Administrator

Administrator

     የየመን ሁቲዎች በባብኤል መንደብ በሚገኙ ደሴቶች ላይ ያከማቹት ከባድ የጦር መሳሪያ በአለምአቀፉ የመርከብ እንቅስቃሴ ላይ ስጋት እንደጋረጠ የጠቆመችው ጅቡቲ፤ በሳዑዲ አረቢያ የሚመራውና የመን ላይ ወታደራዊ እርምጃ በመውሰድ ላይ የሚገኘው ጥምር ሀይል እንዲያስወግደው ጠየቀች፡፡
በአለም አቀፍ ደረጃ ብዙ የባህር ላይ እንቅስቃሴዎችን በማስተናገድ የሚታወቀው የቀይባህር የፀጥታና ደህንነት ሁኔታ በየመኑ ሁቲ አማፂያን ምክንያት ስጋት እንደተጋረጠበት መረጃዎች ይጠቁማሉ። ኢትዮጵያ በብቸኝነት የምትጠቀምበት ወደብ ባለቤት የሆነችው ጅቡቲ፤ የሁቲዎቹ እንቅስቃሴ በአለም አቀፉ የመርከቦች ደህንነት ላይ ስጋት መደቀኑን አስታውቃለች፡
የጅቡቲ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር መሀሙድ አሊ ዩሱፍ ሰሞኑን በሰጡት መግለጫ፤ አገራቸው ጥምር ሀይሉን እንደምትደግፍ ጠቁመው በባብኤል መንደብ ሰርጥ  ባሉ ደሴቶች ላይ በሁቲዎች የተከማቸው ከባድ የጦር መሳሪያ ለአለም አቀፍ የመርከቦች ዝውውር ስጋት በመሆኑ በጥምር ሀይሉ እንዲወገድ ጠይቀዋል፡፡
 በቀይባህር በኩል የተፈጠረው የፀጥታና የደህንነት ስጋት በኢትዮጵያ መርከቦች ጉዞ ላይ የፈጠረውን ሁኔታ በተመለከተ ለማጣራት ያደረግነው ሙከራ ሳይሳካ ቀርቷል፡፡

    ታዋቂው የመኪና አምራች ኩባንያ ሃዩንዳይ ሞተር፤ የሾፌር እገዛ ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ለሙሉ በራሳቸው መንቀሳቀስ የሚችሉበት ቴክኖሎጂ የተገጠመላቸውን ዘመናዊ መኪኖች አምርቶ በመጪዎቹ አምስት አመታት ውስጥ ለአለም ገበያ እንደሚያቀርብ አስታወቀ፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመጣው የዓለማችን የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ የቴክኖሎጂ ውድድር ተፎካካሪ ሆኖ በመዝለቅ ላይ ያለው የደቡብ ኮሪያው የመኪና አምራች ኩባንያ ሃዩንዳይ፣ እነዚህን መኪኖች እ.ኤ.አ እስከ 2020 በገበያ ላይ እንደሚያውል ባለፈው ማክሰኞ ማስታወቁን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ሃዩንዳይ ሞተር፤ ከዚህ በፊትም በተለየ ሁኔታ ባመረታቸው ጄነሲስን የመሳሰሉና እግረኛ ድንገት ወደ መንገድ ሲገባ ያለ ሾፌሩ ትዕዛዝ ፍሬን የሚይዙ ውድ መኪናዎቹ ላይ፣ መሰል ቴክኖሎጂዎችን መግጠሙን ዘገባው አስታውሷል፡፡
የጀርመኑን መርሴድስና የአሜሪካውን ጄኔራል ሞተርስ የመሳሰሉ ታላላቅ የዓለማችን የመኪና አምራች ኩባንያዎች እንዲሁም፤ ጎግልንና አፕልን የመሳሰሉ የቴክኖሎጂው ዘርፍ ፊታውራሪዎች፣ ምንም አይነት የሰው ድጋፍ ሳያስፈልጋቸው ሙሉ ለሙሉ ራሳቸውን ችለው ረጅም ርቀት መሽከርከር የሚችሉ መኪናዎችን ከዚህ ቀደም ማምረታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ይሄም ሆኖ ግን፣ አንዳንድ ተንታኞች ሾፌር አልባ መኪናዎች፣ ከአገራት ጥብቅ የትራንስፖርት ህጎችና አደጋን ለመከላከል ሲባል ከወጡ መመሪያዎች ጋር በተያያዘ በአፋጣኝ ተቀባይነት ያገኛሉ ብለው እንደማያስቡ መናገራቸውን የጠቀሰው ዘገባው፤ እ.ኤ.አ እስከ 2020 አጋማሽ ድረስ ለአለማቀፍ ገበያ ይቀርባሉ የሚል ግምት እንደሌላቸው መግለጻቸውንም አመልክቷል፡፡

- የማስደነስ ፈቃድ የሌላቸው ባሮችና የምሽት ክበቦች ይቀጣሉ
- ፖሊስ ዳንስ ለግርግርና ለብጥብጥ ይዳርጋል ብሏል
- 10 ሺህ ዜጎች የሚሳተፉበት የጎዳና ላይ የዳንስ ተቃውሞ ይደረጋል
   የአገሪቱ ዜጎች ህዝብ በተሰበሰበባቸውና በመዝናኛ ስፍራዎች የሚያደርጉትን እንቅስቃሴ በተመለከተ ገደብ የሚጥል አዋጅ አውጥቶ ሲተገብር የቆየው የስዊድን ፓርላማ፣ የአዋጁ አንድ አካል የሆነውና ህገ-ወጥ ዳንስን የሚከለክለውን አነጋጋሪ ህግ ተግባራዊ መደረጉን እንዲቀጥል መወሰኑን ዴይሊ ሜል ዘገበ፡፡
የአገሪቱ ፖሊስም ህገወጥ ዳንስ፤ለግርግርና ብጥብጥ የሚዳርግ በመሆኑ ህጉን እንደሚደግፈው ያስታወቀ ሲሆን አንዳንድ አስተያየት ሰጪዎች በበኩላቸው፤ አሳፋሪ የቢሮክራሲ መገለጫ በመሆኑ ሊሻር ይገባል ሲሉ ነቅፈውታል፡፡ ፓርላማው ድምጽ የሰጠበትና እንዲቀጥል የወሰነበት ይህ ህግ፣ ሙዚቃ ስለሰሙ ብቻ እግራቸውን ለዳንስ የሚያነሱ ግለሰቦችን በህገወጥነት የሚፈርጅ ሲሆን፣ የማስደነስ ፍቃድ የሌላቸው የባርና የምሽት ክለብ ባለቤቶች ሲያስደንሱ ከተገኙ እንደሚቀጡ ይደነግጋል፡፡
ደንበኞቻቸው በሰሙት ሙዚቃ ሁሉ ሳያቋርጡ ሲደንሱ ወይም ፈቃድ ሳያገኙ ሲውረገረጉ ከተገኙም የባርና የምሽት ክለብ ባለቤቶች እንደሚቀጡ ህጉ ይገልጻል፡፡ ህጉን የተቃወሙት አንድሪያስ ቫርቬስ የተባሉ ስዊድናዊ የምሽት ክለብ ባለቤት፣ ከዚህ በፊት እንደተደረገው ሁሉ በመጪው ነሐሴ ወር ላይ ህጉን የሚቃወም የጎዳና ላይ የዳንስ ተቃውሞ ለማድረግ  ማቀዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በጎዳና ላይ ዳንሱ ከ10 ሺ በላይ ሰዎች ይሳተፋሉ ብለው እንደሚገምቱም ገልጸዋል፡፡

  የቻይና የአውቶሞቲቭ ኢንዱስትሪ መስክ መሃንዲሶች ለመጀመሪያ ጊዜ በባለሶስት አውታር ማተሚያ ማሽን (3D printer) አትመው ያወጧትን ቀላል መኪና ሃይናን በተባለችው የአገሪቱ ግዛት ውስጥ ለእይታ ማብቃታቸውን ቢቢሲ ዘገበ፡፡
3.6 ሜትር ቁመትና 1.63 ሜትር ስፋት ያላትን ይህቺን መኪና፣ በቀላል ወጪ የሚገዙ ቁሳቁሶችን በግብዓትነት በመጠቀም በማተሚያ ማሽኑ አማካይነት ሰርቶ ለማጠናቀቅ፣ አምስት ቀናትን ብቻ እንደፈጀ የጠቆመው ዘገባው፣ ክብደቷም አነስተኛ እንደሆነ ገልጧል፡፡
የመኪናዋ ዋና ዲዛይነር የሆኑት ቼን ሚንጊያኦ እንዳሉት፤ ባለ ሁለት መቀመጫዋ መኪና ክብደቷ አነስተኛ ቢሆንም ጥንካሬን የተላበሰች ናት ብለዋል፡፡ ክብደቷ አነስተኛ መሆኑ ደግሞ ሃይል ለመቆጠብ ያስችላታል ሲሉም ተናግረዋል፡፡ ከኮምፒውተር ጋር በተያያዘ ባለሶስት አውታር ማተሚያ አማካይነት ቁሳቁሶችን ማተም የሚያስችለውን የዘመኑ ቴክኖሎጂ በመጠቀም በቻይና ታሪክ የመጀመሪያዋ የሆነችው ይህቺ መኪና፣ ቻርጅ ከሚደረግ ባትሪ በምታገኘው ሃይል የምትንቀሳቀስ ሲሆን በሰዓት እስከ 40 ኪሎ ሜትር ርቀት የመጓዝ አቅም አላት፡፡

Monday, 06 April 2015 09:06

የየአገሩ አባባል

ለጅል መድሃኒቱ ሞት ብቻ ነው፡፡
በፀሐይ እረስ፣ በዝናብ አንብብ፡፡
ያልተጠየከውን ምክር አትለግስ፡፡
አንዳንዴ መድኀኒቱ ከበሽታው ይከፋል፡፡
የጫማ ሰሪ ልጅ ሁልጊዜ በእግሩ ይሄዳል፡፡
ስጦታ የሚቀበል ነፃነቱን ይሸጣል፡፡
መንሾካሾክ ባለበት ሁሉ ውሸት አለ፡፡
ገንዘብ የሌለው ሰው ገበያ ውስጥ ጥድፍ ጥድፍ ይላል፡፡
አንዴ የሰረቀ ሁልጊዜ ሌባ ነው፡፡
ሆድ ሲሞላ ልብ ደስተኛ ይሆናል፡፡
ቁራ ካረባህ ዓይንህን ይጓጉጡታል፡፡
ማልዶ የተነሳ ያልደፈረሰ ውሃ ይጠጣል፡፡
ጥርጣሬ የዕውቀት ቁልፍ ነው፡፡
ፅጌረዳውን የፈለገ እሾሁን ማክበር አለበት፡፡
ዓይነስውር በራሰ በራ ይስቃል፡፡
እባብ ለመያዝ የጠላትህን እጅ ተጠቀም፡፡
ነፋስ ያመጣውን ነፋስ ይወስደዋል፡፡
ልብ ውስጥ ያለውን ምላስ ያወጣዋል፡፡
በወጣት ትከሻ ላይ አሮጌ ጭንቅላት መትከል አትችልም፡፡
ሰነፍ በግ ፀጉሩ የከበደው ይመስለዋል፡፡

   አሜሪካ ለግብጽ ስትሰጥ የቆየችውንና ለሁለት አመታት ያህል አቋርጣው የነበረውን ወታደራዊ ድጋፍ እንደገና ሙሉ ለሙሉ መስጠት ልትጀምር እንደሆነ ማስታወቋን ዋሽንግተን ፖስት ዘገበ፡፡ የኦባማ አስተዳደር ለግብጽ ሲሰጠው የቆየውንና ከ2013 ጥቅምት ወር ወዲህ አቋርጦት የነበረውን 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት አመታዊ የወታደራዊ መሳሪያዎች ድጋፍ እንደገና ለመጀመር ውሳኔ ላይ መድረሱን ባለፈው ክሰኞ አስታውቋል፡፡የግብጹ ፕሬዚዳንት ሞሃመድ ሙርሲ ከስልጣን መውረዳቸውን ተከትሎ፣ አገሪቱ እስከምትረጋጋና ዲሞክራሲያዊ ማሻሻያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ የሚያስችል ተጨባጭ ለውጥ እስኪታይ ድረስ፣ አሜሪካ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ አቋርጣ መቆየቷን ዘገባው አስታውሷል፡፡ የአሜሪካ መንግስት ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመስጠት መወሰኑ፣ ግብጽን ከፍተኛ ዋጋ የሚያወጡ አሜሪካ ሰራሽ የወታደራዊ መሳሪያዎች ባለቤት ያደርጋታል ያለው ዘገባው፣ ላለፉት ሁለት አመታት በአሜሪካ እጅ የቆዩ 12 ኤፍ-16 ተዋጊ ጀቶችን፣ 20 ቦይንግ ሃርፖን ሚሳየሎችን፣125 አሜሪካ ሰራሽ አብራምስ ኤምዋንኤዋን ታንኮችንና ሌሎች መሳሪያዎችን ማግኘት እንደሚያስችላት የአሜሪካ ብሄራዊ የደህንነት ካውንስል ቃል አቀባይ በርናዴት ሜሃን መናገራቸውን ጠቁሟል፡፡  አሜሪካ ወታደራዊ ድጋፉን እንደገና ለመቀጠል የወሰነችው፣ የራሷን የብሄራዊ ደህንነት ፍላጎት መሰረት በማድረግ ነው ያሉት ቃል አቀባይዋ፣ ለግብጽ የምትሰጠውን ወታደራዊ ድጋፍ በተለይ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት፤ የድንበርና የባህር ደህንነቶችን ለማስጠበቅና አይሲሲ የተባለው ታጣቂ ቡድን በሲናይ አካባቢ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ለመግታት በሚደረጉ እንቅስቃሴዎች ላይ እንዲውሉ በሚያስችል መልኩ ማሻሻሏንም አስታውቀዋል፡፡ ኦባማ ክግብጹ ፕሬዚዳንት አል ሲሲ ጋር ባደረጉት የስልክ ውይይት፣ 1.3 ቢሊዮን ዶላር የሚገመተውን ወታደራዊ ድጋፍ በዘላቂነት ለማስቀጠል ለአሜሪካ ምክር ቤት ጥያቄ እንደሚያቀርቡ ቃል ገብተዋል፡፡ ግብጽ ከ2018 ጀምሮ የጦር መሳሪያዎችን በብድር መግዛቷን ማቆም እንደሚገባት አሳስበዋቸዋል፡፡አልጀዚራ በበኩሉ፤ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት አሜሪካ ለግብጽ ሙሉ ወታደራዊ ድጋፍ ለመስጠት መወሰኗ እንደሚያሳስባቸው መግለጻቸውን ጠቅሶ፣ ሂውማን ራይትስ ፈርስት የተባለው ተቋም ዳይሬክተር ኔል ሂክስ “አሜሪካ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ለሚታዩባት ግብጽ ድጋፏን ለመቀጠል መወሰኗ ለሰብዓዊ መብቶች መከበር ቅድሚያ አትሰጥም የሚል አደገኛ መልዕክት ሊያስተላልፍ ይችላል” ማለታቸውን ዘግቧል፡፡አሜሪካ ባለፈው አመት ተመሳሳይ ወር ለግብጽ የምትሰጠውን ድጋፍ በከፊል እንደምትጀምር ማስታወቋን ያስታወሰው ዘገባው፣ ግብጽ ከአሜሪካ ከፍተኛ ወታደራዊ ድጋፍ በማግኘት ከእስራኤል ቀጥላ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደምትገኝም ጠቁሟል፡፡

Monday, 06 April 2015 08:58

የፍቅር ጥግ

ፍቅር ልዩ ቃል ነው፡፡ የምጠቀምበት ከልቤ ሲሆን ብቻ ነው፡፡ ቃሉን ደጋግማችሁ ስትሉት ይረክሳል፡፡
ሬይ ቻርልስ
ድንገት በጭጋጋማው የለንደን ከተማ ውስጥ አየሁሽ፡፡ ፀሐይዋ ሁሉን ስፍራ አድምቃው ነበር፡፡
ጆርጅ ገርሽዊን
ፍቅር እንደ ቧንቧ መክፈቻ ነው፤ ይዘጋል ይከፈታል፡፡
ቢሊ ሆሊዴይ
ከፍቅረኛህ ጋር ስትለያይ ጠቅላላ ማንነትህ ይፈራርሳል፡፡ ልክ እንደሞት ማለት ነው፡፡
ዴኒስ ቋይድ
ለሥራ ጊዜ አለው፡፡ ለፍቅር ጊዜ አለው፡፡ ከሁለቱ የሚተርፍ ሌላ ጊዜ የለም፡፡
ኮኮ ቻኔል
በዓለም ላይ ምርጡ ጠረን የምትወጂው ወንድ ነው፡፡
ጄኔፈር አኒስተን
ጀግንነት ሰውን ያለቅድመ ሁኔታ፣ ምላሽ ሳይጠብቁ ማፍቀር ነው፡፡
ማዶና
ፍቅር እንደ ጦርነት ሁሉ ለመጀመር ቀላል፤ ለመጨረስ ግን ከባድ ነው፡፡
ያልታወቀ ሰው
ሦስት ነገሮችን መደበቅ አይቻልም፡- ጉንፋን፣ ድህነትና ፍቅር፡፡
የአይሁዳውያን አባባል
ፍቅር ማለቂያ የሌለው ይቅር ባይነት ነው፡፡
ፒተር ኡስቲኖቭ
ፍቅር ነበልባል የመሆኑን ያህል ብርሃንም መሆን አለበት፡፡
ሔነሪ ዴቪድ ቶሪዮ
ፍቅር የሌላው ሰው ደስታ ለራስህ ወሳኝ የሚሆንበት ሁኔታ ነው፡፡
ሮበርት ሔይንሌይን
ፍቅር ሰውን ከራሱ ባርኔጣ ውስጥ ስቦ የሚያወጣ ምትሃተኛ ነው፡፡
ቤን ሄሽት

Monday, 06 April 2015 08:55

የሲኒማ ጥግ

ሥራውን ሰርተህ ሰዎች እንዲያዩልህ ትፈልጋለህ፡፡ ነገር ግን ሥራውን እየሰራሁ ሳለ ስለውጤቱ አላስብም፡፡ ፊልሙ ተወዳጅ ሆኖ ቦክስ ኦፊስ ቢገባ ወይም ከንቱ ቢሆን ግዴለኝም፡፡ ለእኔ ፊልሙ ተሰርቶ ከተጠናቀቀ በራሱ  ስኬት ነው፡፡ ሁሉም በየራሳቸው መንገድ ስኬት ናቸው፡፡
ጆኒ ዲፕ
የአማካዩ የሆሊውድ ኮከብ ተዋናይ ፍላጎት በአሜሪካዊ መደነቅ፣ በጣሊያናዊ መጠበስ፣ ከእንግሊዛዊ ጋር ትዳር መያዝና ፈረንሳዊ ፍቅረኛ መያዝ ነው፡፡
ካትሪን ሄፕበርን
ለወጣት ፊልም ሰሪዎች የምለግሰው ምክር፡- “ያለውን አካሄድ አትከተሉ፤ አዲስ ጀምሩ!” የሚል ነው፡፡
ፍራንክ ካፕራ
ፊልም ከሦስቱ ዓለም አቀፍ ቋንቋዎች አንዱ ነው፡፡ የቀሩት ሁለቱ ሂሳብና ሙዚቃ ናቸው፡፡
ፍራንክ ካፕራ
ለፊልም ፈተና መሄዴ ነው ብዬ ስናገር መላው ቤተሰቤ ከልቡ ነበር የሳቀው፡፡
ቪክቶሪያ አብሪል
ታላቅ የፊልም ተዋናይ እሆናለሁ፡፡ ይሄ የሚሆነው ግን መጠጥና ወሲብ ካልቀደሙኝ ብቻ ነው፡፡
ጄይ ፕሪሰን አለን
ተዋናይ ከሚሰራበት ፊልም የበለጠ ገዝፎ መታየት የለበትም፡፡
ክርስቲያን ቤል
ፊልምን በተመለከተ ሰዎች ብዙ ጊዜ የመጥፎ ማዕከላዊ ገፀ ባህርይ መልዕክትንና የፊልሙን መልዕክት ብዙ ጊዜ አይለዩትም፡፡ ግን ሁለት የተለያዩ ነገሮች ናቸው፡፡
ክርስቲያን ቤል
ሜክሲኮ ያገኘኋት አንዲት ሴት እንድፈውሳት ፈልጋ ነበር፡፡ እኔ ግን ማንንም መፈወስ አልችልም፡፡ እጄን ጭንቅላቷ ላይ አድርጌ፤ “ፊልሙን በማየትሽ አመሰግንሻለሁ” አልኳት፡፡
ጂም ካቪዜል

በኢጋ ሚዲያና ኮሙዩኒኬሽን አዘጋጅነት የሚቀርበው “ሰሙነ ህማማት የስነ ጽሑፍና የበገና ምሽት” የፊታችን ሰኞ ከቀኑ 11፡30 ሰዓት ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል እንደሚካሄድ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡
በዝግጅቱ ላይ አንጋፋና ወጣት ፀሐፍት፤ ግጥሞችንና ወጐችን በባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያዎች እየታጀቡ ያቀርባሉ ተብሏል፡፡
በምሽቱ ከ20 በላይ የበገና ደርዳሪዎች በአንድ ላይ ተጣምረው በገና በመደርደር ዝግጅቱን እንደሚያደምቁም ተገልጿል፡፡ የዝግጅቱ አላማ ባህላዊ የሙዚቃ መሳሪያና ስነ - ጽሑፍ ያላቸውን ተዛምዶ ለማህበረሰቡ ማስገንዘብና ትኩረት እንዲሰጣቸው ማድረግ ነው ብለዋል - አዘጋጆቹ፡፡  

   ወጋገን ኮሌጅ በፊልም ሙያ ያሰለጠናቸውን ከ130 በላይ አንጋፋና ጀማሪ አርቲስቶች በዛሬው እለት ከጠዋቱ 3 ሰዓት ጀምሮ በአለም ሲኒማ አዳራሽ ያስመርቃል፡፡ በምረቃ ስነ ሥርዓቱ ላይ የዩኒቨርስቲ መምህራን፣ ታዋቂ አርቲስቶች እና ጥሪ የተደረገላቸው የመንግስት ባለስልጣናት ይገኛሉ ተብሏል፡፡ የምረቃ ፕሮግራሙን ይታደማሉ ተብሎ ከሚጠበቁ አርቲስቶች መካከል መሰረት መብራቴ፣ ይገረም ደጀኔ፣ ሸዊት ከበደ እና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡