
Administrator
58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ የቦንደስ ሊጋ ሆነች
ለ58ኛዋ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫ ጀርመንን የወከሉ ሁለት ክለቦች ለፍፃሜ ጨዋታ መድረሳቸው የቦንደስ ሊጋን የበላይነት አረጋገጠ፡፡ ከ3 ሳምንት በኋላ የቦንደስሊጋ ደርቢ የተባለውን የሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ የእንግሊዙ ዌምብሌይ ስታድዬም ሲያስተናግድ ቦርስያ ዶርትመንድ ከባየር ሙኒክ ይፋለማሉ፡፡ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የፍፃሜ ጨዋታ በ70 አገራት በ40 የተለያዩ የኮሜንታተር ቋንቋዎች በሚኖረው የቀጥታ ስርጭት ከ120 ሚሊዮን በላይ ተመልካች እንደሚያገኝ ታውቋል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ ግማሽ ፍፃሜ ሁለቱን የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ክለቦች የጀርመን ቦንደስ ሊጋው ክለቦች 11ለ3 በደርሶ መልስ ውጤት አሸንፈዋል፡፡ በዘንድሮ የጀርመን ቦንደስሊጋ ሻምፒዮናነት ፍፁም የበላይነት የነበረው ባየር ሙኒክ በሜዳው አሊያንዝ አሬና ባርሴሎናን 4ለ0 ካሸነፈ በኋላ በመልሱ ኑካምፕ ላይ ባርሴሎናን በድጋሚ 3ለ0 በሜዳው አንበርክኮ በድምር ውጤት 7ሎ በመርታት ወደ ዋንጫው ማለፉን አረጋግጧል፡፡
የአምናው የቦንደስ ሊጋ ሻምፒዮን ቦርስያ ዶርትመንድ በበኩሉ የአምናው የፕሪሚዬራ ሊጋ ሻምፒዮን ሪያል ማድሪድን በሜዳው 4ለ1 ካሸነፈ በኋላ በሳንቲያጎ በርናባኦ 2ለ0 ቢረታም በአጠቃላይ ውጤት 4ለ3 በማሸነፉ ወደ ዋንጫው ፍልሚያ ተሸጋግሯል፡፡ በሻምፒዮንስ ሊጉ የግማሽ ፍፃሜ የዓለም ስፖርት አፍቃሪ አራት አይነት የፍፃሜ ጨዋታዎችን ሲጠባበቅ ነበር፡፡ ከአራቱ ዓይነት የፍፃሜ ፍልሚያዎች ሊከሰት የበቃው ግን ባየር ሙኒክ ከቦርስያ ዶርትመንድ የሚፋጠጡበት የቦንደስ ሊጋ ደርቢ ነው፡፡ ሁለቱ የስፔን ክለቦች ባርሴሎና እና ሪያል ማድሪድ በሜዳቸው ባደረጉት የመልስ ጨዋታዎቻቸው ተጋጣሚዎቻቸውን ቢያሸንፉ ኖሮ ዋንጫው የኤልክላሲኮ ድግስ ነበረ፡፡ ሌሎቹ ሁለት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የዋንጫ ፍልሚያዎች ደግሞ ባርሴሎና ከቦርስያ ዶርትመንድ ወይንም ሪያል ማድሪድ ከባየር ሙኒክ የሚገናኙባቸው እና ቦንደስ ሊጋን ከፕሪሚዬራ ሊጋ የሚያፋጥጡ ድራማዎችም ነበሩ፡፡
በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የቦንደስ ሊጋ ደርቢ ሲያጋጥም የመጀመርያው ነው፡፡ ከዘንድሮ በፊት በውድድሩ ታሪክ የአንድ አገር ተወካይ ክለቦች ለፍፃሜ የተገናኙት በ3 የዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ነበር ፡፡ የመጀመርያው በ2003 እኤአ ላይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በፕሪሚዬራ ሊጋ ደርቢ ሪያል ማድሪድ ቫሌንሽያን 3ለ0 በመርታት ዋንጫ የወሰደበት ነበር፡፡ ሁለተኛው በ2005 እኤአ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በጣሊያን ሴሪኤ ደርቢ ኤሲ ሚላን በመለያ ምቶች ጁቬንትስን 3ለ2 አሸንፎ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃበት ነበር፡፡ ሶስተኛው ደግሞ በ2008 አኤአ ላይ የሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ደርቢ ማን ዩናይትድ ከቼልሲ ጋር አገናኝቶ ፤በመደበኛ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ 1 እኩል አቻ ከተለያዩ በኋላ ማን ዩናይትድ በመለያ ምቶች 6ለ5 አሸንፎ ዋንጫውን ያነሳበት ነበር፡፡ በዘንድሮው የአውሮፓ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ የግማሽ ፍፃሜ ምእራፍ ላይ ከጀርመንና ከስፔን የተወከሉ አራት ክለቦች ሲገኙ ከ13 አመታት በኋላ ለመጀመርያ ጊዜ ነበር፡፡ ይህ ሁኔታ በአውሮፓ ታላላቅ ሊጎች መካከል የነበረው የሃይል ሚዛን ከእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በመሸሽ ወደ ጀርመን ቦንደስ ሊጋ መጠጋቱን አረጋግጧል፡፡
የስፔን እግር ኳስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አንጀላ ማርያ የግማሽ ፍፃሜው ትንቅንቅ ከፕሪሚዬራ ሊጋው እና ከቦንደስ ሊጋው የትኛው እንደሚልቅ ምላሽ ይሰጣል በማለት ተናግረው የነበረ ሲሆን ጀርመኖች ስታድዬሞች ቢኖራቸውም ምርጥ ውድድር ያለን ስፓንያርዶች ነን ብለው ፉክክሩን ለማሸነፍ ፍላጎት አሳይተው አልሆነላቸውም፡፡ የዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ግማሽ ፍፃሜ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ እና የስፔን ፕሪሚዬራ ሊጋ ንፅፅር ውስጥ በማስገባትም አከራካሪ ሆኖ ሰንብቷል፡፡ ከቦንደስ ሊጋ እና ከፕሪሚዬራ ሊጋው የቱ ይበልጣል በሚለው ክርክር ሚዛን ከደፉ አጀንዳዎች የሁለቱ አገር ክለቦች አጨዋወት የመጀመርያው ነው፡፡ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ የመከላከል ስትራቴጂ በብሎኬት ግንብ የተመሰለና የማጥቃት ጨዋታው በከፍተኛ ወራራ የሚታጀብ መሆኑ ተገልጿል፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ደግሞ በሚያምር የኳስ ቁጥጥር እና ቅብብል እንዲሁም በፈጠራ በተሞሉ የግብ አይነቶቹ ተፎካካሪነቱ ተጠቅሷል፡፡ ለጀርመን ቦንደስ ሊጋ ምርጥነት ግን ብዙ ምክንያቶች እየተዘረዘሩ ናቸው፡፡ በአካዳሚዎች ጥራት፤ በስታድዬም ዋጋ መርከስ እና በተመልካች መሞላት፤ በጤናማ የፋይናንስ እንቅስቃሴ የጀርመን እግር ኳስ የአውሮፓ ደረጃ በከፍተኛ ልዩነት እየመራ ይገኛል፡፡
ለዘንድሮ የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ ፍፃሜ በደረሱት ሁለቱ የጀርመን ክለቦች ከአካዳሚዎች የወጡ ከ10 በላይ ወጣት ተጨዋቾች ይገኛሉ፡፡ በባየር ሙኒክ ፊሊፕ ላሃም፤ ባስትያን ሽዋንስታይገር፤ ቶማስ ሙለርእና ዴቪድ አላባ እንዲሁም በዶርትመንድ ማርዮ ጎትሴዜ፤ ማርኮ ሬውስ እና ኑሪ ሳሂን በየክለቦቹ ከሚገኙ አካዳሚዎች የተመለመሉ ናቸው፡፡ የጀርመን እግር ኳስ ላይ በታዳጊ እና ወጣት ፕሮጀክት በስፋት መሰራት ከጀመረ ከ10 ዓመታት በላይ አልፏል፡፡ በዚህ ጊዜ ውስጥ ደግሞ ከ713 ሚሊዮን ዩሮ በላይ እድሜያቸው 19 እና 20 የሚሆናቸው ምርጥ ፕሮፌሽናሎችን ለማፍራት ተችሏል፡፡ ስለሆነም ደግሞ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ክለቦች በአገር ውስጥ ውድድር እና በአህጉራዊ ደረጃ በሚያሳዩት ስኬት ይሄው የአካዳሚዎች አስተዋፅኦ ጎልቶ ወጥቷል፡፡ ከወጣት ተጨዋቾች ባሻገር ከጀርመን ቦንደስ ሊጋ 18 ክለቦች ካንዱ በቀር በሁሉም እየሰሩ ያሉት አሰልጣኞች አገር በቀል መሆናቸው ሌላው ለእግር ኳሱ መጠናከር ምክንያት የሆነ ነው፡፡ በትርፋማነት የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ቀዳሚ ቢሆንም ቦንደስሊጋም በፍጥነት እያደገ ነው፡፡ 2013 ሲገባ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ 2.1 ቢሊዮን ዶላር ባንድ የውድድር ዘመን በሪከርድ ስኬት ገቢ አድርጓል፡፡ በሚቀጥለው የውድድር ዘመን ቦንደስ ሊጋው በቴሌቭዥን የስርጭት መብት የሚያገኘው ገቢ መጨመር ደግሞ የሊጉን ትርፋማነት ያሳድገዋል፡፡ የጀርመን ክለቦች የፋይናንስ ጤንነት እና የቦንደስ ሊጋው አስተዳደር 50 ሲደመር አንድ በሚለው ደንብ የክለቦች ባለቤትነት ድርሻን ለአባላት እንዲሆን ማስገደዱ ተመጣጣኝ አቅምና እና ፉክክር በውድድር እንዲኖር አድርጓል፡፡
የጀርመን ቦንደስ ሊጋ ጨዋታዎችን በስታድዬም ገብቶ ለመመልከት ያለው የትኬት ዋጋም ከሌሎች የአውሮፓ ሊጎች የረከሰ መሆኑም ሌላው ምክንያት ነው፡፡ አንድ የጀርመን ቦንደስ ሊጋን ጨዋታ ለመታደም ርካሹ የትኬት ዋጋ 12 ዩሮ ሲሆን ይህ ገንዘብ የትኛውንም የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ጨዋታ ለማየት አይበቃም፡፡ በአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ የ58 አመታት የውድድር ታሪክ በሁለት ክለቦች 13 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ቢሆንም በ5 ክለቦች ተመሳሳይ የዋንጫ ብዛት በመሰብሰብ የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ በሁለተኛ ደረጃ ይከተላል፡፡ የጣሊያኑ ሴሪኤ በ3 ክለቦች ባገኛቸው 12 ዋንጫዎች ሶስተኛ ደረጃ ሲይዝ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ3 ክለቦች 6 ጊዜ የአውሮፓ ሻምፒዮን በመሆን በአራተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡ በክለብ ደረጃ 9 የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን በመሰብሰብ የሚመራው የስፔኑ ሪያል ማድሪድ ሲሆን የጣሊያኑ ኤሲ ሚላን 7፤ የእንግሊዙ ሊቨርፑል 5 ዋንጫዎችን በመሰብሰብ ሁለተኛ እና ሶስተኛ ናቸው፡፡ ባየር ሙኒክ እና ባርሴሎና እያንዳንዳቸው አራት የሻምፒዮንስ ሊግ የዋንጫ ድሎችን በማስመዝገብ አራተኛ ደረጃ ሲወስዱ በተከታይነት የተመዘገበው ማን ዩናይትድ በሶስት የዋንጫ ድሎቹ ነው፡፡
ዶርትመንድ በ1 የሻምፒዮንስ ሊግ ድሉ በ22ኛ ደረጃ ላይ ተመዝግቧል፡፡ ታዋቂው የቢዝነስ መፅሄት ፎርብስ ይፋ ባደረገው የአውሮፓ ክለቦች የዋጋ ግምት ሪያል ማድሪድ በ2.532 ቢሊዮን ዩሮ ተመን አንደኛ ደረጃ ሲወስድ ማን ዩናይትድ በ2.429 ቢሊዮን ዩሮ ሁለተኛ ነው፡፡ በዚሁ የክለቦች የዋጋ ተመን ደረጃ ባርሴሎና በ1.995 ቢሊዮን ዩሮ ሶስተኛ ደረጃ ሲያገኝ ባየር ሙኒክ 1.017 ቢሊዮን ዩሮ በሚተመነው አርሰናል ተበልጦ በ1.005 ቢሊዮን ዩሮ የዋጋ ግምት አምስተኛ ደረጃን አግኝቷል፡፡ በአውሮፓ እግር ኳስ ማህበር በሚሰጠው ነጥብ መሰረት ባለፈው የውድድር ዘመን የአውሮፓ ታላቅ ሊጎች በወጣላቸው ደረጃ 84.10 በማስመዝገብ የሚመራው የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ ነበር፡፡ የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ በ84.08፤ የጀርመኑ ቦንደስ ሊጋ በ75.18 እንዲሁም የጣሊያኑ ሴሪኤ በ59.81 ነጥብ እስከ አራት ያለውን ደረጃ አከታትለው ይዘዋል፡፡
በስታድዬም የአንድ ጨዋታ አማካይ ተመልካች የሚመራው የጀርመን ቦንደስሊጋ 45116 አስመዝግቦ ሲሆን የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ 34601 እንዲሁም የስፔን ላሊጋ 28403 ተመልካች በአንድ የሊግ ጨዋታ በማግኘት ሁለተኛና ሶስተኛ ደረጃ ይወስዳሉ፡፡ በአንድ የውድድር ዘመን በሚያስገኘው የገቢ መጠን የሚመራው የእንግሊዙ ፕሪሚዬር ሊግ ከ2.5 ቢሊዮን ዩሮ በላይ በመሰብሰብ ነው፡፡ በገቢ መጠን ሁለተኛ ደረጃ የሚወስደው 892 ሚሊዮን ዩሮ በአንድ የውድድር ዘመን የሚያስገባው የጣሊያኑ ሴሪኤ ውድድር ሲሆን የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ በ560 ሚሊዮን ዩሮ እንዲሁም የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ422 ሚሊዮን ዩሮ ገቢያቸው ተከታታይ ደረጃ ተሰጥቷቸዋል፡፡
በ“ግንቦት 7” አባልነት የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል የተባሉ ተከሰሱ
መንግስት “ሽብርተኛ” ብሎ ከፈረጃቸው ድርጅቶች አንዱ የሆነውና በዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የሚመራው የግንቦት 7 አባል በመሆን የፈንጂ ስልጠና ሰጥተዋል በተባሉት ሻለቃ ማሞ ለማና አቶ አበበ ወንድማገኝ ላይ የቀረበው ክስ ከትላንት በስቲያ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ተሰማ፡፡ በእለቱ በተነበበው የክስ መዝገብ ላይ አቶ አበበ ወንድማገኝ፤ በእንግሊዝ ሃገር ከሚገኙት ሻለቃ ማሞ ለማ ጋር በተደጋጋሚ በዱባይና ለንደን በመገኘት የፈንጂ ጥቃት ለማድረስ የሚያስችል ስልጠና በኤርትራ ወስደዋል ይላል፡፡
ወደ አዲስ አበባ ከተመለሱ በኋላ፣ ግለሰቦችን በመመልመል የትጥቅ ትግል ለማድረግ በማሰልጠን ለሽብር ተግባር አነሳስተዋል በማለት አቃቤ ህግ ባቀረበው ክስ፣ አቶ አበበ ወንድማገኝ ጥር 15 ቀን 2005 ዓ.ም ቦሌ ሰሚት አካባቢ መኪና ውስጥ 10 “c4” የተሰኙ ፈንጂዎችንና ማቀጣጠያ ገመዶችን ይዘው ተገኝተዋል ብሏል፡፡ የተከሳሽ ጠበቃ ባቀረቡት መቃወሚያ፤ የአቃቤ ህግ ክስ በየትኛው አዋጅ እንደቀረበ ክሱ እንደማያመለክት ጠቁመው፤ ደንበኛቸው የፈንጂ ስልጠና መስጠቱን እንዳልካደ በመግለፅ፤ አቃቤ ህግ ያቀረበው የክስ አንቀፅ እንዲያሻሽል ፍ/ቤቱን ጠይቀዋል፡፡
ስልጠና መስጠትን ብቻ የሚመለከት ስላልሆነ ራሱን አንዲያሻሽል ጠይቀዋል፡፡ አቃቤ ህግ በበኩሉ፤ የተከሳሽ ድርጊት በሰው ህይወት፣ በአካልና በንብረት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል እንደነበር የሚያካትት ክስ እንዳቀረበ ገልጿል፡፡ “ተከሳሹ ስልጠና ብቻ ነው የሰጠው” የሚባለው ጉዳይ ማስረጃ የምናረጋግጠው ነው በማለት አቃቤ ህግ አክለው ገልፀዋል፡፡ ፍርድ ቤቱ ብይን ለመስጠት ለፊታችን ሰኞ ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል፡፡
አፀያፊ ስድብ የተሳደበች ተቀጣች
የአረብ ሃገር ተጓዧን ያታለሉት በእስራት ተቀጡ የ14 ዓመቷን የቤት ሠራተኛ የደፈረው 10 አመት ተፈርዶበታል በአዲስ አበባ ጐማ ቁጠባ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ሂሩት አጽበሃን “ሸርሙጣ” ብላ የሰደበችው ኪሮስ ሃይሉ በ15 ቀናት የጉልበት ስራ እንድትቀጣ ከትላንት በስቲያ ሐሙስ ተወሰነ፡፡ በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 14ኛ ወንጀል ችሎት በቀረበው የክስ አቤቱታ ላይ እንደተመለከተው፤ ተከሳሽ የ50 አመቷ ወ/ሮ ኪሮስ ተበዳይን ሸርሙጣ፣ ሌባ፣ ቡዳ የሚሉ ስድቦችን የሰደበቻት ሲሆን ይህም በሰው ምስክር መረጋገጡ ተጠቁሟል፡፡ ፍርድ ቤቱም ድርጊቱ ደረጃ እና እርከን ያልወጣለት መሆኑን በመግለጽ፣ ተከሳሽ ለ15 ቀናት የግዴታ የጉልበት ስራ እንድትሰራ የወሰነ ሲሆን ውሳኔው በቀበሌ 12/14 እንዲያስፈጽምና ውጤቱን እንዲያሳውቅ ፍ/ቤቱ አሳስቧል፡፡ አቃቤ ህግ የቅጣት ማክበጃ ባለማቅረቡ እንጂ ቅጣቱ ከዚህም የከበደ ሊሆን እንደሚችል ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል ተከሳሾች ምስሬ ጌትነት መንግስቱ የተባለው ወጣት እና ግብረ አበሩ ሰዓዳ ሙሃቢን የተባለች ግለሰብ ላይ ለፈፀሙት የማጭበርበር ወንጀል እስራትና የገንዘብ ቅጣት ተበይኖባቸዋል፡፡ ሚያዚያ 2 ቀን 2005 ዓ.ም ከጠዋቱ 3 ሰዓት ላይ 1ኛ ተከሳሽ:- ሰአዳ ሙሃቢን የተባለች የግል ተበዳይን በተለምዶ አሜሪካን ግቢ በሚባለው ቦታ አግኝቷት ወደ ጋምካ እንደምትሄድ ስትገልጽለት፣ እኔም የእህቴን ዶክመንት ይዤ ልሄድ ነውና አብረን እንሂድ በማለት ጋምካ ከደረሱ በኋላ፣ ከ2ኛ ተከሳሽ ጋር በመሆን ተበዳይን ሁለት መቶ ብር ተከፍሎ የሚወሰድ ትኬት አለ፤ ይህን ትኬት ካልያዝን ማለፍ አንችልም፣ ትኬቱ ሲገዛም እቃ ወይም ንብረት ይዞ መግባት አይቻልም በማለት፣ ሁለተኛ ተከሳሽ ተበዳይዋን ይዟት ትኬት ይቆረጣል ወደተባለበት ቦታ ሲወስዳት፣ ሁለተኛ ተከሳሽ የግል ተበዳይ ይዛው የነበረውን 10,800 ብር፣ እንዲሁም 2ሺ 400 ብር የሚያወጣ ኖኪያ እና መታወቂያ ካርድ ተቀብሎ ከአካባቢው የተሰወረ በመሆኑ በአታላይነት ተከሰው በ1 አመት ከ3 ወር እስራት እና በ200 ብር እንዲቀጡ ተወስኗል፡፡
በዚያው በፌዴራል ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 7ኛ ወንጀል ችሎት በተሰጠ ሌላ ውሣኔ አቶ ተከስተ ዘሪሁን ለገሠ የተባሉት አባወራ በ26/01/2005 ዓ.ም ከሌሊቱ በግምት ስድስት ሰአት ሲሆን በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ልዩ ቦታ ኮንዶሚኒየም ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፣ የ14 አመቷን ህፃን የቤት ሠራተኛውን፤ ሚስቱ ያለመኖሯን በማረጋገጥ በሹራብ አፍኖ በመድፈር፣ ክብረንፅህናዋን በመገርሰሱ በፈፀመው ወንጀል በ10 ዓመት እስራት እንዲቀጣ ፍርድ ቤቱ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
የፍቺ ቢዝነስ በአሜሪካ፡ ከ900 ሺ ፍቺ በአመት 30 ቢ. ዶላር የኢትዮጵያውንማ፣ “ቤቱ ይቁጠረው” ነው የሚባለው!
(የአሜሪካውያን ነገር! መፍትሄ ይዞ ብቅ የሚል አይጠፋም። ሚቸል ክሮዝቢ፣ የፍቺ ወጪዎችን በሶስት እጅ የሚቀንስ ዘዴ በመፍጠር ቢዝነስ ጀምራለች።) አዲስ አበባ ውስጥ ሁለት መኖሪያ ቤት የነበራቸው ባልና ሚስት፣ በፍቺ ሲለያዩ የፈጠሩትን ፀብ ልንገራችሁ። እንደ ምርጫቸው አንድ አንድ መከፋፈል ይችሉ ነበር። ባል አንደኛውን ቤት መረጠ። ሚስት ምንም አልከፋትም። የመኖሪያ ቤቶቹ ዋጋ ተቀራራቢ ስለሆነ፣ ሌላኛውን ቤት መረጠች። በቃ? በጭራሽ! ሚስትዬው ያለምንም ጣጣ ስለተስማማች፣ ባልዬው በቁጭትና በእልህ ተነሳስቶ ሃሳቡን ቀየረ። እንለዋወጥ አለ - ሚስትን ለማሳረር በመመኘት።
የራሱን ጥቅም ሳይሆን፣ የሚስቱን ጉዳት ለማየት ነው የናፈቀው። በእርግጥ ሚስትዬው፣ አንደኛውን ቤት እስካገኘች ድረስ ግድ አልነበራትም። ግን እልህ ውስጥ ገባች፤ “አይሆንም!” አለች። ሁለቱን ለማስታረቅ ያልተደረገ ሙከራ ባይኖርም አልተሳካም። ስለዚህ መኖሪያ ቤቶቹ ተሸጠው በገንዘብ እንዲከፋፈሉ ተወሰነ። አቶ ባል፣ ነገርዬው እንዲህ እየከረረ እዚህ ደረጃ ላይ የሚደርስ አልመሰለውም ነበር። ግን፣ የተበላሸውን ነገር መልሶ ማስተካከል አይችልም። ቤት የሚገዛ ሰው ፈልገው ማምጣት አለባቸው፤ ወይም ደግሞ በፍርድ አፈፃፀም መስሪያ ቤት በኩል፣ በሃራጅ ቤቶቹ ይሸጣሉ። ያው፤ ለሃራጅ የቀረበ ንብረት ብዙም ዋጋ አያወጣም። ለዚህም ነው፤ ባልዬው ቤት የሚገዙ ሰዎችን አፈላልጎ ያመጣው። ይህን ሁሉ ጣጣ በመፍጠሩ የተበሳጨችው ሚስትዬው ግን ፈቃደኛ አልሆነችም። በሃራጅ ካልተሸጠ ሞቼ እገኛለሁ አለች። የራሷን ጥቅም ከማስላት ይልቅ፣ የባልዬውን መክሰር ለማየት ጓጉታለች።
ከፍርድ አፈፃፀም ሰራተኞች እንደሰማሁት፣ ቤቶቹ በሃራጅ ስለተሸጡ ሁለቱ ሰዎች ወደ 300 ሺ ብር ገደማ ከስረዋል። ከፍቺ ጋር አላስፈላጊ እልህ የሚፈጠረው በኢትዮጵያ ብቻ አይደለም። የትም አገር ቢሆን፣ ትዳር በፍቺ ሲፈርስ፣ ብዙውን ጊዜ አዲስ ጥላቻና ቂም ያበቅላል። ባለትዳሮቹን ለፍቺ ከገፋፋቸው ጥላቻ ይልቅ፣ ለመፋታት ከወሰኑ በኋላ በንብረት ክፍፍልና በልጅ አስተዳደግ ጉዳዮች ላይ ሲከራከሩ የሚፈጠረው ጥላቻ የባሰ ነው። በእርግጥ በሰለጠኑት አገራት፣ የፍቺ ጣጣዎችን በስርዓት ለማስኬድና የመናቆር ስሜቶችን ለማብረድ፣ ባልና ሚስት የህግ ባለሙያዎችን (ጠበቆችን) ይዘው ነው የሚከራከሩት ወይም የሚደራደሩት። ግን፣ ይሄም ቢሆን ወጪው ቀላል አይደለም። አሜሪካ ውስጥ፣ በፍቺ የሚለያዩ ጥንዶች፣ እያንዳንዳቸው በአማካይ 10 ሺ ዶላር ለህግ አማካሪ ይከፍላሉ። አንድ ትዳር ሲፈርስ 20 ሺ ዶላር ለጠበቆች ክፍያ ይውላል ማለት ነው። ሌሎች ወጪዎች ተጨምረውበት፣ በአሜሪካ የፍቺ ነገር በአመት 30 ቢሊዮን ዶላር ገደማ እንደሚፈጅ፣ ሰሞኑን የወጣው የፎርብስ መፅሄት ገልጿል።
ምን ያህል ሰው በዚህ ወጪ እንደሚቸገር አስቡት። የቢዝነስ ስራ ዋነኛ ባህርይ፣ “ችግሮችን የሚያቃልልና ወጪዎችን የሚቀንስ መፍትሄ” ማቅረብ አይደል? ይሄውና፣ የ37 አመቷ ሚቸል ክሮዝቢ፣ የፍቺ ወጪዎችን በሶስት እጅ የሚቀንስ ዘዴ በመፍጠር የቢዝነስ ስራ ጀምራለች። ጥንዶች ለፍቺ ከሃያ ሺ ዶላር በላይ ማውጣት አይኖርባቸውም። ከ7ሺ ዶላር ባነሰ ወጪ ጉዳያቸውን በድርድር ይጨርሳሉ። በዚያ ላይ ደግሞ፣ ከተጨማሪ ቂምና ጥላቻ ይድናሉ የምትለው ክሮዝቢ፣ በቢዝነሷ ስኬታማ በመሆኗ ባለፉት ጥቂት ወራት ድርጅቷ አንድ ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል - ፎርብስ እንደዘገበው።
መቼስ፣ ፍቺ ከተፈፀመ አይቀር፣ ወጪንና ጥላቻን የማያባብስ ዘዴ ሲገኝለት መልካም ነው። በአሜሪካ ከጊዜ ወደ ጊዜ ጋብቻና ፍቺ የሚፈፅሙ ሰዎች ከጠቅላላ የህዝብ ቁጥር ጋር ሲነፃፀሩ፣ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየቀነሱ መጥተዋል። ከሃያ አመት በፊት፣ ከአስር ሺ ሰዎች መካከል በአመት 98 ጋብቻዎች እና 47 ፍቺዎች ይፈፀሙ ነበር። ዛሬ የጋብቻዎቹ ቁጥር ወደ 68፣ የፍቺዎቹ ቁጥር ደግሞ ወደ 34 ቀንሷል። በአጠቃላይ ግን ባለፈው አመት በምድረ አሜሪካ ከ2.1 ሚሊዮን በላይ ጋብቻዎችና ወደ ዘጠኝ መቶ ሺ ገደማ ፍቺዎች ተፈፅመዋል። የአውሮፓም እንዲሁ ተመሳሳይ ነው፤ በአመት 2.2 ሚሊዮን ጋብቻዎችና አንድ ሚሊዮን ገደማ ፍቺዎች ይፈፀማሉ።
ለምርጫ ገንዘብ ያጣች “የአልማዝ” አገር - ዚምባብዌ የመንግስት ካዝና ውስጥ የነበረው ገንዘብ - 217 ዶላር ብቻ! የ“መቶ ትሪሊዮን” ገንዘብ እስከማተም ከተደረሰ ምን ጤና አለ?
በፖለቲካ ግጭትና በገንዘብ እጥረት ሳቢያ የተጓተተው የዚምባብዌ ምርጫ፣ በደቡብ አፍሪካ ሸምጋይነትና በ100 ሚሊዮን ዶላር እርዳታ እርዳታ ቢታገዝም፣ እንደገና ከመራዘም አለመዳኑን ዘ ጋርዲያን ዘግቧል። ለሰኔ ወር ታስቦ የነበረው ምርጫ፣ ወደ ሐምሌ፣ ከዚያም ወደ መጪው ጥቅምት ወር ተሸጋግሯል። በአልማዝ ማዕድን፣ በብረት ምርት፣ በእህል ኤክስፖርትና በሌሎች ጠንካራ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴዎች ትታወቅ የነበረችው አገር፣ እንጦሮጦስ የወረደችው በጥቂት አመታት ውስጥ ነው። ፕሬዚዳንት ሮበርት ሙጋቤ የሚመሩት መንግስት፣ የግለሰቦችን ንብረት እየወረሰና አለቅጥ ገንዘብ እያተመ፣ በ10 አመታት ውስጥ አገሪቱን የረሃብና የስራ አጥነት መናኸሪያ አድርጓቷል። የራሷ የገንዘብ ኖት የሌላትና ምርጫ ማካሄድ የማትችል የቀውስ መንደር የሆነችው ዚምባብዌ እንደአወዳደቋ በፍጥነት፣ ቶሎ ልታገግም ትችላለች ተብሎ አይታሰብም።
ዚምባብዌ፣ እንደ ሶማሊያ ወይም እንደ ኮንጎ በለየለት ጦርነት ውስጥ ሳትዘፈቅ፤ “በመንግስት ጥረት በአጭር ጊዜ ውስጥ የሾቀች አገር” በመሆኗ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ለየት የምትል ትመስላለች። ለዚህም ነው፣ የአውሮፓ አገራትና አሜሪካ በሙጋቤ መንግስት ላይ፣ የተለያዩ ማዕቀቦችን የጣሉት። ነገር ግን፣ የመጠንና የደረጃ ጉዳይ ካልሆነ በቀር፣ ዚምባብዌ ከሌሎች የአፍሪካ አገራት ብዙም አትለይም። እጅግ ገዝፈውና ገንነው የሚታዩት የዚምባብዌ ሁለት ዋና ዋና ችግሮች…፣ ያው በሌሎች የአፍሪካ አገራትም ዘወትር የሚታዩ ችግሮች ናቸው። በአንድ በኩል፣ በፖለቲካ አፈናና ግጭት የምትናጥ አገር ነች - እንደ ብዙዎቹ የአፍሪካ አገራት። በሌላ በኩል ደግሞ የግል ቢዝነስን እንደ ጠላት የሚፈርጅ መንግስት፣ አለቅጥ ገንዘብ ማተምንና የውጭ እርዳታን የለመደ ነው - ይሄም በበርካታ የአፍሪካ አገራት የሚታይ ችግር ነው። የኬቶ ኢንስቲቱይት ጥናት እንደሚያመለክተው፣ የዚምባብዌ መንግስት በየአመቱ ብዙ የገንዘብ ኖት የማተም አባዜው እየተባባሰ የመጣው የዛሬ 15 አመት ገደማ ነው።
ከዚያም በፊት ቢሆን፣ ከልክ ባለፈ የገንዘብ ህትመት ሳቢያ “የዚምባብዌ ዶላር” ቀስ በቀስ ዋጋ እያጣ ነበር። በየአመቱ የሸቀጦች ዋጋ ከአስር እስከ ሃያ በመቶ እየናረ ቆይቷልና። በኢትዮጵያና በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት በየጊዜው ከሚታየው የዋጋ ንረት አይለይም። እ.ኤ.አ ከ1998 በኋላ ግን፣ የገንዘብ ህትመቱ ይበልጥ እየጨመረ መጣ። እናም፣ ሃያ በመቶ የነበረው አመታዊ የዋጋ ንረት፣ ወደ 48% ዘለለ። መንግስት የገንዘብ ህትመቱን አደብ ሊያስገዛ ባለመፈለጉ፣ በቀጣዩ አመት የዋጋ ንረቱ ባሰበት - ወደ 60% ተጠጋ። እንደእብደት ሊቆጠር ይችላል። ግን፣ በአገራችንም ሚሊዬነሙ መባቻና የዛሬ ሁለት አመት የታየው የዋጋ ንረት፣ ስድሳ እና አርባ በመቶ ገደማ የደረሰ እንደነበር አስታውሱ። በእሳት መጫወት ይሉሃል ይሄ ነው! ለምን ቢባል፣ የገንዘብ ህትመት በጊዜ ካልተገታ፣ አብዛኛው ሰው በአገሬው ገንዘብ ላይ እምነት እያጣ፣ የዋጋ ንረት ከቁጥጥር ውጭ ይሆናል።
በዚምባብዌ ለሶስተኛ አመት ከሃምሳ በመቶ በላይ የሆነ የዋጋ ንረት ከተመዘገበ በኋላ ነው ነገር የተበላሸው። በ2001 የዋጋ ንረት ከእጥፍ ላይ በማሻቀቡ ኢኮኖሚው ተመሳቀለ። ከዚህ በኋላ መንግስት ሊቆጣጠረው አልቻለም። አዙሪት ውስጥ እንደመግባት ነው። በገንዘብ ህትመት የተነሳ ዋጋ ይንራል። በዋጋ ንረት ሳቢያ የመንግስት ወጪ ያሻቅባል። ወጪውን ለመሸፈን ገንዘብ ስለሚያትም የዋጋ ንረቱ ይባባሳል። በዚህ አዙሪት ውስጥ የገባው መንግስት፣ በዚያው አመት ለመጀመሪያ ጊዜ ባለ አምስት መቶ ኖት አሳተመ። በቀጣዩ አመት የዋጋ ንረት በእጥፍ ጨመረና 200% ደረሰ። መንግስት ባለ አንድ ሺ ኖት አሳተመ። የዋጋ ንረት ወደ 600% ተወረወረ። አንዴ ከቁጥጥር ውጭ ከሆነ በኋላ፣ እንደ ገና ወደ ጤንነት ለመመለስ ዳገት ነው። ያኔ፣ መንግስት ባለ 5ሺ፣ ከዚያ ባለ10ሺ፣ ከዚያም ባለ20ሺ ኖት አሳተመ - በሶስት ወራት ልዩነት። ትንሽ ቆይቶ ደግሞ ባለ ሃምሳ ሺ! የመቶ ሺ ኖት በታተመበት በ2006፣ የሸቀጦች ዋጋ በአመት ውስጥ በ12 እጥፍ ጨመረ። በ1998 ከነበረው የሸቀጦች ዋጋ ጋር ከተነፃፀረማ፣ የትየለሌ ነው። አንድ የዚምባብዌ ዶላር ይሸጥ የነበረው ክብሪት፣ ዋጋው ወደ ሰላሳ ሺ አሻቅቧል። በዚህ አላቆመም።
በቀጣዩ አመት መንግስት ባለ “ሁለት መቶ ሺ ኖት” ማሳተም ጀመረ። በወር ልዩነት የሩብ ሚሊዮን እና የግማሽ ሚሊዮን ኖቶች በገፍ ታተሙ። የዋጋ ንረት በአንድ አመት ውስጥ በስድስት መቶ እጥፍ ጨመረ። የዚምባብዌ መንግስት የ2008 አዲስ አመትን የተቀበለው ባለ ሚሊዮን ኖት በማሳተም ነው። ከዚያማ ተዉት። ወር ሳይሞላው ባለ አምስትና ባለ አስር ሚሊዮን ኖቶችን አምጥቶ አገሬው ላይ አራገፈው። ሁለት ወር ቆይቶ፣ በባለ 25 እና በባለ 50 ሚሊዮን ኖቶች አገር ምድሩን አጥለቀለቀው። አመቱ ሳይጋመስ፣ የመቶ ሚሊዮንና የአምስት መቶ ሚሊዮን ኖቶች ከታተሙ በኋላ፣ ባለ ቢሊዮን ኖት መጣ። አገር ጉድ አለ። የ25 እና የ50 ቢሊዮን ኖቶች እየታተሙ መሆናቸው አልታወቀም ነበር። የመቶ ቢሊዮን ኖት ደረሰ። በዚህ ወቅት “የዋጋ ንረት የት ደረሰ?” ብሎ ለማስላት መሞከር በጣም ከባድ ሆኗል - የሸቀጦች ዋጋ በየሰዓቱ ስለሚንር። የትሪሊዮን ኖቶች የመጡት በአዲስ አመት ነው - በ2009። በአመቱ የመጀመሪያው ወር ላይ፣ ዚምባብዌ የአለም ሪከርድ ሰበረች።
እስከዚያው ድረስ በአለማችን ከተመዘገቡት የዋጋ ንረት እብደቶች ሁሉ የባሰና፣ 14 ዜሮዎች የተደረደሩበት ባለ መቶ ትሪሊዮን ኖት አሳተመች። ግን ዋጋ የለውም። አንድ ሺ ያህል ባለ መቶ ትሪሊዮን ኖቶች ይዞ፣ አንዲት ዳቦ መግዛት አይቻልም። አብዛኛው ሰው፣ የአገሬውን ገንዘብ መጠቀም አቁሟል። በውጭ ምንዛሬ መገበያየት በአዋጅ ቢከለከልም፣ ሰዉ ሁሉ በዶላርና በዩሮ ብቻ የሚጠቀም ሆኗል። ምንም ማድረግ ስላልተቻለ፣ ከዚያን ጊዜ ወዲህ መንግስትም በዶላርና በዩሮ መጠቀም ጀመረ።
አገሪቱ ከዚያን ጊዜ ወዲህ የራሷ ገንዘብ የላትም። አዲስ አመትን በአዲስ የገንዘብ ህትመት መቀበል የለመደው የዚምባብዌ መንግስት፣ የእንጦሮጦስ ጉዞውን መቀጠል አልቻለም። እናም ዘንድሮ፣ በአዲስ አመት የመንግስት ካዝና ውስጥ የነበረው ገንዘብ 217 ዶላር ብቻ ነበር። ምርጫ ለማካሄድ መቶ ሚሊዮን ዶላር ከየት ይምጣ? እርዳታ ነዋ። አገሪቷ ግን በአልማዝ ማዕድን ከበለፀጉት የአለማችን አገራት መካከል አንዷ ነች። ነገር ግን፤ ኢኮኖሚን ለማቃወስ “የሚተጋ” መንግስት ባለበት አገር፣ መስራትና ማምረት ከባድ ነው። ከተመረተም፣ የዝርፊያና የሙስና ሲሳይ ነው የሚሆነው።
የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል በጋራ መስራት...
Cervical cancer… የማህጸን በር ካንሰር ...80% ያህል በታዳጊ አገሮች ይከሰታል
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፣የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር እና ጀርመን የሚገኘው ማርቲን ሉተር ዩኒቨርሲቲ በኢትዮጵያ የማህጸን በር ካንሰርን ለመከላከል የሚያስችል ፕሮጀክት ተግባራዊ ለማድረግ በአዲስ አበባ ስብሰባ አካሂደዋል፡፡ እንደአውሮፓውያኑ የጊዜ ቀመር 10/4/2013 ማለትም ሚያዝያ 2/2005 በኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር የስብሰባ አዳራሽ በተካሄደው ስብሰባ በጋራ አብረው ለመስራት የታሰቡት ድርጅቶች ተወካዮችና ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስርም እንግዶች ተገኝተው ነበር፡፡ ዶ/ር ተናኘ ጸጥአርጌ ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር ስብሰባውን ሲከፍቱ እንደተናገሩት በኢትዮጵያ ከስነተዋልዶ ጤና ጋር በተያያዘ ለሴቶች ሞት በምክንያትነት ከሚጠቀሱት የማህጸን በር ካንሰር ይገኝበታል፡፡
ይህ በሽታ በብዙ ሴቶች ላይ የሚከሰትና በአስከፊነቱም በቀዳሚነት የተመዘገበ ነው፡፡ ማንኛዋም የግብረስጋ ግንኙነት የምትፈጽም ሴት በበሽታው ለመጠቃት እንደምትችል መረጃዎች እንደሚጠቁሙ ዶ/ር ተናኘ ተናግረዋል፡፡ ዶ/ር ካሳሁን ኪሮስ የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስትና በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ሜዲካል ፋኩልቲ በአንድ ወቅት እንደገለጹት የማህጸን ካንሰር አይነቱ ብዙ ሲሆን በአገራችን በብዛት የሚያጠቃውና ገዳይ የሆነው የማህጸን በር ካንሰር (Human Papiloma Virus) ሒዩማን ፓፒሎማ በተባለው ቫይረስ አማካኝነት የሚከሰተው ነው፡፡ በአሁኑ ጊዜ ለማህጸን በር ካንሰር መከላከያ የሚሆኑ ሁለት አይነት ክትባቶች የተገኙ ሲሆን አንዱ Gardasil ሲሆን ሁለተኛው Cervarix የተሰኘው ነው፡፡ Gardasil K Human Papiloma Virus ለማህጸን በር ካንሰር መንስኤ ለሆነው መከላከያ ክትባት ሲሆን አራት የቫይረስ አይነቶችን ማለትም 16...18...6...እና 11 የተባሉትን የቫይረስ አይነቶች የሚከላከል ነው፡፡ በተመሳሳይም Cervarix የተባለው ክትባት 16...እና...18 የተባሉትን ቫይረሶችን ብቻ የሚከላከል የክትባት አይነት ነው፡፡ የማህጸን በር ካንሰር 70 ኀያህሉ የሚከሰተው በእነዚህ በ16 እና 18 በተባሉ የቫይረስ አይነቶች መሆኑ ተረጋግጦአል፡፡
በዓለማችን በየሁለት ደቂቃ አንድ ሴት በየሰአቱ ደግሞ ሰላሳ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ምክንያት ለህልፈት ይዳረጋሉ፡፡ በዓለም አሀዝ መሰረት በየአመቱ እስከ ግማሽ ሚሊዮን ሴቶች የማህጸን በር ካንሰር ያላቸው መሆኑን በምርመራ የሚያረጋግጡ ሲሆን ከእነዚህም እስከ ሁለት መቶ ሰባ አምስት ሺህ የሚሆኑት በዚሁ ህመም ምክንያት ሕይወታቸው ያልፋል፡፡ ዶ/ር ተናኝ ጸጥአርጌ ከኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር እንደገለጹት በብሄራዊ ደረጃ በየአመቱ ወደ 7619/ ሰባት ሺህ ስድስት መቶ አስራ ዘጠኝ ሴቶች በማህጸን በር ካንሰር ሊያዙ እንደሚችሉና ከነዚህም ወደ 6081/ ስድስት ሺህ ሰማንያ አንድ የሚሆኑት ለህልፈት እንደሚዳረጉ ይገመታል፡፡ ይህ ቁጥር የሚያሳየው ምን ያክል ታማሚዎች እንዳሉና የሞት ቁጥሩም ቀላል እንዳልሆነ ሲሆን በተያያዠነትም ለጉዳዩ የተሰጠው ትኩረት ምን ያህል እንደሆነ እንዲሁም አገልግሎቱ መስፋፋት እንዳለበትም የሚጠቁም ነው፡፡
የኢፊድሪ ጤና ጥበቃ ሚኒስር በብሕራዊ ደረጃ ወደ 118/የሚሆኑ የጤና ተቋማት የማህጸን በር ካንሰርን በሚመለከት ትኩረት ሰጥተው እንዲሰሩ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋት ላይ ነው፡፡ ስለዚህም ይህንን በሽታ ለመከላከል በቂ የሆነ የህክምና አገልግሎት መሰጠት በምእተ አመቱ የልማት ግብ ከታቀዱት መካከል የእናቶችን ሞት ለመቀነስ ይረዳል፡፡ እስከአሁን ባለው አሰራር ለ2015/ የታቀደውን የልማት ግብ ለማሳካት ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ እና ውጤት የሚያስመዘግቡ ስራዎች እየታዩ ቢሆንም አሁንም ገና ብዙ መሰራት እንዳለበት ከሚጠቁሙት እውነታዎች መ..ከል የማህጸን በር ካንሰር ይኝበታል፡፡ ይህም በብሕራዊ ደረጃ ከታቀደው የስነተዋልዶ አካላት ጤና አጠበባበቅ ጋር የሚገናኝ ነው ብለዋል ዶ/ር ተናኘ፡፡ ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የጽንስና ማህጸን ሕክምና እስፔሻሊስት በአ.አ ዩኒቨርሲቲ ሕክምና ፋክልቲ መምህር እና የኢሶግ ፕሬዝዳንት በትብብር መስራትን በሚመለከት በሰጡት ማብራሪያ .. ...እንደሚታወቀው በአብዛኛው ትኩረት የሚሰጠው አጣዳፊ ለሆኑት እና ተላላፊ በሽታዎች ቢሆንም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ይህ አዝማሚያ እየተለወጠ ሌሎች ከሰው ሰው በቀላሉ የማይተላለፉ ነገር ግን ሕይወትን አደጋ ላይ የሚጥሉ የጤና ችግሮችም ትኩረት እያገኙ በመምጣት ላይ ናቸው፡፡
ለምሳሌ..የውስጥ አካላት ሕመሞች...የደም ግፊት...የስኩዋር ሕመም የመሳሰሉት ከሰው ሰው በመተላለፍ ጉዳት የማያስከትሉ ቢሆንም ሰዎችን ግን ጤናቸውን የሚያቃውሱ በመሆኑ በአለም አቀፍ ደረጃ አትኩሮትን ያገኙ ናቸው፡፡ በዚሁ ረገድም ከስነተዋልዶ አካላት ጋር ተያይዘው የሚገኙ የተለያዩ የካንሰር አይነቶችን በሚመለከት የበለጠ ግንዛቤ የሚገኝበት የችግሩም ስፋት የሚታወቅባቸው መድረኮች እየተፈጠሩ ነው፡፡ የኢትዮጵያ የጽንስና ማህጸን ሐኪሞች ማህበር አባላት አብዛኞቹ በቀጥታ ከጽንስና ማህጸን ሕክምና ጋር የተያያዘ የህክምና አገልግሎት የሚሰጡ እንደመሆናቸው ታማሚዎችን በህክምናው አገልግሎት የመርዳት ስራ ይሰራሉ፡፡ በዚህም እንደሚታየው አብዛኞቹ የማህጸን በር ካንሰር ታማሚዎች ወደህክምናው የሚመጡት በሽታው ስር ከሰደደና ከተሰራጨ በሁዋላ በመሆኑ በቀላሉ ለማከምና ለማዳን እጅግ ፈታኝ ሁኔታዎች ይገጥማሉ፡፡ ስለዚህ ይህንን ሁኔታ ለመለወጥ ምን ማድረግ ያስፈልጋል የሚለውን ለመነጋገር የተፈጠረው የምክክር መድረክወደ ሶስት ነገሮችን ማድረግ እንደሚቻል አሳይቶአል፡፡
ግንዛቤ የማስጨበጥ ስራ መስራት ... ሴቶች በችግሩ ስር በሰደደ እና በከፋ ሁኔታ ከመጠቃታቸው በፊት ሊታከሙ በሚችሉበት የህክምና ተቋም በመሄድ ሕክምና እንዲያደርጉ ያስችላል የሚል ግምት አለ፡፡ የችግሩን ስፋትና ጥልቀት ማወቅና የዚያኑ ያህል ተመጣጣኝ የሆኑ እንቅስቃሴ ዎችን ማድረግ አስፈላጊ በመሆኑ አንዳንድ የዳሰሳ ጥናቶችን ማድረግ፣ይህም የሚሰሩ ስራዎች በትክክለኛ መረጃ ላይ የተመሰረተ ከሆነ የተጀመረውን ፣ መሰራት የሚገባውንና ከአመታት በሁወላ ሊደረስበት የሚገባውን ደረጃ ለማወቅ ይረዳል፡፡ ቅድመ ካንሰር ሁኔታውን አስቀድሞውኑም ማወቅ የሚቻልበት የህክምና አሰራሮች ስላሉ ይህንን አገልግሎት በቀላሉና በስፋት እንዴት ማዳረስ ይቻላል የሚለውን ስብሰባው ተመልክቶአል፡፡ ለዚህም ተቋሞችን በሰለጠነ የሰው ኃይል እና በተገቢው መሳሪያ ማጠናከር እና አስፈላጊው ግብአት የሚገኝበትን ሁኔታ ስብሰባው ተነጋግሮአል፡፡ የካንሰር ሕክምና እስከአሁን የሚሰጠው ውስን በሆኑ የህክምና ተቋማት በተለይም በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ሲሆን ነገር ግን የሆስፒታሉ አቅም ውስን በመሆኑ ታካሚዎች በጣም ለረጅም ጊዜ ህክምናውን ለማግኘት ወረፋ የሚጠብቁበት ሁኔታ ይታያል፡፡ ይህንን ለውጦ ተደራሽነትን ለማስፋት እንዴት ይቻላል የሚለው መልስ እንዲያገኝ ክህሎትን የማሳደግና ግብአትን የማሟላት ስራ መስራት አስፈላጊ መሆኑ ተጠቁሞአል፡፡
ይህ እቅድ ከተሳካ በሚቀጥሉት ሁለት አመታት ውስጥ ጠንካራ ስራዎችን መስራት ይቻላል ተብሎ ይታሰባል፡፡ ይህ እሳቤ እውን ከሆነ በሁዋላም የማህጸን በር ካንሰርን የመከላከል ስራ በፕሮጀክት ተይዞ የሚቀጥል ሳይሆን ከተወሰኑ የጊዜ ሂደቶች በሁዋላ እንደማንኛውም መሰረታዊ የጤና ሁኔታ ተይዞ በአገር አቀፍ ደረጃ በተሙዋላ አገልግሎቱን መስጠት ይቻላል የሚል እምነት አለ፡፡ የካንሰር ህክምና በሶስት ደረጃ ተመጣጥኖ የሚሰጥ ነው፡፡ እሱም የጨረር ፣የቀዶ ሕክምና እና በመድሀኒት የሚሰጥ በመሆኑ ከፍተኛ ወጪን የሚጠይቅ ነው፡፡ አሰጣጡም ለየትኛው ታማሚ ምን አይነት ሕክምና ያስፈልገዋል የሚለው በምርመራ አማካኝነት የሚወሰን ሲሆን ወጪው ለምርመራ የሚረዱ መሳሪያዎችን ከማሟላት አንጻር ብቻ ሳይሆን የሙያተኞች እና የሚወሰዱ መድሀኒቶችን ጭምር ያካትታል፡፡ የምርመራ መሳሪያዎችን ሁኔታ ስንመለከት ደግሞ እጅግ ዘመናዊ የሆኑ መሳሪያዎች በአለም ገበያ ላይ የሚገኙ ሲሆን በሌላ በኩል ደግሞ ዋጋቸው ተመጣጣኝ የሆነ ብዙ ሰዎችን ለመርዳት የሚያስችሉም አሉ፡፡ ስለዚህ በከፍተኛ ደረጃ የሚገኘውን የክኖሎጂ ውጤት የምንጠብቅ ከሆነ አቅምም ስለማይፈቅድ ተጠቃሚ የሚሆኑትም ውስን ተቋማት ናቸው፡፡
ዝቅተኛ ወጪ የሚያስወጡ አማራጭ የምርመራ ዘዴዎችን የምንጠቀም ከሆነ ግን አሰራሩን በስፋት እስከጤና ጣቢያ ድረስ መዘርጋት የሚያስችል ሁኔታ ይፈጠራል፡፡ በአገራችን ያለውን የእናቶች ሞት መጠን ለመቀነስ እንዲያስችል አገልግሎቱን በስፋት ማዳረስ አማራጭ የሌለው አሰራር መሆኑን አምኖ በተመጣጣኝ ዋጋ በስፋት ሊዳረስ የሚችለውን መሳሪያ እና ግብአት ወደሀገር በማስገባት የብዙ ሴቶችን ሕይወት ማትረፍ ተገቢ ነው በሚል ከስምምነት የተደረሰበት ነበር የጋራ ምክክሩ ብለዋል ዶ/ር ይርጉ ገ/ሕይወት የኢሶግ ፕሬዝዳንት፡፡ ማንኛዋም ሴት በተለይም እድሜዋ ከሰላሳ አመት በላይ ከሆነ ቢቻል በየአመቱ ባይቻል በየሶስት አመቱ አለበለዚያም በየአምስት አመቱ የቅድመ ካንሰር ምርመራ ብታደርግ ካንሰርን አስቀድሞ መከላከል ይቻላል፡፡ መጥፎ ጠረን ያለው የማህጸን ፈሳሽ ከግብረስጋ ግንኙነት በሁዋላ ወይንም ብልትን በማጽዳት ወቅት እንዲሁም ሰውነት በመንካት ወቅት ደም መፍሰስ ካሳየ ወዲያውኑ ወደሐኪም ሄዶ መፍትሔ ማግኘት ይቻላል፡፡
“የራስ አሽከር” ፊልም ነገ ይመረቃል
ሀዋስ ፋሚሊ ፊልም፤ “የራስ አሽከር” የተሰኘ አዲስ የቤተሰብ ልብ ሰቃይ ፊልም በነገው እለት በ8,፣10 እና 12 እንደሚያስመርቅ አስታወቀ፡፡ በአዲስ አበባና በግል ሲኒማ ቤቶች የሚመረቀውን የ100 ደቂቃ ፊልም የፃፈው ዘካርያስ ካሳ ነው፡፡ ሰርቶ ለማጠናቀቅ ሃያ ዘጠኝ ወራት የፈጀው ፊልም፤ ቀረፃ የተከናወነው በአዲስ አበባ፣ በደብረዘይትና በደቡብ ክልል እንደሆነ ታውቋል፡፡ በፊልሙ ላይ ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ ዝናህብዙ ፀጋዬ፣ ቶማስ ቶራ፣ ዳንኤል ሙሉነህ፣ እሱባለው ተስፋዬ፣ ትዕግስት ዋሲሁን፣ ወንድወሰን ብርሃኑ (ዶክሌ)፣ አንዱአለም ሽፈራው እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡
ጆሲ አዲስ ቶክ ሾው ሊጀምር ነው
ድምፃዊ ዮሴፍ ገብሬ (ጆሲ) አዲስ የቴሌቪዥን ቶክ ሾው ሊጀምር መሆኑን አስታወቀ፡፡ በኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ሰርቪስ (EBS) የሚጀመረው የቴሌቪዥን ቶክ ሾው Jossy in z House የሚል ርእስ ያለው ሲሆን ዝግጅቱ በፋሽን እና ስነጥበብ ላይ ያተኩራል፡፡ የነገ ሳምንት በእለተ ትንሳኤ የሚጀመረው ዝግጅት ዘወትር እሁድ ምሽት ከሁለት ሰዓት ጀምሮ ለአንድ ሰዓት የሚታይ ሲሆን ሐሙስ ከምሽቱ 4 ሰዓት ይደገማል፡፡
በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩት መፃህፍት ነገ ይመረቃሉ
በዶ/ር ግርማ ግዛው የተዘጋጁና በሥራ ፈጠራ ላይ ያተኮሩ ሁለት መፃህፍት በነገው እለት በፑሽኪን አዳራሽ ከረፋዱ 4 ሰዓት ላይ እንደሚመረቁ አዘጋጁ አስታወቁ፡፡ መፃህፍቱ፤ “ሥራ ፈጠራ፣ ጥቃቅን አነስተኛና መካከለኛ የንግድ ድርጅቶች በኢትዮጵያ ሕግ እይታ” እና “ሥራ ፈጠራ፣ ንግድ እና የንግድ ሥነምግባር” በሚሉ አርእስት የተፃፉ ናቸው፡፡
“ፔን ኢትዮጵያ” በትርጉም ሚና ዙሪያ ይወያያል
ሥነ ጽሑፍን፣ ነፃ የሀሳብ መንሸራሸርንና የንባብ ባሕልን በማጐልበት የሚንቀሳቀሰው ፔን ኢትዮጵያ፤ ሁለተኛውን የፀሐፍት ጉባዔ ዛሬ በጣሊያን የባሕል ማዕከል ሊያካሂድ ነው፡፡
የጉባኤው ጭብጥ “የትርጉም ሚና ለኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ እድገት” በሚል ሲሆን፤ ምሁራን ጥናታዊ ጽሑፎቻቸውን እንደሚያቀርቡና ውይይት እንደሚደረግባቸው ተገልጿል፡፡
በጉባኤው ላይ የፔን አባላት የሆኑ ገጣሚያን፣ ፀሐፊ ተውኔቶች፣ ልብወለድ ፀሐፊዎች፣ ጋዜጠኞችና ሌሎች የሥነ ጽሑፍና የሚዲያ ቤተሰቦች ታዳሚ ሲሆኑ የኖርዌይና የጣሊያን ፔን ፕሬዚዳንቶችን በእንግድነት ይገኛሉ፡፡