Administrator

Administrator

ሬት በትለር (ነገም ሌላ ቀን ነው)

አንድ የፖለቲካ ምርጫ ተሳታፊ፤ ሁሌ የቆሸሸና አልባሌ ልብስ ይለብሱ ነበረ ይባላል፡፡ አደባባይ ከሚገኝ አልባሌ መሸታ ቤት እየገቡ ነበር የሚዝናኑት፡፡ ይሰክራሉ፤ የፖለቲካ ክርክር ያበዛሉ፡፡ ይሟዘዛሉ፡፡ በዚህ ምክንያት ጨዋና ደግ ነው የሚባለው መራጭ ህብረተሰብ በተመራጩ ቅሬታ ይሰማዋል፡፡ ደጋፊዎቹም በጣም ይቀየሙዋቸዋል፡፡ የህዝቡን ብሶት የሰማ፤ የተመራጩን ተራ መሆን ና ወረዳ መሆን አስመልክቶ ሊያጋልጣቸው የፈለገ አንድ የተቃዋሚ ጋዜጣ አዘጋጅ ሪፖርተሩን ይጠራና፤
“ስማ እኒህን ተመራጭ በተቻለ መጠን ተከታትለህ፤ እንዴት እንደሚደነፉ፣ የሚያገኟቸውን ሰዎች እንዴት እንደሚከራከሩ፣ የሚሳደቧቸውን ስድቦች፣ ከሚያሽኮረምሟቸው ሴቶች ጋር ምን እንደሚባባሉ፤ በደምብ አዳምጠህ ስታበቃ በመጨረሻ ቃለ-መጠይቅ ታደርግላቸዋለህ፡፡ በጥንቃቄ እንድትዘግብ” ይለዋል፡፡
ጋዜጠኛው ተመራጩ ወደሚዝናኑበት መሸታ ቤት ይሄድና እንደተባለው  አግኝቶ ሲከታተላቸው ይቆያል፡፡ በመጨረሻም፤
“ጌታዬ ኢንተርቪው ላደርግዎ ነበር?” ሲል በትህትና ይጠይቃል፡፡
“ስለ ምንድነው … ቃለ …መጠይቅ … እንድሰጥህ የፈለከው?” አሉ ተመራጩ፡፡ ድምፃቸው ክፉኛ ይንተባተባል፡፡
“በአጠቃላይ ስለ ምርጫው”
“መ..ል..ካም” አሉ በተንጀባረረ ቃና፡፡
ጋዜጠኛው ቴፑን ደግኖ ቃለ-መጠይቁን አደረገና አበቃ፡፡ የቀደመውን መልሶ አዳመጠው፡፡ ወደ ፅሁፍ ለወጠው፡፡ በጣም ደነገጠ፡፡ መንተባተብ በመንተባተብ ሆኗል፡፡ ንግግሩ ቁርጥርጥ ያለና ጭራና ቀንዱ የማይያዝ ነው፡፡ በዚያ ላይ የመጨረሻው አረፍተ ነገር አስደንጋጭ ነው፡፡
“ያልመረጥሺኝ ወዮልሽ! ዋጋሽን ታገኛለሽ!” ነበር ያሉትሰ፡፡ ጋዜጠኛው ኢንተርቪውን አርትዖት እንዲያደርግለት ለአለቃው አሳየው፡፡ አለቃውም እንደዚያው ደነገጠና፤
“በል ጠዋት ወደ ቢሮዋቸው ሄደህ የሚያስተካክሉት ነገር ካለ ይዩት በላቸው” አለው፡፡
እንደታዘዘው ጋዜጠኛው ወደተመራጩ ቢሮ ሄዶ “ጌታዬ የሚያስተካክሉት ነገር ካለ አንዴ ያንብቡት?” አላቸው፡፡ ተመራጩ በዞረ-ድምር እየተጨናበሱ፤ አነበቡት፡፡ ውልግድግዱ የወጣ ፅሁፍ ሆኖ አገኙት፡፡  ለጋዜጠኛው መልሰው ወረቀቱን ሲሰጡትሱ፤ “ስማ አንተ ጋዜጠኛ! አንድ ምክር ልስጥህ! ወደፊት በምንም ዓይነት፤ ሰክረህ ቃለ-መጠይቅ አትሥራ! ካሁን በኋላ እንዲህ እያወለጋገድህ ትፅፍና ከጐንህ ታገኛታለህ!! እኛንኮ ነው የምታሳጣን!!”
*   *   *
የዛሬውን የሀገራችንን ሁኔታ ስናየው ልማት እየተካሄደ ያለበት፤ አያሌ ሹም ሽሮች፣ የተካሄዱበት… እንደ ቴሌ፣ መብራት ኃይልና ውሃ ልማት ያሉ ድርጅቶች ተዳክመውና ድክመታቸውን ለማረም ሁነኛ እንቅስቃሴ ሲያሳዩ የማይታዩበት፣ የህዝባችን የዕለት ተዕለት ኢኮኖሚ እየደቀቀ የመጣበት … ህይወት በየአቅጣጫው ዛሬም አሳሳቢ የሆነበት፤ ባለሥልጣን ትላንት ያለውን ዛሬ የሚክድበት፣ አሊያም ትላንት የካደውን ዛሬ የሚያምንበት፤… ወደድንም ጠላንም ግን ዛሬም ኤጭ አይባል የአገር ጉዳይ የምንልበት ነው! ሁላችንንም ያገባናል! ሚዲያዎች ይህንን ሁኔታ በደከመም ሆነ በከረረ መልኩ ሁሌም ሲያሳውቁ ቆይተዋል፡፡ መረጃ ያላገኘ-ህዝብ (uninformed public) በደመ-ነብስ የሚኖር ህዝብ ይሆናልና፡፡ ሀቅን መቀበል የዲሞክራሲ የበኩር ልጅ ነው፡፡
የሀገራችንን ድክመትና ጥንካሬ የሚመለከታቸው አካላት ሊያሳውቁን ይገባል፡፡ ግልፅነት አንዱ መርሀችን ነው ብለናልና የፓርቲና የፓርቲ ግጭት፣ የፓርቲና የመንግሥት አካላት አለመጣጣም፤ የበላይ መኰንንና የበላይ መኰንን አለመግባባት፤ የአለቃና የምንዝር ፍጥጫ፤ የበዝባዥና የተበዝባዥ ህዝብ መካረር፣ የኮንትራባንዲስቶች ሻጥር፣ አሻጥርና የተከላካይ አካላት ግፍጫ፣ ሹም ሽርና የመተካካት ለውጥ፤ የአይነኬ ባለሥልጣናትና የአውቆ ዝሞች ማቀርቀር፤  … ወዘተ ሳይገለፁና ሳይታሰብባቸው ውጥረትን የሚፈጥሩ፣ ችግርን የሚያባብሱ፣ ምሬትና ብሶትን የሚያቁሩ፤ ፍሬ-ጉዳዮች ናቸው፡፡ በጥንቃቄ ሊታሰብባቸው የሚገቡ ናቸው! የእኔን ከተወጣሁ ሌላው እንደ ፍጥርጥሩ ማለት፤ አገርን ከዝብርቅርቅ ቀለምና ከተበጫጨቀ ጨርቅ ተገጣጥማ የተሰፋች ያስመስላታል፡፡
የሀገራችን ሌላው አሳሳቢ ችግር የሥራ-መቀዛቀዝ መንፈስ ነው፡፡ ዛሬም ለምን መባል አለበት፡፡ ጥቅሙ ለማን እንደሆነ የማይታወቅ ሥራ-ቀልባሽ ሂደት ነው፡፡ ያም ሆኖ የብዙ ውስጥ-ውስጡን የበሰሉና ያረሩ ምሬቶች ጥርቅም ይመስላል፡፡ የሰው-ጤፉነትና የበላይነት ስሜት (Superiority complex)ም ሆነ፣ የበታችነትና ራስን ዝቅ-አድርጐ የመመልከት አስተሳሰብ (Infiriority complex) ስሜት፤ የዴሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ የትምክህተኝነትም (Chauvenism) ሆነ፣ የጠባብ አመለካከት (Narrow Nationalist) ፈርጆች፤ የዲሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ ያለመቻቻል (Tolerance)፣ ወገንተኛነትና ተዓብዮ የዲሞክራሲያዊ አመለካከት አካላት አይደሉም፡፡ እነዚህን ሁሉ መርምሮ “ዴሞክራሲያዊ ነኝ ወይ?” ብሎ ሁሉም ራሱን በጊዜ መፈተሹ የቀኑ ጥያቄ ነው፡፡
ከቶውኑም የውጪ ባላንጣን (external enemy) አሸንፈናል ብሎ መኩራራት፤ የውስጥ ባላንጣ (internal enemy) መፈልፈያውን ጊዜ (incubation time) እንደሚወልድ በቅጡ ማስተዋል ይገባል፡፡ የማንኛውም ሥርዓት የለውጥ ዕድገት ወይ ዝገት እንደሁኔታው የሚያጐነቁላቸው አያሌ እንግዳ-ብቃዮች ይኖራሉ፡፡ በታሪክ የታየ፣ ያለ፣ የነበረ ነው፡፡
ጉልሁንና ዋናውን ስዕል (the bigger picture) በቅጥ በቅጡ ማየቱ አግባብ የመሆኑን ያህል፤ ጥቃቅኖቹንና አንጓ ካንጓ ማያያዣዎቹን (Political ligaments) አበክሮ ማስተዋል ትልቅ ብልህነት ነው፡፡ የተጀመረው ልማት ይህን ያገናዘበ መሆን አለበት፡፡
Even lies mature ይባላል (ውሸትም እንኳን ይበስላል እንደማለት ነው፡፡) ስልክ ስንተክል፣ ኔትዎርክ ስናሰራጭ፤ መብራት ስንዘረጋ፣ ውሃ ስናስገባ፣ አጥንተንና አቅማችንን ለክተን መሆን አለበት፡፡ የልማት ስትራቴጂ ስንቀይስም አጥንተንና አቅማችንን ለክተን መሆን አለበት፡፡ አለበለዚያ “ቀድሞ ነበር እንጂ መጥኖ መደቆስ
አሁን ምን ያደርጋል ድስት ጥዶ ማልቀስ!” የሚለው ግጥም ይመጣል፡፡ በመሠረቱ ልማትን በጐ በጐውን ማየትና መኩራራት ብቻ ሳይሆን ውስጡ ያለውስ ምሥጥና ግንደ-ቆርቁር ምን ይመስላል? ብሎ፣ ይሆነኝ ብሎ ዐይንን ገልጦ ማየት የአባት ነው፡፡ እሸት እሸቱን እያየን ነቀዙን ካላስተዋልን፣ ምርቱን አይተን የግርዱን ብዛት ካላመዛዘንን፤ ሁሌ “ጉሮ-ወሸባዬ” እያልን፤ ውስጥ-ውስጡን መሽመድመዳችን አይቀሬ ይሆናል፡፡ ነገ ስለ ምርጫ ስናወራም ለህዝቡ ዕውነተኛ ገፅታችንን ማሳየት አለብን፡፡ ከልማቱ ተጠቃሚው፤ ህዝብ መሆን አለበት፤ እንጂ ከላይ ከላዩ ቦጥቧጩ መሆን የለበትም፡፡ ማርጋሬት ሚሼል “ነገም ሌላ ቀን ነው” በሚባለው መፅሀፏ ውስጥ የገለፀችው፣ ሬት በትለር የተባለው በጦርነቱ ጥቅም ያጋብስ የነበረ ነጋዴ፤ “አገር ስትለማ ቀስ በቀስ ሀብታም መሆን ይቻላል፡፡ አገር ስትጠፋ ግን በአንድ አፍታ መበልፀግ ይቻላል” የሚለን ለዚህ ነው!!

ከሳምንት በኋላ በፖላንዷ ከተማ ስፖት በሚካሄደው 11ኛው የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮና የሚሳተፈውን የኢትዮጵያ ቡድን ገንዘቤ ዲባባ እና መሃመድ አማን እንደሚመሩት ታወቀ፡፡ በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮናው በወንዶች 800 ሜ፣ 1500 ሜ እና 3000 ሜ እንዲሁም በሴቶች  1500 ሜ እና 3000 ሜ ውድድሮች ኢትዮጵያ 11 አትሌቶችን ታሳትፋለች፡፡ አትሌት ገንዘቤ ዲባባና አትሌት መሃመድ አማን በዓለም በቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ለወርቅ ሜዳልያ ድሎች ከፍተኛ ግምት የተሰጣቸው ሲሆን አዳዲስ ሪከርዶችን እንደሚያስመዘግቡ ተጠብቀዋል፡፡ ገንዘቤ ዲባባ በዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ2 ዓመት በፊት በ1500 ሜ ያገኘችውን የወርቅ ሜዳልያ ክብር የምታስጠብቅበት ወቅታዊ ብቃት ቢኖራትም በ3ሺ ሜ ተሳታፊ ለመሆን እንደወሰነች ያመለከተው የአለም አቀፉ የአትሌቲክስ ፌደሬሽኖች ማህበር ዘገባ፤ ሁለት ወር ባልሞላ ጊዜ ውስጥ የርቀቱን የዓለም ሪከርድ ለሁለተኛ ጊዜ በመስበር የወርቅ ሜዳልያውን ልትወስድ እንደምትችል ግምት ሰጥቷታል፡፡ ባለፈው 1 ወር ጊዜ ውስጥ በ1500ሜና በ3ሺ ሜትር የቤት ውስጥ ውድድሮች እንዲሁም በ2 ማይል ሩጫ ሶስት የዓለም ሪከርዶችን የጨበጠችው ገንዘቤ በስዊድን ስቶክ ሆልም የ3ሺ ሜትር የዓለም ሪከርድን 8 ደቂቃ ከ16.60 ሰኮንዶች በሆነ ጊዜ ማስመዝገቧ ይታወሳል፡፡ በሌላ በኩል በ800 ሜትር በትራክ እና በቤት ውስጥ የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናዎች የወቅቱ ኮከብ  አትሌት የሆነው መሃመድ አማን በርቀቱ የወርቅ ሜዳልያ ክብሩን ለማስጠበቅ እንደሚወዳደር ተገልጿል፡፡  መሃመድ አማን በ800 ሜትር ዘንድሮ ያስመዘገበው 1 ደቂቃ ከ44.52 ሴኮንዶች የሆነ ጊዜ የአፍሪካ ሪኮርድ እንደሆነ ያመለከተው የአይኤኤኤፍ ዘገባ ምናልባትም የርቀቱን የዓለም ሪከርድ ሊያስመዘግብ እንደሚችል ጠቁሟል፡፡ የዓለም የቤት ውስጥ የአትሌቲክስ ሻምፒዮናው ከ2 ዓመት በፊት በቱርክ ኢስታንቡል በተካሄደ ጊዜ በ1500 ሜትር የነሐስ ሜዳልያ ያገኘው መኮንን ገብረመድህንና ዘንድሮ በ3ሺ ሜትር  ውጤታማነት አንደኛ ደረጃ የተሰጠው  ሃጎስ ገብረህይወት ለወርቅ ሜዳልያ የተጠበቁ ሌሎቹ የኢትዮጵያ አትሌቶች ናቸው፡፡ በተጨማሪም በወንዶች ምድብ አማን ዎቴ በ1500ሜትር፤ የኔው አላምረው እና ደጀን ገብረመስቀል በ3ሺ ሜትር እንደሚሳተፉ ሲገለጽ፤ በሴቶች ምድብ ደግሞ በ1500 ሜትር አክሱማይትና ኤምባዬ ጉዳይ ፀጋዬ እንዲሁም በ3ሺ ሜትር አልማዝ አያና ህይወት አያሌው ይወዳደራሉ፡፡ በሻምፒዮናው ከ1 እስከ 6 ደረጃ ለሚያገኙ አትሌቶች የገንዘብ ሽልማት የሚሰጥ ለ1ኛ 40ሺ ዶላር፤ ለ2ኛ 20ሺ ዶላር እንዲሁም ለ3ኛ 10ሺ ዶላር ይሰጣል፡፡ ለአዲስ የዓለም ክብረወሰን ደግሞ  50ሺ ዶላር ቦነስ እንደሚበረከት ታውቋል፡፡
በዓለም የቤት ውስጥ አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተሳትፎ ታሪክ ኢትዮጵያ 19 የወርቅ፤ 5 የብርና 11 የነሐስ በድምሩ 35 ሜዳልያዎችን  በመሰብሰብ ከዓለም አገራት አራተኛ ደረጃ ይዛለች፡፡ በሻምፒዮናው ታሪክ ከምንግዜም ውጤታማ አትሌቶች ተርታ  የሚጠቀሱት  ደግሞ ኃይሌ ገብረስላሴ እና መሰረት ደፋር ናቸው፡፡ ታላቁ አትሌት ሃይሌ ገብረስላሴ በ3ሺ ሜትር 3 የወርቅ ሜዳልያዎችን እንዲሁም በ1500 1 የወርቅ ሜዳልያ ያስመዘገበ ሲሆን በ1997 የ3ሺ ሜትርን ሪከርድ 7 ደቂቃ ከ34.71 ሴኮንዶች እንዲሁም በ1999 እኤአ የ1500ሜ ሪከርድን በ3 ደቂቃ ከ33.77 ሰኮንዶች እንደያዘ ነው፡፡ አትሌት መሰረት ደፋር በበኩሏ በ3ሺ ሜትር 4 የወርቅ፤ 1 የብር እና 1 የነሐስ ሜዳልያዎችን በመሰብሰባቸው ነው፡፡


የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ ቅጥር ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን  ፈታኝ  እንደሆነበት የተለያዩ ሁኔታዎች ያመለክታሉ፡፡ ፌደሬሽኑ ለሁለት ዓመት በዋና አሰልጣኝነት የመሩትን ሰውነት ቢሻው፤ ምክትላቸውንና የግብ ጠባቂዎችን አሰልጣኝ ካሰናበተ በኋላ ብሄራዊ ቡድኑ ያለ አሰልጣኝ አንድ ወር ሆኖታል፡፡ ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር የሚያስፈልጉ ዝርዝር መስፈርቶቹን የቴክኒክና ልማት ኮሚቴ ለፌደሬሽኑ ካሳወቀ በኋላ ክፍት የስራ ቦታ ማስታወቂያው ሰሞኑን ወጥቷል፡፡
ማስታወቂያ
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት አመልካቾችን አወዳድሮ ለመቅጠር ያስቀመጣቸው መስፈርቶች ሃላፊነቱ በከፍተኛ ጫና ውስጥ መውደቁን ያመለክታሉ፡፡ የእግር ኳስ ፌዴሬሽኑ መስፈርቱን የሚያሟሉ አመልካቾች ማስረጃቸውን ፅህፈት ቤት በግንባር ተገኝተው በማቅረብ መመዝገብ እንደሚችሉ ቢያስታውቅም መቼ የቅጥር ሂደቱ እንደሚፈፀም የሰጠው ፍንጭ የለም፡፡ ፌደሬሽኑ ለቅጥሩ ባወጣው ማስታወቂያ ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት  ብቁ የሚሆን ተወዳዳሪ ከታወቀ የትምህርት ተቋም ዲኘሎማ ያገኘና ተመጣጣኝ ወይም ከዛ በላይ የትምህርት ደረጃ ያለው፣ በእግር ኳስ አሰልጣኝነት ከፍተኛ ዓለም አቀፍ ደረጃ ያለው የምስክር ወረቀት ማቅረብ የሚችል፣ በእግር ኳስ የማሰልጠን የCAF “B” ወይም ከዛ በላይ ፈቃድ ላይሰንስ (License) ያለው፣ በብሔራዊ ቡድኖች ወይም በከፍተኛ ሊግ ውድድሮች ደረጃ ከፍተኛ ውጤት ያስመዘገበ፣ ዕድሜው ከ35 በላይ መሆን እንዳለበት አመልክቷል፡፡ የእንግሊዝኛ ቋንቋ መናገር ማንበብና መፃፍ የሚችል፣ በኮምፒዩተር ችሎታ እውቀት ያለው፣ ብሔራዊ ቡድኑን የማስተባበርና የመምራት ችሎታ ያለው፣ከፍተኛ ጫና ባለበት ተቋቁሞ መስራት የሚችልና ፈጣን ውሳኔ የመወሰን ችሎታ ደግሞ ለዋና አሰልጣኝነት የሚወዳደረው አመልካች የሚያስፈልገው ችሎታ እንደሆነም ዘርዝሯል፡፡ ፌደሬሽኑ ለክፍት የስራ ቦታው በጠየቀው የሥራ ልምድ ከ1ዐ ዓመት በላይ በብሔራዊ ቡድኖች ወይም ከፍተኛ ሊጐች ደረጃ በዋና አሰልጣኝነት የሰራ ያሠለጠነ በዓለም አቀፍ ደረጃ የማሰልጠን ልምድ ያለውን እንደሚያበረታታ ገልፆ፤ የቅጥር ሁኔታው     በኮንትራት ሆኖ በሚያስመዘግበው ውጤት እንደ አስፈላጊነቱ ሊራዘም እንደሚችል አስታውቋል፡፡ የሚቀጠረውን አሰልጣኝ ተግባርና ኃላፊነትን በመዘርዘር ካስቀመጣቸው መስፈርቶች መካከል   የአጭር፣ የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የስልጠና ዕቅድ መሠረት ያደረገ ዝግጅትና ተግባር የሚያከናውን፤ ብሔራዊ ቡድኑን በማንኛውም ደረጃ ለሚደረጉ ውድድሮች በብቃት የሚያዘጋጅ፤ ብሔራዊ ቡድኑ ለሚያደርጋቸው ጨዋታዎች፣ ውድድሮች በተመለከተ ከጨዋታ በፊት እቅድና ከጨዋታ በኋላ የአፈፃፀም ሪፖርት በወቅቱ በኃላፊነት የሚያቀርብ ፣ የሩብ፣ የግማሽና የዓመት የዝግጅት አፈጻጸም ዕቅድ የሚያቀርብ፤ ከብሔራዊ ቴክኒክና ልማት ኮሚቴ እና ከዲፖርትመንት ጋር ብሔራዊ ቡድኑ ውጤታማ በሚሆንባቸው ሁኔታዎች ላይ ተባብሮ የሚሰራ፤ የእግር ኳስ አሰልጣኞች ስልጠና እንዲሰጥ በሚጠየቅበት ጊዜ የሚሰጥ፤ ከኘሪሚየር ሊግ እና ከብሔራዊ ሊግ ክለብ አሰልጣኞች ጋር ተቀራርቦ የሚሰራ፤ የሚያሰለጥናቸውን የእያንዳንዱን ብሔራዊ ቡድን ተጫዋቾች የቀድሞ የእግር ኳስ ኘሮፋይል የሚያሰባስብና የሚያደራጅ ፤በአገሪቱ እግር ኳስ ላይ የእግር ኳስ ኘሮፊሽናሊዝም እንዲበረታታ እንዲስፋፋ የሚያደርግና የኢትዮጵያ ወጣት U-17፤ U-20 እና የኦሎምፒክ ቡድንን የሚያግዝ መሆን እንዳለበት አስቀምጧል፡፡
ፈታኞቹ ሁኔታዎች
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝ  ቅጥርን በቶሎ እና በስኬታማ ሂደት ለማከናወን የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ፈተና ያከበዱት በርካታ ሁኔታዎች ናቸው፡፡  የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ዋና ብሄራዊ ቡድኑ ያለ ዋና አሰልጣኝ  ወር እንዲያልፍ ከማድረጉ በተያያዘ በፊፋ የወዳጅነት ጨዋታ ፕሮግራም ተገቢውን ዝግጅት እንዳየደርግ ምክንያት ሆኗል፡፡ በሌላ በኩል ፌደሬሽኑ እያዘጋጀ ያለው ስትራቴጂክ እቅድ ገና በይፋ ካለመፅደቁ ጋር በተያያዘ  የአዲስ አሰልጣኝ ቅጥሩን ለማከናወን ግራ መጋባቱም አልቀረም፡፡ አንዳንድ የመረጃ ምንጮች የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ ክፍቱን የስራ ቦታ በጊዜያዊ ሹመት ሰጥቶ ደረጃውን የጠበቀ ምርጥ አሰልጣኝ ለመቅጠር በቂ ጊዜ መድቦ ለመስራት ፍላጎት እንዳለውም እያመለከቱ ናቸው፡፡
ለብሄራዊ ቡድኑ ዋና አሰልጣኝነት የሚበቃ ኢትዮጵያዊ አሰልጣኝ ለማግኘት በአገር ውስጥ እየሰሩ ካሉ ባለሙያዎች የጎላ ወቅታዊ ብቃት እና ተገቢ ልምድ ያለው አሰልጣኝ ለማግኘት ያለው እድል መጥበቡም ሌላው ፈተና ነው፡፡ በተያያዘም ለብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ኢትዮጵያዊ ወይንስ  የውጭ ዜጋ የቱ ይሻላል በሚለው አጀንዳ በስፖርት ቤተሰቡ መካከል የተቀሰቀሰው ውዝግብ የቅጥሩን ሂደት አጓጊ እና አስጨናቂ አድርጎታል፡፡ ፌደሬሽኑ በጊዜያዊነት ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር ብቻ ትኩረት መስጠቱም ብሄራዊ ቡድኑ ዓለም አቀፍ ተፎካካሪነት እንዲኖረው ለማስቻል ሙሉ አቅም ያለው ስታፍ ማስፈለጉን አለማስተዋሉም ያሳስባል፡፡ እንደ ጋና አይነት ብሄራዊ ቡድኖች ከዋና አሰልጣኙ ጋር የሚሰሩ ከ13 በላይ የተለያዩ ባለሙያዎች ቀጥረዋል፡፡ በጋና ብሄራዊ ቡድን ከዋና አሰልጣኙ ሌላ አንድ ምክትል አሰልጣኝ፤ ሁለት የግብ ጠባቂ አሰልጣኞች፤ የቴክኒክና የተጨዋቾች ምርጫ የሚመለከታቸው ሃላፊዎች፤ የስነልቦና የምግብ እና የፊዚዮ ቴራፒ አገልገሎት የሚሰጡ ባለሙያዎች፤ የብሄራዊ ቡድኑ ቃል አቀባይ፤ የትጥቅ ሃላፊ፤ ልብስ ሰፊ፤ ከበሮ መቺ ተጠቃሽ የሃላፊነት ስፍራዎች ናቸው፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌሬሽን ከዋና አሰልጣኙ ቅጥር ባሻገር ለሌሎች የአሰልጣኝ ድጋፍ ሰጪ ባለሙያዎች ቅጥር ስላለው ፍላጎት የሚታወቅ ነገር የለም፡፡ ወይም የታሰበበት አይመስልም፡፡
ሌላው ፈተና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በሚያከናውነው ቅጥር የውጭ ዜጋ  ከመረጠ በወቅታዊው የገበያ ሁኔታ  የሚያስፈልገው የደሞዝ ክፍያ ከፍተኛነት ሲሆን ይህንንም ለማሳካት የፋይናንስ ምንጩ ከየት እንደሚገኝ በግልፅ አለመታወቁ ናቸው፡፡ የእግር ኳስ ፌደሬሽን ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር የሚከፍለውን ደሞዝ በስምምነት ለማድረግ ይፈልጋል፡፡ በኢትዮጵያ እግር ኳስ በአሰልጣኝነት ከፍተኛው ተካፋይ የነበሩት ሰውነት ቢሻው ይከፈላቸው የነበረው ወርሃዊ ደሞዝ 50 ሺብር በዶላር ሲመነዘር ከ3ሺ ያንሳል ፡፡ ሰውነት ቢሻው ኢትዮጵያዊ በመሆናቸው ክፍያው ተመጣጣኝ ሊሆን በቅቷል፡፡ ይሁንና አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት በአሁኑ ጊዜ በአፍሪካ ደረጃ የሚሰሩ ዋና አሰልጣኞች ለየአገሮቹ ዜጋ በወር እስከ 11ሺ ዩሮ የውጭ አገር ዜጋ ከሆኑ ደግሞ እስከ 110ሺ ዩሮ መተመኑ የገበያውን ውድነት ያሳያል፡፡ የግብፅ ብሄራዊቡድን አሰልጣኝ የነበሩት አሜሪካዊ ቦብ ብራድሌይ በወር 35ሺ ዶላር፤ የምዕራብ አፍሪካ ቡድኖችን ያሰለጠኑት ፈረንሳዊ ሄነሪ ሚሸል 50ሺ ዶላር፤  ስዊድናዊ ሰኤሪክሰን አይቬሪኮስትን ሲያሰለጥኑ እስከ 175ሺ ዶላር፤ የካሜሮን አሰልጣኝ የነበሩት ፖል ሌግዌን 80ሺ ዶላር በላይ የሚከፈላቸው ነበሩ፡፡ በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ ሆነው የሰሩት ጋርዚያቶ እስከ10ሺ ዶላር ከዚያም በኋላ የሰሩት ኢፌም ኦኑራ 13ሺ ዶላር ይከፈላቸው እንደነበር ይታወሳል፡፡ ቶም ሴንት ፌይት ደሞዝ ባይከፈላቸውም ሺ ዶላር ተከፍሏቸው ለመስራት ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን በናይጄርያ የቴክኒክ አማካሪነት 20ሺ ዶላር በወር ያገኙ ነበር፡፡ሚቾ በሩዋንዳ  ብሄራዊ ቡድን ዋና አሰልጣኝነት ሲሰሩ 16ሺ በኡጋንዳ ደግሞ 25ሺ ዶላር እየታሰበላቸው ነው፡፡ከላይ ከተዘረዘሩት የውጭ ዜጋ አሰልጣኞች መካከል እና አስቀድመው በኢትዮጵያ የሰሩ ባለሙያዎችን ወቅታዊ ዋጋ በመመዘን  ፌደሬሽኑ ለዋና አሰልጣኙ ቅጥር ወርሃዊ ክፍያ እስከ 30ሺ ዶላር ሊያስፈልገው እንደሚችል ይገመታል፡፡
ኢትዮጵያዊ ወይንስ  የውጭ ዜጋ?
ለዋና ብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝነት ኢትዮጵያ ውስጥ ከሚገኙ አሰልጣኞች በይፋ ፍላጎቱን የገለፀ እና ያመለከተ ባለሙያ ስለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም፡፡ ይሁንና ባለፉት ሁለት ሳምንታት ከተለያዩ የአውሮፓ አህገራት እና በአፍሪካ ውስጥ ታላላቅ ቡድኖችን ያሰለጠኑ 10 ትልልቅ አሰልጣኞች ብሄራዊ ቡድኑን ለመያዝ ያላቸውን ፍላጎት ለፌደሬሽኑ እንዳስታወቁ ከሁለት ሳምንት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነዲን ባሻህን በማነጋገር በሱፕርስፖርት በተሰራ ዘገባ ተገልጿል፡፡ ይሁንና የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ በሚያከናውነው ቅጥር የውጭ ዜጋ  ከመረጠ በወቅታዊው የገበያ ሁኔታ  የሚያስፈልገው የደሞዝ ክፍያ ከፍተኛነትና ለማሳካት የፋይናንስ ምንጩ ከየት እንደሚገኝ ግልፅ አልሆነም፡፡  ከአገር ውስጥ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ለመረከብ በይፋ ፍላጎታቸውን የገለፁ ባይኖሩም ቀድሞ ዋናውን ብሄራዊ ቡድን ያሰለጠኑት እና የሴቶች ብሄራዊ ቡድንን ያሰለጠኑት ኢንስትራክተር አብርሃም ተክለሃይማኖት ለሃላፊነቱ የታጩበትን ሁኔታ ሳይቀበሉት መቅረታቸው ተነግሯል፡፡ ከዚያ ባሻገር ከኢትዮጵያ ቡና ጋር የፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን የበቃው እና አሁን በሱዳኑ ክለብ አልሃሊ ሼንዲ  የሚሰራው ውበቱ አባተ ፤ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ክለብ አሰልጣኝ የሆነው ፀጋዬ ኪዳነ ማርያም፤ የመከላከያ ክለብ አሰልጣኝ የሆነው ገብረመድህን ሃይሌ እንዲሁም የቀድሞው የብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አስራት ሃይሌ ለሃላፊነቱ ብቁ ስለመሆናቸው ተባራሪ ወሬዎች  ያመለክታሉ፡፡  ከውጭ ዜጎች መካከል ደግሞ ቤልጅማዊው የቀድሞው የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የነበሩት ቶም ሴንትፌይት ወደ ሃላፊነቱ ለመመለስ ያላቸውን ፍላጎት ለሱፕር ስፖርት ሲገልፁ፤ በአሁኑ ጊዜ የኡጋንዳ ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ የሆኑት ሰርቢያዊው ሰርዴጆቪች ሚሉቲን ደግሞ ለአሰልጣኙ ቅጥር የሚጠቅሙ ምክሮችን በመለገስ፤ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን ማሰልጠን ታላቅ ክብር መሆኑን  ከ2 ሳምንት በፊት ከስፖርት አድማስ ጋር ባደረጉት ቃለምምልስ መግለፃቸው አይዘነጋም፡፡  በኡጋንዳ ብሄራዊ በድን ዋና አሰልጣኝነት ኮንትራት ያላቸው ሰርዴጆቪች ሚሉቲን ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የቅጥር  ማመልከቻ ማስገባታቸው አይጠበቅም፡፡ በአንፃሩ ቤልጅማዊው ቶም ሴይንትፌይት የእግር ኳስ ፌደሬሽኑ የቅጥር ማስታወቂያውን ካወጣ በኋላ ለፌደሬሽኑ  ማመልከቻ ሊያስገቡ እንደሚችሉ ይገመታል፡፡ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድንን በዋና አሰልጣኝነት ለመምራት ፍላጎታቸውን በተለያየ መንገድ አሳውቀዋል ከተባሉ 10 የውጭ አገር ባለሙያዎች መካከል በይፋ  ለሃላፊነቱ ለኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የስራ ማመልከቻ ማስገባታቸው እንደማይቀር የተወራላቸው በስፔን ላ ሊጋ በሚወዳደሩ ክለቦች በተጨዋችነት  እና  በአሰልጣኝነትየ25 አመት ከፍተኛ የስራ ልምድ  ያካበቱት የ57 ዓመቱ አንቶኒዮ ሎፔዝ  ናቸው፡፡ እንደሆኑ ሱፕር ስፖርት የገለፀው ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር፡፡  ስፔናዊው አንቶኒዮ ሎፔዝ በስፔን ላ ሊጋ ውስጥ አትሌቲኮ ማድሪድ፣ሲቪላ ጨምሮ በተለያዮ ክለቦች በተጨዋችነት ያሳለፉ እና ሴልታ ቪጎን እና ቫሌንሲያን በማሰልጠን ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ ፤በደቡብ አፍሪካ ሁለት ክለቦችን ያሰለጠኑና በፊት የቦሊቪያን ብሔራዊ ቡድን ሁለት ጊዜ የኮፓ አሜሪካ ውድድር ተሳታፊ እንዲሆን ያስቻሉ ናቸው፡፡

የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ በዓለም 107ኛ፤ በአፍሪካ 17ኛ፤ በምስራቅ አፍሪካ 2ኛ ነው


16 ክለቦች በሚሳተፉበት የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮንስ ሊግ ዛሬ እና ነገ በአንደኛ ዙር ማጣርያ የመጀመርያ ጨዋታዎች በመላው አህጉሪቱ ሲካሄዱ የምስራቅ አፍሪካዎቹ ከተሞች አዲስ አበባ፤ ዳሬሰላም እና ናይሮቢ ትልልቅ ግጥሚያዎችን  ያስተናግዳሉ፡፡ የአምናው የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮን ደደቢት በነገው እለት የቱኒዚያውን ክለብ ሲኤስ ሴፋክሴዬን በአዲስ አበባ ስታድዬም የሚፋለም ይሆናል፡፡ የቱኒዚያው ክለብ ሲኤስ ሴፋክሴዬን ከሳምንት በፊት በአፍሪካ ክለቦች ሱፕር ካፕ በግብፁ ክለብ አልሃሊ 3ለ2 ተሸንፎ ዋንጫ አምልጦታል፡፡ ባለፈው የውድድር ዘመን የአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ዋንጫን ያሸነፈው ሲኤስ ሴፋክሲዬን በሱፕር ካፑ የደረሰበትን ሽንፈት በነገው የአዲስ አበባ ጨዋታ ለማካካስ ትኩረት ማድረጉን የቱኒዚያ ጋዜጦች ዘግበዋል፡፡ ደደቢት በአፍሪካ ደረጃ  ብዙም ልምድ ባይኖረውም በደጋፊው ፊት ከባድ ተፎካካሪ ሆኖ በመጫወት በከፍተኛ የግብ ልዩነት ለማሸነፍ ከቻለ የማለፍ እድሉን ሊያሰፋ ይችላል፡፡ በሌሎች የአፍሪካ ሻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታዎች በዛሬው እለት ናይሮቢ ላይ የኬንያው ክለብ ጎሮማሃያ ለሁለት ጊዜያት የሻምፒዮንስ ሊግ ዋንጫዎችን ያሸነፈውን የቱኒዚያውን ኤስፔራንስ ሲገጥም፤ ዳሬሰላም ላይ ደግሞ የታንዛኒያው ክለብ ያንግ አፍሪካንስ የአምናው የሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊ ከነበረውና ከሳምንት በፊት የሱፕርካፕ ዋንጫ ያገኘውን የግብፁን ክለብ አልሃሊን ያስተናግዳል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ከተመሰረተ ከ70 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው የኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር ፕሪሚዬር ሊግ  ባለፈው የውድድር ዘመን በፉክክር ደረጃው  ከዓለም 107ኛ፤ ከአፍሪካ 17ኛ እንዲሁም ከምስራቅ አፍሪካ 2ኛ ማግኘቱን የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS) አመለከተ፡፡ ተቀማጭነቱን በስዊዘርላንዷ ከተማ ሉዛን ውስጥ ያደረገው የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS)  ለዓለም የእግር ኳስ ሊጎች ደረጃ የሚያወጣው በአገር ውስጥ የሊግ እና የጥሎ ማለፍ ውድድሮች በመመዘን፤ በአህጉራዊ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የየአገሩ ክለቦች ያላቸውን ፉክክር  ደረጃ እና ውጤት በማስላት ነው፡፡ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከዓለም የክለብ ውድድሮች 107ኛ ደረጃን  ያገኘው 157 ነጥብ በማስመዝገብ ነው፡፡ በምስራቅ አፍሪካ በክለቦቿ የሊግ ውድድር አንደኛ የሆነችው 230 ነጥብ በማስመዝገብ ከዓለም 91ኛ ደረጃ የወሰደችው ሱዳን ስትሆን፤ የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ከያዘው ሁለተኛ ደረጃ በመቀጠል፤ የኬንያ ፕሪሚዬር ሊግ  በ123 ነጥብ ከዓለም 114ኛ፤ የታንዛኒያ  ፕሪሚዬር ሊግ በ114.5 ነጥብ ከዓለም 118ኛ፤ የብሩንዲ ፕሪሚዬር ሊግ በ114 ነጥብ ከዓለም 119ኛ፤ የኡጋንዳ ፕሪሚዬር ሊግ በ114 ነጥብ ከዓለም 120ኛ እንዲሁም የሩዋንዳ ፕሪሚዬር ሊግ በ108 ነጥብ ከዓለም 125ኛ ደረጃ በማግኘት ተከታታይ ደረጃ አላቸው፡፡ የእግር ኳስ ስታትስቲክስ እና ታሪክ ዓለም አቀፍ ፌደሬሽን (IFFHS)  የዓለም አንደኛ ምርጥ ሊግ ብሎ የሰየመው 1155 ነጥብ ያስመዘገበውን የስፔኑ ፕሪሚዬራ ሊጋ ሲሆን፤ የእንግሊዝ ፕሪሚዬር ሊግ በ1128 ነጥብ፤ የጀርመን ቦንደስ ሊጋ በ1058 ነጥብ፤ የጣሊያን ሴሪ ኤ በ927 ነጥብ፤ የብራዚል ሴሪኤ በ896 ነጥብ፤ የአርጀንቲና ፕሪሚዬራ ዲቪዥን በ868 ነጥብ፤ የፈረንሳይ ሊግ 1 በ796 ነጥብ፤ የሩስያ ፕሪሚዬር ሊግ በ739.5 ነጥብ፤ የኮሎምቢያ ፕሪሚዬር ሊግ በ724.5 ነጥብ እንዲሁም የሮማንያ ፕሪሚዬር ሊግ በ722.5 ነጥብ ከ2 እስከ 10 ያለውን ደረጃ አግኝተዋል፡፡ በአፍሪካ በምርጥ የፉክክር ደረጃው አንደኛ የተባለው 469.5 ነጥብ በማስመዝገብ በዓለም 31ኛ ደረጃ የወሰደው የቱኒዚያ ሊግ ነው፡፡  ግብፅ በ361.5 ነጥብ ከዓለም 46ኛ፤ ሞሮኮ በ361 ነጥብ ከዓለም 47ኛ፤ ናይጄርያ በ332.5 ነጥብ ከዓለም 53ኛ፤ ማሊ በ322 ነጥብ ነጥብ ከዓለም 56ኛ፤ ደቡብ አፍሪካ በ316.5 በዓለም 61ኛ፤ አልጄርያ በ315.5 ነጥብ ከዓለም 62ኛ፤ አንጎላ በ314.5 ነጥብ ከዓለም 64ኛ እንዲሁም ካሜሮን በ295 ነጥብ ከዓለም 70ኛ በመመዝገብ በአፍሪካ ምርጥ ሊጎች የደረጃ ሰንጠረዥ ከ2 እስከ 10 ተከታትለው ተቀምጠዋል፡፡ ጋና፤ ኮትዲቯር፤ ኮንጎ ዲ ሪፖብሊክ፤ ሱዳን፤ ዛምቢያ፤ ዚምባቡዌ፤ ኮንጎ ኪንሻሳ፤ ኢትዮጵያ፤ በርኪናፋሶ፤ ቦትስዋና እና ኬንያ ከ11 እስከ 20 ደረጃ ያገኙ የአፍሪካ ሊጎች ሆነዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን ያዘጋጀው የኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድር ነገ በቃሊቲና አቃቂ አካባቢ ገላን ገበሬ ማህበር ክልል ውስጥ እንደሚካሄድ ታወቀ ፡፡ የሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ የበላይ ጠባቂ የሆኑት የተከበሩ አቶ አባዱላ ገመዳ ውድድሮቹን በስፍራው ተገኝተው እንዲያስጀምሩ ጥሪ ተደርጎላቸዋል፡፡ ኢንዱራሊ   በ2006 ዓ.ም ለማካሄድ በዕቅድ ከያዛቸው ውድድሮች መካከል አንዱ መሆኑን የገለፁት የአሶሴሽኑ ፕሬዝዳንት አቶ ኤርምያስ አየለ  በቀጣይ ወራት ሁለት የከተማ እና አንድ የከተማ ውጭ ውድድሮችን እንደሚዘጋጁም ተናግረዋል፡፡
በኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድር ላይ 15 መኪናዎችና 27 ሞተርብስክሌቶች እንደሚካፈሉ የሚጠበቅ ሲሆን ከተወዳዳሪዎቹ መካከል 4 ኢትዮጵያዊያን፤ 9 የጣልያናውን፤ 1 ጅቢቲያዊና 1 ህንዳዊ ይገኙበታል፡፡
የመኪናው ውድድር በአራት ምድብ ተከፍሎ እንደሚካሄድ ያመለከተው የሞተር ስፖርት አሶሴሽኑ መግለጫ ባለ 2000 ሲሲ ቱርቦ መኪናዎች በአንደኛው ምድብ፤ ከ1601 እስከ 2000 ሲሲ በሁለተኛው ምድብ፤ ከ1301 እስከ 1600 ሲሲ በሶስተኛው ምድብ፤ በአራተኛው ምድብ ደግሞ እስከ 1300 ሲሲ ጉልበት ያላቸው መኪናዎች ይወዳደሩበታል፡፡ የውድድር መኪናዎቹ የተለያየ ጉልበት ያላቸው ብቻ ሳይሆኑ ዓይነታቸውም እንደሚለያይ የገለፀው አሶሴሽኑ ፎርድ፤ ፔጆት፤ ላንቻ ዴልታ፤ ሚትሱቢሺ፣ ቶዮታ፣ ኦፔል፣ ሱዙኪና ሊፋን መኪናዎች መሆናቸውን አስታውቋል፡፡  
በተጨማሪ በሚካሄደው  የሞተር ብስክሌት እሽቅድምድም ላይ 4 ኢትዮጵያዊያን፤ 7 ፈረንሳዊያን፤ 5 ጣሊያናዊያን፤ 6 ጅቡቲያዊያን፤ 2 አሜሪካዊያን፤ 1 እንግሊዛዊ እና 1 ጀርመናዊ እንደሚሳተፉ ሲታወቅ መወዳደርያዎቹ ሞተር ብስክሌቶች ከ125 እስከ 600 ሲሲ ጉልበት ያላቸው ናቸው፡፡
የኢንዱራሊ የመኪናና የሞተር ብስክሌት ውድድሩን ከጀላዳ ራይደርስ ጋር በመተባበር እንዳዘጋጀው የገለፀው የኢትዮጵያ ሞተር ስፖርት አሶሴሽን  ቢጂአይ አምበር ቢራ፤ ኮባ ኢምፓክት፣ አልታ አውቶ ካር ኬር ጋራጅ፤ ዩኒቨርሳል ፕላስቲክ ፋብሪካ፣ ናሽናል ሞተርስ፣ አምቦውሃ ፋብሪካና አምቼ ኢቪኮ በስፖንሰርነት እንደደገፉት አመልክቷል፡፡

Tuesday, 04 March 2014 11:41

የዲናው የሰንበት ውሎ

ዲናውና ሁለተኛ ልጁ ሉዊስ ስላሴ በአሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ


በ1970 ዓ.ም አዲስ አበባ ውስጥ የተወለደውና በልጅነቱ ወደ አሜሪካ ያቀናው ዲናው መንግስቱ፣ እድገቱ በቺካጎ ሲሆን ከጆርጅ ታውን ዩኒቨርሲቲ በእንግሊዝኛ ቋንቋ የመጀመሪያ ዲግሪውን፣ ከኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ በስነጥበብ ሁለተኛ ዲግሪውን ተቀብሏል፡፡
‘ዘ ቢዩቲፉል ቲንግስ ዛት ሄቨን ቢርስ’፣ ‘ሀው ቱ ሪድ ዘ ኤር’ እና ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በተሰኙት የረዥም ልብወለድ መጽሃፍቱ በሃገረ አሜሪካ ከፍተኛ ታዋቂነትን ያተረፈው ደራሲ ዲናው መንግስቱ፣ ሮሊንግ ስቶንንና ዎልስትሪት ጆርናልን በመሳሰሉ ታዋቂ ጋዜጦችና መጽሄቶች ለንባብ በሚያበቃቸው ስራዎቹም ይታወቃል፡፡ በርካታ የስነጽሁፍ ሽልማቶችንም ለማግኘት በቅቷል፡፡
በ2007 ያሳተመው የመጀመሪያ መጽሃፉ የአመቱ የኒዮርክ ታይምስ ታላቅ መጽሃፍ ተብሎ የተመረጠለት ዲናው፣ ዘ ኒዮርከር ጋዜጣም በ2010 ከአርባ አመት ዕድሜ በታች ያሉ ምርጥ ሃያ ደራሲዎቼ ብሎ ከጠቀሳቸው መካከል ተካትቷል፡፡ ሎስአንጀለስ ታይምስ በ2008 የምርጥ መጽሃፍ ተሸላሚ አድርጎታል።
በ2007 የናሽናል ቡክ አዋርድ ፋውንዴሽን ሽልማትን የተቀበለ ሲሆን፣ በተመሳሳይ አመትም ‘ቺልድረን ኦፍ ዘ ሪቮሊዩሽን’ በሚለው መጽሃፉ የጋርዲያንን ፈርስት ቡክ አዋርድ ያገኘ ተደናቂ ደራሲ ነው፡፡
ደራሲ ዲናው መንግስቱ ለመጨረሻ ዕጩ ተሸላሚነት ከታጨባቸው ታዋቂ ሽልማቶች መካከልም፣ የዳይላን ቶማስ ሽልማት፣ የኒዮርክ ፐብሊክ ላይብራሪ ያንግ ላዮንስ ሽልማት፣ ግራንድ ፕሪክስ ዴስ ሌክትሬ ዲ ኤሌ ሽልማት ይጠቀሳሉ፡፡
‘ኦል አዎር ኔምስ’ የሚል ርዕስ የሰጠው አራተኛ መጽሃፉ በቅርቡ ለህትመት የሚበቃለት ዲናው፣ ነዋሪነቱን ከባለቤቱ አና ኢማኑኤሌ እንዲሁም ከሁለት ወንድ ልጆቹ ጋብሬልና ሉዊስ ስላሴ ጋር በዋሽንግተን ዲሲ አድርጓል፡፡
ዲናው የአንድ ሰንበት ውሎውን ገጽታ፣ ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኛ ጁሊ ቦስማን በራሱ አንደበት እንዲህ ተርኮላታል፡፡ ኒዮርክ ታይምስም የዲናውን ውሎ ባሳለፍነው ሳምንት የዕለተ ሰንበት እትሙ ለንባብ አብቅቶታል፡፡
እነሆ!‘አላርም’ አንፈልግም!
ከቤተሰባችን አባላት ሁሉ ሰነፉ ሰው እኔ ነኝ፡፡ ማልጄ ከአልጋዬ መውረድ አልወድም፡፡ እኔና ሚስቴ ከእንቅልፋችን የሚቀሰቅሰን አላርም አንሞላም። ቀስቅሰው መንጋቱን የሚነግሩን ሁሌም ማልደው የሚነቁት ልጆቻችን ሉዊስ ስላሴና ጋብርኤል ናቸው። ንጋት አስራ ሁለት ሰዓት አካባቢ ከአልጋቸው ብድግ ይሉና የመኝታ ቤታችንን በር በርግደው ከተፍ ይላሉ፡፡ እየተሯሯጡ እኔና እናታቸው የተኛንበት አልጋ ላይ ይወጣሉ፡፡
“በሉ ተነሱ! ረፍዷል!” ብለው ይቀሰቅሱናል፡፡ እኔና ሚስቴ ግን፣ በተለይ በሰንበት ተኝተን ማርፈድ ነው የምንፈልገው፡፡
“እባካችሁ ተውን! ትንሽ እንተኛ አትረብሹን!” እንላቸውና የተወሰነ ጊዜ ተኝተን እንቆያለን፡፡
ከዚያ ሚስቴ ቀድማኝ ትነሳና ለቤተሰቡ ቁርስ ታዘገጃጃለች፡፡ ቁርሳችንን የምንበላው ከአልጋችን ሳንወጣ ነው፡፡ አሪፍ የሆነ ወፍራም ስፕሬሶ እናዘጋጃለን፡፡ እዛው አልጋዬ ውስጥ እንደተጋደምኩ ስፕሬሶዬን እጠጣለሁ፡፡ ከዚያ በኋላ ነው፣ ከእንቅልፌ ሙሉ ለሙሉ ነቅቼ ከአልጋዬ መውረድና የሰንበት ውሎዬን ‘ሀ’ ብዬ መጀመር የምችለው፡፡
ወደ ኬክ ሩጫ
የእለቱ የአየር ሁኔታ የከፋ ካልሆነ በቀር፣ የመጀመሪያው የእሁድ ተግባራችን ልጆቻችንን በተገቢው ሁኔታ ማለባበስና ለሰንበት ሩጫ መዘጋጀት ነው፡፡ የቤተሰቡ የሰንበት ሩጫ መነሻውን ከምንኖርበት አፓርታማ ደጃፍ አድርጎ፣ ከሰፈራችን አቅራቢያ የሚገኝ አንድ ኬክ ቤት በር ላይ ይጠናቀቃል፡፡ የፈረንሳይ ዜጎች የሚያስተዳድሩት ይህ ኬክ ቤት፣ በከተማዋ ምርጥ ኬኮችን ከሚያቀርቡ አሉ የተባሉ ስመጥር ኬክ ቤቶች አንዱ ነው፡፡
የእኛ ቤተሰብም ዘወትር እሁድ ማለዳ ወደዚህ ኬክ ቤት የሰንበት ሩጫ የምናደርገው፣ ‘ቁራሳ’ የሚባለውን ጣፋጭ ኬክ ለመሸመት ነው፡፡ ፓሪስ ውስጥ ነዋሪ እያለንም ማልደን ወደ ኬክ ቤት መሄድና ቁራሳ መግዛት የተለመደ ተግባራችን ነበር፡፡ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ በሰንበት ማለዳ ከልጆቻችን ጋር ወደ ኬክ ሩጫ ማድረጋችንን አልተውነውም፡፡
እንስሳ መሆንን የሚያስመኝ የእንስሳት ፍቅር!
ኬካችንን ገዝተን ወደ ቤታችን ከተመለስንና አጣጥመን ከበላን በኋላ፣ የጠርሙስ ጭማቂዎችንና በግቢያችን  ከሚገኙ የተለያዩ የቤት እንስሳቶች የሳምንቱን ተረኛ የቤት እንስሳ እንመርጣለን። ተረኛው እንስሳ ቀኑን ሙሉ ከእኛ ጋር በሄድንበት ሁሉ ይዘነው ስንዞር የሚውል ነው። ጭማቂዎቻችንን፣ ሌሎች አስፈላጊ ነገሮችንና ተረኛውን እንስሳ ይዘን ረፋድ ላይ ከቤት እንወጣለን - ወደ ጉብኝት፡፡
በየሳምንቱ የምንጎበኛቸውን ቦታዎች እንመርጣለን፡፡ ለምሳሌ በቅርቡ አንድ እሁድ የጎበኘነው፣ በኒውዮርክ ሲቲ የሚገኘውንና በአለማችን ትልቁ የተፈጥሮ ታሪክ ሙዚየም መሆኑ የሚነገርለትን “አሜሪካን ሙዚየም ኦፍ ናቹራል ሂስትሪ” ን ነበር፡፡ ልጆቻችን በግቢያችን ለምናሳድጋቸው ለሁሉም እንስሳት ልዩ ፍቅር ነው ያላቸው፡፡ በተለይ ታናሽዬው ሉዊስ ስላሴ ለእንስሳት ያለው ፍቅር እጅግ የሚገርም ነው፡፡ እንስሳትን አብዝቶ ከመውደዱ የተነሳ፣ ቀሪ የህይወት ዘመኑን እንስሳ ሆኖ ማሳለፍ እንደሚፈልግ ይናገራል፡፡
ጋደም ብሎ ንባብ
የዕለቱን ጉብኝት ካጠናቀቅን በኋላ፣ ሉዊስ ቢያንስ ለአንድ ሰዓት ያህል መተኛት ስላለበት ወደቤታችን እንመለሳለን፡፡ እሱ ከእንቅልፉ እስኪነቃ ቤቱን ስናዘገጃጅ እንቆያለን፡፡ ከዚያም እኔና የመጀመሪያው ልጄ ጋብርኤል አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ማንበብ እንጀምራለን፡፡ እኔ የዕለተ ሰንበት ጋዜጦችን ማገላበጤን ስቀጥል፣ ጋብርኤል ደግሞ በአይፓዱ ጌም ይጫወታል፡፡
ሳትወልድ ብላ!
ምሳ ሰዓት እየደረሰ ነው፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ለትንሹ ልጃችን ሾርባ እናዘጋጃለን፡፡ እኔና ሚስቴ ምግብ ላይ እስከዚህም ነን፡፡ ልጆቻችንን ግን በአግባቡ ነው የምንመግበው፡፡ ሳትወልድ ብላ ይባል የለ!... ልጆች ሲኖሩሽ ብዙ ምግብ አትበይም፡፡ ታላቁ ልጅ ምግብ ላይ አደገኛ ነው፡፡ ምግብ በሰዓቱ ካልደረሰ ጉዳችን ይፈላል፡፡ እንደ ሙዝ ያሉ ቢጫ ቀለም ያላቸውን ምግቦች የበለጠ ይወዳል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ በመጠኑ የተወሰነ ፒዛ መብላት ጀምሯል፡፡
የተሲያት ብስኩት
ዘወትር እሁድ ከሰዓት በኋላ አንድ የተለመደ ፕሮግራም አለን - ብስኩቶችን መጋገር፡፡ ሁለቱም ልጆቻችን ብስኩቶችን መጋገር ይወዳሉ፡፡ እሁድ ከሰዓት በኋላን ኩኪስ በመጋገር ተጠምደው ነው የሚያሳልፉት፡፡ ሊጥ አብኩተው፣ እንቁላል በጥብ
ጠው ኩኪስ ሲጋግሩና ሲጠብሱ ነው የሚውሉት፡፡
የምሽት እንግዳ
ፓሪስ እያለን ሁሌም እሁድ እሁድ ማታ የሆነ እንግዳ ወደ ቤታችን ጎራ ማለቱ አይቀርም ነበር። ለነገሩ እዚህ ከመጣን በኋላም፣ ቢያንስ ከሁለት እሁድ በአንዱ የሆነ እንግዳ ሳናስተናግድ አንቀርም። ብዙ ጊዜ ለእሁድ ማታ ራት የተጠበሰ ዶሮ ነው የምናዘጋጀው፡፡
በነገራችን ላይ እኔ ራሴ የተዋጣልኝ ምግብ ሰሪ ነኝ፡፡ ቶማስ ኬለር የሚባለው ታዋቂ የምግብ አብሳይ በሚጠቀምበት አዘገጃጀት መሰረት ነው የዶሮ ጥብስ የምሰራው፡፡ ዘይት ወይም ቅቤ የሚባል ነገር አይገባበትም፡፡ በተቻለ መጠን ጥብሱ ደረቅ ያለ መሆን አለበት፡፡ በዚህ መልኩ ሲዘጋጅ የዶሮዋ ቆዳ በሚገርም ሁኔታ ስለሚደርቅ ሲበላ ኩርሽም ኩርሽም ይላል፡፡ ዋው!... እንዴት እንደሚጣፍጥ ልነግርሽ አልችልም!
እንግዶች ከመጡ ጥሩ አድርገን ስናስተናግድ እናመሻለን፡፡ ልጆቻችንም ገላቸውን ታጥበው የሌሊት ልብሶቻቸውን ይለብሳሉ፡፡ ልጆቹ በአብዛኛው ከምሽቱ ሁለት ሰዓት አካባቢ ነው የሚተኙት፡፡ ቤታችን ውስጥ ያለውን ሰው በሙሉ ደህና እደሩ ብለው ይሰናበቱና ወደ አልጋዎቻቸው ያመራሉ፡፡ እንቅልፍ እስከሚወስዳቸው ድረስ አንድ ሁለት አጫጭር ታሪኮች ያሏቸው የህጻናት ፊልሞችን ያያሉ፡፡ ከፊልሙ በሚወጣው የህጻናት ጫጫታ ታጅበው ማንቀላፋት ይወዳሉ፡፡
እሁድ ስታልቅ
እሁድ ቀን ከሚስቴና ከልጆቼ ጋር ዘና ስል መዋል እንጂ፣ በስራ ተጠምዶ መዋልም ሆነ ማምሸት አይመቸኝም፡፡ እሁድን ዘና ብዬ በእረፍት አሳልፌ፣ ሰኞን በነቃ ትኩስ ስሜት መቀበል ነው የምፈልገው። አንዳንዴ ግን፣ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሲፈጠሩ በመጠኑም ቢሆን ልሰራ እችላለሁ፡፡ ለምሳሌ በጆርጅ ታውን ማክሰኞ ማክሰኞ ተማሪዎችን አስተምራለሁ፡፡ ስለሆነም ለማስተምረው ትምህርት መዘጋጀት ሲያስፈልገኝ፣ እሁድም ቢሆን የተወሰነ ሰዓት አምሽቼ መዘጋጀቴና ከመሸ  ወደ አልጋ ማምራቴ አይቀርም፡፡
የሰንበት እንግዶቻችንን በወጉ አስተናግደን ከሸኘን በኋላ፣ ከሚስቴ ጋ አልጋችን ላይ ጋደም ብለን ፊልም እያየን አይስክሬም እንበላለን፡፡ ለምሽቱ የምናየውን ፊልም ከሚስቴ ጋር ተነጋግረን ነው የምንመርጠው፡፡  
ፊልሙ የእሷ ምርጫ ከሆነ፣ በአንድ ደራሲ ወይም አርቲስት ህይወት ዙሪያ የሚያጠነጥን ዶክመንታሪ ፊልም መሆኑ አይቀርም። ምርጫው የእኔ ከሆነ ግን፣ እምብዛም ዋጋ የሌለው ፊልም መሆኑ ግድ ነው፡፡


የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የታሪክ ትምህርት ክፍል፣ የተመሰረተበትን 50ኛ ዓመት በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች የሚያከብር ሲሆን በትላንትናው ዕለት በዩኒቨርሲቲው የቢዝነስና ኢኮኖሚክስ ፋኩልቲ ግቢ፣ በእሸቱ ጮሌ አዳራሽ ታላቅ የጥናት ጉባኤ ተጀምሯል። ዛሬም ይቀጥላል የተባለው የጥናት ጉባኤው 40ኛ ዓመቱን የሞላው “የመጀመሪያው” አብዮትና ተከታይ ክስተቶች በኢትዮጵያ የታሪክ ትርጉም ላይ ያሳረፏቸው ተፅዕኖዎች የሚፈተሽበት እንደሚሆን ይጠበቃል፡፡
የፕሮግራሙ አዘጋጆች ለአዲስ አድማስ በላኩት መግለጫ እንዳመለከቱት፤ በሁለቱ ጉባኤ ቀናት 25 የታሪክ ባለሙያዎች የጥናት ወረቀት የሚያቀርቡ ሲሆን ከታሪክ ጋር በተያያዙ ተግዳሮቶችና ዕድሎች ዙሪያ ሰፋ ያለ ውይይት የሚደረግበት የመጀመሪያው አጋጣሚ እንዲሆን ተጠቁሟል፡፡ የዩኒቨርሲቲው ከፍተኛ ኃላፊዎች፣ አካዳሚክ ማህበረሰቡ፣ የታሪክ ባለሙያዎች፣ ለታሪክ ልዩ ቅናት ያላቸው የህብረተሰብ አካሎችና ጋዜጠኞች በሚገኙበት በዚህ ጉባኤ፤ ፍላጎት ያላቸው ሁሉ እንዲታደሙ አዘጋጆቹ ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ተፅፎ በተሻለ አሰፋ የተዘጋጀው “ቅጥልጥል ኮከቦች” ትያትር ባለፈው እሁድ ተመርቆ ተከፈተ፡፡
የትያትሩ ጭብጥ በህክምና ስነ ምግባር ጥሰትና በምርመራ ጋዜጠኝነት ላይ የሚያተኩር ሲሆን ትያትሩ ተመርቆ ከመከፈቱ በፊት በባለሙያዎች እንደተገመገመ ለማወቅ ተችሏል፡፡ በትያትሩ ላይ አርቲስት ሽመልስ አበራ (ጆሮ)፣ መሰረተ ህይወት፣ ስናፍቅሽ ተስፋዬ፣ ሱራፌል ተካና ሌሎችም ይተውኑበታል፡፡
ትያትሩ ዘወትር እሁድ ከ8 ሰዓት ጀምሮ ለተመልካች እንደሚቀርብም ታውቋል፡፡ ፀሃፌ ተውኔት ውድነህ ክፍሌ ከዚህ ቀደም ከአስር በላይ ትያትሮችን ፅፎ ለተመልካች አቅርቧል፡፡

የገጣሚና ሙዚቀኛ ቴዎድሮስ ነጋሽ ሁለተኛ የግጥም መድበል “ስኳር እና ፍቅር” በትላንትናው ዕለት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ያሬድ ሙዚቃ ት/ቤት አዳራሽ ተመረቀ፡፡ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ የደራሲው ቀደምትና አዳዲስ ስራዎች ከሙዚቃ ጋር ታጅበው የቀረቡ ሲሆን ባይላሞር የዳንስ ቡድን በሳልሳ ዳንስ ፕሮግራሙን እንዳደመቀው ታውቋል፡፡

ባለፈው ዓመት በደብረማርቆስ ዩኒቨርሲቲ ስር የተቋቋመው የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም ዛሬና ነገ ሁለተኛ ዓመታዊ ሲምፖዚየሙን በዩኒቨርሲቲው ቅጥር ጊቢ እንደሚያካሂድ ተገለፀ፡፡
በሲምፖዚየሙ ላይ ሰባት ባህል ተኮር ጥናታዊ ፅሁፎች በአገር ውስጥና በውጭ ተመራማሪዎች ይቀርባሉ ተብሏል፡፡ ባለፈው ዓመት የተቋቋመው የባህል ጥናት ተቋሙ፣ ከጀርመኑ “ኢትዮ ስፔር” ጋር በመተባበር፣ በአካባቢው በሚገኙ አብያተ ክርስቲያናት ውስጥ ያሉትን የተለያዩ ቅርሳ ቅርሶች በዲጂታላይዜሽን ሥርዓት አደራጅቶ በመያዝ ለትውልድ ለማስተላለፍ እገዛ እንደሚያደርግ የተናገሩት የተቋሙ ዳይሬክተር አቶ መስፍን ፈቃዴ፤ ተቋሙ የአብነት ት/ቤቶች ባህላዊ አስተምህሮቱን ጠብቀው እንዲዘልቁ የማጠናከሪያ ስራ ይሰራል ብለዋል፡፡
የሃዲስ አለማየሁ የባህል ጥናት ተቋም የአካባቢውን ባህል፣ ወግ፣ ልማድ፣ ትውፊትና ኪነ-ጥበብ ለመጠበቅና በርካታ ትውፊታዊ ሃብቶች ያሏቸው ቅኔና ግዕዝ በምርምር ታግዘው፣  ለቀጣይ ትውልድ እንዲተላለፉ የማድረግ ዓላማ ይዞ መቋቋሙ ይታወሳል፡፡