Administrator

Administrator

Saturday, 19 October 2024 12:41

የግጥም ጥግ

እንዲያው ማሳዘኑ!
   ተበዳዩ ጨቋኝ. . .
   በዳዩ ተጨቋኝ. . .
 የተገላቢጦሽ ኾኗል ነገሩማ፤
   ፍትሕ ተዘንብላ
   ስትወድቅ በአፍጢሟ
 የድረሱልኝ ጥሪ ሩቅ ስታሰማ፤
ሮሮዋን ሰምቶ - አዝኖ ቀረበና
 ሊያነሳት ቢሞክር ተበዳዩ ጨቋኝ፤
 አልተቻለው ከቶ ቢለፋ ቢሞክር
 ከወደቀችበት ሽቅብ ቀና እንድትል
 ማድረጉ ተሳነው የቱን ያህል ቢጥር።
 ሞት አፋፍ ላይ ኾና ጣርን ስታጣጥር
 ጩኸትና ዋይታ አብዝቶ ተሰማ
ከተበዳይ ጨቋኞች ከምስኪኖች ዘንዳ።
 የኩኔዎች ባልተቤት በዳዩ ተጨቋኝ
 ፍትሕን ፈላጊ እሷኑኑ አዳኝ
 መስሎ ቀረበና. . .
 በደስታ - በተድላ - በአሸናፊነት ስሜት
 በወኔም ተሞላ በድል አድራጊነት!
 ዳግም ላታበራ የወደቀችውን ገድሎ ቀበረና
 ደግሞም ላዩ አዝኖ ብሎም ጆሮ ዳባ
 ዓይኑን በጨው አጥቦ የአዞ እንባ እያነባ
 ቀርቦም ተጭቁኖች፣ ተገፊዎች ዘንዳ
 በመርዛም ምላሱ መስሎም ለዘብተኛ
 ይነዛ ጀመረ የአይዟችሁ ጥሪ
 በዳዩ ተጨቋኝ የፍትሕ ቀባሪ!
 እንዲያው ማሳዘኑ. . . .
 (በዒምራን ዑመር

Saturday, 19 October 2024 12:36

ምን ዓይነት እናት ነሽ?

ምን ዓይነት እናት ነሽ?
 አንዱ ልጅሽ ሲያለቅስ፣
 አባብለው ብለሽ፣
 ከሌላው (ከሌለው) ቀምተሽ፣
 እንባውን እያበሽ፣
 አይዞህ ብለሽ ሰጥተሽ።
 ደግሞ ሌላው ልጅሽ፣
ተበደልኩኝ ብሎ ሲመጣ ወደ አንቺ፣
 ሌላውን በድለሽ ችግር የምትፈቺ፣
 በ”ተበዳይ” እና በ”በዳይ” አዙሪት፣
 እየተሽከረከርሽ የማትሄጂ ወደፊት፣
 ምን አይነት እናት ነሽ?
 (ነሐሴ 26 ቀን 2012 ዓ.ም፤ዮናስ ታረቀኝ)

አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ የቀድሞዋን ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴን በመተካት የኢትዮጵያ ርዕሰ ብሔር ሆነው ከተሾሙ
ሳምንት አለፋቸው። አምባሳደሩ ለፓርላማው ባቀረቡት ንግግር የተለያዩ አስተያየቶች ተሰንዝረዋል፡፡ የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት
አሸኛኘትም አነጋጋሪ ሆኗል፡፡ የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የትግራይ ክልል አስተባባሪ አቶ ጊደና መድሕን
የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ሳሕለወርቅ ዘውዴ ስለተሸኙበት መንገድና ስለአዲሱ ፕሬዚዳንት የፓርላማ መክፈቻ ንግግር ሃሳብና
አስተያየታቸውን እንደሚከተለው አጋርተውናል፡፡


የቀድሞዋ ፕሬዚዳንት ስለተሸኙበት መንገድ--
በመጀመሪያ በጣም ነው የማመሰግነው። በመንግሥት ቴሌቪዥን ጣቢያዎች የመቅረብ ዕድል የሌለን ሰዎች ሃሳባችን እንዲሰማ፣ ሕዝቡም ዘንድ እንዲደርስና ሚዛናዊነት እንዲጠበቅ ለምታደርጉት ጥረት ታላቅ ክብር አለኝ።  የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ (ኢሕአፓ) የትግራይ ክልል አስተባባሪ ነኝ። ቀደም ሲል በትግራይ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ዋና ጸሐፊ፣ ከዚያም የትንሳዔ ሰብዓ ዕንደርታ ፓርቲ መስራችና ምክትል ሊቀ መንበርም ነበርኩ። አሁን በኢሕአፓ ውስጥ ነው የምገኘው።
 እንደ እኔ አተያይ -- አይደለም ስድስት ዓመት ያገለገሉ የመጀመሪያዋ ሴት ፕሬዚዳንት ይቅሩና ለማንም ሰው --  ክብር ሊኖረን ይገባል። ኢትዮጵያውያን ራሳችን ሳንከባበር ማንም ሊያከብረን አይችልም። ክብርት ፕሬዚዳንቷ የፈለጉት ዓይነት የፖለቲካ አቋም ሊኖራቸው ይችላል፤ በመጨረሻም በራሳቸው የማሕበራዊ ትስስር ገጽ ያስተላለፉትን መልዕክት የምናውቀው ነው። ማንኛውም ሰው የፈለገውን የፖለቲካ አቋም ያራምድ፣ ኢትዮጵያ የሁላችንም እስከሆነች ድረስ፣ አንድ ዓይነት አስተሳሰቦችን ብቻ ሳይሆን፤ የተለዩ ሃሳቦች መንሸራሸር አለባቸው የሚል አቋም ነው ያለኝ፡፡ ፕሬዚዳንቷም  ስላገለገሉበት ጊዜ በክብር ሃሳባቸውን ገልጸው፣ ፓርላማውም ሃሳባቸውን ሰምቶ በክብር ሊሸኛቸው ይገባ ነበር ብዬ አምናለሁ፡፡ የተሄደበት መንገድ የፖለቲካ ልሂቆቻችን  ልዩነትን የሚያስተናግዱበት መንገድ ምን ያህል ደካማ እንደሆነ ነው ያሳየኝ። እንደ አንድ ፖለቲከኛ በጣም ያዘንኩበትና በጣም ቅር ያለኝ ጉዳይ ነው፡፡  ድሮ በስድሳዎቹ በነበሩት ፖለቲከኞች የምናያቸው ችግሮች አሁንም እንዳልተፈቱ ነው ያየሁት። ይሄ  ኢትዮጵያን እየመሩ ያሉ ሰዎች ልዩነትን የማስተናገድ አቅማቸው ወይም ትችትን የሚሸከመው ትከሻቸው ምን ያህል ለስላሳና ደካማ እንደሆነ ነው የሚያሳየው።
ስለ አዲሱ ፕሬዚዳንት ንግግር--
እንግዲህ ለእኔ የአገሪቱ ፕሬዚዳንት ማለት ገለልተኛ ናቸው፤ ከማንም ጋር የማይወግኑ፡፡ ለእያንዳንዱ 120 ሚሊዮን ለሚገመት ደቂቅ ኢትዮጵያዊ አባት ናቸው። መሪ ናቸው። ስለዚህ ሁላችንንም በእኩል ዓይን ማየት አለባቸው፡፡ ነገሮችን ፖለቲካዊ ቀለም ከመቀባባት ይልቅ የማቻቻል፣ ወደ መፍትሔና አንድነት የማምጣት ትልቁን ሚና መጫወት ያለባቸው ክቡር ፕሬዚዳንቱ ናቸው ብዬ ነው የማስበው። በአንዳንድ ሚዲያዎች እንደሰማሁት ከሆነ፣ አዲሱ ፕሬዚዳንት ጦርነቱ እንደሚቀጥልና የመሳሰሉ ወደ አንድ ጽንፍ፣ በተለይም ወደ ገዢው ፓርቲ ጥግ የሄደ አቋም ነው ያየሁባቸው።
በእርግጠኝነት፣ እኔ ከአንድ የኢትዮጵያ ፕሬዚዳንት የምጠብቀው ዓይነት ንግግር አይደለም፡፡ ወደ አንድ ወገን፣ ወደ አንድ ጽንፍ፣ ወደ አንድ አቅጣጫ የሄዱ ነው የሚመስለኝ፡፡ ይህንን ከእርሳቸው የምጠብቀው አይደለም። እርሳቸው ይበልጡኑ የክብር ፕሬዚዳንት ናቸው። ተምሳሌት ናቸው። የክብር ስራዎችን ነው የሚሰሩት። ለምሳሌ፦ የሌሎች አገራት አምባሳደሮች ሲመጡ መቀበል፣ ከክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር የእኛን አምባሳደሮች መሸኘት፣  ጄኔራሎች በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲቀርቡ የመሾም የመሳሰሉት ተግባራት አገርን ከፍ፣ ሕዝብን ደግሞ አንድ የሚያደርጉ በይበልጥ ተምሳሌታዊ የሆኑ ናቸው። ከየትኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ መሆን ይጠበቅባቸዋል። ሁሉንም ኢትዮጵያዊ -- ተፎካካሪውንም፣ ገዢውንም ---  በአንድ ዓይን መመልከት አለባቸው። ምናልባት ይህንን በቀጣይ ያስተካክሉት ይሆናል። በተለይ እየተዋጉ ያሉ ሃይሎችን ወደ ዕርቅና አንድነት በማምጣት ረገድ  ተምሳሌታዊ ሚና ይጫወታሉ ብዬ ነው የማስበው።
ከአዲሱ ፕሬዚዳንት የምጠብቀው---
አሁን በፕሬዚዳንትነት የተሾሙት አምባሳደር ታዬ አጽቀስላሴ፣ በኢትዮጵያ የፖለቲካ ምሕዳር ውስጥ ከወጣትነታቸው ጀምረው በለሳ ላይ ነፍጥ ይዘው የኢሕአፓ ታጋይ ሆነው የተዋጉ፤ ከእነ አቶ በረከት ስምዖን፣ ኢሕዴን ከመሆናቸው በፊት፣ ከእነ አቶ አዲሱ ለገሰ ጋር የነበሩ የኢሕአፓ ታጋይ ናቸው። በደንብ ፖለቲካን የሚረዱ፣ የሚያውቁ በተለይ ከ1960ዎቹ ጀምሮ  የነበረውን ፖለቲካ መረዳት ብቻ ሳይሆን፣ እራሳቸውም ተሳታፊ የነበሩ  ሰው ናቸው። ከዚያም ቀጥለው ከ1984 ጀምረው በኢሕአዴግ መንግሥት ውስጥ ከፍተኛ ሃላፊነት የነበራቸው፣ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ውስጥ ዋና ዲፕሎማት ሆነው ያገለገሉ ናቸው፡፡ ምናልባት ኢትዮጵያ ውስጥ ካሉ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ይረዳሉ ብዬ ከምጠብቃቸው ጥቂት ሰዎች አንዱ ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ በጣም የዳበረ የዲፕሎማሲና የፖለቲካ ልምድ ያላቸው ሰው ናቸው። ይህ  ሰብዕናቸው ለነገይቱ ኢትዮጵያ ትልቅ ሚና ይጫወታል ብዬ አምናለሁ፡፡ በተለይ ትግራይ ውስጥ ያለው የፖለቲካ ችግር ይታወቃል። አማራ ክልል ያለውም ችግር ይታወቃል። ኦሮሚያ ውስጥም እንዲሁ። ሰላም ከራቀን ቆይቷል። ምንም እንኳን ስልጣናቸው የተገደበ ቢሆንም፣ እኒህን ችግሮች ከመፍታት አንጻር ፕሬዚዳንቱ በጎ ተጽዕኖ ማሳደር ይችላሉ የሚል እምነት አለኝ፡፡



የኢትዮጵያ ብር ከሰሃራ በታች  ደካማ ከሚባሉት ገንዘቦች ተርታ መመደቡን የዓለም ባንክ ባወጣው ሪፖርት አስታውቋል። የዓለም ባንክ አፍሪካ ፐልስ  ሪፖርት ላይ እንደተገለጸው፣ ከኢትዮጵያ ብር ባሻገር የናይጄሪያ ናይራ እና የደቡብ ሱዳን ፓውንድ  በቀጣናው “እጅግ ደካማ” ከሚባሉት ገንዘቦች መካከል ተመድበዋል፡፡  
በዚሁ ሪፖርት ላይ “እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2024 የኢትዮጵያ ብር፣ የናይጄሪያ ናይራ እና የደቡብ ሱዳን ፓውንድ በቀጣናው እጅግ በጣም ደካማ አፈጻጸም ካላቸው ገንዘቦች መካከል ነበሩ” ሲል ይገልጻል። በአንፃሩ ግን እንደ ኬንያ ሽልንግ ያሉ ገንዘቦች ከነበሩበት ደካማነት የማገገም  ምልክቶችን  አሳይተዋል ተብሏል፡፡  
እ.ኤ.አ. በነሐሴ 2024 በዓመት እስከ 21 በመቶ የዋጋ ጭማሪ ማስመዝገባቸውን ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ “ይህ መሻሻል ቢታይም፣ የብዙ አፍሪካ አገራት ምጣኔ ሃብት የውጭ ምንዛሪ ተግዳሮቶች እየገጠመው ነው” ተብሏል። በዚሁ ሪፖርት መሰረት፤ ናይጄሪያ ከሌሎች የቀጣናው አገራት ጋር ከፍተኛ የውጭ ምንዛሪ ዕጥረትና የምንዛሪ ተመን  ጫና እያጋጠማት እንደሆነ ተብራርቷል።  
ናይጄሪያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያን ብትተገብርም፣ የአገሪቱ ገንዘብ  አሁንም እየታገለ መቀጠሉን  ሪፖርቱ ይጠቁማል፡፡ ነገር ግን በኢትዮጵያ የውጭ ምንዛሪ ገበያ ማሻሻያ ተፅዕኖው ገና አልታየም። ኢትዮጵያ እ.ኤ.አ. በጁላይ 2024 የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያን የተገበረች  ሲሆን፣ ይህም በገንዘቧ የመግዛት አቅም ላይ ከፍተኛ መዳከም ማስከተሉ ይታወቃል፡፡  
በሌላ በኩል፤ ኢትዮጵያን ጨምሮ 26 ሃገራት ባለፉት ሁለት ዐሥርተ ዓመታት ውስጥ የከፋ የብድር አዘቅት ውስጥ እንደሚገኙ የዓለም ባንክ ይፋ አድርጓል። የተጠቀሱት ሃገራት እጅግ ደካማ ኢኮኖሚ እንዳላቸው ተገልጧል። በዋናነት የኮቪድ 20 ወረርሽኝ መቀስቀስና ግጭቶች የአገራቱን ኢኮኖሚ ይበልጥ ማድቀቃቸውም ተጠቁሟል።

የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር፣ የ2024 የዓለም ቱሪዝም ቀንን ምክንያት በማድረግ፣ የመጀመሪያውን የቱሪዝም የመገናኛ ብዙኃን የሽልማት ፕሮግራም ከትላንት በስቲያ ጥቅምት 7 ቀን 2024 ዓ.ም  አካሂዷል፡፡
የዘንድሮ የቱሪዝም ቀን “ቱሪዝም እና ሰላም” በሚል መሪ ቃል የሚከበር ሲሆን፤ ማህበሩ ባለፈው ሐሙስ ከቀኑ 11 ሰዓት ጀምሮ በአዲስ አበባ ሙዚየም ቅጥር ግቢ ባካሄደው የሽልማት መርሃ ግብር፣ በሚዲያው ዘርፍ ቱሪዝሙ ላይ አስተዋጽኦ ላበረከቱ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች፣ የመገናኛ ብዙኃን ተቋማት፣ፎቶግራፈሮች እንዲሁም የቱሪዝም ባለሙያዎችና ድርጅቶች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
ለማህበሩ የመጀመሪያው በሆነው በዚህ የሽልማት መርሃግብር 10 ተቋማትና ግለሰቦች  ዕውቅና ያገኙ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን (በሚዲያ ዘርፍ)፣ አንድነት ፓርክ (በመዳረሻ ልማት ዘርፍ)፣ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ማሰልጠኛ ኢንስቲቲዩት (በቱሪዝም ተቋማት ዘርፍ)፣የኃይሌ ሆቴሎችና ሪዞርቶች ግሩፕ (በሆቴልና ሆስፒታሊቲ ዘርፍ)፣ ቴዎድሮስ ደርበው (በቱሪዝም ባለሙያ ዘርፍ)፣ ሄኖክ ያሬድ (በጋዜጠኝነት ዘርፍ)፣ ጸሃይ ተፋረደኝ (በጋዜጠኝነት ዘርፍ)፣ አንቶኒዮ ፍዮሮንቴ (በፎቶግራፍ ዘርፍ)፣ ህሊና ታፈሰ (በፎቶግራፍ ዘርፍ) እና አርቲስት ኪሮስ ኃ/ሥላሴ (በልዩ ተመስጋኝ ዘርፍ) ተሸልመዋል፡፡   
ከትላንት በስቲያ በተካሄደው የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሽልማት መርሃግብር ላይ ከፍተኛ የመንግሥት ባለሥልጣናት፣ ታዋቂ የዘርፉ ባለሙያዎችና ጋዜጠኞች ታድመዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባህልና ቱሪዝም ጋዜጠኞች ማህበር፣ የኢትዮጵያን ተፈጥሮአዊ፣ ባህላዊና ታሪካዊ መስህቦች የሚያስተዋውቁ የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ያቋቋሙት የሙያ ማህበር ነው፡፡


ከ35 በላይ ዳኞች ያላግባብ ታስረው ተፈተዋል


በአማራ ክልል  ከ35 በላይ ዳኞች ያለአግባብ ታስረው መፈታታቸውን ያመለከተው የአማራ ክልል ዳኞች ማሕበር፤ በክልሉ ዳኞችን ያለአግባብ ማሰር መቀጠሉን አስታውቋል፡፡  
ማሕበሩ ከትላንት በስቲያ  ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፣ የዳኝነት ነፃነት አንዱ መገለጫም ዳኞች ከማንኛውም አካል ጣልቃ ገብነትና ተፅዕኖ ነፃ ሆነው በሕግና በሕሊናቸው ብቻ እንዲሰሩ ማድረግ መሆኑን  አስታውሶ፤ “በአማራ ክልል ውስጥ ዳኞችን ያለአግባብ ማሰርና ማዋከብ የተለመደና ከአንድ ዓመት ወዲህ ደግሞ ተባብሶ የቀጠለና ሞትንም እስከማስከተል የደረሰ ሆኗል።” ብሏል፡፡
ባለፈው አንድ ዓመት ውስጥ በአማራ ክልል ሁሉም ዞኖች ከ35 በላይ ዳኞች ያለአግባብ ታስረው መፈታታቸውን ያመለከተው  ማሕበሩ፤ ዳኞቹ  በዋናነት እየታሰሩ የሚገኙት “ከስራቸው ጋር በተገናኘ” ምክንያት መሆኑን ጠቁሟል፡፡ “በወንጀል የሚፈለጉ እንኳን ቢሆን በሕግ አግባብ ምርመራ አጣርቶ መያዝ ሲገባ፣ ከሚያስችሉበት ችሎት ጭምር በአደባባይ በሚያገለግሉት ህዝብ ፊት እየተያዙ የሚታሰሩበት ሁኔታ እጅግ አደገኛና የተቋሙንም ነጻነት ጨርሶ እያጠፋ የሚገኝ ነው።” ሲል ማሕበሩ ተችቷል፡፡
ይኸው እስር “ዳኞች ስራቸውን በነፃነት እንዳይሰሩ እንቅፋት የሆነና ክብራቸውንም የሚነካ ነው፡፡ ሁሉም ዳኛ ለሙያው ያለው ፍቅር እንዲቀንስና የስራ ሞራልን እየጎዳ ያለ ተግባር ነው” ያለው መግለጫው፤ “እስካሁን ባለው ሂደትም የማሕበሩ አመራሮች በተለያየ እርከን ከሚገኙ የፍርድ ቤት አመራሮች ጋር በጋራ በመሆን ችግሩ በንግግር እንዲፈታ ጥረት ሲያደርጉ የቆዩ ቢሆንም፣ ችግሩ አሁንም ተባብሶ ቀጥሏል።” ሲል አመልክቷል።
በእስር ላይ ከሚገኙ የፍርድ ቤት ዳኞች መካከል፣ የባሕር ዳር እና አካባቢዋ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ሁለት ዳኞች፣ የባሕር ዳር ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት ሁለት ዳኞች፣ በሰሜን ሸዋ ዞን፤ በቀወት ወረዳ ፍርድ ቤት ሁለቱ የስራ ሂደት አስተባባሪ ዳኞችና በሸዋ ሮቢት ወረዳ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ እንዲሁም በደቡብ ወሎ ዞን፣ ደሴ ከተማ ወረዳ ፍርድ ቤት አንድ ዳኛ መታሰራቸውን ማሕበሩ በመግለጫው ዘርዝሯል። የአማራ ክልል፤ ዳኞቹ “በአስቸኳይ” እንዲፈቱ እንዲያደርግ፣ በቀጣይም በዳኞች ላይ የሚፈጸም “ያልተገባ” እስር እንዲቆምና ይህን ተግባር በሚፈፅሙ የጸጥታ አካላት ላይ አስተማሪ እርምጃ እንዲወሰድ ሲል ማሕበሩ አሳስቧል፡፡
የአማራ ክልል ዳኞች ማሕበር በ2012 ዓ.ም. ተመስርቶ ወደ ስራ መግባቱ የሚታወስ ነው።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ ኮሬ ዞን የሚስተዋለው የጸጥታ ችግር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ተገልጿል። በተደጋጋሚ ከሚከሰተው የጸጥታ ችግር በስተጀርባ አንዳች ፖለቲካዊ ዓላማ ሊኖር እንደሚችልም ተነግሯል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የኮሬ ተወካይና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ) አባል የሆኑት ዶ/ር  አወቀ አምዛዬ፣ እርሳቸው በሚወክሉት አካባቢ የሚከሰተው የጸጥታ ችግር በሁለት የጊዜ ምዕራፍ ተከፍሎ መታየት እንዳለበት ይገልጻሉ፤ የመጀመሪያው በቀደመው ጊዜ በግጦሽና ውሃ ምክንያት በሚፈጠሩ አለመግባባቶች ሳቢያ ከጉጂ ዞን የሚነሱ ታጣቂዎች ኮሬ ላይ የሚፈጽሟቸው ጥቃቶች እንደሆኑ ያነሳሉ፡፡ “በእነዚሁ ጥቃቶች ሳቢያ የተፈጠሩ ቁርሾዎች ከሁለቱም ወገኖች በኩል ባሉ ሽማግሌዎች አማካይነት በባሕላዊ መንገድ ይፈታሉ።” ይላሉ፤ የምክር ቤት አባሉ፡፡
በ1983 ዓ.ም. ኢሕአዴግ ወደ ስልጣን ከመጣ ወዲህ፣ እነዚህ ጥቃቶች ወደ ፖለቲካዊ “ፍትጊያዎች” ማደጋቸውን ዶ/ር አወቀ አምዛዬ  ይናገራሉ። ግንባሩ በስልጣን ላይ እያለ አልፎ አልፎ ጥቃቶች እንደሚፈጸሙ፣ ነገር ግን ሕዝቡ ወዲያውኑ ወደ ሰላማዊ ሕይወት እንደሚመለስ ያስታውሳሉ፡፡
“ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ግን ኮሬ ዞንን ከጌዲኦ ዞን ጋር የሚያገናኘው መንገድ መዘጋቱን ተከትሎ 20 ቀበሌዎች ደግሞ በታጣቂዎች ተወርረዋል። ታጣቂዎቹ በመንግስት በኩል ‘ሸኔ’ ተብለው ቢጠሩም፣ ሰፊ መዋቅር ያላቸውና ተጠናክረው የሚንቀሳቀሱ ሃይሎች ናቸው።” ብለዋል፣ ዶ/ር አወቀ። ጥቃቱ በተደጋጋሚ የሚፈጸመው ከጉጂ ዞን በሚነሱ ታጣቂዎች መሆኑን ፖለቲከኛው ጠቁመው፤ በታጣቂዎቹ ሁለት ቀበሌዎች ሙሉ በሙሉ እንደወደሙ ተናግረዋል፡፡
“አካባቢውን ሰው አልነበረበትም ለማሰኘት እንደ ሙዝና እንሰት ያሉ ተክሎች በታጣቂዎቹ እንዲወድሙ ተደርገዋል” የሚሉት የምክር ቤት አባሉ፤ በየቀኑ “ይወረራሉ” ያሏቸው 18 ቀበሌዎች እንዳሉ ጠቅሰው፣ “የቀበሌዎቹ ነዋሪዎች ይገደላሉ፣ ማሳቸው ይቃጠላል፣ ከብታቸው ይዘረፋል። ይህ ድርጊት በተለይ ከ2009 ዓ.ም. ወዲህ ተባብሶ ቀጥሏል።” ብለዋል።
ይህንኑ  የጸጥታ መደፍረስ በ2015 ዓ.ም. ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በተገኙበት የሕዝብ ተወካዮች ስብሰባ ላይ እኚሁ የኢዜማ የኮሬ ዞን ተወካይ አንስተውላቸው እንደነበር አስታውሰው፣ ነገር ግን ግልጽ ምላሽ ከጠ/ሚኒስትሩ እንዳልተሰጣቸው ተናግረዋል፡፡  “መሰረታዊ ዕርምጃ ተወስዶ ዘላቂ መፍትሔ ለማምጣት አልተቻለም። ለተወሰኑ ጊዜያት ወደ ኮሬ ተልኮ የነበረው የመከላከያ ሰራዊት ቁጥሩ ተቀንሷል። በዚህም ምክንያት በኮሬ ዞን የሚታየው የጸጥታ ስጋት እየጠነከረ እንጂ እየቀነሰ  አልመጣም።” ሲሉ ምልከታቸውን ለአዲስ አድማስ አጋርተዋል።
እንደ ዶ/ር አወቀ አምዛዬ  ገለጻ፤ ባሳለፍነው መስከረም ወር ብቻ 11 ሰዎች ሲገደሉ፣ የአገር ሽማግሌዎች ወደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት፤ ሰላም ሚኒስቴርና ኦሮሚያ ክልል ደጅ ቢጠኑም፣ ተጨባጭ ምላሽ  አልተሰጣቸውም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
“ግራ የሚያጋባ ነገር ነው። ችግሩ  ምንም መቋጫ አላገኘም። እኛም በተደጋጋሚ ለመንግስት አመልክተናል። ግን ምንም መፍትሔ የለም። በየቀኑ ግድያ እንሰማለን” ብለዋል።
አክለውም፤ “የአገር ሽማግሌዎች፣ እኛም፣ ሁሉም በየቦታው እየጮኸ ነው። ግን መፍትሔ የለም። ግራ የሚያጋባ ሁኔታ ነው። ሕዝቡ ከሚፈጸመው ጥቃት በስተጀርባ ፖለቲካዊ ዓላማ ሳይኖር ‘አይቀርም’ የሚል ጥርጣሬ አለው።” በማለት አስተያየታቸውን ቋጭተዋል፣ ዶ/ር አወቀ አምዛዬ።
የኮሬ ዞን መንግስት ኮሙኒኬሽን መምሪያ ተወካይ አቶ አማረ አክሊሉ ለአዲስ አድማስ ሲናገሩ፤ “የሟቾች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያሻቀበ ነው። ይህንን ጥቃት የሚያስቆም እስካሁን አልተገኘም” ብለዋል። ጥቃቱ የሚደርስበት ወቅት ከወርሃ ሃምሌ እስከ መስከረም 30 ድረስ የእርሻ ወቅት ላይ ነው፤ሲሉም አክለዋል።
“በዚህ ሳቢያ ገበሬው እርሻውን ማረስ አልቻለም” ያሉት አቶ አማረ፤ “ከምዕራብ ጉጂ ዞን፣ ገላና እና ሱረበርጉዳ ወረዳዎች የሚንቀሳቀሱ የ“ሸኔ” ታጣቂዎችና ከሸኔ ውጪ የታጠቁ ሃይሎች ናቸው በኮሬ ላይ ጥቃት የሚያደርሱት” ብለዋል። “አደብ የሚያስገዛ” አካል ባለመገኘቱ ሳቢያ፣ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ብር በላይ የሚገመት ንብረት ለዝርፊያ መዳረጉን፣ ቁጥራቸው በውል የማይታወቅ ከብቶች በታጣቂዎች መዘረፋቸውንም ተወካዩ አስረድተዋል።
በ18ቱ ቀበሌዎች የሚኖሩ ነዋሪዎች ቀዬአቸውን ለቅቀው እንዲወጡ የቀድሞ የገላና ወረዳ  አመራሮች በ2009 ዓ.ም. ላይ ወስነው የነበረ ሲሆን፣ ይህን ተከትሎ አለመረጋጋትና ግጭት ተፈጥሮ ለተወሰኑ ወራት ቆይቶ እንደነበር ያወሱት አቶ አማረ፤ ሐምሌ 16 ቀን 2009 ዓ.ም. የተቀሰቀሰውን አለመረጋጋትና ግጭት ተከትሎ፣ በሌሎች ጊዜያት የተፈጸሙ ጥቃቶችን በዕርቅ ለመፍታት ሦስት ጊዜ ሙከራዎች መደረጋቸውን አብራርተዋል።
እነዚህ ሙከራዎች ፍሬ አለማፍራታቸውን ያነሱት አቶ አማረ፣ ያለመሳካታቸው ዋነኛ ምክንያት “የመሬት ይገባኛልን ጨምሮ በሁለቱም ወገኖች የሚነሱትን ጥያቄዎች በአግባቡ ያለመረዳት ችግር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የደቡብ ኢትዮጵያና ኦሮሚያ ክልሎች “ጉዳዩ ከአቅማችን በላይ ነው” የሚል  መልስ እንደሰጡ፣ የሰላም ሚኒስቴር የተጣለበትን ሃላፊነት በአግባቡ እንዳልተወጣ  አቶ አማረ ለአዲስ አድማስ ተናግረዋል፡፡
ይህን ከግምት ውስጥ በማስገባት  መንግሥት፣ መገናኛ ብዙኃንና የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ሕዝቡን እንዲታደጉ በኮሬ ሕዝብ ስም ጥሪ አስተላልፈዋል፣ ዶ/ር አወቀ አምዛዬና  አቶ አማረ አክሊሉ።
በተያያዘ ዜና፣ የኢትዮጵያ ዜጎች ለማሕበራዊ ፍትሕ (ኢዜማ)፣ በኮሬ በሚስተዋለው የጸጥታ መደፍረስ ዙሪያ ባለፈው ሐሙስ ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ፤ “መንግሥት ጥቃቱን እያደረሱ ያሉት አካላት ማንነትን ይፋ እንዲያደርግ፣ በሕግ ፊት አቅርቦ ተገቢውን የሕግ እርምጃ እንዲወሰድባቸው፣ የኮሬ ሕዝብም ከተፈናቀለበት ወደ ቀዬው እንዲመለስና መልሶ በማቋቋም ሕይወቱን ተረጋግቶ እንዲኖር  በማድረግ መንግሥታዊ ሃላፊነቱን እንዲወጣ በአፅንዖት እንጠይቃለን።” ሲል አሳስቧል።

ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲሾሙ፣
ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ የፍትህ ሚኒስትር ተደርገው ተሾሙ

የፍትህ ሚኒስትር የነበሩት ዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ፤ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው መሾማቸውን የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታወቀ።  
ላለፉት ስምንት ወራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆነው ሲያገለግሉ የነበሩት አምባሳደር ታዬ አጽቀ ሥላሴ የአገሪቱ ርዕሰ ብሔር ሆነው መሾማቸውን ተከትሎ ነው፣ ዶ/ር ጌዲዮን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርን እንዲመሩ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የተሾሙት።
በተጨማሪም፣ ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ  በዶ/ር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ  ምትክ የፍትህ ሚኒስትር  በመሆን ሲሾሙ፣ የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ሚኒስቴር ዴኤታ የነበሩት ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የቱሪዝም ሚኒስትር ተደርገው  ተሾመዋል። ወ/ሮ ሰላማዊት ካሳ የአዲስ አበባ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ የኮሚዩኒኬሽን ሚኒስትር ዴኤታ ከመሆናቸው በፊት በፋና ብሮድካስቲንግና በሌሎች መገናኛ ብዙኃን በጋዜጠኝነት መሥራታቸው ይታወቃል፡፡
ወ/ሮ ሃና አርአያ ሥላሴ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ፖስታ አገልግሎት ሥራ አስኪያጅና የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ኮሚሽነር ሆነው አገልግለዋል፡፡


“ከህወሓት እጅ  የወጣው ስልጣን ወደ ህወሓት መመለስ አለበት”

በዶ/ር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል  የሚመራው የህወሓት ቡድን ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ጥቅምት 7 ቀን 2017 ዓ.ም. በመቐለ፣ ሰማዕታት ሐውልት አዳራሽ ከባለሃብቶች ጋር ባካሄደው ስብሰባ፣ እርሳቸው የሚመሩት ቡድን ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርግ አስታውቋል፡፡ በዚሁ ስብሰባ ላይም፣ ከምርጫ ቦርድ ህጋዊ ዕውቅና ባልተሰጠው ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያልተሳተፉትንና በቡድናቸው የተባረሩትን የድርጅቱን አመራሮች ወቅሷል፡፡
“ጉባዔ እንዳናካሂድ ብዙ ሙከራ ተደርጎብናል፡፡ ጉባዔ አለማካሄድ ድርጅቱን ማፍረስ ነው። ይሁንና ወደ ጉባዔ የመጨረሻ ደረጃ ላይ ደርሰን እያለ፣ እነርሱ ግን ‘አንገባም’ ብለው አንገራገሩ። ‘ጉባዔው ከተካሄደ ጦርነት ይከተላል’ ተባለ። የጉባዔው ተሳታፊዎች ጉባዔው ወደሚካሄድበት ቦታ እንዳይመጡ ጥረት ተደርጓል።” ሲሉ ዶ/ር ደብረጽዮን ተናግረዋል፡፡
 በጉባዔው ላይ እርሳቸው የሚመሩት የህወሓት ቡድን ያለፉትን ስድስት ዓመታት ፖለቲካዊ ስራዎች መገምገሙን የጠቆሙት ዶ/ር ደብረጽዮን፤  “በዚህ ጉባዔ ተበትኖ የሚገኘውን ሕዝባችንን ወደ ቀድሞ ቀዬው እንዲመለስ፣ መሬታችን ተመልሶ በእኛ አስተዳደር ስር እንዲሆን፣ ተጠያቂነት እንዲረጋገጥና በኢኮኖሚ ግንኙነቶችና በሌሎች ተጀምረው በነበሩ ጉዳዮች ላይ ጥናት በማካሄድ እንቅስቃሴው ዳግም እንዲጀመር ውሳኔዎችን አስተላልፈናል” ብለዋል።
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን የህወሓት፣ የትግራይ ሃይሎች፣ የምሁራንና ተቃዋሚ ድርጅቶች በመቀናጀት እንደመሰረቱት በማስረዳት፣ “ለአስተዳደሩ የጊዜ ገደብ አስቀምጠንለት ነበር። ይሁንና በክልላችን ሰላም ልናሰፍን አልቻልንም። ሕዝባችን ወደ ቀዬው አልተመለሰም። ባለሃብቶችና ነጋዴዎች ትግራይን መልሶ ወደ መገንባቱ ሊገቡ አልቻሉም። እነዚህ ተግባራት በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም። ይህ ሁሉ የተፈጠረው ጊዜያዊ አስተዳደሩ መምራት ባለመቻሉ ነው” ሲሉ ወቀሳቸውን ሰንዝረዋል፡፡
“የትግራይ ክልል ብሔራዊ ጥቅም”  አደጋ እየተጋረጠበት መሆኑን የጠቆሙት ሊቀመንበሩ፤ “የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች የትግራይ ሕዝብን ለመበተን በአካባቢያዊነት ላይ አትኩረው እየሰሩ ናቸው” በማለት አብጠልጥለዋቸዋል። “ሃላፊነት ስላለብን ጊዜያዊ አስተዳደሩ እንዲፈርስ አንሻም። መንግሥትን የመጥላት ፍላጎት የለንም። በውስጣችንም ሆነ በፌደራል መንግሥቱ በኩል ያሉንን ጉዳዮች በውይይት ‘እንፍታ’ ነው ያልነው፡፡ ግለሰብ ግን ተቋም እንዲሆን አንፈቅድም። ከሁሉም ወገን ጋር በመግባባት አሰራሮች መከናወን እንዳለባቸው እናምናለን። ለዚህም እየሰራን ነው” ሲሉም ለተሰብሳቢዎቹ አስረድተዋል፡፡
እርሳቸው የሚመሩት የህወሓት ቡድን ሰላማዊ ትግል እንደሚያደርግ ያስታወቁት ሊቀ መንበሩ፤ “ሃላፊነት በተሞላበት መንገድ እንሰራለን” ብለዋል። ወደፊት እንደሚደረግ የተገለጸው ሰላማዊ ትግል፣ “ጊዜያዊ አስተዳደሩ ብቃት ባላቸው አመራሮች  ስር ሆኖ የተሰጡትን ቁልፍ ሃላፊነቶች በተገቢው መንገድ እስኪተገብር ድረስ” እንደሆነም ሊቀመንበሩ አስታውቀዋል፡፡   
በዶ/ር ደብረጽዮን  የሚመራው የህወሓት ቡድን ጽሕፈት ቤት ሃላፊ ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚአብሔር ከቀናት በፊት ከመቐለ ከተማ ነዋሪዎች ጋር ባደረጉት ውይይት፤ “ከህወሓት እጅ  የወጣው ስልጣን ወደ ህወሓት መመለስ አለበት። ይህን ለማድረግም ሕዝባችንን እናስረዳለን፤ እናነሳሳለን። በየደረጃው ዙሩን እያከረርን እንሄዳለን። በሕዝባዊ አመፅ ስልጣኑን እንዲለቅ እናደርገዋለን” ሲሉ መናገራቸው የሚታወስ ነው።


Saturday, 19 October 2024 12:13

ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም!..

ከዕለታት አንድ ቀን አንድ ሰው ወደ አንድ ልብስ ሰፊ ይሄዳል፡፡ ከዚያም፤
“ይሄውልህ ይሄን ምን የመሰለ ሙሉ ሱፍ እንደተሰፋ ገዝቼ እጅጌው ረዘመብኝ፡፡ ስለዚህ ይሄንን እጅጌ ትንሽ እንድታሳጥርልኝ እፈልጋለሁ፡፡ ምን ይመስልሃል?” ሲል ይጠይቀዋል፡፡
ልብስ ሰፊውም፤  “የለም ይሄ ማሳጠር ላያስፈልገው ይችላል፡፡ ዝም ብለህ ክንድህን እዚህ እክርንህ  ጋ አጠፍ ማድረግ ነው፡፡ አየኸው እጅጌህ ወደ ውስጥ እንደገባ?..” ይለዋል፡፡
ሰውዬው የተባለውን ካደረገ በኋላ በመስታወት ሲያየው ኮሌታው ደሞ ወደ ማጅራቱ ተሰቅሏል፡፡
ስለዚህ፤  “ኮሌታዬ ደግሞ አላግባብ ወደ ማጅራቴ ወጣብኝ፤ ይሄው ግማሽ ጭንቅላቴን ሸፈነውኮ! ምን ይሻላል?..” ሲል ጠየቀው፡፡
ልብስ ሰፊውም፤ የሰውዬውን ጭንቅላት ወደ ኋላ ቀና እያደረገ፣ “..በቃ ጭንቅላትህን ወደ ኋላ እንዲህ ቀና አድርገህ ስትለጥጠው ልክ ይገባል..” ይለዋል፡፡
ሰውዬው፤ “..አሁን ደግሞ ግራ ትከሻዬ በሦስት ኢንች ያህል ከቀኝ ትከሻዬ ወደ ታች ወረደ..”
ልብስ ሰፊው፤ “..ችግር የለም፡፡ ከወገብህ በኩል ወደ ግራ ጠመም በል፡፡ ልክ ይገባል፡፡..”
ሰውዬው እንደተባለው ወደ ግራ ከወገቡ ተጣመመ፡፡
ልብስ ሰፊውም፤ “..አሁን ትክክል ሆነሃል፡፡ ሱፉም ልክክ ብሏል፡፡ ገንዘብህን ከፍለህ መሄድ ትችላለህ..” አለው፡፡ ገንዘቡን ከፍሎ ሲወጣ የሰውዬው ቅርጽ እጅግ አስገራሚ ሆነ፡፡ የግራ ክርኑ ተንጋዶ ወደ ውጪ ወጥቷል፡፡ ጭንቅላቱ ወደ ኋላ ተገትሯል፡፡ ወገቡ ወደ ግራ ጥምም ብሏል፡፡ ለመራመድ የሚችልበት ብቸኛ መንገድ ግራና ቀኝ እግሩን እያጠላለፈ እየተወለጋገደ ነው፡፡
እንዲህ እየተወለጋገደ በመሄድ ላይ ሳለ ሁለት መንገደኞች ያዩታል፡፡
አንደኛው፤ “ያን ምስኪን ሽባ ሰውዬ ተመልከተው፡፡ አንጀቴን ነው የበላው፡፡ አያሳዝንም?”
ሁለተኛው፤  “ያሳዝናል፡፡ ግን በጣም የሚደነቀው ልብስ ሰፊው ነው፡፡ ይሄ ሱፍ ልብስ ለዚህ ውልግድግድና ጥምም ላለ ሰው እንዲስማማ አድርጎ ሙሉ ሱፍ እንዲለብስ ማድረግ ትልቅ ጭንቅላት ይጠይቃል፡፡ ያ ልብስ ሰፊ ሊቅ መሆን አለበት!!” አለ፡፡
***
ምሁራን ሆኑም አልሆኑም፣ ፖለቲከኞች ሆኑም አልሆኑም፣ ቀራጮች ሆኑም አልሆኑም ባለሙያዎች ሆኑም አልሆኑም፤ እጅጌ ለማስተካከል ሰውዬውን አጣመው መልቀቃቸው ደግ ነገር አይደለም፡፡ ስህተት ለማረም ሌላ የተጣመመ ስህተት መሥራት የለብንም፡፡ ክርኑን ለማዳን አንገቱን መገተር፣ አንገቱን ለማዳን ወገቡን ማጣመም፤ በመጨረሻም ሰውዬው እንዳይራመድ አርጎ ማሽመድመድ ከቶም አያሳድገንም፡፡ አንድ የአገራችን ፀሃፊ እንዳለው፤ “..የአበሻንግድ የሌላውን ሥራ ማሽመድመድ፡፡ የአበሻ መኪና አነዳድ
በሌላው መንገድ መገድገድ፡፡..” እንዳይሆን ነገረ-ሥራችን፤ ቀና እንሁን፡፡ ከድጡ ወደ ማጡ ነው የሚከተን፡፡ ሌሎች ካላለቀሱ እኔ አልስቅም ዓይነት አስተሳሰብ ቢያንስ ሳዲዝም ነው - በሌሎች ሥቃይ መደሰት፡፡
ሁሉን ጥቅም በሀሰት ሰነድ፣ በአየር - ባየር ገፈፋ ካላገኘሁ የሚል ስግብግብ እንዳለ ሁሉ ንፁህ ነጋዴ መኖሩን በቅጡ ማስተዋል ያስፈልጋል፡፡  ለሀገር በሚጠቅም መንገድ ሂሳቡን የሚሠራ ቢሮና ሠራተኛ እንዳለ ሁሉ፣ ያለማምታታትና ያለግል ኪስ የማይንቀሳቀስ መኖሩንም ልብ ማለት ተገቢ ነው፡፡ የመንግሥት ሠራተኛ የመንግሥት ላይሆን እንደሚችል ሁሉ፤ የግልም የግል ላይሆን ይችላል፡፡ በአገራችን የቤት ልጅ መበደልና ..”እንግዳ ተቀባይ መሆናችንን ማረጋገጥ”.. የተለመደ ነገር ነው፡፡
 “እያንዳንዱ ትውልድ የዱላ ቅብብል የሚጫወትበት እያልን”  የአንድ ትውልድ ብቻ መጫወቻ እንዳናደርገው መጠንቀቅ ይገባል፡፡ ስለገቢ ፍትሐዊነት እየተናገርን፣ ገቢውንም ፍትሁንም እንዳናጣ እናስብ፡፡ The Holy Roman Empire was neither Holy nor Roman nor an Empire እንደተባለው እንዳይሆን (የተቀደሰችው የሮማ ግዛተ - ነገሥት፤ ቅድስትም፣ ሮማዊም፣ ግዛተ - ነገሥትም አልነበረችም፤ እንደማለት ነው)
ታዋቂው ፀሀፌ - ተውኔት ፀጋዬ ገ/መድህን በአንደኛው ተውኔቱ ውስጥ “አንዲት የዱር አውሬ፣ ልጅ በመውለጃዋ ሰሞን ልጇን ትበላለች አሉ፣ ምጥ የጠናባት እንደሆን..” የሚለን ለዚህ ነው፡፡
መልካም እንቅልፍ ለመተኛት መልካም ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡ ከግፍ መራቅ ያሻል፡፡ ከፖለቲካም ሆነ ከኢኮኖሚ ሸር መራቅ ይገባል፡፡ በፈረንጅ አገር አንድ ሰው ለአገሩ አገር ውስጥ ገቢ እንዲህ የሚል ማስታወሻ ጽፎ ነበር :- “የከፈልኩትን ታክስ አጭበርብሬ የከፈልኩ ስለሆነ እንቅልፍ መተኛት አቃተኝ፡፡ ገቢዬን ዝቅ አድርጌ አስገምቼ ነው፡፡ ስለዚህ የ150 ዶላር ቼክ ልኬላችኋለሁ፡፡ ይህም ሆኖ እንቅልፍ እምቢ እሚለኝ ከሆነ ግን ቀሪውን እልክላችኋለሁ፡፡”
ቼኩን በእጁ ያስገባው፤ የአገር ውስጥ ገቢ ሠራተኛውም “..እኔም ቀሪዋን እስክትልክ እንቅልፍ የሚወስደኝ አይመስለኝም..” ብሎ ፃፈለት፡፡ እንቅልፍ ከሚያሳጣ ዘመን ይሰውረን! አንድ የኢትዮጵያ አጎት ደግሞ የእህታቸው ልጅ ይሄንንም ግዛ ይሄንንም ግዛ እያለ ሲያስቸግራቸው፤  “አዬ፤ ልጅና ቀራጭ ችግር አያቅም” አሉ ይባላል፡፡ የሰማነውን በልቦናችን ያሳድርብን፡፡

Page 3 of 732