Administrator

Administrator

    ታዋቂው የቪዲዮ ማሰራጫ ድረገጽ ዩቲዩብ ባለፉት 12 ወራት ብቻ ከሙዚቃው ኢንዱስትሪ ጋር በተያያዘ ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ ክፍያ መፈጸሙን ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል፡፡
በአልፋቤት ኩባንያ ስር የሚገኘው ዩቲዩብ በ2020 የፈረንጆች አመት፣ ከማስታወቂያ 19.78 ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ ማግኘቱን ከሰሞኑ ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህም ውስጥ 20 በመቶ ያህሉን ወይም ከ4 ቢሊዮን ዶላር በላይ የሚሆነውን የተለያዩ ሙዚቃዎችን ላስተላለፈላቸው ሙዚቀኞች፣ የሙዚቃ ደራሲዎች፣ የሙዚቃ ፈጠራ መብት ባለቤቶችና በኢንዱስትሪው ውስጥ ለሚገኙ አካላት መክፈሉን ገልጧል፡፡
በሙዚቃ ስራዎቻቸው ክፍያ የሚፈጽምላቸው ደንበኞቹ ቁጥር በ2021 የመጀመሪያው ሩብ አመት በከፍተኛ ሁኔታ መጨመሩን ያስታወቀው ዩቲዩብ፤ እ.ኤ.አ ከ2019 አንስቶ ለሙዚቃው ኢንዱስትሪ በድምሩ 3 ቢሊዮን ዶላር ያህል መክፈሉንም አስታውሷል፡፡

      ላለፉት 12 ተከታታይ ወራት ጭማሪ ሲያሳይ የቆየው አለማቀፉ የምግብ ዋጋ፤ በግንቦት ወር ባለፉት 10 አመታት ከታየው ሁሉ ከፍተኛ ነው የተባለውን የ40 በመቶ ጭማሪ ማሳየቱን ተመድ አስታውቋል፡፡
የአለም የምግብ ድርጅት ከሰሞኑ ይፋ ያደረገውን አለማቀፍ ሪፖርት ጠቅሶ ብሉምበርግ እንደዘገበው፣ ባለፉት 12 ወራት በሁሉም የምግብ አይነቶች ዋጋ ላይ ከፍተኛ ጭማሪ የተመዘገበ ሲሆን፣ በአመቱ የታየው የምግብ ዋጋ ጭማሪ እ.ኤ.አ በ2008 እና 2011 የተከሰቱትንና ከ30 በላይ በሚሆኑ አገራት ህዝባዊ ተቃውሞዎችን የቀሰቀሱ የምግብ ዋጋ ጭማሪዎችን የሚያስታውስ ነው ተብሏል፡፡
ድርቅና የዝናብ እጥረት በተለያዩ የአለማችን አገራት በቆሎና ቡናን በመሳሰሉ ምርቶች አቅርቦት ላይ ከፍተኛ ጭማሪ ማስከተሉን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ የእንስሳት ተዋጽኦዎች እንዲሁም የአትክልቶችና የቅባት እህሎች ምርትም በአለማቀፍ ደረጃ ቅናሽ ማሳየቱንና ይህም ለዋጋ ጭማሪ ሰበብ መሆኑን አመልክቷል፡፡

Saturday, 05 June 2021 13:34

ዝክረ አብደላ እዝራ

  ሰው በሀገር ይወለዳል ይባላል። ግን ደግሞሀገርን የሚወልዱ ሰዎች አሉ።አብደላ እዝራ ጥበብና ፍቅር የተቃቀፉበት ሀገር በውስጡ ተሸክሟል።አብሮም ኖሯል። የምናውቀው በተባ ብዕሩ፣በሰላ ሂሱ፣ስለ ጥበብ ሲል ሁሉንምበሚተው ኪናዊ ፍቅሩ ነው። የአንጋፋ ደራስያንን ሥራፈትኗል፤የረገበውን የሀገር ጥበብ ቆንጠጥ አድርጎ
በከፍታ አጉልቶ ለማሳየት። ጠቢባን የሚያደንቁ ውብዓረፍተ ነገሮችን ዘክሯል። እምቡጥ አበቦቹን ወጣትደራሲያንን በሚሳሳ እጁ ኮትኩቷል። ቸርነቱ በጥበብም
በቁስም ነው። አብደላ እዝራ ጭው ባለ በረሃ ውስጥ ዕድሜውን ሙሉ ለጥበብ ንጽህና እንደ ምንጭ የፈሰሰ ጅረት ነበር! በፈረሰው ቅጥር -----የቆመ የጥበብ ዘብ!!
አዲስ አድማስ ጋዜጣ
ግንቦት 28 ቀን 2013 ዓ.ም የአብደላ ዕዝራ  የ5ኛ ሙት ዓመት መታሰቢያSunday, 06 June 2021 00:00

በድንጋይና በካቴና

    በዚያ ሰሞን አቦይ ስብሃት ነጋ በመከላከያ ሰዎች ታጅበው፣ እጃቸው በካቴና ታስሮ የሚያሳየው  ፎቶግራፍ፣ በማኅበራዊ ሚዲያ ተለቅቆ ዋና መነጋገሪያ ሆኖ ነበር፡፡ ፎቷቸው እውነተኛ ማንነታችንን ያሳየን ይሆን? የፍትህ አምላክና የሕግ የበላይነት ጨርሶ እንዳልጠፉ ያስታውሰን ይሆን? ሰዎች ስንባል ከንቱነት የሚያጅበን ፍጡራን ነን። የህወሓት መሥራቹ አቦይ ስብሃት፣ እርጅናቸው በዚህ መልኩ ይቋጫል ብሎ ያሰበ መኖሩ ያጠራጥራል፤ እርሳቸውማ ገና ለልጃቸው መንግሥት ይመኙ ነበር… መንግሥት ግን የእግዚአብሔር ነች!
ከዚህ ምን እንማራለን?  ወይስ በሰው ውርደት ጣት እንቀስራለን? በሰው ውርደት መጨፈር የተጀመረው፣ ደርግ በቀየሰው የመደብ ቅራኔ ዘመን ነው። ያ ቅራኔ በህወሓት ዘረኛ ፖለቲካ ተባብሶ መደበኛ የሆነ ይመስላል! ፈሪሃ እግዚአብሔርና የሰው አክብሮት ልታስተምር የተገባት ቤተ ክርስቲያን፣ ከአናት እስከ ጅራት ተበክላለች! ትምህርት ቤቶች፣ ለዝንጀሮና ለዘር ተረት ተረት መደናቆሪያ ከዋሉ ሁለት ትውልድ አሳልፈዋል። እነዚህ ተቋማት ሳይቃኑ እንደ አገር የትም አንደርስም! ጥያቄው ይህ ነው፦ መሪዎቻችን፣ ያፈቀዳቸውን አድርገው አንጠየቅም የሚሉን እስከ መቼ ነው? እኛስ እስከ መቼ ነው ድልድይ ከማነጽ ይልቅ  የምናፈርስ?
መሪ ለመሆን የሚሹ፣ በድንጋይና በካቴና ተሸላልመው ቃለ መሓላ እንዲፈጽሙ ቢደረግ፣ እንደ ሕዝብ ከመገዳደል ይልቅ መደራደር፣አዋርዶ ከመዋረድ ይልቅ መከባበር እንጀምር ይሆን? ድንጋይ፣ የሕዝብን አደራ ስለ መሸከም። ካቴናው ካቴና ነው!
ሦስት ተኲል መንግሥት ያዩ ጥቂት ሚሊዮን ዜጎች ዛሬም በሕይወት አሉ። በስድሳ ስድስት፦ እውነት በመስቀል አይሁን፤ በማጭድና በመዶሻ፣ በምንሽርና ባካፋ ይሁን አልን፤በሰማንያ ሦስት በብሔር በቤልጂግ አልን። ለሁለት ሺ አስራ ሦስት ምን እያልን ይሆን? ከዚህ ቀደም የሞከርነው አንዱም አልጣመንም፤ አንዱም አልጠቀመንም። ዛሬ ለዘር፣ ለንዋይና ለጥላቻ ሃይማኖት እንጂ ለቀጭን እውነት ቆሞ የሚመሰክር ተመናምኗል።
ሦስት ተኲል መንግሥት፦ የአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት። የጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት። የሳሔል እና የደደቢት (ገ) መንግሥት። የህወሓት/ኢሕአዴግ ሦስት ጒርድ መንግሥት፦ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ህወሓት “ኮሌክቲቭ”፤ (መጽሐፍ፦ ስለ አገሪቱ ዓመፀኝነት አለቆችዋ ብዙ ሆኑ ብሏል)፤ እና የዶ/ር ዐቢይ አሕመድ/ብልፅግና መንግሥት። የህወሓት ኲርፊያ ክልላዊ መንግሥት ራሱን የቻለ ታሪክ ስላለው፣ እናሳድረው። ከእነዚህ ሦስቱ አልፈዋል፤ በሽል ያለው ብልጽግና ፍጻሜው ምን ይሆን?
ዛሬም አልተማርንም። ጃንሆይ! በክብር ዙፋን ይልቀቊ ቢባሉ፦ አሳድገናቸው? (እንደ ሉሉ) ከእጃችን ላይ በልተው? ሕዝባችን እንዴት ይሆናል? ይህንስ አያደርጉብንም አሉ። ዘመን ጥሎአቸው እንደ  ነጎደ አላስተዋሉም። ለአልጋ ወራሹ ቀርቶ ለልጅ እንዳልካቸው መኮንን ሥልጣን ማዋስ አንገራገሩ። ይኸ ሲሆን ሻለቃ መንግሥቱና ሻለቃ ዳዊት ወልደጊዮርጊስ በጭለማ ተቀምጠው ይዶልቱ ነበር። ወዲያው የጎባጣ ቮልስዋገን በር አዛጋ፤ ከዚያ ስድሳ እሩምታ ተሰማ! እሩምታው ባመቱ ስድስት መቶ ስድሳ ስድስት ሆነ! ጓድ መንግሥቱ ከአብዮት ኮረብታ ላይ ቆመው ግራ እጃቸውን አነሡ፦“ወይ እናት አገር ወይ ሞት!” አሉ፤ ሁሉም “ሞት!” ይሻለናል አለ፤ ሞት ተቸረው። እናት አገርን ያሰባት የለም! ለአስራ አምስት ዓመታት “በራዥ! አቆርቋዥ! ገንጣይ!” የወትሮ ፀሎት ሆነ። መንጌና አብዮቱ ታሪክ ቀድሟቸው፣ ወደ ኋላ እንደቀሩ ግን አላስተዋሉም። ደፍሮ የሚናገራቸው አልተገኘም፤ በፍጻሜ ላይ ብቻ ለምልክት ሦስት ተገኙ!
ያልታሰቡ፣ አንደበተ ርቱዑ አእምሮ ፈጣኑ ለገሰ፣ የህግ ስማቸውን ሰውረው መለስ አሉ። ለጋሱ መለስ፣ ከእንግዲህ በቀን ሦስቴ ትበላላችሁ ሲሉ ቃል ገቡልን። ተስፋ ለማድረግ ወይም ለመሳቅ ቸገረን። ቆይተው፦ “ያለ ህወሓት ብትሉ ግን መንገዱን ጨርቅ ያርግላችሁ፤ ማይ ዌይ ኦር ዘሃይ ዌይ! ያለ እኔ(ያለ ህወሓት) ዩጎዝላቪያ ነው መንገዱ፤ ሩዋንዳ ነው፤ ሶማልያ ነው፤ ቃሊቲ ነው፤ ኲርባጅ ዥዋዥዌ፤ ቂሊንጦ ነው፤ እርሳስ ነው። ከእኔ (ከህወሓት ጋር) ኮርያ ማሌዥያ፣ ጃፓን፣ ቻይና፣ ኤዥያ፣ ብሩህ ነው መንገዱ!” ማለት ጀመሩ።
ኃይለሥላሴ ያሉትን ብለው እንዳበቊ፣ ጨላልሞ ስለነበር አዳራቸውን ወደ አልጋቸው ወጡ፤ ሲነጋ የሆነውን ለማየት አልበቊም! የንጉሥ ሬሣ የገባበት ጠፋ። መለስ በአሜሪካኖች እርዳታ ከታላቅ ወንድማቸው ከኢሱ ጋር እጅ ለእጅ ተያይዘው (አህያ አስቀድመው፣ ኦነግን፣ አዴፓን፣ ደቡብ ንቅናቄን በአሽከርነት አስከትተው፣በዑመር በሽር ጦርና መንፈስ) መናገሻዪቱን በጭለማ ወረሩ። የደርግን የጥይት ግምጃ ቤት ከጫፍ ጫፍ ድል! ድም! ደምደም! አደረጉት! መጥተናል! መጥተናል! ነው። በነጋታው የየሰውን ደጅና የዘር ኮቴ እየዞሩ አንኳኩ፤ በረበሩ! ለእነርሱ ፈንጠዚያ፣ ሲንገላታ ለኖረ ሕዝብ ስጋትና የትንቢት ቀጠሮ ነበር!
መለስ “መጪው ዘመን ብሩህ ነው!” ባሉ በሁለተኛው ዓመት በስውር ካገር ወጡ። ወጥተው የገቡበት ጠፋ። ከሁለት ወር በኋላ ቤልጂግ ሆስፒታል አልጋ ይዘው በቴሌቪዥን ታዩ። ይገርማል፣ ታመውም እንኳ ላገር ከመሥራት አልቦዘኑም! የሕዝባቸውን ስጋት ለማርገብ፦ "ህክምናችንን እንደ ጨረስን ወደ ምንወዳት አገራችን፣ ወደ ምንወደውና ወደ ሚወደን ሕዝባችን እንመለሳለን" አሉ።
ነሐሴ ፲፭/፳፻፬ በኢትዮጵያ ባንዲራ የተጠቀለለ የሬሣ ሣጥን፣ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ተጭኖ በጭለማ ቦሌ ደረሰ። ሣጥኑ ውስጥ መለስ አሉበት ተባለ፤ ሣጥኑ ውስጥ ለመኖራቸው ግን እርግጠኛ መሆን አልተቻለም። መለስ፣ እንደ አፄ ኃይለሥላሴ፣ ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ተቀበሩ። መካነ መቃብራቸው ማንም እንዳይደርስበት ቶሎ በእብነበረድ ታሸገ፤ የሥላሴ ደጅ በጠብመንጃና በሰንሰለት ታጥራ ከረመች። እርግጥ ነው፣ ኢትዮጵያዉያን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ሬሣ መቆፈር ስላበዛን መጠንቀቁ አልከፋም!
ጓድ መንግሥቱ ያልሸኟቸውን፣ ያስተናገዷቸውን፣ ጥርስ የነከሱባቸውን፣ የጎሪጥ ያዩዋቸውን አንድ ባንድ ሸኛኝተው አሁንም በሕይወት አሉ! አርበኞች ጓዶቻቸው የጣልያን ጥገኛ ሆነው ከረሙ። አንዳንዶችም በስኳር፣ በአልኮልና በበርጩማ አለቊ።
መለስን፣ "ከወቅቱ ጋር ይራመዱ እንጂ፣ ሥልጣን አጋሩ እንጂ" ቢሏቸው፦ (እንደ አፄ ኃይለሥላሴና እንደ ጓድ ሊቀ መንበር መንግሥቱ) "ያለ እኛማ አይሆንም እኮ! አላወቃችሁም? ይልቅ የጀመርነውን እንጨርስ፣ ሥራ አታስፈቱን" አሉ። ህወሓት ሕዝብ ባስመረረ ቊጥር፣ አገሪቷን በሸነሸነ፣ ዘር ዘር ባለ ቊጥር፣ የጃንሆይ “ኢትዮጵያ ሆይ!” እና የመንግሥቱ ኃይለማርያም “ኢትዮጵያ ትቅደም!” ገበያቸው ደራ! ፈጣሪ የትኛውን በጎ ሥራ አይቶላቸው ይሆን? ይኸው፣ ያፈናቀሏቸው ተፈናቅለው፤ ከዋሻ ዋሻ ተንዘላዝለው፤ ለሌሎች በቆፈሩት ቃሊቲ ተጥለዋል። ወደ ኢምፔሪያሊስት አሜሪካና ወደ ደደቢት ተሰድደዋል። መንጌ ከዚምባብዌ እልፍኛቸው ይህን ሁሉ እያዩ (የሚናፍቊትን፣ የሚናፍቃቸውን ሕዝባቸውን እያሰቡ)፣ በፈገግታ፣ “ጓድ ስታሊን እንዳለው፣ እጠቅሳለሁ፦  ‘ይኸ ታሪካዊ ሂደት ነው!’” ሳይሉ አልቀረም! ይባስ፣ እርሳቸው ባቀጣጠሉት አብዮት፣ በአደባባይ አድኃርያንና ቀልባሾችን በጠርሙስ በቆሉበት፣ በስድሳ ስምንት በሻሻ ላይ የተወለደላቸው ወንድ ልጅ፤ በተሰደዱ በሠላሳ ዓመት፣ በእርሳቸውና በ“ኢትዮጵያ ትቅደም” ላይ ያሤሩትን ይበቀልላቸው ጀመር! ይህን በረከት ወይስ እርግማን እንበል?
እንዲያው ምንም አልተማርን? ስለ ሰው ከንቱነት? ስለሥልጣን ጊዜያዊነት? ስለ እግዚአብሔር ፍርድ? ምንም አልተማርን? ከአፄ ኃይለሥላሴ መንግሥት። ከጓድ ሊቀመንበር መንግሥቱ ኃይለማርያም መንግሥት። ከሳሔል እና ከደደቢት (ገ)መንግሥት። ከህወሓት/ኢሕአዴግ ሦስት ጒርድ መንግሥት፣ ከህወሓት ኲርፊያ ክልላዊ መንግሥት። ምንም አልተማርን?
ሦስት ትውልድ፣ከረሃብና ከሰቆቃ እንቅልፍ ስንነቃ፣ ያልታሰቡ ሰዎች ጭለማ ለብሰው መንበር ላይ ቂብ ብለው አገኘናቸው! ሥልጣን አልለቅ ብለው አሰለቹን! ሞት ደርሶ ባይገላግልማ ከነልጅ ልጆቻችን ባርያ ባደረጉን!
ከሚያሠቃዩን እጅ ከሞት በስተቀር የሚገላግል የለም ማለት ግን አይደለም! ዋነኛው ገላጋይ ፀሎት ነው፤ ፀሎት! ፀሎት! ፀሎት! ሌላኛው ገላጋይ፦በሚኒስትር ደረጃ የሚሾሙ ሁሉ ቃለ መሓላ ከመፈጸማቸው አስቀድሞ ለወር ከርቸሌ ይክረሙ! በሳምንት ለአንድ ሰዓት ዥዋዥዌ ይለማመዱ! ሚስቶቻቸውም ወዲያው ስንቅ ማቀበል ይማሩ! ልጆቻቸው ያለ አባት፣ያለ እናት፣ያለአይፓድ ማደግ ይልመዱ! ወሩ ሲያበቃ፣ እጩዎቹ የእስረኛ ልብስ ለብሰው፣ በጫንቃቸው ድንጋይ ተሸክመው፣እጅ እግራቸው በካቴና ተጠፍሮ በሕዝብ ፊት ቃለ መሓላ ይፈጽሙ!
በዚህ ሰዓት፣ ወደ ሥልጣን እርካብ ለመውጣት አኮብኲበው፣ የዳኛ ብርቱካንን ፊሽካ የሚጠባበቊ ፓርቲዎች ቊጥር 50 ገደማ ደርሷል። የ50ዎቹ  ሤራና ግርግር እውን የኢትዮጵያን ሕዝብ ምኞትና ምቾት ለማሳካት ነው? እንግዲያውስ በድንጋይና በካቴና ቃለ መሓላ ይፈጽሙ!
(ምንጭ፡- ኢትዮጵያን ኦብሰርቨር)


  ኮሮና ለስራ አጥነት የዳረጋቸው 220 ሚ. ይደርሳሉ ተባለ

           ባለፈው ጥቅምት ወር ለመጀመሪያ ጊዜ በህንድ የተገኘውና ከሌሎች የኮሮና ቫይረስ ዝርያዎች ሁሉ በቀላሉ የመሰራጨት አቅም እንዳለው የተነገረለት “B.1.617’’ የተባለ ዝርያ፣ እስካሁን ድረስ 62 አገራትን ማዳረሱን የአለም የጤና ድርጅት አስታውቋል፡፡
ከሳምንታት በፊት በአለማቀፍ ደረጃ ልዩ ስጋት ፈጥሯል በማለት በአደገኝነት የፈረጀውና ከሰሞኑ ደግሞ ‹ዴልታ› ሲል አዲስ ስም የሰጠው ይህ የኮሮና ቫይረስ ዝርያ፣ ወደ 62 የአለማችን አገራት መዛመቱን ባለፈው ረቡዕ ያስታወቀው የአለም የጤና ድርጅት፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በጃፓን የተገኘውና ‹ጋማ› የሚል ስያሜ የተሰጠው የቫይረሱ ዝርያ በበኩሉ ወደ 64 የአለማችን አገራት መዛመቱን አክሎ ገልጧል፡፡
በሌላ የኮሮና ቫይረስ ዜና ደግሞ፣ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ፣ እስከ ዘንድሮው የፈረንጆች አመት 2021 መጨረሻ፣ ለስራ አጥነት የሚዳርጋቸው ሰዎች ቁጥር 220 ሚሊዮን ያህል ይደርሳል ተብሎ እንደሚገመትና ወረርሽኙ ለድህነት የዳረጋቸው ሰራተኞች ቁጥር ከ100 ሚሊዮን ማለፉን፣ የአለም የስራ ድርጅት ባወጣው ሪፖርት አመልክቷል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሰቱን ተከትሎ፣ በከፍተኛ ሁኔታ የስራ ሰዓቶች መቀነሳቸውንና የስራ ዕድሎች መዘጋታቸውን የጠቆመው ሪፖርቱ፤ በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰራተኞች ገቢያቸው መቀነሱን፣ ከስራ መፈናቀላቸውንና ለድህነት መዳረጋቸውን አስረድቷል፡፡

   ከዕለታት አንድ ቀን አንድ እንግዳ ወደ ገጠር ይመጣና አንደኛው ባለአገር ቤት ያርፋል፡፡ ለወትሮውም ወታደር ከሆነ በተሰሪነት ነበር የሚኖረው፡፡ ያም ተሰሪነት የተገባበት ባለሀገር የግዱን ነበረ ወታደርነት ይባስ ብሎም ያ ወታደር የባላገሩን ቆንጆ ልጅ አየና እንዲህ ሲል ጠየቀው፡-
“አንተ፤ ይህቺ እህትህ ስንት አመቷ ነው?” አለው፡፡
ነገሩ የክጀላ ነው፡፡
“ያም ባላገር ሚስቴ ናት” ማለት ፈርቶ “የእህቴ እድሜ ይህን ያህል ነው” ብሎ ተናገረ፡፡
ያም ጋጠወጥ ወታደር የባላገሩን ሚስት ይዞበት አደረ፡፡
በነገታው ያ ባላገር ደጁ ተቀምጦ፣ አቀርቅሮ እንደሚከተለው ገጠሞ አንጎራጎረ
ካገር እኖር ብዬ
ከብት እነዳ ብዬ
ልጅ አሳድግ ብዬ
ለባሻ ዳርኩለት ሚስቴን እቴ ብዬ
ይሄ የሆነው በሌሎቹ ነገስታት ዘመን እንጂ በሚኒልክ ዘመን አልነበረም፡፡ ከላይ የተጠቀሰው ታሪክ የተገኘው አፈወርቅ ገ/ኢየሱስ የተባሉ ደራሲ የጻፉት “ዳግማዊ አጼ ሚንልክ” ከተባለው  መፅሐፍ ነው፡፡  አሳጥረን አቅርበነው ነው፡፡
ለአያሌ የጀግንነት አይነቶች ምስክር ሆነናል፡፡ ገናም እንሆናለን፡፡ በየዘመኑ የየነገስታቱ አገዛዝና ስርዓት በሕዝብ ላይ የራሱን አሻራ ሲያሳርፍ እያየን ብዙ ዓመታት ገፍተናል፡፡ ምናልባትም ገና ዛሬም እንቀጥላለን፡፡  ከእያንዳንዱ ስርዓት የምናገኘው፣  በውስጡ እያለ የማይታየን  በርካታ ህፀፅ፣  ከስርዓቱ ወጣ ብለን ስናስተውል ፍንትው ብሎ ይታየናል፡፡
ትውልዱንም ለማብቃት አዳዲስ ጥርጊያ መንገድ እንከፍታለን፡፡ በዚህ ረገድ ስናየው መንገድ መዘርጋት ጀግንነት ነው፤ ትምህርት ቤት መክፈት ጀግንነት ነው፤ ጤና ጣቢያ መስራት ጀግንነት ነው፤ አለማችንን እያመሰ ያለው የኮሮና ቫይረስ መፍትሔ መሻት ቆራጥነት ነው፤ የስፖርት ማነቃቂያ ስራዎችን በጋራ ማደራጀት ጀግንነት ነው፤ ፓርኮችን ማልማት ጀግንነት ነው፤ የመኖሪያ የወላጆችንና የተማሪዎች ኮሚቴዎችን በሶስትዮሽ ስልት ማዋቀር ታላቅ ጀግንነት ነው፤ መማር ያልቻሉ ወጣቶችን በገጠርም በከተማም በማቴሪያልም በገንዘብም እየረዱ እድሜያቸው ለትምህርት ከማለፉ በፊት ማናቸውንም እገዛ ማድረግ ከጀግንነትም የላቀ ጀግንነት ነው፡፡ ዛሬ መሰረተ ልማትን ማንቀሳቀስ እንደ ታላቅ ጸጋ የሚታይበት የሀገርን ጥሪ ከድንበር እስከ መሃል ሀገር  እንደ ተገቢነቱ ውል ማስያዝና ጉዳዬ ብሎ፣ እኔንም ያገባኛል ማለት ታላቅ ኃላፊነትን መቀበል ነው፡፡ በስልጣን ላይ ያሉ አካላት ሂስ ሲያስፈልጋቸው ቸል ሳይሉ፣ ሙያዊ ድጋፍ መስጠትና ስነ-ምግባራዊ ተሞክሮን ማጋራት ዛሬም ወሳኝ ነው፡፡
ከላይ ለጠቀስናቸው ፍሬ ሃሳቦች ዋና መጠቅለያ የሚሆነን፣ የፍትህ አካላትን በተጠናከረ መልኩ አደራጅቶ መምራት መምራት ስለሆነ፣ እዚሁ ላይ ብርቱ ትኩረት የምንጠየቅበት አንገብጋቢ ወቅት ነው፡፡
ከሎሬት ፀጋዬ ገ/መድህን ታዋቂ ድርሰቶች አንዱ ከሆነው ከ”ቴዎድሮስ” ቴአትር አንድ ስንኝ እንዋስ፡-
“ያለፈ ጥረታችንን፣ ሳስታምመው ትዝ ሲለኝ
ከሞከርነው ነገር ይቅ ያልሞከርነው ነው የሚቆጨኝ” የሚለውን ልብ ብለን እናስተውል፡፡
አንድም ድግሞ ከ”ማክቤል” የመጨረሻ ሰዓት በመጥቀስ፡-
“የነገ ውሎ የነገ ውሎ የነገ ውሎ
ከቀን ወደ ቀን ይሳባል፣ በእድሜ ንፉግ ጀርባ ታዝሎ
ትላንትናም ከትላንት በስቲያም፣ ለጅሎች ጥርጊያ አሳምሮ
ዛሬ ፈጥሮ ነገ ቀብሮ…
እግረ መንገዳችንንም  ከብራውን ጋር
“ደግሞም ማወቅ ማለት
ከውጭ ያለውን ሄዶ ከመፈለግ
ከውስጥ የበራውን እንዲወጣ ማድረግ” …ማለትንም አልዘነጋንም፡፡
ለመደምደሚያችንም…
ከኦቴሎ ጋር አንቺስ ሌላይቱ ጮራ አንቺ የጉም ፍንጣቂ
ከእብሪት ከተንኮል ዛፍ ፍሬ የተቀመምሽ ጭማቂ
እፍ ብዬ ባጨልምሽ ልጠፋብኝ ያንቺ ጮራ የለም
 መለኮታዊ ሃይል አንቺን የሚያበራ… እንላለን፡፡


         “… ኢትዮጵያ አገራችን ከፍተኛ ፈተና ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ያው ቪዛ ተከልክሏል፡፡ እኔን አያውቁኝም፤ እኔም አላውቃቸውም፡፡ ስለዚህ ብዙም አይመለከተኝም፡፡ ሞያሌና አድዋ ለመሄድ ቪዛ አያስፈልገኝም፡፡ ከዚያ ውጪ ብዙም እንቅስቃሴ ስለማላድግ….አያውቁኝም አላውቃቸውም፤ስለዚህ ውሳኔው እኔን አይመለከተኝም፡፡  እንድታደርሱልኝ….”
(የኦሮምያ ክልላዊ መንግስት ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ ሰሞኑን በሸራተን አዲስ ለፋሲል ከነማ የገቢ ማሰባሰቢያ ቴሌቶን ላይ የአሜሪካ መንግስት በኢትዮጵያ ባለስልጣናት ላይ የጣለውን የቪዛ ማዕቀብ በተመለከተ ከተናገሩት የተወሰደ)

Saturday, 29 May 2021 14:34

ሀገሬ ዋርካ ናት!!!

ገና በጥዋቱ ~ ለስሟ መጠሪያ
አቢሲንያ ብሎ ~ ሲሰጣት መለያ
አንዳች ዕምቅ ሚስጥር ~ ለኛ ያልተገለጠ
ፈጣሪም አድልቶ ~ ከአርያም ሰጠ
ከግዮን ከወንዙ ~ ከዳሎል ዝቅታ
ከኤርታሌ ረመጥ ~ከዳሽን ከፍታ
አክሱም አናቱ ላይ~ ከላሊበላ ስር
ሀገሬ ተገምዷል ~ በወፍራም የደም ክር
በዚህ የጭንቅ ወቅት~ ምጧ እንዲህ ሲጠና
አዋላጅ ፈልጉ ~ ሳይጠናባት ገና
ለምን ካላችሁኝ
ከራስጌም ከግርጌም ~ ቢታጣ እንኳ ትራስ
ይጋረዳል እንጂ ~ ይፈናቀላል ወይ~ ያልጠነከረ አራስ
አደራ!
አደራ!
አንቺ ብቻ ታገሽ
አንገት እንዳትደፊ ~ ከቶ እንዳትይ ዘንበል~ መጠንከር ነው ደጉ
በጨርቅ ተከልለሽ~ እስኪሰዋ ድረስ ~ የመስዋት በጉ
ቢያድለን ኑሮማ ~ ሀገር ጨርቃችን ናት~ ሁሉን ተሸካሚ
የውስጣችን ጉድፍ~ ሸፍና ያስቀረች ~ ዛሬም አስታማሚ
አዎ ሀገር ጨርቃችን ናት
እንደ እፉኝት ልጆች~ ገመናዋን ሸፋኝ ~ማብቀል የተሳናት
የመጣው የሄደው ~ ቆርጦ ዕጣ ሊጣጣል ~ ሰርክ የሚመኝላት
ሀገር ጨርቃችን ናት
ግና!
ሰንደቋን ጨርቅ ነው ~ ብለው ሲያሟርቱ ~ እነ ግፍ አይፈሩ
አክሱም ለወላይታው ~ምን ያደርግለታል ~ ብለው ሲፎክሩ
ጉደኛ ናትና
ቀብረናታል ሲሉ ~ ቀብራቸው አረፈች~ ይቅለለው አፈሩ
እስኪ ይጠየቅ ጴጥሮስ ~ ያነ ሀዋርያ
የሀምሌ አቦ ስብሃት ~ የክርስቶስ ባሪያ
ያነ ቅዱሱ ጳውሎስ~ በሚያልፍበት መንገድ~ እግሩ በረገጠው
በጨርቅ ጥላ አልነበር~ ድዊ ሚፈወሰው
ይሄው ዛሬ ደግሞ
ከደመቀው በላይ ~ እጅጉን ደምቆልን ~ ተነቅሎልን ሳንካ
ዕድል በለስ ቀንቶን ~ ገዱ ለኛ ሆነ ~ ብርሃኑም ፈካ
ዳሩ ምን ያደርጋል
ሁሉም ደርሶ ተንታኝ ~ ሁሉም ተናጋሪ ~ በሆነበት ዓለም
በሩ ገርበብ ሲል ~ ያለፈውን አዋጅ ~ ማያካክስ የለም
ተንፍሱም እያሉ ~ ብዕር ቢሰጧቸው
እንደምን ይፃፉ ~ ቃታ እየታያቸው
ይልቅ
አለም አድናቆቱን ~ ይቸርሀል ነገ
በመደመር ስሌት ~ መቀነሱም አብሮ~ እኩል ስላደገ
ግና እንደዛሬው~ እንዲህ ሀገር ሲታወክ
የሰራዊት ብዛት ~ ሀገር አያፀናም ~ ቢልም ቅዱስ ቃሉ
ዘመን ተገልብጦ ~አመሉ የበዛውን~ ሰራዊት ይላሉ
ምንም እንኳን
ቅርንጫፏ ወድቆ
ቅጠሏም ረግፎ~ስሯ እንዲህ ቢደርቅም
ሀገሬ ዋርካ ናት
መቸም መቸም ቢሆን
በግፈኞች መጋዝ አትገነደስም፡፡

 ቪዡዋል ካፒታሊስት ድረገጽ ባለፉት 30 አመታት በአለማችን ከፍተኛ ጥቅል ገቢ ያገኙ ዝነኛ ፊልሞችን ዝርዝር ከሰሞኑ ይፋ ያደረገ ሲሆን፣ አቫታር በ2.85 ቢሊዮን ዶላር ገቢ በአንደኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል፡፡
እ.ኤ.አ በ2009 ለእይታ የበቃውና በጄምስ ካሜሩን ዳይሬክተርነት የተሰራው አቫታር አጠቃላይ ወጪው 237 ሚሊዮን ዶላር እንደሆነ ያስታወሰው ድረገጹ፣ ፊልሙ ለእይታ ከበቃበት ጊዜ አንስቶ በድምሩ 2.85 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ማግኘቱንም ገልጧል፡፡
አቬንጀርስ ኢንድጌም በ2.79 ቢሊዮን ዶላር የሁለተኛነትን ደረጃ ሲይዝ፣ ሌላኛው ዘመን አይሽሬ ፊልም ታይታኒክ በ2.2 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ በሶስተኛ ደረጃ ላይ መቀመጡን ድረገጹ አመልክቷል።
ስታር ዎርስ - ዘ ፎርስ አዌክን በ2.06 ቢሊዮን ዶላር፣ አቬንጀስርስ - ኢንፊኒቲ ዎር በ2.04 ቢሊዮን ዶላር፣ ጁራሲክ ዎርልድ በ1.67 ቢሊዮን ዶላር፣ ዘ ላዮንኪንግ በ1.65 ቢሊዮን ዶላር፣ ዘ አቬንጀርስ በ1.518 ቢሊዮን ዶላር፣ ፊዩሪየስ በ1.515 ቢሊዮን ዶላር እንዲሁም ፍሮዝን ቱ በ1.4 ቢሊዮን ዶላር አጠቃላይ ገቢ ከአራተኛ እስከ አስረኛ ያለውን ደረጃ መያዛቸውንም መረጃው ያሳያል፡፡
ባለፉት 30 አመታት ከፍተኛ ገቢ ካገኙ 50 ፊልሞች መካከል 26ቱ በዲዝኒ ስቱዲዮ የተሰሩ መሆናቸውን የጠቆመው ድረገጹ፣ ዩኒቨርሳል ስቱዲዮ እና ዋርነር ብሮስ በተመሳሳይ 8 ፊልሞች እንደሚከተሉም አክሎ ገልጧል፡፡

Page 9 of 536