Administrator

Administrator

ከሳምንት በኋላ በሚጀመረው ቢግ ብራዘር አፍሪካ ላይ ኢትዮጵያ እንደምትሳተፍ የታወቀ ሲሆን የውድድሩ አሸናፊ 300ሺ ዶላር ይሸለማል ተባለ፡፡ “ዘ ቼስ” በሚል ልዩ ስያሜ በሚደረገው የአፍሪካ ትልቁ የሪያሊቲ ሾው ውድድር ላይ ከ14 አገራት የተውጣጡ 28 ተሳታፊዎች ለ91 ቀናት አብረው ለመኖር ተዘጋጅተዋል፡፡ ባለፈው ዓመት ተሳታፊ ያልወከለችው ኢትዮጵያ ዘንድሮ በውድድሩ ውስጥ የገባች ሲሆን አንጎላ፤ ቦትስዋና፤ ጋና፤ ማላዊ፤ ናሚቢያ፤ ናይጄርያ፤ ኬንያ፤ ሴራሊዮን፤ ደቡብ አፍሪካ፤ ኡጋንዳ፤ ታንዛኒያ፤ ዛምቢያ እና ዚምባቡዌም ይሳተፋሉ፡፡

በቀን ለ24 ሰዓታት በሳምንት ለ7 ቀን በዲኤስቲቪ ሁለት ቻናሎች በቀጥታ በሚሰራጨው አብሮ የመኖር ውድድር ላይ እስከመጨረሻው ቀን በመቆየት የሚያሸንፈው ነዋሪ፤ የ300ሺ ዶላር ሽልማት ይጠብቀዋል፡፡ የቢግ ብራዘር አፍሪካ 8 ሙሉ ቀረፃ በደቡብ አፍሪካ የሚከናወን ሲሆን የሚሰራው እና የሚያዘጋጀው አፍሪካ ማጂክ ኢንተርቴይመንት ከደቡብ አፍሪካው ኩባንያ ኤንዴሞል ጋር በመተባበር ነው፡፡ ከሶስት ዓመት በፊት ኢትዮጵያዊው የአመራር ባለሙያ ያዕቆብ አቤሴሎም፤ በቢግ ብራዘር አፍሪካ ተሳትፎ 15ኛ ደረጃ ያገኘ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት የህግ ባለሙያዋ ሃና መኩርያ እና የማርኬቲንግ ባለሙያው ዳንኤል ተሳትፈው በተለይ ሃና እስከመጨረሻው የውድድሩ ምእራፍ መጓዟ ይታወሳል፡፡

በመላው ዓለም ለእይታ ከበቃ ሁለት ሳምንት የሆነው “አይረን ማን 3” እስካሁን 980 ሚሊዮን ብር ገቢ በማስገባት ዘንድሮ ለእይታ ከበቁ ፊልሞች ብቸኛው ሊሆን በቃ፡፡ ፊልሙ ከምረቃው በኋላ በሁለት ሳምንት ጊዜ ውስጥ በመላው ዓለም በ40 አገራት ለእይታ በቅቶ ነው አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊደርስ የተቃረበ ገቢ በማስገባት ሪከርድ ያስመዘገበው፡፡ በቻይና በመጀመርያ ቀኑ 21.5 ሚሊዮን ዶላር በማስገኘትም ሌላ ሪከርድ አስመዝግቧል፡፡ በአይማክስ የፊልም ፎርማት በመላው ዓለም 40 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያስገባው ፊልሙ በዚህም ሌላ ክብረወሰን ይዟል፡፡ በሰሜን አሜሪካ ብቻ በ15 ቀን ውስጥ 295 ሚሊዮን ዶላር ማስገባትም ችሏል፡፡

በሌላ በኩል “አይረን ማን 3” ላይ በመሪ ተዋናይነት የሰራው ሮበርት ዳውኒ ጁኒዬር፤ የፊልሙን አራተኛ እና አምስተኛ ክፍሎች ለመስራት በ100 ሚሊዮን ዶላር ክፍያ መስማማቱ በሆሊውድ የተዋናዮች ክፍያ ታሪክ የመጀመርያው አድርጎታል፡፡ ሮበርት ዳውኒ፤ በሶስቱ የአይረን ማን ፊልሞች 50 ሚሊዮን ዶላር ገቢ አግኝቷል፡፡ ተዋናዩ በአይረን ማን ፊልሞች ላይ ቶኒ ስታርክ የተባለ እና በጦር ኢንዱስትሪ ባለሙያነት በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በሰራው ብረት ለበስ ወታደር፤ ዓለም አቀፍ ወንጀለኞችን በመወጋት የሚንቀሳቀስ ገፀባህርይን ይተውናል፡፡ በ“አይረን ማን 3” ላይ ከሮበርት ዳውኒ ጋር የሚሰሩት ሌሎች ምርጥ ተዋናዮች ጅዌኔትዝ ፓልትሮው፤ ዶን ቺድል፤ ጋሪ ፒርስ እና ሬቤካ ሆል ናቸው፡፡ የፊልም ኢንዱስትሪው ባለሙያዎች፤ በ200 ሚሊዮን ዶላር በጀት የተሰራው “አይረን ማን 3” ፤ በመላው ዓለም 1.15 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በማስገባት ትርፋማ እንደሚሆን ተንብየዋል፡፡ የመጀመርያው “አየረን ማን” ፊልም፤ 585.2 ሚሊዮን ዶላር እንዲሁም “አየረን ማን 2” 623.9 ሚሊዮን ዶላር ገቢ ያገኙ ሲሆን ሶስተኛው ከወጣ ከሁለት ሳምንት በኋላ የአየረን ማን ፊልሞች ገቢ 2.19 ቢሊዮን ዶላር ደርሷል፡፡

በ“ፋስት ኤንድ ፊርዬስ” ተከታታይ ፊልሞች ዓለም አቀፍ ዝናን ያተረፈው ተዋናይ ቪን ዲዝል፤ የፌስቡክ ድረገፅን ተወዳጅ በማድረጌ ኩባንያው አንድ ቢሊዮን ዶላር ሊከፍለኝ ይገባል አለ፡፡ በፌስ ቡክ ድረገፅ 48 ሚሊዮን ወዳጆችን ያፈራው ተዋናዩ፤ የፌስቡክን ተወዳጅነት በመጨመር የሚስተካከለኝ የለም ሲል ለ“ኢንተርቴይመንት ዊክሊ” ተናግሯል፡፡ ከአራት ዓመት በፊት የፌስቡክ ድረገፁን እንደከፈተ አንድ ሚሊዮን የሚደርሱ ወዳጆችን በማፍራት ሊፎካከሩት የቻሉት የአሜሪካው ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ ብቻ እንደነበሩ ያስታወሰው ቪን ዲዝል፤ ከአድናቂዎቹ ጋር በማህበራዊ ድረገፀ መነጋገር በመጀመሩ በተወዳጅነት በዓለም አንደኛ የፌስ ቡክ አድራሻ ይዞ መቆየቱን አብራርቷል፡፡ ተዋናዩ ባለፉት አራት ዓመታት በፌስቡክ ገፁ ከ11 በላይ የፎቶ አልበሞች እና 40 የቪድዮ ምስሎችን በማጋራት ወዳጆቹን ሲያስደስት ቆይቷል፡፡ በአክሽን ፊልሞቹ የሚታወቀው ቪን ዲዝል፤ በ19 ፊልሞች ላይ በመሪ ተዋናይነት፤ በረዳት ተዋናይነት፤ በአዘጋጅነት እና በተባባሪ አዘጋጅነት የሰራ ሲሆን በአጠቃላይ 2.8 ቢሊዮን ዶላር ገቢ አስገኝቷል፡፡

በኢትዮጵያ ብሔረሰቦች የሐዘን ሥርአት ላይ ያተኮረ የሥዕል አውደርእይ ዛሬ እንደሚቀርብ አዘጋጆቹ አስታወቁ፡፡ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የአለ የሥነ ጥበብና ዲዛይን ትምህርት ቤት የሚቀርበውን የአንድ ቀን የኢንስታሌሽን ሥእሎች የሚቀርቡበት አውደርእይ ያዘጋጁት ትምህርት ቤቱ እና ኑሮዋን ኖርዌይ ባደረገችው ኢትዮጵያዊት ሠዐሊ ማህሌት ኦግቤ ሀብቴ ከሌሎች ሠዐሊያን ጋር በመተባበር ነው፡፡ ዝግጅቱ በዳንስ እና ሌሎች ኪነጥበባዊ ግብአቶች ታጅቦ ዛሬ ከቀኑ 11 ሰዓት እንደሚቀርብ የዝግጅቱ ፕሮዳክሽን ማናጀር መሠረት ኃይሌ በተለይ ለአዲስ አድማስ ገልፀዋል፡፡

የኢትዮጵያዊው ሊቅ ቅዱስ ያሬድን 1500ኛ ዓመት ልደት የተመለከተ አውደጥናት ዛሬ እንደሚካሄድ በኢትዮጽያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስትያን ሰንበት ትምህርት ቤቶች ማደራጃ መምርያ ማህበረ ቅዱሳን አስታወቀ፡፡ ዛሬ ከጧቱ 2፡30 እስከ 11፡30 በግዮን ሆቴል በሚደረገው የአንድ ቀን አውደጥናት የቅዱስ ያሬድ ልደትና የምናኔ ሕይወት፣ ዜማና ድርሰት፣ የቅዱስ ያሬድ ድርሳናት ከነገረ መለኮት አንፃር፣ የቅዱስ ያሬድ ዜማ ተፅእኖ በባህላዊና ዘመናዊ ሙዚቃ የሚሉ ርእሶች ለውይይት ይቀርባሉ፡፡ ከዚህ በተያያዘም ነገ ከቀኑ 7 እስከ 11 ሰዓት የቅዱስ ያሬድ ልደትን የተመለከተ ሲምፖዚየም በኢትዮጵያ የስብሰባ ማእከል መዘጋጀቱን ማህበሩ አስታውቋል፡፡

የፋሽስት ኢጣሊያን ወረራ በመቃወም በ1928 ሐምሌ 22 ሰማእት የሆኑትን ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ጴጥሮስን ተንተርሶ በደራሲ ፀሐይ መልአኩ የተፃፈው ረዥም ልቦለድ መጽሐፍ ምርቃት በአንድ ሳምንት ተራዘመ፡፡ ግንቦት 11 ቀን 2005 ዓ.ም ከጧቱ 2፡30 ትያትር ቤቱ ሊመረቅ የነበረው መጽሐፍ ምርቃት ወደ ግንቦት 18 ቀን ተላልፏል፡፡ ደራሲ ፀሐይ መልአኩ ካሁን ቀደም “ቋሳ”፣ “አንጉዝ”፣ “እመምኔት”፣ “ቢስ ራሄል”፣ እና “የንስሐ ሸንጎ” በተሰኙት የረዥም ልቦለድ መፃሕፍቷ እንዲሁም “የስሜት ትኩሳት” ቁጥር ፩ እና ፪ የግጥም መጻሕፍቷ ትታወቃለች፡

ገነት ንጋቱ የኪነጥበበ ፕሮሞሽን እና ፊልም ፕሮዳክሽን በደራሲና አዘጋጅ ገነት ንጋቱ የተሰራውን “ሐማርሻ” ፊልም እንደሚያስመርቅ አስታወቀ። ድርጊታዊ የሆነው የ95 ደቂቃ የቤተሰብ ፊልም ተሠርቶ እስኪጠናቀቅ አንድ ዓመት ወስዷል፡፡ ግንቦት 18 በአዲስ አበባ የግል ሲኒማ ቤቶች በማግስቱ ግንቦት 19 ከምሽቱ 11 ሰዓት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ትያትር በሚመረቀው ፊልም ላይ ገነት ንጋቱ፣ ተዘራ ለማ፣ ካሌብ አርአያስላሴ፣ ዘላለም ይታገሡ፣ ምስራቅ ታዬ እና ሌሎችም ተውነዋል፡፡

በዮሐንስ ሞላ የተደረሱ ሰባ ሁለት ግጥሞች የተካተቱበት “የብርሐን ልክፍት” የግጥም መጽሐፍ ከትናንት ወዲያ ተመረቀ፡፡ ከቀኑ 11 ሰዓት በዋቢ ሸበሌ ሆቴል የተመረቀው ባለ 107 ገፅ መጽሐፍ ለሀገር ውስጥ ገበያ በ28 ብር ለውጭ ሀገራት ደግሞ በ18 ዶላር ለገበያ ቀርቧል፡፡

ዱም ሚዲያና ፕሮሞሽን ወርሃዊ የሥነ ጽሑፍ ምሽቱን ትናንት አቀረበ፡፡ ከምሽቱ 11 ሰዓት “ብእር በዜማ” በሚል ርእስ በአምባሳደር መናፈሻ የቀረበው ወርሃዊ የሥነጽሑፍ ምሽት በከረምቤ ባሕላዊ የሙዚቃ ቡድን ጣእመዜማዎች የታጀበ ነው፡፡ በምሽቱ አልአዛር ሳሙኤል፣ ምልዕቲ ኪሮስ፣ ሰለሞን ሰሀለ፣ ሰናይት አበራ፣ ገነት አለባቸው፣ አንዱዓለም አሰፋ፣ እንድርያስ ተረፈ እና ሌሎች የሥነጽሑፍ ሥራዎቻቸውን አቅርበዋል፡፡

‹መለስ ዋንጫ› በሚል መታሰቢያ በሚደረገው የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ደደቢት ለመጀመርያ የሻምፒዮናነት ክብሩ እየገሰገሰ ነው፡፡ ደደቢት ፕሪሚዬር ሊግን መሳተፍ ከጀመረ ዘንድሮ ገና በአራተኛው የውድድር ዘመኑ ላይ ቢሆንም ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በዋንጫ ተፎካካሪነት በደረጃ ውስጥ ቆይቷል፡፡ ሊጠናቀቅ ከ2ወር ያነሰ እድሜ በቀረውና 14 ክለቦችን በሚያሳትፈው ሊግ ደደቢት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች 43 ነጥብ እና 23 የግብ ክፍያ በመያዝ ይመራል፡፡ ከተመሰረተ 16ኛ ዓመቱን የያዘው ደደቢት ባለፈው የውድድር ዘመን በሊጉ ሁለተኛ ደረጃ ይዞ ያጠናቀቀ ሲሆን ዘንድሮ በአፍሪካ ኮንፌደሬሽን ካፕ ተሳታፊ ሆኖ እስከ ሁለተኛ ዙር መገስገስ የቻለ ነው፡፡ ደደቢት በውድድር ዘመኑ እስከ ባለፈው ሳምንት ባደረጋቸው 20 ጨዋታዎች በ13 ሲያሸንፍ፤ በአራት አቻ ተለያይቶ እና በ3 ተሸንፎ በተጋጣሚዎቹ ላይ 43 ጎሎችን አስቆጥሯል፡፡

ታዳጊ ህፃናትን በማሰልጠን ከ16 ዓመት በፊት የተጀመረው ክለቡ ገና በወጣትነት እድሜው በኢትዮጵያ እግር ኳስ ጉልህ አስተዋፅኦ ማበርከቱ ሲታወቅ በቀጣይ የውድድር ዘመን በኩባንያ ደረጃ ራሱን ችሎ ለመንቀሳቀስ እየሰራ እንደሆነ ይታወቃል፡፡ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ውስጥ የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒየንስ ሊግ ዋንጫን አሸንፎ በዓለም ክለቦች ዋንጫ ላይ አፍሪካን ለመወከል ራእይ የያዘው ደደቢት በኢትዮጵያ ክለቦች ከፍተኛ ውድድር ባለፉት ሶስት የውድድር ዘመናት በሻምፒዮናነት ፉክክር ከሚጠቀሱት 3 ክለቦች አንዱ ሲሆን ለወቅቱ የኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን እስከ 9 ተጨዋቾች በማስመረጥም ግንባር ቀደሙ ነው፡፡ በ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ኢትዮጵያ ቡና በ37 ነጥብ እና በ17 የግብ ክፍያ 2ኛ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በ34 ነጥብ እና 10 የግብ ክፍያ እንዲሁም ሃዋሳ ከነማ በ33 ነጥብና በ8 የግብ ክፍያ 3ኛ እና 4ኛ ደረጃን አከታትለው ይዘዋል፡፡

ኢትዮፉትቦል ድረገፅ በዘንድሮው ውድድር ማን ሻምፒዮን ሊሆን ይችላል በሚል ከ13521 አንባቢዎቹ በሰበሰበው ድምፅ ኢትዮጵያ ቡና 60.79 በመቶ ድርሻ በመያዝ የመጀመርያውን ግምት ሲወስድ፤ ጊዮርጊስ በ27 በመቶ፤ መብራት ሃይል በ7.2 በመቶ፤ አርባምንጭ በ2.66 በመቶ እንዲሁም ደደቢት በ1.83 በመቶ የድምፅ ድርሻ በተከታታይ ደረጃ የሻምፒዮናነት ግምት ወስደዋል፡፡ ደደቢት በቀሪ የሊግ ጨዋታዎች ያለሽንፈት መጓዙ በታሪክ የመጀመርያውን የሻምፒዮንነት ዋንጫ የሚያነሳበትን እድል ይፈጥርለታል፡፡ በኢትዮጵያ ከፍተኛው የክለቦች ውድድር በፕሪሚዬር ሊግ ደረጃ መካሄድ ከጀመረ ዘንድሮ 66ኛ ዓመቱን የያዘ ሲሆን 16 ክለቦች የሻምፒዮናነት ክብር አጣጥመዋል፡፡

ከእነዚህ ክለቦች ለ25 ጊዜ ሻምፒዮን በመሆን የከፍተኛ ውጤት ክብረወሰን የያዘው ቅዱስ ጊዮርጊስ ነው፡፡ የቀድሞው መቻል ክለብ በ11 ጊዜ ሻምፒዮናነት ሁለተኛ ደረጃ ሲይዝ፤ ጥጥ 5 ጊዜ፤ የአስመራው ሃማሴን 4 ጊዜ፤ መብራት ኃይልና ቴሌ 3 ጊዜ እንዲሁም ኢትዮጵያ ቡና፤ ሲምንቶ እና ሃዋሳ ከነማ እያንዳንዳቸው ሁለት ጊዜ የኢትዮጵያ ሊግ ውድድር ሻምፒዮን በመሆን ከ3 እስከ 6 ያለውን የውጤታማነት ደረጃ ይዘዋል፡፡ በፕሪሚዬር ሊጉ ታሪክ እያንዳንዳቸው አንድ ጊዜ ሻምፒዮን ለመሆን የበቁ ሰባት ክለቦች የሚጠቀሱ ሲሆን እነሱም የብሪቲሽ ሚሊታሪ ሚሽን፤ ርምጃችን፤ ቀይባህር፤ ምድር ባቡር፤ ኦጋዴን አንበሳ፤ ኦሜድላ እና ትግል ፍሬ ናቸው፡፡ ደደቢት የዘንድሮውን ፕሪሚዬር ሊግ ሻምፒዮናነት ከወሰደ የኢትዮጵያ ሊግ ሻምፒዮን ለመሆን 17ኛው ክለብ አንዴ ሻምፒዮን ከሆኑ ክለቦች ደግሞ ስምንተኛው ይሆናል፡፡ የ2005 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚዬር ሊግ ‹መለስ ዋንጫ› ላይ በወራጅ ቀጠና አራት ክለቦች ይገኛሉ፡፡ በ4 ነጥብና በ35 የግብ እዳ 14ኛውንና የመጨረሻውን ደረጃ የያዘው ውሃ ስራዎች መውረዱ ሲረጋገጥ፤ 11 ነጥብ እና 17 የግብ እዳ አስመዝግቦ በ13ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አዳማ ከነማም አጣብቂኝ ውስጥ ነው፡፡ ሃረር ቢራ በ19 ነጥብ እና በ11 የግብ እዳ 11ኛ፤ ሙገር በ17 ነጥብ በ12 የግብ እዳ 12ኛ ደረጃ ላይ በመሆን በወራጅ ቀጠናው እየዳከሩ ናቸው፡፡