እንቅስቃሴ በተነባቢነትና በተደራሽነት ሰፊ ይዞታ ያላቸውን “ፋክት”፣ “ሎሚ” እና “አዲስ ጉዳይ” መጽሔቶችን መክሰሱ በሚዲያ ባለቤቶች ላይ ብቻ ሳይሆን በአንባቢያን ላይም ተጽእኖ ያሳርፋል ባይ ነው፡፡
ክሱ በራሱ አደናጋሪ ነው የሚለው ጋዜጠኛ ስለሺ፤ በመገናኛ ብዙሃን አዋጅ መሠረት ጥፋት ካለ በእያንዳንዱ ጽሑፍ ተጠያቂው አካል ይጠየቃል እንጂ ተቋማት ላይ ማነጣጠሩ ተገቢ አይደለም ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ጋዜጠኞች ማህበር ፕሬዚዳንት አቶ አንተነህ አብርሃም በበኩላቸው፤ “ማንኛውም የሚዲያ ተቋም ሲከሰስ አሣሣቢ ቢሆንም መንግስት ህጋዊ እርምጃ መውሰዱን እንደመጥፎ ነገር አናየውም” ብለዋል፡፡
የክሱ ሂደት ሲታይ መጽሔቶችም ሆነ ጋዜጣው መደበኛ ስራቸውን እንዲሰሩ ቢደረግ መልካም ነው ያሉት አቶ አንተነህ፣ “እኛ እንደ ጥሩ ነገር ያየነው ከሚዲያ ተቋማቱ ጋር ጋዜጠኞች ተደርበው አለመከሰሳቸውን ነው፤ የአሁኑ የመንግስት እርምጃ፣ ጋዜጠኛውን ከመክሰስ ይልቅ ተቋሙም ሃላፊነት እንዲሰማው ለማድረግ የጐላ ጠቀሜታ አለው በሚል የተወሰደ እርምጃ ይመስለኛል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
መንግስት ክሱን በሚዲያ መግለፁ ሁለት አይነት መልዕክት እንደሚኖረው አቶ አንተነህ ጠቁመው፤ አንደኛው ጋዜጠኛ ጥፋት ካጠፋ በህግ እንደሚጠየቅ ያስተምራል፣ በሌላ በኩል ፍርሃት ያሳድራል ብለዋል፡፡ ፍርሃት መፈጠሩ በበጐ የሚታይ አይደለም ያሉት ፕሬዚዳንቱ፤ ዞሮ ዞሮ ለህግ የበላይነት ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባ ጠቁመው፤ እርምጃው ከሌሎቹ ጊዜያት በተሻለ ረጋ ተብሎ የተወሰደ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በአሳታሚዎቹና በሚዲያ ተቋማቱ ላይ የተመሰረተውን ክስ በተመለከተ አስተያየት እንዲሰጡ የጠየቅናቸው የህግ አማካሪና ጠበቃ አቶ አመሃ መኮንን፤ በማናቸውም ወንጀል ጉዳይ የክስ ሂደት የሚጀምረው ከፖሊስ ምርመራ መሆኑን አስረድተው፣ በዚህ ጉዳይ ፍትህ ማኒስቴር ያቀረበው ክስ አሣታሚዎች ላይ በመሆኑ ስራ አስኪያጆች በቀረበባቸው ክስ ላይ ቃል መስጠት አለባቸው ይላሉ፡፡ “ይህ ስለመደረጉ የተሟላ መረጃ የለኝም፤ ነገር ግን በተለያዩ ሚዲያዎች ቃል አለመስጠታቸው እየተነገረ መሆኑን እየሰማሁ ነው ያሉት ባለሙያው፤ “ክሱ ይፋ የተደረገበት መንገድ ትክክለኛ ነው” የምልበት ምንም የህግ ምክንያት የለኝም፤ ምናልባት የህትመት ጉዳይ የሚመረመር ጉዳይ የለውም፤ ጋዜጠኞች ሲከሰሱ የጊዜ ቀጠሮ አይጠየቅባቸውም ቢባልም ማንኛውም ተሠራ የተባለ ወንጀል በፖሊስ በኩል ሣያልፍ ቀጥታ በአቃቤ ህግ ክስ ይመሠረታል ማለት አይደለም፤ የምርምራ መዝገብ በፖሊስ መደራጀት አለበት” ብለዋል - አቶ አመሃ፡፡
“ፍትህ ሚኒስቴር ክስ መስርቻለሁ ብሎ በሚዲያ መናገሩ ከህግ አንፃር ብዙም ጥያቄ የሚያስነሳ አይመስለኝም” ያሉት አቶ አመሃ፤ “ክስ መመስረቱ የተነገረበት መንገድ ህገወጥ ነው ማለት ባይቻልም አላማው ምንድን ነው የሚል ጥያቄ ያስነሳል” ብለዋል፡፡
ከህግ አንፃር በዋናነት ሊታይ የሚገባው የተጠያቂነት ቅደም ተከተል ነው የሚሉት የህግ ባለሙያው፤ በፕሬስ አዋጁ መሰረት መጀመሪያ የሚጠየቀው ዋና አዘጋጁ መሆኑን ጠቁመው ዋና አዘጋጁ ከሌለ ወይም ኖሮም የአዘጋጅነትን ሃላፊነት መወጣት የማይችል ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው ሃላፊነቱ ወደ አሣታሚው የሚተላለፈው ይላሉ። “ፍትህ ሚኒስቴር ክሱን ያቀረበው አዘጋጆቹን መጀመሪያ ጠይቆ ነው? ሃላፊነታቸውን መወጣት የማይችሉ ሆኖ አግኝቷቸው ነው ወደ አሣታሚዎች የሄደው? የሚለው ግልጽ አይደለም፤ የህግ አካሄድ ጥያቄም ከዚህ አንፃር ሊነሣ ይችላል” ብለዋል አቶ አመሃ፡፡
የክስ ሂደቱ በፍርድ ቤት እየታየ የሚዲያ ተቋማቱ ከህትመት የሚታገዱበት ሁኔታ ሊኖር ይችላል? ስንል የጠየቅናቸው የህግ አማካሪው፤ አቃቤ ህግ ይታገዱ ብሎ ካመለከተ፣ ተከሳሾች ለእግድ ጥያቄው የሚያቀርቡትን መከራከሪያ ፍ/ቤት አይቶ ሊያግዳቸው ይችላል ብለዋል።
የመንግስት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ፅ/ቤት ሚኒስትር አቶ ሬድዋን ሁሴን ባለፈው ሰኔ ወር ታትሞ ከወጣው ዘመን መፅሄት ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ “እኛ አገር ነፃ የግል ፕሬሱ ውስጥ ያሉ ሚዲያዎች በርከት ያሉት ነፃ አውጪ ናቸው፡፡ ነፃ አውጪ ከሆኑ ውጊያ ገጥመዋል ማለት ነው፡፡ ውጊያ ከገጠሙ እንደማንኛውም ተዋጊ ይታያሉ ማለት ነው፡፡” ብለዋል፡፡
ታዋቂው መጽሄት ዘ ኢኮኖሚስት ከኢትዮጵያ ነጻ ፕሬስ ጋር በተያያዘ ትናንት ለንባብ ባበቃው ዘገባ፣ አገሪቱ ጋዜጠኞችን በማሰር ከኤርትራ ቀጥላ ከአፍሪካ አህጉር በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝ የሲፒጄን መረጃ ጠቅሶ የጻፈ ሲሆን፣ መንግስት በመጽሄቶቹና በጋዜጣው ላይ ክስ የመሰረተው፣ ከመጭው አገራዊ ምርጫ ጋር በተያያዘ ጭንቀት ውስጥ በመግባቱ ሊሆን እንደሚችል ግምቱን አስቀምጧል፡፡
አለማቀፉ የጉዲፈቻ ተቋም በሙስናና በማጭበርበር ሕፃናትን ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ መውሰዱን ኃላፊው አመኑ
ለክልል ባለስልጣንና ለአንድ የስራ ሃላፊ ገንዘብና ውድ ስጦታ ሰጥቻለሁ ብለዋል
ተቀማጭነቱን በአሜሪካ ያደረገው ‘ኢንተርናሽናል አዶፕሽን ጋይድስ’ የተባለ አለማቀፍ የጉዲፈቻ ተቋም የውጭ ፕሮግራም ክፍል ሃላፊ በመሆን ለረጅም አመታት ያገለገሉት አሊያስ ቢቬንስ፣ ተቋሙ በሙስናና በማጭበርበር ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በጉዲፈቻ ወደ አሜሪካ ይወስድ እንደነበር በሳውዝ ካሮሊና የፌደራል ፍርድ ቤት ቀርበው ቃላቸውን እንደሰጡ አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ ዘገበ፡፡
የአሜሪካ መንግስት የፍትህ ተቋም ባለፈው ረቡዕ ያወጣውን መግለጫ የጠቀሰው ዘገባው፣ የስራ ሃላፊው እ.ኤ.አ ከ2006 እስከ 2009 በነበሩት አመታት ኢትዮጵያውያን ህጻናትን በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ ለመውሰድ ሲሉ ጉዳዩ ለሚመለከታቸው የኢትዮጵያ መንግስት ባለስልጣናትና የስራ ሃላፊዎች ጉቦ መስጠታቸውን እንዲሁም ለአሜሪካ መንግስት ሐሰተኛ የጉዲፈቻ ሠነድ በማቅረብ የማጭበርብር ድርጊት ሲፈጽሙ እንደቆዩ ማመናቸውን ጠቁሟል።
የ42 አመቷ አሊያንስ ቢቬንስ ከሌሎች አሜሪካውያንና ኢትዮጵያውያን ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመመሳጠር ከኢትዮጵያ የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ጋር ተፈራርመናቸዋል ያሉትን የተጭበረበሩ የጉዲፈቻ ስምምነቶችና ተያያዥ ሃሰተኛ ሰነዶች ለአሜሪካ መንግስት መስጠታቸውን እንዳመኑ የጠቆመው ዘገባው፣ በዚህ መልኩ በህገወጥ መንገድ ወደ አሜሪካ እንዲገቡ ከተደረጉት ኢትዮጵያውያን መካከል የተወሰኑት፣ ከተቋሙ ጋር የጉዲፈቻ ስምምነት አድርገዋል በተባሉት የወላጅ አልባ ህጻናት ማሳደጊያዎች ውስጥ ያልተመዘገቡና ተገቢው እንክብካቤ ያልተደረገላቸው መሆናቸው እንደተረጋገጠም አመልክቷል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ጉዳዩ የሚመለከታቸውን የመንግስት ባለስልጣንና የስራ ሃላፊ የድርጊቱ ተሳታፊ እንዲሆኑ በማሳመን እንዲሁም በጥቅማጥቅሞች ደልለው ወደ አሜሪካ በመውሰድ፣ የህጻናቱ የቪዛ ጉዳይ በቀላሉ እንዲያልቅና ጉዲፈቻውን በማጭበርበር ለማሳካት እንዲዲያግዟቸው ማድረጋቸውንም አምነዋል ብሏል- የአሶሼትድ ፕሬስ ዘገባ፡፡ የድርጊቱ ተባባሪ ከሆኑት ኢትዮጵያውያን መካከል በመንግስት ትምህርት ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ግለሰብ እንደሚገኙበት ለሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት የተናገሩት ቢቬንስ ፣ ግለሰቡ በአሜሪካ ለሚገኙ የጉዲፈቻ አሳዳጊዎች የህጻናቱን የጤናና ማህበራዊ ሁኔታ የሚገልጽ መረጃ በመስጠት ላደረጉት አስተዋጽኦ ከተቋሙ ገንዘብ እንደተከፈላቸውና ውድ ስጦታዎች እንደተበረከቱላቸው ተናግረዋል፡፡
የክልል የሴቶችና ህጻናት ጉዳይ ቢሮ ሃላፊ እንደሆኑ የተነገረላቸው ሌላው የድርጊቱ ተባባሪም፣ ስልጣናቸውን በመጠቀም ተቋሙ በአገራት መካከል የሚያከናውናቸው የጉዲፈቻ ስራ ማመልከቻዎች በኢትዮጵያ ተቀባይነት እንዲያገኙና ህገወጥ ተልዕኮውን እንዲያሳካ በማገዛቸው፣ ሙሉ ወጪያቸው ተሸፍኖላቸው የውጪ አገራት ጉዞ ከማድረጋቸውም በላይ ጠቀም ያለ ገንዘብ እንደተሰጣቸውም ሃላፊው ቃላቸውን ሰጥተዋል፡፡
የቢቬንስን ጉዳይ ሲመለከት የቆየው የሳውዝ ካሮሊና ፍርድ ቤት፣ከጥቂት ቀናት በኋላ በተከሳሹ ላይ ተገቢውን ቅጣት ይጥልባቸዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
የመካከለኛው ምስራቅ ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ከ21 ቢ. ብር በላይ ያንቀሳቅሳሉ
የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ኩባንዎች በኢትዮጵያ ከ21 ቢሊዮን ብር በላይ የሚያንቀሳቅሱ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንዳላቸው ወርልድ ቡሊቲን ዘገበ፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኤጀንሲ ያወጣውን መረጃ በመጥቀስ ዘገባው እንዳለው፣ ኩባንያዎቹ በአገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች 179 ያህል የምርት፣ የግብርና፣ የሪል እስቴትና የማሽነሪ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እያንቀሳቀሱ ይገኛሉ፡፡ 80 የሚደርሱ ፕሮጀክቶች የአገሪቱ መንግስት ትኩረት በሰጠው የማኑፋክቸሪንግ ዘርፍ ውስጥ እንደሚገኙ ሲታወቅ 35 ያህሉ ደግሞ ለዘርፉ ግብዓት በሚያመነጨው የግብርናው ዘርፍ እንደተካተቱ ዘገባው አመልክቷል፡፡
በኢትዮጵያ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ከተሰማሩት የመካከለኛው ምስራቅ አገራት ቀዳሚውን ስፍራ የምትይዘው ሳኡዲ አረቢያ ስትሆን አገሪቱ በኢትዮጵያ 86 ፕሮጀክቶችን እያከናወነች እንደምትገኝ ዘገባው ጠቁሞ፤ ከመካከለኛው ምስራቅ አገራት በተጨማሪ ሱዳን፣ ግብጽ፣ ደቡብ አፍሪካና ናይጀሪያን የመሳሰሉ የአፍሪካ አገራትም በተለያዩ ኢንቨስትመንቶች ላይ ተሰማርተው እንደሚገኙ አመልክቷል፡፡
የጸጉር ጤና እንክብካቤና ፋሽን በአፍሪካ የቢሊዮኖች ዶላር ቢዝነስ ሆኗል
በደ/አፍሪካ ብቻ አምና ከ20 ቢ. ብር በላይ የሚያወጡ መዋቢያዎች ተሸጠዋል የአህጉሪቱ “የተፈጥሮ ጸጉር” አመታዊ ሽያጭ ከ120 ቢ. ብር በላይ ደርሷል
የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በአፍሪካ ብዙ ቢሊዮን ዶላሮችን የሚያንቀሳቅስ ትልቅ ንግድ እየሆነ መምጣቱን ሮይተርስ ከትናንት በስቲያ ዘግቧል፡፡ በአህጉሪቷ እየተስፋፋ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ የህንድና የቻይናን ኩባንያዎች ከማሳተፍ ባለፈ በአለማቀፍ ደረጃ ታዋቂ የሆኑትን “ሎሬል” እና “ዩኒሊቨር” የመሳሰሉ የፋሽንና የውበት ኩባንያዎች ወደ አህጉሪቷ እንዲገቡ ማድረጉን ነው ዘገባው የገለጸው፡፡ የአፍሪካ ሴቶች የጸጉራቸውን ጤንነት የመጠበቅና የዘመኑን አለማቀፍ የጸጉር ፋሽን የመከተል ፍላጎታቸው እያደገ መምጣቱን ተከትሎ፣ በአህጉሪቱ የተለያዩ አገሮች በመስኩ የሚሰሩ አገር በቀል ድርጅቶች እየተበራከቱ የመጡ ሲሆን እነ “ኦግሎብ”ን የመሳሰሉ ታዋቂ አለማቀፍ ኩባንያዎችም በአህጉሪቱ በስፋት መንቀሳቀስ ጀምረዋል፡፡
ዩሮ ሞኒተር ኢንተርናሽናል የተባለ አለማቀፍ የገበያ ጥናት ተቋም ያወጣው የጥናት መረጃ እንደሚለው፤ ባለፈው የፈረንጆች አመት በደቡብ አፍሪካ ብቻ 1 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጡ የጸጉር ውበት መጠበቂያና መዋቢያ ሻምፖዎች፣ ሎሽኖችና ማለስለሻዎች ለገበያ ቀርበው ጥቅም ላይ ውለዋል፡፡በናይጀሪያና በካሜሩን የፈሳሽ የጸጉር ቅባቶችና ውበት መጠበቂያዎች ገበያ ከአመት ወደ አመት እያደገ መምጣቱን የጠቆመው ዘገባው፤ በመላ አህጉሪቱ ያለው አመታዊ የተፈጥሮ ጸጉር ሽያጭም 6 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውቋል፡፡
ታዋቂዋ ናይጀሪያዊት ድምጻዊት ሙማ ጊ በቅርቡ ከ56 ሺህ ብር በላይ ወጪ በማድረግ አንድ የተፈጥሮ ጸጉር ከነመዋቢያው እንደገዛች ብዙሃን በይፋ መናገሯን በዋቢነት የጠቀሰው ዘገባው፤ በደቡብ አፍሪካ ብቻ ከ100 በላይ የተለያዩ አይነት የንግድ ምልክቶች ያሏቸው የተፈጥሮ ጸጉር አይነቶች በገበያ ላይ እንደሚገኙና አመታዊ ሽያጩም 600 ሚሊዮን ዶላር መድረሱን አስታውሷል፡፡ በመላ አፍሪካ እያደገ የመጣው የጸጉር ጤንነት እንክብካቤና የፋሽን ስራ በተለያዩ አገራት ለሚገኙ ቁጥራቸው በርካታ የሆነ ሴቶች ከፍተኛ የስራ ዕድል መፍጠሩንና በኢኮኖሚው ውስጥ የራሱን ድርሻ እያበረከተ እንደሚገኝ የጠቆመው ዘገባው፣ በናይጀሪያና በአንዳንድ አገራት የቤት ለቤት አገልግሎት መስጠት የሚያስችል አሰራር መጀመሩን ገልጧል፡፡