Administrator

Administrator


             የስነተዋልዶ ጤና ፖሊሲዋን ለማሻሻል ልዩ ትኩረት እንደሰጠች የሚነገርላት ስፔን፣ ሴቶች የወር አበባ በሚመጣበት ወቅት ከሚከሰትባቸው ህመም እንዲያገግሙ ለማገዝ በየወሩ የሶስት ቀናት የስራ እረፍት ፈቃድ ለመስጠት የሚያስችል ህግ ማርቀቋን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ረቂቅ ህጉ በመጪው ሳምንት ለአገሪቱ ፓርላማ ለውሳኔ እንደሚቀርብ የጠቆመው ዘገባው፤ ህጉ ጸድቆ ተግባራዊ የሚሆን ከሆነ ስፔን የወር አበባ እረፍት በመስጠት በምዕራቡ አለም የመጀመሪያዋ አገር እንደምትሆን ቢነገርም አንዳንዶች ግን ሴቶችን ከስራ ገበታ የሚያገልል ነው ሲሉ ህጉን እንደተቃወሙት ገልጧል፡፡
ህጉ የሚጸድቅ ከሆነ የወር አበባ ሲመጣባቸው ከፍተኛ ህመም የሚሰማቸው ሴቶች በየወሩ የ3 ቀናት የስራ እረፍት እንደሚሰጣቸው የጠቆመው ዘገባው፤ በመጪው ማክሰኞ ለአገሪቱ ፓርላማ የሚቀርበው ረቂቅ ህጉ ከወር አበባ እረፍት በተጨማሪ ለተማሪዎችና ለችግረኛ ሴቶች የንጽህና መጠበቂያዎችን በነጻ መስጠትና የሞዴስ ቀረጥ ማንሳትን ጨምሮ ሌሎች አዳዲስ ህጎችን ማካተቱንም አክሎ ገልጧል፡፡
ለሴቶች ተመሳሳይ የወር አበባ እረፍት በመስጠት ላይ የሚገኙ የአለማችን አገራት ጃፓን፣ ደቡብ ኮርያ፣ ኢንዶኔዢያና ዛምቢያ ብቻ መሆናቸውንም አስታውሷል፡፡

   • የአሜሪካው ቤክሻየር ሃታዌ 1ኛ ደረጃን ይዟል
          • ኩባንያዎቹ በ12 ወራት 5 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ አግኝተዋል

              የኩባንያዎችን ሽያጭ፣ ትርፍ፣ ሃብትና የገበያ ዋጋ በማስላት በየአመቱ ደረጃ የሚሰጠው ታዋቂው ፎርብስ መጽሄት ከሰሞኑም የ2022 የፈረንጆች አመት የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎችን ዝርዝር ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአሜሪካው ቤክሻየር ሃታዌ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ኢንሹራንስ፣ ትራንስፖርት፣ ማኑፋክቸሪንግና ኢነርጂን በመሳሰሉ ሰፋፊ የንግድ ዘርፎች የተሰማራውና በአሜሪካዊው ቢሊየነር ዋረን በፌት የሚመራው ቤክሻየር ሃታዌ በ12 ወራት ጊዜ ውስጥ 276.09 ቢሊዮን ዶላር ሽያጭ በማስመዝገብ፣ 89.08 ቢሊዮን ዶላር ትርፍ ያገኘ ሲሆን፤ የኩባንያው ሃብት 958.78 ቢሊዮን ዶላር፣ የገበያ ዋጋው ደግሞ 741.48 ቢሊዮን ዶላር መድረሱን የፎርብስ መረጃ ያሳያል፡፡
ላለፉት 9 ተከታታይ አመታት የአለማችን ቁጥር አንድ ግዙፍ ኩባንያ ሆኖ የዘለቀው የቻይና የኢንዱስትሪና ንግድ ባንክ ዘንድሮ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ዝቅ ያለ ሲሆን፣ የሳዑዲ አረቢያው የነዳጅ ኩባንያ አርማኮ 3ኛ፣ የአሜሪካው ጄፒ ሞርጋን 4ኛ፣ የቻይና ኮንስትራክሽን ባንክ ደግሞ 5ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
በዘንድሮው የፎርብስ የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች ዝርዝር ውስጥ የአሜሪካው አማዞን 6ኛ፣ የአሜሪካው አፕል 7ኛ፣ የቻይና የግብርና ባንክ 8ኛ፣ ባንክ ኦፍ አሜሪካ 9ኛ፣ የጃፓኑ ቶዮታ ሞተርስ 10ኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡
ፎርብስ መጽሄት የአመቱ የአለማችን 2000 ግዙፍ ኩባንያዎች ብሎ የመረጣቸው ኩባንያዎች በድምሩ 47.6 ትሪሊዮን ዶላር ገቢ፣ 5 ትሪሊዮን ዶላር ትርፍ፣ 233.7 ትሪሊዮን ዶላር ሃብትና 7.5 ትሪሊዮን ዶላር የገበያ ዋጋ ማስመዝገባቸውን ለማወቅ ተችሏል፡፡
የአመቱ 2000 የአለማችን ግዙፍ ኩባንያዎች የ58 የተለያዩ የአለማችን አገራት ኩባንያዎች ሲሆኑ፣ አሜሪካ 590 ኩባንያዎችን በዝርዝሩ ውስጥ በማካተት ቀዳሚነቱን ስትይዝ፣ ቻይና በ351፣ ጃፓን በ196 ኩባንያዎች ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃን ይዘዋል፡፡

    ከ50 አመታት በፊት ነው…
ነዋሪነቱ በለንደን የሆነው ጆን ኬነር የተባለው ታዋቂ ካናዳዊ ሰዓሊ፣  አንድ ማለዳ የሆነ ሃሳብ ብልጭ አለለት፡፡ ጊዜም ሳያባክን ከቤቱ ወጥቶ ወደ አንድ ሬስቶራንት ጉዞ ጀመረ፡፡ሬስቶራንቱ ውስጥ እንደገባ፣ የድርጅቱን ባለቤት አይሪን ዴማስን አስጠራት፡፡ ራሱን አስተዋውቋት፣ ምግብ መግዣ ገንዘብ ስለሌለው የራሱን ወይም ወዳጆቹ የሆኑ የሌሎች ሰዓሊያንን የስዕል ስራዎች እየሰጣት በምላሹ ምግብ እንድትሰጠው ጠየቃት፤ ተስማማች፡፡
አንድ ምሽት…
ሰዓሊው ጆን ኬነር ጥሩ ሳንዱች መብላት አማረው፡፡ የቅርብ ወዳጁ የነበረችውና እንደ እሱው በድህነት ስትቆራመድ የኖረች ማውድ ሊዊስ የተባለች ሰዓሊ የሳለችውን “ጥቁር የጭነት መኪና” የሚል ርዕስ ያለው ስዕል ብድግ አደረገ፡፡ስዕሉን እያየ በድህነት ተቆራምዳ የሞተችውን ሰዓሊዋን ማውድ ሊውስን አሰባት፡፡ ኑሮ ዳገት ሆኖ ሲፈትናት የኖረችውንና አንዲት ክፍል ቤት ውስጥ በህመም ስትሰቃይ የባጀችውን ያቺን ምስኪን ሰዓሊ ሊውስን አስታወሳት፡፡
ቸግሯት ነበር፡፡ ድንቅ ሰዓሊነቷን የሚመሰክሩላት የመብዛታቸውን ያህል፣ ከአቅሟ በላይ የሆነውን የኑሮ ውድነት የሚያግዛትም ሆነ የዕለት እንጀራዋን  ለማግኘት ሲቸግራትና ስትራብ ስትጠማ እስኪ ይህቺን ቅመሽ የሚላት አላገኘችም ነበር፡፡ በችጋር ከመሞት ይልቅ የሚያማምሩ ስዕሎቿን እስከ 2 ዶላር በሚደርስ ገንዘብ እየሸጠች ርሃቧን ለማስታገስ ደፋ ቀና ስትል አሳዝናው ነበር፣ በደጉ ጊዜ እሷን ለመርዳት ሲል ገንዘብ አውጥቶ ይህን ስዕል የገዛት፡፡
ኬነር ሰዓሊዋን እያሰበ ትንሽ ተካከዘ፡፡ ሲተካክዝ ቆየናም፣ ስዕሉን ይዞ  ከቤቱ በመውጣት ወደ ሬስቶራንቱ አቀና፡፡
ለሬስቶራንቱ ባለቤት ቀደም ብለው በተስማሙት መሰረት ስዕሉን ሰጣት፤ እሷም ጣፋጭ የሆነ የአይብ ሳንዱች አቀረበችለት፡፡ ጆን ኬነር ከአመታት በፊት ከምስኪኗ ሰዓሊ ሊዊስ የገዛውን ታሪካዊ ስዕል ከፍሎ፣ የቀረበለትን ሳንዱች ማጣጣሙን ቀጠለ፡፡
ይህ ከሆነ ከ50 አመታት በኋላ…
ሰዓሊው ኬነር እ.ኤ.አ በ1973 በዚያች ምሽት ላጣጣማት ሳንዱች በክፍያ መልክ ለሬስቶራንቱ ባለቤት ያበረከታት ያቺ ታሪካዊ ስዕል፣ ከሰሞኑ ኦንታሪዮ ውስጥ ለጨረታ ቀርባ በ350 ሺህ ዶላር ተሸጠች፡፡ሚለር ኤንድ ሚለር በተባለው የካናዳ አጫራች ኩባንያ አማካይነት ለሽያጭ የበቃችው ስዕሏ 35 ሺህ ዶላር ያህል ታወጣለች ተብሎ ቢገመትም፣ በአስር እጥፍ ያህል በሚበልጥ ዋጋ ተሽጣ እነሆ ሰሞንኛ አለማቀፍ የስነጥበብ ወሬ ለመሆን መብቃቷን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል፡፡

 ኡጉር የተባለችዋ የቻይና ግዛት በርካታ ቁጥር ያላቸው ዜጎችን እያፈሰች በገፍ ወደ እስር ቤት በማጋዝ በመላው አለም አቻ እንደማይገኝላት በመረጃ መረጋገጡንና ከግዛቷ 25 ነዋሪዎች አንዱ በሽብርተኝነት ተከስሶ በእስር ቤት እንደሚገኝ ዘ ጋርዲያን ከሰሞኑ ባወጣው ዘገባ አስነብቧል፡፡
አሶሼትድ ፕሬስ አገኘሁት ያለውን መረጃ መሰረት አድርጎ በዘገባው እንዳለው፣ ኡጉር በተባለችውና ሙስሊሞች በሚበዙባት የቻይና ግዛት ህጻናትና አረጋውያንን ጨምሮ ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በሽብር ተከስሰው በእስር ላይ እንደሚገኙና ከ2 እስከ 25 አመት በሚደርስ እስር እንደተቀጡ ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡መረጃው የቻይና መንግስት በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ሰዎችን በተለያዩ ሰበቦች በእስር ቤት አጉሮ ይገኛል የሚለውን ውንጀላ የሚያጠናክር ነው መባሉን የጠቆመው ዘገባው፤ መንግስት በተለይ አናሳ ሙስሊሞች በሚበዙባት ኡጉሩ እየፈጸመው የሚገኘውን የጅምላ እስርም የሚያረጋግጥ ነው ብሏል፡፡

Saturday, 21 May 2022 12:51

የተጠላው እንዳልተጠላ

 ምዕራፍ ስምንት

          ጥርሱ ያለቀው አዛውንት
ፊቱን መምህሩ ፊት ላይ ደቅኖ እንዲህ አለ፡-
#ወንጀለኛውና ትንሹ ሰይጣን፤
ባንዲራችን ከንቱ፤
ሀገራችን ባዶ፤
ዜግነታችን ቆሻሻ፤
ድንበራችን ገሃነም፤
ሉአላዊነታችን ስድብ እንደሆነ አልክ፡፡
እንደምን ድንቅ ተናግረሃል፤
ግንኮ ኢትዮጵያ ለኛ ደግ እንደሆነች ሁሉ
ላንተም ቸር ነበረች፡፡
ስለምን ከዳሀት?;
መምህሩ ሲደበደብ የላላ ደበሎውን አጠባብቆ በትንሽ ፋታ ህመሙን ካስታገሰ
በኋላ እንዲህ አለ---
#ሐገራችሁ ደግ ነበረች፤
ቸርም ነበረች፡፡ ለናንተ ግን አይደለችም፡፡
በስንፍናችሁ ያስጨከናችኋትም እናንተ ናችሁ፡፡ኢትዮጵያ ወድቃ፣ በስብሳና አጎንቁላ የምታፈራ ፍሬ ሳትሆን በጎተራ የምትሞሸር
የደደረች ዘር ሆናለች፡፡
ኢትዮጵያውያን፤
ሬሳ እንዳይፈርስ አዘውትረው የሚታትሩትን የጥንት ግብጻውያንን ይመስላሉ፡፡
እናንት ከእመቤት ኢትዮጵያ አስክሬን ጋር ከነህይወታችሁ የተቀበራችሁ ባሮች፤
የሞተን እንቅልፍ ለማስወገድ ያዘጋጃችሁትን ዝማሬ አታውርዱ፤
እናንተ የሙት ሞግዚቶች
ኢትዮጵያ የሚለው መወድሳችሁ ያብቃ!
ኢትዮጵያ በረዥም ዕረፍት ውስጥ ያለ ጣዕር ሞታለች፡፡ መወድሳችሁን
አቁማችሁ ለፍታት መቋሚያችሁን አንሱ!
መቃብር ቆፋሪውን ቀስቅሱና እያፏጨ ይቅበራት፡፡
የታማሚ ሞት የአስታማሚ ነጻነት እንደሆነ አታውቁምን?
እናንተ አስክሬን አስታማሚዎች፤ እናንተን በመጠበቅ የቀብር መልስ ንፍሯችሁ
ነፍስ ዘራ፤
ጉዝጓዛችሁን መሬት ዋጠው--;
#ኡ! ኡ! ኡ!;
#ሁሉን ዘረፈን!;
#አድባር መስሎ የለም እንዴ?;  አለ አንድ ሰላላ ድምጽ
#መቼም ከድንጋይ ሳይሻል አይቀርምና
አንገቱን ቆርጣችሁ ጭንቅላቱን ትከሉልን
ቅቤ እንቀባው--;
#ኢትዮጵያውያን; ሲል በአካባቢው ያለ ድምጽ እረጭ አለ
#ሀገር ይዘው ህዝብ ይፈልጋሉ፡፡ እንደ እስራኤሎች ህዝብ ይዘው ሀገር በፈለጉ እንዴት ደግ ነበር፤እንደ አሜሪካኖች መስፈሪያ ያጣች የሰፋሪዎች ጀልባ ብንሆን እንዴት መልካም ነበር;
(ከደራሲ አለማየሁ ገላጋይ #የተጠላው እንዳልተጠላ; አዲስ መጽሐፍ የተቀነጨበ)

   • የህወኃት ሃይሎች የአማራ ክልልን ወረው በቆዩባቸው ጊዜያት 6985 ዜጎችን መግደላቸውን ጥናቱ አመልክቷል
        • 1797 ሰዎች በጅምላ የተገደሉ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 579 የሚሆኑት በድብደባ ብዛት የሞቱ ናቸው ተብሏል
        • 1782 ሰዎች ላይ የአስገድዶ መደፈር ወንጀል ሲፈጸምባቸው፤ ሃያሁለቱ ወንዶች ናቸው ተብሏል
              

            በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙ አስር የፌደራል ዩኒቨርስቲዎች የተውጣጣ ከአራት ሺ በላይ ባለሙያዎችና ከብሔራዊ ስታቲስቲክ ኤጀንሲ የተውጣጡ 300 የሚደርሱ ሙያተኞች የተሳተፉባቸውና አምስት ወራትን የፈጀው ጥናት ሰሞኑን ይፋ ተደርጓል፡፡ ጥናቱ የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች በክልሉ ውስጥ የሚገኙ አካባቢዎችን ተቆጣጥረው በቆዩበት ወቅት ያደረሱትን ጥፋት የሚመለከት ነው፡፡
ሰሜን ወሎ፣ደቡብ ወሎ፣ሰሜን ጎንደር፣ደቡብ ጎንደር፣ዋግ ኽምራ ኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደርና ሰሜን ሸዋ የህወኃት ወታደሮች ካለፈው ዓመት ሰኔ ወር ጀምሮ ተቆጣጥረዋቸው የነበሩ ሰባት የአማራ ክልል ዞኖች ናቸው፡፡
ከህወኃት ተዋጊዎች ነፃ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ላለፉት 5 ወራት መከናወኑ በተገለጸው ለዚሁ የአስር ዩኒቨርስቲዎች ጥምር ጥናት ውጤት ላይ እንደተገለጸው፤ በጦርነቱ ውስጥ ምንም  አይነት ተሳትፎ ያልነበራቸው 6985 ንፁሃን ዜጎች በህወኃት ሃይሎች ተገድለዋል፡፡ 7460 ወገኖች ደግሞ በሃይል ታፍነው በመወሰዳቸው አድራሻቸው እስከ አሁንም አለመታወቁ ጥናቱ ተመልክቷል፡፡
የህወኃት ታጣቂ ሃይሎች የአካባቢውን ነዋሪዎች በጅምላ መጨፍጨፋቸውን የጠቆመው የዩኒቨርስቲዎቹ ጥናት፣ በተለይ በጭና ቀወት፣መንዝ ጌራ፣ አንፆኪያ ገምዛ፣ አጋምሳ ኮምቦልቻና መርሳ ከተሞች ከ1797 በላይ ወገኖች በጅምላ ተጨፍጭፈዋል ብሏል፡፡ በጅምላ ከተጨፈጨፉት ወገኖች መካከል 579 የሚሆኑት በተፈፀመባቸው ድብደባ ሳቢያ የሞቱ መሆኑንም ይኸው ጥናት አመልክቷል፡፡
በአማራ ክልል ውስጥ የሚገኙት 10 የፌደራል ዩኒቨርስቲዎች ሰሞኑን ይፋ ያደረጉት የጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው ከ10 ሚሊዮን በላይ የክልሉ ህዝቦች ሰብአዊ ጉዳት ደርሶባቸዋል፡፡የህወኃት ሃይሎች አካባቢውን ተቆጣረው በቆዩባቸው ጊዜያት ከፈፀሟቸው አስከፊ ሰብአዊ ጉዳቶች መካከል አስገድዶ መድፈር ዋነኛው መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፤ የህወኃት ሃይሎች ተቆጣጥረው በቆዩባቸው ሰባቱ የክልሉ ዞኖች ውስጥ በሚኖሩና በተለያዩ የዕድሜ ክልል ውስጥ በሚገኙ 1782 ዜጎች ላይ የአስገድዶ መድፈር ወንጀል መፈፀማቸውን ጠቁሟል፡፡ ጥቃቱ የተፈፀመው በቡድንና በግል ሲሆን በትዳር አጋርና በቤተሰብ ፊት፣ በመነኩሴዎችና በሃይማኖት አባቶች ሚስቶች ላይ የተፈፀመ መሆኑንም  ጥናቱ አመልክቷል፡፡ የአስገድዶ መድፈር ጥቃት ከተፈፀመባቸው ወገኖች መካከል ሃያ ሁለቱ ወንዶች መሆናቸው በጥናቱ ተገልጿል፡፡ ይህ ቁጥር መገለልና መድሎን በመፍራት መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑትን የጥቃቱን ሰለባዎች አያካትትም ተብሏል፡፡
 ጥናቱ ከፌደራልም ሆነ ከክልል መንግስታት ተሳትፎና ፖለቲካዊ ጫና ነፃ ሆኖ መካሄዱ የተገለጸ ሲሆን የህወኃት ሃይሎች በሃይል ተቆጣጥረዋቸው በነበሩት አካባቢዎች ላይ ያደረሱትን የንብረት ውድመትም ያካተተ ነው ተብሏል።
በዚህም መሰረት 1145 የትምህርት ተቋማትና 2 ሺ የሚጠጉ የጤና ተቋማት ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው የተረጋገጠ ሲሆን በአጠቃላይ በክልሉ የደረሰው ውድመት በገንዘብ ሲተመን ከ288 ቢሊዮን ብር በላይ እንደሆነም ተመልክቷል፡፡ በጥናቱ እንደተጠቆመው ከዚህ ውስጥ ከ50 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመተው የግለሰቦች ሃብት እንደሆነም ጥናቱ አመልክቷል።

በኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥር የሚተዳደረው ሩቢ ቪዛ ኮንሰልቲንግ ሦስት ታዋቂ አርቲስቶችን የብራንድ አምባሳደሮቹ አድርጎ ሰየመ፡፡
በብራንድ አምባሳደርነት የተሰየሙት አርቲስት ዳንኤል ተገኝ፣ አርቲስት ሩታ መንግስተአብና አርቲስት ሊዲያና ሰለሞን ሲሆኑ ከአምባሳደሮቹ ጋርም የፊርማ ሥነስርዓት ተከናውኗል፡፡
በኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ሥር ከሚገኙ ተቋማት አንዱ የሆነው ሩቢ ቪዛ ኮንሰልቲንግ፤ በዓለማቀፍ ደረጃ ወደ ባህር ማዶ በሥራ፣ በጉብኝት፣ በቢዝነስና በኢንቨስትመንት ቪዛ ለመሄድ ለሚፈልጉ ኢትዮጵያውያን የቪዛ ማማከር አገልግሎት የሚሰጥ ነው፡፡ ሦስቱ አርቲስቶች በብራንድ አምባሳደርነት የተሰየሙት ይህን ኩባንያና አገልግሎቱን ለማስተዋወቅና ለመወከል ነው ተብሏል፡፡
ከትናንት በስቲያ ሐሙስ፣ በሸራተን አዲስ፣ ሩቢ ቪዛ ኮንሰልቲንግን ለማስተዋወቅና የብራንድ አምባሳደሮችን ይፋ ለማድረግ በተዘጋጀው ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ የኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት ዋና ሥራ አስኪያጅ አቶ ታረቀኝ ቶሎሳ ባደረጉት ንግግር፤ #እ.ኤ.አ በ2007 የተቋቋመው ኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፣ በሥሩ በርካታ ድርጅቶችን ያቀፈ፣ ለህብረተሰብ ችግር ፈቺ የሆኑ የተለያዩ ድርጅቶችን በማቋቋም ለበርካታ ሰዎች የሥራ ዕድልን የፈጠረና በሃገር ኢኮኖሚ ግንባታ የራሱን አስተዋፅኦ እያበረከተ የሚገኝ ትልቅ ተቋም ነው”  ብለዋል፡፡ ድርጅቱ አገሪቱ ለያዘችው የልማትና ብልፅግና ጉዞ በኢኮኖሚው፣ በቱሪዝሙ፣ የውጭ ምንዛሬን በማስገኘትና በኢንቨስትመንቱ ዘርፍ በርካታ ሥራዎችን በመሥራት ላይ እንደሚገኝም ዋና ሥራ አስኪጁ ገልፀዋል፡፡
በመርሃ ግብሩ ማጠቃለያ ላይ የብራንድ አምባሳደሮች ሆነው የተሰየሙት አርቲስቶች፣ ከሩቢ ቪዛ ኮንሰልቲንግ ጋር ለመስራት ዕድሉን በማግኘታቸው የተሰማቸውን ደስታ ገልጸዋል፤ ምስጋናም አቅርበዋል፡፡
በቱሪዝም በውጭ ንግድና ኢንቨስትመንት ላይ አተኩሮ የሚሰራው ኢትዮ ኤርስ ንግድ እና ኢንቨስትመንት፤ ከሩቢ ቪዛ ኮንሰልቲንግ በተጨማሪ ትራቭል ሃይ ቱር፣ ሉክስ ትራቭል የመሳሰሉ ድርጅቶችን በስሩ እንደሚመራ ለማወቅ ተችሏል፡፡ኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ በሦስት ከተሞች ለጎዳና ተዳዳሪነት የተዳረጉ ህፃናትና ታዳጊዎችን ይታደጋል የተባለለትን  የ5 ዓመት ፕሮጀክት ይፋ አድርጓል፡፡ ፕሮጀክቱ ይፋ የሆነው ግንቦት 2 ቀን 2014 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስካይ ላይት ሆቴል ሲሆን ፤ለፕሮጀክቱም 273 ሚ. ብር (4 ሚ 376 ሺህ 073 ዩሮ) መመደቡን የኤስኦኤስ ኢንተርናሽል ዳይሬክተር ወ/ሮ ሰናይት ገብረእግዚአብሔር ለጋዜጠኞች ተናግረዋል፡፡ በዚህ ፕሮጀክት ለአራት የአፍሪካ ሀገራት ማለትም-ለኢትዮጵያ፣ለኬኒያ ለሩዋንዳና ለኡጋንዳ 30 ሚ ዩሮ በጀት መለቀቁን የጠቆሙት ኢንተርናሽናል ዳይሬክተሯ በመጀመሪያ ለኢትዮጵያ ለኡጋንዳ 15 ሚ ዩሮ  መለቀቁን ተናግረዋል፡፡ድርጅቱ የዛሬ 48  ዓመት የሰሜኑን የሀገራችንን ድርቅ ተከትሎ፣ ለችግር ተጋላጭ ወገኖች የአስቸኳይ ጊዜ እርዳታ በመስጠት ስራውን የጀመረውንና በኋላም ፊቱን ወደ ቤተሰብና ማህበረሰብ  ልማት ማዞሩን ያመለከቱት የኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በኢትዮጵያ ናሽናል ዳይሬክተር አቶ ሳህለማሪያም አበበ፤ የገለፁ ሲሆን እስካሁንም ከ30 ሺህ በላይ ህጻናትና ወጣቶች በኤስ ኦኤስ ታቅፈው ሁለንተናዊ ድጋፍና እንክብካቤ እየተደረገላቸው ተናግረዋል፡፡
በቀጣይ በርካታ የጎዳና ልጆች ለሚገኙባቸው ሁለት ሀገራት የሚውል በጀት እንደሚለቀቅና በኢትዮጵያም የ5 ዓመቱ ፕሮጀክቱ ስኬት ካስመዘገበ ተጨማሪ በጀት ሲለቀቅ እንደሚችል የተገለጸ ሲሆን በዚህ ፕሮጀክት በአዲስ አበባ፣ በድሬደዋና በአዳማ በጎዳና ላይ ህይወታቸውን  ያደረጉ ዘጠን ሺህ ህጻናትና ታዳጊዎች ከገቡበት ሱስ፣ ከደረሰባቸው የስነ- ልቦናም ሆነ የጤና ጉዳት ተላቅቀው ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚላቀሉበት ሁኔታ የፕሮጀክቱ ዋናኛ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም የድርጅቱ ናሽናል ዳይሬክተር አቶ ሳህለማርያም አበበ ጨምረው ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ በሰባት ክልሎችና በሁለት ከተማ አስተዳደሮች የሚንቀሳቀሰው ኤስኦኤስ የህጻናት መንደሮች በተጠቀሱት ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች ያሉት ቢሮዎች ችግሩን ከምንጩ ለማድረቅ ለማህበረሰቡ ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ በርካታ የቤተሰብና የማህበረሰብ ጥበቃና እንክብካቤዎችን እንደሚሰራ  ዳይሬክተሩ ገልፀዋል፡፡
እንደ አቶ ሳህለ ማርያም ገለፃ፤ በዚህ ፕሮጀክት በጣም ትኩረትና ቅድሚያ የተሰጣቸው ህጻናትና ታዳጊዎች በጤና፣ በስነ- ልቦናና በአጠቃላይ ሁኔታቸው ከፍተኛ ጉዳትና ችግር ውስጥ የገቡት ናቸው፡፡በፕሮጀክቱ ተካተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ሲደረግ ልጆቹ ወደ ጎዳና የወጡባቸው ምክንያቶች አብረው መጠናታቸውን የጠቆሙት አቶ ሳህለማርያም፤ አብዛኛዎቹ ልጆች ወደ ጎዳና ለመውጣት ምክንያት የሆናቸው በቤታቸው ውስጥ ምቹ ሁኔታ አለመኖር ነውም ብለዋል፡፡
በዚህ የፕሮጀክት ይፋ ማድረጊያ መርሃ  ግበር ላይ የተገኙት የሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር ሚኒስትር፣ኤርጎጌ ተስፋዬ (ዶ/ር) ኤስኦኤስ የህጻናት መንደር፣  በኢትዮጵያ በተለይ በህጻናት ጥበቃና እንክብካቤ ላይ የሚሰራውን ስራ አድንቀው፣ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸውም ቀደም ባለው ጊዜ በ11 ክልሎች 22 ሺህ የጎዳና ተዳደሪዎችን ማንሳት እንደተቻለ ገልጸው፤ በሌሎች ከተሞችም ቀጣይ ስራዎችን ለመስራት ዝግጅት መጠናቀቁን አብራርተዋል፡፡
የህጻናትና ታዳጊዎች ወደ ጎዳና መውጣት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ መምጣቱን የገለፁት ሚኒስትሯ ችግሩን ከምንጩ ለመቅረፍ በሚያስችል ሁኔታም ላይ እየተሰራ ስለመሆኑ ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድ በዕለቱ በኤስ ኦኤስ የህጻናት መንደር ይፋ የሆነው የአምስት ዓመት ፕሮጀክት ትልቅ ሚና እንደሚጫወትና በትግበራውም ላይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤታቸው ለግብረ ሰናይ ድርጅቱ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ቃል ገብተዋል። ኤስ ኦኤስ የህጻናት መንደር ከተመሰረተ በዓለም  አቀፍ ደረጃ 70 ዓመት ያስቆጠረ ሲሆን በኢትዮጵያ 48 ዓመት እንደሞላውና በመላው ዓለም በ137 አገሮች እንደሚሰራም ታውቋል። የመንግስት ሪፖርት በአገር አቀፍ ደረጃ 150 ሺህ ህጻናት በጎዳና ላይ እንደሚኖሩ ከነዚህም ውስጥ 60 ሺህ ያህሉ አዲስ አበባ እንደሚገኙ ቢያመለክትም ዩኒሴፍ ግን በኢትዮጵያ ከ600 ሺህ በላይ ህጻናትና ታዳጊዎች በጎዳና ላይ ይኖራሉ ተብሎ እንደሚገመትና ከ100 ሺህ በላይ ያሉት በአዲስ አበባ እንደሚገኙ ይፋ ማድረጉም በእለቱ ተገልጿል፡፡

በአሜሪካ ቴክሳስ ግዛት ውስጥ ነው።የሁለት ዓመቱ ህፃን ባሬት ጎልደን ሁልጊዜ በእናቱ የሞባይል ስልክ መጫወት ይወዳል። እናቱ እንደምትለው፤ በሞባይል ስልኩ ራሱን ፎቶግራፍ እያነሳ ይዝናናል፡፡ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ  ግን ራሱን ፎቶ በማንሳት ብቻ አልተወሰነም፡፡ እናቱን ላልታሰበ የገንዘብ ኪሳራ ዳርጓል፤ያውም የኑሮ ውድነት ጣራ በነካበት በዚህ ወቅት፡፡ ባሬት ጎልደን ድንገት በተጫነው ቁልፍ 91 ዶላር (4550 ብር ገደማ) ክፍያ ፈፅሞ 31 ቺዝ በርገሮች ያዘዘ ሲሆን 16 ዶላር (900 ብር ገደማ) ቲፕም (ጉርሻ) መስጠቱን ስካይ ኒውስ ዘግቧል፡፡
 እናት እንደተናገረችው፣ የሞባይል ስልኳን የቆለፈችው (ሎክ ያደረገችው) ነበር የመሰላት፡፡ ነገር ግን አለመቆለፏን ያወቀችው የታዘዙት 31 ቺዝ በርገሮች ተጠቅልለው ቤቷ ድረስ ሲመጡላት ነው፡፡ የ4550 ብር ቺዝ በርገሮች!
 በደቂቃዎች ውስጥ ከ5 ሺ ብር በላይ ኪሳራ የደረሰባት የህጻኑ እናት ወዲያው ሞባይል ስልኳን እንደቆለፈች የዘገበው ስካይ ኒውስ፤ ቺዝ በርገሮቹም ለጎረቤት ተከፋፍለዋል ብሏል፡፡

 የአሜሪካውያን የድንገተኛና የአደጋ ጊዜ ማሳወቂያ የስልክ መስመር በሆነው 911 በመደወል “ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ዘብጥያ መውረድ አለበት; ያለው የፍሎሪዳ ነዋሪ፣ ራሱ ወህኒ ተወርውሮ አረፈው።
የ29 ዓመቱ ጃኮብ ፊልቤክ ባለፈው እሁድ ለእስር የተዳረገው በተደጋጋሚ 911 በመደወል “ኢል-ቻፓ ከእስር መፈታትና ፕሬዚዳንት ባይደን ወህኒ ቤት መግባት አለባቸው” ሲል መስመሩን ያለአግባቡ በመጠቀሙ ነው ተብሏል።የ911 መልዕክት ተቀባዮች የፊልቤክ አስተያየት ከድንገተኛ ጊዜ አደጋ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት እንደሌለው በመጠቆም፣ ለዚህ ጉዳይ ዳግም እንዳይደውል አስጠንቅቀውት ነበር። እሱ ግን አልሰማቸውም፡፡
ጥቂት ቆይቶ 911 ዳግም በመደወል ያንኑ ተመሳሳይ ጉዳይ ይወተውታቸው ገባ፤ “ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ወህኒ ቤት መወርወር አለባቸው” በማለት። ወዲያውኑ ፖሊስ ወደ ሰውየው ቤት በማምራት፣ ለምን 911 ላይ ድንገተኛ ላልሆነ ጉዳይ ደጋግሞ እንደደወለ ይጠይቀዋል፡፡ ፊልቤክም እንደለመደው፤ “ኢል-ቻፓ በነፃ ከእስር መለቀቅና ፕሬዚዳንት ባይደን መታሰር አለባቸው” ሲል ያለአንዳች ማመንታት መለሰ፡፡
በዚህም 911 ሽቦ አልባ የስልክ መስመርን ድንገተኛና ወንጀል ነክ ላልሆነ ጉዳይ ያለ አግባብ በመጠቀሙ በቁጥጥር ሥር ውሎ ዘብጥያ ወርዷል፡፡ ፊልቤክ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ በ911 የስልክ መስመር በግምት ለሦስት ጊዜ ያህል መደወሉን የእስር ሰነዱ ያስረዳል። ለፕሬዚዳንት ጆ ባይደን የተመኘውንም እስር ራሱ አግኝቶታል፡፡

Page 1 of 604