Administrator

Administrator

አልሸባብ ፅንፈኛ ድርጅት የሆነው ኢትዮጵያ ወደ ሶማሊያ ጦር ሰራዊት በማዝመቷ ነው በማለት ኒው አፍሪካን መጽሔት የዘገበ ሲሆን፣ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ የአልሸባብ ታጣቂዎች አፍጋኒስታን ሄደው ስልጠና የወሰዱት ገና ድሮ ነው በማለት ዘገባውን አጣጣለ፡፡
አልሸባብ በዩጋንዳ እና በኬኒያ በፈፀማቸው ጥቃቶች ሳቢያ የምስራቅ አፍሪካ አገራት ውስጥ ስጋት መፍጠሩን በመጥቀስ ነው መጽሔቱ አልሸባብን የሚመለከት ሰፊ ዘገባ ያቀረበው፡፡
ዜጐች በሄዱበት ሁሉ በፍተሻ መከራቸውን እያዩ እንደሆነ መጽሔቱ ገልፆ፤ በኬኒያ እና በዛንዚባር የቱሪዝም ገቢ ክፉኛ አሽቆልቁሏል፤ የኬኒያ መንግስት የመከላከያ በጀቱን ለመጨመር ተገዷል፡፡
አልሸባብ ወደ አክራሪነት የተለወጠው፤ በ2006 የኢትዮጵያ መከላከያ ሀይል በአሜሪካ ድጋፍ ወደ ሶማሊያ  በመዝመቱ ነው ሲልም መጽሔቱ ኢትዮጵያን ተጠያቂ አድርጓል፡፡ በመጽሔቱ የቀረበው ውንጀላ መሰረተ ቢስ ነው ሲል ያጣጣለው የኢትዮጵያ የውጪ ጉዳይ ሚኒስቴር በበኩሉ፤ ኢትዮጵያ አልሸባብን አዳከመች እንጂ ወደ አክራሪነት እንዲለወጥ አላደረገችም በማለት ሰፊ ምላሽ ሰጥቷል፡፡ እንዲህ አይነቱ ውንጀላ በተደጋጋሚ የሚሰነዘር መሆኑን ሚኒስቴሩ ጠቅሶ፤ ነገር ግን ምንም አይነት ማስረጃ የማይቀርብበት መሰረተ ቢስ ውንጀላ ነው ብሏል፡፡
በሶማሊያ እየገነነ የነበረው የእስልምና ፍርድ ቤቶች ምክር ቤት በኢትዮጵያ ጦር በመመታቱ አይደለም አልሸባብ ያቆጠቆጠው፡፡ እንዲያውም የፍርድ ቤቶች ምክር ቤት ሶማሊያ ውስጥ እየተንቀሳቀሰ በነበረበት ወቅትና ከዚያ በፊት ወደ አፍጋኒስታን ለስልጠና ተልከው በነበሩ ቡድኖች ናቸው አልሸባብን የመሰረቱት ብሏል ሚኒስቴሩ፡፡
የእስልምና ፍርድ ቤቶች ህብረት ኢትዮጵያ ላይ ጦርነት አውጆ እንደነበር ሚኒስቴሩ አስታውሶ፤ ያንን ጥቃት ለመከላከል የተወሰደው ወታደራዊ እርምጃ ተገቢ ነበር ብሏል፡፡
ወታደራዊ እርምጃ የወሰድነውም፤ አለም አቀፍ ህጐችን በማይጥስ መንገድና ከሶማሊያ የሽግግር መንግስት በተደረገልን ግብዣ ነው ብሏል - ሚኒስቴሩ፡፡  የኢትዮጵያ ጦር ሶስት አመት ሶማሊያ ውስጥ በቆየበት ወቅት ምንም አይነት ድጋፍ ከአሜሪካን እንዳልተሰጠውም ጠቅሷል፡፡

የሸራተን ሠራተኛ ማህበርና ማኔጅመንቱ ለድርድር እንዲቀርቡ በሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ባለፈው ማክሰኞ የወሰነ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፣ አደራዳሪ እንዲመደብ ትዕዛዝ ሰጥቷል፡፡
የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው፤ ክሱ እንዲሰረዝና ያለ አደራዳሪ ራሳቸው እንዲደራደሩ ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት ሳያገኝ ቀርቷል፡፡
ላለፉት 6 ወራት የሸራተን ሰራተኛ ማህበር ማኔጅመንቱ በህብረት ስምምነቱ ላይ እንዲደራደር ጥያቄ ሲያቀርብ ቢቆይም ማኔጅመንቱ ለድርድር ፈቃደኛ ባለመሆኑ፣ ለኢንዱስትሪ ፌዴሬሽን የእገዛ ጥያቄ ማቅረቡን እንዲሁም ጉዳዩ ከፌዴሬሽኑ አቅም በላይ በመሆኑ ለኢሰማኮ ደብዳቤ መፃፉንና ኢሰማኮ ለማኔጅመንቱ የአምስት ቀን ጊዜ መስጠቱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ ማኔጅመንቱ የተሰጠውን የአምስት ቀን የጊዜ ገደብ ከጨረሰ በኋላ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ለአሰሪና ሰራተኛ ወሳኝ ቦርድ ክስ መስርቶ፣ ባለፈው ማክሰኞ  የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመርና የማኔጅመንቱ ጠበቃ የቀድሞው የስፖርት ፌዴሬሽን ም/ፕሬዚዳንት አቶ ተካ አስፋው በተገኙበት ውሳኔ ተሰጥቷል፡፡
ቦርዱ፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ሰራተኛና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ፤ አደራዳሪ እንዲመድብ ትዕዛዝ እንደሚያስተላልፍ ገልጿል፡፡
በጉዳዩ ላይ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት እንዲገባ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር የጠየቁ ሲሆን የሸራተን ሆቴል ጠበቃ አቶ ተካ አስፋው ጥያቄውን ተቃውመውታል፡፡ “በጭራሽ መደረግ የለበትም፤ ፌዴሬሽኑ በአደራዳሪነት ገባ ማለት በእሳት ላይ ቤንዚን እንደማርከፍከፍ ይቆጠራል” ብለዋል - አቶ ተካ፡፡ የፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ በበኩላቸው፤ “በህግ አምላክ! ህጋዊ ሰውነት ያለውን ድርጅት በዚህ መልኩ መዝለፍ በህግ ያስቀጣዎታል” ሲሉ ምላሽ የሰጡ ሲሆን ቦርዱ አቶ ተካ ከንግግራቸውን እንዲታቀቡ አድርጓል፡፡
የሠራተኛ ማህበሩና ማኔጅመንቱ ለድርድር ቀርበው እስከ ሀምሌ 1 ቀን 2006 ዓ.ም  የደረሱበትን ሁኔታ ለቦርዱ ሪፖርት እንዲያደርጉ ትዕዛዝ ተሰጥቷል፡፡
በእለቱ ጉዳዩን ለመከታተል ከመጡት በርካታ የሸራተን ሰራተኞች መካከል አብዛኞቹ እንደገለፁልን፤ ሰራተኞች ችግራቸውን በሚዲያ ከገለፁ በኋላ፣ ሥራ አድረው ጠዋት ወደ ቤት ለሚሄዱ ሰራተኞች የሚቀርበው ሰርቪስ (የትራንስፖርት አገልግሎት) የቆመ ሲሆን በህመም፣ በጋብቻና በዘመድ ሞት ምክንያት አስፈቅዶ የቀረ ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አይከፈለውም ተብሎ በድርጅቱ ሰሌዳ ላይ እንደተለጠፈም ጠቁመዋል፡፡
“የኪችን ሰራተኛ 350 ብር፣ የላውንደሪ ሰራተኛ፣ 400 ብር፣ የጥበቃ ሰራተኛ 450 ብር፣ እንግዳ ተቀባይ 700 ብር፣ አስተናጋጅ 450 ብር ደሞዝ እያገኘ በችግር ምክንያት የቀረን ሰው ሰርቪስ ቻርጅ አንከፍልም ማለት አሳፋሪ ነው” ብለዋል ሰራተኞቹ፡፡ የኢንዱስትሪ ፌዴሬሽኑ ጠበቃ አቶ ሰኢድ ይመር በበኩላቸው፤ በሰራተኞቹ ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃ አግባብ ባለመሆኑ ድርጅቱ ከዚህ ድርጊቱ እንዲታቀብ ለቦርዱ አቤቱታ አቅርበዋል፡፡
ሰራተኞቹም የተወሰደው እርምጃ በህብረት ስምምነቱ የሌለና አዲስ የመጣ በመሆኑ ድርጅቱ የወሰደውን እርምጃ በአሰሪና ሰራተኛ አዋጁ መሰረት እንዲያነሳ ጠይቀዋል፡፡
ስለቀጣዩ የማህበሩና ማኔጅመንቱ ድርድር የጠየቅናቸው የሰራተኛ ማህበሩ ፕሬዚዳንት አቶ ዳዊት ሳሙኤል፤ ጉዳዩ በፍ/ቤት የተያዘ መሆኑን ጠቅሰው፤ አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡  

“...እኔና ባለቤቴ ከተጋባን እነሆ ሀምሳ ሶስት አመታችን ነው፡፡ የመጀመሪያ ልጃችን ሴት ስትሆን እሱዋም እድሜዋ ወደ ሀምሳ ሁለት ደርሶአል። በጠቅላላውም ወደ አስራ አንድ ልጅ የወለድን ሲሆን የመጨረሻ ልጃችን ሀያ አምስት አመት ሆኖአታል፡፡ በነበረው ሁኔታ ከቤተሰብ የተወረሰ ሀብት እና እኛም በየበኩላችን የሰራነው ተጨማምሮ ልጆቻችንን በደንብ አሳድገን ዛሬ ሁሉም የየራሳቸውን ሀብትና ንብረት ይዘዋል፡፡ እንዲያውም ከግማሽ በላይ የሚሆኑት በውጭ ሀገራት ኑሮአቸውን መስርተዋል፡፡ ሀገር ውስጥ ያሉትም ቢሆኑ ያገቡትም አግብተው ያላገቡትም ቢሆኑ ቤት እየተከራዩ ወጥተው እነሆ ዛሬ እኔና ባለቤቴ ብቻችንን እንኖራለን፡፡ በስልክም ይሁን በአካል እንደጠያቂ ከመጠየቅ ወይንም ስንፈልጋቸው አቤት ከማለት ውጭ በቀጥታ የምናገኘው ልጅ የለንም፡፡ ሁሉም የራሳቸውን ኑሮ መስርተዋል፡፡ እናም ጊዜው አልፈቅድ ብሎ እንጂ ልጅ ምንጊዜም አይጠላም። ታዲያ ...አሁን ...ልጆቻችንን ስንጠይቅ እኛ እንደእናንተ ጊዜ ብዙ ልጅ አንወልድም ዛሬ ጊዜው ተሸሽሎአል...በልክ ነው የሚወለደው...ይሉናል፡፡ በእርግጥ አጥግቦ አብልቶ...አልብሶ እና አስተምሮ ማሳደግ ካልተቻለ ዝም ብሎ መውለድም አስቸጋሪ ይሆን ይሆናል...”
ወ/ሮ ይርገዱ ተዋበ ከአዲስ አበባ
ወ/ሮ ይርገዱ የሰባ  አመት እድሜ ባለጸጋ ናቸው፡፡ ዛሬ ለሚመለከታቸው ግን ምናልባት ወደ ሀምሳዎቹ መጨረሻ እንጂ ሰባ አመት አይመስሉም። ምክንያቱንም ሲጠየቁ የሰጡት መልስ “...እኔ ልጆቼን ለማሳደግና ቤቴን ለማስተዳደር ስል እስከዛሬ ድረስ ያለእረፍት እንቀሳቀስ ነበር፡፡ ምናልባትም እሱ እንደ ስፖርት ሆኖ ይሆናል...” የሚል ነበር መልሳቸው፡፡ በእርግጥም አልተሳሳቱም፡፡ ብዙ ልጅ እንደመውለዳቸውም ስለአለመጎዳታቸውን ሲገልጹ ...ምንጊዜም ልጅ የሚወልዱት በሆስፒታል እንጂ በቤት ውስጥ አለመሆኑን እና የተማሩ በመሆናቸውም እራሳቸውን ለመርዳት አለመቦዘናቸውን ነው፡፡ ወ/ሮ ይርገዱ የሊሴ ፍራንሴ እና የንግድ ስራ ኮሌጅ ተማሪ ነበሩ፡፡ በእርግጥ አሉ ወ/ሮ ይርገዱ “...በእርግጥ ወደመጨረሻ የተወለዱትን ሁለት ልጆች ስወልድ ችግር ገጥሞኝ ነበር፡፡ አንዱዋም በሰባት ወርዋ የተወለደች ስትሆን ሌላዋ ደግሞ የተለያዩ የጤና ጉድለቶች ነበሩባት። እናም በከፍተኛ ሁኔታ እንክብካቤ ተደርጎ እና በሐኪሞችም ያላሳለሰ ክትትል ሰው ሆነው ዛሬ ጥሩ አቋም ላይ ይገኛሉ” ብለዋል፡፡
ከወ/ሮ ይርገዱ ታሪክ መለስ በማለት በዘመኑ ያሉትን ወላዶች አነጋግረናል፡፡ በክሊኒክ ክትትል ሲያደርጉ ካገኘናቸው መካከል የምትከተለው እናት ትገኝበታለች፡፡
“...ወ/ሮ ኤልሳቤጥ እባላለሁ፡፡ አሁን አንድ ልጅ አለኝ፡፡ የወለድኩት  በኦፕራሲዮን ስለሆነ ለመውለድ የሚፈቀድልኝ ጊዜ ገና ስለሆነ እንጂ እኔ ልጅ መውለድ እፈልጋለሁ፡፡
ጥ/    እስከስንት ልጅ መውለድ ትፈልጊያለሽ?
መ/    እኔ እስከ አራትም ይሁን አምስት ልጅ ብወልድ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጥ/    ባለቤትሽ በዚህ ይስማማል?
መ/    በእርግጥ እሱ እስከሶስት ይላል... እኔ ግን ልጅ እወዳለሁ፡፡
ጥ/    የማሳደግ ሁኔታውስ እንዴት ነው?
መ/    እኔ እማምነው ልጆች በረከት ናቸው በሚለው ነው፡፡ ልጅ ሲወለድ የራሱን ነገር ይዞ ይመጣል በሚለው ስለማምን ብወልድ ደስ ይለኛል።
ጥ/    ይህ ስሜት ከምን የመጣ ይመስልሻል?
መ/    አባቴ ቀደም ብሎ ስለሞተ እኛ ቤት እኔና ወንድሜ ብቻ ነን የተወለድነው፡፡ በአንድ ወቅት ወንድሜ ሲታመም እኔ የማዋራው ሰው እንኩዋን አጥቼ ነበር፡፡ እህት ወንድም ቢኖረኝ ኖሮ እያልኩ አስብ ነበር፡፡ እናም ከዚያ በመነሳት ልጄ ብቻዋን እንድትሆን ስለማልፈልግ ይመስለኛል፡፡  
ሌላው እንግዳችን አባት ነው፡፡ የእርሱ ሀሳብ ደግሞ በፍጹም ከወ/ሮ ኤልሳቤጥ ይለያል፡፡
“...እኔ ቢኒያም ጌታቸው እባላለሁ፡፡ አንድ ልጅ አለኝ፡፡ እድሜውም ወደሶስት አመት ደርሶአል፡፡ እኔ ልጅ እንዲበዛ አልፈልግም፡፡
ጥ/    ለምን?
መ/    የልጅን ቁጥር መወሰን አስፈላጊ ነው። ልጅን መውለድ ማለት ወልዶ በማሳደግ ደረጃ ብቻ መወሰን ያለበት አይመስለኝም፡፡ ለምሳሌ ወደ ወላጆቻችን አኑዋኑዋር ስንመለስ የምንታዘበው ነገር አለ፡፡ እነእርሱ በዘመናቸው መሬት... ቤት... ሌላም ሌላም ሀብት የነበራቸው ሲሆን ልጅ እየወለዱ ያለሀሳብ አስተምረው አሳድገው ሲያልፉም ለእኛ መቋቋሚያ አውርሰው ይሆናል፡፡ በእርግጥ ይህ የሁሉም ሰው አኑዋኑዋር ባይሆንም በነበረው ልምድ የጎረቤት ልጅ የራስ ልጅ ተደርጎ የሚወሰድበት ሁኔታ ስለነበር ሀብታሙ ከደሀው ጋር ተጋግዞ እንዲሁም አንዱ አንዱን እረድቶ በሚያሰኝ ሁኔታ አድገናል፡፡ ዛሬ ግን ያለው ሁኔታ ፈጽሞ የተለየ ነው፡፡ ወላጅም እንደድሮው ያለ አኑዋኑዋር የለውም...እርስ በእርስ መተጋገዙም ቢሆን እስከዚህ የሚታይ አይደለም፡፡ ስለዚህ አንድ ወላጅ የሚያሳድገውን ብቻም ሳይሆን ወደፊት የወለደው ልጅ እንዴት እንደሚኖር ማሰብም ይጠበቅበታል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/    ልጅን በኑሮው ማቋቋም አስፈላጊ ነው ብለህ ታስባለህ?
መ/    ቢያንስ ቢያንስ የወለድኩት ልጅ በደንብ ተምሮ አድጎ ...ወደፊት ምን ሊሰራ እንደሚችል ማመላከት ...ምናልባትም የስራ ፈጠራን ማሳየት... ብችል እራሴ ስራ ፈጥሬ የወለድኩት ልጅ እንዲያስፋፋው ማድረግ ይጠበቅብኛል ብዬ አምናለሁ፡፡
ጥ/    በአንድ ልጅ ተወስኖ መቅረት ነው? ወይንስ?
መ/    አ.አ.ይ፡፡ አንድ ልጅ ጨምረን ሁለት እንደሚሆኑ ከባለቤቴ ጋር ተስማምተናል፡፡
ሌላዋ እንግዳ ወ/ሮ ሳራ ትባላለች፡፡ ያገኘናት ለእራስዋ የህክምና ክትትል ለማድረግ ከሄደችበት ክሊኒክ ነው፡፡
“...እኔ ሁለት ልጆች አሉኝ፡፡ እድሜያቸውም ትልቅዋ ስምንት አመት ሲሆን ትንሹ ደግሞ ስድስት አመቱ ነው፡፡
ጥ/    ከባለቤትሽ ጋር ...ሁለት ልጅ ይበቃናል ብላችሁ ወስናችሁዋል?  
መ/    ልጅ ብንጨማምር ደስ ይለን ነበር፡፡ ነገር ግን የማሳደግ ሁኔታው እጅግ አስመርሮናል፡፡
ጥ/    ኢኮኖሚው ነው... ወይንስ?
መ/    አ.አ.ይ... ኢኮኖሚውን እንደብልሀቱ ልናደርገው እንችል ነበር፡፡ ነገር ግን የሚረዳኝ ሰው በማጣቴ ሁለቱን ልጆች ለማሳደግ በጣም ተሰቃይቻለሁ፡፡ ሰራተኛ እንደልብ አይገኝም። ቢገኙም ባልታሰበ ሁኔታ ትተው ይሄዳሉ፡፡ ስለዚህ ...ግማሽ በግማሽ ከስራዬ እየቀረሁ ማለት በሚያስችል ሁኔታ ልጆቼን አሳድጌያለሁ፡፡ ከዚህ በሁዋላ ያ ሁኔታ እንዲደገም አልፈልግም እንጂ ቢያንስ ቢያንስ አንድ ሴት ልጅ ብደግም እፈልግ ነበር፡፡
ጥ/    ልጆችን ለመንከባከብ ከስራ መቅረት ያንቺ ብቻ ድርሻ ነበር ወይንስ የባለቤትሽም?
መ/    እንደሁኔታው ሁለታችንም እየተጋገዝን ነው ልጆቻችንን ያሳደግነው፡፡ እንደስራው ክብደትና ሁኔታ እየተነጋገርን ነበር ያንን የምናደርገው፡፡ ከእኔና እሱ በተጨማሪም ቤተሰቦቻችንም እያገዙን ነው የተወጣነው።
በመቀጠል ሀሳቡን የሰጠን አባት ነው፡፡ አቶ ክፍሎም ገብረሕይወት ይባላል፡፡ የአንድ ልጅ አባት ነው፡፡ ልጁ ወደሶስት አመት ይሆነዋል፡፡
ጥ/    አንተ እና ባለቤትህ ሌላ ልጅ የመውለድ እቅድ አላችሁ?
መ/    ልጅ መውለድ እንፈልጋለን፡፡ ነገር ግን እራሳችንን ማደራጀት ስላለብን ቆም ማለት ፈልገናል፡፡
ጥ/    እራስን ማደራጀት ሲባል ምን ማለት ነው?
መ/    የምንወልዳቸውን ልጆች በሚገባ አስተምረን በብቃት ለማሳደግ እንድንችል እራሳችንን ማስተማር... ኑሮአችንን ማደራጀት... የመሳሰሉት ስለሚያስፈልጉን ባለቤቴም ሁለተኛ ዲግሪዋን እኔም ሶስተኛውን ዲግሪዬን በመስራት ላይ እንገኛለን፡፡ ይሄንን ካስተካከልን እኛ እያደግን ስለምንሄድ የምንወልዳቸውም ልጆች በጥሩ ሁኔታ ያድጋሉ የሚል እምነት አለን፡፡
በስተመጨረሻ የተነሳውን ፍሬ ሀሳብ የሚጠቀልሉልን የህክምና ባለሙያ ዶ/ር ዳንኤል አስፋው ናቸው፡፡
የቤተሰብ እቅድ ዘዴን መጠቀም የሚያስፈልገው በተለያዩ ምክንያቶች ነው፡፡ የቤተሰብ እቅድ አገልግሎት እንደሚያስረዳው ልጆችን አራርቆና ጤናማ በሆነ መንገድ ለማሳደግ ቤተሰብ የተወሰኑ ልጆችን የመውለድ እቅድ እንዲኖረው ያስፈልጋል፡፡ በሕክምናው፣ ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚው እና ከወቅቱ ሁኔታ ጋር በተያያዘ አስገዳጅ ነገሮች መኖራቸው ልብ ሊባል ይገባል፡፡ ከኢኮኖሚ አቅም በላይ መውለድ የልጆችን አስተዳደግ ጥራት ሊቀንስ ይችላል፡፡ በሌላ አቅጣጫ ደግሞ ገንዘብ አለን ተብሎም ስፍር ቁጥር የሌላቸውን ልጆች መውለድም አይመከርም፡፡ ይሄም ከህክምናው አገልግሎት ይሁን ከኢኮኖሚው እንዲሁም ወቅታዊ ሁኔታ ጋር የማይታረቅ ውሳኔ ይሆናል፡፡ የቤተሰብ እቅድ ሲባል አለምአቀፋዊ ትኩረት ያለው አሰራር ነው፡፡ ቤተሰብ ሲባል ደግሞ አንድ ተቋም ሲሆን ያ ተቋም የራሱ የሆነ ቪዥን እና ሚሽን ያለው እንዲሆን ይጠበቃል፡፡ የዚህም ውጤት በትዳር አለም በእቅድ የተወሰኑ ልጆችን ወልዶ አስተምሮ እና አንጾ በማሳደግ ለሀገር ብቁ ዜጋን ማስረከብ ነው። በቀጣይም የመልካም ዜጋ መተካካት በሀገር ላይ እንዲፈጠርና ወገን እንዲጠቀም ...ሀገር እንድታድግ የሚያስችል አካሄድ ነው፡፡

   የኢትዮጵያ ብሔራዊ የባህል ማዕከልና ኤልሰን ፕሮሞሽን በመተባበር ያዘጋጁት “የጀበና ሙሽሮች” የተሰኘ የቡናና የኪነጥበብ ፌስቲቫል በትላንትናው እለት በብሔራዊ ቴአትር የተከፈተ ሲሆን ፌስቲቫሉ እስከ ነገ እንደሚቆይም ታውቋል፡፡ የተለያዩ ክልሎች የቡና አፈላል ስርዓታቸውን ከነ አቀራረቡና ሙሉ ስርዓቱ ወክለው በተገኙበት በዚህ ፌስቲቫል ላይ የኢፌድሪ ባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሙሉጌታ ሰኢድ እና የቀድሞው የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ክቡር ዶ/ር ግርማ ወ/ጊዮርጊስ በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡ “”ቡና ከእለት የእለት ህይወታችን ጋር የተገናኘ ቢሆንም በደንብ አናውቀውም፤ ይህን ቡና ለራሳችን በደንብ ለማስተዋወቅ ታስቦ የተዘጋጀ ፌስቲቫል ነው” ብሏል - ፕሮሞተር ዮናስ ታደሰ፡፡ በአሜሪካ የአቦል ቡናና የመርካቶ ገበያ መስራች የሆኑት አቶ ታምሩ ደገፋና ከፈረንሳይ የመጡት ወ/ሮ አለም ፀሐይ ንባብ፤ የኢትዮጵያን ቡና በያሉበት እንዴት እንደሚያስተዋውቁ በፌስቲቫሉ መክፈቻ የገለፁ ሲሆን፤ አቶ ታምሩ ደገፋ በአሜሪካ ለታዋቂው ሙዚቀኛ ለማይክል ጃክሰን በአንድ ወቅት ስለ ኢትዮጵያ ቡና ሰፊ ማብራሪያ እንዳደረጉለት ተናግረዋል፡፡ ፌስቲቫሉ እስከ ነገ የሚቆይ ሲሆን የአማራ፣ የትግሬ፣ የኦሮሞ፣ የጉራጌና የሌሎች ብሔሮች የቡና ስርዓት ለእይታ ቀርቦ እየተጐበኘ ነው፡፡   

ዩኒቲ ዩኒቨርስቲ ዓመታዊ የጥናትና ምርምር ጉባኤውን በትላንትናው ዕለት የጀመረ ሲሆን፤ ዛሬ እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል፡፡ መቻሬ ሜዳ በሚገኘው ሚድሮክ ቴክኖሎጂ ግሩፕ ኮርፖሬት ሴንተር የሚካሄደው ይሄው ጉባኤ፤ ዘንድሮ ለ13ኛ ጊዜ እየተካሄደ ሲሆን በተለያዩ ዩኒቨርስቲዎች የሚሰሩ ምሁራንና የምርምር ተቋማት የሰሯቸው የተመረጡ የጥናትና ምርምር ውጤቶች ቀርበው ውይይት ይደረግባቸዋል ተብሏል፡፡ በየአመቱ የሚካሄደው ይሄው “Multidisciplinary Research Conference” በትላንትናው እለት ከጠዋቱ 2፡30 ሰዓት ተጀምሮ በተለያዩ ምሁራን እየቀረበ ሲሆን የምርምር ውጤቶቹም የማህበረሰቡን ችግር በመፍታትና በማቃለል ረገድ ጉልህ ሚና ይኖራቸዋል ተብሏል፡፡

ካለፈው መጋቢት ወር ጀምሮ “በማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ” አማካኝነት በኢቲቪ ቻናል ሶስት ሲተላለፉ ከነበሩ 12 ፊልሞች ሶስቱ ባለፈው ረቡዕ ምሽት በኢሊሊ ኢንተርናሽናል ሆቴል ተሸለሙ፡፡ ማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ በሚል መጠሪያ በቻናል ሶስት የኢትየጵያ ፎልሞችን ቅዳሜ ምሽት ከ4፡30 ሰዓት ጀምሮ የሚያስተላልፈው ድርጅት ፊልሞቹን ከማስተላለፍ በተጨማሪ በባለሙያዎችና በአዘውታሪ ተመልካቾች የተመረጡና ከ1 እስከ 3 የወጡ ፊልሞችን አወዳድሮ የመሸለም ዓላማ እንደነበረውም የፕሮግራሙ ዳይሬክተር ወ/ሪት ፌቨን ታደሰ በእለቱ ገልፃለች፡፡ ለተከታታይ 12 ሳምንታት ከተላለፉት 12 የአማርኛ ፊልሞች ውስጥ በ2001 ዓ.ም ለእይታ የበቃው “አልተኛም” ፊልም አንደኛ በመውጣት የ20ሺህ ብር ተሸላሚ ሲሆን በ2001 ዓ.ም የተሰራው “የታፈነ ፍቅር” ሁለተኛ በመውጣት የ10 ብር ሽልማት አግኝቷል፡፡ በ2004 ዓ.ም የተሰራው “አየሁሽ” ፊልም ሶስተኛ በመውጣት የአምስት ሺህ ብር ተሸላሚ ሆኗል፡፡
በእለቱ የኢቲቪ የስራ ኃላፊዎች፣ የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች፣ የማቭሪክ ፊልሞች የኢትዮጵያ ስፖንሰር የሆነው ፍሊንት ስቶን ሆምስ ባለቤቶችና ሌሎች ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች የተገኙ ሲሆን አርቲስት ስለሺ ደምሴ (ጋሽ አበራ ሞላ) በሙዚቃው ታዳሚዎቹን ሲያዝናና አምሽቷል፡፡

    በደራሲ ብርሃኑ አበጋዝ የተፃፈው “ጥምር ቁስል” ልብወለድ መጽሐፍ ሰሞኑን ገበያ ላይ ዋለ፡፡ መጽሐፉ ትኩረት የደረገው በኢትዮ - ኤርትራ ጦርነትና በሁለቱ ሀገራት ህዝቦች ቁርኝት ላይ ሲሆን የኢትዮጵያና የሶማሊያ ጦርነትም በልብወለዱ ውስጥ ተዳስሷል፡፡ በ161 ገጽ የተቀነበበው ልብወለዱ፤ 37 ክፍሎች ያሉት ሲሆን ታሪኩ በሃሳብ ደረጃ ከተፀነሰ 14 ዓመታት፣ መፃፍ ከተጀመረ ደግሞ ሰባት ዓመታትን እንዳስቆጠረ ደራሲው በመግቢያው ላይ ገልጿል፡፡ ታሪካዊ ልብ ወለድ መጽሐፉ ዛሬ ከቀኑ በ10፡30 በኢዮሃ ሲኒማ የሚመረቅ ሲሆን በ40 ብር ከ60 ሳንቲም እየተሸጠ ይገኛል፡፡

የኢትዮጵያን ፊልም 50ኛ ዓመት በዓል ምክንያት በማድረግ በኢዮሃ ሲኒማና በባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር የተዘጋጀው የፊልም ስልጠና ረቡዕ ተጠናቀቀ፡፡ ስልጠናው የተሰጠው ወደ 60 ለሚጠጉ የፊልም ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ሲሆን በፊልም መመሪያና ስነ ምግባር፤ በፊልም ዝግጅት፣ በፊልም ስክሪፕት አፃፃፍና በፊልም ትወና ላይ ያተኮረ እንደነበር በማጠናቀቂያው ላይ ተገልጿል፡፡
ለአራት ቀናት በቆየው በዚህ ስልጠና ላይ ዮናስ ብርሃነ መዋ፣ ብርሃኑ ሽብሩ፣ ሄኖክ አየለ እና ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የመጡ የስነ ልቦና ባለሙያዎች በአሰልጣኝነት መሳተፋቸውም ታውቋል፡፡

የገጣሚ ሶልያና አብዲ “ሼም ይናፍቅሃል” የተሰኘ የግጥም መድበልና ሲዲ ዛሬ ከ3ሰዓት ጀምሮ በጣይቱ ሆቴል ጃዝ አምባ አዳራሽ ይመረቃል፡፡
በመድበሉ ውስጥ የተካተቱት ግጥሞች በሴቶች ጥቃት፣ በህገወጥ ጉዞ አስከፊነት፣ በወጣትነትና በፍቅር ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ሲሆን የግጥሙ ሲዲ ደግሞ በኢትዮጵያ ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድኖች (ዋሊያዎቹና ሉሲዎች) ጀግንነት ላይ የሚያተኩር ነው ተብሏል፡፡ 94 ያህል ግጥሞችን የያዘው መድበሉ በ30 ብር ለሽያጭ ቀርቧል፡፡

“በሰው ለሰው” ድራማ የአዱኛን ገፀ - ባህሪ ወክሎ በመጫወት እና በበርካታ ስራዎቹ አድናቆትን ያተረፈው አርቲስት ይገረም ደጀኔ፤ “ቆምኩኝ ለምስጋና” የተሰኘ የምስጋና የመዝሙር ሲዲ ያወጣ ሲሆን፤ ሰኞ ገበያ ላይ እንደሚውል ተገለፀ፡፡ አርቲስቱ ለመዝሙሩ ከተከፈለው 40ሺህ ብር ላይ 20ሺህ ብሩን ለሜቄዶንያ አረጋዊያን መርጃ በእርዳታ ሲሰጥ ቀሪውን እያገለገለ ላደገበት ሰንበት ት/ቤት መለገሱን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
በመዝሙር ሲዲው ውስጥ 11 መዝሙሮች የተካተቱ ሲሆን፤ አምስቱን ለብቻው ሁለቱን ከዘማሪ ዲያቆን ፍቃዱ አዱኛ ጋር በጋራ መስራቱንና ቀሪዎቹ አራት መዝሙሮች በዘማሪ አዱኛ እንደተሰሩ ይገረም ገልጿል፡፡
“የዘመርኩት ማመስገን ስለምወድ” ነው ያለው አርቲስቱ፤ ሌሎችም የተሰጣቸውን ፀጋ ተጠቅመው የድርሻቸውን እንዲያበረክቱ ለማነቃቃት በስራው ላይ መሳተፉን ተናግሯል፡፡  
“ወደፊት ከእኔ ጋር በበጎ ስራዎች ላይ ለመሰማራት የሚፈለግ ሰው ካለ አብሬ ለመስራት ዝግጁ ነኝ” ብሏል - አርቲስት ይገረም ደጀኔ፡፡ አርቲስቱ ከዚህ ቀደም ለአቡነ መልከፀዴቅ ገዳም ለገቢ ማሰባሰቢያ የሚውል የመዝሙር ቪሲዲ ከሙያ አጋሮቹ ጋር መስራቱ ይታወሳል፡፡