Administrator

Administrator

የኢትዮጵያ መንግስት ከትናንት በስቲያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የተለያዩ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ ሃላፊነት ላይ የሚሰሩ ሰባት ሰራተኞች በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ ገብተዋል በማለት በ72 ሰዓታት ውስጥ አገሪቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙን ተከትሎ፣ አሜሪካ ውሳኔውን “ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው ነው”  ስትል አውግዛለች።
የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ ጄን ሳኪ ትላንት በሰጡት መግለጫ፤ “ያልተጠበቀውን የኢትዮጵያ ውሳኔ የአሜሪካ መንግስት አጥብቆ ይቃወማል” ብለዋል።
በተመሳሳይ፤ በአዲስ አበባ የሚገኙት የእንግሊዝና የጀርመን ኤምባሲዎች፤ ኢትዮጵያ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዟ እንዳሳሰባቸው አስታውቀዋል፡፡
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ፣ ኢትዮጵያ የተመድ ሠራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው፤ በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት እየሞቱ ነው የሚል የማስጠንቀቂያ ሪፖርት ከወጣ በኋላ ነው ሲሉ ከሰዋል፡፡ ቃል አቀባይዋ፤ የኢትዮጵያ መንግሥት፣ የምግብ፣ መድኃኒትና ሌሎች ሕይወት አድን የሰብዓዊ አቅርቦቶች ለሚያስፈልጋቸው ወገኖች እንዳይደርሱ እንቅፋት መሆኑ እጅጉን አሳስቦናል ብለዋል።
“ሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦትን ማደናቀፍ እና የራስን ዜጋ መሠረታዊ አማራጭን ማሳጣት ተቀባይነት እንደሌለው የተባበሩት መንግሥታት የጸጥታው  አባላትና ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ለኢትዮጵያ መንግሥት ግልጽ እንዲያደርጉ ጥሪ እናቀርባለን” ብለዋል።
ፕሬስ ሴክሬታሪዋ ጨምረውም፤ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የተከሰተው ጦርነት እንዲራዘም ምክንያት በሆኑ ግለሰቦች ላይ የፋይናንስ ማዕቀብ መጣል የሚያስችል ትዕዛዝ መፈረማቸውን አስታውሰዋል።
የሰብዓዊ ድጋፍ ሥራዎችን በሚያደናቅፉ አካላት ላይ ፕሬዚዳንቱ ያስተላለፉትን ውሳኔንም ሆነ “በእጃችን ያለ የትኛውንም አማራጭ ከመጠቀም ወደ ኋላ አንልም” ሲሉ አስጠንቅቀዋል፤ የዋይት ሃውስ ፕሬስ ሴክሬተሪ፡፡
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ፣ ኢትዮጵያ የተቋማቸው ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችን ከአገር እንዲወጡ መወሰኗ “አስደንግጦኛል” ሲሉ ከትላንት በስቲያ መግለጻቸው አይዘነጋም፡፡
ዋና ፀሐፊው በመግለጫቸው፤ ሁሉም የተባበሩት መንግሥታት ሰብዓዊ ተግባራት የሚመሩት በሰብዓዊነት፣ከአድልዎ ነጻ በሆነ መንገድ፣በገለልተኛነትና በነጻነት መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህም ድርጅታቸው በኢትዮጵያ በችግር ላይ ላሉ ሰዎች ምግብ፣መድኃኒት፣ ውሃና ንጽሕና መጠበቂያ የመሳሰሉ ሕይወት አድን እርዳታዎችን እያቀረበ ይገኛል ብለዋል።
“የሚመለከታቸው የመንግሥታቱ ድርጅት ሠራተኞች አስፈላጊ ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ከኢትዮጵያ መንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው” ብለው ነበር።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እርምጃውን በተመለከተ ለመንግሥታቱ ድርጅት በጻፈው ደብዳቤ፤ ግለሰቦቹ በአገሪቱ የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባታቸው፣ በ72 ሰዓታት ውስጥ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ መታዘዙን አስታውቋል፡፡
ከኢትዮጵያ በ72 ሰዓታት ውስጥ ከአገር እንዲወጡ የታዘዙት ተከታዮቹ የመንግስታቱ ድርጅት ከፍተኛ የሥራ ሃላፊዎች መሆናቸው ታውቋል፡፡
የተባበሩት መንግሥታት የሕጻናት አድን የኢትዮጵያ ተወካይ አደልኾደር
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ማርሲ ቪጎዳ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ   የጽህፈት ቤቱ የሰላምና ልማት አማካሪ ክሰዌሲ ሳንስኩሎቴ
የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ እርዳታ መስተባበሪያ ጽህፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ሳኢድ ሞሐመድ ሄርሲ
የተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብት ድርጅት የክትትል፣ የሪፖርት እና አድቮኬሲ ቡድን መሪ ሶኒ ኦንዬግቡላ
የተባበሩት መንግሥታ ትድርጅት በኢትዮጵያ ምክትል የሰብዓዊ እርዳታ አስተባባሪ ግራንት ሌኢተይ እና
የተባበሩት መንግሥታት ተጠባባቂ የሰብአዊ እርዳታ አስተባባሪ ጋዳ ኤልታሂር ሙዳዊ
ፕሬስ ሴክረተሬዋ “ኢትዮጵያ የመንግስታቱ ድርጅት ሰራተኞችን ከአገር ለማስወጣት የወሰነችው በሰሜኑ የአገሪቱ ክፍል በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ሳቢያ እየሞቱ ነው የሚል ሪፖርት ከወጣ በኋላ  ነው  ሲሉ ከሰዋል።
በአዲስ አበባ የሚገኙት የእንግሊዝና የጀርመን ኤምባሲዎችም፤ በተመሳሳይ የኢትዮጵያ መንግስት የመንግስታቱ ድርጅት ሠራተኞች ግዛቱን ለቀው እንዲወጡ ማዘዙ እንዳሳሰባቸው በመግለጽ፣ መንግስት እርምጃውን ዳግም እንዲያጤነው ጠይቀዋል።

አዲስ የተመሰረተው የአማራ ክልላዊ መንግስት የቅድሚያ ትኩረቱ ከፌደራል መንግስት ጋር በመሆን የህልውና ዘመቻውን በአጭር ጊዜ  በማጠናቀቅ፣ ዘላቂ ሠላም ማስፈን እንደሚሆን አስታውቋል፡፡
ክልሉን ላለፉት 15 ወራት በርዕሰ መስተዳደርነት ከመሩት አቶ አገኘሁ ተሻገር መንበረ ስልጣኑን የተረከቡት ዶ/ር ይልቃል ከፈለ ስለ መንግስታቸው የትኩረት አቅጣጫዎች ባደረጉት ንግግር፣ የመጀመሪያው ተግባር በትህነግ ወረራ በሃይል የተያዙትን የአማራ መሬቶች በአጭር ጊዜ ውስጥ ማስለቀቅ እንደሚሆን አብራርተዋል፡፡
የዚህ ዘመቻ ፍጻሜም “የጁንታውን” ሃይል  ሙሉ ለሙሉ የሚቀብር እንደሚሆን ይጠበቃል ብለዋል-ርዕሰ መስተዳደሩ፡፡
በጦርነቱ ወቅት የተፈናቀሉ መልሰው እንዲቋቋሙ የማድረግ ተግባር ከህልውና ዘመቻው ጎን ለጎን በትኩረት እንደሚሰራ የተናገሩት ለዚህም የክልሉ መንግስት የድጋፍ ማሰባሰብ እንቅስቃሴዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
የአማራ ክልል በጦርነቱ መጎዳቱንና የልማት እንቅስቃሴዎች መስተጓጎላቸውን ተከትሎም ክልሉ ለ2014 ከመደበው የ80 ቢሊዮን ብር በጀት ውጭ የተጨማሪ በጀት ጥያቄ ለፌደራል መንግስቱ ማቅረቡ የተጠቆመ ሲሆን ተጨማሪው በጀት በጦርነቱ ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች መልሶ ማቋቋሚያ ይሆናል ተብሏል፡፡
አዲሱ የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ዶ/ር ይልቃል ከፈለ የክልሉን የአስር ዓመት መሪ እቅድ ለማሳካት መንግስታቸው በግብርና፣ በስራ እድል ፈጠራ እንዲሁም በመሰረተ ልማት ግንባታዎች ላይ አተኩሮ ይሰራል ብለዋል፡፡
አዲሱ የአማራ አስተዳደር የተቃዋሚ ፓርቲ አብን የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ አቶ ጣሂር መሃመድን የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ሃላፊ እንዲሁም የአማራ ዲሞክራሲያዊ ሃይሎች ንቅናቄ (አዲሀን) ሊቀ መንበር አቶ ተስፋሁን አለምነህን የክልሉ ተፈጥሮ ሃብት ቢሮ ሃላፊ አድርጎ የሾመ ሲሆን የተፊካካሪ         ፓርቲዎች አባላት በመንግስት ውስጥ የማሳተፍ ተግባር በየደረጃው ባሉ የመንግስ መዋቅሮችም ይቀጥላል ተብሏል፡፡

በትግራይ በጦርነት ሳቢያ ከትውልድ ቀያቸው ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 14 በመቶ ያህሉ ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ እንደማይፈልጉ አለማቀፍ ተቋማት በሰራው ጥናት  አመልክቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ድጋፍ ማስተባበሪያ ፅ/ቤት ከትናት በስቲያ ይፋ ባደረገው የጥናት ሪፖርት፤ ከቀየአቸው በተፈናቀሉ ዜጎች ፍላጎት ላይ አተኩሮ በተሰራው ጥናት መሰረት 86 በመቶ የሚሆኑት በቀድሞ ቀዬአቸው ሠላም ከተረጋገጠና በቂ የምግብ አቅርቦት ካገኙ ለመመለስ እንደሚፈልጉ ቀሪዎቹ 11 በመቶ ተፈናቃዮች ግን ወደ ቀድሞ መኖሪያቸው መመለስ እንደማይሹ ገልጸዋል፡፡
በትግራይ በጦርነቱ ሳቢያ ከተፈናቀሉ ዜጎች መካከል 95 በመቶ ያህሉ በአሁኑ ወቅት በእጅጉ የቸገራቸው የምግብ አቅርቦት እጥረት መሆኑን መግለፃቸውን የሚጠቁመው ሪፖርቱ በተጨባጭም ታጣቂዎች መንገድ በየጊዜው በመዘጋታቸው ምክንያት ለምግብ እጥረት ሪፖርቱ አስታውቋል፡፡
በአሁኑ ወቅት ወደ ቀድሞ ቀያቸው መመለስ የሚፈልጉትን ለመመለስ እንዲሁም በሌላ አካባቢ ለመስፈር የሚፈልጉትን ማስፈር ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑም በሪፖርቱ ተካትቷል፡፡
በአጠቃላይ 20 ሺህ ያህል ሰዎችን ሊያሰፍር መቀሌ አካባቢ በሚገኝ ቦታ ላይ 2.727 ሰዎችን በቋሚነት ማስፈር መቻሉንም ተመልክቷል። ከዚሁ ጋር በተያያዘ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊነት ጉዳዮች ሃላፊ ማርቲን ግሪ ፎዝ በትግራይ የከፋ ረሀብ ከመከሰቱ በፊት በሁሉም አቅጣጫ መንገዶች ክፍት ሆነው፣ ያልተቋረጠ የእርዳታ አቅርቦት እንዲኖር ጥሪ አቅርበዋል፡፡

በኢትዮጵያ የጋዜጠኝነት ታሪክ ፈር ቀዳጅ ከሆኑት መካከል አንዱ የነበሩት አንጋፋው ጋዜጠኛ ከበደ አኒሳ ከዚህ ዓለም በሞት ተለዩ፡፡
በአሜሪካ ማካልስተር ኮሌጅ ጋዜጠኝነት የተማሩት አቶ ከበደ፤ ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› እና ‹‹የዛሬይቱ ኢትዮጵያ›› ጋዜጦች ዋና አዘጋጅ እንዲሁም የአሜሪካ ድምፅ (VOA) ሪፖርተር ሆነው ሰርተዋል፡፡ ‹‹The Ethiopian Herald›› ጋዜጣ ላይም ሰርተዋል።
አቶ ከበደ ደርግ ከመመስረቱ ዘጠኝ ዓመታት በፊት፣ በ1957 ዓ.ም፣ “ኢትዮጵያ ትቅደም” የሚለውን  ቃል  በ‹‹የኢትዮጵያ ድምፅ›› ጋዜጣ ላይ መሪ መፈክር አድርገው ያሳተሙ ሰው ነበሩ፡፡   እርሳቸውም ‹‹በጋዜጠኝነቴ  ዘመን የላቀ ደስታ የሰጠኝ ነገር ቢኖር ‹የኢትዮጵያ ድምፅ› ጋዜጣ ላይ መሪ መፈክር አድርጌ ያስቀመጥኩት ‹ኢትዮጵያ ትቅደም› የሚለው ቃል ነው›› ብለው ተናግረው ነበር።
የአቶ ከበደ የሙያ አጋራቸውና ከ35 ዓመታት በላይ የቅርብ ወዳጃቸው የሆኑት አንጋፋው የሮይተርስ (Reuters) ጋዜጠኛ አቶ ፀጋዬ ታደሰ ስለዚህ ጉዳይ በሰጡት ምስክርነት ‹‹በወቅቱ ቀዳማዊ አፄ ኃ/ሥላሴ ‹ኢትዮጵያ ትቅደም ስትል ምን ማለትህ ነው?› ብለው ጠይቀውት ነበር። እሱም ‹ኢትዮጵያን ስለምወድ፣ ሕዝቡንም ስለማከብር ሃገሬ በሁሉ ነገር ቀድማ ማየት ስለምፈልግ ነው› ብሎ መልሷል›› በማለት ተናግረዋል።
አንጋፋው ጋዜጠኛ አቶ ከበደ በዘውዳዊው አገዛዝ ዘመን ማብቂያ ላይ በወሎ ተከስቶ የነበረውን ረሃብ ለእንግሊዛዊው የBBC ጋዜጠኛ ጆናታን ድምቢልቢ በማሳየት ረሀቡ ለዓለም ይፋ እንዲሆን ያደረጉ፤ ሙሉጌታ ሉሌን፣ ብዙ ወንድማገኘሁንና ሌሎች ጋዜጠኞችን ወደ ሙያው እንዲገቡና አርዓያ የሆኑና ለታላቅነት ያበቁ፤ ገብረክርስቶስ ደስታንና ሌሎች ገጣሚያንን እያበረታቱ ለክብርና ለዝና ያደረሱ  እንደሆኑም ይነገርላቸዋል፡፡ የመጀመሪያው የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች ማኅበር ፕሬዝደንትም ነበሩ፡፡
ከጋዜጠኝነት በተጨማሪ በቆጵሮስ እና በእስራኤል የማኅበራዊ ሳይንስ ጥናቶችን ያጠኑት አቶ ከበደ፣ በመምህርነት፣ በትምህርት ቤት ሥራ መሪነት፣ በአገር አስተዳደር ሚኒስቴር እንዲሁም በሕዝባዊ ኑሮ እድገትና ዘመቻ መምሪያ  ለበርካታ ዓመታት አገራቸውን አገልግለዋል።
አቶ ከበደ አኒሳ የተወለዱት ታህሳስ 19 ቀን 1924 ዓ.ም በወለጋ ጠቅላይ ግዛት፣ ነቀምት ከተማ ሲሆን የአንደኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በነቀምት ቀዳማዊ ኃ/ሥላሴ ትምህርት ቤት ካጠናቀቁ በኋላ የሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን ደግሞ በአዲስ አበባ መምህራን ማሰልጠኛ ኮሌጅ ተከታትለዋል።
አቶ ከበደ አኒሳ የዘጠኝ ልጆች አባት ሲሆኑ ስምንት የልጅ ልጆችንም ዐይተዋል።


• በፀጥታ ስጋት ሳቢያ የመስከረም 20 ምርጫ፣ በ3 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 32 ምርጫ ክልሎች አይካሄድም
       • በሱማሌ ክልል ለምርጫ ከሚወዳደሩ 4 ፓርቲዎች 3ቱ ራሳቸውን አግልለዋል
                          በፀጥታ ችግር፣ በመራጮች ምዝገባ ወቅት በታዩ ግድፈቶችና በቀረቡ አቤቱታዎች ምክንያት  ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም 6ኛው አገር አቀፍ ምርጫ ባልተካሄደባቸው  አካባቢዎች፣ መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ሊካሄድ የታቀደው  ቀጣይ ምርጫ፤ በፀጥታ ስጋት ሳቢያ በ3 ክልሎች ውስጥ በሚገኙ 32 የምርጫ ክልሎች ውስጥ አይካሄዱም፡፡
ከኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የተገኘ መረጃ እንደሚያመለክተው፤ የመስከረም 20 ምርጫ በአማራ ክልል፣በኦሮሚያ ክልልና በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል ውስጥ በሚገኙ 32 ከተሞች ውስጥ አይደረግም፣፡፡ እንደ ቦርዱ መረጃ ምርጫ በአማራ ክልል በማጀቴ፣በአርጎባ፣ሸዋሮቢት፣ ኤፌሲዮን፣በጭልጋ አንድና ጭልጋ ሁለት  በአንኮበርና በበላይ አርማጭሆ ምርጫ ክልሎች በፀጥታ ስጋት ሳቢያ የመስከረም 20 ቀን  አገር አቀፍ ምርጫ  አይከናወንም፡፡ ለዚህም በአካባቢው በተከሰተው የፀጥታ ችግር ሳቢያ የመራጮች ምዝገባ ለማካሄድ ባለማቻሉም እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡ በኦሮሚያ ክልል ቤጊ፣ ሰኞ ገበያ፣አያና፣ገሊላ፣አሊቦ፣ጊዳሚና ኮምቦልቻ ምርጫ ክልሎች  ምርጫው አይከናውንም፡፡ በቤኒሻንጉል ጉምዝ ክልል በመተከል፣ሺናሻ ልዩና ካማሺ ምርጫ ክልሎች መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ድምጽ የመስጠት ሂደት አይከናወንባቸውም፡፡
በመስከረም ምርጫ የማይካሄድባቸው አካባቢዎች ቀጣይ እጣ ፈንታ አለመወሰኑንም  የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ የኮሚሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ተናግረዋል፡፡
መስከረም 20ቀን 2014 ዓ.ም በሱማሌ፣በደቡብና በሐረሪ ክልሎች እንደሚከናወን የገለፁት አማካሪዋ፤ ከስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በተጨማሪ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚካሄደው ህዝበ ውሳኔም በዚሁ ቀን እንደሚከናወን ተናግረዋል፡፡ በ965 ምርጫ ጣቢያዎች ለሚከናወነው ህዝበ ውሳኔም 890 ሺ750 መራጮች ተመዝግበዋል ብለዋል፡፡ በሦስቱ ክልሎች ለሚካሄደው ምርጫም በአጠቃላይ ከ7.6 ሚሊዮን በላይ ህዝብ ተመዝግቧል ሲሉም ተናግረዋል፡፡
የሀረሪ ምርጫ ክልልን አስመልክቶ የክልሉ ተወላጆች በስፋት በሚኖሩባቸው አካባቢዎች ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች እንዲቋቋሙ  በተጠየቀው መሰረት በአዲስ አበባ፣በድሬደዋና በኦሮሚያ 17 ልዩ የምርጫ ጣቢያዎች ተቋቁመዋል ብለዋል፡፡ በደቡብ ክልል ቁጫ ወረዳ ላይ ባለው የፀጥታ ችግር ሳቢያ ምርጫው መስከረም 20 እንደማይከናውን ተናግረዋል፡፡
በሱማሌ ክልል በሚካሄደው ምርጫ ተሳታፊ ከነበሩ አራት የፖለቲካ ፓርቲዎች መካከል  ሶስቱ ኢዜማ፣ የኦጋዴን ነፃነት ግንባር (አብንግ) እና የነፃነትና እኩልነት ፓርቲ ራሳቸውን ከምርጫው ማግለላቸውን አስታውቀዋል፡፡ ምርጫ ቦርድ  በበኩሉ፤ ከምርጫው ራሳችንን አግልለናል ካሉት ፓርቲዎች መካከል ስለ ጉዳዩ ለቦርዱ ያላሳወቁ መኖራቸውን ተልጿል፡፡
በክልሉ የሚወዳደሩት ሶስቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች፣ “የቦርዱ ምርጫ አስፈፃሚዎች በክልሉ አስተዳደር ጫና ስር ወድቀዋል፤ አጠቃላይ የምርጫው ሂደት ነፃና ፍትሃዊ አይደለም” በሚል ምክንያት ከምርጫው ራሳቸውን ያገለሉ መሆናቸውንም ገልፀዋል፡፡ በክልሉ የሱማሌ ክልል ብልፅና ፓርቲ ለምርጫ መቅረቡም ታውቋል፡፡
የምርጫ አስፈፃሚዎች የገለልተኝነት ችግር አለባቸው የሚል ቅሬታ ከሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ሲነሳ መቆየቱን የገለፁት የምርጫ ቦርድ የኮሚኒኬሽን አማካሪዋ፤ ቦርዱ ሁሉም ተፎካካሪ ፓርቲዎች ተነጋግረውና ተስማምተው የሚያቀርቧቸውን ምርጫ አስፈፃሚዎች ለመቀበል ዝግጁ ቢሆኑም ፓርቲሪዎች ግን ይህንን ማድረግ አልቻሉም ብለዋል፡፡ ይህ ባልሆነበት ሁኔታ ቦርዱ የሚመድባቸው ምርጫ አስፈፃሚዎች የገለልተኝነት ችግር አለባቸው የሚል ጥያቄ ማንሳት ተገቢነት የለውም ሲሉም ተናግረዋል፡፡
መስከረም 20 ቀን 2014 ዓ.ም በሱማሌ በደቡብና በሀረሪ ክልሎች ለተወካዮች ምክር ቤት በ47 ለክልል ምክር ቤት፣ በ105 ምርጫ ክልሎች ምርጫው ይካሄዳል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

ባለፉት አስር አመታት የህጻናትን የተመጣጠነ ምግብ እጥረት ለመቀነስ የተደረጉ ጥረቶች ምንም አይነት ውጤት አለማስገኘታቸውን የገለጸው ተመድ፤ በማደግ ላይ በሚገኙ የአለማችን ድሃ አገራት ከሚኖሩ ህጻናት መካከል 67 በመቶ ያህሉ ለጤናማ የአካልና አእምሮ እድገት የሚያስፈልጋቸውን በቂ ምግብ እንደማያገኙ አስታውቋል፡፡
በተባበሩት መንግስታት የህጻናት መርጃ ድርጅት ዩኒሴፍ ባለፈው ረቡዕ ይፋ ባደረገው አዲስ ሪፖርት እንዳለው፣ በበርካታ የአለማችን ድሃ አገራት ከ6 ወር እስከ 23 ወር ዕድሜ ክልል ውስጥ ከሚገኙ ህጻናት መካከል ግማሽ ያህሉ በየዕለቱ ማግኘት የሚገባቸውን ዝቅተኛ የምግብ መጠን እያገኙ አይደለም፡፡  
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና የአየር ንብረት ለውጥን ጨምሮ የተለያዩ ችግሮች በ91 የአለማችን አገራት ህጻናት የተመጣጠነ በቂ ምግብ እንዳያገኙና ለመቀንጨር እንዲዳረጉ ሰበብ መሆናቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ ህጻናት በተመጣጠነ ምግብ እጥረት ሳቢያ ትምህርታቸውን ለማቋረጥ እንዲሁም  በቀላሉ ለበሽታ እየተጋለጡና ለመቀንጨር እየተዳረጉ እንደሚገኙም አስታውቋል፡፡

 ባለፈው ቅዳሜ በየመን የሁቲ ታጣቂዎች፣ ፍርድ ቤት በሌሉበት ሞት የተፈረደባቸው የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ ማክሰኞ ዕለት ደግሞ እሳቸው በወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕና በኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣ ላይ የ100 ሚሊዮን ዶላር ክስ መመስረታቸው ተዘግቧል፡፡
ትራምፕ የወንድማቸውን ፍሬድ ትራምፕን ሴት ልጅና ኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጣን የከሰሱት ተንኮል በተሞላበት ሴራ የግል የፋይናንስ መረጃዎቼን ያለ አግባብ በመጎልጎል የታክስ ማጭበርበር እንደፈጸምኩ የሚያስመስልና በሃሰት የሚወነጅል ዘገባ ሰርተው ለንባብ አብቅተዋል፤ 100 ሚሊዮን ዶላር ሊክሱኝ ይገባል በሚል መሆኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የወንድማቸው ልጅ ሜሪ ትራምፕ ባለፈው አመት ባሳተመቺው የግል ማስታወሻ መጽሃፍ ላይ የትራምፕ ቤተሰብ በምን መልኩ ሃብት እንዳፈራ የሚያጋልጡ መረጃዎችን ይፋ ማድረጓን ተከትሎ፣ የቤተሰቡን የግል የፋይናንስ መረጃዎች ለጋዜጣው አሳልፋ ሰጥታለች ተብላ በትራምፕ መከሰሷንና ይህም ለኒውዮርክ ታይምስ ጋዜጠኞች ሰፊ የምርመራ ዘገባ ዋነኛ መነሻ መሆኑን ሮይተርስ አብራርቷል፡፡
የጋዜጣው ሪፖርተሮች ወራትን በፈጀ ምርመራ ያገኙትን ግላዊ መረጃ በማቀነባበር በሰሩት ሰፊ ዘገባ፣ ትራምፕ በተጭበረበረ መንገድ ከአባታቸው ግዙፍ የሪልስቴት ኩባንያ ከ400 ሚሊዮን ዶላር በላይ በታክስ ተመላሽ መልኩ ተቀብለዋል ሲሉ ማጋለጣቸውን የጠቆመው ሮይተርስ፣ ዘገባውን የሰሩት የጋዜጣው ሶስት ሪፖርተሮች በዚህ ስራቸው በ2019 የታዋቂው ፑልቲዘር ሽልማት ተሸላሚ ለመሆን መብቃታቸውንም አስታውሷል፡፡
ትራምፕ ከ100 ሚሊዮን ዶላሩ በተጨማሪ የወንድማቸው ልጅ ካሳተመቺው መጽሃፍ የሚገኘው ገቢ በሙሉ እንዲሰጣቸው ለፍርድ ቤት ባቀረቡት 27 ገጽ ክስ መጠየቃቸውንም ዘገባው አክሎ ገልጧል፡፡
ዶናልድ ትራምፕ በ2018 በተፈጸመው የአየር ጥቃት ከተገደሉት የየመን ሁቲ ከፍተኛ የፖለቲካ ምክር ቤት ሃላፊ ሳልህ አል ሳማድ ግድያ ጋር በተያያዘ በሑቲ ታጣቂዎች ፍርድ ቤት በተመሰረተባቸው ክስ ባለፈው ቅዳሜ ከሳኡዲው ልዑል መሐመድ ቢን ሳልማን ጋር  በሌሉበት ሞት እንደተፈረደባቸው ያስነበበው ቢቢሲ ሲሆን፣ ከእነ ትራምፕ ጋር የተከሰሱ 9 ሰዎች በአደባባይ የሞት ቅጣቱ እንደተፈጸመባቸውና ይህም ውሳኔ ተመድና የአውሮፓ ህብረትን ጨምሮ በበርካታ አገራት መንግስታት ክፉኛ መተቸቱን ለማወቅ ተችሏል፡፡

 የኢንተርኔት ነጻነትን የሚጻረሩ የተለያዩ አፈናዎችና ገደቦች ባለፈው የፈረንጆች አመት 2021 በአለማቀፍ ደረጃ ተባብሶ መቀጠሉንና በአመቱ በ41 አገራት ውስጥ የሚኖሩ ተጠቃሚዎች በኢንተርኔት ባስተላለፏቸው መልዕክቶች ሳቢያ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ከሰሞኑ የወጣ አንድ አለማቀፍ ጥናት አመለከተ፡፡
ፍሪደም ሃውስ የተባለው ተቋም ሰሞኑን ያወጣውን አለማቀፍ የኢንተርኔት ነጻነት ሁኔታ አመላካች ሪፖርት ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን እንደዘገበው፣ መንግስታት በመብት ጥሰቶች መግፋታቸውንና ጥናት ከተደረገባቸው 70 የአለማችን አገራት መካከል በ56ቱ ከኢንተርኔት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ ዜጎች መታሰራቸውንና መከሰሳቸውን ለማረጋገጥ ተችሏል፡፡
የኢንተርኔት መብቶች ጥሰት ዘንድሮም በአለማቀፍ ደረጃ ለ11ኛ ተከታታይ አመት ተባብሶ መቀጠሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ ተጠቃሚዎችን በተለያዩ መንገዶች የሚያፍኑና ለእስር የሚዳርጉ መንግስታት ቁጥር መበራከታቸውንና በአንጻሩ ደግሞ በኢንተርኔት የሚሰራጩ የተሳሳቱ መረጃዎች መበራከታቸውንም አክሎ ገልጧል፡፡
በአመቱ 20 የተለያዩ የአለማችን አገራት የኢንተርኔት አገልግሎትን ማቋረጣቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፣ 20 ያህል መንግስታት ደግሞ የማህበራዊ ድረገጾችን መዝጋታቸውን አስታውሷል፡፡
በአመቱ ከአለማችን አገራት መካከል እጅግ የከፋ የኢንተርኔት አፈና የታየባት ቀዳሚዋ አገር ተብላ በሪፖርቱ የተጠቀሰችው ቻይና ስትሆን፣ የኢንተርኔት አፈና በከፍተኛ ሁኔታ የተባባሰባቸው ተብለው የተጠቀሱት ቀዳሚዎቹ ሶስት የአለማችን አገራት ደግሞ ማይንማር፣ ቤላሩስና ኡጋንዳ ናቸው፡፡


 የአለማችን 2ኛው ግዙፍ የሞባይል አምራች ኩባንያ የሆነው የአሜሪካው አፕል ከተመሰረተ ጊዜ ጀምሮ ለገበያ ያቀረባቸው የአይፎን ስማርት ስልኮች ቁጥር ከ2 ቢሊዮን ማለፉን አንድ ዘገባ አመልክቷል፡፡
በመላው አለም ስማርት ስልኮችን ከሚጠቀሙ 3.8 ቢሊዮን ያህል ሰዎች መካከል 26 በመቶ ያህሉ የአይፎን ተጠቃሚዎች መሆናቸውን የዘገበው ዳብሊውሲሲኤፍቴክ የተባለ ድረገጽ፣ በአሜሪካ 60 በመቶ ያህል የስማርት ስልኮች ተጠቃሚዎች አይፎን እንደሚጠቀሙም አመልክቷል፡፡
አፕል በተለይ በቅርቡ ያወጣው አዲሱ ምርቱ አይፎን 13፤ ከዚህ ቀደም ያልነበሩ በርካታ አዳዲስ ቴክኖሎጂዎችን ያካተተ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሽያጩ ያድጋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተነግሯል፡፡


 ሶስት ጊዜ የእድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በፈረንሳይ በእስር ላይ የሚገኘውና ከአለማችን ጨካኝ ወንጀለኞች አንዱ እንደሆነ የሚነገርለት ቬንዙዌላዊው የ71 አመት ገዳይ ካርሎስ ቀበሮው፣ ከሰሞኑ በፈረንሳይ ለሚገኝ ፍርድ ቤት ባቀረበው አቤቱታ የእስራት ዘመኑ እንዲቀነስለት መማጸኑን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
ካርሎስ ቀበሮው በሚል ስሙ የሚታወቀውና እ.ኤ.አ በ1974 በፓሪስ በሚገኝ የገበያ ማዕከል በፈጸመው ጥቃት ከ4 አመታት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት ተፈርዶበት በእስር ላይ የሚገኘው ኢሊች ራሚሬዝ ሳንቼዝ፣ ባለፈው ረቡዕ ለፍርድ ቤት ባስገባው ማመልከቻ እስሩ እንዲቀንስለት መማጸኑን ዘገባው አመልክቷል፡፡
ከአራት አመታት በፊት የዕድሜ ልክ እስራት በተፈረደበት ችሎት ላይ ሲቀርብ የሙያ መስክህ ምንድን ነው በሚል ከችሎቱ ለቀረበለት ጥያቄ፣ ብቁ አብዮተኛ ሲል ምላሽ መስጠቱን ያስታወሰው ዘገባው፣ ዕድሜውን ሲጠየቅም 17 ነው፤ ደስ ካላችሁ 50 አመት ጨምሩበት ሲል ማላገጡን አስነብቧል፡፡
ከ27 አመታት በፊት በፈረንሳይ ልዩ ሃይል ክትትል በካርቱም በቁጥጥር ስር የዋለው ቬንዙዋላዊው አደገኛ ገዳይ ካርሎስ፤ በ1970 ዎቹ እና 80 ዎቹ በፈጸማቸውና ባስፈጸማቸው በርካታ የግድያ ወንጀሎች ለሶስት ጊዜያት የእድሜ ልክ እስራት እንደተፈረደበትና ከዚያ ጊዜ አንስቶ በፈረንሳይ በእስር ላይ እንደሚገኝም ዘገባው አስታውሷል፡፡


Page 8 of 555