Administrator
ተጓዡ ጋዜጠኛ በሚል ቅፅል ስሙ የሚታወቀው ሄኖክ ስዩም
ባለፉት አስራ ሰባት ዓመታት በኢትዮጵያ ተፈጥሮ ጥበቃ፣ ቅርስ፣ ታሪክ እና ባህል ዙሪያ ሲሰራ የቆየ ኢትዮጵያዊ የጉዞና ጉብኝት ጋዜጠኛ ነው። ከዚህ ቀደም "የመንገድ በረከት"፣ "ጎንደርን ፍለጋ"፣ "ሀገሬን" እና "ወደ ኢትዮጵያ ሰዎች" የተባሉ መጻሕፍትን አሳትሞ ለአንባቢያን አድርሷል።
የተጓዡ ጋዜጠኛ ሄኖክ ስዩም "መንገድ ዐይኑ ይፍሰስ..." የተሰኘ የጉዞ ማስታወሻ መጽሐፍ ገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ የተለያዩ አካባቢዎችን ታሪካዊ፣ ባህላዊና ተፈጥሯዊ ትረካዎች ይዟል።
አዎ ነቢይ በሀገሩ ይከበራል ሠዓሊ እሸቱ ጥሩነህ
የዘላለም ጥግ
የህይወታችን ዓላማ ደስተኛ መሆን
ነው።
ዳላይ ላማ
የምትኖረው አንድ ጊዜ ብቻ ነው፤
በትክክል ከኖርከው ግን አንዱ በቂ ነው።
ማ ዌስት
ገንዘብና ስኬት ሰዎችን አይለውጡም፤
የነበረውን ብቻ ነው የሚያጎሉት።
ዊል ስሚዝ
ስለ ህይወት ለመጻፍ መጀመሪያ አንተ
ራስህ መኖር አለብህ።
ኧርነስት ሄሚንግዌይ
እኔ ትችት እወዳለሁ። ጠንካራ
ያደርግሃል።
ሌብሮን ጄምስ
በእውነቱ እራስህ የምትናገረውን
ከመስማት ብዙም አትማርም።
ጆርጅ ክሉኒ
ህይወት ብስክሌት እንደ መጋለብ ነው።
ሚዛንህን ለመጠበቅ መጓዝህን መቀጠል
አለብህ።
አልበርት አንስታይን
ለህይወት በጣም ጤናማው ምላሽ
ደስተኝነት ነው።
ዴፓክ ቾፕራ
እያንዳንዱ ቅፅበት አዲስ ጅማሮ ነው።
ቲ.ኤስ.ኢሊዮት
ማለም ስታቆም መኖር ታቆማለህ።
ማልኮልም ፎርብስ
‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ›› ሐሙስ ይመረቃል
የተለያዩ ወጎችንና አጫጭር ታሪኮችን በመጻፍ የምትታወቀው ደራሲ ሕይወት እምሻው፤ ‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ›› የተሰኘ የአጫጭር ታሪኮች ስብስብ መጽሐፍ ለተደራሲያን ልታቀርብ ነው።
መጽሐፉ የፊታችን ሐሙስ ሐምሌ 25 ቀን 2016 ዓ.ም. አራት ኪሎ በሚገኘው ኢክላስ ሕንፃ፣ ዋልያ መጽሐፍ መደብር ከምሽቱ 11 ሰዓት ጀምሮ የሥነ ጽሑፍ ባለሙያዎች፣ ደራሲያን፣ የጥበብ አፍቃሪዎችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት ይመረቃል፡፡
‹‹ለእርቃን ሩብ ጉዳይ››፤ 27 አጫጭር ታሪኮች የተካተቱበትና በ208 ገጾች የተቀነበበ ሲሆን፤ በ300 ብር ለገበያ እንደሚቀርብ ታውቋል፡፡
ደራሲዋ ከዚህ ቀደም ‹‹ባርቾ›› ፣ ‹‹ፍቅፋቂ›› እና ‹‹ማታ ማታ›› የተሰኙ የወግና የአጫጭር ታሪኮች መጽሐፍትን ለተደራሲያን ማቅረቧም ይታወሳል፡፡
ኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳን አለማድነቅ አይቻልም!
ባለፈው ሳምንት እኔና ባለቤቴ ልጆቻችንን ይዘን ለጥቂት ቀናት እረፍት ወደ ሃዋሳ ተሻግረን ነበር- ለመዝናናት። እንደሚታወቀው ሃዋሳ ከአገራችን ምርጥ ከተሞች ተጠቃሽ ናት፡፡
አየሯ ምቹ ነው፡፡ ውብ መልክአ ምድር የታደለች ናት፡፡ በሃይቆች ተከባለች፡፡ በዚያ ላይ እንደ ኃይሌ ሪዞርት ዓይነት ባለ 4 ኮከብ ምርጥ ሆቴሎች ታንጸውላታል፡፡ ቢያንስ ሁለት ሆቴሎች እንግዶቻቸውን በመኪና ከአየር ማረፍያ እንደሚቀበሉና እንደሚሸኙ አይተናል፡፡ ሌሎችም ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጡ ሆቴሎች እንደሚኖሩ እንገምታለን፡፡
በዚህች አጭር ማስታወሻዬ፣ እኔና መላው ቤተሰቤ በሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት የቀናት ቆይታችን የገጠመንንና ያስተዋልነውን ለመመስከር እወዳለሁ፤ ሊመሰከርለት ይገባልና፡፡ እርግጥ ነው ሁሉም የኃይሌ ሪዞርቶች በእንግዳ አቀባበላቸውና መስተንግዶአቸው የሚታሙ አይደሉም፤ ይልቁንም ለብዙዎቹ የአገራችን ሆቴሎች በአርአያነት የሚጠቀሱ እንጂ፡፡ ይሄ ደግሞ እንደው በአጋጣሚ የተከሰተ ሳይሆን ብዙ የተለፋበት ነው፡፡ ልብ በሉ፤ ኃይሌ በብቃት የሰለጠኑ የሆቴል ባለሙያዎች በአገሪቱ እንደሌሉ ሲገነዘብ መፍትሄ ነው ብሎ የወሰደው እርምጃ፣ የሆቴል ሙያ ማሰልጠኛ ተቋም መክፈት ነው፡፡ ለዚህ ነው አሁን 10 በሚደርሱ ሪዞርቶቹ ተመሳሳይ (ደረጃውን የጠበቀ) የእንግዳ አቀባበልና መስተንግዶ ማቅረብ የቻለው፡፡ እርግጠኛ ነኝ የራሱን የሰለጠነ ባለሙያ እጥረት ለማሟላት የከፈተው የሆቴል ማሰልጠኛ ተቋሙ፣ የአገርንም የሆቴል ባለሙያ እጥረት ይቀርፋል፡፡ ኃይሌ ሲከፍተውም ለአገርም ጭምር አስቦ እንጂ ለራሱ ሆቴሎች ብቻ እንደማይሆን መገመት ይቻላል፡፡
ወደ ኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ስንመጣ፣ ከህንጻው አሰራርና ህንጻው ካረፈበት መልክአ ምድር ይጀምራል - ውበቱና መለያው፡፡ እያንዳንዱ ነገር በጥንቃቄና በዕውቀት መሰራቱን መመስከር ይቻላል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ለሆቴሉ ሰራተኞች የተሰጣቸው ሥልጠና ቀላል እንዳልሆነ መስተንግዷቸውና አገልግሎት አሰጣጣቸው ይናገራል፡፡
የመስተንግዶ ባለሙያዎቹ ብቻ ሳይሆኑ፣ ጠቅላላ የሆቴሉ ሠራተኞች (የምግብ ዝግጅት ባለሙያዎቹ፣ የእድሳትና ጥገና ሰራተኞቹ፣ ሴኩሪቲዎቹ እንዲሁም ሃውስ ኪፐሮቹና አትክልተኞቹን ጨምሮ) እንግዶችን አይተው በዝምታ አያልፉም፤ ወዳጃዊ የአክብሮት ሰላምታ ይሰጣሉ፡፡ ግራ የገባው ወይም አንዳች ነገር የቸገረው እንግዳ ከገጠማቸው ከመቅጽበት ደርሰው ለመርዳት ይተጋሉ፡፡
በሆቴሉ ቅጥር ግቢ ውስጥ እስካላችሁ ድረስ በፈገግታ የተሞላ የአክብሮት ሠላምታ የማይሰጣችሁ አንድም ሠራተኛ አታገኙም። በዚህም የተነሳ ፈፅሞ ባይተዋርነትና እንግድነት አይሰማችሁም፤ የሆቴሉ እንግዳ ብትሆኑም። ባለፋችሁ ባገደማችሁ ቁጥር ፈገግታና ሰላምታ በሽበሽ ነው፤ በኃይሌ ሪዞርት፡፡ ምግቡም ቢሆን ግሩም ነው፤ ጣዕሙ--ዓይነቱ---መጠኑ አጥጋቢ ነው፡፡
በመስተንግዶው፣ በምግቡ ወይም በመኝታ ክፍል አገልግሎቱ አሊያም በሌላ ቅር ከተሰኛችሁ ደግሞ መፍትሄው ቀላል ነው፤ ከናንተ የሚጠበቀው ቅሬታችሁን ለቅርብ ሃላፊ ማቅረብ ብቻ ነው። አትጠራጠሩ፤ ፈጣን ምላሽ ታገኛላችሁ። ያውም አጥጋቢ ምላሽ፡፡
አሁን ይህችን ማስታወሻ ለመከተብ ሰበብ የሆነኝን አንድ የኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ አስገራሚ ገጠመኝ ላጋራችሁ፡፡ ነገሩ የተከሰተው የመኝታ ክፍላችንን ተከራይተን እንደገባን ነው፡፡ እስካሁንም ድረስ ባላወቅነው ምክንያት (ምናልባት ተዘንግቶ ሊሆን ይችላል) ወደ መኝታ ክፍላችን ስንገባ የተለመደው የእንኳን ደህና መጣችሁ አቀባበል ሳይደረግልን ቀረ፡፡ በሆቴሉ አሰራር መሰረት ወደ ክፍላችን ስንገባ፣ የፍራፍሬ ጭማቂዎች ሊቀርብልን ይገባ ነበር- የእንኳን ደህና መጣችሁ የቤቱ ግብዣ መሆኑ ነው፡፡ በዚህም ሳቢያ ቅሬታችንን በቀጥታ ለሆቴሉ አስተዳደር አቀረብን።
ቅሬታችን ታዲያ እንደ ብዙዎቹ የአገራችን አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ጆሮ ዳባ ልበስ አልተባለም። ወዲያው ነው ምላሽ የተሰጠን፡፡ በሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ የተፃፈና የተፈረመ የይቅርታ ደብዳቤ - የተለያዩ ፍራፍሬዎችን ከተሞላ ቅርጫት ጋር መኝታ ክፍላችን ድረስ መጣልን፡፡ ይቅርታና ካሣ እንደማለት ነው፡፡
ከሆቴሉ ዋና ሥራ አስኪያጅ በእንግሊዝኛ የተፃፈልንን የይቅርታ ደብዳቤ (ለኢትዮጵያውያን በአማርኛ ቢሆን ይመረጥ ነበር) በግርድፉ ተርጉሜ ታነቡት ዘንድ ከዚህ በታች አቅርቤዋለሁ፡፡
በዚህ አጋጣሚ የሃዋሳው ኃይሌ ሪዞርት አስተዳደር፣ ለቅሬታችን ለሰጠን በአክብሮት የተሞላ ፈጣን ምላሽ በራሴና በቤተሰቤ ስም ከልብ ላመሰግንና ላደንቅ እወዳለሁ። ከዚህ በኋላ እኔና ቤተሰቤ፣ ኃይሌ ሪዞርት፣ ቁጥር አንድ ምርጫችን እንደሚሆን ለመግለጽ እወዳለሁ፡፡
በነገራችን ላይ ጀግናው አትሌታችን ኃይሌ ገ/ሥላሴ፣ እንደ ሩጫው ሁሉ፣ በሆቴል ኢንዱስትሪውም ሪከርድ እየሰበረና ታሪክ እየሰራ መሆኑን እያስተዋልን ነው! ለራሱም ለአገሩም፡፡ ሌሎች የአገራችን ሆቴሎችና በአገልግሎት ዘርፉ የተሰማሩ ሁሉ ከኃይሌ ሪዞርት ብዙ ሊማሩ እንደሚችሉ ሳልጠቁም አላልፍም። እነሆ ደብዳቤው፡-
ለውድ ወ/ሮ ሃና ጎሳዬ፡-
በኃይሌ ሪዞርት ሃዋሳ ቡድን ስም፤ ለገጠማችሁ ችግር ልባዊ ይቅርታ ልጠይቅ እወዳለሁ፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለተከሰቱት አጠቃላይ የአቀባበል ክፍተቶች ይቅርታ እንጠይቃለን፤ እርስዎ ከጠበቁን በታች በመሆናችንም በጣም አዝነናል። በመሆኑም፤ ይህ ሁኔታ ዳግም እንደማይከሰት ልናረጋግጥልዎ እንፈልጋለን፡፡
በሁኔታው በእጅጉ እያዘንኩ፤ ይህችን ትንሽዬ የፍራፍሬ ግብዣ ይቀበሉኝ ዘንድ በትህትና እጠይቃለሁ። በሃይሌ ሪዞርት ሀዋሳ ባደረጋችሁት ቆይታ ሊፈጠርባችሁ የሚችለውን የተዛባ ምስል ለማንጻት ላደርግ የምችለው ትንሹ ነገር ይህ ነው።
የዋና ሥራ አስኪያጁ ስምና ፊርማ
ሁሉ ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?
ብላቴን ጌታ ኅሩይ ወልደሥላሴ “ሱካርና ወተት የልጆች ማሳደጊያ።” በሚለው ጽሁፋቸው፤ ስለ አንድ ሽማግሌ ሰውና ስለ አንዲት ልጅ በሚል፤ በመስኮብ የሚነገር አንድ ተረት እንዳለ ይናገራሉ።
በመስኮብ አገር ሦስት ሴቶች ልጆች ያሉት አንድ ሽማግሌ ነበረ። አንዲቱ በመልኳና በጥበብዋ እጅግ ስመ ጥሩ ናት፤ አንድ ቀን ወደ ገበያ ሲወጣ፡-
“ልጆቼ ሆይ፤ ከገበያ ምን ገዝቼላችሁ ልምጣ?” አላቸው። ሁለቱ ልጆቹ “ጌጥ ገዝተህልን ና” አሉት፡፤ አንዲቱ ግን፤ “እኔ ምንም አልፈልግም። ነገር ግን የምመክርህን ምክር ስማኝ” አለችው። ለጊዜው ነገሩ ከበደው፤ ነገር ግን ልጁ እጅግ ብልህ መሆኗን ያውቃልና “እሺ ይሁን ንገሪኝ” አላት። “ወይንማውን በሬ ወደ ገበያ አውጥተህ ስትሸጥ ዋጋ ንገረን ያሉህ እንደሆነ፣ የንጉሡን ግራ አይን አምጡና በሬውን ውሰዱ በላቸው” አለችው።
እርሱም በገበያ ተቀመጠና “የበሬውን ዋጋ ንገር?” ሲሉት፤ ልጁ እንደመከረችው፤
“የንጉሡን ግራ አይን አምጡና ውሰዱት” ይል ጀመረ።
ይህንም ወሬ ንጉሡ ሰሙና፤
“እጁን ይዛችሁ አምጡልኝ!” ብለው አዘዙ።
ሽማግሌውም በቀረበ ጊዜ “ንጉሥ ሆይ፤ እንደዚህ ያደረገችኝ ልጄ ናትና ማሩኝ እያለ ይለምን ጀመረ። ንጉሡም ይህን በሰሙ ጊዜ “ሔደህ ልጅህን አምጣትና እምርሃለሁ” አሉት።
ሽማግሌው እያዘነና እየተንቀጠቀጠ ሄዶ ልጁን ይዞ ወደ ንጉሡ ቀረበ። ንጉሡም ልጅቱን ባዩዋት ጊዜ፤ “ለበሬው ዋጋ የንጉሡን ግራ ዓይን አምጡና ውሰዱ በላቸው ብለሽ ለአባትሽ የመከርሽው ስለምን ነው?” አሏት።
“ንጉሥ ሆይ አልቀጣሽም ብለው ይማሉልኝና እነግርዎታለሁ” አለች።
“አልቀጣሽም!” ብለው ማሉላት።
“ንጉሥ ሆይ፤ ድኃና ጌታ ተጣልተው ወደርሶ የመጡ እንደሆነ በቀኝ የቆመውን ጌታውን ብቻ ያያሉ እንጂ በግራ የቆመውን ድኃውን አያዩም፤ ስለዚህ መቼም ግራ ዓይንዎ ሥራ ካልያዘ ብዬ ነው” አለቻቸው።
ንጉሡም የልጅቱን ንግግር ሰምተው እጅግ አደነቁ። ወዲያውም ወንድ ልጃቸውን ጠርተው “ልጄ ሆይ፤ በመልክና በእውቀት ከርሷ የምትሻል ሴት የለችምና እርሷን አግብተህ መንግሥቴን ይዘህ ኑር” አሉት። ልጁም እርሷን አግብቶ እርሱ ንጉሥ፣ እርሷ ንግሥት ተብለው ኖሩ።
***
በተናገረው ነገር ዕምነት ያለው ብልህ ህዝብና በኃይል የማያምን መሪ፣ ኃላፊና አለቃ ለማግኘት አለመቻል መርገምት ነው። ይህ አለመቻል በተደጋጋሚ ዕውነትነቱ ታይቷል። ይህ እየሆነ እያዩ ምክር አለመቀበል ደግሞ የባሰው አባዜ ነው።
ቮልቴር እንዳለው፡-
የክፉ ገዢ ጦስ፣
ስም ነው ክፉ ጥላ፣ የቀን ሌት መጋኛ
ስም ዕዳ ያለበት
እንቅልፍ አይወስደውም
ቢተኛም ባይተኛ።
አንዳንድ ጊዜ ገዢዎችና መሪዎች የተናገሩት በተግባራዊ ዕውነታ በተጨባጭ ቢፋለስና ቢረክስም እንኳ፤ ጉዳዩን መርምረው በተቃና መንገድ አገርን ፓርቲንና የሥራ ኃላፊነትን ከመምራት ይልቅ እኔ ያልኩት ከሚፈርስ፣ የኔ ዝናና ስም ከሚጎድፍ የቀረው ይቅር ማለት ይቀናቸዋል። ለዚህም ነው አጋጣሚንና ሁኔታዎችን ተገን በማድረግ፣ ለተቃና ጥያቄ፣ የተዛባ መልስ፤ ለቀላል ጥያቄ ውስብስብ ምላሽ፤… መስጠትን እንደ ልዩ ዘዴ መቁጠር የነጋ ጠባ ትዝብታችን እየሆነ የመጣው።
የኢኮኖሚ አቅም ግንባታንም በተመለከተ የዘመቻ ባህል መቀነስ አለበት ሲባል፣ ሲነገር ሲዘከር ኖሯል። የሚሰማ የለም። እንደ እውነቱ ከሆነ ከአንድ ሰሞን ግርግርና ዘራፍ ዘራፍ የተለየ እርምጃ ከሌለ፤ እንደ ጧት ጤዛ መሆን ነው። ጥሞና ያለው፣ ከጀርባው ማናቸውም ዓይነት ጥንስስና እኩይ ዓላማ የሌለው፣ ክንዋኔ ብቻ ነው ወደፊት የመጓዝ መሠረት። ተግባራዊ ጽናቱና ጥረቱ በሌለበት፤ በጀማ፣ በኮሚቴ፣ በሸንጎ ላይ ዲስኩር ማድረግ ብቻ፤ እንኳንስ ትላልቅ ፅንሰ-ሀሳቦችን ማስረፅ አፍአዊ ሂደት ከመሆን አይታለፍም። በየጊዜው አድገናል ተመንድገናል በሚል ዜማ ድግግሞሽ ብቻ የዕውነቱ ብልጽግና አይመጣም። ይብሱንም አንድ አዛውንት፤ “ይህን ሁሉ ያወራህልንን በአይናችን የምናየው ማንኛችን እንሆን? እኛ ነን አንተ?” እንዳሉት እንዳያሰኝ ያሰጋል።
ከቶውንም፤”አልቀጣህም ብለው ይማሉልኝና ዕውነቱን እነግርዎታለሁ” የሚል ህዝብም ሆነ፤ “አልቀጣም!” የሚል የበላይ ባለበት ንፍቀ-ክበብ፤ የዲሞክራሲ አየር እንደማይነፍስ አሌ የሚባል ነገር አይደለም። የምህረት አድራጊና የምህረት ተቀባይ ግንኙነት መኖር የዲሞክራሲ ዋስትና አይሆንም። ይልቁንም የበላይና የበታች፣ የአዛዥና የታዣዥ ቁርኝት ነው። እኔ በነፃነት እናገራለሁ የሚል ህዝብና ነፃነትና መብትህን አከብራለሁ የሚል የበላይ ይኖር ዘንድ ነው የረዥሙ ዘመን ትግል ሁሉ መጠንጠኛ። ይህን የሚገድብ ሁኔታ፣ ማስፈንጠሪያ፣ ለበጣ፣ ትዕዛዝ ወዘተ-- ዛሬም ጊዜያዊ ማስታገሻ እንጂ ዘላቂ ፈውስ አይደሉም።
አጋጣሚን በመጠቀም የሩቅም ሆነ የቅርብ ግላዊ ጥቅምን ለማግኘት መሯሯጤ በህዝብ ዘንድ አይታወቅም ብሎ መገመትም ፍፁም የዋህነት ነው። እንዲህ ያለ ተግባር ከተፈጸመ ግመል ሰርቆ ማጎንበስ ብቻ ሳይሆን፤ ግመሏም እንሽላሊት ናት ብሎ እንደ መሟገት ይሆናል። የህዝብ አደራ እንደ ዩኒቨርሲቲ ማሟያ ኮርስ አይደለም። ስለሆነም የህዝብን አደራ ለግል ህይወት ማሻሻያ፣ ለግል የሩቅ ጊዜ ምኞት ማሳኪያ፤ ለማድረግ መጣር በቀላሉ የማይስተሰረይ ኃጢአት ነው። ያስጠይቃል፤ ያስቀጣል፤ ዋጋ ያስከፍላል። አተርፍ ባይ አጉዳይ ያደርጋል። የገብሬልን መገበሪያ የበላ፤ በገብሬል በገብሬል! ሲል ይገኛል እንዲሉ፤ ብዙም ሳይርቁ መጋለጥ አለ።
እንዲህ ያለው እኩይ ተግባር የህዝቡን የረዥም ጊዜ ግብና የዕድገቱን ዋስትና ያኮላሻል። የህዝብ አደራ የሥልጣን ጥም መወጫ አይደለም። የወንበር ፍቅር ማሞቂያም አይደለም። የግል ዝና ማካበቻ አይሆንም። የፖለቲካ ሽኩቻ ማድሪያ ሊሆንም አይገባም። የጀብደኝነት ወሸነኔም ዘመን አይደለም። የውስጥ-አርበኝነት የበግ ለምድም ሊሆን ከቶ አይችልም። የህዝብ አደራ የዳተኝነትና የዐድር ባይነት መሸፈኛም አይደለምና፣ አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱን መገንዘብ ያስፈልጋል።
መቼም ቢሆን መቼ የህዝብ አደራ በግልጽ፣ የህዝብን ጥቅም ማስከበሪያ ኃላፊነት ነው።
በአግባቡ ካልያዙት፣ ዙፋኑን ካገኘ በኋላ የሚይዝ የሚጨብጠውን አጥቶ “ምነው ይሄን ዘውድ የሰጡኝ ዕለት ማጥለቂያ እራስ ባይኖረኝ ኖሮ?” እንዳለው ንጉሥ መፀፀቻ ይሆናል። በአንጻሩ መደረግ የሚገባውን ነገር በጥሞና ማስተዋል፣ የሂደትና ክንዋኔውን የወደፊት ችግሮችና እንቅፋቶች ከወዲሁ መለየት ያሻል። ምክንያቱም በተነሱት ግላዊ ጉዳዮች ላይ ልብና ልቦናን ከተከሉና ጥቅምን ብቻ ላሳድድ ካሉ፤ እንደ ንጉሱ ከግራና ከቀኝ ላሉ ወገኖች አድሏዊ መሆን አይቀርምና፤ “ግራ ዐይንዎ ስራ አልያዘም ብዬ ነው” ብሎ እሚያሳይ ሰው መኖር አለበት። “ሁሉም ፈረስ ላይ ልውጣ ካለ፣ ገደሉን ማን ሊያሳይ ነው?” ማለትም ይኼው ነው።
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚ/ር ኢትዮጵያና ሶማሊያ ድርድር አላካሄዱም አሉ
የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትብብር ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም ፋቂ ኢትዮጵያና ሶማሊያ ከሁለት ወራት በፊት በቱርክ አመቻችነት ድርድር አላካሄዱም ሲሉ ተናገሩ፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት ባለፈው ረቡዕ ሃምሌ 17 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በኳታር ዶሃ የሶማሊያ ዲያስፖራ ኮንፈረንስ ከተጠናቀቀ በኋላ፣ “አል አረቢ አል ጃዲድ” ከተሰኘ የዜና አውታር ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ነው።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድር አላካሄድንም። ነገር ግን እነርሱ አሁን እያደረጉ ካሉት አደገኛ አካሄድ እንዲመለሱ የሚያሳምን ንግግር ነው በእኛ በኩል የተደረገው። ከሶማሌላንድ ጋር ያደረጉትን ስምምነት እንዲያቋርጡ ነግረናቸዋል፡፡” ብለዋል፤ ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ።
“ከኢትዮጵያ ጋር ድርድሮች አልተደረጉም። ያደረግናቸው ውይይቶችም እንደ ድርድር የሚቆጠሩ አይደሉም” ነው ያሉት አህመድ፡፡
በኢትዮጵያና ሶማሌላንድ መካከል የተደረገውን ስምምነት “ሕገ ወጥ” ሲሉ ያጣጣሉት የሶማሊያው ሚኒስትር፤ “ኢትዮጵያ ወራሪ አገር ነች። መሬታችንንና አገራችንን ማስከበር አለብን። ስምምነታቸው ሕገ ወጥ በመሆኑ፣ መሬት ላይ መተግበር የለበትም” ሲሉም በሃይለቃል ተናግረዋል፡፡
ሚኒስትሩ ለዜና አውታሩ፣ ሁለቱ አገራት ድርድር አላደረጉም ቢሉም፤ ከወራት በፊት የሶማሊያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፣ ኢትዮጵያና ሶማሊያ በቱርክ ድርድር እንደሚያደርጉ የሚገልጽ መረጃ በቀድሞው ትዊተር (ኤክስ) ገጹ ላይ አስፍሮ ነበር። ይህን መረጃ ግን ብዙም ሳይቆይ ከገጹ ያስወገደው ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ በምትኩ “የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በቱርክ አደራዳሪነት ለሚደረገው ንግግር አንካራ ገብተዋል” ሲል መግለጹ አይዘነጋም፡፡
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ ቀደም ብለው ወደ ቱርክ አቅንተው የነበር ሲሆን፣ የሶማሊያው አቻቸው እርሳቸውን ተከትለው መግባታቸው በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በቱርክ ዋና ከተማ አንካራ የተካሄደውን ይህን ውይይት ተከትሎም፣ የሶማሊያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አሕመድ ሞአሊም፣ አገራቱ ልዩነታቸውን በሰላማዊ ንግግር ለመፍታት መስማማታቸውን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያና ሶማሊያ “በሁለቱም ወገን ተቀባይነት ባለው ማዕቀፍ” ልዩነታቸውን ለመፍታት ሁለተኛውን ዙር ድርድር፣ በፈረንጆቹ አቆጣጠር መስከረም 2 ቀን 2024 ዓ.ም በአንካራ ለማድረግ ስምምነት ላይ መድረሳቸውንም ነበር፣ የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሃካን ፊዳን የገለጹት።
እ.ኤ.አ. በ2011 ፕሬዚዳንት ረሲፕ ጣይብ ኤርዶጋን ሞቃዲሾን መጎብኘታቸውን ተከትሎ፣ የጸጥታ ሃይሎች በማሰልጠንና የልማት ዕርዳታዎችን በማቅረብ ቱርክ፣ የሶማሊያ መንግስት የቅርብ አጋር ሆናለች። ኢትዮጵያና ሶማሌላንድ ከስምምነት ላይ ከደረሱ ከወር በኋላም፣ ቱርክና ሶማሊያ የ10 ዓመት የወታደራዊ ስምምነት መፈራረማቸው የሚታወስ ነው።
"አዘቦት"
የዩንቨርሲቲ ተማሪ ነው፣ አዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ ይጽፋል፣ ሞጋች ነው፣ የውይይት ባሕሉ ድንቅ ነው፣ መጻሕፍት ቆንጆ አድርጎ መተንተን ያውቅበታል፣ ምልከታውን እወድለታለሁ...ሌላም ሌላም! አሁን ደግሞ "አዘቦት" የተሰኘ የአጭል አጭር ታሪኮችን/Post card stories ይዞልን ቀርቧል።
የት ማግኘት እንችላለን? ቢሉ በእጅ ስልክዎ፥ #afro read app የሞባይል መተግበሪያ ላይ በ50 ብር ብቻ ሸምተው ማንበብ ይቻላል!
Sirak Wondemu ን በሀሳብ አግዙት፤ አንብቡለትም፤ በሀሳብ የሚያምን ትሁት ወንድማችን ነው፤ ዕድሜው ከእኔ ብዙ ቢያንስም ስራዎቹ ትልቅ እንደሆኑ እመሰክራለሁ፤ በእኔ ይሁንባችሁ አንብቡት ትወዱታላችሁ! ሰሞኑን በሰፊው እመለሳለሁ።
መልካም ዕድል ለታናሽ ወንድማችን!
“ናዋዥ” የተሰኘ አዲስ መፅሐፍ ለንባብ በቃ
በደራሲ እያዩ ዳኛው የተሰናዳውና “ናዋዥ” የተሰኘው አዲስ የግለ ታሪክ መፅሐፍ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ መፅሐፉ በዋናነት በደራሲው የግል ህይወት ላይ የሚያጠነጥን ቢሆንም፤ ኢትዮጵያዊያን በሱዳንና በሊቢያ በኩል ወደ አውሮፓ ለመግባት የሚያደርጉትን አስከፊና አስቸጋሪ የስደት ህይወት የሚያሳይ ነው ተብሏል፡፡
ነዋሪነቱን በጀርመን ያደረገው ደራሲ እያዩ ዳኛው፤ መፅሐፉ ከደቡብ ጎንደር ክምር ድንጋይ እስከ ጣሊያን የወደብ ከተማ ትራፓኒ የዘለቀውን የስደትና የውጣ ውረድ ጉዞ የሚዳስስ መሆኑን ለአዲስ አድማስ ተናግሯል፡፡
“ናዋዥ”፤ደራሲው ልጅነቱን የአፍላ ወጣትነቱን፣ የኢትዮጵያውያንን የስደት ኑሮ፣ በሱዳንና በሰሃራ በረሃ ለማቋረጥ ስደተኞች የሚከፍሉትን መስዋዕትነት እንዲሁም በመንግሥት አልባዋ ሊቢያ የነበረውን ኑሮና በሜድትራንያን ባህር የሚያጋጥምን ፈተና ያስቃኛል፡፡
በ470 ገፅ የተቀነበበው “ናዋዥ”፤ የግለ ታሪክ መፅሐፍ በ500 ብር ለገበያ ቀርቧል፡፡
የሌሊሳ ግርማ “ደማቆቹ” በገበያ ላይ ዋለ
የዓለማችንን ምርጥና ስመጥር የአጭር ልብወለድ ድርሰቶችን ትርጉም የያዘው “ደማቆቹ“ የተሰኘ መድበል በገበያ ላይ ውሏል፡፡ መጽሐፉ ከአሥራ አራት በላይ ደራስያንን ሥራዎች ያካተተ ሲሆን፤ ከእነዚህም ውስጥ አርነስት ሄሚንግዌይ፣ አየን ራንድ፣ ገብርኤል ጋርሺያ ማርኩዌዝ፣ አንቷን ቼኮቭ፣ ናጂብ ማህፉዝ፣ ማርጋሬት አትዉድና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡
በ254 ገጾች የተቀነበበው መድበሉ፤ አሥራ ስድስት የተለያዩ ርዝመት ያላቸውን የገናና ደራስያን ሥራዎች ያካተተ ነው፡፡ “ደማቆቹ” የተሰኘውን መድበል በዋናነት የሚያከፋፍለው የጃፋር መጻሕፍት መደብር ሲሆን፤ በ400 ብር ለገበያ እንደቀረበ ለማወቅ ተችሏል፡፡
የዚህ መጽሐፍ ተርጓሚ ከዚህ ቀደም “የንፋስ ህልምና ሌሎች ታሪኮች”፣ “አፍሮጋዳ” ፣ “መሬት-አየር-ሰማይ”፣ “የሰከረ እውነታ”፣ “እስቲ ሙዚቃ”፣ “ነጸብራቅ” እና “ይመስላል ዘላለም” በሚሉ የአጭር ልብወለድና የመጣጥፍ ስብስብ ሥራዎቹ በአንባቢያን ዘንድ ይታወቃል፡፡
ደራሲ ሌሊሳ ግርማ፤ ላለፉት ረዥም ዓመታት፣ በአዲስ አድማስ ጋዜጣ ላይ አጭር ልብወለዶችንና ወጎችን በአምደኝነት በመጻፍም የሚታወቅ ትጉህ የብዕር ሰው ነው፡፡