Administrator

Administrator

 መሪዋ የተገደሉባት ሃይቲ አዲስ ጠ/ ሚኒስትር ሾማለች


           በማሊ ከወራት በፊት በተካሄደው መፈንቅለ መንግስት ወደ ስልጣን የመጡት የአገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ባለፈው ማክሰኞ በመዲናዋ ባማኮ በሚገኝ መስጊድ በሶስት ታጣቂዎች ከተፈጸመባቸው የግድያ ሙከራ ማምለጣቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ፕሬዚዳንቱ በመዲናዋ ባማኮ በሚገኝ አንድ መስጊድ በተዘጋጀ የኢድ አል አድሃ አረፋ በዓል የጸሎት ስነስርዓት ላይ እያሉ ሁለት ታጣቂዎች ስለት ከያዘ ሌላ ተባባሪያቸው ጋር በመሆን የግድያ ሙከራ እንዳደረጉባቸው የጠቆመው ዘገባው፣ የደረሰባቸው ጉዳት ይኑር አይኑር በይፋ የታወቀ ነገር አለመኖሩን አመልክቷል፡፡
ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ጥቃቱ ከተሞከረባቸው ከሰዓታት በኋላ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፣ ነገርዬው የስራው አካል ነው፤ ምንም ችግር አልደረሰም ሲሉ ጉዳዩን ቀለል አድርገው መናገራቸውንም ዘገባው አስረድቷል፡፡
የ38 አመቱ ኮሎኔል አስሚ ጎይታ ባለፈው ነሃሴ ወር በመሩት መፈንቅለ መንግስት ፕሬዚዳንት አቡበከር ኬታን በማስወገድ ጊዜያዊ መንግስት መስርተው አገሪቷን ሲመሩ እንደቆዩ ያስታወሰው ዘገባው፣ ከ3 ወራት በፊት ደግሞ ራሳቸውን ጊዜያዊ ፕሬዚዳንት አድርገው መሾማቸውን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ፣ ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስ ከሳምንታት በፊት ታጣቂዎች በመኖሪያ ቤታቸው ባደረሱባቸው ጥቃት  መገደላቸውን ተከትሎ በባላደራ መሪ ስትተዳደር የቆየቺው ሃይቲ ባለፈው ማክሰኞ አሪየል ሄንሪን በጠቅላይ ሚኒስትርነት የሾመች ሲሆን፣ ሄንሪ አዲሱን ካቢኒያቸውን በማስተዋወቅ እስከ ቀጣዩ ምርጫ አገሪቱን የሚያስተዳድር መንግስት እንደሚመሰርቱ በቃለ መሃላ ስነስርዓቱ ላይ ቃል ገብተዋል፡፡
አገሪቱን ላለፉት 5 አመታት ያስተዳደሩትን ፕሬዝዳንት ጆቬናል ሞይስን የገደሉት ታጣቂዎች ማንነት አሁንም ገና በግልጽ አልታወቀም ያለው ዘገባው፣ ፖሊስ 26 ያህል ተጠርጣሪዎችን አስሮ በመመርመር ላይ እንደሚገኝና ከእነዚህም መካከል አስራ ስምንቱ የቀድሞ የኮሎምቢያ ጦር አባላት፣ ሶስቱ ደግሞ ሃይቲና አሜሪካውያን መሆናቸውንም ገልጧል፡፡
  የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ጆ ባይደን ልጅ ሃንተር ባይደን በቅርቡ በዋይት ሃውስ በኩል ለጨረታ ሊያቀርባቸው ያቀዳቸው ሁለት ስዕሎች ጉዳይ ብዙዎችን እያወዛገበ እንደሚገኝ ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡
ሃንተር ባይደን የሳላቸው ሁለት ስዕሎች በዋይት ሃውስ ለጨረታ ሊቀርቡ መሆኑንና እያንዳንዳቸው እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይሸጣሉ ተብሎ እንደሚጠበቅ የጠቆመው ዘገባው፣ ስዕሎቹ በሃንተር የፕሬዚዳንት ልጅነት ሰበብ በማይገባቸው ከፍተኛ ዋጋ እንዲሸጡ የተኬደበት መንገድ አግባብ አይደለም በሚል በብዙዎች ትችት እየቀረበባቸው እንደሚገኝ አመልክቷል፡፡
ስዕሎቹ ሙያዊ አካሄድን በተከተለ መልኩ በአርቲስቶችና ልምድ ባላቸው አጫራች ኩባንያዎች አማካይነት ለጨረታ መቅረብ ሲገባቸው ሰውዬው የፕሬዚዳንቱ ልጅ በመሆኑ ብቻ ስዕሎቹ በነጩ ቤተመንግስት አሻሻጭነት ለጨረታ መቅረባቸውና የተጋነነ ዋጋ እንዲያወጡ መደረጋቸው አግባብ አይደለም በሚል ብዙዎች ተቃውሞ ማሰማታቸውን ገልጧል፡፡
ዋይት ሃውስ የፕሬዚዳንቱ ልጅ ጉዳይ በአባቱና በአሜሪካ አስተዳደር ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንዳይፈጥር ለማድረግ ማቀዱን እንዳስታወቀ የተነገረ ሲሆን፣ ሃንተር ባይደን  በዩክሬንና ቻይና ያደረጋቸው የንግድ ስምምነቶች ከአባቱ ጋር በተያያዘ የጥቅም ግጭት ሲያስነሱ መቆየታቸውን በማስታወስ የስዕሎቹ ሽያጭም መሰል ጥያቄን ሊያጭር እንደሚችል አስነብቧል፡፡
የ51 አመቱ ሃንተር ባይደን በአንድ የኒው ዮርክ ጋለሪ አማካይነት ለጨረታ የሚያቀርባቸው ስዕሎች እስከ ግማሽ ሚሊዮን ዶላር ይሸጣሉ መባላቸው ብዙዎችን ማስገረሙን የጠቆመው ዘገባው፣ ከዚህ ቀደም ይህ ነው የሚባል የስነጥበብ ታሪክም ሆነ ችሎታ የሌለው ጀማሪ ሰዓሊ ለሰራቸው እዚህ ግባ የማይባሉ ስራዎች ዋጋው እጅግ መጋነኑን የሚናገሩ መኖራቸውንም ገልጧል፡፡


 የዘንድሮ የአፍሪካ ሕፃናት ቀንና “የአንድሮ ሜዳ ቁጥር 2” መፅሐፍ ምረቃ ነገ በባህርዳር አቫንገር ብሎ ናይል ሆቴል እንደሚካሄድ አዘጋጁ ሰምና ወርቅ ሚዲያና ፕሮሞሽን አስታወቀ።
በዕለቱ  ጥናታዊ የምርምር ስራ በመጋቤ ሀዲስ  ዶ/ር ሮዳስ ታደሰና ዶ/ር ጌትነት ፈለቀ የሚቀርብ ሲሆን በአዲስ አበባና በባህርዳር ያሉ ተመራማሪ የአንድሮ ሜዳ ህጻናት ይሳተፋሉም ተብሏል፡፡ በዚሁ ሥነ-ስርዓት ላይ “አንድሮሜዳ ቁጥር ሁለት” እና “የወርቅ ዘንግ” መፃህፍት የሚመረቁ ሲሆን በእውቅ ገጣሚያን ግጥም፣ በኢትዮጵያ የባህል ቡድን ምርጥ ኪነ- ጥበባዊ ዝግጅቶች፣ በስነ-ፈለክ መመልከቻ የሰማይ ምልከታ ሥነ-ስርዓት እንደሚከናወን የጠቆመው አዘጋጁ፣ በፕሮግራሙ ላይ ታዋቂ ግለሰቦች እንደሚታደሙ ተገልጿል፡፡

 ቻይና በአለማችን ታሪክ በፍጥነቱ አቻ አይገኝለትም የተባለውንና በሰዓት 600 ኪሎሜትር የመጓዝ አቅም ያለውን እጅግ ፈጣን ባቡር ከሰሞኑ ኪንዳኦ በተባለው አካባቢ በይፋ ማስመረቋን ሲኤንኤን ዘግቧል፡፡ ማግሊቭ የሚል ስያሜ የተሰጠውና ቻይና ሬልዌይ ሮሊንግ ስቶክ ኮርፖሬሽን በተባለው የአገሪቱ መንግስት ተቋም የተሰራው ይህ እጅግ ፈጣን ባቡር ከተነጠፈለት ሃዲድ ከፍ ብሎ በኤሌክትሮ ማግኔቲክ ስበት አማካይነት እየተንሳፈፈ ሲከንፍ ማየት እጅግ እንደሚያስደምም ዘገባው አስነብቧል፡፡
ባቡሩ ከፍጥነቱ በተጨማሪ የሚያወጣው የድምጽ ብክለት አነስተኛ መሆኑ እንዲሁም ከሌሎች ፈጣን ባቡሮች ጋር ሲነጻጸር አነስተኛ ጥገና የሚያስፈልገው መሆኑ ለየት እንደሚያደርገው የጠቆመው ዘገባው፣ በቻይና በስራ ላይ የሚገኙ ፈጣን ባቡሮች በአማካይ 350 ኪሎሜትር በሰዓት የመጓዝ አቅም ያላቸው መሆናቸውም አክሎ ገልጧል፡፡

ሊቨርፑል ከዩኔስኮ የአለም ቅርሶች መዝገብ ተሰረዘች

            ኤርላይን ሬቲንግስ የተባለው አለማቀፍ ተቋም የ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ 20 አየር መንገዶችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ የአለማችን አቪየሽን ኢንዱስትሪ ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ክፉኛ በተደቆሰበት የፈተና ጊዜ ስኬታማ ሆኖ የዘለቀው ኳታር ኤርዌይስ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
ተቀማጭነቱ በአውስትራሊያ የሆነው ኤርላይን ሬቲንግስ በዘንድሮው ዝርዝሩ በሁለተኛነት ደረጃ ላይ ያስቀመጠው አየር መንገድ አምና በአንደኛ ደረጃ ላይ የነበረው ኤር ኒውዚላንድ ሲሆን፣ ሲንጋፖር ኤርላይንስ፣ ኳንታስ ኤሜሬትስ እና ካቲ ፓሲፊክ እስከ አምስተኛ ያለውን ደረጃ ይዘዋል፡፡
በ2021 የፈረንጆች አመት የአለማችን ምርጥ 20 አየር መንገዶች ዝርዝር ውስጥ የተካተቱት ቀሪዎቹ አየር መንገዶች ደግሞ ቨርጂን ጋላክቲክ፣ ዩናይትድ ኤርላይንስ፣ ኢቫ ኤር፣ ብሪቲሽ ኤርዌይስ፣ ሉፍታንዛ፣ ኤኤንኤ፣ ፊናኤር፣ ጃፓን ኤርላይንስ፣ ኬኤልኤም፣ ሃዋያን ኤርላይንስ፣ አላስካ ኤርላይንስ፣ ቨርጂን አውስትራሊያ፣ ዴክታ ኤርላይንስ እና ኢትሃድ ኤርዌይስ ናቸው፡፡
ተቋሙ የአመቱን ምርጥ አየር መንገዶች ለመምረጥ ከሚጠቀምባቸው መስፈርቶች መካከል ትርፋማነት፣ ከ7 ኮከብ በላይ የደህንነት ደረጃ መያዝ፣ ለመንገደኞች ምቾት ፈጠራ የታከለበት አመራር መስጠት እንደሚገኝበትም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ አለማቀፍ ዜና ደግሞ፣ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ተቋም ዩኔስኮ የእንግሊዟን ከተማ ሊቨርፑል ከአለም ቅርሶች መዝገብ መሰረዙንና ይህም የከተማዋን ከንቲባና ነዋሪዎችን ክፉኛ ማስቆጣቱን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ተቋሙ እ.ኤ.አ በ2004 በአለም ቅርስነት የመዘገባትን ሊቨርፑል ከዝርዝሩ ለማውጣት የወሰነው፣ የከተማዋን ጥንታዊነትና ውበት የሚቀንሱ የእግር ኳስ ስቴዲየምን ጨምሮ በርካታ አዳዲስ ህንጻዎች መገንባታቸውን ማረጋገጡን ተከትሎ እንደሆነም ዘገባው ገልጧል፡፡

Sunday, 25 July 2021 00:00

ዕዳ ከሜዳ!

  ከዕለታት አንድ ቀን አንድ አዝማሪ ለሚስቱ በጠዋት ተነስቶ
“ዛሬ ዕዳ ከሜዳ ሲለኝ አደረ” አላት።
ሚስትየውም፡-
“ይሄ ነገር የመልካም ነገር ምልኪ አይመስለኝም። ዛሬ ከቤትህ ፈፅሞ ንቅንቅ ባትል ጥሩ ነው።” አለችው።
“በጭራሽ የታየኝን ሳላሳካ አልውልም፤ አላድርም” አላትና እምቢ ብሏት ከቤት ወጣ።
ከቤት ወጥቶ ወደ አንድ ጫካ ሄደና መሰንቆውን ይዞ ሲጫወት በድንገት አንዳች መንጋ ህዝብ መጥቶ ከበበው። አንደኛው፤
“ይኸው ይሄ ጥጋበኛ የሰረቀውን የእኛን በሬ አርዶ በልቶ ጠግቦ እየዘፈነ ነው።”
“በዚሁ ምክንያት እሥር ቤት መግባት አለበት።” አሉ፡፡
 በዚሁ ወንጀል እሥር ቤት ገባ።
*   *   *
እኛም ሆንን ሌላ ሰው ሲቀፈው ወይም የሆነ ስሜት ሲሰማው አሊያም ሲታየው መጠርጠር ወይም ነገሩን ጉዳዬ ማለት በጣም ተገቢ ነው። መፍትሄ የሚገኘው ነገርን አጥብቆ ከማስተዋል ነው። ከዚያ ቀረብ ብሎ ማጤኑ ሊከተል ይችላል። አስተውሎን ወደ ከፍተኛ ደረጃ ለማድረስ ይበጃል።
የማያስተኛ ነገር ነግረውን ተኝተው አደሩ። የተባለው ተረት የሀገራችንን እውነታ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ ነው። ብዙ ቃል ተገብቷል፤ ብዙ ማስረጃ የሌለው ጥናት ቀርቧል። ብዙ መላምት በድፍረት ተሰንዝሯል። ሳናውቅ በድፍረት አውቀን በስህተት መጠነ ሰፊ ጥፋት አድርሰናል። ከዚያ የከፋው ደግሞ ምክር አለመስማትን አለማወቅን አለማወቅ ነው።
ደራሲ ከበደ ሚካኤልን ማድመጥ እጅግ መልካም ነገር ነው።
.. “አሁን የት ይገኛል ቢፈልጉ  ዞሮ
መስማት ከማይፈልግ የባሰ ደንቆሮ"
ከአቶ ከበደ አንድ እርከን አድገን ስናስብ፤
“ደግሞ ማወቅ ማለት ከውጪ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ ነው” የሚለው የደግ  ስነ-ምግባር ምልክት ነው።
ሀገርን ለመለወጥ፣ አንድም ራስን መለወጥ፣ አንድም ሌላውን መለወጥ ተገቢ ነው።
“ለውጥ የእረፍት እኩያ ነው - A change is as equal to rest- ይላሉ ፀሀፍት።” ለውጥ የጊዜ ለውጥ አለው። ለውጥ የቦታ ለውጥ አለው። ለውጥ የአስተሳሰብ ለውጥ አለው። ለውጥ የወዳጅነት ለውጥ አለው፡፡ ለውጥ ለውጥን መውለዱ፣ ያለ የነበረና የሚመጣ ነው።
ከዚህ ጋር የግል ዕድገት አለ። አንዳንዴ ለውጥ የኋሊት የሚጎትተን ወቅት አለ። እንዲህ ያለውን ጎታች መንፈስ በየትኛውም ገፅታው መወልወልና ንፁህ ማድረግ ተገቢነት ያለው ሂደት ነው። ጎታች ይሁን እንጂ ቀስ በቀስ የተለየ ባህሪ እያዳበረ መልካም ህልውናው ያጸኸያል። ከእያንዳንዱ የህይወት ቅንጣት ቀንበጥ ተስፋ፣ ምኞትና ሕልም ህላዌውን ያገኛል። እነዚህ አላባውያን ሁልጊዜ አዳጊ፣ ሁልጊዜ አፍሪ ብቻ ላይሆኑ ይችላሉ። በዚሁ ውስጥ ወደ ኋላ የመቀልበስ አደጋም ንፋሱ ያንዣብብባቸዋል። ዋናው ነገር ግን አዎንታም አሉታም ውስጡ አለ። ደስታና ሐዘንም ከአብራኩ የሚወጡ ልጆቹ ናቸው። በገዛ ልጆቹ የሚያፍር ልጆቹን በወጉ ያሳደገ ወላጅ ብቻ ነው። የግል ህይወቱን ከማህበረሰባዊ ህይወቱ ነጥሎ ተገቢ ቦታ ያልሰጣት ሰው ነው!
ኑሮን በአግባቡ በመቃኘት ልዩ ዜማ፣ ሰምና ወርቅም ካላወጣላት በማንነቱ ውስጥ በሳል ጣዕም ያጣባታል። ረዥሙን አግባብ ባጭር ባጭሩ በመመርመር ቅጥ ቅጥ በማበጀት ምጣኔ መፍጠር የብልህና የአስተዋይ ሰው ተስፋ፣ የዳተኛ ራሱን በራሱ  መዋጫ ነው። ራስን በራስ መርሻ ነው።
ማስተዋል ያለብን ግን፣ ልጆቻችን ከእኛ በወጉ መማር ያለባቸውን አያሌ ጉዳዮች በስርዓት መመርመር እንዳለባቸው ነው።
ነገራችንን በሰከነ መልኩ ማጤን የአስተውሎት ሁሉ መሰረት ነው! አርባ በመቶ ለሚዛናዊ አመለካከት ሰጥተናል ካልን፣ ስልሳ በመቶውን ለጥናት ለምርምር ወደመጣንበት የመመለሻ አቅም ለማድረግ ዕድሉ አለን!
ጨለምተኝነት የተስፋ መቁረጥ ጥዋ ነው ብለን አንደምድም። ብዙም ረዥም መንገድ፣ አያሌ አቋራጮችን የያዘ መሆኑን አንርሳ! የአቋራጮችን አካሄድ ማጤን ጊዜን፣ ጉልበትን፣ እንቅስቃሴን ያበለፅጋል። ይህም የዕድገትን መሰረት ይጥላል። ይህን በሚገባ እንመዘግብ ዘንድ ልብና ልቦና ይስጠን! ኢዜማ በ28 የምርጫ ጣቢያዎች ላይ ምርጫው እንዲደገም ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ያቀረበው ማመልከቻ ተቀባይነት በማጣቱ ጉዳዩን ወደ ፍ/ቤት መውሰዱ ታውቋል፡፡
ሰኔ 14 ቀን 2013 በተካሄደው 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ኢዜማ ከተወዳደረባቸው የምርጫ  ክልሎች 28 ያህሉ ላይ የተለያዩ ማጭበርበሮች ተፈፅመዋል የሚል አቤቱታ ውጤቱ  ከመገለፁ በፊት ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ማስገባቱን፣ ነገር ግን ቦርዱ የምርጫ ክልሎቹን በተመለከተ የቀረቡበትን ቅሬታዎችና ማስረጃዎች  ሳይገመግም ውሳኔ ማሳለፉ ቅሬታ እንደፈጠረበት አመልክቷል። ይህን የቦርዱን ምላሽ ተከትሎም ጉዳዩን ወደ ጠቅላይ ፍ/ቤት ለመውሰድ መገደዱን ነው ያስታወቀው፡፡
ኢዜማ ምርጫው እንዲደገም አቤቱታ ያቀረበባቸው የምርጫ ክልሎች 27 በደቡብ አንድ በጋምቤላ ክልል የሚገኙ ሲሆን ከእነዚህም አራቱ የክልል ም/ቤት ምርጫ ብቻ  የተካሄደባቸው መሆኑ ተጠቁሟል፡፡
ኢዜማ ከተወዳደረባቸው ከ4 መቶ በላይ የምርጫ ወረዳዎች በአምስቱ የህዝብ ተወካዮች ም/ቤት ወንበር ያገኘ ሲሆን እነዚህም በደቡብ ክልል የሚገኙ የምርጫ ወረዳዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡

 - በሚቀጥሉት አምስት ዓመታት 5.ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት እንደሚያደርግ ታውቋል
            - የአገልግሎት አድማሱን ወደ ምግብ ማድረስና የክልል ከተሞች ያስፋፋል ተብሏል።


          “ሊትል” በሚል ስያሜ የሚታወቀው የኬንያው የራይድ ኩባንያ በቅርቡ የኢትዮጵያን ገበያ በመቀላቀል አገልግሎቱን በአዲስ አበባ እንደሚጀምር ተገለፀ። ግዙፉ  የቴሌኮም ኩባንያ “ሳፋሪኮም” እና  ሌሎች በርካታ የኬንያ ኩባንያዎች እስካሁን ለውጭ የንግድ ተቋማት ተዘግቶ የቆየውን የኢትዮጵያ ገበያ መቀላቀል ተከትሎ ነው “ሊትል” በአዲስ አበባ አገልግሎት ለማቅረብ የተነሳሳው ተብሏል።
የ“ሊትል” ዋና ስራ አስፈጻሚ ካማል ቡድሃብሃቲ ለኬንያው “ቢዝነስ ዴይሊ” እንደተናገሩት፤ ኩባንያው በመጪዎቹ  አምስት ዓመታት በኢትዮጵያ 5 ሚሊዮን ዶላር ኢንቨስት ሚያደርግ ሲሆን በዕድገት ትንበያው ላይ ተመስርቶ ተጨማሪ የ5 ሚ.ዶላር መዋዕለ ንዋይ የማፍሰስ  ዕቅድ እንዳለውም ተጠቁሟል፡፡
በኬንያ ዩጋንዳ፣ ሞዛምቢክና ታንዛኒያ ውስጥ ከሚንቀሰቀሱት “ኡበር” እና “ታክሲፋይ” የተሰኙ ዓለማቀፍ የራይድ አገልግሎት ሰጪዎች ጋር የሚፎካከረው “ሊትል” የኢትዮጵያ አገልግሎቱን በአጭር ጊዜ ውስጥ እንደሚጀምር ታውቋል፡፡
ኩባንያዎችንና ግለሰብ ተጠቃሚዎችን በደንበኝነት ታላሚ አድርጎ ወደ አገልግሎት የሚገባው  የራይድ ኩባንያ፤ 2 ሺ ሹፌሮችን እንደሚቀጥር “ቢዝነስ ዴይሊ” ዘግቧል። በኋላ ላይም ምግብ የማድረስ (food delivery) እንዲሁም ከአዲስ አበባ ውጭ ባሉ የክልል ከተሞች አገልግሎቱን የማስፋት ዕቅድ እንዳለው ተጠቁሟል፡፡
“ኢትዮጵያ ሁልጊዜም በእይታ ትኩረታችን ውስጥ ነበረች” ብለዋል- ዋና ስራ አስፈጻሚው  ከ“ቢዝነስ ቱዴይ” ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፡፡
“የኬንያው ሳፋሪኮም ወደ ኢትዮጵያ ማምራቱን ስናይ፣ እኛም ገበያውን ለመቀላቀል ድፍረቱን ተቀዳጀን፡፡ እዚያ ሰፊ ገበያ ነው ያለው፤ እናም አገልግሎታችንን በዚያ አገር የማስፋፋት ትልቅ ዕድል መኖሩን ተገነዘብን” ሲሉ አስረድተዋል-ዋና ስራ አስፈፃሚው፡፡
 “ሊትል” ኩባንያ በቅርቡ “ቴሌብር” የተሰኘውን የሞባይል የገንዘብ አገልግሎት ከጀመረውና በመንግስት ባለቤትነት ከሚመራው ኢትዮ-ቴሌኮም ጋር በአጋርነት እንደሚሰራ ተዘግቧል፡፡
“አንዳንድ ግሩም የኢትዮጵያ አጋሮች አሉን፡፡ በጣም ግዙፍ የሆነ  ገበያ እንዳለ ይሰማናል፤ በዚህ ሥፍራ ስኬት ለመቀዳጀት ደግሞ የበለፀገ አገር በቀልና ባህላዊ ዕውቀት ይዘው ከሚመጡ የኢትዮጵያ ኩባንያዎች ጋር በቅርበት መስራት ይኖርብናል” ሲሉም አክለዋል ሚ/ር ቡድሃባቲ  በቃለ ምልልሳቸው፡፡ በአሸባሪው ህወሃት የሚፈጸመው የሰብዓዊ ድጋፍ በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ የማግኘት ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አመለከተ።
ጽህፈት ቤቱ ባወጣው መግለጫ፤የኢትዮጵያ መንግስት አርሶ አደሩ እንዲያርስና የሰብዓዊ ድጋፍ እንዲቀላጠፍ በማሰብ የተናጠል የተኩስ አቁም ማድረጉን ተከትሎ፣ የአሸባሪው ህወሃት ትርፍራፊዎች የሰብዓዊ ድጋፍ ሂደቱን ችግር ውስጥ እንደከተቱት አስታውቋል፡፡
የተናጠል የተኩስ አቁም ውሳኔው ከተላለፈበትና የአገር መከላከያ ሰራዊት ከመቀሌና ሌሎች የክልሉ ከተሞች እንዲወጡ ከተደረገበት ከሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም በፊት በነበረው ሁኔታ የብሔራዊ የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ ኮሚቴ በሶስት ዙር የሰብዓዊ ድጋፍ ሲያደርግ እንደነበር አስታውሷል።
ከዚያ በተጨማሪም ለስርጭት የተዘጋጀ 400 ሺህ ኩንታል ስንዴ እና 2 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሊትር የምግብ ዘይት ተከማችቶ እንደነበር ገልጿል። 14 ሚሊዮን ሊትር ነዳጅም ህዝቡ እንዲጠቀምበት በሚል በክልሉ ዲፖዎች ውስጥ ተከማችቶ እንደነበር ጠቅሷል።
አጋሮችና አለም ዓቀፍ ለጋሽ ድርጅቶች በክልሉ ድጋፍ ማድረግ እንዲችሉ ምቹ ሁኔታ በመንግስት መፈጠሩን ያወሳው መግለጫው፤ መንግስት አሁንም ቢሆን ለህዝቡ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽ እንዲሆን የብሔራዊ ደህንነትን ለአደጋ በማያጋልጥ መንገድ በቁርጠኝነት እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ጠቁሟል፡፡
ከአዲስ አበባ ተነስተው እንዲሁም ወደ አዲስ አበባ ተመልሰው እንዲያርፉ በማድረግ የተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ በረራ ፈቃድ መሰጠቱን የጠቀሰው መግለጫው፤ በአዲስ አበባ በኩል የማለፍ ቅድመ ሁኔታ የተቀመጠው የማይጣስና የሚከበረውን የአገር ደህንነትን ለመጠበቅ በማሰብ እንደሆነ አመልክቷል። ባለፈው ሳምንት የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሁለት በረራ ማድረጉንም አስታውሷል። በከባድ መኪና የሰብአዊ ድጋፉ በአፋር ክልል በኩል እንዲጓጓዝ እየተደረገ መሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ መዘግየትን ለማስቀረትና የተቀላጠፈ የፍተሻ ስራ እንዲከናወን ለማድረግም ጥረቶች እንዳሉ ጠቅሷል።
ከቀናት በፊት የሰብዓዊ ድጋፍ ከሰመራ አባላ መስመር ሲያጓጉዙ የነበሩ መኪናዎች ላይ በአሸባሪው ህወሃት አማካኝነት የተፈጸመውን ጥቃት ያወገዘው መግለጫው፤ በቡድኑ አማካኝነት እየተፈጸመ ያለው የሰብዓዊ ድጋፍን በማደናቀፍ የፖለቲካ ትርፍ ለማግኘት የሚደረገው ጥረት በዓለም ዓቀፉ ማህበረሰብ ሊወገዝ እንደሚገባው አሳስቧል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት ከአጋሮች ጋር ያለመታከት እየሰራ እንደሚገኝ ገልጾ፤ ምግብና መድሃኒት ለሚያስፈልጋቸው ሰዎች ተደራሽ እንዲሆን እንደሚሰራም አረጋግጧል። ከሰብዓዊ ድጋፍ ሰጪዎች ጋርም በትብብር መስራቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል።

   ጀርመናዊው ኡዌ (ባንተን) ሸፈር፤ ድምፃዊ፤ ጊታር ተጫዋችና የሩት ሮክ ሬጌ ሙዚቃ አርቲስት ነው፡፡ ለመጀመርያ ጊዜ ማይክ የጨበጠው በ19 ዓመቱ ሲሆን “ባንተን” የሚለውን ቅፅል ስም ያወጡለት የሙያ ባልደረቦቹ የጃማይካ ሙዚቀኞች ናቸው፡፡ በስነግጥም የተካነ የሙዚቃ አጫዋች ወይም ዲጄ መሆኑን በማድነቅ ነው ቅፅል ስሙን የሰጡት፡፡ ኡዌ "FREE YOUR MIND" በሚል ስያሜ አዲስ  አልበሙን  ከወር በፊት ለዓለም ገበያ አቅርቧል፡፡ ሙዚቃዎቹ የተሰሩት ሶስቱን አህጉራት አፍሪካ፤ አሜሪካና አውሮፓን በማካለል ሲሆን በተለይ ኮስታሪካ፤ ኢትዮጵያ፤ ጀርመን፤ ጃማይካና ደቡብ አፍሪካ ላይ ቀረፃዎች ተከናውነዋል፡፡ ከሰላሳ በላይ ሙዚቀኞችና ከስምንት የተለያዩ አገራት ተሳትፈውበታል፡፡ በጀርመንና በአውሮፓ ስሙ የናኘው የሬጌ አሳታሚ ጋንጃማን የአልበሙን ሚክሲንግና ማስተሪንግ የሰራው ሲሆን በዲጂታል የሙዚቃ አውታሮችና በሲዲ አሳትሞ ለዓለም ገበያ ያቀረበው ደግሞ ራስታ ያርድ ሬከርድስ ነው፡፡
‹‹ፍሪ ዩር ማይንድ›› ለኡዌ አራተኛ የሙዚቃ አልበሙ ሲሆን የመጨረሻ አልበሙን “ሜንታል ዋር” ካሳተመ ከ9 ዓመታት በኋላ ለገበያ የቀረበ ነው፡፡ ዘፈኖቹ በእንግሊዘኛ፤ በጀርመንኛ፤ በፓቶዋ እና በአማርኛ ዜማዎች መቀንቀናቸው አልበሙን ልዩ ያደርገዋል፡፡ አብረውት የሰሩት ድምፃውያን የበርሊኑ ጋንጃማን፤ የኢትዮጵያው ራስ ጃኒ እንዲሁም የደቡብ አፍሪካው አፍሪካ ሴሌ ናቸው፡፡
አርቲስቱ በመላው አውሮፓ በተለይ ጀርመን ውስጥ በሬጌ ሙዚቃ ስሙ የገነነ ሲሆን በካሬቢያን ቅኝት የተሟሹት ዜማዎቹ፤ ጥልቅ እሳቤ ያላቸው ስንኞቹና ምርጥ የሙዚቃ ቅንብሮቹ ተወዳጅነትን አትርፈውለታል፡፡ በአዲስ አልበሙ “ፍሪ ዩር ማይንድ” ላይ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት (Ark of the covenant) በሚል ርእስ ሁለት ሙዚቃዎችን በሬጌ እና ደብ  ስልቶች፣ ከታዋቂው የኢትዮጵያ ሬጌ ሙዚቀኛ ራስ ዮሃንስ (ራስ ጃኒ) ጋር በመጣመር ሰርቷቸዋል፡፡ ኡዌ ባንተን ከሚኖርበት የጀርመን ከተማ ቢሌፌልድ ከግሩም ሠይፉ ጋር ተከታዩን አጭር ቃለ ምልልስ አድርጓል፡፡ እነሆ፡-


                  ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን መጎብኘትህ በቅርቡ ላሳተምከው አዲስ አልበም አስተዋጽኦ አድርጓል?
አዎም አይደለምም፡፡ አዎ፤ ምክንያቱም ለእኔ ወደ ኢትዮጵያ ለመጀመርያ ጊዜ መምጣቴ ነበር፡፡ ጉብኝቱ ለእኔ በጣም ትልቅ ትርጉም ያለውና የመጀመርያውን ተሞክሮ ያገኘሁበት ነበር፡፡ ጉዞው የረዥም ጊዜ ምኞቴና እቅዴ ስለነበር ጉዞውን እንዳሳካ  የባረከኝን ልዑል እግዚአብሔርን  አመሰግነዋለሁ፡፡  እምነቴን ይበልጥ ጠንካራ እንዲሆን አድርጎታል።
አይደለም ስል ደግሞ ዋናው ምክንያት ስለ ኢትዮጵያ ያለኝን አመለካከትና ትርጉም ጉብኝቱ አልቀየረውም፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ከመምጣቴ በፊት ሁሉንም ነገር ለብዙ ዓመታት ስማረውና ሳጠናው ነው የኖርኩት። የሆነ ሆኖ፣ ኢትዮጵያውያንን እንዲሁም በኢትዮጵያ የሚገኙ የራስታ ማህበረሰቦችን በአካል ለመገናኘት መቻሌን እንደ በረከት እቆጥረዋለሁ፡፡ ከሁሉም  ጋር በግንባር መወያየትና መማማር መቻሌ ፍፁም አስደሳች ነበር፡፡ ቀደም ብዬ እንደተናገርኩት፣ የኢትዮጵያ ጉብኝቴ በእምነት እንድጠነክር አድርጎኛል፡፡ እናም የአምላክ ፈቃድ ከሆነ፣ በቅርቡ እንደገና እንደምመጣ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት የሰራኸው ሙዚቃና የፃፍካቸው ግጥሞች እጅግ አስደማሚ ናቸው፡፡ ለመሆኑ ሀሳቡ ከየት ነው የመነጨው? ለዓለምስ ምንድነው ፋይዳው?
የቃል ኪዳኑ ታቦት ለመጀመሪያ ጊዜ በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ ካነበብኩበት ጊዜ አንስቶ በአእምሮዬና በተመስጦዬ ውስጥ የቆየ ጉዳይ ነበር፡፡ ከ27 ዓመታት በፊት “ክብረ ነገስት” የተሰኘውን መፅሐፍ የጀርመንኛ ትርጉም ማንበቤም ሌላው ምክንያት ነው። በክብረ ነገስት ላይ የቃል ኪዳኑ ታቦት ወደ ኢትዮጵያ እንዴት እንደመጣ ያነበብኩት ታሪክ ሁሌም ያስደንቀኛል፡፡ ምንም እንኳን ለኢትዮጵያዊ ማንነት፣ ታሪክና ባህል ማዕከላዊ ሚና ቢጫወትም፣ እስከ ዛሬ ድረስ ለአብዛኛው የአለም ክፍል ምስጢር ሆኖ ቆይቷል፡፡ አሁን አሁን የምንኖረው በአንድ ወቅት ተሰውሮ የነበረው ነገር ሁሉ ወደ ብርሃን በሚወጣበት ዘመን ላይ ነው፡፡ የሰው ልጅ በቴክኖሎጂ አማካኝነት ከመቼውም ጊዜ በበለጠ በዓለም ዙሪያ ያለውን ግንኙነት የሚያፋጥንባቸውን መንገዶች ፈጥሯል። ይህ ለበጎም ለክፉም ዓላማዎች ሊውል ይችላል፡፡ እውቀትና ጥሩ መልእክቶች በፍጥነት እንደሚሰራጩበት ሁሉ ለፖለቲካ ግጭት አደገኛ መቀስቀሻም ሊሆን ይችላል። በዚህ ውጥንቅጥ መሃል የእግዚአብሔር መልእክትና የሰው ልጅ መዳን ወደ አራቱ የዓለም ማዕዘናት መዳረሱን አስፈላጊ ሆኖ አግኝቼዋለሁ፡፡ ሰዎች ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ሲያውቁና በክብረ ነገስት ወደ ኢትዮጵያ የደረሰበትን ታሪክ ሲረዱ፣ አሥርቱን የእግዚአብሔር ትእዛዛት እውነተኛ ባህሪ እንዲገነዘቡ ሊረዳቸው ይችላል፡፡
በዘፈኖችህ ውስጥ ኢትዮጵያን ደጋግመህ ጠቅሰሃል፡፡ በዓለም የሬጌ ሙዚቃ ውስጥ ኢትዮጵያ ያላት ሚና እንዴት ይገለጻል?
በራስ ታፋሪያኖች እምነት፣ በሬጌ ሙዚቃ ልዩ መልእክት፣ ኢትዮጵያ ሁልጊዜም ጉልህ ሚና ትጫወታለች፡፡ መነሻው በጃማይካ፣ በካሪቢያንና በአሜሪካ ውስጥ ቢሆንም፤  በትራንስ አትላንቲክ የባሪያ ንግድ ወቅት  ወደ ምዕራቡ ዓለም የተጋዙት አፍሪካውያን ያመጡት ውጤት ነው፡፡ በብዙዎች ዘንድ እንደ ነቢይ የሚቆጠረው ማርከስ ጋርቬይ ወደ አፍሪካ እንድንመለከትና  በተከበረው አፍሪካዊ ማንነት ላይም አፅንዖት ሰጥቶ አስተምሯል፡፡ ኢትዮጵያ በፋሺስት ወራሪዎች ጥቃት ሲሰነዘርባት በምዕራቡ ዓለም የሚገኙ ብዙ አፍሪካውያን ኢትዮጵያን ዳግም ነፃ ለማውጣት በተደረገው ትግል ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴን ይደግፉ ነበር፡፡ ከጦርነቱ በኋላ ተወዳጁ ንጉስ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ባደረጉት ጥረት፣ ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት መቀመጫ እንዲሁም ከተባበሩት መንግስታት መስራቾች አንዷ ሆናለች፡፡ ይህ ሁሉ ባለፉት ዓመታት በሰው ልጆች ለፍትህና ለእኩልነት የሚደረግ ዓለም አቀፍ ትግል ጠንካራ ተምሳሌትና ምልክት ሆኗል፡፡ እና አሁን በዓለም ዙሪያ በሬጌ ሙዚቃ ተወዳጅነት ሳቢያ ብዙ ሰዎች ስለ ኢትዮጵያና ስለ ኢትዮጵያ ታሪክም ግንዛቤ እያገኙ መጥተዋል፡፡
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር እንዴት አብራችሁ ልትሰሩ ቻላችሁ?
ከራስ ጃኒ (ራስ ዮሐንስ) ጋር የተገናኘነው በአዲስ አበባው ጥሩ ጓደኛዬ ራስ ሳም አማካኝነት ነው፡፡ ከሁለት ዓመት በፊት ኢትዮጵያን በጎበኘሁበት ወቅት ከራስ ሳም ጋር የተዋወቅሁ ሲሆን፤ ከዛም በኋላ ወደ አውሮፓ በዛው ክረምት ላይ መጥቶ የሙዚቃ ስራዎቼን ባቀረብኩበት የሬጌ ጃም ፌስቲቫል ላይ  ተገናኝተን ብዙ ተጫውተናል፡፡
 በወቅቱ ስለ ቃል ኪዳኑ ታቦት ስለሰራሁት ዘፈኔ ለራስ ሳም ስነግረው፣ ኢትዮጵያዊ አርቲስት በአማርኛ ቋንቋ የዘፈኑን ታሪክ እንዲጫወት ማሰቤን ገለፅኩለት፡፡ ይሄን ጊዜ ከራስ ዮሐንስ ጋር እንድሰራው የጠቆመኝ ራስ ሳም ነው፡፡ ራስ ዮሐንስ ዘፈኑንና ሀሳቡን ስለወደደው ወዲያውኑ ስቱዲዮ ገብቶ ቀረፃውን በማከናወን የድርሻውን ተወጥቷል፡፡ ራስ ጃኒ እና ባለቤቱ ኢየሩሳሌም ሀብቴ እጅግ በጣም ግሩምና አፍቃሪ ሰዎች ናቸው፡፡ የሙዚቃውን ቀረፃ እውን ለማድረግ እንዲሁም ለሙዚቃ ቪዲዮው ስራ ቅን ትብብር አድርገዋል፡፡ ከልብ አመሰግናቸዋለሁ፡፡
በመጨረሻ  የምታስተላልፈው መልእክት…
በአንድ ወቅት በታሪክ ውስጥ ተደብቆ የነበረው ነገር ከእንግዲህ እንቆቅልሽ አይደለም፡፡ የዓለም ህዝቦች ለመዳን  ወደ ኢትዮጵያ ይመለከታሉ፡፡ ጠላቶቿ ብዙ ናቸው፣ ግን ልክ ቁራጭ ሻማ በብርሃኗ ጨለማውን እንደምታበራው ኢትዮጵያም እምነቷን ጠብቃ መቀጠል አለባት፡፡ ማንም ሰው ጊዜውን ማቆም አይችልም፡፡ ኢትዮጵያ እጆቿን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች፤ በክፉም ላይ መልካም ድል እንደሚያደርግ እናምናለን። አንድነት ጥንካሬ ነው፡፡ ጸሎታችን ከእናንተ ጋር ነው፡፡ ኢትዮጵያን ዛሬም ለዝንተ ዓለምም እንወዳታለን።


Page 11 of 546