Administrator

Administrator

 “በጎ ፈቃደኝነት ድንበር፣ ወሰንና ዘር አያውቅም”



        ነገርን ከሥሩ ውሃን ከምንጩ እንዲሉ፣ በጎ ፈቃደኝነት ምንድን ነው? እንዴትስ ይገለጻል? በሚለው መሰረታዊ  ጥያቄ  የዛሬ ርዕሰ ጉዳያችንን  እንጀምር፡፡ እርግጥ ነው በጎ ፈቃደኝነት ለኢትዮጵያውያን አዲስ ጉዳይ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በአገራቸው ብቻ ሳይሆን ባህር ማዶ ጭምር ተሻግረው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ፈጽመዋል፡፡ ኮንጎና ኮሪያ ድረስ ዘምተው ዓለማቀፍ የበጎ ፈቃድ ተግባር  ተወጥተዋል፡፡
 በሌላ በኩል፣ በጎ ፈቃደኝነት ወይም በጎ አድራጎት የሚል መደበኛ ስም አይሰጠው እንጂ፣ በዕለት ተዕለት ህይወታችንም  ቢሆን  አንዱ ለሌላው በጎ እያደረገ ነው እዚህ የደረስነው፡፡ ሆኖም ዘመናዊነትና ግላዊነት ባሳደሩብን አሉታዊ ተጽዕኖ ሳቢያ፣ ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ  ይህ ቱባ  እሴታችን እየተሸረሸረ መጥቷል፡፡ ለዚህም ነው ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ በመንግስት ደረጃ ጭምር፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ላይ ትኩረት ተደርጎ ሥራ  የተጀመረው፡፡ በእኒህ ዓመታት በተለይ በመዲናዋ የተከናወኑ የበጎ ፈቃድ ተግባራትን መቃኘት የዚህ ጽሁፍ ዓቢይ ዓላማ ነው፡፡   
ከዚያ በፊት ግን መነሻችን ላይ ያነሳነውን መሰረታዊ  ጥያቄ አስቀድመን እንመልስ፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ምንድን ነው? እንዴትስ ይገለጻል? በጎ ፈቃደኝነት የራስን ጊዜ፣ አቅምና ችሎታ ወይም ሃብትና ክህሎት ሌላውን  ለማገዝ ወይም ሸክሙን ለማቅለል  የማዋል ተግባር ነው - በምላሹ ምንም ዓይነት ክፍያና ጥቅም ሳይፈልጉ፡፡ በሌላ አነጋገር፣ ለማህበረሰብ ወይም ለአገር በፈቃደኝነት ነጻ አገልግሎት መስጠት ብንለውም ያስኬዳል፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ዋና ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ በበኩላቸው፤ “በጎ ፈቃደኝነት ማለት ሁሉም ሰው በራሱ ተነሳሽነትና ፍላጎት፣ ያለማንም አስገዳጅነት፣ በነጻ ፍላጎት ላይ ተመስርቶ፣ ያለምንም ክፍያ የሚሰጠው አገልግሎት ነው፡፡” ይላሉ፡፡ አክለውም፤ “በጎ ፈቃደኝነት ለሰዎች ጊዜህን፣ ገንዘብህንና ጉልበትህን በመስጠት ዘላቂ የሆነ የመንፈስ እርካታ የምታገኝበትና አብሮነትና ትብብርን ለማዳበር የሚያግዝ ተግባር ነው፡፡” በማለት ይገልጹታል፡፡
ከለውጡ ማግስት ጀምሮ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በጠ/ሚኒስትር ዐቢይ መሃመድ ፊት አውራሪነት እየተለመደና እየተስፋፋ የመጣ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅትም በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎችን የሚያሳትፍ ዘርፍ ሆኗል፡፡ በተለይ በመዲናዋ  ልዩ ትኩረት ተሰጥቶት ተቋማዊ በሆነ አሰራር እየተተገበረ ነው፡፡ በቅርቡ ይህንኑ ዘርፍ የሚመራ ተቋም በኮሚሽን ደረጃ ተዋቅሮ ወደ ሥራ መግባቱ ይታወቃል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን ዋና ተግባሩ ይሄው ነው፡፡
በነገራችን ላይ በዓለም  ላይ ለረዥም ዘመናት የዘለቀ ጠንካራ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል ያላቸው በርካታ አገራት ይገኛሉ፡፡ እነ አሜሪካ፣ ካናዳ፣ አውስትራሊያ፣ እንግሊዝ፣ ኔዘርላንድና ስዊድን ይጠቀሳሉ፡፡ በወጉ የዳበረና የበለጸገ የበጎ ፈቃደኝነት ባህል እንዳላት በሚነገርላት አሜሪካ፣ በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች  በተለያዩ የማህበረሰብ አገልግሎቶች ውስጥ  በንቃት እንደሚሳተፉ መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡ እኒህ  አገራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎታቸውን ከራሳቸው አልፈው  ለሌሎችም ማድረስና ማዳረስ  ማዳረስ ችለዋል፤ ድንበር እየተሻገሩ፡፡  
በጎ ፈቃደኝነት ሌላው  ባህርይው - ወሰን፣ ድንበርና ዘር የማይገድበው መሆኑ ነው፡፡ የሰው ልጅ በመሆናችን ብቻ የተቸረን ጸጋ ነው፡፡ ስለዚህም የሰው ልጆች ባሉበት ሁሉ ይተገበራል፡፡ ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ያለ ልዩነት የሚሳተፍበት ዘርፍም ነው፡፡ ከሕጻናት እስከ አረጋውያን፣ ከሊቅ እስከ ደቂቅ---ሁሉንም ያሳትፋል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት እርዳታ አይደለም፤ ይልቁንም የፍቅርና አጋርነት መገለጫ ነው፡፡
መረጃዎች እንደሚጠቁሙት፤ ባለፉት አምስት ዓመታት፣ በመዲናዋ፣ በሰብአዊ፣ ማህበራዊና ሌሎች መርሃ ግብሮች አማካኝነት 22.7 ቢሊዮን ብር የሚገመት  የመንግስት ወጪ መሸፈን ተችሏል፡፡ በእኒህ ፕሮግራሞች በየዓመቱ በአማካይ ከ2 ሚሊዮን በላይ በጎ ፈቃደኞች የተሳተፉ ሲሆን፤ 900ሺህ ገደማ ነዋሪዎችም  ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡
በአዲስ አበባ የሚከናወኑ  የበጎ ፈቃድ ተግባራት ዘርፈ ብዙ ናቸው፡፡ በተለይ በክረምት ወራት  የአቅመ ደካሞችና  አዛውንቶች  ቤትን  የማደስና የመገንባት ተግባር እየተስፋፋና እየተለመደ  መምጣቱን አለመመስከር ንፉግነት ነው፡፡ የዛሬ አምስት አመት ገደማ ጠ/ሚኒስትሩ የአንዲት አረጋዊት ቤት በማደስ ሀ ብለው ያስጀመሩት የበጎ ፈቃድ እንቅስቃሴ፣ ዛሬ ተስፋፍቶና ተጠናክሮ  በአቧሬና አካባቢዋ  አጀብ የሚያሰኝ ውጤት አስመዝግቧል፡፡ የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት በተጨባጭ  ለውጧል፡፡ በአካባቢው ባለ አስራ ሁለት ወለል የመኖሪያ  ሕንጻዎች ተገንብተዋል፡፡ የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቱ ታዲያ በአቧሬ ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡  ልደታ አካባቢ “የበጎነት መንደር” ተመስርቷል - በበጎ ፈቃድ አገልግሎት፡፡ በተመሳሳይ .በአራዳ፣ በቂርቆስ፣ በቦሌ፣ በየካ፣ በለሚ ኩራ፣ በንፋስ ስልክ፣ በኮልፌ፣ በአዲስ ከተማና በሌሎችም ...የአቅመ ደካማዎችና አረጋውያንን ቤቶች  የማደስና የመገንባት ተግባራት በስፋት ተከናውነዋል፡፡
በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች፣ ማዕድ ማጋራትም፣ ሌላው በስፋት እየተለመደ የመጣ የበጎ አድራጎት ተግባር  ነው፡፡  በዚህ ዓመት ብቻ ከ1.1 ሚሊዮን በላይ ለሚሆኑ ነዋሪዎች  ማዕድ የማጋራት ተግባር ተከናውኗል፡፡ በገንዘብ ሲሰላ ከ3.5 ቢሊዮን ብር በላይ የሚገመት ነው፡፡
የአዲስ አበባ አስተዳደር “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሰው” እና “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ህፃን” በሚል በጀመራቸው መርሃ ግብሮች ቁጥራቸው ቀላል የማይባል አረጋውያንና ህጻናትን መደገፍ ተችሏል፡፡ የአዲስ አበባ አስተዳደር የህብረተሰብ ተሳትፎና በጎ ፈቃድ ማስተባበሪያ ኮሚሽን፣ ዋና ኮሚሽነር አቶ አብርሃም ታደሰ እንደሚናገሩት፤ ”ባለፈው ዓመት ከ24 ሺህ 500 በላይ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ በዚህ ትስስር ተቆራኝተው፣ ትናንት ለአገር ውለታ የከፈሉ አዛውንቶችን  እያገዙና  እየደገፉ ነው፡፡ ለአብነት ያህል፡- ”ታፍ ኢትዮጵያ“ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው አርባ እናቶችን፣ ለሁለት ዓመት፣ በየወሩ አራት ሺህ ብር እየሰጠ በመደገፍ ላይ ይገኛል፡፡” ብለዋል፡፡
 “አንድ ቤተሰብ ለአንድ ሕጻን” በሚል መርሃ ግብርም፣ አንድ ባለሃብት 100 ሕጻናትን ከጨቅላነት እስከ ዩኒቨርስቲ ድረስ ለማስተማር መረከቡን የኮሚሽኑ ሃላፊ ገልጸዋል፡፡ ነገሩ እንዲህ ነው፡፡ ባለሃብቱ መቶ ሕጻናትን ከእናቶቻቸው ሳይለዩ በየወሩ 3 ሺህ 500 ብር በመስጠት በእንክብካቤ ያድጋሉ፡፡ በባለሃብቱ ድጋፉ እስከ ዩኒቨርስቲ ትምህርት ድረስ የሚዘልቅ ነው፡፡ በተመሳሳይም 430 የሚሆኑ ሕጻናት በየክፍለ ከተማው እንዲሁ ድጋፍ እየተደረገላቸው ነው - ባለሃብቶች  ህጻናትን እየወሰዱ እያሳደጉ ነው፤ አረጋውያንን እየጦሩ እየደገፉ ነው፡፡
 እኒህ ሁሉ በመዲናዋ እየተካሄዱ ያሉ  የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቶች ናቸው፡፡ ነዋሪዎች በሌላ በኩል በአረንጓዷ አሻራ መርሃ ግብር፣ ችግኝ በመትከል በንቃት ይሳተፋሉ፡፡ በጤናው ዘርፍ ደግሞ ነዋሪዎች ደም በመለገስ ለወገናቸው ይደርሳሉ፡፡ የመንግስትና የግል የጤና ተቋማት፣ እስከ ቀዶ ጥገና የሚደርስ ብዙ ወጪ የሚጠይቅ  ነጻ የህክምና አገልግሎት እየሰጡ ይገኛሉ፡፡
ከዚህ አንጻር በመዲናዋ የሚከናወኑ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት ድርብርብ የሆነ ትርፍ እንዳላቸው የሚናገሩት አቶ አብርሃም፤  የበጎ ፈቃደኝነት ተግባር የሃብት  ክፍፍልን በማረጋገጥ ረገድ ትልቅ ሚና እንደሚጫወት ይገልጻሉ፡፡  ከዚህ ሌላ “ትልቁ ሃብት” የሚባለው የወጣቶች ሰብዕና ግንባታ ላይ ያመጣው ለውጥ ነው ባይ ናቸው። ”ወጣቶች ለአካባቢያቸው፤ ለማሕበረሰባቸውና ለአገራቸው በነጻ መስራትና ማገልገል ሲለምዱ፣ አገር ወዳድ ትውልድ ይፈጠራል።” ብለዋል፡፡
የበጎ ፈቃደኝነት ትሩፋቶች ተቆጥረው አያልቁም፡፡  በነዋሪዎች መሃል የአንድነትና የትብብር ስሜት በመፍጠር የማህበረሰብ ግንኙነትን ያጠናክራል፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ሙያዊ ዕድገትን ያዳብራል፡፡ በጎ ፈቃደኞች  በበጎ አድራጎት ተግባራት ሲሳተፉ፣ እግረ መንገዳቸውን አዳዲስ ክህሎቶችና ልምዶችን ይቀስማሉ፡፡ ይሄ ብቻ ግን አይደለም፡፡ በጎ ፈቃደኝነት ማህበራዊ ግንኙነትንም ያሰፋል፡፡ አዳዲስ ሰዎችን ለመተዋወቅ፣ ወዳጅነትን ለመመስረትና ማህበራዊ ትስስርን ለማስፋት ዕድሎችን ይፈጥራል፡፡ አስገራሚ ቢመስልም በጎ ፈቃደኝነት የጤና ትሩፋቶችም አሉት፡፡ ጥናቶች እንደሚጠቁሙት፣ በጎ ፈቃደኝነት ውጥረትን በመቀነስ፣ ድባቴን በማስወገድና በአጠቃላይ የመንፈስ እርካታና  የደስታ ስሜትን በመጨመር የአዕምሮ ጤንነትን ያሻሽላል፡፡
መንግሥት በተደጋጋሚ እንደሚለው፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ በአገራችን እንደ ባህል እንዲዳብርና ጥቂቶች ብቻ ሳይሆኑ በርካታ ሚሊዮኖች የሚሳተፉበት ተግባር  ይሆን ዘንድ፣ በጽንሰ ሃሳቡ ዙሪያ ትርጉም ያለው  የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ ማከናወን ተገቢ ነው፡፡ በዚህ ረገድ የአዲስ አበባ አስተዳደር፣ በየጊዜው የተለያዩ የግንዛቤ ማስጨበጥና ማስረጽ ተግባራትን እያከናወነ  ይገኛል፡፡  
በጎ ፈቃደኝነት፤ የማህበረሰብ አንድነትንና ትብብርን እንዲሁም ማህበረሰባዊ ለውጥን ለማምጣት ትልቅ መሳሪያ ነው፡፡ ትሩፋቱ ለብዙሃን የሚዳረስ ነው፡፡ በድፍን አገር ላይ  አዎንታዊ ተጽዕኖ ይፈጥራል፡፡
ባለፉት ጥቂት  ዓመታት፣ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት፣ ከሌሎች የአገሪቱ አካባቢዎች በተሻለ መጠንና ፍጥነት  በመዲናዋ  እየተስፋፋ መጥቷል፡፡ ሌሎች የክልል መንግስታትና የከተማ አስተዳደሮችም የመዲናዋን አርአያነት በመከተል የበጎ ፈቃድ  አገልግሎትን ለማስፋፋትና ለማዳበር እየተጉ ይገኛሉ፡፡  
በመዲናችንም ሆነ በመላው አገሪቱ  የበጎ ፈቃደኝነት ጥረቶችንና ጅምሮችን በማበረታታትና በመደገፍ፣ ጠንካራና አይበገሬ ማህበረሰቦችን መገንባት እንዲሁም ለሁሉም  የምትመች ኢትዮጵያን መፍጠር የሁላችንም ሃላፊነት ነው፡፡ ክረምቱ ስኬታማ የበጎ ፈቃደኝነት ተግባራት የሚከናወንበት ይሁን!!

ከእለታት አንድ ቀን፣ አንዲት ወፍ፣ አንድ ባህር አጠገብ፣ ጎጆዋን መስራት ትፈልጋለች፡፡ ጥሩ ቦታ ስትፈልግ ቆይታ በገደል አፋፍ ላይ አንድ ጥላ ያለው ጎድጎድ ያለ ቦታ ታገኛለች፡፡ እዚህ ቦታ ጎጆዬን ብሰራ በደንብ የተከለለና ከአደጋ የተሰወረ ይሆናል ብሎ ወሰነች፡፡ ሳርም፣ ቄጤማም አምጥታ ጎጆዋን አሳምራ ሰራች፡፡ እሷ ጎጆዋን ስታሳምር ባህሩ በፀጥታ፣ ቀስ በቀስ ዳርቻውን አልፎ ወደ ገደሉ አፋፍ እየመጣ ነበር፡፡ ወደ ገደሉ ደርሶ ከጠርዙ ጋር እየተላተመ መመለስ ጀመረ፡፡ ውሎ አድሮም ወፏ ጎጆ ጋ ደረሰና፣ ጥርግርግ አድርጎ ወሰደባት፡፡ ወፊቱ እየጮኸች ክንፏን እያራገበችና በንዴት እያጨበጨበች ወደ ሰማይ በረረች፡፡ ከላይ ሆናም ጎጆዋ ባህር ውስጥ ገብቶ ሲፈራርስ ተመለከተች፡፡


 “እንዴት እንዲህ ትደፍረኛለህ? እንዴት ዋናውን መቀመጫ ቤቴን ታፈርሳለህ? ስገነባው አላየህም? ምን ያህል ጊዜና ጉልበት እንደወሰደብኝስ ሳታውቅ ቀርተህ ነው?” እያለች ጮኸች፡፡
ሆኖም ባህሩ ምንም መልስ አልሰጣትም፡፡ እንደተለመደው ገደሉ አፋፍ ድረስ እየመጣ ተመልሶ ወደ ቦታው ይመለሳል፡፡ ወፊቱም “ቆይ ሳልሰራልህ ብቀር!” ብላ ከበረረችበት ወደ መሬት ወርዳ፣ በኩምቢዋ ጥቂት ውሃ ጨልፋ ወስዳ፣ ሜዳው ሳር ላይ ትተፋለች፡፡ እንደገናም ትመጣና ሌላ ውሃ ጨልፋ ትወስዳለች፣ እሳሩ ላይም ትደፋለች፡፡ “በዚህ ሁኔታ ቀኑን ሙሉ እየተመላለስኩ ውሃውን ብወስድበት ባዶ አደርገዋለሁ” ብላ አስባ ነው፡፡ ሆኖም ከጥቂት ጊዜ በኋላ ደከማት፡፡ ውሃውን መጨለፏን ግን አላቋረጠችም፡፡ ምክንያቱም እበቀለዋለሁ ብላ ቆርጣ ተነስታለችና ነው፡፡ ያልተገነዘበችው ነገር ቢኖር ምንም ያህል ውሃ እየቀዳች ብትወስድ፣ ባህሩን ልታጎድለው አለመቻሏን ነው፡፡ ውሃ እንደቀድሞው እየመጣ ማዕበሉም ከዳርቻው ጋር በሃይል እየተላተመ ይመለሳል፡፡ ወፏ ወደ ሞት እስከምትቃረብ ድረስ ለፍታ ለፍታ ደከማትና፣ አንድ ቋጥኝ ላይ ተቀምጣ አረፍ እንዳለች፣ አንድ ሌላ ትልቅ ወፍ ወደ እሷ ይመጣል፡፡ መጤው ወፍም፤ “ወፊት ሆይ! እስካሁን ስትሰሪ የነበረውን ነገር ሁሉ ራቅ ብዬ ስመለከት ነበር፡፡ ምን ለማድረግ እየሞከርሽ እንደሆነ ገብቶኛል፡፡ ግን አንድ ምክር እንድሰጥሽ ትፈቅጂልኛሽ?” አላት፡፡ የደከማት ወፍ መልስ ለመስጠት እንኳን አቅም አልነበራትም፡፡ ስለዚህም እንግዳው ወፍ ቀጠለ፡፡ “በቀል የደካማ በትር ነው፡፡ አቅምሽን ሁሉ በበቀል ላይ መጨረስ አያዋጣሽም፡፡ ራስሽን ተመልከቺ፡፡ ከጊዜ ጊዜ እየደቀቅሽ፣ እየተመናመንሽ እየሄድሽ ነው፡፡ ምን ተጠቀምሽ? ባህሩ እንደሆን ምንጊዜም ባህር ነው፡፡ ምንጊዜም ውሃ አለው፡፡ ምንጊዜም እንደሞላ ነው፡፡ ምን ጊዜም ጠንካራ ነው፡፡ ስለሆነም ልበቀለው ብለሽ የፈለግሽውን ያህል ብትፍጨረጨሪ ከንቱ ድካም ነው፡፡ ይልቅ አቅምና ጉልበትሽን በሚጠቅም ነገር ላይ አውይው፡፡ አስቢበት፡፡” ብሏት በረረ፡፡ ወፊቱ ቋጥኙ ላይ ተቀምጣ ድካሟን እያስታመመች ብዙ ካሰበች በኋላ፣ ቀጥሎ የምትሰራውን ወሰነች፡፡ ከዚያ ተነስታ ከባህሩ ዳርቻ ራቅ ብሎ፣ ለጎጆ መስሪያ አመቺ ቦታ መረጠች፡፡ ሳርና ቅጠል እየሰበሰበች እንደገና አዋቅራ አዲስ ጎጆ ሰራች፡፡ ቀጥላም፤ “እንግዳው ወፍ የነገረኝ እውነት ነው፡፡ አቅምና ጉልበቴን ጠቃሚ ነገር ላይ ባውለው ይሻላል፡፡ በቀል የደካማ በትር ነው፡፡ ትላንት የሰራሁትን ስህተት እንዳይ ያደርገኛል” አለች፡፡
        ***
በቀል በማንኛውም መልኩ ቢሆን የጥፋት ዝርያ ነው፡፡ ከማይቋቋሙት ባላጋራ ጋር መቀያየም፣ አልፎም ለበቀል መነሳት ትርፉ ፀፀት ነው፡፡ ጨልፈው የማይጨርሱትን ባህር ቀድቼ ባዶ አደርገዋለሁ ብሎ ማሰብ ከንቱ ቅዥት ነው፡፡ በቀል ለትውልድ ቂም ማኖር እንጂ የሀገርን አብራክ አያለመልምም፡፡ የህዝቧንም ተቀራርቦ ተስማምቶና ተቻችሎ የመኖር ተስፋ አይጠቁምም፡፡ ይልቁንም አድሮ ይቆጠቁጣል፡፡ የእንግሊዙ ገጣሚና ደራሲ ጆን ሚልተን ይህንኑ በግጥም ሲገልጽ፣ “ምን መጀመሪያ ቢጣፍጥ፣ በቀልም እንደማር ቢጥምም፣ ብዙ ሳይቆይ መምረሩ አይቀር፣ ዞሮ በራስ ሲጠመጠም፡፡” እንዳለው ሁሉ፣ ዛሬ በሌላው የምንወስደው እርምጃ፣ ነገ በእኛው ላይ የሚያነጣጥር በቀል-መላሽ ትውልድ እንደ መፈልፈል ነው፡፡ የሀገራችን እውቅ ገጣሚ መንግሥቱ ለማ፤ “… ማን ያውቃል እንዳለው ለድንጋይስ ቋንቋ፣ ዛፍ ለሚቆረጥ ዛፍ፣ እንዳለው ጠበቃ…” ያሉትም የዚሁ የበቀል መንፈስ ሌላው ገፅታ ምን እንደሆነ ሲጠቁሙ ነው፡፡ በፖለቲካ ፓርቲ፣ በድርጅት፣ በማህበር፣ በመስሪያ ቤት፣ በግለሰብ ወዘተ ላይ ወይም መካከል የሚደረግ የበቀል እንቅስቃሴ፣ “በቀልን የመረጠ የራሱን ቁስል እንዳስመረቀዘ ይኖራል” እንዳለው ፍራንሲስ ቤከን፣ ነገ የሚያቆጠቁጥና የሚቆጠቁጥ የትውልድ ህመም፤ ታሪካዊ ተውሳክ መትከል ነው፡፡ መቼም ይፈፀም መቼ፣ ማንም ይፈፅመው ማን ህዝብ ባህር ነው፡፡ የበቀል እርምጃ ሲወሰድ ዞሮ ዞሮ ህዝቡ የሀገሩ ባለቤት ነውና፣ በትዝብት ዐይን አስተውሎ በታሪክ ማህደር ጽፎ፣ አጥፊውን መጠየቁ አይቀሬ ነው፡፡ ኢፍትሐዊም ነውና በህግ መሟገቱ ሳይታለም የተፈታ ነው፡፡ ነፃነቴ ተነካ ሲል ሰብዓዊ መብቱ፣ መብቴ ተደፈረ ሲል ለዲሞክራሲያዊ መብቱ መቆሙ አይቀርም፡፡ ከቶውንም በየጊዜው የሚነገሩም ሆነ የሚተገበሩ የህግ የበላይነት አከባበር፣ አፈርሳታ፣ አውጫጪኝ፣ አዲስ አወቃቀር፣ ተሐድሶ፣ አዲስ አደረጃጀት ምልመላ፣ አሮጌ ጠላ በአዲስ ጋን፣ አሮጌ ሰው በአዲስ ጠበል ወዘተ… እያልን ላይ ታች የምንልባቸው ጉዳዮች፣ ልባችን ውስጥ የበቀል ቋጠሮ ቋጥረን፣ “ቆይ ሳልሰራልህ ብቀር” “ረዥም እረፍት ሳላስወስድህ ብቀር” እያልን ከሆነ፣ ተጫውቶ ተጫውቶ ቁር ሲሉ፤ “ፉርሽ ትሉኝ” ብሎ ከመጀመሪያው የገበጣ ቤት እንደ መጀመር ይሆናል፡፡ የፈሰሰ ንዋይ፣ የባከነ የስው አዕምሮ፣ የባከነ ጊዜ… የሀገር ሀብት  መሆኑን መዘንጋት በታሪክ ተጠያቂ ያደርጋል፡፡ ያ ሳያንስ ጥፋተኛ ለመፈለግ በወገናዊ መንገድ መሄድና እሱንም በበቀል ቀመር ለማከናወን መጣር፣ ለሀገርና ለህዝብ ጥፋት መደገስ ይሆናል፡፡ ከቶውንም ፓርቲና ፓርቲ፣ የፖለቲካ ድርጅትና የፖለቲካ ድርጀት፣ አለቃና አለቃ፣ አለቃና ምንዝር ለመበቃቀል እቅድ ይዘው ስለመድብለ ፓርቲ፣ ድህነትን ስለመቀነስ ቢያወሩ፣ የትም ፈቀቅ ማለት አይቻልም፡፡
ወደ መተሳሰብ፣ ወደ መወያየት፣ ችግርን ከሀገር አንፃር ወደ መፍታት ሳይጓዙ ክፉ ክፉውን ወደ ማየት መጓዝ፣ ወደ ትንኮሳና አምባጓሮ ማምራት ለእድገት አያበቃም፡፡ ይልቁንም “ለመራመድ ያቃተው እግር፣ ለመርገጥ ሲሉት ይነሳል” እንደሚባለው ይሆናል፡፡

ጊዜያዊ አስተዳደሩ እርምጃ ባለውሰድ ተወቅሷል


         በትግራይ ክልል የሚንቀሳቀሱ አራት ተቃዋሚ ፓርቲዎች፣ በትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሱ የፆታ ጥቃቶች በአስቸኳይ እንዲገቱና የመፍትሔ እርምጃ እንዲወሰድባቸው ጠይቀዋል። ፓርቲዎቹ ባለፈው ሰኞ ሰኔ 17 ቀን 2016 ዓ.ም. መቐለ ከተማ በሚገኘው የሳልሳይ ወያነ ፓርቲ ጽሕፈት ቤት በሰጡት የጋራ መግለጫ፤ በክልሉ በሴቶች ላይ የሚፈፀሙ ጥቃቶች መነሻቸው ሥርዓተ አልበኝነት ነው ብለዋል።
ጋዜጣዊ መግለጫውን በጋራ የሰጡት አረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ፣ ሳልሳይ ወያነ፣ ባይቶና እና የትግራይ ነጻነት ፓርቲ (ውናት) ናቸው።
 “ትግራይ በአሁኑ ሰዓት የመንግስት አልባነት ሁኔታ ገጥሟታል ያሉት የአረና ትግራይ ለሉዓላዊነትና ለዴሞክራሲ ፓርቲ ሊቀመንበር አቶ አምዶም ገብረስላሴ፤  በተለያዩ የክልሉ አካባቢዎች በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ እገታዎች፣ ግድያዎችና ጾታዊ ጥቃቶች የተበራከቱበትን ምክንያት ዘርዝረዋል።
እገታ እንደ አንድ የገቢ ማግኛ ዘዴ ማገልገሉ አንደኛው ምክንያት መሆኑን  ያነሱት አቶ አምዶም፤ በዚህም የተነሳ የወንጀል ድርጊቱን ለመፈጸም የተደራጁ ቡድኖች፣ ታዳጊና ወጣት ሴቶችን በማገት ረብጣ ብር እንደሚጠይቁ ተናግረዋል። “እነዚህ ቡድኖች በክልሉ የፖሊስ ኮሚሽነሮችና ሌሎች ባለስልጣናት ከለላ እየተሰጣቸው  ወንጀሉን ይፈጽማሉ፤ ፍትሕ ስለማይሰጥ ተጎጂዎች ስጋት ውስጥ ይገባሉ” ሲሉም ለጋዜጠኞች አስረድተዋል፡፡
 የባይቶና ፓርቲ ሊቀ መንበር  አቶ ክብሮም በርሄ በበኩላቸው፤ “በጠቅላላ ከሕግና ስርዓት ውጪ የሆኑ አሰቃቂ ድርጊቶችን በሴቶች ላይ የሚፈጽሙ ሃይሎች ተፈጥረዋል። እነዚህ ሃይሎች ደግሞ ህወሓት ያደራጃቸው ቡድኖች ናቸው። ስለዚህም እኒህን ቡድኖች ለማውገዝ ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተጠራው” ብለዋል።
አክለውም ሲያስረዱ፤ “የወንጀል ድርጊቶቹ ከፖሊስ ምክትል ኮሚሽነሩ ጋር የተያያዙ ናቸው፡፡ ፖሊስ ክስ አቅርቦ፣ እንዳይመረምር ተደርጓል። ምክንያቱም ከእነዚህ የወንጀል ድርጊቶች መካከል አንደኛውን የፈጸመው የምክትል ኮሚሽነሩ  ልጅ ነው። በአጠቃላይ በህወሓት ተመርጠው፣ በጊዜያዊ አስተዳደሩ የተሾሙ ሃላፊዎችም በጉዳዩ ተሳታፊ ናቸው።” በማለት  ከስሰዋል፡፡ ፡
የሴቶች ተገድዶ መደፈርና መገደል የአራቱም ፓርቲዎች “ቀይ መስመር” መሆኑን የገለጹት አቶ ክብሮም፤ የፓርቲዎቹ ዓላማ ለጥቃት ተጋላጭ የሆኑ ሴቶች ለመብታቸው እንዲቆሙ መቀስቀስ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  “ከወንጀል ድርጊቶቹ ጋር በተያያዘ የታሰሩት ዋናዎቹ ሳይሆኑ ሌሎች ሰዎች ናቸው። ነገሩ የይስሙላ ነው። ባደረግነው ጥናት መሰረት፤ ይሄ ተራ ሰዎች የሚፈጽሙት ወንጀል አይደለም። ታጋቾቹን ሆቴል ውስጥ በማስቀመጥ፣ ከታጋች ቤተሰቦች ጋር የዋጋ ድርድር ይደረጋል።  ከዛም ብሩ ወደ አጋቾቹ አካውንት ይገባል። ካልሆነ ደግሞ ትኬትና መታወቂያ ለታጋቾቹ ተዘጋጅቶ ወደ አዲስ አበባ ይላካሉ” ሲሉ የወንጀል ድርጊቱ ሂደት ምን እንደሚመስል በጥቂቱ አብራርተዋል፤ አቶ ክብሮም።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ “የስርዓተ አልበኞች አስተዳደር ሆኗል” ሲሉ የወቀሱት አቶ ክብሮም፤ “ህወሓት ፖለቲካው አልሆንለት ሲለው ክልሉን ወደ ማመስ፣ ወደ መዝረፍና የወንጀል ቡድኖችን ወደ ማደራጀት ገብቷል፡፡” ብለዋል።
የፓርቲዎቹ የወደፊት ዕቅድ ሰላማዊ ሰልፍ በመጥራት፣ ጉዳዩ የበለጠ ትኩረት እንዲያገኝ መስራት መሆኑን የባይቶና ሊቀ መንበር ጠቁመዋል፤ በፆታዊ ጥቃት ዙሪያ ሌሎች እንቅስቃሴዎችንም እንደሚያደርጉ በማከል፡፡
በተያያዘ ዜና፣ ባለፈው ማክሰኞ ሰኔ 18 ቀን 2016 ዓ.ም. በመቐለ ከተማ በሺዎች የሚቆጠሩ ሴቶች፤ “መንግስት ጸጥታን ያስከብር”፣ “ፍትህ ለትግራይ ሴቶች”፣ “ፆታ ተኮር ጥቃት ይቁም” በማለት የተቃውሞ ሰልፍ አካሂደዋል፡፡ በቅርቡ ታፍነው የተወሰዱና የተገደሉ ሁለት እንስት የጥቃት ሰለባዎችን ስም በመጥራትም፣ ተቃውሟቸውን አሰምተዋል። ከችግሩ ጋር በተያያዘ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር እርምጃ ለመውሰድ ቸልተኝነት አሳይቷል ሲሉም ወቅሰዋል።
ለሴት ሰልፈኞቹ ምላሽ የሰጡት፣ የትግራይ ክልል ፍትሕ ቢሮ ሃላፊ አቶ ሓዱሽ ተስፋ፤ በክልሉ በተለይ በሴቶች ላይ አሰቃቂና በጭካኔ የተሞሉ ያልተለመዱ ጥቃቶች መበራከታቸውን ገልፀው መንግስት ችግሩን ለመፍታት እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

 “ጎረቤትህ ሲታማ ለእኔ ብለህ ስማ”


          ከሰሞኑ በኬንያ የተቀጣጠለው ሕዝባዊ ተቃውሞ አልበረደም። ይህ ተቃውሞ ረቂቅ ዓዋጅን ከማሰረዝ አንስቶ የተጓዘባቸው ሂደቶች አነጋጋሪ ሆነዋል። ለተቃውሞው መቀስቀስ እንደ አጣዳፊ ምክንያት የሚጠቀሰው፣ ለኬንያ ምክር ቤት የቀረበው የፋይናንስ ረቂቅ ዓዋጅ ሲሆን፤ በሂደት ግን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ተሸጋግሯል። ተቃዋሚዎች ፕሬዚዳንት ዊሊያም ሩቶ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቀዋል።
እንደቢቢሲ ዘገባ ከሆነ፤ መንግስት ገቢውን በማሳደግ አገሪቱ የተከማቸባትን ከ80 ቢ.ብር በላይ የውጭ ዕዳ ለመቀነስ በሚል ዳቦን ጨምሮ በምግብ ዘይት፣ በሴቶች የንጽህና መጠበቂያ፣ በሞባይል ስልኮች፣ በኮምፒውተሮች፣ በተሽከርካሪዎችና በሌሎች ምርቶችና አገልግሎቶች ላይ የቀረጥ ጭማሪን ያካተተ ረቂቅ የፋይናንስ ሕግ አዘጋጅቶ ለፓርላማ እንዲፀድቅ አቀረበ። ሕጉ በተለያዩ የማሕበራዊ ትስስር ገጾች ላይ ተሰራጭቶ ከጫፍ እስከ ጫፍ ተቃውሞን ጫረ። ይሁንና ተቃውሞው የኬንያ የሕዝብ እንደራሴዎችን ቀልብ ሊስብ አልቻለም። ነገሩ ያበገናቸው ኬንያውያን ሰኔ 11 ቀን 2016 ዓ.ም. አደባባዩን በሰላማዊ ሰልፍ ባረኩት። ሰላማዊ ሰልፉ የዋዛ አልነበረም፤ ‘ፓርላማውን እንቆጣጠር - “Occupy The parliament” በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀ ነበር።
አገሪቷ የነሱ ብቻ አይደለችም። የሁላችንም ናት። ስልጣን የህዝብ ነው። ፓርላማውን ተቆጣጥረን፣ የሕዝብ ተወካዮች የኬንያ ሕዝብ የሚለውን እንዲሰሙ እናደርጋቸዋለን” አለ-በተደጋጋሚ መንግስትን በድፍረት በመቃወም የሚታወቀው ቦኒፈስ ምዋንጊ፣ ለሰልፍ ከመውጣቱ በፊት። ዜጎች ወደ አደባባይ ተመሙ። የኬንያን ሰንደቅ ዓላማና የተለያዩ መፈክሮችን ይዘው የወጡ ተቃዋሚዎች እየዘፈኑ፣ እየጨፈሩ ነበር- ወደ ፓርላማው ያመሩት።
ተቃውሟቸው ወዲያውኑ ፍሬ አላፈራም!
የምክር ቤቱን አብላጫ ወንበር የተቆጣጠረው፣ የፕሬዚዳንት ዊልያም ሩቶ ፓርቲ የምክር ቤት አባላት 195 የድጋፍ ድምፃቸውን የሰጡ ሲሆን፣ በ106 ተቃውሞ ረቂቅ ዓዋጁ ፀደቀ። ይሄኔ ወጣቶች የሚበዛበት ኬንያ ተቃዋሚዎች፣ ከምክር ቤቱ አዳራሽ ውጭ ሆነው የተቃውሞ ድምጹን ያሰማ ያዘ፤ ሰሚ ቢያጣም ቅሉ።
የተቃውሞ እንቅስቃሴው በሰላማዊ ሂደቱ ግን አልቀጠለም፤ ከፖሊስ ጋር ፍጥጫው ጠንክሮ ነበር። ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝና ውሃ መርጨት ብቻ ሳይሆን ጥይትም መተኮስ ጀመረ። ፖሊስ ሊቆጣጠረው ባልቻለው ሁኔታ ወጣቶቹ ጥብቅ ቁጥጥር የሚደረግበት የፓርላማ በሮች ገነጣጥለው ወደ ውስጥ ገቡ። ። መስኮቶች ተሰባበሩ። የፓርላማው ሕንጻም እሳት ተለኮሰበት።
የተቆጡ ወጣቶች ፓርላማውን ጥሰው ሲገቡ፣ ተቃውሞ የቀረበበትን ሕግ ያጸደቁትን የፓርላማ አባላት ከአዳራሹ ለማስወጣት ሄሊኮፕተር አንዣበበች። ፖሊስም በምላሹ ጥይት ተኮሰ። በርካታ አስከሬኖችም በጎዳናዎች ላይ ታዩ። በሰላማዊ መንገድ የተጀመረው የኬንያውያን ተቃውሞ ወደ ሁካታ ተለወጠ።
የኬንያው ዋነኛ ተቃዋሚና የአዚሚዮ ጥምረትን የሚመሩት ራይላ ኦዲንጋ፣ መንግስት “በአገራችን ልጆች ላይ ጭካኔ የተሞላበት የሃይል በትሩን እየሰነዘረ ነው” ሲሉ ነቀፉ። በኬንያ የተፈጸመውን ያልተጠበቀ  የዜጎች ግድያ ተከትሎ፣ የትዊተር ገጽ ለሰዓታት ተቋረጠ፣ ኢንተርኔት ተጨናጎለ፣ ዩቲዩብ ቀጥ አለ።
ኢንተርኔት ከመዘጋቱ በተጨማሪ የግል ንብረት የሆነው ኬቲኤን ቴሌቪዥን ጣቢያ፣ በተቃውሞ ዘገባው ምክንያት፣ ከመንግስት ‘እዘጋችኋለሁ’ የሚል ማስፈራሪያ እንደደረሰው አስታወቀ።
ነገሮች ጦዙ፤ ከረሩም!
ተቃውሞው በመዲናዋ ብቻ ሳይሆን የሩቶ የትውልድ ስፍራ የሆነችው የጊሹ ግዛትን ጨምሮ፤ በኪሱሙ፣ ሞምባሳ ወዘተ ተቀጣጠለ- ከአገሪቷ 47 ግዛቶች ውስጥ በ35ቱ ተቃውሞው ተስፋፋ።
በኬንያ የፓርላማውን በር ጥሰው በገቡ ተቃዋሚ ወጣቶች ላይ ብቻ ሳይሆን፣ በሌሎች ከተሞችም በዜጎች ላይ ግድያዎች ተፈጽመዋል። አንዳንድ የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች፣ የሟቾችን ቁጥር ከ20 በላይ አድርሰውታል።
በኬንያ ሕይወትን የቀጠፈና አገሪቱን ያመሳቀለው አወዛጋቢ የፋይናንስ ሕግ ምንጩ፣ ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) ነው ተብሏል። IMF ኬንያ በአሁኑ ጊዜ ያለባትን 80 ቢሊዮን ዶላር የሚጠጋ ብሔራዊ ዕዳን ለመቀነስ፣ የተለያዩ ግብሮችን መጣል እንዳለባት ምክሩን መለገሱ ተጠቁሟል። ተቋሙ በተለይ በአፍሪካ አገራት ጥሩ ስም እንደሌለው ሲታወቅ፣ ተረኛዋ ኬንያ በዜጎቿ በኩል በመንግሥት ላይ ብቻ ሳይሆን ኬንያን በእጅ አዙር እየጠመዘዟት ነው ባሏቸው ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትም ላይ ተቃውሟቸውን እየገለጹ ነው።
ሩቶ በዚያው የተቃውሞ ዕለት ማምሻውን በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ፣ መንግስታቸው “ሁከትና ስርዓት አልበኝነት” ሲሉ የጠቀሷቸው ድርጊቶች ላይ ጠንከር ያለ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠነቀቁ። ከሰዓታት በኋላም የአገሪቱ የመከላከያ ሚኒስትር የአገሪቱ ሰራዊት እንዲሰማራ ትዕዛዝ መስጠታቸው ተሰማ። ሆኖም ተቃውሞውን አላረገበውም።
በማግስቱ ረቡዕ ግን ፕሬዚደንት ዊሊያም ሩቶ፣ የተለያዩ ታክሶችን ለመጣል በታቀደው የፋይናንስ ረቂቅ ሕግ ላይ ፊርማቸውን እንደማያኖሩ አስታወቁ።
ረቂቅ ህጉን የኬንያ ህዝብ ስለተቃወመው ውድቅ ተደርጓል አሉ። እንዲያም ሆኖ ግን ዜጎች በደስታ ጮቤ አልረገጡም። ይልቁንስ ሌላ ከባድ ጥያቄ አነሱ- ፕሬዚዳንት ሩቶ ከሥልጣን እንዲወርዱ ጠየቁ።
የኬንያ ተቃውሞ ተምሳሌትነቱ በብዙ መልኩ ሰፊ ነው፤  ነገር ግን አንድ አንጓ አለው። የመንግስት ለሕዝብ ተገዢ መሆን። በሕዝብ ገንዘብና በሕዝብ ድምጽ ስልጣን የተቆናጠጠ አንድ የፖለቲካ ፓርቲ፣ የሕዝቡን ድምጽ ካልሰማ፤ እምቢተኝነት ምሳው፣ ተቃውሞ ራቱ ይሆናል። ልክ እንደ ሰሞኑ ኬንያ ማለት ነው። ግልጽነትን ካጎለበተ፣ አገሪቱን ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ ከመራ ግን ነገሮች ተደላድለው ለዜጎች ምቹ ምሕዳርን ይፈጥራሉ።


* ሌሎች አካባቢዎችም እንደዚሁ ለምተው ለማየት እጓጓለሁ
* እኛ ለቅቀን ስንሄድ አካባቢው ጭልምልም ያለ ነበር
* አዲስ አበባ የእውነትም ”አዲስ አበባ“ ሆናለች



የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማት የተጀመረ ሰሞን ብዙ ቅሬታዎችና ተቃውሞዎች መስተጋባታቸው አይዘነጋም፡፡  ”ታሪካዊ ቅርሶች እየፈረሱ  ነው“ ከሚለው ጀምሮ፣ ”የልማት ተነሺዎች ከመኖሪያቸው እየተፈናቀሉ ነው“ እስከሚለው ድረስ፣ የተለያዩ እውነታ ላይ ያልተመሰረቱና በሃቀኛ የመቆርቆር ስሜት የተንጸባረቁ ድምጾች  ተደምጠዋል፡፡
ይሄ ብቻም አይደለም፡፡  የኮሪደር ልማቱ በሦስት ወር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል የሚለውን የከተማዋን አስተዳደር መግለጫ  በጥርጣሬ የተመለከቱም ቁጥራቸው ቀላል አልነበረም፡፡ አንዳንዶች እንደውም  የኮሪደር ልማቱ ከመጠናቀቁ በፊት ክረምት እንደሚገባና የልማት ሥራው እንደሚስተጓጎል ገምተው  ነበር፡፡ በዚህም የተነሳ ነው  የኮሪደር ልማቱ በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መገባደዱን ሲመለከቱ በእጅጉ የተገረሙት፡፡     

ለነገሩ ቢገረሙም  አይፈረ

ድባቸውም፡፡ ለምን? ቢሉ፣ ለረዥም ዘመን  መንግሥት የገባውን ቃል ባለማክበር ነበር  የሚታወቀው፡፡ አያሌ የልማት ሥራዎችና ፕሮጀክቶች ተጀምረው መሃል ከደረሱ በኋላ ሲቋረጡ ታይተዋል፡፡

በፕሮጀክቶች መጓተት ሳቢያ ህዝብና አገር ለኪሳራ ተዳርገዋል፡፡ በርካታ የመሰረት ድንጋዮች አንቱ በተባሉ የመንግሥት ሃላፊዎች ተጥለው የተረሱበት አጋጣሚም ብዙ ነው፡፡  በአጠቃላይ ፕሮጀክቶችን በተቀመጠላቸው ዕቅድና በተገባላቸው ቃል መሰረት አከናውኖ ማጠናቀቅ ለአገራችን እንግዳ ነበር ማለት ይቻላል፡፡  
በእርግጥ የፕሮጀክቶች ክንውን ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በእጅጉ ተለውጧል፡፡ በለውጡ ማግስት በአዲስ አበባ ብቻ በርካታ ፕሮጀክቶች በአስደናቂ ፍጥነትና የጥራት ደረጃ ተጠናቅቀው ብዙዎችን  አጀብ አሰኝተዋል፡፡ የአዲስ አበባ የኮሪደር ልማትም ከእነዚህ መሰል ክንውኖች አንዱ ነው ቢባል ያስኬዳል፡፡ የፕሮጀክቶች ክንውን እየተለወጠ መምጣቱን ከሚያረጋግጡ የልማት ሥራዎች ተርታ የሚጠቀስም ነው፡፡
የኮሪደር ልማት ተነሺዎች ከመኖሪያ ቀዬአቸው ከመነሳታቸው በፊት ከአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አበቤ ጋር ባደረጉት ውይይት፣ የሚሰራውን የልማት ሥራ በፈለጉ  ጊዜ መጎብኘት እንደሚችሉ ቃል ተገብቶላቸው ነበር፡፡ በዚህም መሰረት ነው ባለፈው ቅዳሜ ሰኔ 8 ቀን 2016 ዓ.ም ከሰዓት በኋላ የከተማ አስተዳደሩ ከፍተኛ ሃላፊዎችና ሌሎች የወረዳ ሃላፊዎች የልማት ተነሺዎችን በቡድን ተከፋፍለው፣ የለሙ የከተማዋን  አካባቢዎች ያስጎበኙት፡፡
በዚህ ጉብኝት ወቅት ነዋሪዎች በሞባይላቸው የለሙ አካባቢዎችን ፎቶ ሲያነሱና እርስ በርስ ሲነሱ፤ እንዲሁም በደስታ ሲያዜሙና  ሲጨፍሩ ተስተውለዋል፡፡ በአጠቃላይ ነዋሪዎቹ ባዩት የልማት ሥራ መደሰታቸውንና መደነቃቸውን ሁለመናቸው ይናገር ነበር፡፡ አስተያየታቸውን የሰጡን ጎብኚዎች የነገሩንም ይሄንኑ መንፈስና ድባብ የሚያረጋግጥ ነው - ደስታንና መደነቅን፡፡  
በዕለተ ቅዳሜው የጉብኝት መርሃግብር፣ የልማት ተነሺ የከተማዋ ነዋሪዎች፣ ከአራት ኪሎ አንስተው እስከ ፒያሳና ቴዎድሮስ አደባባይ ድረስ የለሙ አካባቢዎችን በእግራቸው ተዘዋውረው  ጎብኝተዋል፡፡
እንግሊዝ ኤምባሲ አካባቢ ተወልደው ለ50 ዓመታት ያህል መኖራቸውን የገለጹልን  ወ/ሮ ትዕግስት አዘዘ፤ እነዚህን  የልማት ሥራዎች በመመልከታቸው  በእጅጉ መደሰታቸውን ተናግረዋል፡፡ ጠላ በመሸጥ ሥራ እንደሚተዳደሩ ያወጉን  እኚህ እናት፤ ”አካባቢውን በፊት አውቀው ነበር፤ እንደዚህ ግን አልነበረም“  ይላሉ፡፡ “አሁን በጣም ተለውጧል፤ እንዲህ በመልማቱም ደስተኛ ነኝ፡፡” ሲሉም ወይዘሮ ትዕግስት አስተያየታቸውን ሰንዝረዋል፡፡    
ከየካ ክፍለከተማ፣ ወረዳ 7 የመጡት ወ/ሮ የወይንሸት አለባቸውም እንዲሁ በጉብኝቱ  በተመለከቱት ልማት  መደነቃቸውን  ነው የተናገሩት፡፡
“እኔ ይህን ቦታ ሳውቀው ዝም ብሎ መንደር ነበር፤ መንገዱ ወጣ ገባ የሆነ፣ በሸራ የተከለለ፣ ለዕይታ ደስ የማይሉ ቤቶች የነበሩበት ሥፍራ ነው” ያሉት ወ/ሮ የወይንሸት፤ “አሁን ሳየው አዲስ አበባ ውስጥ ያለሁ ሁሉ አልመስል ነው ያለኝ፤ አዲስ አበባ የእውነትም አዲስ አበባ ሆናለች” ሲሉ አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡
በመዲናዋ ሲኖሩ  ብዙ ልጆች ወልደው ማሳደጋቸውንና የዕድሜያቸውን አጋማሽ ማሳለፋቸውን  የጠቆሙት ወ/ሮ የወይንሸት፤ ያዩት ልማት በተለይ ለልጆቻቸው ብሩህ ተስፋን የሚፈጥር አለኝታ እንደሚሆናቸው  ተናግረዋል፡፡
ለኮሪደር ልማቱ ከመነሳቸው በፊት  ፒያሳ  ዳርማር ተብሎ በሚታወቀው  ፎቅ ላይ ለብዙ ዓመታት መኖራቸውን የነገሩን አቶ ግርማ ገዜ፤ አካባቢው የቆሻሻ መጣያ እንደነበር ያስታውሳሉ፡
“እንደዚያ ቆሻሻ የነበረ አካባቢ እንዲህ ተለውጦ፣ ህይወት ዘርቶ እናየዋለን ብዬ አላሰብኩም ነበር፤ በዓይናችን የተመለከትነው ልማት ለትውልድ የሚተላለፍ ነው“ ሲሉ አስተያየታቸውን  ገልጸዋል፡፡
አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ሲናገሩም፤ ”በአቃቂ ክፍለከተማ አዲስ መኖሪያ  ቤት ተሰጥቶኝ  በደስታ እየኖርኩ ነው“ ብለዋል፤ አቶ ግርማ፡፡   
ለመልሶ ማልማቱ ከፒያሳ ተነስተው  ቃሊቲ አካባቢ መኖሪያ ቤት የተሰጣቸው አቶ ሸቢር አብደላ ደግሞ  በፒያሳ አካባቢ ያዩትን ለውጥ ከቀድሞው ጋር እያነጻጸሩ  በዝርዝር ገልጸውልናል፡፡  
”እኛ ከዚህ ለቅቀን ስንሄድ እንደዚህ አልነበረም፡፡ ያኔ አካባቢው ያስፈራ ነበር--ጨለማ ነው---በነጻነት የምትሄድበት ቦታ አልነበረም ---ቤቶች አሰራራቸው ወጥ አይደለም---ሁሉነገሩ ጭልምልም ያለ ነበር፡፡“ ይላሉ፤ የቀድሞ የፒያሳ አካባቢ ገጽታን ሲያስታውሱ፡፡
አሁንስ? አቶ ሸቢር አሁን ያስተዋሉትን ለውጥ እንዲህ ይገልጹታል፡-
“አሁን ቤቶችና ህንጻዎች እየታደሱ  ነው---ዛፎቹ በጣም ያምራሉ---ጽዶችና አበቦች ተተክለዋል---የእግረኛው መንገድ ሰፍቷል---ብስክሌቶች የሚሄዱበት መንገድ ለብቻው ተሰርቷል---ለሞተር ብስክሌቶች እንዲሁ መንገድ ተሰርቶላቸዋል---አሁን ሁሉ ነገር ጽድት ብሏል---መብራቱ ራሱ ኩልል ብሎ መርፌ ቢወድቅ እንኳን የሚታይበት ሆኗል፡፡”
በጉብኝታችን ያየነው የልማት ሥራ  በእጅጉ የሚያስደንቅና የሚያስደስት ነው ያሉት አቶ ሸቢር አብደላ፤ሌሎች የከተማዋ አካባቢዎችም እንደዚሁ ለምተው ለማየት ጉጉት እንዳላቸው  ተናግረዋል፡፡
 ይሄ ጉጉት የእርሳቸው ብቻ ሳይሆን የሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች  ጉጉት ነው፡፡ ሁሉም አካባቢው እንዲጸዳና እንዲዋብ ይፈልጋል፡፡ሁሉም ኑሮው እንዲሻሻልና እንዲዘምን ይመኛል፡፡ ሁሉም አዲስ አበባ እንደ ስሟ አዲስ አበባ እንድትሆን ይሻል፡፡ ደሞም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ እንኳን አዲስ አበባ መላዋ ኢትዮጵያ መልማቷ አይቀሬ ነው፡፡


  አሸናፊዎች በሚሊዮን ዶላሮች ይንበሸበሻሉ
 
በነዳጅ ሀብቷ የበለጸገችው ሳውዲ አረቢያ፣ ከአንድ ዓመት በፊት ኢ-ስፖርት የዓለም ዋንጫ የሚል አዲስ የስፖርት ውድድር እንደምታዘጋጅ አስታውቃ ነበር፡፡  በየዓመቱ ክረምት ወር ላይ እንደሚካሄድ የተነገረለት አዲሱ ውድድር፤ ቴክኖሎጂዎችን መሰረት ያደረጉ የዓለም ዋንጫ ውድድሮችን ያካትታል፡፡  

ሀገሪቱ ለዋንጫ አሸናፊዎች በአጠቃላይ 60 ሚሊዮን ዶላር የምትሸልም ሲሆን፤ ውድድሩ ከሰኔ 26 ቀን እስከ ነሐሴ 18 ቀን 2016 ዓ.ም ድረስ በሪያድ እንደሚካሄድ ታውቋል፡፡  የሳውዲ አረቢያ ዜና አገልግሎት እንደዘገበው፤ በዚህ የዓለም ዋንጫ ላይ በ21 የውድድር አይነቶች 30 ክለቦችን የወከሉ 1ሺህ 500 ተጫዋቾች ይሳተፋሉ፡፡

ለጨዋታው አሸናፊዎች 33 ሚሊዮን ዶላር፣ በየውድድሩ ኮከብ ለሆኑ ተጫዋቾች 1 ሚሊዮን ዶላር፣ ወደ ቀጣይ ዙር ለሚያልፉ 7 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም ለሌሎች የማጣሪያ ጨዋታ አሸናፊዎች 20 ሚሊዮን ዶላር እንደሚሸለሙ ተነግሯል፡፡  

 በውድድሩ ላይ ከሚሳተፉ መካከል በስፖርት ቴክኖሎጂ ዘርፍ የተሰማሩ ተቋማት፣ የመዝናኛ ፕሮግራም አዘጋጆችና ፈጣሪዎች ይገኙበታል፡፡ አዲዳስ፣ ሶኒ እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የንግድ ኩባንያዎች የውድድሩ ስፖንሰሮች እንደሆኑም ተገልጿል፡፡

ሳውዲ አረቢያ ይህን ውድድር ይፋ ያደረገችው ወደ ሀገሪቱ የሚመጡ ጎብኚዎችን ለመሳብ፣ የ2029 የእስያ ዓመታዊ ውድድሮችን ለማዘጋጀት፣ እንዲሁም  የ2034 ፊፋ ዓለም ዋንጫና ኦሎምፒክ ውድድሮችን ለማስተናገድ በማለም  ነው፡፡

ዓለም አቀፋዊ ማህበር የሆነው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሕክምና ማህበር፣ አርቲስት ትዕግሥት ግርማን፣ የበጎ ፈቃድ አምባሳደር አድርጎ መሾሙን በዛሬው ዕለት ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም፣ በቤስት ዌስተርን ፕላስ ሆቴል በተካሄደ የፊርማ ሥነሥርዓት ላይ አስታውቋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሕክምና ማህበር ከተመሰረተ ጊዜ እንስቶ ዘር፣ ቀለም ሀይማኖትም ሆነ ማንነት ያልገደበው ሰብዓዊ ድጋፍና አገልግሎትን በመላው ኢትዮጵያ  በመስጠት ላይ የሚገኝ ማህበር ነው ተብሏል።

ማህበሩ አዲስ አበባን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች 35 የሚሆኑ የህክምና ጉዞዎችን በማድረግ፣ ሰብዓዊነትን ባስቀደመ ተግባሩ፣ ከ25 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረገ ሲሆን፤ ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ሰብዓዊ ግልጋሎት ሰጥቷል።

በቀጣይም ማህበሩ አቅም የሌላቸው ዜጎችን ታሳቢ ያደረገ የሕክምና አገልግሎት ባልተዳረሰባቸው አካባቢዎች፣ ሙያዊ ፍቅርና አክብሮት የታነጸ የሕክምና አገልግሎት ለመስጠት እንዲሁም  የህክምና አገልግሎት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሚያስችሉ የድጋፍ ስራዎችን፣ በአቅም ግንባታና በግብዓት ማሟላት ላይ አተኩሮ ለመስራት አቅዷል፡፡

በዚህ መነሻነትም ማህበሩ ከዚህ ቀደም ከሰራቸው የሰብዓዊነት ስራዎች በተጨማሪ በዚህ ወቅት እያከናወናቸው የሚገኙ ተግባራትንና ወደፊት ሊከውን ያቀዳቸውን ውጥኖቹን መነሻ በማድረግ ተወዳጇን ተዋናይትና የቴሌቪዥን ፕሮግራም አቅራቢ አርቲስት ትዕግስት ግርማን የበጎ አድራጎት አምባሳደር አድርጎ ሾሟል።


ታሊስማን ጋላሪ የተመሰረተው በአቶ ማሲሞ ዴ ቪታ በ2009 ዓ.ም ብስራተ ገብርኤል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ ሳልቫቶሬ ዴ ቪታ ኮምፕሌክስ ህንፃ ላይ  ሲሆን፤ የአርትስ ጋላሪውን ታዋቂና ታዳጊ የስነ-ጥበብ አርቲስቶች ስራቸውን ለህዝብ እንዲያሳዩና ከህዝቡም ጋር እንዲተዋወቁ  እድሉን በማመቻቸት እንዲጠቀሙ ሲያደርግ  ቆይቷል፡፡
ፈረንሳይ ለጋሲዮን የሚገኘው አዲሱ ታሊስማን ጋላሪ የቅርስ ቤት፣ ዛሬ ሰኔ 20 ቀን 2016  ዓ.ም፣ ከፍተኛ የቢሮ ኃላፊዎች፣ የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሣ ቤተሰቦችና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በተገኙበት በይፋ ተመርቋል።

የአዲስ አበባ ከተማ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ በቅርስነት የመዘገባቸውን የቅርስ ቤቶች የነበራቸውን ይዘት ሳይለቁ ተጠግነውና ታድሰው፣ ቅርሶቹ ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ በርካታ ተግባራት ያከናውናል።

ተቋሙ የገንዘብ አቅምና ሙያዊ ብቃት ላላቸው ወገኖች ተላልፈው እንዲለሙና በእንክብካቤ እንዲቆዩ ለማድረግ ባወጣው መስፈርት ተወዳድረው፣ የደጃዝማች አምዴ አበራ ካሣ መኖሪያ ቤት የነበረውን የቅርስ ቤት ለማልማት፣ ከቢሮው ጋር ውል በመፈፀም፣ ቀድሞ የነበረበትን ይዘት ሳይለቅ በመጠገንና በማደስ፣ አሁን ላለበት ደረጃ እንዲደርስ የበኩላቸውን አድርገዋል፡፡

በምረቃ ስነስርአቱ ላይ ተገኝተው መልዕክት ያስተላለፉት የአዲስ አበባ ባህል፣ ኪነ-ጥበብና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ሂሩት ካሳው (ዶ/ር)፤ “ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአዲስ አበባ ከተማ ያሏት ቅርሶች፣ በአብዛኛው አቧራ ለብሰውና ተጎሳቁለው ነበር የሚታዩት፡፡ አሁን ግን በልማት በተለይም በኮሪደሩ ልማት ቅርሶቻችን ደረጃቸውንና ታሪካቸውን በሚመጥን መልኩ ተጠብቀው እንዲለሙና እንዲጠበቁ እየተደረገ ይገኛል” ብለዋል።
ቅርሶች በመንግስት ብቻ ሊለሙ እንደማይችሉ የገለጹት የቢሮ ኃላፊዋ፤ ቅርሶችን ከባለሀብቶች ጋር በመሆን አልምቶ ለቱሪስት ክፍት እንዲሆንና ጥበብን የምናሳድግበት፣ የምናለማበትና ለትውልድ የምናስተላልፍበት አሰራር ተፈጥሯል ብለዋል።

ሕብረት ባንክ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት፣ የአንድ ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ ተገለጸ፡፡ የገንዘብ ድጋፉ የተደረገው ባለፈው ረቡዕ ሰኔ 20 ቀን 2016 ዓ.ም. በባንኩ ዋና መስሪያ ቤት ነው፡፡

በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው የገንዘብ ድጋፉን ያበረከቱት የሕብረት ባንክ ሲኒየር ምክትል ዋና ስራ አስፈጻሚ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ ባደረጉት ንግግር፤ ማሕበሩ ለሚሰራቸው ሰብዓዊ ስራዎች ምስጋናቸውን አቅርበዋል። አክለውም፣ የማሕበሩ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤትም የበጐ አድራጎት ስራውን በስፋት ለማከናወን የሚረዳውን የሕንፃ ግንባታ መደገፍ ለባንኩ ትልቅ ኩራት መሆኑን አመልክተዋል፡፡

ባንኩ ከተቋቋመበት ጊዜ ጀምሮ የባንክ አገልግሎቱን ከመስጠት ባሻገር ቀጣይነት ባለው መልኩ ለማሕበረሰቡ ዕድገት፣ ጤናማነትና ለውጥ የሚሰሩ ድርጅቶችን በተቀመጡት መመዘኛዎች መሰረት ቅድሚያ በመስጠት እየደገፈ እንደሚገኝ ወ/ሮ ጽጌረዳ ተስፋዬ  አብራርተዋል፡፡  

የባንኩ ዕድገትና ስኬት መሰረቱም ከማሕበረሰቡ ጋር በሕብረት መስራቱ መሆኑን በመግለፅ፣ ሕብረት ባንክ የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓሉን በዚህ ዓመት በተለያዩ ዝግጅቶች እያከበረ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል። አያይዘውም፣ ለኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የተደረገው የገንዘብ ድጋፍም የዝግጅቱ አንድ አካል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

በኢትዮጵያ ቀይ መስቀል ማሕበር፣ አዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት የቦርድ ሰብሳቢ አቶ ተስፋሚካኤል ታፈሰ በበኩላቸው፣ ማሕበሩ እየሰጠ ያለውን የሰብዓዊ አገልግሎት አሁን ካለበት ደረጃ በማሻሻል፣ ለሁሉም የከተማዋ ነዋሪዎች አገልግሎቱን ተደራሽ ለማድረግና ራዕዩን ለማስፋት የእያንዳንዱ ባለድርሻ ድጋፍና ትብብር ወሳኝ መሆኑን ተናግረዋል።

ሕብረት ባንክ ሕዳር 13 ቀን 2016 ዓ.ም. ባካሄደው የ25ኛ ዓመት የብር ኢዮቤልዩ በዓል ይፋዊ የማብሰሪያ መርሐ ግብሩ ላይ፣ ለአስር የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ለእያንዳንዳቸው 1 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር፣ በድምሩ 15 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉ የሚታወስ ነው፡፡

ሁለተኛ ክፍል

      ሐ. በዓሉ ግርማ
በዓሉ ግርማ በዐማርኛ ልቦለድ ታሪክ የታወቀ ብቻ ሳይሆን፣ ለጥበቡ ሰማዕትነትን የከፈለም ነው። በዓሉ፣ በኢላባቡር ክፍለ ሀገር ሱጴ ውስጥ በ1928 ዓ.ም. ተወለደ። የ፩ኛ ደረጃ ትምህርቱን በልዕልት ዘነበወርቅ ትምሕርት ቤት ተከታትሏል፤ ፪ኛ ደረጃን የተማረው ደግሞ በጄኔራል ዊንጌት ትምህርት ቤት ነው። በትምህርቱ ትጉሕ ስለነበረ፣ በሁለተኛ መልቀቂያ ፈተና ባስመዘገበው ከፍተኛ ነጥብ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ ለመሆን በቅቷል። በዩኒቨርሲቲ በመጀመሪያ ዲግሪው ያጠናው ሥነፖሊቲካልና የዓለም አቀፍ ግንኙነት መስክ ነበር። ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የመጀመሪያ ዲግሪውን ካገኘ በኋላ፣ በተመሳሳይ የሙያ መስክ በውጪ ሀገር ተምሮ ሁለተኛ ዲግሪውን አግኝቷል።
ከደረሳቸው በርካታ ልቦለዶች መካከል ከአድማስ ባሻገር የተሰኘው ሥራው በኢትዮጵያ ሥነጽሑፍ ታሪክ እንደ ቀዳሚ ዘመናዊ ልቦለድ ይታያል። ይህ መጽሐፍ ታትሞ ሲወጣ ነው ሊቃውንቱ «አሁን ስለኢትዮጵያ ልቦለድ መነጋገር እንችላለን» አሉ እየተባለ የሚነገረው። ከአድማስ ባሻገር  ዓለማቀፋዊ አድናቆት አትርፎ፣ በሩስኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለመስኮባውያን አንባብያንም ቀርቧል። ከዚህ መጽሐፍ በተጨማሪ፣ የሕሊና ደወል (በኋላ ተሻሽሎ ሐዲስ የተባለው)፣ የቀይ ኮኮብ ጥሪ፣ ደራሲው እና ኦሮማይ የተሰኙ ረጃጅም ልቦለዶችን ደርሷል።  ይህ ዕውቅ ደራሲ፣ አጫጭር ልቦለዶችም እንዳሉት ይታወቃል። ለምሳሌ፣ ጭጋግና ጠል በተባለው መድበል ውስጥ «የፍጻሜው መጀመሪያ» በሚል ርእስ አንድ አጭር ልቦለድ አስነብቦናል።  
በበዓሉ ልቦለዶች ውስጥ ዓለማት የስሜት ብርሃን ለብሰው የሚከሰቱ ናቸው። ትረታውን የሆነ ተራኪ የሚነግረን ሳይሆን፣ ራሳችን በዐውደ ዓለሙ ላይ በአካለ ሥጋ ተገኝተን የምንከታተል እስኪመስለን ድረስ ዓለማት ግልጽና ክሱት ናቸው። የሚከተለውን መቀንጭብ እንመልከት፤  
ከባድ ዝናብ ያረገዘው የሀምሌ ሰማይ አጣዳፊ ምጥ ይዞት በጣር ያጉረመርማል። አዲስ አበባ ጥቁር የጉም ብርድ ልብስ ለብሳለች። በጥፊ የሚማታ፤ ቀዝቃዛ ስለታም ንፋስ እያፏጨ የሽምጥ ክንፍ አውጥቶ ይበራል። ዛፎችና ቅጠሎች የዛር ዳንኪራ እየረገጡ ይወዛወዛሉ።
ጠብ ያለሽ በዳቦ እያለ ሲፎክር ከመጣው አህያ ከማይችለው ዝናብ ለማምለጥ እግረኞች ወደየቤታቸው ወይም መጠለያ ካለው ሱቅ ለመጠጋት ይሮጣሉ፤ ወፎች ጫጫታቸውንና እልልታቸውን ትተው ወደየጎጆአቸው ይበራሉ። ሁሉም ወደሰማይ እያዬ ሲሮጥ፤ ሽብር የመጣ ይመስል ነበር።  
ያለርህራሄ በጥፊ የሚማታው ንፋስ አቧራ አንስቶ እሰዉ አይን ውስጥ እየሞጀረ፤ የሴቶችን ቀሚስ ወደላይ እየገለበና ጃንጥላቸውን ለመንጠቅ እየታገለ መንገደኞችን ይተናኮላል። ንፋሱ ከራሱ ላይ የነጠቀውን ባርኔጣ የሚያባርር አንድ መላጣ ሰው አይቶ አበራ ፈገግ አለ። ከታች የሚመጣ አንድ ሰው ባርኔጣውን ባይዝለት ኖሮ ሰውዬው መቆሚያ አልነበረውም።
የበዓሉ ልቦለዶች ስሜት የሚያናውጡት በሐሳባዊ አቀራረብ አይደለም፤ ይልቅስ ተጨባጭ በመሆናቸው የእውነታ መልክና ገጽታ ተላብሰው ነው። ለዚህም ነው፣ በዓሉ የእውነታዊነት ልቦለድ ፈር ቀዳጅ ነው የሚባለው።

ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በበዓሉ ግርማ ድርሰት
በዓሉ ግርማ፣ በጋዜጠኝነት ሙያም ስሙ የተጠራ ነበር። «የዛሬይቱ ኢትዮጵያ» ጋዜጣ አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል፤ የ«መነን መጽሔት» አዘጋጅም ነበር። «አዲስ ረፖርተር» መጽሔትን በአዘጋጅነት በመምራትም ስሙን ተክሎ ያለፈ ሰው ነው። «አዲስ ሪፖርተር» የዓለም አቀፍ መስፈርትን የሚያሟላ ብቃት ያገኘው በበዓሉ አዘጋጅነት ዘመን ነበር። በጋዜጠኝነት ሙያ በኢትዮጵያ ራዲዮ መሥራቱም ይታወቃል።
በኋላ ግን ጋዜጠኛ አልነበረም። በሙያው ላይ ያልቀጠለው፣ ምናልባት፣ ከነበረበት የኃላፊነት ደረጃ እንዲሁም በወቅቱ ከነበረው የትምህርት ደረጃው ከፍተኛነት የተነሳ ሊሆን ይችላል። በሚንስቴር ደረጃ የነበረ ሰው በጋዜጠኝነት ደረጃ ተመልሶ ለመሥራት የኃላፊነት ደረጃው አይፈቅድም። ይሁን እንጂ፣ ከሙያው ጋር የነበረው ፍቅር እስከ ኦሮማይ ድረስ ጅራቱን አንቆ ይከተለው እንደነበር እንመለከታለን። ኦሮማይ ልቦለድ ብቻ አይደለም፤ ዘጋቢ ፊልም ዓይነት ጠባይ ያለውም ነው። ምክንያቱም፤
ትኩረቱ በአንድ ወሳኝ ታሪካዊ ፕሮግራም ላይ ያነጣጠረ ነው። በቀይ ኮከብ ዘመቻ ነባራዊ ተግባራት ላይ ካሜራውን ደግኖ፣ የፈጣሪ ፍጡራን ያከናወኗቸውን ተግባራት ከሥር … ከሥር … እየተከታተለ በመቅረጽ ነው የሚተርከው።
በውሱን ነባራዊ መልክዓ ምድር ዳራ ላይ አተኩሮ፣ በገሐድ የነበሩ ምስላዊ ትረካዎችን ያቀርባል።
ታሪኩ እውነት ከመሆኑም በላይ፣ በታሪክ የሚታወቁ ሰዎች ናቸው ስማቸው እየተቀየረ፣ በገጸባሕርይነት የተሣሉት። በዘመኑ የነበሩ ሰዎችን አግኝተን የማነጋገር ዕድል ብናገኝ፣ «ፊያሜታ እገሊት ናት፤… ሥዕልም እግሌ ነው፤ … እያሉ፣ የፈጣሪ ፍጡራን የሆኑ ሰዎች ይነግሩን ነበር።
ተራኪው ጋዜጠኛ ነው።
እነዚህ ጉዳዮች የጋዜጠኝነት ሙያ በበዓሉ ውስጥ ካሳደረው የክሂሎት ተፅዕኖ የመነጩ ናቸው።
ለነገሩ፣ የበዓሉ ልቦለዶች ወደ ኣማናዊ ዓለም ተጠግተው የዘጋቢ ፊልም ጠባይ የተላበሱ ናቸው። ኦሮማይ ደግሞ፣ ከታሪካዊ እውነታው ጋር ሲገናዘብ የበለጠ ዘጋቢ ፊልም የመሆን ጠባዩ ጎላ። ይህ ብቃት የበለጠ እውን የሚሆነው ደግሞ በሙያው ሠልጥኖ፣ ልምድና ክሂሎት ካዳበረ ጠንቃቃ ጋዜጠኛ ነው። ለዚህ ነው፣ በዓሉ በአካሉ ከጋዜጠኛ ቢሮ ቢርቅም፣ ሙያው ግን ጥበቡን እያበለጸገለት ቀጥሏል ማለት ያለብን፤ ሙያና ጥበብ አንገትና ክታብ ሆነዋል፤ ሙያው አንገት አካሉን ገንብቷል፤ ክታቡ አካሉን አስጊጦታል።  
መ. ደምሴ ጽጌ
ደምሴ ጽጌ ታኅሳስ 21 ቀን 1943 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ ነው የተወለደው። የ፩ኛ ደረጃ ትምህርቱን በስብስቴ ነጋሢ ተከታትሎ፣ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ደግሞ በሽመልስ ሀብቴ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀቀ። ከዚያ በመምህርነት ሙያ ሠልጥኖ፣ ለተወሰኑ ዓመታት ከሠራ በኋላ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ  ቋንቋዎችና ሥነጽሑፍ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ደምሴ፣ ከመምህርነት ሙያ በኋላ ያመራው ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ ነው። ጋዜጠኝነት የጀመረው፣ በቱሪዝም ኮሚሽን ይታትም በነበረው «ዜና ቱሪዝም» ጋዜጣ ላይ ምክትል አዘጋጅ ሆኖ በመሥራት ነው። ከዚያ በኋላ፣ ማስታወቂያ ሚኒስቴርን ተቀላቀለ። በማስታወቂያ ሚኒስቴር «የዛሬይቱ» ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ከዚያ፣ በዚያው በማስታወቂያ ሚኒስቴር ወደ «አዲስ ዘመን» ጋዜጣ ተሸጋግሮ፣ የዚህ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ በመሆን ለረጅም ጊዜ ሠርቷል።
ከዚህ ሙያው ጎን-ለጎን፣ የተለያዩ ግለፈጠራ ልቦለዶችን አበርክቷል። መጀመሪያ የልቦለድ እጁን ያሟሸው ፍለጋ በተባለው ኖቬላ ነው። ሌላው ግለፈጠራው ምትሐት የተሰኘው ልቦለዱ ነው። አጫጭር ልቦለዶችንም ይጽፍ ነበር። ለምሳሌ፣ ጭጋግና ጠል በተሰኘው መድበል ውስጥ «ማን ያውቃል» በሚል ርእስ አንድ አጭር ልቦለድ ድርሰት አስነብቦናል። ከግለፈጠራ ሥራዎች በተጨማሪ፣ ከባሴ ሀብቴ ጋር ሆኖ በጣም ተነባቢ የነበረውን የካርንጌን ሥራ ጠብታ ማር በሚል ርእስ ተርጉሞ ለአንባብያን አቅርቧል።
ደምሴ ጽጌ በአርትኦት ሥራውም  ይጠቀሳል። በጋዜጣ አዘጋጅነት ሙያው ከዐበይት ተግባራቱ  አንዱ አርትኦት መሆኑን ማንም አይዘነጋውም። ከዚያ ውጪ የአርታኢነት ብቃቱን የሚያረጋግጥለት በስብሐት ገብረ እግዚአብሔር ሥራዎች ያተመው የአርትኦት አሻራ ነው። በዚህ ተግባሩ፣ የስብሐት የተፈጥሯዊነት አጻጻፍ ይትበሃል ከአንባቢው ማኅበረሰብ ባህልጋር እንዲቀራረብ በማድረግ ረገድ ጉልሕ ሚና መጫወቱን ስብሐት ራሱ መስክሯል። ከስብሐት ምስክርነት ባሻገር፣ በደምሴ አርትኦት የተቃናውን ቅጽና የደምሴ አርታኢነትን አሻፈረኝ ብሎ የታተመውን ቅጽ ልዩነት ተመልክቶ፣ የዚህን ደራሲ የአርታኢነት አሻራ ማጠየቅ ቀላል ነው።  
ሠ. ስብሐት ገብረ እግዚአብሔር
ትግራይ ውስጥ አድዋ አካባቢ በምትገኝ በእርባ ገረድ መንደር ሚያዚያ 27 ቀን 1928 ተወለደ። አባቱ ገብረ እግዚአብሔር ገብረ ዮሐንስ ይባላሉ፤ እናቱ ደግሞ ወይዘሮ መዓዛ ተወልደ መድኅን። በልጅነት ዕድሜው አዲስ አበባ ከዘመድ ዘንድ መጥቶ መጀመሪያ ስዊድን ት/ቤት ተማረ። በኋላ ደግሞ በተፈሪ መኮንን ት/ቤት ተምሯል። በትምህርቱ ውጤታማ ሆኖ፣ ከአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በትምህርት አስተዳደር የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል። ዲግሪውን እንደተቀበለ፣ በአስፋ ወሰን ት/ቤት ለሁለት ዓመታት ያህል እንግሊዝኛ አስተምሯል። ቀጥሎም በትምህርት ሚኒስቴር የውጪ ትምህርት ዕድል ጽ/ቤት ውስጥ የሕዝብ ግንኙነት ባልደረባ በመሆን አገልግሏል። በኋላም፣ የተባበሩት መንግሥታት የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በሰጠው የትምህርት ዕድል በፈረንሳይ ሀገር ተምሯል። ይህን የትምህርት ዕድል ለዘለቄታው ባይገፋበትም፣ ከአውሮፓ የሥነጽሑፍ ባህል ጋር እንዲተዋወቅ ግን ሰፊ በር ከፍቶለታል። ይህንን የምናረጋግጠው በቀጣይ ዘመኑ በድርሰት ቆሌ በመለከፉ ብቻ ሳይሆን፣ ፈረንሳይ ሌቱም አይነጋልኝ ለተባለው ድርሰቱ መጻፍ ዐበይ ማዕከል በመሆኗ ነው። የልቦለዷንም መዋጣት ከሚያሳዩን ጉዳዮች አንዱ Les Nuits d’Addis-Abeba በሚል ስያሜ ወደ ፈረንሳይኛ በመተርጎሟ ነው።
ስብሐት፣ ከምንም በላይ፣ የሚታወቀው በልቦለድ ደራሲነቱ ነው።  ካበረከተልን ልቦለዶች መካከል የሚከተሉትን እንጥቀስ፤
አምስት ስድስት ሰባት እና ሌሎችም ታሪኰች
(1981)
እግረ-መንገድ  (በተለያዩ ቅጾች፤ 1985-
1990)
ትኩሳት (1990)
ሰባተኛው መልአክ (1992)
ሌቱም አይነጋልኝ (1992)
እነሆ ጀግና (1997)
የጋዜጠኛነት ሙያ ተመክሮ ካላቸው የሥነጽሑፍ ደራስያን መካከል ስብሐት አንዱ ነው። ስብሐትን መጀመሪያ ወደ ጋዜጠኝነት ሙያ የሳበው የልብ ወዳጁ የነበረው በዓሉ ግርማ ነው። አንድ ቀን በዓሉ፣ «እዚህ ዝም ብለህ ከቢሮክራሲ ጋር ጊዜህን አታባክን፡፡ … ላንተ ተፈጥሮ የእኛ ሙያ ነው የሚስማማህ” እንዳለው ይናገራል። ከዚያም፣ “እሺ እውነትህን ነው …» ብሎ ከበዓሉ ጋር በማስታወቂያ ሚኒስቴር ሥራ ጀመረ። ስብሐት ከ1946-1947 “የተፈሪ መኮንን አላማ” የተባለ መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ እንደሠራም ታሪኩ ይናገራል። ከ1960-1962 ባሉት ዘመናትም የኢትዮጵያ ጀግኖች ማኅበር የእንግሊዝኛው መጽሔት አዘጋጅ ሆኖ ሠርቷል። ለረጅም ዘመናት ታዋቂ በነበረው «የካቲት መፅሔት» ውስጥም ተቀጥሮ መስራቱ ይታወቃል፡፡ በዘመነ ደርግ  ኩራዝ አሳታሚ ድርጅት ሲቋቋም በአርታኢነት አገልግሏል።

ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በስብሐት የድርሰት ሕይወት
ስብሐት የድርሰት ዓለምን የተቀላቀለው በጋዜጠኛነት ነው። ሒደቱን ብንገምት፣ በስኮላርሽፕ ቢሮ በሚሠራበት ዘመን፣ በዓሉ «ላንተ ተፈጥሮ የእኛ ሙያ ነው የሚስማማህ” ብሎ ከወሰደው ጊዜ ጀምሮ ጋዜጠኛ ሆነ፤ የሙያውን ብዕር አነሳ። ሙያው እያደር የመጻፍ ተነሳሽነትን እያሳደገበት ሔዶ፣ የድርሰት ክሂሎት መበልጸግ ቀጠለ። የድርሰቱ ክሂሎት መበልጸግ ተፈጥሮ ያስታጠቀችውን የሥነጽሑፍ ተሰጥኦ አነቃውና፣ ወደ ጥበቡ መድረክ ተሳበ።
ስብሐት በኋላም መነቃቃትና ክሂሎት የፈጠረለትን የጋዜጠኝነት ሙያ አልተወም፤ ሁለቱን እያዋሐደ ቀጥሏል። ለዚህ አስረጂ የሚሆነን፣ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ላይ ይጽፍ የነበረው «እግረ መንገድ» ነው። በጥናት ቢፈተሽ፣ አዲስ ዘመን ጋዜጣ ተፈልጎ የተነበበበት ዘመን ቢኖር፣ «እግረ መንገድ» ይጻፍ የነበረበት ሳይሆን አይቀርም። ይህ የሙያውንና የጥበቡን በተዋህዶ መክበር ያጠይቃል። አምዱ ዋዘኛ ወጎች የሚተረክበት ነበር። በኢ-መደበኛ፣ በንግግር አከል፣እንደዋዛ፣ … ይተረክ የነበረው «እግረ መንገድ» የጋዜጣውን ጣዕም የማር-እና-ወተት ባሕርይ ሰጠው። ሥነጽሑፋዊነት ለጋዜጠኝነት ኃይል ሰጠው ማለት ነው። ይህ ኃይል መመንጫው የጋዜጠኝነት ክሂሎት መሆኑ ደግሞ እርግጥ ነው። በአጭር አባባል፣ ጋዜጠኝነት ሥነጽሑፍን ወለደ፤ ሥነጽሑፍ ጋዜጠኝነትን አጣፈጠ፤ ለጋዜጣው መነበብ ዐቢይ ምክንያት ሆነ። ከዚህ ማጠየቂያ ተነስተን፣ በስብሐት የድርሰት ዓለም ሙያና ጥበብ ተገጣጠሙ፤ ጋዜጠኛና ደራሲ በሁለት አምዶች ቆሙ እንበል።  

ረ. ነቢይ መኮንን
ነቢይ መኮንን ደራሲ፣ ተርጓሚ፣ አርታኢ እንዲሁም ጋዜጠኛ ነው። ነቢይ ዕውቅና ያተረፈው በብዙ ዘርፍ ነው፤ ግሩም ችሎታ ያለው ተርጓሚ ነው። ይህም በተለይ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያለውን ድንቅ ሥነጽሑፍን የመረዳት ችሎታ ያረጋግጣል። ከዚያ በላይ ግን፣ ሥራዎችን ከእናት ቋንቋ ወደ መጥለፊያ ቋንቋ (ዐማርኛ) በመመለስ ሒደት የሚያጋጥሙ በርካታ ተግዳሮቶች የመጋፈጥ ጥንካሬውንም ጭምር የሚመሰክር ነው። ነቢይ አንቱ የተባለ ገጣሚም ነው። ግጥሞቹ ልብን ይመስጣሉ። በተለይ በግጥሞቹ የሚያነሳቸው ርእሰ ጉዳዮች ከአዲስ እይታ የሚፈልቁና፣ ሀገራዊ አንድምታ ያላቸው ናቸው። በዚያ ላይ የተነገረለት አርታኢም ነው። በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ለረጅም ዓመታት በአዘጋጅነት ሲሠራ ያበረከተውን አስተዋጽኦ ያስተዋለ ሰው፣ ጠንካራ አርታኢነቱን ለመመስከር ግንባሩን አያጥፍም።  
በርካታ የነቢይ ተደራስያን ነቢይን የሚያውቁት በተለይ በ«አዲስ አድማስ» ጋዜጣ ላይ በሚጽፋቸው ተረቶቹ ነው። ከዶ/ር እንዳለጌታ ከበደ ጋር ባደረገው አንድ ውይይት ላይ እንዳስተዋልነው፣ በበርካታ መቶዎች የሚቆጠሩ ተረቶችን በተጠቀሰው ጋዜጣ ላይ በርእሰ አንቀጽነት ጽፏል። ይህ ለየት ያለ የርእሰ አንቀጽ ይትበሃል ለጋዜጣ የተለየ የተነባቢነት ሞገስ እንዳጎናጸፈው መናገር ይቻላል።
ነቢይ መኮንን በደርግ ዘመን እሥር ቤት ሆኖ፣ Gone with the Wind የተሰኘውን መጽሐፍ ነገም ሌላ ቀን ነው በሚል ርእስ ተርጉሟል። ይህ የትርጉም ሥራ ለየት ያለ ታሪክ ያለው ነው። መጽሐፉን የተረጎመው በቁርጥራጭ የሲጋራ ወረቀቶች መሆኑ አንዱ የሚያስገርም ጉዳይ ነው። Gone with the Wind የማርጋሬት ሚሼል ረጅም ልቦለድ ነው። የመጀመሪያ እትሙ ዋል-አደር ያለ ነው፤ 1936። ዋል-አደር ይበል እንጂ፣ በጣም ተወዳጅ መጽሐፍ ነበር። በጥቂት ወራት ውስጥ በሚሊየን ቅጂዎች የተሸጠ ልቦለድ ነው። በኋላም ወደ ፊልም ተቀይሮ ለተመልካች ቀርቧል። ይህን የመጽሐፉን ተደናቂነት ያነሳነው፣ ነቢይ መኮንን ጠንካራ ሥራዎችን የማጣጣም ሥነጽሑፋዊ ብቃቱን ለማስታወስ ያህል ነው። Gone with the Wind በነቢይ ወደ ዐማርኛ ተተርጉሞ ለሕትመት ቢቀርብም፣ የሳንሱር መቀስ እየተለተለ ጉዳተኛ አድርጎት ነው የታተመው። ከታተመ በኋላም፣ ምንም እንኳን በገበያ ላይ ተፈላጊነት ቢኖረውም፣ ዳግም እንዳይታተም ተፈርዶበት፣ በመጀመሪያ እትም ብቻ እንዲቀር የተደረገ ሥራ ነው።
ነቢይ መኮንን በወርኃ ነሐሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም. በኢትዮጵያ ቤተመዛግብትና ቤተመጻሕፍት አገልግሎት አጋርነት፣ በፍሬንድሺፕ ሆቴል ሦስት የትርጉም መጻሕፍት ተመርቀውለታል። ከሦስቱ አንዱ ራሱ ነገም ሌላ ቀን ነው ሲሆን፣ ሁለቱ ደግሞ የመጨረሻው ንግግር እና የእኛ ሰው በአሜሪካ ናቸው።
ነቢይ ሌላው በጣም የሚደነቅበት የሥነጽሑፍ ጥበብ ሥነግጥም ነው። የተለዩ የሥነግጥም መድበሎች አሉት፤ ስውር ስፌት (በሁለት ቅጾች) እና ጥቁር፣ ነጭ፣ ግራጫ ግጥሞች የተሰኙት ሥራዎቹ የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ የሚያውቃቸው ናቸው። «ጁሊየስ ቄሳር»፣ «ናትናኤል ጠቢቡ» እንዲሁም “ማደጎ” የተሰኙ በመድረክና በቴሌቪዥን የቀረቡ የተውኔት ሥራዎችም እንዳሉት ይታወቃል። ባለካባና ባለዳባን  በመሳሰሉ ተውኔቶች ውስጥ በተዋናይነትም መሳተፉን መረጃዎች ያሳያሉ። “ማለባበስ ይቅር” የተባለውንና በኤች-አይቪ ላይ ያተኮረውን የዘፈን ግጥምም የገጠመው እሱ ነው።
ጋዜጠኝነትና ሥነጽሑፍ በነቢይ የድርሰት ዓለም
«አዲስ አድማስ»ን ተወዳጅና ተነባቢ ካደረጉት ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ርእሰ አንቀጹ ነው። ርእሰ አንቀጹ በትውፊታዊ ትረታዎች እየተቀመመ ሲቀርብ ኖሯል። ትረታዎቹ ልቦለዶች መሆናቸው ነው፤ ሥነጽሑፍ። ነቢይ መኮንን በጋዜጠኝነት ሙያው የሚታወቀው፣ ከልቦለድ ዓለም ለሙያው ማበልጸጊያ የሚሆኑትን እነዚህን ትረታዎች እያመጣ፣ ሙያንና ጥበብን በማስተቃቀፍ ነው። ጋዜጠኝነቱን ለልቦለዱ ድልድይ ወይም መድረክ እንዲሆን ሲያበቃው፣ ልቦለዱን ደግሞ የጋዜጣውን የተነባቢነት ጸጋ ማጎናጸፊያ አደረገው። በሌላ አባባል፣ ልቦለድ ለጋዜጠኝነት ማጣፈጫ ቅመም ሆነ ማለት ነው። በሁለተኛ ደረጃ፣ ጋዜጣው ትረታዎቹን አትሞ ሲያቀርብ ልቦለዶቹ የሚነበቡበት መድረክ አገኙ፤ ሙያው ለጥበቡ መናኘት አብነት ሆነ። የነቢይም ስም የናኘው ሁለቱ በሚያመነጩት መልካም መዓዛ እየታወደ ነው።
ሰ. ዓለማየሁ ገላጋይ
ዓለማየሁ ገላጋይ በ1960 ዓ.ም. አራት ኪሎ አካባቢ እንደተወለደና፣ በዚያው አካባቢ እንዳደገ ለዚህ ጽሑፍ አዘጋጅ በየምክንያቱ አውግቶታል፡፡ ፩ኛ ደረጃን የተማረው በዳግማዊ ምኒልክ ት/ቤት ነው። ወደ ፯ኛ ሲያልፍ ግን ፈተና ገጠመው፣ አሳዳጊው የነበሩት አያቱ በእኛ ዘር ከዚህ በላይ የተማረ የለምና፣ ይበቃሃል ብለው፣የትምህርት ማዕቀብ ጣሉበት። እናቱ ግን አልተስማሙም፤ ካልተማርክ የማላይህ ሀገር ሔደህ ዱርዬ ሁን ብለው ስለተቆጡት፣ ትምህርቱን በዳግማዊ ምኒልክ ፪ኛ ደረጃ ት/ቤት ቀጥሎ ማጠናቀቅ ነበረበት፡፡ በኋላም፣ በአዲስ አበባ ስኩል ኦፍ ጆርናሊዝም ጋዜጠኝነት አጥንቶ ተመርቋል፡፡ የሥነተግባቦት ባለሙያ ነው እንበል።
የዓለማየሁ መጀመሪያ ቀለም የቀመሱት ሥራዎቹ ዜማ በተሰኘው መድበል ውስጥ የታተሙ ሁለት አጫጭር ልቦለዶች ናቸው፤ «ሙትና ሐውልት» እንዲሁም «ሚዛኑ-ሰብእ ወ እንስሳት» የተሰኙት። በዚያው ቀጥሎ፣ ዛሬ የሙሉ ጊዜ ደራሲ ሆኗል። በዚህ ዘመን በሰፊው ከሚነበቡ ልቦለድ ደራስያን መካከል በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ዓለማየሁ ነው። በርካታ ልቦለዶችን ደርሷል፤ አጥቢያ፣ ወሪሳ፣ የብርሃን ፈለጎች፣ ታለ በእውነት ስም፣ ኩርቢት፣ የመሳሰሉትን። ከልቦለዶቹ በተጨማሪ፣ የስብኃት ገብረ እግዚአብሔር ሕይወትና ክህሎት፣ ኢህአዴግን እከሳለሁ፣ የፍልስፍና አፅናፎት እንዲሁም መልክአ ስብሐት የተሰኙ ኢ-ልቦለዳዊ መጻሕፍትን አሳትሟል::
ከጋዜጠኝነት ት/ቤት ተመርቆ ከወጣ በኋላ፣ በቀጥታ የተሰማራው በተመረቀበት ሙያ ነው። የሠራባቸው ጋዜጦች በርካታ ናቸው። “ኔሽን”፣ “አዲስ አድማስ”፣ “ፍትሕ”፣ “አዲስ ታይምስ”፣ እና “ፋክት” ሊጠቀሱ ይችላሉ። በነዚህ የንባብ ሚዲያዎች ላይ ኂሳዊ መጣጥፎችን የሚጽፈው በግንባር ሥጋነት ነበር፡፡ በድርሰቶች፣ በሰዎች አመለካከትና በማኅበራዊ ጉዳዮች ዙሪያ ሙያዊ ዕውቀቱንና የብዕር ክሂሎቱን ተጠቅሞ ትንታኔ ይሰጣል፤ ይተቻልም። ያልታየውን የሚያይ መረር ያለ ኃያሲ ነው። ባጭሩ፣ ዓለማየሁ ጋዜጠኝነትን፣ ደራሲነትንና ኃያሲነትን አስተባብሮ በስፋት የሠራ፣ ወደፊትም ብዙ እንደሚሠራ የምንጠብቅበት ለሚዲያ ባልደረባው፣ ለሥነጽሑፍ ባለካባው ነው።
በዓለማየሁ ሥራዎች ሙያና ጥበብ ምንና ምን ናቸው?
ዓለማየሁ ገላጋይ ራሱን ከጋዜጠኛነት ሙያ አፋቶ ከልቦለድ ጋር የቃልኪዳን ቀለበት ማጥለቁን የዚህ ጽሑፍ አቅራቢ ያምናል፤ አልፎ-አልፎ፣ በሚዲያዎች የሚለቃቸው መጣጥፎች ሳይዘነጉ። ሆኖም፣ አንድ ባል ከሚስቱ ሲፋታ፣ የሚጋራው ባሕርይም ሀብትም እንዳለ ሁሉ፣ ጋዜጠኝነትም ለዓለማየሁ ያጋራው ነገር ይኖራል። ምን?
ዛሬ አያምስልበትና፣ ዓለማየሁ በሙያው ለተለያዩ ጋዜጦች ሲሠራ ነበር። ያ አጋጣሚ ለልቦለድ ጥበቡ ብዙ ትሩፋቶች መቸሩ ግልጽ ነው። አስቀድሞ ነገር፣ ሙያው የድርሰት ክሂሎቱን አበልጽጎለታል፤ ብዕሩን ስሎለታል፤ የድርሰት ክሂሎት አስታጥቆታል። በሁለተኛ ደረጃ፣ ሙያው በተደራስያን ዘንድ ዓይን ውስጥ የሚገባ ብዕረኛ አድርጎታል። ዓለማየሁ (እንደጋዜጠኛ)፣ ከሌሎች ጋዜጠኞች (ለምሳሌ ከስብሐትም ከነቢይም) ተለይቶ እንዲነበብ የሚያደርግ ባሕርይ አለው። ስብሐትና ነቢይ መኮንን በማዝናናት ላይ ያተኩራሉ። ዓለማየሁ ግን ተደራሲን በመተንኮስ የሚታወቅ አምደኛ ነበር (ዛሬም ነው)። ተንኳሽ ርእሰ ጉዳዮችን ያነሳል። እይታው ምን ጊዜም ብርቅዬ ነው፡ በዚያ ላይ፣ ትንኮሳው ልብ በሚያርድ-ትጥቅ የሚያስፈታ የቋንቋ አረር የሚተኮስ ነው። ይህ የአጻጻፍ ባህሉ የተወሰነውን አንባቢ በተቃውሞ፣ የተቀረውን ደግሞ በተደሞ ለንባብ የሚያቁነጠንጥ ነው። ዓለማየሁ ጻፈ ሲባል፣ አንባብያን ጽሑፉን በማደን ሥራ ይጠመዳሉ። ይህ ሁኔታ ለዓለማየሁ የልቦለድ ጥበብ ምንድግና አንዱ ቁልፍ ጉዳይ ነበር።
ጋዜጠኝነት ያተረፈለት ሌላም ትሩፋት አለ፤ የተመክሮ ክምችት ባለጸጋ አድርጎታል። ጋዜጠኛ በነበረባቸው ዘመናት፣ በበርካታ የሀገሪቱ አካባቢዎች ተዘዋውሮ የገበየው ሰብአዊ፣ መልክዓ ምድራዊ፣ ባህላዊ፣ ወዘተ፣ ቁምነገር ለቁጥር ያታክታል። ይህ ግብይት በየዘመኑ ለሚጽፋቸው ልቦለዶች የስሜት፣ የምናብ፣ የጭብጥ፣ … ጥሪትና እርሾ ማስገኘቱን ማን ይክዳል? ባጭሩ፣ ከዓይነተ ብዙ ዐውደ ዓለም የተገበየ የተመክሮ ክምችት፣ በጋዜጣ የታሸ የድርሰት ክሂሎት፣ ከእይታ ብርቅዬነት የተገበየ ተነባቢነት፣ … ዓለማየሁ ከጋዜጠኝነት ሙያው ገብይቶ ለልቦለድ ድርሰቱ በግብአትነት የተጠቀመባቸው ጥሪቶች ናቸው። በዚህ የተነሳ፣ የጋዜጠኝነት ሙያ ለዓለማየሁ ልቦለዶች ፋና ወጊና መንገድ ጠራጊ ነበር ብለን እንፈጠማለን።
፬. ማጠቃለያ   
የደራሲነት ጸጋ ከተሰጥኦ ነው የሚገኘው ብለን እንፈጠም። ሆኖም፣ የሚያዳብረው ክሂሎት ይሻል። ጥበቡን የማመንጨት ጸጋ ተሰጥቶ በወጉ ካላቀረብነው ጥበቡ ግቡን አይመታም። ጥበቡን የማመንጨት ጸጋውን በክሂሎት ስናግዘው ግን የታለመው ጥበብ ይሳካል። በብዙዎቹ ደራሲዎቻችን ተመክሮ እንደምናስተውለው፣ ጋዜጠኝነት የድርሰትን ቴክኒካዊ ክሂሎት ማዳበሩ ግልጽ ነው። ይህን የሚያረጋግጥልን ተተኳሪዎቹ ደራስያን ወደ ድርሰት ዓለም የገቡት በጋዜጠኝነት ሙያ ሐዲድ ላይ ተጉዘው ነው።
በልቦለድ ድርሰት የሚያመረቃ ሥራ ደርሶ ለአንባብያን በማድረስ ረገድ ውጤታማ ለመሆን ሦስት ጉዳዮች የግድ ናቸው።      
የሥራው ጥበባዊ ጥራት (ብቃት)፡- ይህ የመጀመሪያው ጉዳይ ነው። የጥበቡ ብቃት እንዲረጋገጥ፣ አስቀድሞ ደራሲው የጥበቡ ተሰጥኦ ያለው መሆን አለበት። የጋዜጠኝነት ሙያ በእርግጥ ሰውዬው ተሰጥኦው እንዳለው ወይም እንደሌለው ለማረጋገጥ የመፈተሻ ሜዳ ነው። በሙያው ውስጥ እየሠራ የተሰጥኦውን ልክና መልክ ማጤን ይችላል።      
የመነበብ ጥያቄ፡- አንድ ተሰጥኦው ያለው ደራሲ ቀጥሎ የሚያሳስበው ጉዳይ፣ ብጽፍ  ማን ያነበኛል የሚለው ነው። የጋዜጠኝነት ሙያ የተሰጥኦ ጸጋ ለተለገሰው ደራሲ የመነበብ መድረክ ያመቻቻል። ጋዜጠኝነትን እንደሙያ በሚሠራበት ዘመን የጥበብ ተሰጥኦው በአንባብያን ዓይን ውስጥ እንዲገባ ያደርገውና፣ በጋዜጣ መጣጥፎች ከሰው ቀልብ የመግባት ዕድል ያገኛል። ለተተኳሪ ደራሲዎቻችን ጋዜጣ ይህን የዕድል ማዕድ እንደዘረጋላቸው እንገነዘባለን።
የማሳተም አቅም፡- ይህ ኪስን የሚመለከት ጉዳይ ነው። ተሰጥኦንና ተነባቢነትን በጋዜጠኝነት ሙያ ያዳበረ አንድ ደራሲ፣ የሚያወጣው የጥበብ ሥራ የመሸጥ ዕድሉ ከፍተኛ ነው። ይህን የሚፈጥረው የመነበብ ዕድሉ ስፋት ነው። የሥራው የመነበብ ዕድሉ ከፍተኛ ሆኖ ከተገኘ፣ ደራሲው በኪሱ መሳሳት ምክናት ሥራውን ከማሳተም የሚታቀብበት ሁኔታ አነስተኛ ነው፤ አቅሙ ያላቸው የገበያ ሰዎች ተሻምተው ያሳትሙለታል።
በእነዚህ ሁኔታዎች ሁሉ የጋዜጠኝነት ሙያ ለልቦለድ ጥበብ የሚኖረውን ውለታ ማስተዋል ይቻላል። ተተኳሪ ደራሲዎቻችንም በዚህ የሙያው ውለታ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ መገመት ይቻላል።  
ማስታወሻ፡- (ጽሁፉ በኢትዮጵያ ብሮድ ካስቲንግ ኮርፖሬሽን፤ የኤፍ.ኤም. 97.1 ሬዲዮ ጣቢያ  24ኛ ዓመት ክብረ በዓል ላይ ለውይይት መነሻ የቀረበ (ግርድፍ ሐሳብ) ነው፡፡ ግንቦት 27 ቀን 2016 ዓ.ም.)

Page 13 of 722