Administrator

Administrator

Saturday, 19 November 2022 19:40

በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ

 ከዕለታት አንድ ቀን ሁለት እውቅ ሀብታም ገበሬዎች በአንድ መንደር ይኖራሉ። ሁለቱም ራሳቸው ላይ ምናምኒት ፀጉር አልነበራቸውም። በዚህም ምክንያት “ሁለቱ እንቁላሎች” የሚል ቅጽል ስም ተሰጥቷቸው ነበር። በጣም የሚዋደዱ ባልንጀሮች ናቸው። አንድ ቀን  አብረው በመንገድ እየሄዱ ሳሉ፣ ከሩቅ አንድ የሚያብረቀርቅ ነገር አዩ። በሩጫ እኔ እቀድም እኔ እቀድም እያሉ እየተገፋፉ፣ እየተናነቁ ወደቁ።
ይሄ ሁሉ ሲሆን ትግላቸውን በቅርብ ሆነው ያስተውሉ የነበሩ አዛውንት ሰው፣ ያንን የሚያብረቀርቅ ነገር አነሱና እንዲህ አሏቸው፡-
“እንደምታዩት ይህ እቃ ማበጠሪያ ነው፤ ለመሆኑ በዚህ ማበጠሪያ አስቀድሞ ጸጉሩን የሚያበጥር ከሁለታችሁ ማን ነው” አሉ።
ሁለቱ ጓደኛሞች ተያይዘው በሀፍረት ተሳሳቁ። ሰው ሁሉ የሚፈልገው ነገር ምን እንደሆነ ሳያውቅ እርስ በእርስ መባላቱ  እጅግ ያስገርማል።
“ምን ፍላጎት ቢኖር ቢፈልግ ቢቃጣ
ምን ያደርግለታል ሚዶ ለመላጣ!”
               (ከበደ ሚካኤል)
***
የምንሻውን ነገር ጥቅሙን ሳናስተውል ፈጥነን ጠብ ውስጥ አንግባ። ረጅም ጊዜ ያኖርነውን ማንነት በአፍታ ፍላጎት አናበላሸው!
ሰሞኑን  በመንግስትና በተቃዋሚዎች መካከል እየተካሄደ የሰነበተው ፍሬ ጉዳይ  ጦርነት ሁሉ እርቅና ድርድርን፣ የተኩስ አቁም ስምምነትን፣ የሰላም ቅድመ ሁኔታን ግድ ያለ፣ የመሳሪያ ክምችትን ያዘለ፣ የአስታራቂና አደራዳሪዎችን ራስ ያዞረ፣ ለያዥ ለገራዥ ያስቸገረ ሁኔታን የቀፈቀፈ፣ ጎረቤት አገሮችን ያነቃቃ፣ የመሸምገልንም መንገድንም፣ የመሸንገልንም ጥበብ ያካተተ ከባድና ውስብስብ ሂደት እንደነበረ አሳይቶናል።
በየወገኑና በየጎራው፤
“ፈጥነህ ጠብ ውስጥ አትስጠም
አንዴ ከገባህበት ግን እጅህ ከባላንጣህ ይቅደም”
እየተባባሉ የሄዱበት አይነት መሆኑንም  ያረጋግጣል።
ናፖሊዮን ቦናፓርት እንዳለው፤
“Place, you can recapture,
Time, you can not!”
“ቦታን መልሰህ መቆጣጠር ትችላለህ
ጊዜን ግን በጭራሽ!”
ጊዜ እየገፋ ይሄዳል። መንግስት መለዋወጡ ያለና የነበረ ነው። ለውጥ አይቀሬ ነው። ዛሬ ያሸነፈ ነገ ሊሸነፍ ይችላል። በደምና በኢኮኖሚ ረገድ የሚከፈለው መስዋዕትነት የትየለሌ ነው። የአያሌ አምራች ወጣት ኃይል ይጠፋል። ብዙ ተስፋና ምኞት ይቀጫል።
የየጦርነቱ መላ ይሄው ነው! መንግሥት ሊያስብበት ይገባል። ኢትዮጵያና ጦርነት መቼም ተለያይተው አያውቁም። በየጦርነቱ ዋዜማና ማግስት “እገሌ ይውደም! እገሌ ይለምልም!” ሲባልባት ነው የኖረችው። እየተካሄደ ያለው የሰላም ስምምነትና ድርድር የተሻለ አቅጣጫ ይመስላል- በቅን ልቦና ከሆነ! አለበለዚያ ጊዜ መግዣ ብቻ ነው የሚሆነው- ሂሳዊ ግብብነት (Pseudo deal እንዲሉ) ፤ ሌላ አዙሪት ውስጥ ነው የሚከትተን።
ከላይ ከተረቱ ያገኘነው ትምህርት:-
አንደኛ፡- “የሚያብረቀርቅ ሁሉ ወርቅ አለመሆኑን
ሁለተኛ፡ “ከጥሩ ወዳጅነት የሚበልጥ ነገር አለመኖሩንና
ሦስተኛ፡- ስስት ለሀዘን እንደሚዳርግ ነው!”
እነኚህን ሶስት ትምህርቶች ወደ ሀገር ጉዳይ መንዝሮ ማጤን ነው። ብዙ አስመሳዮች (አብረቅራቂዎች) አሉና፤ እንጠንቀቅ!
ወዳጅነት ስንመሰርት ከልብ ይሁን!
አድርባዮችን እንዋጋ!
የመሳሪያ ጋጋታ የጦርነት ሱሳችንን የማርካት አባዜን ያጠነክራል እንጂ ከውድቀት አያድንም! ባለብን የኢኮኖሚ ድቀት ላይ፣ ጦርነት “በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ” ነው የምንለው ለዚህ ነው! ጦርነት ስካር ነው፡- It is like chamagne. It goes to the head of fools, as well as brave men at the same speed. (ጅሉም ጀግናውም አንዴ ጦርነት ውስጥ ከገቡ እኩል ይሰክራሉ) እንዳሉት ነው ጸሐፍት። ስለዚህ ከጦርነት አባዜ እንላቀቅ። ክብ ጠጴዛው ላይ እናተኩር። የመከርንበት ነገር በጎ ነው። ቢያንስ አድረን ከመጸጸት ያድነናል?
በአራቱም ማእዘናት ጦር የሚሰብቅባትና ሻቦል የሚመዘዝባት አገር ከደም በላ ለመውጣት ብዙ ጊዜ ይፈጅባታል። ልበ-ንፁሕ ሆነን ካላገዝናት መከራ እንዳባዘተች ትኖራለች። ፈጣሪ በቃሽ ይበላት!

Wednesday, 16 November 2022 10:23

የእሾክ ላይ ሶረኔ

የእሾክ ላይ ሶረኔ

አንድ የአፈ ታሪክ ወፍ
አሳረኛ ፍጡር
የእሾክ ላይ ሶረኔ
ሽቅብ መጥቃ በራ
ካጋም ዛፍ ጫፍ ሰፍራ
ገላዋን በእሾኩ
ጠቅጥቃ እያደማች
ሥቃይ ሲያጣድፋት
ግቢ ነብስ
ውጪ ነብስ
የሞት ጣር ሲይዛት
ከጣሩ ማህፀን ከሰቆቃ ላንቃ
ስልቱ የረቀቀ ድንቅ የተሰኘ ድምፅ
ልዕለ ሙዚቃ…….
የዘመነ-ብሉይ ከያኒ ያላየው
የዘመነ- ሐዲሰ ጠቢብ ያልቀሰመው
የተቃኘ ቃና፤
በህይወቷ ዋዜማ
ፈጥራ ታላቅ ዜማ
ህላዌ ሙዚቃ ፤
ወዲያው ትሞታለች ከህይወት ተላቃ፤
የአንድ አፈ-ታሪክ ወፍ
የአፈ-ታሪክ ወግ ነው
የጥበብን ልደት….
የአጉል ዘመን ጠቢብ
ምጧን ያስረዝማል
ሥቃይዋን ያበዛል
ድልድይ ሥራም “እምቢ”
ድልድይ ሁንም “እንቢ”
አሳልፍ “እምቢየው”
እለፍ “አሻፈረኝ”
ተወለድ “በጭራሽ”
ሙት ሲሉት “ሞቴ ነው”
ልጅ የለ፤ አባት የለ፤ ሁለተዜ በደል
ግራ- ገብ ጥበብ የህይወት እርግማን
ባንድ-ፊት የሙት ልጅ ባንድ- ፊቱ መካን!
*****
የጥበብ አበሣ የእሾክ ላይ ሶረኔ
የዘመኔ ስዕል የዘመኔ ቅኔ
ዜማና ሙዚቃው ስልትና ምጣኔ
በአበባ ዕድሜ ሙሾ
በእርጅናዬ ዘፈን፤
ጥበብ ያልወጣለት ግራ-ገብ ዘመን
ከእንግዲህ ለእንግዲህ
የጥበብ ፈተና….
ፀሐይ ለመጨበጥ
ብርሃን ለማየት
ከየግል ጓዳ ከራስ ዓለም መውጣት
ከህብረ-ሰው መኖር
በሀሳብ መጋጨት መላተም መካረር
ህብረ -ጥበብ መፍጠር
በምጥ የመለምለም
በሞት የመወለድ
አዲስ ዓለም ማለም
የስሜት ረሀብ
የጥበብ ሰው ጩኸት
የውብ ህይወት ጠኔ
የጥበብ አሻራ
ለስላሳ ሻካራ
እንደሶረኔ እሾክ ወግ ምጡ መከራ
አዲስ ህይወት ማለም…..
አስፋልቱን ሜዳውን ካንቫስ ሸራ ማድረግ
ሰው እንዲሄድበት ቀለም ላዩ ማፍረጥ
አሻራና ዱካው ውበትን እንዲገልጥ
መንገድ ላይ መዘመር
ብርሃን ላይ መጫር
ብርሃን ላይ መፃፍ
….. ፀሐይን መሻማት
ያኔ ነው ዝግ- ባህል በራፉ እሚከፈት
ስዕል ፈገግ ሲል
ሳቅ ሲል ሙዚቃ
ዕውነት ሲሆን ትያትር
ደፈር ሲል ቅኔ
የእሾክ ላይ ሶረኔ ወልዳ
አትሞትም ያኔ
ወልዳ አትሞትም ያኔ
የእሾክ ላይ ሶረኔ!
(ለአዲስ የኪነ-ጥበብ ሳምንት)
ነቢይ መኮንንSunday, 13 November 2022 00:00

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

ሰርፀ ፍሬስብኃት ስለ አርቲስት አሊ ቢራ፤


     ዓሊ ሞሐመድ “ብራ”
ዓሊ፥ የጥዑም ድምጽ ባለተሰጥዖነቱ ብቻ አልነበረም የሚያስደንቀው። ፈረንጆቹ “genius” የሚሉት ዓይነት የሙዚቃ ሰው ስለነበረም እንጂ። ሙዚቃን፤ በዕውቀት ምሥጢሯን ዐውቆ የተጫወታት ታላቅ ድምጻዊ፣ ዓሊ ሞሐመድ “ብራ” ነበር።
ዓሊ፥ ሙዚቃዎቹን ራሱ ያቀናብራል። ዑድ፣ ጊታር፣ ኪቦርድ፣ ፒያኖ፣ አኮርዲዮን እና ሐርሞኒካ አሳምሮ ይጫወታል። ከክብር ዘበኛ፣ ከአይቤክስ፣ ከኢትዮ ስታር ሙዚቀኞች ጋር በሠራቸው የሙዚቃ ሥራዎች፣ አድማጮቹ ብቻ ሳይኾኑ፣ አብረውት የሠሩት ሙዚቀኞች ኹሉ እንደተደነቁበት፣ ሙዚቃን እንዳስከበረ ዕድሜ ልኩን የኖረ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር።
የኦሮሚኛ ሙዚቃን፥ ቋንቋውን የማንናገር እና የማንሰማ  ትርጉሙን ሳንጠይቅ በተመሥጦ እንድናዳምጥ ያደረገን፣ የኦሮሚኛ ሙዚቃ ባለውለታ ነበር። ዓሊ፥ የሐረሪን፣ የሶማሊኛን፣ የሱዳኒኛን እና የዐረቢኛ ቋንቋ ሙዚቃዎችን አሳምሮ የተጫወተ ታላቅ ድምጻዊም ነበር።
ዓሊ፥ በመድረክም፣ በስቱዲዮም፣ በአጠቃላይ ሙዚቃዊ ሰብእና፣ የሙዚቃን ፈተና በብቃት የተወጣ ታላቅ ሙዚቀኛ ነበር።
ዓሊ፥ ለሀገርህ ያለህን ኹሉ አበርክተሀል፣ እስከ መጨረሻይቱ ሰዓት ድረስ ሙያህን እና ሀገርህን አክብረሀል። ምድራዊ ስንብትህ ከልብ ያሳዝነኛል። ግን ከዚህ ኹሉ በላይ፣ ክብርህ ልቆ ይታየኛል።
ቸር አምላክ፥ ለነፍስህ ይዘንላት። ሰላማዊ ዕረፍተ ነፍስ ይሥጥህ። መላውን አድናቂዎችህን፣ ቤተሰቦችህን፣ የሙያ ጓደኞችህን እግዚአብሔር ያጽናናልን።
***
ከጋዜጠኛና ደራሲ ሔኖክ ስዩም
የክብር ዶክተር ዓሊ ሞሐመድ “ብራ” አንጋፋ ድምፃዊ ብቻ አይደለም። ከዚያ የሚያልፍ፣ አፍሪቃ ቀንድ ላይ የተደመጠ፤ ጅቡቲ ጆሮ የሰጠችው፣ ሞቃዲሾ የሰማችው፣ ሀርጌሳ አብራው ያዜመችለት ድምፃዊ ነው። ምን እንደሚል መረዳት ሳያስፈልጋቸው የሌላ ቋንቋ ተናጋሪዎች በሙዚቃዎቹ ፍቅር አብደዋል። ለእኔም ከልጅነቴ ጀምሮ ስሰማቸው ከማልጠግባቸው ድምፃውያን አንዱ ነው።
ነፍሱ በሰላም ትረፍ።
መፅናናትን ለአድናቂዎቹ እመኛለሁ።
***
ሥነጥበብ ምን ዳር አለው!
አሊ ቢራ ከአንጋፋና ወጣት ድምጻዊያን ጋር የተለያዩ ሙዚቃዎችን ሰርቷል። ከነዚህ ውስጥ አንደኛው ከድምጻዊ አብርሃም በላይነህ ጋር ከዓመት በፊት የለቀቁት “ዳርም የለው” የተሰኘው ሙዚቃ አንደኛው ነው። ስለዚህ ሙዚቃ ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ  እንዲህ ብሎ ነበር፡-
አሊ ቢራ ‹‹ዳርም የለው!››
መነሻ
አንዲት ወጣት አውቃለሁ፤ ወጣት ሳለሁ። ጆሮዋን ቢቆርጧት ኦሮምኛ አትሰማም። አሊ ቢራ ሲዘፍን ግን ጆሮዋን ቢወትፏት ትሰማዋለች፡፡ ቃላቱን ስትደረድር፣ ቅላጼውን ስትቀልጽ ለጉድ ነው! ስትዘፍን የሰማት ሰው፣ ‹‹ኦሮምኛ ትችያለሽ?›› ሲላት፤‹‹የአሊን እችላለሁ›› ትል ነበር፡፡ ስቀንባታል፡፡ ጥበብ የሰዎች ሳይሆን የተፈጥሮ ቋንቋ መሆኑ ያኔ - ድሮ ገና ገብቷት ነበር፡፡
ዋና ጉዳይ-
ሥነጥበብ ምን ዳር አለው? ከህይወትም ይገዝፋል፡፡ ከዘመንም ያልፋል፡፡ ዘላለም ነው። ተፈጥሮ ያለ ሰው እርቃኗንም ጥበቧ ይበዛል። ተፈጥሮ ጥበቧን ያኖረችበት አይጠፋትም፡፡ ጥበበኛ ስትሆን ከጥበቧ ትቀይጥህና ዘላለሟ ትሆናለህ፡፡
አሊ ቢራን ተፈጥሮ ከኗሪ ጥበቧ ቀይጣዋለች። ኗሪ ጥበብ በቋንቋ አይታጠርም። በባህል አይሰፈርም፡፡ ዘመን ይሻገራል፡፡ በወጣትነቱ ‹‹BIRRAA DHAA  BARIHE›› ብሎ የጨበጣትን ጥበብ፣ ዛሬም በአዛውንትነቱ ከዘራ ተመርኩዞ ‹‹ዳርም የለው›› ይላታል። ርእሱ የዘፈኑ ሳይሆን የህይወቱ ነው፡፡ የአሊ ቢራ የጥበብ ስራዎች (ዘፈኖች አላልኩም) ሞት እንኳን የወሰን ድንጋይ ሊያስቀምጥላቸው አይቻለውም፡፡ ተፈጥሮ በጥበብ ህዋዋ ላይ አንድ ኮከብ አድርጋዋለችና ስራው ዳር የለውም፤ ዘላለም ነው፡፡
አሊ ቢራ፣ የተፈጥሮን የጥበብ ስጦታ በየሰበቡ (መቼም ሰበብ አይገድም) አድበስብሰህ ሰው ባለመሆንህ፣ ጥበበኛ ሆነህ የተፈጥሮን ለተፈጥሮ በመመለስህ እናመሰግናለን፡፡ ዳር የለህም፡፡ ተፈጥሮ ምን ዳር አላት!Wednesday, 16 November 2022 09:54

ልንፋታ ተስማምተናል?!

  ሊፋቱ መሆናቸውም አስደነገጠኝ!!
ለመሆኑ እርስዎ ትዳርዎት በምን አይነት ሁኔታ ውስጥ ነው የሚገኘው?
በትዳር ውስጥ ካልሆኑም  የእርስዎ ትዳር ምን ዓይነት እንዲሆን አስበዋል?
በእነዚህ ጥንዶች ቤት ውስጥ ነገሮች ጠረናቸውን ቀይረዋል። ትዳሩ ውስጥ ጭቅጭቅ በዝቷል!! አለመግባባትና መጠላላት ነግሷል!! መናናቅ ቤቱን ሞልቶታል!! በትዳር ውስጥ እናገኘዋለን ብለው ያሰቡት መልካም ነገር ሁሉ እንዳሰቡት አላገኙትም፤ ሁሉ ነገር እንደ ጉም በኖ ጠፍቷል!!
በሁሉ ነገር መግባባት አቅቷቸው ለመፋታት ግን ቁጭ ብለው ተስማምተውና ተግባብተው ጨርሰዋል። ለመፋታት የፈጠሩት መግባባትና መስማማት አብሮ ለመኖር ሲሆን ግን ጦርነትና መጠላላት ነገሰበት። ይህን መጽሀፍ ወደ እርስዎ ለማድረስ እያዘጋጀሁ ባለሁበት ወቅት ፍርድ ቤቶች አካባቢ ስላለው የባልና ሚስት ጉዳይ ሳጣራ፣ ከፍተኛ ቁጥር ያለው የፍቺ ጉዳይ ሆኖ ፍ/ቤቶችን አጨናንቆ ይገኛል። በየቀኑ ፍቺ አለ። ያዙኝ ልቀቁኝ ብለው ተጋብተው፣ ሲደባደቡና ሲፋቱ ይውላሉ። አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሰናል!!
ዘንድሮ ልብስ ሲጋባ!! የሙሽራ ልብሶች ተጋቡ!! በወሬና በሶሻል ሚዲያው አጩኸው፣ በመኪና ክላክስ አደንቁረውን መድፍ ተኩሰው አስደንግጠውን፣ የለኮሱት ርችት ብልጭ ብሎ ሳይጠፋ ይፋታሉ!!
ያስታውሳሉ አይደል ሞባይልዎትን ሲገዙት ጋራንቲ  እንደነበረው? ድርጅቱ ምርቱ እንደማይበላሽ እርግጠኛ ስለነበር ለሆነ ዓመት ጋራንቲ ሰጥትዎት ነበር። ጋብቻን የፈጠረው አምላክስ የምን ያህል ዓመት ጋራንቲ ለፈጠረው ትዳር የሰጠው ይመስልዎታል።
ይህን በትክክል ለመመለስ የሰጠንን የትዳር መተዳደሪያ ማነዋሉን ማንበብ ግድ ይላል። አሁን መጽሐፍ ቅዱስ ገልጠን እንያዝ። በእርግጥ መጽሐፍ ቅዱስ ዋና ትኩረቱ ትዳር አይደለም። ዋና ትኩረቱ አምላክ ከሰው ልጆች ጋር ስላለው ግንኙነትና በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ በኩል የአዳም ዘር በሙሉ ያገኘው ደህንነት ዋና ትኩረቱ ነው።
ነገር ግን ከዚህ ዋና ጉዳይ ባሻገር የሰው ልጆች ኑሮን ትኩረት ሰጥቷል። ትኩረት ከተሰጣቸው ነገሮች ውስጥ ቀዳሚው ደግሞ ጋብቻ ነው። ሌላው መጽሐፍ ቅዱስ የየትኛውም ሃይማኖት የግል መጽሐፍ አይደለም። ለአዳም ዘር በሙሉ ከአምላክ ዘንድ የተሰጠ የተከበረ ስጦታ ነው።
ወደ ዋናው ጉዳያችን እንመለስ። የትዳር መተዳደርያ ደንቦችን እንይ።
መተዳደሪያ ደንብ አንድ
“መፋታትን እጠላለሁ”
ትንቢቱ ሚልክያስ ምዕራፍ 2፤ ከቁጥር 16
ጋብቻን የሰራው አምላክ፤ ለጋብቻ የሰጠው ጋራንት የእድሜ ልክ ዘመን ነው። ፈጣሪ ጋብቻን ሲፈጥረው መፋታት ከሚባል ሀሳብና ድርጊት ውጪ እንዲሆን አድርጎ ነው የፈጠረው። ጋብቻ ኤክስፓየርድ ዴት አልታተመበትም።
ወይኔ ሲያናድድ!!
ፈጣሪ መፋታትን እንደዚህ ከጠላ ሳንፋታ እንድንኖር ሊያደርገን ነው እንዴ? ዶክተሮች፣ ዘማሪዎች፣ ቄሶች፣ ሼኮች፣ ፓስተሮች፣ አርቲስቶች፣ አትሌቶች ተፋተው የለ እንዴ እያሉ ነው ያሉት? እነዚህ ሁሉ በፈተና የወደቁና ከዜሮ በታች ያመጡ ሰነፍ ሰዎች ናቸው። ለምንም ነገር ምሳሌ አርገው አይውሰዷቸው!! እርስዎ እንዳይበላሹ እነዚህ ቀሽሞች ካሉበት አካባቢ ይራቁ።
“መፋታትን እጠላለሁ” ያለው ፈጣሪ ነው።
እርስዎ ማንን ነው የሚሰሙት?
ፈጣሪን ወይስ ተሸንፈው የወዳደቁ ሰዎችን? ፈጣሪን ቢሰሙት ያዋጣዎታል። ባልና ሚስት ጋብቻቸውን በፍርድ ቤት በህግ በኩል ቢፋቱና ቢለያዩ እንኳን በፈጣሪ ዘንድ ግን ጋብቻው ፈጽሞ ሊፈርስ የማይችል መለኮታዊ ተቋም ነው። ሁለቱም በህይወት እስካሉ ድረስ ቤተ ክርስቲያንም በእግዚአብሔር እንደተሳሰሩ ትቆጥራቸዋለች። ስለዚህ ቢለያዩም አልተፋቱም። ከሌላ ሰው ጋር ተጋብተውም ከሆነ የሚያደርጉት ግንኙነት እንደ ዝሙት ይቆጠራል።
እንደሚያውቁት ሰይጣን በአምላክና በሰው መካከል ያለውን ድልድይ እየሰባበረ የሰው ልጅን ከአምላኩ ጋር ህብረት እንዳያደርግ እርቃኑን ለማስቀረት ለብዙ ዘመናት እየሰራ ይገኛል። በእኔና በእርስዎ ዘመንም ይሄ እረጅም እድሜና ብልሃት ያለው ሰይጣን ስራውን ያለ እረፍት እየሰራና እያከናወነ ይገኛል።
ትዳር ሌላኛው የአምልኮ ስርዓት የሚፈጽምበት ቤተ ክርስቲያን ነው። ይህን ተቋም አፍርሶ ከአምላክ ጋር የምናደርገውን አምልኮ ለማቋረጥ ሰይጣን በተለያየ መንገድ ትዳራችንን እየፈተነው ይገኛል። አንዳንድ ትዳራቸው የፈረሰ ሰዎች እንዳጫወቱኝ ከሆነ፤ ትዳራቸው በምን ምክንያት እንኳን እንደፈረሰ አያውቁትም።
ወደ ሚጠላኝ ሰውዬ ትዳር ታሪክ እንመለስ
የሚስቴ ማንበብ ኑሮዬን በጠበጠው። አሁን ላለሁበት የውድቀት ደረጃ ዋና ተጠያቂዋ ሚስቴ ናት። ስለዚህ በዚህ ሁኔታ መኖር ስለማልችል “ልንፋታ ተስማምተናል”
ነበር ያለኝ!! በተጋቢዎቹ እንፋታለን ስምምነት እና ጋብቻን በፈጠረው ፈጣሪ “መፋታትን እጠላለሁ፤ በፍጹም አትፋቱም” በሚል ክርክር ውስጥ ጥንዶቹ ለመፋታት ከበቂ በላይ ነው ያሉትን ምክንያታቸውን አቅርበዋል። አብረው መኖር የማይችሉበት ምክንያቶችን አንድ ሁለት እያሉ በዝርዝር አስቀመጡ።
(ከደራሲ ሱራፌል ኪዳኔ “እንዳትገቡ” መፅሐፍ የተቀነጨበ)

ከዕለታት አንድ ቀን የተራቡ ጅቦች በየገደላ ገደሉ እየተዘዋወሩ የሚበላ ነገር ሲፈልጉ አንድ እጅግ ግዙፍ ዝሆን አዘቅት የሆነ ገደል ውስጥ ወድቆ ሞቶ አዩ።
አንደኛው ጅብ፤
“ጎበዝ ምን ትጠብቃላችሁ፤ እንግባና እንሸክሽከው እንጂ!” አለ።
ሁለተኛው፤
“ምን ጥርጥር አለው። ገብተን እንዘልዝለው እንጂ!”
ሦስተኛው፤
“ላሜ ወለደች ማለት ይሄ’ኮ ነው!”
ከሞላ ጎደል ሁሉም በሀሳቡ ተስማምተው ድጋፋቸውን ገለጡ።
ከሁሉም ወጣት የሆነው አንድ ጅብ ግን ተቃወመ።
“ምክንያትህን አስረዳ?” ተባለ።
ወጣቱ ጅብም፤
“እርግጥ ነው ስለራበን ገብተን መብላታችን ትክክል ይሆናል። ሆኖም ሙዙን ስታይ መዘዙንም እይ የሚባል ተረት አለ። ከበላን በኋላ ሆዳችን ሲሞላ ከዚህ አዘቅት ገደል እንዴት ሽቅብ ለመውጣት እንችላለን የሚለውንም አስቡ” አላቸው።
አንደኛው ለመብላት የቸኮለ ጅብ፤
“ኧረ ቶሎ እንግባ፤ እንብላና እዚያው ዘዴ እንፈልጋለን” አለ።
ሁሉም ተስማሙና እየተንደረደሩ ገቡ። ያ ወጣት ጅብም ምርጫ ሲያጣ ከወገኖቹ እንዳይለይ ብሎ አብሮ ገባ።
ያን ግዙፍ ዝሆን ቡጭቅጭቅ አድርገው ነጩት። ተቀራመቱት።
ሆዳቸው ሞላ! ጠገቡ።
ቀና ብለው የገደሉን አፋፍ ሲያዩት ለመውጣት የማይመች አቀበት ነው።
“ቀስ ብለን ነገ ከነገ ወዲያ ዘዴ እንፈልጋለን። የተራረፈውን አጥንት እየቆረጣጠምን እናስብበታለን” ተባባሉ፤ ተስማሙ!  
ቀናቱ አንድ ሁለት እያሉ ሲገፉ ረሀብ መጣ። ደክሟቸው ተኙ። እኩለ ሌሊት እንዳለፈ አንዱ የነቃ ጅብ ጎኑ ያለውን ጅብ ቀስቅሶ፤ “በረሀብ ከምንሞት በጣም ያንቀላፋውን ጅብ ለምን ቅርጭጭ አናደርገውም?”
“እውነት ነው! እውነት ነው!” ብለው ተመሳጥረው ያንን እንቅልፋም ጅብ ሰፈሩበት! በየሌሊቱ ትርዒቱ ተደጋጋሚ ሆነ።
በመጨረሻ ሁለት ብቻ ቀሩ።
እየተፋጠጡ ማደር ሆነ።
በመካያው ግን አንደኛው ደከመና እንቅልፍ ጣለው። የነቃው የተኛውን በልቶ ለጥቂት ቀናት ነብስ ዘራ።
ሆኖም በመጨረሻ እንቅልፍ ጣለው። በዚያው እንደተዝለፈለፈ አንድያውን አሸለበ! ህይወቱ አለፈ።
***
ጅብ መቼም ጅብ ነው። አበው ሲተርቱ “ከጅብ ጅማት የተሰራ ክራር ቅኝቱ ´ልብላው ልብላው”´ ነው ይላሉ። አገራችን ኢትዮጵያ የጅብ ደሀ ሆና አታውቅም። የቀን ጅብም የሰው ጅብም፣ ነባር ጅብም መጤ ጅብም አስተናግዳለች። ያም ሆኖ አስፈጻሚና ክትትል አድራጊ አጥታ ነው እንጂ ዕቅዶችም አላጣችም!
ወጣትና አዋቂ ልጆችም አሏት። ከጥንት ከዘመነ-ስካውት ጀምሮ፣ የወጣት ወንዶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወወክማ) የወጣት ሴቶች ክርስቲያናዊ ማህበር (ወሴክማ) ውሎ አድሮም፣ አኢወማ (የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣት ማህበር) እና የአብዮታዊት ኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ማህበር (አኢሴማ) በወቅቱ የነበረው ትኩስ ኃይል ማሰባሰቢያ ነበሩ። በዚህ ላይ የተደራጁት የፖለቲካ ፓርቲዎች የየራሳቸው የወጣት ክንፍ ነበራቸውና የወጣቱን ጉልበት ይዘዋል። አሰልፈውታል። በየፊናቸው ኢትዮጵያን የተወሰነ ርቀት አስኪደዋል። የተወሰነ ርቀትም የኋሊት አንደርድረዋታል። የብዙ ልጆቿ ደምም ፈስሶባታል። ከባባድ መስዋዕትነት ተከፍሎላታል! “ጉዟችን ረጅም ትግላችን መራራ” ተብሎላታል። መራራ ከሆነ አጠር ይበል እንጂ ለምን ረጅም ይሆናል? ተብሎም ተሹፎባታል። ይህ ሁሉ ታልፎ ሲያበቃ ዛሬ ደግሞ አዲስ ጦርነት፣ አዲስ መፈናቀል፣ አዲስ ስደት እንዳመረቀዘ ቁስል እየደገመን ነው! የአንድ አገር ልጆች ደም እየፈሰሰ ነው።
“እንደካራ ማራ፣ እንደ ጭናክሶን
ሰሜንም ደማቅ እሳት አሳየን!”
ብለን ዘምረን ያቀጣጠልነው እሳት በተለያየ አቅጣጫ እያዳረሰ ይገኛል። መላና መፍትሄ ያጣው ህዝብ በከንቱ ህይወቱን መገበሩ ያሳዝናል። የተባበሩት መንግስታት፣ የአፍሪካ ህብረት፣ ወዘተ ከጀርባ የሚጭሩትን እሳት ከፊት ለፊት እናጠፋለን በሚል እንደተለመደው ድርድር…ድርድር እያሉ ተደርድረው፤ ጉብ - ቂጥ ይላሉ፡፡ መንግስታችንም ያው እንደተለመደው እጁን ተጠምዝዞ መፈራረሙን ይያያዘዋል። የማይነጥፍ የፖለቲካ አዙሪት! ለዘመናት የማይዘጋ በር! አገራችንም ዕቃውን እንዳላወጣ  ቤት ለቃቂ፤
“እንኳን ቤትና የለኝም አጥር?
እደጅ አድራለሁ ኮከብ ስቆጥር”
እያለች መዝፈኗን ትቀጥላለች! መታከትን የማያውቅ ረዥም ሙሾ!
ዕርቅና ድርድር የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ መሆኑ የማያጠያይቅ መሆኑ ግልጽና ይፋ የወጣ ጉዳይ ሆኗል። ጊዜ የማይፈታው ጉዳይ የለም! እያንዳንዱ ቀን አንዳንድ ለውጥ ማርገዙ እየታየ ነው። ይህም በጎ ምልክት ነው! ቶሎ-ተናኝ (Volatile) በሆነው የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ያሁኑ መልካም ጅምር ይመስላልና፣ ወጣቱ ትውልድ ልቡና ውስጥ እንዲሰርጽ ተስፋ እናደርጋለንና፡-
“ዕቅድህ የ1 ዓመት ከሆነ (ጤፍ) ሩዝ ዝራ
ዕቅድህ የ5 ዓመት ከሆነ ባሕር ዛፍ ትከል
ዕቅድህ የዘላለም ከሆነ ልጅህን አስተምር”
የምንለው ለዚህ ነው!!


ባለፈው ሰኞ በመንግስትና በሕወሓት ወታደራዊ አመራሮች መካከል በናይሮቢ የተጀመረው ንግግር ረቡዕ ይጠናቀቃል ተብሎ ቢጠበቅም ወደ ህትመት እስከገባንበት ሰዓት ድረስ አልተጠናቀቅም። ውይይቱ ዛሬ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህ የናይቢው ንግግር የሁለቱ ወገኖች ወታደራዊ አዛዦች፣ የህወሓት ሃይሎች ትጥቅ በሚፈቱበት ዝርዝር ሁኔታ ላይ የተወያዩ ሲሆን ሌሎች ታጣቂዎች የኤርትራና የአማራ ክልል ከትግራይ የሚወጡበት ጊዜ ግን አሳሳቢ መሆኑን አሶሼትድ ፕሬስ ምንጮችን ጠቅሶ ዘግቧል።
በደቡብ አፍሪካው የሰላም ንግግር፤ የህውሓት ሃይሎች በ30 ቀናት ውስጥ ትጥቅ እንደሚፈቱ ስምምነት ላይ መደረሱ ይታወቃል። በዚህ ንግግር ለውይይት ከሚቀርቡ ጉዳዮች መካከል እንደ ኢንተርኔት፣ ቴሌኮም፣ መብራና ባንክ ያሉ አገልግሎቶችን ወደነበሩበት መመለስ  እንዲሁም የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቶችን ማስጀመር ይገኙበታል።  በትግራይ  መሰረታዊ መድኃኒቶች ማለቃቸውን የጠቆመው የተባበሩት መንግስታት፤ ወደ ክልሉ ሰብአዊ እርዳታ ለማድረስ ከአጋሮቻችን ጋር እየተጠባበቅን ነው ብሏል።
ይህ በዚህ እንዳለ የኢትዮጵያ መንግስት ዋና ተደራዳሪና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሔራዊ ደህንነት አማካሪው አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን፤ ሰብአዊ እርዳታዎች ወደ ክልሉ በስፋት መጓዝ መጀመራቸውንና 35 የምግብ ሸቀጦችንና 3 መድኃኒትና የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችን የጫኑ መኪኖች ሽሬ መግባታቸውን ገልጸዋል። አምባሳደሩ በዚሁ የቲውተር መልዕክታቸው ላይ እንዳሰፈሩት የኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት 70 በመቶውን የትግራይ ክልል መቆጣጠሩንና ለሰብአዊ እርዳታ የአውሮፕላን በረራዎች ዳግም መፈቀዳቸውን ገልጸዋል። የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ቢሮ በበኩሉ፤ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ ነው ብሏል።
የፕሪቶሪያውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ ምንም አስተያየት ከመስጠት ተቆጥበው የሰነበቱት የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴዎድሮስ አድሃኖም፤ ሰሞኑን ለሪፖርተሮች በሰጡት ምግብና መድኃኒት ወደክልሉ እየገባ አይደለም ማለታቸውን ተከትሎ፣ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ዴኤታዋ ሰላማዊት ካሳ እንደተናገሩት፤ በትግራይ የተለያዩ አካባቢዎች የምግብ እርዳታ እየቀረበ እንደሆነ አመልክተው በሽሬ፣ ሽራሮ፣ አክሱም፣ አዲሃጋላይ፣ አዲቃሮ፣ ሰለክላካና አዲነብሪ ከተሞች 108 ሺ ለሚሆኑ ወገኖች 16 ሺ 100 ኩንታል ስንዴና ከ65,000 ኩንታል በላይ አልሚ ምግቦች እንዲከፋፈሉ ተደርጓል። በራያ አላማጣና ኮረም ከ43,200 በላይ ኩንታል ስንዴና ከ7,300 ኩንታል በላይ አልሚ ምግብ 287 ሺ ለሚሆኑ ዜጎች ተዳርሷል ተብሏል።

  የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት በሴቶችና ሕፃናት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸው ተጠቁሟል

        የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ)፤ ከመስከረም 2014 ዓ.ም. እስከ ነሐሴ 2014 ዓ.ም. ያለውን ጊዜ የሚሸፍን የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ ሪፖርቱን ሰሞኑን ይፋ አድርጓል።
ይህ ባለ 36 ገጽ ዓመታዊ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች የዘርፍ ሪፖርት፣ ኢሰመኮ ሐምሌ 1 ቀን 2014 ዓ.ም. ይፋ ካደረገው አጠቃላይ የኢትዮጵያ ዓመታዊ የሰብአዊ መብቶች ሁኔታ ሪፖርት በተጨማሪነት በተለይ የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶች አያያዝ ላይ በዝርዝር በማተኮር ኮሚሽኑ የለያቸውን አበረታች እመርታዎች፣ ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮችና ምክረ-ሃሳቦችን አካቷል። ኮሚሽኑ ሪፖርቱን ያዘጋጀው ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምርመራዎችና የመስክ ምልከታዎች፣ ባስተናገዳቸው የግለሰቦች አቤቱታዎች፣ የሕግና የፖሊሲ ግምገማዎች፣ ጥናቶችና ምክክሮች፣ የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች እንዲሁም የውትወታና ሌሎች ሥራዎቹ ላይ በመመስረት መሆኑን ጠቁሟል።
የሴቶችና የሕፃናት ሰብአዊ መብቶችን ከማስጠበቅና ከማስፋፋት አንፃር በሕግ ረገድ የታዩ ክፍተቶች፣ የሴቶችና የሕፃናት ከጥቃትና ከብዝበዛ የመጠበቅ፣ ፍትሕና ውጤታማ መፍትሔ የማግኘት፣ ሕዝባዊ ተሳትፎ የማድረግ፣ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ ያለው አያያዝ፣ የቤተሰብ መብቶች እንዲሁም የሴት ሠራተኞች ሁኔታ ሪፖርቱ ትኩረት ያደረገባቸው ርዕሰ ጉዳዮች ናቸው ተብሏል።
በኢትዮጵያ በተከሰቱት ሰው ሠራሽና ተፈጥሯዊ ችግሮች ምክንያት ሕፃናት ከመንግሥት፣ ከማኅበረሰብና ከቤተሰብ ማግኘት ያለባቸው ጥበቃ በመጓደሉ ለተደራራቢ የመብቶች ጥሰት መጋለጣቸውና ሴቶች በተፈጸሙባቸው ጾታዊ መድሎዎችና ጥቃቶች ምክንያት መሰረታዊ መብቶቻቸውን የሚጥሱ፣ ነጻነቶቻቸውን የሚገድቡ እንዲሁም ሰብአዊ ክብራቸውን የሚያጎድፉ በደሎች እንደደረሱባቸው በሪፖርቱ ተገልጿል። በተጨማሪም በብሔራዊ የሕግ ማዕቀፍ ውስጥም ለሕፃናትና ለሴቶች ሰብአዊ መብቶች በቂ የሕግ ከለላ በመስጠት ረገድ የተለያዩ ክፍተቶች መስተዋላቸው ተጠቅሷል።
በኢትዮጵያ የሰሜኑ ክፍል በተነሳው ጦርነትና ቀጥሎም በየመሀሉ ማገርሸቱ በሴቶችና በሕፃናት ላይ መጠነ-ሰፊ ጥቃቶች፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች ለጦርነት ዓላማ ስልታዊ በሆነ መልኩ ጭምርም መፈጸማቸውም ተዘግቧል። ይሁን እንጂ ለተፈጸሙ ጥቃቶች ውጤታማ ፍትሕና መፍትሔ የሚያስገኝ የወንጀልና የፍትሐ-ብሔር የሕግ ማዕቀፍ አለመኖር፣ ዓለም አቀፍ መመዘኛዎችን ያሟላ የወንጀል ምርመራና የክስ አመሰራረት መጓደል በሪፖርቱ ከተዘረዘሩት ዋና ዋና አሳሳቢ ጉዳዮች መካከል ይጠቀሳሉ። በሌላም በኩል በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች በሶማሌ፣ በአፋር፣ በኦሮሚያ፣ በጋምቤላ፣ በቤኒሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ብሔሮች ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልሎች በተለያየ ወቅት በተነሱ ግጭቶችም ሴቶችና ሕፃናት ለተለያዩ የሰብአዊ መብቶች ጥሰቶች መጋለጣቸው በሪፖርቱ ተጠቅሷል።
ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሴቶችና ሕፃናት ከመኖሪያቸው መፈናቀላቸው፣ በተፈናቃይ መጠለያ ጣቢያዎች ውስጥም ለጾታዊ ጥቃቶችና ጎጂ ልማዳዊ ድርጊቶች ተጋላጭ መሆናቸውና ልዩ ፍላጎታቸውን መሰረት ያደረጉ የሰብአዊ ድጋፎች አለማግኘታቸው ተደራራቢ የመብቶች ጥሰትን አስከትሏል ተብሏል። በሀገሪቱ በተከሰቱ የኮቪድ ወረርሽኝ፣ ድርቅ፣ ጦርነትና ግጭት ሳቢያ የትምህርትና የጤና አገልግሎቶች በመቋረጣቸው፣ ወይም የተለያዩ ገደቦች መኖራቸው በሴቶችና ሕፃናት ትምህርትና ጤና የማግኘት መሰረታዊ መብቶች ላይ ከፍተኛ ጫና ማሳደራቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል።
በተጨማሪም፣ ሴቶችና ሕፃናት ለሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርና ለብዝበዛ መጋለጥ፣ በኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚሠሩ ሴት ሠራተኞች መሰረታዊ መብቶች ጥሰቶች መቀጠልና በእነዚህ የመብቶች ጥሰት ረገድ የቁጥጥርና የተጠያቂነት መላላት ሌላው አሳሳቢ ጉዳይ መሆኑ ነው በሪፖርቱ የተጠቆመው።
በሕዝባዊ ጉዳዮች ላይ ከመሳተፍ መብት ጋር በተያያዘም፣ ሕፃናት በማናቸውም ጉዳይ ላይ ሃሳባቸውን በነፃ የመግለጽና በሚመለከታቸው ጉዳዮች ላይ ተሳትፎ የማድረግ መብታቸውን ለመተግበር የሚያስችል ሕግ አለመኖር፤ ሴቶችም በምርጫና በፖለቲካ ውስጥ ውጤታማ ተሳትፎ እንዳያደርጉ የአመለካከት ችግሮችና ጾታን መሰረት ያደረጉ ጥቃቶች እክል መፍጠራቸው፤ እንዲሁም በሰላም ግንባታና በሀገራዊ ምክክር እና ሌሎች የሕዝባዊ ውይይት መዋቅሮች ውስጥም ጾታዊ አካታችነት በእጅጉ ውስን በመሆኑ፣ የሴቶች ተሳትፎ ተገድቧል ብሏል፤ ሪፖርቱ።
ከወንጀል ጉዳይ ጋር በተያያዘ በፍትሕ ሥርዓት ውስጥ የሚያልፉ ልጆች አያያዝ ከሕፃናት ፍትሕ መርሆዎችና መመዘኛዎች ውጪ መሆን፣ በወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሴቶች ሁኔታ ከመሰረታዊ የሴት እስረኞች አያያዝ መስፈርቶች ጋር አለመጣጣም፣ ከእናቶቻቸው ጋር በእስር ቤት የሚቆዩ ሕፃናት ትምህርትና አማራጭ እንክብካቤ የማግኘት መብቶች መጓደል፣ በወንጀል ፍትሕ አስተዳደር ሥርዓት ውስጥ ያሉ ክፍተቶች በሪፖርቱ ከተለዩ ጉድለቶች መካከል ናቸው። ከዓለም አቀፍ የሰብአዊ መብቶች መስፈርቶች ጋር በተጣጣመ ሁኔታ ለሕፃናት ነፃና ለሁሉ ተደራሽ የሆነ የልደት ምዝገባ አሠራር በሀገር አቀፍ ደረጃ በሕግ አለመደንገጉ እንዲሁም በተወሰኑ ክልሎች ደግሞ የቤተሰብ ሕግ አለመውጣቱ ከተስተዋሉት የሕግ ክፍተቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።
በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የደኅንነት ሥጋቶች መቀጠላቸው የሴቶችንና ሕፃናትን ሁኔታ በሚፈለገው ቅርበት እና ፍጥነት ለመከታተል እንዳይቻል እንቅፋት የፈጠረ መሆኑ፣ በእነዚህ አካባቢዎች የሚሠሩ የሲቪል ማኅበራትና አጋሮች አቅምም መዳከሙና በኮሚሽኑ የሚሰጡ ምክረ ሃሳቦችን ተግባራዊ ከማድረግ አኳያ በቅንጅት ለመሥራት የሚያስችል ጠንካራ የጋራ መድረክ አለመኖር ፈታኝ ሁኔታ መፍጠሩም ተጠቁሟል።
የኢሰመኮ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች ኮሚሽነር መስከረም ገስጥ፣ የሴቶችንና የሕፃናት መብቶችን በተመለከተ ኮሚሽኑ ባከናወናቸው ክትትሎች፣ ምክክሮችና የተለያዩ ክንውኖች ትብብር በማድረግና ግብዓት በመስጠት ኃላፊነታቸውን ለተወጡ መንግሥታዊም ሆነ መንግሥታዊ ያልሆኑ አካላት ምስጋናቸውን አቅርበው፣ በኢትዮጵያ ለሚገኙ ሕፃናትና ሴቶች ከግጭት፣ ከጥቃትና ከመድልዎ ነፃ የሆነ፤ ዘላቂ ሰላምና እኩልነት የሰፈነበት ሕይወትን እውን ለማድረግ በሪፖርቱ የተካተቱትን ምክረ-ሃሳቦች በመፈጸምና በማስፈጸም የተቀናጀ ጥረትና ርብርብ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ኮሚሽነር መስከረም አክለውም፤ “ሰብአዊ መብቶችን ማክበር፣ ማስጠበቅና ማሟላት የመንግሥት ዋነኛ ግዴታ በመሆኑ የሕግ ማዕቀፎችን፣ ተቋማትንና አሠራሮችን በማሻሻል፣ ፍትሕን ተደራሽ በማድረግ፣ በግጭቶች የወደሙ የትምህርትና የጤና ተቋማትንና ሌሎች መሰረተ-ልማቶችን መልሶ በመገንባትና ለተጎጂዎች ሁለንተናዊ ተሐድሶን በማመቻቸት የሕፃናትንና የሴቶችን ሰብአዊ መብቶች የማሻሻል ኃላፊነቱን መወጣት አለበት። በተጨማሪም መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ፣ እንዲሁም ሌሎች ባለድርሻ አካላትና ጠቅላላ ማህበረሰቡ በሰብአዊ መብቶች ማዕቀፍ በተቀመጠው አግባብ በሀገሪቱ የሴቶችና የሕፃናት መብቶች አፈጻጸምን በማረጋገጥ ረገድ የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቀርባለሁ” ብለዋል።

 ታዋቂው የኦሮምኛ ዜማ አቀንቃኙ ክቡር ዶክተር ዓሊ ቢራ ባደረበት ህመም ህክምና ሲከታተል ቆይቶ፣ ከዚህ ዓለም በሞት መለየቱን የመንግስት መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል፡፡

 ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ባስተላለፉት የሃዘን መልዕክት፤"የአንጋፋው ድምጻዊ ዓሊ ቢራ ኅልፈት ለኢትዮጵያ ጉዳት ነው። በዜማዎቹ ኅብረትን፣ ጽናትንና ባህልን አቀንቅኗል። ለብዙዎችም አርአያ ሆኗል። ላደረከው ሁሉ ኢትዮጵያ ታመሰግንሃለች።" ብለዋል፡፡

 አርቲስት ዓሊ ቢራ በ1954 ዓ.ም የኦሮምኛ ሙዚቃን ለማስተዋወቅ ዓላማ ያደረገ የባህላዊ ሙዚቃ ቡድን “አፍረን ቀሎ”ን በመቀላቀል ነበር፣ የሙዚቃ ስራውን የጀመረው። አርቲስቱ ከኦሮምኛ በተጨማሪ፣ በሶማሊኛ፣ አፋርኛ፡ ሐረሪ፣ አማርኛና አረብኛ ቋንቋዎች በርካታ ዘፈኖችን ተጫውቷል።

 ዝግጅት ክፍሉ በክቡር ዶክተር አሊ ቢራ ህልፈት የተሰማውን ጥልቅ ሃዘን እየገለጸ፤ፈጣሪ ለቤተሰቦቹ ወዳጆቹና አድናቂዎቹ መጽናናትን ይመኛል፡፡

   ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

   “እየሰማን ያለነው የሰላም መልእክት ሳይሆን ተከታታይ ማስጠንቀቂያዎችን ነው። ነገር ግን በርካታ የፖለቲካ ምስቅልቅሎችን ማለፍ እንደቻለች ኩሩ አፍሪካዊት ሀገር [የተባበሩት መንግሥታት] አባል ሀገራትን አንድ ነገር ማስታወስ እፈልጋለሁ።
በርካታ ችግሮቻችንን ተጋፍጠን እንዳለፍናቸው ሁሉ፣ ዛሬም የገጠሙንን ችግሮች በእርግጠኝነት እንሻገራቸዋለን። በአንዳንድ ኃያላን ሀገሮች ዐይን ፊት ልክ በሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወቅት እንደሆነው [ኢትዮጵያውያን] ዐቅመቢስ መስለን እንታይ ይሆናል።
ክቡር ሊቀ መንበር፤ ...
አንድ ነገር ግን ላረጋግጥልዎት እወዳለሁ።
የውስጣችን መንፈስ ጽኑ ነው! ... የውስጣዊ መንፈሳችን ጥንካሬ ኢትዮጵያዊ ሆኖ ለመቆም ብቻ ሳይሆን ሰላማዊ ለመሆን እና ተግዳሮቶቻችንን ለመፍታትም ጭምር ነው።
የ120 ሚሊዮን ሕዝባችንን ዕድል ለ200 ኤክስፐርቶች ልንተወው አንችልም።
ይህንን ብዬ፤ ... ሁልጊዜም ቢሆን በጎ ሀሳብ ያላቸውን ተሳታፊዎች በደስታ የምንቀበል ሲሆን ሊያወግዙን እና ለሞት አሳልፈው ሊሰጡን ቀድመው የወሰኑትን ግን “የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር ይበላቸው” እላለሁ።
ስለዚህ እንደ [ኢትዮጽያ] መንግሥት ላረጋግጥላችሁ የምፈልገው፤ ሁሉም የሰብአዊ መብት ጥሰት ላይ የተሳተፉትን ተጠያቂ እናደርጋቸዋለን።  ይህንንም የምናደርገው የተወሰኑ ድርጅቶችን ወይንም ኤክስፐርቶችን ለማስደሰት ሳይሆን ለራሳችን መርህ ስንል ነው። ዘላቂ ሰላም መስፈን የሚችለው በሁሉም አካባቢዎች ለተሠሩ ወንጀሎች ተጠያቂነት እና ፍትሕ ሲሰፍን ብቻ መሆኑን እንረዳለን። ነገር ግን ይህ በሀገሪቱ ባለቤትነት መመራት አለበት።
አመሠግናለሁ፤ ክቡር ሊቀ መንበር፡፡”

Saturday, 05 November 2022 11:41

ከሶሻል ሚዲያ በጨረፍታ

 “በሀገሬ ተስፋ አልቆርጥም የምለው ለዚህ ነው!”

      ምስጋናና ክብር ለኢትዮጵያ ሀገራችን ለተዋደቃችሁ የሀገር መከላከያ ሰራዊት አባላት!
ምስጋናና ክብር ለአማራ ፋኖ፣ ልዩ ሀይልና ሚሊሻ አባላት!
ምስጋናና ክብር ለአፋር ሚሊሻና ልዩ ሀይል አባላት!
ምስጋናና ክብር በዲፕሎማሲው ጦርነት ከምእራባውያን ጋር ለታገላችሁ በሙሉ!
ልክ የዛሬ ሁለት አመት ነው የኢትዮጵያውያንን ተስፋ ያጨለመ ዜና የሰማነው፤ በሰሜን እዝ ላይ የደረሰው ጭፍጨፋና የትህነግ የጦርነት ክተት፡፡ ዛሬ በሁለት አመቱ ደግሞ ያ ተስፋችን ላይ ብርሀን ፈንጥቋል፡፡ በእርግጥ ትህነግ ወደ ድርድር የገባው በጦርነት ተሸንፎ በመሆኑ፣ ይህ ነው የሚባል ተጽእኖ እንደማያሳድር ግልጽ ነበር።  ይሁን እንጂ የአሜሪካና የአውሮፓ ህብረት ትህነግ ላይ ነፍስ ለመዝራት በኢትዮጵያ ላይ ያሳደሩት ጫናና በተደጋጋሚ የሚያወጡት መግለጫ ሲታይ፣ ትህነግ እንዲህ በቀላሉ ትጥቁን ለመፍታትና እራሱን ለማክሰም ይስማማል ተብሎ አልተጠበቀም፡፡ ይህ ድል የመላው ኢትዮጵያውያን ድል ነው፤ ሽንፈቱ ደግሞ የምእራባውያን፡፡ በቅርቡ ምእራባውያን በዚህ መጠን ዘምተው የተሸነፉበት ግንባር ያለ አይመስለኝም፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት በአንድ ጊዜ በሶስት ጦር ሜዳዎች ድል አድርጓል፤ (1) በምድር ላይ ባለው ጦርነት (2) በዲፕሎማሲ፣ (3) በፓን አፍሪካኒዝም፡፡ ይህ ለሀገራችን ትልቅ ሀይል ነው፡፡ በሸኔና በሌሎች ታጣቂዎች ላይ በአጭር ጊዜ ተመሳሳይ ድል ማስመዝገብና ጅምሩ ያማረውን የእርሻ ምርት በስፋት ማስቀጠል ከተቻለ፣ የሀገራችንን የሰላምና የእድገት ተስፋ የተሟላና እውን ማድረግ ይቻላል፡፡ . . . ምንጊዜም ኢትዮጵያ ተስፋ አላት!
(በድሉ ዋቅጅራ)

Page 7 of 632