Administrator

Administrator

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትርን ላለፉት ሁለት አመታት በተጠባባቂ ሥራ አስኪያጅነት ሲመሩ በቆዩት አቶ ደስታ ካሳ ምትክ አርቲስት ተስፋዬ ሽመልስ የትያትር ቤቱ አዲስ ሥራ አስኪያጅ ሆኖ ተሾመ፡፡ በጠቅላይ ሚኒስትር ኃይለማርያም ደሳለኝ የተፈረመ የሹመት ደብዳቤ የደረሰው አርቲስት ተስፋዬ፤ ከሐምሌ 4 ጀምሮ ትያትር ቤቱን እንዲመራ በደብዳቤው ላይ ተገልጿል፡፡ መደበኛ ሥራውን ከመጀመሩ በፊትም ዘንድሮ የባህልና ቱሪዝም ሚኒስትር ዴኤታ ሆነው በተሾሙት አቶ ሙልጌታ ሰኢድ አማካኝነት ከትያትር ቤቱ ሠራተኞች ጋር ተዋውቋል፡፡ በትያትር ፀሃፊነቱ የሚታወቀው አርቲስት ተስፋዬ፤ “ስንብት” እና “ሰማያዊ አይን” የተሰኙ ትያትሮችን ለመድረክ ማብቃቱ ይታወቃል፡፡
በፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት በጋዜጠኛነት የሰራው አርቲስቱ፤ እስከ ቅርብ ጊዜ ድረስ በሸገር ኤፍኤም ሬዲዮ የአየር ሰአት ገዝቶ የራሱን ፕሮግራም ሲያቀርብ ቆይቷል፡፡

የ“አለ ኪነጥበባት” ትምህርት ቤት ሰዓሊዎች ከ“ነፃ አርት ቪሌጅ” ጋር በመተባበር የአዲስ አበባ ከተማ ነዋሪዎች ስለ ሥዕል እና ቅርፃ ቅርፅ ያላቸው ግንዛቤ እንዲዳብር “ሰምና ወርቅ” የተሰኘ የጐዳና ላይ ትርዒት በማዘጋጀት የመነጋገርያ ሃሳብ አቀረቡ፡፡ ባለፈው ረቡዕ የቀረበው ዝግጅት በ”አለ ኪነጥበባት” ትምህርት ቤት ተጀምሮ ከአራት ሰአታት የከተማዋ ጉብኝት በኋላ የተጠናቀቀ ሲሆን አራት ኪሎ፣ ፒያሳ፣ ተክለሃይማኖት፣ ሜክሲኮ፣ ራስ መኮንን ድልድይ፣ መርካቶና ጃንሜዳን ያካተተ ነው፡፡ በጐዳና ትእይንቱ ሰዓሊ ታምራት ገዛኸኝ፣ ተስፋሁን ክብሩ፣ ዳንኤል አለማየሁ፣ ሙልጌታ ካሳ እና ለይኩን ናሁሰናይ እና ሌሎች ተሳትፈዋል፡፡ ረዳት ፕሮፌሰር በቀለ መኮንን፣ ዶክተር ኤልሳቤጥ ወልደጊዮርጊስ እና የውጭ አገር ኮሙኒቲ አባላት በክብር እንግድነት ተገኝተዋል፡፡

 

“የሰው ነገር” የተሰኘ አዲስ የሬዲዮ መዝናኛ ፕሮግራም ነገ በሸገር ኤፍኤም 102.1 እንደሚጀመር ማርቭል ፕሮሞሽን እና ኮሙኒኬሽን አስታወቀ፡፡ በየሳምንቱ እሁድ በ8 ሰዓት የሚቀርበውን ዝግጅት የፋና ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬት ጋዜጠኞች የነበሩት ሲሳይ ጫንያለው፣ ዘላለም ሙላቱ፣ ብስራት ከፈለኝና ስዩም ፍቃዱ እንደሚያቀርቡት ድርጅቱ አስታውቋል፡፡ “የሰው ነገር” በፊልም፣ በሙዚቃ፣ በሥነ ፅሁፍ፣ በስዕል እና ሌሎች የጥበብ ዘርፎች ላይ የሚያተኩር ሲሆን ፕሮግራሙ መዝናኛና ቁምነገርን በሚዛናዊነት እንደሚያቀርብ ተገልጿል፡፡

በፊልም ባለሙያው ተስፋዬ ማሞ ወንድም አገኘሁ የተፃፈው “የጨረቃ ጥሪ” ወንጀል ነክ ረዥም ልቦለድ ሰሞኑን ለንባብ በቃ፡፡ ልቦለዱ ከ21 ዓመት በፊት የተፃፈ መሆኑን ደራሲው ገልጿል፡፡
በ1982 ለንባብ የበቃችው “ዕፀበለስ” የተሰኘች መፅሐፉ በአንባቢያን ዘንድ መወደዷ በፈጠረበት ግለት ተነሳስቶ “የጨረቃ ጥሪ” የተባለውን ሁለተኛ መፅሐፉን ቢፅፍም የህትመት ብርሃን ሳያይ መቆየቱን ተናግሯል፡፡
በኤችዋይ ኢንተርናሽናል ፕሪንቲንግ የታተመው ባለ 212 ገፅ ልቦለድ መፅሐፍ፤ ለኢትዮጵያ ገበያ በ50 ብር፣ ከኢትዮጵያ ውጭ ደግሞ በ15 ዶላር ይሸጣል፡፡ “ሉሲ ተሸጣለች” የተሰኘው ረዥም ልቦለድም ለንባብ የበቃው በዚህ ሳምንት ነው፡፡
በአንድነት አየለ ኃይሌ የተፃፈው ባለ 289 ገፅ መፅሐፍ፤ በአሀዱ ማተሚያ ቤት የታተመ ሲሆን ለሀገር ውስጥ በ44.96 ብር ፣ ለውጭ ሀገራት በ45 ዶላር እንደሚሸጥ ታውቋል፡፡

*“የኢትዮጵያ የእግር ኳስ ጉዞ” መፅሐፍ ለገበያ በቃ

“ጳጉሜ፣ የኢትዮጵያ ቀን መቁጠርያ የማን ነው?” የሚል መፅሐፍ ዛሬ ገርጂ በሚገኘው የዩኒቲ ዩኒቨርስቲ አዳራሽ እንደሚመረቅ አዘጋጁ አስታወቁ፡፡
የመፅሐፉ አዘጋጅ የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ፋሲል ጣሰው፤ የቀን አቆጣጠሩ የኢትዮጵያ ብቻ አይደለም የሚል መሟገቻ በመፅሐፋቸው ያቀረቡ ሲሆን ወርሃ ጳጉሜ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም ማስገኘት አለባት በማለትም፣ ሠራተኞች ተጨማሪ ደመወዝ፣ የቤት አከራዮች የኪራይ ገንዘብ ጳጉሜን ታሳቢ በማድረግ ማግኘት እንዳለባቸው ገልፀዋል፡፡ በምረቃ ሥነስርዓቱ ላይ ዶ/ር አረጋ ይርዳውን ጨምሮ ሌሎች የሚድሮክ የሥራ ኃላፊዎች ይገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ መፅሐፉ ለሀገር ውስጥ በ100 ብር፣ ለውጭ ሀገራት በ35 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡በሌላም በኩል “ነገር በምሳሌ” ቁጥር 1 መፅሐፍ በመጪው ሐሙስ በ10፡30 በብሉ በርድ ሆቴል ይመረቃል፡፡

አቶ አብርሃም ሐዲሽ ያዘጋጁት ባለ 103 ገፅ መፅሐፍ፤ የሥራ ባህል እንዳይዳብር መሰናክል ሆነው የቆዩ ልማዶችን ለመዋጋት የመፍትሄ ሀሳቦችን ያቀርባል፡፡ መፅሐፉ በ30 ብር እየተሸጠ ነው፡፡በፈለቀ ደምሴ (ኤርምያስ) የተዘጋጀው “የኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉዞ” መፅሐፍ ለንባብ በቃ፡፡ በበርካታ መረጃዎች እና ፎቶግራፎች የተደገፈው ባለ 179 ገፅ መፅሐፍ፤ በፋርኢስት ትሬዲንግ የታተመ ሲሆን ዋጋው 47 ብር ነው፡፡ በመፅሐፉ የኋላ ሽፋን ላይ የቀድሞ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቡድን እና የቡና ክለብ ተጫዋች አሰግድ ተስፋዬ፣ ጋዜጠኛ ኢብራሂም ሻፊ አህመድ፣ የቅዱስ ጊዮርጊስ እግር ኳስ ክለብ ምክትል አሰልጣኝ ዘሪሁን ሸንገታ እና የኢትዮጵያ የሴቶች ብሔራዊ ቡድን ተጫዋች አልፊያ ጃርሶ አስተያየታቸውን አስፍረዋል፡፡

ላለፉት 20 ዓመታት በሂፕሆፕ ሙዚቃ ከፍተኛ ተወዳጅነት እና ስኬት ባገኘው ራፐር ናስ ስም ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ፌሎውሺፕ ማቋቋሙን አስታወቀ፡፡ በሂፕሆፕ ሙዚቃ ታሪክ ያላቸውና ነባራዊ ገፅታን በረቀቀ መንገድ የሚያንፀባርቁ ሃሳቦችን በብዛት በመስራት ክብርና ዝና የተቀዳጀው ናስ፤ በሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ ናስር ጆንስ ፌሎሺፕ ተቋቁሞለታል፡፡ ዌብ ዱ ቦይስ ኢንስቲትዩት እና ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ የሂፕሆፕ ክምችት ፌሎሺፑን የሚያስተዳድሩ ሲሆን የሂፕሆፕ ሙዚቃ ባህል፤ በታሪክ እና በፈጠራ ሂደት የሚኖረውን ሚና ለማጎልበት በሚል እንዲሁም ከሂፕሆፕ ጋር የተገናኘ የኪነጥበብ ትምህርት ለሚወስዱ ተማሪዎች ድጋፍ እንደሚሰጥበት ታውቋል፡፡ በሙሉ ስሙ ናስር ቢን ኦሉ ዳራ ጆንስ ተብሎ የሚታወቀው ራፕሩ፤ ባለፈው ዓመት “ላይፍ ኢዝ ጉድ” በሚል መጠርያ 11ኛ አልበሙን ለገበያ ማብቃቱ ይታወሳል፡፡

ኦስካር ተሸላሚው ፎረስት ዊቴከር በመሪ ተዋናይነት የሰራበት አዲስ ፊልም ርእሱ ተኮርጇል በሚል መከሰሱን ሎስ አንጀለስ ታይምስ ገለፀ ፡፡ “ዘ በትለር” የተባለው የፊልሙ ርእስ እ.ኤ.አ በ1916 ዓ.ም ከተሰራ ድምፅ አልባ ፊልም የተወሰደ ነው የሚል ነው ክሱ፡፡ ከአንድ ወር ባነሰ ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም ለእይታ የሚበቃው ፊልሙ፣ በተመሰረተበት ክስ ከተሸነፈ ርእሱን ለመቀየር ይገደዳል፡፡ “በሲኒማው ኢንዱስትሪ ታሪክ ለ122 ጊዜያት ርእሶች ተደጋግመዋል፣ ተመሳስለው ተገኝተዋል” ይላል ፊልሙን የሰራው የዌይንስተን ኩባንያ ስራ አስኪያጅ - “ዘ በትለር” ፊልም ላይ የተለየ ነገር መነሳቱ አግባብ አይደለም በሚል ሲከራከር፡፡
በ25 ሚሊዮን ዶላር በጀት በዋርነር ብሮስ የተሰራው “ዘ በትለር”፤ ለስምንት የአሜሪካ ፕሬዚዳንቶች በአገልጋይነት ስለሰራ አንድ ጥቁር አሜሪካዊ የህይወት ታሪክ ያሳያል፡፡ ፎረስት ዊቴከር በዚህ አዲስ ፊልሙ ለኦስካር የሚያበቃ የትወና ብቃት ማሳየቱን የጠቀሰው ሎስ አንጀለስ ታይምስ፤ በዚሁ ፊልም ላይ ኦፕራ ዊንፍሬይ፤ ሊያም ኔሰን እና ሮቢን ዊልያምስ መተወናቸውን አመልክቷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2006 “ዘ ላስት ኪንግ ኦፍ ስኮትላንድ” በተባለው ፊልም ላይ የኢድ አሚንን ገፀባህርይ በመጫወት በምርጥ ተዋናይነት ኦስካር የተሸለመው ፎረስት ዊቴከር፤ በተመሳሳይ የጎልደን ግሎብ እና የባፍታ ሽልማቶችንም ወስዷል - በምርጥ ተዋናይነት፡፡ የ52 ዓመቱ የፊልም ባለሙያ ከተዋናይነቱ በተጨማሪ በፊልም ፕሮዱዩሰርነትና ዳሬክተርነትም ይታወቃል፡፡

Saturday, 20 July 2013 10:20

የትግራይ ጉዞ ማስታወሻ

ተናጋሪዋ ምድር
ትግራይ የትራጀዲና ኮሜዲ መድረክ ናት!
ከክርስቶስ ልደት 2006 ዓመት በፊት “አልሙጋህ” የተባለ ጣኦት ይመለክበት የነበረውን አዲአካውህን ጐብኝተን ውቅሮ ስንገባ ነው ጽሑፌን በይደር የቋጨሁት፡፡
ውቅሮ ለጥ ባለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች ዘመናዊ ከተማ ናት፡፡ ከዚያች ውብ ከተማ ዳር እንደደረስን የከተማዋ ከንቲባና ነዋሪዎችዋ እንደሌሎች ከተሞች ነዋሪዎች ሁሉ በጭፈራ፣ በሆታና በዕልልታ ነው የተቀበሉን፡፡ ደመቅ ያለ ቁርስም ከቡና ጋር ጋብዘውናል፡፡ እንግዳን በክብር መቀበልና መጋበዝ የትግራዮች ባህል መሆኑን በተደጋጋሚ ስላየን ብዙም ላይደንቅ ይችላል፡፡ ግን የውቅሮ ከተማ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችና ሠራተኞች ሊወደሱበት የሚገባ አንድ እንግዳ ነገር ተገንዝበናል፡፡ በውቅሮ ቅዳሜ የሥራ ቀን ነው፡፡ ህዝቡን ለማገልገል ሲባል ሠራተኛው በሙሉ ፈቃደኝነት ቅዳሜን በሥራ እንደሚያሳልፍ ተነግሮን “ይበል በሌሎች የሀገሪቱ ከተሞችም ይለመድ” ብለናል፡፡
የውቅሮ ቆይታችንን በአጭሩ አጠናቀን መጓዝ ስላለብን፣ ወደ አውቶቡሳችን መሰባሰብ ጀምረናል፡፡ ጊዜውም የተሳፈርንበት አውቶቡስም እሽቅድምድም የያዙ ይመስል በየፊናቸው ይከንፋሉ፡፡ አውቶቡሳችን ሲከንፍ ተናጋሪዋን ምድር እየቃኘን፣ በአየነው ተራራ፣ ወይም የተፈጥሮ ጥበቃ እየተደመምን ስንጓዝ ሌላ አስደናቂ ነገር ሲቀበለን፤ በቃ ትግራይ ማለት ቢገልጧት፣ ቢገልጧት ተነብባ የማታልቅ ግዙፍ መጽሐፍ ትመስላለች፡፡
በዚህ አይነት ስንጓዝ ቆይተን በአገራችን ታሪክ የመጀመሪያው ውቅር ቤተክርስቲያን ከሚገኝበት አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ ደረስን፡፡ አብርሃ በአራተኛው መቶ ክፍለዘመን የአክሱም ንጉሥ የነበረና ክርስትና መንግሥታዊ ሃይማኖት እንዲሆን የደነገገ ነው፡፡ የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ በስሙ የተሰየመውም በዚሁ ታሪካዊ ምክንያት ሲሆን መቃብሩም በዚሁ ቤተክርስቲያን ውስጥ ይገኛል፡፡
ስለቤተክርስቲያኑ የአሰራር ጥበብና በውስጡ ስለሚገኙት ቅርሶች፣ ስለ ሶስቱ ቤተመቅደሶች፣ ስለ ቦታው አቀማመጥ፣ ወዘተ ብዙ እጅግ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ግን ቦታም ጊዜም የለም፣ እንደ ጉብኝታችን ሁሉ ጽሑፌንም ፈጠን ማድረግ አለብኝ፡፡ አለዚያ ጋዜጣችን ትግራይ ላይ ብቻ ቢከርምም ስለ ትግራይ ምስጢር፣ ስለ ትግራይ ተአምራዊነት ጽፎ መጨረስ አይቻልም፡፡ የገደላትና ተአምራት ፀሐፊዎች እንዲህ አይነቱ እጹብ ድንቅ የሆነ ጉዳይ ሲገጥማቸው “ሰማዩ ሰሌዳ ወይም ብራና፣ የክረምቱ ዝናም ቀለም ቢሆኑም ጽፌ መጨረስ አልችልም” ይላሉ፡፡ የትግራይ ጉዳይ ያለምንም ማጋነን ለእኔ እንዲያ ነው፡፡
አብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ከታሪካዊው ቤተክርስቲያኗ በተለይ የምትደነቅበት አጋጣሚም ተፈጥሯል፡፡ ቀበሌዋ እጅግ ከተራቆቱት የክልሉ ቀበሌዎች አንዷ ነበረች፡፡ ግን በህዝቡ እንደ ብረት የፀና ትግስትና ጥረት ዛሬ ተቀይራለች፤ ተራሮችዋ በተፈጥሮ ደን እየተሸፈኑ ናቸው፡፡
የአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ስም ሲነሳ የአንድ ጀግና አርሶ አደር ስም አብሮ መወሳቱ ግድ ነው፡፡ ስሙ “አባ ሐዊ” ይባላል፡፡ በትግርኛ “አባ እሳት” ማለት ነው፡፡ ትክክለኛ ስሙ ግን ገብረሚካኤል ዓደይ ይባላል፡፡ “አባ ሐዊ” የሚለው ቅጽል ስም የወጣለት በግብሩ ነው፡፡ ሲናገር እሳት ነው፤ ሲሰራ ደግሞ የበለጠ ነበልባል ነው፡፡ ኃላፊዎች ከቢሮአቸው ቁጭ ብለው ወይም ህዝብን ሰብስበው “እንዲህ ብታደርጉ የተሻለ ምርት ታገኛላችሁ፤ ወይም ምርታችሁ እንዲያድግ ይህን ፍጠሩ ማለት የለባቸውም፡፡ እንዲህ ብለው ሲያዝዙ ህዝቡ “የምትነግረን እውነት ከሆነ ለምን አንተ አልከበርህም?” የሚል ጥያቄ ቢያነሳ መልስ የለውም፡፡ ስለዚህ መሪዎች ሠርቶ በማሳየት አርአያዎች እንጂ የወሬ ጀግኖች መሆን የለባቸውም” ብሎናል በኩራት፡፡
አብርሃ ወአጽብሃ ቀበሌ እጅግ ዘግናኝ ከሆነ ድህነትና መራቆት የተራቀቀችው በአባ ሐዊ ፋና ወጊነትና አመራር ሰጭነት መሆኑን ተገንዝበናል፡፡ አባ ሐዊ በዚህ የልማት ጀግንነቱ በዓለምአቀፍ ደረጃ አንድ ጊዜ፣ በአገር አቀፍ ደግሞ 15 ጊዜ ተሸልሟል፡፡ የአባ ሐዊ የአመራር ጥበብ ቀድሞ ሠርቶ በማሳየት በመሆኑ፣ በህዝቡ ዘንድ ትልቅ አመኔታና ከበሬታን አግኝቷል፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ ተገኝተን በአይናችን አይተን ያረጋገጥነው እውነትም ይኸው ነው፡፡ ያ አስፈሪ የነበረ ራቁት መሬት በደን ከመሸፈኑም በላይ ልዩ ልዩ አትክልቶችና ፍራፍሬዎች ተንዠርግገው ይታያሉ፡፡ የሰው ልጅ ከፈለገ አጥፊ ከፈለገ ደግሞ ተፈጥሮን ከነሙሉ ለዛዋና ክብሯ ሊመልሳት እንደሚችል መልካም አብነት ነው፡፡
ከአባ ሐዊ ጓሮ የተንዠረገጉትን ልዩ ልዩ አትክልትና ፍራፍሬዎችን በአድናቆት ከጐበኘን በኋላ ወደ እንግዳ መቀበያው ወሰደን፡፡ የእልፍኝ ቅርጽ ካለው እንግዳ መቀበያ ቤቱ ቁጭ እንዳልን፣ በሚያስገርም ፍጥነት ሻሽ የመሰለ ማር በዳቦ እያደረገ ለእያንዳንዱ ተጓዥ አደለ፡፡
ጠንክረው ከሰሩ ጣፋጭ ውጤት እንደሚገኝ ከአባ ሐዊ ተምረን፣ አመስግነንም ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ አክሱም ገብተን ማደር ስላለብን እንጂ ልክ እንደ ማሩ ሁሉ ያንን የሚጣፍጥ አንደበቱን እያዳመጥን ትንሽ ጊዜ ብንቆይ ደስታውን አንችለውም ነበር፡፡
የጥበብ ተጓዦች ጉዞ ከጀመሩበት ዕለት አንስተው በአውቶቡሱ ውስጥ መዝፈን፣ ማቅራራትና መዘመር ወይም ግጥምና ዜና በማንበብ ራሳቸውን ማዝናናት የተካኑበት ቢሆንም ከአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ጉብኝታቸው በኋላ ግን የሆነ ህመም የያዛቸው ይመስል እየፈዘዙ መጡ፡፡
እርግጥ ነው ትግራይ ግራ ታጋባለች፤ ትግራይን ከራስ እስከ እግሯ ሳይጐበኙ “ኢትዮጵያዊ ነኝ” ማለትም ይከብዳል፡፡ ወይም ያሳፍራል፡፡ ትግራይ ተራራዋ ሁሉ፣ ከርሰምድሯ ሁሉ፣ ገዳሟ መስጊዷ ሁሉ የአገሪቱን ወይም የመላ አፍሪካን ምስጢር ደብቀው ይዘዋል፡፡
ጉዟችን ቀጥሏል፡፡ መንገዱ ገና እየሰፋ ስለሆነ ኮረኮንች ነው፡፡ በአብርሃ ወአጽብሐ ቀበሌ ህዝብ ጥንካሬ፣ በአባ ሐዊ የአመራር ስልት፣ በገዳሙ ጥንታዊነት ድንቅ ጥበብ እየተደነቅን ስንጓዝ በስተግራ በኩል እውቅ ቀራጺ ተጠንቅቆ ያዘጋጀው የሚመስሉት የገርዓልታ ሰንሰለታማ ተራሮች ከፊት ለፊታችን ድንቅ አሉ፡፡ ተራሮቹ እንደ ማንኛውም ተራራ የድንጋይ ቁልሎች አይደሉም፡፡ ይልቁንም ከአፍ እስከ ገደፋቸው የአገራችን የሥልጣኔ፣ የታሪክ፣ የሥነ ጥበብ፣ የሥነ ሕንፃና የሥነ ፈለክ ምስጢሮች የታጨቁባቸው የምስጢር ጐተራዎች ናቸው፡፡
አስደናቂውን የአባ ቶምዓታን ቤተክርስቲያን ጨምሮ በአብዛኞቹ ተራሮች ላይ ከ34 በላይ ከአንድ አለት የተፈለፈሉ አብያተክርስቲያናት አሉ፡፡ እያንዳንዳቸውን ጐብኝቶ ለመጨረስ ቢያን ለአንዱ ቤተክርስቲያን የአንድ ቀን ቆይታን ይጠይቃል፡፡
በገርዓልታ ተራሮች ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ፣ በውስጣቸው ስላሉ ምስጢራት እየተደነቅን በመጓዝ ላይ ሳለን ከፊት ለፊታችን፤ ግን በርቀት አስደናቂው እና በር አልባው የደብረዳሞ ተራራ በኩራት ተጀንኖ ታየን፡፡
ደብረ ዳሞ በ6ኛው መቶ ክፍለ ዘመን አባ አረጋዊ የሚባሉ መነኩሴ የመሠረቱትና እንደ ግዑዝ ነገር በመጫኛ ብቻ እየተጐተቱ የሚወጡበት ታላቅ ደብር ነው፡፡ የመጐብኘት ዕድሉ ስላልነበረን ውስጤ እያዘነ ግን ደግሞ በካሜራዬ ምስሉን ለማስቀረት እየሞከርኩ ማለፍ ግድ ሆነ፡፡ ጥላሁን ገሠሠ “በዓይን እየተያዩ የመናፈቅ ጣጣ…” ያለው እንዲህ አይነቱ የውስጥ ስቃይ ገጥሞት ይሆን?
ትግራይ የሃይማኖት፣ የስልጣኔ፣ የፍልስፍና፣ የዕውቀትና የማንነት ምስጢራት ዋሻ ብቻ ሳትሆን የትራጄዲና ኮሚዲ መድረክም ናት፡፡ አሁን ደግሞ ሐውዜን ገባን፡፡ ሐውዜን መራራ ትራጄዲ ከተተወነባቸው መድረኮች አንዷ ናት፡፡ በቀድሞው መንግሥት የጦር አውሮፕላኖች በአንድ የገበያ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰላማዊ ዜጐች እንደ ቅጠል ረግፈውባታል፡፡
የትራጄዲውን መድረክ ሐውዜንን በሀዘን ተሰናብተን ወደፊት እየተጓዝን ነው፡፡ ትግራይ ክልል ውስጥ ተራራ ላይ ቢወጡ አስደናቂ ጥበብ ይነበባል፤ መሬቱን ቢቆፍሩ እጅግ የሚገርም ምስጢር ይገኛል፡፡ ስለሆነም ማየት ያለብን ብዙ ነገር ቢኖርም በጊዜ አክሱም ለመግባት መፍጠን ይጠበቅብናል፡፡ ግን ደግሞ ውቧን ከተማ አድግራትን ማግኘት አለብን፡፡
አድግራትም የተለመደው ህዝባዊና ደማቅ አቀባበል ከምሳ ግብዣ ጋር ተደረገልን፡፡ ምሳው ደግሞ ከሚጣፍጠው የትግራይ ባህላዊ ምግብ “ጥህሎ” እና ከንፁህ የማር ጠጅ ጋር ነበር፡፡ በነገራችን ላይ “አድግራት” ማለት “አድገራሕት” ማለትም “የእርሻ አገር” ማለት መሆኑን አቶ ከበደ አማረ አስረድተውናል፡፡ ለጥ ካለ ሜዳ ላይ የተመሰረተች በመሆኗ እውነትም ለእርሻ ምቹ የነበረች መሆኗን መገንዘብ አያዳግትም፡፡
አድዓራት ውብ ከተማ ናት፡፡ የዩኒቨርሲቲው መመሥረት ከሻዕቢያ ጦርነት በኋላ ተቀዛቅዛ የነበረችውን ከተማ አነቃቅቷል፡፡ የአድግራት ከተማ ባለሥልጣናትና ነዋሪዎችን ግብዣ አጠናቀን በምስጋና ተሰነባበትንና ጉዟችንን ቀጠልን፡፡ የእኛ ነገር መሄድ፣ ማየት፣ ባየነው ነገር መደነቅ ነው፡፡ ድካም የሚባል ነገር የለም፡፡ ከሁሉ የሚገርመኝ የ78 አመቱ አዛውንት አቶ አስፋው ዳምጤ የእግር ጉዞን የሚጠይቁ ታሪካዊ ቦታዎችን ለመጐብኘት ከወጣቶች እኩል፤ ብዙ ጊዜ ግን ቀድመው ሲራመዱ ማየት የትግራይ መስህብ ቦታዎች ምን ያህል ጉጉት ፈጣሪዎች እንደሆኑ ያስረዳል፡፡
ወደፊት እየገሰገስን ነው፡፡ ከፊትለፊታችን ደግሞ የዓለም ጥቁር ህዝቦች ብቻ ሳይሆኑ ራሳቸው ጣሊያኖች በወርቅ ቀለም ብዙ እጅግ ብዙ ቁምነገሮችን የጻፉለት አድዋ ይጠብቀናል፡፡ ጊዜው ግን ከእኛ ፈጥኖ እየተጓዘ ነው፡፡ የአክሱም ከተማ ከንቲባ አቶ አበራም ህዝቡን አሰልፈው እየጠበቁን ነው፡፡ ስለዚህ ዝነኛዋን አድዋን በዝምታ አልፈን፣ ስንመለስ በደንብ ልንጐበኛት ቀጠሮ ይዘን ወደ አክሱም ገሰገስን፡፡
ጉዞ ወደ አክሱም ማለት ደግሞ ወደ ጥንተ ታሪክ፣ ወደ ማንነታችን መፍለቂያ በከፍተኛ ጉጉት መጓዝ ማለት ነው፡፡ በተለያዩ ጽሑፎችና ምስሎች አይተን የምንጓጓላትን አክሱምን ልናያት፣ አይተንም በአግባቡ ልናውቃት ነው፡፡ ግን ጊዜው ከእኛ ጋር እልህ የተጋባ ይመስል ይከልባል፤ እነሆ 1፡30 ሆነ፡፡
እናም የናፈቅናትን አክሱምን ሌባ ይመስል በጨለማ ገባንባት፡፡ ለብዙ ሰዓታት ሲጠብቁን የቆዩት የከተማዋ ባለሥልጣናትና ህዝቡም እስከዚህ ሰዓት ድረስ በከፍተኛ ትዕግስት ሲጠብቁን አምሽተው ነበርና በክብር ተቀበሉን፡፡ ሞቅ ያለ ራት ከጋበዙን በኋላ ወደተያዙልን ሁለት ሆቴሎች አመራን፡፡ በየደረስንበት ቦታ ሁሉ የቅዱስ ጊዮርጊስ ቢራ “እኔም ከጥበብ ተጓዦች ጐን አልለይም” ብሎ ሲከተለን እንደነበር በዚህ አጋጣሚ መግለጽም ማመስገንም እፈልጋለሁ፡፡ አክሱምን ሲነጋ በደንብ እናያታለን፡፡

 

(ሃተን ሙነቅዮ ዴሬ ኢተ ጋደ ጩቸን መነቅዮ ዴሬ ገከውሱ) - የወላይትኛ ተረት

ከእለታት አንድ ቀን አንድ ዛፍ ቆራጭ ከወንዝ ዳር ዛፍ እየቆረጠ ሳለ መጥረቢያው ከእጁ ወጥቶ፣ ግንዱ ላይ ነጥሮ ወንዙ ውስጥ ወደቀበት፡፡ በወንዙ ዳር ቆሞ፣
“አዬ ጉድ! የእንጀራ ገመዴ ተበጠሰ!” እያለ ሲያለቅስ፤ የውሃው አማልክት መልክተኛ ሜርኩሪ ብቅ አለና፤
“ምን ሆነህ ታለቅሳለህ? ለምን አዘንክ?” አለው፡፡
“የሥራ መጥረቢያዬ ወንዝ ውስጥ ገባብኝ” አለው፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃው በዋና ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ወጣ፡፡ ከዚያም፤ “ይሄ መጥረቢያ ያንተ ነውን?” ሲል ጠየቀው፡፡
ዛፍ ቆራጩም፤
“የለም ይሄ የእኔ መጥረቢያ አይደለም” አለና መለሰ፡፡
ሜርኩሪ ለሁለተኛ ጊዜ በዋና ወደ ወንዙ ጠለቀና አንድ ሌላ ከብር የተሰራ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፡፡
“ይሄስ ያንተ ነውን?” አለና ጠየቀው፡፡
“እረ የለም ይሄ የእኔ አይደለም” አለ ዛፍ ቆራጩ፡፡
ሜርኩሪ ለሦስተኛ ጊዜ ወደ ውሃው ጠልቆ ሌላ ተራ መጥረቢያ አወጣ
“ይሄስ?” አለው
ዛፍ ቆራጩ “በትክክል ይሄኛው የእኔ መጥረቢያ ነው!” አለ በከፍተኛ ሐሴት ተውጦ፡፡ “እጅግ አድርጌ አመሰግናለሁ!” አለ፡፡
ሜርኩሪም በጣም ረክቶ፤
“ስለታማኝነትህ እነዚህን ሁለት መጥረቢያዎች - ከወርቅ የተሰራውንና ከብር የተሰራውን፤ ሸልሜሃለሁ!” ብሎ ሰጠው፡፡
ዛፍ ቆራጩ ወደ ሰፈሩ ሲደርስ፤
“ዛሬ ትልቅ ፌሽታ ነው ያጋጠመኝ!” ብሎ የሆነውን ሁሉ ለባልንጀሮቹ ነገራቸው፡፡
ከዛፍ ቆራጮቹ አንዱ ቅናት ይይዘዋል፡፡ ስለዚህ ወደ ወንዙ ሄዶ እሱም እድሉን ለመሞር ይወስናል፡፡
ቀናተኛው ዛፍ ቆራጭ አንድ ከወንዙ ዳር ያለ ዛፍ መቁረጥ ይጀምራል፡፡ ከዚያም አውቆ ወደ ውሃው መጥረቢያውን ይወረውረውና፤
“ወይኔ መጥረቢያዬ! ወይኔ የሥራ መሣሪያዬ!” እያለ ይጮሃል፡፡
ይሄኔ ሜርኩሪ ብቅ አለ፡፡
“ምን ሆነህ ነው የምትጮኸው?”
“መጥረቢያዬ በሥራ ላይ ሳለሁ ውሃ ውስጥ ወደቀብኝ” አለ፡፡
ሜርኩሪ ወደ ውሃ ውስጥ ጠለቀና አንድ የወርቅ መጥረቢያ ይዞ ብቅ አለ፤ ከዚያም
“የጠፋብህ መጥረቢያ…” ብሎ ሊጠይቀው ሲጀምር፤
ዛፍ ቆራጩ በስግብግብነት፤
“አዎን፡፡ የኔ የራሴ መጥረቢያ ነው! የገዛ ራሴ መጥረቢያ ነው!!” አለና ሁለት እጆቹን ዘረጋ፡፡
ሜርኩሪ የማይታመን ሰው በመሆኑ በጣም በመከፋት፤
“አንተ ታማኝ አይደለህም! ስለዚህም እንኳንስ፤ የወርቅ መጥረቢያ ውሃ ውስጥ የጣልከውን የራስህን ተራ መጥረቢያም፣ አታገኝም!” አለው፡፡
***
ታማኝነት የህይወታችን መሰረት መሆን አለት፡፡ ለሥራ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለእውቀት ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለፖለቲካ ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ለኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ ከሁሉ በላይ ደግሞ ለሀገራችንና ለህዝባችን ታማኝ መሆን አለብን፡፡ በሌሎች ላይ ልናደርገው ያሰብነውን ወይም ያደግነውን በራሳችን ላይ ሲሆን የምንሸሽ፣ አሊያም መመሪያ የምናወጣበት ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “ሲያቃጥል በማንኪያ፣ ሲበርድ በእጅ” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡ “እኔ ከሞትኩ ሰርዶ አይብቀል” የምንል ከሆነ ታማኝነት የጐደለው ድርጊት ነው፡፡
ጐር ቫይዳል፤ ምቀኝነትን ሲገልፅ፤ “ጓደኛዬ ሲሳካለት፣ አንድ ነገር ከውስጤ ይሞታል/ይቀንሳል” እንዳለው፤ ጓደኛችን የተሻለ አገኘ ብለን ዐይናችን የሚቀላ ከሆነ ታማኝነት የጐደለው መንፈስ ነው፡፡ “ጐረቤታችን ጫጩት ሲያረባ ስናይ፣ እኛ ሸለምጥማጥ ማርባት የምንጀምር” ከሆነ ፍፁም ታማኝነት የጐደለው የምቀኝነት ድርጊት ነው፡፡ ለእድገት የበቃ ባልደረባችን በደስታ ሲጥለቀለቅ ስናይ እንባ የሚተናነቀን ከሆነ ፈርዶብናል ማለት ነው፡፡ የተያይዘን እንለቅ ፍልስፍና የትም አያደርሰንም - እርግማን ነው፡፡ በሌሎች ደስታ ውስጥ የእኛን ደስታ ለማየት መቻል አለብን፡፡ ደስታችንን ለሌሎች እናጋራ፡፡ ራስ ወዳድነትን እንታገል!
“ደስታን ከራሱ ጋር፣ አጥብቆ ያሰረ
ክንፍ - ያላትን ህይወት፣ ትንፋሽ አሳጠረ፡፡
ደስታ እየከነፈች፣ የሳማት ሰው ግና
የዘለዓለም ፀሀይ ይሞቀዋል ገና”፤ እንዳለው ነው ዊልያም ብሌክ፡፡
ደስታችን የአገር ይሁን እንደማለት ነው፡፡ ደስታ የእኔና የእኔ ብቻ ይሁን ብሎ የሙጥኝ አለማለት ነው፡፡ ከአገር ካዝና የወጣ ደስታ የአገር ነውና ለህዝብ እናዳርሰው፡፡ ለራሳችን ሸሽገን አንቀራመተው ማለት ነው፡፡ የጋራ ቤታችንን እናስብ፡፡ በፓርቲ አጥር አንታጠር፡፡ ደፋር - መሀይም ብቻ ሳይሆን፣ ጭምት - ምሁር የሚኖርባትም አገር እናልም! ዕቡይ - ምሁር ብቻ ሳይሆን ያልተማረ - ጨዋ ህዝብ ያላት አገር እናስብ፡፡ ከፓርቲም ውጪ በቤተሰብ፣ በቢሮ፣ በተቋም፣ በንግድ ድርጅት ውስጥ የሚኖር ነፃ ዜጋ አለ ብለን፣ ከሳጥን ውጪ እንመልከት! ቢያንስ ባስበው ያስበኛል ብሎ ግንዛቤ መውሰድ ያባት ነው፡፡ “የእኔ ወንበር እስካልተነካች ድረስ” የሚል እሳቤ ኃላፊነትን ዘንግቶ አጥር ማጠር፣ ረጅም ጊዜ መኖርን ከዘለዓለማዊነት ጋር ማምታታት ነው (Mistaking Longevity for immortality እንደማለት ነው)፡፡ በዚህም እሳቤ ምክንያት ነው መተካካትን ከብወዛ ጋራ አንድ አድርገን (Mistaking Replacement for Reshuffling እንደማለት) የምናየው፡፡ ወደድንም ጠላንም ቢያንስ ማንም ሰው ሊተካ የሚችል ነው፤ የማይተካ የለም (No one is indespansable) የሚለውን ሁለንተናዊ መርህ ያለራስ ወዳድነት፤ ያለ ምቀኝነት እንቀበል፡፡ ከአጠቃላይ ነባራዊ እውነታው፤ የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር፤ አናመልጥም፡፡ እውነታውን ተቀብሎ መፍትሄውን መሻት ከአላስፈላጊና ከማናመልጥበት ሽሽት ይገላግለናል፡፡ አገርም ለቅቀን እንሽሽ ብንል አይሆንም፡፡ ከራስ የህሊና ቁስል ማምለጥ አይቻልምና፡፡ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ የናዚም ወታደር ይያዛል፤ ተብሏል፡፡ በመሸሽ፣ በመሸሸግና ሌላ አገር በድሎት ከመኖር ጋር ራስን ማስተሳሰር ቢያንስ የዋህነት ነው፡፡ እንኳን በባሌ በቦሌም ምቾት ቅርብ አደለም፡፡ ምቾትና ነፃነትን በሌላ ምድር ማግኘት ቀላል አይደለም፡፡ በሰሜንኛ “ጠላ አገኛለሁ ብለህ ውሃ ረግጠህ አትሂድ” ይባላል፡፡ በወላይትኛ ደግሞ “በውሃ የሚያቦኩበት አገር መጥፎ ነው ብላ፤ በምራቅ የሚያቦኩበት አገር ደረሰች” ማለት ነው፡፡ በማህል አገርኛ “ከድጡ ወደ ማጡ” ብለው ያጠቃልሉት ይሆናል፡፡ ብቻ ከዚህ ይሰውረን!!

 

 

 

የቦይንግ ኩባንያ ዘመናዊ ምርት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ድሪም ላይነር አውሮፕላን (“B787”) ባለፈው አርብ ለንደን ደርሶ ካረፈ በኋላ ጭራው አካባቢ እሳት ተነስቶበት መለብለቡ የሚታወስ ሲሆን፤ የቃጠሎው መነሻ ከሬዲዮ መገናኛ አንቴና ጋር የተያያዘ እንደሆነ በምርመራ ተረጋገጠ፡፡ የእንግሊዝ የአየር አደጋ ምርመራ ክፍል ትናንት ባወጣው ሪፖርት፤ ከአውሮፕላኑ ጭራ አካባቢ የተተከለው አንቴና በመደበኛ በረራ ላይ አገልግሎት የማይሰጥ መጠባበቂያ አንቴና መሆኑን ገልጿል፡፡ የራሱ አነስተኛ ባትሪ ጋር የተገጠሙ አንቴና ላይ በሽቦዎች መጠላለፍ አልያም ባትሪው ላይ በተፈጠረ አንዳች እክል እሳት እንደተፈጠረ የምርመራ ክፍሉ ገልፆ፤ በተጨማሪ ምርመራ ትክክለኛው መንስኤ ከነመፍትሔው እስኪታወቅ ድረስ፣ መጠባበቂያውን አንቴና ለጊዜው በማላቀቅ አውሮፕላኖች ያለ ስጋት መብረር ይችላሉ ብሏል፡፡

አዲሱና ዘመናዊው ድሪም ላይነር (“B787”) ከወራት በፊት በዋናው የባትሪ ማስቀመጫ ቦታ እሳት በመነሳቱ፣ በመላው አለም ሁሉም “B787” አውሮፕላኖች ከበረራ ታግደው መቆየታቸው ይታወሳል፡፡ ባትሪው ላይ የዲዛይን ማሻሻያ ተደርጐ አውሮፕላኖቹ ወደ በረራ ከተመለሱ በኋላ እንደገና ተጨማሪ ችግር መፈጠሩ የቦይንግ ኩባንያን እና እንደ ኢትዮጵያ አየር መንገድ የ (“B787”) ቀዳሚ ተጠቃሚ ደንበኞች በእጅጉ አሳስቧቸው ነበር፡፡ ባለፈው አርብ የተፈጠረው ችግር ለክፉ የሚሰጥ እንዳልሆነ በምርመራ ተረጋግጦ ትናንት በይፋ ከተነገረ ወዲህ፣ የቦይንግ የአክሲዮን ዋጋ ወዲያውኑ እንዳንሰራራ ተገልጿል፡፡